The Old Testament of the Holy Bible

ዘፍጥረት 1

1 በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ። 2 ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። 3 እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። 4 እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ። 5 እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን። 6 እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ። 7 እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ። 8 እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን። 9 እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ። 10 እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። 11 እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ። 12 ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። 13 ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን። 14 እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤ 15 በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ። 16 እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። 17 እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤ 18 በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። 19 ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን። 20 እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ። 21 እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። 22 እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ። 23 ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን። 24 እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ። 25 እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ። 26 እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። 27 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 28 እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። 29 እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤ 30 ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ። 31 እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።

ዘፍጥረት 2

1 ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ። 2 እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ። 3 እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና። 4 እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ አምላክ ሰማይንና ምድርን ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው። 5 የሜዳ ቁጥቋጦ ሁሉ በምድር ላይ ገና አልነበረም፤ የሜዳውም ቡቃያ ሁሉ ገና አልበቀለም ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክ ምድር ላይ አላዘነበም ነበርና፥ ምድርንም የሚሠራባት ሰው አልነበረም፤ 6 ነገር ግን ጉም ከምድር ትወጣ ነበር፥ የምድርንም ፊት ሁሉ ታጠጣ ነበር። 7 እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። 8 እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። 9 እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ። 10 ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለአራት ክፍል ይከፈል ነበር። 11 የአንደኛው ወንዝ ስም ፊሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፤ የዚያም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ 12 ከዚያም ሉልና የከበረ ድንጋይ ይገኛል። 13 የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል። 14 የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሦር ምሥራቅ የሚሄድ ነው። 15 አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው። 16 እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ 17 ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። 18 እግዚአብሔር አምላክም አለ። ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። 19 እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። 20 አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። 21 እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። 22 እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። 23 አዳምም አለ። ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። 24 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። 25 አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።

ዘፍጥረት 3

1 እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም። በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። 2 ሴቲቱም ለእባቡ አለችው። በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ 3 ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ። እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። 4 እባብም ለሴቲቱ አላት። ሞትን አትሞቱም፤ 5 ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። 6 ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። 7 የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ። 8 እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። 9 እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ። ወዴት ነህ? አለው። 10 እርሱም አለ። በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም። 11 እግዚአብሔርም አለው። ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን? 12 አዳምም አለ። ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ። 13 እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን። ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም አለች። እባብ አሳተኝና በላሁ። 14 እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው። ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። 15 በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። 16 ለሴቲቱም አለ። በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል። 17 አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ 18 እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። 19 ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና። 20 አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። 21 እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። 22 እግዚአብሔር አምላክም አለ። እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ 23 ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። 24 አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።

ዘፍጥረት 4

1 አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም። ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች። 2 ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ። 3 ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ 4 አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ 5 ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። 6 እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? 7 መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት። 8 ቃየንም ወንድሙን አቤልን። ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም። 9 እግዚአብሔርም ቃየንን አለው። ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ። አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? 10 አለውም። ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። 11 አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። 12 ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። 13 ቃየንም እግዚአብሔርን አለው። ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። 14 እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል። 15 እግዚአብሔርም እርሱን አለው። እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። 16 ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ። 17 ቃየንም ሚስቱን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፥ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም ሄኖሕ አላት። 18 ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሣኤልን ወለደ፤ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። 19 ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበረ። 20 ዓዳም ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። 21 የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፤ እርሱም በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ። 22 ሴላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። 23 ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው። እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፥ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጕልማሳውን ለቍስሌ፥ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና፤ 24 ቃየንን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ። ይበቀሉታል 25 አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም። ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው። 26 ለሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ። a

ዘፍጥረት 5

1 የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ 2 ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው። 3 አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ፤ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው። 4 አዳምም ሴትን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 5 አዳምም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 6 ሴትም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፥ ሄኖስንም ወለደ፤ 7 ሴትም ሄኖስን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 8 ሴትም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 9 ሄኖስም መቶ ዘጠና ዓመት ኖረ፥ ቃይናንንም ወለደ፤ 10 ሄኖስም ቃይናንን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አሥራ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 11 ሄኖስም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምስት ዓመት ሆነ ሞተም። 12 ቃይናንም መቶ ሰባ ዓመት ኖረ፥ መላልኤልንም ወለደ፤ 13 ቃይናንም መላልኤልን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ አርባ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 14 ቃይናንም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አሥር ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 15 መላልኤልም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ያሬድንም ወለደ፤ 16 መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሠላሳ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 17 መላልኤልም የኖረበት ዘመን ሁሉ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 18 ያሬድም መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሄኖክንም ወለደ 19 ያሬድም ሄኖክን ከወለደ በኋላ የኖረው ስምንት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 20 ያሬድም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 21 ሄኖክም መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ማቱሳላንም ወለደ፤ 22 ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፤ ማቱሳላንም ከወለደ በኋላ የኖረው ሁለት መቶ ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 23 ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ። 24 ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና። 25 ማቱሳላም መቶ ሰማኒያ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ላሜሕንም ወለደ፤ 26 ማቱሳላም ላሜሕን ከወለደ በኋላ የኖረው ሰባት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 27 ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 28 ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ። 29 ስሙንም። እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው። 30 ላሜሕም ኖኅን ከወለደ በኋላ የኖረው አምስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ፤ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። 31 ላሜሕ የኖረበት ዘመን ሁሉ ሰባት መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆነ፤ ሞተም። 32 ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ።

ዘፍጥረት 6

1 እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ 2 የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። 3 እግዚአብሔርም። መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ። 4 በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ። 5 እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። 6 እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። 7 እግዚአብሔርም። የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። 8 ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። 9 የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ። 10 ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ። 11 ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች። 12 እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና። 13 እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። 14 ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፥ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። 15 እርስዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን። 16 ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመትዋም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ። 17 እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል። 18 ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። 19 ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን። 20 ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። 21 ከሚበላውም መብል ሁሉ ለአንተ ውሰድ፥ ወደ አንተም ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተም ለእነርሱም መብል ይሆናል። 22 ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። a

ዘፍጥረት 7

1 እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና። 23 ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባትና እንስት፥ ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ። 4 ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና። 5 ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። 6 ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። 7 ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ። 8 ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥ 9 እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ። 10 ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ። 11 በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤ 12 ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ። 13 በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ። 14 እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥ 15 ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ። 16 ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት። 17 የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ፤ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች። 18 ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች። 19 ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ። 20 ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ተራሮችም ተሸፈኑ። 21 በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ። 22 በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ። 23 በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ። 24 ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።

ዘፍጥረት 8

1 እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ፤ 2 የቀላዩም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፥ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ 3 ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። 4 መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች። 5 ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ። 6 ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ 7 ቁራንም ሰደደው፤ እርሱም ወጣ፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8 ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት። 9 ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፥ ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት። 10 ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ። 11 ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ። 12 ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም። 13 በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅም የመርከቢቱን ክዳን አነሣ፥ እነሆም፥ ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ። 14 በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ደረቀች። 15 እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው። 16 አንተ ሚስትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ። 17 ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ። 18 ኖኅም ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወጣ፤ 19 አራዊት ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ ወፎችም ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚርመሰምሰው ሁሉ በየዘመዳቸው ከመርከብ ወጡ። 20 ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ። 21 እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ። ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም። 22 በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም። a

ዘፍጥረት 9

1 እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው። ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት። 2 አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል። 3 ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ። 4 ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፤ 5 ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። 6 የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና። 7 እናንተም ብዙ፥ ተባዙ፤ በምድር ላይ ተዋለዱ፥ እርቡባትም። 8 እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ። 9 እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤ 10 ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል። 11 ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። 12 እግዚአብሔርም አለ። በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤ 13 ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። 14 በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤ 15 በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። 16 ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። 17 እግዚአብሔርም ኖኅን። በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው። 18 ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው። 19 የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች። 20 ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ። 21 ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። 22 የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23 ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። 24 ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ። 25 እንዲህም አለ። ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን። 26 እንዲህም አለ። የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን። 27 እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን። 28 ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ። 29 ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።

ዘፍጥረት 10

1 የኖኅ ልጆች የሴም የካም የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ ከጥፋት ውኃም በኋላ ልጆች ተወለዱላቸው። 2 የያፌት ልጆች ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ ያዋን፥ ይልሳ፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ ናቸው። 3 የጋሜርም ልጆች አስከናዝ፥ ሪፋት፥ ቴርጋማ ናቸው። 4 የያዋንም ልጆች ኤሊሳ፥ ተርሴስ፥ ኪቲም፥ ሮድኢ ናቸው። 5 ከእነዚህም የአሕዛብ ደሴቶች ሁሉ በየምድራቸው በየቋንቋቸው በየነገዳቸው በየሕዝባቸው ተከፋፈሉ። 6 የካምም ልጆች ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን ናቸው። 7 የኩሽም ልጆች ሳባ፥ ኤውላጥ፥ ሰብታ፥ ራዕማ፥ ሰበቃታ ናቸው። የራዕማ ልጆችም ሳባ፥ ድዳን ናቸው። 8 ኩሽም ናምሩድን ወለደ፤ እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆንን ጀመረ። 9 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም። በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደ ናምሩድ ተባለ። 10 የግዛቱም መጀመሪያ በሰናዖር አገር ባቢሎን፥ ኦሬክ፥ አርካድ፥ ካልኔ ናቸው። 11 አሦርም ከዚያች አገር ወጣ፤ ነነዌን፥ የረሆቦትን ከተማ፥ ካለህን፥ 12 በነነዌና በካለህ መካከልም ሬሴንን ሠራ፤ እርስዋም ታላቂቱ ከተማ ናት። 13 ምጽራይምም ሉዲምን፥ ዐናሚምን፥ ላህቢምን፥ ነፍታሌምን፥ ፈትሩሲምን፥ 14 ከእነርሱ የፍልስጥኤም ሰዎች የወጡባቸውን ከስሉሂምን፥ ቀፍቶሪምንም ወለደ። 15 ከነዓንም የበኵር ልጁን ሲዶንን፥ ኬጢያውያንንም፥ 16 ኢያቡሳውያንንም፥ አሞራውያንንም፥ 17 ጌርጌሳውያንንም፥ ኤዊያውያንንም፥ 18 ዐሩኬዎንንም፥ ሲኒንም፥ አራዴዎንንም፥ ሰማሪዎንንም፥ አማቲንም ወለደ። ከዚህም በኋላ የከነዓናውያን ነገድ ተበተኑ። 19 የከነዓናውያንም ወሰን ከሲዶን አንሥቶ ወደ ጌራራ በኩል ሲል እስከ ጋዛ ድረስ ነው፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ፥ ወደ አዳማና ወደ ሰቦይም በኩልም ሲል እስከ ላሣ ድረስ ነው። 20 የካም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራችውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። 21 ለሴምም ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የያፌት ታላቅ ወንድምና የዔቦር ልጆች ሁሉ አባት የሆነ ነው። 22 የሴምም ልጆች ኤላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ፥ አራም ናቸው። 23 የአራምም ልጆች ዑፅ፥ ሁል፥ ጌቴር፥ ሞሶሕ ናቸው። 24 አርፋክስድም ቃይንምን ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን፥ ሳላም ዔቦርን ወለደ። 25 ለዔቦርም ሁለት ልጆች ተወለዱለት፤ የአንደኛው ስሙ ፋሌቅ ነው፥ ምድር በዘመኑ ተከፍላለችና፤ የወንድሙም ስም ዮቅጣን ነው። 26 ዮቅጣንም ኤልሞዳድን፥ ሣሌፍንም፥ ሐስረሞትንም፥ 27 ያራሕንም፥ ሀዶራምንም፥ አውዛልንም፥ 28 ደቅላንም፥ ዖባልንም፥ አቢማኤልንም፥ 29 ሳባንም፥ ኦፊርንም፥ ኤውላጥንም፥ ዩባብንም ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። 30 ስፍራቸውም ከማሴ አንሥቶ ወደ ስፋር ሲል እስከ ምሥራቅ ተራራ ድረስ ነው። 31 የሴም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። 32 የኖኅ የልጆቹ ነገዶች እንደ ትውልዳቸው በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው። አሕዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከእነዚህ ተከፋፈሉ። a

ዘፍጥረት 11

1 ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች። 2 ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ። 3 እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፋት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው። 4 እንዲህም። ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ። 5 እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። 6 እግዚአብሔርም አለ። እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም። 7 ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው። 8 እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ። 9 ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። 10 የሴም ትውልድ ይህ ነው። ሴም የመቶ ዓመት ሰው ነበረ፥ አርፋክስድንም ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ወለደ። 11 ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 12 አርፋክስድም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ቃይንምንም ወለደ፤ 13 አርፋክስድም ቃይንምን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። ቃይንምም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሳላንም ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን ከወለደ በኋላ ሶስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 14 ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ዔቦርንም ወለደ፤ 15 ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 16 ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፥ ፋሌቅንም ወለደ፤ 17 ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 18 ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ራግውንም ወለደ፤ 19 ራግውንም ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 20 ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሴሮሕንም ወለደ፤ 21 ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 22 ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ናኮርንም ወለደ፤ 23 ናኮርንም ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 24 ናኮርም መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ታራንም ወለደ፤ 25 ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። 26 ታራም መቶ ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ። 27 የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ። 28 ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። 29 አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው። 30 ሦራም መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም። 31 ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ። 32 የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።

ዘፍጥረት 12

1 እግዚአብሔርም አብራምን አለው። ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። 2 ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ 3 የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። 4 አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ። 5 አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን፥ ያገኙትን ከብት ሁሉና በካራን ያገኙአቸውን ሰዎች ይዞ ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ወጣ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ገቡ። 6 አብራምም እስከ ሴኬም ስፍራ እስከ ሞሬ የአድባር ዛፍ ድረስ በምድር አለፈ፤ የከነዓን ሰዎችም በዚያን ጊዜ በምድሩ ነበሩ። 7 እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለትና። ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠውያን ሠራ። 8 ከዚያም በቤቴል ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ወጣ፥ በዚያም ቤቴልን ወደ ምዕራብ ጋይን ወደ ምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። 9 አብራምም ከዚያ ተነሣ፥ እየተጓዘም ወደ አዜብ ሄደ። 10 በምድርም ራብ ሆነ፤ አብራምም በዚያ በእንግድነት ይቀመጥ ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፥ በምድር ራብ ጸንቶ ነበርና። 11 ወደ ግብፅም ለመግባት በቀረበ ጊዜ ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት። አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ እነሆ እኔ አውቃለሁ 12 የግብፅ ሰዎች ያዩሽ እንደ ሆነ። ሚስቱ ናት ይላሉ እኔንም ይገድሉኛል፥ አንቺንም በሕይወት ይተዉሻል። 13 እንግዲህ በአንቺ ምክንያት መልካም ይሆንልኝ ዘንድ፥ ስለ አንቺም ነፍሴ ትድን ዘንድ። እኅቱ ነኝ በዪ። 14 አብራምም ወደ ግብፅ በገባ ጊዜ የግብፅ ሰዎች ሴቲቱን እጅግ ውብ እንደ ሆነች አዩ፤ 15 የፈርዖንም አለቆች አዩአት፥ በፈርዖንም ፊት አመሰገኑአት፤ ሴቲቱንም ወደ ፈርዖን ቤት ወሰዱአት። 16 ለአብራምም ስለ እርስዋ መልካም አደረገለት፤ ለእርሱ በጎችም በሬዎችም አህዮችም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም ግመሎችም ነበሩት። 17 እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና የቤቱን ሰዎች በታላቅ መቅሠፍት መታ። 18 ፈርዖንም አብራምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? እርስዋ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልገለጥህልኝም? 19 ለምንስ። እኅቴ ናት አልህ? እኔ ሚስት ላደርጋት ወስጄአት ነበር። አሁንም ሚስትህ እነኋት፤ ይዘሃት ሂድ። 20 ፈርዖንም ሰዎቹን ስለ እርሱ አዘዘ፥ እርሱንም ሚስቱንም ከብቱንም ሁሉ ሸኙአቸው። a

ዘፍጥረት 13

1 አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ። 2 አብራምም በከብት በብርና በወርቅ እጅግ በለጠገ። 3 ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል በኩል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤ 4 ያም ስፍራ አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። 5 ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳንም ነበረው። 6 በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም የነበራቸው እጅግ ነበረና በአንድነት ሊቀመጡ አልቻሉም። 7 የአብራምንና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት መካከልም ጠብ ሆነ በዚያም ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር። 8 አብራምም ሎጥን አለው። እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ። 9 ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ። 10 ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ። 11 ሎጥም በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን አገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ። 12 አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ። 13 የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ። 14 ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው። ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ 15 የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና። 16 ዘርህንም እንደ ምድር አሸዋ አደርጋለሁ፤ የምድርን አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል። 17 ተነሣ በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና። 18 አብራምም ድንኳኑን ነቀለ መጥቶም በኬብሮን ባለው በመምሬ የአድባር ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።

ዘፍጥረት 14

1 በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቲድዓል ዘመን እንዲህ ሆነ፤ 2 ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፥ ከሰቦይም ንጉሥ ከሰሜበር፥ ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥም ጋር ሰልፍ አደረጉ። 3 እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። 4 አሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ተገዝተው ነበር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። 5 በአሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ዙዚምንም በሃም፥ ኤሚምንም በሴዊ ቂርያታይም መቱ፤ 6 የሖር ሰዎችንም በሴይር ተራራቸው በበረሀ አጠገብ እስካለች እስከ ኤል ፋራን ድረስ መቱ። 7 ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ዓይንሚስፓጥ መጡ፤ የአማሌቅን አገር ሁሉና ደግሞ በሐሴሶን ታማር የነበረውን አሞራውያንን መቱ። 8 የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሰቦይም ንጉሥ፥ ዞዓር የተባለች የቤላ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በሲዲም ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤ 9 የኤላምን ንጉሥ ኮሎዶጎምርን፥ የአሕዛብን ንጉሥ ቲድዓልን፥ የሰናዖርን ንጉሥ አምራፌልን፥ የእላሳርን ንጉሥ አርዮክን ለመውጋት አምስቱ ነገሥታት በእነዚህ በአራቱ ላይ ወጡ። 10 በሲዲም ሸለቆ ግን የዝፍት ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥ የገሞራ ንጉሥም ሸሹና ወደዚያ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራራ ሸሹ። 11 የሰዶምንና የገሞራን ከብት ሁሉ መብላቸውንም ሁሉ ወስደው ሄዱ። 12 በሰዶም ይኖር የነበረውን የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ። 13 አንድ የሸሸ ሰውም መጣ፥ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊ መምሬ የአድባር ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። 14 አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ። 15 ብላቴኖቹንም ከፍሎ በሌሊት እርሱ ከባሪያዎቹ ጋር ወረደባቸው፥ መታቸውም፥ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። 16 ከብቱንም ሁሉ አስመለሰ፥ ደግሞም ወንድሙን ሎጥንና ከብቶቹን ሴቶችንና ሕዝቡን ደግሞ መለሰ። 17 ኮሎዶጎምርንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመለሰ በኋላም የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። 18 የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ፤ እርሱም የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ። 19 ባረከውም። አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ነው፤ 20 ጠላቶችህን በእጅህ የጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው። 21 የሰዶም ንጉሥም አብራምን። ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው። 22 አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው። ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ 23 24 አንተ። አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ፤ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። a

ዘፍጥረት 15

1 ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል። አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው። 2 አብራምም። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ። 3 አብራምም። ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ። 4 እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት። ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል። 5 ወደ ሜዳም አወጣውና። ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው። 6 አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። 7 ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው። 8 አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ። 9 እርሱም። የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም ያዝልኝ አለው። 10 እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፤ ወፎችን ግን አልከፈለም። 11 አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው። 12 ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፤ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፤ 13 አብራምንም አለው። ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። 14 ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። q2 ኤሊዔዘር የተባለውን የግዕዙን መጽሐፍ ኢያውብር ይለዋል። 15 አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። 16 በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና። 17 ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ። 18 በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ። ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤ 19 ቄናውያንን ቄኔዛውያንንም 20 ቀድሞናውያንንም ኬጢያውያንንም 21 ፌርዛውያንንም ራፋይምንም አሞራውያንንም ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም ኢያቡሳውያንንም።

ዘፍጥረት 16

1 የአብራም ሚስት ሦራ ግን ለአብራም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፤ ስምዋ አጋር የተባለ ግብፃዊት ባሪያም ነበረቻት። 2 ሦራም አብራምን። እነሆ፥ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ፤ ምናልባት ከእርስዋ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርስዋ ግባ አለችው። 3 አብራምም የሦራን ቃል ሰማ። አብራምም በከነዓን ምድር አሥር ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው። 4 እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። 5 ሦራም አብራምን። መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው። 6 አብራምም ሦራን። እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች። 7 የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። 8 እርሱም። የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም። እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች። 9 የእግዚአብሔር መልአክም። ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት። 10 የእግዚአብሔር መልአክም። ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት። 11 የእግዚአብሔር መልአክም አላት። እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና። 12 እርሱም የበዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል። 13 እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። 14 ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። 15 አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው። 16 አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ። a

ዘፍጥረት 17

1 አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና። እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ 2 ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። 3 አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው። እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ 4 ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። 5 ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። 6 እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7 ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። 8 በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ። 9 እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። 10 በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11 የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12 የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። 13 በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል። 14 የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፤ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና። 15 እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። 16 እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ። 17 አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ። የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? 18 አብርሃምም እግዚአብሔርን። እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። 19 እግዚአብሔርም አለ። በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። 20 ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። 21 ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ። 22 ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። 23 አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ፥ ከአብርሃም ቤተ ሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ፥ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። 24 አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፤ 25 ልጁ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። 26 በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ ልጁ እስማኤልም። 27 በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።

ዘፍጥረት 18

1 በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። 2 ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። 3 አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ 4 ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ 5 ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት። 6 አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና። ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት። 7 አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። 8 እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። 9 እነርሱም። ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም። በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው። 10 እርሱም። የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች። 11 አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። 12 ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች። ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል። 13 እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? 14 በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች። 15 ሣራም ስለ ፈራች። አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም። አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት። 16 ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው ወደ ሰዶም አቀኑ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ሄደ። 17 እግዚአብሔርም አለ። እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? 18 አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፥ የምድር አሕዛብም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉና። 19 ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤቱን እንዲያዝዝ አውቃለሁና፤ ይህም እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ የተናገረውን ነገር ሁሉ ያመጣ ዘንድ ነው። 20 እግዚአብሔርም አለ። የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ 21 እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ። 22 ሰዎቹም ከዚያ ፊታቸውን አቀኑ፥ ወደ ሰዶምም ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት ገና ቆሞ ነበር። 23 አብርሃምም ቀረበ አለም። በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? 24 አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱንስ በእርስዋ ስለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? 25 ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን? 26 እግዚአብሔርም። በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ አለ። 27 አብርሃምም መለሰ አለም። እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ 28 ከአምሳው ጻድቃን አምስት ቢጐድሉ ከተማይቱን ሁሉ በአምስቱ ምክንያት ታጠፋለህን? ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም አለ። 29 ደግሞም ተናገረው፥ እንዲህም አለ። ምናልባት ከዚያ አርባ ቢገኙሳ? እርሱም። ለአርባው ስል አላደርገውም አለ። 30 እርሱም። ጌታዬ አይቆጣ እኔም እናገራለሁ ምናልባት ከዚያ ሠላሳ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም አለ። 31 ደግሞም። እነሆ፥ ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ አንድ ጊዜ ጀመርሁ፤ ምናልባት ከዚያ ሀያ ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ከዚያ ሀያ ቢገኙ ስለ ሀያው አላደርገውም አለ። 32 እርሱም። እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ብናገር ጌታዬ አይቆጣ፤ ምናልባት ከዚያ አሥር ቢገኙሳ? አለ። እርሱም። ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ። 33 እግዚአብሔርም ከአብርሃም ጋር ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ስፍራው ተመለሰ። a

ዘፍጥረት 19

1 ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም። 2 ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም። በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት። 3 እጅግም ዘበዘባቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ። 4 ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት። 5 ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት። በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው። 6 ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፤ 7 እንዲህም አለ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፤ 8 እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና። 9 እነርሱም። ወዲያ ሂድ አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ። ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፤ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። 10 ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት። 11 በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ። 12 ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት። ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤ 13 እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል። 14 ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም። ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው። 15 ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን። ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር። 16 እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። 17 ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው። ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ። 18 ሎጥም፤ አላቸው። ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤ 19 እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤ 20 እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን? 21 እርሱም አለው። የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤ 22 በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና። ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። 23 ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። 24 እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ 25 እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። 26 የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች። 27 አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ 28 ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ። 29 እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው። 30 ሎጥም ከዞዓር ወጣ፤ በዞዓር ይቀመጥ ዘንድ ስለ ፈራም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፤ በዋሻም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር ተቀመጠ። 31 ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት። አባታችን ሸመገለ፥ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው ከምድር ላይ የለም፤ 32 ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። 33 በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። 34 በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት። እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፤ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። 35 አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። 36 የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። 37 ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው። 38 ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም። የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው።

ዘፍጥረት 20

1 አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሱር መካከልም ተቀመጠ፤ በጌራራም በእንግድነት ተቀመጠ። 2 አብርሃምም ሚስቱን ሣራን። እኅቴ ናት አለ፤ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክም ላከና ሣራን ወሰዳት። 3 እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ እንዲህም አለው። እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና። 4 አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን? 5 እኅቴ ናት ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርስዋም ደግሞ ራስዋ። ወንድሜ ነው አለች፤ በልቤ ቅንነትና በእጄ ንጹሕነት ይህንን አደረግሁ። 6 እግዚአብሔርም በሕልም አለው። ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም። 7 አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ። 8 አቢሜሌክም በነገታው ማለደ፥ ባሪያዎቹንም ሁሉ ጠራ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ በጆሮአቸው ተናገረ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈሩ። 9 አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት አውርደሃልና፤ የማይገባ ሥራ በእኔ ሠራህብኝ። 10 አቢሜሌክም አብርሃምን አለው። ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው? 11 አብርሃምም አለ። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው። 12 እርስዋም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፤ ለእኔም ሚስት ሆነች። 13 እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት። በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው። ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ። 14 አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15 አቢሜሌክም። እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፤ በወደድኸው ተቀመጥ አለ። 16 ሣራንም አላት። እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፤ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዓይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፤ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና። 17 አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤ 18 እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና። a

ዘፍጥረት 21

1 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት። 2 ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት። 3 አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። 4 አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው። 5 አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። 6 ሣራም። እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች። 7 ደግሞም። ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና አለች። 8 ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ። 9 ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። 10 አብርሃምንም። ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው። 11 ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። 12 እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። 13 የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና። 14 አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። 15 ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው፤ 16 እርስዋም ሄደች። ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። 17 እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት። አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። 18 ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። 19 እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች። 20 እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ። 21 በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት። 22 በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ 23 አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ። 24 አብርሃምም። እኔ እምላለሁ አለ። 25 አቢሜሌክንም ባሪያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት አብርሃም ወቀሰው። 26 አቢሜሌክም አለ። ይህን ነገር ያደረገውን አላወቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም። 27 አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ። 28 አብርሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ። 29 አቢሜሌክም አብርሃምን። ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ሰባት ቄቦች በጎች ምንድር ናቸው? አለው። 30 እርሱም። እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው። 31 ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ሁለቱ ተማምለዋልና። 32 በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ። 33 አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። 34 አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ።

ዘፍጥረት 22

1 ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ። 2 የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ። 3 አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ። 4 በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ። 5 አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው። አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን። 6 አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ሁለቱም አብረው ሄዱ። 7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው። አባቴ ሆይ አለ። እርሱም። እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ። 8 አብርሃምም። ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። 9 እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው። 10 አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። 11 የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤ 12 እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። 13 አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። 14 አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል። 15 የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥ 16 እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና 17 በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ 18 የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና። 19 አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ። 20 ይህም ከሆነ በኋልላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤ 21 እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥ 22 ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው። 23 ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች። 24 ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች። a

ዘፍጥረት 23

1 የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ። 2 በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ። 3 አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፥ 4 ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ። እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር። 5 የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም። 6 ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ፤ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም። 7 አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ ለኬጢ ልጆች፥ ሰገደ። 8 እንዲህም አላቸው። ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤ 9 በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን። 10 ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት። 11 አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፤ እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር። 12 አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤ 13 የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ። ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፤ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ። 14 ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት። 15 ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር። 16 አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው፤ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ። 17 በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤ 18 እርሻው በእርሱም ያለው ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ። 19 ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ። 20 እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።

ዘፍጥረት 24

1 አብርሃምም ሸመገለ በዘመኑም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው። 2 አብርሃምም ሎሌውን የቤቱን ሽማግሌ የከብቱን ሁሉ አዛዥ አለው። 3 እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ እኔም አብሬ ከምኖራቸው ከከነዓን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳትወስድለት በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ 4 ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፥ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ። 5 ሎሌውም። ሴቲቱ ምናልባት ወደዚህ አገር ከእኔ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ልጅህን ወደ ወጣህበት አገር ልመልሰውን? አለው። 6 አብርሃምም አለው። ልጄን ወደዚያ እንዳትመልስ ተጠንቀቅ፤ 7 ከአባቴ ቤት ከተወለድሁባት ምድርም ያወጣኝ። ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ መልአኩን በፊትህ ይሰድዳል፥ ከዚያም ለልጄ ሚስትን ትወስዳለህ። 8 ሴቲቱም ከአንተ ጋር ለመምጣት እንቢ ያለች እንደ ሆነ ከዚህ ካቀረብሁህ መሐላ ንጹሕ ነህ፤ ልጄን ግን ወደዚያ አትመልሰው። 9 ሎሌውም ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች እጁን አደረገ ስለዚሁም ነገር ማለለት። 10 ሎሌውም ከጌታው ግመሎች መካከል አሥር ግመሎችን ወስዶ፥ ከጌታውም ዕቃ መልካም መልካሙን ይዞ ተነሣ፤ ተነሥቶም ወደ መስጼጦምያ ወደ ናኮር ከተማ ሄደ። 11 ሲመሽም ሴቶች ውኃ ሊቀዱ በሚወጡበት ጊዜ ከከተማይቱ ውጪ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ግመሎቹን አስበረከከ። 12 እንዲህም አለ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። 13 እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ 14 ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። 15 ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። 16 ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። 17 ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና። ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። 18 እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። 19 እርሱንም ካጠጣች በኋላ። ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። 20 ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። 21 ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። 22 ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዮው ግማሽ ሰቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ 23 እንዲህም አላት። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፤ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? 24 አለችውም። እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። 25 በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። 26 ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ ። 27 እንዲህም አለ። ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ። 28 ብላቴናይቱም ሮጠች፥ ለእናትዋም ቤት ይህን ነገር ሁሉ ተናገረች። 29 ለርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ ላባም ወደ ውጪ ወደ ውኃው ምንጭ ወደ ሰውዮው ሮጠ። 30 ቀለበቱንና አምባሮቹን በእኅቱ እጅ ባየ ጊዜ፥ የእኅቱን የርብቃንም ነገር። ያ ሰው እንዲህ አለኝ ያለችውን በሰማ ጊዜ፥ እርሱ ወደዚያ ሰው መጣ፤ እነሆም፥ በውኃው ምንጭ አጠገብ ከግመሎቹ ዘንድ ቆሞ ነበር። 31 እርሱም አለው። አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ፥ ግባ፤ ስለምን አንተ በውጪ ቆመሃል? እኔም ቤቱን ለግመሎችህም ስፍራ አዘጋጅቼአለሁ። 32 ሰውዮውም ወደ ቤት ገባ፥ ግመሎቹንም አራገፈ፤ ገለባና ገፈራም ለግመሎቹ አቀረበ፤ እግሩን ይታጠብ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ላሉት ሰዎች እግር ውኃ አቀረበ። 33 መብልንም በፊቱ አቀረበለት፤ እርሱ ግን። ነገሬን እስክናገር ድረስ አልበላም አለ። እርሱም። ተናገር አለው። 34 እርሱም አለ። እኔ የአብርሃም ሎሌ ነኝ። 35 እግዚአብሔርም ጌታዬን እጅግ ባረከው፥ አገነነውም፤ በጎችንና ላሞችን፥ ብርንም፥ ወርቅንም፥ ወንዶች ባሪያዎችንና ሴቶች ባሪያዎችን፥ ግመሎችንም አህዮችንም ሰጠው። 36 ሣራም የጌታዬ ሚስት በእርጅናው ለጌታዬ ወንድ ልጅን ወለደች፤ የነበረውንም ሁሉ ሰጠው። 37 ጌታዬም እንዲህ ሲል አማለኝ። እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስትን አትውሰድ 38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኔም ሂድ፥ ለልጄም ሚስትን ውሰድለት። 39 ጌታዬንም። ሴቲቱ ምናልባት ባትከተለኝሳ? አልሁት። 40 እርሱም አለኝ። አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁለት እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፥ መንገድህንም ያቀናል። ለልጄም ከወገኖቼ ከአባቴም ቤት ሚስትን ትወስዳለህ፤ 41 የዚያን ጊዜ ከመሐላዬ ንጹሕ ነህ፤ ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ባይሰጡህ ካማልሁህ መሐላ ንጹሕ ትሆናለህ። 42 ዛሬም ወደ ውኃው ምንጭ መጣሁ፥ እንዲህም አልሁ። የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የምሄድበትን መንገዴን ብታቀናልኝ፤ 43 እነሆ፥ እኔ በውኃው ምንጭ ላይ ቆሜአለሁ፤ ውኃ ልትቀዳ ለምትመጣውም ቆንጆ። ጥቂት ውኃ ከእንስራሽ አጠጪኝ ስላት፥ 44 እርስዋም። አንተ ጠጣ፥ ደግሞም ለግመሎችህ እቀዳለሁ የምትለኝ፥ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ ያዘጋጃት ሴት እርስዋ ትሁን። 45 እኔም የልቤን መናገር ገና ሳልፈጽም፥ እነሆ፥ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ወጣች፥ ወደ ምንጭም ወርዳ ውኃ ቀዳች፤ እኔም። እስኪ አጠጪኝ አልኋት። 46 ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ አወረደችና። አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህንም ደግሞ አጠጣለሁ አለች፤ እኔም ጠጣሁ፥ ግመሎቼንም ደግሞ አጠጣች። 47 እኔም። አንቺ የማን ልጅ ነሽ? ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም። ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ አለች፤ ቀለበትም አደረግሁላት፥ ለእጆችዋም አምባሮች አደረግሁላት። 48 በግምባሬም አጎነበስሁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገድሁ፤ የጌታዬን የወንድሙን ልጅ ለልጁ እወስድ ዘንድ በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። 49 አሁንም ቸርነትና እውነት ለጌታዬ ትሠሩ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ ይህም ባይሆን ንገሩኝ፥ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ እል ዘንድ። 50 ላባና ባቱኤልም መለሱ እንዲህም አሉ። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአል ክፉም በጎም ልንመልስልህ አንችልም። 51 ርብቃ እንኋት በፊትህ ናት፤ ይዘሃት ሂድ፥ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ለጌታህም ልጅ ሚስት ትሁን። 52 የአብርሃምም ሎሌ ነገራቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ምድር ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 53 ሎሌውም የብርና የወርቅ ጌጥ ልብስም አወጣ፥ ለርብቃም ሰጣት፤ የከበረ ስጦታንም ለወንድምዋና ለእናትዋ አቀረበ። 54 እርሱም ከእርሱም ጋር ያሉት በሉ ጠጡም፥ ከዚያም አደሩ፤ ማልደውም ተነሡና። ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው ። 55 ወንድምዋና እናትዋም። ብላቴናይቱ አንድ አሥር ቀን ያህል እንኳ ከእኛ ዘንድ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለች አሉ። 56 እርሱም። እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው። 57 እነርሱም። ብላቴናይቱን እንጥራና ከአፍዋ እንጠይቅ አሉ። 58 ርብቃንም ጠርተው። ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም። እሄዳለሁ አለች። 59 እኅታቸውንም ርብቃን ሞግዚትዋንም የአብርሃምን ሎሌና ሰዎቹንም አሰናበቱአቸው። 60 ርብቃንም መረቁአትና። አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። 61 ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎችም ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት፤ ሎሌውም ርብቃን ተቀብሎ ሄደ። 62 ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ በሚሉአት ምንጭ መንገድ መጣ፤ በአዜብ ምድር ተቀምጦ ነበርና። 63 ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር፤ ዓይኖቹንም አቀና፥ እነሆም ግመሎች ሲመጡ አየ። 64 ርብቃም ዓይኖችዋን አቀናች፥ ይስሐቅንም አየች፥ ከግመልም ወረደች። 65 ሎሌውንም። ሊገናኘን በሜዳ የሚመጣ ይህ ሰው ማን ነው? አለችው። ሎሌውም። እርሱ ጌታዬ ነው አላት፤ እርስዋም መሸፈኛ ወስዳ ተከናነበች። 66 ሎሌውም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። a

ዘፍጥረት 25

1 አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ። 2 እርስዋም ዘምራንን፥ ዮቅሳንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የስቦቅን፥ ስዌሕን ወለደችለት። 3 ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን፥ ለጡሳውያን፥ ለኡማውያን ናቸው። 4 የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። 5 አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤ 6 የአብርሃምም ለነበሩ ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው። 7 አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። 8 አብርሃምም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካም ሽምግልናም ሞተ፤ ሸመገለም፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። 9 ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት ። 10 አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ። 11 አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ። 12 የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ 13 የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ 14 ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥ 15 ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ። 16 የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። 17 እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞተም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። 18 መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ። 19 የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ 20 ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፤ እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት። 21 ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች። 22 ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም። እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች። 23 እግዚአብሔርም አላት። ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። 24 ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። 25 በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ። 26 ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር። 27 ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር። 28 ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፥ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። 29 ያዕቆብም ወጥ ሠራ፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ 30 ዔሳውም ያዕቆብን። ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው፤ ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ። 31 ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው። 32 ዔሳውም። እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ ። 33 ያዕቆብም። እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ። 34 ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት።

ዘፍጥረት 26

1 በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ በላይ ራብ ሆነ፤ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። 2 እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው። ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። 3 በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፤ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ። 4 ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም አህዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ 5 አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና። 6 ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። 7 የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት፤ እርሱም። እኅቴ ናት አለ፤ የዚህ ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፤ እርስዋ ውብ ነበረችና። 8 በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። 9 አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ፥ እንዲህም አለው። እነሆ ሚስትህ ናት፤ እንዴትስ እርስዋን። እኅቴ ናት አልህ? ይስሐቅም። በእርስዋ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው አለው። 10 አቢሜሌክም አለ። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር። 11 አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ። ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት ብሎ አዘዘ። 12 ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፤ እግዚአብሔርም ባረከው። 13 ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፤ 14 የበግና የላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፤ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት። 15 በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጕድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው አፈርንም ሞሉባቸው። 16 አቢሜሌክም ይስሐቅን። ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና አለው። 17 ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ። 18 ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጕድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፤ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፤ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። 19 የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጕድጓድ አገኙ። 20 የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር። ውኃው የእኛ ነው ሲሉ ተከራከሩ፤ የዚያችንም ጕድጓድ ስም ኤሴቅ ብሎ ጠራት፥ ለእርስዋ ሲሉ ተጣልተዋልና። 21 ሌላ ጕድጓድም ማሱ፥ ስለ እርስዋም ደግሞ ተጣሉ፤ ስምዋንም ስጥና ብሎ ጠራት ። 22 ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርስዋም አልተጣሉም፤ ስምዋንም ርኆቦት ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል። አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን። 23 24 ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው። እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ ባሪያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ። 25 በዚያም መሠዊያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፤ የይስሐቅም ሎሌዎች በዚያ ጕድጓድ ማሱ። 26 አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱም አለቃ ፊኮል ከጌራራ ወደ እርሱ ሄዱ። 27 ይስሐቅም። ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? እናንተ ጠልታችሁኛል፥ ከእናንተም ለይታችሁ አሳድዳችሁኛል አላቸው። 28 29 እነርሱም አሉት። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንዳለ በእርግጥ አየን፤ ስለዚህም። በእኛና በአንተ መካከል መሐላ ይሁን፤ እኛ አንተን እንዳልነካንህ፥ በጎነትንም ብቻ እንዳሳየንህ፥ በደኅናም እንደ ሰደድንህ፥ አንተም ክፉ እንዳትሠራብን ቃል ኪዳን ከአንተ ጋር እናድርግ አልን፤ አንተ አሁን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረክህ ነህ። 30 ይስሐቅም ማዕድ አቀረበላቸው፥ በሉም ጠጡም። 31 ማልደውም ተነሡ፥ እርስ በርሳቸውም ተማማሉ፤ ይስሐቅም አሰናበታቸው፥ ከእርሱም ወጥተው በደኅና ሄዱ። 32 በዚያም ቀን የይስሐቅ ሎሌዎች መጡ፥ ስለቈፈሩአትም ጕድጓድ። ውኃ አገኘን ብለው ነገሩት። 33 ስምዋንም ሳቤህ ብሎ ጠራት፤ ስለዚህም የከተማይቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ነው። 34 ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የኬጢያዊ የብኤሪን ልጅ ዮዲትን፥ የኬጢያዊ የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ፤ 35 እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር። a

ዘፍጥረት 27

1 ይስሐቅ ሸምግሎ ዓይኖቹ ከማየት በፈዘዙ ጊዜ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ። ልጄ ሆይ አለው፤ እርሱም። እነሆ አለሁ አለው። 2 እርሱም አለው። እነሆ እኔ አረጀሁ፥ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። 3 አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፥ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፥ አደንም አድንልኝ፤ 4 ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ የጣፈጠ መብል እኔ እንደምወደው አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ። 5 ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም አደን አድኖ ሊያመጣ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። 6 ርብቃም ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው። እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው። 7 አደን አድነህ አምጣልኝ፥ ሳልሞትም በልቼ በእግዚአብሔር ፊት እንድባርክህ የጣፈጠ መብል አድርግልኝ ብሎ ሲነግረው ሰማሁ። 8 አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እኔ በማዝዝህ ነገር ስማኝ፤ 9 ወደ መንጋ ሄደህ ሁለት መልካካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ጣፋጭ መብል ለአባትህ እንደሚወደው አደርጋለሁ፤ 10 ለአባትህም፥ ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ታገባለታለህ። 11 ያዕቆብም ርብቃን እናቱን አላት። እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤ 12 ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደሚዘብት እሆናለሁ፤ መርገምንም በላዬ አመጣለሁ፥ በረከትን አይደለም። 13 እናቱም አለችው። ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፤ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና አምጣልኝ። 14 ሄዶም አመጣ፥ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም የጣፈጠውን መብል አባቱ እንደሚወደው አደረገች። 15 ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረችውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፥ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አለበሰችው፤ 16 የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤ 17 የሠራችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው። 18 ወደ አባቱም ገብቶ። አባቴ ሆይ አለው እርሱም። እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አለ። 19 ያዕቆብም አባቱን አለው። የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኽኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና በልና ተቀመጥ፥ ካደንሁትም ብላ። 20 ይስሐቅም ልጁን። ልጄ ሆይ፥ እንዴት ፈጥነህ አገኘኸው? አለው። እርሱም። እግዚአብሔር አምላክህ ወደ እኔ ስለ አቀረበው ነው አለ። 21 ይስሐቅም ያዕቆብን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ እዳስስህ ዘንድ ቅረበኝ አለው። 22 ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፥ እንዲህም። ይህ ድምፅ የያዕቆብም ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው አለው። 23 እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ስለዚህም ባረከው። 24 አለውም። አንተ ልጄ ዔሳው ነህን? እርሱም። እኔ ነኝ አለ። 25 እርሱም። ከልጄ አደን እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አቅርብልኝ አለ። አቀረበለትም፥ በላም፤ የወይን ጠጅ አመጣለት፥ እርሱም ጠጣ። 26 አባቱ ይስሐቅም። ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ ሳመኝም አለው። 27 ወደ እርሱም ቀረበ፥ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፥ ባረከውም፥ እንዲህም አለ። የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው፤ 28 እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል ከምድርም ስብ የእህልንም የወይንንም ብዛት ይስጥህ፤ 29 አሕዛብ ይገዙልህ ሕዝብም ይስገዱልህ፤ ለወንድሞችህ ጌታ ሁን፥ የእናትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን። 30 ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብም ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ከወጣ በኋላ፥ ወዲያው በዚያው ጊዜ ዔሳው ከአደኑ መጥቶ ገባ። 31 እርሱም ደግሞ ጣፋጭ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አገባ፤ አባቱንም። አባቴ ይነሣ፥ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ከልጁ አደን ይብላ አለው። 32 አባቱ ይስሐቅም። አንተ ማን ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ አለው። 33 ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ እንዲህም አለ። ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣ ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ሆኖ ይኖራል። 34 ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፥ አባቱንም። አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ አለው። 35 እርሱም። ወንድምህ በተንኮል ገብቶ በረከትህን ወሰደብህ አለ። 36 እርሱም አለ። በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፥ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ ብኵርናዬን ወሰደ፥ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ። ደግሞም። ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን? አለ። 37 ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው። እነሆ፥ ጌታህ አደረግሁት፥ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች ይሆኑ ዘንድ ሰጠሁት፥ በእህልም በወይንም አበረታሁት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግ? 38 ዔሳውም አባቱን አለው። አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ። ዔሳውም ቃሉን አንሥቶ አለቀሰ። 39 አባቱ ይስሐቅም መለሰ አለውም። እነሆ፥ መኖሪያህ ከምድር ስብ ከላይ ከሚገኝ ከሰማይም ጠል ይሆናል፤ 40 በሰይፍህም ትኖራለህ፥ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ። 41 ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ። ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል፥ ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ። 42 ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል ደረሰላት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው፥ አለችውም። እነሆ፥ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል። 43 አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤ 44 በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ፥ የወንድምህ ቍጣ እስኪበርድ ድረስ፤ 45 የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ፥ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ? 46 ርብቃም ይስሐቅን አለችው። ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?

ዘፍጥረት 28

1 ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፥ ባረከውም፥ እንዲህ ብሎም አዘዘው። ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፤ 2 ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፤ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ። 3 ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ፥ ያፍራህ፥ ያብዛህ፤ 4 ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃምን በርከት ለአንተ ይስጥህ፥ ለዘርህም እንዲሁ እንደ አንተ። 5 ይስሐቅም ያዕቆብን ሰደደው፥ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊ ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ። 6 ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው ባየ ጊዜ፥ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለት ወንዞች መካካል እንደ ሰደደው፥ በባረከውም ጊዜ። ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ ብሎ እንዳዘዘው፥ 7 ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደሄደ፥ 8 የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደሆኑ ዔሳው ባየ ጊዜ፥ 9 ዔሳው ወደ እስማኤል ሄደ፥ ማዕሌትንም በፊት ካሉት ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባ፤ እርስዋም የአብርሃም ልጅ የሆነ የእስማኤል ልጅና የነባዮት እኅት ናት። 10 ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። 11 ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። 12 ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። 13 እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ። የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ 14 ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። 15 እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና። 16 ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ። በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ። 17 ፈራ፥ እንዲህም አለ። ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው። 18 ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት። 19 ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ። 20 ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ 21 ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤ 22 ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ። a

ዘፍጥረት 29

1 ያዕቆብም ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሰዎች አገር ሄደ። 2 በሜዳውም እነሆ ጕድጓድን አየ፥ በዚያም ሦስት የበጎች መንጎች በላዩ ተመስገው ነበር፤ ከዚያ ጕድጓድ በጎቹን ያጠጡ ነበርና፤ በጕድጓዱም አፍ የነበረው ድንጋይ ትልቅ ነበረ። 3 መንጎችም ሁሉ ከዚያ በተከማቹ ጊዜ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ ገለል አድርገው በጎቹን ያጠጡ ነበር፤ ድንጋዩንም ወደ ስፍራው መልሰው በጕድጓዱ አፍ እንደ ገና ይገጥሙት ነበር። 4 ያዕቆብም። ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንት የወዴት ናችሁ? አላቸው። እነርሱም። እኛ የካራን ነን አሉት። 5 የናኮርን ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን? አላቸው። እነርሱም። እናውቀዋለን አሉት። 6 እርሱ። ደኅና ነውን? አላቸው። እነርሱም። አዎን ደኅና ነው፤ አሁንም ልጁ ራሔል ከበጎች ጋር መጣች አሉት። 7 እርሱም። ቀኑ ገና ቀትር ነው፥ ከብቶቹ የሚከማቹበት ሰዓቱም ገና አልደረሰም፤ አሁንም በጎቹን አጠጡና ሄዳችሁ አሰማሩአቸው አላቸው። 8 እነርሱም አሉ። መንጎች ሁሉ እስኪከማቹና ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ እስኪገለብጡት ድረስ አንችልም፤ ከዚያም በኋላ በጎቹን እናጠጣለን። 9 እርሱም ገና ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ የላባ ልጅ ራሔል ከአባትዋ በጎች ጋር ደረሰች፤ እርስዋ የአባትዋን በጎች ትጠብቅ ነበርና። 10 ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የእጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጕድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የአጎቱን የላባን በጎችንም አጠጣ። 11 ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 12 ያዕቆብም የአባትዋ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፤ እርስዋም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው። 13 ላባም የእኅቱን ልጅ የያዕቆብን ወሬ በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ሮጠ፥ አቅፎም ሳመው፥ ወደ ቤቱም አገባው። ነገሩንም ሁሉ ለላባ ነገረው ። 14 ላባም። በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ። 15 ላባም ያዕቆብን። ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው። 16 ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ። 17 ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ። 18 ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፤ እንዲህም አለ። ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ። 19 ላባም። ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ። 20 ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት። 21 ያዕቆብም ላባን። ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው። 22 ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ። 23 በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። 24 ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት። 25 በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም። ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው። 26 ላባም እንዲህ አለ። በአገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤ 27 ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ። 28 ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፥ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው። 29 ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት ። 30 ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፤ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት። 31 እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። 32 ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፤ እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና። 33 ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ደገመኝ አለች፤ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው። 34 ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው። 35 ደግሞም ፀነስች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።

ዘፍጥረት 30

1 ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፤ ያቆብንም። ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው። 2 ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ። በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት። 3 እርስዋም ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ድረስባት፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች። 4 ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት። 5 ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። 6 ራሔልም። እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። 7 የራሔልም ባሪያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች። 8 ራሔልም። ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው። 9 ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው። 10 የልያ ባሪያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች። 11 ልያም። ጉድ አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው። 12 የልያ ባሪያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች። 13 ልያም። ደስታ ሆነልኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው። 14 ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን። የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት። 15 እርስዋም። ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን? አለቻት። ራሔልም። እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች። 16 ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው። ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ። 17 እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 18 ልያም። ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። 19 ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 20 ልያም። እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። 21 ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት። 22 እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤ 23 ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና። እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ አለች፤ 24 ስሙንም። እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው። 25 ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው። ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ። 26 ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና። 27 ላባም። በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው። 28 ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ አለ። 29 እርሱም አለው። እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ። 30 ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው? 31 እርሱም። የምሰጥህ ምንድር ነው? አለ። ያዕቆብም አለው። ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደ ገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም። 32 ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር ያለበቱን እለያለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ። 33 ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ። 34 ላባም። እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን አለ። 35 በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው። 36 በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር። 37 ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። 38 የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎቹ ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር። 39 በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ። 40 ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ሁሉ በላባ በጎች ፊት ለፊት አኖረ፤ መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም። 41 እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፤ 42 በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፤ የደከሙትም ለላባ፥ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ። 43 ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት።

ዘፍጥረት 31

1 ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ። 2 ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም። 3 እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው። 4 ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥ 5 እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። 6 እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። 8 ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ። 9 እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ። 10 እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ። 11 የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት። 12 እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። 13 ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ። 14 ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን? 15 እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና። 16 ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ። 17 ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18 መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። 19 ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች። 20 ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም። 21 እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና። 22 በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው። 23 ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት። 24 እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው። 25 ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ። 26 ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው። 27 ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም? 28 ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ። 29 ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ። 30 አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ? 31 ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ። 32 አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና።

ዘፍጥረት 32

1 ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት። 2 ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው። 3 ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ለጌታዬ ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት። በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፤ 5 ላሞችንም አህዮችንም በጎችን ወንዶች ባሪያዎችንም ሴቶች ባሪያዎችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማስታወቅ ላክሁ። 6 መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት። ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ። 7 ያዕቆብም እጅግ ፈርቶ ተጨነቀ፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች መንጎችንም ላሞችንም ግመሎችንም በሁለት ወገን ከፈላቸው፤ 8 እንዲህም አለ። ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል። 9 ያዕቆብም አለ። የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ። ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤ 10 ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። 11 ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። 12 አንተም። በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር። 13 በዚያችም ሌሊት ከዚያው አደረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻን አወጣ፤ 14 ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥ 15 ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ አሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ አሥርም የእህያ ግልገሎችን። 16 መንጎቹን በየወገኑ ከፍሎ በባሪያዎቹ እጅ አደረጋቸው፤ ባሪያዎቹንም። በፊቴ እለፉ መንጋውንና መንጋውንም አራርቁት አለ። 17 የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው። ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ። አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው? ብሎ የጠየቀህም እንደ ሆነ፥ 18 በዚያን ጊዜ አንተ። ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደደው የባሪያህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው በለው። 19 እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ። ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤ 20 እንዲህም በሉት። እነሆ ባሪያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና። 21 እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ። 22 በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንዱንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። 23 ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው፥ ከብቱንም ሁሉ አሻገረ። 24 ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። 25 እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ። 26 እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው። 27 እንዲህም አለው። ስምህ ማን ነው? እርሱም። ያዕቆብ ነኝ አለው። 28 አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና። 29 ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው። 30 ያዕቆብም። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም Dኒኤል ብሎ ጠራው። 31 Dኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32 ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርችን ሹልዳ አደንዝዞአልና። q ቍ@ 30 ጵኒኤል የሚለውን ቃል የግእዝ መጽሐፍ ራእየ እግዚአብሔር ይለዋል። a

ዘፍጥረት 33

1 ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ባሪያዎች አደረጋቸው፤ 2 ባሪያዎችንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም በኋለኛው ስፍራ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ። 3 እርሱም በፊታቸው አለፈ፤ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ። 4 ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ተላቀሱም። 5 ዓይኑንም አነሣና ሴቶችንና ልጆችን አየ፥ እንዲህም አለ። እነዚህ ምኖችህ ናቸው? እርሱም። እግዚአብሔር ለእኔ ለባሪያህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው አለ። 6 ሴቶች ባሪያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ፤ 7 ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱ፤ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ። 8 እርሱም። ያገኘሁት ይህ ሠራዊት ሁሉ ምንህ ነው? አለ። እርሱም። በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው አለ። 9 ዔሳውም። ለእኔ ብዙ አለኝ፤ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ። 10 ያዕቆብም አለ። እንደዚህ አይደለም፤ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፤ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና። 11 ይህችንም ያመጣሁልህን በረከቴን ተቀበል፤ እግዚአብሔር በቸርነት ሰጥቶኛልና፥ ለእኔም ብዙ አለኝና። እስኪቀበለውም ድረስ ዘበዘበው። 12 እርሱም። ተነሣና እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ አለ። 13 እርሱም አለው። ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ። 14 ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ። 15 ዔሳውም። ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን? አለ። እርሱም። ይህ ለምንድር ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል አለ። 16 ዔሳውም በዚያን ቀን ወደ ሴይር መንገዱን ተመለሰ። 17 ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ በዚያም ለእርሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶችም ዳሶችን አደረገ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ሱኮት ብሎ ጠራው። 18 ያዕቆብም ከሁለት ወንዞች መካከል በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም ከተማ በደኅንነት መጣ፤ በከተማይቱም ፊት ሰፈረ። 19 ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የእርሻውን ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው። 20 በዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።

ዘፍጥረት 34

1 ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። 2 የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። 3 ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት። 4 ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው። 5 ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ። 6 የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። 7 የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና። 8 ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት። 9 ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። 10 ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም። 11 ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። 12 ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ። 13 የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤ 14 እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና። 15 እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤ 16 ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። 17 ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን። 18 ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። 19 ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። 20 ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ። 21 እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። 22 ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ። 23 ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ። 24 ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። 25 ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤ 26 ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። 27 የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤ 28 በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። 29 ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። 30 ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ። 31 እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a

ዘፍጥረት 35

1 እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው። ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ። 2 ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤ 3 ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ። 4 በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው። 5 ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም። 6 ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት። 7 በዚያም መሰውያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና። 8 የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፥ በቤቴልም ከአድባር ዛፍ በታች ተቀበረች፤ ስሙም አሎንባኩት ተብሎ ተጠራ። 9 እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም። 10 እግዚአብሔርም። ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። 11 እግዚአብሔርም አለው። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ። 13 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14 ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት። 15 ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው። 16 ከቤቴልም ተነሡ፤ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች። 17 ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ። አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት። 18 እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው። 19 ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተልሔም ናት። 20 ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው። 21 እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ። 22 እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፤ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው፤ 23 የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤ 24 25 የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ የራሔል ባርያ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤ 26 የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው። 27 ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂርያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ። 28 የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ። 29 ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፤ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

ዘፍጥረት 36

1 የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፤ እርሱም ኤዶም ነው። 2 ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን፥ የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳትን አህሊባማን፥ 3 የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ቤሴሞትን። 4 ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፤ ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤ 5 አህሊባማም የዑስን፥ የዕላምን፥ ቆሬን ወለደች፤ በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። 6 ዔሳውም ሚስቶቹን ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን ቤተሰቡንም ሁሉ ከብቱንም ሁሉ እንስሶቹንም ሁሉ በከነዓንም አገር ያገኘውን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ወደ ሌላ አገር ሄደ። 7 ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፤ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። 8 ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፤ ዔሳውም ኤዶም ነው። 9 በሴይር ተራራ የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት የዔሳው ትውልድም ይህ ነው። 10 የዔሳው ልጆች ስም ይህ ነው፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝ፤ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጅ ራጉኤል። 11 የኤልፋዝም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጎቶም፥ ቄኔዝ። 12 ቲምናዕም ለዔሳው ልጅ ለኤልፋዝ የጭን ገረድ ነበረች፥ አማሌቅንም ለኤልፋዝ ወለደችለት፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጆች እነዚህ ናቸው። 13 የራጉኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሣማ፥ ሚዛህ፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው። 14 የፅብዖን ልጅ የዓና ልጅ የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳውም የዑስን፥ የዕላማን፥ ቆሬን ወለደች። 15 የዔሳው ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳው የበኵር ለኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን አለቃ፥ ኦማር አለቃ፥ ስፎ አለቃ፥ ቄኔዝ አለቃ፥ 16 ቆሬ አለቃ፥ ጎቶም አለቃ፥ አማሌቅ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህ የዓዳ ልጆች ናቸው። 17 የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት አለቃ፥ ዛራ አለቃ፥ ሣማ አለቃ፥ ሚዛህ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የራጉኤል ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው። 18 የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የዑስ አለቃ፥ የዕላማ አለቃ፥ ቆሬ አለቃ፤ የዔሳው ሚስት የዓና ልጅ የአህሊባማ አለቆች እነዚህ ናቸው። 19 የዔሳው ልጆችና አለቆቻቸው እነዚህ ናቸው፤ እርሱም ኤዶም ነው። 20 በዚያች አገር የተቀመጡ የሖሪው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን፥ ሦባል፥ ፅብዖን፥ ዓና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን፤ 21 እነዚህ በኤዶም ምድር የሖሪው የሴይር ልጆች አለቆች ናቸው። 22 የሎጣን ልጆችም ሖሪ፥ ሄማም ናቸው፤ የሎጣንም እኅት ቲምናዕ ናት። 23 የሦባል ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ አውናም። 24 የፅብዖን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ አያ፥ ዓና፤ ይህም ዓና በምድረ በዳ የአባቱን የፅብዖንን አህዮች ሲጠብቅ ፍልውኆችን ያገኘ ነው። 25 የዓና ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ 26 ዲሶን፥ አህሊባማም የዓና ሴት ልጅ። የዲሶንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሔምዳን፥ ኤስባን፥ ይትራን፥ ክራን። 27 የኤጽር ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ቢልሐን፥ ዛዕዋን፥ ዓቃን። 28 የዲሳን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዑፅ፥ አራን። 29 የሖሪ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን አለቃ፥ ሦባል አለቃ፥ ፅብዖን አለቃ፥ 30 ዓና አለቃ፥ ዲሶን አለቃ፥ ኤጽር አለቃ፥ ዲሳን አለቃ፤ በሴይር ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪ አለቆቹ እነዚህ ናቸው። 31 በእስራኤል ልጆች ላይ ንጉሥ ከመኖሩ በፊት በኤዶም አገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። 32 በኤዶምም የቢዖር ልጅ ባላቅ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ናት። 33 ባላቅም ሞተ፥ በስፍራውም የባሶራው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ። 34 ኢዮባብም ሞተ፥ በስፍራውም የቴማኒው አገር ሑሳም ነገሠ። 35 ሑሳምም ሞተ፥ በስፍራውም የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ሜዳ የመታ የባዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዓዊት ተባለ። 36 ሃዳድም ሞተ፥ በስፍራውም የመሥሬቃው ሠምላ ነገሠ። 37 ሠምላም ሞተ፥ በስፍራውም በወንዝ አጠገብ ካለችው ከርሆቦት ሳኦል ነገሠ። 38 ሳኦልም ሞተ፥ በስፍራውም የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ነገሠ። 39 የዓክቦር ልጅ በኣልሐናንም ሞተ፥ በስፍራውም ሃዳር ነገሠ፤ የከተማውም ስም ፋዑ ነው፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ መጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባላለች። 40 የዔሳውም የአለቆቹ ስም በወገናቸው በስፍራቸው በስማቸውም ይህ ነው፤ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥ 41 አህሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥ 42 ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብሳር አለቃ፥ 43 መግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፥ እነዚህ በግዛታቸው ምድር በየመኖሪያቸው የኤዶም አለቆች ናቸው። የኤዶማውያን አባት ይህ ዔሳው ነው። a

ዘፍጥረት 37

1 ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ። 2 የያዕቆብም ትውልድ ይህ ነው። ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ። 3 እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፤ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት ። 4 ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም። 5 ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት። 6 እርሱም አላቸው። እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤ 7 እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ። 8 ወንድሞቹም። በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት። 9 ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ። እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ። 10 ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው። ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን? 11 ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር። 12 ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ። 13 እስራኤልም ዮሴፍን። ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም። እነሆኝ አለው ። 14 እርሱም። ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ አለው። እንዲህም ከኬብሮን ቈላ ሰደደው፥ ወደ ሴኬምም መጣ። 15 እነሆም በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም። ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው። 16 እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ። 17 ሰውዮውም። ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው። 18 እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። 19 አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። 20 አሁንም ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። 21 ሮቤልም ይህን ሰማ፥ ከእጃቸውም አዳነው፥ እንዲህም አለ። ሕይወቱን አናጥፋ። 22 ሮቤል። ደም አታፍስሱ፤ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው። 23 እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፤ 24 ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ። 25 እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር። 26 ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው። ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነው? 27 ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና። ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት። 28 የምድያም ነጋዶችም አለፉ፤ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት፤ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። 29 ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም፤ ልብሱንም ቀደደ። 30 ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ። ብላቴናው የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ። 31 የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት። 32 ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት፥ እንዲህም አሉት። ይህንን አገኘነ፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው። 33 እርሱም አውቆ። የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ። 34 ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ። 35 ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ። ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ። 36 እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።

ዘፍጥረት 38

1 በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ። 2 ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ ወሰዳትም፥ ወደ እርስዋም ገባ። 3 ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4 ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው። 5 እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፥ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች። 6 ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። 7 የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 8 ይሁዳም አውናን። ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፥ አግባትም፥ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው። 9 አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር። 10 ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው። 11 ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን። ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች። 12 ከብዙ ዘመንም በኋላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፥ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፥ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ። 13 ለትዕማርም። እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት። 14 እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች፥ ተሸፈነችም፥ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና። 15 ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው፤ ፊትዋን ተሸፍና ነበርና። 16 ወደ እርስዋም አዘነበለ። እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤ እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም። ወደኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው። 17 የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም። እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው። 18 እርሱም። ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም። ቀለበትህን፥ አምባርህን፥ በእጅህ ያለውን በትር አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ጋር ደረሰ፥ እርስዋም ፀነሰችለት። 19 እርስዋም ተነሥታ ሄደች፥ መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች። 20 ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም። 21 እርሱም የአገሩን ሰዎች። በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት። 22 ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው። አላገኘኋትም፤ የአገሩም ሰዎች ደግሞ። ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ። 23 ይሁዳም። እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት፥ አንተም አላገኘሃትም አለ። 24 እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ። ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም። አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ። 25 እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች። ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት፥ ይህ አምባር፥ ይህ በትር የማን ነው? 26 ይሁዳም አወቀ። ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም። 27 በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ። 28 ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች። ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች። 29 እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም። ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው። 30 ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ። a 30"> 30 30"> Потом вышел брат его с красной нитью на руке. И наречено ему имя: Зара.

ዘፍጥረት 39

1 ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው። 2 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ። 3 ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ። 4 ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፥ እርሱንም ያገለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። 5 እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ። 6 ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ። 7 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው። 8 እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት። እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ 9 ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ? 10 ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም። 11 እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ፤ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም። 12 ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ። 13 እንዲህም ሆነ፤ ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ፥ 14 የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው። እዩ፤ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፥ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤ 15 ድምፄንም ከፍ አድርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ። 16 ጌታው ወደ ቤቱ እስኪገባ ድረስም ልብሱን ከእርስዋ ዘንድ አኖረች። 17 ይህንም ነገር እንዲህ ብላ ነገረችው። ያገባህልን ዕብራዊው ባሪያ ሊሣለቅብኝ ወደ እኔ ገባ፤ 18 እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን በእጄ ተወና ወደ ውጭ ሸሸ። 19 ጌታውም። ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ ብላ የነገረችውን የሚስቱን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። 20 የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው፤ ከዚያም በግዞት ነበረ። 21 እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው። 22 የግዞት ቤቱም አለቃ በግዞት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም የሚደረገው ነገር ሁሉ እርሱ የሚያደርገው ነበረ። 23 የግዞት ቤቱም አለቃ በእጁ ያለውን ነገር ከቶ አላሰበም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር።

ዘፍጥረት 40

1 ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ። 2 ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤ 3 ዮሴፍ ታስሮ በነበረበትም በግዞት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው። 4 የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ። 5 በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ። 6 ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፥ እነሆም አዝነው አያቸው። 7 በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው። እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኋል? 8 እነርሱም። ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት። ዮሴፍም አላቸው። ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ። 9 የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው። በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ፥ 10 በዛፊቱም ሦስት አረግ አለባት፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤ 11 የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበረ፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፥ ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት። 12 ዮሴፍም አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ አረግ ሦስት ቀን ነው፤ 13 እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። 14 ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤ 15 እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም። 16 የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው። እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር፥ እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤ 17 በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋሪዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር። 18 ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19 እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል። 20 በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ። 21 የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው፥ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤ 22 የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው፥ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው። 23 የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ። a

ዘፍጥረት 41

1 ከሁለት ዓመት በኋላም ፈርዖን ሕልምን አየ፥ እነሆም፥ በወንዙ ዳር ቆሞ ነበር። 2 እነሆም፥ መልካቸው ያማረ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፥ በውኃውም ዳር በመስኩ ይሰማሩ ነበር። 3 ከእነርሱም በኋላ እነሆ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዝ ወጡ፥ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ይቆሙ ነበር። 4 መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያም ላሞች መልካቸው ያማረውን ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ። 5 ደግሞም ተኛ ሁለተኛም ሕልምን አየ። እነሆም በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ ያማሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 6 እነሆም ከእነርሱ በኋላ የሰለቱና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 7 የሰለቱትም እሸቶች ሰባቱን ያማሩና የዳበሩ እሸቶች ዋጡአቸው። 8 ፈርዖንም ነቃ፥ እነሆም ሕልም ነበረ። በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታወከችበት፤ ወደ ሕልም ተርጓሚዎች ሁሉ ወደ ግብፅ ጠቢባንም ሁሉ ልኮ ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው፥ ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን የሚተረጕም አልተገኘም። 9 የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፈዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ። እኔ ኃጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤ 10 ፈርዖን በባሪይዎቹ ላይ ተቆጣ፥ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ስፍራ በዘበኞች አለቃ ቤት አኖረን፤ 11 እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን፥ እኔና እርሱ፤ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን። 12 በዚያም የዘበኞቹ አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጕልማሳ ከእኛ ጋር ነበረ፤ ለእርሱም ነገርነው፥ ሕልማችንንም ተረጐመልን፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሕልሙ ተረጐመልን። 13 እንዲህም ሆነ፤ እንደ ተረጐመልን እንደዚያው ሆነ፤ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ፥ እርሱም ተሰቀለ። 14 ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራ፥ ከግዞት ቤትም አስቸኰሉት፤ እርሱም ተላጨ፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ ፈርዖንም ገባ። 15 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ሕልምን አየሁ፥ የሚተረጕመውም አልተገኘም፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ። 16 ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ። ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በደኅንነት ይመልስለታል። 17 ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው። እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ 18 እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፥ በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤ 19 ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤ 20 የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ወፍራሞቹን ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፥ 21 በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም እንደተዋጡ አልታወቀም፥ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ። ነቃሁም። 22 በሕልሜም እነሆ የዳበሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች በአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤ 23 ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደረቁና የሰለቱ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 24 የሰለቱት እሸቶች ያማሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ የሚተረጕምልኝም አጣሁ። 25 ዮሴፍም ፈርዖንን አለው። የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን ነግሮታል። 26 ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙ አንድ ነው። 27 ከእነርሱም በኋላ የወጡት የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ የሰለቱትና የምሥራቅ ነፋስ የመታቸው ሰባቱም እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው። 28 ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው። 29 እነሆ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤ 30 ደግሞ ከዚህ በኋላ የሰባት ዓመት ራብ ይመጣል፥ በግብፅ አገር የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል፤ ራብም ምድርን በጣም ያጠፋል፤ 31 በኋላ ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣም በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፥ እጅግ ጽኑ ይሆናልና። 32 ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል። 33 አሁንም ፈርዖን ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ፥ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው። 34 ፈርዖን በምድር ላይ ሹማምትን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ። 35 የሚመጡትን የመልካሞቹን ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፥ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ። 36 በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም። 37 ነገሩም በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆነ፤ 38 ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው። በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን? 39 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም፥ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና። 40 አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፥ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ። 41 ፈርዖንም ዮሴፍን። በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ አለው። 42 ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ በዮሴፍ እጅም አደረገው፥ ነጭ የተልባ እግር ልብስንም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍን አደረገለት፤ 43 የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፥ አዋጅ ነጋሪም። ስገዱ እያለ በፊት በፊቱ ይጮኽ ነበር፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ተሾመ። 44 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እኔ ፈርዖን ነኝ፤ በግብፅ አገር ሁሉ ያለ አንተ ማንም እጁንም እግሩንም አያንሣ። 45 ፈርዖንም የዮሴፍን ስም ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ጠራው፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ የምትሆን አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በግብፅ ምድር ሁሉ ወጣ። 46 ዮሴፍም በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ የግብፅ ምድርንም ሁሉ ዞረ። 47 በሰባቱም በጥጋብ ዓመታት የምድሪቱ ፍሬ ክምር ሆነ። 48 በግብፅ ምድር ሁሉ ያለውን የሰባቱን ዓመት እህል ሁሉ ሰበሰበ፥ እህልንም በከተሞቹ አደለበ፤ በየከተማይቱ ዙሪያ ያለውን የእርሻውን እህል ሁሉ በዚያው ከተተ። 49 ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ስንዴን አከማቸ፥ መስፈርን እስኪተው ድረስ፤ ሊሰፈር አልተቻለምና። 50 ለዮሴፍም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ አስናት የወለደችለት ሁለት ልጆች የራብ ዘመን ገና ሳይመጣ ተወለዱለት። 51 ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ፤ 52 የሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ። 53 በግብፅ ምድር የነበረውም የሰባቱ ዓመት ጥጋብ አለፈ፥ 54 ዮሴፍም እንደ ተናገረ የሰባቱ ዓመት ራብ ጀመረ። በየአገሩም ሁሉ ራብ ሆነ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ግን እህል ነበረ። 55 የግብፅ ምድርም ሁሉ ተራበ፥ ሕዝቡም ስለ እህል ወደ ፈርዖን ጮኸ፤ ፈርዖንም የግብፅ ሰዎችን ሁሉ። ወደ ዮሴፍ ሂዱ፥ እርሱ ያላችሁንም ሁሉ አድርጉ አላቸው። 56 በምድርም ሁሉ ላይ ራብ ሆነ፤ ዮሴፍም እህል ያለበትን ጎተራ ሁሉ ከፍቶ ለግብፅ ሰዎች ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ ራብም በግብፅ ምድር ጸንቶ ነበር። 57 አገሮችም ሁሉ እህል ይገዙ ዘንድ ወደ ግብፅ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ በምድር ሁሉ ራብ እጅግ ጸንቶ ነበርና።

ዘፍጥረት 42

1 ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን። ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው። 2 እንዲህም አለ። እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቼአለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን። 3 የዮሴፍም አሥሩ ወንድሞቹ ስንዴን ከግብፅ ይሸምቱ ዘንድ ወረዱ፤ 4 የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ግን ያዕቆብ ከወንድሞቹ ጋር አልሰደደውም። ምናልባት ክፉ እንዳያገኘው ብሎአልና። 5 የእስራኤልም ልጆች ለእህል ሸመታ ከመጡቱ ጋር ገቡ፤ በከነዓን አገር ራብ ነበረና። 6 ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት። 7 ዮሴፍም ወንድሞቹን አይቶ አወቃቸው፤ ተለወጠባቸውም፥ ክፉ ቃልንም ተናገራቸው። እናንተ ከወዴት መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም። ከከነዓን ምድር እህል ልንሸምት የመጣን ነን አሉት። 8 ዮሴፍም ወንድሞቹን አወቃቸው፥ እነርሱ ግን አላወቁትም፤ 9 ዮሴፍም ስለ እነርሱ አይቶት የነበረውን ሕልም አሰበ። እንዲህም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የምድሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። 10 እነርሱም አሉት። ጌታችን ሆይ አይደለም፤ ባሪያዎችህ ስንዴን ሊገዙ መጥተዋል፤ 11 እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ እውነተኞች ነን፥ ባሪያዎችህስ ሰላዩች አይደሉም። 12 እርሱም አላቸው። አይደለም፤ ነገር ግን የአገሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። 13 እነርሱም አሉ። ባሪያዎችህ አሥራ ሁለት ወንድማማች በከነዓን ምድር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ታናሹም እነሆ ዛሬ ከአባታችን ጋር ነው፥ አንዱም ጠፍቶአል። 14 ዮሴፍም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ ብዬ የተናገርኋችሁ ይህ ነው፤ 15 በዚህ ትፈተናላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁ ካልመጣ በቀር የፈርዖንን ሕይወት ከዚህ አትወጡም። 16 እውነትን የምትናገሩ ከሆነ ነገራችሁ ይፈተን ዘንድ ከእናንተ አንዱን ስደዱ፥ ወንድማችሁንም ይዞ ይምጣ እናንተም ታሥራችሁ ተቀመጡ፤ ይህ ካልሆነ የፈርዖንን ሕይወት ሰላዮች ናችሁ። 17 ሦስት ቀን ያህል በግዞት ቤት ጨመራቸው። 18 በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው። ትድኑ ዘንድ ይህን አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔርን እፈራለሁና። 19 እናንተ የታመናችሁ ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ ወንድማችሁ በግዞታችሁ ቤት ይታሰር እናንተ ግን ሂዱ፥ እህሉንም ለቤታችሁ ራብ ውሰዱ፤ 20 ታናሹንም ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ፤ ነገራችሁም የታመነ ይሆናልና አትሞቱም። እንዲህም አደረጉ። 21 እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል፥ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን። 22 ሮቤልም መልሶ እንዲህ አላቸው። ብላቴናውን አትበድሉ ብያችሁ አልነበረምን? እኔም አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህ እነሆ አሁን ደሙ ይፈላለገናል። 23 እነርሱም ዮሴፍ ነገራቸውን እንደሚሰማባቸው አላወቁም፥ በመካከላቸው አስተርጓሚ ነበረና። 24 ከእነርሱም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ደግሞም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተናገራቸው፥ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ወሰዶ በፊታቸው አሰረው። 25 ዮሴፍም ዓይበታቸውን እህል ይሞሉት ዘንድ አዘዘ፤ የእየራሳቸውንም ብር በእየዓይበታቸው ይመልሱት ዘንድ ደግሞም የመንገድ ስንቅ ይሰጡአቸው ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ተደረገላቸው። 26 እነርሱም እህሉን በአህዮቻቸው ላይ ጫኑ፥ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ። 27 ከእነርሱም አንዱ ባደሩበት ስፍራ ለአህያው ገፈራን ይሰጥ ዘንድ ዓይበቱን ሲፈታ ብሩን አየ፥ እነሆም በዓይበቱ አፍ ላይ ነበረች። 28 ለወንድሞቹም። ብሬ ተመለሰችልኝ፥ እርስዋም በዓይበቴ አፍ እነኋት አላቸው። ልባቸውም ደነገጠ፥ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው ተባባሉ። እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ምንድር ነው? 29 ወደ አባታቸውም ወደ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር መጡ፥ የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ እንዲህ ብለው አወሩ። 30 የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በክፉ ንግግር ተናገረን፥ የምድሪቱም ሰላዮች አስመሰለን። 31 እኛም እንዲህ አልነው። እውነተኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤ 32 እኛ የአባታችን ልጆች አሥራ ሁለት ወንድማማች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፥ ታናሹም በከነዓን ምድር ዛሬ ከአባታችን ጋር አለ። 33 የአገሩም ጌታ ያ ሰው እንዲህ አለን። የታመናችሁ ሰዎች ከሆናችሁ በዚህ አውቃለሁ፤ አንደኛውን ወንድማችሁን ከእኔ ጋር ተዉት፥ ለቤታችሁም ራብ እህልን ወስዳችሁ ሂዱ፤ 34 ታናሹንም ወንድማችሁን አምጡልኝ፥ እውነተኞች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም በዚህ አውቀዋለሁ፤ ወንድማችሁንም እሰጣችኋለሁ፥ እናንተም በምድሩ ትነግዳላችሁ። 35 እንዲህም ሆነ፤ ዓይበታቸውን በፈቱ ጊዜ እነሆ ከእነርሱ እያንዳንዳቸው ብራቸውን በእየዓይበታቸው ተቋጥሮ አገኙት፤ እነርሱም አባታቸውም የብራቸውን ቍጥራት አይተው ፈሩ። 36 አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው። ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ፤ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ። 37 ሮቤልም አባቱን አለው። ወደ አንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደ ሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል፤ እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደ አንተ እመልሰዋለሁ። 38 እርሱም አለ። ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። a

ዘፍጥረት 43

1 2 ራብም በምድር ጸና። ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው። እንደ ገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው። 3 ይሁዳም እንዲህ አለው። ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎ በብርቱ ቃል አስጠነቀቀን። 4 ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትሰድደው እንወርዳለን፥ እህልም እንሸምትልሃለን፤ 5 ባትሰድደው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎናልና። 6 እስራኤልም አላቸው። ለምን በደላችሁኝ? ለዚያውስ። ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት? 7 እነርሱም አሉ። ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ወገናችን ፈጽሞ ጠየቀን እንዲህም አለን። አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን? እኛም እንደዚሁ እንደ ጥያቄው መለስንለት፤ በውኑ። ወንድማችሁን አምጡ እንዲለን እናውቅ ነበርነን? 8 ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው። እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን። 9 እኔ ስለ እርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን። 10 ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር። 11 እስራኤልም አባታቸው እንዲህ አላቸው። ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህንን አድርጉ፤ ከተመሰገነው ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፥ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ። 12 ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ፤ በዓይበታችሁ አፍ የተመለሰውንም ብር መልሳችሁ ውሰዱ፤ ምናልባት በስሕተት ይሆናል። 13 ወንድማችሁንም ውሰዱ፥ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ተመለሱ። 14 ሁሉን የሚችል አምላክም ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ከእናንተ ጋር ይሰድድ ዘንድ በዚያ ሰው ፊት ምሕረትን ይስጣችሁ፤ እኔም ልጆቼን እንዳጣሁ አጣሁ። 15 ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና አጠፌታውን ብር ብንያምንም ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በዮሴፍም ፊት ቆሙ። 16 ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው። እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፥ እርድም እረድ አዘጋጅም፥ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና። 17 ያ ሰውም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ያ ሰውም ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባ። 18 እነርሱም ወደ ዮሴፍ ቤት ስለ ገቡ ፈሩ፤ እንዲህም አሉ። በዓይበታችን ቀድሞ ስለ ተመለሰው ብር ሊተነኰልብን ሊወድቅብንም፥ እኛንም በባርነት ሊገዛ አህዮቻችንንም ሊወስድ ወደዚህ አስገባን። 19 ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥም ቀረቡ፥ በቤቱም ደጅ ተናገሩት፥ 20 እንዲህም አሉት። ጌታዬ ሆይ፥ ቀድሞ እህልን ልንሸምት ወርደን ነበር፤ 21 ወደምናድርበትም ስፍራ በደረስን ጊዜ ዓይበታችንን ከፈትን፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ብር በየዓይበቱ አፍ እንደ ሚዛኑ ብራችን ነበረ፤ አሁንም በእጃችን መለስነው። 22 እህል እንሸምትበት ዘንድ ሌላም ብር በእጃችን አመጣን፤ ብራችንንም በዓይበታችን ማን እንደ ጨመረው አናውቅም። 23 እርሱም አላቸው። ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ አምላካችሁና የአባታችሁ አምላክ በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁስ ደርሶኛል። 24 ስምዖንንም አወጣላቸው። ሰውዮውም እነዚያን ስዎች ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ ውኃ አመጣላቸው፥ እግራቸውንም ታጠቡ፤ ለአህዮቻቸው አበቅ ሰጣቸው። 25 ዮሴፍም በእኩለ ቀን እስኪገባ ድረስ እነርሱ እጅ መንሻቸውን አዘጋጁ፥ ከዚያ እንጀራን እንደሚበሉ ሰምተዋልና። 26 ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፥ ወደ ምድርም ወድቀው ሰገዱለት። 27 እርሱም ደኅንነታቸውን ጠየቃቸው፥ እንዲህም አለ። የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን? ገና በሕይወት አለን? 28 እነርሱም አሉት። ባሪያህ አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ። አጐንብሰውም ሰገዱለት። 29 ዓይኑንም አንሥቶ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየው፥ እርሱም አለ። የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን? እንዲህም አለው። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ። 30 ዮሴፍም ቸኮለ፥ አንጀቱ ወንድሙን ናፍቆታልና፤ ሊያለቅስም ወደደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ከዚያ አለቀሰ። 31 ፊቱንም ታጥቦ ወጣ፥ ልቡንም አስታግሦ። እንጀራ አቅርቡ አለ። 32 ለእርሱም ለብቻው አቀረቡ፥ ለእነርሱም ለብቻቸው፥ ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ለግብፅ ሰዎችም ለብቻቸው፤ የግብፅ ሰዎች ከዕብራውያን ጋር መብላት አይሆንላቸውምና፥ ይህ ለግብፅ ሰዎች እንደ መርከስ ነውና። 33 በፊቱም በኵሩ እንደ ታላቅነቱ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ ተቀመጡ፤ ሰዎቹም እርስ በርሳቸው ተደነቁ። 34 በፊቱም ካለው መብል ፈንታቸውን አቀረበላቸው፤ የብንያምም ፈንታ ከሁሉ አምስት እጅ የሚበልጥ ነበረ። እነርሱም ጠጡ ከእርሱም ጋር ደስ አላቸው።

ዘፍጥረት 44

1 ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘ። ዓይበታቸው የሚያነሣውን ያህል እህል ሙላላቸው፥ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤ 2 በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው። እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። 3 ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ ተሰናበቱ። 4 ከከተማይቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ። ተነሥተህ ሰዎቹን ተከተላቸው፤ በደረስህባቸውም ጊዜ እንዲህ በላቸው። በመልካሙ ፋንታ ስለ ምን ክፉን መለሳችሁ? 5 ጌታዬ የሚጠጣበት ምሥጢርንም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ። 6 እርሱም ደርሰባቸው ይህንም ቃል ነገራቸው። 7 እነርሱም አሉት። ጌታዬ እንደዚህ ያለውን ቃል ለምን ይናገራል? ባሪያዎችህ ይህን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም። 8 እነሆ፥ በዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር ይዘን ከከነዓን አገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን? 9 ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን ባሪያዎች እንሁን። 10 እርሱም አለ። አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ ባሪያ ይሁነኝ፥ እናንተም ንጹሐን ትሆናላችሁ። 11 እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፥ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ። 12 እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፥ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው። 13 ልብሳቸውንም ቀደዱ፥ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ። 14 ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፥ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ። 15 ዮሴፍም። ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድር ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን? አላቸው። 16 ይሁዳም አለ። ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ፤ እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበቱም ደግሞ ለጌታዬ ባሪያዎቹ ነን። 17 እርሱም እላቸው። ይህን አደርግ ዘንድ አይሆንልኝም፤ ጽዋው የተገኘበቱ ሰው እርሱ ባሪያ ይሁነኝ፤ እናንተም ወደ አባታችሁ በደኅና ውጡ። 18 ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ እንዲህም አለ። ጌታዬ ሆይ፥ እኔ ባርያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና። 19 ጌታዬ ባሪያዎቹን። አባት አላችሁን ወይስ ወንድም? ብሎ ጠየቀ። 20 እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልነ። ሸማግሌ አባት አለን፥ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙም ሞተ፥ ከእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፥ አባቱም ይወድደዋል። 21 አንተም ለባሪያዎችህ። ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም አየዋለሁ አልህ። 22 ጌታዬንም። ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልነው። 23 ባርያዎችህንም። ታናሽ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኽን። 24 ወደ ባርያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታዬን ቃል ነገርነው። 25 አባታችንም። ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለ። 26 እኛም አልነው። እንሄድ ዘንድ አይሆንልንም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ይወርድ እንደ ሆነ እኛም እንወርዳለን፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና። 27 ባሪያህ አባቴም እንዲህ አለን። ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤ 28 አንዱም ከእኔ ወጣ። አውሬ በላው አላችሁኝ፥ እስከ ዛሬም አላየሁትም፤ 29 ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። 30 አሁንም እኔ ወደ አባቴ ወደ ባሪያህ ብሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ባየ ጊዜ ይሞታል፤ 31 ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ። 32 እኔ ባሪያህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና። እርሱንስ ወደ አንተ ባላመጣው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኃጢአተኛ እሆናለሁ። 33 ስለዚህም እኔ ባሪያህ በጌታዬ ዘንድ ባሪያ ሆኜ በብላቴናው ፋንታ ልቀመጥ፤ ብላቴናውም ከወንድሞቹ ጋር ይውጣ። 34 አለዚያም ብላቴናው ከእኔ ጋር ከሌለ ወደ አባቴ እንዴት እወጣለሁ? አባቴን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ። a

ዘፍጥረት 45

1 ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም። ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም። 2 ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። 3 ዮሴፍም ለወንድሞቹ። እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና። 4 ዮሴፍም ወንድሞቹን። ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው። ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5 አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና። 6 ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ። 7 እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። 8 አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። 9 አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት። ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው። እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤ 10 በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፥ ወደ እኔም ትቀርባለህ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ። 11 በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና። 12 እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል። 13 ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት። 14 የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። 15 ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ። 16 በፈርዖንም ቤት። የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ በዚያውም ፈርዖንና ሎላልቱ ደስ ተሰኙበት። 17 ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ይህን አድርጉ፤ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤ 18 አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ። 19 አንተም ወንድሞችህን። እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤ 20 ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና። 21 የእስራኤል ልጆችም እንደዚሁ አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤ 22 ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፥ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው። 23 ለአባቱም እንደዚሁ ሰደደ፥ የግብፅን በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን። 24 ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው። በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ። 25 እነርሱም ሄዱ፥ ከግብፅ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ። 26 እንዲህም ብለው ነገሩት። ዮሴፍ ገና በሕይወቱ ነው፥ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ አላመናቸውም ነበርና። 27 እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት፤ እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደሰች። 28 እስራኤልም። ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።

ዘፍጥረት 46

1 እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ መጣ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ። 2 እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ። ያዕቆብ ያዕቆብ ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም። እነሆኝ አለ። 3 አለውም። የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና። 4 እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም እጁን በዓይንህ ላይ ያኖራል። 5 ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ። 6 እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤ 7 ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው። 8 ወደ ግብፅም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል። 9 የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ። 10 የስሞዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል። 11 የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 12 የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፤ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል። 13 የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን። 14 የዛብሎንም ልጆች፤ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል። 15 ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ነፍስ ናቸው። 16 የጋድም ልጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤስቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ። 17 የአሴርም ልጆች፤ ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሤራሕ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ሔቤር፥ መልኪኤል። 18 ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን አሥራ ስድስቱንም ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች። 19 የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው። 20 ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው። 21 የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቤኬር፥ አስቤል፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ናዕማን፥ አኪ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፊም፤ ጌራም አርድን ወለደ። 22 ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም አሥራ አራት ነፍስ ናቸው። 23 የዳንም ልጆች፤ ሑሺም። 24 የንፍታሌምም ልጆች፤ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም። 25 ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው። 26 ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጉልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ስድስት ናቸው። 27 በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው። 28 ይሁዳንም በጌሤም እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከ፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ። 29 ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፤ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ። 30 እስራኤልም ዮሴፍን። አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይቼአለሁና አሁን ልሙት አለው። 31 ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው። እኔ መጥቼ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ። በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤ 32 እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ። 33 ፈርዖንም ቢጠራችሁ። ተግባራችሁስ ምንድር ነው? ቢላችሁ፥ 34 በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኵስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት። እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን። q ቍ@ 28 ጌሤም የሚለውን የግእዝ መጽሐፍ ራምሴ ይለዋል። a

ዘፍጥረት 47

1 ዮሴፍም ገባ ለፈርዖንም ነገረው እንዲህ ብሎ። አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውም ላሞቻቸውም ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር ወጡ፤ እነርሱም እነሆ በጌሤም ምድር ናቸው። 2 ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው። 3 ፈርዖንም ወንድሞቹን። ሥራችሁ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን። እኛ ባሪያዎችህ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን አሉት። 4 ፈርዖንንም እንዲህ አሉት። በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ የባርያዎችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም ባሪያዎችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን። 5 ፈርዖንም ዮሴፍን ተናገረው እንዲህ ብሎ። አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤ 6 የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱም ውስጥ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደ ሆነ በእንስሶቼ ላይ አለቆች አድርጋቸው። 7 ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። 8 ፈርዖንም ያዕቆብን። የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው። 9 ያዕቆብም ለፈርዖን አለው። የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም። 10 ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው ከፈርዖንም ፊት ወጣ። 11 ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ጉልትን ሰጣቸው። 12 ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው። 13 በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። 14 ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው። 15 ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ። እንጀራ ስጠን፤ ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና። 16 ዮሴፍም። ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ አለ። 17 ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንታ እህልን መገባቸው። 18 ዓመቱም ተፈጸመ፤ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት። እኛ ከጌታችን አንሰውርም፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፤ 19 እኛ በፊትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን። 20 ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። 21 ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባሪያዎች አደረጋቸው። 22 የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። 23 ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ። እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤ 24 በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን። 25 እነርሱም። አንተ አዳነኸን፤ በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ፥ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት። 26 ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት። 27 እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፤ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ። 28 ያዕቆብም በግብፅ ምድር አሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም ሙላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው። 29 የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው። በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤ 30 ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ። እርሱም። እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ። 31 እርሱም። ማልልኝ አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።

ዘፍጥረት 48

1 ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እነሆ አባትህ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2 ለያዕቆብም። እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፥ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብ ዮሴፍን አለው። ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም 4 እንዲህም አለኝ። እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘላለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ። 5 አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። 6 ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። 7 እኔም ከመስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በመንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት፥ ቀበርኋት። 8 እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ። እነዚህ እነማን ናቸው? አለው። 9 ዮሴፍም ለአባቱ። እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው አለ። እርሱም። እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ አለ። 10 የእስራኤልም ዓይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም። 11 እስራኤልም ዮሴፍን። ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ አለው። 12 ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ። 13 ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። 14 እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና። 15 ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ 16 ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ። 17 ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። 18 ዮሴፍም አባቱን። አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ አለው። 19 አባቱም እንቢ አለ እንዲህ ሲል። አወቅሁ ልጄ ሆይ፥ አወቅሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል። 20 በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው። 21 እስራኤልም ዮሴፍን። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ 22 እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ አለው። a

ዘፍጥረት 49

1 ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ። 2 እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ። 3 ሮቤል፥ አንተ በኵር ልጄና ኃይሌ፥ የጕብዝናዬም መጀመሪያ ነህ፤ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ። 4 እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ። 5 ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። 6 በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። 7 ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ። 8 ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። 9 ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? 10 በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል። 11 ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም። 12 ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል። 13 ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው። 14 ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጕረኖም መካከል ያርፋል። 15 ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በሥራም ገበሬ ሆነ። 16 ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ። 17 ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፤ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል። 18 እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ። 19 ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፤ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል። 20 የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል። 21 ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል። 22 ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። 23 ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤ 24 ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ 25 በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። 26 የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ። 27 ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል። 28 እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው። 29 እንዲህ ብሎም አዘዛቸው። እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤ 30 እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት። 31 አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፤ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፤ 32 እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው። 33 ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።

ዘፍጥረት 50

1 ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም። 2 ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት። 3 አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት። 4 የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። 5 አባቴ አምሎኛል እንዲህ ሲል። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ። 6 ፈርዖንም። ውጣ፥ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው። 7 ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤ 8 የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ። 9 ሰረገሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ። 10 በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። 11 በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ። ይህ ለግብፅ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። 12 ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤ 13 ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። 14 ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ። 15 የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ። ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል። 16 ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት። አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል። 17 ዮሴፍን እንዲህ በሉት። እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል። 18 ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው። እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት። 19 ዮሴፍም አላቸው። አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን? 20 እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። 21 አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። 22 ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ፥ እርሱና የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ። 23 ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ፤ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። 24 ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ። እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል። 25 ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች። እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው። 26 ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።

ዘጸአት 1

1 ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ። 2 ሮቤል፥ 3 ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ 4 ብንያም፥ ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር። 5 ከያቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ። 6 ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ። 7 የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ አጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች። 8 በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ። 9 እርሱም ሕዝቡን። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ 10 እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ። 11 በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ። 12 ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር። 13 ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው። 14 በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር። 15 የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ። 16 እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር። 17 አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው። 18 የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው። 19 አዋላጆቹም ፈርዖንን። የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት። 20 እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ጸና። 21 እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው። 22 ፈርዖንም። የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።

ዘጸአት 2

1 ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። 2 ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። 3 ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። 4 እኅቱም የሚደረግበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎበኘው ነበር። 5 የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው። 6 በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም። ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው አለች። 7 እኅቱም ለፈርዖን ልጅ። ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን? አለቻት። 8 የፈርዖንም ልጅ። ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። 9 የፈርዖንም ልጅ። ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። 10 ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፥ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። 11 በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። 12 ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። 13 በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም። ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ? አለው። 14 ያም። በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም። በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ። 15 ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ። 16 ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ። 17 እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። 18 ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ። ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ? አላቸው። 19 እነርሱም። አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ አሉ። 20 ልጆቹንም። እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ አላቸው። 21 ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። 22 ወንድ ልጅም ወለደች። በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። 23 ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። 24 እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። 25 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።

ዘጸአት 3

1 ሙሴም የዮቶርን የአማቱን የምድያምን ካህን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ ወደ ምድረ በዳ ዳርቻም በጎቹን ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ መጣ። 2 የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ። 3 ሙሴም። ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ ራእይ ልይ አለ። 4 እግዚአብሔር እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደ መጣ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጥቋጦው ውስጥ እርሱን ጠርቶ። ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ አለ። 5 እርሱም። እነሆኝ አለ። ወደዚህ አትቅረብ፤ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ አለው። 6 ደግሞም። እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ። 7 እግዚአብሔርም አለ። በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ 8 ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ። 9 አሁንም እነሆ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ወጣ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ። 10 አሁንም ና፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ። 11 ሙሴም እግዚአብሔርን። ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። 12 እርሱም። በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ አለ። 13 ሙሴም እግዚአብሔርን። እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ። የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ። ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን። <<ያለና የሚኖር>>እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች። <<ያለና የሚኖር>>ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው። 15 እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ። የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። 16 ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ። እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ። መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፥ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ 17 ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ በላቸው። 18 እነርሱም ቃልህን ይሰማሉ፤ አንተና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትገባላችሁ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ አሁንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንሠዋ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንሂድ ትሉታላችሁ። 19 ነገር ግን በጽኑ እጅ ካልሆነ በቀር ትሄዱ ዘንድ የግብፅ ንጉሥ እንደማይፈቅድላችሁ እኔ አውቃለሁ። 20 እኔም እጄን እዘረጋለሁ፥ በማደርግባቸውም ተአምራቴ ሁሉ ግብፅን እመታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይለቅቃችኋል። 21 በግብፃውያንም ፊት ለዚህ ሕዝብ ሞገስን እሰጣለሁ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሄዳችሁ ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም፤ 22 ነገር ግን እያንዳንዲቱ ሴት ከጎረቤትዋ በቤትዋም ካለችው ሴት የብር ዕቃ የወርቅ እቃ ልብስም ትለምናለች፤ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁ ላይ ታደርጉታላችሁ፤ ግብፃውያንንም ትበዘብዛላችሁ።

ዘጸአት 4

1 ሙሴም መለሰ። እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም። እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ። 2 እግዚአብሔርም። ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም። በትር ናት አለ። 3 ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ። 45 እግዚአብሔርም ሙሴን። የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ እግዚአብሔር እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ እጅህን ዘርግተህ ጅራትዋን ያዝ አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዛት በእጁም ውስጥ በትር ሆነች። 6 እግዚአብሔርም ደግሞ። እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። 7 እርሱም። እጅህን ወደ ብብትህ መልስ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች። 8 ደግሞም አለው። እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ። 9 እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፥ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል። 10 ሙሴም እግዚአብሔርን። ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። 11 እግዚአብሔርም። የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? 12 እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው። 13 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። 14 የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ። ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። 15 አንተም ትናገረዋለህ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። 16 እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ። 17 ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። 18 ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ። እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ አለው። ዮቶርም ሙሴን። በሰላም ሂድ አለው። 19 እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም። ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ አለው። 20 ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። 22 ፈርዖንንም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 23 እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ ትለዋለህ። 24 እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። 25 ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፥ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው። አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች። 26 ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ። ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች። 27 እግዚአብሔርም አሮንን። ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። 28 ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ተናገረው። 29 ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። 30 አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31 ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጐነበሱ ሰገዱም።

ዘጸአት 5

1 ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን መጥተው ፈርዖንን እንዲህ አሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ፈርዖንም። ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም አለ። 3 እነርሱም። የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን አሉት። 4 የግብፅ ንጉሥም። አንተ ሙሴ አንተም አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ አላቸው። 5 ፈርዖንም። እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ አለ። 6 ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ። 7 እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ። 8 ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ። ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ እያሉ ይጮኻሉ። 9 እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ። 10 የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም። ፈርዖን እንዲህ ይላል። ገለባ አልሰጣችሁም። 11 እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጐድልም አሉአቸው። 12 ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። 13 አስገባሪዎቹም። ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ እያሉ አስቸኰሉአቸው። 14 የፈርዖንም አስገባሪዎች። ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቈጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም? እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ። 15 የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ። ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ? 16 ገለባ አይሰጡንም፥ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው ብለው ጮኹ። 17 እርሱ ግን። ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም። እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ ትላላችሁ። 18 አሁንም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ አላቸው። 19 የእስራኤልም ልጆች አለቆች። ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። 20 ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። 21 እነርሱም። በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ ይፍረድባችሁም አሉአቸው። 22 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና። ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ? 23 በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም አለ።

ዘጸአት 6

1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ። 2 እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 3 ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። 4 የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። 5 ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። 6 ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥ 7 ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 9 ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 11 ግባ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር። 12 ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ ብሎ ተናገረ። 13 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው። 14 የአባታቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው። 15 የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ዶሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው። 16 እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 17 የጌድሶንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው። 18 የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። 19 የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው። 20 እንበረምም የአጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፥ አሮንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 21 የይስዓር ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው። 22 የዑዝኤል ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልዳፋን፥ ሥትሪ ናቸው። 23 አሮንም የአሚናዳብን የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፥ እርስዋም ናዳብንና አብዮድን አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት። 24 የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ወገኖች ናቸው። 25 የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ልጆች ሚስት አገባ፥ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። 26 እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር። ከግብፅ ምድር በየሠራዊቶቻቸው የእስራኤልን ልጆች አውጡ ያላቸው ናቸው። 27 እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህ ሙሴና አሮን ናቸው። 28 እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤ 29 እግዚአብሔር ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር ብሎ ተናገረው። 30 ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? አለ።

ዘጸአት 7

1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። 2 ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ከፈርዖን ጋር ይናገራል። 3 እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ። 4 ፈርዖንም አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴንም የእስራኤልን ልጆች ሕዝቤን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ አገር አወጣለሁ። 5 ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ። 6 ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7 ፈርዖንንም በተናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበረ፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበረ። 8 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ተናገራቸው። 9 ፈርዖን። ተአምራትን አሳዩኝ ሲላችሁ፥ አሮንን። በትርህን ወስደህ እባብ እንድትሆን በፈርዖን ፊት ጣላት በለው። 10 ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች። 11 ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ። 12 እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች። 13 እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ። 15 ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። 16 እንዲህም ትለዋለህ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር። በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፥ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል። 18 በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፥ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ። 19 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ውሰድ፥ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል። 20 ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። 21 በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፥ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ። 22 የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም። 23 ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። 24 ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ። 25 እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ።

ዘጸአት 8

1 እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው። ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤ 3 ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤ 4 ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ በለው። 6 አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፥ የግብፅንም አገር ሸፈኑ። 7 ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ። 8 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ አላቸው። 9 ሙሴም ፈርዖንን። ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ አለው። እርሱም። ነገ አለ። 10 ሙሴም። አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን። 11 ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ አለ። 12 ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13 እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ። 14 እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች። 15 ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው። 17 እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። 18 ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። 19 ጠንቋዮችም ፈርዖንን። ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። 20 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21 ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ በባሪያዎችህም በሕዝብህም በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ። 22 በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ። 23 በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል። 24 እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች። 25 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ሂዱ፥ በአገሩ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ አላቸው። 26 ሙሴም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችን የግብፃውያንን ርኵሰት እንሰዋለንና እንዲህ ይደረግ ዘንድ አይገባም፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኵሰት በፊታቸው ብንሠዋ አይወግሩንምን? 27 እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እንደሚያዝዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን አለ። 28 ፈርዖንም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፥ ጸልዩልኝ አለ። 29 ሙሴም። እነሆ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፥ የዝንቡም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከሕዝቡም ነገ እንዲሄዱ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን አለ። 30 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 31 እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ የዝንቡንም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከህዝቡም አስነሣ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32 ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።

ዘጸአት 9

1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥ 3 እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል። 4 እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም። 5 እግዚአብሔርም። ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ። 6 እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። 7 ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም። 8 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9 እርሱም በግብፅ አገር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብፅም አገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻህኝ የሚያመጣ ቍስል ይሆናል አላቸው። 10 ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ሻህኝ የሚያወጣ ቍስል ሆነ። 11 ጠንቋዮችም ቍስል ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ ቍስል በጠንቋዮችና በግብፃያን ሁሉ ላይ ነበረና። 12 እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው አልሰማቸውም። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14 በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ። 15 አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ 16 ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ። 17 እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን? 18 እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ። 19 በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንስሳ ሁሉ በረዶ ወርዶበት ይሞታልና አሁን እንግዲህ ላክ፥ ከብቶችህንም በሜዳም ያለህን ሁሉ አስቸኵል። 20 ከፈርዖንም ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ቃል የፈራ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤ 21 የእግዚአብሔርንም ቃል ያላሰበ ባሪያዎቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር በሰው በእንስሳም በእርሻም ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብፅ አገር ሁሉ በረዶ ይሆን ዘንድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ አለው። 23 ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ላይ በረዶ አዘነበ። 24 በረዶም ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እሳት ይቃጠል ነበር፥ በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ ሕዝብ ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያልሆነ እጅግ ታላቅ ነበረ። 25 በረዶውም በግብፅ አገር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ሰውንና እንስሳን መታ፤ በረዶውም የእርሻን ቡቃያ ሁሉ መታ፥ የአገሩንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 26 የእስራኤል ልጆች ተቀምጠው በነበሩባት በጌሤም አገር ብቻ በረዶ አልወረደም። 27 ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን ጠራ። በዚህ ጊዜ በደልሁ፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም ኃጢያተኞች ነን። 28 የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ፤ እለቅቃችሁማለሁ፥ ከዚያም በኋላ በዚህ አትቀመጡም አላቸው። 29 ሙሴም። ከከተማ በወጣሁ ጊዜ እጄን ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር እንደሆነች ታውቅ ዘንድ ነጎድጓዱ ይቀራል፥ በረዶውም ደግሞ አይወርድም። 30 ነገር ግን አንተና ባሪያዎችህ አምላክን እግዚአብሔርን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁ አለው። 31 ገብሱ እሸቶ ተልባውም ኣፍርቶ ነበርና ተልባና ገብሱ ተመታ። 32 ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም። 33 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ተቋረጠ፥ ዝናቡም በምድር ላይ አልፈሰሰም። 34 ፈርዖንም ዝናቡ በረዶውም ነጎድጓዱም እንደ ተቋረጠ ባየ ጊዜ ኃጢያትን ጨመረ፥ እርሱና ባሪያዎቹም ልባቸውን አደነደኑ። 35 የፈርዖንም ልብ ጸና፤ እግዚአብሔርም በሙሴ አፍ እንደተናገር የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።

ዘጸአት 10

1 [see v2] 2 እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጅህ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፥ ይህችንም ተአምራቴን በመካከላቸው አደረግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው። 3 ሙሴም አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ አሉትም። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 4 ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤ 5 የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታልና ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም አምልጦ የተረፈላችሁን ትርፍ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤ 6 ቤቶችህም የባሪያዎችህም ሁሉ ቤቶች የግብፃውያንም ሁሉ ቤቶች በእነርሱ ይሞላል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው። ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 7 የፈርዖንም ባሪያዎች። ይህ ሰው እስከ መቼ ዕንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን? አሉት። 8 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን መልሶ አስመጣቸው። ሂዱ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው? አላቸው። 9 ሙሴም። እኛ እንሄዳለን፥ የእግዚአብሔር በዓል ሆኖልናልና ታናናሾቻችንና ሽማግሌዎቻችን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም በጎቻችንና ከብቶቻችንም ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አለ። 10 ፈርዖንም። እናንተን ከልጆቻችሁ ጋር ስለቅቅ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ። 11 እንዲህም አይይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፥ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አገልግሉ አላቸው። ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር ላይ እንዲወጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ አለው። 13 ሙሴም በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ። 14 አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደ ፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም። 15 የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት አገሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም። 16 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን እናንተንም በደልሁ፤ 17 አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ አላቸው። 18 ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመነ። 19 እግዚአብሔርም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፥ አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም። 20 እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን አለው። 22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ፤ 23 ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው። 24 ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ። ሂዱ፥ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁ ደግሞ ከእናንተ ጋር ይሂዱ አለው። 25 ሙሴም። አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ። 26 አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፥ አንድ ሰኮናም አይቀርም፤ አምላካችን የምናገለግለው ምን እንደሆነ ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም አለ። 27 እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም። 28 ፈርዖንም። ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ አለው። 29 ሙሴም። እንደ ተናገርህ ይሁን፤ ፊትህን እንደ ገና አላይም አለ።

ዘጸአት 11

1 እግዚአብሔርም ሙሴን። በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሰፍት አመጣለሁ፥ ከዚያ ወዲያም ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አባርሮ ይሰድዳችኋል። 2 ወንዱ ከወዳጁ ሴቲቱም ከወዳጅዋ የብርና የወርቅ ዕቃ ይሹ ዘንድ በሕዝቡ ጆሮ ተናገር አለው። 3 እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠው። ሙሴም በፈርዖን ባሪያዎችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ አገር እጅግ የከበረ ሰው ነበረ። 4 ሙሴም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእኩል ሌሊት እኔ በግብፅ መካከል እወጣለሁ፤ 5 በግብፅም አገር ያለ በኵር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባሪያይቱ በኵር ድረስ፥ የከብቱም በኵር ሁሉ ይሞታል። 6 በግብፅም አገር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ ኋላም ደግሞ የማይሆን ታላቅ ጩኸት ይሆናል። 7 እግዚአብሔር ግን በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል እንዲለይ እንድታውቁ በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም። 8 እነዚህም ባሪያዎችህ ሁሉ። አንተ ውጣ የሚከተሉህም ሕዝብ ሁሉ ይውጡ እያሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፥ ለእኔም ይሰግዳሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ። ሙሴም በጽኑ ቁጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን። ተአምራቴ በግብፅ አገር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም አለው። 10 ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ አልለቀቀም።

ዘጸአት 12

1 እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። 3 ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። 4 የቤቱ ሰዎች ቍጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። 5 የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። 6 በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። 7 ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት። 8 በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል። 9 ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። 10 ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት። 11 ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። 12 እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። 14 ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ። 15 ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። 16 በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላው በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፥ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ። 17 በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። 18 በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። 19 ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ። 20 እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ። 21 ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው። በየቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፥ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት። 22 ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ። 23 እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም። 24 ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ። 25 እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት። 26 እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ። ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው? 27 ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ። በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ። 28 ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። 29 እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ። 30 ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ። 31 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ። እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ 32 እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ አለ። 33 ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኵሉአቸው ነበር። ሁላችን እንሞታለን ብለዋልና። 34 ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት። 35 የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። 36 እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ። 37 የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ። 38 ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። 39 ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ እንጎቻ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኰሉአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር። 40 የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድር የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው። 41 እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ። 42 ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት። 43 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አለ። ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ። 44 በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ። 45 መጻተኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ። 46 በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንትም አትስበሩበት። 47 የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት። 48 እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። 49 ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል። 50 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። 51 በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ።

ዘጸአት 13

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው። 2 በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ የእኔ ነው። 3 ሙሴም ሕዝቡን አለ። ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፥ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና፤ ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4 እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5 እግዚአብሔርም ለአንተ ይሰጣት ዘንድ ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አምልኮ በዚህ ወር ታደርጋለህ። 6 ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል። 7 ሰባት ቀንም ሙሉ ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፥ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት እንጀራ አይታይ፥ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ። 8 በዚያም ቀን። ከግብፅ በወጣሁ ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነው ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9 እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና የእግዚአብሔር ሕግ በአፍህ ይሆን ዘንድ በእጅህ እንደ ምልክት በዓይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ። 10 በዓመት በዓመት በወራቱ ይህችን ሥርዓት ጠብቃት። 11 እግዚአብሔርም ለአንተ ለአባቶችህም እንደ ማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ባገባህ ጊዜ፥ እርስዋንም በሰጠህ ጊዜ፥ 12 ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ለይ፤ ከሚሆንልህ ከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለእግዚአብሔር ይሆናል። 13 የአህያውን በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኵር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14 እንዲህም ይሆናል፤ በሚመጣው ጊዜ ልጅህ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ። እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤ 15 ፈርዖንም እንዳይሰድደን ልቡን ባጸና ጊዜ እግዚአብሔር ከሰው በኵር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኵር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ፥ ነገር ግን የልጆቼን በኵር ሁሉ እዋጃለሁ። 16 እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዓይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ። 17 እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር። ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብፅም እንዳይመለስ ብሎአልና። 18 ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ምድር ተሰልፈው ወጡ። 19 ዮሴፍም። እግዚአብሔር ሳይጎበኛችሁ አይቀርም፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ታወጣላችሁ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና ሙሴ የእርሱን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ። 20 ከሱኮትም ተጓዙ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። 21 በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ። 22 የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም።

ዘጸአት 14

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። 3 ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች። በምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል። 4 እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። 5 ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና። እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል? አሉ። 6 ሰረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ 7 ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ። 8 እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። 9 ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው። 10 ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። 11 ሙሴንም። በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? 12 በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት። 13 ሙሴም ለሕዝቡ። አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። 14 እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። 15 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። 16 አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። 17 እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። 18 ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 19 በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ 20 በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። 21 ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ። 22 የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው። 23 ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሁሉ፥ እያሳደዱ በኋላቸው ወደ ባሕር መካከል ገቡ። 24 ንጋትም በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዓምድ ሆኖ የግብፃውያንን ሠራዊት ተመለከተ፥ የግብፃውያንንም ሠራዊት አወከ። 25 የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም። እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ። 26 እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፥ ውኃውም በግብፃውያን በሰረገሎቻቸውም በፈረሰኞቻቸውም ላይ ይመለስ አለው። 27 ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፥ ባሕሩም ማለዳ ወደ መፍሰሱ ተመለሰ፤ ግብፃውያንም ከእርሱ ሸሹ፥ እግዚአብሔርም ግብፃውያንን በባሕሩ መካከል ጣላቸው። 28 ውኃውም ተመልሶ በኋላቸው ወደ ባሕር የገቡትን ሰረገሎችን ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም። 29 የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ሄዱ፤ ውኆችም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆኑላችው። 30 እግዚአብሔር በዚያን ቀን እስራኤልን እንደዚህ ከግብፃውያን እጅ አዳነ፤ እስራኤልም የግብፃውያንን ሬሳ በባሕር ዳር አዩ። 31 እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፥ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፥ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ።

ዘጸአት 15

1 በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። 2 ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። 3 እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥ 4 የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። 5 ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። 6 አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። 7 በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። 8 በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። 9 ጠላትም። አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። 10 ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። 11 አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? 12 ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። 13 በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። 14 አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። 15 የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። 16 አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ። 17 አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። 18 እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል። 19 የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ። 20 የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። 21 ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። 22 ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። 23 ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። 24 ሕዝቡም። ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። 25 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ 26 እርሱም። አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ። 27 እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።

ዘጸአት 16

1 ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። 2 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጐራጐሩ። 3 የእስራኤልም ልጆች። ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ። 5 እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው። 6 ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ 7 የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ። 8 ሙሴም። እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ። 9 ሙሴም አሮንን። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው። 10 እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። 11 12 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ። ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። 13 እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት፤ ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። 14 የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። 15 የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው። ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም። ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው። 16 እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም፤ በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው። 17 የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ። 18 በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጐደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ። 19 ሙሴም። ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው። 20 ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው። 21 ሰውም ሁሉ ዕለት ዕለት የሚበላውን ያህል በጥዋት ለቀመ፤ ፀሐይም በተኰሰ ጊዜ ቀለጠ። 22 እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሞር እንጀራ ለቀሙ፤ የማኀበሩም አለቆች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት። 23 እርሱም። እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው። ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ለነገ እንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው። 24 ሙሴም እንዳዘዘ ለነገ አኖሩት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልሆነበትም። 25 ሙሴም። የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም። 26 ስድስት ቀን ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ። 27 በሰባተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንምን አላገኙም። 28 እግዚአብሔርም ሙሴን። ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ? 29 እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፥ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ አለው። 30 ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። 31 የእስራኤልም ወገን ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው። 32 ሙሴም። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ ጎሞር ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ አለ። 33 ሙሴም አሮንን። አንድ ማድጋ ወስደህ ጎሞር ሙሉ መና አግባበት፥ ለልጅ ልጃችሁም ይጠበቅ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው አለው። 34 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ይጠበቅ ዘንድ አሮን በምስክሩ ፊት አኖረው። 35 የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ። 36 ጎሞርም የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ነው።

ዘጸአት 17

1 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፥ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም። 2 ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም። ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው። 3 ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ። እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ሲሉ በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። 4 ሙሴም። ሊወግሩኝ ቀርበዋልና በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። 6 እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። 7 ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር። እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው። 8 አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር በራፊድም ተዋጋ። 9 ሙሴም ኢያሱን። ጕልማሶችን ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው። 10 ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። 11 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። 12 የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ። 13 ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን። የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ ተናገር አለው። 15 ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም ይህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፤ 16 እርሱም። እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ።

ዘጸአት 18

1 የምድያምም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣ ሰማ። 2 በዚያን ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር መልሶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን ሁለቱንም ልጆቿን ወሰደ። 3 ከእነርሱ የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ። በሌላ አገር ስደተኛ ነበርሁ ብሎአልና፤ 4 የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ። የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ ብሎአልና። 5 የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ። 6 ሙሴንም። እኔ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም፥ ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ መጥተንልሃል አለው። 7 ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ። 8 ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው። 9 ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው። 10 ዮቶርም። ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ። 11 ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ። 12 የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ። 13 እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። 14 የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ። ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው። 15 ሙሴም አማቱን። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ 16 ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። 17 የሙሴም አማት አለው። አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። 18 ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። 19 አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ 20 ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። 21 አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው። 22 በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል። 23 ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል። 24 ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። 25 ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። 26 በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። 27 ሙሴም አማቱን ሰደደው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።

ዘጸአት 19

1 በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። 2 ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ። 3 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር። 4 በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። 5 አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ 6 እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው። 7 ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። 8 ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን። ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘላለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ 11 በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ። 12 ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው። ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤ 13 የማንም እጅ አይንካ፤ ነገር ግን የሚነካው ሁሉ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን አይድንም በላቸው። ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ። 14 ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ። 15 ሕዝቡንም። ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴቶቻችሁ አትቅረቡ አለ። 16 እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። 17 ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ። 18 እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር። 19 የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። 20 እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን። ውረድ፥ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤ 22 ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ አለው። 23 ሙሴም እግዚአብሔርን። አንተ። በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም አለው። 24 እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይተላለፉ አለው። 25 ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ይህንንም ነገራቸው።

ዘጸአት 20

1 እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ። 2 ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። 3 ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። ፕ 4 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። 5 አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ 6 ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ፕ 7 የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። 8 የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። 9 ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ 10 ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ 11 እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም። 12 አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም። 13 አትግደል። 14 አታመንዝር። 15 አትስረቅ። 16 በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። 17 የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። 18 ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ባዩ ጊዜ ተርበደበዱ፥ ርቀውም ቆሙ። 19 ሙሴንም። አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ እንዳንሞት ግን እግዚአብሔር አይናገረን አሉት። 20 ሙሴም ለሕዝቡ። እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኃጢያትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ ይሆን ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ አለ። 21 ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፥ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። 22 እግዚአብሔር ሙሴን አለው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በል። እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። 23 በአጠገቤ ምንም አታድርጉ፤ የብር አማልክት የወርቅም አማልክት ለእናንተ አታድርጉ። 24 የጭቃ መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። 25 የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። 26 ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።

ዘጸአት 21

1 በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው። 2 ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ። 3 ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ። 4 ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ፥ እርሱም ብቻውን ይውጣ። 5 ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥ 6 ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን። 7 ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ። 8 ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም። 9 ለልጁም ብድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት። 10 ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት። 11 ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ። 12 ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 13 ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ። 14 ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውን በተንኰል ቢገድለው፥ እንዲሞት ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው። 15 አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። 16 ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 17 አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል። 18 ሁለት ሰዎችም ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን ታምሞ በአልጋው ላይ ቢተኛ፥ 19 ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይከፍለው ዘንድ፥ ያስፈውሰውም ዘንድ ግዴታ አለበት። 20 ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ። 21 የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ። 22 ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል። 23 ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥ 24 ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ 25 እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል። 26 ሰውም የባሪያውን ወይም የባሪይይቱን ዓይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ አርነት ያውጣው። 27 የባሪያውን ወይም የባሪያይቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ አርነት ያውጣው። 28 በሬም ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው። 29 በሬው ግን አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባይጠብቀውም፥ ወንድንም ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል። 30 ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ዎጆ የጫኑበትን ያህል ይስጥ። 31 ደግሞ ወንድን ልጅ ቢወጋ ሴትንም ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት። 32 በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር። 33 ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅበት፥ 34 የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን። 35 የሰው በሬ የሌላውን በሬ እስኪሞት ድረስ ቢወጋ፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ። 36 በሬውም አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው።

ዘጸአት 22

1 ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፥ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው፥ በበሬው ፋንታ አምስት በሬዎች፥ በበጉም ፋንታ አራት በጎች ይክፈል። 2 ሌባው ቤት ሲምስ ቢገኝ፥ እርሱም እስኪሞት ቢመታ፥ በመታው ሰው ላይ የደም ዕዳ አይሆንበትም። 3 ፀሐይ ግን ከወጣችበት የደም ዕዳ አለበት፤ ሌባው የሰረቀውን ይመልስ፤ የሚከፍለውም ቢያጣ ስለ ሰረቀው ይሸጥ። 4 የሰረቀው ደኅና ሆኖ በእጁ ቢገኝ፥ በሬም ወይም አህያ ወይም በግ ቢሆን፥ የሰረቀውን ያህል ሁለት እጥፍ ይክፈል። 5 ማንም ሰው ወደ እርሻ ወይም ወደ ወይን ስፍራ ከብቱን ቢነዳው፥ የሌላውንም እርሻ ቢያስበላ፥ ከተመረጠ እርሻው ከማለፊያውም ወይኑ ይካስ። 6 እሳት ቢነሣ፥ እሾኽንም ቢይዝ፥ ክምሩንም ወይም ያልታጨደውን እህል ወይም እርሻውን ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያነደደው ይካስ። 7 ሰው በባልንጀራው ዘንድ ብር ወይም ሌላ ነገር እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር ከቤቱም ቢሰረቅ፥ ሌባው ቢገኝ ስለ አንድ ሁለት ይክፈል። 8 ሌባውም ባይገኝ ባለቤቱ ወደ ፈራጆች ይቅረብ፥ እጁንም በባልንጀራው ከብት ላይ እንዳልዘረጋ ይማል። 9 ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለ ሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካሰሱ፥ አንዱም። ይህ የእኔ ነው ቢል፥ ክርክራቸው ወደ ፈራጆች ይድረስ፤ ፈራጆቹም የፈረዱበት እርሱ ለባልንጀራው በአንድ ሁለት ይክፈል። 10 ሰው በባልንጀራው ዘንድ አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እንስሳ እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጎዳ ወይም ቢማረክ፥ 11 በባልንጀራው ከብት ላይ እጁን እንዳልዘረጋ የእግዚአብሔር መሐላ በሁለታቸው መካከል ይሁን፤ የከብቱም ባለቤት መሐላውን ይቀበል፥ እርሱም ምንም አይክፈል። 12 ከእርሱም ዘንድ ቢሰረቅ የጠፋውን ያህል ለባለቤቱ ይመልስ። 13 ተቧጭሮም ቢገኝ ለምስክር ያምጣው፤ በመቧጨሩም ምክንያት አይክፈል። 14 ከባልንጀራው አንዳች ቢዋስ ባለቤቱ ከእርሱ ጋር ሳይኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ፈጽሞ ይክፈለው። 15 ባለቤቱ ግን ከእርሱ ጋር ቢኖር አይክፈል፤ ቢከራየው በክራዩ ይግባ። 16 ሰው ያልታጨችውን ድንግል ቢያስታት፥ ከእርስዋም ጋር ቢተኛ፥ ማጫዋን ሰጥቶ ሚስት ያድርጋት። 17 አባትዋም እርስዋን እንዳይሰጠው ፈጽሞ እንቢ ቢል እንደ ደናግል ማጫ ያህል ብር ይክፈላት። 18 መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት። 19 ከእንስሳ ጋር የሚረክስ ፈጽሞ ይገደል። 20 ከእግዚአብሔር በቀር ለአንዳች አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። 21 እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው፥ ግፍም አታድርግበት። 22 መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን አታስጨንቁአቸው። 23 ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ፤ 24 ቍጣዬም ይጸናባችኋል፥ በሰይፍም አስገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁም መበለት፥ ልጆቻችሁም ድሀ አደጎች ይሆናሉ። 25 ከአንተ ጋር ለተቀመጠው ለወገኔ ለድሀው ገንዘብ ብታበድረው፥ እንደ ባለ አራጣ አትሁን፥ አራጣም አትጫንበት። 26 የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት፤ 27 ሥጋውን የሚከድንበት እርሱ ብቻ ነውና፤ የሚተኛበትም ሌላ የለውምና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ መሐሪ ነኝና እሰማዋለሁ። 28 ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው። 29 ነዶህንም የወይንህንም ጭማቂ ለማቅረብ አትዘግይ፤ የልጆችህንም በኵር ትሰጠኛለህ። 30 እንዲህም በበሬዎችህና በበጎችህ ታደርገዋለህ፤ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፥ በስምንተኛውም ቀን ለእኔ ትሰጠዋለህ። 31 ቅዱስ ወገን ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ በምድረ በዳ አውሬ የቧጨረውን ሥጋ ለውሻ ጣሉት እንጂ አትብሉት።

ዘጸአት 23

1 ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ። 2 ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። 3 በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ። 4 የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት። 5 የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አንሣው። 6 በሚምዋገትበት ጊዜ የድሀህን ፍርድ አታጥምም። 7 ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጻድቅን አትግደል። 8 ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 9 በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና። 10 ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ፍሬዋንም አግባ፤ 11 በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህም ድሆች ይበሉታል፤ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። እንዲሁም በወይንህና በወይራህ አድርግ። 12 ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ ያርፉ ዘንድ ለባሪያህም ልጅ ለመጻተኛውም ዕረፍት ይሆን ዘንድ በሰባተኛው ቀን ዕረፍ። 13 ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፋችሁም አይሰማ። 14 በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ታደርግልኛለህ። 15 የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 16 በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ። 17 በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ። 18 የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር። 19 የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣ። ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል። 20 በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። 21 በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት። 22 አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ። 23 መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። 24 ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው። 25 አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ። 26 በምድርህም መካን ወይም የምትጨነግፍ አትሆንም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ። 27 መፈራቴንም በፊትህ እሰድዳለሁ፥ የምትሄድበትንም ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ። 28 በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ። 29 ምድር ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ከፊታችሁ አላባርራቸውም። 30 ነገር ግን እስክትበዛ ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ። 31 ድንበርህንም ከኤርትራ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳም እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድር የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፤ ከፊትህም ታባርራቸዋለሁ። 32 ከእነርሱና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ። 33 አማልክቶቻቸውንም ብታመልክ ወጥመድ ይሆኑብሃልና እኔን እንድትበድል እንዳያደርጉህ በአገርህ አይቀመጡ።

ዘጸአት 24

1 ሙሴንም። አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ 2 ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው። 3 ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። 4 ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። 5 የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ። 6 ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7 የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። 8 ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ። 9 ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ 10 የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። 11 እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን። ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው። 13 ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። 14 ሽማግሌዎችንም። ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው። 15 ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። 16 የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። 17 በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። 18 ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።

ዘጸአት 25

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ። 3 ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤ 4 ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥ 5 የፍየልም ጠጕር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፥ 6 የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥ 7 መረግድም፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። 8 በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። 9 እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። 10 ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11 በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13 መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 14 ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። 15 መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። 16 በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። 17 ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። 18 ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 19 ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ። 20 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። 21 የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። 22 በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። 23 ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ። 24 በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ 25 በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። 26 አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ። 27 ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። 28 ገበታውን ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29 ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። 30 በገበታም ላይ የገጽ ኅብስት ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። 31 መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። 32 በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። 33 በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ። 34 በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አድርግ። 35 ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን። 36 ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ። 37 ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዘንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል። 38 መኰስተሪያዎችዋን የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ። 39 መቅረዙም ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ። 40 በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።

ዘጸአት 26

1 ደግሞም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ የተሠሩ አሥር መጋረጆች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። 2 የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን። 3 አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። 4 ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። 5 አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ። 6 አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ ማደሪያውንም አንድ እንዲሆን መጋረጆችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። 7 ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጕር አድርግ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች ታደርጋለህ። 8 እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ይሁን። 9 አምስቱ መጋረጆች አንድ ሆነው ይጋጠሙ፥ ስድስቱም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። 10 ከተጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንድኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11 አምሳም የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፥ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን አጋጥመው። 12 ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። 13 ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። 14 ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አድርግ። 15 ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቆች ከግራር እንጨት አድርግ። 16 የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 17 ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18 ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አድርግ። 19 ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 20 ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች፥ 21 ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 22 ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቆችን አድርግ። 23 ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆችን አድርግ። 24 ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። 25 ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። 26 ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ 27 በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። 28 መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29 ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። 30 ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም። 31 መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። 32 በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። 33 መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። 34 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። 35 ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። 36 ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። 37 ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።

ዘጸአት 27

1 ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። 2 በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው። 3 አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። 4 እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። 5 መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ በመሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው። 6 ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው። 7 መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ። 8 ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት። 9 የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤ 10 ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት፤ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ። 11 እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ፤ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ። 12 በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት። 13 በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን። 14 በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 15 በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 16 ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፤ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ። 17 በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው። 18 የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን፤ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ። 19 ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ። 20 አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 21 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።

ዘጸአት 28

1 አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን አብዮድንም አልዓዛርንም ኢታምርንም፥ አቅርብ። 2 የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። 3 አንተም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አሮን ቅዱስ ይሆን ዘንድ ልብስ እንዲሠሩለት የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። 4 የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ ኤፉድም ቀሚስም ዝንጕርጕር ሸሚዝም መጠምጠሚያም መታጠቂያም፤ እነዚህም ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። 5 ወርቅንም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ። 6 ኤፉዱንም በብልሃት የተሠራ በወርቅና በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ያድርጉ። 7 ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን። 8 በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉድ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን። 9 ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ 10 እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስም በአንድ ድንጋይ፥ የቀረውንም ስድስቱን ስም በሌላው ቅረጽ። 11 በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ በወርቅም ፈርጥ አድርግ። 12 የእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቍዎች በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል። 13 14 የወርቅም ፈርጦች ሁለትም ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ እንደ ተጐነጐነም ገመድ አድርግ፤ የተጐነጐኑትንም ድሪዎች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል። 15 ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን የደረት ኪስ ሥራው እንደ ኤፉዱም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም ሥራው። 16 ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር ሆኖ ትክክልና ድርብ ይሆናል። 17 በአራት ተራ የሆነ የዕንቍ ፈርጥ አድርግበት፤ በፊተኛው ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤ 18 በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤ 19 በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤ 20 በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ይደረጋሉ። 21 የዕንቈቹም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች አሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ይቀረጹ፤ ስለ አሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ። 22 ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው። 23 ለደረቱ ኪስም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አድርጋቸው። 24 የተጐነጐኑትንም ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች ታገባቸዋለህ። 25 የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው ታደርጋቸዋለህ። 26 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሥራ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለቱ ጫፎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27 ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፥ በኤፉዱም ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ በመያዣው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። 28 የደረቱም ኪስ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን ከኤፉዱም እንዳይለይ፥ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያስሩታል። 29 አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ በደረት ኪስ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። 30 በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል። 31 የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው። 32 ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት። 33 በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሮማኖች አድርግ፤ በዚያም መካከል በዙሪያው የወርቅ ሻኵራዎች አድርግ፤ 34 የወርቅ ሻኵራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኵራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። 35 በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል። 36 ከጥሩ ወርቅም ቅጠል የሚመስል ምልክት ሥራ፥ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ። 37 በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ፊት ላይ ታንጠለጥለዋለህ። 38 በአሮንም ግምባር ላይ ይሆናል፥ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱስ ስጦታቸው ሁሉ ላይ ያለውን ኃጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ እንዲሆንላቸው ቅጠል የሚመስለው ምልክቱ ሁልጊዜ በግምባሩ ላይ ይሁን። 39 ሸሚዙንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ መጠምጠሚያውን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራር መታጠቂያም ትሠራለህ። 40 ለአሮንም ልጆች ሸሚዞችን መታጠቂያዎችንም ቆቦችንም ለክብርና ለጌጥ ታደርግላቸዋለህ። 41 ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፥ ትክናቸዋለህ፥ ትቀድሳቸውማለህ። 42 ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የበፍታ ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ 43 ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው እንዳይሞቱም፥ ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገቡ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።

ዘጸአት 29

1 እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ። 2 ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጐቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ። 3 በአንድ ሌማትም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በሌማቱ ታቀርባቸዋለህ። 4 አሮንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ። 5 ልብሶችን ወስደህ ለአሮን ሸሚዝና የኤፉድ ቀሚስ ኤፉድም የደረት ኪስም ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ ታስታጥቀዋለህ፤ 6 መጠምጠሚያውንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ። 7 የቅብዓትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባውማለህ። 8 ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ ሸሚዞቹንም ታለብሳቸዋለህ። 9 አሮንንና ልጆቹንም በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብንም ታለብሳቸዋለህ፤ ለዘላለም ሥርዓትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም አሮንንና ልጆቹን ትክናቸዋለህ። 10 ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ። 11 ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ። 12 ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ። 13 የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ በጉልበቱም ላይ ያለውን መረብ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ። 14 የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቁርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 15 አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ። 16 አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 17 አውራውንም በግ በየብልቱ ትቈርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ። 18 አውራውንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው። ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው። 19 ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ። 20 አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ። 21 በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዓት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ። 22 ደግሞም የሚካኑበት አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ። 23 አንድ እንጀራ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ቂጣ እንጀራ ትወስዳለህ፤ 24 ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ። 25 ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በመሠዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው። 26 ለአሮንም ክህነት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል። 27 ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። 28 ያውም የማንሣት ቍርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ለዘላለም የአሮንና የልጆቹ ወግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የማንሣት ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ይሆናል። 29 የተቀደሰውም የአሮን ልብስ ይቀቡበትና ይካኑበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን። 30 ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው። 31 የሚካንበትንም አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። 32 አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ በሌማትም ያለውን እንጀራ በመገናኛው ድንኳን በር ይበሉታል። 33 የተካኑና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ ሌላ ሰው ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና። 34 የተካኑበትም ሥጋ ወይም እንጀራ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም። 35 እንዳዘዝሁህም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን ትክናቸዋለህ። 36 ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ። 37 ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 38 በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ። 39 አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ። 40 ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ። 41 ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል። 42 ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። 43 ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል። 44 የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45 በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ። 46 በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።

ዘጸአት 30

1 የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው። 2 ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱም አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ። 3 ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። 4 ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት። በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ። 5 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 6 በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ ይህንም አንተን በምገናኝበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ። 7 አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው። 8 ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል። 9 ሌላም ዕጣን፥ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቍርባን አታፈስስበትም። 10 አሮንም በአመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በአመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን ናት። 11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 12 አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ። 13 አልፎ የሚቈጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል። 14 ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቈጠረ ሁሉ፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል። 15 ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ድሀውም አያጕድል። 16 የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 18 የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ። 19 አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል። 20 ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ፥ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል። 21 እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23 አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ፤ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ 24 ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ። 25 በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል። 26 የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ 27 ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ 28 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። 29 ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 30 በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም። 31 አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር። ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሁንልኝ። 32 በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱም የተሰራ ሌላ ቅብዓት አታድርጉ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን። 33 እንደ እርሱ ያለውን የሚያደርግ ሰው፥ በሌላም ሰው ላይ የሚያፈስሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 34 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም እጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ትክክል ይሁን። 35 በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፥ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው። 36 ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ። 37 እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን። 38 ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

ዘጸአት 31

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ። 3 በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤ 4 የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥ 5 ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። 6 እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ። 7 የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፥ 8 ገበታውንም ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ ጋር የነጻውን መቅረዝ፥ የዕጣን መሠዊያውን፥ 9 ለሚቃጠል መሥዋት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፥ በብልሃት የተሠራውንም ልብስ፥ 10 በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ 11 የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን የጣፋጭ ሽቱውንም ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 13 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ። 14 ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 15 ስድስት ቀን ሥራን ሥራ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። 16 የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። 17 እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው። 18 እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።

ዘጸአት 32

1 ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። 2 አሮንም። በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። 3 ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። 4 ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው። 5 አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም።ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ። 6 በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን። ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ። 8 ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። 10 አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። 11 ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? 12 ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። 13 ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። 14 እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ። 15 ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። 16 ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ። 17 ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን። የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው። 18 እርሱም። ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው። 19 እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው። 20 የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው። 21 ሙሴም አሮንን። ይህን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ? አለው። 22 አሮንም እንዲህ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ቍጣህ አይቃጠል፤ ይህ ሕዝብ ክፋትን እንዲወድድ አንተ ታውቃለህ። 23 እነርሱም። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ። 24 እኔም። ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ከእርሱ ሰብሮ ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ። 25 ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ 26 በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ፤ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 27 እርሱም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው። 28 የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። 29 ሙሴም። ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ እያንዳንዳችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ ዛሬ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቅዱስ አድርጉ አለ። 30 በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ። እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው። 31 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ። ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ 32 አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ። 33 እግዚአብሔርም ሙሴን። የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34 አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው። 35 አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።

ዘጸአት 33

1 [see v2] 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ሂድ፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም። ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር፥ ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ምድር አንተ ከግብፅ ምድር ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህም ውጣ። አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንህ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ በአንተ መካከል አልወጣምና በፊትህ መልአክ እሰድዳለሁ፤ ከነዓናዊውን አሞራዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም አወጣልሃለሁ። 4 ሕዝቡም ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው አዘኑ፤ ከእነርሱም ማንም ጌጡን አልለበሰም። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን። ለእስራኤል ልጆች። እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፥ አንድ ጊዜ በእናንተ መካከል ብወጣ አጠፋችኋለሁ፤ አሁንም የማደርግባችሁን አውቅ ዘንድ ጌጣችሁን ከእናንተ አውጡ በላቸው አለው። 6 የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወጡ። 7 ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። 8 ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። 9 ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። 10 ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። 11 እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። 12 ሙሴም እግዚአብሔርን። እነሆ አንተ። ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም። በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። 13 አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። 14 እግዚአብሔርም። እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። 15 እርሱም። አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። 16 በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን። በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው። 18 እርሱም። እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። 19 እግዚአብሔርም። እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። 20 ደግሞም። ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። 21 እግዚአብሔርም አለ። እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ 22 ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ 23 እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።

ዘጸአት 34

1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2 ነገም የተዘጋጀህ ሁን፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። 3 ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ። 4 ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፥ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ወሰደ፥ 5 እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። 6 እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ። እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ 7 እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። 8 ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ። 9 አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና ጌታዬ በመካከላችን ይሂድ፤ ጠማማነታችንንና ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ ለርስትህም ተቀበለን አለ። 10 እርሱም አለው። እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ተአምራት በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤ እኔም በአንተ ዘንድ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና አንተ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። 11 በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም በፊትህ አወጣለሁ። 12 በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትሄድባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13 ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውንም ትሰብራላችሁ፥ የማምለኪያ ዓፀዶቻቸውንም ትቈርጣላችሁ፤ 14 ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። 15 በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ 16 ሴት ልጆቻቸውንም ከወንድ ልጆችህ ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። 17 ቀልጠው የተሠሩትን የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ። 18 የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በአቢብ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ። 19 ማኅፀንንም የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባት በኵር ሁሉ፥ በሬም ቢሆን በግም ቢሆን፥ የእኔ ነው። 20 የአህያውንም በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። 21 ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። 22 የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23 በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። 24 አሕዛብን ከፊትህ አወጣለሁ፥ አገርህንም አሰፋለሁ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። 25 የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። 26 የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ታገባለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅልም። v 27 እግዚአብሔርም ሙሴን። በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። 28 በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። 29 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30 አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። 31 ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩን አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። 32 ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33 ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። 34 ሙሴም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገረ። 35 የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት ቁርበት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር።

ዘጸአት 35

1 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ታደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ይህ ነው፤ 2 ስድስት ቀን ሥራ ይደረጋል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የዕረፍት ሰንበት የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል። 3 በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ። 4 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ 5 ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቍርባን ያምጣ፤ ወርቅና ብርም ናስም፤ 6 ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤ 7 ቀይም የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣም ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፤ 8 ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፤ 9 መረግድ ለኤፉዱና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። 10 በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ። 11 ማደሪያውን፥ ድንኳኑንም መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ 12 ታቦቱን መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም በእርሱም ፊት የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ 13 ገበታውን መሎጊያዎቹንም ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ 14 መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን ዕቃውንም፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 15 የዕጣኑን መሠዊያም መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ 16 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፤ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ 17 የአደባባዩን መጋረጆች ምሰሶቹንም እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 18 የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች አውታሮቻቸውንም፤ 19 በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች። 20 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ። 21 ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። 22 ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ። 23 ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበትም፥ የአቆስጣ ቁርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። 24 ስእለት የተሳለ ሁሉ የብርንም የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የግራርም እንጨት ያለው ሁሉ ለማገልገያ ሥራ አመጣ። 25 በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። 26 ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። 27 አለቆችም መረግድን፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ 28 ለመብራትም ለቅብዓት ዘይትም ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። 29 ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ። 30 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። እዩ፥ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። 31 በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት፤ 32 የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ፥ 33 በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። 34 እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው። 35 በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ በቀይም ግምጃ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ።

ዘጸአት 36

1 ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኞችም ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ። 2 ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው። 3 እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። 4 የመቅደሱንም ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ የሚያደርጉትን ሥራ ትተው መጡ፥ 5 እነርሱም ሙሴን። እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ ብለው ተናገሩት። 67 ያመጡትም ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ስለ ነበረ ሙሴ አዘዘና። ወንድ ወይም ሴት ለመቅደስ ስጦታ ከዚህ የበለጠ የሚያመጣ አይኑር ብሎ በሰፈሩ ውስጥ አሳወጀ። ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። ፕ 8 በእነርሱም ዘንድ ያሉት ሥራ ሲሠሩ የነበሩት በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ ማደሪያውን ከአሥር መጋረጆች ሠሩ፤ እነርሱንም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን አደረጉባቸው። 9 የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ነበረ፤ የመጋረጆቹ ሁሉ ልክ ትክክል ነበረ። 10 አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አጋጠሙ፤ አምስቱንም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠሙ። 11 ከሚጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አደረጉ። 12 አምሳ ቀለበቶችንችን በአንድ መጋረጃ አደረጉ፤ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አደረጉ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ። 13 አምሳም የወርቅ መያዣዎች ሠሩ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠሙአቸው፤ አንድ ማደሪያም ሆነ። 14 ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆችን ከፍየል ጠጕር አደረጉ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች አደረጉ። 15 እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ነበረ። 16 አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ አድርገው፥ ስድስቱንም መጋረጆች አንድ አድርገው አጋጠሙአቸው። 17 ከተጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ። 18 ድንኳኑም አንድ እንዲሆን ያጋጥሙት ዘንድ አምሳ የናስ መያዣዎችን ሠሩ። v 19 ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አደረጉ። 20 ለማደሪያውም ከግራር እንጨት የሚቆሙትን ሳንቆች አደረጉ። 21 የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 22 ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩ፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። 23 ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አደረጉ፤ 24 ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮች አደረጉ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ነበሩ። 25 ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች አደረጉ፤ 26 ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረጉ። 27 ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገበስተ ኋላ ስድስት ሳንቆች አደረጉ። 28 ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆች አደረጉ። 29 ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ። 30 ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስቱ የብር እግሮቻቸው፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት ሁለት እግሮች ነበሩ። 31 ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንደኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ 32 በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራቡ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አደረጉ። 33 መካከለኛውንም መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር አሳለፉ። 34 ሳንቆቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ አደረጉ፤ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው። 35 መጋረጃውንም ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረጉ። 36 ከግራርም እንጨት አራት ምሰሶች አደረጉለት፥ በወርቅም ለበጡአቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች አደረጉ። 37 ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አደረጉ፤ 38 አምስቱንም ምሰሶች፥ ኩላቦቻቸውንም አደረጉ፤ ጕልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ አምስቱም እግሮቻቸው የናስ ነበሩ።

ዘጸአት 37

1 ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 2 በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። 3 አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። 4 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 5 ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ። 6 ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ። 7 ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው። 8 ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው። 9 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ። 10 ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ። 11 በጥሩም ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። 12 በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። 13 አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። 14 ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ። 15 ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16 ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን ጽዋዎቹንም መቅጃዎቹንም፥ ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው። 17 መቅረዙንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጕብጕቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ። 18 በስተ ጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ወጡ። 19 በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። 20 በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። 21 ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ። 22 ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። 23 ሰባቱንም መብራቶች መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 24 መቅረዙንም ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ። 25 የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ። 26 ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። 27 ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ነበሩ። 28 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 29 የተቀደሰውንም የቅብዓቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ።

ዘጸአት 38

1 ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ። 2 ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው። 3 የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ። 4 እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያ አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው። 5 ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ። 6 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በናስም ለበጣቸው። 7 ይሸከሙትም ዘንድ በመሠዊያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው። 8 የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ። 9 አደባባዩንም አደረገ፤ በደቡብ ወገን ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ የተፈተለ የጥሩ በፍታ መጋረጆች ነበሩ። 10 ከናስ የተሠሩ ሀያውን ምሰሶችና ሀያውን እግሮች አደረገ፤ የምሰሶቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ። 11 በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ ከናስም የተሠራ ሀያ ምሰሶችንና ሀያ እግሮችን፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 12 በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ አሥሩንም ምሰሶች፥ አሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ። 13 በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች አደረገ። 14 በአንድ ወገንም የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ። 15 እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ አሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ሦስትም ምሰሶች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ። 16 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጆች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር። 17 የምሰሶቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶችም ጕልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው። 18 የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ነበረ፥ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጆች አምስት ክንድ ነበረ፤ 19 ከናስ የተሠሩ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኩላቦቹ የብር ነበሩ፤ ጕልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር። 20 የማደሪያውም ካስማዎች በዙሪያውም ያለ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ። 21 በሙሴ ትእዛዝ ለሌዋውያን ማገልገል ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ እንደ ተቈጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው። 22 ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23 ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም የቅርጽ ሠራተኛና ብልህ ሠራተኛ፥ በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ፥ በጥሩም በፍታ የሚሠራ ጠላፊ ነበረ። 24 የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ በመቅደሱ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ። 25 በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ። 26 እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የሰቅል ግማሽ ከተቈጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ። 27 መቶውም የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶውም መክሊት መቶ እግሮች አደረገ፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ነበረ። 28 ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶቹን ኩላቦችና ዘንጎች አደረገ፥ የምሰሶቹንም ጕልላቶች ለበጠ። 29 የተሰጠውም ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 30 ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ 31 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የማደሪያውንም ካስማዎች ሁሉ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።

ዘጸአት 39

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ። 2 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ። 3 ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ። 4 ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት። 5 በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ። 6 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው። 7 ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ አደረጋቸው። 8 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገው። 9 አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱን ኪስም ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ። 10 ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤ 11 በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤ 12 በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤ 13 በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ። 14 የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ አሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ አሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ። 15 ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ። 16 ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አደረጉ። 17 ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ። 18 የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ። 19 ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው። 20 ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው። 21 የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ጋር ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የኤፉዱን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አደረገው። 23 በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ። 24 በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ። 25 ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፥ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ። 26 በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኵራንና ሮማንን ለማገልገል አደረጉ። 27 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ሸሚዞችን፥ 28 ከጥሩ በፍታም መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የእግር ሱሪዎችን፥ 29 ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን አደረጉ። 30 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት። 31 በመጠምጠሚያውም ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት። 32 እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። 33 ማደሪያውንም፥ ድንኳኑንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ 34 ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፤ 35 የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤ 36 ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ 37 ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 38 የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 39 የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ 40 የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው ማገልገያ የሚሆኑን ዕቃዎች ሁሉ፤ 41 በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ። 42 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ። 43 ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።

ዘጸአት 40

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ። 3 በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። 4 ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። 5 ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። 6 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ። 7 የመታጠቢያውን ሰንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ። 8 በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ። 9 የቅብዓቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል። 10 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል። 11 የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀብተህ ትቀድሳለህ። 12 አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ። 13 የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ። 14 ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ፤ 15 በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፤ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል። 16 ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 17 እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ። 18 እግዚአብሔርም እንዳዘዘው ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹንም አኖረ፥ ሳንቆቹንም አቆመ፥ መወርወሪያዎቹንም አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ። 19 ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑን መደረቢያ በላዩ አደረገበት። 20 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ዘንድ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤ 21 ታቦቱን ወደ ማደሪያው አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤ 23 እንጀራውን በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ። 24 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤ 25 ቀንዲሎቹን በእግዚአብሔር ፊት ለኰሰ። 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤ 27 የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ዐጠነበት። 28 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በማደሪያው ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ። 29 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠለውንና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት። 30 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት። 31 በእርሱም ሙሴና አሮን ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ፤ 32 ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር። 33 በማደሪያውና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ። 34 ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35 ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም። 36 ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር። 37 ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38 በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና።

ዘሌዋውያን 1

1 እግዚአብሔርም ከመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን ጠርቶ እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው። ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ። 3 መባውም የሚቃጠል መሥዋዕት ከላሞች መንጋ ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርባል፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ያቀርበዋል። 4 እጁንም በሚቃጠለው መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል። 5 በሬውንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን ያቀርባሉ፤ ደሙንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ፊት ባለው በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 6 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ይገፍፈዋል፥ በየብልቱም ይቈርጠዋል። 7 የካህኑም የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሳት ያነድዳሉ፥ በእሳቱም ላይ እንጨት ይደረድራሉ፤ 8 የአሮንም ልጆች ካህናቱ የተቈረቱትን ብልቶች ራሱንም ስቡንም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርቡታል፤ 9 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል፤ ካህኑም ሁሉን የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን አድርጎ በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10 ቍርባኑም የሚቃጠል መሥዋዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ተባቱን ያቀርበዋል። 11 በመሠዊያውም አጠገብ በሰሜን ወገን በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 12 በየብልቱም ራሱንም ስቡንም ይቈርጠዋል፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ይረበርበዋል፤ 13 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ግን በውኃ ያጥባል። ካህኑም ሁሉን አቅርቦ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው። 14 ለእግዚአብሔርም የሚቀርበው ቍርባን የሚቃጠል መሥዋዕት ከወፎች ቢሆን፥ ቍርባኑን ከዋኖስ ወይም ከርግብ ያቀርባል። 15 ካህኑም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል፥ ራሱንም ይቈለምመዋል፥ በመሠዊያውም ላይ ያቃጥለዋል። ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፈጠፋል፤ 16 የሆድ ዕቃውንም ከላባዎች ጋር ለይቶ በመሠዊያው አጠገብ በምሥራቅ ወገን በአመዱ ስፍራ ይጥለዋል፤ 17 በክንፎቹም ይቀድደዋል፥ ነገር ግን አይከፍለውም። ካህኑም በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥለዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕት የእሳት ቍርባን በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ ነው።

ዘሌዋውያን 2

1 ማናቸውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ቍርባኑ ከመልካም ዱቄት ይሁን፤ ዘይትም ያፈስስበታል፥ ዕጣንም ይጨምርበታል፤ 2 ወደ አሮንም ልጆች ወደ ካህናቱ ያመጣዋል፤ ከመልካም ዱቄቱና ከዘይቱም አንድ እፍኝ ሙሉና ዕጣኑን ሁሉ ወስዶ ካህኑ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 3 ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 4 በእቶን የተጋገረውን የእህል ቍርባን ስታቀርብ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት የቂጣ እንጐቻ ወይም በዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ይሁን። 5 ቍርባንህም በምጣድ የተጋገረ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ በዘይት የተለወሰ የመልካም ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6 ቈርሰህም ዘይት ታፈስስበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 7 ቍርባንህም በመቀቀያ የበሰለ የእህል ቍርባን ቢሆን፥ ዘይት የገባበት ከመልካም ዱቄት የተደረገ ይሁን። 8 ከዚህም የተደረገውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታመጣለህ፤ ለካህኑም ይሰጣል፥ እርሱም ወደ መሠዊያው ያቀርበዋል። 9 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መታሰቢያውን አንሥቶ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10 ከእህሉም ቍርባን የተረፈው ለአሮንና ለልጆቹ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሆን የእሳት ቍርባን ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 11 እርሾ ያለበት ነገር ማርም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ይሆን ዘንድ አታቀርቡምና ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የእህል ቍርባን ሁሉ እርሾ አይሁንበት። 12 እነዚህንም የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደ ጣፋጭ ሽታ ግን በመሠዊያው ላይ አይቃጠሉም። 13 የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ታጣፍጠዋለህ፤ የአምላክህንም ቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አታጐድልም፤ በቍርባንህ ሁሉ ላይ ጨው ታቀርባለህ። 14 ከበኵራትም የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርብ ስለዚህ ቍርባን በእሳት የተጠበሰና የተፈተገ የእህል እሸት ታቀርባለህ። 15 ዘይትም ታፈስስበታለህ፥ ዕጣንም ትጨምርበታለህ፤ የእህል ቍርባን ነው። 16 ካህኑም ከተፈተገው እህል ከዘይቱም ወስዶ ከዕጣኑ ሁሉ ጋር መታሰቢያውን ያቃጥላል፤ ይህ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።

ዘሌዋውያን 3

1 ቍርባኑም የደኅንነት መሥዋዕት ቢሆን፥ ከላሞች መንጋ ተባት ወይም እንስት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 2 እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 3 ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 4 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 5 የአሮንም ልጆች ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በመሠዊያው ላይ በእሳቱ ላይ ባለው በእንጨቱ ላይ ያቃጥሉታል፤ የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ነው። 6 ለእግዚአብሔርም ለደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርበው ቍርባኑ ከበጎች ተባት ወይም እንስት ቢሆን፥ ነውር የሌለበትን ያቀርባል። 7 ለቍርባኑ ጠቦትን ቢያቀርብ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 8 እጁንም ለቍርባን በቀረበው ራስ ላይ ይጭናል፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 9 ከደኅንነቱም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርባል፤ ስቡን፥ እስከ ጀርባውም ድረስ የተቈረጠ ላቱን ሁሉ፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 10 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 11 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ለእግዚአብሔር የተደረገ የቍርባን መብል ነው። 12 ቍርባኑም ፍየል ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል፤ 13 እጁንም በራሱ ላይ ይጭንበታል፥ በመገናኛውም ድንኳን ፊት ያርደዋል፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጩታል። 14 ከእርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አድርጎ ያቀርበዋል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 15 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር ይወስዳል። 16 ካህኑም በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ በእሳት ላይ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የተደረገ መብል ነው። ስቡ ሁሉ ለእግዚአብሔር ነው። 17 ስብና ደም እንዳትበሉ በምትኖሩበት ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።

ዘሌዋውያን 4

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ 3 የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኃጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። 4 ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፥ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። 5 የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ 6 ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 7 ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 8 ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 9 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ 10 ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል። ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። 11 የወይፈኑን ቁርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ 12 ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስደዋል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። 13 የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፥ 14 እንዲህም ቢበድሉ፥ የሠሩት ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። 15 የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል። 16 የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ 17 ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 18 በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 19 ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 20 እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንዳደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። 21 ወይፈኑንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስደዋል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 22 አንድ መኰንንም ኃጢአትን ሲሠሩ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ሲተላለፍ፥ እንዲህም ሲበድል፥ 23 የሠራው ኃጢአት ቢታወቅ፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርበዋል፤ 24 በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 25 ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 26 ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 27 ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ኃጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ 28 ለእርሱም የሠራው ኃጢአት ቢታወቀው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። 29 እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መስዋዕት ያርዳል። 30 ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 31 ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 32 ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። 33 እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። 34 ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 35 ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።

ዘሌዋውያን 5

1 ማንም ሰው የሚያምለውን ቃል ቢሰማ፥ ምስክር ሆኖም አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ ወይም አውቆ እንደ ሆነ ባይናገር፥ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል። 2 ማናቸውም ሰው ሳይታወቀው ርኩስ ነገር ቢነካ፥ የረከሰም አውሬ በድን፥ ወይም የረከሰ ከብት በድን፥ ወይም የረከሰ የተንቀሳቀሰ እንስሳ በድን ቢሆን፥ እርሱም ርኩስ ቢሆን ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል፤ 3 ወይም ርኩስነቱን ሳይውቅ ርኩስን ሰው ቢነካ፥ በማናቸውም ርኵሰት ቢረክስ፥ ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል። 4 ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ክፉን ወይም መልካምን ያደርግ ዘንድ ሳያስብ በከንፈሩ ተናግሮ ቢምል፤ ሳያስብ የማለው ስለ ማናቸውም ነገር ቢሆን፤ በታወቀው ጊዜ ከዚህ ነገር በአንዱ በደለኛ ይሆናል። 5 ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ሲሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። 6 ስለ ሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ እርሱም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆናል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። 7 ስለ ሠራው ኃጢአት ለበደል መሥዋዕት ጠቦትን ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። 8 ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ እርሱም አስቀድሞ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ያቀርባል፥ ራሱንም ከአንገቱ ይቈለምመዋል፥ ነገር ግን አይቈርጠውም። 9 ከኃጢአቱም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ግድግዳ ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈውም ደም ከመሠዊያው በታች ይንጠፈጠፋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 10 እንደ ሥርዓቱም ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘጋጀዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 11 ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ስለ ሠራው ኃጢአት የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካም ዱቄት ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና ዘይት አያፈስስበትም፥ ዕጣንም አይጨምርበትም። 12 ወደ ካህኑም ያመጣዋል፥ ካህኑም መታሰቢያው ይሆን ዘንድ ከእርሱ እፍኝ ሙሉ ይውሰድ፥ ለእግዚአብሔርም በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 13 ካህኑም ከእነዚያ በአንዳቸው ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ለካህኑ ይሆናል። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 15 ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል፤ እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል። 16 በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኃጢአት ዕዳ ይከፍላል፥ አምስተኛውንም እጅ ይጨምርበታል፥ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 17 ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ ባያውቅም፥ ያ ሰው በደለኛ ነው፥ ኃጢአቱንም ይሸከማል። 18 ነውር የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት እንደ ግምጋሜህ መጠን ወደ ካህኑ ያመጣዋል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሳተው ስሕተት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 19 እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው፤ በእውነት በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ነው።

ዘሌዋውያን 6

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥ 3 ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ 4 እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ 5 ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ፤ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። 6 ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ። 7 ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል። 8 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 9 አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። 10 ካህኑም የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። 11 ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል። 12 እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። 13 ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም። 14 የእህሉም ቍርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ያቀርቡታል። 15 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 16 ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። 17 በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን ከእሳቱ ቍርባኔ ለእነርሱ እድል ፈንታ እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 18 ለእግዚአብሔር ከቀረበ ከእሳት ቍርባን ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ እድል ፈንታቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 20 በተቀቡበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኵሌታውን በጥዋት፥ እኵሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቍርባን ይህ ነው። 21 ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይደረጋል፤ ሲለወስ ታገባዋለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ። 22 ከልጆቹም በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ይቃጠላል። 23 ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም። 24 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 25 አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 26 ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል። 27 ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸው ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ። 28 የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል። 29 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 30 ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።

ዘሌዋውያን 7

1 የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 2 የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል። 3 ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል። 4 ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 5 ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው። 6 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 7 የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል። 8 የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቁርበት ለዚያው ካህን ይሆናል። 9 በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። 10 በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለሁሉም ይሆናል። 11 ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 12 ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል። 13 ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። 14 ከቍርባኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን እንዲሆን ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15 ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ በሚቀርብበት ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያድርም። 16 የቍርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ 17 ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቆየው በእሳት ይቃጠላል። 18 በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቍርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል። 19 ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ይቃጠል። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። 20 ሰውም የረከሰ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 21 ማናቸውንም ርኵስ ነገር ቢነካ፥ የሰውን ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ሌላውን የተጠላ ርኩስን ቢነካ፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23 የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። 24 የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም አትብሉ፤ 25 ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ፥ ያ የበላ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 26 በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። 27 ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 28 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 29 የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቍርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። 30 የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቍርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባው በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዝ ዘንድ ስቡንና ፍርምባውን ያመጣል። 31 ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። 32 ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቍርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላችሁ። 33 ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። 34 የሚወዘወዘውን ፍርምባና የሚነሣውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘላለም እድል ፈንታ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ። 35 እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ ባቀረባቸው ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቍርባን የአሮንና የልጆቹ እድል ፈንታ ይህ ነው። 36 ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም እድል ፈንታቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። 37 የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 38 እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቍርባናቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።

ዘሌዋውያን 8

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ ሌማት ውሰድ፤ 3 ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው። 4 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰቡ። 5 ሙሴም ማኅበሩን። እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው። 6 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። 7 ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። 8 የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል፥ ቅጠል የሚመስለውን የወርቅ ምልክት፥ አደረገ። 10 ሙሴም የቅብዓቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 11 ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ። 12 ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው። 14 የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15 አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። 16 በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቁርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 18 ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19 አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20 አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። 21 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 22 ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 23 አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። 24 የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25 ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26 በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከቂጣው እንጀራ ሌማት አንድ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27 ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዛቸው። 28 ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው፤ የጣፋጭ ሽታ መቀደሻ ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባን ነበረ። 29 ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ። 30 ሙሴም ከቅብዓቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። 31 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው። ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይበሉታል ብዬ እንዳዘዝሁ በዚያ እርሱንና በሌማቱ ያለውን የቅድስናውን እንጀራ ብሉ። 32 ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33 ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34 በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ። 35 እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓት ጠብቁ። 36 አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።

ዘሌዋውያን 9

1 በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። 2 አሮንንም አለው። ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው እምቦሳውን፥ ስለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ነውር የሌለባቸውን ወስደህ በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው። 34 የእስራኤልንም ልጆች። ዛሬ እግዚአብሔር ይገለጥላችኋልና ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይሠዉ ዘንድ ውሰዱ ብለህ ንገራቸው። 5 ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 6 ሙሴም። ታደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥላችኋል አለ። 7 ሙሴም አሮንን። ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአትህን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቍርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም አለው። 8 አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። 9 የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች አስነካ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኵላሊቶቹን፥ የጕበቱንም መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 11 ሥጋውንና ቁርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 12 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። 13 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በየብልቱ፥ ራሱንም አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14 የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 15 የሕዝቡንም ቍርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው ሠዋው። 16 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቀረበ፥ እንደ ሥርዓቱም አደረገው። 17 የእህሉንም ቍርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው። 18 ስለ ሕዝቡ የሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ 19 በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ የበሬውንና የአራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኩላሊቶቹንም፥ የጉበቱንም መረብ አመጡለት። 20 ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ ስቡንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘው። 22 አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ የኃጢያቱን የሚቃጠለውንም የደኅንነቱንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። 23 ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ወጡም፥ ሕዝቡንም ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24 እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ወደቁ።

ዘሌዋውያን 10

1 የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። 2 እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3 ሙሴም አሮንን። እግዚአብሔር። ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀድሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ 4 ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ። ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው። 5 እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው። 6 ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን። እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። 7 የእግዚአብሔር የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም አላቸው። እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ። 8 እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 9 እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ 10 በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤ 11 እግዚአብሔርም በሙሴ ቃል የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራላችሁ። 12 ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው። ቅዱስ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን የቀረውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት እግዚአብሔርም እንዲህ አዞኛል፥ 13 ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዓት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 14 እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዓት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ። 15 የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘውዙ የእሳት ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ለልጆችህ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል። 16 ሙሴም የኃጢያቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልአዛርንና ኢታምርን ተቈጥቶ። 17 ቅዱስ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኃጢያትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? 18 እነሆ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንዳዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር አላቸው። 19 አሮንም ሙሴን። እነሆ ዛሬ የኃጢያታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢያት መሥዋዕት በበላሁ ኖሮ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኖሮአልን? አለው። 20 ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።

ዘሌዋውያን 11

1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በሉአቸው። ከምድር እንስሶች ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው። 3 የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። 4 ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 5 ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 6 ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 7 እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 8 የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 9 በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ በውኆች በባሕሮችም በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10 በውኆቹ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ካላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 11 በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ፤ ሥጋቸውንም አትበሉም፥ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ። 12 ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 13 ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ 14 ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭላት፥ ጭልፊት በየወገኑ፥ 15 ቁራ ሁሉ በየወገኑ፥ 16 ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥ 17 18 ጕጕት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ የውኀ ዶሮ፥ 19 ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 20 የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሔድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 21 ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ። 22 ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አራቱን ዓይነት አንበጣዎች በየወገናቸው። 23 ነገር ግን የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 24 በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 25 ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 26 ሰኮናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኮናው ያልተሰነጠቀ፥ የማያመሰኳም እንሰሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው። 27 በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 28 በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 29 በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቅሳሽ እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥ 30 ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። 31 ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 32 ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የእንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቁርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱ በውኃ ውስጥ ይደረግ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33 ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፥ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው። 34 በእርሱ ውስጥ ያለው፥ ውኃም የሚፈስስበት የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው። 35 ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሶች ናቸው፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሆናሉ። 36 ነገር ግን ምንጩ፥ ጕድጓዱም፥ የውኃውም ኵሬ ንጹሐን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው። 37 ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢወድቅ እርሱ ንጹሕ ነው። 38 ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 39 ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሶች የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 40 ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 41 በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ የተጸየፈ ነው፥ አትብሉትም። 42 በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የተጸየፉ ናቸውና አትብሉአቸው። 43 በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታስጸይፉ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው። 44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ። 45 እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 46 የእንስሳና የወፍ፥ በውኃም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። 47 በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።

ዘሌዋውያን 12

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤ እንደ ሕመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች። 3 በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ። 4 ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ። 5 ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ። 6 የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣለት። 7 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላትማል፤ ከደምዋም ፈሳሽ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው። 8 ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርስዋም ትነጻለች።

ዘሌዋውያን 13

1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 ማናቸውም ሰው በሥጋው ቁርበት ላይ እባጭ ወይም ብጕር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሥጋው ቁርበት እንደ ለምጽ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3 ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ። ርኩስ ነው ይበለው። 4 ቋቁቻውም በሥጋው ቁርበት ላይ ቢነጣ፥ ከቁርበቱም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 5 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። 6 ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 7 ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። 8 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው። 9 የለምጽ ደዌ በሰው ውስጥ ቢሆን እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡለታል። 10 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቁርበቱ ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ 11 እርሱ በሥጋው ቁርበት ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፥ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይዘጋበትም። 12 ለምጹም በቁርበቱ ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቁርበቱን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፥ ካህኑ ያያል፤ 13 እነሆም፥ ለምጹ ሥጋውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሥጋው ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። 14 የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። 15 ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው። 16 የሚያዠውም ሥጋ ተለውጦ ቢነጣ እንደ ገና ወደ ካህኑ ይመጣል። 17 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው። 18 በሥጋውም ቁርበት ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥ 19 በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። 20 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል። 21 ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 22 በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። 23 ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የቍስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል። 24 በሥጋውም ቁርበት የእሳት ትኵሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢታይ፥ 25 ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 26 ካህኑም ቢያየው፥ በቋቁቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 27 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 28 ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኵሳት እባጭ ነው፤ የትኵሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል። 29 ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ ደዌ ቢኖርበት፥ 30 ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው። 31 ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 32 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ይላጫል፥ 33 ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። 34 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 35 ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤ 36 እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነው። 37 ቈረቈሩ ግን በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል። 38 ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቁርበት ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርበት፥ 39 ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቁርበት ላይ ያለው ቋቁቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቁርበቱ ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው። 40 የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 41 ጠጕሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 42 በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው። 43 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሥጋው ቁርበት ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥ 44 ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ። በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው። 45 የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል። 46 ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል። 47 የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን፥ 48 በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጕር ቢሆን፥ አጐዛ ወይም ከአጐዛ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥ 49 ደዌው በልብሱ ወይም በአጐዛው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ይታያል። 50 ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 51 በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በአጐዛው ወይም ከአጐዛው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 52 ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን ወይም ከአጐዛው የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ፥ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠል። 53 ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥ 54 ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ሌላም ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 55 ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየፋገ የሚሄድ ደዌ ነው። 56 ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከአጐዛው ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። 57 በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር አቃጥለው። 58 አንተም ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከአጐዛው ከተደረገው ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። 59 በበግ ጠጕር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።

ዘሌዋውያን 14

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2 በመንጻቱ ቀን የለምጻሙ ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። 3 ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ 4 ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። 5 ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ይዝዛል። 6 ሕያውንም ወፍ ዝግባውንም እንጨት ቀዩንም ግምጃ ሂሶጱንም ወስዶ ከሕያው ወፍ ጋር በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። 7 ከለምጹ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ነው ይለዋል፥ ሕያውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቅቀዋል። 8 የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። 9 በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 10 በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 11 የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች የሚነጻውንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያኖራቸዋል። 12 ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ያንንም የሎግ መስፈሪያ ዘይት፤ ስለ መወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል። 13 የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ የኃጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 14 ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 15 ካህኑም ከዘይቱ ከሎግ መስፈሪያው ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 16 ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። 17 ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 18 በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 19 ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኵሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ በኋላም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። 20 ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፥ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። 21 ድሀም ቢሆን ይህንም ለማምጣት ገንዘቡ ባይበቃው፥ ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፥ ከመስፈሪያውም ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 22 ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች እንደሚቻለው፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ይወስዳል። 23 በስምንተኛውም ቀን ስለ መንጻት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣቸዋል። 24 ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦት የሎግ መስፈሪያውንም ዘይት ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል። 25 የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 26 ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 27 ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ካለው ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይረጨዋል። 28 ካህኑም በእጁ ውስጥ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 29 በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በካህኑ እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል። 30 እንደሚቻለው ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል። 31 እንደሚቻለው አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቍርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 32 ለመንጻቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማያገኝ የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕግ ይህ ነው። 33 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 34 ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ በርስታችሁ ምድር በአንድ ቤት ባደረግሁ ጊዜ፥ 35 ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን። ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ ይመስለኛል ብሎ ይንገረው። 36 ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። 37 ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ 38 ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። 39 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ 40 ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። 41 ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። 42 በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሎች ድንጋዮች ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። 43 ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ 44 ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 45 ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። 46 በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47 በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል። 48 ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን። ንጹሕ ነው ይለዋል። 49 ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። 50 አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። 51 የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሕያውንም ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 52 ቤቱንም በወፉ ደም በምንጩም ውኃ በሕያውም ወፍ በዝግባውም እንጨት በሂሶጱም በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። 53 ሕያውንም ወፍ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድደዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ ንጹሕም ይሆናል። 54 ይህም ሕግ ነው ለሁሉ ዓይነት ለምጽ ደዌ፥ 55 ለቈረቈርም፥ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ 56 ለእባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቋቁቻም፤ 57 በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።

ዘሌዋውያን 15

1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው። ማንም ሰው ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ፥ ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው። 3 ስለሚፈስሰው ነገር ርኵስነቱ ይህ ነው፤ ፈሳሹ ነገር ከሥጋው ቢፈስስ ወይም ከመፍሰሱ ቢቆም፥ ርኩስ መሆኑ ነው። 4 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 5 መኝታውንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 6 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 7 ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 8 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ፥ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 9 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው። 10 ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 11 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ በውኃም ይታጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 12 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የእንጨቱም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይታጠብ። 13 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሱንም ያጥባል፥ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። 14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይመጣል፥ ለካህኑም ይሰጣቸዋል። 15 ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ያስተሰርይለታል። 16 የማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 17 ዘር የነካው ልብስ ሁሉ ቁርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 18 ወንዱ በሴቲቱ ቢደርስባት ሁለቱ በውኃ ይታጠባሉ፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩሶች ናቸው። 19 ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 20 መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 21 መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 22 የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 23 በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 24 ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው። 25 ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኩስ ናት። 26 ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት ርኵስ ነው። 27 እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 28 ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። 29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች። 30 ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል። 31 እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ማደሪያዬን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኵስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኵስነታቸው ለያቸው። 32 ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥ 33 በመርገምዋም ለታመመች፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ የረከሰችንም ሴት ለሚገናኝ ሰው ሕጉ ይኸው ነው።

ዘሌዋውያን 16

1 በእግዚአብሔር ፊት የቀረቡና የሞቱ ሁለት የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው፤ 2 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። 3 እንዲሁ አሮን ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰ ስፍራ ይግባ። 4 የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፥ የበፍታውም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፥ የበፍታውንም መታጠቂያ ይታጠቅ፥ የበፍታውንም መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው። 5 ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። 6 አሮንም ለእርሱ ያለውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፥ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል። 7 ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቆማቸዋል። 8 አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፥ አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር ሌላውንም ዕጣ ለሚለቀቅ። 9 አሮንም የእግዚአብሔር ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያቀርባል፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል። 10 የመለቀቅም ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያስተሰርይበት ዘንድ፥ ለመለቀቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰድደው ዘንድ በሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል። 11 አሮንም ስለ ራሱ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኃጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል። 12 በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል። 13 እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል። 14 ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል። 15 ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል። 16 ከእስራኤል ልጆች ርኵስነት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል። 17 እርሱም ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተ ሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም። 18 በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል። 19 ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኵስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰውማል። 20 መቅደሱንም፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤ 21 አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዝዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል። 22 ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሀ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል። 23 አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ መቅደሱም በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤ 24 በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ለብሶ ይወጣል፤ የእርሱንም የሚቃጠል መስዋዕት፥ የሕዝቡንም የሚቃጠል መስዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል። 25 የኃጢያቱንም መስዋዕት ስብ በመሰዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 26 ለመለቀቅ የሚሆነውን ፍየል የወሰደ ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል። 27 ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደ መቅደስ የገባውን የኃጢአቱን መስዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መስዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ወደ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቁርበታቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 28 ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል። 29 30 ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቋት፥ የአገር ልጅም በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። 31 ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘላለም ሥርዓት ነው። 32 የሚቀባውም፥ በአባቱ ፋንታ ካህን ሊሆን የሚካነው ካህን ያስተስርይ፥ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤ 33 ለቅድስተ ቅዱሳኑም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ። 34 ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተስርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።

ዘሌዋውያን 17

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፥ እንዲህም አለ። 3 ከእስራኤል ቤት ማናቸውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥ 4 በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 5 ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለደኅንነት መሥዋዕት ይሠዉታል። 6 ካህኑም በመገኛኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል። 7 መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ሥርዓት ይሁን። 8 ለእነርሱም እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥ 9 ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 10 ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ። 11 የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። 12 ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች። ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፥ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ። 13 ከእስራኤልም ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል። 14 የሥጋ ሁሉ ሕይወትና ደሙ አንድ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች። የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው። 15 የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16 ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል።

ዘሌዋውያን 18

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 3 እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ። 4 ፍርዴን አድርጉ፥ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5 የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 6 ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 7 የአባትህን ኃፍረተ ሥጋና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 8 የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋ ነው። 9 የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 10 የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና። 11 ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እህትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 12 የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት። 13 የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናት። 14 የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት። 15 የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ። 16 የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው። 17 የሴትንና የሴት ልጅዋን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ትግለጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው። 18 ሚስትህ በሕይወት ሳለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ከእርስዋ ጋር እኅትዋን አታግባ። 19 እርስዋም በመርገምዋ ርኵሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ። 20 እንዳትረክስባትም ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ። 21 ከዘርህም ለሞሎክ በእሳት አሳልፈህ አትስጥ፥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 22 ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና። 23 እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና። 24 በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። 25 ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች። 26 ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤ 27 ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤ 28 ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ። 29 ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 30 ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

ዘሌዋውያን 19

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 3 ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 4 ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5 የደኅንነትንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሰዉ እርሱን ደስ እንድታሰኙበት ሠዉት። 6 በምትሠዉት ቀንና በነጋው ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል። 7 በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ ደስም አያሰኝም፤ 8 የበላውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ኃጢአቱን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 9 የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። 10 የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11 አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ። 12 በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። የሞያተኛው ዋጋ እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አይደርብህ። 14 ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 15 በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በእውነት ፍረድ። 16 በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር፤ በባልንጀራህም ደም ላይ አትቁም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 17 ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። 18 አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 19 ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። 20 ማናቸውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እርስዋም ለባል የተሰጠች ዋጋዋም ያልተከፈለ አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ቅጣት አለባቸው፤ አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። 21 እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። 22 ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል። 23 ወደ አገሩም በገባችሁ ጊዜ፥ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁም ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት እንዳልተገረዘ ይሆንላችኋል፤ አይበላም። 24 የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቅዱስ ይሁን። 25 ፍሬውም ይበዛላችሁ ዘንድ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 26 ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ፤ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ። 27 የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት። 28 ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 29 ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኵሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት። 30 ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31 ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 32 በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33 በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። 34 እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 35 በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ። 36 የእውነትም ሚዛን፥ የእውነትም መመዘኛ፥ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፥ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ። 37 ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

ዘሌዋውያን 20

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ደግሞ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ልጆች ወይም በእስራኤል ዘንድ ከሚቀመጡ እንግዶች ማናቸውም ሰው ዘሩን ለሞሎክ ቢሰጥ ፈጽሞ ይገደል፤ የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። 3 መቅደሴን ያረክስ ዘንድ፥ የተቀደሰውንም ስሜን ያጐሰቍል ዘንድ ዘሩን ለሞሎክ ሰጥቶአልና እኔ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4 ዘሩንም ለሞሎክ ሲሰጥ፥ የአገሩ ሕዝብ ያን ቸል ቢለው ባይገድሉትም፥ 5 እኔ በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፤ እርሱንም፥ ከሞሎክም ጋር ያመነዝሩ ዘንድ የሚከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋለሁ። 6 መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም በሚከተል፥ በሥራቸውም በሚያመነዝር፥ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 7 እንግዲህ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ። 8 ሥርዓቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 9 ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ፈጽሞ ይገደል፥ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው። 10 ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ። 11 ማናቸውም ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ የአባቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 12 ማናቸውም ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ደማቸውም በላያቸው ነው። 13 ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 14 ማናቸውም ሰው እናቲቱንና ልጂቱን ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ በመካከላችሁ ኃጢአት እንዳይሆን እርሱና እነርሱ በእሳት ይቃጠሉ። 15 ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳይቱንም ግደሉአት። 16 ማናቸይቱም ሴት ወደ እንስሳ ብትቀርብ፥ ከእርሱም ጋር ብትገናኝ፥ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 17 ማናቸውም ሰው የአባቱን ልጅ ወይም የእናቱን ልጅ እኅቱን ቢያገባ፥ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢያይ፥ እርስዋም ኃፍረተ ሥጋውን ብታይ፥ ይህ ጸያፍ ነገር ነው፤ በሕዝባቸውም ልጆች ፊት ይገደሉ፤ የእኅቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአልና ኃጢአቱን ይሸከማል። 18 ማናቸውም ሰው ከባለ መርገም ሴት ጋር ቢተኛ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢገልጥ፥ ፈሳሽዋን ገልጦአልና፥ እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። 19 የአባትህን ወይም የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ይህን የሚያደርግ የዘመድን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 20 ሰውም ከአጎቱ ሚስት ጋር ቢተኛ፥ የአጎቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ያለ ልጅ ይሞታሉ። 21 ሰውም የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ የወንድሙን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ያለ ልጅ ይሆናሉ። 22 እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባችሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፥ አድርጉትም። 23 ከፊታችሁ በምጥላቸውም ሕዝብ ወግ አትሂዱ፤ ይህን ሁሉ አድርገዋልና ተጸየፍኋቸው። 24 ነገር ግን እናንተን። ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 25 እንግዲህ ንጹሑን እንስሳ ከርኩሱ፥ ንጹሑንም ወፍ ከርኩስ ትለያላችሁ፤ ርኩሶች ናቸው ብዬ በለየኋቸው በእንስሳና በወፍ በምድርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ነፍሳችሁን አታርክሱ። 26 እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ። 27 ሰው ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጽመው ይገደሉ፤ በድንጋይ ይውገሩአቸው፤ ደማቸው በላያቸው ነው።

ዘሌዋውያን 21

1 እግዚአብሔርም ሙሴን። ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለው። ማንም ሰው ከሕዝቡ ስለ ሞተው፥ 2 ከሚቀርበው ዘመዱ፥ ከእናቱ፥ ወይም ከአባቱ፥ ወይም ከወንድ ልጁ፥ ወይም ከሴት ልጁ፥ ወይም ከወንድሙ በቀር አይርከስ። 3 ወይም የቀረበችው ያልተጋባች ድንግል እኅቱ በእርስዋ ይርከስ። 4 የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ። 5 ራሳቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ሥጋቸውንም አይንጩ። 6 ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፥ የአምላካቸውንም ስም አያጐስቍሉ፤ የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባንና የአምላካቸውን እንጀራ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ። 7 ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ። 8 የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ። 9 የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል። 10 በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ። 11 ወደ በድንም ሁሉ አይግባ፥ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ። 12 የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13 እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ። 14 ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ ወይም ጋለሞታይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ድንግሊቱን ያግባ። 15 እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 17 ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 18 ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥ 19 ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥ 20 ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ። 21 ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ። 22 የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤ 23 ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 24 ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ።

ዘሌዋውያን 22

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3 እንዲህ በላቸው። ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 4 ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥ 5 ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዓይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥ 6 እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ። 7 ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ይብላ። 8 በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 9 ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ ስለ እርስዋም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 10 ልዩ ሰው ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ። 11 ካህኑ ግን በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ እርሱ ይብላው፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ። 12 የካህንም ልጅ ከልዩ ሰው ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ቍርባን አትብላ። 13 የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ልዩ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ። 14 ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ። 15 16 የምቀድሳቸውም እግዚአብሔር እኔ ነኝና ከተቀደሰው በበሉ ጊዜ ኃጢአትንና በደልን እንዳይሸከሙ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን በእስራኤል ልጆች ዘንድ የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 18 ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥ 19 ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ። 20 ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን አታቅርቡ። 21 ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት። 22 ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት ወይም እከካም ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር አታሳርጉ። 23 በሬው ወይም በጉ የተጨመረበት ወይም የጐደለበት ነገር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም። 24 የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ። 25 ከእነዚህም ከእንግዳ ሰው እጅ ለአምላካችሁ እንጀራ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም። 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 27 በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል። 28 ላም ወይም በግ ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ። 29 የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ ሠዉለት። 30 በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31 ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 32 የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤ 33 የምቀድሳችሁ፥ አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

ዘሌዋውያን 23

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው። 3 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። 4 እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው። 5 በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። 6 በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ። 7 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 8 ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 10 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤ 11 እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ይወዝውዘው። 12 ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። 13 የእህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን። 14 እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 15 የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤ 16 እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ። 17 ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ለበኵራት ቍርባን እንዲሆን በእርሾ ይጋገራል። 18 ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሁኑ፤ ከእህልም ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሁኑ። 19 አንድም አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ። 20 ካህኑም ከበኵራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዛቸዋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ለካህኑ ይሁን። 21 በዚያም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችሁ ዘንድ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 22 የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 24 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ። 25 የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። 26 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 27 በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ። 28 በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ። 29 በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 30 በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ። 31 ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። 32 የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፥ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ። 33 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 34 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በዚህ በሰባተኛው ወር ከአሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል። 35 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። 36 ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት። 37 የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው። 39 ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። 40 በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የሰሌን ቅርንጫፍ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። 41 ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው፤ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። 42 43 ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የአገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 44 ሙሴም የእግዚአብሔርን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።

ዘሌዋውያን 24

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 መብራቱን ሁልጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 3 በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን። 4 በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው። 5 መልካሙንም ዱቄት ወስደህ አሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን። 6 እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ገበታ ላይ አኑራቸው። 7 ለእግዚአብሔርም ለእሳት ቍርባን በእንጀራው ላይ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሁለቱ ተርታ ላይ ጥሩ ዕጣን አድርግ። 8 በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያድርገው፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9 ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን በዘላለም ሥርዓት ለእርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት። 10 አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤ 11 የእስራኤላዊቱም ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ። 12 ከእግዚአብሔርም አፍ ስለ እርሱ ፍርድ እስኪወጣላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት። 13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 14 ተሳዳቢውን ከስፈሩ ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው። 15 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ። ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል። 16 የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል። 17 ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። 18 እንስሳንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል። 19 ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። 20 ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት። 21 እንስሳውንም የሚገድል ካሣ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል። 22 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይሁንላችሁ። 23 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

ዘሌዋውያን 25

1 እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ። 3 ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ። 4 በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ። 5 የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን። 6 የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛውም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን። 7 ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን። 8 ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ። 9 ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ። 10 አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ። 11 ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ። 12 ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ። 13 በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል። 14 ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል። 15 ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል። 16 እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ታበዛለህ፥ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል። 17 እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 18 ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። 19 ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። 20 እናንተም። ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥ 21 እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። 22 በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ። 23 ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ። 24 በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ። 25 ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል። 26 የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥ 27 የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። 28 ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ። 29 ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል። 30 አንድ ዓመትም እስኪጨረስ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለበት ከተማ የሚሆን ቤት ለገዛው ለልጅ ልጁ ለዘላለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ አይወጣም። 31 ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ይወጣሉ። 32 በእነርሱ ከተማ ያለ የሌዋውያን ቤት ግን ሌዋውያን ለዘላለም መቤዠት ይችላሉ። 33 ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተማ ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል። 34 በከተማቸውም ዙሪያ ያለችው መሰምርያ የዘላለም ርስታቸው ናትና አትሸጥም። 35 ወንድምህ ቢደኸይ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር። 36 ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 37 ብርህን በወለድ አታበድረው፤ መኖህንም በትርፍ አትስጠው። 38 የከነዓንን ምድር እሰጣችሁ ዘንድ፥ አምላክም እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 39 ወንድምህም ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው። 40 እንደ ምንደኛና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ። 41 በዚያን ጊዜም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይውጣ፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለስ። 42 ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸውና እንደ ባሪያዎች አይሸጡ። 43 በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 44 ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ መግዛት ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባሪያዎችን ግዙ። 45 ደግሞም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ከዘራቸው ውስጥ ባሪያዎችን ግዙ፤ ርስትም ይሁኑላችሁ። 46 ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ይወርሱአቸው ዘንድ ተዉአቸው፤ ከእነርሱም ባሪያዎችን ለዘላለም ትወስዳላችሁ፤ ነገር ግን የእስራኤልን ልጆች ወንድሞቻችሁን በጽኑ እጅ አትግዙአቸው። 47 በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥ 48 ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤ 49 ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው። 50 ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን። 51 ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 52 እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመታቱም መጠንየመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ። 53 በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ በጽኑ እጅ አይግዛው። 54 በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ። 55 የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

ዘሌዋውያን 26

1 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። 2 ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3 በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ 4 ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። 5 የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። 6 በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። 7 ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። 8 ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 9 ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10 ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። 11 ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12 በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። 13 ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ። 14 ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 15 ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥ 16 እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17 ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። 18 እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 19 የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20 ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም። 21 በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 22 በመካከላችሁም የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቃሉ፥ እንስሶቻችሁንም ያጠፋሉ፥ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። 23 እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱ፥ 24 እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25 የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። 26 የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም። 27 እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ፥ 28 እኔ ደግሞ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29 የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። 30 የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ የፀሐይ ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31 ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትትም። 32 ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም በእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። 33 እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ። 34 በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበትንም በማድረግዋ ትደሰታለች። 35 እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። 36 በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ። 37 ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። 38 በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39 ከእናንተም ተለይተው የቀሩት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይከሳሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይከሳሉ። 40 በእኔም ላይ በእንቢተኝነት ስለ ሄዱብኝ የበደሉኝን በደል፥ ኃጢአታቸውንም፥ የአባቶቻቸውንም ኃጢአት ይናዘዛሉ። 41 እኔም ደግሞ በእንቢተኝነት ሄድሁባቸው፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አገባኋቸው፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥ 42 እኔ ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞ ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43 ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የኃጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። 44 ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝኛ እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። 45 እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸውን የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 46 እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ ያደረጋቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።

ዘሌዋውያን 27

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ። 3 ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን። 4 ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5 ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። 6 ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። 7 ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። 8 ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው። 9 ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 10 መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11 እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያኑረው። 12 መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እነሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። 13 ይቤዠውም ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ በላይ አምስተኛ ይጨምር። 14 ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል። 15 የቀደሰውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል። 16 ሰውም ከርስቱ እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ እንደ መዘራቱ መጠን ይገመት፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ አምሳ የብር ሰቅል ይገመታል። 17 እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምቱ መጠን ይቆማል። 18 እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ገንዘቡን ይቈጥርለታል፤ ከግምቱም ይጐድላል። 19 እርሻውንም የቀደሰ ሰው ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ፥ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ለእርሱም ይሆናል። 20 እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ይቤዠው ዘንድ አይቻለውም። 21 እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ሲወጣ እንደ እርም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ርስቱ ለካህኑ ይሆናል። 22 ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ 23 ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ይቈጥርለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለእግዚአብሔር ይሰጣል። 24 በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደ ነበረው ወደ ሸጠው ሰው ይመለሳል። 25 ግምቱም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል። 26 ለእግዚአብሔር ግን የሚቀርበውን የእንስሳ በኵራት ማንም ይቀድሰው ዘንድ አይቻለውም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለእግዚአብሔር ነው። 27 የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምቱ ይቤዠው፥ በእርሱም የዋጋውን አምስተኛ ይጨምርበታል፤ ባይቤዠውም እንደ ግምቱ ይሸጣል። 28 ለእግዚአብሔርም የተለየ እርም የሆነ ነገር ሁሉ፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 29 ከሰዎችም እርም የሆነ ሁሉ አይቤዥም፤ ፈጽሞ ይገደላል። 30 የምድርም አሥራት፥ ወይም የምድር ዘር ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 31 ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ አምስተኛ ይጨምርበታል። 32 ከበሬም ሁሉ ከአሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከአሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል። 33 መልካም ወይም ክፉ እንዲሆን አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዠውም። 34 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።

ዘኍልቍ 1

1 እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን በየራሱ፥ ውሰዱ። 3 ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው። 4 ከየነገዱም አንድ ሰው የአባቶቹ ቤት አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን። 5 ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ 6 ኤሊሱር፥ ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፥ 7 ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥ 8 ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፥ 9 10 ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፍዳሱ ልጅ ገማልኤል፥ 11 12 ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፥ ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፥ 13 ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፥ 14 ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፥ 15 ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ። 16 ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል አእላፍ ታላላቆች፥ የአባቶቻቸው ነገድ አለቆች እነዚህ ናቸው። 17 ሙሴና አሮንም እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤ 18 በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን በየራሱ በየወገኑም በየአባቶቻቸውም ቤቶች በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ። 19 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው። 20 የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 21 ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 22 የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 23 ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 24 የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 25 ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ። 26 የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 27 ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 28 የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 29 ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 30 የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 31 ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 32 ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 33 ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 34 የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 35 ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 36 የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 37 ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 38 የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 39 ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 40 የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 41 ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 42 የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 43 ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 44 የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን አሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው፤ እያንዳንዱ የአባቶቹ ቤት አለቃ ነበረ። 45 ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 46 የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 47 ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። 48 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። የሌዊን ነገድ አትቍጠረው፥ 49 ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር አታድርግ፤ 50 ነገር ግን በምስክሩ ማደሪያና በዕቃዎች ሁሉ ለእርሱም በሚሆነው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ማደሪያውንና ዕቃዎችን ሁሉ ይሸከሙ፥ ያገልግሉትም፥ በማደሪያውም ዙሪያ ይስፈሩ። 51 ማደሪያውም ሲነሣ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያውም በሰፈረ ጊዜ ሌዋውያን ይትከሉት፤ ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል። 52 የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ በየሰፈሩ፥ በየዓላማውም፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ። 53 ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ሌዋውያን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይስፈሩ፤ ሌዋውያንም የምስክሩን ማደሪያ ይጠብቁ። 54 የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።

ዘኍልቍ 2

1 እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ። 2 የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን አፋዛዥ ዙሪያ ይስፈሩ። 3 በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳ ሰፈር ዓላማ ሰዎች ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 4 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 5 በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ። 6 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 7 በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ። 8 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 9 ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ። 10 በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ። 11 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 12 በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ። 13 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 14 በእነርሱም አጠገብ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ። 15 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ። 16 ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ አምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ። 17 ከዚያም በኋላ የመገናኛው ድንኳን በሰፈሮቹም መካከል የሌዋውያን ሰፈር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው ሰው ሁሉ በየስፍራው በየዓላማውም ይጓዛሉ። 18 በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ። 19 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 20 በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ይሆናል፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ። 21 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 22 በእነርሱም አጠገብ የብንያም ነገድ ይሆናል፤ ይብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ። 23 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 24 ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ። 25 በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ። 26 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 27 በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ። 28 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 29 በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ይሆናል፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ። 30 ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 31 ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ አምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ። 32 ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 33 ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 34 የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ተጓዙ።

ዘኍልቍ 3

1 እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። 2 የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። 3 የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው። 4 ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 6 የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። 7 የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ። 8 የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ። 9 ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ። 10 አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል። 11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 12 እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ 13 በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 15 የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው። 16 ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው። 17 የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 18 የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ። 19 የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል። 20 የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው። 21 ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 22 ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 23 የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ። 24 የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። 25 ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ 26 በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል። 27 ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 28 ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር። 29 የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። 30 የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል። 31 ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ። 32 የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል። 33 ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው። 34 ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 35 የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። 36 የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥ 37 ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ። 38 በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል። 39 በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ። 40 እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤ 41 ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው። 42 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ። 43 ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። 44 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 45 ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 46 በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ 47 እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። 48 ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ። 49 ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ። 50 ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ። 51 እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።

ዘኍልቍ 4

1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤ 3 ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ። 4 በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤ 5 ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ 6 በላዩም የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 7 በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን። 8 በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 9 ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤ 10 እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። 11 በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 12 በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። 13 አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ 14 የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉም ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። 15 ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው። 16 የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል። 17 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 18 የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤ 19 ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤ 20 ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 22 የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ። 23 የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። 24 የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤ 25 የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ 26 በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ። 27 የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ። 28 የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ። 29 የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው። 30 የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። 31 በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥ 32 በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ። 33 የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ክአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው። 34 ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው። 35 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ 36 በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ። 37 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 38 በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥ 39 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 40 በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 41 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 42 በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ 43 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 44 በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 45 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። 46 በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥ 47 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ 48 ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ እምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። 49 እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ።

ዘኍልቍ 5

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ 3 ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አውጡአቸው። 4 የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 6 ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤ 7 የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው። 8 ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተሰረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር። 9 የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን። 10 የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን። 11 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 12 ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥ 13 ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥ 14 በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ 15 ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት። 16 ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤ 17 ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤ 18 ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል። 19 ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል። ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤ 20 ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤ 21 ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን። እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤ 22 እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም። አሜን አሜን ትላለች። 23 ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤ 24 እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ይጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል። 25 ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ 26 ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል። 27 ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። 28 ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች። 29 30 ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት። 31 ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች።

ዘኍልቍ 6

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥ 3 ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ። 4 ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ። 5 ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል። 6 ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። 7 ለአምላኩ ያደረገው እስለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው። 8 ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 9 ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው። 10 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 11 ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። 12 ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። 13 የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ 14 ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥ 15 አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ። 16 ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። 17 አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል። 18 ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። 19 ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤ 20 ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል። 21 ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል። 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23 ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው። 24 እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ 25 እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ 26 እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። 27 እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።

ዘኍልቍ 7

1 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ማደሪያውን ፈጽሞ ከተከለ በኋላ፥ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፤ 2 የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ እነዚህም ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙ የነገዶች አለቆች ነበሩ። 3 መባቸውንም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፥ የተከደኑ ስድስት ሰረገሎች አሥራ ሁለትም በሬዎች፤ በየሁለቱም አለቆች አንድ ሰረገላ አቀረቡ፥ ሁሉም እያንዳንዱ አንድ በሬ በማደሪያው ፊት አቀረቡ። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 5 ለመገናኛው ድንኳን ማገልገል ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ስጣቸው። 6 ሙሴም ሰረገሎችንና በሬዎችን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። 7 ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው። 8 ከካህኑም ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ላሉት ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው። 9 ለቀዓት ልጆች ግን መቅደሱን ማገልገል የእነርሱ ነውና፥ በትከሻቸውም ይሸከሙት ነበርና ምንም አልሰጣቸውም። 10 መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቍርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ። 11 እግዚአብሔርም ሙሴን። አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ መባቸውን እያንዳንዱ በቀን በቀኑ ያቅርቡ አለው። 12 በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበ ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 13 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 14 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 15 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 16 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 17 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ። 18 በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ። 19 ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ድስት፤ 20 ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 21 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 22 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 23 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሶገር ልጅ የናትናኤ መባ ይህ ነበረ። 18 በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ። 19 ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆvንውንአንድ የብር ድስት፤ 20 ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 21 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 22 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 23 ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ የሶገር ልጅ የናትናኤል መባ ይህ ነበረ። 24 በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤ 25 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 26 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 27 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 28 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 29 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ። 30 በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤ 31 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 32 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 33 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 34 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 35 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሰዲዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ። 36 በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤ 37 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 38 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 39 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 40 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 41 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሱሪሰዳይ ልጅ የሰለሚኤል መባ ይህ ነበረ። 42 በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤ 43 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ማዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 44 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 45 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 46 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 47 ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ። 48 በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤ 49 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 50 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 51 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 52 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 53 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዓሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ። 54 በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤ 55 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 56 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 57 ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 58 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 59 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፍዳሱር ልጅ የገማልኤል መባ ነበረ። 60 በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤ 61 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 62 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 63 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 64 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 65 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ። 66 በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤ 67 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 68 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 69 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 70 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 71 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዳይ ልጅ የአኪዔዘር መባ ይህ ነበረ። 72 በአሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤ 73 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 74 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 75 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 76 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 77 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ። 78 በአሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ፤ 79 መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 80 ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 81 ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ 82 አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 83 ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ። 84 መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች ለመቀደሻው ያቀረቡት ቍርባን ይህ ነበረ፤ አሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ አሥራ ሁለት የብር ድስቶች፥ አሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፤ 85 እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ድስት ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 86 ዕጣንም የተሞሉ አሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎች፥ እያንዳንዱ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን አሥር አሥር ሰቅል ነበረ፤ የጭልፋዎቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሀያ ሰቅል ነበረ። 87 የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ከእህሉ ቍርባን ጋር አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ አሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ አሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ነበሩ፤ የኃጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች አሥራ ሁለት ነበሩ። 88 የደኅንነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ ሀያ አራት በሬዎች፥ ስድሳም አውራ በጎች፥ ስድሳም አውራ ፍየሎች፥ ስድሳም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቀደሻው የቀረበ ቍርባን ይህ ነበረ። 89 ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር፤ እርሱም ይናገረው ነበር።

ዘኍልቍ 8

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 መብራቶቹን ስትለኵስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው። 3 አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ። 4 መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ። 5 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 6 ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። 7 ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም። 8 ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ። 9 ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። 10 ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። 11 አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 12 ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ። 13 ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው። 14 እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ። 15 ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ። 16 እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። 17 በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። 18 በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። 19 የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ። 20 ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። 21 ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው። 22 ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 24 የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ። 25 ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤ 26 የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ፤ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ።

ዘኍልቍ 9

1 ከግብፅ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሲና ምድረ በዳ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤል ልጆች በጊዜው ፋሲካውን ያድርጉ፤ 3 በዚህ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በጊዜው አድርጉት፤ እንደ ሥርዓቱ ሁሉ እንደ ፍርዱም ሁሉ አድርጉት። 4 ሙሴም ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ተናገራቸው። 5 በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ። 6 በሞተ ሰው ሬሳ የረከሱ ሰዎችም ነበሩ፥ ስለዚህም በዚያ ቀን ፋሲካን ያደርጉ ዘንድ አልቻሉም። በዚያም ቀን ወደ ሙሴና ወደ አሮን ቀረቡ። 7 እነዚያም ሰዎች። በሞተ ሰው ሬሳ ረክሰናል፤ በእስራኤል ልጆች መካከል በጊዜው ቍርባን ለእግዚአብሔር እንዳናቀርብ ስለ ምን እንከለከላለን? አሉት። 8 ሙሴም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስክሰማ ድረስ ቈዩ አላቸው። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 10 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእናንተ ወይም ከትውልዶቻችሁ ዘንድ ሰው በሬሳ ቢረክስ፥ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ፥ እርሱ ደግሞ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያድርግ። 11 በሁለተኛው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ያድርጉት፤ ከቂጣ እንጀራና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 12 ከእርሱም እስከ ነገ ምንም አያስቀሩ፥ ከእርሱም አጥንትን አይስበሩ፤ እንደ ፋሲካ ሥርዓት ሁሉ ያድርጉት። 13 ነገር ግን ንጹሕ የሆነ ሰው በመንገድም ላይ ያልሆነ ፋሲካን ባያደርግ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ የእግዚአብሔርን ቍርባን በጊዜው አላቀረበምና ያ ሰው ኃጢአቱን ይሸከማል። 14 በመካከላችሁም መጻተኛ ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ፋሲካን ያደርግ ዘንድ ቢወድድ፥ እንደ ፋሲካ ሥርዓት እንደ ፍርዱም እንዲሁ ያድርግ፤ ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ሥርዓት ይሁንላችሁ። 15 ማደሪያውም በተተከለ ቀን ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከማታም ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ በማደሪያው ላይ እንደ እሳት ይመስል ነበር። 16 እንዲሁ ሁልጊዜ ነበረ፤ በቀን ደመና በሌሊትም የእሳት አምሳል ይሸፍነው ነበር። 17 ደመናውም ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በቆመበት ስፍራ በዚያ የእስራኤል ልጆች ይሰፍሩ ነበር። 18 በእግዚአብሔር ትእዛዝ የእስራኤል ልጆች ይጓዙ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር። ደመናው በማደሪያው ላይ በተቀመጠበት ዘመን ሁሉ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር። 19 ደመናውም በማደሪያው ላይ ብዙ ቀን በተቀመጠ ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር። 20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው ጥቂት ቀን በማደሪያው ላይ ይሆን ነበር፤ በዚያን ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፤ እንደ እግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር። 21 አንዳንድ ጊዜም ደመናው ከማታ ጀምሮ እስከ ጥዋት ድረስ ይቀመጥ ነበር፤ በጥዋትም ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር፤ በቀንም በሌሊትም ቢሆን፥ ደመናው በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 22 ደመናውም ሁለት ቀን ወይም አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ቆይቶ በማደሪያው ላይ ቢቀመጥ የእስራኤል ልጆች በሰፈራቸው ይቀመጡ ነበር፥ አይጓዙምም ነበር፤ ነገር ግን በተነሣ ጊዜ ይጓዙ ነበር። 23 በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍሩ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዙ ነበር፥ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።

ዘኍልቍ 10

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ። 3 ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ። 4 አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ። 5 መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ። 6 ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ። 7 ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት። 8 የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ። 9 በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ። 10 ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11 በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ። 12 የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጕዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ። 13 በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ። 14 በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ። 15 በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ። 16 በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ። 17 ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ። 18 የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ። 19 በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ። 20 በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ። 21 ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ። 22 የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ። 23 በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ። 24 በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ። 25 ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ። 26 በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ። 27 በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ። 28 እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ። 29 ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን። እግዚአብሔር። ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው። 30 እርሱም። አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው። 31 እርሱም። እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤ 32 ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ። 33 ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው። 34 ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ። 35 ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር። 36 ባረፈም ጊዜ። አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር።

ዘኍልቍ 11

1 ሕዝቡም ክፉ ሆነው በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ሰምቶ ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ነደደች፥ የሰፈሩንም ዳር በላች። 2 ሕዝቡም ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እሳቲቱም ጠፋች። 3 የእግዚአብሔርም እሳት በመካከላቸው ስለነደደች የዚያን ስፍራ ስም ተቤራ ብሎ ጠራው። 4 በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ፤ የእስራኤል ልጆች ደግሞ ያለቅሱ ነበር። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? 5 በግብፅ ያለ ዋጋ እንበላው የነበረውን ዓሣ፥ ዱባውንም፥ በጢኹንም፥ ኩራቱንም፥ ቀዩንም ሽንኩርት፥ ነጩንም ሽንኩርት እናስባለን፤ 6 አሁን ግን ሰውነታችን ደረቀች፤ ዓይናችንም ከዚህ መና በቀር ምንም አታይም አሉ። 7 መናውም እንደ ድንብላል ዘር ነበረ፥ መልኩም ሙጫ ይመስል ነበር። 8 ሕዝቡም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፥ በወፍጮም ይፈጩት፥ ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ይቀቅሉት ነበር፥ እንጐቻም ያደርጉት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ እንጐቻ ነበረ። 9 ሌሊትም ጠል በሰፈሩ ላይ በወረደ ጊዜ መናው በላዩ ይወርድ ነበር። 10 ሙሴም ሕዝቡ በወገኖቻቸው፥ ሰው ሁሉ በድንኳኑ ደጃፍ፥ ሲያለቅሱ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እጅግ ነደደ፤ ሙሴም ተቈጣ። 11 ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? 12 አንተ ለአባቶቻቸው ወደ ማልህላቸው ምድር አደርሳቸው ዘንድ። ሞግዚት የሚጠባውን ልጅ እንድታቀፍ በብብትህ እቀፋቸው የምትለኝ፥ በውኑ ይህን ሕዝብ ሁሉ እኔ ፀነስሁትን? ወለድሁትንስ? 13 በፊቴ ያለቅሳሉና። የምንበላውን ሥጋ ስጠን ይላሉና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ የምሰጠው ሥጋ ከወዴት እወስዳለሁ? 14 እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም። 15 እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። 17 እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። 18 ሕዝቡንም በላቸው። የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። 19 አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ 20 ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም። ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ። 21 ሙሴም። እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም። ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ። 22 እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ። 23 እግዚአብሔርም ሙሴን። በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው። 24 ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25 እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም። 26 ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። 27 አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ። ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው። 28 ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ። ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው። 29 ሙሴም። የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው። 30 ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። 31 ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ። 32 በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ አሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚያህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። 33 ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ። 34 የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ። 35 ሕዝቡም ከምኞት መቃብር ወደ ሐጼሮት ተጓዙ በሐጼሮትም ተቀመጡ።

ዘኍልቍ 12

1 ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። 2 እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ። 3 ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ። 4 እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ። 5 እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ። 6 እርሱም። ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። 7 ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። 8 እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ። 9 እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ። 10 ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር። 11 አሮንም ሙሴን። ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን። 12 ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን። 13 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ። አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት አለው። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን። አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ አለው። 15 ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተዘግታ ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም። 16 ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።

ዘኍልቍ 13

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ። 3 ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ። 4 ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤ 5 ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤ 6 ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ 7 ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤ 8 ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤ 9 10 ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤ 11 ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ 12 ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤ 13 ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤ 14 ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤ 15 ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። 16 ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው። 17 ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም። ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤ 18 ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥ 19 ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥ 20 ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ። 21 ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ። 22 በደቡብም በኩል ውጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር። 23 ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ። 24 የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት። 25 ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ። 26 በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27 እንዲህም ብለው ነገሩት። ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው። 28 ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን። 29 በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል። 30 ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና። ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ። 31 ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን። በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ። 32 ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ። እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው። 33 በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።

ዘኍልቍ 14

1 ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ። 2 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ። በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! 3 እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው። 4 እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ። 5 ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ። 6 ምድርን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7 ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ። ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። 8 እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። 9 ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው። 10 ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ተገለጠ። 11 እግዚአብሔርም ሙሴን። ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምንብኝም? 12 ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ፤ አንተም ከእነርሱ ለሚበዛና ለሚጠነክር ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። 13 ሙሴም እግዚአብሔርን አለው። ግብፃውያን ይሰማሉ፤ ይህን ሕዝብ ከመካከላቸው በኃይልህ አውጥተኸዋልና፤ 14 ለዚችም ምድር ሰዎች ይናገራሉ። አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ፊት ለፊት ተገልጠሃል፥ ደመናህም በላያቸው ቆሞአል፥ በቀንም በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15 ይህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ። 16 እግዚአብሔር ይህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው ብለው ይናገራሉ። 17 18 አሁንም፥ እባክህ። እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው ብለህ እንደ ተናገርህ፥ የጌታ ኃይል ታላቅ ይሁን። 19 ይህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እባክህ፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል። 20 እግዚአብሔርም አለ። እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21 ነገር ግን እኔ ሕያው ነኛ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22 በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ 23 ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤ 24 ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25 አማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆው ውስጥ ተቀምጦአል፤ በነጋው ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ። 26 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 27 የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ። 28 እንዲህ በላቸው። እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 29 በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥ 30 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31 ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ። 32 እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33 ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ። 34 ምድሪቱን በሰላለችሁባት ቀን ቍጥር፥ አርባ ቀን፥ ስለ አንድ ቀንም አንድ ዓመት፥ ኃጢአታችሁን አርባ ዓመት ትሸከማላችሁ፥ ቍጣዬንም ታውቃላችሁ። 35 እኔ እግዚአብሔር። በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፥ በዚያም ይሞታሉ። 36 ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ክፉ ወሬም ስለ ምድሪቱ እያወሩ በእርሱ ላይ ማኅበሩ ሁሉ እንዲያጕረመርሙ ያደረጉ፥ 37 ክፉ ወሬ ያወሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ። 38 ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ተቀመጡ። 39 ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ፥ ሕዝቡም እጅግ አዘኑ። 40 በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ መጥተው። እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ። 41 ሙሴም አለ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም። 42 እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ። 43 አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም። 44 እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም። 45 በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።

ዘኍልቍ 15

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ወደ መኖሪያችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ 3 ስእለታችሁን ልትፈጽሙ፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ታደርጉ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርቡ፥ 45 ቍርባኑን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ያዘጋጃል። 67 ለአንዱም አውራ በግ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታዘጋጃለህ፤ የኢን መስፈሪያ ሢሶም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለህ። 8 ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለደኅንነት መሥዋዕት ወይፈንን ለእግዚአብሔር ብታዘጋጅ፥ 9 ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታቀርባለህ። 10 ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ለተደረገ ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለ። 11 እንዲሁ ለእያንዳንዱ ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ይደረጋል። 12 እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር፥ እንዲሁ እንደ ቍጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ። 13 የአገር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ባቀረበ ጊዜ እንዲሁ ያደርጋል። 14 መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ቢያቀርብ፥ እናንተ የምታደርጉትን እርሱ እንዲሁ ያደርጋል። 15 ለእናንተ በጉባኤው ላላችሁ በእናንተም መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሥርዓት ይሆናል፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁ እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት መጻተኛ ይሆናል። 16 ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሕግና አንድ ፍርድ ይሆናል። 17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 18 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ 19 እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታደርጋላችሁ። 20 መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ አንድ እንጐቻ ለማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማም እንደምታነሡት ቍርባን እንዲሁ ታነሣላችሁ። 21 መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ የማንሣት ቍርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ። 22 ብትስቱም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 23 እግዚአብሔር ካዘዘበት ከፊተኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥ 24 ማኅበሩ ሳያውቁ በስሕተት ቢደረግ፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር እንደ ሕጉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀርባሉ። 25 ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ስሕተትም ነበረና ይሰረይላቸዋል፤ ስለ ስሕተታቸውም ለእግዚአብሔር ቍርባናቸውን በእሳት አቅርበዋል፥ ለእግዚአብሔርም የኃጢአታቸውን መሥዋዕት አቅርበዋል። 26 በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ያለ እውቀት ተደርጎአልና ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል። 27 አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል። 28 ኃጢአት ሠርቶ ሳያውቅ፥ ለሳተ ለዚያ ሰው ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ይሰረይለትማል። 29 ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ሳያውቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆንለታል። 30 የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 31 የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ነው። 32 የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። 33 እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። 34 ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት። 35 እግዚአብሔርም ሙሴን። ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት አለው። 36 ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገሩት። 37 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 38 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው። 39 የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥ 40 ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን። 41 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

ዘኍልቍ 16

1 የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። ች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ 2 ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ። 3 በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ። 4 ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤ 5 ለቆሬም ለወገኑም ሁሉ። ነገ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆነውን፥ ቅዱስም የሚሆነውን ያስታውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ ያቀርበዋል። 6 እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ወገንህ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤ 7 ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ እጅግ አብዝታችኋል ብሎ ተናገራቸው። 8 ሙሴም ቆሬን አለው። እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙ፤ 9 የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁ አይበቃችሁምን? 10 አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ክህነትንም ደግሞ ትፈልጋላችሁን? 11 ስለዚህም አንተና ወገንህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማን ነው? 12 ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም። አንመጣም፤ 13 በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን? 14 ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ። 15 ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ እግዚአብሔርንም። ወደ ቍርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ ስንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም አለው። 16 ሙሴም ቆሬን። ነገ አንተ፥ ወገንህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁኑ፤ 17 ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎች፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ አለው። 18 እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፥ እሳትም አደረገበት፥ ዕጣንም ጨመረበት፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆመ። 19 ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ። 20 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 21 ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ። 22 እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው። አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ። 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 24 ለማኅበሩ። ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው። 25 ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። 26 ማኅበሩንም። እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው። 27 ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ። 28 ሙሴም አለ። ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ። 29 እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም። 30 እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ። 31 እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ 32 ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። 33 እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ። 34 በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ። ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ። 35 እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች። 36 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 37 ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው። ተቀድሰዋልና ጥናዎቹን ከተቃጠሉት ዘንድ ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ ጣለው፤ 38 በኃጢአታቸው ሰውነታቸውን ያጠፉትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፈህ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጋቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ። 39 ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያው መለበጫ አደረጋቸው። 40 በቆሬና በወገኑ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው። 41 በነጋውም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። 42 እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን አዩ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ። 43 ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት መጡ። 44 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 45 ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ። በግምባራቸውም ወደቁ። 46 ሙሴም አሮንን። ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል አለው። 47 አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው። 48 በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። 49 በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 50 አሮንም ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ።

ዘኍልቍ 17

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፥ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸው ከየአባቶቻቸው ቤት አሥራ ሁለት በትሮች፥ ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ። 3 አንድ በትርም ለአባቶቻቸው ቤት አለቃ ይሆናልና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። 4 እኔ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው። 5 እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ታቈጠቁጣለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ። 6 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ አለቆቻቸው ሁሉ አሥራ ሁለት በትሮች፥ እያንዳንዱም አለቃ በየአባቱ ቤት አንድ አንድ በትር፥ ሰጡት፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች። 7 ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው። 8 እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች። 9 ሙሴም በትሮችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፥ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን። የአሮንን በትር ወደ ምስክሩ ፊት መልስ፤ ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ እነርሱም እንዳይሞቱ ለሚያምፁብኝ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ አለው። 11 ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ። 12 የእስራኤልም ልጆች ሙሴን።እነሆ፥ እንሞታለን፥ እንጠፋለን፥ ሁላችንም እንጠፋለን። 13 የሚቀርብ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ የሚቀርብ፥ ይሞታል፤ በውኑ ሁላችን እንሞታለንን? ብለው ተናገሩት።

ዘኍልቍ 18

1 እግዚአብሔርም አሮንን አለው። አንተ ከአንተም ጋር ልጆችህና የአባቶችህ ቤት የመቅደስን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ የክህነታችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ። 2 ደግሞም የአባትህን የሌዊን ነገድ ወንድሞችህን ከአንተ ጋር አቅርብ፤ ከአንተም ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ያገልግሉህም፤ አንተ ግን ከአንተም ጋር ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት ትሆናላችሁ። 3 እነርሱም ትእዛዝህን የድንኳኑንም ሁሉ አገግሎት ይጠብቁ፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ፥ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር እንዳትሞቱ፥ እነርሱ ወደ መቅደሱ ዕቃና ወደ መሠዊያው አይቅረቡ። 4 ነገር ግን ከእናንተ ጋር በአንድነት ይሁኑ፥ ለድንኳኑም አገልግሎት ሁሉ የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁ፤ ሌላም ሰው ወደ እናንተ አይቅረብ። 5 እንደ ገና በእስራኤል ልጆች ላይ ቍጣ እንዳይሆንባቸው እናንተ መቅደሱንና መሠዊያውን ጠብቁ። 6 እኔም፥ እነሆ፥ ሌዋውያንን ወንድሞቻችሁን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያደርጉ ዘንድ ለእግዚአብሔር የተሰጡ ለእናንተ ስጦታ ናቸው። 7 አንተም ከአንተም ጋር ልጆችህ ለመሠዊያው ሥራ የሚሆነውን ሁሉ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የሚሆነውን ታደርጉ ዘንድ ክህነታችሁን ጠብቁ፥ አገልግሉም፤ ክህነቱን ለስጦታ አገልግሎት ሰጥቼአችኋለሁ፤ ሌላም ሰው ቢቀርብ ይገደል። 8 እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ። 9 በእሳት ከሚቀርበው ከተቀደሰው ይህ ለአንተ ይሆናል፤ ለእኔ የሚያመጡት መባቸው ሁሉ፥ የእህሉ ቍርባናቸው ሁሉ፥ የኃጢአታቸውም መስዋዕት ሁሉ፥ የበደላቸውም መሥዋዕት ሁሉ፥ ለአንተ ለልጆችህም የተቀደሰ ይሆናል። 10 በተቀደሰ ስፍራ ብላው፤ ወንዶች ሁሉ ይብሉት፤ የተቀደሰ ይሆንልሃል። 11 ይህም ለአንተ ነው፤ የእስራኤል ልጆች ለስጦታ ያቀረቡትን የማንሣትና የመወዝወዝ ቍርባን ሁሉ ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። 12 ለእግዚአብሔር ከሚሰጡት የፍሬ መጀመሪያ ከዘይትና ከወይን ከእህልም የተመረጠውን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ። 13 ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡት በምድራቸው ያለው ሁሉ የፍሬ መጀመሪያ ለአንተ ይሆናል፤ በቤትህ ውስጥ ንጹሕ የሆነ ሁሉ ይብላው። 14 በእስራኤል ዘንድ እርም የሆነው ሁሉ ለአንተ ይሆናል። 15 ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን በኵራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ፥ ያልነጻውንም እንስሳ በኵራት ትቤዠዋለህ። 16 ከአንድ ወር ጀምሮ የምትቤዠውን እንደ ግምትህ ትቤዠዋለህ፤ ግምቱም እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን አምስት ሰቅል ይሆናል፤ እርሱም ሀያ አቦሊ ነው። 17 ነገር ግን የላም በኵራት ወይም የበግ በኵራት ወይም የፍየል በኵራት አትቤዥም፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ ትረጨዋለህ፥ ስባቸውንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ታቃጥለዋለህ። 18 ሥጋቸውም ለአንተ ይሆናል፤ እንደ መወዝወዝ ፍርምባ እንደ ቀኙም ወርች ለአንተ ይሆናል። 19 የእስራኤል ልጆች ከተቀደሰው ነገር ሁሉ አንሥተው ለእግዚአብሔር ያቀረቡትን ለአንተ ከአንተም ጋር ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ለአንተ ከአንተም ጋር ለዘርህ የጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም ነው። 20 እግዚአብሔርም አሮንን አለው። በምድራቸው ርስት በመካከላቸውም ድርሻ አይሆንልህም፤ በእስራኤል ልጆች መካከል ድርሻህና ርስትህ እኔ ነኝ። 21 ለሌዊም ልጆች፥ እነሆ፥ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ስለሚያገለግሉ፥ የእስራኤልን ልጆች አሥራት ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ። 22 ከዚህም በኋላ ኃጢአትን እንዳይሸከሙ እንዳይሞቱም፥ የእስራኤል ልጆች ወደ መገናኛው ድንኳን አይቅረቡ። 23 ሌዋውያን ግን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ይሥሩ፥ እነርሱም ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም። 24 ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን የሚያቀርቡትን የእስራኤልን ልጆች አሥራት ለሌዋውያን ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህ። በእስራኤል ልጆች መካከል ርስት አይወርሱም አልኋቸው። 25 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 26 ለሌዋውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ልጆች ለእናንተ ርስት አድርጌ የሰጠኋችሁን አሥራት በተቀበላችሁ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የአሥራት አሥራት ታቀርባላችሁ። 27 የማንሣት ቍርባናችሁም እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ይቈጠርላችኋል። 28 እንዲሁ እናንተ ደግሞ ከእስራኤል ልጆች ከምትቀበሉት አሥራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም የማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአሮን ትሰጣላችሁ። 29 ከምትቀበሉት ስጦታ ሁሉ፥ ከተመረጠው ከተቀደሰውም ድርሻ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የማንሣት ቍርባን ሁሉ ታቀርባላችሁ። 30 ስለዚህ ትላቸዋለህ። ከእርሱ የተመረጠውን ባነሣችሁ ጊዜ እንደ አውድማው እህልና እንደ ወይን መጭመቂያው ፍሬ ለሌዋውያን ይቈጠራል። 31 እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የማገልገላችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 32 የተመረጠውንም ከእርሱ ባነሣችሁ ጊዜ ስለ እርሱ ኃጢአትን አትሸከሙም፤ እንዳትሞቱም የእስራኤል ልጆች የቀደሱትን አታረክሱም።

ዘኍልቍ 19

1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2 እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። 3 እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል። 4 ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል። 5 ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል። 6 ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል። 7 ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል። 8 ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል። 9 ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው። 10 የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል። 11 የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል፤ 12 በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም። 13 የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው። 14 ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል። 15 መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው። 16 በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል። 17 ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል። 18 ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤ 19 ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ ባሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል። 20 ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው። 21 ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 22 ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

ዘኍልቍ 20

1 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች። 2 ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ። 3 ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ! 4 እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ? 5 ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም። 6 ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 8 በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ። 9 ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። 10 ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው። 11 ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ። 12 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው። 13 የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው። 14 ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ። ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል። ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ 15 አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤ 16 ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። 17 እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም። 18 ኤዶምያስም። በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው። 19 የእስራኤልም ልጆች። በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት። 20 እርሱም። አታልፍም አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ። 21 ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ። 22 ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ። 23 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 24 አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዐመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም። 25 አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤ 26 ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት። 27 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ። 28 ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ። 29 ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ።

ዘኍልቍ 21

1 በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። 2 እስራኤልም ለእግዚአብሔር። እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ። 3 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት። 4 ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ። 5 ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። 6 እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። 7 ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት። 8 ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። 9 ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። 10 የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ። 11 ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። 12 ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13 ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአሮኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አሮኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። 14 ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ። ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥ 15 ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ የሸለቆች ፈሳሽ። 16 ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን። ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው። 17 በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ። አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተ ዘምሩለት፤ 18 በበትረ መንግሥት በበትራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥ አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ። 19 ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥ 20 ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ። 21 22 እስራኤልም። በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ። 23 ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። 24 እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ። 25 እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። 26 ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር። 27 ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ። ወደ ሐሴቦን ኑ፤ የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤ 28 እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤ 29 ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ። 30 ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው። 31 እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ። 32 ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ። 33 ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። 34 እግዚአብሔርም ሙሴን። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው። 35 እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።

ዘኍልቍ 22

1 የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። 2 የሴፎር ልጅ ባላቅ እስራኤል በአሞራውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ አየ። 3 ብዙም ነበረና ሞዓብ ከሕዝቡ እጅግ ፈራ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ሞዓብ ደነገጠ። 4 ሞዓብም የምድያምን ሽማግሌዎች። በሬ የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል አላቸው። በዚያን ጊዜም የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበረ። 56 በወንዙ አጠገብ ባለችው በሕዝቡ ልጆች ምድር በፋቱራ ወደ ተቀመጠው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ አለ፤ እነሆም፥ የምድሩን ሁሉ ፊት ሸፈነ፥ በአቅራቢያችንም ተቀምጦአል፤ አሁንም ይህ ሕዝብ ከእኔ ይበልጣልና ልወጋቸውና ከምድሪቱ ላሳድዳቸው እችል እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ና ርገምልኝ፤ አንተ የመረቅኸው ምሩቅ የረገምኸውም ርጉም እንደ ሆነ አውቃለሁና ብሎ ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞቹን ላከ። 7 የሞዓብ ሽማግሌዎችና የምድያም ሽማግሌዎችም የምዋርቱን ዋጋ በእጃቸው ይዘው ሄዱ፤ ወደ በለዓምም መጡ፥ የባላቅንም ቃል ነገሩት። 8 እርሱም። ዛሬ ሌሊት በዚህ እደሩ፥ እግዚአብሔርም እንደሚነግረኝ እመልስላችኋለሁ አላቸው፤ የሞዓብም አለቆች በበለዓም ዘንድ ተቀመጡ። 9 እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ። እነዚህ በአንተ ዘንድ ያሉ ሰዎች እነማን ናቸው? አለው። 10 11 በለዓምም እግዚአብሔርን። የሞዓብ ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ። እነሆ፥ ከግብፅ የወጣ ሕዝብ የምድርን ፊት ሸፈነ፥ አሁንም ና እርሱንም ርገምልኝ፤ ምናልባት እወጋው አሳድደውም ዘንድ እችል እንደ ሆነ ብሎ ወደ እኔ ልኮአል አለው። 12 እግዚአብሔርም በለዓምን። ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤ የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትረግምም አለው። 13 በለዓምም ሲነጋ ተነሥቶ የባላቅን አለቆች። ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀደምና ወደ ምድራችሁ ሂዱ አላቸው። 14 የሞዓብ አለቆች ተነሡ፥ ወደ ባላቅም መጥተው። በለዓም ከእኛ ጋር ይመጣ ዘንድ አልፈቀደም አሉት። 15 ባላቅም ደግሞ ከፊተኞች የበዙና የከበሩ ሌሎችን አለቆች ሰደደ። 16 17 ወደ በለዓምም መጥተው። የሴፎር ልጅ ባላቅ። ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና እባክህ፥ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ምንም አይከልክልህ፤ እባክህ፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ አለ ብለው ነገሩት። 18 በለዓምም መልሶ የባላቅን ባሪያዎች። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ወርቅና ብር ቢሰጠኝ፥ በትንሹ ወይም በትልቁ ቢሆን የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ 19 አሁንም እግዚአብሔር ደግሞ የሚነግረኝን አውቅ ዘንድ፥ እባካችሁ፥ ዛሬ ሌሊት ደግሞ በዚህ እደሩ አላቸው። 20 እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ። ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። 21 በለዓምም ሲነጋ ተነሣ፥ አህያይቱንም ጭኖ ከሞዓብ አለቆች ጋር ሄደ። 22 እርሱም ስለ ሄደ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ሊቋቋመው በመንገድ ላይ ቆመ። እርሱም በአህያይቱ ላይ፥ ሁለቱም ሎሌዎቹ ከእርሱ ጋር ነበሩ። 23 አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየች፤ ከመንገዱም ፈቀቅ ብላ ወደ እርሻው ውስጥ ገባች፤ በለዓምም ወደ መንገድ ይመልሳት ዘንድ አህያይቱን መታት። 24 የእግዚአብሔርም መልአክ ከወይኑ ቦታዎች መካከል በወዲያና በወዲህ ወገን ግንብ በነበረበት በጠባብ መንገድ ላይ ቆመ። 25 አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ወደ ቅጥሩ ተጠጋች፥ የበለዓምንም እግር ከቅጥሩ ጋር አጣበቀች፤ እርሱም ደግሞ መታት። 26 የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ፊት ሄደ፥ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። 27 አህያይቱም የእግዚአብሔርን መልአክ አየች፥ ከበለዓምም በታች ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጣ፥ አህያይቱንም በበትሩ ደበደባት። 28 እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ፥ በለዓምንም። ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው? አለችው። 29 በለዓምም አህያይቱን። ስላላገጥሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር አላት። 30 አህያይቱም በለዓምን። ከብዙ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ እንዲህ አደርግ ዘንድ ልማዴ ነበረን? አለችው። እርሱም። እንዲህ አላደረግሽብኝም አላት። 31 እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ፤ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። 32 የእግዚአብሔርም መልአክ። አህያህን ሦስት ጊዜ ለምን መታህ? እነሆ፥ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ነውና እቋቋምህ ዘንድ ወጥቼአለሁ፤ 33 አህያይቱም አይታኝ ከፊቴ ሦስት ጊዜ ፈቀቅ አለች፤ ከፊቴስ ፈቀቅ ባላለች በእውነት አሁን አንተን በገደልሁህ፥ እርስዋንም ባዳንኋት ነበር አለው። 34 በለዓምም የእግዚአብሔርን መልአክ። በድያለሁ፤ አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህም አሁን አትወድድ እንደ ሆነ እመለሳለሁ አለው። 35 የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን። ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። 36 ባላቅም በለዓም እንደ መጣ በሰማ ጊዜ በአርኖን ዳር ዳርቻ በመጨረሻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኘው ወጣ። 37 ባላቅም በለዓምን። በውኑ አንተን ለመጥራት አልላክሁብህምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? በውኑ አንተን ለማክበር እኔ አልችልምን? አለው። 38 በለዓምም ባላቅን። እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ በውኑ አሁን አንዳችን ነገር እናገር ዘንድ እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ አለው። 39 በለዓምም ከባላቅ ጋር ሄደ፥ ወደ ቂርያት ሐጾትም መጡ። 40 ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ከእርሱም ጋር ወዳሉት አለቆች ላከ። 41 በነጋውም ባላቅ በለዓምን ይዞ ወደ በኣል ኮረብታ መስገጃ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን ዳርቻ አየ።

ዘኍልቍ 23

1 በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው። 2 ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ። 3 በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ። 4 እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው። 5 እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው። 6 ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር። 7 ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ። 8 እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? 9 በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም። 10 የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን። 11 ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው። 12 እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው። 13 ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው። 14 ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ። 15 ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው። 16 እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው። 17 ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው። 18 ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ 19 ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን? 20 እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም። 21 በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ። 22 እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው። 23 በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል። 24 እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም። 25 ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው። 26 በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው። 27 ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው። 28 ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው። 29 በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው። 30 ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።

ዘኍልቍ 24

1 በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና። 2 በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። 3 ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ 4 የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል። 5 ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ! 6 እንደ ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬት በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል። 7 ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል። 8 እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል። 9 እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተገመ ይሁን። 10 የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን። ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ 11 እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው። 12 13 በለዓምም ባላቅን አለው። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን? 14 አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ። 15 ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ 16 የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል። 17 አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል። 18 ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል። 19 ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል። 20 አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል። 21 ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤ 22 ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል። 23 ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ! ማን በሕይወት ይኖራል? 24 ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል። 25 በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ።

ዘኍልቍ 25

1 እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር። 2 ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ። 3 እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን። የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው። 5 ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች። እናንተ ሁሉ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው። 6 እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ምድያማዊቱን አንዲቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት፤ እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያለቅሱ ነበር። 7 የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤ 8 ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ። 9 በመቅሠፍትም የሞተው ሀያ አራት ሺህ ነበረ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 11 የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም። 12 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ። 13 ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል። 14 ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ። 15 የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ። 16 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 17 18 በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና ምድያማውያንን አስጨንቁአቸው ግደሉአቸውም።

ዘኍልቍ 26

1 እንዲህም ሆነ፤ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና የካህኑን የአሮን ልጅ አልዓዛርን። 2 ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ በእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቍጠሩ ብሎ ተናገራቸው። 3 ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ። 4 እግዚአብሔር ሙሴን ከግብፅም ምድር የወጡትን የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዛቸው፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝቡን ቍጠሩ ብለው ተናገሩአቸው። 5 የእስራኤል በኵር ሮቤል፤ የሮቤል ልጆች፤ ከሄኖኅ የሄኖኀውያን ወገን፥ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን፥ 6 ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፥ ከከርሚ የከርማውያን ወገን። 7 እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 8 የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ። 9 የኤልያብም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን፤ እነዚህ ዳታንና አቤሮን ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ከቆሬ ወገን ጋር በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን ተጣሉ፤ 10 ያም ወገን በሞተ ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ በዚያም ጊዜ እሳቲቱ ሁለት መቶ አምሳውን ሰዎች አቃጠለቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ። 11 የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም። 12 የስምዖን ልጆች በየወገናቸው፤ ከነሙኤል የነሙኤላውያን ወገን፥ ከያሚን የያሚናውያን ወገን፥ ከያኪን የያኪናውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን፥ 13 ከሳኡል የሳኡላውያን ወገን። 14 እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 15 የጋድ ልጆች በየወገናቸው፤ ከጽፎን የጽፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥ 16 ከሹኒ የሹናውያን ወገን፥ ከኤስናን የኤስናናውያን ወገን፥ ከዔሪ የዔራውያን ወገን፥ 17 ከአሮድ የአሮዳውያን ወገን፥ ከአርኤሊ የአርኤላውያን ወገን። 18 እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 19 የይሁዳ ልጆች ዔርና አውናን፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ። 20 የይሁዳም ልጆች በየወገናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን። 21 የፋሬስም ልጆች፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከሐሙል የሐሙላውያን ወገን። 22 እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 23 የይሳኮር ልጆች በየወገናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉዋ የፉዋውያን ወገን፥ 24 ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሺምሮን የሺምሮናውያን ወገን። 25 እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ አራት ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 26 የዛብሎን ወገኖች በየወገናቸው፤ ከሴሬድ የሴሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎን የኤሎናውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን። 27 እነዚህ የዛብሎናውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስድሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 28 የዮሴፍ ልጆች በየወገናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም። 29 የምናሴ ልጆች፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገልዓዳውያን ወገን። 30 የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኢዔዝር የኢዔዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥ 31 ከአሥሪኤል የአሥሪኤላውያን ወገን፥ 32 ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ ከሸሚዳ የሸሚዳውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን። 33 የኦፌርም ልጅ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 34 እነዚህ የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 35 በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን፥ ከቤኬር የቤኬራውያን ወገን፥ ከታሐን የታሐናውያን ወገን። 36 እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን የዔዴናውያን ወገን። ከዔዴን የዔዴናውያና ወገን። 37 እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው። 38 የብንያም ልጆች በየወገናቸው፤ ከቤላ የቤላውያን ወገን፥ ከአስቤል የአስቤላውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥ 39 ከሑፋም የሑፋማውያን ወገን። 40 የቤላም ልጆች፤ አርድና ናዕማን፤ ከአርድ የአርዳውያን ወገን፥ ከናዕማን የናዕማናውያን ወገን። 41 በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 42 በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዔ የሰምዔያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 43 የሰምዔያውያን ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ እንደ ተቈጠሩ ስድሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 44 የአሴር ልጆች በየወገናቸው፤ ከዪምና የዪምናውያን ወገን፥ ከየሱዋ የየሱዋውያን ወገን፥ ከበሪዓ የበሪዓውያን ወገን። 45 ከበሪዓ ልጆች፤ ከሔቤር የሔቤራውያን ወገን፥ ከመልኪኤል የመልኪኤላውያን ወገን። 46 የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሤራሕ ነበረ። 47 እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 48 የንፍታሌም ልጆች በየወገናቸው፤ ከያሕጽኤል የያሕጽኤላውያን ወገን፥ ከጉኒ የጉናውያን ወገን፥ 49 ከዬጽር የዬጽራውያን ወገን፥ ከሺሌም የሺሌማውያን ወገን። 50 በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 51 ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 52 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 53 ለእነዚህ በየስማቸው ቍጥር ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፈላለች። 54 ለብዙዎቹ እንደ ብዛታቸው፥ ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል። 55 ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ስም ይወርሳሉ። 56 በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፈላለች። 57 ከሌዋውያንም በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን። 58 እነዚህ የሌዊ ወገኖች ናቸው፤ የሊብናውያን ወገን፥ የኬብሮናውያን ወገን፥ የሞሖላውያን ወገን፥ የሙሳውያን ወገን፥ የቆሬያውያን ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ። 59 የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። እርስዋ በግብፅ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት። 60 ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ተወለዱለት። 61 በእግዚአብሔርም ፊት ሌላ እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ። 62 ከአንድ ወርም ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉ ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሀያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 63 በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጥሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው። 64 ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም። 65 እግዚአብሔር ስለ እነርሱ። በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም።

ዘኍልቍ 27

1 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 2 በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው። 3 አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። 4 ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን አሉ። 5 ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ። 6 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 7 የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ። 8 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤ 9 ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ፤ 10 ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ፤ 11 የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ስጡ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ 13 ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። 14 እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው። 15 ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 16 17 የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው። 18 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ 19 በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። 20 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። 21 በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ። 22 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ 23 እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።

ዘኍልቍ 28

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። መብሌን፥ ለእኔ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የተደረገውን ቍርባኔን፥ መባዬን በየጊዜው ታቀርቡልኝ ዘንድ ጠብቁ። 3 እንዲህም በላቸው። በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ። 4 አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤ 5 ለእህልም ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ታቀርባለህ። 6 በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የቀረበ በሲና ተራራ የተሠራ ለዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 7 የመጠጡ ቍርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ነው፤ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ለመጠጥ ቍርባን መጠጥ ታፈስሳለህ። 8 ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን በማለዳ እንዳቀረብህ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ታቀርበዋለህ። 9 በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቍርባን ታቀርባላችሁ። 10 በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው። 11 በወሩም መባቻ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 12 ለእያንዳንዱም ወይፈን ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለአውራው በግም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ 13 ለእያንዳንዱም ጠቦት ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ታቀርባላችሁ። 14 የመጠጥ ቍርባናቸውም ለአንድ ወይፈን የኢን ግማሽ፥ ለአውራው በግም የኢን ሢሶ፥ ለአንዱም ጠቦት የኢን አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ይሆናል፤ ይህ ለዓመቱ የወር መባቻ ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 15 ለእግዚአብሔርም ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል። 16 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። 17 ከዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። 18 በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል፤ በእርሱም የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 19 በእሳትም የተደረገውን ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑላችሁ። 20 የእህል ቍርባናቸውንም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራውም በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 21 ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። 22 ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 23 ማልዶ ከሚቀርበው በዘወትር ከሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ እነዚህን ታቀርባላችሁ። 24 ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚደረገውን የቍርባኑን መብል ሰባት ቀን በየዕለቱ እንዲሁ ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል። 25 በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 26 ደግሞ በበኵራት ቀን ከሰባቱ ሱባዔ በዓላችሁ አዲሱን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ባቀረባችሁ ጊዜ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 27 ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 28 ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንዱም አውራ በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 29 ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። 30 ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 31 በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ሌላ እነርሱንና የመጠጥ ቍርባናቸውን ታቀርባላችሁ፤ ነውርም የሌለባቸው ይሁኑ።

ዘኍልቍ 29

1 በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው። 2 ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 3 ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 4 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ። 5 ማስተስረያም የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ። 6 በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው። 7 ከዚህም ከሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቁት፤ ከሥራ ሁሉ ምንም አታድርጉ። 8 ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑ። 9 ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 10 ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥ 11 ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጥ ቍርባናቸውም ሌላ አቅርቡት። 12 ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ። 13 ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ። 14 ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥ 15 ለአሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥ 16 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 17 በሁለተኛውም ቀን አሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥ 18 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥ 19 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየልን ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባናቸው ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 20 በሦስተኛውም ቀን አሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 21 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥ 22 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 23 በአራተኛውም ቀን አሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 24 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ፥ 25 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 26 በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 27 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥ 28 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 29 በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 30 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥ 31 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 32 በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ 33 ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥ 34 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ። 35 በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት። 36 ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 37 የእህል ቍርባናቸውና የመጠጥ ቍርባናቸው ለወይፈኑ ለአውራውም በግ ለጠቦቶቹም እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ይሆናሉ። 38 ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው። 39 እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቍርባን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 40 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።

ዘኍልቍ 30

1 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። 2 ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር፤ ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ። 3 ሴትም ደግሞ ለእግዚአብሔር ስእለት ብትሳል፥ እርስዋም በአባትዋ ቤት ሳለች በብላቴንነትዋ ጊዜ ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 4 አባትዋም ራስዋን ያሰረችበትን መሐላ ስእለትዋንም ቢሰማ፥ አባትዋም ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ሁሉ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 5 አባትዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላዋ አይጸኑም፤ አባትዋ ከልክሎአታልና እግዚአብሔር ይቅር ይላታል። 6 በተሳለችም ጊዜ ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበት ነገር ከአፍዋ በወጣ ጊዜ ባል ያገባች ብትሆን፥ 7 ባልዋም ቢሰማ፥ በሰማበትም ቀን ዝም ቢላት፥ ስእለትዋ ይጸናል፥ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸናል። 8 ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ቢከለክላት፥ በእርስዋ ላይ ያለውን ስእለትዋን ራስዋንም በመሐላ ያሰረችበትን የአፍዋን ነገር ከንቱ ያደርገዋል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። 9 ባልዋ የሞተባት ወይም የተፋታች ግን ስእለትዋ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ይጸኑባታል። 10 ሴትም በባልዋ ቤት ሳለች ብትሳል፥ ወይም ራስዋን በመሐላ ብታስር፥ 11 ባልዋም ሰምቶ ዝም ቢላት ባይከለክላትም፥ ስእለትዋ ሁሉ ራስዋንም ያሰረችበት መሐላ ሁሉ ይጸናል። 12 ባልዋ ግን በሰማበት ቀን ከንቱ ቢያደርገው፥ ስለ ስእለትዋ ወይም ራስዋን ስላሰረችበት መሐላ ከአፍዋ የወጣው ነገር አይጸናም፤ ባልዋ ከንቱ አድርጎታል፤ እግዚአብሔርም ይቅር ይላታል። 13 ስእለትዋን ሁሉ ነፍስዋንም የሚያዋርደውን መሐላ ሁሉ ባልዋ ያጸናዋል፥ ባልዋም ከንቱ ያደርገዋል። 14 ባልዋ ግን በየዕለቱ ዝም ቢላት፥ ስእለትዋን ሁሉ በእርስዋም ላይ ያለውን መሐላ ሁሉ አጽንቶታል፤ በሰማበት ቀን ዝም ብሎአታልና አጽንቶታል። 15 ከሰማው በኋላ ግን ከንቱ ቢያደርገው ኃጢአትዋን ይሸከማል። 16 እርስዋ በብላቴንነትዋ ጊዜ በአባትዋ ቤት ሳለች በአባትና በልጂቱ መካከል፥ ወይም በባልና በሚስት መካከል ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው ሥርዓት ይህ ነው።

ዘኍልቍ 31

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ። 3 ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤ 4 ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው። 5 ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ። 6 ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ። 8 ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት። 9 የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ። 10 የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። 11 የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ። 12 የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ። 13 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ። 14 ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ። 15 ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን? 16 እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ። 17 አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ። 18 ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው። 19 ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ። 20 ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ። 21 ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤ 22 ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥ 23 አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ። 24 በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ። 25 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 26 አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ። 27 ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል። 28 ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ። 29 ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው። 30 ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ። 31 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 32 ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ 33 34 ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስድሳ አንድ ሺህ አህዮች፥ 35 ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ። 36 በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥ 37 ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ። 38 በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ። 39 አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ። 40 ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ። 41 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው። 42 ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥ 43 የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ 44 ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥ 45 ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥ 46 አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ። 47 ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ። 48 በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥ 49 ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም። 50 ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት። 51 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ። 52 ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ። 53 ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ። 54 ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።

ዘኍልቍ 32

1 የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥ 2 የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው። 34 እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን። 5 እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን። 6 ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው። ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? 7 እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ? 8 ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ። 9 ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ። 10 በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፥ 11 12 እርሱም። በእውነት እግዚአብሔርን ፈጽመው ከተከተሉ ከእነዚህ ከቄኔዛዊው ከዮፎኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፥ ከግብፅ የወጡት ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁበትን ምድር አያዩም ብሎ ማለ። 13 የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው። 14 እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል። 15 እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ። 16 ወደ እርሱም ቀርበው አሉት። በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤ 17 እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ። 18 የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤ 19 ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም። 20 ሙሴም አላቸው። ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥ 21 እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ 22 ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች። 23 እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ። 24 ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ። 25 የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት። እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። 26 ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ 27 እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን። 28 ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ። 29 ሙሴም። የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። 30 ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው። 31 የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው። እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። 32 ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት። 33 ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው። 34 የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥ 35 ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥ 36 ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። 37 የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥ 38 ቂርያታይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው። 39 የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ። 40 ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ። 41 የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው። 42 ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።

ዘኍልቍ 33

1 የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ። 2 ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ። 3 በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ። 4 በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው። 5 የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ። 6 ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ። 7 ከኤታምም ተጕዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ። 8 ከፊሀሒሮትም ተጕዘው በባሕሩ ውስጥ ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ። 9 ከማራም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ። 10 ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ። 11 ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ። 12 ከሲን ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ። 13 ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ። 14 ከኤሉስም ተጕዘው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። 15 ከራፊዲምም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 16 ከሲናም ምድረ በዳ ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ። 17 ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በሐጼሮት ሰፈሩ። 18 ከሐጼሮትም ተጕዘው በሪትማ ሰፈሩ። 19 ከሪትማም ተጕዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ። 20 ከሬሞን ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ። 21 ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ። 22 ከሪሳም ተጕዘው በቀሄላታ ሰፈሩ። 23 ከቀሄላታም ተጕዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ። 24 ከሻፍር ተራራም ተጕዘው በሐራዳ ሰፈሩ። 25 ከሐራዳም ተጕዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ። 26 ከመቅሄሎትም ተጕዘው በታሐት ሰፈሩ። 27 ከታሐትም ተጕዘው በታራ ሰፈሩ። 28 ከታራም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ። 29 ከሚትቃም ተጕዘው በሐሽሞና ሰፈሩ። 30 ከሐሽሞናም ተጕዘው በሞሴሮት ሰፈሩ። 31 ከሞሴሮትም ተጕዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ። 32 ከብኔያዕቃንም ተጕዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ። 33 ከሖርሃጊድጋድም ተጕዘው በዮጥባታ ሰፈሩ። 34 ከዮጥባታም ተጕዘው በዔብሮና ሰፈሩ። 35 ከዔብሮናም ተጕዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ። 36 ከዔጽዮንጋብርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት። 37 ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ። 38 ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። 39 አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር። 40 በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ። 41 እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ። 42 ከሴልሞናም ተጕዘው በፉኖን ሰፈሩ። 43 ከፉኖንም ተጕዘው በኦቦት ሰፈሩ። 44 ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ። 45 ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። 46 ከዲቦንጋድም ተጕዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። 47 ከዓልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። 48 ከዓብሪምም ተራሮች ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። 49 በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ። 50 እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 51 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ 52 የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ 53 ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም። 54 ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ። 55 የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። 56 እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።

ዘኍልቍ 34

1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በዳርቻዋ ያለች የከነዓን ምድር፥ 3 ይህች ናት፤ የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ በኩል ይሆናል፤ የደቡቡም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤ 4 ዳርቻችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ያልፋል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤ 5 ዳርቻውም ከዓጽሞን ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፥ መውጫውም በባሕሩ በኩል ይሆናል። 6 ለምዕራብም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ዳርቻችሁ ይሆናል። 7 የሰሜንም ዳርቻችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ ምልክት ታመለክታላችሁ፤ 8 ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ ምልክት ታመለክታላችሁ የዳርቻውም መውጫ በጽዳድ ይሆናል፤ 9 ዳርቻውም ወደ ዚፍሮን ያልፋል እስከ ሐጸርዔናንም ድረስ ይወጣል፤ ይህ የሰሜን ዳርቻችሁ ይሆናል። 10 የምሥራቁንም ዳርቻችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ ምልክት ታመለክታላችሁ፤ 11 ዳርቻውም ከሴፋማ በዓይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤ 12 ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት። 13 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። እግዚአብሔር ለዘጠኝ ነገድ ተኩል ይሰጡአቸው ዘንድ ያዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤ 14 የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል። 15 እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 17 ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ። 18 ምድሪቱንም ርስት አድርገው ይከፍሉ ዘንድ ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ። 19 የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥ 20 ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥ 21 ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥ 22 ከዳን ልጆች ንገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥ 23 ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥ 24 ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥ 25 ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥ 26 ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥ 27 ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥ 28 ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል። 29 እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።

ዘኍልቍ 35

1 እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰምርያ ለሌዋውያን ስጡ። 3 እነርሱም በከተሞቹ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ መሰምርያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም ለእነርሱም ላለው ሁሉ ይሁን። 4 ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰምርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን። 5 ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰምርያ ይሆንላቸዋል። 6 ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ። 7 ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰምርያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ። 8 ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 10 ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ 11 በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ። 12 ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 13 የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 14 በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። 15 በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። 16 በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 17 ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 18 ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 19 ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው። 20 እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 21 ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። 22 ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 23 ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥ 24 ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤ 25 ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። 26 ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥ 27 ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ 28 ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። 29 እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። 30 ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። 31 ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 32 ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። 33 ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። 34 እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።

ዘኍልቍ 36

1 ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤ 2 አሉም። ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ። 3 ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል። 4 ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይጐድላል። 5 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ። 6 እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ። 7 እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ። 8 ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ። 9 እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ። 11 የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። 12 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና። 13 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው።

ዘዳግም 1

1 በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። 2 በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የአሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። 34 በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ፥ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። 5 በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ ይገልጥ ጀመር። 6 አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን። በዚህ ተራራ የተቀመጣችሁት በቃ፤ 7 ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር ወደ ድንበሮቹም ሁሉ፥ በዓረባም በደጋውም በቈላውም በደቡብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። 8 እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ። 9 በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ። እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ 10 አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። 11 የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቁጥር ላይ እልፍ አእላፋት ይጨምር፥ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ። 12 እኔ ብቻዬን ድካምችሁን ሸክማችሁንም ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? 13 ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮዎችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ። 14 እናንተም። እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው ብላችሁ መለሳችሁልኝ። 15 ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች መረጥሁ፥ በእናንተም ላይ አለቆች የሻለቆችም የመቶ አለቆችም የአምሳ አለቆችም የአሥር አለቆችም ገዦችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። 16 በዚያን ጊዜም። የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። 17 በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፤ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፤ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፤ ከነገርም አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ ብዬ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። 18 በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ። 19 ከኮሬብም ተጓዝን፥ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። 20 እኔም። አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፤ 21 እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊትህ አድርጎአል፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም አልኋችሁ። 22 እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ። ምድሪቱን እንዲጎበኙልንና እንወጣበት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንስደድ አላችሁኝ። 23 ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም አሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። 24 ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ጎበኙአት። 25 ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ። አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት ብለውም አወሩልን። 26 በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤ 27 በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ። እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን አጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። 28 ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት። 29 እኔም አልኋችሁ። አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤ 30 በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ 31 ወደዚህም ስፋራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል። 32 33 ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም። 34 እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣ። 35 ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከእነዚህ ሰዎች ከዚህ ክፉ ትውልድ ማንም አያይም፥ 36 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር እርሱ ግን ያያታል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ ብሎ ማለ። 37 እግዚአብሔርም ደግሞ በእናንተ ምክንያት በእኔ ተቆጣ እንዲህም አለ። አንተ ደግሞ ወደዚያ አትገባም፤ 38 በፊትህ የሚቆም የነዌ ልጅ ኢያሱ እርሱ ወደዚያ ይገባል፤ እርሱ ለእስራኤል ምድሪቱን ያወርሳልና አደፋፍረው። 39 ደግሞ። ለምርኮ ይሆናሉ ያላችኋቸው ሕፃናቶቻችሁ፥ ዛሬም መልካሙን ከክፉ መለየት የማይችሉ ልጆቻችሁ፥ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፥ ምድሪቱንም ለእነርሱ እስጣለሁ ይወርሱአታልም። 40 እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ። 41 እናንተም። እግዚአብሔርን በድለናል፤ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን ሁሉ እንወጣለን፥ እንዋጋማለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር መውጣትን አቀለላችሁት። 42 እግዚአብሔርም። እኔ በእናንተ መካከል አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው አለኝ። እኔም ተናገርኋችሁ፤ 43 እናንተ ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ አልሰማችሁም፤ በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ። 44 በዚያም በተራራማው አገር ይኖሩ የነበር አሞራውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፥ ንብ እንደምታሳድድም አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር መቱአችሁ። 45 ተመልሳችሁም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን አልሰማም፥ ወደ እናንተም አላዳመጠም። 46 እንደ ተቀመጣችሁበትም ዘመን መጠን በቃዴስ ብዙ ቀን ተቀመጣችሁ።

ዘዳግም 2

1 እግዚአብሔርም እንዳለኝ ተመልሰን በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄድን፤ የሴይርንም ተራራ ብዙ ቀን ዞርን። 2 እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። 3 ይህን ተራራ መዞር ይበቃችኋል፤ ተመልሳችሁ ወደ ሰሜን ሂዱ። 4 ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። በሴይር ላይ በተቀመጡት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ልጆች አገር ታልፋላችሁ፥ እነርሱም ይፈሩአችኋል፤ እንግዲህ እጅግ ተጠንቀቁ። 5 የሴይርን ተራራ ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ እኔ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታህል እንኳ አልሰጣችሁምና አትጣሉአቸው። 6 ከእነርሱ በገንዘብ ምግብ ገዝታችሁ ትበላላችሁ፤ ውኃም ደግሞ በገንዘብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ። ብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ። 7 አምላክህ እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና፤ በዚህ በታላቅ ምድረ በዳ መሄድህን አውቆአል፤ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነበረ፥ አንዳችም አላጣህም። 8 በሴይርም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችን ከዔሳው ልጆች በዓረባ መንገድ ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር አለፍን። ተመልሰንም በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ አለፍን። 9 እግዚአብሔርም አለኝ። እኔ ዔርን ለሎጥ ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከምድሩ ርስት አልሰጣችሁምና ሞዓብን አትጣላ በሰልፍም አትውጋቸው። 10 አስቀድሞ ታላቅና ብዙ ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች በቁመት የረዘሙ ኤሚማውያን በዚያ ይቀመጡ ነበር። 11 እነርሱም ደግሞ እንደ ዔናቅ ልጆች ራፋይም ይባሉ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚም ይሉአቸዋል። 12 ሖራውያንም ደግሞ አስቀድሞ በሴይር ላይ ተቀምጠው ነበር፥ የዔሳው ልጆች ግን አሳደዱአቸው፤ እግዚአብሔርም በሰጠው በርስቱ ምድር እስራኤል እንዳደረገ፥ ከፊታቸው አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ። 13 እግዚአብሔርም። ተነሡ የዘሬድንም ፈፋ ተሻገሩ አለ። 14 የዘሬድንም ፈፋ ተሻገርን። የዘሬድንም ፈፋ እስከ ተሻገርንበት ድረስ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለባቸው የሰልፈኞች ትውልድ ሁሉ ከሰፈሩ መካከል እስከ ጠፉ ድረስ፥ ከቃዴስ በርኔ የተጓዝንበት ዘመን ሠላሳ ስምንት ዓመት ሆነ። 15 ከሰፈርም መካከል ተቈርጠው እስኪጠፉ ድረስ የእግዚአብሔር እጅ በላያቸው ነበረ። 16 እንዲህም ሆነ፤ ሰልፈኞቹ ከጠፉ ከሕዝቡም መካከል ከሞቱ በኋላ፥ 17 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። 18 አንተ ዛሬ የሞዓብን ዳርቻ ዔርን ታልፋለህ፤ 19 ለሎጥም ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከአሞን ልጆች ምድር ርስት አልሰጥህምና በአሞን ልጆች አቅራቢያ ስትደርስ አትጣላቸው አትውጋቸውም። 20 ያም ደግሞ የራፋይም ምድር ተብሎ ተቆጠረ፤ ራፋይምም አስቀድሞ በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሩአቸዋል። 21 ታላቅና ብዙም ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች ቁመታቸው የረዘመ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከፊታቸው አጠፋቸው፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው ተቀመጡ። 22 ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍቶ በሴይር ለተቀመጡት ለዔሳው ልጆች እንዳደረገ እንዲሁ ለእነርሱ አደረገ፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተቀመጡ። 23 እስከ ጋዛም ድረስ በመንደሮች ተቀምጠው የነበሩትን ኤዋውያንን ከከፍቶር የወጡ ከፍቶራውያን አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ። 24 ደግሞም አለ። ተነሥታችሁ ሂዱ፥ የአርኖንንም ሸለቆ ተሻገሩ፤ እነሆ፥ አሞራዊውን የሐሴቦንን ንጉሥ ሴዎንን ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፤ እርስዋን በመውረስ ጀምር፥ ከእርሱም ጋር ተዋጋ። 25 ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስደንገጥህንና ማስፈራትህን እሰድድ ዘንድ ዛሬ እጀምራለሁ፤ ወሬህን በሰሙ ጊዜ በፊትህ ይንቀጠቀጣሉ፥ ድንጋጤም ይይዛቸዋል። 26 ከቅዴሞትም ምድረ በዳ የሰላምን ቃል ይነግሩት ዘንድ ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁ። በአገርህ ላይ ልለፍ፤ 27 በአውራ ጎዳና እሄዳለሁ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አልተላለፍም። 28 29 የምበላውን ምግብ በገንዘብ ሽጥልኝ፥ የምጠጣውንም ውኃ በገንዘብ ስጠኝ፤ በሴይር የተቀመጡ የዔሳው ልጆች በዔርም የተቀመጡ ሞዓባውያን እንዳደረጉልኝ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ዮርዳኖስን እስክሻገር ድረስ ብቻ በእግሬ ልለፍ። 30 የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን ግን ያሳልፈን ዘንድ አልፈቀደም፤ እንደ ዛሬው ሁሉ በእጅህ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መንፈሱን አደንድኖታልና፥ ልቡንም አጽንቶታልና። 31 እግዚአብሔርም። ሴዎንንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ መስጠት፥ እነሆ፥ ጀመርሁ፤ ምድሩን ትገዛት ዘንድ መውረስ ጀምር አለኝ። 32 ሴዎንም ሕዝቡም ሁሉ ሊጋጠሙን ወደ ያሀጽ ወጡ። 33 አምላካችንም እግዚአብሔር እርሱን አሳልፎ ሰጠን፤ እርሱንም ልጆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ መታን። 34 በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን የተቀመጡባቸውንም ሰዎች ሁሉ ሴቶችንም ሕፃናቶችንም አጠፋን፤ አንዳችም አላስቀረንም፥ 35 ከብቶቻቸውንና ከከተሞቻቸው ያገኘነውን ብዝበዛ ለራሳችን ወሰድን እንጂ። 36 በአርኖን ቈላ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ከሸለቆውም ውስጥ ካለችው ከተማ ጀምረን እስከ ገለዓድ ድረስ ማናቸይቱም ከተማ አልጠነከረችብንም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን አሳልፎ ሰጠን። 37 ዳሩ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ወደ ከለከለን ሁሉ፥ ወደ አሞን ልጆች ምድር በያቦቅም ወንዝ አጠገብ ወዳለው ስፍራ ሁሉ በተራራማውም አገር ወዳሉት ከተሞች አልደረስንም።

ዘዳግም 3

1 ተመልሰን በባሳን መንገድ ወጣን፥ የባሳን ንጉሥ ዐግም ሕዝቡም ሁሉ በኤድራይ ሊዋጉን ወጡ። 2 እግዚአብሔርም። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ። 3 አምላካችን እግዚአብሔርም ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዐግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም መታነው፤ አንድ ሰው እንኳ አምልጦ አልቀረለትም። 4 በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፤ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን። 5 በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ። 6 በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ አጠፋናቸው፤ ከተሞቹን ሁሉ ከወንዶችና ከሴቶች ከሕፃናቶችም ጋር አጠፋናቸው። 7 ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለእኛ በዘበዝን። 8 በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤ 9 ሲዶናውያን አርሞንዔምን ሢርዮን ብለው ይጠሩታል፥ አሞራውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል። 10 በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን። 11 ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በነበረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ። 12 ይህችንም ምድር በዚያን ዘመን ወረስን፤ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ አገር እኩሌታ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው። 13 ከገለዓድም የቀረውን የዐግንም መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፤ ያችም ባሳን ሁሉ የራፋይም አገር ተብላ ተቈጠረች። 14 የምናሴ ልጅ ኢያዕር እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ ድረስ የአርጎብን ምድር ሁሉ ወሰደ፤ ይህችንም የባሳንን ምድር እስከ ዛሬ ድረስ በስሙ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ጠራ። 15 ለማኪርም ገልዓድን ሰጠሁት። 16 ለሮቤል ነገድና ለጋድም ነገድ ከገለዓድ ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥ 17 ከኪኔሬት እስከ ዓረባ ባሕር እርሱም የጨው ባሕር ድረስ ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ ያለውን ዓረባ ዮርዳኖስንም ዳሩንም ሰጠኋቸው። 18 በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ አርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ። 19 ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤ 20 ይኸውም እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፈ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ሁሉ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ። 21 በዚያም ጊዜ ኢያሱን። አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዓይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል። 22 አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና አትፍራቸውም ብዬ አዘዝሁት። 23 በዚያም ዘመን እኔ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ለመንሁ። 24 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለባሪያህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይና በምድርም እንደ ሥራህ እንደ ኃይልህም ይሠራ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው? 25 እኔ ልሻገር በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር ያንም መልካሙን ተራራማውን አገር ሊባኖስንም ልይ። 26 እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ አልሰማኝምም፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይበቃሃል፤ በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ። 27 ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ፈስጋ ራስ ውጣ፤ ዓይንህንም ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም አንሥተህ በዓይንህ ተመልከት። 28 ኢያሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና ኢያሱን እዘዘው፥ አደፋፍረውም፥ አጽናውም። 29 በቤተፌጎርም ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን።

ዘዳግም 4

1 አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። 2 እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። 3 ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ያደረገውን ዓይኖቻችሁ አይተዋል። 4 እናንተ ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ ሁላችሁ በሕይወት ትኖራላችሁ። 5 እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ ታደርጉ ዘንድ አምላኬ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ፍርድን አስተማርኋችሁ። 6 ጠብቁአት አድርጉአትም፤ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው። በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና፤ 7 አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? v8 በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? 9 10 እግዚአብሔር። ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው። 11 እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፤ እስከ ሰማይም መካከል ድረስ አሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፤ ጨለማና ደመና ድቅድቅ ጨለማም ነበረ። 12 እግዚአብሔርም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃልን ድምፅ ሰማችሁ፥ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅን ብቻ ሰማችሁ። 13 ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ፤ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። 14 ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉአትን ሥርዓትና ፍርድ አስተምራችሁ ዘንድ እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ አዘዘኝ። 15 እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ፤ 16 እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥ 17 በምድር ላይ ያለውን የእንስሳን ሁሉ ምሳሌ፥ በሰማይም በታች የሚበርረውን የወፍን ሁሉ ምሳሌ፥ 18 በምድርም ላይ የሚሽከረከረውን ሁሉ ምሳሌ፥ ከምድርም በታች በውኃ ውስጥ የሚኖረውን የዓሣን ሁሉ ምሳሌ እንዳታደርጉ፥ 19 ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ፥ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ። 20 እናንተን ግን እንደ ዛሬው ሁሉ የርስቱ ሕዝብ ትሆኑለት ዘንድ እግዚአብሔር ወስዶ ከብረት እቶን ከግብፅ አወጣችሁ። 21 እግዚአብሔርም በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ፥ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገር፥ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22 እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ፥ ዮርዳኖስንም አልሻገርም፤ እናንተ ግን ትሻገራላችሁ፥ ያችንም መልካሚቱን ምድር ትወርሳላችሁ። 23 አምላካችሁም እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ አምላክህም እግዚአብሔር የከለከለውን በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። 24 አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና። 25 ልጆችን የልጅ ልጆችንም፥ በወለዳችሁ ጊዜ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ በረከሳችሁም ጊዜ፥ በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል ባደረጋችሁ ጊዜ፥ ታስቈጡትም ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር በሠራችሁ ጊዜ፥ 26 ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ፤ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትቀመጡባትም። 27 እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። 28 በዚያም የማያዩትን የማይሰሙትንም የማይበሉትንም የማያሸቱትንም፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። 29 ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ። 30 ይህም ሁሉ በደረሰብህ ጊዜ፥ ስትጨንቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ። 31 አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም። 32 እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። 33 አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን? 34 አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን? 35 እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። 36 ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ፤ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ፤ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። 37 38 አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። 39 እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። 40 ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ። 41 42 በዚያን ጊዜ ሙሴ ትናንት ከትናንት በስቲያም ጠላቱ ያልሆነውን ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ ገዳዩ ይሸሽባቸው ዘንድ፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት ይኖር ዘንድ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ለየ። 43 ከተሞቹም ለሮቤል ነገድ በምድረ በዳ በደልዳላ ስፍራ ያለ ቦሶር፥ ለጋድም ነገድ በገለዓድ ያለ ራሞት፥ ለምናሴም ነገድ በባሳን ያለ ጎላን ነበሩ። 44 ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት ያኖራት ሕግ ይህች ናት፤ 45 46 ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመቱት፥ በሐሴቦን ተቀምጦ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፥ በቤተ ፌጎር አንጻር ባለው ሸለቆ በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከግብፅ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ምስክርና ሥርዓት ፍርድም ይህ ነው። 47 የእርሱንና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ምድር፥ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩትን የሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ምድር፥ 48 በአርኖን ወንዝ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ እስከ ሲዎን ተራራ እስከ አርሞንዔም ድረስ፥ 49 በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለውን ዓረባ ሁሉ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ወሰዱ።

ዘዳግም 5

1 ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። 2 አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 3 እግዚአብሔር ዛሬ በዚህ በሕይወት ካለነው ከእኛ ከሁላችን ጋር እንጂ ከአባቶቻችን ጋር ይህችን ቃል ኪዳን አላደረገም። 4 በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር ፊት ለፊት ተናገራችሁ። 5 እኔ የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር፤ እናንተ በእሳቱ ምክንያት ፈርታችኋልና፥ ወደ ተራራውም አልወጣችሁምና። እርሱም አለ። 6 ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። 7 ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። 8 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ 9 10 በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኛና አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም። 11 የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። 12 እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ። 13 ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ 14 ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ። 15 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ። 16 እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ። 17 አትግደል። 18 አታመንዝር። 19 አትስረቅ። 20 በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። 21 የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። 22 እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳትና በደመናው በጨለማውም ውስጥ ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤአችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጣቸው። 23 ተራራው በእሳት ሲነድድ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፥ እናንተ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች ሽማግሌዎቻችሁም፥ ወደ እኔ ቀረባችሁ፤ 24 አላችሁም። እነሆ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፥ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ሲነጋገር ሰውዮውም በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል። 25 አሁን እንግዲህ ይህች ታላቂቱ እሳት ታቃጥለናለችና ለምን እንሞታለን? እኛ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ ብንሰማ እንሞታለን። 26 ከሥጋ ለባሽ ሁሉ እኛ እንደ ሰማን በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወቱ የኖረ ማን ነው? 27 አንተ ቅረብ፥ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እናደርገዋለን። 28 በተናገራችሁኝም ጊዜ እግዚአብሔር የእናንተን ቃል ጽምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይህ ሕዝብ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ፤ የተናገሩህ ሁሉ መልካም ነገር ነው። 29 ለእነርሱም ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፥ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው! 30 ሄደህ። ወደ ድንኳናችሁ ተመለሱ በላቸው። 31 አንተ ግን በዚህ በእኔ ዘንድ ቁም፥ ርስት አድርጌ በምሰጣቸውም ምድር ላይ ያደርጉአት ዘንድ የምታስተምራቸውን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ፍርዴንም ሁሉ እነግርሃለሁ። 32 እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዳዘዛችሁ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። 33 በሕይወት እንድትኖሩ፥ መልካምም እንዲሆንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።

ዘዳግም 6

1 [see v2] 2 አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም በዕድሜአችሁ ሁሉ ልትወርሱአት በምትገቡባት ምድር ታደርጉአት ዘንድ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ፈርተህ እኔ ለአንተ ያዘዝሁትን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንዳስተምራችሁ ያዘዛት ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድም ይህች ናት። 3 እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካምም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ። 4 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ 5 አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። 6 እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። 7 ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። 8 በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። 9 በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። 10 አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ 11 ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤ 12 በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። 13 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ በስሙም ማል። 14 15 በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቍጣ እንዳይነድድብህ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ፥ በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎችን አማልክት አትከተሉ። 16 በማሳህ እንደ ፈተናችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። 17 ለእናንተ ያዘዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ምስክሩንም ሥርዓቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ። 18 19 መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያወጣልህ ዘንድ፥ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። 20 በኋለኛው ዘመንም ልጅህ። አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ምስክርና ሥርዓት ፍርድስ ምንድር ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ 21 አንተ ልጅህን በለው። በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ ከግብፅ አወጣን፤ 22 እግዚአብሔርም ከግብፅና በፈርዖን በቤቱም ሁሉ ላይ እኛ እያየን ታላቅና ክፉ ምልክት ተአምራትም አደረገ። 23 ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር አግብቶ እርስዋን ይሰጠን ዘንድ ከዚያ አወጣን። 24 እንደ ዛሬም በሕይወት እንዲያኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፈራ ዘንድ፥ ይህችንም ሥርዓት ሁሉ እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘን። 25 እርሱም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።

ዘዳግም 7

1 አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ 2 አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በመታሃቸውም ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፥ አትማራቸውም፤ 3 ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። 4 እንዳይከተለኝ ሌሎችንም አማልክት እንዲያመልክ ልጅህን ያስታልና፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። 5 ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የተቀረጸውን ምስላቸውንም በእሳት አቃጥሉ። 6 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። 7 እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ 8 ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። 9 አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ እወቅ፤ 10 የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፥ ነገር ግን በፊቱ ብድራት ይመልስበታል። 11 እንግዲህ ታደርጋት ዘንድ እኔ ዛሬ ለአንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዓት ፍርድንም ጠብቅ። 12 እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤ 13 ይወድድህማል፥ ይባርክህማል፥ ያበዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል። 14 ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ በሰውህና በከብትህም ዘንድ ወንድ ቢሆን ወይም ሴት ብትሆን መካን አይሆንብህም። 15 እግዚአብሔርም ሕማምን ሁሉ ከአንተ ያርቃል፤ የምታውቀውንም ክፉውን የግብፅ በሽታ ሁሉ በአንተ ላይ አያደርስብህም፥ በጠላቶችህም ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል። 16 አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚጥላቸውን አሕዛብን ሁሉ ታጠፋቸዋለህ፤ ዓይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ወጥመድ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። 17 በልብህም። እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብትል፥ አትፍራቸው፤ 18 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ያደረገውን፥ 19 አምላክህ እግዚአብሔር፥ ዓይንህ እያየች፥ ታላቅን መቅሠፍት ምልክትንም ተአምራትንም የጸናችውን እጅ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፥ አስብ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። 20 ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ተርብ ይሰድድባቸዋል። 21 አምላክህ እግዚአብሔር፥ ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ፥ በመካከልህ ነውና ከእነርሱ የተነሣ አትደንግጥ። 22 አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም። 23 አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ድንጋጤ ያስደነግጣቸዋል። 24 ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም በፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም። 25 የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። 26 እንደ እርሱም ርጉም እንዳትሆን ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ ርጉም ነውና ተጸየፈው፥ ጥላውም።

ዘዳግም 8

1 በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንድትበዙም፥ እግዚአብሔርም ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱአት፥ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ። 2 አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ። 3 ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ። 4 በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም። 5 ሰውም ልጁን እንደሚገሥፅ እንዲሁም አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ አስተውል። 6 በመንገዱም እንድትሄድ እርሱንም እንድትፈራ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 7 አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፥ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፥ 8 ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፥ 9 ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት አንዳችም ወደማታጣባት ምድር፥ ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፥ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር ያገባሃል። 10 ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ፥ ስለሰጠህም ስለመልካሚቱ ምድር አምላክህን እግዚአብሔርን ትባርካለህ። 11 ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤ 12 ከበላህና ከጠገብህ በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ 13 የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ 14 ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ 15 እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ 16 በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ 17 በልብህም። ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። 18 ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ። 19 አምላክህንም እግዚአብሔርን ብትረሳ፥ ሌሎችንም አማልክት ብትከተል ብታመልካቸውም ብትሰግድላቸውም፥ ፈጽሞ እንድትጠፉ እኔ ዛሬውኑ እመሰክርባችኋለሁ። 20 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው እንደ አሕዛብ እንዲሁ እናንተ ትጠፋላችሁ።

ዘዳግም 9

1 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ከአንተ የበለጡትንና የበረቱትን አሕዛብ፥ እስከ ሰማይም ድረስ የተመሸጉትን ታላላቆች ከተሞች ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገረዋለህ። 2 አንተም የምታውቃቸው ስለ እነርሱም። በዔናቅ ልጆች ፊት መቆም ማን ይችላል? ሲባል የሰማኸው ታላቁና ረጅሙ ሕዝብ የዔናቅ ልጆች ናቸው። 3 አምላክህም እግዚአብሔር እንደሚበላ እሳት ሆኖ በፊትህ እንዲያልፍ ዛሬ እወቅ፤ እርሱ ያጠፋቸዋል፥ በፊትህም ያዋርዳቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረህ አንተ ታሳድዳቸዋለህ፥ ፈጥነህም ታጠፋቸዋለህ። 4 አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ካወጣቸው በኋላ። ስለ ጽድቄ እወርሳት ዘንድ ወደዚች ምድር እግዚአብሔር አገባኝ ስትል በልብህ አትናገር፤ እነዚህን አሕዛብ ስለ ኃጢአታቸው እግዚአብሔር ከፊትህ ያወጣቸዋል። 5 ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው። 6 እንግዲህ አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነህና አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳይደለ እወቅ። 7 አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዳስቈጣኸው፤ ከግብፅ አገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ አስብ፥ አትርሳ። 8 በኮሬብ ደግሞ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁ፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ ተቈጣባችሁ። 9 የድንጋዩን ጽላቶች፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላቶች፥ እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። 10 እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፋትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ፤ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የነገራችሁ ቃል ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር። 11 ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊትም በኋላ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች፥ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች፥ ሰጠኝ። 12 እግዚአብሔርም። ተነሥተህ ከዚህ ፈጥነህ ውረድ፤ ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ረክሰዋል፤ ፈጥነው ካዘዝኋቸው መንገድ ፈቀቅ ብለዋል፥ ቀልጦ የተሠራ ምስልም ለራሳቸው አድርገዋል አለኝ። 13 እግዚአብሔርም። ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ሕዝብ እንደሆነ አይቼአለሁ፤ 14 አጠፋቸው ዘንድ፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስስ ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ለሚበረታና ለሚበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። 15 እኔም ተመልሼ ከተራራው ወረድሁ፥ ተራራውም በእሳት ይነድድ ነበር፤ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላቶች በሁለቱ እጆቼ ነበሩ። 16 ተመለከትሁም፤ እነሆ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በድላችሁ ነበር፥ ለእናንተም ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ሠርታችሁ ነበር፤ እግዚአብሔር ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ፈቀቅ ብላችሁ ነበር። 17 ሁለቱንም ጽላቶች ያዝሁ፥ ከሁለቱም እጆቼ ጣልኋቸው፥ እናንተም ስታዩ ሰበርኋቸው። 18 19 ስለ ሠራችሁት ኃጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ሊያጠፋችሁ ከተቈጣባችሁ ከቍጣውና ከመዓቱ የተነሣ ስለ ፈራሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ወደቅሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሰማኝ። 20 እግዚአብሔርም አሮንን ሊያጠፋው እጅግ ተቈጣው፤ ስለ አሮንም ደግሞ በዚያን ጊዜ ጸለይሁ። 21 ያደረጋችሁትንም ኃጢአት ጥጃውን ወሰድሁ፥ በእሳትም አቃጠልሁት፥ አደቀቅሁትም፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨሁት፤ ትቢያውንም ከተራራ በሚወርድ ወንዝ ጣልሁት። 22 በተቤራም በማሳህም በምኞት መቃብርም እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። 23 እግዚአብሔርም። ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ድምፁንም አልሰማችሁም። 24 እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዓመፀኞች ነበራችሁ። 25 እግዚአብሔርም። አጠፋችኋለሁ ብሎ ስለ ተናገረ በወደቅሁበት ዘመን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ወደቅሁ። 26 በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅነትህ የተቤዠኸውን፥ በጠነከረችውም እጅ ከግብፅ ያወጣኸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። 27 ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ደንዳንነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት፤ 28 ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች። እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። 29 እነርሱም በታላቅ ኃይልህ በተዘረጋውም ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።

ዘዳግም 10

1 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር። እንደ ፊተኞች ያሉትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርበህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ፤ 2 በሰበርሃቸውም በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች በእነዚህ ጽላቶች እጽፋለሁ፥ በታቦቱም ውስጥ ታደርጋቸዋለህ አለኝ። 3 ከግራርም እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደ ፊተኞችም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4 ስብሰባ ተደርጎ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የተናገራችሁን አሠርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። 5 ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፥ ጽላቶችንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ በዚያ ኖሩ። 6 የእስራኤልም ልጆች ከብኤሮት ብኔያዕቃን ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ በዚያም አሮን ሞተ በዚያም ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። 7 ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ ከጉድጎዳም ወደ ውኃ ፈሳሾች ምድር ወደ ዮጥባታ ተጓዙ። 8 በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከም ዘንድ፥ እርሱንም ለማገልገል በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ። 9 ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው እግዚአብሔር ርስቱ ነው። 10 እኔም እንደ ፊተኛው ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ተቀመጥሁ፤ እግዚአብሔርም በዚህ ጊዜ ደግሞ ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ አልወደደም። 11 እግዚአብሔርም። ተነሥተህ በሕዝቡ ፊት ተጓዝ፤ ለአባቶቻቸውም ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር ይግቡ ይውረሱአትም አለኝ። 12 13 እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው? 14 እነሆ፥ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርስዋም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው። 15 ብቻ እግዚአብሔር ስለ አባቶችህ ደስ ብሎታል፥ እነርሱንም ወድዶአል፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መረጠ። 16 17 እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። 18 ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል። 19 እናንተ በግብፅ አገር ስደተኞች ነበራችሁና ስለዚህ ስደተኛውን ውደዱ። 20 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ፤ ከእርሱም ተጣበቅ፥ በስሙም ማል። 21 ዓይኖችህ ያዩትን እነዚህን ታላላቆች የሚያስፈሩትንም ነገሮች ያደረገልህ እርሱ ክብርህ ነው፥ እርሱም አምላክህ ነው። 22 አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ፤ አሁንም አምላክህ እግዚአብሔር ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ።

ዘዳግም 11

1 እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፥ ሕጉንም ሥርዓቱንም ፍርዱንም ትእዛዙንም ሁልጊዜ ጠብቅ። 2 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱንም፥ የጸናችም እጁን፥ የተዘረጋውንም ክንዱን፥ 3 በግብፅም መካከል በንጉሡ በፈርዖንና በአገሩ ሁሉ ላይ ያደረጋትን ተአምራቱንና ሥራውን፥ 4 በተከተሉአችሁም ጊዜ በኤርትራ ባሕር ውኃ እንዳሰጠማቸው፥ እግዚአብሔርም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳጠፋቸው፥ በግብፅ ጭፍራ በፈረሶቻቸውም በሰረገሎቻቸውም ያደረገውን፥ 5 ወደዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በምድረ በዳ ያደረገላችሁን፥ 6 በእስራኤልም ሁሉ መካከል ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን ድንኳኖቻቸውንም ለእነርሱም የነበራቸውን ሁሉ በዋጠቻቸው በሮቤል ልጅ በኤልያብ ልጆች በዳታንና በአቤሮን ያደረገውን ላላወቁትና ላላዩት ልጆቻችሁ አልነግራቸውምና እናንተ ዛሬ እወቁ። 7 ነገር ግን እግዚአብሔር ያደረጋትን ታላቂቱን ሥራ ሁሉ ዓይኖቻችሁ አይተዋል። 89 እንግዲህ እንድትጠነክሩ፥ ትወርሱአትም ዘንድ ወደምትሻገሩባት ምድር እንድትገቡ እንድትወርሱአትም፥ እግዚአብሔርም ለእነርሱና ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ በማለላቸው ወተትና ማርም በምታፈስሰው ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ። 10 ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፥ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደዘራህባት፥ በእግርህም እንዳጠጣሃት፥ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። 11 ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች። 12 አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው። 13 እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዜን ፈጽማችሁ ብትሰሙ፥ 14 እህልህን ወይንህንም ዘይትህንም ትሰበስብ ዘንድ በየጊዜው የበልጉን ዝናብና የክረምቱን ዝናብ ለምድራችሁ አወርዳለሁ። 15 በሜዳ ለእንስሶችህ ሣርን እሰጣለሁ፥ ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ። 16 ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም፥ 17 የእግዚአብሔርም ቍጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፤ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ። 18 እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፥ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደክታብ ይሁኑ። 19 ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው። 20 21 እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፥ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፥ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። 22 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ ብታደርጉአትም፥ 23 እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፥ ከእናንተም የሚበልጡትን የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ። 24 የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም ከሊባኖስም ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። 25 በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል። 26 እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤ 27 በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ፤ 28 መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬም ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቋቸውን አማልክት ብትከተሉ ነው። 29 አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ አንተን ወደምትሄድባት ምድር ባገባህ ጊዜ፥ በረከቱን በገሪዛን ተራራ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ። 30 እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከፀሐይ መግቢያ ካለችው መንገድ በኋላ፥ በዓረባ በተቀመጡት በከነዓናውያን ምድር፥ በጌልገላ ፊት ለፊት በሞሬ የአድባር ዛፍ አጠገብ ናቸው። 31 አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፥ ትወርሱአታላችሁም፥ ትቀመጡባታላችሁም። 32 እኔም ዛሬ በፊታችሁ የማኖራትን ሥርዓትና ፍርድ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።

ዘዳግም 12

1 በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ለመውረስ በሰጣችሁ አገር፥ የምትጠብቁአትና የምታደርጉአት ሥርዓትና ፍርድ እነዚህ ናቸው። 2 እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን በረጅም ተራሮች በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉአቸው፤ 3 መሠዊያቸውንም አፍርሱ፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ፥ የአማልክቶቻቸውንም የተቀረጹ ምስሎች አንከታክቱ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ። 4 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ አትሥሩ። 5 ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ ሁሉ ስሙን በዚያ ያኖር ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ ትመጣላችሁ፥ ማደሪያውንም ትሻላችሁ። 6 ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁም ያነሣችሁትን ቍርባን፥ ስእለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ። 7 በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፥ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ። 8 ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታደርጉም፤ 9 አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ዕረፍትና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልገባችሁምና። 10 ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሃትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥ 11 በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ሌላ መሥዋዕታችሁንም፥ አሥራታችሁንም፥ በእጃችሁ ያነሣችሁትንም ቍርባን፥ ለእግዚአብሔርም ተስላችሁ የመረጣችሁትን ስእለታችሁን ሁሉ ውሰዱ። 12 እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ባሪያዎቻችሁም፥ ገረዶቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14 ነገር ግን እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፥ በዚያም የማዝዝህን ሁሉ አድርግ። 15 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ ሰውነትህ እንደ ፈቀደ፥ በደጆችህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ብላ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቋና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው። 16 ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 17 የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም አሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኩራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህም ያቀረብኸውን፥ በእጅህም ያነሣኸውን ቍርባን በደጆችህ ውስጥ መብላት አትችልም። 18 ነገር ግን አንተ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም፥ ባሪያዎችህና ገረዶችህም፥ በአገርህም ደጅ ያለው ሌዋዊ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 19 በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ። 20 አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ አገርህን ባሰፋ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች። ሥጋ ልብላ ስትል፥ እንደ ሰውነትህ ፈቃድ ሥጋን ብላ። 21 አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙን ያኖር ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፥ እንደ ሰውነትህም ፈቃድ ሁሉ በአገርህ ደጅ ውስጥ ብላው። 22 ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ይብላው። 23 ነገር ግን ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍሱንም ከሥጋው ጋር መብላት አይገባህምና ደሙን እንዳትበላ ተጠንቀቅ። 24 በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25 በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው። 26 ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን ስእለትህንም ይዘህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። 27 የሚቃጠለውንም መሥዋዕትህን፥ ሥጋውንና ደሙን፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው። 28 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘላለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ። 29 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብን በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥ 30 በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ። እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። 31 እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኵሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋልና አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ። 32 እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።

ዘዳግም 13

1 በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥ 2 እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም። ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥ 3 አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ። 4 አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ። 5 አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ። 67 የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ በስውር። ና፥ ሄደን ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወደ አንተ የቀረቡት ከአንተም የራቁት አንተን ከብበውህ ያሉ አሕዛብ ከሚያመልኩአቸው አማልክት፥ አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥ 8 አትስማውም፤ ዓይንህም አይራራለት፥ እትማረውም፥ አትሸሽገውም፤ 9 ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ እርሱን ለመግደል በፊት የአንተ እጅ፥ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ በላዩ ትሁን። 10 ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ወድዶአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። 11 እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፥ እንዲህም ያለ ክፉ ሥራ እንደ ገና በአንተ መካከል አያደርጉም። 12 13 አምላክህ እግዚአብሔር ልትኖርባት በሚሰጥህ በአንዲቱ ከተማህ። ክፋተኞች ሰዎች ከእናንተ ዘንድ ወጥተው። ሄደን የማታውቋቸውን ሌሎችን አማልክት እናምልክ ብለው የከተማቸውን ሰዎች አሳቱ ሲሉ ወሬ ብትሰማ፥ 14 ትፈልጋለህ፥ ትመረምራለህም፥ ትጠይቃለህም፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ ይህም ክፉ ነገር በመካከልህ እንደ ተደረገ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥ 15 የዚያችን ከተማ ሰዎች በሰይፍ ስለት ፈጽሞ ትመታቸዋለህ፤ ከተማይቱን፥ በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ እንስሳውንም በሰይፍ ስለት ታጠፋቸዋለህ። 16 ዕቃዋንም ሁሉ ወደ አደባባይዋ ትሰበሰባለህ፥ ከተማይቱንም ዕቃዋንም ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በእሳት ፈጽመህ ታቃጥላለህ፤ ለዘላለምም ወና ትሆናለች፥ ደግሞም አትሠራም። 17 18 ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኘውን ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ስትሰማ፥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ቍጣ ይመለስ ዘንድ፥ ለአባቶችህም እንደ ማለላቸው ይምርህ ዘንድ፥ ይራራልህም ዘንድ፥ ያበዛህም ዘንድ፥ እርም ከሆነው አንዳች ነገር በእጅህ አይንጠልጠልብህ።

ዘዳግም 14

1 2 እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔ አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና ስለ ሞተው ሰው አካላችሁን አትንጩ፥ በዓይኖቻችሁም መካከል ራሳችሁን አትላጩ። 34 ርኩስን ነገር ሁሉ አትብላ። የምትበሉአቸው እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ በሬ፥ 5 በግ፥ ፍየል፥ ዋላ፥ ሚዳቋ፥ የበረሃ ፍየል፥ አጋዘን፥ አጭ፥ በራይሌ፥ ድኵላ። 6 ከእንስሶች ሰኮናው የተሰነጠቀውን፥ ጥፍሩም ከሁለት የተከፈለውን፥ የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ። 7 ነገር ግን ከሚያመሰኩ ወይም ሰኮናቸው ከተሰነጠቀ እነዚህን አትበሉም፤ ግመልን፥ ጥንቸልን፥ ሽኮኮን አትበሉም። ያመሰኳሉና፥ ነገር ግን ሰኮናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሶች ናቸው። 8 እርያም፥ ሰኮናው ስለ ተሰነጠቀ ነገር ግን ስላላመሰኳ እርሱ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ ሥጋውን አትብሉ፥ በድኑንም አትንኩ። 9 በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፤ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10 ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸውን አትበሉም፤ ለእናንተ ርኩስ ናቸው። 11 ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 12 ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፤ 13 ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭልፊት፥ ጭላት በየወገኑ፥ 14 15 ቍራም ሁሉ በየወገኑ፥ ሰጎን፥ 16 ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥ ጕጕት፥ 17 ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ 18 እርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 19 የሚበርርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ አይበላም። 20 ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 21 አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነህና የበከተውን ሁሉ አትብላ፤ ይበላው ዘንድ በአገርህ ደጅ ለተቀመጠ መጻተኛ ትሰጠዋለህ፥ ወይም ለእንግዳ ትሸጠዋለህ። የፍየሉን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል። 22 ከእርሻህ በየዓመቱ ከምታገኘው ከዘርህ ፍሬ ሁሉ አሥራት ታወጣለህ። 23 ሁልጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራት ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን የወይን ጠጅህንም የዘይትህንም አሥራት የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ። 24 አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ ጊዜ፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ ትሸጠዋለህ፥ 25 የዋጋውንም ገንዘብ በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። 26 በዚያም በገንዘቡ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ ወይም የወይን ጠጅ ወይም ብርቱ መጠጥ ሰውነትህም የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፥ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። 27 ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በአገርህ ደጅ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል። 28 በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን አሥራት ሁሉ አምጥተህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ታኖረዋለህ፤ 29 ሌዋዊውም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በአገርህም ደጅ ያለ መጻተኛ ድሀ አደግም መበለትም መጥተው ይበላሉ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።

ዘዳግም 15

1 በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት ታደርጋለህ። 2 ለምሕረቱም የሚገባ ወግ ይህ ነው፤ አበዳሪ ሁሉ ለባልንጀራው ያበደረውን ይተዋል፤ የእግዚአብሔር ይቅርታ ታውጆአልና ያበደረውን ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ አይሻ። 3 ከእንግዳ ላይ ያበደርኸውን መፈለግ ትችላለህ፤ በወንድምህ ላይ ያለውን ሁሉ ግን እጅህ ይተወዋል። 45 አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሰጠህ ምድር ላይ እግዚአብሔር በእውነት ይባርክሃልና አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ በመካከልህ ድሀ አይኖርም። 6 አምላክህም እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፥ አንተን ግን አይገዙህም። 7 አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ፥ ልብህን አታጽና፥ በድሀው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ። 8 ነገር ግን እጅህን ለእርሱ ክፈት፥ የለመነህንም አስፈላጊውን ነገር አበድረው። 9 ሰባተኛው ዓመት የዕዳ ምሕረት ዓመት ቀርቦአል ብለህ ክፉ አሳብ በልብህ እንዳታስብ፥ ለድሀውም ወንድምህ አንዳች የማትሰጥ እንዳትሆን፥ ዓይንህም በእርሱ ላይ ክፉ እንዳይሆን፥ እርሱም ወደ እግዚአብሔር በአንተ ላይ እንዳይጮህ፥ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ተጠንቀቅ። 10 እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና ፈጽመህ ስጠው፥ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት። 11 ድሆች ከምድሪቱ ላይ አያልቁምና ስለዚህ እኔ። በአገርህ ውስጥ ላለው ድሀ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ። 12 አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፤ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጣው። 13 ከአንተም ዘንድ አርነት ባወጣኸው ጊዜ ባዶውን አትስደደው፤ 14 ነገር ግን ከመንጋህ፥ ከአውድማህም፥ ከወይንህም መጥመቂያ ትለግስለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። 15 አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ አምላክህም እግዚአብሔር እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። 16 እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለወደደ፥ ከአንተም ጋር መልካም ስለ ሆነለት። ልወጣ አልወድድም ቢል፥ 17 አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፥ ለዘላለምም ባሪያ ይሆንልሃል። በሴት ባሪያህ ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ። 18 እርሱንም አርነት ባወጣኸው ጊዜ የምንደኝነቱን ሥራ ሁለት እጥፍ አድርጎ ስድስት ዓመት አገልግሎሃልና አይክበድህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል። 19 ላምህና በግህ የወለዱትን ተባት የሆነውን በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ትቀድሳለህ፤ በበሬህ በኵራት አትሥራበት፥ የበግህንም በኵራት አትሸልት። 20 አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ አንተና ቤተ ሰብህ በየዓመቱ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉአቸው። 21 ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፥ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው፥ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው። 22 በአገርህ ደጅ ውስጥ ትበላዋለህ፤ ንጹሕ ሰው ንጹሕም ያልሆነ ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ ይበሉታል። 23 ነገር ግን ደሙን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።

ዘዳግም 16

1 በአቢብ ወር አምላክህ እግዚአብሔር በሌሊት ከግብፅ ስላወጣህ የአቢብን ወር ጠብቅ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ፋሲካ አድርግበት። 2 አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ከበግና ከላም መንጋ ፋሲካ ሠዋ። 3 የቦካውን እንጀራ ከእርሱ ጋር አትብላ፤ ከግብፅ አገር በችኰላ ስለ ወጣህ ከግብፅ አገር የወጣህበትን ቀን በዕድሜህ ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራን እንጀራ፥ ቂጣ እንጀራ፥ ሰባት ቀን ከእርሱ ጋር ብላ። 4 ሰባት ቀንም በአገርህ ሁሉ እርሾ አይታይም፤ በመጀመሪያው ቀን ማታ ከሠዋኸው ሥጋ እስከ ነገ ድረስ ምንም አይደር። 5 አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከአገርህ ደጆች በማንኛይቱም ፋሲካን ትሠዋ ዘንድ አይገባህም። 6 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው በዚያ ስፍራ ከግብፅ በወጣህበት ወራት፥ ፀሐይ ሲገባ፥ ማታ ፋሲካን ሠዋ። 7 አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ታበስለዋለህ፥ ትበላውማለህ፤ በነጋውም ተነሥተህ ወደ ድንኳንህ ትሄዳለህ። 8 ስድስት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ፤ በሰባተኛውም ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ጉባኤ ይሁን፤ ሥራን ሁሉ አታድርግበት። 9 ሰባት ሳምንትም ትቈጥራለህ፤ መከሩን ማጨድ ከምትጀምርበት ቀን ጀምሮ ሰባት ሳምንት መቍጠር ትጀምራለህ። 10 አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን በፈቃድህ የምታቀርበውን አምጥተህ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሰባቱ ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ። 11 አንተ፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለው ሌዋዊ፥ በመካከልህም ያሉት መጻተኛና ድሀ አደግ መበለትም አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 12 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ይህንንም ሥርዓት ጠብቅ፥ አድርገውም። 13 ከአውድማህና ከመጥመቂያህ ፍሬህን በሰበሰብህ ጊዜ የዳስ በዓል ሰባትን ቀን ትጠብቃለህ። 14 አንተም፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፥ ድሀ አደግና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ። 15 አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ሁሉ በእጅህም ሥራ ሁሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል። 16 በዓመት ሦስት ጊዜ፥ በቂጣ በዓል፥ በሰባቱ ሱባዔም በዓል፥ በዳስም በዓል ወንዶችህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ በመረጠው ስፍራ ይታዩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ። 17 አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ። 18 አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በአገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና አለቆችን ሹም፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድ ይፍረዱ። 19 ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል። 20 በሕይወት ትኖር ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚሰጥህን ምድር ትወርስ ዘንድ እውነተኛውን ፍርድ ተከተል። 21 ለአንተ በምትሠራው በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ አጠገብ ከማናቸውም ዛፍ የማምለኪያ ዐፀድ አድርገህ አትትከል። 22 አምላክህ እግዚአብሔርም የሚጠላውን ሐውልት ለአንተ አታቁም።

ዘዳግም 17

1 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ። 2 አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከአገርህ ደጆች በማንኛይቱም ውስጥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ቃል ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት የሠራ ቢገኝ፥ 3 ሄዶም ሌሎች አማልክትን ያመለከ፥ እኔ ላላዘዝኋቸው ለፀሐይና ለጨረቃ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የሰገደ ቢገኝ፥ 4 ቢያወሩልህም ብትሰማም፥ ያንን ፈጽመህ መርምር፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ በእስራኤልም መካከል እንዲህ ያለ ርኵሰት እንደ ተሠራ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥ 5 ይህን ክፉ ነገር የሠሩትን ያን ወንድ ወይም ያችን ሴት ወደ በርህ ታመጣቸዋለህ፥ እስኪሞቱም ድረስ በድንጋይ ትወግራቸዋለህ። 6 በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ሞት የሚገባው ይገደል፤ በአንድ ምስክር አፍ አይገደል። 7 እርሱን ለመግደል በመጀመሪያ የምስክሮች እጅ በኋላም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ትሁንበት፤ እንዲሁም ክፋቱን ከመካከልህ አስወግድ። 8 በደምና በደም፥ በፍርድና በፍርድ፥ በመቍሰልና በመቍሰል መካከል በአገርህ ደጅ ውስጥ ሰዎች ስለሚከራከሩበት ክርክር የሚሳንህ የፍርድ ነገር ቢነሣ፥ አንተ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትወጣለህ፤ 9 ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ ተሾመው ፈራጅ መጥተህ ትጠይቃለህ፤ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። 10 እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ የነገሩህን የፍርድ ነገር ታደርጋለህ፤ እንዳስተማሩህም ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 11 እንዳስተማሩህም ሕግ፥ እንደ ነገሩህም ፍርድ አድርግ፤ ከነገሩህ ፍርድ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 12 ማናቸውም ሰው ቢኰራ፥ በዚያም አምላክህን እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚቆመውን ካህኑን ወይም ፈራጁን ለመስማት ባይወድድ፥ ያ ሰው ይሙት፥ ከእስራኤልም ዘንድ ክፋትን አስወግድ፤ 13 ሕዝቡም ሁሉ ሰምቶ ይፈራል፥ ከዚያም ወዲያ አይኰራም። 14 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በተቀመጥህባትም ጊዜ። በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ ንጉሥ አነግሣለሁ ስትል፥ 15 አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ፤ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ንጉሥ ታነግሣለህ፤ ወንድምህ ያልሆነውን ከሌላ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም። 16 ነገር ግን ለእርሱ ፈረሶችን አያበዛም፤ እግዚአብሔር። በዚያ መንገድ ደግማችሁ አትመለሱም ብሎአችኋልና ፈረሶችን ለማብዛት ሕዝቡን ወደ ግብፅ አይመልስም። 17 ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያበዛም፤ ወርቅና ብርም ለእርሱ እጅግ አያበዛም። 18 በመንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። 19 20 አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፥ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኰራ ከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል፥ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረጅም ዘመን ይነግሡ ዘንድ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፥ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።

ዘዳግም 18

1 ለሌዋውያን ካህናት፥ ለሌዊም ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር ድርሻና ርስት አይሆንላቸውም፤ በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕቱንና ርስቱን ይበላሉ። 2 በወንድሞቻቸውም መካከል ርስት አይሆንላቸውም፤ እርሱ እንደተናገራቸው ርስታቸው እግዚአብሔር ነው። 3 በሬ ወይም በግ ለመሥዋዕት ከሚያቀርቡት ሕዝብ የካህናቱ ወግ ይህ ይሆናል፤ ወርቹንና ሁለቱን ጉንጮቹን ጨጓራውንም ለካህኑ ይሰጣሉ። 4 የእህልህን የወይን ጠጅህን የዘይትህንም በኵራት፥ አስቀድሞም የተሸለተውን የበግህን ጠጕር ለእርሱ ትሰጣለህ። 5 እርሱ ከልጆቹ ጋር ተነሥቶ በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም ያገለግል ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ሁሉ ስለ መረጠው ነው። 6 አንድ ሌዋዊ ሰው ከሚቀመጥባቸው በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ካሉት ከአገር ደጆች ከአንዲቱ ቢወጣ፥ በፍጹም ፈቃድም እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ቢመጣ፥ 7 በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙት እንደ ወንድሞቹ እንደ ሌዋውያን ሁሉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ያገለግላል። 8 ከተሸጠው ከአባቶቹ ከብት ዋጋ ሌላ እንደ ባልንጀሮቹ ከመብል ድርሻውን ይወስዳል። 9 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። 10 ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ 11 አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። 12 ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል። 13 አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን። 14 የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከልክሎሃል። 15 16 አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን። እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ። 17 እግዚአብሔርም አለኝ። የተናገሩት መልካም ነው፤ 18 ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አደርጋለሁ፥ ያዘዝሁትንም ቃል ሁሉ ይነግራቸዋል፤ 19 በስሜም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው እኔ እበቀልለታለሁ። 20 ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል። 21 በልብህም። እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፥ 22 ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፤ ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው።

ዘዳግም 19

1 አምላክህ እግዚአብሔር ምድራቸውን የሚሰጥህን አሕዛብ ባጠፋ ጊዜ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ 2 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በምድርህ መካከል ሦስት ከተሞችን ለራስህ ትለያለህ። 3 ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ ወደ እነርሱ የሚወስደውን መንገድ ታዘጋጃለህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር የሚያወርስህን ምድር ከሦስት አድርገህ ትከፍላለህ። 4 የነፍሰ ገዳይ ወግ ይህ ነው፤ አስቀድሞ ጠላቱ ሳይሆን ባልንጀራውን ሳያስብ የገደለ ወደዚያ ሸሽቶ በሕይወት ይኑር። 56 ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ሊቈርጥ ወደ ዱር ቢሄድ፥ ዛፉንም ሊቈርጥ ምሳሩን ሲያነሣ ብረቱ ከእጀታው ቢወልቅ፥ ባልንጀራውንም እስኪሞት ድረስ ቢመታው፥ ደም ተበቃዩ ነፍሰ ገዳዩን በልቡ ተናድዶ እንዳያሳድደው መንገዱም ሩቅ ስለ ሆነ አግኝቶ እንዳይገድለው፥ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት ይኖራል፤ አስቀድሞ ጠላቱ፤ አልነበረምና ሞት አይገባውም። 7 ስለዚህ እኔ። ለአንተ ሦስት ከተሞችን ለይ ብዬ አዝዤሃለሁ። 8 አምላክህም እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ዳርቻህን ቢያሰፋ፥ ይሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶችህ የተናገረውን ምድር ሁሉ ቢሰጥህ፥ 9 10 አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ ሁልጊዜም በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ታደርጋት ዘንድ ብትጠብቅ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ ንጹሕ ደም እንዳይፈስስ ደምም በአንተ ላይ እንዳይሆን፥ በእነዚህ በሦስት ከተሞች ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራለህ። 11 ሰው ግን ባልንጀራውን ቢጠላ፥ ቢሸምቅበትም፥ ተነሥቶም እስኪሞት ድረስ ቢመታው፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፥ 12 የከተማው ሽማግሌዎች ይልካሉ፥ ከተማጠነበትም ከተማ ይነጥቁታል፥ እንዲሞትም በደም ተበቃዩ እጅ አሳልፈው ይሰጡታል። 13 ዓይንህ አትራራለት፤ ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ንጹሑን ደም ከእስራኤል ታስወግዳለህ። 14 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር በምትወርሳት ርስትህ የቀደሙ ሰዎች የተከሉትን የባልንጀራህን የድንበር ምልክት አትንቀል። 15 ስለ በደል ሁሉ፥ ክፉ በማድረግም ስለ ሠራት ኃጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይቁም፤ በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ነገር ሁሉ ይጸናል። 16 በዓመፃ ይከስሰው ዘንድ በሰው ላይ ሐሰተኛ ምስክር ቢቆም፥ 17 ሁለቱ ጠበኞች በእግዚአብሔር ፊት በካህናቱና በዚያ ዘመን በሚፈርዱ ፈራጆች ፊት ይቆማሉ፤ 18 ፈራጆቹም አጥብቀው ይመረምራሉ፤ ያም ምስክር ሐሰተኛ ምስክር ሆኖ በወንድሙ ላይ በሐሰት ተናግሮ ቢገኝ፥ 19 በወንድሙ ላይ ያደርገው ዘንድ ያሰበውን በእርሱ ላይ ትመልሱበታላችሁ፤ እንዲሁም ከአንተ መካከል ክፋቱን ታስወግዳለህ። 20 የቀሩትም ሰምተው ይፈራሉ፥ እንደዚህ ያለውንም ክፋት ከመካከልህ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አያደርጉም። 21 ዓይንህም አትራራለት፤ ነፍስ በነፍስ፥ ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥ ይመለሳል።

ዘዳግም 20

1 ጠላቶችህን ለመውጋት በወጣህ ጊዜ፥ ፈረሶችንና ሰረገሎችን ሕዝቡንም ከአንተ ይልቅ በዝተው ባየህ ጊዜ፥ ከግብፅ አገር ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና አትፍራቸው። 2 ወደ ሰልፍም በቀረባችሁ ጊዜ ካህኑ ይቅረብ ለሕዝቡም እንዲህ ብሎ ይንገራቸው። 3 እስራኤል ሆይ፥ ስሙ፤ ዛሬ ጠላቶቻችሁን ለመውጋት ትቀርባላችሁ፤ ልባችሁ አይታወክ፥ አትፍሩ፥ አትንቀጥቀጡ፥ በፊታቸውም አትደንግጡ፤ 4 ከእናንተ ጋር የሚሄድ፥ ያድናችሁም ዘንድ ጠላቶቻችሁን ስለ እናንተ የሚወጋ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና። 5 አለቆችም ለሕዝቡ እንዲህ ብለው ይናገሩ። አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያስመርቀው ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 6 ወይንም ተክሎ ፍሬውንም ያልበላ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው ፍሬውን እንዳይበላ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 7 ሚስትም አጭቶ ያላገባትም ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያገባት ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ። 8 አለቆቹም ደግሞ ጨምረው። ማንም ፈሪና ድንጉጥ ሰው ቢሆን እርሱ ፈርቶ የወንድሞቹን ልብ ደግሞ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ ብለው ለሕዝቡ ይናገሩ። 9 አለቆቹም ለሕዝቡ ነግረው በጨረሱ ጊዜ በየጭፍራው በሕዝቡ ላይ የጦር አለቆችን ይሹሙ። 10 ለመዋጋት ወደ አንዲት ከተማ በደረስህ ጊዜ አስቀድመህ በዕርቅ ቃል ጥራቸው። 11 የዕርቅ ቃልም ቢመልሱልህ ደጅም ቢከፍቱልህ፥ በከተማ ውስጥ ያለው ሕዝብ ሁሉ ይገብሩልህ ያገልግሉህም። 12 የዕርቅ ቃልም ባይመልሱልህ ከአንተም ጋር መዋጋት ቢወድዱ፥ አንተ ከተማይቱን ትከብባለህ ታስጨንቃትማለህ፤ 13 አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣት ጊዜ፥ በእርስዋ ያሉትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ስለት ትገድላቸዋለህ፤ 14 ነገር ግን ሴቶቹንና ሕፃናትን እንስሶቹንም በከተማይቱም ያለውን ምርኮ ሁሉ በዝብዘህ ለአንተ ትወስዳለህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የጠላቶችህን ምርኮ ትበላለህ። 15 የእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ባይደሉት ከአንተ እጅግ በራቁት ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ታደርጋለህ። 16 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ከሚሰጥህ ከእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ምንም ነፍስ አታድንም። 17 18 ነገር ግን ለአማልክቶቻቸው ያደረጉትን ርኵሰት ሁሉ ታደርጉ ዘንድ እንዳያስተምሩአችሁ፥ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት እንዳትሠሩ፥ አምላክህ እግዚአብሔር እንዳዘዘህ ኬጢያዊውን አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽመህ ታጠፋቸዋለህ። 19 ከተማይቱን ለመውሰድ በመውጋት ብዙ ቀን ከብበህ ባስጨነቅሃት ጊዜ፥ ምሳርህን አንሥተህ ዛፎችዋን አትቍረጥ፤ ከእነርሱ ትበላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋው የምድር ዛፍ ሰው መሆኑ ነውን? 20 ለመብል የማይሆኑትን የምታውቃቸውን ዛፎች ታጠፋቸዋለህ፥ ትቈርጣቸውማለህ፤ እስክታሸንፋትም ድረስ በምትዋጋህ ከተማ ላይ ምሽግ ትመሽጋለህ።

ዘዳግም 21

1 አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር የተገደለ ሰው በሜዳ ወድቆ ቢገኝ፥ 2 ገዳዩም ባይታወቅ፥ ሽማግሌዎችህና ፈራጆችህ ወጥተው በተገደለው ሰው ዙሪያ እስካሉት ከተሞች ድረስ በስፍር ይለኩ፤ 3 ወደ ተገደለውም ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችውን ቀንበርም ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፤ 4 የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ጊደሪቱን ይዘው ፈሳሽ ውኃ ወዳለበት ወዳልታረሰና ዘርም ወዳልተዘራበት ሸለቆ ይሄዳሉ፤ በዚያም በሸለቆው ውስጥ የጊደሪቱን አንገት ይሰብራሉ። 5 የሌዊ ልጆች ካህናትም ይቀርባሉ፤ በፊቱ እንዲያገለግሉ፥ በስሙም እንዲባርኩ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦአቸዋልና፥ በእነርሱም ቃል ክርክር ሁሉ ጉዳትም ሁሉ ይቈረጣልና፤ 6 ወደ ተገደለው ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ አንገትዋ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ሲታጠቡ። 7 እጃችን ይህን ደም አላፈሰሰችም፥ ዓይናችንም አላየችም፤ 8 አቤቱ፥ የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቍጠር ብለው ይናገራሉ። ስለ ደሙም ይሰረይላቸዋል። 9 አንተም በእግዚአብሔር ዓይን የቀናውን ባደረግህ ጊዜ የንጹሑን ደም በደል ከመካከልህ ታርቃለህ። 10 ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በማረክሃቸውም ጊዜ፥ 11 በተማረኩት መካከል የተዋበች ሴት ብታይ፥ ብትመኛትም ሚስትም ልታደርጋት ብትወድድ፥ ወደ ቤትህ ታመጣታለህ፤ 12 እርስዋም ራስዋን ትላጫለች፥ ጥፍርዋንም ትቈረጣለች፤ 13 የተማረከችበትንም ልብስ ታወልቃለች፥ በቤትህም ተቀምጣ ስለ አባትዋና ስለ እናትዋ አንድ ወር ሙሉ ታለቅሳለች፤ ከዚያም በኋላ ትደርስባታለህ፥ ባልም ትሆናታለህ፥ እርስዋም ሚስት ትሆንልሃለች። 14 ከዚያም በኋላ በእርስዋ ደስ ባይልህ አርነት አውጥተህ ወደ ወደደችው ትሰድዳታለህ፤ በዋጋ ግን አትሸጣትም፤ እፍረት አድርገህባታልና እንደ ባሪያ አትቈጥራትም። 15 ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኵሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥ 16 ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኵሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኵር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤ 17 ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኵር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኃይሉ መጀመሪያ ነውና በኵርነቱ የእርሱ ነው። 18 ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ 19 አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖሩበትም ስፍራ በር ያምጡት፤ 20 የከተማውንም ሽማግሌዎች። ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፥ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው። 21 የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ። 22 ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ 23 በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።

ዘዳግም 22

1 የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፤ ወደ ወንድምህ መልሰው። 2 ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘህ ወደ ቤትህ ትገባለህ፤ ወንድምህ እስኪሻው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣል፥ ለእርሱም ትመልሰዋለህ። 3 እንዲህም በአህያው ወይም በልብሱ ታደርጋለህ፤ እንዲህም በወንድምህ በጠፋበት ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፤ ቸል ልትለው አይገባህም። 4 የወንድምህ አህያ ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ከእርሱ ጋር ሆነህ አነሣሣው እንጂ ቸል አትበለው። 5 ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና። 6 በመንገድ ስትሄድ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ እናቲቱ በጫጩቶችዋ ወይም በእንቍላሎችዋ ላይ ተኝታ ሳለች የወፍ ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ከጫጩቶዋ ጋር አትውሰድ። 7 ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ እናቲቱን ስደድ፥ ጫጩቶችንም ለአንተ ውሰድ። 8 አዲስ ቤት በሠራህ ጊዜ ማንም ከእርሱ ወድቆ ደሙን በቤትህ ላይ እንዳታመጣ በጣራው ዙሪያ መከታ አድርግለት። 9 የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ። 10 በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ። 11 ከተልባ እግርና ከበግ ጠጕር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ። 12 በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ። 13 ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ ከደረሰባትም በኋላ ቢጠላት፥ 14 የነውር ነገር አውርቶ። እኔ ይህችን ሴት ሚስት አድርጌ አገባኋት፥ በደርስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም ብሎ በክፉ ስም ቢያሳጣት፥ 15 የብላቴናይቱ አባትና እናት የድንግልናዋን ምልክት ወስደው በበሩ በአደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፤ 16 የብላቴናይቱም አባት ሽምግሌዎቹን። እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት እርሱም ጠላት፤ 17 እነሆም። በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም ብሎ የነውር ነገር አወራባት፤ የልጄም ምልክት ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ። 18 የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ያንን ሰው ወስደው ይግረፉት፤ 19 በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል ያስከፍሉት፥ ለብላቴናይቱም አባት ይስጡት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነው፥ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። 20 ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ በብላቴናይቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥ 21 ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። 22 ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለታቸው ይሙቱ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ። 23 ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ 24 ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዮውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። 25 ነገር ግን ሰው የታጨችውን ልጃገረድ በሜዳ ቢያገኛት፥ በግድ አሸንፎም ቢደርስባት፥ ያ የደረሰባት ሰው ብቻውን ይገደል። 26 በብላቴናይቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉ በብላቴናይቱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የለባትም፤ ሰው በባልንጀራው ላይ ተነሥቶ እንደሚገድለው ይህ፤ ነገር ደግሞ እንደዚሁ ነውና፤ 27 በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ጮኻለችና፥ የሚታደጋትም አልነበረምና። 28 ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ ወስዶም ቢደርስባት፥ ቢያገኙትም፥ 29 ያ የደረሰባት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፤ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። 30 ማናቸውም ሰው የአባቱን ሚስት አይውሰድ፥ የአባቱንም ልብስ ጫፍ አይግለጥ።

ዘዳግም 23

1 ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። 2 ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። 34 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እንጀራና ውኃ ይዘው በመንገድ ላይ አልተቀበሉአችሁምና፥ በመስጴጦምያ ካለው ከፋቱራ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግምህ ዘንድ አምጥተውብሃልና አሞናዊና ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ለዘላለም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ። 5 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም፤ አምላክህም እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ። 6 በዘመንህ ሁሉ ለዘላለም ሰላምና ልማት ለእነርሱ አትሻ። 7 ኤዶማዊው ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፤ ግብፃዊውንም በአገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። 8 ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ይግቡ። 9 ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። 10 በእናንተ መካከል ሌሊት በሚሆነው ርኵሰት የረከስ ሰው ቢኖር፥ ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፥ ወደ ሰፈርም አይግባ። 11 በመሸም ጊዜ በውኃ ይታጠብ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ። 12 ወደ ሜዳም ትወጣበት ዘንድ ከሰፈር ውጭ ቦታ ይሁንልህ። 13 ከመሣሪያህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በሜዳም በተቀመጥህ ጊዜ ትምስበታለህ፥ ዞረህም ከአንተ የወጣውን በአፈር ትከድነዋለህ። 14 አምላክህ እግዚአብሔር ሊያድንህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥ በሰፈርህ መካከል ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ፥ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሰፈርህ የተቀደስ ይሁን። 15 ከጌታው ኮብልሎ ወደ አንተ የመጣውን ባሪያ ለጌታው አሳልፈህ አትስጥ። 16 ከደጆችህ በሚመርጣት በአንዲቱ በሚወድዳት ስፍራ ከአንተ ጋር በመካከልህ ይቀመጥ፥ አንተም አታስጨንቀው። 17 ከእስራኤል ሴቶች ልጆች ሴት ጋለሞታ አትገኝ፥ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች ወንድ ጋለሞታ አይገኝ። 18 ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና። 19 ለወንድምህ በወለድ አታበድር፤ የብር ወይም የእህል ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ። 20 ለእንግዳው በወለድ አበድረው፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ለወንድምህ በወለድ አታበድር። 21 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘገይ። 22 ባትሳል ግን ኃጢአት የለብህም። 23 በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 24 ወደ ባልንጀራህ ወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ፤ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አታግባ። 25 ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ፤ ወዳልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታግባ።

ዘዳግም 24

1 ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት። 2 ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ 3 ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥ 4 የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ። 5 አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፥ ነገርም አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፥ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት። 6 የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ። 7 ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ አንዱን ሰርቆ እንደ ባሪያ ሲያደርግበት ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ያ ሌባ ይሙት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። 8 በለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 9 አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን አስብ። 10 ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ። 11 አንተ በውጭ ቁም ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ያውጣልህ። 12 ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር። 13 ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይሆንልሃል 14 ድሀና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ፥ ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻተኞች ቢሆን፥ አታስጨንቀው። 15 ድሀ ነውና፥ ነፍሱም ጠንክራ ትፈልገዋለችና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው። 16 አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል። 17 የመጻተኛውንና የድሀ አደጉን ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱን ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት። 18 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። 19 የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ አደግ ለመበለትም ተወው። 20 የወይራህን ፍሬ ባረገፍህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ ማርገፉን ለማጣራት አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን። 21 የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን። 22 አንተም በግብፅ አገር ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።

ዘዳግም 25

1 በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍርድም ቢመጡ፥ ፈራጆችም ቢፈርዱባቸው፥ ጻድቁን። ደኅና ነህ፥ የበደለውንም። በደለኛ ነህ ይበሉአቸው። 2 በደለኛውም መገረፍ ቢገባው እንዲገረፍ ፈራጁ በፊቱ በምድር ላይ ያጋድመው፤ የግርፋቱም ቍጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን ይሁን። 3 ግርፋቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግርፋት ቢገርፈው ወንድምህ በፊትህ ነውረኛ ይሆናልና ከዚህ በላይ አይጨመርበት። 4 እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። 5 ወንድማማቾች በአንድነት ቢቀመጡ፥ አንዱም ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ የሞተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አትሂድ፤ ነገር ግን የባልዋ ወንድም ወደ እርስዋ ገብቶ እርስዋን ያግባ፥ ከእርስዋም ጋር ይኑር። 6 የምዋቹ ስም ከእስራኤል ዘንድ እንዳይጠፋ ከእርስዋ የሚወለደው በኵር ልጅ በሞተው በወንድሙ ስም ይጠራ። 7 ያም ሰው የወንድሙን ሚስት ማግባት ባይወድድ፥ ዋርሳይቱ በበሩ አደባባይ ወደሚቀመጡ ሽማግሌዎች ሄዳ። ዋርሳዬ በእስራኤል ዘንድ ለወንድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእኔ ጋር ሊኖርም አልወደደም ትበላቸው። 8 የከተማውም ሽማግሌዎች ጠርተው ይጠይቁት፤ እርሱም በዚያ ቆሞ። አገባት ዘንድ አልወድድም ቢል፥ 9 ዋርሳይቱ በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ። የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ይደረግበታል ስትል ጫማውን ከእግሩ ታውጣ፥ በፊቱም እንትፍ ትበልበት። 10 በእስራኤልም ዘንድ ስሙ የጫማ ፈቱ ቤት ተብሎ ይጠራ። 11 ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ 12 እጅዋን ቍረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። 13 በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት ሚዛን አይኑርልህ። 14 በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈሪያ አይኑርልህ። 15 16 ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ። 17 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን አስብ፤ 18 በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተስኖህ ደክመህም ሳለህ ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራም። 19 ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንን አትርሳ።

ዘዳግም 26

1 አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር በገባህም ጊዜ፥ በወረስሃትም በኖርህባትም ጊዜ፥ 2 አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ፍሬ ሁሉ በኵራት ውሰድ በዕንቅብም አድርገው፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደ መረጠውም ስፍራ ይዘህ ሂድ። 3 በዚያም ወራት ወደሚሆነው ካህን መጥተህ። እግዚአብሔር ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስታውቃለሁ በለው። 4 ካህኑም ዕንቅቡን ከእጅህ ወስዶ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠውያ ፊት ያኑረው። 5 በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ተናገር። አባቴ የተቅበዘበዘ ሶርያዊ ነበረ፤ በቍጥር ጥቂት ሳለ ወደ ግብፅ ወረደ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ የሆነ የበረታም ቍጥሩም የበዛ ሕዝብ ሆነ። 6 ግብፃውያንም ክፉ ነገር አደረጉብን፥ አስጨነቁንም፥ በላያችንም ጽኑ ከባድ ሥራን ጫኑብን፤ 7 ወደ አባቶቻችንም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ድምፃችንን ሰማ፥ ጭንቀታችንንም ድካማችንንም ግፋችንንም አየ፤ 8 እግዚአብሔርም በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ድንጋጤ፥ በተአምራትም፥ በድንቅም ከግብፅ አወጣን፤ 9 ወደዚህም ስፍራ አገባን፥ ወተትና ማር የምታፈስሰውንም ይህችን ምድር ሰጠን። 10 አሁንም እነሆ፥ አቤቱ፥ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን ፍሬ በኵራት አቅርቤአለሁ። አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ስገድ። 11 አንተም በመካከልህም ያለ ሌዋዊና መጻተኛ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው ቸርነት ሁሉ ደስ ይበላችሁ። 12 አሥራት በምታወጣበት በሦስተኛው ዓመት የፍሬህን ሁሉ አሥራት አውጥተህ በፈጸምህ ጊዜ፥ በአገርህ ደጅ ውስጥ ይበሉ ዘንድ ይጠግቡም ዘንድ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም ስጣቸው። 13 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል። የተቀደሰውን ነገር ከቤቴ ወስጄ ለሌዋዊው ለመጻተኛውም ለድሀ አደጉም ለመበለቲቱም እንዳዘዝኸኝ ትእዛዝ ሁሉ ሰጥቼአለሁ፤ ትእዛዝህን ምንም አላፈረስሁም፥ አልረሳሁምም፤ 14 በኀዘኔ ጊዜ እኔ ከእርሱ አልበላሁም፥ ለርኵስነቴም ከእርሱ አላወጣሁም፥ ከእርሱም አንዳች ለሞተ ሰው አልሰጠሁም፤ የአምላኬንም የእግዚአሔርን ቃል ሰምቼአለሁ፥ ያዘዝኸኝንም ሁሉ አድርጌአለሁ። 15 ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደ ማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈስሰውን አገር ባርክ። 16 አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። 17 አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል። 18 እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ 19 ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።

ዘዳግም 27

1 ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ብለው ሕዝቡን አዘዙ። ዛሬ ያዘዝኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ። 2 አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ ታላላቅ ድንጋዮችን ለአንተ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው። 3 የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር ትገባ ዘንድ በተሻገርህ ጊዜ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ጻፍባቸው። 4 ዮርዳኖስንም በተሻገርህ ጊዜ፥ ዛሬ እንዳዘዝሁህ፥ እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ አቁም፥ በኖራም ምረጋቸው። 5 በዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ መሠዊያውም ብረት ካልነካው ድንጋይ ይሁን። 6 ካልተጠረበም ድንጋይ የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ሥራ፤ ለአምላክም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት፤ 7 የደኅንነትም መሥዋዕት ሠዋበት፥ በዚያም ብላ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 8 የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ የተገለጠ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ። 9 ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብላችሁ አድምጡ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል። 10 ለአምላክህም ለእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፥ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዓቱን አድርግ። 11 ሙሴም በዚያን ቀን እንዲህ ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። 12 ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ እነዚህ፥ ስምዖንና ሌዊ ይሁዳና ይሳኮር ዮሴፍና ብንያም፥ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ። 13 ይረግሙም ዘንድ እነዚህ፥ ሮቤልና ጋድ አሴርና ዛብሎን ዳንና ንፍታሌም፥ በጌባል ተራራ ላይ ይቁሙ። 14 ሌዋውያንም ከፍ ባለች ድምፅ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገራሉ። 15 በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን የተቀረጸ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ። 16 አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 17 የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 18 ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 19 በመጻተኛ በድሀ አደጉም በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 20 ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የአባቱን ልብስ ገልጦአልና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 21 ከማናቸይቱም እንስሳ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 22 ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 23 ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 24 ባልንጀራውን በስውር የሚመታ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 25 የንጹሑን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። 26 የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።

ዘዳግም 28

1 እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። 2 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል። 3 አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። 4 የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል። 5 እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል። 6 አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ። 7 እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ። 8 እግዚአብሔር በረከቱ በአንተ ላይ በጐተራህ በእጅህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ያዝዛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል። 9 የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። 10 የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል። 11 እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ እግዚአብሔር በጎነቱን በላይህ ያበዛል። 12 እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብ ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዝብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም። 13 14 ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። 15 ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል። 16 በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ። 17 እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል። 18 የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል። 19 አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። 20 እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል። 21 እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ቸነፈርን ያጣብቅብሃል። 22 እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል። 23 በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፥ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች። 24 እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል፤ እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል። 25 እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል፤ በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፥ በሰባት መንገድ ከእነርሱ ትሸሻለህ፤ ለምድርም መንግሥታት ሁሉ ድንጋጤ ትሆናለህ። 26 ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራቸውም የለም። 27 እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል። 28 እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በድንጋጤም ይመታሃል። 29 በቀትርም ጊዜ ዕውር በጨለማ እንደሚርመሰመስ ትርመሰመሳለህ፥ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተጨነቅህ የተዘረፍህም ትሆናለህ፥ የሚያድንህም የለም። 30 ሚስት ታጫለህ፥ ሌላም ሰው ከእርስዋ ጋር ይተኛል፤ ቤት ትሠራለህ፥ አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፥ ከእርሱም አትበላም። 31 በሬህ በፊትህ ይታረዳል፥ ከእርሱም አትበላም፤ አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፥ ወደ አንተም አይመለስም፤ በግህ ለጠላቶችህ ትሰጣለች፥ የሚያድንህም አታገኝም። 32 ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፥ ዓይኖችህም ያያሉ፥ ሁልጊዜም ስለ እነርሱ ሲባክኑ ያልቃሉ፤ በእጅህም ኃይል ምንም አይገኝም። 33 የምድርህን ፍሬ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ የተገፋህም ትሆናለህ። 34 ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። 35 እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል። 36 እግዚአብሔርም አንተን በአንተም ላይ የምታነግሠውን ንጉሥ አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካለህ። 37 እግዚአብሔርም በሚያገባህ በአሕዛብ መካከል ሁሉ ድንጋጤ ምሳሌም ተረትም ትሆናለህ። 38 እጅግ ዘር ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ። 39 ወይን ትተክላለህ ታበጀውማለህ፤ ትልም ይበላዋልና ከእርሱ ምንም አትሰበስብም፥ የወይን ጠጁንም አትጠጣም። 40 የወይራ ዛፍ በአገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ወይራህም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም። 41 ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይወለዱልሃል፤ በምርኮም ይሄዳሉና ለአንተ አይሆኑልህም። 42 ዛፍህን ሁሉ የምድርህንም ፍሬ ኩብኩባ ይወርሰዋል። 43 በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አንተም ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44 እርሱ ያበድርሃል፥ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፥ አንተም ጅራት ትሆናለህ። 45 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዓቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፥ ያሳድዱህማል፥ ያገኙሁማል። 46 በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ። 47 ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሤት አላመለክህምና 48 በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል። 49 50 እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን፥ ፊታቸው የደነደነውን፥ ሽማግሌውንም የማያፍሩትን፥ ሕፃኑንም የማይምሩትን ሕዝብ ንስር እንደሚበርር ከሩቅ አገር ከምድር ዳር ያመጣብሃል። 51 እስክትጠፋ ድረስ የከብትህን ፍሬ የምድርህንም ፍሬ ይበላሉ፤ እስኪያጠፉህም ድረስ እህልን የወይንም ጠጅ ዘይትንም የላምህንና የበግህን ርቢ አይተዉልህም። 52 በአገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ደጆች ሁሉ ከብበው ያስጭንቁሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ በደጆች ሁሉ ከብበው ያስጨንቁሃል። 53 ጠላቶችህም ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54 በአንተ ዘንድ የተለሳለሰና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ይኖር የነበረ ሰው በወንድሙ፥ አቅፋውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆች ይቀናል፤ 55 በደጆችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም። 56 በአንተ ዘንድ ያለችው የተለሳለሰችና በቅምጥልነት ሁልጊዜ ትኖር የነበረችው፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥ 57 በወንድና በሴት ልጅዋም፥ በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅ፥ በምትወልዳቸውም ልጆች ትቀናለች፤ በደጆችህም ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች። 58 በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም <<አምላክህ እግዚአብሔር>> የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥ 59 እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል። 60 የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል። 61 ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። 62 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል። 63 እግዚአብሔርም በጎ ያደርግላችሁ ዘንድ ያበዛችሁም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋችሁ ሲያፈርሳችሁም ደስ ይለዋል፤ ትወርሱአትም ዘንድ ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ። 64 እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወዳሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን፥ ታመልካለህ። 65 በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፥ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ፥ ፈዛዛ ዓይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል። 66 ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም፤ 67 አንተ ስለ ፈራህበት ስለ ልብህ ፍርሃት፥ በዓይንህም ስለምታየው አስተያየት፥ ማለዳ። መቼ ይመሻል? ትላለህ፤ ማታም። መቼ ይነጋል? ትላለህ። 68 ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ፤ የሚገዛችሁም አይገኝም።

ዘዳግም 29

1 እግዚአብሔር በኮሬብ ካደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞዓብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው። 2 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እግዚአብሔር በፊታችሁ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሁሉ ያደረገውን ሁሉ፥ 3 ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎች፥ ታላላቆች ተአምራትና ድንቆች፥ አይታችኋል፤ 4 እግዚአብሔር ግን አስተዋይ ልብ፥ የሚያዩ ዓይኖች፥ የሚሰሙም ጆሮች እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም። 5 አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀም። 6 እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥ አልጠጣችሁም። 7 ወደዚህም ስፍራ በመጣችሁ ጊዜ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን የባሳንም ንጉስ ዐግ ሊወጉን ወጡብን፥ እኛም መታናቸው፤ 8 ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤልና ለጋድ ለምናሴም ነገድ እኵሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው። 9 ስለዚህ በምታደርጉት ሁሉ ትከናወኑ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ቃሎች ጠብቁ አድርጉም። 10 11 ሁላችሁ፥ አለቆቻችሁም ነገዶቻችሁም ሽማግሌዎቻችሁም ሹማምቶቻችሁም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ልጆቻችሁም ሴቶቻችሁም በሰፈራችሁም ያለ እንጨትህን የሚቈርጥ ውኃህንም የሚቀዳ መጻተኛ፥ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤ 12 13 ይኸውም ዛሬ ለእርሱ ሕዝብ አድርጎ ያስነሣህ ዘንድ፥ እርሱም ለአንተ እንደ ተናገረ ለአባቶችህም ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንደ ማለ አምላክ ይሆንልህ ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ዛሬ በሚያደርገው ቃል ኪዳን ትገባ ዘንድና የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሐላ ትሰማ ዘንድ ነው። 14 እኔም ይህን ቃል ኪዳንና ይህን መሐላ የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤ 15 ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር፥ ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው እንጂ፤ 16 ነገር ግን እኛ በግብፅ ምድር እንደ ተቀመጥን በመካከላቸውም ባለፋችሁባቸው አሕዛብ መካከል እንዳለፍን አውቃችኋልና፥ 17 ርኩስነታቸውንም በእነርሱም ዘንድ የነበሩትን የእንጨትና የድንጋይ የብርና የወርቅም ጣዖቶቻቸውን አይታችኋልና፥ 18 ሄዶ የእነዚያን አሕዛብ አማልክት ያመልክ ዘንድ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ልቡን ዛሬ የሚያስት ወንድ ወይም ሴት ወይም ወገን ወይም ነገድ አይኑርባችሁ፤ ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ። 19 የዚህንም እርግማን ቃሎች የሰማ ሰው። ምንም እንኳ በልቤ ደንዳንነት ብሄድ፥ ለጥማቴም ስካር ብጨምር፥ ሰላም ይሆንልኛል ብሎ ሰውነቱን በልቡ የሚባርክ ቢኖር፥ 20 የእግዚአብሔር ቍጣ ቅንዓቱም በዚያ ሰው ላይ ይጤሳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው እርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፥ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21 እግዚአብሔርም በዚህ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው እንደ ቃል ኪዳኑ እርግማን ሁሉ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል። 22 ከዚያም በኋላ የሚነሣ ትውልድ ከእናንተም በኋላ የሚሆኑ ልጆቻችሁ ከሩቅ አገርም የሚመጣ እንግዳ፥ የዚህን አገር መቅሠፍት፥ እግዚአብሔርም በእርስዋ ያደረገውን ሥቃይዋን፥ 23 ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው መቃጠልም እንደ ሆነባት፥ እንዳትዘራም እንዳታበቅልም፥ ማናቸውም ሣርና ልምላሜም እንዳይወጣባት፥ እግዚአብሔር በቍጣውና በመዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ እንደ አዳማና እንደ ሲባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥ 24 አሕዛብ ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህች ምድር ስለ ምን እንደዚህ አደረገ? ይህስ የቍጣው ታላቅ መቅሠፍት ምንድር ነው? ይላሉ። 25 ሰዎችም እንዲህ ይላሉ። የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለተዉ፥ 26 ሄደውም የማያውቋቸውንና ያልታዘዙትን ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስለ ሰገዱላቸው፥ 27 ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያወርድባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ነደደ፤ 28 ዛሬም እንዳሉ እግዚአብሔር በቍጣና በመቅሠፍት በታላቅም መዓት ከምድራቸው ነቀላቸው፥ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው። 29 ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።

ዘዳግም 30

1 እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በሚበትንህ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ባሰብኸው ጊዜ፥ 2 ወደ አምላክህም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥ 3 አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። 4 ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል። 5 አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ያጋባሃል፥ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ያደርግልሃል፥ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል። 6 በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል። 7 አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል። 8 አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፥ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ። 9 10 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በዚህም ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ እግዚአብሔር በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ በሆድህም ፍሬ በከብትህም ፍሬ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ይባርክሃል። 11 እኔ ዛሬ የማዝዝህ ይህች ትእዛዝ ከባድ አይደለችም፥ ከአንተም የራቀች አይደለችም። 12 ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም። 13 ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም። 14 ነገር ግን ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው። 15 ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ። 16 በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ። 17 ልብህ ግን ቢስት አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም፥ 18 ፈጽማችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመናችሁን አታስረዝሙም። 19 በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ 20 እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።

ዘዳግም 31

1 ሙሴም ሄዶ ይህንን ቃል ለእስራኤል ሁሉ ነገረ። 2 አላቸውም። እኔ ዛሬ መቶ ሀያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም ብሎኛል። 3 አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሻገራል። 4 እግዚአብሔርም ባጠፋቸው በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ በምድራቸውም እንዳደረገ ያደርግባቸዋል። 5 እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፥ እንዳዘዝኋችሁም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ። 6 ጽኑ፥ አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፥ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፥ አይተውህም። 7 ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት። አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። 8 በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ አለው። 9 ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፥ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት። 10 ሙሴም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ፥ በዕዳ ምሕረት ዘመን፥ በዳስ በዓል፥ 11 እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው። 12 ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ። 13 የሕግ ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ። 14 እግዚአብሔርም ሙሴን። የምትሞትበት ቀን፥ እነሆ፥ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቆሙ። 15 እግዚአብሔርም በድንኳኑ ውስጥ በደመና ዓምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ። 16 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ። 17 በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን። በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። 18 ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ። 19 አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት። 20 ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደ ምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፥ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፥ እኔንም ይንቃሉ፥ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ። 21 ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፥ ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች። 22 ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት። 23 የነዌንም ልጅ ኢያሱን። የእስራኤልን ልጆች ወደ ማልሁላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፥ አይዞህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ ብሎ አዘዘው። 24 እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥ 25 ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ። 26 ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፥ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት። 27 እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? 28 ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤ 29 ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል። 30 ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህች መዝሙር ቃሎች እስኪፈጸሙ ድረስ ተናገረ።

ዘዳግም 32

1 ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ። 2 ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥ ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ። 3 የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ። 4 እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው። 5 እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው። 6 ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው። 7 የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። 8 ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ። 9 የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው። 10 በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው። 11 ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው። 12 እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም። 13 በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የእርሻውን ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥ ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤ 14 የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ። 15 ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ። 16 በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት። 17 እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ። 18 የወለደህን አምላክ ተውህ፥ ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ። 19 ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው። 20 እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤ ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤ ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸው። 21 አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤ 3ቍ. 15 በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል። በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤ እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ። 22 እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥ የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች። 23 መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤ በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ። 24 በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤ በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤ የአራዊትን ጥርስ፥ የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ። 25 ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል። 26 እበትናቸዋለሁ አልሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ። 27 ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ። እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም እንዳይሉ፥ ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ። 28 ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም። 29 አእምሮ ቢኖራቸው፥ ይህንን ያስተውሉ ነበር፥ ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር። 30 እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥ እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር? 31 አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤ ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው። 32 ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ነው፤ ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤ ዘለላውም መራራ ነው። 33 የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥ የእፉኝትም ሥራይ ነው። 34 ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን? በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን? 35 የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥ የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና እግራቸው ሲሰናከል በቀልና ፍርድ የእኔ ነው። 36 ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥ የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል። 37 እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት? 38 የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ። 39 አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም። 40 እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና 41 የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ። 42 ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤ ከጠላት አለቆችም ራስ ሰይፌ ሥጋ ይበላል። 43 የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ። 44 ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ። 45 ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ። 46 እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት። 47 ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ። 48 በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 49 ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤ 50 ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤ 51 በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥ 52 ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።

ዘዳግም 33

1 የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት። 2 እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥ በሴይርም ተገለጠ፤ ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤ በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው። 3 ሕዝቡንም ወደዳቸው፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤ በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ ቃሎችህን ይቀበላሉ። 4 ሙሴ ለያዕቆብ ጉባኤ ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን። 5 የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተከማቹ ጊዜ፥ ንጉሥ በይሹሩን ነበረ። 6 ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት፤ ሰዎቹም በቍጥር ብዙ ይሁኑ። 7 የይሁዳ በረከት ይህ ነው፤ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ የይሁዳን ድምፅ ስማ፥ ወደ ወገኖቹም አግባው፤ እጆቹ ይጠንክሩለት፤ በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ። 8 ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥ ቱሚምህና ኡሪምህ ለቅዱስህ ሰው ነው፥ በማሳህ ለፈተንኸው፥ በመሪባ ውኃም ለተከራከርኸው፤ 9 ስለ አባቱና ስለ እናቱ። አላየሁም ላለ፥ ወንድሞቹንም ላላስተዋለ፥ ልጆቹንም ላላወቀ፤ ቃልህን አደረጉ፥ ቃል ኪዳንህንም ጠበቁ። 10 ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕት ይሠዋሉ። 11 አቤቱ፥ ሀብቱን ባርክ፥ የእጁንም ሥራ ተቀበል፤ የሚነሣበትን ወገብ ውጋው፥ የሚጠሉትም አይነሡ። 12 ስለ ብንያምም እንዲህ አለ። በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤ ቀኑን ሁሉ ይጋርደዋል፥ በትከሻውም መካከል ያድራል። 13 ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፥ ምድሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረከ ይሁን፤ በሰማያት ገናንነት በጠል፥ በታችኛውም ቀላይ፥ 14 በፀሐዩ ፍሬያት ገናንነት፥ በጨረቃውም መውጣት ገናንነት 15 በቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥ በዘላለሙም ኮረብቶች ገናንነት፥ 16 በምድሪቱም ገናንነትና ሞላዋ፥ በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት በዮሴፍ ራስ ላይ፥ ከወንድሞቹም በተለየው ራስ አናት ላይ ይውረድ። 17 ለላሞች በኵር ግርማ ይሆናል፤ ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤ በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤ የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥ የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው። 18 ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ። ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥ ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ። 19 የተሰወረውን የአሸዋውን መዝገብ፥ የባሕሩንም ባለጠግነት ይጠባሉና አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤ በዚያ የጽድቅ መሥዋዕት ይሠዋሉ። 20 ስለ ጋድም እንዲህ አለ። ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤ እንደ አንበሳይቱ ዐርፎአል፤ ክንድንና ራስን ይቀጠቅጣል። 21 በዚያ የአለቃ እድል ፈንታ ቀርቶአልና የመጀመሪያውን ክፍል ለራሱ መረጠ፤ ወደ ሕዝብ አለቆችም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ጽድቅ፥ ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ። 22 ስለ ዳንም እንዲህ አለ። ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤ ከባሳን ዘልሎ ይወጣል። 23 ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ። ንፍታሌም በሞገስ ጠግቦአል፥ የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤ ባሕሩንና ደቡቡን ይወርሳል። 24 ስለ አሴርም እንዲህ አለ። አሴር በልጆች የተባረከ ይሁን፤ በወንድሞቹ የተወደደ ይሁን፤ እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ። 25 ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤ እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኃይልህ ይሆናል። 26 ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። 27 መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ። አጥፋው ይላል። 28 እስራኤልም ተማምኖ፥ የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥ እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ። 29 እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።

ዘዳግም 34

1 ሙሴም ከሞዓብ ሜዳ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ወደ ፈስጋ ራስ ወጣ፤ እግዚአብሔርም እስከዳን ድረስ ያለውን የገለዓድን ምድር፥ 2 የንፍታሌምንም ምድር ሁሉ፥ የኤፍሬምንና የምናሴንም ምድር፥ እስከ ምዕራብም ባሕር ድረስ ያለውን የይሁዳን ምድር ሁሉ፥ ደቡብንም፥ 3 እስከ ዞዓር ድረስ ያለውንም የዘንባባ ዛፎች ያሉባትን ከተማ የኢያሪኮን ሸለቆ ሜዳ አሳየው። 4 እግዚአብሔርም። ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት፤ በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፥ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም አለው። 5 የእግዚአብሔር ባሪያም ሙሴ እንደ እግዚአብሔር ቃል በዚያ በሞዓብ ምድር ሞተ። 6 በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሞዓብ ምድር በሸለቆው ውስጥ ተቀበረ፤ እስከ ዛሬም ድረስ መቃብሩን ማንም አላወቀም። 7 ሙሴም በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ዓመት ነበረ፤ ዓይኑ አልፈዘዘም፥ ጕልበቱም አልደነገዘም። 8 የእስራኤልም ልጆች በሞዓብ ሜዳ ሠላሳ ቀን ለሙሴ አለቀሱለት፤ ለሙሴም ያለቀሱለት የልቅሶው ወራት ተፈጸመ። 9 ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጆች ታዘዙለት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 10 እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ከዚያ ወዲህ በእስራኤል ዘንድ አልተነሣም፤ 11 በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ምልክትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከው ያለ፥ 12 በእስራኤል ሁሉ ፊት በጸናች እጅ ሁሉና በታላቅ ማስደንገጥ ሁሉ እንዳደረገው እንደ ሙሴ ያለ አልተነሣም።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 1

1 እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2 ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። 3 ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። 4 ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። 5 በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። 6 ለአባቶቻቸው። እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። 7 ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 8 የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። 9 በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን? 10 11 ኢያሱም የሕዝቡን አለቆች። በሰፈሩ መካከል እለፉ፥ ሕዝቡንም። አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው ብሎ አዘዘ። 12 ኢያሱም የሮቤልን ልጆች የጋድንም ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 13 የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ። አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፥ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል። 14 ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ ምድር ይቀመጡ፤ ነገር ግን እናንተ፥ ጽኑዓን ኃያላን ሁሉ፥ ተሰልፋችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ተሻገሩ፥ እርዱአቸውም፥ 15 እግዚአብሔር እናንተን እንዳሳረፋችሁ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በፀሐይ መውጫ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትመለሳላችሁ ትወርሱአትማላችሁ። 16 እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት። ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ እንሄዳለን። 17 በሁሉም ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 18 በትእዛዝህ የሚያምፅ ሁሉ የምታዝዘውንም ቃል ሁሉ የማይሰማ፥ እርሱ ይገደል፤ ብቻ ጽና፥ አይዞህ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 2

1 የነዌም ልጅ ኢያሱ። ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ። ሄዱም፤ ረዓብም ወደሚሉአት ጋለሞታ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። 2 የኢያሪኮም ንጉሥ። እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ ሲባል ወሬ ሰማ። 3 የኢያሪኮም ንጉሥ። አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። 4 ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም። አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ 5 በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ አለች። 6 እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። 7 ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፤ እሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ። 8 እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። 9 ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው። እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። 10 ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። 11 ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተንሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም። 12 አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥ 13 አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ። 14 ሰዎቹም። ይህን ነገራችንን ባትገልጪ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፤ እግዚአብሔርም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ከአንቺ ጋር ቸርነትንና እውነትን እናደርጋለን አሉአት። 15 ቤትዋም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበርና ከመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። 16 እርስዋም። አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ ኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለቻቸው። 17 ሰዎቹም አሉአት። እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። 18 እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። 19 ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። 20 ይህንን ነገራችንን ግን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። 21 እርስዋም። እንደ ቃላችሁ ይሁን አለች፤ ሰደደቻቸውም እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። 22 እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። 23 ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። 24 ኢያሱንም። በእውነት እግዚአብሔር አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ በአገሩም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፊታችን ይቀልጣሉ አሉት። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 3

1 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እርሱና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሰጢም ተነሥተው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። 2 ከሦስት ቀንም በኋላ አለቆች በሰፈሩ መካከል አለፉ። 3 ሕዝቡን። የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። 4 በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፤ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ። 5 ኢያሱም ሕዝቡን። ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ። 6 ኢያሱም ካህናቱን። የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት እለፉ ብሎ ተናገራቸው፤ የቃል ኪዳኑንም ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት አለፉ። 7 እግዚአብሔርም ኢያሱን። ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ሁሉ ዓይን ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ። 8 አንተም የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት። በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ አለው። 9 ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች። ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ አለ። 10 ኢያሱም አለ። ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽሞ እንዲያወጣ በዚህ ታውቃላችሁ። 11 እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ ቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ወደ ዮርዳኖስ ያልፋል። 12 አሁንም ከእስራኤል ነገዶች አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጡ፤ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን። 13 እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ ከላይ የሚወርደው የዮርዳኖስ ውኃ ይቋረጣል፤ እንደ ክምርም ሆኖ ይቆማል። 14 እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። 15 እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እጅግ ሞልቶ ነበርና ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ ሲደርሱ፥ ታቦቱንም የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ፥ 16 ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ በጻርታን አጠገብ ባለችው አዳም በምትባል ከተማ በሩቅ ቆሞ በአንድ ክምር ተነሣ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃ ፈጽሞ ተቋረጠ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ተሻገሩ። 17 የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፥ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 4

1 እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ እግዚአብሔርም ኢያሱን። 2 ከሕዝቡ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ አሥራ ሁለት ሰዎች ምረጥና። 3 በዮርዳኖስ መካከል የካህናት እግር ከቆመበት ስፍራ አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሡ፤ ተሸክማችሁም በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ስፍራ አኑሩአቸው ብለህ እዘዛቸው አለው። 4 ኢያሱም ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው፥ ከእስራኤል ልጆች ያዘጋጃቸውን አሥራ ሁለት ሰዎች ጠራ። 5 ኢያሱም አላቸው። በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፤ ከእናንተም ሰው ሁሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም። 6 ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይሆናል፤ ልጆቻችሁም በሚመጣው ዘመን። የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው? ብለው ሲጠይቁአችሁ፥ 7 እናንተ። በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለተቋረጠ ነው፤ ዮርዳኖስን በተሻገረ ጊዜ የዮርዳኖስ ውኃ ተቋረጠ፥ እነዚህም ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘላለም መታሰቢያ ይሆናሉ ትሉአቸዋላችሁ። 8 የእስራኤልም ልጆች ኢያሱ እንዳዘዘ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን እንደ ተናገረው በእስራኤል ነገድ ቍጥር ከዮርኖስ መካከል አሥራ ሁለት ድንጋዮች አንሥተው ወደሚያድሩበት ስፍራ ወሰዱ፥ በዚያም አኖሩአቸው። 9 ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች በቆሙበት ስፍራ በዮርዳኖስ መካከል ሌሎችን አሥራ ሁለት ድንጋዮች ተከለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። 10 ሙሴም ኢያሱን እንዳዘዘው ሁሉ፥ እግዚአብሔር ኢያሱን ለሕዝቡ እንዲነግር ያዘዘው ነገር ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ነበርና፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ። 11 ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተሻገሩ ጊዜ፥ ሕዝቡ እያዩ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ ተሻገሩ። 12 ሙሴም እንዳዘዛቸው የሮቤል ልጆች፥ የጋድም ልጆች፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ተሰልፈው በእስራኤል ልጆች ፊት ተሻገሩ። 13 አርባ ሺህ ያህል ሰዎች ጋሻና ጦራቸውን ይዘው ለሰልፍ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ። 14 በዚያም ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ አደረገው፤ ሙሴንም እንደ ፈሩ በዕድሜው ሁሉ ፈሩት። 15 16 እግዚአብሔርም ኢያሱን። የምስክሩን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ እንዲወጡ እዘዝ ብሎ ተናገረው። 17 ኢያሱም ካህናትን። ከዮርዳኖስ ውጡ ብሎ አዘዛቸው። 18 የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ከዮርዳኖስ መካከል በወጡ ጊዜ፥ የካህናቱም እግር ጫማ ደረቅ መሬት መርገጥ በጀመረ ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ውኃ ወደ ስፍራው ተመለሰ፥ ቀድሞም እንደ ነበረ በዳሩ ሁሉ ላይ ሄደ። 19 ሕዝቡም በመጀመሪያው ወር በአሥረኛው ቀን ከዮርዳኖስ ወጡ፥ በኢያሪኮም ዳርቻ በምሥራቅ በኩል በጌልገላ ሰፈሩ። 20 ከዮርዳኖስም ውስጥ የወሰዱአቸውን እነዚያን አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ኢያሱ በጌልገላ አቆማቸው። 21 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ አባቶቻቸውን። እነዚህ ድንጋዮች ምንድር ናቸው? ብለው ሲጠይቁ፥ 22 ለልጆቻችሁ እንዲህ ብላችሁ ታስታውቃላችሁ። እስራኤል ይህን ዮርዳኖስን በደረቅ ተሻገረ፤ 23 እስክንሻገር ድረስ አምላካችሁ የኤርትራን ባሕር ከፊታችን እንዳደረቀ እንዲሁ እስክትሻገሩ ድረስ አምላካችሁ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ውኃ ከፊታችሁ አደረቀ። v 24 ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ጠንካራ እንደ ሆነች የምድር አሕዛብ ሁሉ እንዲያውቁ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ለዘላለሙ እንድትፈሩ ነው። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 5

1 v1 እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የከነዓናውያን ነገሥት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩት ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ነፍስ ከዚያ ወዲያ አልቀረላቸውም። v2 በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ኢያሱን። የባልጩት መቍረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ ግረዛቸው አለው። v3 ኢያሱም የባልጩት መቍረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ። v4 ኢያሱ የገረዘበትም ምክንያት ይህ ነው፤ ከግብፅ የወጡት ሕዝብ ወንዶች ሰልፈኞች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ። v5 የወጡት ሕዝብ ሁሉ ተገርዘው ነበር፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጡበት መንገድ በምድረ በዳ የተወለዱት ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበር። v6 እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው የማለላቸው፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር። v7 ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፥ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፤ በመንገድ ሳሉ ስላልገረዙአቸው ሸለፈታሞች ነበሩና። v8 ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው በተገረዙ ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ በየስፍራቸው ተቀመጡ። v9 እግዚአብሔርም ኢያሱን። ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ። v 10 የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በኢያሪኮ ሜዳ ፋሲካ አደረጉ። v 11 ከፋሲካውም በኋላ በነጋው የምድሪቱን ፍሬ የቂጣ እንጎቻ ቆሎም በዚያው ቀን በሉ። v 12 በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ። v 13 እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዓይኑን አንሥቶ ተመለከተ፥ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ። ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን? አለው። v 14 እርሱም። አይደለሁም፤ እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና። ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው። v 15 የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን። አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 6

1 ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ ከእርስዋም የሚወጣ ማንም አልነበረም። 2 እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው። ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። 3 ሰልፈኞቻችሁ ሁሉ ከተማይቱን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። 4 ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። 5 ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱንም ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ይገባባታል። 6 የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ። የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አላቸው። 7 ሕዝቡንም። ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ሰልፈኞችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ አለ። 8 ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። 9 ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 10 ኢያሱም ሕዝቡን። እኔ። ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው። 11 እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ። 12 ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። 13 ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 14 በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። 15 በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። 16 በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ። እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። 17 ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። 18 እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ። 19 ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ። 20 ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ። 21 በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። 22 ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች። ወደ ጋለሞታይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ አላቸው። 23 ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። 24 ከተማይቱንም በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አደረጉት። 25 ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የሰደዳቸውንም መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች። 26 በዚያን ጊዜም ኢያሱ። ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኵር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ። 27 እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ወጣ። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 7

1 v1 የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። 2 ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ። ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፤ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። 3 ወደ ኢያሱም ተመልሰው። ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። 4 ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። 5 የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቍልቍለቱም መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። 6 ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7 ኢያሱም አለ። ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! 8 ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? 9 ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? 10 እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው። ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፤ 11 እስራኤል በድሎአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። 12 ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13 ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው። እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ። 14 ነገም በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ቤተ ሰብ በየሰዉ ይቀርባል። 15 እርም የሆነውም ነገር የተገኘበት ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል አድርጎአልና እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ። 16 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው አቀረበ፤ የይሁዳም ነገድ ተለየ፤ 17 የይሁዳንም ወገን አቀረበ የዛራንም ወገን ለየ፤ የዛራንም ወገን ሰዎች አቀረበ፤ 18 ዘንበሪም ተለየ፤ የቤቱንም ሰዎች አቀረበ፤ ከይሁዳም ነገድ የሆነ የከርሚ ልጅ የዘንበሪ ልጅ የዛራ ልጅ አካን ተለየ። 19 ኢያሱም አካንን። ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ አለው። 20 አካንም መልሶ ኢያሱን። በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። 21 በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው። 22 ኢያሱም መልክተኞች ሰደደ ወደ ድንኳኑም ሮጡ፤ እነሆም፥ በድንኳኑ ውስጥ ተሸሽጎ ነበር፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። 23 ከድንኳኑም ውስጥ ወስደው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አመጡት፤ በእግዚአብሔርም ፊት አኖሩት። 24 ኢያሱና እስራኤል ሁሉ የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ካባውንም፥ ወርቁንም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ያለውንም ሁሉ ወስደው ወደ አኮር ሸለቆ አመጡአቸው። 25 ኢያሱም። ለምን አስጨነቅኸን? እግዚአብሔር ዛሬ ያስጨንቅሃል አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉአቸው፥ በድንጋይም ወገሩአቸው። 26 በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ እግዚአብሔርም ከቍጣው ትኵሳት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ተጠራ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 8

1 እግዚአብሔርም ኢያሱን። አትፍራ፥ አትደንግጥ፤ ሰልፈኞችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፥ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እይ፥ የጋይን ንጉሥ ሕዝቡንም ከተማውንም ምድሩንም በእጅህ ሰጥቼሃለሁ። 2 በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ ምርኮዋንና ከብትዋን ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማይቱም በስተ ኋላ ድብቅ ጦር አስቀምጥ አለው። 3 ኢያሱም ሰልፈኞቹም ሁሉ ወደ ጋይ ሊወጡ ተነሡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን ኃያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ በሌሊትም ሰደዳቸው፥ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እነሆ፥ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ተደበቁ፤ ከከተማይቱ አትራቁ፥ ሁላችሁም ተዘጋጁ፤ 5 እኔ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ እኛንም ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ 6 አስቀድመን እንደ ሸሸን የምንሸሽ ይመስላቸዋልና ከከተማይቱ እስክናርቃቸው ድረስ ወጥተው ይከተሉናል፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን። 7 እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና ከተማይቱን ያዙ። 8 በያዛችኋትም ጊዜ ከተማይቱን በእሳት አቃጥሉአት፤ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ። 9 ኢያሱም ሰደዳቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፥ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በምዕራብ በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ። 10 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፥ ሕዝቡንም አሰለፈ፤ እርሱም የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። 11 ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፥ ወደ ከተማይቱም ፊት ደረሱ፥ በጋይም በሰሜን በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። 12 አምስት ሺህ ያህል ሰዎችንም ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በከተማይቱም በምዕራብ በኩል ደብቆ አስቀመጣቸው። 13 በከተማይቱ በሰሜን በኩል የነበሩትን ሠራዊት ሁሉ በከተማይቱም በምዕራብ በኩል የተደበቁትን ሕዝብ አኖሩ፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ። 14 የጋይም ንጉሥ ባየ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ቸኵለው በማለዳ ተነሡ፤ እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ወዳለው ወደ አንድ ስፍራ እስራኤልን በሰልፍ ለመገናኘት ወጡ፤ ከከተማይቱ በስተ ኋላ ግን ድብቅ ጦር እንዳለ አያውቅም ነበር። 15 ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ድል የተነሡ መስለው ከፊታቸው በምድረ በዳው መንገድ ሸሹ። 16 በከተማይቱም የነበሩ ሰዎች ሁሉ ሊያሳድዱአቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፥ ከከተማይቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። 17 በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማይቱንም ከፍተው ተዉ፥ እስራኤልንም አሳደዱት። 18 እግዚአብሔር ኢያሱን። ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ አለው፤ ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር በከተማይቱ ላይ ዘረጋ። 19 የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፥ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ሮጡ፥ ወደ ከተማይቱም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም ከተማይቱን በእሳት አቃጠሉአት። 20 የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፥ ወዲህና ወዲያም መሸሽ አልቻሉም፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ። 21 ኢያሱም እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማይቱን እንደ ያዙ፥ የከተማይቱም ጢስ እንደ ተነሣ ባዩ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉ። 22 ሌሎቹም በላያቸው ከከተማይቱ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች በእስራኤል መካከል ሆኑ፥ እስራኤልም ከበቡአቸው፤ አንድ እንኳ ሳይቀር ሳያመልጥም ገደሉአቸው። 23 የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት። 24 እንዲህም ሆነ፤ እስራኤልን ሊያሳድዱ ሄደው የነበሩትን የጋይን ሰዎች ሁሉ በሜዳና በምድረ በዳ ከገደሉአቸው በኋላ፥ እነርሱም በሰይፍ ስለት እስኪያልቁ ድረስ ከወደቁ በኋላ፥ እስራኤል ሁሉ ወደ ጋይ ተመለሱ፥ በሰይፍም ስለት መቱአት። 25 በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም ሴትም የጋይ ሰዎች ሁሉ አሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ። 26 ኢያሱም በጋይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም። 27 ነገር ግን እግዚአብሔር ኢያሱን እንዳዘዘው ቃል የዚያችን ከተማ ከብትና ምርኮ እስራኤል ለራሳቸው ዘረፉ። 28 ኢያሱም ጋይን አቃጠላት፥ እስከ ዛሬም ድረስ ድብድባና በረሃ ለዘላለም አደረጋት። 29 የጋይንም ንጉሥ እስከ ማታ ድረስ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ሬሳውንም ከዛፍ አወረዱት፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ጣሉት፥ በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት። 30 የዚያን ጊዜም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። 31 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዘ፥ በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፥ መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ፤ በእርሱም ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት ሠዉ። 32 የእስራኤልም ልጆች ሲያዩ በዚያ ስፍራ በድንጋዮቹ ላይ የሙሴን ሕግ ጻፈባቸው። 33 የእስራኤልንም ሕዝብ አስቀድሞ ይባርኩ ዘንድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘ፥ እስራኤል ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ፈራጆቻቸውም፥ የአገሩ ልጆችም፥ መጻተኞችም፥ እኩሌቶቹ በገሪዛን ተራራ ፊት እኩሌቶቹም በጌባል ተራራ ፊት ሆነው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፥ በታቦቱም ፊት በወዲህና በወዲያ ቆመው ነበር። 34 ከዚህም በኋላ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሁሉ፥ የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና እርግማኑን አነበበ። 35 ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶቹም በሕፃናቱም በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሁሉን አነበበ እንጂ ሙሴ ካዘዘው አንዲት ቃል አላስቀረም። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 9

1 እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ 2 ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። 3 የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ 4 እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ። 5 ያረጀ የተጠቀመም ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። 6 ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች። ከሩቅ አገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን አድርጉ አሉ። 7 የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያንን። ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን? አሉአቸው። 8 ኢያሱንም። እኛ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ኢያሱም። እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ? አላቸው። 9 እነርሱም አሉት። ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባሪያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብፅም ያደረገውን ሁሉ፥ 10 በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11 ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ። ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ። እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን። 12 ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፤ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም። 13 እነዚህም የጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል። 14 ሰዎቹም ከስንቃቸው ወሰዱ፥ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም። 15 ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፥ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው። 16 ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ በመካከላቸውም እንደ ኖሩ ሰሙ። 17 የእስራኤልም ልጆች ተጕዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው መጡ፤ የከተሞቻቸውም ስም ገባዖን፥ ከፊራ፥ ብኤሮት፥ ቂርያትይዓሪም ነበረ። 18 የሕዝቡም አለቆች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በአለቆቹ ላይ አጕረመረሙ። 19 አለቆቹም ሁሉ ለማኅበሩ ሁሉ። በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ምለንላቸዋል፤ ስለዚህም እንነካቸው ዘንድ አይገባንም። 20 ስለ ማልንላቸው መሓላ ቍጣ እንዳይወርድብን ይህን እናድርግባቸው፥ በሕይወትም እንተዋቸው አሉአቸው። 21 አለቆቹም። በሕይወት ይኑሩ አሉአቸው፤ አለቆቹም እንደ ተናገሩአቸው ለማኅበሩ ሁሉ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች ሆኑ። 22 ኢያሱም ጠርቶ። እናንተ በመካከላችን ስትኖሩ። ከእናንተ እጅግ የራቅን ነን ብላችሁ ለምን አታለላችሁን? 23 አሁንም የተረገማችሁ ናችሁ፤ ለአምላኬም ቤት እንጨት ቈራጭ ውኃም ቀጂ የሆነ ባሪያ ከእናንተ ለዘላለም አይጠፋም አላቸው። 24 መልሰውም ኢያሱን። እኛ ባሪያዎችህ ምድሪቱን ሁሉ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ ያጠፋ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፥ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን፥ ይህንንም ነገር አድርገናል። 25 አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ውስጥ ነን፤ ለዓይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን አሉት። 26 እንዲሁም አደረገባቸው፥ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፥ አልገደሉአቸውምም። 27 በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠውም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቈራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 10

1 እንዲህም ሆነ፤ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ኢያሱ ጋይን እንደ ያዘ ፈጽሞም እንዳጠፋት፥ በኢያሪኮና በንጉሥዋም ያደረገውን እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ እንዳደረገ፥ የገባዖንም ሰዎች ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዳደረጉ በመካከላቸውም እንደ ሆኑ በሰማ ጊዜ፥ 2 ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለ ሆነች፥ ከጋይም ስለ በለጠች፥ ሰዎችዋም ሁሉ ኃያላን ስለ ነበሩ፥ እጅግ ፈራ። 3 ስለዚህም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ሆሃም፥ ወደ የርሙት ንጉሥም ወደ ጲርአም፥ ወደ ለኪሶ ንጉሥም ወደ ያፊዓ፥ ወደ አዶላም ንጉሥም ወደ ዳቤር ልኮ። ወደ እኔ ውጡ፥ 4 ከኢያሱና ከእስራኤልም ልጆች ጋር ሰላም አድርገዋልና ገባዖንን ለመምታት አግዙኝ አለ። 5 አምስቱም የአሞራውያን ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ የአዶላም ንጉሥ፥ ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር ተሰብስበው ወጡ፥ ከገባዖንም ጋር ሊጋጠሙ ከበቡአት። 6 የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው። ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ አድነንም እርዳንም አሉት። 7 ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ። 8 እግዚአብሔርም ኢያሱን። በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው የሚቋቋምህ የለም አለው። 9 ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው። 10 እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በመንገድ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው። 11 ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቍልቍለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ። 12 እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ፤ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ። በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤ 13 ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም። 14 እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም። 15 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈራቸው ወደ ጌልገላ ተመለሱ። 16 እነዚህም አምስት ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተሸሸጉ። 17 ለኢያሱም። አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ተሸሽገው ተገኙ ብለው ነገሩት። 18 ኢያሱም እንዲህ አለ። ወደ ዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ፥ ይጠብቁአቸው ዘንድ ሰዎችን በዚያ አኑሩ፤ 19 እናንተ ግን አትዘግዩ፥ ጠላቶቻችሁንም አባርሩአቸው፥ በኋላም ያሉትን ግደሉ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሉአቸው አለ። 20 እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በታላቅ መምታት መምታታቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥ 21 ሕዝብ ሁሉ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ በደኅና ተመለሱ፤ በእስራኤል ልጆች ላይ ምላሱን ማንቀሳቀስ የደፈረ ማንም ሰው የለም። 22 ኢያሱም። የዋሻውን አፍ ክፈቱ፥ እነዚያንም አምስት ነገሥታት ከዋሻው ወደ እኔ አውጡአቸው አለ። 23 እንዲህም አደረጉ፤ አምስቱንም ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ የኬብሮንንም ንጉሥ የየርሙትንም ንጉሥ የለኪሶንም ንጉሥ የኦዶላምንም ንጉሥ፥ ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡአቸው። 24 እነዚያንም ነገሥታት ወደ ኢያሱ ባወጡአቸው ጊዜ ኢያሱ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፥ ከእርሱም ጋር የሄዱትን የሰልፈኞች አለቆች። ቅረቡ፥ በእነዚህም ነገሥታት አንገት ላይ እግራችሁን አኑሩ አላቸው። ቀረቡም በአንገታቸውም ላይ እግራቸውን አኖሩ። 25 ኢያሱም። እግዚአብሔር በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጋልና አትፍሩ፥ አትደንግጡ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ አላቸው። 26 ከዚህም በኋላ መትተው ገደሉአቸው፥ በአምስቱም ዛፎች ላይ ሰቀሉአቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፎቹ ተሰቅለው ቈዩ። 27 ፀሐይም ልትገባ በቀረበች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ከዛፎችም አወረዱአቸው፥ ተሸሽገውም በነበሩበት ዋሻ ጣሉአቸው፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ ተደርጎአል። 28 በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዛት፥ እርስዋንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ከእነርሱም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገ በመቄዳ ንጉሥ አደረገ። 29 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፥ ልብናንም ወጉ። 30 እግዚአብሔርም እርስዋንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፥ በእርስዋም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገው በልብና ንጉሥ አደረገ። 31 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ለኪሶ አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም። 32 እግዚአብሔርም ለኪሶን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፥ በሁለተኛውም ቀን ያዙአት፤ በልብናም እንዳደረጉት ሁሉ፥ እርስዋን በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱአቸው። 33 በዚያን ጊዜም የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ኢያሱም አንድ ስንኳ ሳይቀር እርሱንና ሕዝቡን መታ። 34 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከለኪሶ ወደ ኦዶላም አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም፤ 35 በዚያም ቀን ያዙአት፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፤ በለኪሶም እንዳደረገው ሁሉ፥ በእርስዋ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በዚያ ቀን ፈጽሞ አጠፋ። 36 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከኦዶላም ወደ ኬብሮን ወጡ፥ ወጉአትም፥ ያዙአትም፤ 37 እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ሁሉ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ በኦዶላም እንዳደረገው ሁሉ ማንንም አላስቀረም፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። 38 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ዳቤር ተመለሱ፥ ወጉአትም፥ 39 እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ያዙ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ በእነርሱም ውስጥ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽመው አጠፉ፤ ማንንም አላስቀረም፤ በኬብሮን፥ ደግሞ በልብናና በንጉሥዋ እንዳደረገው እንዲሁ በዳቤርና በንጉሥዋ አደረገ። 40 እንዲሁም ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ተራራማውን አገር ደቡቡንም ቈላውንም ቍልቍለቱንም ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ መታ፤ ማንንም አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ነፍስ ያለበትን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። 41 ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ ድረስ የጎሶምንም ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታ። 42 የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ። 43 ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈሩ ወደ ጌልገላ ተመለሱ። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 11

1 እንዲህም ሆነ፤ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥ 2 በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥ 3 በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። 4 እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞችና ሠረገሎች ጋር ወጡ፤ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ። 5 እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ። 6 እግዚአብሔርም ኢያሱን። ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው። 7 ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም። 8 እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው። 9 ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። 10 በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች። 11 በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፤ አሶርንም በእሳት አቃጠላት። 12 የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው። 13 እስራኤልም በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም፤ ነገር ግን እስራኤል አሶርን ብቻ አቃጠሉአት። 14 የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም። 15 እግዚአብሔርም ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም። 16 ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥ 17 እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም። 18 ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። 19 በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፤ ሁሉን በሰልፍ ያዙ። 20 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ ሞገስንም እንዳያገኙ ፈጽመውም እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ። 21 በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው። 22 በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም። 23 እግዚአብሔርም ለሙሴ እንደ ነገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸውና እንደ ነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከሰልፍ ዐረፈች።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 12

1 የእስራኤልም ልጆች የመቱአቸው፥ ከአርኖንም ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በምሥራቅ ያለውን ዓረባ ሁሉ በዮርዳኖስም ማዶ በፀሐይ መውጫ ያለውን አገራቸውን የወረሱአቸው ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ 2 በሐሴቦን የተቀመጠው፥ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር፥ ከሸለቆውም መካከል ጀምሮ የገለዓድን እኩሌታ እስከ ያቦቅ ወንዝ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ 3 በምሥራቅም በኩል ያለውን ዓረባ እስከ ኪኔሬት ባሕር ድረስ፥ በቤትየሺሞት መንገድ አጠገብ እስካለው እስከ አረባ ባሕር እስከ ጨው ባሕር ድረስ፥ በደቡብም በኩል ከፈስጋ ተራራ አፋፍ በታች ያለውን ምድር የገዛው የአሞራውያን ንጉሥ ሴዎን፤ 4 ከራፋይምም ወገን የቀረ፥ በአስታሮትና በኤድራይ የተቀመጠው፥ የአርሞንዔምንም ተራራ፥ 5 ሰልካን፥ ባሳንንም ሁሉ እስከ ጌሹራውያንና እስከ ማዕካታውያን ዳርቻ፥ የገለዓድንም እኩሌታ እስከ ሐሴቦን ንጉሥ እስከ ሴዎን ዳርቻ ድረስ የገዛው የባሳን ንጉሥ ዐግ። 6 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ልጆች መቱአቸው፤ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ርስት አድርጎ ለሮቤል ልጆች ለጋድም ልጆች ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ምድሪቱን ሰጣቸው። 78 በዮርዳኖስም ማዶ በምዕራብ በኩል በሊባኖስ ሸለቆ ካለችው ከበኣልጋድ ወደ ሴይር እስከሚያወጣው ወና እስከ ሆነው ተራራ ድረስ ኢያሱ በየክፍላቸው ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገድ በሰጣት ምድር፥ በተራራማው አገር፥ በቈላውም፥ በዓረባም፥ በቍልቍለቱም፥ በምድረ በዳውም፥ በደቡቡም ያሉ ኬጢያውያን አሞራውያንም ከነዓናውያንም ፌርዛውያንም ኤዊያውያንም ኢያቡሳውያንም የሆኑ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች የመቱአቸው የምድር ነገሥታት እነዚህ ናቸው፤ 9 የኢያሪኮ ንጉሥ፥ በቤቴል አጠገብ ያለችው የጋይ ንጉሥ፥ 10 የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ 11 የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ 12 13 የኦዶላም ንጉሥ፥ የጌዝር ንጉሥ፥ የዳቤር ንጉሥ፥ 14 የጌድር ንጉሥ፥ የሔርማ ንጉሥ፥ 15 የዓራድ ንጉሥ፥ የልብና ንጉሥ፥ የዓዶላም ንጉሥ፥ 16 የመቄዳ ንጉሥ፥ የቤቴል ንጉሥ፥ 17 18 የታጱዋ ንጉሥ፥ የኦፌር ንጉሥ፥ የአፌቅ ንጉሥ፥ 19 የለሸሮን ንጉሥ፥ የማዶን ንጉሥ፥ 20 የአሶር ንጉሥ፥ የሺምሮን ሚሮን ንጉሥ፥ 21 የአዚፍ ንጉሥ፥ የታዕናክ ንጉሥ፥ የመጊዶ ንጉሥ፥ 22 የቃዴስ ንጉሥ፥ በቀርሜሎስ የነበረ የዮቅንዓም ንጉሥ፥ 23 በዶር ኮረብታ የነበረ የዶር ንጉሥ፥ የጌልገላ አሕዛብ ንጉሥ፥ 24 የቲርሳ ንጉሥ፥ ነገሥታቱ ሁሉ ሠላሳ አንድ ናቸው። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 13

1 ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ፤ እግዚአብሔርም አለው። አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤ 2 የቀረችውም ምድር ይህች ናት፥ የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ፥ 3 በግብፅ ፊት ካለው ከሺሖር ወንዝ ጀምሮ በሰሜን በኩል እስካለችው የከነዓናውያን ሆና እስከ ተቈጠረችው እስከ አቃሮን ዳርቻ ድረስ፥ የጋዛ፥ የአዛጦን፥ የአስቀሎና፥ የጌት፥ የአቃሮን፥ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ 4 በደቡብም በኩል የኤዋውያን፥ የከነዓናውያን ምድር ሁሉ፥ ለሲዶናውያንም የምትሆን መዓራ እስከ አሞራውያን ዳርቻ እስከ አፌቅ ድረስ፥ 5 የጌባላውያውንም ምድር፥ በምሥራቅም በኩል ከአርሞንዔም ተራራ በታች ካለችው በኣልጋድ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ያለችው ሊባኖስ ሁሉ፥ 6 በተራራማውም አገር የሚኖሩትን ሁሉ ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ማሴሮን ድረስ ሲዶናውያን ሁሉ፤ እነዚህን ከእስራኤል ልጆች ፊት አባርራቸዋለሁ፤ እንዳዘዝሁህም ምድራቸውን ለእስራኤል ርስት አድርገህ አካፍላቸው። 7 አሁንም ይህን ምድር ለዘጠኙ ነገድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ ክፈለው። 8 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንደ ሰጣቸው ከእርሱ ከምናሴ ጋር የሮቤልና የጋድ ልጆች በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀበሉ። 9 በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር፥ በሸለቆውም መካከል ካለችው ከተማ ጀምሮ የሜድባን ሜዳ ሁሉ እስከ ዲቦን ድረስ፥ 10 በሐሴቦንም የነገሠ የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተሞች ሁሉ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ ድረስ፥ 11 ገለዓድንም፥ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ዳርቻ ሁሉ፥ የአርሞንዔምንም ተራራ ሁሉ፥ 12 ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ፥ በባሳን የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የዐግን መንግሥት ሁሉ፤ እርሱም ከራፋይም የቀረ ነበረ፤ እነዚህንም ሙሴ መታቸው አወጣቸውም። 13 የእስራኤል ልጆች ግን ጌሹራውያንንና ማዕካታውያንን አላወጡም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ጌሹርና ማዕካት በእስራኤል መካከል ይኖራሉ። 14 ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የቀረበው በእሳት የተደረገ መሥዋዕት ርስታቸው ነው፥ እርሱ እንደ ተናገራቸው። 15 ሙሴም ለሮቤል ልጆች ነገድ በየወገናቸው ርስትን ሰጣቸው። 16 ድንበራቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ በሸለቆው መካከል ያለችው ከተማ፥ የሜድባ ሜዳ ሁሉ፥ 17 ሐሴቦንም፥ በሜዳውም ያሉት ከተሞችዋ ሁሉ፥ ዲቦን፥ ባሞትበኣል፥ 18 ቤትበኣልምዖን፥ ያሀጽ፥ ቅዴሞት፥ 19 ሜፍዓት፥ ቂርያታይም፥ ሴባማ፥ በሸለቆውም ተራራ ያለችው ጼሬትሻሐር፥ 20 ቤተ ፌጎር፥ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለው ምድር፥ ቤትየሺሞት፥ 21 የሜዳውም ከተሞች ሁሉ፥ በሐሴቦንም የነገሠው የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ሁሉ ነበረ፤ ሙሴም እርሱንና በምድሪቱ የተቀመጡትን የሴዎንን መሳፍንት፥ የምድያምን አለቆች ኤዊን፥ ሮቆምን፥ ሱርን፥ ሑርን፥ ሪባን መታቸው። 22 ከገደሉአቸውም ሰዎች ጋር የእስራኤል ልጆች ምዋርተኛውን የቢዖርን ልጅ በለዓምን በሰይፍ ገደሉት። 23 የሮቤልም ልጆች ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝና ዳርቻው ነበረ። የሮቤል ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 24 ሙሴም ለጋድ ነገድ ለጋድም ልጆች በየወገኖቻቸው ርስት አድርጎ ሰጣቸው። 25 ድንበራቸውም ኢያዜርና የገለዓድ ከተሞች ሁሉ፥ የአሞንም ልጆች ምድር እኩሌታ በረባት ፊት እስካለችው እስከ አሮዔር ድረስ፥ 26 ከሐሴቦን ጀምሮ እስከ ራማት ምጽጴ፥ እስከ ብጦኒም ድረስ፥ ከመሃናይም ጀምሮ እስከ ዳቤር ዳርቻ ድረስ፥ 27 በሸለቆውም ቤትሀራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮት፥ ጻፎን፥ የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን መንግሥት ቅሬታ ነበረ። ድንበሩም ዮርዳኖስና በምሥራቅ በኩል ባለው በዮርዳኖስ ማዶ የኪኔሬት ባሕር ወዲያኛው ዳርቻ ነበር። 28 የጋድ ልጆች ርስት ከተሞቻቸውም መንደሮቻቸውም በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 29 ሙሴም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት ሰጣቸው፤ ለምናሴም ልጆች ነገድ እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 30 ድንበራቸውም ከመሃናይም ጀምሮ የባሳን ንጉሥ የዐግ መንግሥት፥ ባሳን ሁሉ፥ በባሳንም ያሉት የኢያዕር መንደሮች ሁሉ ስድሳው ከተሞች፥ የገለዓድም እኩሌታ፥ 31 በባሳንም ያሉት የዐግ መንግሥት ከተሞች፥ አስታሮትና ኤድራይ ነበረ። እነዚህም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ልጆች ሆኑ፤ ለማኪር ልጆች እኩሌታ በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 32 ሙሴ በምሥራቅ በኩል በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የከፈለው ርስት ይህ ነው። 33 ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳላቸው ርስታቸው እርሱ ነው።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 14

1 የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር የወረሱት፥ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ የእስራኤልም ልጆች ነገድ የአባቶቻቸው አለቆች ያካፈሉአቸው ርስት ይህ ነው፤ 2 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው በየርስታቸው በዕጣ አካፈሉአቸው። 3 ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ ርስት ሰጥቶ ነበረ፤ ነገር ግን በመካከላቸው ለሌዋውያን ርስት አልሰጣቸውም። 4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም ከሚቀመጡባቸው ከተሞች ለእንስሶቻቸውና ለከብቶቻቸውም ከሚሆን መሰምርያቸው በቀር በምድሩ ውስጥ ድርሻ አልሰጡአቸውም። 5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፥ ምድሪቱንም ተካፈሉ። 6 የይሁዳም ልጆች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ቄኔዛዊውም የዮፎኒ ልጅ ካሌብ አለው። ለአምላክህ ሰው ለሙሴ ስለ እኔና ስለ አንተ እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ የተናገረውን ነገር ታውቃለህ። 7 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድርን እሰልል ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ እኔም በልቤ የነበረውን ቃል መለስሁለት። 8 ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ። 9 ሙሴም በዚያ ቀን። አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም በእርግጥ ርስት ይሆናል ብሎ ማለ። 10 አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። 11 ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፥ ዛሬ ጕልበታም ነኝ፤ ጕልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው። 12 አሁን እንግዲህ በዚያን ቀን እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ተራራማ አገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይሆናል፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ አሳድዳቸዋለሁ። 13 ኢያሱም ባረከው፤ ለዮፎኒም ልጅ ለካሌብ ኬብሮንን ርስት አድርጎ ሰጠው። 14 ስለዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ ዛሬ ለቄኔዛዊው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነች። 15 የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ትባል ነበር፤ ይህም አርባቅ በዔናቅ ሰዎች መካከል ከሁሉ ከፍ ያለ ነበረ። ምድሪቱም ከውጊያ ዐረፈች። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 15

1 ለይሁዳም ልጆች ነገድ በየወገናቸው እስከ ጺን ምድረ በዳ እስከ ደቡብ መጨረሻ እስከ ኤዶምያስ ዳርቻ ድረስ ዕጣ ሆነላቸው። 2 በደቡብም በኩል ያለው ድንበራቸው እስከ ጨው ባሕር መጨረሻ ወደ ደቡብ እስከሚያይ እስከ ባሕር ልሳን ነበረ። 3 ከዚያም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ወጣ፥ ወደ ጺንም አለፈ፥ በቃዴስ በርኔ ወደ ደቡብ በኩል ወጣ፥ በሐጽሮንም በኩል አለፈ፥ ወደ አዳርም ወጣ፥ 4 ወደ ቀርቃ ዞረ፥ ወደ አጽሞንም አለፈ፥ በግብፅም ወንዝ በኩል ወጣ፥ የድንበሩም መውጫ በባሕሩ አጠገብ ነበረ፤ በደቡብ በኩል ያለው ድንበራቸው ይህ ነው። 5 በምሥራቅም በኩል ያለው ድንበር እስከ ጨው ባሕር እስከ ዮርዳኖስም መጨረሻ ነበረ። በሰሜንም በኩል ያለው ድንበር በዮርዳኖስ መጨረሻ እስካለው እስከ ባሕሩ ልሳን ድረስ ነበረ፤ 6 ከዚያም ድንበሩ ወደ ቤትሖግላ ወጣ፥ በቤትዓረባ በሰሜን በኩል አለፈ፥ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወጣ፤ 7 ድንበሩም ከአኮር ሸለቆ ወደ ዳቤር ወጣ፥ በሰሜን በኩል በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት፥ በወንዙ በደቡብ በኩል ወዳለችው ወደ ጌልገላ ተመለከተ፤ ድንበሩም ወደ ቤት ሳሚስ ውኃ አለፈ፥ መውጫውም በዓይንሮጌል አጠገብ ነበረ፤ 8 ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ አጠገብ ኢየሩሳሌም ወደምትባለው ወደ ኢያቡሳዊው ወደ ደቡብ ወገን ወጣ፤ ድንበሩም በራፋይም ሸለቆ ዳር በሰሜን በኩል ባለው በሄኖም ሸለቆ ፊት ለፊት በምዕራብ ወገን ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ወጣ፤ 9 ድንበሩም ከተራራው ራስ ወደ ኔፍቶ ውኃ ምንጭ ደረሰ፥ ወደ ዔፍሮንም ተራራ ከተሞች ወጣ፤ ቂርያትይዓሪም ወደምትባል ወደ በኣላ ደረሰ። 10 ድንበሩም ከበኣላ በምዕራብ በኩል ወደ ሴይር ተራራ ዞረ፤ ክሳሎን ወደምትባል ወደ ይዓሪም ተራራ ወገን በሰሜን በኩል አለፈ፤ ወደ ቤትሳሚስ ወረደ፥ በተምና በኩልም አለፈ። 11 ድንበሩም ወደ አቃሮን ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፤ ወደ ሽክሮን ደረሰ፤ ወደ በኣላ ተራራ አለፈ፥ በየብኒኤል በኩልም ወጣ፤ የድንበሩም መውጫ በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 12 በምዕራቡም በኩል ያለው ድንበር እስከ ታላቁ ባሕርና እስከ ዳርቻው ድረስ ነበረ። ለይሁዳ ልጆች በየወገናቸው በዙሪያው ያለ ድንበራቸው ይህ ነው። 13 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዳዘዘው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ በይሁዳ ልጆች መካከል ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ ድርሻ አድርጎ ሰጠው፤ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። 14 ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ልጆች ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ከዚያ አሳደደ። 15 ከዚያም በዳቤር ሰዎች ላይ ወጣ፤ የዳቤርም ስም አስቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር። 16 ካሌብም። ቂርያትሤፍርን ለሚመታ ለሚይዛትም ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ። 17 የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው። 18 እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው፤ እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ 19 ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት። እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና አሁን ደግሞ የውኃውን ምንጭ ስጠኝ አለችው። እርሱም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጭ ሰጣት። 20 በየወገኖቻቸውም የይሁዳ ልጆች ነገድ ርስት ይህ ነው። 21 በደቡብም በኩል በምድራቸው ዳርቻ አጠገብ እስከ ኤዶምያስ ድንበር ያሉት የይሁዳ ልጆች ነገድ ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ 22 ቀብስኤል፥ ዔዴር፥ ያጉር፥ ቂና፥ 23 ዲሞና፥ ዓድዓዳ፥ ቃዴስ፥ ሐጾር፥ ዪትናን፥ 24 25 ዚፍ፥ ጤሌም፥ በዓሎት፥ ሐጾርሐዳታ፥ ሐጾር የምትባለውም ቂርያትሐጾር፥ 26 27 አማም፥ ሽማዕ፥ ሞላዳ፥ ሓጸርጋዳ፥ ሐሽሞን፥ 28 ቤትጳሌጥ፥ ሐጸርሹዓል፥ ቤርሳቤህ፥ ቢዝዮትያ፥ 29 30 በኣላ፥ ዒዪም፥ ዓጼም፥ ኤልቶላድ፥ 31 ኪሲል፥ ሔርማ፥ ጺቅላግ፥ ማድማና፥ ሳንሳና፥ 32 ልባዎት፥ ሺልሂም፥ ዓይን፥ ሪሞን፤ ሀያዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 33 34 በቈላው ኤሽታኦል፥ ጾርዓ፥ አሽና፥ ዛኖዋ፥ 35 ዓይንገኒም፥ ታጱዋ፥ ዓይናም፥ የርሙት፥ 36 ዓዶላም፥ ሰኰት፥ ዓዜቃ፥ ሽዓራይም፥ ዓዲታይም፥ ግዴራ፥ ግዴሮታይም፤ አሥራ አራት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 37 38 ጽናን፥ ሐዳሻ፥ ሚግዳልጋድ፥ ዲልዓን፥ 39 ምጽጳ፥ ዮቅትኤል፥ ለኪሶ፥ ቦጽቃት፥ 40 41 ኦዶላም፥ ከቦን፥ ለሕማስ፥ ኪትሊሽ፥ ግዴሮት፥ ቤትዳጎን፥ ናዕማ፥ መቄዳ፤ አሥራ ስድስት ከተሞችና መደሮቻቸው። 42 43 ልብና፥ ዔቴር፥ ዓሻን፥ ይፍታሕ፥ አሽና፥ 44 ንጺብ፥ ቅዒላ፥ አክዚብ፥ መሪሳ፤ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 45 አቃሮን ከተመሸጉና ካልተመሸጉ መንደሮችዋ ጋር፤ 46 ከአቃሮንም ጀምሮ እስከ ባሕር ድረስ በአዛጦን አጠገብ ያሉት ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር። 47 አዛጦንና የተመሸጉና ያልተመሸጉ መንደሮችዋም፥ ጋዛና የተመሸጉ ያልተመሸጉም መንደሮችዋ፥ እስከ ግብፅ ወንዝና እስከ ታላቁ ባሕር ዳርቻ ድረስ። 48 በተራራማውም አገር ሳምር፥ የቲር፥ 49 ሶኮ፥ ደና፥ ዳቤር የምትባለው ቂርያትሰና፥ 50 51 ዓናብ፥ ኤሽትሞዓ፥ ዓኒም፥ ጎሶም፥ ሖሎን፥ ጊሎ፤ አሥራ አንድ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 52 53 አራብ፥ ዱማ፥ ኤሽዓን፥ ያኒም፥ ቤትታጱዋ፥ 54 አፌቃ፥ ሑምጣ፥ ኬብሮን የምትባል ቂርያትአርባቅ፥ ጺዖር፤ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 55 56 ማዖን፥ ቀርሜሎስ፥ ዚፍ፥ ዩጣ፥ ኢይዝራኤል፥ 57 ዮቅድዓም፥ ዛኖዋሕ፥ ቃይን፥ ጊብዓ፥ ተምና፤ አሥር ከተሞችና መንደሮቻቸው። 58 59 ሐልሑል፥ ቤትጹር፥ ጌዶር፥ ማዕራት፥ ቤትዓኖት፥ ኤልትቆን፤ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 60 ቂርያትይዓሪም የምትባለው ቂርያትበኣል፥ ረባት፤ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 61 በምድረ በዳ ቤትዓረባ፥ ሚዲን፥ ስካካ፥ 62 ኒብሻን፥ የጨው ከተማ፥ ዓይንጋዲ፤ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 63 በኢየሩሳሌም የተቀመጡትን ኢያቡሳውያንን ግን የይሁዳ ልጆች ሊያሳድዱአቸው አልተቻላቸውም፤ ኢያቡሳውያንም እስከ ዛሬ በይሁዳ ልጆች መካከል በኢየሩሳሌም ውስጥ ተቀምጠዋል።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 16

1 የዮሴፍም ልጆች ዕጣ በኢያሪኮ አጠገብ በምሥራቁ በኩል ካለው ከዮርዳኖስ አንሥቶ በምድረ በዳውና በተራራማው በኩል ከኢያሪኮ ወደ ቤቴል ወጣ፤ 2 ከቤቴል ወደ ሎዛ ወጣ፥ በአርካውያንም ዳርቻ በኩል ወደ አጣሮት አለፈ፥ 3 ወደ ምዕራብም እስከ የፍሌጣውያን ዳርቻ እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ዳርቻ እስከ ጌዝር ድረስ ወረደ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 4 የዮሴፍም ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ወረሱ። 5 የኤፍሬምም ልጆች ድንበር በየወገኖቻቸው እንደዚህ ነበረ፤ በምሥራቅ በኩል የርስታቸው ድንበር አጣሮትአዳር እስከ ላይኛው ቤትሖሮን ድረስ ነበረ፤ 6 ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ ሚክምታት በሰሜን በኩል ወጣ፤ ድንበሩም ወደ ምሥራቅ ወደ ተአናትሴሎ ዞረ፥ ወደ ኢያኖክ በምሥራቅ በኩል አለፈ፥ 7 ከኢያኖክም ወደ አጣሮትና ወደ ነዓራት ወረደ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሰ፥ ወደ ዮርዳኖስም ወጣ። 8 ድንበሩም ከታጱዋ ወደ ምዕራብ እስከ ቃና ወንዝ ድረስ አለፈ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የኤፍሬም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 9 ይኸውም በምናሴ ልጆች ርስት መካከል ለኤፍሬም ልጆች ከተለዩ ከተሞች ጋር፥ ከተሞች ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር፥ ነው። 10 በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላሳደዱአቸውም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ከነዓናውያን በኤፍሬም መካከል ተቀምጠዋል፤ የጕልበት ግብርም ያስገብሩአቸው ነበር። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 17

1 ለምናሴ ነገድ ዕጣ ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ሰልፈኛ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ። 2 ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለአቢዔዝር ልጆች፥ ለኬሌግ ልጆች፥ ለአሥሪኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች፥ ለሸሚዳ ልጆች ሆነ፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ወንዶች ልጆች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው። 3 ለምናሴ ልጅ፥ ለማኪር ልጅ፥ ለገለዓድ ልጅ፥ ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 4 እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው። እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዘዘ አሉ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው። 5 በዮርዳኖስ ማዶ ካለው ከገለዓድና ከባሳን አገር ሌላ ለምናሴ አሥር ዕጣ ሆነ፤ 6 የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆች መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና። 7 የምናሴም ድንበር ከአሴር ጀምሮ በሴኬም ፊት ልፊት እስካለው እስከ ሚክምታት ድረስ ነበረ፤ ድንበሩም በቀኝ በኩል ወደ ዓይንታጱዋ ሰዎች አለፈ። 8 የታጱዋ ምድር ለምናሴ ነበረ፤ በምናሴ ዳርቻ ያለው ታጱዋ ግን ለኤፍሬም ልጆች ሆነ። 9 ድንበሩም ወደ ቃና ወንዝ ከወንዙ በደቡብ ወገን ወረደ፤ በምናሴም ከተሞች መካከል የነበሩት እነዚህ ከተሞች ለኤፍሬም ሆኑ፤ የምናሴም ድንበር በወንዙ በኩል በሰሜን ወገን ነበረ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 10 በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፥ በሰሜንም በኩል ያለው ለምናሴ ነበረ፥ ድንበሩም ባሕሩ ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ደረሰ። 11 በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ ዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ዓይንዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ታዕናክና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ መጊዶና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ሦስቱ ኮረብቶች ለምናሴ ነበሩ። 12 የምናሴ ልጆች ግን የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። 13 የእስራኤልም ልጆች በጸኑ ጊዜ ከነዓናውያንን የጕልበት ግብር አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላሳደዱአቸውም። 14 የዮሴፍ ልጆች ኢያሱን። እኔ ብዙ ሕዝብ ስለ ሆንሁ እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከኝ ለምን አንድ ክፍል አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸኝ? አሉት። 15 ኢያሱም። ብዙ ሕዝብስ ከሆንህ ተራራማውም የኤፍሬም አገር ጠብቦህ እንደ ሆነ ወደ ዱር ወጥተህ በፌርዛውያንና በራፋይም ምድር ለአንተ ስፍራ መንጥር አላቸው። 16 የዮሴፍም ልጆች። ተራራማው አገር አይበቃንም፤ በሸለቆውም ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የብረት ሰረገሎች አላቸው አሉት። 17 ኢያሱም የዮሴፍ ወገን ለሚሆኑ ለኤፍሬምና ለምናሴ። አንተ ብዙ ሕዝብ ነህ፥ ጽኑም ኃይል አለህ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንልህም፤ 18 ነገር ግን ተራራማው አገር ለአንተ ይሆናል፥ ዱር እንኳን ቢሆንም ትመነጥረዋለህ፥ ለአንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው የበረቱም ቢሆኑ ታሳድዳቸዋለህ አላቸው።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 18

1 የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፤ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው። 2 ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። 3 ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ እስከ መቼ ለመግባት ቸል ትላላችሁ? 4 ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፤ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይጽፉታል፤ ወደ እኔም ይመለሳሉ። 5 በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ። 6 እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወዲህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ። 7 ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ እድል ፈንታ የላቸውም፤ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል። 8 ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን። ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ ብሎ አዘዛቸው። 9 ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ። 10 ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው፤ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደ ክፍሎቻቸው ምድሩን ከፈለ። 11 የብንያምም ልጆች ነገድ ዕጣ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ የዕጣቸውም ዳርቻ በይሁዳ ልጆችና በዮሴፍ ልጆች መካከል ወጣ። 12 በሰሜን በኩል ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ጀመረ፤ ድንበሩም ወደ ኢያሪኮ ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፥ ከዚያም በተራራማው አገር ወደ ምዕራብ ወጣ፥ መውጫውም በቤትአዌን ምድረ በዳ ነበረ። 13 ድንበሩም ከዚያ በደቡብ በኩል ቤቴል ወደምትባል ወደ ሎዛ አለፈ፤ ድንበሩም በታችኛው ቤትሖሮን በደቡብ በኩል ባለው ተራራ ወደ አጣሮትአዳር ወረደ። 14 ድንበሩም ወደ ምዕራብ ሄደ፥ በቤትሖሮንም ፊት ለፊት ካለው ተራራ ወደ ደቡብ ዞረ፤ መውጫውም ቂርያትይዓሪም በምትባል በይሁዳ ልጆች ከተማ በቂርያትበኣል ነበረ፤ ይህ የምዕራቡ ዳርቻ ነበረ። 15 የደቡብም ዳርቻ ከቂርያትይዓሪም መጨረሻ ነበረ፤ ድንበሩም በምዕራብ በኩል ወደ ነፍቶ ውኃ ምንጭ ወጣ። 16 ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ፊት ለፊት ወዳለው ተራራ መጨረሻ ወረደ፥ እርሱም በራፋይም ሸሰቆ በሰሜን በኩል ነው፤ ወደ ሄኖም ሸለቆ ወደ ኢያቡስ ዳር በደቡብ በኩል ወረደ፥ ወደ ዓይንሮጌልም ወረደ። 17 ወደ ሰሜንም አለፈ በቤትሳሚስ ምንጭ ላይ ወጣ፥ በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ጌሊሎት ደረሰ፤ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወረደ፤ 18 በሰሜንም ወገን ወደ ዓረባ አጠገብ አለፈ፥ ወደ ዓረባም ወረደ፤ 19 ድንበሩም ወደ ቤትሖግላ ወደ ሰሜን ወገን አለፈ፤ መውጫውም በዮርዳኖስ መጨረሻ በደቡብ በኩል ባለው በጨው ባሕር ልሳን አጠገብ ነበረ፤ ይህ የደቡቡ ዳርቻ ነበረ። 20 በምሥራቅም በኩል ድንበሩ ዮርዳኖስ ነበረ። ይህ በዙርያቸው ዳርቻ በየወገኖቻቸው የብንያም ልጆች ርስት ነበረ። 21 የብንያምም ልጆች ነገድ ከተሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ኢያሪኮ፥ ቤትሖግላ፥ ዓመቀጺጽ፥ 22 ቤትዓረባ፥ ዘማራይም፥ ቤቴል፥ 23 24 ዓዊም፥ ፋራ፥ ኤፍራታ፥ ክፊርዓሞናይ፥ ዖፍኒ፥ ጋባ፤ አሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 25 ገባዖን፥ ራማ፥ ብኤሮት፥ 26 ምጽጳ፥ ከፊራ፥ አሞቂ፥ 27 28 ሬቄም፥ ይርጵኤል፥ ተርአላ፥ ጼላ፥ ኤሌፍ፥ ኢየሩሳሌም የምትባል የኢያቡስ ከተማ፥ ቂርያትጊብዓት፤ አሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የብንያም ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 19

1 ሁለተኛውም ዕጣ ለስምዖን ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ ርስታቸውም በይሁዳ ልጆች ርስት መከከል ነበረ። 2 እነዚህም ርስታቸው ሆኑላቸው፤ ቤርሳቤህ፥ ሤባ፥ ሞላዳ፥ 34 ሐጸርሹዓል፥ ባላ፥ ዔጼም፥ ኤልቶላድ፥ 5 በቱል፥ ሔርማ፥ ጺቅላግ፥ ቤትማርካቦት፥ 6 ሐጸርሱሳ፥ ቤተ ለባኦት፥ ሻሩሔን፤ አሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው፤ 7 ዓይን፥ ሪሞን፥ ዔቴር፥ አሻን፤ አራት ከተሞችና መንደሮቻቸው፤ 8 እስከ ባዕላትብኤርና እስከ ደቡቡ ራማት ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ያሉ መንደሮች ሁሉ። የስምዖን ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ። 9 ከይሁዳ ልጆች ክፍል የስምዖን ልጆች ርስት ሆነ፤ የይሁዳም ልጆች እድል ፈንታ ስለ በዛባቸው የስምዖን ልጆች በርስታቸው መካከል ወረሱ። 10 ሦስተኛውም ዕጣ ለዛብሎን ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ፤ የርስታቸውም ድንበር ወደ ሣሪድ ደረሰ፤ 11 ድንበራቸውም በምዕራብ በኩል ወደ መርዓላ ወጣ፥ እስከ ደባሼትም ደረሰ፤ በዮቅንዓም ፊት ለፊት ወዳለው ወንዝ ደረሰ፤ 12 ከሣሪድም ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ ወደ ኪስሎትታቦር ዳርቻ ዞረ፤ 13 ወደ ዳብራትም ወጣ፥ ወደ ያፊዓም ደረሰ፤ ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ጋትሔፍርና ወደ ዒታቃጺን አለፈ፤ ወደ ሪምንና ወደ ኒዓ ወጣ። 14 ድንበሩም በሰሜን በኩል ወደ ሐናቶን ዞረ፥ መውጫውም በይፍታሕኤል ሸለቆ ነበረ። 15 ቀጣት፥ ነህላል፥ ሺምሮን፥ ይዳላ፥ ቤተ ልሔም፤ አሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 16 የዛብሎን ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። 17 አራተኛውም ዕጣ ለይሳኮር ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ። 18 ድንበራቸውም ወደ ኢይዝራኤል፥ 19 ወደ ከስሎት፥ ወደ ሱነም፥ ወደ ሐፍራይም፥ ወደ ሺኦን፥ ወደ አናሐራት፥ 20 ወደ ረቢት፥ ወደ ቂሶን፥ ወደ አቤጽ፥ 21 ወደ ሬሜት፥ ወደ ዓይንጋኒም፥ ወደ ዓይንሐዳ፥ ወደ ቤትጳጼጽ ደረሰ፤ 22 ድንበሩም ወደ ታቦርና ወደ ሻሕጹማ፥ ወደ ቤትሳሚስ ደረሰ፥ የድንበራቸውም መውጫ ዮርዳኖስ ነበረ፤ አሥራ ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 23 የይሳኮር ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። 24 አምስተኛውም ዕጣ ለአሴር ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ። 25 ድንበራቸውም ሔልቃት፥ ሐሊ፥ ቤጤን፥ አዚፍ፥ 26 አላሜሌክ፥ ዓምዓድ፥ ሚሽአል ነበረ፤ በምዕራብ በኩል ወደ ቀርሜሎስና ወደ ሺሖርሊብናት ደረሰ፤ 27 ወደ ፀሐይም መውጫ ወደ ቤትዳጎን ዞረ፥ ወደ ዛብሎንም ወደ ይፍታሕኤል ሸለቆ፥ በሰሜን በኩል ወደ ቤትዔሜቅና ወደ ንዒኤልም ደረሰ፤ በስተ ግራ በኩልም ወደ ካቡል ወጣ፤ 28 ከዚያም ወደ ዔብሮን፥ ወደ ረአብ፥ ወደ ሐሞን፥ ወደ ቃና እስከ ታላቁ ሲዶናም ደረሰ። 29 ድንበሩም ወደ ራማ፥ ወደ ተመሸገውም ከተማ ወደ ጢሮስ ዞረ፤ ድንበሩም ወደ ሖሳ ዞረ፤ መውጫውም በአክዚብ በኩል ወደ ባሕሩ ነበረ፤ 30 ዑማ፥ አፌቅ፥ ረአብ ደግሞ ነበሩ፤ ሀያ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው። 31 የአሴር ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። 32 ስድስተኛውም ዕጣ ለንፍታሌም ልጆች በየወገኖቻቸው ወጣ። 33 ድንበራቸውም ከሔሌፍ፥ ከጸዕነኒም ዛፍ፥ ከአዳሚኔቄብ፥ ከየብኒኤል እስከ ለቁም ድረስ ነበረ፤ መውጫውም በዮርዳኖስ ነበረ። 34 ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ አዝኖትታቦር ዞረ፥ ከዚያም ወደ ሑቆቅ ወጣ፤ ከዚያም በደቡብ በኩል ወደ ዛብሎን፥ በምዕራብ በኩል ወደ አሴር፥ በዮርዳኖስም በፀሐይ መውጫ ወደ ይሁዳ ደረሰ። 35 የተመሸጉትም ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤ ጺዲም፥ ጼር፥ ሐማት፥ 36 ረቃት፥ ኬኔሬት፥ አዳማ፥ ራማ፥ አሶር፥ 37 38 ቃዴስ፥ ኤድራይ፥ ዓይንሐጾር፥ ይርኦን፥ ሚግዳልኤል፥ ሖሬም፥ ቤትዓናት፥ ቤትሳሚስ፤ አሥራ ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 39 የንፍታሌም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። 40 ሰባተኛውም ዕጣ ለዳን ልጆች ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ። 41 የርስታቸውም ዳርቻ ይህ ነበረ፤ ጾርዓ፥ ኤሽታኦል፥ ዒርሼሜሽ፥ 42 43 ሸዕለቢን፥ ኤሎን፥ ይትላ፥ ኤሎን፥ ተምና፥ 44 አቃሮን፥ ኢልተቄ፥ ገባቶን፥ ባዕላት፥ 45 46 ይሁድ፥ ብኔብረቅ፥ ጋትሪሞን፥ ሜያርቆን፥ በኢዮጴ ፊት ለፊት ካለው ዳርቻ ጋር ራቆን። 47 የዳንም ልጆች ዳርቻ አልበቃቸውም፤ የዳንም ልጆች ከሌሼም ጋር ሊዋጉ ወጡ፥ ያዙአትም፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፥ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም፤ ስምዋንም በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት። 48 የዳን ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው እነዚህ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው። 49 ምድሩንም ሁሉ በየድንበሩ ርስት እንዲሆን ከፍለው ከጨረሱ በኋላ፥ የእስራኤል ልጆች ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በመካከላቸው ርስት ሰጡት። 50 በኤፍሬም ተራራማ አገር ያለችውን ተምናሴራ የምትባለውን የፈለጋትን ከተማ እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጡት፤ ከተማም ሠርቶ ተቀመጠባት። 51 ካህኑ አልዓዛር፥ የነዌም ልጅ ኢያሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ነገዶች የአባቶች አለቆች በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በዕጣ የተካፈሉት ርስት ይህ ነው። ምድሪቱንም መካፈል ጨረሱ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 20

1 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23 ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። ሳይወድድ ሳያውቅም ሰውን የገደለ ገዳይ እንዲሸሽባቸው በሙሴ እጅ የነገርኋችሁን መማፀኛ ከተሞችን ለዩ፤ ከደም ተበቃዩ መማፀኛ ይሆኑላችኋል። 4 ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ይሸሻል፥ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሞ በከተማይቱ ሽማግሌዎች ጆሮ ነገሩን ይናገራል፤ እነርሱም ወደ ከተማይቱ ይቀበሉታል፥ የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል። 5 ደም ተበቃዩ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን በስሕተት ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። 6 በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፤ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፥ ወደ ከተማውም ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣባትም ከተማ ይገባል። 7 በንፍታሌም ባለው በተራራማው አገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው አገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው አገር ኬብሮን የምትባለውን ቂርያትአርባቅን ለዩ። 8 በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ራሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። 9 በማኅበሩ ፊት እስኪቆም ድረስ በደም ተበቃዩ እጅ እንዳይሞት ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በመካከላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተለዩ ከተሞች እነዚህ ናቸው። a

ኢያሱ ወልደ ነዌ 21

1 የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፤ 2 በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ። እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የምንቀመጥባቸውን ከተሞች፥ ለከብቶቻችንም መሰምርያዎች ትሰጡን ዘንድ አዝዞአል ብለው ተናገሩአቸው። 3 የእስራኤልም ልጆች እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ። 4 ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፤ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። 5 ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ አሥር ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። 6 ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። 7 ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ አሥራ ሁለት ከተሞች ሆኑላቸው። 8 እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። 9 ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ። 10 የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። 11 በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰምርያ ሰጡአቸው፤ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። 12 የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። 13 ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፤ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንንና መሰምርያዋን፥ ልብናንና መሰምርያዋን፥ 14 የቲርንና መሰምርያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰምርያዋን፥ 15 ሖሎንንና መሰምርያዋን፥ ዳቤርንና መሰምርያዋን፥ 16 ዓይንንና መሰምርያዋን፥ ዮጣንና መሰምርያዋን፥ ቤትሳሚስንና መሰምርያዋን፤ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። 17 ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰምርያዋን፥ ናሲብንና መሰምርያዋን፥ 18 አናቶትንና መሰምርያዋን፥ አልሞንንና መሰምርያዋን፤ አራት ከተሞችን ሰጡ። 19 የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር አሥራ ሦስት ናቸው። 20 ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ወገኖች ሌዋውያን የዕጣቸው ከተሞች ከኤፍሬም ነገድ ደረሱአቸው። 21 በኤፍሬም ተራራማ አገር ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ሴኬምንና መሰምርያዋን፥ ጌዝርንና መሰምርያዋን፥ 22 ቂብጻይምንና መሰምርያዋን፥ ቤትሖሮንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 23 ከዳንም ነገድ ኤልተቄንና መሰምርያዋን፥ ገባቶንንና መሰምርያዋን፥ ኤሎንንና መሰምርያዋን፥ 24 ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 25 ከምናሴም ነገድ እኩሌታ ታዕናክንና መሰምርያዋን፥ ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 26 የቀሩት የቀዓት ልጆች ወገኖች ከተሞች ሁሉ ከመሰምርያቸው ጋር አሥር ናቸው። 27 ለሌዋውያንም ወገኖች ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ በባሳን ውስጥ የሆነችውን ጎላንንና መሰምርያዋን፥ በኤሽትራንና መሰምርያዋን፤ ሁለቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 28 ከይሳኮርም ነገድ ቂሶንንና መሰምርያዋን፥ ዳብራትንና መሰምርያዋን፥ 29 የርሙትንና መሰምርያዋን፥ ዓይንጋኒምንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 30 ከአሴርም ነገድ ሚሽአልንና መሰምርያዋን፥ ዓብዶንንና መሰምርያዋን፥ 31 ሔልቃትንና መሰምርያዋን፥ ረአብንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 32 ከንፍታሌምም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገሊላ ውስጥ ቃዴስንና መሰምርያዋን፥ ሐሞትዶርንና መሰምርያዋን፥ ቀርታንንና መሰምርያዋን፤ ሦስቱን ከተሞች ሰጡአቸው። 33 የጌድሶን ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው አሥራ ሦስት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር ናቸው። 34 ከሌዋውያንም ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ወገን ከዛብሎን ነገድ ዮቅንዓምንና መሰምርያዋን፥ 35 ቀርታንና መሰምርያዋን፥ ዲሞናንና መሰምርያዋን፥ ነህላልንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 36 ከሮቤልም ነገድ ቦሶርንና መሰምርያዋን፥ ያሀጽንና መሰምርያዋን፥ 37 ቅዴሞትንና መሰምርያዋን፥ ሜፍዓትንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 38 ከጋድም ነገድ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን በገለዓድ ውስጥ ራሞትንና መሰምርያዋን፥ መሃናይምንና መሰምርያዋን፥ 39 ሐሴቦንንና መሰምርያዋን፥ ኢያዜርንና መሰምርያዋን፤ አራቱን ከተሞች ሰጡ። 40 ከሌዋውያን ወገኖች የቀሩት የሜራሪ ልጆች ከተሞች ሁሉ በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ዕጣቸውም አሥራ ሁለት ከተማ ነበረ። 41 በእስራኤል ልጆች ርስት መካከል የነበሩት የሌዋውያን ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞችና መሰምርያቸው ነበሩ። 42 እነዚህም ከተሞች እያንዳንዳቸው ከመሰምርያቸው ጋር ነበሩ፤ እነዚህም ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ነበሩ። 43 እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። 44 እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ከጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 45 እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 22

1 በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። 2 የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤ 3 ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። 4 አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፤ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። 5 ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ። 6 ኢያሱም መረቃቸው፥ ሰደዳቸውም፤ ወደ ቤታቸውም ሄዱ። 7 ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ በባሳን ውስጥ ርስት ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለቀረው ለእኩሌታው ግን ኢያሱ በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ ወገን በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ሰጣቸው። ኢያሱም ወደ ቤታቸው በሰደዳቸው ጊዜ እንዲህ ብሎ መረቃቸው። 8 በብዙ ብልጥግና በእጅግም ብዙ ከብት፥ በብርም፥ በወርቅም፥ በናስም፥ በብረትም፥ በእጅግም ብዙ ልብስ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ የጠላቶቻችሁንም ምርኮ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ። 9 የሮቤልም ልጆች የጋድም ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሄዱ፤ በሙሴም እጅ በተሰጠ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ተቀበሉአት ወደ ርስታቸው ወደ ገለዓድ ምድር ይገቡ ዘንድ በከነዓን ምድር ካለችው ከሴሎ ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ተመለሱ። 10 በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ አቅራቢያም በመጡ ጊዜ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዚያ በዮርዳኖስ አጠገብ ታላቅ መሠዊያ ሠሩ። 11 ለእስራኤልም ልጆች። እነሆ፥ በከነዓን ምድር ዳርቻ በዮርዳኖስ አጠገብ ባለው ግዛት፥ የእስራኤል ልጆች ባሉበት ወገን፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ መሠዊያ ሠርተዋል የሚል ወሬ ደረሰላቸው። 12 የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ወጥተው እነርሱን ሊዋጉ በሴሎ ተሰበሰቡ። 13 የእስራኤልም ልጆች በገለዓድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ላኩ። 14 ከእርሱም ጋር አሥር አለቆች ነበሩ፥ ከእስራኤል ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ የአባቶች ቤት አለቃ፤ እያንዳንዱም በእስራኤል አእላፋት መካከል የእየአባቶቻቸው ቤት አለቃ ነበረ። 15 በገለዓድም ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤል ልጆችና ወደ ጋድ ልጆች ወደ ምናሴም ነገድ እኩሌታ መጡ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩአቸው። 16 የእግዚአብሔር ማኅበር ሁሉ የሚለው ይህ ነው። ይህ በእስራኤል አምላክ ላይ ያደረጋችሁት ኃጢአት ምንድር ነው? ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋል፤ ዛሬም መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል። 17 እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ። 18 እናንተ ዛሬ እግዚአብሔርን ከመከተል ትመለሳላችሁን? ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ብታምፁ ነገ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ይቈጣል። 19 ነገር ግን የርስታችሁ ምድር የረከሰ ቢመስላችሁ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደሚቀመጥበት ወደ እግዚአብሔር ርስት ምድር አልፋችሁ በመካከላችን ውረሱ፤ ከአምላካችንም ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለእናንተ መሠዊያ በመሥራታችሁ በእግዚአብሔርና በእኛ ላይ አታምፁ። 20 የዛራ ልጅ አካን እርም ነገር በመውሰድ ኃጢአትን ስለ ሠራ በእስራኤል ማኅበር ሁሉ ላይ ቍጣ አልወረደምን? እርሱም በኃጢአቱ ብቻውን አልሞተም። 21 የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል አእላፋት አለቆች እንዲህ ብለው መለሱላቸው። 22 የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፥ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር እርሱ አውቆታል፥ እስራኤልም ያውቀዋል፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀንና ተላልፈን እንደ ሆነ ዛሬ አታድነን፤ 23 እግዚአብሔርን ከመከተል እንድንመለስ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህል ቍርባን እንድናሳርግበት፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት እንድናቀርብበት ብለን መሠዊያ ሠርተን እንደ ሆነ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ይበቀለን፤ 24 ይልቁንም ከልባችን ፍርሃት የተነሣ። በሚመጣው ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን። ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ምን አላችሁ? 25 እናንተ የሮቤልና የጋድ ልጆች፥ እግዚአብሔር በእኛና በእናንተ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጎአልና በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም ይሉአቸዋል ብለን ይህን አደረግን። በዚህም ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን ከመፍራት አስተዋቸዋል። 26 ስለዚህም። መሠዊያ እንሥራ አልን፤ ነገር ግን ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት አይደለም፤ 27 ነገር ግን በእኛና በእናንተ መካከል ከእኛም በኋላ በትውልዳችንና በትውልዳችሁ መካከል በሚቃጠል መሥዋዕትና በቍርባን በደኅንነትም መሥዋዕታችን እግዚአብሔርን እናመልክ ዘንድ፥ በሚመጣውም ዘመን ልጆቻችሁ ልጆቻችንን። በእግዚአብሔር ዘንድ እድል ፈንታ የላችሁም እንዳይሉ ምስክር ይሆናል። 28 ስለዚህም አልን። በሚመጣው ዘመን ለእኛ ወይም ለትውልዳችን ይህን ሲሉ፥ እኛ። እነሆ፥ አባቶቻችን ያደረጉትን የእግዚአብሔርን መሠዊያ ምሳሌ እዩ፤ በእኛና በእናንተ መካከል ምስክር ነው እንጂ ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት አይደለም እንላለን። 29 በማደሪያው ፊት ካለው ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መሠዊያ ሌላ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለእህል ቍርባን ለሌላ መሥዋዕትም የሚሆን መሠዊያን የሠራነው በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እግዚአብሔርንም ዛሬ መከተልን ለመተው በማለት እንደ ሆነ ይህ ከእኛ ይራቅ። 30 ካህኑ ፊንሐስና የማኅበሩ አለቆች፥ ከእርሱ ጋር የነበሩት የእስራኤል አእላፋት አለቆች፥ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የምናሴም ልጆች የተናገሩትን ቃል በሰሙ ጊዜ ነገሩ እጅግ ደስ አሰኛቸው። 31 የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች ለምናሴም ልጆች። ይህን መተላለፍ በእግዚአብሔር ላይ አላደረጋችሁምና እግዚአብሔር በመካከላችን እንዳለ ዛሬ እናውቃለን፤ አሁን የእስራኤልን ልጆች ከእግዚአብሔር እጅ አድናችኋል አላቸው። 32 የካህኑም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስና አለቆቹ ከሮቤል ልጆችና ከጋድ ልጆች ዘንድ ከገለዓድ አገር ወደ ከነዓን አገር ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ ወሬም አመጡላቸው። 33 ነገሩም የእስራኤልን ልጆች ደስ አሰኘ፤ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ ከዚያም ወዲያ የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች የተቀመጡባትን ምድር ያጠፉ ዘንድ ወጥተው እንዲወጉአቸው አልተናገሩም። 34 የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም። እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆነ ይህ በመካከላችን ምስክር ነው ሲሉ መሠዊያውን ምስክር ብለው ጠሩት።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 23

1 እንዲህም ሆነ፤ ብዙ ዘመን ከሆነ በኋላ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፈ በኋላ፥ ኢያሱም በሸመገለ በዕድሜውም ባረጀ ጊዜ፥ 2 ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ ሽማግሌዎቻቸውንም አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። እኔ ሸምግያለሁ፥ በዕድሜም አርጅቻለሁ፤ 3 እናንተም አምላካቸሁ እግዚአብሔር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው። 4 እነሆ፥ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ከፈልሁላችሁ። 5 አምላካችሁም እግዚአብሔር እርሱ ከፊታችሁ በብርቱ ይበትናቸዋል፥ ከፊታችሁም ያሳድዳቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁም ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። 6 ስለዚህም በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። 7 በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፤ 8 እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ እንጂ። 9 እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኃይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ አስወጥቶአል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም። 10 አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። 11 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። 12 እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ 13 አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በጎናችሁም መግረፊያ፥ በዓይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያሳድዳቸው ፈጽማችሁ እወቁ። 14 እነሆም፥ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም። 15 አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። 16 አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ስታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ስታመልኩ፥ ስትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።

ኢያሱ ወልደ ነዌ 24

1 ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴኬም ሰበሰበ፥ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች አለቆቻቸውንም ፈራጆቻቸውንም ሹማምቶቻቸውንም ጠራ። እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 2 ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። 3 አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት። 4 ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ። 5 ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው። 6 አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው። 7 ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። 8 እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። 9 የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። 10 እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። 11 ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። 12 በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። 13 ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። 14 አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ። 15 እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። 16 ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ። እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ 17 እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። 18 እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን። 19 ኢያሱም ሕዝቡን። እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። 20 እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። 21 ሕዝቡም ኢያሱን። እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት። 22 ኢያሱም ሕዝቡን። እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ አላቸው፤ እነርሱም። ምስክሮች ነን አሉ። 23 እርሱም። አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ አላቸው። 24 ሕዝቡም ኢያሱን። አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን አሉት። 25 በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው። 26 ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። 27 ኢያሱም ለሕዝቡ። እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል አላቸው። 28 ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ። 29 እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። 30 በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። 31 ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ። 32 የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ያወጡትን የዮሴፍን አጥንት ያዕቆብ ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በግ በገዛው እርሻ በሴኬም ቀበሩት፤ እርሻውም ለዮሴፍ ልጆች ርስት ሆነ። 33 የአሮንም ልጅ አልዓዛር ሞተ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓ መሬት ቀበሩት።

መሣፍንት 1

1 እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። 2 እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ። 3 ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ። 4 ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ። 5 አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው። 6 አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ። 7 አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ። 8 የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት። 9 ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ። 10 ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ። 11 ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ። 12 ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ። 13 የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው። 14 እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት። 15 እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት። 16 የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ። 17 ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት። 18 ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ። 19 እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም። 20 ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ። 21 ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል። 22 የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ። 23 የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር። 24 ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት። 25 የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው። 26 ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው። 27 ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ። 28 እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም። 29 ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ። 30 ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ። 31 አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም። 32 በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ። 33 ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ። 34 አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው። 35 አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም። 36 የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።

መሣፍንት 2

1 የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤ 2 እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤ 3 ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ። 4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ። 5 የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ። 6 ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደ እየርስታቸው ሄዱ። 7 ኢያሱም በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ ለእስራኤልም ያደረገውን ታላቁን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባዩት፥ ከኢያሱ በኋላ በነበሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለኩ። 8 የእግዚአብሔርም ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። 9 በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሔሬስ ቀበሩት። 10 ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ። 11 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ። 12 ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፥ በዙሪያቸውም ካሉት ከአሕዛብ አማልክት ሌሎችን አማልክት ተከተሉ፥ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡ። 13 እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አመለኩ። 14 የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ወደ ማረኩአቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጠላቶቻቸውንም ከዚያ ወዲያ ሊቋቋሙ አልቻሉም። 15 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ። 16 እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፥ ከሚማርኩአቸውም እጅ አዳኑአቸው። 17 ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ አባቶቻቸውም ይሄዱበት ከነበረ መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ አባቶቻቸው ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ታዘዙ እንዲሁ አላደረጉም። 18 እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው። 19 መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ይመለሱ ነበር፥ ሌሎችንም አማልክት በመከተላቸው እነርሱንም በማምለካቸውና ለእነርሱ በመስገዳቸው አባቶቻቸው አድርገውት ከነበረው የከፋ ያደርጉ ነበር፤ የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር። 20 የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ እንዲህም አለ። ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ አባቶቻቸውም እንደ ጠበቁ፥ 21 22 ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም። 23 እግዚአብሔርም እነዚህን አሕዛብ አስቀረ፥ ፈጥኖም አላወጣቸውም፥ በኢያሱም እጅ አሳልፎ አልሰጣቸውም።

መሣፍንት 3

1 2 ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፤ 3 አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን። 4 እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ። 5 የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ። 6 ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። 7 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ። 8 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኵሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት። 9 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው። 10 የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመስጴጦምያን ንጉሥ ኵሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኵሰርሰቴም ላይ አሸነፈች። 11 ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ። 12 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው። 13 የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፥ ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት። 14 የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም አሥራ ስምንት ዓመት ተገዙለት። 15 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ። 16 ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው። 17 ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም ግብሩን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ። 18 ግብሩንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ ግብር የተሸከሙትን ሰዎች ሰደደ። 19 ናዖድ ግን በጌልገላ ከነበሩት ትክል ድንጋዮች ዘንድ ተመልሶ። ንጉሥ ሆይ፥ የምሥጢር ነገር አለኝ አለ፤ ንጉሡም። ዝም በል አለ፤ በዙሪያውም የቆሙት ሁሉ ወጡ። 20 ናዖድም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እርሱም በሰገነት ቤት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም። የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ አለ። ከዙፋኑም ተነሣ። 21 ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤ 22 የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ። 23 ናዖድም ወደ ደርቡ ወጣ፥ የሰገነቱንም ደጅ ዘግቶ ቈለፈው። 24 ናዖድም ከሄደ በኋላ ባሪያዎቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ። ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል አሉ። 25 እስኪያፍሩም ድረስ እጅግ ዘገዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፥ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት። 26 በዘገዩበትም ጊዜያት ናዖድ ሸሸ፥ ትክል ድንጋዮቹንም አለፈ፥ ወደ ቤይሮታም አመለጠ። 27 በመጣም ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው አገር ወረዱ፥ እርሱም በፊታቸው ሄደ። 28 እርሱም። እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተከተሉኝ አላቸው። ተከትለውትም ወረዱ፥ ወደ ሞዓብም የሚያሻግረውን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙ፥ ማንንም አላሳለፉም። 29 የዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፥ ጕልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፥ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም። 30 በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች። 31 ከእርሱም በኋላ የዓናት ልጅ ሰሜጋር ተነሣ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ስድስት መቶ ሰው በበሬ መውጊያ ገደለ፤ እርሱም ደግሞ እስራኤልን አዳነ።

መሣፍንት 4

1 ናዖድም ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ። 2 እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተቀመጠው ሲሣራ ነበረ። 3 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፥ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር። 4 በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች። 5 እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር። 6 ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤ 7 እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፥ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን? አለችው። 8 ባርቅም። አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት። 9 እርሷም። በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች። 10 ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን ወደ ቃዴስ ጠራቸው፥ አሥር ሺህም ሰዎች ተከትለውት ወጡ፤ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ወጣች። 11 ቄናዊውም ሔቤር ከሙሴ አማት ከኦባብ ልጆች ከቄናውያን ተለይቶ ድንኳኑን በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም እስከ ነበረው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ተከለ። 12 የአቢኒኤምም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደ ወጣ ለሲሣራ ነገሩት። 13 ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝቡን ሁሉ ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው። 14 ዲቦራም ባርቅን። እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባርቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ። 15 እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፤ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። 16 ባርቅም ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም። 17 በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ። 18 ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጥታ። ግባ፥ ጌታዬ ሆይ፥ ወደ እኔ ግባ፤ አትፍራ አለችው። ወደ እርስዋም ወደ ድንኳንዋ ገባ፥ በመጐናጸፊያዋም ሸፈነችው። 19 እርሱም። ጠምቶኛልና እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ አላት፤ እርስዋም የወተቱን አቁማዳ ፈትታ አጠጣችው፥ ሸፈነችውም። 20 እርሱም። ከድንኳኑ ደጃፍ ቁሚ፤ ሰውም መጥቶ። በዚህ ሰው አለን? ብሎ ቢጠይቅሽ አንቺ። የለም ትዪዋለሽ አላት። 21 የሔቤርም ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች፥ በእጅዋም መዶሻ ያዘች፥ ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ እንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፥ እርሱም ሞተ። 22 እነሆም፥ ባርቅ ሲሣራን ሲያባርር ኢያዔል ልትገናኘው ወጥታ። ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ አለችው። ወደ እርስዋም ገባ፥ እነሆም፥ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው፥ ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ። v 23 በዚያም ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤል ልጆች ፊት አዋረደ። 24 የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስንም እስኪያጠፉ ድረስ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ ላይ የእስራኤል ልጆች እጅ እየበረታች ሄደች።

መሣፍንት 5

1 በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ። 2 በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ። 3 ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤ እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። 4 አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ። 5 ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ። 6 በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር። 7 አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም። 8 አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም። 9 ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ። 10 በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ። 11 በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤ ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ። 12 ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤ ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ። 13 በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤ እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ። 14 በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ። 15 የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ። 16 መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ። 17 ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ። 18 ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው። 19 ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤ የብር ዘረፋም አልወሰዱም። 20 ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ። 21 ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ። 22 ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ። 23 የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤ እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ። 24 የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን። 25 ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤ በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት። 26 እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም። 27 በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ። 28 ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ። ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች። 29 ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤ እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች። 30 ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ። 31 አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።

መሣፍንት 6

1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። 2 የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ። 3 እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፤ 4 በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፤ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም። 5 እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር። 6 ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 7 እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ 8 እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤ 9 ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤ 10 እናንተንም። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም። 11 የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። 12 የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው። 13 ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው። 14 እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው። 15 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው። 16 እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው። 17 እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፤ 18 ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ። 19 ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት። 20 የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ። 21 የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ። 22 ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ። 23 እግዚአብሔርም። ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም አለው። 24 ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም። እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ። 25 እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት። የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኣል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፤ 26 በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው። 27 ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው። 28 የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፥ እነሆም፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያው ያለውም የማምለኪያ ዐፀድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት። 29 እርስ በርሳቸውም። ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው? ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ። ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው አሉ። 30 የከተማውም ሰዎች ኢዮአስን። የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቈርጦአልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ አሉት። 31 ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ። ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው። 32 ስለዚህም በዚያ ቀን። መሠዊያውን አፍርሶአልና በኣል ከእርሱ ጋር ይምዋገት ብሎ ጌዴዎንን። ይሩበኣል ብሎ ጠራው። 33 ምድያማውያንም አማሌቃውያንም ሁሉ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ሰፈሩ። 34 የእግዚአብሔርም መንፈስ በጌዴዎን ገባበት፥ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ የአቢዔዝርም ሰዎች ተጠርተው በኋላው ተከተሉት። 35 ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ እነርሱም ደግሞ ተጠርተው በኋላው ተከተሉት፤ መልክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ሰደደ፥ እነርሱም ሊገናኙአቸው ወጡ። 36 ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥ 37 እነሆ፥ በአውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ። 38 እንዲሁም ሆነ፤ በነጋውም ማልዶ ተነሣ፥ ጠጕሩንም ጨመቀው፥ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል ቆሬ ሙሉ ውኃ ሆነ። 39 ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እኔ ይህን አንድ ጊዜ ስናገር አትቈጣኝ፤ እኔ ይህን አንድ ጊዜ በጠጕሩ፥ እባክህ፥ ልፈትን፤ አሁንም በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ይሁን፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ይሁን አለው። 40 እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ነበረ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ። a

መሣፍንት 7

1 ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፥ በሐሮድ ምንጭ አጠገብም ሰፈሩ፤ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ። 2 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፤ ስለዚህ እስራኤል። እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም። 3 አሁንም እንግዲህ። የፈራ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ አለው። ከሕዝቡም ሀያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፥ አሥርም ሺህ ቀሩ። 4 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፤ ወደ ውኃ አውርዳቸው፥ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ እኔም። ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም አለው። 5 ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፤ እንዲሁም ሊጠጣ በጕልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው አለው። 6 በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቍጥር ሦስት መቶ ነበረ፤ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጕልበታቸው ተንበረከኩ። 7 እግዚአብሔርም ጌዴዎንን። በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፥ ምድያማውያንንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ አለው። 8 የሕዝቡንም ስንቅና ቀንደ መለከት በእጃቸው ወሰዱ፤ የቀሩትንም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፥ ሦስቱን መቶ ሰዎች ግን በእርሱ ዘንድ ጠበቃቸው፤ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ። 9 በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና ተነሥተህ ወደ ሰፈር ውረድ። 10 አንተም ለመውረድ ብትፈራ አንተ ከሎሌህ ከፉራ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ 11 የሚናገሩትንም ትሰማለህ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትወርድ ዘንድ እጅህ ትበረታለች አለው። እርሱና ሎሌው ፉራ በሰፈሩ ዳርቻ ወደ ነበሩት ሰልፈኞች ወረዱ። 12 ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ሰዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት ቍጥር እንደ ሌለው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ። 13 ጌዴዎንም በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለባልንጀራው ሲያጫውት። እነሆ፥ ሕልም አለምሁ፤ እነሆም፥ አንዲት የገብስ እንጎቻ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ወረደች፥ ወደ ድንኳኑም ደርሳ እስኪወድቅ ድረስ መታችው፥ ገለበጠችውም፥ ድንኳኑም ተጋደመ ይል ነበር። 14 ባልንጀራውም መልሶ። ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፤ እግዚአብሔር ምድያምንና ሠራዊቱን ሁሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል አለው። 15 ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜውን በሰማ ጊዜ ሰገደ፤ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ። እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ አለ። 16 ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮውም ውስጥ ችቦ ሰጠ። 17 እርሱም። እኔን ተመልከቱ፥ እንዲሁም አድርጉ፤ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፤ 18 እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ። ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን በሉ አላቸው። 19 ጌዴዎንም ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት ትጋቱም በተጀመረ ጊዜ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፥ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮች ሰባበሩ። 20 ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፥ ማሰሮችንም ሰበሩ፥ በግራ እጃቸውም ችቦችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ። የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ ብለው ጮኹ። 21 ሁሉም በየቦታው በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፥ ጮኸ፥ ሸሸም። 22 ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶች ነፉ፥ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራውና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፤ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሺጣ ድረስ በጠባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልምሖላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። 23 የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ። 24 ጌዴዎንም። ምድያምን ለመገናኘት ውረዱ፥ እስከ ቤትባራም ድረስ ያለውን ውኃ፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙባቸው ብሎ መልክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ተራራማ አገር ሁሉ ሰደደ። የኤፍሬም ሰዎችም ሁሉ ተሰብስበው እስከ ቤትባራ ድረስ ውኃውን፥ ዮርዳኖስን፥ ያዙ። 25 የምድያምን ሁለቱን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን ያዙ፤ ሔሬብንም በሔሬብ ዓለት አጠገብ ገደሉት፥ ዜብንም በዜብ መጥመቂያ ላይ ገደሉት፤ ምድያምንም አሳደዱ፥ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ጌዴዎን መጡ።

መሣፍንት 8

1 የኤፍሬም ሰዎች። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም? አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት። 2 እርሱም። እኔ ካደረግሁት እናንተ ያደረጋችሁት አይበልጥምን? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዝር ወይን መከር አይሻልምን? 3 እግዚአብሔር የምድያምን መኳንንት ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፤ እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖሮአል? አላቸው። ይህን በተናገረ ጊዜ ቍጣቸው በረደ። 4 ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ፤ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር። 5 የሱኮትንም ሰዎች። የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ሳሳድድ፥ ደክመዋልና እኔን ለተከተሉ ሕዝብ እንጀራ፥ እባካችሁ፥ ስጡ አላቸው። 6 የሱኮትም አለቆች። እኛ ለሠራዊትህ እንጀራ እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? አሉ። 7 ጌዴዎንም። እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ሲሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኵርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ አለ። 8 ከዚያም ወደ ጵኒኤል ወጣ፥ ለጵኒኤልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የጵንኤልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት። 9 እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች ደግሞ። በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ ብሎ ተናገራቸው። 10 ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ አሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። 11 ጌዴዎንም የድንኳን ተቀማጮች ባሉበት መንገድ በኖባህና በዮግብሃ በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ነበርና ሠራዊቱን መታ። 12 ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፥ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፥ ሠራዊቱንም ሁሉ አስደነገጠ። 13 የኢዮአስ ልጅም ጌዴዎን ከሔሬስ ዳገት ከሰልፍ ተመለሰ። 14 ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ ጠየቀው፤ እርሱም የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎች ሰባ ሳባት ሰዎች ጻፈለት። 15 ወደ ሱኮትም ሰዎች መጥቶ። ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥ አለ። 16 የከተማይቱንም ሽማግሌዎች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኵርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው። 17 የጵኒኤልንም ግንብ አፈረሰ፥ የከተማይቱንም ሰዎች ገደላቸው። 18 ዛብሄልንና ስልማናን። በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ? አላቸው። እነርሱም። እንደ አንተ ያሉ ነበሩ፥ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ንጉሥ ልጆች መልክ ነበረ ብለው መለሱለት። 19 እርሱም። የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር አለ። 20 በኵሩንም ዬቴርን። ተነሥተህ ግደላቸው አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ብላቴና ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21 ዛብሄልና ስልማናም። የሰው ኃይሉ እንደ ሰውነቱ ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፥ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ። 22 የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን። ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ ልጅህም የልጅ ልጅህም ደግሞ ግዙን አሉት። 23 ጌዴዎንም። እኔ አልገዛችሁም፥ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል አላቸው። 24 እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን። ሁላችሁ ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ አላቸው። 25 እነርሱም። ፈቅደን እንሰጥሃለን ብለው መለሱለት። መጎናጸፊያም አነጠፉ፥ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ። 26 የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ፥ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ፥ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ። 27 ጌዴዎንም ኤፉድ አድርጎ አሠራው፥ በከተማውም በዖፍራ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎት አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። 28 ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረደ፥ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች። 29 የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። 30 ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከወገቡ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። 31 በሴኬምም የነበረችው ቁባቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፥ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። 32 የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፥ በአቢዔዝራውያንም ከተማ በዖፍራ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ። 33 እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፥ በኣሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ። 34 የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤ 35 እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ለጌዴዎን ለይሩበኣል ቤት ወረታ አላደረጉም።

መሣፍንት 9

1 የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሴኬም ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፥ ለእነርሱም ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ። 2 በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ። ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ደግሞ እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ ብሎ ተናገራቸው። 3 የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሴኬም ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፤ እነርሱም። እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን ለመከተል ልባቸውን አዘነበሉት። 4 ከበኣልብሪትም ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ምናምንቴዎችንና ወሮበሎችን ቀጠረበት፥ እነርሱም ተከተሉት። 5 ወደ አባቱም ቤት ወደ ዖፍራ ሄደ፤ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ አረዳቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ። 6 የሴኬምም ሰዎች ሁሉ ቤትሚሎም ሁሉ ተሰበሰቡ፥ ሄደውም በሴኬም በዓምዱ አጠገብ ባለው በአድባሩ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ። 7 ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፥ ድምፁንም አንሥቶ ጮኸ፥ እንዲህም አላቸው። የሴኬም ሰዎች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲሰማችሁ ስሙኝ። 8 አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ጌዱ፤ ወይራውንም። በእኛ ላይ ንገሥ አሉት። 9 ወይራው ግን። እግዚአብሔርና ሰዎች በእኔ የሚከበሩበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 10 ዛፎችም በለሱን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 11 በለሱ ግን። ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 12 ዛፎችም ውይኑን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 13 ወይኑም። እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን ትቼ በዛፎች ላይ እንድሰፍፍ ልሂድ? አላቸው። 14 ዛፎችም ሁሉ እሾህን። መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 15 እሾሁም ዛፎችን። በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ታነግሡኝ እንደ ሆነ ኑ ከጥላዬ በታች ተጠጉ። እንዲሁም ባይሆን እሳት ከእሾህ ይውጣ፥ የሊባኖስንም ዝግባ ያቃጥል አላቸው። 16 አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ እንዳደረገውም መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ 17 አባቴ ስለ እናንተ ተጋድሎ ነበርና፥ ከምድያምም እጅ ሊያድናችሁ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶ ነበርና፥ 18 እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋልና፥ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ አርዳችኋልና፥ ወንድማችሁም ስለ ሆነ የባሪያይቱን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ሰዎች ላይ አንግሣችኋልና፥ 19 እንግዲህ ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፥ እርሱ ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤ 20 እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ይውጣ፥ የሴኬምንም ሰዎች ቤትሚሎንም ይብላ፤ ከሴኬምም ሰዎች ከቤትሚሎም እሳት ይውጣ፥ አቤሜሌክንም ይብላ። 21 ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፥ በዚያም ተቀመጠ። 22 አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ። 23 እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሴኬምም ሰዎች በአቤሜሌክ ላይ ተንኰል አደረጉ። 24 ይህም የሆነው፥ በሰባ የይሩበኣል ልጆቹ ላይ የተደረገው ዓመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሴኬም ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው። 25 የሴኬምም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፥ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፤ አቤሜሌክም ይህን ወሬ ሰማ። 26 የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጥቶ ወደ ሴኬም ገባ፤ የሴኬምም ሰዎች ታመኑበት። 27 ወደ እርሻውም ወጡ ወይናቸውንም ለቀሙ፥ ጠመቁትም፥ የደስታም በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፥ በሉም ጠጡም፥ አቤሜሌክንም ሰደቡ። 28 የአቤድም ልጅ ገዓል። የምንገዛለት አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድርነው? እርሱ የይሩብኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልም የእርሱ ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ 29 ስለ ምንስ ለዚህ እንገዛለን? ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር አለ። አቤሜሌክንም። ሠራዊትህን አብዝተህ ና፥ ውጣ አለው። 30 የከተማይቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 31 እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ በተንኰል መልክተኞች ላከ። እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተዋል፥ በአንተም ላይ ከተማይቱን አሸፍተዋል። 32 አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፥ በሜዳም ሸምቁ፤ 33 ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፥ በከተማይቱም ላይ ውደቅባት፤ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት። 34 አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፥ በሴኬምም አቅራቢያ በአራት ወገን ሸመቁበት። 35 የአቤድም ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማይቱ በር አደባባይ ቆመ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ ከሸመቁበት ስፍራ ተነሱ። 36 ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን። እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል አለው። ዜቡልም። ሰዎች የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ አለው። 37 ገዓልም ደግሞ። እነሆ፥ ሕዝብ በምድር መካከል ይወርዳል፤ አንድም ወገን በምዖንኒም በአድባሩ ዛፍ መንገድ ይመጣል ብሎ ተናገረ። 38 ዜቡልም። እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ አለው። 39 ገዓልም በሴኬም ሰዎች ፊት ወጣ፥ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ። 40 አቤሜሌክም አሳደደው፤ በፊቱም ሸሸ፥ እስከ በሩም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ። 41 አቤሜሌክም በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሴኬም እንዳይኖሩ አሳደዳቸው። 42 በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፤ አቤሜሌክም ሰማ። 43 ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፥ በሜዳም ሸመቀ፤ ተመለከተም፥ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፥ ተነሣባቸውም መታቸውም። 44 አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ወገኖች ተጣደፉ በከተማይቱም በር አደባባይ ቆሙ፤ ሁለቱም ወገኖች በእርሻው ውስጥ በነበሩት ሁሉ ላይ ሮጡባቸው፥ መቱአቸውም። 45 አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማይቱ ጋር ተዋጋ፤ ከተማይቱንም ይዞ በእርሷ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፤ ከተማይቱንም አፈረሰ፥ ጨውም ዘራባት። 46 በሴኬምም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ ኤልብሪት ቤት ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ። 47 አቤሜሌክም በሴኬም ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ሰማ። 48 አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፥ አንሥቶም በጫንቃው ላይ አደረገው፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ። እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ አላቸው። 49 ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፥ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፥ ምሽጉንም በላያቸው አቃጠሉት፤ የሴኬምም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ። 50 አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ መጣ፥ ቴቤስንም ከብቦ ያዛት። 51 በከተማይቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፥ የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፥ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ። 52 አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ቀርቦ ይዋጋ ነበር፥ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ደረሰ። 53 አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፥ አናቱንም ሰበረችው። 54 እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ። እኔን። ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ አለው፤ ጕልማሳውም ወጋው፥ ሞተም። 55 የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ። 56 እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት። 57 እግዚአብሔርም የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፤ የይሩበኣልም ልጅ የኢዮአታም እርግማን ደረሰባቸው።

መሣፍንት 10

1 ከአቤሜሌክም በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ተቀምጦ ነበር። 2 በእስራኤልም ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፤ ሞተም፥ በሳምርም ተቀበረ። 3 ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፥ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ። 4 በሠላሳ የአህያ ግልገሎች ይቀመጡ የነበሩ ሠላሳ ልጆችም ነበሩት፤ ለእነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች የተባሉ በገለዓድ ምድር ያሉ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው። 5 ኢያዕርም ሞተ፥ በቃሞንም ተቀበረ። 6 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም። 7 የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 8 በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፤ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው። 9 የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ። 10 የእስራኤልም ልጆች። አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥ 12 ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ። 13 እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፤ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም። 14 ሄዳችሁም የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፤ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ። 15 የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን። እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፤ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት። 16 ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጕስቍልና አዘነች። 17 የአሞንም ልጆች ተሰብስበው በገለዓድ ሰፈሩ። የእስራኤልም ልጆች ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ። 18 ሕዝቡም፥ የገለዓድ አለቆች፥ እርስ በእርሳቸው። ከአሞን ልጆች ጋር መዋጋት የሚጀምር ማን ነው? እርሱ በገለዓድ ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል አሉ። a

መሣፍንት 11

1 ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ። 2 የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፤ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን። የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት። 3 ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፤ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት። 4 ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር። 5 የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ። 6 ዮፍታሔንም። ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት። 7 ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። 8 የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፤ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት። 9 ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው። 10 የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፤ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት። 11 ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፤ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ። 12 ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ። አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ። 13 የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው። 14 ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥ 15 እንዲህም አለው። ዮፍታሔ እንዲህ ይላል። እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፤ 16 ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥ 17 እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ። በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፤ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም። 18 እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፤ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም። 19 እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም። በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው። 20 ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። 21 የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፤ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ። 22 ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ። 23 የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፤ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን? 24 አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን። 25 ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን? 26 እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር? 27 እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ። 28 ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም። 29 የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፤ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ። 30 ዮፍታሔም። በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥ 31 ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ። 32 ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው። 33 ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ። 34 ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፤ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፤ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም። 35 እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት። 36 እርስዋም። አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው። 37 አባትዋንም። ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው። 38 እርሱም። ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፤ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች። 39 ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር። 40 የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።

መሣፍንት 12

1 የኤፍሬም ሰዎች ተሰበሰቡ፥ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለ ምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን አሉት። 2 ዮፍታሔም። ከአሞን ልጆች ጋር ለእኔና ለሕዝቤ ጽኑ ጠብ ነበረን፤ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም። 3 እንዳላዳናችሁኝም ባየሁ ጊዜ ነፍሴን በእጄ አድርጌ በአሞን ልጆች ላይ አለፍሁ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። 4 ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም። ገለዓዳውያን ሆይ፥ እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁት ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ። 5 ገለዓዳውያንም ኤፍሬም የሚያልፍበትን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ያዙባቸው፤ የሸሸም የኤፍሬም ሰው። ልለፍ ባለ ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች። አንተ ኤፍሬማዊ ነህን? አሉት፤ እርሱም። አይደለሁም ቢል፥ 6 እነርሱ። አሁን ሺቦሌት በል አሉት፤ እርሱም አጥርቶ መናገር አልቻለምና። ሲቦሌት አለ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሻገሪያ አረዱት፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ። 7 ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ስድስት ዓመት ፈረደ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፥ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ። 8 ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 9 ሠላሳም ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ አገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ አገር ሴቶች ልጆችን አመጣ። በእስራኤልም ላይ ሰባት ዓመት ፈረደ። 10 ኢብጻንም ሞተ፥ በቤተ ልሔምም ተቀበረ። 11 ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ አሥር ዓመት ፈረደ። 12 ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፥ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ። 13 ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 14 አርባም ልጆች ሠላሳም የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በሰባም አህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈረደ። 15 የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፥ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በጲርዓቶን ተቀበረ። a

መሣፍንት 13

1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። 2 ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም። 3 የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት። እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4 አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። 5 እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል። 6 ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ። አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም። 7 እርሱም። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች። 8 ማኑሄም። ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። 9 እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም። 10 ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም። እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ ብላ ነገረችው። 11 ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፥ ወደ ሰውዮውም መጥቶ። ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ። 12 ማኑሄም። ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድር ነው? የምናደርግለትስ ምንድር ነው? አለው። 13 የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። ሴቲቱ ከነገርኋፅት ሁሉ ትጠንቀቅ። 14 ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፥ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፥ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ አለው። 15 ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ቆይ አለው። 16 የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን። አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17 ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ። ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው? አለው። 18 የእግዚአብሔርም መልአክ። ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ? አለው። 19 ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። 20 ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ። 21 የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ። 22 ማኑሄም ሚስቱን። እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን አላት። 23 ሚስቱም። እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር አለችው። 24 ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ እግዚአብሔርም ባረከው። 25 የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።

መሣፍንት 14

1 ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። 2 ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ። በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው። 3 አባቱና እናቱም። ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን። ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው። 4 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ፤ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም። በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ። 5 ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ። 6 የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም። 7 ወርዶም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ደስ አሰኘችው። 8 ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፥ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፥ ማርም ነበረበት። 9 በእጁም ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ መጣ፥ ማሩንም ሰጣቸው፥ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው ሬሳ ውስጥ እንደ ወሰደ አልነገራቸውም። 10 አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጎበዞችም እንዲህ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ በዓል አደረገ። 11 ባዩትም ጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ሰዎች ሰጡት። 12 ሶምሶንም። እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤ 13 መፍታትም ባትችሉ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ አላቸው። እነርሱም። እንድንሰማው እንቆቅልሽህን ንገረን አሉት። 14 እርሱም። ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፥ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም። 15 በአራተኛውም ቀን የሶምሶንን ሚስት። እንቈቅልሹን እንዲነግረን ባልሽን ሸንግዪው፥ አለዚያም እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወደዚህ ጠራችሁን ልትገፉን ነውን? አሉአት። 16 የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰች። በእውነት ጠልተኸኛል፥ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች እንቈቅልሽ ሰጥተሃቸዋልና ትርጓሜውንም አልነገርኸኝም አለችው። እርሱም። እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፥ ለአንቺ እነግርሻለሁን? አላት። 17 ሰባቱንም የበዓል ቀን በፊቱ አለቀሰች፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ትርጓሜውንም ለሕዝብዋ ልጆች ነገረች። 18 በሰባተኛውም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማይቱ ሰዎች። ከማር የሚጣፍጥ ምንድር ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው? አሉት። እርሱም። በጥጃዬ ባላረሳችሁ የእንቈቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ ነበር አላቸው። 19 የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ በኃይል ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፥ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፥ ልብሳቸውንም ወስዶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጠ። ቍጣውም ነደደ፥ ወደ አባቱም ቤት ወጣ። 20 የሶምሶን ሚስት ግን ከተባበሩት ከሚዜዎቹ ለአንደኛው ሆነች። a

መሣፍንት 15

1 ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና። ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፤ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው። 2 አባትዋም። ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋፅት፤ ታናሽ እኅትዋ ከርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት አለው። 3 ሶምሶንም። ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ አላቸው። 4 ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፥ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ። 5 ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ። 6 ፍልስጥኤማውያንም። ይህን ያደረገው ማን ነው? አሉ። እነርሱም። ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ። 7 ሶምሶንም። እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፥ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ አላቸው። 8 እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ። 9 ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፥ በይሁዳም ሰፈሩ፥ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ። 10 የይሁዳም ሰዎች። በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድር ነው? አሉ። እነርሱም። ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል አሉ። 11 ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን። ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድር ነው? አሉት። እርሱም። እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው አላቸው። 12 እነርሱም። አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል አሉት። ሶምሶንም። እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ አላቸው። 13 እነርሱም። አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት። 14 ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ። 15 አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፥ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፥ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። 16 ሶምሶንም። በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ አለ። 17 መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ራማትሌሒ ብሎ ጠራው። 18 እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና። አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፥ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 19 እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፥ ከእርሱም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፥ ነፍሱም ተመለሰች፥ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ዓይንሀቆሬ ብሎ ጠራው፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ። 20 በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ።

መሣፍንት 16

1 ሶምሶንም ወደ ጋዛ ሄደ፥ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርስዋ ገባ። 2 የጋዛ ሰዎችም ሶምሶን ወደ ከተማ ውስጥ እንደ ገባ ሰሙ፥ ከበቡትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ በከተማይቱ በር ሸመቁበት። ማለዳ እንገድለዋለን ብለውም ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ። 3 ሶምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ተኛ፤ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሥቶ የከተማይቱን በር መዝጊያ ያዘ፥ ከሁለቱ መቃኖችና ከመወርወሪያውም ጋር ነቀለው፥ በትከሻውም ላይ አደረገ፥ በኬብሮንም ፊት ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ በዚያም ጣለው። 4 ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ። 5 የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው። እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት። 6 ደሊላም ሶምሶንን። ታላቅ ኃይልህ በምን እንደ ሆነ፥ እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው። 7 ሶምሶንም። በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት። 8 የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ሰባት ያልደረቀ እርጥብ ጠፍር አመጡላት፥ በእርሱም አሰረችው። 9 በጓዳዋም ውስጥ ሰዎች ተደብቀው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። እርሱም የተልባ እግር ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፤ ኃይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም። 10 ደሊላም ሶምሶንን። እነሆ፥ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሀሰት ነው፤ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው። 11 እርሱም። ሥራ ባልተሠራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት። 12 ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ በእርሱ አሰረችው፤ በጓዳዋም የተደበቁ ሰዎች ተቀምጠው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ገመዱንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። 13 ደሊላም ሶምሶንን። እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ ንገረኝ አለችው። እርሱም። የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ብትጐነጕኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት። 14 ሶምሶንም በተኛ ጊዜ ደሊላ የራሱን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፥ በችካልም ቸከለችውና። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፥ ችካሉንም ከነቆንዳላው ድሩንም ነቀለ። 15 እርስዋም። አንተ። እወድድሻለሁ እንዴት ትለኛለህ፥ ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም? ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኃይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም አለችው። 16 ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች። 17 እርሱም። ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደክማለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት። 18 ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ገለጠላት ባየች ጊዜ። የልቡን ሁሉ ገልጦልኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መኳንንት ጠራች። የፍልስጥኤማውያን መኳንንትም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ። 19 እርስዋም በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው፤ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ። 20 እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ። እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም። 21 ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። 22 የራሱም ጠጕር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር። 23 የፍልስጥኤምም መኳንንት። አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ። 24 ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ። ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ። 25 ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ። በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት አሉ። ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፥ በፊታቸውም ተጫወተ፤ ተዘባበቱበትም፥ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት። 26 ሶምሶንም እጁን የያዘውን ብላቴና። ቤቱን የደገፉትን ምሰሶች እጠጋባቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ አስይዘኝ አለው። 27 በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፥ የፍልስጥኤምም መኳንንት ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። 28 ሶምሶንም። ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ። 29 ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶች ያዘ፤ አንዱን በቀኝ እጁ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ተጠጋባቸው። 30 ሶምሶንም። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት አለ፤ ተጎንብሶም ምሰሶቹን በሙሉ ኅይሉ ገፋ፥ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ። 31 ወንድሞቹም የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፥ ይዘውም አመጡት፤ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት። እርሱም በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ። a

መሣፍንት 17

1 በተራራማውም በኤፍሬም አገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 2 እናቱንም። ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው። 3 አንዱን ሺህ አንዱን መቶ ብርም መለሰላት፤ እናቱም። ይህን ብር የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ አለች። 4 ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወስዳ ለአንጥረኛ ሰጠችው፥ እርሱም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። ያም በሚካ ቤት ነበረ። 5 ሰውዮውም ሚካ የአምላክ ቤት ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፥ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፥ ካህንም ሆነለት። 6 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። 7 በቤተ ልሔም ይሁዳም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ በዚያም ይቀመጥ ነበር። 8 ይህም ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወጣ፤ ሲሔድም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ። 9 ሚካም። ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። ከቤተ ልሔም ይሁዳ የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ አለው። 10 ሚካም። ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በእየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ አለው። ሌዋዊውም ገባ። 11 ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር መቀመጥን ፈቀደ፤ ጕልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12 ሚካም ሌዋዊውን ቀደሰ፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ። 13 ሚካም። ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ አለ።

መሣፍንት 18

1 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም። እስከዚያም ቀን ድረስ ለዳን ነገድ በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስት አልደረሳቸውም ነበርና በዚያ ዘመን የሚቀመጡባት ርስት ይሹ ነበር። 2 የዳንም ልጆች ከወገናቸው አምስት ጽኑዓን ሰዎች ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ። ሂዱ ምድሪቱንም ሰልሉ ብለው ከጾርዓና ከኤሽታኦል ሰደዱ። እነዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። 3 በሚካ ቤት አጠገብም በነበሩ ጊዜ የሌዋዊውን የጕልማሳውን ድምፅ አወቁ፤ ወደ እርሱም ቀርበው። ወደዚህ ማን አመጣህ? በዚህስ የምታደርገው ምንድር ነው? በዚህስ ምን አለህ? አሉት። 4 እርሱም። ሚካ እንዲህ እንዲህ አደረገልኝ፥ ቀጠረኝም፥ እኔም ካህን ሆንሁለት አላቸው። 5 እነርሱም። የምንሄድበት መንገድ የቀና መሆኑን እናውቅ ዘንድ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅልን አሉት። 6 እርሱም። የምትሄዱበት መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና በደኅና ሂዱ አላቸው። 7 አምስቱም ሰዎች ሄዱ ወደ ሌሳም መጡ፥ በውስጡም የነበሩትን ሕዝብ ተዘልለው አዩአቸው፥ አንደ ሲዶናውያንም ልማድ ጸጥ ብለው ተዘልለው ተቀምጠው ነበር፤ የሚያስቸግራቸውም የሚገዛቸውም አልነበረም፥ ከሲዶናውያንም ርቀው ከሰውም ሁሉ ተለይተው ለብቻቸው ይኖሩ ነበር። 8 ወደ ወንድሞቻቸውም ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል ተመለሱ፤ ወንድሞቻቸውም። ምን ወሬ ይዛችኋል? አሉአቸው። 9 እነርሱም ምድሪቱን እግጅ መልካም እንደ ሆነች አይተናልና ተነሡ፥ በእነርሱ ላይ እንውጣ፤ እናንተ ዝም ትላላችሁን? ትሄዱ ዘንድ ምድሪቱንም ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ቸል አትበሉ። 10 በሄዳችሁ ጊዜ ተዘልለው ወደ ተቀመጡ ሕዝብ ትደርሳላችሁ፥ ምድሪቱም ሰፊ ናት፤ እግዚአብሔርም በምድር ካለው ነገር ሁሉ አንዳች የማይጎድልበትን ስፍራ በእጃችሁ ሰጥቶአል አሉ። 11 ከዳን ወገንም የጦር ዕቃ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከዚያ ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሥተው ሄዱ። 12 ወጥተውም በይሁዳ ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር ተብሎ ተጠራ፤ እነሆም፥ ከቂርያትይዓሪም በስተ ኋላ ነው። 13 ከዚያም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር አለፉ፤ ወደ ሚካም ቤት መጡ። 14 የሌሳን ምድር ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎችም ወንድሞቻቸውን። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ኤፉድና ተራፊም፥ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስልም እንዳሉ ታውቃላችሁን? አሁንም የምታደርጉትን ምከሩ ብለው ተናገሩአቸው። 15 ከመንገዱም ፈቀቅ ብለው ጕልማሳው ሌዋዊ ወደ ነበረበት ወደ ሚካ ቤት መጡ፥ ደኅንነቱንም ጠየቁት። 16 የጦር ዕቃ የታጠቁት፥ ከዳን ልጆችም የሆኑት ስድስቱ መቶ ሰዎች በደጃፉ አጠገብ ቆመው ነበር። 17 ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሄደው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ወጥተው ወደዚያ ገቡ፤ የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም ወሰዱ፤ ካህኑም የጦር ዕቃ ከታጠቁት ከስድስት መቶ ሰዎች ጋር በደጃፉ አጠገብ ቆሞ ነበር። 18 እነዚህም ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስል ኤፉዱንም ተራፊሙንም ቀልጦ የተሠራውን ምስልም በወሰዱ ጊዜ፥ ካህኑ። ምን ታደርጋላችሁ? አላቸው። 19 እነርሱም። ዝም በል፥ እጅህንም በአፍህ ላይ ጫን፥ ከእኛም ጋር መጥተህ አባትና ካህን ሁንልን፤ ለአንድ ሰው ቤት ካህን መሆን ወይስ በእስራኤል ዘንድ ለነገድና ለወገን ካህን መሆን ማናቸው ይሻልሃል? አሉት። 20 ካህኑም በልቡ ደስ አለው፥ ኤፉዱንም ተራፊሙንም የተቀረጸውንም ምስል ወሰደ፥ በሕዝቡም መካከል ሄደ። 21 እነርሱም ዞረው ሄዱ፥ ሕፃናቶችንና ከብቶችን ዕቃዎችንም በፊታቸው አደረጉ። 22 ከሚካም ቤት በራቁ ጊዜ የሚካ ጐረቤቶች ተሰበሰቡ፥ የዳንም ልጆች ተከትለው ደረሱባቸው። 23 ወደ ዳንም ልጆች ጮኹ፥ የዳንም ልጆች ፊታቸውን መልሰው ሚካን። የምትጮኸው ምን ሆነህ ነው? አሉት። 24 እርሱም። የሠራኋቸውን አማልክቴን ካህኑንም ይዛችሁ ሄዳችኋል፤ ሌላ ምን አለኝ? እናንተስ። ምን ሆነሃል እንዴት ትሉኛላችሁ? አለ። 25 የዳንም ልጆች። የተቈጡ ሰዎች እንዳይወድቁብህ ነፍስህም የቤተ ሰቦችህም ነፍስ እንዳይጠፋብህ፥ ድምፅህን በእኛ መካከል አታሰማ አሉት። 26 የዳንም ልጆች መንገዳቸውን ሄዱ፤ ሚካም ከእርሱ እንደ በረቱ ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ። 27 እነርሱም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ለእርሱ የነበረውን ካህን ይዘው ወደ ሌሳ፥ ጸጥ ብሎ ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ፥ መጡ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት። 28 ከተማይቱ ከሲዶና ራቅ ያለች ነበረችና፥ እነርሱም ከሌሎች ሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ይኖሩ ነበርና የሚታደግ አልነበራቸውም። ሌሳም በቤትሮዖብ አጠገብ ባለች ሸለቆ ውስጥ ነበረች። ከተማይቱንም ሠርተው ተቀመጡባት። 29 ከተማይቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ የከተማይቱም ስም አስቀድሞ ሌሳ ነበረ። 30 የዳንም ልጆች የተቀረጸውን ምስል ለራሳቸው አቆሙ፤ የሙሴም ልጅ የጌርሳም ልጅ ዮናታን፥ እርሱና ልጆቹ የአገሩ ሰዎች እስከሚማረኩበት ቀን ድረስ የዳን ነገድ ካህናት ነበሩ። 31 ሚካም ያደረገውን የተቀረጸ ምስል የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ ባለበት ዘመን ሁሉ አቆሙ። a

መሣፍንት 19

1 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ በሌለበት ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ማዶ የተቀመጠ ሌዋዊ ነበረ፤ ከቤተ ልሔምም ይሁዳ ቁባት አገባ። 2 ቁባቱም አመነዘረችበት፥ ትታውም ወደ አባትዋ ቤት ወደ ቤተ ልሔም ይሁዳ ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጠች። 3 ባልዋም ተነሣ፥ ከእርስዋም ዕርቅ ሽቶ ወደ ቤቱ ሊመልሳት ፍለጋዋን ተከትሎ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር አንድ አሽከር ሁለትም አህዮች ነበሩ። እርስዋም ወደ አባትዋ ቤት አገባችው፤ አባትዋም ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኘው። 4 የብላቴናይቱም አባት አማቱ የግድ አለ፥ በቤቱም ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ በሉም፥ ጠጡም፥ በዚያም አደሩ። 5 በአራተኛውም ቀን ማልደው ተነሡ፥ እርሱም ለመሄድ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት አማቹን። ሰውነትህን በቍራሽ እንጀራ አበርታ፥ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ አለው። 6 ተቀመጡም በአንድ ላይም በሉ ጠጡም፤ የብላቴናይቱም አባት ሰውዮውን። ዛሬ ደግሞ ከዚህ ለማደር፥ እባክህ፥ ፍቀድ፥ ልብህንም ደስ ይበለው አለው። 7 ሰውዮውም ሊሄድ ተነሣ፤ አማቱ ግን የግድ አለው፥ ዳግመኛም በዚያ አደረ። 8 በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ የብላቴናይቱም አባት። እባክህ፥ ሰውነትህን አበርታ፥ ቀኑም እስኪዋገድ ድረስ ቆይ አለው። ሁለቱም በሉ። 9 ሰውዮውም ከቁባቱና ከአሽከሩ ጋር ለመሄድ በተነሣ ጊዜ የብላቴናይቱ አባት አማቱ። እነሆ፥ ቀኑ ተዋግዶአል፤ በዚህ እደሩ፤ እነሆ፥ ቀኑ ለማለፍ ተዋግዶአል፤ ልባችሁ ደስ እንዲለው በዚህ እደሩ፤ ነገም ወደ ቤታችሁ እንድትደርሱ ማልዳችሁ መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለው። 10 ሰውዮው ግን በዚያ ሌሊት ለማደር አልፈቀደም፥ ተነሥቶም ሄደ፥ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለች ወደ ኢያቡስ ፊት ለፊት ደረሰ። ከእርሱም ጋር ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩ፥ ቁባቱም ከእርሱ ጋር ነበረች። 11 ወደ ኢያቡስም በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፥ አሽከሩም ጌታውን። ና፥ ወደዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ፥ እባክህ፥ እናቅና፥ በእርስዋም እንደር አለው። 12 ጌታውም። ከእስራኤል ወገን ወዳልሆነች ወደ እንግዳ ከተማ አንገባም፤ እኛ ወደ ጊብዓ እንለፍ አለው። 13 አሽከሩንም። ና፥ ከእነዚህ ስፍራ ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር አለው። 14 መንገዳቸውንም ይዘው ሄዱ፤ የብንያምም ነገድ በምትሆነው በጊብዓ አጠገብ ሳሉ ፀሐይ ገባችባቸው። 15 በጊብዓም ገብተው ያድሩ ዘንድ ወደዚያ አቀኑ። በገባም ጊዜ ሊያሳድራቸው ማንም በቤቱ አልተቀበላቸውምና በከተማው አደባባይ ተቀመጡ። 16 እነሆም፥ አንድ ሽማግሌ ከእርሻው ሥራ ወደ ማታ መጣ፤ ይህም ሰው ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ነበረ በጊብዓም በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ። 17 ዓይኑንም አንሥቶ መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየ፤ ሽማግሌውም። ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ? አለው። 18 እርሱም። እኛ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ማዶ እናልፋለን፤ እኔ ከዚያ ነኝ፥ ወደ ቤተ ልሔምም ይሁዳ ሄጄ ነበር፥ አሁንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ በቤቱም የሚያሳድረኝ አጣሁ፤ 19 ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ ለእኔና ለገረድህ ከባሪያዎችህም ጋር ላለው አሽከር እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ አንዳችም አላጣንም አለው። 20 ሽማግሌውም። ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን፤ የምትሻውንም ሁሉ እኔ እሰጥሃለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደር አለው። 21 ወደ ቤቱም አስገባው፥ ለአህዮቹም ገፈራ ጣለላቸው፤ እግራቸውንም ታጠቡ፥ በሉም ጠጡም። 22 ሰውነታቸውንም ደስ ባሰኙ ጊዜ ወስላቶች የሆኑ የከተማው ሰዎች ቤቱን ከበቡ በሩንም ይደበድቡ ነበር፤ ባለቤቱንም ሽማግሌውን። ወደ ቤትህ የገባውን ሰው እንድንደርስበት አውጣልን አሉት። 23 ባለቤቱም ሽማግሌው ወደ እነርሱ ወጥቶ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር፥ እባካችሁ፥ አታድርጉ፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ገብቶአልና እንደዚህ ያለ ኃጢአት አትሥሩ። 24 ድንግል ልጄና የእርሱም ቁባት፥ እነሆ፥ አሉ፥ አሁንም አወጣቸዋለሁ፤ አዋርዱአቸው እንደ ወደዳችሁም አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ ኃጢአት አታድርጉ አላቸው። 25 ሰዎቹ ግን ነገሩን አልሰሙም፤ ሰውዮውም ቁባቱን ይዞ አወጣላቸው፤ ደረሱባትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ እስኪነጋ ድረስ አመነዘሩባት፤ ጎህ በቀደደም ጊዜ ለቀቁአት። 26 ሴቲቱም ማለዳ መጣች፥ ጌታዋም ባለበት በሰውዮው ቤት ደጅ ወድቃ እስኪነጋ ድረስ በዚያ ቀረች። 27 ጌታዋም ማለዳ ተነሣ የቤቱንም ደጅ ከፈተ፥ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፤ እነሆም ቁባቲቱ ሴት በቤቱ ደጃፍ ወድቃ፥ እጅዋም በመድረክ ላይ ነበረ። 28 እርሱም። ተነሺ፥ እንሂድ አላት፤ እርስዋ ግን ሞታ ነበርና አልመለሰችም፤ በዚያን ጊዜ በአህያው ላይ ጫናት፥ ተነሥቶም ወደ ስፍራው ሄደ። 29 ወደ ቤቱም በመጣ ጊዜ ካራ አነሣ፥ ቁባቱንም ይዞ ከአጥንቶችዋ መለያያ ላይ ለአሥራ ሁለት ቈራርጦ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ሰደደ። 30 ያየም ሁሉ። የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አልተደረገም፥ አልታየምም፤ አስቡት፥ በዚህም ተመካከሩ፥ ተነጋገሩም ይባባል ነበር።

መሣፍንት 20

1 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወጡ፥ ማኅበሩም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፥ ከገለዓድም አገር ሰዎች ጋር፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ። 2 ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ የሆኑ የሕዝብ ሁሉ አለቆች ሰይፍ በሚመዝዙ በቍጥርም አራት መቶ ሺህ እግረኞች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ቆሙ። 3 የብንያምም ልጆች የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ወጡ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች። ይህ ክፉ ነገር እንደምን እንደ ተደረገ ንገሩን አሉ። 4 የተገደለችውም ሴት ባል ሌዋዊው እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔና ቁባቴ በዚያ ለማደር ወደ ብንያም አገር ወደ ጊብዓ መጣን። 5 የጊብዓም ሰዎች ተነሡብኝ፥ ቤቱንም በሌሊት በእኛ ላይ ከበቡት፤ ሊገድሉኝም ወደዱ፥ በቁባቴም አጥብቀው አመነዘሩባት፥ እርስዋም ሞተች። 6 እኔም ቁባቴን ይዤ ቈራረኋጥጥኋት በእስራኤልም ዘንድ እንደዚህ ያለ ኃጢአትና ስንፍና ስለ ተሠራ ወደ እስራኤል ርስት አገር ሁሉ ሰደድሁ። 7 እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ሁላችሁ፥ ምክራችሁንና እዝናታችሁን በዚህ ስጡ። 8 ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ተነሥተው አሉ። ከእኛ ዘንድ ማንም ወደ ድንኳኑ አይሄድም፥ ወደ ቤቱም አይመለስም። 9 ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ነገር ይህ ነው፤ በዕጣ እንወጣባታለን። 10 ወደ ብንያም ጊብዓ በመጡ ጊዜ እርስዋ በእስራኤል ላይ እንዳደረገችው እንደ ስንፍናዋ እንዲያደርጉ፥ ለሕዝብ ስንቅ የሚይዙ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመቶው አሥር ሰው ከሺሁም መቶ ሰው ከአሥሩም ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። 11 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በከተማይቱ ላይ ተሰበሰቡ።

መሣፍንት 21

1 የእስራኤልም ሰዎች። ከእኛ ማንም ሰው ልጁን ለብንያም ልጆች አያጋባ ብለው በምጽጳ ተማምለው ነበር። 2 ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑ ልቅሶ አለቀሱ። 3 እነርሱም። አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለ ምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ? አሉ። 4 በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፥ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፥ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ። 5 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው። እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ። 6 የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያም ልጆች ተጸጽተው። ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል። 7 እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እናድርግ? አሉ። 8 እነርሱም። ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር። 9 ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ በኢያቢስ ገለዓድ የሚኖር ሰው አልተገኘም። 10 ማኅበሩም ወደዚያ አሥራ ሁለት ሺህ ኃያላን ሰዎች ሰድደው። ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ጋር በሰይፍ ስለት ግደሉ። 11 የምታደርጉትም ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፥ ከወንድ ጋር የተኛችይቱንም ሴት ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ ብለው አዘዙአቸው። 12 ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቈነጃጅት ደናግሎች በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከል አገኙ፤ በከነዓንም አገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው። 13 ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዓለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልክተኞችን ላኩ፥ በዕርቅ ቃልም ተናገሩአቸው። 14 በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ተመለሱ፤ ከኢያቢስ ገለዓድም ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች አገቡአቸው። ነገር ግን የሚበቁ ሴቶች አላገኙም። 15 እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም ተጸጸቱ። 16 የማኅበሩ ሽማግሌዎች። ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ሰዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን? አሉ። 17 ደግሞም። ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር። 18 የእስራኤልም ልጆች። ልጁን ለብንያም የሚድር ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ልጆቻችንን ለእነርሱ ማጋባት አይሆንልንም አሉ። 19 እነርሱም። እነሆ፥ በቤቴል በሰሜን በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል፥ በለቦና በደቡብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ አሉ። 20 የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው። ሂዱ በወይኑ ስፍራ ተደበቁ፤ 21 ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ። 22 አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ። ስለ እኛ ማሩአቸው፤ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበረ አላጋባችኋቸውምና፥ እንላችኋለን። 23 የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው። 24 በዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፥ እያንዳንዱም ወደ ነገዱና ወደ ወገኑ ሄደ፤ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ። 25 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

ሩት 1

1 እንዲህም ሆነ፤ መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ሊቀመጥ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ። 2 የሰውዮውም ስም አቤሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፤ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ በዚያም ተቀመጡ። 3 የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ እርስዋና ሁለቱ ልጆችዋ ቀሩ። 4 እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፤ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም አሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ። 5 መሐሎንና ኬሌዎንም ሁለቱ ሞቱ፤ ሴቲቱም ከሁለቱ ልጆችዋና ከባልዋ ተለይታ ቀረች። 6 እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች። 7 እርስዋም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፤ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ በመንገድ ሄዱ። 8 ኑኃሚንም ምራቶችዋን። ሂዱ፥ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፤ በእኔና በሞቱት እንዳደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ቸርነት ያድርግላችሁ። 9 እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ አለቻቸው። ሳመቻቸውም፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ። 10 እነርሱም። ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን አሉአት። 11 ኑኃሚንም አለች። ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን? 12 ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥ 13 እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ። 14 ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት። 15 ኑኃሚንም። እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ አለቻት። 16 ሩትም። ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ 17 በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፥ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ አለች። 18 ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች። 19 ሁሉቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ። ይህች ኑኃሚን ናትን? እያሉ ተንጫጩ። 20 እርስዋም። ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ። 21 በሙላት ወጣሁ፥ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ? አለቻቸው። 22 ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።

ሩት 2

1 ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። 2 ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን። በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት። 3 ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋኋኋ ላ በእርሻ ውስጥ ቃረ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። 4 እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት። 5 ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን። ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው። 6 የአጫጆቹም አዛዥ። ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤ 7 እርስዋም። ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው። 8 ቦዔዝም ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ። 9 ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ አላት። 10 በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት። እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን? አለችው። 11 ቦዔዝም። ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። 12 እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን አላት። 13 እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ አለችው። 14 በምሳም ጊዜ ቦዔዝ። ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም። 15 ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን። በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፤ 16 ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም ብሎ አዘዛቸው። 17 በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ። 18 ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። 19 አማትዋም። ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን አለቻት። እርስዋም። ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት። 20 ኑኃሚንም ምራትዋን። ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ። ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው አለቻት። 21 ሞዓባዊቱ ሩትም። ደግሞ። መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ አለኝ አለቻት። 22 ኑኃሚንም ምራትዋን ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ከገረዶቹ ጋር ብትወጪ፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው አለቻት። 23 ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝን ገረዶች ተጠጋች፤ በአማትዋም ዘንድ ትቀመጥ ነበር።

ሩት 3

1 አማትዋም ኑኃሚን አለቻት። ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? 2 አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። 3 እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። 4 በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል። 5 ሩትም። የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት። 6 ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። 7 ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። 8 መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። 9 እርሱም። ማን ነሽ? አለ። እርስዋም። እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው። 10 ቦዔዝም አላት። ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። 11 አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ። 12 የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ። 13 ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ። 14 እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም። ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች። 15 እርሱም። የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት አሸከማትም። 16 እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም። ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ? አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት። 17 ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት። 18 እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ አለች።

ሩት 4

1 ቦዔዝም ወደ ከተማይቱ በር አደባባይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። እነሆም፥ ቦዔዝ ስለ እርሱ ይናገር የነበረው የቅርብ ዘመድ ሲያልፍ ቦዔዝ። አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው። እርሱም ቀረብ ብሎ ተቀመጠ። - አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው። 2 ቦዔዝም ከከተማይቱ ሽማግሌዎች አሥር ሰዎች ጠርቶ። በዚህ ተቀመጡ አላቸው። 3 እነርሱም ተቀመጡ። ቦዔዝም የቅርብ ዘመዱን። ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ኑኃሚን የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ ትሸጣለች። 4 እኔም በዚህ በተቀመጡት በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው አስታውቅህ ዘንድ አሰብሁ። መቤዠት ብትወድድ ተቤዠው፤ መቤዠት ባትወድድ ግን ከአንተ በቀር ሌላ ወራሽ የለምና፥ እኔም ከእአንተ በኋላ ነኝና እንዳውቀው ንገረኝ አለው። እርሱም። እቤዠዋለሁ አለው። 5 ቦዔዝም። እርሻውን ከኑኃሚን እጅ በምትገዛበት ቀን፥ ለሞተው በርስቱ ስሙን እንድታስነሣለት ከምዋቹ ሚስት ከሞዓባዊቱ ከሩት ደግሞ ትገዛለህ አለ። 6 የቅርብ ዘመዱም። የራሴን ርስት እንዳላበላሽ መቤዠት አልችልም፤ እኔ መቤዠቱን አልችልምና አንተ ከእኔ መቤዠቱን ውሰደው አለ። 7 በጥንት ጊዜም፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ። ይህም በእስራኤል ምስክር ነበረ። 8 የቅርብ ዘመዱም ቦዔዝን። አንተ ግዛው አለው፤ ጫማውንም አወለቀ። 9 ቦዔዝም ሽማግሌዎችንና ሕዝቡን ሁሉ። ለአቤሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከኑኃሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ። 10 ደግሞም የምዋቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል ከአገሩም ደጅ እንዳይጠፋ፥ የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ አላቸው። 11 በከተማይቱ በር አደባባይም የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ሽማግሌዎቹም። እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ ባለ ጠጋ ሁን፥ ስምህም በቤተ ልሔም ይጠራ። 12 ቤትህም እግዚአብሔር ከዚህች ቈንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን አሉት። 13 ቦዔዝም ሩትን ወሰደ፥ ሚስትም ሆነችው፤ ደረሰባትም፥ እግዚአብሔርም ፅንስ ሰጣት፥ ወንድ ልጅም ወለደች። 14 ሴቶችም ኑኃሚንን። ዛሬ ዋርሳ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ ስሙም በእስራኤል ይጠራ። 15 ከሰባትም ወንዶች ልጆች ይልቅ ለአንቺ ከምትሻል ከምትወድድሽ ምራት ተወልዶአልና ሰውነትሽን ያሳድሰዋል፥ በእርጅናሽም ይመግብሻል አሉአት። 16 ኑኃሚንም ሕፃኑን ወሰደች አቀፈችውም፥ ሞግዚትም ሆነችው። 17 ሴቶችም ጎረቤቶችዋ፥ ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት እያሉ ስም አወጡለት፤ ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት። እርሱም የዳዊት አባት የእሴይ አባት ነው። 18 የፋሬስም ትውልድ ይህ ነው፤ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፥ 19 ኤስሮምም አራምን ወለደ፥ አራምም አሚናዳብን ወለደ፥ 20 አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፥ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፥ 21 ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፥ 22 ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፥ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ።

1 ሳሙኤል 1

1 በተራራማው በኤፍሬም አገር ከአርማቴም መሴፋ የሆነ ስሙ ሕልቃና የተባለ ኤፍሬማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የኢያሬምኤል ልጅ የኢሊዮ ልጅ የቶሑ ልጅ የናሲብ ልጅ ነበረ። 2 ሁለትም ሚስቶች ነበሩት፤ የአንዲቱ ስም ሐና የሁለተኛይቱም ስም ፍናና ነበረ፤ ለፍናናም ልጆች ነበሩአት፥ ለሐና ግን ልጅ አልነበራትም። 3 ያም ሰው በሴሎ ይሰግድ ዘንድ ለሠራዊት ጌታም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ከከተማው በየዓመቱ ይወጣ ነበር። የእግዚአብሔርም ካህናት ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በዚያ ነበሩ። 4 ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው። 5 ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር። 6 እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር። 7 በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፤ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር። 8 ባልዋም ሕልቃና። ሐና ሆይ፥ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትቀምሺም? ለምንስ ልብሽ ያዝንብሻል? እኔስ ከአሥር ልጆች አልሻልልሽምን? አላት። 9 በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች። ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ መቃን አጠገብ በመንበሩ ላይ ተቀምጦ ነበር። 10 እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ልቅሶም አለቀሰች። 11 እርስዋም። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። 12 ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። 13 ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። 14 ዔሊም። ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት። 15 ሐናም። ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ 16 ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት። 17 ዔሊም። በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት። 18 እርስዋም። ባሪያህ በዓይንህ ፊት ሞገስ ላግኝ አለች። ሴቲቱም መንገድዋን ሄደች በላችም፥ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም። 19 ማልደው ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፥ ተመልሰውም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው መጡ። ሕልቃናም ሚስቱን ሐናን አወቃት፤ እግዚአብሔርም አሰባት፤ 20 የመፅነስዋም ወራት ካለፈ በኋላ ሐና ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርስዋም። ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው። 21 ሰውዮውም ሕልቃና ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር የዓመቱን መሥዋዕትና ስእለቱን ለእግዚአብሔር ያቀርብ ዘንድ ወጣ። 22 ሐና ግን አልወጣችም፥ ባልዋንም። ሕፃኑ ጡት እስኪተው ድረስ እቀመጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ፥ በዚያም ለዘላለም ይሆን ዘንድ አመጣዋለሁ አለችው። 23 ባልዋም ሕልቃና። በዓይንሽ ደስ ያሰኘሽን አድርጊ፥ ጡትም እስኪተው ድረስ ተቀመጪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽና አላት። ሴቲቱም ልጅዋን እያጠባች ጡት እስኪተው ድረስ በቤትዋ ተቀመጠች። 24 ጡትም በተወ ጊዜ ከእርስዋ ጋር እርሱንና አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፥ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት፥ አንድ አቁማዳ የወይን ጠጅ ይዛ ወደ ሴሎ ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፤ ሕፃኑም ገና ታናሽ ነበረ። 25 ወይፈኑንም አረዱ፥ ሕፃኑንም ወደ ዔሊ አመጡት። 26 እርስዋም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታ ሆይ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ በዚህ በአንተ ዘንድ ቆማ የነበረች ሴት እኔ ነኝ። 27 ሰለዚህ ሕፃን ጸለይሁ፤ 28 እግዚአብሔርም የለመንሁትን ልመናዬን ሰጥቶኛል፤ እኔም ደግሞ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።

1 ሳሙኤል 2

1 ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች። ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። 2 እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። 3 አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። 4 የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። 5 ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። 6 እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል። 7 እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። 8 ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። 9 እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል ኃጥኣን ግን ዝም ብለው በጨለማ ይቀመጣሉ፤ ሰው በኃይሉ አይበረታምና። 10 ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሡም ኃይል ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 11 ሕልቃናም ወደ ቤቱ ወደ አርማቴም ሄደ፤ ብላቴናውም በካሁኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር። 12 የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። 13 የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፤ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበር፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፤ 14 ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፤ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር። 15 ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው። ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር። 16 ሰውዮውም። አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ። አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር። 17 ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቍርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች። 18 ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። 19 እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር። 20 ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን። ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። 21 እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ። 22 ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ። 23 እርሱም አላቸው። ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? 24 ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም። 25 ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው? እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። 26 ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ። 27 የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ አለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በግብጽ በፈርዖን ቤት ባሪያ ሳለ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤ 28 ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። 29 በማደሪያዬ ያቀርቡት ዘንድ ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቍርባኔን ስለ ምን ረገጣችሁ? እንድትወፍሩም የሕዝቤን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ መጀመሪያ በመብላታችሁ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ? 30 ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእውነት ቤትህ የአባትህም ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም። 31 እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ ክንድህን የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል። 32 በእስራኤል በረከት ሁሉ፥ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም። 33 ከመሠዊያዬ ያልተቈረጠ ልጅህ ቢገኝ ዓይንህን ያፈዝዘዋል፥ ነፍስህንም ያሳዝናል ከቤትህም የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጐልማስነት ይሞታሉ። 34 ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ። 35 የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። 36 ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፥ በፊቱም ሰግዶ፥ ቍራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ከካህናት ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ አንድ ብር አንድ እንጀራም ይለምናል።

1 ሳሙኤል 3

1 ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር። 2 በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር። 3 ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥ 4 እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። 5 ወደ ዔሊም ሮጠ። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ አለው። ሄዶም ተኛ። 6 እግዚአብሔርም ደግሞ። ሳሙኤል ሆይ ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለው። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ ብሎ መለሰ። 7 ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር። 8 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና። እነሆኝ የጠራኸኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ። 9 ዔሊም ሳሙኤልን። ሄደህ ተኛ ቢጠራህም። አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ። 10 እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም። ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው። 11 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ። 12 በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ። 13 ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ። 14 ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ። 15 ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ። 16 ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ። ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። 17 እርሱም። እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው። 18 ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም። እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ። 19 ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቀም ነበር። 20 እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ። 21 እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።

1 ሳሙኤል 4

1 እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያን በአፌቅ ሰፈሩ። 2 ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፤ ሰልፉም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። 3 ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች። ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ። 4 ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። 5 የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች። 6 ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ። በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። 7 ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው። እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ። ወዮልን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም። 8 ወዮልን፤ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። 9 እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ። 10 ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። 11 የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ። 12 በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ። 13 በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኸች። 14 ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው። 15 ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር። 16 ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው። 17 ወሬኛውም መልሶ። እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ። 18 ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ። 19 ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች። 20 ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም። 21 እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው። 22 እርስዋም። የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች።

1 ሳሙኤል 5

1 ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወሰዱ፤ ከአቤንኤዘርም ወደ አዛጦን ይዘውት መጡ። 2 ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት። 3 በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት። 4 በነጋውም ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር፤ የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር፤ የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር። 5 ስለዚህም የዳጎን ካህናት ወደ ዳጎንም ቤት የሚገቡት ሁሉ በአዛጦን ያለውን የዳጎንን መድረክ እስከ ዛሬ ድረስ አይረግጡም። 6 የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደች፥ አጠፋቸውም፥ አዛጦንንና ድንበራቸውንም በእባጭ መታቸው። 7 የአዛጦንም ሰዎች እንዲህ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ። እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክራለችና የእስራኤል አምላክ ታቦት ከእኛ ዘንድ አይቀመጥ አሉ። 8 ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ወደ እነርሱ ሰበሰቡና። በእስራኤል አምላክ ታቦት ምን እናድርግ? አሉ፤ እነርሱም። የእስራኤል አምላክ ታቦት ወደ ጌት ይዙር ብለው መለሱ። የእስራኤልንም አምላክ ታቦት ወደዚያ ተሸከሙት። 9 ከተሸከሙትም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በታላቅ ድንጋጤ በከተማይቱ ላይ ሆነች፤ ከታናሹም እስከ ታላቁ ድረስ የከተማይቱን ሰዎች መታ፥ እባጭም መጣባቸው። 10 የእግዚአብሔርንም ታቦት ወደ አስቀሎና ሰደዱት። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አስቀሎና በመጣ ጊዜ አስቀሎናውያን። እኛንና ሕዝባችንን ሊገድሉ የእስራኤልን አምላክ ታቦት አመጡብን ብለው ጮኹ። 11 በከተማይቱ ሁሉ የሞት ድንጋጤ ነበርና፥ የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ እጅግ ከብዳ ነበረችና ልከው የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱ፥ እኛንና ሕዝባችንን እንዳይገድል ወደ ስፍራው ይመለስ አሉ። 12 ያልሞቱትም ሰዎች በእባጭ ተመቱ፤ የከተማይቱም ዋይታ እስከ ሰማይ ወጣ።

1 ሳሙኤል 6

1 የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ሰባት ወር ተቀመጠ። 2 ፍልስጥኤማውያንም ካህናትንና ምዋርተኞችን ጠርተው። በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራውስ በምን እንስደደው? አስታውቁን አሉ። 3 እነርሱም። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ። 4 እነርሱም። ስለ በደል መሥዋዕት የምንመልስለት ምንድር ነው? አሉ። እነርሱም እንዲህ አሉ። እናንተንና አለቆቻችሁን ያገኘች መቅሠፍት አንዲት ናትና እንደ ፍልስጥኤማውያን አለቆች ቍጥር አምስት የወርቅ እባጮች አምስትም የወርቅ አይጦች አቅርቡ። 5 የእባጫችሁንም ምሳሌ፥ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፤ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል። 6 ግብጻውያንና ፈርዖንም ልባቸውን እንዳጸኑ ልባችሁን ለምን ታጸናላችሁ? እግዚአብሔር ኃይሉን ካደረገባቸው በኋላ ያወጡአቸው አይደሉምን? 7 እነርሱም አልሄዱምን? አሁንም ወስዳችሁ አንዲት ሰረገላ ሥሩ፤ የሚያጠቡም፥ ቀንበር ያልተጫነባቸውን ሁለት ላሞች በሰረገላ ጥመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም ለይታችሁ ወደ ቤት መልሱአቸው። 8 የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩት፤ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፤ ይሄድም ዘንድ ስደዱት። 9 ተመልከቱም በድንበሩም መንገድ ወደ ቤትሳሚስ ቢወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እግዚአብሔር ነው፤ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን። 10 ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ፤ የሚያጠቡትን ሁለቱን ላሞች ወሰዱ፥ በሰረገላም ጠመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም በቤት ዘጉባቸው፤ 11 የእግዚአብሔርም ታቦት፥ የወርቁ አይጦችና የእባጮቻቸው ምሳሌ ያሉበትንም ሣጥን በሰረገላው ላይ ጫኑ። 12 ላሞችም ወደ ቤትሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ አቅንተው እምቧ እያሉ በጎዳናው ላይ ሄዱ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላሉም፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች እስከ ቤትሳሚስ ዳርቻ ድረስ በኋላ በኋላቸው ይሄዱ ነበር። 13 የቤትሳሚስ ሰዎችም በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ዓይናቸውንም ከፍ አድርገው ታቦቱን አዩ፥ በማየታቸውም ደስ አላቸው። 14 ሰረገላውም ወደ ቤትሳሚሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ መጣ፥ ታላቅም ድንጋይ በነበረበት በዚያ ቆመ፤ የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ። 15 ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ፥ በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት፤ በዚያም ቀን የቤትሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ መሥዋዕትንም ሠዉ። 16 ፍልስጥኤማውያንም አምስቱ አለቆች ባዩት ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አስቀሎና ተመለሱ። 17 ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዲቱ ለአዛጦን፥ አንዲቱም ለጋዛ፥ አንዲቱም ለአስቀሎና፥ አንዲቱ ለጌት፥ 18 አንዲቱ ለአቃሮን የወርቁም አይጦች ቍጥር ለአምስቱ የፍልስጥኤማውያን አለቆች እንደ ነበሩት ከተሞች ሁሉ ቍጥር እንዲሁ ነበረ፤ እነርሱም እስከ ታላቁ ድንጋይ የሚደርሱ ከተሞችና መንደሮች ናቸው። በዚህም ድንጋይ ላይ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡ፥ ድንጋዩም እስከ ዛሬ ድረስ በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ እርሻ አለ። 19 ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ። 20 የቤትሳሚስም ሰዎች። በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? አሉ። 21 በቂርያትይዓሪምም ወደ ተቀመጡት ሰዎች መልክተኞች ልከው። ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፤ ወርዳችሁም ወደ እናንተ አውጡት አሉ።

1 ሳሙኤል 7

1 የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት አወጡ፥ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። 2 ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ። 3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ። በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው። 4 የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ። 5 ሳሙኤልም። እስራኤልን ሁሉ ወደ ምጽጳ ሰብስቡ፥ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ አለ። 6 ወደ ምጽጳም ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፥ በዚያም ቀን ጾሙ፥ በዚያም። እግዚአብሔርን በድለናል አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በምጽጳ ፈረደ። 7 ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ። 8 የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን። ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ትጸልይልን ዘንድ አትታክት አሉት። 9 ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው። 10 ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጐድጓድ አንጐደጐደ፥ አስደነገጣቸውም በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። 11 የእስራኤልም ሰዎች ከምጽጳ ወጡ፥ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤትካር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው። 12 ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አኖረው፤ ስሙንም። እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል አቤንኤዘር ብሎ ጠራው። 13 ፍልስጥኤማውያንም ተዋረዱ፥ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤል ዕድሜ ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። 14 ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ ጌት ድረስ ከእስራኤል የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳነ። በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ዕርቅ ነበረ። 15 ሳሙኤልም በዕድሜው ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 16 በየዓመቱም ወደ ቤቴል ወደ ጌልገላ ወደ ምጽጳም ይዞር ነበር፤ በእነዚያም ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። 17 ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

1 ሳሙኤል 8

1 እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው። 2 የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር። 3 ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር። 4 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና። 5 እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት። 6 የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 7 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ። 8 ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል። 9 አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው። 10 ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። 11 እንዲህም አለ። በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤ 12 ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ። 13 ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። 14 ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። 15 ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። 16 ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል። 17 ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። 18 በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም። 19 ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥ 20 እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት። 21 ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ። 22 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች። እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።

1 ሳሙኤል 9

1 ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ። 2 ለእርሱም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፤ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው አልነበረም፤ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻውና ከዚያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ። 3 የሳኦልም አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን። ከብላቴኖቹ አንዱን ወስደህ ተነሣ፥ አህዮችንም ለመሻት ሂድ አለው። 4 በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አለፉ፥ አላገኙአቸውምም በሻዕሊም ምድርም አለፉ፥ በዚያም አልነበሩም፤ በብንያም ምድርም አለፉ፥ አላገኙአቸውምም። 5 ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜም ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን ብላቴና። አባቴ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ ስለ እኛ እንዳይጨነቅ፥ ና፥ እንመለስ አለው። 6 እርሱም። እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፤ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፤ አሁን ወደዚያ እንሂድ፤ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው። 7 ሳኦልም ብላቴናውን። እነሆ፥ እንሄዳለን፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው ምን እናመጣለታለን? እንጀራ ከከረጢታችን አልቆአልና፥ እጅ መንሻም የለንምና ለእግዚአብሔር ሰው የምናመጣለት ምን አለን? አለው። 8 ብላቴናው ደግሞ ለሳኦል መልሶ። እነሆ፥ በእጄ የሰቅል ብር ሩቡ አለኝ፤ እርሱንም መንገዳችንን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጣለሁ አለ። 9 ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ። ኑ፥ ወደ ባለ ራእይ እንሂድ ይል ነበር። 10 ሳኦልም ብላቴናውን። የተናገረኸው ነገር መልካም ነው፤ ና፥ እንሂድ አለውና የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። 11 በከተማይቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቆነጃጅት ውኃውን ሊቀዱ ሲወጡ አገኙና። ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ? አሉአቸው። 12 እነርሱም። አዎን፤ እነሆ፥ በፊታችሁ ነው፤ ዛሬ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በኮረብታው ላይ ባለው መስገጃ መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸውና ፈጥናችሁ ውጡ። 13 ወደ ከተማይቱም በገባችሁ ጊዜ መሥዋዕቱን እርሱ የሚባርክ ስለ ሆነ እርሱ ሳይወጣ ሕዝቡ ምንም አይቀምሱምና፥ ከዚያም በኋላ የተጠሩት ይበላሉና ለመብላት ወደ ኮረብታው መስገጃ ሳይወጣ ታገኙታላችሁ፤ በዚህም ጊዜ ታገኙታላችሁና አሁን ውጡ አሉአቸው። 14 ወደ ከተማይቱም ወጡ፤ በከተማይቱም ውስጥ በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙኤል ወደ ኮረብታው መስገጃ ለመውጣት ወደ እነርሱ መጣ። 15 ገናም ሳኦል ሳይመጣ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር። 16 ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድድልሃለሁ፤ ልቅሶአቸው ወደ እኔ የደረስ ሕዝቤን ተመልክቻለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሕዝቤን ያድናል። 17 ሳሙኤልም ሳኦልን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር። ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም በሕዝቤ ላይ ይሠለጥናል አለው። 18 ሳኦልም በበሩ ወደ ሳሙኤል ቀርቦ። የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። 19 ሳሙኤልም መልሶ ሳኦልን። ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬም ከእኔ ጋር ትበላላችሁና በፊቴ ወደ ኮረብታው መስገጃ ውጡ፤ ነገም አሰናብትሃለሁ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ፤ 20 ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤል ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው። 21 ሳኦልም መልሶ። እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ? አለው። 22 ሳሙኤልም ሳኦልንና ብላቴናውን ወስዶ ወደ አዳራሽ አገባቸው፥ በመርፈቂያውም ራስ አስቀመጣቸው፤ የተጠሩትም ሠላሳ ሰዎች ያህል ነበሩ። 23 ሳሙኤልም ወጥቤቱን። በአንተ ዘንድ አኑረው ብዬ የሰጠሁህን እድል ፈንታ አምጣ አለው። 24 ወጥቤቱም ጭኑንና በእርሱ ላይ የነበረውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ሳሙኤልም። ሕዝቡን ከጠራሁ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተጠብቆአልና እነሆ፥ የተቀመጠልህን በፊትህ አኑረህ ብላው አለ። በዚያም ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ። 25 ከኮረብታውም መስገጃ ወደ ከተማይቱ ወረዱ፤ ሳሙኤልም ለሳኦል በሰገነቱ ላይ መኝታ አዘጋጀለት፥ እርሱም ተኛ። 26 ማልዶም ተነሡ፤ በነጋም ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ። ተነሣና ላሰናብትህ አለው። ሳኦልም ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ። 27 እነርሱም በከተማይቱ ዳር ሲወርዱ ሳሙኤል ሳኦልን። ብላቴናውን ወደ ፊታችን እንዲያልፍ እዘዘው፤ አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው። ብላቴናውም አለፈ።

1 ሳሙኤል 10

1 ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው። በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፤ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ። 2 ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ዳርቻ በጼልጻህ አገር ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም። ልትሻቸው ሄደህ የነበርህላቸ አህዮች ተገኝተዋል፤ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ። የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል። 3 ከዚያም ደግሞ ወደ ፊት ትሄዳለህ፤ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ፤ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች፥ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል፤ 4 ሰላምታም ይሰጡሃል፥ ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላለህ። 5 ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል። 6 የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። 7 እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምታገኘውን ሁሉ አድርግ። 8 በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፤ እኔም፥ እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፤ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደርገውን እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን ትቆያለህ። 9 ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፤ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት። 10 ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ። 11 ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው። የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን? ተባባሉ። 12 ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው። አባታቸውስ ማን ነው? ብሎ መለሰ። ስለዚህም። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን? የሚል ምሳሌ ሆነ። 13 ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው መስገጃ መጣ። 14 አጎቱም ሳኦልንና ብላቴናውን፥ ወዴት ሄዳችሁ ኖሮአል? አላቸው። እርሱም። አህዮችን ልንሻ ሄደን ነበር፤ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን አለ። 15 የሳኦልም አጎት። ሳሙኤል የነገረህን፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። 16 ሳኦልም አጎቱን። አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው፤ ነገር ግን ሳሙኤል የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም። 17 ሳሙኤልም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ጠራ። 18 የእስራኤልንም ልጆች። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን ከግብጽ አወጣሁ፥ ከግብጻውያንም እጅ ከሚያስጨንቁአችሁም ነገሥታት ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ። 19 ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ ያዳናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ አታንግሥልን አላችሁት። አሁንም በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ አላቸው። 20 ሳሙኤልም የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ አቀረበ፥ ዕጣውም በብንያም ነገድ ላይ ወደቀ። 21 የብንያምንም ነገድ በየወገናቸው አቀረበ፥ ዕጣውም በማጥሪ ወገን ላይ ወደቀ። የማጥሪንም ወገን በየሰዉ አቀረበ፥ ዕጣውም በቂስ ልጅ በሳኦል ላይ ወደቀ፤ ፈለጉትም፥ አላገኙትምም። 22 ከእግዚአብሔርም። ገና ወደዚህ የሚመጣ ሰው አለን? ብለው ደግሞ ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል ብሎ መለሰ። 23 እነርሱም ሮጠው ከዚያ አመጡት፤ እርሱም በሕዝቡ መካከል ቆመ፥ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻው ወደ ላይ ከፍ ያለ ቁመተ ረጅም ነበረ። 24 ሳሙኤልም ለሕዝቡ ሁሉ። ከሕዝቡ ሁሉ እርሱን የሚመስል እንደሌለ እግዚአብሔር የመረጠውን ታያላችሁን? አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ። ንጉሥ ሕያው ይሁን እያሉ እልልታ አደረጉ። 25 ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፥ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው። ሳሙኤልም ሕዝቡን ሁሉ ወደ እየቤታቸው አሰናበታቸው። 26 ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን የነካ ኃያላንም ከእርሱ ጋር ሄዱ። 27 ምናምንቴዎች ሰዎች ግን። ይህ ሰው እንዴት ያድነናል? ብለው ናቁት፥ እጅ መንሻም አላመጡለትም።

1 ሳሙኤል 11

1 እንዲህም ሆነ፤ ከአንድ ወር በኋላ አሞናዊው ናዖስ ወጣ፥ በኢያቢስ ገለዓድም ሰፈረ፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ። ቃል ኪዳን አድርግልን፥ እኛም እንገዛልሃለን አሉት። 2 አሞናዊውም ናዖስ። ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ ስድብ አደረጋለሁ አላቸው። 3 የኢያቢስም ሽማግሌዎች። ወደ እስራኤል አገር ሁሉ መልክተኞችን እንድንልክ ሰባት ቀን ቆይልን፤ ከዚያም በኋላ የሚያድነን ባይኖር ወደ አንተ እንመጣለን አሉት። 4 መልክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ነገር በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5 እነሆም፥ ሳኦል በሬዎቹን ተከትሎ ከእርሻው መጣ፤ ሳኦልም። ሕዝቡ የሚያለቅስ ምን ሆኖ ነው? አለ። የኢያቢስንም ሰዎች ነገር ነገሩት። 6 ይህንም ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፥ ቍጣውም እጅግ ነደደ። 7 ጥምዱንም በሬዎች ወስዶ ቈራረጣቸው፥ ወደ እስራኤልም ዳርቻ ሁሉ በመልክተኞቹ እጅ ሰደደና። ሳኦልንና ሳሙኤልን ተከትሎ የማይወጣ ሁሉ፥ በበሬዎቹ እንዲሁ ይደረግ አለ። ድንጋጤም በሕዝቡ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደቀ፥ እንደ አንድ ሰውም ሆነው ወጡ። 8 በቤዜቅም ቈጠራቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ሦስት መቶ ሺህ፥ የይሁዳም ሰዎች ሠላሳ ሺህ ነበሩ። 9 የመጡትንም መልክተኞች። የኢያቢስ ገለዓድን ሰዎች። ነገ ፀሐይ በተኮሰ ጊዜ ማዳን ይሆንላችኋል በሉአቸው አሉአቸው። መልክተኞችም መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሩ፤ ደስም አላቸው። 10 የአያቢስም ሰዎች። ነገ እንወጣላችኋለን፥ ደስ የሚያሰኛችሁንም አድርጉብን አሉ። 11 በነጋውም ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ወገን አደረጋቸው፤ ወገግም ባለ ጊዜ ወደ ሰፈሩ መካከል ገቡ፥ ቀትርም እስኪሆን ድረስ አሞናውያንን መቱ፤ የቀሩትም ተበተኑ፥ ሁለትም በአንድ ላይ ሆነው አልቀሩላቸውም። 12 ሕዝቡም ሳሙኤልን። ሳኦል አይንገሥብን ያሉ እነማናቸው? አውጡአቸውና እንግደላቸው አሉት። 13 ሳኦልም። ዛሬ እግዚአብሔር ለእስራኤል ማዳን አድርጎአልና ዛሬ አንድ ሰው አይሞትም አለ። 14 ሳሙኤልም ሕዝቡን። ኑ፥ ወደ ጌልገላ እንሂድ፥ በዚያም መንግሥቱን እናድስ አላቸው። 15 ሕዝቡም ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄዱ፥ በዚያም ሳኦልን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ አነገሡት፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ በዚያም ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ አደረጉ።

1 ሳሙኤል 12

1 ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ። የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ። 2 አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። 3 እነሆኝ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። 4 እነርሱም። አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ። 5 እርሱም። በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፤ እነርሱም። ምስክር ነው አሉ። 6 ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው። 7 አሁንም እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ስላደረገው ጽድቅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እምዋገታችሁ ዘንድ በዚህ ቁሙ። 8 ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፤ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው። 9 አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፥ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጉ። 10 እነርሱም። እግዚአብሔርን ትተን በኣሊምንና አስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፥ እናመልክህማለን ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11 እግዚአብሔርም ይሩበአልም፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፥ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳናችሁ፤ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ። 12 የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ። 13 አሁንም የመረጣችሁትንና የፈለጋችሁትን ንጉሥ እዩ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ አደረገላችሁ። 14 እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል። 15 ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች። 16 አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ። 17 የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፥ እርሱም ነጎድጓድና ዝናብ ይልካል፤ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ታያላችሁም። 18 ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው። 19 ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን። ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት። 20 ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። አትፍሩ፤ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። 21 ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ። 22 እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም። 23 ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። 24 ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት። 25 ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።

1 ሳሙኤል 13

1 ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥ 2 ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ። 3 ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም። ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ። 4 እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። 5 ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ። 6 ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቍጥቋጦ በገደልና በግንብ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ። 7 ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት። 8 ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ። 9 ሳኦልም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። 10 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ። 11 ሳሙኤልም። ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም። ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤ 12 ሰለዚህ። ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ። 13 ሳሙኤልም ሳኦልን። አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ። 14 አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው። 15 ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከተለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። 16 ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ጊብዓ ተቀመጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ ሰፈሩ። 17 ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በዖፍራ መንገድ ወደ ሦጋል ምድር ሄደ። 18 ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤት ሖሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በበረሃው አጠገብ ባለው ወደ ስቦይም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻ መንገድ ዞረ። 19 ፍልስጥኤማውያንም። ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረተ ሠሪ አልተገኘም። 20 እስራኤልም ሁሉ የማረሻውን ጫፍና ማጭዱን መጥረቢያውንና መቆፈሪያውን ይስል ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር። 21 ለማረሻው ጫፍና ለመቆፈሪያው ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 2ቱ እጅ ነበረ። መጥረቢያውንም ለማሳል መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 1ዱ እጅ ነበረ። 22 ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ።

1 ሳሙኤል 14

1 አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም። 2 ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። 3 የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም። 4 ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ። 5 አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ። 6 ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ጭፍራ እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው። 7 ጋሻ ጃግሬውም። ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፤ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው። 8 ዮናታንም አለ። እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፤ 9 እነርሱም። ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም። 10 ነገር ግን። ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፤ ምልክታችንም ይህ ይሆናል። 11 ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም። እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ ይወጣሉ አሉ። 12 የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን። ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን። እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው። 13 ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፤ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። 14 የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ። 15 በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፤ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ። 16 በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። 17 ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ። እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። 18 በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል። ኤፉድን አምጣ አለው። 19 ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን። እጅህን መልስ አለው። 20 ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፤ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ። 21 ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት አስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ። 22 ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኰበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ። 23 እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፤ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር። 24 የእስራኤልም ሰዎች በዚያ ቀን ተጨነቁ፤ ሳኦል። ጠላቶቼን እስክበቀል እስከ ማታ ድረስ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን አምሎአቸው ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ መብል አልቀመሱም። 25 ሕዝቡም ሁሉ ወደ ዱር ገባ፤ ማርም በምድር ላይ ነበረ። 26 ሕዝቡም ወደ ዱር በገባ ጊዜ እነሆ፥ የሚፈስስ ማር ነበረ፤ ሕዝቡ መሐላውን ፈርቶ ነበርና ማንም እጁን ወደ አፉ አላደረገም። 27 ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ባማለ ጊዜ አልሰማም ነበር፤ እርሱም በእጁ ያለችውን በትር ጫፍዋን ወደ ወለላው ነከረ፥ እጁንም ወደ አፉ አደረገ፤ ዓይኑም በራ። 28 ከሕዝቡም አንድ ሰው መልሶ። አባትህ። ዛሬ መብል የሚበላ ሰው ርጉም ይሁን ብሎ ሕዝቡን መሐላ አምሎአቸዋል አለው፤ ሕዝቡም ደከሙ። 29 ዮናታንም። አባቴ ምድሪቱን አስቸገረ፤ ከዚህ ማር ጥቂት ብቀምስ ዓይኔ እንደ በራ እዩ። 30 ይልቅስ ሕዝቡ ካገኙት ከጠላቶቻቸው ምርኮ በልተው ቢሆኑ የፍልስጥኤማውያን መመታት ይበልጥ አልነበረምን? አለ። 31 በዚያም ቀን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ መቱአቸው፤ ሕዝቡም እጅግ ደከሙ። 32 ሕዝቡም ለምርኮ ሳሱ፤ በጎችን በሬዎችንም ጥጆችንም ወስደው በምድር ላይ አረዱ፤ ሕዝቡም ከደሙ ጋር በሉ። 33 ለሳኦልም። እነሆ፥ ሕዝቡ ከደሙ ጋር በመብላታቸው እግዚአብሔርን በደሉ ብለው ነገሩት። ሳኦልም። እጅግ ተላለፋችሁ፤ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አቅርቡልኝ አላቸው። 34 ሳኦልም። በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ። እያንዳንዱ ሰው በሬውንና በጉን ወደ እኔ ያቅርብ፥ በዚህም እረዱና ብሉ፤ ከደሙም ጋር በመብላታችሁ እግዚአብሔርን አትበድሉ በሉአቸው አለው። እያንዳንዱም ሰው ሁሉ በእጁ ያለውን በሬውን በዚያች ሌሊት አቀረበ፥ በዚያም አረደው። 35 ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ይኸውም ለእግዚአብሔር የሠራው መጀመሪያ መሠዊያ ነው። 36 ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን በሌሊት ተከትለን እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድ ሰው እንኳ አናስቀርላቸው አለ። እነርሱም። ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አድርግ አሉት። ካህኑም። ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ አለ። 37 ሳኦልም። ፍልስጥኤማውያንን ልከተልን? በእስራኤልስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀው። በዚያ ቀን ግን አልመለሰለትም። 38 ሳኦልም። እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ፥ ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ይህ ኃጢአት በምን እንደ ሆነ እወቁ፥ ተመልከቱም፤ 39 እስራኤልን የሚያድን ሕያው እግዚአብሔርን! ኃጢአቱ በልጄ በዮናታን ቢሆን ፈጽሞ ይሞታል አለ። ከሕዝቡም ሁሉ አንድ የመለሰለት ሰው አልነበረም። 40 እስራኤልንም ሁሉ። እናንተ በአንድ ወገን ሁኑ፥ እኔና ልጄ ዮናታንም በሌላ ወገን እንሆናለን አለ። ሕዝቡም ሳኦልን ደስ የሚያሰኝህን አድርግ አሉት። 41 ሳኦልም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን። እውነትን ግለጥ አለው። ሳኦልና ዮናታንም ተያዙ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ። 42 ሳኦልም። በእኔና በልጄ በዮናታን መካከል ዕጣ ጣሉ አለ። ዮናታንም ተያዘ። 43 ሳኦልም ዮናታንን። ያደረግኸውን ንገረኝ አለው፤ ዮናታንም። በእጄ ባለው በበትሬ ጫፍ ጥቂት ማር በእርግጥ ቀምሻለሁ፤ እነሆኝ፥ እሞታለሁ ብሎ ነገረው። 44 ሳኦልም። እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብኝ እንዲህም ይጨምርብኝ፤ ዮናታን ሆይ፥ ፈጽመህ ትሞታለህ አለ። 45 ሕዝቡም ሳኦልን። በውኑ በእስራኤል ዘንድ ታላቅ መድኃኒት ያደረገ ዮናታን ይሞታልን? ይህ አይሁን፤ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎአልና ሕያው እግዚአብሔርን! ከራሱ ጠጕር አንዲት በምድር ላይ አትወድቅም አሉት። ሕዝቡም እንዳይሞት ዮናታንን አዳነው። 46 ሳኦልም ፍልስጥኤማውያንን ከመከተል ተመለሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ስፍራቸው ሄዱ። 47 ሳኦልም መንግሥቱን በእስራኤል ላይ አጸና፤ በዙሪያውም ካሉት ከጠላቶቹ ሁሉ ጋር፥ ከሞዓብም፥ ከአሞንም ልጆች፥ ከኤዶምያስም፥ ከሱባም ነገሥታት፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ይዋጋ ነበር፤ በየሄደበትም ሁሉ ድል ይነሣ ነበር። 48 እርሱም ጀግና ነበረ፥ አማሌቃውያንንም መታ፥ እስራኤልንም ከዘራፊዎቹ እጅ አዳነ። 49 የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ የሱዊ፥ ሜልኪሳ ነበሩ፤ የሁለቱም ሴቶች ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ የታላቂቱ ስም ሜሮብ፥ የታናሺቱም ስም ሜልኮል ነበረ። 50 የሳኦልም ሚስት ስም የአኪማአስ ልጅ አኪናሆም ነበረ፤ የሠራዊቱም አለቃ ስም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ አበኔር ነበረ። 51 የሳኦልም አባት ቂስ ነበረ፤ የአበኔርም አባት ኔር የአቢኤል ልጅ ነበረ። 52 በሳኦልም ዕድሜ ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጽኑ ውጊያ ነበረ፤ ሳኦልም ጽኑ ወይም ኃያል ሰው ባየ ጊዜ ወደ እርሱ ይሰበስብ ነበር።

1 ሳሙኤል 15

1 ሳሙኤልም ሳኦልን አለው። በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እቀባህ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ፥ አሁንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ስማ። 2 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ እየተቃወመ ያደረገበትን እበቀላለሁ። 3 አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል። 4 ሳኦልም ሕዝቡን ጠርቶ በጌልገላ ቈጠራቸው፤ ሁለት መቶ ሺህ እግረኞች፥ ከይሁዳም አሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ። 5 ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ወጣ፥ በሸለቆውም ውስጥ ተደበቀ። 6 ሳኦል ቄናውያንን። ተነሥታችሁ ሂዱ፤ ከግብጽ በወጡ ጊዜ ለእስራኤል ልጆች ቸርነት አድርጋችኋልና ከአማሌቅ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከመካከላቸው ውረዱ አላቸው፤ ቄናውያንም ከአማሌቃውያን መካከል ሄዱ። 7 ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብጽ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው። 8 የአማሌቅንም ንጉሥ አጋግን በሕይወቱ ማረከው፥ ሕዝቡንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው። 9 ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት። 10 11 የእግዚአብሔርም ቃል። ሳኦል እኔ ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቈጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 12 ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ። ሳኦልም ወደ ቀርሜሎስ መጣ፤ እነሆም፥ የመታሰቢያ ዓምድ ባቆመ ጊዜ ዞሮ አለፈ፥ ወደ ጌልገላም ወረደ የሚል ወሬ ለሳሙኤል ደረሰለት። 13 ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም። አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው። 14 ሳሙኤልም። ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ። 15 ሳኦልም። ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፤ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው። 16 ሳሙኤልም ሳኦልን። ቆይ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት የነገረኝን ልንገርህ አለው፤ እርሱም። ተናገር አለው። 17 ሳሙኤልም አለ። በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ። 18 እግዚአብሔርም። ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ። 19 ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ? 20 ሳኦልም ሳሙኤልን። የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። 21 ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው። 22 ሳሙኤልም። በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። 23 ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። 24 ሳኦልም ሳሙኤልን። ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ። 25 አሁንም፥ እባክህ፥ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው። 26 ሳሙኤልም ሳኦልን። የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም አለው። 27 ሳሙኤልም ሊሄድ ዘወር ባለ ጊዜ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፥ ተቀደደም። 28 ሳሙኤልም። እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት፤ 29 የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው። 30 እርሱም። በድያለሁ፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው። 31 ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ። 32 ሳሙኤልም። የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም። በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ። 33 ሳሙኤልም። ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፤ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቈራረጠው። 34 ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ፤ 35 ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።

1 ሳሙኤል 16

1 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው። 2 ሳሙኤልም። እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም። አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል። 3 እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው። 4 ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና። የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት። 5 እርሱም። ለደኅንነት ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው። 6 እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። 7 እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን። ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። 8 እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። 9 እሴይም ሣማን አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። 10 እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን። እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው። 11 ሳሙኤልም እሴይን። የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም። ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን። እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው። 12 ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም። ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ። 13 ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። 14 የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው። 15 የሳኦልም ባሪያዎች። እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፤ 16 በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። 17 ሳኦልም ባሪያዎቹን። መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። 18 ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ። እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ። 19 ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ። 20 እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። 21 ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። 22 ሳኦልም ወደ እሴይ። በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ። 23 እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።

1 ሳሙኤል 17

1 ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን በይሁዳ ባለው በሰኮት አከማቹ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌስደሚም ሰፈሩ። 2 ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ተከማቹ፥ በዔላ ሸለቆም ሰፈሩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። 3 ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። 4 ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ። 5 በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ። 6 በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። 7 የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 8 እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ። ለሰልፍ ትሠሩ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል ባሪያዎች አይደላችሁምን? ለእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፥ ወደ እኔም ይውረድ፤ 9 ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፥ ለእኛም ትገዛላችሁ አለ። 10 ፍልስጥኤማዊውም። ዛሬ የእስራኤልን ጭፎሮች ተገዳደርኋቸው፤ እንዋጋ ዘንድ አንድ ሰው ስጡኝ አለ። 11 ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ እንዲህ የሚላቸውን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ደነገጡም። 12 ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንትም ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። 13 የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ ሁለተኛውም አሚናዳብ ሦስተኛውም ሣማ ነበረ። 14 ዳዊት የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆች ሳኦልን ተከትለው ነበር። 15 ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። 16 ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ ይቀርብ፥ አርባ ቀንም ይታይ ነበር። 17 እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው። ከዚህ ከተጠበሰው እሸት አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም አሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፥ ወደ ሰፈሩም ወደ ወንድሞችህ ፈጥነህ አድርሳቸው፤ 18 ይህንም አሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ። 19 ሳኦልና እነርሱ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በዔላ ሸለቆ ነበሩ። 20 ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። 21 እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር። 22 ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። 23 እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ። 24 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ። 25 የእስራኤልም ሰዎች። ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ። 26 ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች። ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። 27 ሕዝቡም። ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። 28 ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ የኤልያብም ቍጣ በዳዊት ላይ ነድዶ። ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው። 29 ዳዊትም። እኔ ምን አደርግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ። 30 ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። 31 ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም አስጠራው። 32 ዳዊትም ሳኦልን። ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። 33 ሳኦልም ዳዊትን። አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። 34 ዳዊትም ሳኦልን አለው። እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። 35 በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። 36 እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። 37 ዳዊትም። ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን። ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው። 38 ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው። 39 ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን። አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው። 40 ዳዊትም አወለቀ። በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ። 41 ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 42 ጎልያድም ዳዊትን ትኵር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። 43 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። 44 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን። ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። 45 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው። አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46 እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ 47 ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል። 48 ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። 49 ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፤ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። 50 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። 51 ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52 የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎች ተነሥተው እልል አሉ፥ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በርድረስ አሳደዱአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ከሸዓራይም ጀምሮ እስከ ጌትና እስከ አቃሮን ድረስ በመንገድ ላይ የተመቱት ወደቁ። 53 የእስራኤልም ልጆች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራቸውን በዘበዙ። 54 ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ጋሻ ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው። 55 ሳኦልም ዳዊትን ወደ ፍልስጥኤማዊው ሲወጣ ባየው ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው? አለው። አበኔርም። ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! አላውቅም አለ። 56 ንጉሡም። ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅ አለ። 57 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አበኔር ወሰደው፥ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፤ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር። 58 ሳኦልም። አንተ ብላቴና፥ የማን ልጅ ነህ? አለው። ዳዊትም። እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ ብሎ መለሰ።

1 ሳሙኤል 18

1 ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። 2 በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም። 3 ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 4 ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ሸለመው። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው። 5 ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፤ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፤ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይን እና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ። 6 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። 7 ሴቶችም። ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። 8 ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፤ እርሱም። ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ። 9 ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው። 10 በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ።ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። 11 ሳኦልም። ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። 12 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13 ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። 14 ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 15 ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። 16 ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ። 17 ሳኦልም ዳዊትን። ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል አለው። ሳኦልም። የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር። 18 ዳዊትም ሳኦልን። ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው። 19 ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች። 20 የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው። 21 ሳኦልም። ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፤ ሳኦልም ዳዊትን። ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው። 22 ሳኦልም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው። 23 የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም። እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ። 24 የሳኦልም ባሪያዎች። ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት። 25 ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ። የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው። 26 የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው። 27 ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም መቶ ሰዎች ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። 28 ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት። 29 ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። 30 የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

1 ሳሙኤል 19

1 ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። 2 ዮናታንም። አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፤ 3 እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። 4 ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። እርሱ አልበደለህምና። ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ 5 ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ፤ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ። 6 ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። 7 ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። 8 ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ። 9 ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። 10 ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። 11 ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል። በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው። 12 ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ። 13 ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው። 14 ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም። ታምሞአል አለቻቸው። 15 ሳኦልም። እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ። 16 መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ። 17 ሳኦልም ሜልኮልን። ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል። እርሱ። አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት። 18 ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፥ ወደ አርማቴምም ወደ ሳሙኤል መጣ፥ ሳኦልም ያደረገበትን ሁሉ ነገረው፤ እርሱና ሳሙኤልም ሄዱ በነዋትዘራማም ተቀመጡ። 19 ሳኦልም። ዳዊት፥ እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ተቀምጦአል የሚል ወሬ ሰማ። 20 ሳኦልም ዳዊትን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ሰደደ፤ የነቢያት ጉባኤ ትንቢት ሲናገሩ፥ ሳሙኤልም አለቃቸው ሆኖ ሲቆም ባዩ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል መልእክተኞች ላይ ወረደ፥ እነርሱም ትንቢት ይናገሩ ጀምር። 21 ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። ሳኦልም እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ሰደደ፥ እነርሱም ደግሞ ትንቢት ተናገሩ። 22 የሳኦልም ቍጣ ነደደ፥ እርሱም ደግሞ ወደ አርማቴም መጣ፥ በሤኩም ወዳለው ወደ ታላቁ የውኃ ጕድጓድ ደረሰ። ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው? ብሎ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። እነሆ፥ በአርማቴም አገር በነዋትዘራማ ናቸው አለው። 23 ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ ሄደ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ደግሞ ወረደ፥ እርሱም ሄደ፥ ወደ አርማቴምም አገር ወደ ነዋትዘራማ እስኪመጣ ድረስ ትንቢት ይናገር ነበር። 24 ልብሱንም አወለቀ፥ በሳሙኤልም ፊት ትንቢት ተናገረ፥ ራቁቱንም ወድቆ በዚያ ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ ተጋደመ። ስለዚህ። ሳኦል ደግሞ ከነቢያት መካከል ነውን? ይባባሉ ነበር።

1 ሳሙኤል 20

1 ዳዊትም ከአርማቴም አገር ከነዋትዘራማ ሸሸ፥ ወደ ዮናታንም መጥቶ። ምን አደረግሁ? እኔንስ ለመግደል የሚፈልግ በአባትህ ፊት ጠማምነቴና ኃጢአቴ ምንድር ነው? ብሎ ተናገረው። 2 ዮናታንም። ይህንስ ያርቀው፥ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ትንሽም ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም አለው። 3 ዳዊትም። እኔ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም። ዮናታን እንዳይከፋው አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ያህል ቀርቶአል ብሎ ማለ። 4 ዮናታንም ዳዊትን። ነፍስህ የወደደችውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው። 5 ዳዊትም ዮናታንን አለው። እነሆ፥ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ሦስተኛው ቀን ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ። 6 አባትህም ቢፈልገኝ። ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው። 7 እርሱም። መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ደኅንነት ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች እወቅ። 8 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነት አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ? 9 ዮናታንም። ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈጠረች ያወቅሁ እንደ ሆነ አልነግርህምን? አለ። 10 ዳዊትም ዮናታንን። አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆን ማን ይነግረኛል? አለው። 11 ዮናታንም ዳዊትን። ና ወደ ሜዳ እንውጣ አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። 12 ዮናታንም ዳዊትን አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁን፤ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ፥ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ ልኬ እገልጥልሃለሁ፤ 13 አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ እኔም ባላስታውቅህ በደህና ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 14 እኔም እንዳልሞት በሕይወቴ ዘመን የእግዚአብሔርን ቸርነት አድርግልኝ፤ 15 ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱ ከምድር ባጠፋቸው ጊዜ ለዘላለም ቸርነትህን ከቤቴ አታርቀው። 16 ዮናታንም። እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 17 ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት። 18 ዮናታንም አለው። ነገ መባቻ ነው፥ መቀመጫህም ባዶ ሆኖ ይገኛልና ትታሰባለህ። 19 ሦስት ቀንም ያህል ቆይ፤ ከዚህም በኋላ ፈጥነህ ውረድ፥ ነገሩም በተደረገበት ቀን ወደ ተሸሸግህበት ስፍራ ሂድ፥ በኤዜል ድንጋይም አጠገብ ቆይ። 20 እኔም በዓላማ ላይ እወረውራለሁ ብዬ ሦስት ፍላጻዎችን ወደ አጠገቡ እወረውራለሁ። 21 እነሆም። ሂድ ፍላጻዎችን ፈልግ ብዬ ብላቴናውን እልከዋለሁ፤ ብላቴናውንም። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ይዘኸው ወደ እኔ ና ያልሁት እንደ ሆነ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! ለአንተ ደኅንነት ነውና ምንም የለብህም። 22 ብላቴናውን ግን። እነሆ፥ ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ያልሁት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር አሰናብቶሃልና መንገድህን ሂድ። 23 አንተና እኔም ስለ ተነጋገርነው፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለዘላለም በመካከላችን ምስክር ነው። 24 ዳዊትም በሜዳው ተሸሸገ፤ መባቻም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ግብር ለመብላት ተቀመጠ። 25 ንጉሡም እንደ ቀድሞው በግንቡ አጠገብ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮናታንም ቆሞ ነበር፥ አበኔርም በሳኦል አጠገብ ተቀመጠ፤ የዳዊትም ስፍራ ባዶውን ነበረ። 26 ሳኦልም። አንድ ነገር ሆኖአል፥ ንጹሕም አይደለም፤ በእውነት ንጹሕ አይደለም ብሎ አስቦአልና በዚያን ቀን ምንም አልተናገረም። 27 ከመባቻም በኋላ በማግሥቱ በሁለተኛው ቀን የዳዊት ስፍራ ባዶውን ነበረ፤ ሳኦልም ልጁን ዮናታንን። የእሴይ ልጅ ትናንትና ወይም ዛሬ ግብር ሊበላ ያልመጣ ስለ ምን ነው? አለው። 28 ዮናታንም ለሳኦል። ዳዊት ወደ ቤተ ልሔም ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለመነኝ፤ 29 እርሱም። ዘመዶቼ በከተማ ውስጥ መሥዋዕት አላቸውና፥ ወንድሜም ጠርቶኛልና እባክህ፥ አሰናብተኝ፤ አሁንም በዓይኖችህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ልሂድና ወንድሞቼን ልይ አለ፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥ ሰደቃ አልመጣም ብሎ መለሰለት። 30 የሳኦልም ቍጣ በዮናታን ላይ ነደደና። አንተ የጠማማ ሴት ልጅ፥ የእሴይን ልጅ ለአንተ ማፈርያ ለእናትህም ኀፍረተ ሥጋ ማፈርያ እንደ መረጥህ እኔ አላውቅምን? 31 የእሴይም ልጅ በምድር ላይ በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉ አንተና መንግሥትህ አትጸኑም፤ አሁንም የሞት ልጅ ነውና ልከህ አስመጣልኝ አለው። 32 ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል። ስለ ምን ይሞታል? ያደረገውስ ምንድር ነው? ብሎ መለሰለት። 33 ሳኦልም ሊወጋው ጦሩን ወረወረበት፤ ዮናታንም አባቱ ዳዊትን ፈጽሞ ሊገድለው እንደ ፈቀደ አወቀ። 34 አባቱ ዳዊትን ስላሳፈረው ዮናታን ስለ ዳዊት አዝኖአልና እጅግ ተቈጥቶ ከሰደቃው ተነሣ፥ በመባቻውም በሁለተኛ ቀን ግብር አልበላም። 35 እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ዮናታን ከዳዊት ጋር ወደ ተቃጠረበት ቦታ ወደ ሜዳ ወጣ፥ ከእርሱም ጋር ታናሽ ብላቴና ነበረ። 36 ብላቴናውንም። ሮጠህ የምወረውራቸውን ፍላጻዎች ፈልግልኝ አለው። ብላቴናውም በሮጠ ጊዜ ፍላጻውን ወደ ማዶ ወረወረው። 37 ብላቴናውም ዮናታን ፍላጻውን ወደ ወረወረበት ስፍራ በመጣ ጊዜ ዮናታን። ፍላጻው ከአንተ ወዲያ ነው ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ። 38 ዮናታንም ደግሞ። ቶሎ ፍጠን፥ አትቆይ ብሎ ወደ ብላቴናው ጮኸ፤ የዮናታንም ብላቴና ፍላጻዎቹን ሰብስቦ ወደ ጌታው መጣ። 39 ዮናታንና ዳዊት ብቻ ነገሩን ያውቁ ነበር እንጂ ብላቴናው ምንም አያውቅም ነበር። 40 ዮናታንም መሣርያውን ለብላቴናው ሰጥቶ። ወደ ከተማ ውሰድ አለው። 41 ብላቴናውም በሄደ ጊዜ ዳዊት ከስፍራው በደቡብ አጠገብ ተነሣ፥ በምድርም ላይ በግምባሩ ተደፋ፥ ሦስት ጊዜም ለሰላምታ ሰገደ፤ እየተላቀሱም እርስ በእርሳቸው ተሳሳሙ፥ ይልቁንም ዳዊት እጅግ አለቀሰ። 42 ዮናታንም ዳዊትን። በደኅና ሂድ፤ እነሆ፥ እኛ ሁለታችን በእኔና በአንተ፥ በዘሬና በዘርህ መካከል ለዘላለም እግዚአብሔር ይሁን ብለን በእግዚአብሔር ስም ተማምለናል አለው። ዳዊትም ተነሥቶ ሄደ፤ ዮናታንም ወደ ከተማ ገባ።

1 ሳሙኤል 21

1 ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቢሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፤ አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና። ስለ ምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለ ምን ማንም የለም? አለው። 2 ዳዊትም ካህኑን አቢሜሌክን። የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፤ ስለዚህም ብላቴኖቹን እንዲህ ባለ ስፍራ ተውኋቸው። 3 አሁንስ በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን በእጄ ስጠኝ አለው። 4 ካህኑም ለዳዊት መልሶ። ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፥ ነገር ግን የተቀደስ እንጀራ አለ፤ ብላቴኖቹ ከሴቶቹ ንጹሐን እንደ ሆኑ መብላት ይቻላል አለው። 5 ዳዊትም ለካህኑ መልሶ። በእውነት ከወጣን ጀምረን እኛ ሰውነታችንን ከሴቶች ሦስት ቀን ጠብቀናል፤ የብላቴኖችም ዕቃ የተቀደሰች ናት፤ ስለዚህ ዛሬ ዕቃቸው የተቀደሰች በመሆንዋ እንጀራው እንደሚበላ እንጀራ ይሆናል አለው። 6 ካህኑም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ ከእግዚአብሔር ፊት ከተነሣው ከገጹ ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የተቀደሰውን እንጀራ ሰጠው። 7 በዚያም ቀን ከሳኦል ባሪያዎች አንድ ሰው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት ተገኝቶ ነበር፤ ስሙም ኤዶማዊው ዶይቅ ነበረ፥ ለሳኦልም የእረኞቹ አለቃ ነበረ። 8 ዳዊትም አቢሜሌክን። የንጉሥ ጉዳይ ስላስቸኰለኝ ሰይፌንና መሣሪያዬን አላመጣሁምና በአንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አለ ወይ? አለው። 9 ካህኑም። በኤላ ሸለቆ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ፥ እነሆ፥ በመጎናጸፊያ ተጠቅልሎ ከዚህ ከኤፉዱ በኋላ አለ፤ ትወድደውም እንደ ሆነ ውሰደው፤ ሌላ ከዚህ የለም አለ። ዳዊትም። እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱን ስጠኝ አለው። 10 ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ሳኦልን ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ። 11 የአንኩስ ባሪያዎችም። ይህ ዳዊት የአገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን? አሉት። 12 ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፥ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ። 13 በፊታቸውም አእምሮውን ለወጠ፥ በያዙትም ጊዜ እንደ እብድ ሆነ፥ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፥ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር። 14 አንኩስም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፤ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እብድ ጠፍቶብኝ ነውን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን? አላቸው።

1 ሳሙኤል 22

1 ዳዊትም ከዚያ ተነሣ ወደ ዓዶላም ዋሻ ኮበለለ፤ ወንድሞቹና የአባቱም ቤተ ሰብ ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ ወደዚያ ወረዱ። 2 የተጨነቀውም ሁሉ፥ ብድርም ያለበት ሁሉ፥ የተከፋም ሁሉ ወደ እርሱ ተከማቸ፤ እርሱም በላያቸው አለቃ ሆነ፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። 3 ዳዊትም ከዚያ በሞዓብ ምድር ወዳለችው ወደ ምጽጳ ሄደ፤ የሞዓብንም ንጉሥ። እግዚአብሔር የሚያደርግልኝን እስካውቅ ድረስ አባቴና እናቴ ከአንተ ጋር ይቀመጡ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 4 በሞዓብም ንጉሥ ፊት አመጣቸው፤ ዳዊትም በአምባ ውስጥ በነበረበት ወራት ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀመጡ። 5 ነቢዩ ጋድም ዳዊትን። ተነሥተህ ወደ ይሁዳ ምድር ሂድ እንጂ በአምባው ውስጥ አትቀመጥ አለው፤ ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ሔሬት ዱር መጣ። 6 ሳኦልም ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንደ ተገለጡ ሰማ። ሳኦልም በጊብዓ በአጣጥ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ በእጁም ጦር ይዞ ነበር፤ ባሪያዎቹም ሁሉ በአጠገቡ ቆመው ነበር። 7 ሳኦልም በአጠገቡ የቆሙትን ባሪያዎቹን። ብንያማውያን ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ የእሴይ ልጅ እርሻና የወይን ቦታ ለሁላችሁ ይሰጣችኋልን? ሁላችሁንስ ሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋችኋልን? 8 ሁላችሁ በላዬ ዶልታችሁ ተነሣችሁብኝ፤ ልጄ ከእሴይ ልጅ ጋር ሲማማል ምንም አይገልጥልኝም፤ ከእናንተም አንድ ለእኔ የሚያዝን የለም፥ ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ልጄ ባሪያዬን እንዲዶልት ሲያስነሣብኝ ማንም አላስታወቀኝም አላቸው። 9 በሳኦልም ባሪያዎች አጠገብ የቆመው ኤዶማዊው ዶይቅ መልሶ። የእሴይ ልጅ ወደ ኖብ ወደ አኪጦብ ልጅ ወደ አቢሜሌክ ሲመጣ አይቼዋለሁ። 10 እግዚአብሔርንም ጠየቀለት፥ ስንቅንም ሰጠው፥ የፍልስጥኤማዊውንም የጎልያድን ሰይፍ ሰጠው አለ። 11 ንጉሡም የአኪጦብን ልጅ ካህኑን አቢሜሌክን በኖብም ያሉትን ካህናት የአባቱን ቤት ሁሉ ልኮ አስጠራቸው፤ ሁላቸውም ወደ ንጉሡ መጡ። 12 ሳኦልም። የአኪጦብ ልጅ ሆይ፥ እንግዲህ ስማ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ፥ ጌታዬ ሆይ ብሎ መለሰ። 13 ሳኦልም። አንተና የእሴይ ልጅ ለምን ዶለታችሁብኝ? እንጀራና ሰይፍ ሰጠኸው፥ ዛሬም እንደ ተደረገው ጠላት ሆኖ ይነሣብኝ ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ እርሱ ጠየቅህለት አለው። 14 አቢሜሌክም መልሶ ንጉሡን። ከባሪያዎችህ ሁሉ የታመነ፥ ለንጉሥም አማች የሆነ፥ በትእዛዝህ የሚሄድ፥ በቤትህም የከበረ እንደ ዳዊት ያለ ማን ነው? 15 በውኑ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ ዛሬ ጀመርሁን? ይህ ከእኔ ይራቅ፤ እኔ ባሪያህ ይህን ሁሉ እጅግ ወይም ጥቂት ቢሆን አላውቅምና ንጉሡ እንደዚህ ያለውን ነገር በእኔ በባሪያውና በአባቴ ቤት ሁሉ ላይ አያኑር አለ። 16 ንጉሡም። አቢሜሌክ ሆይ። አንተና የአባትህ ቤት ሁሉ ፈጽማችሁ ትሞታላችሁ አለ። 17 ንጉሡም በዙሪያው የቆሙትን እግረኞች። የእግዚአብሔር ካህናት እጅ ከዳዊት ጋር ነውና፥ ኵብለላውንም ሲያውቁ በጆሮዬ አልገለጡምና ዞራችሁ ግደሉአቸው አላቸው። የንጉሡ ባሪያዎች ግን እጃቸውን በእግዚአብሔር ካህናት ላይ ይዘረጉ ዘንድ እንቢ አሉ። 18 ንጉሡም ዶይቅን። አንተ ዞረህ በካህናቱ ላይ ውደቅባቸው አለው። ኤዶማዊውም ዶይቅ ዞሮ በካህናቱ ላይ ወደቀ፥ በዚያም ቀን የበፍታ ኤፉድ የለበሱትን ሰማንያ አምስት ሰዎች ገደለ። 19 የካህናቱም ከተማ ኖብን በሰይፍ ስለት መታ፤ ወንዶችንና ሴቶችንም፥ ብላቴኖችንና ጡት የሚጠቡትን፥ በሬዎችንና አህዮችንም በጎችንም በሰይፍ ስለት ገደለ። 20 ከአኪጦብም ልጅ ከአቢሜሌክ ልጆች ስሙ አብያታር የሚባል አንዱ ልጅ አምልጦ ወደ ዳዊት ሸሸ። 21 አብያታርም ሳኦል የእግዚአብሔርን ካህናት እንደ ፈጀ ለዳዊት ነገረው። 22 ዳዊት አብያታርን። ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያ መኖሩን ባየሁ ጊዜ። ለሳኦል በእርግጥ ይነግራል ብዬ በዚያው ቀን አውቄዋለሁ፤ ለአባትህ ቤት ነፍስ ሁሉ የጥፋታቸው ምክንያት እኔ ነኝ። 23 ነፍሴን የሚፈልግ የአንተን ነፍስ ይፈልጋልና፥ ከእኔም ጋር ተጠብቀህ ትኖራለህና በእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አትፍራ አለው።

1 ሳሙኤል 23

1 ለዳዊትም። እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ቅዒላን ይወጋሉ፥ አውድማውንም ይዘርፋሉ የሚል ወሬ ደረሰው። 2 ዳዊትም። ልሂድን? እነዚህንስ ፍልስጥኤማውያን ልምታን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን። ሂድ፥ ፍልስጥኤማውያንን ምታ ቅዒላንም አድን አለው። 3 የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ በዚህ በይሁዳ መቀመጥ እንፈራለን፥ ይልቁንስ በፍልስጥኤማውያን ጭፍሮች ላይ ወደ ቅዒላ ብንሄድ እንዴት ነው? አሉት። 4 ዳዊትም ደግሞ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም መልሶ። ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጣለሁና ተነሥተህ ወደ ቅዒላ ውረድ አለው። 5 ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ቅዒላ ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ እንስሶቻቸውንም ማረኩ፥ በታላቅም አገዳደል ገደሉአቸው። ዳዊትም በቅዒላ የሚኖሩትን አዳነ። 6 እንዲህም ሆነ፤ የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ዳዊት ወደ ቅዒላ በኰበለለ ጊዜ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር። 7 ሳኦልም ዳዊት ወደ ቅዒላ እንደ መጣ ሰማ፤ ሳኦልም። መዝጊያና መወርወሪያ ወዳለባት ከተማ ገብቶ ተገኝቶአልና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶታል አለ። 8 ሳኦልም ወደ ቅዒላ ወርደው ይዋጉ ዘንድ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ይከብቡ ዘንድ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ። 9 ዳዊትም ሳኦል ክፉን እንዳሰበበት አወቀ፤ ካሁኑን አብያታርንም። ኤፉዱን ወደዚህ አምጣ አለው። 10 ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በእኔ ምክንያት ከተማይቱን ያጠፋ ዘንድ ሳኦል ወደ ቅዒላ ሊመጣ እንደሚፈልግ እኔ ባሪያህ ፈጽሜ ሰምቻለሁ። 11 የቅዒላ ሰዎች በእጁ አሳልፈው ይሰጡኛልን? ባሪያህስ እንደ ሰማ ሳኦል በውኑ ይወርዳልን? የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ እንድትነግረኝ እለምንሃለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ይወርዳል አለ። 12 ዳዊትም። የቅዒላ ሰዎች እኔንና ሰዎቼን በሳኦል እጅ አሳልፈው ይሰጡናልን? አለ። እግዚአብሔርም። አሳልፈው ይሰጡአችኋል ብሎ ተናገረ። 13 ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎችም ተነሥተው ከቅዒላ ወጡ፥ መሄድም ወደሚችሉበት ሄዱ። ሳኦልም ዳዊት ከቅዒላ እንደ ሸሸ ሰማ፤ ስለዚህም ከመውጣት ቀረ። 14 ዳዊትም በምድረ በዳ በአምባ ውስጥ ይኖር ነበር፥ ከዚፍ ምድረ በዳም ባለው በተራራማው አገር ተቀመጠ፤ ሳኦልም ሁልጊዜ ይፈልገው ነበር፥ እግዚአብሔር ግን በእጁ አሳልፎ አልሰጠውም። 15 ዳዊትም ሳኦል ነፍሱን ሊፈልግ እንደ ወጣ አየ፤ ዳዊትም በዚፍ ምድረ በዳ በጥሻው ውስጥ ይኖር ነበር። 16 የሳኦልም ልጅ ዮናታን ተነሥቶ ወደ ዳዊት ወደ ጥሻው ስጥ ሄደ፤ እጁንም በእግዚአብሔር አጽንቶ። 17 የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፤ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፤ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው። 18 ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ። 19 የዚፍ ሰዎችም ወደ ሳኦል ወደ ጊብዓ መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ደቡብ በኩል በኤኬላ ኮረብታ ላይ በጥሻ ውስጥ ባሉት አምባዎች በእኛ ዘንድ ተሸሽጎ የለምን? 20 አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ ትወርድ ዘንድ ነፍስህ እንደ ወደደች ውረድ፤ በንጉሡም እጅ እርሱን አሳልፎ ለመስጠት እኛ አለን አሉት። 21 ሳኦልም አለ። እናንተ ስለ እኔ አዝናችኋልና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረካችሁ ሁኑ፤ 22 አሁንም ደግሞ ሂዱ፤ እርሱም እጅግ ተንኰለኛ እንደ ሆነ ሰምቻለሁና አጥብቃችሁ ፈልጉት፥ እግሩም የሚሄድበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በዚያ ያየውንም ሰው አግኙ። 23 እርሱ የሚደበቅበትንና የሚሸሸግበትን ስፍራ እዩና እወቁ፥ በእርግጥም ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምድርም ውስጥ ቢሸሸግ በይሁዳ አእላፋት ሁሉ መካከል እፈልገዋለሁ። 24 እነዚያም ተነሥተው ከሳኦል በፊት ወደዚፍ ሄዱ፤ ዳዊትና ሰዎቹ ግን በየሴሞን ደቡብ በኩል በዓረባ በማዖን ምድረ በዳ ነበሩ። 25 ሳኦልና ሰዎቹም ሊፈልጉት ሄዱ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ዓለቱ ወርዶ በማዖን ምድረ በዳ ተቀመጠ፤ ሳኦልም ያንን በሰማ ጊዜ ዳዊትን በማዖን ምድረ በዳ አሳደደው። 26 ሳኦልም በተራራው በአንድ ወገን ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም በተራራው በሌላው ወገን ሄዱ። ሳኦልና ሰዎቹም ዳዊትንና ሰዎቹን ለመያዝ ከብበዋቸው ነበርና ዳዊት ከሳኦል ፊት ያመልጥ ዘንድ ፈጠነ። 27 ወደ ሳኦልም መልእክተኛ መጥቶ። ፍልስጥኤማውያን አገሩን ወርረውታልና ፈጥነህ ና አለው። 28 ሳኦልም ዳዊትን ማሳደድ ትቶ ተመለሰ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጋ ሄደ። ስለዚህ የዚህ ስፍራ ስም የማምለጥ ዓለት ተባለ። 29 ዳዊትም ከዚያ ወጥቶ በዓይንጋዲ አምባዎች ተቀመጠ።

1 ሳሙኤል 24

1 እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ። እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት። 2 ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ። 3 በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፤ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። 4 የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገረህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቈረጠ። 5 ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቈረጠ የዳዊት ልብ በኀዘን ተመታ። 6 ሰዎቹንም። እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው። 7 ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፤ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ። 8 ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፤ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጐንብሶ እጅ ነሣ። 9 ዳዊትም ሳኦልን አለው። እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ? 10 እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፤ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተናገሩኝ፤ እኔ ግን። በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ። 11 ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፤ የልብስህንም ዘርፍ በቈረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፤ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ። 12 እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። 13 በጥንት ምሳሌ። ከኃጢአተኞች ኀጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። 14 የእስራኤል ንጉሥ ማንን ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን? 15 እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ። 16 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል። ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፤ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 17 ዳዊትን አለው። እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። 18 እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ። 19 ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። 20 አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ። 21 አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቈርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ። 22 ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ።

1 ሳሙኤል 25

1 ሳሙኤልም ሞተ፤ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ። 2 በማዖንም የተቀመጠ አንድ ሰው ነበረ፥ ከብቱም በቀርሜሎስ ነበረ፤ እጅግም ታላቅ ሰው ነበረ፥ ለእርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር። 3 የሰውዮውም ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ፤ የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፤ ሰውዮው ግን ባለጌ ነበረ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፤ ከካሌብም ወገን ነበረ። 4 ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ። ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ። 5 ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ። ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፤ 6 እንዲህም በሉት። በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን። 7 አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፤ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም። 8 ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፤ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፤ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ። 9 የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ። 10 ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች። ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። 11 እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው። 12 የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት። 13 ዳዊትም ሰዎቹን። ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ። 14 ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት። እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፤ እርሱ ግን ሰደባቸው። 15 እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፤ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፤ 16 ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር። 17 ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቈርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ። 18 አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች። 19 ለብላቴኖችዋም። አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም። 20 እርስዋም በአህያው ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፤ እርስዋም ተገናኘቻቸው። 21 ዳዊትም። ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ። 22 ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው፥ እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር። 23 አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። 24 በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። 25 በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፤ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፤ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም። 26 አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። 27 አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። 28 የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፤ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። 29 ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፤ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል። 30 እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ 31 አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተካስህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ። 32 ዳዊትም አቢግያን አላት። ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። 33 ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ። 34 ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር። 35 ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ። በደኅና ወደቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት። 36 አቢግያም ወደ ናባል መጣች፤ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፤ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፤ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር። 37 በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፤ ልቡም በውስጡ ሞተ፥ 38 እንደ ድንጋይም ሆነ፤ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ። 39 ዳዊትም ናባል እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ። ከናባል እጅ የስድቤን ፍርድ የፈረደልኝ፥ ባሪያውንም ከክፋት የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እግዚአብሔርም የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰ አለ። ዳዊትም ልኮ ያገባት ዘንድ አቢግያን ተነጋገራት። 40 የዳዊትም ባሪያዎች ወደ ቀርሜሎስ ወደ አቢግያ በመጡ ጊዜ። ዳዊት ያገባሽ ዘንድ ወደ አንቺ ልኮናል ብለው ነገሩአት። 41 ተነሥታም በግምባርዋ ወድቃ እጅ ነሣችና። እነሆ፥ እኔ ገረድህ የጌታዬን ሎሌዎች እግር አጥብ ዘንድ አገልጋይ ነኝ አለች። 42 አቢግያም ፈጥና ተነሣች፤ በአህያም ላይ ተቀመጠች፥ አምስቱም ገረዶችዋ ተከተሉአት፤ የዳዊትንም መልእክተኞች ተከትላ ሄደች፥ ሚስትም ሆነችው። 43 ዳዊትም ደግሞ ኢይዝራኤላዊቱን አኪናሆምን ወሰደ፤ ሁለቱም ሚስቶች ሆኑለት። 44 ሳኦል ግን የዳዊትን ሚስት ልጁን ሜልኮልን አገሩ ጋሊም ለነበረው ለሌሳ ልጅ ለፈልጢ ሰጥቶ ነበር።

1 ሳሙኤል 26

1 የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው። እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጎአል አሉት። 2 ሳኦልም ተነሥቶ ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ይሻ ዘንድ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎች ይዞ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ። 3 ሳኦልም በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ በመንገዱ አጠገብ ሰፈረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፥ ሳኦልም በስተ ኋላው ወደ ምድረ በዳ እንደ መጣ አየ። 4 ዳዊትም ሰላዮች ሰደደ፥ ሳኦልም ወደዚህ እንደ መጣ በእርግጥ አወቀ። 5 ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ መጣ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አበኔርም የተኙበትን ስፍራ አየ፤ ሳኦልም በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር። 6 ዳዊትም ኬጢያዊውን አቢሜሌክንና የጽሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን። ወደ ሳኦል ወደ ሰፈሩ ከእኔ ጋር የሚወርድ ማን ነው? ብሎ ጠየቃቸው፤ አቢሳም። እኔ ከአንተ ጋር እወርዳለሁ አለ። 7 ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፤ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩ በራሱ አጠገብ በምድር ተተክሎ በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ አበኔርና ሕዝቡም በዙርያው ተኝተው ነበር። 8 አቢሳም ዳዊትን። ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው። 9 ዳዊትም አቢሳን። እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው። 10 ደግሞም ዳዊት። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፤ 11 እኔ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ። 12 ዳዊትም በሳኦል ራስ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውኃውን መንቀል ወሰደ፤ ማንም ሳያይ ሳያውቅም ሄዱ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ወድቆባቸው ነበርና ሁሉ ተኝተው ነበር እንጂ የነቃ አልነበረም። 13 ዳዊትም ወደዚያ ተሻገረ፤ በተራራውም ራስ ላይ ርቆ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ስፍራ ነበረ። 14 ዳዊትም ለሕዝቡና ለኔር ልጅ ለአበኔር። አበኔር ሆይ፥ አትመልስምን? ብሎ ጮኸ። አበኔርም መልሶ። ለንጉሡ የምትጮኸው አንተ ማን ነህ? አለ። 15 ዳዊትም አበኔርን። አንተ ጕልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለ ምን ነው? 16 ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል፤ አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃው መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት አለው። 17 ሳኦልም የዳዊት ድምፅ እንደ ሆነ አውቆ። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለው። ዳዊትም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ድምፄ ነው አለው። 18 ደግሞ አለ። ጌታዬ ባሪያውን ስለ ምን ያሳድዳል? ምን አደረግሁ? ምንስ ክፋት በእጄ ላይ ተገኘብኝ? 19 አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የእኔን የባሪያህን ቃል ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አስነሥቶህ እንደ ሆነ፥ ቁርባንን ይቀበል፤ የሰው ልጆች ግን ቢሆኑ። ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ላይ እንዳልቀመጥ ዛሬ ጥለውኛልና በእግዚአብሔር ፊት ርጉማን ይሁኑ። 20 አሁንም በተራራው ላይ ሰው ቆቅን እንደሚሻ የእስራኤል ንጉሥ ነፍሴን ለመሻት ወጥቶአልና ደሜ ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ በምድር ላይ አይፍሰስ። 21 ሳኦልም። በድያለሁ፤ ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በዓይንህ ፊት ከብራለችና ከዚህ በኋላ ክፉ አላደርግብህም እነሆ፥ ስንፍና አድርጌአለሁ፥ እጅግ ብዙም ስቻለሁ አለ። 22 ዳዊትም መልሶ አለ። የንጉሥ ጦር እነሆ፥ ከብላቴኖችም አንድ ይምጣና ይውሰዳት። 23 ዛሬም እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ አልወደድሁምና ለሁሉ እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ጽድቁና እንደ እምነቱ ፍዳውን ይክፈለው። 24 ነፍስህም ዛሬ በዓይኔ ፊት እንደ ከበረች እንዲሁ ነፍሴ በእግዚአብሔር ዓይን ፊት ትክበር፥ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ። 25 ሳኦል ዳዊትን። ልጄ ዳዊት ሆይ፥ ቡሩክ ሁን፤ ማድረግን ታደርጋለህ፥ መቻልንም ትችላለህ አለው። ዳዊትም መንገዱን ሄደ፥ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

1 ሳሙኤል 27

1 ዳዊትም በልቡ። አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ፤ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፤ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲሁም ከእጁ እድናለሁ አለ። 2 ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ። 3 ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፤ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ። 4 ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኰበለለ ሰማ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም። 5 ዳዊትም አንኩስን። በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፤ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው። 6 በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች። 7 ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቍጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበረ። 8 ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፤ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር። 9 ዳዊትም ምድሪቱን መታ፤ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፤ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ። 10 አንኩስም። ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፤ ዳዊትም። በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ። 11 ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም። 12 አንኩስም። በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፤ ስለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።

1 ሳሙኤል 28

1 እንዲህም ሆነ፤ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፤ አንኩስም ዳዊትን። አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው። 2 ዳዊትም አንኩስን። አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን። እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው። 3 ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር። 4 ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ። 5 ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። 6 ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም። 7 ሳኦልም ባሪያዎቹን። ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት። 8 ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም። እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት። 9 ሴቲቱም። እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው። 10 ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት። 11 ሴቲቱም። ማንን ላስነሣልህ? አለች፤ እርሱም። ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ። 12 ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን። አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው። 13 ንጉሡም። አትፍሪ፤ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን። አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው። 14 እርሱም። መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም። ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጐነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ። 15 ሳሙኤልም ሳኦልን። ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ። ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው። 16 ሳሙኤልም አለ። እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? 17 እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። 18 የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል። 19 እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል። 20 ሳኦልም በዚያን ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፥ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኃይል አልቀረለትም። 21 ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፥ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበረ አይታ። እነሆ፥ እኔ ባሪያህ ቃልህን ሰማሁ፥ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፥ የነገርኸኝንም ቃል ሰማሁ። 22 አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የባሪያህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፥ በፊትህም ቍራሽ እንጀራ ላኑርልህ፤ በመንገድም ስትሄድ ትበረታ ዘንድ ብላ አለችው። 23 እርሱ ግን። አልበላም ብሎ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ባሪያዎቹና ሴቲቱ አስገደዱት፥ ቃላቸውንም ሰማ፤ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ። 24 ለሴቲቱም ማለፊያ እንቦሳ ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፥ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው። 25 በሳኦልና በባሪያዎቹም ፊት አቀረበችው፤ በልተውም ተነሡ፥ በዚያም ሌሊት ሄዱ።

1 ሳሙኤል 29

1 ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ሁሉ ወደ አፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ባለው ውኃ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። 2 የፍልስጥኤማውያንም አለቆች በመቶ በመቶ በሺህ በሺህ እየሆኑ ያልፉ ነበር፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ ጋር በኋለኛው ጭፍራ በኩል ያልፉ ነበር። 3 የፍልስጥኤማውያንም አለቆች። እነዚህ ዕብራውያን በዚህ ምን ያደርጋሉ? አሉ፤ አንኩስም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች። ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ባሪያ ዳዊት አይደለምን? እርሱም በእነዚህ ቀኖች በእነዚህ ዓመታት ከእኔ ጋር ነበረ፥ ወደ እኔም ከተጠጋበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምንም አላገኘሁበትም አላቸው። 4 የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን ተቆጥተው። ይህ ሰው ባስቀመጥኸው ስፍራ ይቀመጥ ዘንድ ይመለስ፤ በሰልፉ ውስጥ ጠላት እንዳይሆነን ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይውረድ፤ ከጌታው ጋር በምን ይታረቃል? የእነዚህን ሰዎች ራስ በመቍረጥ አይደለምን? 5 ወይስ ሴቶች። ሳኦል ሺህ ገደለ፥ ዳዊት እልፍ ገደለ ብለው በዘፈን የዘመሩለት ይህ ዳዊት አይደለምን? አሉት። 6 አንኩስም ዳዊትን ጠርቶ። ሕያው እግዚአብሔርን! አንተ ቅን ነህ፥ ከእኔም ጋር በጭፍራው በኩል መውጣትህና መግባትህ በፊቴ መልካም ነው፤ ወደ እኔም ከመጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንዳች ክፋት አላገኘሁብህም፤ ነገር ግን በአለቆች ዘንድ አልተወደድህም። 7 አሁንም ተመልሰህ በደኅና ሂድ፥ በፍልስጥኤማውያንም አለቆች ዓይን ክፋት አታድርግ አለው። 8 ዳዊትም አንኩስን። ምን አድርጌአለሁ? ሄጄስ ከጌታዬ ከንጉሡ ጠላቶች ጋር እንዳልዋጋ፥ በፊትህ ከተቀመጥሁ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ በባሪያህ ምን አግኝተህብኛል? አለው። 9 አንኩስም መልሶ ዳዊትን። እንደ አምላክ መልእክተኛ በዓይኔ ፊት መልካም እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን አለቆች። ከእኛ ጋር ወደ ሰልፍ አይወጣም አሉ። 10 አሁንም አንተ ከአንተም ጋር የመጡ የጌታህ ባሪያዎች ማልዳችሁ ተነሡ፤ ሲነጋም ተነሥታችሁ ሂዱ አለው። 11 ዳዊትና ሰዎቹም ማልደው ይሄዱ ዘንድ፥ ወደ ፍልስጥኤማውያንም አገር ይመለሱ ዘንድ ተነሡ። ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።

1 ሳሙኤል 30

1 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፤ 2 ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር። 3 ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ። 4 ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ። 5 የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር። 6 ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ። 7 ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን። ኤፉዱን አቅርብልኝ አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት። 8 ዳዊትም። የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት። 9 ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፥ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፤ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ። 10 ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፤ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ። 11 በበረሀውም ውስጥ አንድ ግብጻዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፤ እንጀራም ሰጡትና በላ፥ ውኃም አጠጡት፤ 12 ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች። 13 ዳዊትም። አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ፤ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። 14 እኛም በከሊታውያን ደቡብ፥ በይሁዳም ምድር፥ በካሌብም ደቡብ ላይ ዘመትን፤ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልናት አለ። 15 ዳዊትም። ወደ እነዚያ ሠራዊት ዘንድ ልትመራኝ ትወድዳለህን? አለው፤ እርሱም። እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ አለ። 16 ወደ ታችም እንዲወርድ ባደረገው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው ጠጥተውም የበዓልም ቀን አድርገው በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው ነበር። 17 ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ማታ ድረስ መታቸው፤ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹ ከአራት መቶ ጕልማሶች በቀር አንድ ያመለጠ የለም። 18 ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ። 19 ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱትም ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የጐደለባቸው የለም፤ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ። 20 ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፥ ከራሱም ከብት ፊት እየነዳ። ይህ የዳዊት ምርኮ ነው አለ። 21 ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። 22 ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ። እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም አሉ። 23 ዳዊትም። ወንድሞቼ ሆይ፥ የጠበቀን በእኛም ላይ የመጣውን ጭፍራ በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እግዚአብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ፤ 24 ይህንስ ነገ ማን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት እድል ፈንታ እኩል ይሆናል፥ አንድነት ይካፈላሉ አለ። 25 ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ፍርድ አደረገው። 26 ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ ለዘመዶቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች። እነሆ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ ብሎ ከምርኮው ሰደደላቸው። 27 በቤቴል ለነበሩ፥ በራሞት በደቡብ ለነበሩ 28 በየቲር ለነበሩ፥ በአሮዔር ለነበሩ፥ በሢፍሞት ለነበሩ፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ፥ 29 በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞችም ለነበሩ፥ 30 በሔርማ ለነበሩ፥ በቦራሣን ለነበሩ፥ በዓታክ ለነበሩ፥ በኬብሮን ለነበሩ፥ 31 ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።

1 ሳሙኤል 31

1 ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። 2 ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። 3 ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ። 4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወደቀ፥ ከእርሱም ጋር ሞተ። 6 በዚያም ቀን ሳኦል ሦስቱም ልጆቹ ጋሻ ጃግሬውም ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። 7 በሸለቆውም ማዶና በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰዎች እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8 በማግሥቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9 የሳኦልንም ራስ ቈረጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ። 10 የጦር ዕቃውንም በአስታሮት መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውንም በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት። 11 ፍልስጥኤማውያንም በሳኦል ላይ ያደረጉትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች በሰሙ ጊዜ፥ 12 ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፥ በዚያም አቃጠሉት። 13 አጥንታቸውንም ወሰዱ በኢያቢስም ባለው በአጣጡ ዛፍ በታች ቀበሩት፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።

2 ሳሙኤል 1

1 እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ። 2 በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ። 3 ዳዊትም። ከወዴት መጣህ? አለው እርሱም። ከእስራኤል ሰፈር ኰብልዬ መጣሁ አለው። 4 ዳዊትም። ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ። ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ። 5 ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው። 6 ወሬኛውም ጕልማሳ አለ። በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኵዞ ቆሞ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። 7 ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁ። 8 እርሱም። አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም። አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። 9 እርሱም። ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። 10 እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት። 11 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ። 12 በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። 13 ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ። አንተ ከወዴት ነህ? አለው፤ እርሱም። እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት። 14 ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው። 15 ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ። ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም። 16 ዳዊትም። እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው። 17 ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኀዘን ቅኔ ተቀኘ፥ 18 የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል። 19 የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፤ ኃያላን እንዴት ወደቁ! 20 የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቈላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፤ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ። 21 እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ። 22 ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም። 23 ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። 24 የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት። 25 ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል። 26 ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ። 27 ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!

2 ሳሙኤል 2

1 ከዚያም በኋላ ዳዊት። ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። ውጣ አለው። ዳዊትም። ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም። ወደ ኬብሮን ውጣ አለው። 2 ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። 3 ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። 4 የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት። 5 ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው። እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። 6 አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ። 7 አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፤ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል። 8 የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደመሃናይም አሻገረው፤ 9 በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። 10 የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ፤ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ። 11 ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። 12 የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። 13 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። 14 አበኔርም ኢዮአብን። ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቈራቈሱ አለው፤ ኢዮአብም። ይነሡ አለ። 15 ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አስራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ። 16 ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው። 17 በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። 18 በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፤ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ። 19 አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። 20 አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና። አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም። እኔ ነኝ አለ። 21 አበኔርም። ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውሰድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። 22 አበኔርም አሣሄልን። ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅኝቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው። 23 ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፤ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። 24 ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች። 25 የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። 26 አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ። ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው። 27 ኢዮአብም። ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ። 28 ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰልፍም አላደረገም። 29 አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ። 30 ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ። 31 የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ። 32 አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።

2 ሳሙኤል 3

1 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ብዙ ዘመን ጦርነት ሆነ፤ የዳዊት ቤት እየበረታ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ የሚሄድ ሆነ። 2 ለዳዊትም ወንድ ልጆች በኬብሮን ተወለዱለት፤ በኵሩም ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበረ። 3 ሁለተኛውም የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረች ከአቢግያ የተወለደው ዶሎሕያ ነበረ። ሦስተኛውም ከጌሹር ንጉሥ ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም ነበረ። 4 አራተኛውም የአጊት ልጅ አዶንያስ፥ አምስተኛውም የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያስ ነበረ። 5 ስድስተኛውም የዳዊት ልጅ ሚስት የዔግላ ልጅ ይትረኃም ነበረ። እነዚህም ለዳዊት በኬብሮን ተወለዱለት። 6 በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነት ሆኖ ሳለ አበኔር በሳኦል ቤት ይበረታ ነበር። 7 ለሳኦልም የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ የተባለች ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን። ወደ አባቴ ቁባት ለምን ገባህ? አለው። 8 አበኔርም በኢያቡስቴ ቃል እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹም ለዘመዶቹም ቸርነት አድርጌአለሁ፥ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፤ አንተም ዛሬ ከዚህች ሴት ጋር ስለ ሠራሁት ኃጢአት ትከስሰኛለህ፤ በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝን? 9 10 መንግሥትን ከሳኦል ቤት ያወጣ ዘንድ የዳዊትንም ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ከፍ ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ለዳዊት እንደ ማለለት እንዲሁ ከእርሱ ጋር ባላደርግ እግዚአብሔር በአበኔር ይህን ያድርግበት ይህንም ይጨምርበት። 11 ኢያቡስቴም አበኔርን ይፈራው ነበርና አንዳች ይመልስለት ዘንድ አልቻለም። 12 አበኔርም ለዳዊት። ምድሪቱ ለማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ ብለው ይነግሩት ዘንድ መልእክተኞች ሰደደለት። 13 ዳዊትም። ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፤ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም አለ። 14 ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ። በመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ ብሎ መልእክተኞችን ሰደደ። 15 ኢያቡስቴም ልኮ ከሌሳ ልጅ ከባልዋ ከፈልጢኤል ወሰዳት። 16 ባልዋም እያለቀሰ ከእርስዋ ጋር ሄደ፥ እስከ ብራቂም ድረስ ተከተላት። አበኔርም። ሂድ፥ ተመለስ አለው፤ እርሱም ተመለሰ። 17 አበኔርም ለእስራኤል ሽማግሌዎች። አስቀድሞ ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ፈልጋችሁ ነበር። 18 እግዚአብሔርም ስለ ዳዊት። በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ አድናለሁ ብሎ ተናግሮአልና እንግዲህ አሁን አድርጉ ብሎ ነገራቸው። 19 አበኔርም ደግሞ በብንያም ወገን ጆሮ ተናገረ፤ አበኔርም ደግሞ በእስራኤልና በብንያም ቤት ሁሉ መልካም የነበረውን ለዳዊት ሊነግረው ወደ ኬብሮን ሄደ። 20 አበኔርም ከሀያ ሰዎች ጋር ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጣ። ዳዊትም ለአበኔርና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21 አበኔርም ዳዊትን። ተነሥቼ ልሂድ፥ ከአንተ ጋርም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ነፍስህም እንደ ወደደች ሁሉን እንድትገዛ እስራኤልን ሁሉ ለጌታዬ ለንጉሥ ልሰብስብ አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፥ በደኅናም ሄደ። 22 በዚያን ጊዜም የዳዊት ባሪያዎችና ኢዮአብ ከዘመቻ ታላቅ ምርኮ ይዘው መጡ። አበኔር ግን ዳዊት አሰናብቶት በደኅና ሄዶ ነበር እንጂ በኬብሮን አልነበረም። 23 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረ ጭፍራ ሁሉ በመጡ ጊዜ። የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ መጣ፥ አሰናበተውም በደኅናውም ሄደ ብለው ሰዎች ለኢዮአብ ነገሩት። 24 ኢዮአብም ወደ ንጉሥ ገብቶ። ምን አደረግህ? እነሆ፥ አበኔር መጥቶልህ ነበር፤ በደኅና እንዲሄድ ስለ ምን አሰናበትኸው? 25 የኔር ልጅ አበኔር ያታልልህ ዘንድ፥ መውጫህንና መግቢያህንም ያውቅ ዘንድ፥ የምታደርገውንም ነገር ሁሉ ያስተውል ዘንድ እንደ መጣ አታውቅምን? አለው። 26 ኢዮአብም ከዳዊት በወጣ ጊዜ መልእክተኞችን ከአበኔር በኋላ ላከ፥ ከሴይርም ጕድጓድም መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም። 27 አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በበር ውስጥ በቈይታ ይናገረው ዘንድ ወደ አጠገቡ ወሰደው፤ በዚያም ለወንድሙ ለአሣሄል ደም ተበቅሎ ሆዱን መታው፥ ሞተም። 28 በኋላም ዳዊት ይህ ነገር እንደ ተደረገ በሰማ ጊዜ። ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘላለም እኔ ንጹሕ ነኝ፥ መንግሥቴም ንጹሕ ነው፤ 29 በኢዮአብ ራስ ላይና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይምጣበት፤ በኢዮአብም ቤት ፈሳሽ ነገር ያለበት ወይም ለምጻም ወይም አንካሳ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሌለው ሰው አይታጣ አለ። 30 ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳም በሰልፍ በገባዖን ወንድማቸው አሣሄልን ገድሎ ነበርና አበኔርን ገደሉት። 31 ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ። ልብሳችሁን ቅደዱ፥ ማቅም ልበሱ፥ በአበኔርም ፊት አልቅሱ አላቸው። ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። 32 አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በአበኔር መቃብር አጠገብ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር። 33 አበኔር ሰነፍ እንደሚሞት ይምታልን? 34 እጅህ አልታሰረም፥ እግርህም በሰንሰለት አልተያዘም፤ ሰው በዓመፀኞች ፊት እንደሚወድቅ አንተ እንዲሁ ወደቅህ ብሎ የልቅሶ ቅኔ ተቀኘለት። ሕዝቡም ሁሉ ዋይታ አብዝተው አለቀሱ። 35 ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፤ ዳዊት ግን። ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ ብሎ፤ ማለ። 36 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ተመለከቱ፥ ደስ አሰኛቸውም፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ንጉሥ ያደረገው ሁሉ ደስ አሰኛቸው። 37 በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉ እስራኤልም ሁሉ የኔር ልጅ የአበኔር ሞት ከንጉሡ ዘንድ እንዳልሆነ አወቁ። 38 ንጉሡም ባሪያዎቹን። ዛሬ በእስራኤል ዘንድ መኰንንና ታላቅ ሰው እንደ ወደቀ አታውቁምን? 39 እኔም ዛሬ ምንም ለመንገሥ የተቀባሁ ብሆን ደካማ ነኝ፤ እነዚህም ሰዎች የጽሩያ ልጆች በርትተውብኛል፤ እግዚአብሔር ክፋት በሠራ ላይ እንደ ክፋቱ ይመልስበት አላቸው።

2 ሳሙኤል 4

1 የሳኦልም ልጅ ኢያቡስቴ አበኔር በኬብሮን እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ እጁ ደከመች፥ እስራኤላውያንም ሁሉ ደነገጡ። 2 ለሳኦልም ልጅ ለኢያቡስቴ የጭፍራ አለቆች የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩት፤ የአንዱም ስም በዓና፥ የሁለተኛውም ስም ሬካብ ነበረ፥ ከብንያምም ልጆች የብኤሮታዊው የሬሞን ልጆች ነበሩ፤ ብኤሮትም ለብንያም ተቈጥራ ነበር። 3 ብኤሮታውያንም ወደ ጌቴም ሸሽተው ነበር፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ተጠግተው ነበር። 4 ለሳኦልም ልጅ ለዮናታን አንድ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው። የሳኦልና የዮናታን ወሬ ከኢይዝራኤል በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ፥ ሞግዚቱም አዝላው ሸሸች፤ ፈጥናም ስትሸሽ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜምፊቦስቴ ነበር። 5 የብኤሮታዊውም የሬሞን ልጆች ሬካብና በዓና ቀኑ ሲሞቅ ወደ ኢያቡስቴ ቤት መጡ፤ እርሱም በቀትር ጊዜ በምንጣፍ ላይ ተኝቶ ነበር። 6 በረኛይቱም ስንዴ ታበጥር ነበር፥ አንቀላፍታም ተኝታ ነበር፤ ሬካብና ወንድሙ በዓናም በቀስታ ገቡ። 7 ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ እርሱ በእልፍኙ በምንጣፉ ላይ ተኝቶ ሳለ መቱት፥ ገደሉትም፤ ራሱንም ቈርጠው ወሰዱት፥ በዓረባም መንገድ ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ። 8 የኢያቡስቴንም ራስ ይዘው ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጡ፥ ንጉሡንም። ነፍስህን ይሻ የነበረው የጠላትህ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ እነሆ፤ እግዚአብሔርም ዛሬ ከሳኦልና ከዘሩ ለጌታችን ለንጉሥ ተበቀለለት አሉት። 9 ዳዊትም ለብኤሮታዊው ለሬሞት ልጆች ለሬካብና ለወንድሙ ለበዓና እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነ ሕያው እግዚአብሔርን! 10 መልካም ወሬ የያዘ መስሎት። እነሆ፥ ሳኦል ሞተ ብሎ የነገረኝን የምስራቹ ዋጋ እንዲሆን ይዤ በጺቅላግ ገደልሁት። 11 ይልቁንስ በቤቱ ውስጥ በምንጣፉ ላይ ንጹሑን ሰው የገደላችሁትን እናንተን ኃጢአተኞችንማ እንዴት ነዋ? ደሙን ከእጃችሁ አልሻውምን? ከምድርም አላጠፋችሁምን? 12 ዳዊትም ጕልማሶቹን አዘዘ፥ ገደሉአቸውም፤ እጃቸውንና እግራቸውን ቈርጠው በኬብሮን በውኃ መቆሚያ አጠገብ አንጠለጠሉአቸው። የኢያቡስቴንም ራስ ወስደው በአበኔር መቃብር በኬብሮን ቀበሩት።

2 ሳሙኤል 5

1 የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን። 2 አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ እግዚአብሔርም። አንተ ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ ትሆናለህ ብሎህ ነበር አሉት። 3 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሡ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በእስራኤልም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት። 4 ዳዊትም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ልጅ ነበረ፥ አርባ ዓመትም ነገሠ። 5 በኬብሮን በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። 6 ንጉሡና ሰዎቹም በአገሩ ውስጥ ከተቀመጡት ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ እነርሱም። ዳዊት ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበርና ዳዊትን። ዕውሮችንና አንካሶችን ካላወጣህ በቀር ወደዚህ አትገባም አሉት። 7 ነገር ግን ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፥ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት። 8 በዚያም ቀን ዳዊት። ኢያቡሳውያንን የሚመታ በውኃ መሄጃው ይውጣ፤ የዳዊትም ነፍስ የምትጠላቸውን ዕውሮችንና አንካሶችን ያውጣ አለ። ስለዚህም በምሳሌ። ዕውርና አንካሳ ወደ ቤት አይግቡ ተባለ። 9 ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፥ የዳዊትም ከተማ ብሎ ጠራት። ዳዊትም ዙሪያዋን ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ ቀጠራት። 10 ዳዊትም እየበረታ ሄደ፤ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 11 የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም አናጢዎችንም ጠራቢዎችንም ላከ፤ ለዳዊትም ቤት ሠሩለት። 12 ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው፥ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ። 13 ዳዊትም ከኬብሮን ከመጣ በኋላ ሌሎቹን ቁባቶቹንና ሚስቶቹን ከኢየሩሳሌም ወሰደ፤ ለዳዊትም ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። 14 በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት ስማቸው ይህ ነው፤ ሳሙስ፥ 15 ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ 16 ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት። 17 ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ምሽጉ ወረደ። 18 ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። 19 ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን። ፍልስጥኤማውያንን በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው። 20 ዳዊትም ወደ በኣልፐራሲም መጣ፥ በዚያም መታቸውና። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በፊቴ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣልፐራሲም ብሎ ጠራው። 21 ጣዖቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው። 22 ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ መጡ፥ በራፋይምም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። 23 ዳዊትም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ አትውጣ። 24 በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ፥ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያን ጊዜ ቸኵል አለው። 25 ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ።

2 ሳሙኤል 6

1 ዳዊትም ዳግም ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ። 2 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 3 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። 4 በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት የእግዚአብሔርን ታቦት ባመጡ ጊዜ አሒዮ በታቦቱ ፊት ይሄድ ነበር። 5 ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። 6 ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። 7 የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፤ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ። 8 እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ። 9 በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? አለ። 10 ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣው ዘንድ አልወደደም፤ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባው። 11 የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያህል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። 12 ንጉሡ ዳዊትም እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው። 13 የእግዚአብሔርንም ታቦት የተሸከሙ ስድስት እርምጃ በሄዱ ጊዜ አንድ በሬና አንድ ፍሪዳ ሠዋ። 14 ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር። 15 ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ። 16 የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው። 17 የእግዚአብሔርንም ታቦት አገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ በስፍራው አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ። 18 ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ማሳረግ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ። 19 ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ። 20 ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና። ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! አለችው። 21 ዳዊትም ሜልኮልን። በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ። 22 አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ፤ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት። 23 የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።፤

2 ሳሙኤል 7

1 እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ 2 ንጉሡ ነቢዩን ናታንን። እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው። 3 ናታንም ንጉሡን። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው። 4 በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው። 56 ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። 7 ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ። ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 8 አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ 9 በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። 10 11 ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፤ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋኋላ አይናወጥ፤ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ። ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል። 12 ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 13 እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። 14 እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ፤ 15 ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 16 ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል። 17 እንደዚህ ቃል ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው። 18 ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? 19 ቤቴስ ምንድር ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ ስለ ባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። 20 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድር ነው? 21 ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። 22 ስለዚህም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። 23 ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? 24 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። 25 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘላለም አጽናው፥ እንደ ተናገርህም አድርግ። 26 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፤ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን። 27 አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ። እኔ ቤት እሠራልሃለሁ ብለህ ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ። 28 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፥ ቃልህም እውነት ነው፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 29 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘላለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት፥ እባክህ፥ ባርክ፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረክ።

2 ሳሙኤል 8

1 ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሜቴግ አማ የተባለችውን ከተማ ወሰደ። 2 ሞዓብን መታ፥ ሞዓባውያንንም በምድር ጥሎ በገመድ ሰፈራቸው፤ በሁለትም ገመድ ለሞት፥ በአንድም ገመድ ሙሉ ለሕይወት ሰፈራቸው፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። 3 ዳዊትም ደግሞ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ የረአብን ልጅ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን መታ። 4 ዳዊትም ከእርሱ ሺህ ሰባት መቶ ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ያዘ፤ ዳዊትም የሰረገለኛውን ፈረስ ሁሉ ቋንጃ ቈረጠ፤ ለመቶ ሰረገላ ብቻ አስቀረ። 5 ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደለ። 6 ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፥ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው። 7 ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሾች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8 ንጉሡም ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከቤጣሕና ከቤሮታይ እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ። 9 የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10 ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ድል ስለ መታ ቶዑ ልጁን አዶራምን ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ፥ ይመርቀውም ዘንድ ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የብርና የወርቅ የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። 11 12 ንጉሥ ዳዊትም ካሸነፋቸው ከአሕዛብ ሁሉ ከሶርያ ከሞዓብም ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከረአብም ልጅ ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር ምርኮ ከቀደሰው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ። 13 ዳዊትም በተመለሰ ጊዜ ከኤዶምያስ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች በጨው ሸለቆ ውስጥ በመምታቱ ስሙ ተጠራ። 14 በኤዶምያስ ሁሉ ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ዳዊት በሚሄድበት ሁሉ ድልን ሰጠው። 15 ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ዳዊትም ለሕዝቡ ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 16 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፤ 17 የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቢሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሠራያም ጸሐፊ ነበረ፤ 18 የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች አማካሪዎች ነበሩ።

2 ሳሙኤል 9

1 ዳዊትም። ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው ቀርቶአልን? አለ። 2 ከሳኦልም ቤት ሲባ የሚባል አንድ ባሪያ ነበረ፥ ወደ ዳዊትም ጠሩት፤ ንጉሡም። አንተ ሲባ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ነኝ አለ። 3 ንጉሡም። የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው አልቀረምን? አለ። ሲባም ንጉሡን። እግሩ ሽባ የሆነ አንድ የዮናታን ልጅ አለ አለው። 4 ንጉሡም። ወዴት ነው? አለው፤ ሲባም ንጉሡን። እነሆ፥ እርሱ በሎዶባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት አለ አለው። 5 ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው። 6 የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም። ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም። እነሆኝ ባሪያህ አለ። 7 ዳዊትም። ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው። 8 እርሱም። የሞተ ውሻ ወደምመስል ወደ እኔ የተመለከትህ እኔ ባሪያህ ምንድር ነኝ? ብሎ እጅ ነሣ። 9 ንጉሡም የሳኦልን ባሪያ ሲባን ጠርቶ። ለሳኦልና ለቤቱ ሁሉ የነበረውን ሁሉ ለጌታህ ልጅ ሰጥቻለሁ። 10 አንተና ልጆችህ ሎሌዎችህም ምድሩን እረሱለት፤ ለጌታህም ልጅ እንጀራ ይሆነው ዘንድ ፍሬውን አግባ፤ የጌታህ ልጅ ሜምፊቦስቴ ግን ሁልጊዜ ከገበታዬ ይበላል አለው። ለሲባም አሥራ አምስት ልጆችና ሀያ ባሪያዎች ነበሩት። 11 ሲባም ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሡ ባሪያውን እንዳዘዘ እንዲሁ ባሪያህ ያደርጋል አለው። ሜምፊቦስቴም ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት ገበታ ይበላ ነበር። 12 ለሜምፊቦስቴም ሚካ የተባለ ታናሽ ልጅ ነበረው። በሲባም ቤት ያሉ ሁሉ ለሜምፊቦስቴ ያገለግሉ ነበር። 13 ሜምፊቦስቴም ከንጉሥ ገበታ ሁልጊዜ እየበላ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ነበር፤ ሁለት እግሩም ሽባ ነበረ።

2 ሳሙኤል 10

1 ከዚህ በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ሞተ፥ ልጁም ሐኖን በፋንታው ነገሠ። 2 ዳዊትም። አባቱ ወረታ እንዳደረገልኝ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው ባሪያዎቹን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ አሞን ልጆች አገር መጡ። 3 የአሞንም ልጆች አለቆች ጌታቸውን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ ሊያጽናናህ ባሪያዎቹን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ዳዊትስ ከተማይቱን ለመመርመርና ለመሰለል ለማጥፋትም ባሪያዎቹን የላከ አይደለምን? አሉት። 4 ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ የጢማቸውን ገሚስ ላጨ፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5 ዳዊትም ያን በሰማ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበሩና ተቀባዮች ላከ። ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አላቸው። 6 የአሞን ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደተጠሉ ባዩ ጊዜ፥ የአሞን ልጆች ልከው ከሶርያውያን ከቤትሮዖብና ከሱባ ሀያ ሺህ እግረኞች፥ ከመዓካ ንጉሥም አንድ ሺህ ሰዎች፥ ከጦብም አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ። 7 ዳዊትም በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 8 የአሞንም ልጆች ወጥተው በበሩ መግቢያ ፊት ለፊት ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን፥ የጦብና የመዓካም ሰዎች ለብቻቸው በሰፊ ሜዳ ላይ ነበሩ። 9 ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦቹን ሁሉ መረጠ፥ በሶርያውያንም ፊት ለሰልፍ አኖራቸው። 10 የቀረውንም ሕዝብ በወንድሙ በአቢሳ እጅ አድርጎ በአሞን ልጆች ፊት ለሰልፍ አኖራቸው። 11 ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ፤ የአሞን ልጆች ቢበረቱብህ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ። 12 አይዞህ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ። 13 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። 14 የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ፤ ኢዮአብም ከአሞን ልጆች ዘንድ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 15 ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ በአንድነት ተሰበሰቡ። 16 አድርአዛርም ልኮ በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን፥ አመጣ፤ ወደ ኤላምም መጡ፥ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶባክ በፊታቸው ነበረ። 17 ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ ወደኤላም መጣ፤ ሶርያውያንም በዳዊት ፊት ተሰልፈው ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18 ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ። 19 ለአድርአዛርም የሚገብሩ ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ታረቁ፥ ገበሩላቸውም። ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ ፈሩ።

2 ሳሙኤል 11

1 እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፥ ረባትንም ከበቡ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር። 2 እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች። 3 ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ። 4 ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች። 5 ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም። አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት። 6 ዳዊትም ወደ ኢዮአብ። ኬጢያዊውን ኦርዮን ስደድልኝ ብሎ ላከ። ኢዮአብም ኦርዮን ወደ ዳዊት ሰደደው። 7 ኦርዮም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዳዊት የኢዮአብንና የሕዝቡን ደኅንነት፥ ሰልፉም እንዴት እንደ ሆነ ጠየቀው። 8 ዳዊትም ኦርዮን። ወደ ቤትህ ሂድ፥ እግርህንም ታጠብ አለው። ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ የንጉሥ መብል ተከትሎት ሄደ። 9 ኦርዮ ግን ከጌታው ባሪያዎች ሁሉ ጋር በንጉሥ ቤት ደጅ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም። 10 ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ኦርዮን። አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለምን? ስለ ምን ወደ ቤትህ አልወረድህም? አለው። 11 ኦርዮም ዳዊትን። ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ተቀምጠዋል፤ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ባሪያዎች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም አለው። 12 ዳዊትም ኦርዮን። ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ። 13 ዳዊትም ጠራው፥ በፊቱም በላና ጠጣ፥ አሰከረውም፤ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ባሪያዎች ጋር በምንጣፉ ላይ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም። 14 በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው። 15 በደብዳቤውም። ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ። 16 ኢዮአብም ከተማይቱን በከበበ ጊዜ ጀግኖች እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው። 17 የከተማይቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ተዋጉ፤ ከዳዊትም ባሪያዎች ከሕዝቡ አንዳንዱ ወደቁ፤ ኬጢያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ። 18 ኢዮአብም ልኮ በሰልፍ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 19 ለመልእክተኛውም እንዲህ ብሎ አዘዘው። የሰልፉን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነግረህ በፈጸምህ ጊዜ። 20 ስትዋጉ ወደ ከተማይቱ ለምን ቀረባችሁ? ከቅጥሩ በላይ ፍላጻ እንዲወረወር አታውቁምን? 21 የሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላ በቴቤስ ላይ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ስለ ምን ወደ ቅጥሩ እንደዚህ ቀርባችሁ? ብሎ ንጉሡ ሲቈጣ ብታይ፥ አንተ። ባሪያህ ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ በለው። 22 መልእክተኛውም ተነሥቶ ሄደ፥ ኢዮአብም ያዘዘውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው። 23 መልእክተኛውም ዳዊትን። ሰዎቹ በረቱብን፥ ወደ ሜዳም ወጡብን፤ እኛም ወደቅንባቸው፥ እስከ ከተማይቱም በር ድረስ ተከተልናቸው። 24 ፍላጻ የሚወረውሩም በቅጥሩ ላይ ሆነው በባሪያዎችህ ላይ ወረወሩ፤ ከንጉሡም ባሪያዎች አንዳንድ ሞቱ፥ ባሪያህም ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ አለው። 25 ዳዊትም መልእክተኛውን። ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜም ያን ያጠፋልና ይህ ነገር በዓይንህ አይክፋ፤ ከተማይቱን የሚወጉትን አበርታ፥ አፍርሳትም ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፤ አንተም አጽናው አለው። 26 የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች። 27 የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።

2 ሳሙኤል 12

1 እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው። በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። 2 ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። 3 ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፤ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። 4 ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። 5 ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን። ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። 6 ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። 7 ናታንም ዳዊትን አለው። ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ 8 የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። 9 አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። 10 ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። 12 አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ። 13 ዳዊትም ናታንን። እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን። እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም። 14 ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው። 15 ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር። 16 ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። 17 የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። 18 በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች። ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። 19 ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹን። ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም። ሞቶአል አሉት። 20 ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ። እንጀራ አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም። 21 ባሪያዎቹም። ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት። 22 እርሱም። ሕፃኑ ሕያው ሳለ። እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቅሰሁም። 23 አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ። 24 ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፤ 25 ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው። 26 ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ። 27 ኢዮአብም ወደ ዳዊት። ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። 28 አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ። 29 ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት። 30 የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 31 በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፤ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

2 ሳሙኤል 13

1 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት። 2 አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። 3 ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፤ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ። 4 እርሱም። የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም። የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ አለው። 5 ኢዮናዳብም። ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው። 6 እንዲሁም አምኖን። ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን። እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው። 7 ዳዊትም። መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ። 8 ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም። 9 ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም። ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፤ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። 10 አምኖንም ትዕማርን። ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። 11 መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና። እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት። 12 እርስዋ መልሳ። ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፤ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ። 13 እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው። 14 ቃልዋን ግን አልሰማም፤ ከእርስዋም ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ። 15 ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም። ተነሥተሽ ሂጂ አላት። 16 እርስዋም። አይሆንም፤ ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ አኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፤ እርሱ ግን አልሰማትም። 17 የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ። ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው። 18 ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና፤ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። 19 ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች። 20 ወንድምዋም አቤሴሎም። ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበረን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ነው፤ ይህን ነገር በልብሽ አትያዢው አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት ብቻዋን ተቀመጠች። 21 ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖን ነፍስ አላሳዘነም። 22 አቤሴሎምም እኅቱን ትዕማርን ስላሳፈራት አምኖንን ጠልቶታልና አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካምም አልተናገረውም። 23 ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፤ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። 24 አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ። እነሆ፥ ባሪያህ በጎቹን ያሸልታል፤ ንጉሡና ሎሌዎቹ ከባሪያህ ጋር ይሂዱ አለው። 25 ንጉሡም አቤሴሎምን። ልጄ ሆይ፥ እንከብድብሃለንና ሁላችን እንመጣ ዘንድ አይሆንም አለው። የግድም አለው፥ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ። 26 አቤሴሎምም። አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ አለ። ንጉሡም። ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል? አለው። 27 አቤሴሎምም የግድ አለው፥ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰደደ። 28 አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፤ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን። አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ። አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁም ጊዜ ግደሉት፥ አትፍሩም፤ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ ጽኑም ብሎ አዘዛቸው። 29 የአቤሴሎም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ። 30 ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት። አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገድሎአል፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም የሚል ወሬ መጣለት። 31 ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፥ በምድር ላይም ወደቀ፤ ባሪያዎቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀድደው በአጠገቡ ቆሙ። 32 የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ። ጌታዬ ጕልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው። 33 አሁንም የሞተ አምኖን ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያኑር አለው። 34 አቤሴሎምም ኰበለለ። ጕበኛውም ጕልማሳ ዓይኑን ከፍ አደረገ፥ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ። 35 ኢዮናዳብም ንጉሡን። እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ ባሪያህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል አለው። 36 ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ደግሞ ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ። 37 አቤሴሎም ግን ኰብልሎ ወደ ጌሹር ንጉሥ ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ። ዳዊትም ሁልጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር። 38 አቤሴሎም ኰብልሎ ወደ ጌሹር ሄደ፥ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። 39 ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።

2 ሳሙኤል 14

1 የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ። 2 ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና። አልቅሺ፥ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፤ 3 ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። 4 እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም። ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች። 5 ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት። እርስዋም መልሳ አለች። በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። 6 ለእኔም ለባሪያህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፥ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፥ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። 7 እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው። ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፥ የባሌን ስምና ዘርም ከምድር ላይ አያስቀሩም። 8 ንጉሡም ሴቲቱን። ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ አላት። 9 የቴቁሔይቱም ሴት ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኃጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን አለችው። 10 ንጉሡም። የሚናገርሽን አምጪልኝ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም አለ። 11 እርስዋም። ደም ተበቃዮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያጠፉ ልጄንም እንዳይገድሉ፥ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ያስብ አለች። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ አንድ ጠጕር በምድር ላይ አይወድቅም አለ። 12 ሴቲቱም። እኔ ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር አለች፤ እርሱም። ተናገሪ አለ። 13 ሴቲቱም አለች። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን አሰብህ? ንጉሡ ይህን ነገር ተናግሮአልና ያሳደደውን ስላላስመለሰ በደለኛ ነው። 14 ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፤ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል። 15 አሁንም ሕዝቡ ስለሚያስፈራኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም ባሪያህ። ምናልባት የእኔን የባሪያውን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደሆነ ለንጉሡ ልናገር፤ 16 እርስዋንና ልጅዋን ከእግዚአብሔር ርስት ያጠፋቸው ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ ባሪያውን ይሰማል አልሁ። 17 እኔም ባሪያህ። መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኛል፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን አልሁ። 18 ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ። የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ አላት። ሴቲቱም። ጌታዬ ንጉሥ ይናገር አለች። 19 ንጉሡም። በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር ነውን? አላት። ሴቲቱም መልሳ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ ባሪያህ ኢዮአብ አዝዞኛል፥ ይህንም ቃል ሁሉ በባሪያህ አፍ አደረገው። 20 ባሪያህ ኢዮአብ የዚህ ነገር መልክ እንዲለወጥ አደረገ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጠቢብ እንደ ሆነ፥ አንተም ጌታዬ በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ ታውቅ ዘንድ ጠቢብ ነህ አለች። 21 ንጉሡም ኢዮአብን። እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ እንግዲህ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው አለው። 22 ኢዮአብም በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ እጅ ነሣ፥ ንጉሡንም ባረከ፤ ኢዮአብም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የባሪያህን ነገር አድርገሃልና በዓይንህ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ባሪያህ ዛሬ አወቀ አለ። 23 ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ። 24 ንጉሡም። ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም። 25 በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። 26 ጠጕሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር። 27 ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ የሴቲቱም ልጅ ስም ትዕማር ነበረ፥ እርስዋም የተዋበች ሴት ነበረች። 28 አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ። 29 አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፥ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፥ ሊመጣ ግን አልወደደም። 30 ባሪያዎቹንም። በእርሻዬ አጠገብ ያለውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፥ በዚያም ገብስ አለው፤ ሂዳችሁ በእሳት አቃጥሉት አላቸው። የአቤሴሎምም ባሪያዎች እርሻውን አቃጠሉት። 31 ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና። ባሪያዎችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት? አለው። 32 አቤሴሎምም ኢዮአብን መልሶ። ከጌሹር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጩ ብሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ጠራሁህ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት ልይ፥ ኃጢአት ቢሆንብኝ ይግደለኝ አለው። 33 ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ በንጉሥ ፊት ወደ ምድር በግምባሩ ተደፋ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።

2 ሳሙኤል 15

1 ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። 2 አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደበባይ ይቆም ነበር፤ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ። አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም። እኔ ባሪያህ ከእስራኤል ነገድ ከአንዲቱ ነኝ ብሎ ይመልስ ነበር። 3 አቤሴሎምም። ነገርህ እውነትና ቅን ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ታዝዞ የሚሰማህ የለም ይለው ነበር። 4 አቤሴሎምም። ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ? ይል ነበር። 5 ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። 6 እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር፤ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። 7 እንዲህም ሆነ፤ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሡን። ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለመስጠት ወደ ኬብሮን፥ እባክህ፥ ልሂድ። 8 እኔ ባሪያህ በሶርያ ጌሹር ሳለሁ። እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር አለው። 9 ንጉሡም። በደኅና ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። 10 አቤሴሎምም በእስራኤል ነገድ ሁሉ። የቀንደ መለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ። አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ የሚሉ ጕበኞች ላከ። 11 የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር በየዋህነት ከኢየሩሳሌም ሄዱ፤ የሚሆነውንም ነገር ከቶ አያውቁም ነበር። 12 አቤሴሎምም የዳዊት መካር የነበረውን የጊሎ ሰው አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ አስጠራው። ሴራውም ጽኑ ሆነ፤ ከአቤሴሎምም ጋር ያለ ሕዝብ እየበዛ ሄደ። 13 ለዳዊትም። የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል የሚል ወሬኛ መጣለት። 14 ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን ባሪያዎቹን ሁሉ። ተነሡ፥ እንሽሽ ያለዚያ ከአቤሴሎም እጅ የሚድን ከእኛ የለምና፤ መጥቶም እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ አላቸው። 15 የንጉሡም ባሪያዎች ንጉሡን። እነሆ፥ ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ እኛ ባሪያዎችህ እሺ ብለን እናደርጋለን አሉት። 16 ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ ወጡ፤ ንጉሡም አሥሩን ሴቶች ቁባቶቹን ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። 17 ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ወጡ፥ በቤትሜርሐቅም ቆሙ። 18 ባሪያዎቹም ሁሉ በፊቱ አለፉ፤ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ሁሉ፥ ከእርሱም በኋላ ከጌት የመጡት ስድስት መቶው ጌትያውን ሁሉ በንጉሡ ፊት አለፉ። 19 ንጉሡም የጌት ሰው ኢታይን። ከእኛ ጋር ለምን መጣህ? አንተ ከስፍራህ የመጣህ እንግዳና ስደተኛ ነህና ተመለስ፥ ከንጉሡም ጋር ተቀመጥ። 20 የመጣኸው ትናንት ነው፤ ዛሬ ከእኛ ጋር ላዙርህን? እኔ ወደምሄድበት እሄዳለሁ፤ አንተ ግን ተመለስ፥ ወንድሞችህንም ከአንተ ጋር ውሰድ፥ እግዚአብሔርም ምሕረቱንና እውነቱን ያድርግልህ አለው። 21 ኢታይም ለንጉሡ መልሶ። ሕያው እግዚአብሔርን! በጌታዬም በንጉሡ ሕይወት እምላለሁ! በእውነት ጌታዬ ባለበት ስፍራ ሁሉ፥ በሞትም ቢሆን በሕይወትም፥ በዚያ ደግሞ እኔ ባሪያህ እሆናለሁ አለው። 22 ዳዊትም ኢታይን። ሂድ ተሻገር አለው፤ የጌት ሰው ኢታይና ሰዎቹም ሁሉ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕፃናት ሁሉ ተሻገሩ። 23 በአገርም የነበሩት ሁሉ በታላቅ ድምፅ አለቀሱ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻገሩ፥ ንጉሡም ደግሞ የቄድሮንን ፈፋ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ምድረ በዳ መንገድ ተሻገሩ። 24 እነሆም፥ ደግሞ ሳዶቅ ከእርሱም ጋር ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው መጡ፤ የእግዚአብሔርንም ታቦት አስቀመጡ፥ ሕዝቡም ሁሉ ከከተማይቱ ፈጽሞ እስኪያልፍ ድረስ አብያታር ወጣ። 25 ንጉሡም ሳዶቅን። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልስ፤ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆንሁ፥ መልሶ እርሱንና ማደሪያውን ያሳየኛል፤ 26 ነገር ግን። አልወድድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ፥ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግብኝ አለው። 27 ንጉሡም ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን። እነሆ፥ አንተና ልጅህ አኪማአስ የአብያታርም ልጅ ዮናታን ሁለቱ ልጆቻችሁ በደኅና ወደ ከተማ ተመለሱ። 28 እኔም፥ እነሆ፥ ከእናንተ ዘንድ ወሬ እስኪመጣልኝ ድረስ በምድረ በዳው መሻገርያ እቆያለሁ አለው። 29 ሳዶቅም አብያታርም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መለሱት፥ በዚያም ተቀመጡ። 30 ዳዊትም ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ። 31 አኪጦፌል ከአቤሴሎም ጋር በሴራ አንድ ነው ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም። አቤቱ፥ የአኪጦፌልን ምክር ስንፍና አድርገህ እንድትለውጥ እለምንሃለሁ አለ። 32 ዳዊትም ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ወደ ተራራው ራስ በመጣ ጊዜ፥ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። 33 ዳዊትም አለው። ከእኔ ጋር ብትመጣ ትከብደኛለህ፤ 34 ወደ ከተማ ግን ተመልሰህ ለአቤሴሎም። ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያ እሆንሃለሁ፤ አስቀድሞ ለአባትህ ባሪያ እንደ ነበርሁ እንዲሁ አሁን ለአንተ ባሪያ እሆንሃለሁ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ታደርግልኛለህ። 35 ካህናቱ ሳዶቅና አብያታርም በዚያ ከአንተ ጋር አይደሉምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። 36 እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፤ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ። 37 የዳዊትም ወዳጅ ኩሲ ወደ ከተማ መጣ፤ አቤሴሎምም ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

2 ሳሙኤል 16

1 ዳዊትም ከተራራው ራስ ጥቂት ፈቀቅ ባለ ጊዜ የሜምፊቦስቴ ባሪያ ሲባ ሁለት መቶ እንጀራ፥ አንድ መቶም ዘለላ ዘቢብ፥ አንድ መቶም በለስ፥ አንድ አቁማዳም ወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ተገናኘው። 2 ንጉሡም ሲባን። ይህ ምንድር ነው? አለው። ሲባም። አህዮቹ የንጉሥ ቤተ ሰቦች ይቀመጡባቸው ዘንድ፥ እንጀራውና በለሱ ብላቴኖቹ ይበሉት ዘንድ፥ የወይን ጠጁም በበረሀ የሚደክሙት ይጠጡት ዘንድ ነው አለ። 3 ንጉሡም። የጌታህ ልጅ ወዴት ነው? አለ። ሲባም ንጉሡን። እነሆ። የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል ብሎ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል አለው። 4 ንጉሡም ሲባን። እነሆ፥ ለሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ለአንተ ይሁን አለው። ሲባም። እጅ እነሣለሁ፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ ላግኝ አለ። 5 ንጉሡ ዳዊትም ወደ ብራቂም መጣ፤ እነሆም፥ ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር። 6 ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎችም ድንጋይ ይወረውር ነበር፤ በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ። 7 ሳሚም ሲረግም። ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ። 8 በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል አለ። 9 የጽሩያም ልጅ አቢሳ ንጉሡን። ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቍረጠው አለው። 10 ንጉሡም። እናንተ የጽሩም ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር። ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፤ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ። 11 ዳዊትም አቢሳንና ባሪያዎቹን ሁሉ። እነሆ ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፤ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ። 12 ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው። 13 ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር፤ ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም፤ ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር። 14 ንጉሡና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ሁሉ ደክመው ነበር፥ በዚያም ዐረፉ። 15 አቤሴሎምና ሕዝቡ ሁሉ የእስራኤልም ሰዎች አኪጦፌልም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 16 የዳዊትም ወዳጅ አርካዊው ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ ኩሲ። ሺህ ዓመት ያንግሥህ አለው። 17 አቤሴሎምም ኩሲን። ስለ ወዳጅህ ያደረግኸው ቸርነት ይህ ነውን? ከወዳጅህ ጋር ያልሄድህ ስለምንድር ነው? አለው። 18 ኩሲም አቤሴሎምን። እንዲህ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ከዚህም ሕዝብ ከእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ ከእርሱም ጋር እቀመጣለሁ። 19 ዳግምም የማገለግል ለማን ነው? በንጉሥ ልጅ ፊት አይደለምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ እንዲሁ በአንተ ፊት እሆናለሁ አለው። 20 አቤሴሎምም አኪጦፌልን። ምከሩ ምን እናድርግ? አለው። 21 አኪጦፌልም አቤሴሎምን። ቤት ሊጠብቁ ወደ ተዋቸው ወደ አባትህ ቁባቶች ግባ፤ እስራኤልም ሁሉ አባትህን እንዳሳፈርኸው ይሰማሉ፤ ከአንተም ጋር ያሉት ሁሉ እጃቸው ይበረታል አለው። 22 ለአቤሴሎምም በሰገነት ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ አቤሴሎምም በእስራኤል ሁሉ ፊት ወደ አባቱ ቁባቶች ገባ። 23 በዚያም ወራት የመከራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ነበረች፤ የአኪጦፌልም ምክር ሁሉ ከዳዊትና ከአቤሴሎም ጋር እንዲህ ነበረች።

2 ሳሙኤል 17

1 አኪጦፌልም አቤሴሎምን። አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ልምረጥና 1 አኪጦፌልም በዚህች ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን ላሳድድ። 2 ደክሞና እጁ ዝሎ ሳለ እወድቅበታለህ፥ አስፈራውማለሁ፤ ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ይሸሻል፥ ንጉሡንም ብቻውን እመታዋለሁ፤ 3 ሙሽራ ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ፤ ሕዝቡ ሁሉ ደኅና ይሆናል፤ የምትፈልገው አንድ ሰው ብቻ ነው። 4 ነገሩም አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ። 5 አቤሴሎምም። አርካዊውን ኩሲን ጥሩ፥ ደግሞም እርሱ የሚለውን እንስማ አለ። 6 ኩሱም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ አቤሴሎም። አኪጦፌል ያለው ይህ ነው፤ ነገሩን እናደርገው ዘንድ ይገባልን? ባይሆን ግን አንተ ንገረን ብሎ ተናገረው። 7 ኩሲም አቤሴሎምን። አኪጦፌል በዚህ ጊዜ የመከራት ምክር መልካም አይደለችም አለው። 8 ኩሲ ደግሞ አለ። ግልገሎችዋ በዱር በተነጠቁ ጊዜ ድብ መራራ እንደ ሆነች በልባቸው መራሮች እጅግም ኃያላን መሆናቸውን አባትህንና ሰዎቹን ታውቃለህ፤ አባትህ አርበኛ ነው፥ ከሕዝብም ጋር አያድርም። 9 አሁንም ምናልባት በአንድ ጕድጓድ ወይም በማናቸውም ስፍራ ተሸሽጎ ይሆናል፤ በመጀመሪያም ከእነርሱ አያሌዎች ቢወድቁ፥ የሚሰማው ሁሉ። አቤሴሎምን የተከተለው ሕዝብ ተመታ ይላል። 10 እስራኤልም ሁሉ አባትህ ኃያል እንደ ሆነ፥ ከእርሱም ጋር ያሉት ሰዎች ጽኑዓን እንደ ሆኑ ያውቃልና ጽኑዕ ልቡም እንደ አንበሳ ልብ የሆነው ፈጽሞ ይቀልጣል። 11 ነገር ግን የምመክርህ ይህ ነው፤ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለ እስራኤል ሁሉ በብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ ሆኖ ወደ አንተ ይሰብሰብ፥ አንተም በመካከላቸው ወደ ሰልፍ ውጣ። 12 እርሱንም ወደምናገኝበት ወደ አንድ ስፍራ እንደርስበታለን፥ ጠልም በምድር ላይ እንደሚወድቅ እንወርድበታለን፤ እርሱና ከእርሱም ጋር ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ስንኳ አናስቀርም። 13 ወደ ከተማም ቢገባ እስራኤል ሁሉ ወደዚያች ከተማ ገመድ ይወስዳል፥ እኛም አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይገኝባት ድረስ ወደ ወንዙ ውስጥ እንስባታለን። 14 አቤሴሎምና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ። የአርካዊው የኩሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይሻላል አሉ። እግዚአብሔርም በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ። 15 ኩሲም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር። አኪጦፌል ለአቤሴሎምና ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህና እንዲህ መክሮአል፤ እኔ ግን እንዲህና እንዲህ መክሬአለሁ። 16 አሁን እንግዲህ ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ እንዳይዋጡ፥ ፈጥናችሁ። ሳትዘገይ ተሻገር እንጂ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ መሻገሪያ አትደር ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው። 17 ዮናታንና አኪማአስ ተገልጠው ወደ ከተማ ይገቡ ዘንድ አልቻሉም ነበርና በዓይንሮጌል ተቀምጠው ነበር፤ አንዲትም ባሪያ ሄዳ ትነግራቸው ነበር፤ እነርሱም ሄደው ለንጉሡ ለዳዊት ይነግሩት ነበር። 18 አንድ ብላቴናም አይቶ ለአቤሴሎም ነገረው፤ እነርሱ ግን ፈጥነው ሄዱ፤ ወደ ብራቂምም ወደ አንድ ሰው ቤት መጡ፤ በግቢውም ውስጥ ጕድጓድ ነበረ፥ ወደዚያም ውስጥ ወረዱ። 19 ሴቲቱም በጕድጓድ አፍ ላይ ዳውጃ ዘረጋችበት፥ የተከካ እህልም በላዩ አሰጣችበት፤ ነገሩም እንዲህ ተሰወረ። 20 የአቤሴሎም ባሪያዎች ወደ ሴቲቱ ወደ ቤት መጥተው። አኪማአስና ዮናታን የት አሉ? አሉ፤ ሴቲቱም። ፈፋውን ተሻግረው ሄዱ አለቻቸው። እነርሱም ፈልገው ባላገኟቸው ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 21 ከሄዱም በኋላ እነርሱ ከጕድጓድ ወጥተው ሄዱ፥ ለንጉሡም ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትንም። አኪጦፌል በእናንተ ላይ እንዲህ መክሮአልና ተነሡ፥ ፈጥናችሁም ውኃውን ተሻገሩ አሉት። 22 ዳዊትና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሥተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስኪነጋም ድረስ ዮርዳኖስን ሳይሻገር አንድ ሰው እንኳ አልቀረም። 23 አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉ ባየ ጊዜ አህያውን ጫነ፥ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ወደ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም አደራጅቶ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፥ በአባቱም መቃብር ተቀበረ። 24 ዳዊትም ወደ መሃናይም መጣ፤ አቤሴሎምም ከእርሱም ጋር የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 25 አቤሴሎምም በጭፍራው ላይ በኢዮአብ ስፍራ አሜሳይን ሾመ፤ አሜሳይም የይስማኤላዊ ሰው የዬቴር ልጅ ነበረ፤ እርሱም የኢዮአብን እናት የጽሩያን እኅት የናዖስን ልጅ አቢግያን አግብቶ ነበር። 26 እስራኤልና አቤሴሎምም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ። 27 ዳዊትም ወደ መሃናይም በመጣ ጊዜ በአሞን ልጆች አገር በረባት የነበረ የናዖስ ልጅ ኡኤስቢ፥ የሎዶባርም ሰው የዓሚኤል ልጅ ማኪር፥ የሮግሊምም ሰው ገለዓዳዊ ቤርዜሊ፥ 28 29 ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቦአል፥ ደክሞአል፥ ተጠምቶአል ብለው ምንጣፍ፥ ዳካ፥ የሸክላም ዕቃ፥ ይበሉም ዘንድ ስንዴ፥ ገብስ፥ ዱቄት፥ የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላ፥ ምስር፥ የተቈላ ሽንብራ፥ ማር፥ ቅቤ፥ በጎች፥ የላምም እርጎ ለዳዊትና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ አመጡላቸው።

2 ሳሙኤል 18

1 ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ሻለቆችንና የመቶ አለቆችንም ሾመላቸው። 2 ዳዊትም ሕዝቡን ከኢዮአብ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከኢዮአብም ወንድም ከጽሩያ ልጅ ከአቢሳ እጅ በታች ሲሶውን፥ ከጌት ሰውም ከኢታይ እጅ በታች ሲሶውን ሰደደ። ንጉሡም ሕዝቡን። እኔ ደግሞ ከእናንተ ጋር እወጣለሁ አላቸው። 3 ሕዝቡ ግን። አትወጣም፤ ብንሸሽ ስለ እኛ አያስቡም፤ ከእኛም እኩሌታው ቢሞት ስለ እኛ አያስቡም፤ አንተ ግን ለብቻህ ከእኛ ከአስሩ ሺህ ይልቅ ትበልጣለህ፤ አሁንም በከተማ ተቀምጠህ ብትረዳን ይሻላል አሉ። 4 ንጉሡም። መልካም የሚመስላችሁን አደርጋለሁ አላቸው። ንጉሡም በበሩ አጠገብ ቆመ፥ ሕዝቡም ሁሉ መቶ በመቶ ሺህ በሺህ እየሆኑ ወጡ። 5 ንጉሡም እዮአብንና አቢሳን ኢታይንም። ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡም ስለአቤሴሎም አለቆቹን ሁሉ ሲያዝዝ ሕዝቡ ሁሉ ሰማ። 6 ሕዝቡም በእስራኤል ላይ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ሰልፉም በኤፍሬም ሁሉ ውስጥ ሆነ። 7 በዚያም የእስራኤል ሕዝብ በዳዊት ባሪያዎች ፊት ተመቱ፥ በዚያም ቀን ታላቅ ውጊያ በዚያ ሆነ፥ ሃያ ሺህ ሰውም ሞተ። 8 ከዚያም ሰልፉ በአገሩ ሁሉ ፊት ላይ ተበተነ፤ በዚያም ቀን ሰይፍ ከዋጠው ሕዝብ ሁሉ ይልቅ ዱር ብዙ ዋጠ። 9 አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር፥ በቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ፥ ራሱም በዛፉ ተያዘ፤ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፥ ተቀምጦበትም የነበረ በቅሎ አለፈ። 10 አንድ ሰውም አይቶ። እነሆ፥ አቤሴሎም በትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁ ብሎ ለኢዮአብ ነገረው። 11 ኢዮአብም ለነገረው ሰው። እነሆ፥ ካየኸው ለምን ወደ ምድር አልመታኸውም? አስር ብርና አንድ ድግ እሰጥህ ነበር አለው። 12 ሰውዮውም ኢዮአብን። እኛ ስንሰማ ንጉሡ አንተንና አቢሳን ኢታይንም። ብላቴናውን አቤሴሎምን ማንም እንዳይነካው ተጠንቀቁ ብሎ አዝዞአልና ሺህ ብር በእጄ ላይ ብትመዝን እጄን በንጉሡ ልጅ ላይ ባልዘረጋሁም ነበር። 13 እኔ ቅሉ በነብሱ ላይ ብወነጅል ኖሮ ይህ ከንጉሥ ባልተሰወረም፥ አንተም በተነሳህብኝ ነበር አለው። 14 ኢዮአብም። እኔ ከአንተ ጋር እንዲህ እዘገይ ዘንድ አልችልም ብሎ ሦስት ጦሮች በእጁ ወሰደ፥ አቤሴሎምም ገና በዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ሕያው ሳለ በልቡ ላይ ተከላቸው። 15 አስሩም የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች ከበቡት፥ አቤሴሎምንም መትተው ገደሉት። 16 ኢዮአብም ሕዝቡን ከልክሎ ነበርና ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም እስራኤልን ከማሳደድ ተመለሰ። 17 አቤሴሎምንም ወስደው በዱር ባለ በታላቅ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፥ እጅግም ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እስራኤልም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 18 አቤሴሎምም ሕያው ሳለ። ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሃውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሃውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቤሴሎም መታሰቢያ ተብሎ ይጠራል። 19 የሳዶቅ ልጅ አኪማኣስ ግን። እግዚአብሔር ጠላቶቹን እንደተበቀለለት ሮጬ ለንጉሥ የምሥራች ልንገር አለ። 20 ኢዮአብም። በሌላ ቀን እንጂ ዛሬ ወሬ አትናገርም፤ የንጉሥ ልጅ ሞቶአልና ዛሬ ወሬ አትናገርም አለው። 21 ኢዮአብም ኵሲን። ሂድ ያየኸውንም ለንጉሡ ንገር አለው። ኵሲም ለኢዮአብ እጅ ነስቶ ሮጠ። 22 ዳግመኛም የሳዶቅ ልጅ አኪማአስ ኢዮአብን። የሆነ ሆኖ ኵሲን ተከትዬ፥ እባክህ፥ ልሩጥ አለው። ኢዮአብም። ልጄ ሆይ፥ መልካም ወሬ የምትወስድ አይደለህምና ትሮጥ ዘንድ ለምን ትወድዳለህ? አለ። 23 እርሱም። እኔ ብሮጥ ምን ይገድዳል? አለ። እርሱም። ሩጥ አለው። አኪማአስም በሜዳው መንደር በኩል ሮጠ፥ ኵሲንም ቀደመው። 24 ዳዊትም በሁለት በር መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ዘበኛውም በቅጥሩ ላይ ወዳለው ወደ በሩ ሰገነት ወጣ፥ ዓይኑንም አቅንቶ ብቻውን የሚሮጥ ሰው አየ። 25 ዘበኛውም ለንጉሡ ሊነግረው ጮኸ። ንጉሡም። ብቻውን እንደሆነ በአፉ ወሬ ይኖራል አለ። 26 እርሱም ፈጥኖ ቀረበ። ዘበኛውም ሌላ ሰው ሲሮጥ አየ፤ ዘበኛውም ለደጅ ጠባቂው ጮኾ። እነሆ፥ ብቻውን የሚሮጥ ሌላ ሰው አየሁ አለ። ንጉሡም። እርሱ ደግሞ ወሬ ይዞ ይሆናል አለ። 27 ዘበኛውም። የፊተኛው ሩጫ እንደ ሳዶቅ ልጅ እንደ አኪማአስ ሩጫ ይመስላል አለ፤ ንጉሡም። እርሱ መልካም ሰው ነው፥ መልካምም ወሬ ያመጣል አለ። 28 አኪማአስም ጮኾ ንጉሡን። ሁሉ ደህና ሆኖአል አለው። በንጉሡም ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፍቶ። በንጉሡ በጌታዬ ላይ እጃቸውን ያነሱትን ሰዎች አሳልፎ የሰጠ አምላክህ እግዚአብሔር ይመስገን አለ። 29 ንጉሡም። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለ። አኪማአስም። ኢዮአብ እኔን ባሪያህንና የንጉሡን ባሪያ በላከ ጊዜ ትልቅ ሽብር አይቻለሁ፥ ምን እንደሆነ ግን አላወቅሁም ብሎ መለሰለት። 30 ንጉሡም። ፈቀቅ ብለህ ቁም አለ፤ እርሱም ፈቀቅ ብሎ ቆመ። 31 እነሆም፥ ኵሲ መጣ፤ ኵሲም። እግዚአብሔር በላይህ የተነሡትን ሁሉ ዛሬ እንደተበቀለልህ ለጌታዬ ለንጉሡ ወሬ አምጥቻለሁ አለ። 32 ንጉሡም ኵሲን። ብላቴናው አቤሴሎም ደህና ነውን? አለው። ኵሲም። የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች፥ በክፉም የተነሡብህ ሁሉ እንደዚያ ብላቴና ይሁኑ ብሎ መለሰለት። 33 ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር። ች

2 ሳሙኤል 19

1 ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። 2 በዚያም ቀን። ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ። 3 ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። 4 ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ። ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። 5 ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ። ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፤ 6 አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፥ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህንና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፤ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። 7 አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፤ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። 8 ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደ ተቀመጠ ሰማ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ነበር። 9 ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ነገድ ሁሉ ውስጥ። ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከአገር ሸሽቶአል። 10 በላያችን እንዲሆን የቀባነው አቤሴሎም በሰልፍ ሞቶአል፤ አሁንም እንግዲህ ንጉሡን ለመመለስ ስለምን ዝም ትላላችሁ? እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር። 11 ንጉሡም ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው። ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው። የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? 12 እናንተ ወንድሞቼ፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እናንተ ንጉሡን ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? 13 ለአሜሳይም። አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት። 14 የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፤ ወደ ንጉሡም ልከው። አንተ ከባሪያዎችህ ሁሉ ጋር ተመለስ አሉት። 15 ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ሊቀበሉ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። 16 ከብራቂምም አገር የነበረው ብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። 17 ከእርሱም ጋር ብንያማውያን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፥ የሳኦልም ቤት ባሪያ ሲባ ከእርሱም ጋር አሥራ አምስቱ ልጆችና ሀያው ባሪያዎች ነበሩ፤ በንጉሡም ፊት ፈጥነው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 18 ታንኳውም የንጉሥን ቤተ ሰብ ያሻግር ዘንድ ንጉሡም ደስ ያሰኘውን ያደርግ ዘንድ ይሸጋገር ነበር። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በፊቱ ተደፋ። 19 ንጉሡንም። ጌታዬ ሆይ፥ ኃጢአቴን አትቍጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀን ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ ንጉሡም በልቡ አያኑረው። 20 ባሪያህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፥ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ አለው። 21 የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን። ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ። 22 ዳዊትም። እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን? አለ። 23 ንጉሡም ሳሚን። አትሞትም አለው። ንጉሡም ማለለት። 24 የሳኦልም ልጅ ሜምፊቦስቴ ንጉሡን ሊቀበል ወረደ፤ ንጉሡም ከሄደ ጀምሮ በደኅና እስከ ተመለሰበት ቀን ድረስ እግሩን አልጠገነም፥ ጢሙንም አልቈረጠም፥ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 25 ንጉሡም ሊቀበለው ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ስለ ምን አልወጣህም? አለው። 26 እርሱም መልሶ አለ። ጌታዬን፥ ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያዬ አታለለኝ፤ እኔ ባሪያህ አንካሳ ነኝና። ከንጉሥ ጋር እሄድ ዘንድ የምቀመጥበትን አህያ ልጫን አልሁት። 27 እርሱም እኔን ባሪያህን ለጌታዬ ለንጉሡ አማ፤ አንተ ጌታዬ ንጉሥ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፤ ደስም ያሰኘህን አድርግ። 28 የአባቴ ቤት ሁሉ በጌታዬ በንጉሡ ዘንድ ሞት የሚገባቸው ነበሩ፤ አንተ ግን እኔን ባሪያህን በገበታህ በሚበሉ መካከል አስቀመጥኸኝ፤ ለንጉሥ ደግሞ ለመናገር ምን መብት አለኝ? 29 ንጉሡም። ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ እርሻውን ትካፈሉ ዘንድ ብያለሁ አለው። 30 ሜምፊቦስቴም ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሡ በደኅና ወደ ቤቱ ከተመለሰ እርሱ ሁሉን ይውሰደው አለው። 31 ገለዓዳዊውም ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ሊሸኘውም ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 32 ቤርዜሊም እጅግ ያረጀ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ እጅግም ትልቅ ሰው ነበረና ንጉሡ በመሃናይም ሳለ ይቀልበው ነበር። 33 ንጉሡም ቤርዜሊን። በኢየሩሳሌም እቀልብህ ዘንድ ከእኔ ጋር እለፍ አለው። 34 ቤርዜሊም ንጉሡን አለው። ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እወጣ ዘንድ ከሕይወቴ ዘመን ምን ያህል ቀረኝ? 35 ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን? የወንዱንና የሴቲቱን ዘፈን ድምፅ መስማት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን እከብድብሃለሁ? 36 እኔ ባሪያህ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ከንጉሡ ጋር ጥቂት ልሄድ ነበር፤ ንጉሡ እንዲህ ያለ ወረታ ለምን ይመልስልኛል? 37 እኔ ባሪያህ ተመልሼ በከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ፥ እባክህ፥ ልሙት። ነገር ግን ባሪያህን ከመዓምን እይ፤ እርሱ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም ለእርሱ አድርግ። 38 ንጉሡም። ከመዓም ከእኔ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም አደርግለታለሁ፤ አንተም ከእኔ የምትሻውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው። 39 ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፥ ንጉሡም ተሻገረ፤ ንጉሡም ቤርዜሊን ሳመው፥ መረቀውም፤ ወደ ስፍራውም ተመለሰ። 40 ንጉሡም ወደ ጌልገላ ተሻገረ፥ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ ደግሞም የእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ንጉሡን አሻገረው። 41 እነሆም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሥ መጡ፥ ንጉሡንም። ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ለምን ሰረቁህ? ንጉሡንም ቤተ ሰቡንም ከእርሱም ጋር የዳዊትን ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን አሻገሩ? አሉት። 42 የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል ሰዎች መልሰው። ንጉሡ ለእኛ ቅርባችን ነው፤ ስለ ምን በዚህ ነገር ትቈጣላችሁ? በውኑ ከንጉሡ አንዳች በልተናልን? ወይስ እርሱ በረከት ሰጥቶናልን? አሉ። 43 የእስራኤልም ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች መልሰው። በንጉሡ ዘንድ ለእኛ አሥር ክፍል አለን፥ በዳዊትም ዘንድ ደግሞ ከእናንተ ይልቅ መብት አለን፤ ስለ ምን ናቃችሁን? ስለ ምንስ ንጉሣችንን ለመመለስ ቀድሞ ምክር አልጠየቃችሁንም? አሉ። የይሁዳም ሰዎች ቃል ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ ጠነከረ።

2 ሳሙኤል 20

1 እንዲህም ሆነ፤ አንድ ብንያማዊ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የሚባል ምናምንቴ ሰው ነበረ፤ እርሱም። ከዳዊት ዘንድ እድል ፈንታ የለንም፥ ከእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፥ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ ብሎ ቀንደ መለከት ነፋ። 2 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከዳዊት ተለይተው የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተሉ፤ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ ጀምረው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ንጉሣቸውን ተከተሉ። 3 ዳዊትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤቱ መጣ፤ ንጉሡም ቤቱን ሊጠብቁ የተዋቸውን አሥሩን ቁባቶች ወስዶ ለጠባቂ ሰጣቸው፥ ቀለብም ሰጣቸው፥ ነገር ግን ወደ እነርሱ አልገባም፤ በቤት ተዘግተው እስኪሞቱም ድረስ ባልቴቶች ሆነው ተቀመጡ። 4 ንጉሡም አሜሳይን። የይሁዳን ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ ጥራልኝ፥ አንተም አብረህ በዚህ ሁን አለው። 5 አሜሳይም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይጠራ ዘንድ ሄደ፤ ነገር ግን እርሱ የተቀጠረውን ቀን አሳልፎ ዘገየ። 6 ዳዊትም አቢሳን። አሁን ከአቤሴሎም ይልቅ የሚጎዳን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ ነው፤ እርሱ የተመሸጉትን ከተሞች አግኝቶ ከዓይናችን እንዳያመልጥ፥ አንተ የጌታህን ባሪያዎች ወስደህ አሳድደው አለው። 7 አቢሳንም ተከትለው የኢዮአብ ሰዎች ከሊታውያንም ፈሊታውያንም ኃያላንም ሁሉ ሄዱ፤ የቢክሪንም ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ከኢየሩሳሌም ወጡ። 8 በገባዖንም ወዳለው ወደ ታላቁ ድንጋይ በደረሱ ጊዜ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፤ ኢዮአብም የሰልፍ ልብስ ለብሶ ነበር፥ በላዩም መታጠቂያ ነበረ፥ በወገቡም ላይ ሰገባ ያለው ሰይፍ ታጥቆ ነበር፤ እርሱም ሲራመድ ሰይፉ ወደቀ። 9 ኢዮአብም አሜሳይን። ወንድሜ ሆይ፥ ደኅና ነህን? አለው ኢዮአብም አሜሳይን የሚስም መስሎ በቀን እጁ ጢሙን ያዘው። 10 አሜሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ከነበረው ሰይፍ አልተጠነቀቀም ነበር፤ ኢዮአብም ሆዱን ወጋው፥ አንጀቱንም በምድር ላይ ዘረገፈው፤ ሁለተኛም አልወጋውም፥ ሞተም። ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን አሳደዱ። 11 ከኢዮአብም ብላቴኖች አንዱ በአሜሳይ ሬሳ አጠገብ ቆሞ። ለኢዮአብ ወዳጅ የሚሆን ለዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል ይል ነበር። 12 አሜሳይም በመንገድ መካከል ወድቆ በደሙ ላይ ይንከባለል ነበር፤ ያም ሰው ወደ እርሱ የሚመጣ ሁሉ ሲቆም አይቶአልና ሕዝቡ ሁሉ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ አሜሳይን ከመንገድ ላይ ወደ እርሻ ውስጥ ፈቀቅ አደረገው፥ በልብስም ከደነው። 13 ከመንገድ ራቅ ባለ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ኢዮአብን ተከትሎ ያልፍ ነበር። 14 እርሱ ግን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ አቤል፥ ወደ ቤትመዓካ፥ ወደ ቤሪም ሁሉ አለፈ፤ ሰዎችም ደግሞ ተሰብስበው ተከተሉት። 15 በቤትመዓካ ባለ በአቤልም መጥተው ከበቡት፥ በከተማይቱም ላይ እስከ ቅጥርዋ ድረስ የአፈርን ድልድል ደለደሉ፤ ቅጥሩንም ያፈርሱ ዘንድ ከኢዮአብ ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ይደባደቡ ነበር። 16 ከከተማይቱም አንዲት ብልሃተኛ ሴት። ስሙ፥ ስሙ፤ ኢዮአብንም። እነግርህ ዘንድ ወደዚህ ቅረብ በሉት ስትል ጮኸች። 17 ወደ እርስዋም ቀረበ፤ ሴቲቱም። ኢዮአብ አንተ ነህን? አለች። እርሱም። እኔ ነኝ ብሎ መለሰላት። እርስዋም። የባሪያህን ቃል ስማ አለችው። እርሱም። እሰማለሁ አላት። 18 እርስዋም። ቀድሞ። የሚጠይቅ በአቤል ዘንድ ይጠይቅ ይባል ነበር፤ እንዲሁም ነገሩ ይፈጸም ነበር። 19 በእስራኤል ዘንድ ሰላምንና እውነትን ከሚወድዱ እኔ ነኝ፤ አንተ በእስራኤል ያለችውን ከተማና እናት ለማፍረስ ትሻለህ፤ ስለ ምንስ የእግዚአብሔርን ርስት ትውጣለህ? ብላ ተናገረች። 20 ኢዮአብም መልሶ። ይህ መዋጥና ማጥፋት ከእኔ ይራቅ፤ 21 ነገሩ እንዲህ አይደለም፤ ከተራራማው ከኤፍሬም አገር የሚሆን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ የሚባል አንድ ሰው ግን በንጉሡ በዳዊት ላይ እጁን አነሣ፤ እርሱን ብቻውን ስጡኝ፥ እኔም ከከተማይቱ እርቃለሁ አላት። ሴቲቱም ኢዮአብን። እነሆ፥ ራሱ ከቅጥር ላይ ይጣልልሃል አለችው። 22 ሴቲቱም በብልሃትዋ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሳቤዔን ራስ ቈርጠው ወደ ኢዮአብ ጣሉት። እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፥ ሰውም ሁሉ ከከተማይቱ ርቆ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሄደ። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 23 ኢዮአብም በእስራኤል ሠራዊት ሁሉ ላይ አለቃ ነበረ፤ የዩዳሄም ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ 24 አዶኒራምም ግብር አስገባሪ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፤ 25 ሱሳም ጸሐፊ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤ 26 የኢያዕር ሰውም ዒራስ ለዳዊት አማካሪ ነበረ።

2 ሳሙኤል 21

1 በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም። የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። 2 ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። 3 ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች። የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድር ነው? አላቸው። 4 የገባዖን ሰዎችም። በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም። የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ። 5 ንጉሡንም። እኛን ካጠፋ፥ በእስራኤልም ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን 6 ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም። እሰጣችኋለሁ አለ። 7 ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። 8 ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ 9 ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። 10 የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። 11 የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። 12 ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፤ 13 ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። 14 የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ። 15 በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ሰልፍ ነበረ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹ ወረዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ ዳዊትም ደከመ። 16 ከራፋይም ወገን የነበረው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ይገድል ዘንድ አሰበ፤ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበረ፥ አዲስም የጦር መሣሪያ ታጥቆ ነበር። 17 የጽሩያም ልጅ አቢሳ አዳነው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች። አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም ብለው ማሉለት። 18 ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፥ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሳፍን ገደለ። 19 ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የቤተ ልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ። 20 ደግሞም በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 21 እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው። 22 እነዚያም አራቱ በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።

2 ሳሙኤል 22

1 ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ እጅ ሁሉ ባዳነው ቀን የዚህን ቅኔ ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ። 2 እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው፤ 3 እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ። 4 ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። 5 የሞት ጣር ያዘኝ፤ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤ 6 የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድ ደረሰብኝ። 7 በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። 8 ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የሰማዮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። 9 ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። 10 ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፤ ጨለማም ከእግሩ በታች ነበረ። 11 በኪሩብም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ ሆኖ ታየ፤ 12 መሰወርያውን ጨለማ፥ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን፥ በደመና ውስጥ የነበረ የጨለማ ውኃ አደረገ። 13 በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ። 14 እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ፤ 15 ፍላጻውን ላከ፥ በተናቸውም መብረቆችን ላከ፥ አወካቸውም። 16 ከእግዚአብሔር ዘለፋ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። 17 ከላይ ሰደደ፥ ወሰደኝም፤ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። 18 ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ በርትተውብኝ ነበርና። 19 በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ። 20 ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ። 21 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል፤ 22 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና። 23 ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና። 24 በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። 25 እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ፥ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። 26 ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ 27 ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። 28 አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ። 29 አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። 30 በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፤ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና። 31 የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፤ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። 32 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? 33 ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥ 34 እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያበረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። 35 እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፤ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ። 36 የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፤ ተግሣጽህም አሳደገኝ። 37 አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። 38 ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። 39 አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። 40 ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። 41 የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። 42 ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም። 43 እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፤ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም። 44 ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፤ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፤ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። 45 የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፤ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ። 46 የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፤ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ። 47 እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፤ 48 በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥ 49 ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። 50 አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። 51 የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፤ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።

2 ሳሙኤል 23

1 የዳዊትም የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብም አምላክ የተቀባው፥ በእስራኤል ዘንድ መልካም ባለ ቅኔ የሆነ፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት ንግግር፤ 2 የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ። 3 የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ፤ የእስራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ። በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፥ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፥ 4 እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ፀሐይ አወጣጥ፥ በጥዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፥ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል። 5 በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁ አይደለምን? ከእኔም ጋር በሁሉ ነገር ቅንና ጽኑ የሆነውን የዘላለም ቃል ኪዳን አድርጎአል፤ መድኃኒቴንና ፈቃዴን ሁሉ ያበቅላል። 6 ዓመፀኞች ሁሉ ግን ሰው በእጁ እንደማይዘው፥ እንደ ተጣለ እሾህ ናቸው። 7 ማናቸውም ሰው ይነካው ዘንድ ቢወደድ፥ በእጁ ብረትና የጦሩን የቦ ይይዛል፤ በሥራቸውም በእሳት ፈጽሞ ይቃጠላሉ። 8 የዳዊት ኃያላን ስም ይህ ነው። የአለቆች አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ ስምንት መቶ ያህል በአንድ ጊዜ ገደለ። 9 ከእርሱም በኋላ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከሦስቱ ኃያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ። 10 እርሱ ግን ተነሥቶ እጁ እስኪደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። 11 ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት እርሻ በአንድነት ሆነው ተከማችተው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 12 እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኃኒትአደረገ። 13 ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 14 በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። 15 ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ? ብሎ ተመኘ። 16 ሦስቱም ኃያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፥ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ። 17 አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ በነፍሳቸው ደፍረው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን? ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። 18 የጽሩያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሠላሳው አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ተጠርቶ ነበር። 19 እርሱ በሠላሳው መካከል የከበረ አልነበረምን? ስለዚህ አለቃቸው ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። 20 በቀብጽኤል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የቀብስኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 21 ረጅሙንም ግብጻዊ ሰው ገደለ፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው። 22 የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። 23 ከሠላሳውም ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በክብር ዘበኞቹ ላይ ሾመው። 24 የኢዮአብም ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፥ የቤተ ልሔም ሰው የዱዲ 25 ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሣማ፥ ሒሮዳዊው ኤሊቃ፥ 26 ፈልጣዊው ሴሌስ፥ የቴቁሐዊው 27 የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው 28 አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ምቡናይ፥ አሆሃዊው 29 ጸልሞን፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን 30 ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው 31 ሂዳይ፥ ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ በርሑማዊው 32 ዓዝሞት፥ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ 33 የአሳን ልጆች፥ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሣማ 34 የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የማዕካታዊው ልጅ የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥ 35 ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ አርባዊው ፈዓራይ፥ 36 የሱባ ሰው የናታን ልጅ ይግዓል፥ ጋዳዊው 37 ባኒ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬዎች አሞናዊው ጼሌቅ፥ ብኤሮታዊው 38 ነሃራይ፥ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው 39 ጋሬብ፥ ኬጢያዊው ኦርዮ፤ ሁሉ በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።

2 ሳሙኤል 24

1 ደግሞም የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ዳዊትንም። ሂድ፥ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር ብሎ በላያቸው አስነሣው። 2 ንጉሡም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊት አለቆች። የሕዝቡን ድምር አውቅ ዘንድ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ተመላለሱ፥ ሕዝቡንም ቍጠሩአቸው አላቸው። 3 ኢዮአብም ንጉሡን። የጌታዬ የንጉሡ ዓይን እያየ አምላክህ እግዚአብሔር ዛሬ ካለው ሕዝብ መጠን በላይ መቶ እጥፍ ይጨምርበት፤ ጌታዬ ንጉሡ ግን ይህን ነገር ለምን ይወድዳል? አለው። 4 ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብና በሠራዊቱ አለቆች ላይ አሸነፈ። ኢዮአብና የሠራዊቱ አለቆችም የእስራኤልን ሕዝብ ይቈጥሩ ዘንድ ከንጉሥ ዘንድ ወጡ። 5 ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፤ በጋድ ሸለቆ መካከል ባለችው በኢያዜር ከተማ ቀኝ በኩል በአሮዔር ላይ ሰፈሩ። 6 ወደ ገለዓድም ወደ ተባሶን አዳሰይ አገር መጡ፤ ወደ ዳንየዓንም ደረሱ፥ ወደ ሲዶናም ዞሩ፥ 7 ወደ ጢሮስም ምሽግ ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያንም ከተሞች ሁሉ መጡ፤ በይሁዳም ደቡብ በኩል በቤርሳቤህ ወጡ። 8 በአገሪቱም ሁሉ ላይ ተመላልሰው ከዘጠኝ ወርና ከሀያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 9 ኢዮአብም የሕዝቡን ቁጥር ድምር ለንጉሡ ሰጠ፤ በእስራኤልም ሰይፍ የሚመዝዙ ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ሰዎች ነበሩ፤ የይሁዳም ሰዎች አምስት መቶ ሺህ ነበሩ። 10 ሕዝቡንም ከቈጠረ በኋላ ዳዊትን ልቡ መታው፤ ዳዊትም እግዚአብሔርን። ባደረግሁት ነገር እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን፥ አቤቱ፥ ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታርቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 11 ዳዊትም ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዳዊት ባለ ራእይ ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ እንዲህ ሲል መጣ። 12 ሂድ ለዳዊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሦስት ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው አለው። 13 ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ። የሦስት ዓመት ራብ በአገርህ ላይ ይምጣብህን? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ከእነርሱ ትሸሽን? ወይስ የሦስት ቀን ቸነፈር በአገርህ ላይ ይሁን? አሁንም ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስብና መርምር ብሎ ነገረው። 14 ዳዊትም ጋድን። እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ አለው። 15 ዳዊትም ቸነፈሩን መረጠ፤ የስንዴም መከር ወራት በሆነ ጊዜ ቸነፈሩ በሕዝቡ መካከል ጀመረ፤ ከሕዝቡም ሰባ ሺህ ሰው ሞተ። 16 የእግዚአብሔርም መልአክ ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ እጁን በዘረጋ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ክፉው ነገር አዘነ፥ ሕዝቡንም የሚያጠፋውን መልአክ። እንግዲህ በቃህ፤ እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ነበረ። 17 ዳዊትም ሕዝቡን የሚመታውን መልእክ ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን። እነሆ፥ እኔ በድያለሁ ጠማማም ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፤ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ ብሎ ተናገረው። 18 በዚያም ቀን ጋድ ወደ ዳዊት መጥቶ። ውጣ፥ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ አለው። 19 ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20 ኦርናም ሲመለከት ንጉሡና ባሪያዎቹ ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ ኦርናም ወጥቶ በንጉሡ ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፋ። 21 ኦርናም። ጌታዬን ንጉሡን ወደ ባሪያው ያመጣው ምክንያት ምንድር ነው? አለ። ዳዊትም። መቅሠፍቱ ከሕዝቡ ላይ ይከለከል ዘንድ አውድማውን ከአንተ ገዝቼ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ልሠራ ነው አለው። 22 ኦርናም ዳዊትን። ጌታዬ ንጉሡ እንደ ወደደ ወስዶ ያቅርብ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች፥ ለሚቃጠልም እንጨት የአውድማ ዕቃና የበሬ ቀንበር አለ። 23 ንጉሥ ሆይ፥ ይህን ሁሉ ኦርና ለንጉሡ ይሰጣል አለው፤ ኦርናም ንጉሡን። አምላክህ እግዚአብሔር ይቀበልህ አለው። 24 ንጉሡም ኦርናን። እንዲህ አይደለም፥ ነገር ግን በዋጋ ከአንተ እገዛለሁ፤ ለአምላኬም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ያለ ዋጋ አላቀርብም አለው። ዳዊትም አውድማውንና በሬዎቹን በአምሳ ሰቅል ብር ገዛ። 25 በዚያም ዳዊት ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠልና የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርም ስለ አገሪቱ የተለመነውን ሰማ፥ መቅሠፍቱም ከእስራኤል ተከለከለ።

1 ነገሥት 1

1 ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር። 2 ባሪያዎቹም። ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት። 3 በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ። 4 ቈንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፥ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር። 5 የአጊትም ልጅ አዶንያስ። ንጉሥ እሆናለሁ ብሎ ተነሣ፤ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። 6 አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ። እንዲህ ለምን ታደርጋለህ? ብሎ አልተቈጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር። 7 ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፥ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር። 8 ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኃያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም። 9 አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 10 ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኃያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም። 11 ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት። ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን? 12 አሁንም ነዪ፥ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ። 13 ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ለእኔ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል? በዪው። 14 እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፥ ቃልሽንም አጸናለሁ። 15 ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፥ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር። 16 ቤርሳቤህም አጐንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም። ምን ትፈልጊያለሽ? አለ። 17 እርስዋም አለችው። ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ለባሪያህ። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ይቀመጣል ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤ 18 አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤ 19 እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካህኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ሰሎሞንን ግን አልጠራውም። 20 አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዓይን ይመለከትሃል። 21 ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኃጢአተኞች እንቈጠራለን። 22 እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ። 23 ለንጉሡም። እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ። 24 ናታንም አለ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ። ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለሃልን? 25 እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፥ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ። አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ ይላሉ። 26 ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም። 27 በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን? 28 ንጉሡም ዳዊት። ቤርሳቤህን ጥሩልኝ ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፥ በንጉሡም ፊት ቆመች። 29 ንጉሡም። ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን! 30 በእውነት። ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፥ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ ብሎ ማለ። 31 ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና። ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር አለች። 32 ንጉሡም ዳዊት። ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ። 33 ንጉሡም አላቸው። የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፥ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፥ ወደ ግዮንም አውርዱት፤ 34 በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ በሉ። 35 በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፥ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ። 36 የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ፥ ያበጅ ያድርግ፤ የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር። 37 እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፥ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ። 38 ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፥ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት። 39 ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ። ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ አሉ። 40 ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፥ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፥ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች። 41 አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምፅ ምንድር ነው? አለ። 42 እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም። አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ አለ። 43 ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ። በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው። 44 ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፥ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት። 45 ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፥ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምፅ ይህ ነው። 46 ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል። 47 የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ። 48 ንጉሡም ደግሞ። ዓይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን አለ። 49 አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፥ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ። 50 አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፥ ተነሥቶም ሄደ፥ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ። 51 ለሰሎሞንም። እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ። ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ ብሎ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞአል አሉት። 52 ሰሎሞንም። እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል አለ። 53 ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፥ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፥ ሰሎሞንም። ወደ ቤትህ ሂድ አለው።

1 ነገሥት 2

1 ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው። 2 እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ 3 በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 4 ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ። ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቈረጥብህም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 5 አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፥ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ። 6 አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፥ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው። 7 ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፥ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ። 8 እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፥ እኔም። በሰይፍ አልገድልህም ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ። 9 አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ያለ ቅጣት አትተወው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፥ ሽበቱንም ከደም ጋር ወደ መቃብር አውርድ። 10 ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። 11 ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠው ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። 12 ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና። 13 የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም። ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን? አለች፤ 14 እርሱም። በሰላም ነው አለ። ደግሞም። ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ አለ፤ እርስዋም። ተናገር አለች። 15 እርሱም። መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። 16 አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ አለ። እርስዋም። ተናገር አለችው። 17 እርሱም። አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ አለ። 18 ቤርሳቤህም። መልካም ነው፥ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ አለች። 19 ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም፥ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፥ በቀኙም ተቀመጠች። 20 እርስዋም። አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ አለች። ንጉሡም። እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኝ አላት። 21 እርስዋም። ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት አለች። 22 ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ። ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው አላት። 23 ንጉሡም ሰሎሞን። አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ። 24 አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል ብሎ በእግዚአብሔር ማለ። 25 ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፥ ሞተም። 26 ንጉሡም ካህኑን አብያታርን። አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ አለው። 27 በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው። 28 ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር እንጂ አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 29 ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን፥ ሂድ ውደቅበት ብሎ አዘዘው። 30 በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ። ንጉሡ። ውጣ ይልሃል አለው፤ እርሱም። በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም አለ። በናያስም። ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ። 31 ንጉሡም አለው። እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው። 32 አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው። 33 ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን። 34 የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ። 35 ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ። 36 ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና። በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፥ ወዲህና ወዲያም አትውጣ። 37 በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል አለው። 38 ሳሚም ንጉሡን። ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ። 39 ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ሳሚንም። እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው ብለው ነገሩት። 40 ሳሚም ተነሣ፥ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ። 41 ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ። 42 ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና። ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም። ቃሉ መልካም ነው፥ ሰምቻለሁ አልኸኝ። 43 የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም? አለው። 44 ንጉሡም ደግሞ ሳሚን። አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል። 45 ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፥ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል አለው። 46 ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፥ ወጥቶም ወደቀበት፥ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና። a

1 ነገሥት 3

1 ሰሎሞንም ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንን ልጅ አገባ፥ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አመጣት። 2 እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ስም መቅደስ አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋ ነበር። 3 ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፥ በአባቱም በዳዊት ሥርዓት ይሄድ ነበር፤ ብቻ በኮረብታ መስገጃ ይሠዋና ያጥን ነበር። 4 ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 5 እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም። ምን እንድሰጥህ ለምን አለ። 6 ሰሎሞንም አለ። እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል። 7 አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። 8 ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው። 9 ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል? 10 ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። 11 እግዚአብሔርም አለው። ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥ 12 እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ። 13 ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ። 14 አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ። 15 ሰሎሞንም ነቃ፥ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጥቶ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፥ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፥ ለባሪያዎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ። 16 በዚያን ጊዜም ሁለት ጋለሞቶች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ። 17 አንደኛይቱም ሴት አለች። ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ። 18 እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም። 19 እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። 20 እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች። 21 ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፥ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም። 22 ሁለተኛይቱም ሴት። ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች። ይህችም። የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፥ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር። 23 በዚያን ጊዜም ንጉሡ። ይህች። ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትላለች፤ ያችኛይቱም። አይደለም፥ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች አለ። 24 ንጉሡም። ሰይፍ አምጡልኝ አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ። 25 ንጉሡም። ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ አለ። 26 ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና። ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን። ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን አለች። 27 ንጉሡም መልሶ። ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት አለ። 28 ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ።

1 ነገሥት 4

1 ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። 2 የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥ 3 ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥ 4 የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤ 5 የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤ 6 አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ። 7 ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ አሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር። 8 ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤ 9 በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፤ 10 በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤ 11 በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤ 12 ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤ 13 በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፥ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወረወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤ 14 በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤ 15 በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤ 16 በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤ 17 በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤ 18 በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤ 19 በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ። 20 ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። 21 ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፥ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር። 22 ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥ 23 ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር አሥር ፍሪዳዎች ሀያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ። 24 ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር። 25 በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር። 26 ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች አሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት። 27 እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር። 28 እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር። 29 እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። 30 የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። 31 ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። 32 እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ። 33 ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። 34 ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። a

1 ነገሥት 5

1 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጅ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ ባሪያዎቹን ወደ ሰሎሞን ሰደደ። 2 ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ። 3 እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ። 4 አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም። 5 እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት። በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ። 6 አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቈረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ ባሪያዎችህን እዘዝ፤ ባሪያዎቼም ከባሪያዎችህ ጋር ይሁኑ፤ የባሪያዎችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ። 7 ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና። በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን አለ። 8 ኪራምም። የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ። 9 ባሪያዎቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ይጐትቱታል፤ እኔም በታንኳ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፥ በዚያም እፈታዋለሁ፥ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤቴም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ ብሎ ወደ ሰሎሞን ላከ። 10 እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት እንደሚሻው ያህል ሁሉ ለሰሎሞን ይሰጠው ነበር። 11 ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሀያ ሺ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ሀያ ኮርም ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር። 12 እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተጋቡ። 13 ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ። 14 በየወሩም እያከታተለ ወደ ሊባኖስ አሥር አሥር ሺህ ይሰድድ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም አስገባሪ ነበረ። 15 ሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት። 16 ይኸውም በሠራተኛው ሕዝብ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ሌላ ነው። 17 ንጉሡም ታላላቅ ምርጥ ምርጥ ድንጋዮችን ይቈፍሩና ይጠርቡ ዘንድ ለቤቱም መሠረት ይረበርቡት ዘንድ አዘዘ። 18 የሰሎሞንና የኪራምም አናጢዎች ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፥ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን አዘጋጁ።

1 ነገሥት 6

1 የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። 2 ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ። 3 በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት አሥር ክንድ ነበረ። 4 ለቤቱም በዓይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ። 5 በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፥ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። 6 የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ። 7 ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። 8 የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር። 9 ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው። 10 በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው። 11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል። 12 ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። 13 በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም። 14 ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፥ ፈጸመውም። 15 የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው። 16 በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሀያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው። 17 በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። 18 የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። 19 በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። 20 የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ስፋቱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 21 በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 22 ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው። 23 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ። 24 የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ። 25 ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ። 26 የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። 27 ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። 28 ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። 29 በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ። 30 የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። 31 ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። 32 ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው። 33 እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። 34 ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፥ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። 35 የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው። 36 የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው። 37 በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ። 38 በአሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዓቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው። a

1 ነገሥት 7

1 ሰሎሞንም የራሱን ቤት በአሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፥ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 2 የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ። 3 በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ አሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ አሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ። 4 መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፥ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። 5 ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። 6 አዕማዱም ያሉበቱን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ። 7 ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር። 8 ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ። 9 እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጕልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ። 10 መሠረቱም አሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር። 11 በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ። 12 በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር። 13 ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ። 14 እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብና በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ። 15 ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዓምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፥ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዓምድ እንዲሁ ነበረ። 16 በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ። 17 በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ። 18 ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፥ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ። 19 በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ። 20 በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ። 21 አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዓምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዓምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው። 22 በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበረ፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ። 23 ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። 24 ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ አሥር ለአንድ ክንድም አሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። 25 ኵሬውም በአሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። 26 ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር። 27 አሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ። 28 የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር። 29 በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር። 30 በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መንኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ። 31 በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፥ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም። 32 አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመንኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ። 33 የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ነበረ፥ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበር። 34 በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር። 35 በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር። 36 በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፥ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ። 37 እንዲሁ አሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ። 38 አሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በአሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር። 39 አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው። 40 ኪራምም ምንችቶችንና መጫሪያዎችን ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 41 ሁለቱም አዕማድ፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥ 42 በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። 43 አሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎችም ላይ የሚቀመጡትን አሥሩን መታጠቢያ ሰን፥ 44 አንዱንም ኵሬ፥ ከኵሬውም በታች የሚሆኑትን አሥራ ሁለቱን በሬዎች፥ 45 ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም አደረገ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራው ይህ ዕቃ ሁሉ የጋለ ናስ ነበረ። 46 በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። 47 ሰሎሞንም ዕቃውን ሁሉ ሳያስመዝን አኖረ፤ የናሱም ሚዛን ከብዛቱ የተነሣ አይቈጠርም ነበር። 48 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥ 49 በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች መኰስተሪያዎችም፥ 50 ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ። 51 እንዲሁ ንጉሡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ብርና ወርቅ ዕቃም፥ ሰሎሞን አገባ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አኖረው።

1 ነገሥት 8

1 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆችን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች የአባቶቻቸውን ቤቶች መሳፍንት፥ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው። 2 የእስራኤልም ሰዎች ኤታኒም በሚባል በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ተከማቹ። 3 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፤ ካህናቱም ታቦቱን አነሡ። 4 የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ በድንኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። 5 ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከእርሱ ጋር በታቦቱ ፊት ሆነው፥ ከብዛታቸው የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 6 ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት። 7 ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላይ በኩል ሸፍነው ነበር። 8 መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩ፤ በቅድስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ በውጭ ያለ ግን አያያቸውም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። 9 በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ፥ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። 10 ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 11 የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም። 12 ሰሎሞንም። እግዚአብሔር። በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል፤ 13 እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤት በእውነት ሠራሁልህ አለ። 14 ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 15 16 እርሱም አለ። ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ፥ በእርስዋም ቤት ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማ አልመረጥሁም፤ አሁን ግን ስሜ በዚያ ይሆን ዘንድ ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ይሆን ዘንድ ዳዊትን መርጫለሁ ብሎ ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። 17 አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አሰበ። 18 እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን። ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። 19 ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም አለው። 20 እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል አጸና፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። 21 ከግብጽም ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላለበት ታቦት ስፍራ በዚያ አደረግሁለት። 22 የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ። 23 እንዲህም አለ። የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ 24 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው። 25 አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ። አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። 26 አሁንም፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል፥ እባክህ፥ ይጽና። 27 በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! 28 ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ፤ 29 ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ። በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ። 30 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። 31 ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ 32 በሰማይ ስማ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑን አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። 33 ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 34 አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። 35 አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ 36 የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ። 37 በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ የሕዝብህም ጠላት የአገሩን ቀበሌዎች ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ 38 ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም አውቆ ጸሎትና ልመና ቢጸልይ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 39 40 ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው። 41 42 ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋውንም ክንድህን ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 43 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። 44 ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለእግዚአብሔር ቢጸልዩ፥ 45 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው። 46 የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች አገር ቢማረኩም፥ 47 በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በማራኪዎቹም አገር ሳሉ ተመልሰው። ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥ 48 በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 49 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ 50 ፍርድንም አድርግላቸው፥ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረት ስጣቸው፤ 51 ከግብፅ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና። 52 በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዓይኖችህ የተገለጡ ይሁኑ። 53 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አባቶቻችንን ከግብጽ ባወጣህ ጊዜ በባሪያህ በሙሴ እጅ እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና። 54 ሰሎሞንም ይህችን ጸሎትና ልመና ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸልዮ በፈጸመ ጊዜ፥ በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ነበርና ከእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ተነሣ። 55 ቆሞም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ በታላቅ ድምፅ ሲመርቅ እንዲህ አለ። 56 እንደ ተናገረው ተስፋ ሁሉ ለሕዝቡ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በባሪያው በሙሴ ከሰጠው ከመልካም ተስፋ ሁሉ አንድ ቃል አልወደቀም። 57 አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደ ነበረ ከእኛ ጋር ይሁን፤ አይተወን፥ አይጣለንም፤ 58 በመንገዱም ሁሉ እንሄድ ዘንድ፥ ለአባቶቻችንም ያዘዛትን ሥርዓትና ፍርድ ትእዛዙንም እንጠብቅ ዘንድ፥ ልባችንን ወደ እርሱ ያዘነብል ዘንድ። 59 ለባሪያውና ለሕዝቡ ለእስራኤል በየዕለቱ ፍርድን ያደርግ ዘንድ ይህች በእግዚአብሔር ፊት የለመንኋት ቃል በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር የቀረበች ትሁን፤ 60 የምድር አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ከእርሱም በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቅ ዘንድ። 61 እንደ ዛሬው ቀን በሥርዓቱ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር ልባችሁ ፍጹም ይሁን። 62 ንጉሡም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ሠዉ። 63 ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ለደኅንነት መሥዋዕት ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች አቀረበ። ንጉሡና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ። 64 በእግዚአብሔር ፊት ያለው የናሱ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ ይይዝ ዘንድ ታናሽ ስለ ነበረ፥ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ አሳርጎአልና በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩ መካከል ንጉሡ በዚያ ቀን ቀደሰ። 65 በዚያም ዘመን ሰሎሞን ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያለው ታላቅ ጉባኤ፥ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን በዓሉን አደረጉ። 66 በስምንተኛውም ቀን ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነርሱም ንጉሡን መረቁ፥ እግዚአብሔርም ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ። a

1 ነገሥት 9

1 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ 2 እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። 3 እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። 4 ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ 5 እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። 6 እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ 7 እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። 8 ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። 9 መልሰውም። ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ። 10 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 11 ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሀያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም የሚሻውን ያህል የዝግባና የጥድ እንጨት የሚሻውንም ያህል ወርቅ ሁሉ ለሰሎሞን ሰጥቶት ነበር። 12 ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ደስም አላሰኙትም። 13 እርሱም። ወንድሜ ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድር ናቸው? አለ። እስከ ዛሬም ድረስ የከቡል አገር ተብለው ተጠሩ። 14 ኪራምም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ ለንጉሡ ላከ። 15 ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት፥ ሚሎንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ ሐጾርንም፥ መጊዶንም፥ ጌዝርንም ይሠራ ዘንድ ገባሮችን መልምሎ ነበር። 16 የግብጽም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዝርን ይዞ ነበር፥ በእሳትም አቃጥሎ ነበር፥ በከተማም የኖሩትን ከነዓናውያን ገድሎ ነበር፤ ለልጁም ለሰሎምን ሚስት ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር። 17 ሰሎሞንም ጌዝርን፥ የታችኛውንም ቤት 18 ሖሮን፥ ባዕላትንም፥ በምድረ በዳም አገር ያለችውን ተድሞርን፥ 19 ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። 20 ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞራውያንና ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን፥ 21 የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ በኋላቸው የቀሩትን ልጆቻቸውን፥ ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 22 ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ። 23 ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 24 የፈርዖንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤትዋ ወጣች በዚያን ጊዜም ሚሎን ሠራ። 25 ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የደኅንነቱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ። 26 ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤሎት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። 27 ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር የባሕሩን ነገር የሚያውቁ መርከበኞች ባሪያዎቹን ሰደደ። 28 ወደ ኦፊርም መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ሀያ መክሊተ ወርቅ ወሰዱ፥ ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን ይዘው መጡ።

1 ነገሥት 10

1 የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። 2 በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 3 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። 4 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ 5 የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም። 6 ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 7 እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል። 8 በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። 9 አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ። 10 ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር። 11 ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም መርከቦች እጅግ ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ከኦፊር አመጡ። 12 ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያ ያለ የሰንደል እንጨት ከቶ አልመጣም አልታየምም። 13 ንጉሡም ሰሎሞን፥ በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች። 14 15 ግብርም የሚያስገብሩ ሰዎች ነጋዴዎችም የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድርም ሹማምት ከሚያወጡት ሌላ፥ በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 16 ንጉሡም ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላበሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 17 ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 18 ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። 19 ወደ ዙፋንም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተ ኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 20 በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 21 ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር የተባለውም ቤት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ እንጂ ብር አልነበረም። በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። 22 ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስ፥ ዝንጀሮና ዝንጕርጕር ወፍ ይዘው ይመጡ ነበር። 23 ንጉሡም ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ ነበር። 24 ምድርም ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰማ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ይመኝ ነበር። 25 ከእነርሱም እያንዳንዱ በዓመቱ በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎች እየያዘ ይመጣ ነበር። 26 ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 27 ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 28 ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነገዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። 29 አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያወጡላቸው ነበር። a

1 ነገሥት 11

1 ንጉሡም ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ፥ በሞዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያን በሲዶናውያንና በኬጢያውያን ሴቶች፥ በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ። 2 እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች። አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ ካላቸው ከአሕዛብ፥ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ። 3 ለእርሱም ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት። 4 ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም። 5 ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ። 6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም። 7 በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ። 8 ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 9 10 ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። 11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው። ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ። 12 ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። 13 ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም። 14 እግዚአብሔርም ከኤዶምያስ ነገሥታት ዘር የኤዶምያስን ሰው ሃዳድን ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው። 15 16 ኢዮአብና እስራኤልም ሁሉ የኤዶምያስን ወንድ ሁሉ እስኪገድሉ ድረስ ስድስት ወር በዚያ ተቀምጠው ነበርና ዳዊት በኤዶምያስ በነበረ ጊዜ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ ተወግተው የሞቱትን ሊቀብር በወጣ ጊዜ፥ የኤዶምያስንም ወንድ ሁሉ በገደለ ጊዜ፥ 17 ሃዳድ ገና ብላቴና ሳለ ሃዳድና ከእርሱ ጋር ጥቂቶቹ ከኤዶምያስ ሰዎች የሆኑ የአባቱ ባሪያዎች ወደ ግብጽ ኰብልለው ነበር። 18 ከምድያምም ተነሥተው ወደ ፋራን መጡ፤ ከእነርሱም ጋር ከፋራን ሰዎች ወሰዱ፥ ወደ ግብጽም መጡ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ፈርዖን ዘንድ ገቡ፤ እርሱም ቤት ሰጥቶ ቀለብ ዳረገው፥ ምድርም ሰጠው። 19 የሚስቱንም የእቴጌይቱን የቴቄምናስን እኅት እስኪያጋባው ድረስ ሃዳድ በፈርዖን ፊት እጅግ ባለምዋል ሆነ። 20 የቴቄምናስ እኅት ጌንባትን ወለደችለት፥ ቴቄምናስም በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም በፈርዖን ቤት በፈርዖን ልጆች መካከል ነበረ። 21 ሃዳድም በግብጽ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ፥ የሠራዊቱም አለቃ ኢዮአብ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ፥ ሃዳድ ፈርዖንን። ወደ አገሬ እሄድ ዘንድ አሰናብተኝ አለው። 22 ፈርዖንም። እነሆ፥ ከእኔ ዘንድ ወደ አገርህ መሄድ የፈለግህ ምን አጥተህ ነው? አለው። እርሱም። አንዳች አላጣሁም፤ ነገር ግን ልሂድ ብሎ መለሰ። ሃዳድም ወደ አገሩ ተመለሰ፥ ሃዳድም ያደረገው ክፉ ነገር ይህ ነው፤ እስራኤልን አስጨነቀ፥ በኤዶምያስም ላይ ነገሠ። 23 እግዚአብሔርም ደግሞ ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር የኰበለለውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ጠላት አድርጎ አስነሣበት። 24 ዳዊትም የሱባን ሰዎች በገደለ ጊዜ ሬዞን ሰዎችን ሰብስቦ የጭፍራ አለቃ ሆነ፤ ወደ ደማስቆም ሄዱ፥ በዚያም ተቀመጡ፤ በደማስቆም ላይ አነገሡት። 25 ሃዳድም ካደረገው ክፋት ሌላ በሰሎሞን ዘመን ሁሉ የእስራኤል ጠላት ነበረ። 26 ከሳሪራ አገር የሆነ የሰሎሞን ባሪያ የኤፍሬማዊው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እናቱም ጽሩዓ የተባለች ባልቴት ሴት ነበረች። 27 በንጉሡም ያመፀበት ምክንያት ይህ ነው፤ ሰሎሞን ሚሎን ሠራ፥ የአባቱንም የዳዊትን ከተማ ሰባራውን ጠገነ። 28 ኢዮርብዓምም ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ፤ ሰሎሞንም ጕልማሳው በሥራ የተመሰገነ መሆኑን ባየ ጊዜ በዮሴፍ ነገድ ሥራ ሁሉ ላይ ሾመው። 29 በዚያን ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ሴሎናዊው ነቢዩ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ ልብስ ለብሶ ነበር ሁለቱም በሜዳው ለብቻቸው ነበሩ። 30 አኪያም የለበሰውን አዲስ ልብስ ይዞ ከአሥራ ሁለት ቈራረጠው። 31 ኢዮርብዓምንም አለው። አሥር ቍራጭ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እቀድዳለሁ፥ አሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ፤ 32 ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ነገድ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን አንድ ነገድ ይቀርለታል፤ 33 ጥለውኛልና፥ ለሲዶናውያንም አምላክ ለአስታሮት፥ ለሞዓብም አምላክ ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች አምላክ ለሚልኮም ሰግደዋልና፥ አባቱም ዳዊት እንዳደረገ በፊቴ ቅን ነገር ያደርጉ ዘንድ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ይጠብቁ ዘንድ በመንገዴ አልሄዱምና። 34 መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዓቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ። 35 መንግሥቱንም ከልጁ እጅ እወስዳለሁ፥ ለአንተም አሥሩን ነገድ እሰጥሃለሁ። 36 ስሜንም ባኖርሁባት በዚያች በመረጥኋት ከተማ በኢየሩሳሌም ለባሪያዬ ለዳዊት በፊቴ ሁልጊዜ መብራት ይሆንለት ዘንድ ለልጁ አንድ ነገድ እሰጠዋለሁ። 37 አንተንም እወስድሃለሁ፥ ነፍስህም በወደደችው ሁሉ ላይ ትነግሣለች፥ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ትሆናለህ። 38 ባሪያዬም ዳዊት እንዳደረገ፥ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትሰማ፥ በመንገዴም ብትሄድ፥ በፊቴም የቀናውን ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትጠብቅ፥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ለዳዊትም እንደ ሠራሁለት ጽኑ ቤት እሠራልሃለሁ፥ እስራኤልንም ለአንተ እሰጥሃለሁ። 39 ስለዚህም የዳዊትን ዘር አስጨንቃለሁ፤ ነገር ግን በዘመን ሁሉ አይደለም። 40 ሰሎሞንም ኢዮርብዓምን ሊገድለው ወደደ፤ ኢዮርብዓምም ተነሥቶ ወደ ግብጽ ኰበለለ፥ ወደ ግብጽም ንጉሥ ወደ ሺሻቅ መጣ፥ ሰሎሞንም እስኪሞት ድረስ በግብጽ ተቀመጠ። 41 የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 42 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። 43 ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በፋንታው ነገሠ።

1 ነገሥት 12

1 እስራኤል ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2 እንዲህም ሆነ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፥ እርሱም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብጽ ተቀምጦ ነበርና፥ በግብጽም ሳለ ልከው ጠርተውት ነበርና 3 ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም። 4 አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። 5 እርሱም። ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። 6 ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7 እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት። 8 እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9 እርሱም። አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። 10 ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። 11 አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት። 12 ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13 ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው። 14 እንደ ብላቴኖችም ምክር። አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው። 15 እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም። 16 እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17 በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። 18 ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ሰደደ፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ደበደቡት፥ ሞተም። ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19 እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ። 20 እስራኤልም ሁሉ ኢዮርብዓም እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ ልከው ወደ ሸንጎአቸው ጠሩት፥ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሡት። ከብቻው ከይሁዳ ነገድ በቀረ የዳዊትን ቤት የተከተለ አንድ ሰው አልነበረም። 21 ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእስራኤልንም ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሰሎሞን ልጅ ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳ ቤት ሁሉና ከብንያም ነገድ የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ። 22 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ። 23 ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና ለይሁዳ ለብንያምም ቤት ሁሉ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ። 24 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ የእስራኤልንም ልጆች ወንድሞቻችሁን አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ ብለህ ንገራቸው ሲል መጣ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል ተመልሰው ሄዱ። 25 ኢዮርብዓምም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሴኬምን ሠርቶ በዚያ ተቀመጠ፤ ደግሞም ከዚያ ወጥቶ ጵኒኤልን ሠራ። 26 ኢዮርብዓምም በልቡ። አሁን መንግሥቱ ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል። 27 ይህ ሕዝብ በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ቢወጣ፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ወደ ጌታቸው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል፥ እኔንም ይገድሉኛል አለ። 28 ንጉሡም ተማከረ፥ ሁለትም የወርቅ ጥጆች አድርጎ። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ አላቸው። 29 አንዱን በቤቴል፥ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ። 30 ለአንዱ ጥጃ ይሰግድ ዘንድ ሕዝቡ እስከ ዳን ድረስ ይሄድ ነበርና ይህ ኃጢአት ሆነ። 31 በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎች ሠራ፥ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ። 32 በስምንተኛው ወር በአሥራ አምስተኛውም ቀን በይሁዳ እንደሚደረግ በዓል ያለ በዓል አደረገ፥ በመሠዊያውም ላይ ሠዋ፤ ለሠራቸውም ጥጆች ይሠዋ ዘንድ እንዲሁ በቤቴል አደረገ፤ ለኮረብታ መስገጃዎችም የመረጣቸውን ካህናት በቤቴል አኖራቸው። 33 በስምንተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በልቡ ባሰበው ቀን በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ ሠዋ፤ ለእስራኤልም ልጆች በዓል አደረገላቸው፤ በመሠዊያውም ሠዋ፥ ዕጣንም ዐጠነ። a

1 ነገሥት 13

1 እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር። 2 በመሠዊያውም ላይ። መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። 3 በዚያም ቀን። እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፥ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል ብሎ ምልክት ሰጠ። 4 ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ። ያዙት አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፥ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። 5 የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፥ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ። 6 ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፥ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፥ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እንደ ቀድሞም ሆነች። 7 ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና እንጀራም ብላ፥ በረከትም እሰጥሃለሁ አለው። 8 የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን። የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፥ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤ 9 እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና አለው። 10 በሌላም መንገድ ሄደ፥ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም። 11 በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይቀመጥ ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት። 12 አባታቸውም። በማናቸው መንገድ ሄደ? አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት። 13 ልጆቹንም። አህያውን ጫኑልኝ አላቸው፤ አህያውንም በጫኑለት ጊዜ ተቀመጠበት። 14 ከእግዚአብሔርም ሰው በኋላ ሄደ፤ በአድባርም ዛፍ በታች ተቀምጦ አገኘውና። ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን? አለው። እርሱም። እኔ ነኝ አለ። 15 እርሱም። ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ አለው። 16 እርሱም። ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም፤ 17 በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፥ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና አለ። 18 እርሱም። እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም። እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ አለው። ዋሽቶም ተናገረው። 19 ከእርሱም ጋር ተመለሰ፥ በቤቱም እንጀራ በላ፥ ውኃም ጠጣ። 20 በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤ 21 ከይሁዳም ወደ መጣው ወደ እግዚአብሔር ሰው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ዐምፀሃልና፥ አምላክህም እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ 22 ተመልሰህም። እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይደርስም ብሎ ጮኸ። 23 እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ አህያውን ጫነለት። 24 ተመልሶም በሄደ ጊዜ በመንገዱ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፥ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር። 25 እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳው በመንገዱ ወድቆ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ መጥተውም ሽማግሌው ነቢይ ተቀምጦባት በነበረው ከተማ አወሩ። 26 ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን በሰማ ጊዜ። በእግዚአብሔር አፍ ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል፥ እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ሰብሮም ገድሎታል አለ። 27 ልጆቹንም። አህያ ጫኑልኝ አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት። 28 ሄደም፥ ሬሳውም በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳው ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ። 29 ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፥ በአህያውም ላይ ጭኖ መለሰው፤ ያለቅስለትና ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው ይዞት መጣ። 30 ሬሳውንም በገዛ መቃብሩ አኖረው፤ ዋይ ዋይ ወንድሜ ሆይ እያሉ አለቀሱለት። 31 ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤ 32 በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና። 33 ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፉ መንገድ አልተመለሰም፥ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፥ እርሱም ለኮርብታዎቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር። 34 እስኪፈርስም ከምድርም እስኪጠፋ ድረስ ይህ ነገር ለኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት ሆነ።

1 ነገሥት 14

1 በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ። 2 ኢዮርብዓምም ሚስቱን። ተነሺ፥ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ እንዳትታወቂ ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንድነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ። 3 በእጅሽም አሥር እንጀራና እንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል አላት። 4 የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፥ ተነሥታም ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት መጣች። አኪያም ስለ መሸምገሉ ዓይኖቹ ፈዝዘው ነበርና፤ ማየት አልቻለም። 5 እግዚአብሔርም አኪያን። እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት አለው። 6 እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፥ እንዲህም አለ። የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ፤ ስለ ምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ። 7 ሂጂ፥ ለኢዮርብዓምም እንዲህ በዪው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፥ 8 ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። 9 ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፥ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ። 10 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራ አመጣለሁ፥ ከኢዮርብአምም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ እቈርጣለሁ፤ ሰውም ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ እኔ የኢዮርብዓምን ቤት ፈጽሜ እጠርጋለሁ። 11 ከኢዮርብዓምም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። 12 እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል። 13 እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፥ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል። 14 እግዚአብሔርም ደግሞ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ያስነሣል፤ እርሱም በዚያ ዘመን የኢዮርብዓምን ቤት ያጠፋል። 15 በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፥ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል። 16 ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኃጢአት እስራኤልን ይጥላል። 17 የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፥ ወደ ቴርሳ መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ። 18 በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት አለቀሱለትም። 19 የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20 ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሀያ ሁለት ዓመት ነበረ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናዳብ በፋንታው ነገሠ። 21 የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጉልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፤ እርስዋም አሞናዊት ነበረች። 22 ይሁዳም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቻቸውም ከሠሩት ሁሉ ይልቅ አብዝተው በሠሩት ኃጢአት አስቈጡት። 23 እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ። 24 በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር። 25 ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። 26 የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትንና የንጉሥ ቤት መዛግብትን ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ሰሎሞንም የሠራውን የወርቁን ጋሻ ሁሉ ወሰደ። 27 ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፥ የንጉሥንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። 28 ንጉሡም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። 29 የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 30 በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። 31 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያም በፋንታው ነገሠ። a

1 ነገሥት 15

1 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2 በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 3 ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኃጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም። 4 ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤ 5 ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና። 6 በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ። 7 የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያምና በኢዮርብዓምም መካከል ሰልፍ ነበረ። 8 አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ። 9 በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 10 በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 11 አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 12 ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፥ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ። 13 በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፥ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው። 14 ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ። 15 አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው። 16 በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። 17 የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ። 18 አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር። 19 በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ ሰደደ። 20 ወልደ አዴርም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ። 21 ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ። 22 ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፥ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። 23 የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ። 24 አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ። 25 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 26 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ። 27 ከይሳኮርም ቤት የሆነ የአኪያ ልጅ ባኦስ ተማማለበት፤ ናዳብና እስራኤልም ሁሉ ገባቶንን ከብበው ነበርና ባኦስ በፍልስጥኤም አገር ባለው በገባቶን ገደለው። 28 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት ባኦስ ናዳብን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ። 29 30 ንጉሥም በሆነ ጊዜ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ መታ፤ ኢዮርብዓምም ስለ ሠራው ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ስላስቈጣበት ማስቈጫ፥ በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ እስኪያጠፋው ድረስ ከኢዮርብዓም አንድ ትንፋሽ ያለው አላስቀረም። 31 የቀረውም የናዳብ ነገርና ያደረገው ሁሉ፥ ( 32) በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 33 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በእስራኤል ሁሉ ላይ በቴርሳ ንጉሥ ሆኖ ሀያ አራት ዓመት ነገሠ። 34 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በኢዮርብዓምም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።

1 ነገሥት 16

1 የእግዚአብሔርም ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ። 2 እኔ ከመሬት አስነሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄደሃል፥ በኃጢአታቸውም ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን አስተሃቸዋል። 3 ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ እጠርጋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ። 4 ከባኦስም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል። 5 የቀረውም የባኦስ ነገር፥ ሥራውና ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 6 ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በፋንታው ነገሠ። 7 በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ኢዩ መጣ። 8 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ። 9 የእኩሌቶቹም ሰረገሎች አለቃ ዘምሪ ተማማለበት፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፥ በቴርሳም በነበረው በቤት አሽከሮች አለቃ በኦሳ ቤት ይሰክር ነበር። 10 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ መታው ገደለውም፥ በፋንታውም ነገሠ። 11 ንጉሥም በሆነ ጊዜ፥ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ፤ ከዘመዶችና ከወዳጆች ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ አልቀረም። 12 13 ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኃጢአት ሁሉ፥ በምናምንቴም ሥራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኃጢአት፥ በነቢዩ በኢዩ እጅ በባኦስ ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ። 14 የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 15 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። ሕዝቡም በፍልስጥኤም አገር የነበረው ገባቶንን ከብበው ነበር። 16 ከተማይቱንም ከብበው የነበሩ ሕዝብ ዘምሪ እንደ ዐመፀ፥ ንጉሡንም እንደ ገደለ ሰሙ፤ እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ። 17 ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። 18 ዘምሪም ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፥ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤ 19 ስላደረገውም ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኃጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ። 20 የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 21 በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተለው፤ እኩሌታውም ዘንበሪን ተከተለ። 22 ዘንበሪንም የተከተለ ሕዝብ የጎናትን ልጅ ታምኒን በተከተለ ሕዝብ ላይ በረታ፤ ታምኒም ሞተ፥ ዘንበሪም ነገሠ። 23 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ አሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ። 24 ከሳምርም በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው። 25 ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፥ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ። 26 በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በምናምንቴም ነገራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኃጢአት ሄደ። 27 የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 28 ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በፋንታው ነገሠ። 29 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማሪያ ሀያ ሁለት ዓመት ነገሠ። 30 የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 31 በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፥ ሄዶም በኣልን አመለከ ሰገደለትም። 32 በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ። 33 አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ። 34 በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ። a

1 ነገሥት 17

1 በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን። በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው። 2 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት። 3 ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ። 4 ከወንዙም ትጠጣለህ፥ ቍራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ። 5 ሄደም እንደ እግዚአብሔር ቃልም አደረገ። ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተቀመጠ። 6 ቍራዎቹም በየጥዋትና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከወንዙም ይጠጣ ነበር። 7 ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ወንዙ ደረቀ። 8 ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ፤ 9 እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት ባልቴት አዝዣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣለት። 10 ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማይቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት ባልቴት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ እርሱም ጠርቶ። የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። 11 ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ ቁራሽ እንጀራ በእጅሽ ይዘሽ ትመጭ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። 12 እርስዋም። አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ አለች። 13 ኤልያስም አላት። አትፍሪ፤ ይልቅስ ሄደሽ እንዳልሺው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ 14 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋ አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጎድልም። 15 እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያሳ ቃል አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ቤትዋም ብዙ ቀን በሉ። 16 በኤልያስም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አልጎደለም። 17 ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ። 18 እርስዋም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው። 19 ኤልያስም። ልጅሽን ስጪኝ አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው በአልጋውም ላይ አጋደመው። 20 ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን? ብሎ ጮኸ። 21 በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፥ ወደ እግዚአብሔርም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጮኸ። 22 እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እርሱም ዳነ። 23 ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ኤልያስም። እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል ብሎ ለእናቱ ሰጣት። 24 ሴቲቱም ኤልያስን። የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ አለችው።

1 ነገሥት 18

1 ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት። ሂድ፥ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ። 2 ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር። 3 አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር። 4 ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር። 5 አክዓብም አብድዩን። በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን አለው። 6 ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ። 7 አብድዩም በመንገድ ሲሄድ፥ እነሆ፥ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፥ በግምባሩም ተደፍቶ። ጌታዬ ሆይ፥ ኤልያስ አንተ ነህን? አለ። 8 ኤልያስም። እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ። ኤልያስ ተገኝቶአል በል አለው። 9 አብድዩም አለ። እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ? 10 አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም። በዚህ የለም ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር። 11 አሁንም፥ እነሆ። ሂድ፥ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ። 12 እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር፥ ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር። 13 ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ፥ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ፥ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ፥ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው፥ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን? 14 አሁንም። ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ፤ እርሱም ይገድለኛል። 15 ኤልያስም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ አለ። 16 አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፥ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ። 17 አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ። እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው። 18 ኤልያስም። እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም። 19 አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ። 20 አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ። 21 ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ። እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም። 22 ኤልያስም ሕዝቡን አለ። ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው። 23 ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም። 24 እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ። ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ። 25 ኤልያስም የበኣልን ነቢያት። እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታችሁም እሳት አትጨምሩ አላቸው። 26 ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ። በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር። 27 በቀትርም ጊዜ ኤልያስ። አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው። 28 በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር። 29 ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም። 30 ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ። ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ። 31 ኤልያስም። ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ። 32 ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚያዝ ጕድጓድ ቈፈረ። 33 እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና። 34 አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ አሉ። ደግሞም። ድገሙ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም። ሦስተኛ አድርጉ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ። 35 ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው። 36 መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ። አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። 37 አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ። 38 የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች። 39 ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ። 40 ኤልያስም። ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው። 41 ኤልያስም አክዓብን። የዝናቡ ውሽንፍር እጅግ ነውና ተነሥተህ ውጣ፥ ብላም ጠጣም አለው። 42 አክዓብም ሊበላና ሊጠጣ ወጣ፤ ኤልያስም ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቱ መካከል አድርጎ በግምባሩ ተደፋ። 43 ብላቴናውንም። ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት አለው። ወጥቶም ተመልክቶም። ምንም የለም አለ። እርሱም። ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው። ብላቴናውም ሰባት ጊዜ ተመላለሰ። 44 በሰባተኛውም ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጥች አለ። እርሱም። ወጥተህ አክዓብን። ዝናብ እንዳይከለክልህ ሰረገላን ጭነህ ውረድ በለው አለ። 45 ከጥቂትም ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ፥ ብዙም ዝናብ ሆነ፤ አክዓብም በሰረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። 46 የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች፤ ወገቡንም አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።

1 ነገሥት 19

1 አክዓብም ኤልያስ ይህን ሁሉ እንዳደረገ፥ ነቢያትንም ሁሉ በሰይፍ እንደ ገደለ ለኤልዛቤል ነገራት። 2 ኤልዛቤልም። ነገ በዚህ ጊዜ ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብላ ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች። 3 ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፥ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፥ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። 4 እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና። ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ። 5 በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና። ተነሥተህ ብላ አለው። 6 ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም ጠጣም፥ ተመልሶም ተኛ። 7 የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና። የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ አለው። 8 ተነሥቶም በላ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኃይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። 9 እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆም። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። 10 እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ። 11 እርሱም። ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። 12 ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። 13 ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ። ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። 14 እርሱም። ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ። 15 እግዚአብሔርም አለው። ሂድ፥ በመጣህበትም መንገድ በምድረ በዳ ወደ ደማስቆ ተመለስ፤ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በሶርያ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አዛሄልን ቅባው፤ 16 በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ የናሜሲን ልጅ ኢዩን ቅባው፤ በፋንታህም ነቢይ ይሆን ዘንድ የአቤልምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው ከአዛሄልም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ። 17 ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል። 18 እኔም ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ። 19 ከዚያም ሄደ፥ የሣፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን በአሥራ ሁለት ጥማድ በሬዎች ሲያርስ፥ እርሱም ከአሥራ ሁለተኛው ጋር ሆኖ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ አልፎ መጐናጸፊያውን ጣለበት። 20 በሬዎቹንም ተወ፥ ከኤልያስም በኋላ ሮጦ። አባቴንና እናቴን እስማቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ተወኝ፥ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ አለው። እርሱም። ሂድና ተመለስ፤ ምን አድርጌልሃለሁ? አለው። 21 ከእርሱም ዘንድ ተመልሶ ሁለቱን በሬዎች ወስዶ አረዳቸው፥ ሥጋቸውንም በበሬዎቹ ዕቃ ቀቀለው፥ ለሕዝቡም ሰጣቸው፥ በሉም፤ እርሱም ተነሥቶ ኤልያስን ተከትሎ ሄደ፥ ያገለግለውም ነበር።

1 ነገሥት 20

1 ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። 2 አክዓብም ናቡቴን። በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው። 3 ናቡቴም አክዓብን። የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው። 4 ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ። የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም። 5 ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ። ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው። 6 እርሱም። ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን። የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን። የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት። 7 ሚስቱም ኤልዛቤል። አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ እንጀራም ብላ፥ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ አለችው። 8 በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች። 9 በደብዳቤውም። ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት፤ 10 ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች። 11 በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ። 12 የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት። 13 ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ፤ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት። 14 ወደ ኤልዛቤልም። ናቡቴ ተወግሮ ሞተ ብለው ላኩ። 15 ኤልዛቤልም ናቡቴ ተወግሮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ኤልዛቤል አክዓብን። ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ አለችው። 16 አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርድ ተነሣ። 17 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ። 18 ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ። 19 አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው። 20 አክዓብም ኤልያስን። ጠላቴ ሆይ፥ አገኘኸኝን? አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራስህን ሽጠሃልና። 21 እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፥ ፈጽሞም እጠርግሃለሁ፥ ከአክዓብም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ፤ 22 በሥራህም አስቈጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 23 ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ኤልዛቤል። በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል ብሎ ተናገረ። 24 ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል። 25 በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም። 26 እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራውያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖታትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገር ሠራ። 27 አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ ገላውን ማቅ አለበሰ፥ ጾመም፥ በማቅ ላይም ተኛ፥ ቅስስ ብሎም ሄደ። 28 29 ደግሞም። አክዓብ በፊቴ እንደ ተዋረደ አየህን? በፊቴ የተዋረደ ስለ ሆነ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ።

1 ነገሥት 21

1 የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥት ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም። 2 ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ። 3 ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፤ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ። 4 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፤ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው አለ። 5 ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው። ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር፤ 6 ነገም በዚህ ጊዜ ባሪያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባሪያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ አሉ። 7 የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ። ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም አለ። 8 ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ። አትስማው፥ እሺም አትበለው አሉት። 9 ለወልደ አዴርም መልእክተኞች። ለጌታዬ ለንጉሥ። ለእኔ ለባሪያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህን ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት አላቸው። መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት። 10 ወልደ አዴርም። ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደ ሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ ብሎ ላከበት። 11 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። በቃ፤ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ አለው። 12 ወልደ አዴርም ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባሪያዎቹንም። ተሰለፉ አላቸው፤ እነርሱም በከተማይቱ ትይዪ ተሰለፉ። 13 እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ አለ። 14 አክዓብም። በማን? አለ፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአውራጆቹ አለቆች ጕልማሶች አለ፤ እርሱም። ሰልፉን ማን ይጀምራል? አለ፤ እርሱም። አንተ አለው። 15 የአውራጆቹንም አለቆች ጕልማሶች ቈጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ቈጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ። 16 ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴር ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር። 17 የአውራጆቹም አለቆች ጕልማሶች አስቀድመው ወጡ፤ ወልደ አዴርም መልእክተኞችን ላከ፥ እነርሱም። ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል ብለው ነገሩት። 18 እርሱም። ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። 19 እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጕልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፥ ሠራዊትም ተከተላቸው። 20 ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፥ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር በፈረሱ አመለጠ። 21 የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፥ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊት ገደላቸው። 22 ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ። የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ አለው። 23 የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎች እንዲህ አሉት። አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን። 24 ይህንም አድርግ፤ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። 25 አንተም ቀድሞ እንደ ጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውንም በሰረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቍጠር፤ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን። ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። ፕ 26 በሚመጣውም ዓመት ወልደ አዴር ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። 27 የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር። 28 የእግዚአብሔርም ሰው ቀርቦ የእስራኤልን ንጉሥ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶርያውያን። እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ አለው። 29 እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፥ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ። 30 የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሀያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማይቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ። 31 ባሪያዎቹም። እነሆ፥ የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፥ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንውጣ፤ ምናልባት ነፍስህን ይምራታል አሉት። 32 ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፥ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ መጥተው። ባሪያህ ወልደ አዴር። ነፍሴን ትምራት ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎአል አሉት። እርሱም። ገና በሕይወቱ አለን? ወንድሜ ነው አለ። 33 ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው። ወንድምህ ወልደ አዴር አለ አሉት። እርሱም። ሂዱ፥ አምጡት አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ ወጣ፥ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው። 34 ወልደ አዴርም። አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተ በደማስቆ ገበያ ታደርጋለህ አለው። አክዓብም። እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው። 35 ከነቢያትም ወገን አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን። ምታኝ አለው። ሰውዮውም ይመታው ዘንድ እንቢ አለ። 36 እርሱም። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና እነሆ፥ ከእኔ በራቅህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል አለው። ከእርሱም በራቀ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37 ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ። ምታኝ አለው። ሰውዮውም መታው፥ በመምታቱም አቈሰለው። 38 ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ቆየው፤ ዓይኖቹንም በቀጸላው ሸፍኖ ተሸሸገ። 39 ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኸ። ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ አንድ ሰው አመጣና። ይህን ሰው ጠብቅ፥ ቢኰበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፥ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ። 40 ባሪያህም ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርድኸዋል አለው። 41 ፈጥኖም ቀጸላውን ከዓይኑ አነሣ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ አወቀው። 42 እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እርም ያልሁትን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ አለው። 43 የእስራኤልም ንጉሥ እየተቈጣና እየተናደደ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ወደ ሰማርያም መጣ።

1 ነገሥት 22

1 የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥት ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም። 2 ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ። 3 ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፤ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ። 4 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፤ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው አለ። 5 ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው። ወልደ አዴር እንዲህ ይላል። ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር፤ 6 ነገም በዚህ ጊዜ ባሪያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባሪያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ አሉ። 7 የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ። ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም አለ። 8 ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ። አትስማው፥ እሺም አትበለው አሉት። 9 ለወልደ አዴርም መልእክተኞች። ለጌታዬ ለንጉሥ። ለእኔ ለባሪያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህን ግን አደርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት አላቸው። መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት። 10 ወልደ አዴርም። ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደ ሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህን ይጨምሩብኝ ብሎ ላከበት። 11 የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ። በቃ፤ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ አለው። 12 ወልደ አዴርም ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባሪያዎቹንም። ተሰለፉ አላቸው፤ እነርሱም በከተማይቱ ትይዪ ተሰለፉ። 13 እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ አለ። 14 አክዓብም። በማን? አለ፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአውራጆቹ አለቆች ጕልማሶች አለ፤ እርሱም። ሰልፉን ማን ይጀምራል? አለ፤ እርሱም። አንተ አለው። 15 የአውራጆቹንም አለቆች ጕልማሶች ቈጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ቈጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ። 16 ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴር ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር። 17 የአውራጆቹም አለቆች ጕልማሶች አስቀድመው ወጡ፤ ወልደ አዴርም መልእክተኞችን ላከ፥ እነርሱም። ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል ብለው ነገሩት። 18 እርሱም። ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። 19 እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጕልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፥ ሠራዊትም ተከተላቸው። 20 ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፥ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር በፈረሱ አመለጠ። 21 የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፥ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊት ገደላቸው። 22 ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ። የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ አለው። 23 የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎች እንዲህ አሉት። አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን። 24 ይህንም አድርግ፤ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። 25 አንተም ቀድሞ እንደ ጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውንም በሰረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቍጠር፤ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን። ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። ፕ 26 በሚመጣውም ዓመት ወልደ አዴር ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። 27 የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር። 28 የእግዚአብሔርም ሰው ቀርቦ የእስራኤልን ንጉሥ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶርያውያን። እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ አለው። 29 እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፥ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ። 30 የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሀያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማይቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ። 31 ባሪያዎቹም። እነሆ፥ የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፥ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንውጣ፤ ምናልባት ነፍስህን ይምራታል አሉት። 32 ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፥ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ መጥተው። ባሪያህ ወልደ አዴር። ነፍሴን ትምራት ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎአል አሉት። እርሱም። ገና በሕይወቱ አለን? ወንድሜ ነው አለ። 33 ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው። ወንድምህ ወልደ አዴር አለ አሉት። እርሱም። ሂዱ፥ አምጡት አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ ወጣ፥ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው። 34 ወልደ አዴርም። አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተ በደማስቆ ገበያ ታደርጋለህ አለው። አክዓብም። እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው። 35 ከነቢያትም ወገን አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን። ምታኝ አለው። ሰውዮውም ይመታው ዘንድ እንቢ አለ። 36 እርሱም። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና እነሆ፥ ከእኔ በራቅህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል አለው። ከእርሱም በራቀ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37 ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ። ምታኝ አለው። ሰውዮውም መታው፥ በመምታቱም አቈሰለው። 38 ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ቆየው፤ ዓይኖቹንም በቀጸላው ሸፍኖ ተሸሸገ። 39 ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኸ። ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ አንድ ሰው አመጣና። ይህን ሰው ጠብቅ፥ ቢኰበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፥ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ። 40 ባሪያህም ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርድኸዋል አለው። 41 ፈጥኖም ቀጸላውን ከዓይኑ አነሣ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ አወቀው። 42 እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እርም ያልሁትን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ አለው። 43 የእስራኤልም ንጉሥ እየተቈጣና እየተናደደ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ወደ ሰማርያም መጣ።

2 ነገሥት 1

1 አክዓብም ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። 2 አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ ከዓይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም። ሂዱ ከዚህም ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ ብሎ መልእክተኞችን ላከ። 3 የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን። ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? 4 ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ። 5 መልእክተኞችም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፥ እርሱም። ለምን ተመለሳችሁ? አላቸው። 6 እነርሱም። አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና። ሂዱ፥ ወደ ላካችሁም ንጉሥ ተመልሳችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላከህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በሉት አለን አሉት። 7 እርሱም። ሊገናኛችሁ የወጣው፥ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል? አላቸው። 8 እነርሱም። ሰውዮው ጠጕራም ነው፥ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር አሉት። እርሱም። ቴስብያዊው ኤልያስ ነው አለ። 9 ንጉሡም የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፥ ወደ እርሱም ወጣ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ ነበር። እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ውረድ ይልሃል አለው። 10 ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች። 11 ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ እርሱም። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ንጉሡ። ፈጥነህ ውረድ ይላል ብሎ ተናገረ። 12 ኤልያስም። እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው። የእግዚአብሔርም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች። 13 ደግሞም ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ሰደደ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና። የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ነፍሴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። 14 እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳውን ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን ብሎ ለመነው። 15 የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን። ከእርሱ ጋር ውረድ፥ አትፍራውም አለው። ተነሥቶም ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ። 16 ኤልያስም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ መልእክተኞችን ልከሃልና ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም አለው። 17 ኤልያስም እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ። ልጅም አልነበረውምና በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ልጅ በኢዮራም በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 18 አካዝያስ ያደረገው የቀረው ነገር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

2 ነገሥት 2

1 እንዲህም ሆነ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ሊያወጣው በወደደ ጊዜ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ከጌልገላ ተነሣ። 2 ኤልያስም ኤልሳዕን። እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቆይ አለው። ኤልሳዕም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ወደ ቤቴልም ወረዱ። 3 በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ወጥተው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን፥ አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ አላቸው። 4 ኤልያስም። ኤልሳዕ ሆይ፥ እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። 5 ወደ ኢያሪኮም መጡ። በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው። እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው አውቀሃልን? አሉት። እርሱም። አዎን አውቄአለሁ፤ ዝም በሉ ብሎ መለሰ። 6 ኤልያስም። እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቆይ አለው። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም አለ። ሁለቱም ሄዱ። 7 ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፥ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። 8 ኤልያስም መጐናጸፊያውን ወስዶ ጠቀለለው፥ ውኃውንም መታ፥ ወዲህና ወዲያም ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። 9 ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን። ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም። መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። 10 እርሱም። አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ። 11 ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ። 12 ኤልሳዕም አይቶ። አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው። 13 ከኤልያስም የወደቀውን መጐናጸፊያ አነሣ፥ ተመልሶም በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። 14 ከኤልያስም የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ውኃውን መታና። የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? አለ፤ ውኃውንም በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ። 15 ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ። 16 እነርሱም። እነሆ፥ ከባሪያዎችህ ጋር አምሳ ኃያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ሸለቆ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት ዘንድ እንለምንሃለን አሉት። እርሱም። አትስደዱ አላቸው። 17 እስኪያፍርም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ። ስደዱ አለ፤ አምሳም ሰዎች ሰደዱ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም። 18 በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም። አትሂዱ አላልኋችሁምን? አላቸው። v 19 የከተማይቱም ሰዎች ኤልሳዕን። እነሆ፥ ጌታችን እንደምታይ የዚች ከተማ ኑሮ መልካም ነው፤ ውኃው ግን ክፉ ነው፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ትጨነግፋለች አሉት። 20 እርሱም። አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ፥ ጨውም ጨምሩበት አለ፤ ያንንም አመጡለት። 21 ውኃው ወዳለበቱም ምንጭ ወጥቶ ጨው ጣለበትና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ፤ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም አለ። 22 ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሶአል። 23 ከዚያም ወደ ቤቴል ወጣ፤ በመንገድም ሲወጣ ብላቴኖች ከከተማይቱ ወጥተው። አንተ መላጣ፥ ውጣ፤ አንተ መላጣ፥ ውጣ ብለው አፌዙበት። 24 ዘወርም ብሎ አያቸው፥ በእግዚአብሔርም ስም ረገማቸው፤ ከዱርም ሁለት ድቦች ወጥተው ከብላቴኖች አርባ ሁለቱን ሰባበሩአቸው። 25 ከዚያም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄደ፥ ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

2 ነገሥት 3

1 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፥ አሥራ ሁለትም ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ያሠራውን የበኣልን ሐውልት አርቆአልና እንደ አባቱና እንደ እናቱ አልነበረም። 3 ነገር ግን እስራኤልን ባሳታቸው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ተያዘ፤ ከእርሱም አልራቀም። 4 የሞዓብም ንጉሥ ሞሳ ባለ በጎች ነበረ፤ ለእስራኤልም ንጉሥ የመቶ ሺህ ጠቦትና የመቶ ሺህ አውራ በጎች ጠጕር ይገብርለት ነበር። 5 አክዓብም ከሞተ በኋላ የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ። 6 በዚያም ጊዜ ንጉሡ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ እስራኤልን ሁሉ አሰለፈ። 7 ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥ። የሞዓብ ንጉሥ ዐምፆብኛልና ከእኔ ጋር በሞዓብ ላይ ለሰልፍ ትሄዳለህን? ብሎ ላከ። እርሱም። እወጣለሁ፤ እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለ። 8 ደግሞም። በምን መንገድ እንሄዳለን? አለ፤ እርሱም። በኤዶምያስ ምድረ በዳ መንገድ ብሎ መለሰ። 9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ የኤዶምያስም ንጉሥ ሄዱ፤ የሰባትም ቀን መንገድ ዞሩ፤ ለሠራዊቱና ለተከተሉአቸውም እንስሶች ውኃ አልተገኘም። 10 የእስራኤልም ንጉሥ። ወዮ! እግዚአብሔር በሞዓብ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ እነዚህን ሦስቱን ነገሥታት ጠርቶአልና ወዮ አለ። 11 ኢዮሣፍጥም። በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎች አንዱ። በኤልያስ እጅ ላይ ውኃ ያፈስስ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ ብሎ መለሰ። 12 ኢዮሣፍጥም። የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል አለ። የእስራኤል ንጉሥና ኢዮሣፍጥ የኤዶምያስም ንጉሥ ወደ እርሱ ወረዱ። 13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ። አይደለም፥ በሞዓብ እጅ ይጥላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶአል አለው። 14 ኤልሳዕም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ያላፈርሁ ብሆን ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር። 15 አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ አለ። ባለ በገናውም በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ መጣችበት፤ 16 እንዲህም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ። 17 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 18 ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው፤ ደግሞም ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣል። 19 የተመሸጉትንና ያማሩትን ከተሞች ሁሉ ትመታላችሁ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ትቈርጣላችሁ፥ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ትደፍናላችሁ፥ መልካሞችንም እርሻዎች ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ። 20 በነጋውም የቍርባን ጊዜ ሲደርስ፥ እነሆ፥ ውኃ በኤዶምያስ መንገድ መጣ፥ ምድሪቱም ውኃ ሞላች። 21 ሞዓባውያንም ሁሉ ነገሥታት ሊወጉአቸው እንደ መጡ በሰሙ ጊዜ በወገባቸው ሰይፍ የሚታጠቁ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም በአገሩ ድንበር ላይ ቆሙ። 22 ማልደውም ተነሡ፤ ፀሐይም በውኃው ላይ አንጸባረቀ፥ ሞዓባውያንም በፊታቸው ውኃው እንደ ደም ቀልቶ አዩና። ይህ ደም ነው፤ 23 በእርግጥ ነገሥታት እርስ በርሳቸው ተዋጉ፥ እርስ በርሳቸውም ተጋደሉ፤ ሞዓብ ሆይ፥ እንግዲህ ወደ ምርኮህ ሂድ አሉ። 24 ወደ እስራኤል ሰፈር በመጡ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው ሞዓባውያንን መቱ፥ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ፤ ሞዓባውያንንም እየመቱ ወደ አገሩ ውስጥ ገቡ። 25 ከተሞችንም አፈረሱ፤ በመልካሞቹም እርሻዎች ሁሉ ላይ እስኪሞሉ ድረስ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ድንጋይ ይጥል ነበር፤ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ደፈኑ፥ የሚያፈሩትንም ዛፎች ሁሉ ቈረጡ፤ የቂርሐራሴትን ድንጋዮች ብቻ አስቀሩ፤ ባለ ወንጭፎች ግን ከብበው መቱአት። 26 የሞዓብም ንጉሥ ሰልፍ እንደ በረታበት ባየ ጊዜ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰባት መቶ ሰዎች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ ወደ ኤዶምያስም ንጉሥ ያልፉ ዘንድ ሞከሩ፤ አልቻሉምም። 27 በዚያም ጊዜ በእርሱ ፋንታ ንጉሥ የሚሆነውን የበኵር ልጁን ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በቅጥሩ ላይ አቀረበው። በእስራኤልም ዘንድ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ርቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ።

2 ነገሥት 4

1 ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት። ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች። 2 ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም። ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች። 3 እርሱም። ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ፤ አታሳንሻቸውም አላት። 4 ገብተሽም ከአንቺና ከልጆችሽ በኋላ በሩን ዝጊ፥ ወደ እነዚህም ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን ገልብጪ፤ የሞላውንም ፈቀቅ አድርጊ አለ። 5 እንዲሁም ከእርሱ ሄዳ በሩን ከእርስዋና ከልጆችዋ በኋላ ዘጋች፤ እነርሱም ማድጋዎቹን ወደ እርስዋ ያመጡ ነበር፥ እርስዋም ትገለብጥ ነበር። 6 ማድጋዎቹም በሞሉ ጊዜ ልጅዋን። ደግሞም ማድጋ አምጣልኝ አለችው፤ እርሱም። ሌላ ማድጋ የለም አላት፤ ዘይቱም ቆመ። 7 መጥታም ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው፤ እርሱም። ሄደሽ ዘይቱን ሽጪ ለባለ ዕዳውም ክፈዪ፤ አንቺና ልጆችሽም ከተረፈው ተመገቡ አለ። 8 አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ ኤልሳዕ ወደ ሱነም አለፈ፥ በዚያም ታላቅ ሴት ነበረች፤ እንጀራ ይበላ ዘንድ የግድ አለችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር እንጀራ ሊበላ ወደዚያ ይገባ ነበር። 9 ለባልዋም። ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ። 10 ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ፤ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት፤ ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው። 11 አንድ ቀንም ወደዚያ በመጣ ጊዜ ወደ ቤቱ ገብቶ በዚያ ዐረፈ። 12 ሎሌውንም ግያዝን። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። 13 በጠራትም ጊዜ በፊቱ ቆመች። እርሱም። እነሆ፥ ይህን ሁሉ አሳብ አሰብሽልኝ፤ አሁንስ ምን ላድርግልሽ? ለንጉሥ ወይስ ለሠራዊት አለቃ ልንገርልሽን? በላት አለው፤ እርስዋም። እኔ በወገኔ መካከል ተቀምጫለሁ ብላ መለሰች። 14 እርሱም። እንግዲህ ምን እናድርግላት? አለ። ግያዝም። ልጅ የላትም፤ ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ። 15 እርሱም። ጥራት አለ። በጠራትም ጊዜ በደጃፉ ቆመች። 16 እርሱም። በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ፤ እርስዋም። አይደለም ጌታዬ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች። 17 ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች። 18 ሕፃኑም አደገ፥ አንድ ቀንም እህል አጫጆች ወዳሉበት ወደ አባቱ ወጣ። 19 አባቱንም። ራሴን ራሴን አለው፤ እርሱም ሎሌውን። ተሸክመህ ወደ እናቱ ውሰደው አለው። 20 አንሥቶም ወደ እናቱ ወሰደው፤ በጕልበትዋም ላይ እስከ ቀትር ድረስ ተቀመጠ፥ ሞተም። 21 ወጥታም በእግዚአብሔር ሰው አልጋ ላይ አጋደመችው፥ በሩንም ዘግታበት ወጣች። 22 ባልዋንም ጠርታ። ወደ እግዚአብሔር ሰው በፍጥነት ደርሼ እመለስ ዘንድ አንድ ሎሌና አንድ አህያ ላክልኝ አለችው። 23 እርሱም። መባቻ ወይም ሰንበት ያይደለ ዛሬ ለምን ትሄጂበታለሽ? አለ። እርስዋም። ደኅና ነው አለች። 24 አህያውንም አስጭና ሎሌዋን። ንዳ፥ ሂድ፤ እኔ ሳላዝዝህ አታዘግየኝ አለችው። 25 እንዲሁም ሄደች፥ ወደ እግዚአብሔርም ሰው ወደ ቀርሜሎስ ተራራ መጣች። የእግዚአብሔርም ሰው ከሩቅ ባያት ጊዜ ሎሌውን ግያዝን፥ እነኋት ሱነማዊቲቱ መጣች፤ 26 ትቀበላትም ዘንድ ሩጥና። በደኅናሽ ነውን? ባልሽ ደኅና ነውን? ልጅሽስ ደኅና ነውን? በላት አለው። እርስዋም። ደኅና ነው አለች። 27 ወደ ተራራው ወደ እግዚአብሔር ሰው በመጣች ጊዜ እግሮቹን ጨበጠች፤ ግያዝም ሊያርቃት ቀረበ፤ የእግዚአብሔርም ሰው። ነፍስዋ አዝናለችና ተዋት፤ እግዚአብሔርም ያንን ከእኔ ሰውሮታል አልነገረኝምም አለ። 28 እርስዋም። በውኑ ከጌታዬ ልጅን ለመንሁን? እኔም አታታልለኝ አላልሁህምን? አለች። 29 ግያዝንም። ወገብህን ታጠቅ፥ በትሬንም በእጅህ ይዘህ ሂድ፤ ሰውም ብታገኝ ሰላም አትበል፥ እርሱም ሰላም ቢልህ አትመልስለት፤ በትሬንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኑር አለው። 30 የሕፃኑም እናት። ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! አልተውህም አለች፤ ተነሥቶም ተከተላት። 31 ግያዝም ቀደማቸው፥ በትሩንም በሕፃኑ ፊት ላይ አኖረው፤ ነገር ግን ድምፅ ወይም መስማት አልነበረም፤ እርሱንም ሊገናኘው ተመልሶ። ሕፃኑ አልነቃም ብሎ ነገረው። 32 ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። 33 ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 34 መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ፤ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት፤ የሕፃኑም ገላ ሞቀ። 35 ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ፤ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ፤ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ። 36 ግያዝንም ጠርቶ። ይህችን ሱነማዊት ጥራ አለው። ጠራትም፥ ወደ እርሱም በገባች ጊዜ። ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ አላት። 37 ገብታም በእግሩ አጠገብ ወደቀች በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጅዋንም አንሥታ ወጣች። 38 ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም። ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው። 39 አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው፤ ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም። 40 ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ፤ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ ብለው ጮኹ፤ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም። 41 እርሱም። ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም። 42 አንድ ሰውም ከበኣልሻሊሻ የበኵራቱን እንጀራ፥ ሀያ የገብስ እንጀራ፥ የእህልም እሸት በአቁማዳ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ሰው መጣ፤ እርሱም። ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ። 43 ሎሌውም። ይህን እንዴት አድርጌ ለመቶ ሰው እሰጣለሁ? አለ። እርሱም። ይበላሉ ያተርፋሉም ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ስጣቸው አለ። 44 እንዲሁም በፊታቸው አኖረው፥ እንደ እግዚአብሔርም ቃል በሉ፥ አተረፉም።

2 ነገሥት 5

1 የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ በጌታው ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ፥ ነገር ግን ለምጻም ነበረ። 2 ከሶርያውያንም አገር አደጋ ጣዮች ወጥተው ነበር፥ ከእስራኤልም ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማርከው ነበር፤ የንዕማንንም ሚስት ታገለግል ነበር። 3 እመቤትዋንም። ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር አለቻት። 4 ንዕማንም ገብቶ ለጌታው። ከእስራኤል አገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ ብላለች ብሎ ነገረው። 5 የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን። ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ አለው። እርሱም ሄደ፥ አሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወርቅ፥ አሥርም መለውጫ ልብስ በእጁ ወሰደ። 6 ለእስራኤልም ንጉሥ። ይህች ደብዳቤ ወደ አንተ ስትደርስ ባሪያዬን ንዕማንን ከለምጹ ትፈውሰው ዘንድ እንደ ሰደድሁልህ እወቅ የሚል ደብዳቤ ወሰደ። 7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያትም እንደሚፈልግብኝ እዩ አለ። 8 የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ። ልብስህን ለምን ቀደድህ? ወደ እኔ ይምጣ፥ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ። 9 ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፥ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ። 10 ኤልሳዕም። ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህም ይፈወሳል፥ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ። 11 ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፥ እንዲህም አለ። እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር። 12 የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? በእነርሱስ ውስጥ መታጠብና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን? ዘወርም ብሎ ተቈጥቶ ሄደ። 13 ባሪያዎቹም ቀርበው። አባት ሆይ፥ ነቢዩ ታላቅ ነገርስ እንኳ ቢነግርህ ኖሮ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ። ታጠብና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ! ብለው ተናገሩት። 14 ወረደም፥ የእግዚአብሔርም ሰው እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ሆኖ ተመለሰ፥ ንጹሕም ሆነ። 15 እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመለሰ፥ ወጥቶም በፊቱ ቆመና። እነሆ፥ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ፤ አሁንም ከባሪያህ በረከት ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ አለ። 16 እርሱም። በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ። 17 ንዕማንም። እኔ ባሪያህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር እንድወስድ እሺ ትለኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 18 እግዚአብሔርም ለእኔ ለባሪያህ በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬሞን ቤት በገባ ጊዜ፥ እኔም በሬሞን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ለእኔ ለባሪያህ ይቅር ይበለኝ አለ። 19 እርሱም። በደኅና ሂድ አለው። አንድ አግድመትም ያህል ከእርሱ ራቀ። 20 የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ። ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፥ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፥ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ አለ። 21 ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ። ሁሉ ደኅና ነውን? አለው። 22 እርሱም። ደኅና ነው። አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ አለ። 23 ንዕማንም። ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ። 24 ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፥ እነርሱም ሄዱ። 25 እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም። ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም አለ። 26 እርሱም። ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን? 27 እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ፥ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።

2 ነገሥት 6

1 የነቢያትም ልጆች ኤልሳዕን። እነሆ፥ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠብቦናል። 2 ወደ ዮርዳኖስም እንሂድ፥ ከእኛም እያንዳንዱ ከዚያ ምሰሶ ያምጣ፥ የምንቀመጥበትንም ስፍራ በዚያ እንሥራ አሉት፤ እርሱም። ሂዱ አለ። 3 ከእነርሱም አንዱ። አንተ ደግሞ ከእኛ ከባሪያዎችህ ጋር ለመሄድ ፍቀድ አለ። እርሱም። እሄዳለሁ አለ። 4 ከእነርሱም ጋር ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ እንጨት ቆረጡ። 5 ከእነርሱም አንዱ ምሰሶውን ሲቆርጥ የምሳሩ ብረት ወደ ውኃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም። ጌታዬ ሆይ፥ ወየው! ወየው! የተዋስሁት ነበረ ብሎ ጮኽ። 6 የእግዚአብሔርም ሰው። የወደቀው ወዴት ነው? አለ ስፍራውንም አሳየው፤ እንጨትም ቆርጦ በዚያ ጣለው፥ ብረቱም ተንሳፈፈ። 7 እርሱም። ውሰደው አለ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው። 8 የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከባሪያዎቹም ጋር ተማክሮ። በዚህ ተደብቀን እንሰፍራለን አለ። 9 የእግዚአብሔርም ሰው። ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። 10 የእስራኤልም ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ነገረው ስፍራ ሰደደ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ። 11 የሶርያም ንጉሥ ልብ ስለዚህ እጅግ ታወከ፤ ባሪያዎቹንም ጠርቶ። ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ አትነግሩኝምን? አላቸው። 12 ከባሪያዎቹም አንዱ። ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ። 13 እርሱም። ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደ ሆነ እዩ አለ። እነርሱም። እነሆ፥ በዶታይን አለ ብለው ነገሩት። 14 ወደዚያም ፈረሶችንና ሰረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ። 15 የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሰረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም። ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናደርጋለን? አለው። 16 እርሱም። ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው። 17 ኤልሳዕም። አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር። 18 ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ። ይህን ሕዝብ ዕውር ታደርገው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል ዕውር አደረጋቸው። 19 ኤልሳዕም። መንገዱ በዚህ አይደለም፥ ከተማይቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ አላቸው፤ ወደ ሰማርያም መራቸው። 20 ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ። አቤቱ፥ ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዓይኖች ግለጥ አለ፤ እግዚአብሔርም ዓይኖቻቸውን ገለጠ፥ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል ነበሩ። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን። አባቴ ሆይ፥ ልግደላቸውን? ልግደላቸውን? አለው። 22 እርሱም። አትግደላቸው፤ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኸውን ትገድል ዘንድ ይገባሃልን? እንጀራና ውኃ በፊታቸው አኑርላቸው፥ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይሂዱ አለው። 23 ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፥ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም። 24 ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፥ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት። 25 በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በአምሳ ብር፥ የርግብም ኩስ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ ከበቡአት። 26 የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ በተመላለሰ ጊዜ አንዲት ሴት ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እርዳኝ ብላ ወደ እርሱ ጮኸች። 27 እርሱም። እግዚአብሔር ያልረዳሽን እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጥመቂያው ነውን? አለ። 28 ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት፤ እርስዋም። ይህች ሴት። ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ። 29 ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም። እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት። 30 ንጉሡም የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተ ውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ። 31 ንጉሡም። የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ አለ። 32 ኤልሳዕ ግን በቤቱ ተቀምጦ ነበር፥ ሽማግሌዎችም ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር፤ ንጉሡ ሰው ላካ፤ መልእክተኛውም ገና ሳይደርስ ለሽማግሌዎች። ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደ ላከ እዩ፤ መልእከተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው አላቸው። 33 ሲናገራቸውም መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ፤ እርሱም። እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድር ነኝ? አለ።

2 ነገሥት 7

1 ኤልሳዕም። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ። 2 ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ። ፕ 3 በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም። እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን? 4 ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፥ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን ተባባሉ። 5 ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም። 6 እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሰረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም። እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል ይባባሉ ነበር። 7 ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ። 8 እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ ጠጡም፥ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፥ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፥ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ። 9 ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው። መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፥ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተ ሰብ እንናገር ተባባሉ። 10 መጥተውም። ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፥ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፥ የሰውም ድምፅ አልነበረም ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ። 11 የደጁም ጠባቂዎች ጠሩ፥ ለንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ። 12 ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን። ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ። ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፥ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል አላቸው። 13 ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ። በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፥ እንይም አለ። 14 ሁለትም ሰረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም። ሄዳችሁ እዩ ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ። 15 በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት። 16 ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ። 17 ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ። 18 የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ። ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ። 19 ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? ብሎ ነበር፤ እርሱም። እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም ብሎት ነበር። 20 እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።

2 ነገሥት 8

1 ኤልሳዕም ልጅዋን ያስነሣላትን ሴት። አንቺ ከቤተ ሰብሽ ጋር ተነሥተሽ ሂጂ፥ በምታገኚውም ስፍራ ተቀመጪ፤ እግዚአብሔር ራብ ጠርቶአል፤ ሰባት ዓመትም በምድር ላይ ይመጣል ብሎ ተናገራት። 2 ሴቲቱም ተነሥታ እንደ እግዚአብሔር ሰው ቃል አደረገች፤ ከቤተ ሰብዋም ጋር ሄዳ በፍልስጥኤም አገር ሰባት ዓመት ተቀመጠች። 3 ሰባቱም ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሴቲቱ ከፍልስጥኤም አገር ተመለሰች፤ ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ልትጮኽ ወደ ንጉሡ ወጣች። 4 ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ከግያዝ ጋር። ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ንገረኝ እያለ ይጫወት ነበር። 5 እርሱም የሞተውን እንደ አስነሣ ለንጉሡ ሲናገር፥ እነሆ፥ ልጅዋን ያስነሣላት ሴት ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ወደ ንጉሥ ጮኸች፤ ግያዝም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሴቲቱ ይህች ናት፥ ኤልሳዕም ያስነሣው ልጅዋ ይህ ነው አለ። 6 ንጉሡም ሴቲቱን ጠየቀ፥ ነገረችውም። ንጉሡም። የነበረላትን ሁሉ፥ መሬትዋንም ከተወች ጀምራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የእርሻዋን ፍሬ ሁሉ መልስላት ብሎ ስለ እርስዋ ጃንደረባውን አዘዘ። 7 ኤልሳዕም ወደ ደማስቆ መጣ፤ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ታምሞ ነበር፤ ወሬኞችም። የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት። 8 ንጉሡም አዛሄልን። ገጸ በረከት በእጅህ ወስደህ የእግዚአብሔርን ሰው ልትገናኝ ሂድ፤ በእርሱም አፍ። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ አለው። 9 አዛሄልም ሊገናኘው ሄደ፥ ከእርሱም ጋር ከደማስቆ መልካሙን ነገር ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ወሰደ፤ መጥቶም በፊቱ ቆመና። ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ሲል ወደ አንተ ልኮኛል አለ። 10 ኤልሳዕም። ሂድ፥ መዳንስ ትድናለህ በለው፤ ነገር ግን እንዲሞት እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው። 11 እስኪያፍርም ድረስ ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው አነባ። 12 አዛሄልም። ጌታዬ ለምን ያነባል? አለ። እርሱም። በእስራኤል ልጆች ላይ የምታደርገውን ክፋት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፥ ጕልማሶቻቸውንም በሰይፍ ትገድላለህ፥ ሕፃናቶቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፥ እርጉዞቻቸውንም ትቀድዳለህ አለው። 13 አዛሄልም። ይህን ታላቅ ነገር አደርግ ዘንድ እኔ ውሻ ባሪያህ ምንድር ነኝ? አለ። ኤልሳዕም። አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው። 14 ከኤልሳዕም ርቆ ወደ ጌታው መጣ፤ እርሱም። ኤልሳዕ ምን አለህ? አለው። 15 እርሱም። እንድትፈወስ ነገረኝ አለው። በነጋውም ለሐፍ ወስዶ በውኃ ነከረው በፊቱም ላይ ሸፈነው፥ ሞተም። አዛሄልም በፋንታው ነገሠ። 16 በእስራኤልም ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ። 17 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 18 የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 19 ነገር ግን ለእርሱና ለልጆቹ ለዘመኑ ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ተስፋ እንደ ሰጠ፥ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠፋ ዘንድ አልወደደም። 20 በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ ለይሁዳ እንዳይገብር ሸፈተ፥ በላያቸውም ንጉሥ አነገሡ። 21 ኢዮራምም ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ወደ ጸዒር አለፈ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 22 ኤዶምያስ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር እስከ ዛሬ ድረስ ሸፈተ። በዚያም ዘመን ደግሞ ልብና ሸፈተ። 23 የተረፈውም የኢዮራም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 24 ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በፋንታውም ልጁ አካዝያስ ነገሠ። 25 በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 26 መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች። 27 በአክዓብም ቤት መንገድ ሄደ፥ እንደ አክዓብም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ለአክዓብ ቤት አማች ነበረና። 28 ከአክዓብም ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊጋጠም ሄደ፤ ሶርያውንም ኢዮራምን አቆሰሉት። 29 ንጉሡም ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የአክዓብም ልጅ ኢዮራም ታምሞ ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊያየው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

2 ነገሥት 9

1 ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው። ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ማሰሮ በእጅህ ያዝ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ። 2 በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፥ ወደ ጓዳም አግባው። 3 የዘይቱንም ማሰሮ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ በለው፤ በሩንም ከፍተህ ሽሽ፥ አትዘግይም። 4 እንዲሁም ጕልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ። 5 በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነገር አለኝ አለ። ኢዩም። ከማንኛችን ጋር ነው? አለ። እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነው አለ። 6 ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ። 7 የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። 8 የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል፤ በእስራኤልም ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ ከአክዓብ አጠፋለሁ። 9 የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10 ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፥ የሚቀብራትም አታገኝም። በሩንም ከፍቶ ሸሸ። 11 ኢዩም ወደ ጌታው ባሪያዎች ወጣ፤ እነርሱም። ደኅና ነውን? ይህ እብድ ለምን መጣብህ? አሉት። እርሱም። ሰውዮውንና ነገሩን ታውቃላችሁ አላቸው። 12 እነርሱም። ሐሰት ነው፤ ንገረን አሉት፤ እርሱም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ ብሎ እንዲህ እንዲህ ነገረኝ አላቸው። 13 ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ፥ በሰገነቱ መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት፥ ቀንደ መለከትም እየነፉ፥ ኢዩ ነግሦአል አሉ። 14 እንዲሁም የናሜሲ ልጅ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ ተማማለ። ኢዮራምና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል የተነሣ ሬማት ዘገለዓድን ይጠብቁ ነበር። 15 ንጉሡ ኢዮራም ግን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም። ልባችሁስ ከእኔ ጋር ከሆነ በኢይዝራኤል እንዳያወራ ማንም ከከተማ ኰብልሎ አይውጣ አለ። 16 ኢዮራምም በዚያ ታምሞ ተኝቶ ነበርና ኢዩ በሰረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮራምን ለማየት ወርዶ ነበር። 17 በኢይዝራኤልም ግንብ ላይ የቆመው ሰላይ የኢዩ ጭፍራ ሲመታ አይቶ። ጭፍራ አያለሁ አለ። ኢዮራምም። የሚገናኘው ፈረሰኛ ላክ፥ እርሱም። ሰላም ነውን? ይበለው አለ። 18 ፈረሰኛውም ሊገናኘው ሄዶ። ንጉሡ እንዲህ ይላል። ሰላም ነውን? አለ። ኢዩም። አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ አለ። ሰላዩም። መልእክተኛው ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም ብሎ ነገረው። 19 ሁለተኛም ፈረሰኛ ሰደደ፥ ወደ እነርሱም ደርሶ። ንጉሡ እንዲህ ይላል። ሰላም ነውን?አለ። ኢዩም። አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ አለ። 20 ሰላዩም። ደረሰባቸው፥ ነገር ግን አልተመለሰም፤ በችኰላ ይሄዳልና አካሄዱ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አካሄድ ነው ብሎ ነገረው። 21 ኢዮራምም። ሰረገላ አዘጋጁ አለ፤ ሰረገላውንም አዘጋጁለት። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮራም የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ በሰረገሎቻቸው ተቀምጠው ወጡ፥ ኢዩንም ሊገናኙት ሄዱ፤ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ውስጥ አገኙት። 22 ኢዮራምም ኢዩን ባየ ጊዜ። ኢዩ ሆይ፥ ሰላም ነውን? አለ። እርሱም። የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተትዋ ሲበዛ ምን ሰላም አለ? ብሎ መለሰ። 23 ኢዮራምም መልሶ ነዳና ሸሸ፥ አካዝያስንም። አካዝያስ ሆይ፥ ዓመፅ ነው አለው። 24 ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ፥ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ፥ ወደ ሰረገላውም ውስጥ ወደቀ። 25 ኢዩም አለቃውን ቢድቃርን እንዲህ አለው። አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ጣለው፥ አንተና እኔ ጎን ለጎን በፈረስ ተቀምጠን አባቱን አክዓብን በተከተልን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይህን መከራ እንደ ተናገረበት አስብ። 26 በእውነት የናቡቴንና የልጆቹን ደም ትናንትና አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚህም እርሻ እመልስብሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ወስደህ በእርሻው ውስጥ ጣለው። 27 የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ያንን ባየ ጊዜ በአትክልት ቤት መንገድ ሸሸ። ኢዩም። ይህን ደግሞ በሰረገላው ላይ ውጉት እያለ ተከተለው፤ በይብለዓምም አቅራቢያ ባለችው በጉር ዐቀበት ላይ ወጉት። ወደ መጊዶም ሸሸ፥ በዚያም ሞተ። 28 ባሪያዎቹም በሰረገላው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፥ በዳዊትም ከተማ በመቃብሩ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። 29 በአክዓብም ልጅ በኢዮራም በአሥራ አንደኛው ዓመት አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 30 ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል መጣ፤ ኤልዛቤልም በሰማች ጊዜ ዓይንዋን ተኳለች፥ ራስዋንም አስጌጠች፥ በመስኮትም ዘልቃ ትመለከት ነበር። 31 ኢዩም በበሩ ሲገባ። ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሆይ፥ ሰላም ነውን? አለችው። 32 ፊቱንም ወደ መስኮቱ አንሥቶ። ከእኔ ጋር ማን ነው? አለ። ሁለት ሦስትም ጃንደረቦች ወደ እርሱ ተመለከቱ። 33 እርሱም። ወደ ታች ወርውሩአት አለ፤ ወረወሩአትም፥ ደምዋም በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ፥ ረገጡአትም። 34 በገባም ጊዜ በላ ጠጣም፤ ከዚያም በኋላ። ይህችን የተረገመች እዩ፤ የንጉሥ ልጅ ናትና ቅበሩአት አለ። 35 ሊቀብሩአትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍም በቀር ምንም አላገኙም። 36 ተመልሰውም ነገሩት፤ እርሱም። በባሪያው በቴስብያዊ ኤልያስ። በኢይዝራኤል እርሻ የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ፤ 37 የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል እርሻ መሬት ላይ እንደ ፍግ ይሆናልና ማንም። ይህች ኤልዛቤል ናት ይል ዘንድ አይችልም ብሎ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው አለ።

2 ነገሥት 10

1 ለአክዓብም በሰማርያ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ ኢዩም ደብዳቤ ጻፈ፤ የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ለሰማርያ ታላላቆችና ሽማግሌዎች። 2 ይህ ደብዳቤ አሁን በደረሳችሁ ጊዜ የጌታችሁ ልጆች ሰረገሎችና ፈረሶችም የተመሸገችም ከተማ መሣሪያዎችም በእናንተ ዘንድ አሉና፥ 3 ከጌታችሁ ልጆች ደስ የሚያሰኛችሁንና የሚሻላችሁን ምረጡ፥ በአባቱም ዙፋን አስቀምጡት፥ ስለ ጌታችሁም ቤት ተዋጉ ብሎ ወደ ሰማርያ ሰደደ፤ 4 እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው። እነሆ፥ ሁለቱ ነገሥታት በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም፤ እኛስ እንዴት እንቆማለን? አሉ። 5 የቤቱ አለቃ፥ የከተማይቱም አለቃ፥ ሽማግሌዎችና ልጆቹን የሚያሳድጉ። እኛ ባሪያዎችህ ነን፥ ያዘዝኸንም ሁሉ እናደርጋለን፤ ንጉሥም በላያችን አናነግሥም፤ የምትወድደውን አድርግ ብለው ወደ ኢዩ ላኩ። 6 ሁለተኛም። ወገኖቼስ እንደ ሆናችሁ፥ ነገሬንም ከሰማችሁ፥ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቍረጡ፥ ነገም በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ ብሎ ደብዳቤ ጻፈላቸው። የንጉሡም ልጆች ሰባው ሰዎች በሚያሳድጓቸው በከተማይቱ ታላላቆች ዘንድ ነበሩ። 7 ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ የንጉሡን ልጆች ሰባውን ሰዎች ይዘው ገደሉአቸው፤ ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ወደ እርሱ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ። 8 መልእክተኛም መጥቶ። የንጉሡን ልጆች ራስ ይዘው መጥተዋል ብሎ ነገረው። እርሱም። እስከ ነገ ድረስ በበሩ አደባባይ ሁለት ክምር አድርጋችሁ አኑሩአቸው አለ። 9 በነጋውም ወጥቶ ቆመ፥ ሕዝቡንም ሁሉ። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ እነሆ፥ ጌታዬን የወነጀልሁ የገደልሁትም እኔ ነኝ፤ እነዚህንስ ሁሉ የገደለ ማን ነው? 10 እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል አላቸው። 11 ኢዩም ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው። 12 ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥ 13 ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ። እናንተ እነማን ናችሁ? አለ። እነርሱም። እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌይቱን ልጆች ደኅንነት ለመጠየቅ እንወርዳለን አሉት። 14 እርሱም። በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። ያዙአቸውም፥ በበግ ጠባቂዎችም ቤት አጠገብ ባለው ጕድጓድ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ማንንም አላስቀረም። 15 ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው፤ ደኅንነቱንም ጠይቆ። ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን? አለው፤ ኢዮናዳብም። እንዲሁ ነው አለው። ኢዩም። እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሰረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና። 16 ከእኔ ጋር ና፥ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው። በሰረገላውም አስቀመጠው። 17 ወደ ሰማሪያም በመጣ ጊዜ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከአክዓብ በሰማርያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። 18 ኢዩም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ። አክዓብ በኣልን በጥቂቱ አመለከው፤ ኢዩ ግን በብዙ ያመልከዋል። 19 አሁንም የባኣልን ነቢያት ሁሉ፥ አገልጋዮቹንም ሁሉ፥ ካህናቱንም ሁሉ ወደ እኔ ጥሩ፤ ማንም አይቅር፤ ለባኣል ታላቅ መሥዋዕት አቀርባለሁ፥ የቀረውም ሁሉ በሕይወት አይኖርም አላቸው። ኢዩም የበኣልን አገልጋዮች ያጠፋ ዘንድ በተንኰል ይህን አደረገ። 20 ኢዩም። ለበኣል ዋና ጉባኤ ቀድሱ አለ። 21 እነርሱም አወጁ። ኢዩም ወደ እስራኤል ሁሉ ላከ፥ የበኣልም አገልጋዮች ሁሉ መጡ፤ ሳይመጣ የቀረ አንድ ስንኳ አልነበረም። ወደ በኣልም ቤት ገቡ፥ የበኣልም ቤት ከዳር እስከ ዳር ድረስ ሞልቶ ነበር፤ 22 ዕቃ ቤቱንም። ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ ልብስ አውጣ አለው። 23 ልብሱንም አወጣላቸው። ኢዩም የሬካብም ልጅ ኢዮናዳብ ወደ በኣል ቤት ገቡ። የበኣልንም አገልጋዮች። መርምሩ፥ ከበኣል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ አላቸው። 24 የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትም ያቀረቡ ዘንድ ገቡ፤ ኢዩም። በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች አንድ ሰው ያመለጠ እንደ ሆነ ነፍሱ በዚያ ነፍስ ፋንታ ትሆናለች ብሎ በውጪ ሰማንያ ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር። 25 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቅርበው በፈጸሙ ጊዜ ኢዩ ዘበኞቹንና አለቆቹን። ግቡና ግደሉአቸው፤ አንድም አይውጣ አላቸው። በሰይፍም ስለት ገደሉአቸው፤ ዘበኞችና አለቆችም ወደ ውጭ ጣሉአቸው፥ ወደ በኣልም ቤት ከተማ ሄዱ። 26 ከበኣልም ቤት ሐውልቶቹን አወጡ አቃጠሉአቸውም። 27 የበኣልን ሐውልት ቀጠቀጡ፥ የበኣልንም ቤት አፈረሱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ የውዳቂ መጣያ አደረጉት። 28 እንዲሁም ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ። 29 ነገር ግን እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት፥ በቤቴልና በዳን ከነበሩት ከወርቁ እምቦሶች፥ ኢዩ አልራቀም። 30 እግዚአብሔርም ኢዩን። በፊቴ ቅን ነገር አድርገሃልና፥ በልቤም ያለውን ሁሉ በአክዓብ ቤት ላይ አድርገሃልና ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ አለው። 31 ኢዩ ግን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም፤ እስራኤልንም ካሳተው ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። 32 በዚያም ወራት እግዚአብሔር እስራኤልን ይከፋፍላቸው ዘንድ ጀመረ፤ አዛሄልም በእስራኤል ዳርቻ ሁሉ መታቸው። 33 በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን አገር ሁሉ፥ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የጋድንና የሮቤልን የምናሴንም አገር፥ ገለዓድንና ባሳንን መታ። 34 የቀረውም የኢዩ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 35 ኢዩም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት። በፋንታውም ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ። 36 ኢዩም በሰማርያ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበረ።

2 ነገሥት 11

1 የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች። 2 የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ወስዳ ከተገደሉት ከንጉሥ ልጆች መካከል ሰረቀችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፥ እንዳይገደልም ከጎቶልያ ሸሸጉት። 3 በእርስዋም ዘንድ ተሸሸጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች። 4 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ በካራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፥ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው። 5 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤ 6 ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በሱር በር ሁኑ፤ አንዱም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም ጠብቁ፥ ከልክሉም፤ 7 ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ በንጉሥ ዙሪያ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ። 8 ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፥ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁ መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ። 9 መቶ አለቆችም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበቱም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10 ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 11 ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ። 12 የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፥ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብተውም ንጉሥ አደረጉትና። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ እጃቸውን አጨበጨቡ። 13 ጎቶልያም የሠራዊቱንና የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 14 እነሆም፥ ንጉሡ እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የአገሩም ሕዝብ ሁል ደስ ብሎአቸው ቀንደ መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች። 15 ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ። በእግዚአብሔር ቤት አትገደል ብሎአልና። 16 እጃቸውንም በእርስዋ ላይ ጫኑ፥ በፈረሱም መግቢያ መንገድ ወደ ንጉሥ ቤት ወሰዱአት፥ በዚያም ገደሉአት። 17 ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ። 18 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑም ለእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪዎችን ሾመ። 19 መቶ አለቆቹንና ካራውያንንም፥ ዘበኞችንና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፥ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን ተቀመጠ። 20 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት። 21

2 ነገሥት 12

1 ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ። 2 በኢዩ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 3 ካህኑ ዮዳሄም ያስተምረው በነበረ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 4 ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 ኢዮአስም ካህናቱን። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገባውን የተቀደሰውን ገንዘብ ሁሉ፥ ስለ ነፍሱም ዋጋ የሚቀርበውን ገንዘብ፥ በልባቸውም ፈቃድ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚያመጡትን ገንዘብ ሁሉ፥ 6 ካህናቱ እያንዳንዱ ሰው ከሚያመጣው ይውሰዱ በመቅደስም ውስጥ የተናዱትን ይጠግኑበት አላቸው። 7 ነገር ግን እስከ ንጉሡ እስከ ኢዮአስ እስከ ሀያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ካህናቱ አልጠገኑትም ነበር። 8 ኢዮአስም ካህኑን ዮዳሄንና ካህናቱን ጠርቶ። በመቅደሱ ውስጥ የተናዱትን ስፍራዎች ስለ ምን አትጠግኑአቸውም? ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ ለቤቱ መጠገኛ ይሰጥ እንጂ ከሚያመጡት ሰዎች አትቀበሉ አላቸው። 9 ካህናቱም። ከሕዝቡ ገንዘቡን አንወስድም፥ በቤቱም ውስጥ የተናዱትን አንጠግንም ብለው እሺ አሉ። 10 ካህኑ ዮዳሄ ግን ሣጥን ወስዶ መክደኛውን ነደለው፥ በመሠዊያውም አጠገብ ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚገቡበት መግቢያ በስተ ቀኝ አኖረው፤ ደጁንም የሚጠብቁ ካህናት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ ሁሉ ያኖሩበት ነበር። 11 በሣጥንም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን ባዩ ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊና የካህናቱ አለቃ ይመጡ ነበር፥ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ቈጥረው በከረጢት ውስጥ ያኖሩት ነበር። 12 የተመዘነውንም ገንዘብ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት በተሾሙት እጅ ይሰጡ ነበር። 13 የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመጠገን መክፈል ለሚያሻው ሁሉ ድንጋይና እንጨት ይገዙ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ አናጢዎችና ሠራተኞች ግንበኞችና ድንጋይ ወቃሪዎች ይሰጡት ነበር። 14 ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከሚመጣው ገንዘብ ለእግዚአብሔር ቤት የሚሆኑ የብር ጽዋዎችና ጕጠቶች ድስቶችም መለከቶችም የወርቅና የብር ዕቃዎችም አልተሠሩም ነበር። 15 ነገር ግን ለሚሠሩት ይሰጡት ነበር፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ጠገኑበት። 16 ለሠራተኞችም ይከፍሉ ዘንድ ገንዘቡን የሚወስዱትን ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፤ በታማኝነት ይሠሩ ነበርና። 17 ስለ በደልና ሰለ ኃጢአት መሥዋዕት የቀረበውም ገንዘብ ለካህናት ነበረ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አያገቡትም ነበር። 18 በዚያም ወራት የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጥቶ ጌትን ወጋ፥ ያዘውም፤ አዛሄልም ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት ፊቱን አቀና። 19 የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአስ አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥና ኢዮራም አካዝያስም የቀደሱትን ቅዱስ ነገር፥ እርሱም የቀደሰውን፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ወሰደ፥ ወደ ሶርያም ንጉሥ ወደ አዛሄል ላከው። እርሱም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ። 20 የቀረውም የኢዮአስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 21 ባሪያዎቹም ተነሥተው ዐመፁበት፥ ወደ ሲላ በሚወርደውም መንገድ በሚሎ ቤት ገደሉት። [..]፤ ባሪያዎቹም የሰምዓት ልጅ ዮዘካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት መቱት፥ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም አሜስያስ በፋንታው ነገሠ።

2 ነገሥት 13

1 በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፥ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም። 3 የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። 4 ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው። 5 እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፥ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ። 6 ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ። 7 ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከአሥርም ሰረገሎች፥ ከአሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳላ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና። 8 የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 9 ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ። 10 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ። 11 በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም። 12 የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 13 ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ። 14 ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና። አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች አለ። 15 ኤልሳዕም። ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ። 16 የእስራኤልንም ንጉሥ። እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ። 17 የምስራቁን መስኮት ክፈት አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም። ወርውር አለ፤ ወረወረውም። እርሱም። የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያዊያንን በአፌቅ ትመታለህ አለ። 18 ደግሞም። ፍላጻዎቹን ውሰድ አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ። ምድሩን ምታው አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ። 19 የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ። አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ። 20 ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር። 21 ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ። 22 የሶርያም ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤ 23 እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም። 24 የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ። 25 አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፥ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።

2 ነገሥት 14

1 በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም። 4 ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 መንግሥቱም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 6 በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም። ሁሉ በኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች አይሙቱ ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም። 7 እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ አሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላን በሰልፍ ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅትኤል ብሎ ጠራት። 8 በዚያን ጊዜም አሜስያስ። ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ። 9 የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ። የሊባኖስ ኵርንችት፥ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 10 ኤዶምያስን በእውነት መታህ፥ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፥ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻለህ? ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ። 11 አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወጣ፥ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት ሳሚስ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 12 ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13 የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስክ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 14 ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በመያዣም የተያዙትን ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 15 የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ጭከናውም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 16 ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ። 17 የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 18 የቀረውም የአሜስያስ ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 19 በኢየሩሳሌምም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፥ እርሱም ወደ ለኪሶ ኰበለለ፤ በኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፥ በዚያም ገደሉት። 20 በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። 21 የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስዶ በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሠው። 20 ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት። 23 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በአሥራ አምስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ። 24 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ አልራቀም። 25 የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ። 26 የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ። 27 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው። 28 የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ እንደ ተዋጋም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሐማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29 ኢዮርብዓምም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያ በፋንታው ነገሠ።

2 ነገሥት 15

1 በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በሀያ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ልጅ ዓዛርያስ ነገሠ። 2 መንገሥም በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3 አባቱ አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 4 ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 እግዚአብሔርም ንጉሡን ቀሠፈው፥ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጻም ሆነ፥ በተለየ ቤትም ይቀመጥ ነበር፥ የንጉሡም ልጅ ኢዮአታም በንጉሥ ቤት ላይ ሠልጥኖ ለአገሩ ሕዝብ ይፈርድ ነበር። 6 የቀረውም የዓዛርያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 7 ዓዛርያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 8 በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ስድስት ወር ነገሠ። 9 አባቶቹም እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። 10 የኢያቤስም ልጅ ሰሎም ተማማለበት፥ በይብልዓም መትቶ ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 11 የቀረውም የዘካርያ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 12 ለኢዩ። ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነበረ፤ እንዲሁም ሆነ። 13 በይሁዳ ንጉሠ በዖዝያን በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የኢያቤስ ልጅ ሰሎም ነገሠ፤ በሰማርያም አንድ ወር ያህል ነገሠ። 14 የጋዲም ልጅ ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ወደ ሰማርያ መጣ፥ በሰማርያም የኢያቤስን ልጅ ሰሎምን መታ፥ ገደለውም፤ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 15 የቀረውም የሰሎም ነገር፥ የተማማለውም ዓመፅ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 16 በዚያን ጊዜም ምናሔም ከቴርሳ ወጥቶ ቲፍሳን በእርስዋም ያሉትን ሁሉ ዳርቻዋንም መታ፤ ይከፍቱለትም ዘንድ አልወደዱምና መታት፤ በእርስዋም የነበሩትን እርጉዞች ሁሉ ቀደዳቸው። 17 በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ላይ መንገሥ ጀመረ፤ በሰማርያም አሥር ዓመት ነገሠ። 18 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። 19 በዘመኑም የአሦር ንጉሥ ፎሐ በምድሪቱ ላይ ወጣ፤ ምናሔምም መንግሥቱን በእጁ ያጸናለት ዘንድ የፎሐ እጅ ከእርሱ ጋር እንዲሆን አንድ ሺህ መክሊት ብር ሰጠው። 20 ምናሔምም ብሩን ለአሦር ንጉሥ ይሰጥ ዘንድ በእስራኤል ባለ ጠጎች ሁሉ ላይ በእያንዳንዱ ላይ አምሳ ሰቅል ብር አስገብሮ አወጣ። የአሦርም ንጉሥ ተመለሰ፥ በአገሪቱም አልተቀመጠም። 21 የቀረውም የምናሔም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 22 ምናሔም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ፋቂስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 23 በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፋቂስያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ። 24 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። 25 የሠራዊቱም አለቃ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ተማማለበት፥ በሰማርያም በንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ከአርጎብና ከአርያ ጋር መታው፤ ከእርሱም ጋር አምሳ የገለዓድ ሰዎች ነበሩ፤ ገደለውም፥ ፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 26 የቀረውም የፋቂስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 27 በይሁዳ ንጉሥ በዓዛርያስ በአምሳ ሁለተኛው ዓመት የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ሀያ ዓመትም ነገሠ። 28 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። 29 በእስራኤልም ንጉሥ በፋቁሔ ዘመን የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ ዒዮንና አቤልቤትመዓካን፥ ያኖዋንም፥ ቃዴስንና አሶርንም፥ ገለዓድንና ገሊላንም፥ የንፍታሌምን አገር ሁሉ ወሰደ፤ ወደ አሦርም አፈለሳቸው። 30 በዖዝያንም ልጅ በኢዮአታም በሀያኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ ላይ ተማማለ፥ መትቶም ገደለው፥ በእርሱም ፋንታ ነገሠ። 31 የቀረውም የፋቁሔ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 32 በእስራኤል ንጉሥ በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የዖዝያን ልጅ ኢዮአታም ነገሠ። 33 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱ የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ነበረች። 34 በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ አባቱ ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 35 ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። እርሱም የላይኛውን የእግዚአብሔርን ቤት በር ሠራ። 36 የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 37 በዚያም ወራት እግዚአብሔር የሶርያን ንጉሥ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ፋቁሔን በይሁዳ ላይ መስደድ ጀመረ። 38 ኢዮአታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ነገሥት 16

1 በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 3 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት ልጁን በእሳት አሳለፈው። 4 በመስገጃዎችና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 የዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ሊዋጉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አካዝንም ከበቡት፥ ሊያሸንፉት ግን አልቻሉም። 6 በዚያም ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን ኤላትን ወደ ሶርያ መለሰ፥ አይሁድንም ከኤላት አሳደደ፤ ኤዶማውያንም ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ ድረስ በእርስዋ ተቀምጠዋል። 7 አካዝም። እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብን ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ላከ። 8 አካዝም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደደው። 9 የአሦርም ንጉሥ ሰማው፤ የአሦርም ንጉሥ በደማስቆ ላይ ወጣባት ወሰዳትም፥ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፥ ረአሶንንም ገደለ። 10 ንጉሡም አካዝ የአሦርን ንጉሠ ቴልጌልቴልፌልሶርን ሊገናኘው ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በደማስቆ የነበረውን መሠዊያ አየ፤ ንጉሡም አካዝ የመሠዊያውን ምሳሌና የአሠራሩን መልክ ወደ ካህኑ ወደ ኦርያ ላከው። 11 ካህኑም ኦርያ መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ ልኮ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው። 12 ንጉሡም ከደማስቆ በመጣ ጊዜ መሠዊያውን አየ፤ ንጉሡም ወደ መሠዊያው ቀርቦ በእርሱ ላይ ወጣ። 13 በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን አሳረገ፥ የመጠጡንም ቍርባን አፈሰሰ፥ የደኅንነቱንም መሥዋዕት ደም ረጨ። 14 በእግዚአብሔርም ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከመቅደሱ ፊት ከመሠዊያውና ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ በመሠውያው አጠገብ በሰሜን በኩል አኖረው። 15 ንጉሡም አካዝ። የሚቃጠለውን የጥዋት መሥዋዕት፥ የማታውንም የእህሉን ቍርባን፥ የንጉሡንም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ ለአገሩም ሕዝብ የሚሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን የመጠጡንም ቍርባን በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ደም ሁሉ የሌላ መሥዋዕቱንም ደም ሁሉ ርጭበት፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ እጠይቅበት ዘንድ ይሁን ብሎ ካህኑን ኦርያን አዘዘው። 16 ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። 17 ንጉሡም አካዝ የመቀመጫዎችን ክፈፍ ቈረጠ፥ ከእነርሱም የመታጠቢያውን ሰኖች ወሰደ፤ ኵሬውንም ከበታቹ ከነበሩት ከናሱ በሬዎች አወረደው፥ በጠፍጣፋውም ድንጋይ ላይ አኖረው። 18 በእግዚአብሔርም ቤት የዙፋኑን መሠረት ሠራ፤ ስለ አሦርም ንጉሥ በውጭ ያለውን የንጉሡን መንገድ ወደ እግዚአብሔር ቤት አዞረው። 19 የቀረውም አካዝ ያደረገው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 20 አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ነገሥት 17

1 በይሁዳ ንጉሥ በአካዝ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ንጉሥ ሆነ፤ ዘጠኝ ዓመትም ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አይደለም። 3 የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ወጣ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፥ ግብርም አመጣለት። 4 የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዓመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ይዞ በወህኒ ቤት አሰረው። 5 የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፥ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት። 6 በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ወሰደ፥ እስራኤልንም ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው። 7 የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፥ 8 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ባሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዓት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዓት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ። 9 የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ንገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎቹ ላይ መስገጃዎችን ሠሩ። 10 በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ ታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐፀዶችን ተከሉ፤ 11 እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ ክፉ ነገር አደረጉ፤ 12 እግዚአብሔርም የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ። 13 እግዚአብሔርም። ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ። 14 ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ እንደ አባቶቻቸው አንገት አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም። 15 ሥርዓቱንም ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፥ ምናምንቴዎችም ሆኑ፥ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ። 16 የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፥ በኣልንም አመለኩ። 17 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አሳለፉአቸው፥ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፥ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ። 18 ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፥ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም። 19 ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዓት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም። 20 እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፥ አስጨነቃቸውም፥ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 21 እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፥ ታላቅም ኃጢአት አሠራቸው። 22 የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኃጢአት ሁሉ ሄዱ፤ 23 እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ። 24 የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፥ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። 25 በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፥ ይገድሉአቸውም ነበር። 26 ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ። ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፥ እነሆም፥ ገደሉአቸው ብለው ተናገሩት። 27 የአሦርም ንጉሥ። ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፥ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው ብሎ አዘዘ። 28 ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር። 29 በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፥ ሰምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። 30 የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤ 31 የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። 32 እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፥ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፥ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። 33 እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። 34 እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፥ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም። 35 እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ሌሎችን አማልክት አትፍሩ፥ አትስገዱላቸው፥ አታምልኩአቸው፥ አትሠዉላቸው፤ 36 ነገር ግን በታላቅ ኃይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔር እርሱን ፍሩ፥ ለእርሱም ስገዱ፥ ለእርሱም ሠዉ፤ 37 የጻፈላችሁንም ሥርዓትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 38 ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 39 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። 40 ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም። 41 እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።

2 ነገሥት 18

1 እንዲህም ሆነ፤ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ ነገሠ። 2 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ነበረች። 3 እርሱም አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 4 በኮረብታም ያሉትን መስገጃዎች አስወገደ፥ ሐውልቶችንም ቀለጣጠመ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት ነበርና ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ፤ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው። 5 በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱም በኋላ ከእርሱም በፊት ከነበሩት ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ እርሱን የሚመስል አልነበረም። 6 ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፥ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዛቱን ጠበቀ። 7 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤ በአሦርም ንጉሥ ላይ ዐመፀ፥ አልገበረለትም። 8 ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጋዛና እስከ ዳርቻዋ ድረስ፥ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ምሽጉ ከተማ ድረስ መታ። 9 በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፥ ከበባትም። 10 ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠኝኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች። 11 የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፥ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤ 12 የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና። 13 በንጉሡም በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፥ ወሰዳቸውም። 14 የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ። በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። 15 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። 16 በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው። 17 የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ በመጡም ጊዜ በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። 18 ንጉሡንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ። 19 ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? 20 የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኃይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 21 እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። 22 እናንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ሰገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያውቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? 23 አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 24 ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱ አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? 25 አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚች አገር ወጥተህ አጥፋት አለኝ። 26 የኬልቅያስም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት። 27 ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው። 28 ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኽ። የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል። 29 ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ 30 ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፥ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። 31 ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ 32 ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ ቢያታልላችሁ አትስሙት። 33 በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 34 የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? 35 ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከአገሮቹ አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው? 36 ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 37 የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

2 ነገሥት 19

1 ንጉሡም ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2 የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3 እነርሱም። ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል። ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል፥ ለመውለድም ኃይል የለም። 4 ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል ሁሉ አምላካህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት። 5 እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ። 6 ኢሳይያስም። ለጌታችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7 እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ በሉት አላቸው። 8 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። 9 እርሱም። የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ በሰማ ጊዜ ደግሞ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ እንዲህ ሲል። 10 ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11 እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፋአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12 አባቶቼ ያጠፉአቸውን፥ ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች፥ የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13 የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ? 14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15 ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ። በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን የምድር ነገሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። 16 አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬምን ቃል ስማ። 17 አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት አሕዛብንና ምድራቸውን አፍርሰዋል፥ 18 አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና፤ ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 19 እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ እንድታድነን እለምንሃለሁ። 20 የአሞጽም ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላካ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ የለመንኽውን ሰምቻለሁ። 21 እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው። ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ በላይህ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። 22 የተገዳደርኸው፥ የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው ዓይንህንም ወደ ላይ ያነሣኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። 23 አንተስ። በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ አገሩም ዳርቻና ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። 24 ቈፈርሁም፥ እንግዳውንም ውኃ ጠጣሁ፤ የተገደበውንም ውኃ ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ ብለህ በመልእክተኞችህ እጅ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደርህ። 25 እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። 26 ስለዚህም የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለምለምም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታውም እህል ሆነዋል። 27 እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህንም መግቢያህንም፥ በእኔም ላይ የተቈጠኸውን ቍጣ አውቄአለሁ። 28 ቍጣህና ትዕቢትህ ወደ ጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ፥ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፥ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። 29 ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ታጭዱማላችሁ፥ ወይንንም ትተክላላችሁ፥ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 30 ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። 31 ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 32 ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። 33 በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፥ ወደዚህችም ከተማ አይመጣም፥ ይላል እግዚአብሔር። 34 ስለ እኔም፥ ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ። 35 በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 36 የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 37 በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አደራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ነገሥት 20

1 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው። 2 ፊቱንም ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 3 አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። 4 ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ከተማ አደባባይ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት። 5 ተመልሰህ የሕዝቤን አለቃ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ እፈውስሃለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወጣለህ። 6 በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ፤ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ። 7 ኢሳይስም፥ የበለስ ጥፍጥፍ አምጡልኝ አለ፤ አምጥተውም በእባጩ ላይ አደርጉለት፥ እርሱም ተፈወሰ። 8 ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ እግዚአብሔር እንዲፈውሰኝ፥ እኔስ በሦስተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድወጣ ምልክቱ ምንድር ነው? አለው። 9 ኢሳይያስም፥ እግዚአብሔር የተናገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል፤ ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ፊት ይሄድ ዘንድ ወይም አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ ዘንድ ትወድዳለህን? አለ። 10 ሕዝቅያስም፥ ጥላው አሥር ደረጃ ቢጨምር ቀላል ነገር ነው፤ እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ጥላው አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ይመለስ አለው። 11 ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ጥላውንም በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት ላይ በወረደበት መንገድ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ መለሰው። 12 በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ እንደ ታመመ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ወደ ሕዝቅያስ ላከ። 13 ሕዝቅያስም ደስ አለው፥ ግምጃ ቤቱንም ሁሉ፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። 14 ነቢዩም ኢሳያሳ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ። እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ? አለው። ሕዝቅያስም። ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡ አለው። 15 እርሱም። በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም። በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው። 16 ኢሳይያስም ሕዝቅያስን። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 17 እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ አለው። 19 ሕዝቅያስም ኢሳይያስን። የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም። በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን? አለ። 20 የቀረውም የሕዝቅያስ ነገር፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ኵሬውንና መስኖውንም እንደ ሠራ፥ ውኃውንም ወደ ከተማይቱ እንዳመጣ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 21 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ነገሥት 21

1 ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱ ስም ሐፍሴባ ነበረ። 2 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3 አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ለበኣል መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ አመለካቸውም። 4 እግዚአብሔርም። ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ። 5 በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6 ልጁንም በእሳት አሳለፈ፥ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። 7 እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ 8 ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ። 9 ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው። 10 እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት እጅ እንዲህ ሲል ተናገረ። 11 የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ርኵሰት አድርጎአልና፥ ከፊቱም የነበሩ አሞራውያን ከሠሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሥራ ሠርቶአልና፥ ይሁዳንም ደግሞ በጣዖታቱ አስቶአልና 12 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገርን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። 13 የሰማርያንም ገመድ የአክዓብንም ቤት ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ ሰውም ወጭቱን እንዲወለውል ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። 14 የርስቴንም ቅሬታ እጥላለሁ፥ በጠላቶቻቸውም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ምርኮና ብዝበዛ ይሆናሉ፤ 15 አባቶቻቸው ከግብጽ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ሠርተዋልና፥ አስቈጥተውኝማልና። 16 ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኃጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ። 17 የምናሴም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ያደረገውም ኃጢአት፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 18 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም አጠገብ ባለው በዖዛ አትክልት ተቀበረ፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 19 አሞጽም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሜሶላም ነበረች። 20 አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ። 21 አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ ሰገደላቸውም። 22 የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም። 23 የአሞጽም ባሪያዎች አሴሩበት ንጉሡንም በቤቱ ውስጥ ገደሉት፥ 24 የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ ያሴሩበትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። 25 የአሞጽም የቀረው ነገርና የሠራው ሥራ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 26 በዖዛም አትክልት ባለው በመቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ነገሥት 22

1 ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ከባሱሮት የሆነ የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ቀኝም ግራም አላለም። 3 በንጉሡም በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር ንጉሡ ጸሐፊውን የሜሶላምን ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ላከው፥ እንዲህም አለው። 4 የመቅደሱ በረኞች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ወደ እግዚአብሔር ቤት የገባውን ገንዘብ ይደምር ዘንድ ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሂድ። 5 በእግዚአብሔርም ቤት ላሉት ሠራተኞች አለቆች ይስጡት፤ እነርሱም የተናደውን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚጠግኑት ሠራተኞች፥ 6 ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች፥ ለድንጋይም ወቃሪዎች፥ መቅደሱንም ለመጠገን እንጨትንና የተወቀረውን ድንጋይ ለሚገዙ ይክፈሉት። 7 ነገር ግን እነርሱ የታመኑ ነበሩና በእጃቸው ስለ ተሰጠ አይቈጣጠሩአቸውም ነበር። 8 ካህኑም ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን፥ የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቻለሁ አለው፤ ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፥ እርሱም አነበበው። 9 ጸሐፊውም ሳፋን ወደ ንጉሡ መጣ፥ ለንጉሡም። በመቅደሱ የተገኘውን ገንዘብ ባሪያዎችህ አፈሰሱት፥ በእግዚአብሔርም ቤት ሠራተኞች ላይ ለተሾሙት አለቆች ሰጡት ብሎ አወራለት። 10 ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 11 ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 12 ንጉሡም ካህኑን ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓክቦርን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን። 13 አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው። 14 እንዲሁም ካህኑ ኬልቅያስና አኪቃም ዓክቦርም ሳፋንና ዓሳያም ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢያቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ተነጋገሩ። 15 እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የይሁዳ ንጉሥ እንዳነበበው እንደ መጽሐፉ ቃል ሁሉ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ። 17 በእጃቸው ሥራ ሁሉ ያስቈጡኝ ዘንድ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። 18 እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል፥ ልብህ ገር ሆኖአልና፥ 19 እነርሱም ለድንቅና ለመርገም እንዲሆኑ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የተናገርሁትን ሰምተህ በእግዚአብሔር ፊት ተዋርደሃልና፥ ልብስህን ቀድደሃልና፥ በፊቴም አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር። 20 ስለዚህም ደግሞ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራ ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሡ አወሩለት።

2 ነገሥት 23

1 ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰባቸው። 2 ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 3 ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ። 4 ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናትን በረኞቹንም ለባኣልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠላቸው፥ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው። 5 የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መገጃዎች በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበኣልና ለፀሐይ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትንም አስወገደ። 6 የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጣለው። 7 ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ። 8 ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማይቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማይቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ። 9 የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር። 10 ማንም ሰው ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዳያሳልፍ በሄኖም ልጆች ሸለቆ የነበረውን ቶፌትን ርኩስ አደረገው። 11 የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በጃንደረባው በናታንሜሌክ መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡትን ፈረሶች አስወገደ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ። 12 የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፥ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ። 13 በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵሰት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵሰት ለአስታሮት ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሚልኮም ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ። 14 ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፥ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት። 15 ደግሞም በቤቴል የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህን መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው። 16 ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በተራራው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ በመሠዊያ አጠገብ ሲቆም እነዚህን ነገሮች የተነባ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ አቃጠላቸው አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዓይኖቹን አቅንቶ። 17 ያ የማየው የመታሰቢያ ምልክት ምንድር ነው? አለ። የዚያችም ከተማ ሰዎች። ከይሁዳ ወጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው ብለው ነገሩት። 18 እርሱም። ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው አለ፤ እነርሱም ከሰማርያ ከወጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር አጥንቱን ተዉ። 19 በሰማሪያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፥ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው። 20 በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። 21 ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ። በዚህ በቃል ኪዳን መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርጉ ብሎ አዘዛቸው። 22 እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተፈሰከም። 23 ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ። 24 ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ። 25 እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔርም የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም። 26 ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም። 27 እግዚአብሔርም። እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋላሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና። ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ አለ። 28 የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29 በእርሱም ዘመን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው። 30 ከሞተም በኋላ ባሪያዎቹ በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፥ በመቃብሩም ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፥ ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት። 31 ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32 አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 33 በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ባለችው በሪብላ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት። 34 ፈርዖን ኒካዑም የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ኢዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብጽ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ። 35 ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ይሰጥ ዘንድ ከአገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ። 36 ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች። 37 አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

2 ነገሥት 24

1 በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነዖር ወጣ፥ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት። 2 እግዚአብሔርም የከለዳውያንንና የሶርያውያንን የሞዓባውያንንም የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው። 3 ምናሴ ስላደረገው ኃጢአት ሁሉ ስላፈሰሰውም ንጹሕ ደም፥ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለሞላ ከፊቱ ያስወግዳቸው ዘንድ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ በይሁዳ ላይ ሆነ፤ 4 እግዚአብሔርም ይራራ ዘንድ አልወደደም። 5 የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 6 ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዮአኪን፤ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 7 የባቢሎንም ንጉሥ ለግብጽ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብጽ ንጉሥ ከዚያ ወዲያ ከአገሩ አልወጣም። 8 ዮአኪን መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኔስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9 አባቱም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 10 በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነዖር ባሪያዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፥ ከተማይቱም ተከበበች። 11 ባሪያዎቹም በከበቡአት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናብከደነዖር ወደ ከተማይቱ ወጣ። 12 የይሁዳም ንጉሥ ዮአኮንና እናቱ፥ ባርያዎቹም፥ አለቆቹም፥ ጃንደረቦቹም ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጡ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው። 13 የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትን ሁሉ የንጉሡም ቤት መዛግብትን ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ። 14 ኢየሩሳሌምንም ሁሉ፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹን ሁሉ አሥር ሺህ ምርኮኞች አፈለሰ፤ ከድሆች ከአገሩ ሕዝብ በቀር ማንም አልቀረም። 15 ዮአኮንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የአገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ። 16 የባቢሎንም ንጉሥ ብርቱዎቹንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኃያላኑን ሁሉ ሰባት ሺህ ያህል፥ ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም አንድ ሺህ፥ ወደ ባቢሎን ማረከ። 17 የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው። 18 ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19 ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 20 ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።

2 ነገሥት 25

1 ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት። 2 ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። 3 በአራተኛውም ወር በዘጠኝኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበርና ለአገሩ ሰዎች እንጀራ ታጣ። 4 ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ። 5 የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉ፥ በኢያሪኮም ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር። 6 ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት። 7 የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጡ፥ በሰንሰለትም አሰሩት፥ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት። 8 በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9 የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። 10 ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ። 11 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ። 12 የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። 13 ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 14 ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። 15 የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ። 16 ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም። 17 የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት። 18 የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ። 19 ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ። 20 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 21 የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ። 22 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን አለቃ አደረገው። 23 የጭፍሮቹም አለቆች ሁሉ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። 24 ጎዶልያስም። ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፥ በአገሩ ተቀመጡ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው። 25 በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር አሥር ሰዎች መጥተው ጎዶልያስንና ከእርሱ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንን እስኪሞቱ ድረስ መቱአቸው። 26 ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጭፍሮቹም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብጽ መጡ። 27 እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማከረ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን ከወህኒ አወጣው፤ 28 በፍቅርም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 29 በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 30 ንጉሡም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።

1 ዜና መዋዕል 1

1 2 አዳም፥ ሴት፥ ሄኖስ፥ ቃይናን፥ መላልኤል፥ 3 ያሬድ፥ ሄኖክ፥ ማቱሳላ፥ ላሜሕ፥ 4 ኖኅ፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት። 5 የያፌት ልጆች፤ ጋሜር፥ ማጎግ፥ ማዴ፥ 6 ያዋን፥ ቶቤል፥ ሞሳሕ፥ ቴራስ። 7 የጋሜርም ልጆች፤ አስከናዝ፥ ሪፋት፥ ቴርጋማ። የያዋንም ልጆች፤ ኤሊሳ፥ ተርሴስ፥ ኪቲም፥ ሮድኢ። 8 የካምም ልጆች፤ ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ፥ ከነዓን። 9 የኩሽም ልጆች፤ ሳባ፥ ኤውላጥ፥ ሰብታ፥ ራዕማ፥ ሰብቃታ። የራዕማም ልጆች፤ ሳባ፥ ድዳን። 10 ኩሽም ናምሩድን ወለደ፤ እርሱም በምድር ኃያል መሆንን ጀመረ። 11 ምጽራይምም ሉዲምን፥ ዐናሚምን፥ ላህቢምን፥ 12 ነፍተሂምን፥ ፈትሩሲምን፥ ፍልስጥኤማውያን የወጡበትን ከስሉሂምን፥ ከፍቶሪምን ወለደ። 13 ከነዓንም የበኵር ልጁን ሲዶንን፥ 14 ኬጢን፥ ኢያቡሳዊውን፥ አሞራዊውን፥ 15 ጌርጌሳዊውን፥ ኤዊያዊውን፥ ዐርካዊውን፥ 16 ሲኒያዊውን፥ አራዴዎንን፥ ሰማሪዎንን፥ አማቲን ወለደ። 17 የሴምም ልጆች፤ ኤላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ፥ አራም፥ ዑፅ፥ ሁል፥ ጌቴር፥ ሞሳሕ። 18 አርፋክስድም ቃይንምን ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን ወለደ፤ ሳላም ዔቦርን ወለደ። 19 ለዔቦርም ሁለት ልጆች ተወለዱለት፤ በዘመኑ ምድር ተከፍላለችና የአንደኛው ስም ፋሌቅ ተባለ፤ የወንድሙም ስም ዮቅጣን ነበረ። 20 ዮቅጣንም አልሞዳድን፥ 21 ሣሌፍን፥ ሐስረሞትን፥ ያራሕን፥ ሀዶራምን፥ 22 አውዛልን፥ ደቅላን፥ ዖባልን፥ አቢማኤልን፥ 23 ሳባን፥ ኦፊርን፥ ኤውላጥን፥ ዮባብን ወለደ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ነበሩ። 24 25 ሴም፥ አርፋክስድ፥ ሳላ፥ ዔቦር፥ ፋሌቅ፥ 26 27 ራግው፥ ሴሮሕ፥ ናኮር፥ ታራ፥ አብርሃም የተባለ አብራም። 28 የአብርሃምም ልጆች፤ ይስሐቅ፥ እስማኤል። 29 ትውልዳቸውም እንደዚህ ነው። የእስማኤል በኵር ልጅ ነባዮት፤ ከዚህ በኋላ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ 30 ማስማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ 31 ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ፤ እነዚህ የእስማኤል ልጆች ናቸው። 32 የአብርሃምም ገረድ የኬጡራ ልጆች፤ ዘምራን፥ ዮቅሳን፥ ሜዳን፥ ምድያም፥ የስቦቅ፥ ስዌሕ። የዮቅሳንም ልጆች፤ ሳባ፥ ድዳን። 33 የምድያምም ልጆች፤ ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ነበሩ። 34 አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ። የይስሐቅም ልጆች ዔሳውና እስራኤል ነበሩ። 35 የዔሳው ልጆች፤ ኤልፋዝ፥ ራጉኤል፥ የዑስ፥ የዕላም፥ ቆሬ። 36 የኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጎቶም፥ ቄኔዝ፥ ቲምናዕ፥ አማሌቅ። 37 የራጉኤል ልጆች፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሣማ፥ ሚዛህ። 38 የሴይርም ልጆች፤ ሎጣን፥ ሦባል፥ ጽብዖን፥ ዓና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን። 39 የሎጣንም ልጆች፤ ሖሪ፥ ሔማም፤ ቲሞናዕ የሎጣን እኅት ነበረች። 40 የሦባል ልጆች፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ አውናም። የጽብዖንም ልጆች፤ አያ፥ ዓና። 41 የዓና ልጅ፤ ዲሶን። የዲሶንም ልጆች፤ ሔምዳን፥ ኤስባን፥ ይትራን፥ ክራን። 42 የኤጽር ልጆች፤ ቢልሐን፥ ዛዕዋን፥ ዓቃን። የዲሳን ልጆች፤ ዑፅ፥ አራን። 43 በእስራኤልም ልጆች ላይ ገና ንጉሥ ሳይነግሥ በኤዶምያስ ምድር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። የቢዖር ልጅ ባላቅ፤ የከተማይቱም ስም ዲንሃባ ነበረ። 44 ባላቅም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የባሶራ ሰው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ። 45 ኢዮባብም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የቴማን አገር ሰው ሑሳም ነገሠ። 46 ሑሳምም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ በሞዓብ ሜዳ ምድያምን የመታው የባዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማይቱም ስም ዓዊት ነበረ። 47 ሃዳድም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የመሥሬቃ ሰው ሠምላ ነገሠ። 48 ሠምላም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ በወንዙ አጠገብ ያለችው የረሆቦት ሰው ሳኡል ነገሠ። 49 ሳኡልም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ነገሠ። 50 በኣልሐናንም ሞተ፥ በእርሱም ፋንታ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማይቱም ስም ፋዑ ነበረ፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ የመጥሬድ ልጅ መሄጣብኤል ነበረች፤ ሃዳድም ሞተ። 51 የኤዶምያስም አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥ 52 አህሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥ 53 ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብሳር አለቃ፥ 54 መግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፤ እነዚህ የኤዶምያስ አለቆች ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 2

1 የእስራኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥ 2 ዳን፥ ዮሴፍ፥ ብንያም፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር። 3 የይሁዳ ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፤ እነዚህ ሦስቱ ከከነዓናዊቱ ከሴዋ ልጅ ተወለዱለት። የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ ገደለውም። 4 ምራቱም ትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደችለት፤ የይሁዳም ልጆች ሁሉ አምስት ነበሩ። 5 የፋሬስ ልጆች፤ ኤስሮም፥ ሐሙል። 6 የዛራም ልጆች፤ ዘምሪ፥ ኤታን፥ ሄማን፥ 7 ከልኮል፥ ዳራ፤ ሁሉም አምስት ነበሩ። የከርሚም ልጅ እስራኤልን ያስጨነቀ፥ እርሙንም ሰርቆ የበደለ አካን ነበረ። 8 የኤታንም ልጅ አዛርያ ነበረ። 9 ለኤስሮም የተወለዱለት ልጆች፤ ይረሕምኤል፥ አራም፥ ካልብ ነበሩ። 10 አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም የይሁዳን ልጆች አለቃ ነአሶንን ወለደ፤ 11 ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፤ 12 ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤ 13 እሴይም የበኵር ልጁን ኤልያብን፥ ሁለተኛውንም አሚናዳብን፥ ሦስተኛውንም ሣማን፥ 14 አራተኛውንም ናትናኤልን፥ 15 አምስተኛውንም ራዳይን፥ ስድስተኛውንም አሳምን፥ ሰባተኛውንም ዳዊትን ወለደ፤ 16 እኅቶቻቸውም ጽሩያና አቢግያ ነበሩ። የጽሩያም ልጆች አቢሳ፥ ኢዮአብ፥ አሣሄል ሦስቱ ነበሩ። 17 አቢግያም አሜሳይን ወለደች፤ የአሜሳይም አባት እስማኤላዊው ዬቴር ነበረ። 18 የኤስሮምም ልጅ ካሌብ ከሚስቱ ከዓዙባ ከይሪዖትም ልጆች ወለደ፤ ልጆቹዋም ያሳር፥ ሶባብ፥ አርዶን ነበሩ። 19 ዓዙባም ሞተች፥ ካሌብም ኤፍራታን አገባ፤ እርስዋም ሆርን ወለደችለት። 20 ሆርም ኡሪን ወለደ፥ ኡሪም ባስልኤልን ወለደ። 21 ከዚያም በኋላ ኤስሮም ስድሳ ዓመት በሆነው ጊዜ ወዳገባት ወደ ገለዓድ አባት ወደ ማኪር ልጅ ገባ፤ ሠጉብንም ወለደችለት። ሠጉብም ኢያዕርን ወለደ፤ 22 ለእርሱም በገለዓድ ምድር ሀያ ሦስት ከተሞች ነበሩት። 23 ጌሹርና አራምም የኢያዕርን ከተሞች ከቄናትና ከመንደሮችዋ ጋር ስድሳውን ከተሞች ወሰዱባቸው። እነዚህ ሁሉ የገለዓድ አባት የማኪር ልጆች ነበሩ። 24 ኤስሮምም በካሌብ ኤፍራታ ከሞተ በኋላ የኤስሮም ሚስት አቢያ የቴቁሔን አባት አሽሑርን ወለደችለት። 25 የኤስሮምም የበኵር ልጁ የይረሕምኤል ልጆች በኵሩ ራም፥ ቡናህ፥ ኦሬን፥ ኦጼም፥ አኪያ ነበሩ። 26 ለይረሕምኤልም ዓጣራ የተባለች ሌላ ሚስት ነበረችው፤ እርስዋም የኦናም እናት ነበረች። 27 የይረሕምኤል የበኵሩ የራም ልጆች መዓስ፥ ያሚን፥ ዔቄር ነበሩ። 28 የኦናምም ልጆች ሸማይና ያዳ ነበሩ። የሸማይ ልጆች ናዳብና አቢሱር ነበሩ። 29 የአቢሱርም ሚስት አቢካኢል ነበረች፤ አሕባንንና ሞሊድን ወለደችለት። 30 የናዳብም ልጆች ሴሊድና አፋይም ነበሩ፤ ሴሌድም ያለ ልጆች ሞተ። 31 የአፋይምም ልጅ ይሽዒ፥ የይሽዒም ልጅ ሶሳን፥ የሶሳንም ልጅ አሕላይ ነበረ። 32 የሸማይም ወንድም የያዳ ልጆች ዬቴርና ዮናታን ነበሩ፤ ዬቴርም ያለ ልጆች ሞተ። 33 የዮናታንም ልጆች ፌሌትና ዛዛ ነበሩ፤ እነዚህ የይረሕምኤል ልጆች ነበሩ። 34 ለሶሳንም ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ ለሶሳንም ኢዮሄል የተባለ ግብጻዊ አገልጋይ ነበረው። 35 ሶሳንም ለአገልጋዩ ለኢዮሄል ልጁን አጋባት፥ እርስዋም ዓታይን ወለደችለት። 36 ዓታይም ናታንን ወለደ፤ ናታንም ዛባድን ወለደ፤ 37 ዛባድም ኤፍላልን ወለደ፤ ኤፍላልም ዖቤድን ወለደ፤ ዖቤድም ኢዩን ወለደ፤ 38 ኢዩም ዓዛርያስን ወለደ፤ 39 ዓዛርያስም ኬሌስን ወለደ፤ ኬሌስም ኤልዓሣን ወለደ፤ 40 ኤልዓሣም ሲስማይን ወለደ፤ 41 ሲስማይም ሰሎምን ወለደ፤ ሰሎምም የቃምያን ወለደ፤ የቃምያም ኤሊሳማን ወለደ። 42 የይረሕምኤልም ወንድም የካሌብ ልጆች በኵሩ የዚፍ አባት ሞሳ፥ የኬብሮንም አባት የመሪሳ ልጆች ነበሩ። 43 የኬብሮንም ልጆች ቆሬ፥ ተፉዋ፥ ሬቄም፥ ሽማዕ ነበሩ። 44 ሽማዕም የዮርቅዓምን አባት ረሐምን ወለደ፤ ሬቄምም ሸማይን ወለደ። 45 የሸማይም ልጅ ማዖን ነበረ፤ ማዖንም የቤት ጹር አባት ነበረ። 46 የካሌብም ቁባት ዔፋ ሐራንን፥ ሞዳን፥ ጋዜዝን ወለደች። 47 ሐራንም ጋዜዝን ወለደ። የያህዳይም ልጆች ሬጌም፥ ኢዮታም፥ ጌሻን፥ ፋሌጥ፥ ሔፋ፥ ሸዓፍ ነበሩ። 48 የካሌብም ቁባት ማዕካ ሸቤርንና ቲርሐናን ወለደች። 49 ደግሞም የመድማናን አባት ሸዓፍንና የመክቢናንና የጊብዓን አባት ሱሳን ወለደች፤ የካሌብም ሴት ልጅ ዓክሳ ነበረች። 50 የካሌብ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የኤፍራታ የበኵሩ የሆር ልጅ የቂርያትይዓሪም አባት ሦባል፥ 51 የቤተ ልሔም አባት ሰልሞን፥ የቤት ጋዴር አባት ሐሬፍ። 52 ለቂርያትይዓሪምም አባት ለሦባል ልጆች ነበሩት፤ ሀሮኤ የመናሕታውያን እኵሌታ። 53 የቂርያትይዓሪምም ወገኖች፤ ይትራውያን፥ ፉታውያን፥ ሹማታውያን፥ ሚሽራውያን፤ ከእነዚህም ጾርዓውያንና ኤሽታኦላውያን ወጡ። 54 የሰልሞንም ልጆች ቤተ ልሔም፥ ነጦፋውያን፥ ዓጣሮትቤትዮአብ፥ የመናሕታውያን እኵሌታ፥ ጾርዓውያን ነበሩ። 55 በያቤጽም የተቀመጡ የጸሐፊዎች ወገኖች፤ ቲርዓውያን፥ ሺምዓታውያን፥ ሡካታውያን ነበሩ፤ እነዚህ ከሬካብ ቤት አባት ከሐማት የወጡ ቄናውያን ናቸው።

1 ዜና መዋዕል 3

1 በኬብሮንም ለዳዊት የተወለዱለት ልጆች እነዚህ ናቸው። በኵሩ አምኖን ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም፥ ሁለተኛውም ዳንኤል ከቀርሜሎሳዊቱ ከአቢግያ፥ 2 ሦስተኛው አቤሴሎም ከጌሹር ንጉሥ ከተልማይ ልጅ ከመዓካ፥ አራተኛው አዶንያስ ከአጊት፥ 3 አምስተኛው ሰፋጥያስ ከአቢጣል፥ ስድስተኛው ይትረኃም ከሚስቱ ከዔግላ። 4 ስድስቱ በኬብሮን ተወለዱለት፤ በዚያም ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። 5 እነዚህ ደግሞ በኢየሩሳሌም ተወለዱለት፤ ከዓሚኤል ልጅ ከቤርሳቤህ፥ ሳሙስ፥ ሶባብ፥ ናታን፥ 6 ሰሎሞን፥ አራት፤ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ 7 ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ 8 ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት፥ ዘጠኝ። 9 እነዚህ ሁሉ ከቁባቶች ልጆች በቀር የዳዊት ልጆች ነበሩ፤ ትዕማርም እኅታቸው ነበረች። 10 የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም ነበረ፤ ልጁ አቢያ፥ 11 ልጁ አሳ፥ ልጁ ኢዮሣፍጥ፥ ልጁ ኢዮራም፥ ልጁ አካዝያስ፥ ልጁ ኢዮአስ፥ 12 ልጁ አሜስያስ፥ ልጁ ዓዛርያስ፥ ልጁ ኢዮአታም፥ 13 ልጁ አካዝ፥ ልጁ ሕዝቅያስ፥ ልጁ ምናሴ፥ 14 ልጁ አሞጽ፥ ልጁ ኢዮስያስ። 15 የኢዮስያስም ልጆች፤ በኵሩ ዮሐናን፥ ሁለተኛውም ኢዮአቄም፥ ሦስተኛውም ሴዴቅያስ፥ አራተኛውም ሰሎም። 16 የኢዮአቄምም ልጆች፤ ልጁ ኢኮንያን፥ ልጁ ሴዴቅያስ። 17 የምርኮኛውም የኢኮንያን ልጆች ሰላትያል፥ መልኪራም፥ 18 ፈዳያ፥ ሼናጻር፥ ይቃምያ፥ ሆሻማ፥ ነዳብያ ነበሩ። 19 የፈዳያ ልጆች ዘሩባቤልና ሰሜኢ ነበሩ፤ የዘሩባቤልም ልጆች፤ ሜሱላም፥ ሐናንያ፥ እኅታቸውም ሰሎሚት። 20 ሐሹባ፥ ኦሄል፥ በራክያ፥ ሐሳድያ፥ ዮሻብሒሴድ አምስት ናቸው። 21 የሐናንያም ልጆች ፈላጥያና የሻያ ነበሩ። የረፋያ ልጆች፥ የአርናን ልጆች፥ የአብድዩ ልጆች፥ የሴኬንያ ልጆች። 22 የሴኬንያም ልጅ ሸማያ ነበረ። የሸማያም ልጆች ሐጡስ፥ ይግኣል፥ ባርያሕ፥ ነዓርያ፥ ሻፋጥ ስድስት ነበሩ። 23 የነዓርያም ልጆች ኤልዮዔናይ፥ ሕዝቅያስ፥ ዓዝሪቃም ሦስት ነበሩ። 24 የኤልዮዔናይም ልጆች ሆዳይዋ፥ ኤልያሴብ፥ ፌልያ፥ ዓቁብ፥ ዮሐናን፥ ደላያ፥ ዓናኒ ሰባት ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 4

1 የይሁዳ ልጆች ፋሬስ፥ ኤስሮም፥ ከርሚ፥ ሆር፥ ሦባል ናቸው። 2 የሦባልም ልጅ ራያ ኢኤትን ወለደ፤ ኢኤትም አሑማይንና ላሃድን ወለደ። እነዚህ የጾርዓውያን ወገኖች ናቸው። 3 እነዚህም የኤጣም አባት ልጆች ናቸው፤ ኢይዝራኤል፥ ይሽማ፥ ይድባሽ፥ እኅታቸውም ሃጽሌልፎኒ። 4 የጌዶርም አባት ፋኑኤል፥ የሑሻም አባት ኤጽር፤ እነዚህ የቤተ ልሔም አባት የኤፍራታ የበኵሩ የሆር ልጆች ናቸው። 5 ለቴቁሔም አባት ለአሽሑር ሔላና ነዕራ የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት። 6 ነዕራም አሑዛምን፥ ኦፌርን፥ ቴምኒን፥ አሐሽታሪን ወለደችለት። እነዚህ የነዕራ ልጆች ናቸው። 7 የሔላም ልጆች ዴሬት፥ ይጽሐር፥ ኤትናን ናቸው። 8 ቆጽ ዓኑብን፥ ጾቤባን፥ የሃሩምንም ልጅ የአሐርሔልን ወገኖች ወለደ። 9 ያቤጽም ከወንድሞቹ ይልቅ የተከበረ ነበረ፤ እናቱም። በጣር ወልጄዋለሁና ብላ ስሙን። ያቤጽ ብላ ጠራችው። 10 ያቤጽም። እባክህ፥ መባረክን ባርከኝ፥ አገሬንም አስፋው፤ እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን፤ እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ የእስራኤልን አምላክ ጠራ፤ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው። 11 የሹሐም ወንድም ክሉብ የኤሽቶንን አባት ምሒርን ወለደ። 12 ኤሽቶንም ቤትራ ፋንና ፋሴሐን የዒርናሐሽንም አባት ተሒናን ወለደ፤ እነዚህ የሬካ ሰዎች ናቸው። 13 የቄኔዝም ልጆች ጎቶንያልና ሠራያ ነበሩ። የጎቶንያልም ልጅ ሐታት ነበረ። 14 መዖኖታይ ዖፍራን ወለደ። ሠራያም የጌሃራሽምን አባት ኢዮአብን ወለደ፤ እነርሱም ጠራቢዎች ነበሩ። 15 የዮፎኒም ልጅ የካሌብ ልጆች ዒሩ፥ ኤላ፥ ነዓም ነበሩ። 16 የኤላም ልጅ ቄኔዝ ነበረ። የይሃሌልኤል ልጆች ዚፍ፥ ዚፋ፥ ቲርያ፥ አሣርኤል ነበሩ። 17 የዕዝራም ልጆች ዬቴር፥ ሜሬድ፥ ዔፌር፥ ያሎን ነበሩ፤ ዬቴርም ማርያምን፥ ሸማይን፥ የኤሽትምዓን አባት ይሽባን ወለደ። 18 አይሁዳዊቱም ሚስቱ የጌዶርን አባት ዬሬድን፥ የሦኮንም አባት ሔቤርን፥ የዛኖዋንም አባት ይቁቲኤልን ወለደች። እነዚህም ሜሬድ ያገባት የፈርዖን ልጅ የቢትያ ልጆች ናቸው። 19 የሆዲያ ሚስት የነሐም እኅት ልጆች የገርሚው የቅዒላ አባትና ማዕካታዊው ኤሽትሞዓ ነበሩ። 20 የሺሞንም ልጆች አምኖን፥ ሪና፥ ቤንሐናን፥ ቲሎን ነበሩ። የይሽዒም ልጆች ዞሔትና ቢንዞሔት ነበሩ። 21 የይሁዳም ልጅ የሴሎም ልጆች የሌካ አባት ዔር፥ የመሪሳ አባት ለዓዳ፥ ከአሽቤዓ ቤት የሚሆኑ ጥሩ በፍታ የሚሠሩ ወገኖች፥ 22 ዮቂም፥ የኮዜባ ሰዎች፥ ኢዮአስ፥ ሞዓብን የገዛ ሣራፍ፥ ያሹቢሌሔም ነበሩ። 23 ይህ ዝና ከቀድሞ ጀምሮ ነበረ። እነዚህ በነጣዒምና በጋዴራ የሚቀመጡ ሸክላ ሠራተኞች ነበሩ። በዚያ በንጉሡ ዘንድ ስለ ሥራው ይቀመጡ ነበር። 24 የስምዖንም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ያሚን፥ ያሪን፥ ዛራ፥ ሳኡል፤ 25 ልጁ ሰሎም፥ ልጁ መብሳም፥ ልጁ ማስማዕ። 26 የማስማዕም ልጆች፤ ልጁ ሃሙኤል፥ ልጁ ዘኩር፥ ልጁ ሰሜኢ። 27 ለሰሜኢም አሥራ ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ለወንድሞቹ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፥ ወገናቸውም ሁሉ እንደ ይሁዳ ልጆች አልተባዙም። 28 በቤርሳቤህም፥ በሞላዳ፥ 29 በሐጸርሹዓል፥ በቢልሃ፥ በዔጼም፥ 30 በቶላድ፥ በቤቱኤል፥ በሔርማ፥ በጺቅላግ፥ 31 በቤትማርካቦት፥ በሐጸርሱሲም፥ በቤትቢሪ፥ በሸዓራይም ይቀመጡ ነበር። እስከ ዳዊትም መንግሥት ድረስ ከተሞቻቸው እነዚህ ነበሩ። 32 መንደሮቻቸውም ኤጣም፥ ዓይን፥ ሬሞን፥ ቶኬን፥ ዓሻን፥ አምስቱ ከተሞች፤ 33 እስከ በኣልም ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበሩ መንደሮቻቸው ሁሉ ነበሩ። መቀመጫቸውና የትውልዳቸው መዝገቦች እነዚህ ናቸው። 34 ምሾባብ፥ የምሌክ፥ የአሜስያስ ልጅ ኢዮስያ፥ 35 ኢዮኤል፥ የዮሺብያ ልጅ፥ የሠራያ ልጅ የዓሢኤል ልጅ ኢዩ፥ 36 ኤልዮዔናይ፥ ያዕቆባ፥ የሾሐያ፥ ዓሣያ፥ ዓዲዔል፥ ዩሲምኤል፥ በናያስ፥ 37 የሺፊ ልጅ ዚዛ፥ የአሎን ልጅ የይዳያ ልጅ የሺምሪ ልጅ የሸማያ ልጅ፤ 38 እነዚህ በስማቸው የተጠሩ በወገኖቻቸው ላይ አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸውም ቤቶች በዝተው ነበር። 39 ለመንጎቻቸው መሰምርያ ይሹ ዘንድ ወደ ጌዶር መግቢያ እስከ ሸለቆው ምሥራቅ ድረስ ሄዱ። 40 የለመለመችም እጅግም ያማረች መሰምርያ አገኙ፤ ምድሪቱም ሰፊና ጸጥተኛ ሰላም ያላትም ነበረች፤ በቀድሞም ጊዜ በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ከካም ወገን ነበሩ። 41 እነዚህም በስማቸው የተጻፉ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን መጥተው ድንኳኖቻቸውንና በዚያ የተገኙትን ምዑናውያንን መቱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ ፈጽመው አጠፉአቸው፤ በዚያም ለመንጎቻቸው መሰምርያ ነበረና በስፍራቸው ተቀመጡ። 42 የስምዖንም ልጆች አምስት መቶ ሰዎች ወደ ሴይር ተራራ ሄዱ፤ አለቆቻቸውም የይሽዒ ልጆች፥ ፈላጥያ፥ ነዓርያ፥ ረፋያ፥ ዑዝኤል ነበሩ። 43 ያመለጡትንም የአማሌቃውያንን ቅሬታ መቱ፥ በዚያም እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጠዋል።

1 ዜና መዋዕል 5

1 የእስራኤልም በኵር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኵር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኵርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኵርና ጋር አልተቈጠረም። 2 ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኵርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ። 3 የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ። 4 የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥ 5 ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ ልጁ ሚካ፥ 6 ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱ የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ። 7 ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥ 8 ዘካርያስ፥ እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ፤ 9 በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ። 10 በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ። 11 የጋድም ልጆች በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ በአፋዛዣቸው ተቀመጡ። 12 አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በበሳን ተቀመጡ። 13 የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ ሰባት ነበሩ። 14 እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ። 15 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ ወንድም ነበረ። 16 በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰምርያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር። 17 እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ። 18 የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኵሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ ሰልፍ የሚያውቁ ሰልፈኞችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ነበሩ። 19 ከአጋራውያንና ከኢጡር ከናፌስና ከናዳብ ጋር ተዋጉ። 20 በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ በላያቸውም ረዳት ሆናቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተሰጡ። 21 ከከብቶቻቸውም አምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ አምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ። 22 ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ። 23 የምናሴ የነገድ እኵሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ። 24 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ። 25 የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ። 26 የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኵሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ ኦቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው።

1 ዜና መዋዕል 6

1 የሌዊ ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 2 የቀዓትም ልጆች፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል። 3 የእንበረምም ልጆች፤ አሮን፥ ሙሴ፥ ማርያም። የአሮን ልጆች፤ ናዳብ፥ አብዮድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። 4 አልዓዛር ፊንሐስን ወለደ፤ ፊንሐስ አቢሱን ወለደ፤ 5 አቢሱም ቡቂን ወለደ፤ ቡቂም ኦዚን ወለደ፤ 6 ኦዚም ዘራእያን ወለደ፤ ዘራእያም መራዮትን ወለደ፤ 7 መራዮት አማርያን ወለደ፤ 8 አማርያም አኪጦብን ወለደ፤ አኪጦብም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪማአስን ወለደ፤ 9 አኪማአስም ዓዛርያስን ወለደ፤ 10 ዓዛርያስም ዮሐናንን ወለደ፤ ዮሐናንም ዓዛርያስን ወለደ፤ እርሱም ሰሎሞን በኢየሩሳሌም በሠራው ቤት ካህን ነበረ፤ 11 ዓዛርያስም አማርያን ወለደ፤ አማርያም አኪጦብን ወለደ፤ 12 አኪጦብም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም ሰሎምን ወለደ፤ 13 ሰሎምም ኬልቅያስን ወለደ፤ ኬልቅያስም ዓዛርያስን ወለደ፤ 14 ዓዛርያስም ሠራያን ወለደ፤ ሠራያም ኢዮሴዴቅን ወለደ፤ 15 እግዚአብሔርም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን በናቡከደነፆር እጅ ባስማረከ ጊዜ ኢዮሴዴቅ ተማርኮ ሄደ። 16 የሌዊ ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 17 የጌድሶንም ልጆች ስም ይህ ነው፤ ሎቤኒ ሰሜኢ። 18 የቀዓትም ልጆች፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ነበሩ። 19 የሜራሪ ልጆች፤ ሞሖሊም፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው። 20 ከጌድሶን፤ ልጁ ሎቤኒ፥ ልጁ ኢኤት፥ ልጁ ዛማት፥ 21 ልጁ ዮአክ፥ ልጁ አዶ፥ ልጁ ዛራ፥ ልጁ ያትራይ። 22 የቀዓት ልጆች፤ ልጁ አሚናዳብ፥ 23 ልጁ ቆሬ፥ ልጁ አሴር፥ ልጁ ሕልቃና፥ 24 ልጁ አቢሳፍ፥ ልጁ አሴር፥ ልጁ ኢኢት፥ ልጁ ኡሩኤል፥ ልጁ ዖዝያ፥ ልጁ ሳውል። 25 የሕልቃናም ልጆች፤ አማሢ፥ አኪሞት። 26 የሕልቃናም ልጆች፤ ልጁ ሱፊ፥ 27 ልጁ ናሐት፥ ልጁ ኤልያብ፥ ልጁ ይሮሐም፥ ልጁ ሕልቃና። 28 የሳሙኤልም ልጆች፤ በኵሩ ኢዮኤል፥ ሁለተኛውም አብያ። 29 የሜራሪ ልጆች፤ ሞሖሊ፥ ልጁ ሎቤኒ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ 30 ልጁ ዖዛ፥ ልጁ ሳምዓ፥ ልጁ ሐግያ፥ ልጁ ዓሣያ። 31 ዳዊትም ታቦቱ ዐርፎ ከተቀመጠ በኋላ በእግዚአብሔር ቤት ያቆማቸው የመዘምራን አለቆች እነዚህ ናቸው። 32 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት በኢየሩሳሌም እስኪሠራ ድረስ በመገናኛ ድንኳን ማደሪያ ፊት እያዜሙ ያገለግሉ ነበር፤ በየተራቸውም ያገለግሉ ነበር። 33 አገልጋዮቹና ልጆቹ እነዚህ ናቸው፤ ከቀዓት ልጆች ዘማሪው ኤማን ነበረ፤ እርሱም የኢዮኤል ልጅ፥ 34 የሳሙኤል ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የይሮሐም ልጅ፥ የኤሊኤል ልጅ፥ የቶዋ ልጅ፥ 35 የሱፍ ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የመሐት ልጅ፥ 36 የአማሢ ልጅ፥ የሕልቃና ልጅ፥ የኢዮኤል ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የሶፎንያስ ልጅ፥ 37 የታሐት ልጅ፥ የአሴር ልጅ፥ 38 የአብያሳፍ ልጅ፥ የቆሬ ልጅ፥ የይስዓር ልጅ፥ የቀዓት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የእስራኤል ልጅ ነው። 39 በቀኙም የቆመ ወንድሙ አሳፍ ነበረ፤ አሳፍም የበራክያ ልጅ፥ 40 የሳምዓ ልጅ፥ የሚካኤል ልጅ፥ የበዓሤያ ልጅ፥ 41 የመልክያ ልጅ፥ የኤትኒ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ 42 የዓዳያ ልጅ፥ የኤታን ልጅ፥ የዛማት ልጅ፥ 43 የሰሜኢ ልጅ፥ የኢኤት ልጅ፥ የጌድሶን ልጅ፥ የሌዊ ልጅ ነው። 44 በግራቸውም በኩል ወንድሞቻቸው የሜራሪ ልጆች ነበሩ፤ ኤታን የቂሳ ልጅ፥ የአብዲ ልጅ፥ 45 የማሎክ ልጅ፥ የሐሸብያ ልጅ፥ የአሜስያስ ልጅ፥ 46 የኬልቅያስ ልጅ፥ የአማሲ ልጅ፥ 47 የባኒ ልጅ፥ የሴሜር ልጅ፥ የሞሖሊ ልጅ፥ የሙሲ ልጅ፥ የሜራሪ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ። 48 ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ቤት ማደሪያ አገልግሎት ሁሉ ተሰጡ። 49 አሮንና ልጆቹ ግን የእግዚአሔር ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው ሁሉ ለቅድስተ ቅዱሳን ሥራ ሁሉ ስለ እስራኤልም ያስተሰርይ ዘንድ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ይሠዉ ነበር፥ በዕጣኑም መሠዊያ ላይ ያጥኑ ነበር። 50 የአሮንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ልጁ አልዓዛር፥ 51 ልጁ ፊንሐስ፥ ልጁ አቢሱ፥ ልጁ ቡቂ፥ 52 ልጁ ኦዚ፥ ልጁ ዘራእያ፥ ልጁ መራዮት፥ 53 ልጁ አማርያ፥ ልጁ አኪጦብ፥ ልጁ ሳዶቅ፥ ልጁ አኪማአስ። 54 ማደሪያዎቻቸውም በየሰፈራቸው በየዳርቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ለአሮን ልጆች ለቀዓት ወገኖች አንደኛው ዕጣ ነበረ። 55 ለእነርሱ በይሁዳ አገር ያለችውን ኬብሮንን፥ በእርስዋም ዙሪያ የነበረውን መሰምርያ ሰጡ፤ 56 የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጡ። 57 ለአሮንም ልጆች የመማፀኛውን ከተሞች፥ ኬብሮንን፥ ልብናንና መሰምርያዋን፥ ደግሞ የቲርን፥ 58 ኤሽትሞዓንና መሰምርያዋን፥ ሖሎንንና መሰምርያዋን፥ ዳቤርንና መሰምርያዋን፥ 59 ዓሳንንና መሰምርያዋን፥ ቤትሳሚስንና መሰምርያዋን፤ 60 ከብንያምም ነገድ ጌባንና መሰምርያዋን፥ ጋሌማትንና መሰምርያዋን፥ ዓናቶትንና መሰምርያዋን ሰጡ። ከተሞቻተው ሁሉ በየወገናቸው አሥራ ሦስት ነበሩ። 61 ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከነገዱ ወገን ከምናሴ ነገድ እኵሌታ አሥር ከተሞች በዕጣ ተሰጡ። 62 ለጌድሶንም ልጆች በየወገናቸው ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ፥ አሥራ ሦስት ከተሞች ተሰጡ። 63 ለሜራሪ ልጆች በየወገናቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ፥ አሥራ ሁለት ከተሞች በዕጣ ተሰጡ። 64 የእስራኤልም ልጆች ለሌዋውያን ከተሞችን ከመሰምርያዎቻቸው ጋር ሰጡ። 65 ከይሁዳም ልጆች ነገድ፥ ከስምዖንም ልጆች ነገድ፥ ከብንያምም ልጆች ነገድ፥ እነዚህን በስማቸው የተጠሩትን ከተሞች በዕጣ ሰጡ። 66 ከቀዓትም ልጆች ወገኖች ለአንዳንዶቹ ከኤፍሬም ነገድ ከተሞች ድርሻ ነበራቸው። 67 በተራራማው በኤፍሬም አገር ያሉትን የመማፀኛውን ከተሞች ሴኬምንና መሰምርያዋን፥ ደግሞም ጌዝርንና መሰምርያዋን፥ ዮቅምዓምንና መሰምርያዋን፥ 68 ቤትሖሮንንና መሰምርያዋን፥ 69 ኤሎንንና መሰምርያዋን፥ ጋትሪሞንንና መሰምርያዋን ሰጡአቸው። 70 ከምናሴም ነገድ እኵሌታ ዓኔርንና መሰምርያዋን፥ ቢልዓምንና መሰምርያዋን ከቀዓት ልጆች ወገን ለቀሩት ሰጡ። 71 ለጌድሶን ልጆች ከምናሴ ነገድ እኵሌታ ወገን በባሳን ያለችው ጎላንና መሰምርያዋ፥ አስታሮትና መሰምርያዋ፤ 72 ከይሳኮርም ነገድ ቃዴስና መሰምርያዋ፥ ዳብራትና መሰምርያዋ፥ 73 ራሞትና መሰምርያዋ፥ ዓኔምና መሰምርያዋ፤ 74 ከአሴርም ነገድ መዓሳልና መሰምርያዋ፥ ዓብዶንና መሰምርያዋ፥ 75 ሑቆቅና መሰምርያዋ፥ ረአብና መሰምርያዋ፤ 76 ከንፍታሌምም ነገድ በገሊላ ያለችው ቃዴስና መሰምርያዋ፥ ሐሞንና መሰምርያዋ፥ ቂርያታይምና መሰምርያዋ ተሰጡ። 77 ከሌዋውያን ለቀሩት ለሜራሪ ልጆች ከዛብሎን ነገድ ሬሞንና መሰምርያዋ፥ ታቦርና መሰምርያዋ፤ 78 ከሮቤልም ነገድ በኢያሪኮ አንጻር በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል በምድረ በዳ ያለችው ቦሶርና መሰምርያዋ፥ 79 ያሳና መሰምርያዋ፥ ቅዴሞትና መሰምርያዋ፥ ሜፍዓትና መሰምርያዋ፤ 80 ከጋድም ነገድ በገለዓድ ያለችው ሬማትና መሰምርያዋ፥ መሃናይምና መሰምርያዋ፥ 81 ሐሴቦንና መሰምርያዋ፥ ኢያዜርና መሰምርያዋ ተሰጡ።

1 ዜና መዋዕል 7

1 የይሳኮርም ልጆች፥ ቶላ፥ ፉዋ፥ ያሱብ ሺምሮን፥ አራት ናቸው። 2 የቶላም ልጆች፥ ኦዚ፥ ራፋያ፥ ይሪኤል፥ የሕማይ፥ ይብሣም፥ ሽሙኤል፥ የአባታቸው የቶላ ቤት አለቆች፥ በትውልዳቸው ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በዳዊት ዘመን ቍጥራቸው ሀያ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ። 3 የኦዚም ልጆች ይዝረሕያ፤ የይዝረሕያም ልጆች ሚካኤል፥ አብድዩ፥ ኢዮኤል፥ ይሺያ አምስት ናቸው፤ ሁሉም አለቆች ነበሩ። 4 ከእነርሱም ጋር በየትውልዳቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሰልፍ የተዘጋጁ የሠራዊት ጭፍሮች ነበሩ፤ ብዙም ሴቶችና ልጆች ነበሩአቸውና ሠላሳ ስድስት ሺህ ነበሩ። 5 ወንድሞቻቸውም በይሳኮር ወገኖች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች በትውልዳቸው ሁሉ የተቈጠሩ ሰማኒያ ሰባት ሺህ ነበሩ። 6 የብንያም ልጆች ቤላ፥ ቤኬር፥ ይዲኤል ሦስት ነበሩ። 7 የቤላም ልጆች፥ ኤሴቦን፥ ኦዚ፥ ዑዝኤል፥ ኢያሪሙት፥ ዒሪ፥ አምስት ነበሩ፤ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በትውልድ የተቈጠሩ ሀያ ሁለት ሺህ ሠላሳ አራት ነበሩ። 8 የቤኬርም ልጆች፤ ዝሚራ፥ ኢዮአስ፥ አልዓዛር፥ ኤልዮዔናይ፥ ዖምሪ፥ ኢያሪሙት፥ አብያ፥ ዓናቶት፥ ዓሌሜት፤ እነዚህ ሁሉ የቤኬር ልጆች ነበሩ። 9 በየትውልዳቸው መዝገብ የተቈጠሩ፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ሀያ ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 10 የይዲኤልም ልጅ ቢልሐን ነበረ፤ የቢልሐንም ልጆች የዑስ፥ ብንያም፥ ኤሁድ፥ ክንዓና፥ ዜታን፥ ተርሴስ፥ አኪሳአር ነበሩ። 11 እነዚህ ሁሉ የይዲኤል ልጆች ነበሩ፤ በየአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጭፍራ እየሆኑ ወደ ሰልፍ የሚወጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች አሥራ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 12 ደግሞም ሳፊን፥ ሑፊም የዒር ልጆች፥ ሑሺም የአሔር ልጆችም ነበሩ። 13 የንፍታሌም ልጆች፥ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም፥ የባላ ልጆች ነበሩ። 14 የምናሴ ልጆች ሶርያይቱ ቁባቱ የወለደችለት እሥርኤልና የገለዓድ አባት ማኪር ናቸው። 15 ማኪርም ከሑፊምና ከሳፊን ወገን ሚስት አገባ፤ የእኅትዋም ስም መዓካ ነበረ፤ የሁለተኛውም ስም ሰለጰአድ ነበረ፤ ለሰለጰዓድም ሴቶች ልጆች ነበሩት። 16 የማኪርም ሚስት መዓካ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው፤ የወንድሙም ስም ሱሮስ ነበረ፤ ልጆቹም ኡላም፥ ራቄም ነበሩ። 17 የኡላምም ልጅ ባዳን ነበረ፤ እነዚህ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ነበሩ። 18 እኅቱ መለኬት ኢሱድን፥ አቢዔዝርን፥ መሕላን ወለደች። 19 የሸሚዳም ልጆች አሒያን፥ ሴኬም፥ ሊቅሒ፥ አኒዓም ነበሩ። 20 የኤፍሬም ልጆች፤ ሹቱላ፥ ልጁ ባሬድ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ኤልዓዳ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ዛባድ፥ ልጁ ሽቱላ፥ 21 የአገሩም ተወላጆች የጌት ሰዎች ከብቶቻቸውን ሊወስዱ ወርደው ነበርና የገደሉአቸው ልጆቹ ኤድርና ኤልዓድ ነበሩ። 22 አባታቸውም ኤፍሬም ብዙ ቀን አለቀሰ፥ ወንድሞቹም ሊያጽናኑት መጡ። 23 ወደ ሚስቱም ገባ፥ አረገዘችም፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ በቤቱም መከራ ሆኖአልና ስሙ በሪዓ ብሎ ጠራው። 24 ሴት ልጁም ታችኛውንና ላይኛውን ቤትሖሮንንና ኡዜንሼራን የሠራች ሲአራ ነበረች። 25 ወንዶች ልጆቹም ፋፌ፥ ሬሴፍ፥ ልጁ ቴላ፥ 26 ልጁ ታሐን፥ ልጁ ለአዳን፥ ልጁ ዓሚሁድ፥ ልጁ ኤሊሳማ፥ 27 ልጁ ነዌ፥ ልጁ ኢያሱ። 28 ግዛታቸውና ማደሪያቸው ቤቴልና መንደሮችዋ፥ በምሥራቅም በኩል ነዓራን፥ በምዕራብም በኩል ጌዝርና መንደሮችዋ፥ ደግሞ ሴኬምና መንደሮችዋ እስከ ጋዛና እስከ መንደሮችዋ ድረስ፥ 29 በምናሴም ልጆች ዳርቻ ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ታዕናክና መንደሮችዋ፥ መጊዶና መንደሮችዋ፥ ዶርና መንደሮችዋ ነበሩ፤ በእነዚህ የእስራኤል ልጅ የዮሴፍ ልጆች ተቀመጡ። 30 የአሴር ልጆች ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸውም ሤራሕ። 31 የበሪዓም ልጆች፤ ሔቤር፥ የቢርዛዊት አባት የነበረው መልኪኤል። 32 ሔቤርም ያፍሌጥን፥ ሳሜንር፥ ኮታምን፥ እኅታቸውንም ሶላን ወለደ። 33 የያፍሌጥም ልጆች ፋሴክ፥ ቢምሃል፥ ዓሲት ነበሩ፤ እነዚህ የያፍሌጥ ልጆች ነበሩ። 34 የሳሜርም ልጆች አኪ፥ ሮኦጋ፥ ይሑባ፥ አራም ነበሩ። 35 የወንድሙም የኤላም ልጆች ጾፋ፥ ይምና፥ ሰሌስ፥ ዓማል ነበሩ። 36 የጾፋም ልጆች ሱዋ፥ ሐርኔፍር፥ 37 ሦጋል፥ ቤሪ፥ ይምራ፥ ቤጼር፥ ሆድ፥ ሳማ፥ ሰሊሳ፥ ይትራን፥ ብኤራ ነበሩ። 38 የዬቴር ልጆች ዮሮኒ፥ ፊስጳ፥ አራ ነበሩ። 39 የዑላ ልጆች ኤራ፥ ሐኒኤል፥ ሪጽያ ነበሩ። 40 እነዚህ ሁሉ የአሴር ልጆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ የተመረጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች፥ የመኳንንቱ አለቆች ነበሩ። በትውልዳቸውም በሰልፍ ለመዋጋት የተቈጠሩ ሀያ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 8

1 ብንያምም በኵሩን ቤላን፥ ሁለተኛውንም አስቤልን፥ 2 ሦስተኛውንም አሐራን፥ አራተኛውንም ኖሐን፥ አምስተኛውንም ራፋን ወለደ። 3 ለቤላም ልጆች ነበሩት፤ አዳር፥ 4 ጌራ፥ አቢሁድ፥ አቢሱ፥ ናዕማን፥ አሖዋ፥ ጌራ፥ ሰፉፋም፥ ሑራም። 56 እነዚህም የኤሁድ ልጆች ናቸው፤ እነዚህ በጌባ የሚቀመጡ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ናቸው፤ 7 ወደ መናሐትም ተማረኩ፤ ናዕማን፥ አኪያ፥ ጌራ፥ እነርሱም ተማረኩ። ዖዛንና አሒሑድን ወለደ። 8 ሸሐራይምም ሚስቶቹን ሑሺምንና በዕራን ከሰደደ በኋላ በሞዓብ ሜዳ ልጆች ወለደ። 9 ከሚስቱ ከሖዴሽ ዮባብን፥ 10 ዲብያን፥ ማሴን፥ ማልካምን፥ ይዑጽን፥ ሻክያን፥ ሚርማን ወለደ። እነዚህም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 11 ከሑሺምም አቢጡብንና ኤልፍዓልን ወለደ። 12 የኤልፍዓልም ልጆች፤ ዔቤር፥ ሚሻም፥ ኦኖንና ሎድን መንደሮቻቸውንም የሠራ ሻሚድ፤ 13 በሪዓ፥ ሽማዕ የጌትን ሰዎች ያሳደዱ የኤሎን ሰዎች የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ፤ 14 አሒዮ፥ ሻሻቅ፥ ይሬምት፥ 15 16 ዝባድያ፥ ዓራድ፥ ዔድር፥ ሚካኤል፥ ይሽጳ፥ ዮሐ፥ የበሪዓ ልጆች፤ 17 ዝባድያ፥ ሜሱላም፥ 18 ሕዝቂ፥ ሔቤር፥ ይሽምራይ፥ ይዝሊያ፥ ዮባብ፥ የኤልፍዓል ልጆች፤ 19 ያቂም፥ ዝክሪ፥ ዘብዲ፥ 20 21 ኤሊዔናይ፥ ጺልታይ፥ ኤሊኤል፥ ዓዳያ፥ ብራያ፥ ሺምራት፥ የሰሜኢ ልጆች፤ 22 ይሽጳን፥ 23 ዔቤር፥ ኤሊኤል፥ ዓብዶን፥ ዝክሪ፥ 24 25 ሐናን፥ ሐናንያ፥ ኤላም፥ ዓንቶትያ፥ ይፍዴያ፥ ፋኑኤል፥ የሶሴቅ ልጆች፤ 26 ሸምሽራይ፥ 27 ሸሃሪያ፥ ጎቶልያ፥ ያሬሽያ፥ ኤልያስ፥ ዝክሪ፥ የይሮሐም ልጆች። 28 እነዚህ በትውልዶቻቸው አለቆች ነበሩ፤ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ፤ እነዚህ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 29 የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው የገባዖን አባት ይዒኤል፥ 30 የበኵር ልጁ ዓብዶን፥ 31 ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ናዳብ፥ ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር በገባዖን ተቀመጡ። 32 ሚቅሎት ሳምአን ወለደ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ተቀመጡ። 33 ኔር ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሚልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስባኣልን ወለደ። 34 የዮናታንም ልጅ መሪበኣል ነበረ፤ መሪበኣልም ሚካን ወለደ። 35 የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሬዓ፥ አካዝ ነበሩ። 36 አካዝም ይሆዓዳን ወለደ፤ ይሆዓዳም ዓሌሜትን፥ ዓዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ። 37 ሞጻም ቢንዓን ወለደ፤ ልጁም ረፋያ ነበረ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል፤ 38 ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሽዓርያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ ሁሉ የኤሴል ልጆች ነበሩ። 39 የወንድሙም የአሴል ልጆች፤ በኵሩ ኡላም፥ ሁለተኛውም ኢያስ፥ ሦስተኛውም ኤሊፋላት። 40 የኡላም ልጆች ጽኑዓን ኃያላንና ቀስተኞች ነበሩ፤ ለእነርሱም መቶ አምሳ የሚያህሉ ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆች ነበሩአቸው፤ እነዚህ ሁሉ የብንያም ልጆች ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 9

1 እስራኤልም ሁሉ በየትውልዳቸው ተቈጠሩ፤ እነሆም፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። ይሁዳም ስለ ኃጢአታቸው ወደ ባቢሎን ተማረኩ። 2 በአውራጃዎቻቸውና በከተሞቻቸው መጀመሪያ የተቀመጡ እስራኤልና ካህናት ሌዋውያንም ናታኒምም ነበሩ። 3 ከይሁዳ ልጆችና ከብንያም ልጆች ከኤፍሬምና ከምናሴ ልጆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 4 ከይሁዳ ልጅ ከፋሬስ ልጆች የባኒ ልጅ የአምሪ ልጅ የፆምሪ ልጅ የዓሚሁድ ልጅ ዑታይ ደግሞ ተቀመጠ። 5 ከሴሎናዊያንም በኵሩ ዓሣያና ልጆቹ። 6 ከዛራም ልጆች ይዑኤልና ወንድሞቻቸው፥ ስድስት መቶ ዘጠና። 7 ከብንያምም ልጆች የሐስኑአ ልጅ የሆዳይዋ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሉ፤ 8 የይሮሐም ልጅ ብኔያ፤ የሚክሪ ልጅ የኦዚ ልጅ ኤላ፤ የዪብኒያ ልጅ የራጉኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ ሜሱላም፤ 9 በየትውልዳቸውም ወንድሞቻቸው ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ስድስት ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10 ከካህናቱም ዮዳሄ፥ ዮአሪብ፥ ያኪን፤ 11 የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ የመራዮት ልጅ የሳዶቅ ልጅ ሜሱላም ልጅ የኬልቂያስ ልጅ ዓዛርያስ፤ 12 የመልኪያ ልጅ የጳስኮር ልጅ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፤ የኢሜር ልጅ የምሺላሚት ልጅ የሜሱላም ልጅ የየሕዜራ ልጅ የዓዲኤል ልጅ መዕሣይ፤ 13 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ወንድሞቻቸው ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ነበሩ፤ ለእግዚአብሔር ቤት ማገልገል ሥራ እጅግ ብልሃተኞች ሰዎች ነበሩ። 14 ከሌዋውያንም የሜራሪ ልጆች የአሳብያ ልጅ የዓዝሪቃም ልጅ የአሱብ ልጅ ሸማያ፤ 15 በቅበቃር፥ ኤሬስ፥ ጋላል፥ የኣሳፍ ልጅ የዝክሪ ልጅ የሚካ ልጅ መታንያ፤ 16 የኤዶታም ልጅ የጋላል ልጅ የሰሙስ ልጅ አብድያ፤ በነጦፋውያንም መንደሮች የተቀመጠው የሕልቃና ልጅ የአሳ ልጅ በራክያ። 17 በረኞችም ሰሎም፥ ዓቁብ፥ ጤልሞን፥ አሒማን፥ ወንድሞቻቸውም ነበሩ፤ ሰሎምም አለቃ ነበረ። 18 እስከ ዛሬም ድረስ በንጉሥ በር በምሥራቅ በኩል ነበሩ፤ ለሌዊ ልጆች ሰፈር በረኞች ነበሩ። 19 የቆሬም ልጅ የአብያሳፍ ልጅ የቆሬ ልጅ ሰሎም ከአባቱም ቤት የነበሩ ወንድሞቹ ቆሬያውያን በማገልገል ሥራ ላይ ነበሩ፥ የድንኳኑንም መድረክ ይጠብቁ ነበር። አባቶቻቸውም የእግዚአብሔርን ሰፈር መግቢያ ጠብቀው ነበር። 20 አስቀድሞም የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ አለቃቸው ነበረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 21 የሜሱላም ልጅ ዘካርያስ የመገናኛው ድንኳን ደጅ በረኛ ነበረ። 22 የመድረኩ በረኞች ይሆኑ ዘንድ የተመረጡ እነዚህ ሁሉ ሁለት መቶ አሥራ ሁለት ነበሩ። ዳዊትና ነቢዩ ሳሙኤል በሥራቸው ያቆሙአቸው እነዚህ በመንደሮቻቸው በየትውልዳቸው ተቈጠሩ። 23 እነርሱና ልጆቻቸውም በእግዚአብሔር ቤት በድንኳኑ ደጆች ላይ ዘበኞች ነበሩ። 24 በአራቱ ማዕዘኖች፥ በምሥራቅ፥ በምዕራብ፥ በሰሜን፥ በደቡብ፥ በረኞች ነበሩ። 25 ወንድሞቻቸውም በመንደሮቻቸው ሆነው፥ በየሰባትም ቀን ከእነርሱ ጋር ሊሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይገቡ ነበር። 26 ከሌዋውያንም የነበሩ አራቱ የበረኞች አለቆች ዘወትር በሥራቸው ይቀመጡ ነበር፤ በእግዚአብሔርም ቤት ባሉ ጓዳዎችና ቤተ መዛግብት ላይ ነበሩ። 27 የእግዚአብሔርንም ቤት የሚጠብቁ፥ ጥዋት ጥዋትም ደጆቹን የሚከፍቱ እነርሱ ነበሩና በዚያ ያድሩ ነበር። 28 ዕቃውም በቍጥር ይገባና ይወጣ ነበርና ከእነዚህ አንዳንዱ በማገልገያው ዕቃ ላይ ሹሞች ነበሩ። 29 ከእነርሱም አንዳንዶቹ በመቅደሱ ዕቃ ሁሉ በመልካሙም ዱቄት፥ በወይን ጠጁ፥ በዘይቱም፥ በዕጣኑም፥ በሽቱውም ላይ ሹሞች ነበሩ። 30 ከካህናቱም ልጆች አንዳንዶቹ የሽቱውን ቅባት ያጣፍጡ ነበር። 31 የቆሬያዊውም የሰሎም በኵር ሌዋዊው ማቲትያ በምጣድ በሚጋገረው ነገር ላይ ሹም ነበረ። 32 በየሰንበቱም ያዘጋጁ ዘንድ ከወንድሞቻቸው ከቀዓታውያን አንዳንዱ በገጹ ኅብስት ላይ ሹሞች ነበሩ። 33 ከሌዋውያኑም ወገን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች የነበሩ መዘምራን እነዚህ ናቸው፤ ሥራቸውም ሌሊትና ቀን ነበረና ያለሌላ ሥራ በየጓዳቸው ይቀመጡ ነበር። 34 እነዚህ ከሌዋውያን የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች በየትውልዳቸው አለቆች ነበሩ። እነዚህም በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ነበር። 35 የሚስቱ ስም መዓካ የነበረው የገባዖን አባት ይዒኤል፥ 36 የበኵር ልጁም ዓብዶን፥ 37 ዱር፥ ቂስ፥ በኣል፥ ኔር፥ ናዳብ፥ ጌዶር፥ አሒዮ፥ ዛኩር፥ ሚቅሎት፥ በገባኦን ይቀመጡ ነበር። 38 ሚቅሎትም ሳምአን ወለደ፤ እነርሱ ደግሞ ከወንድሞቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ይቀመጡ ነበር። 39 ኔርም ቂስን ወለደ፤ ቂስም ሳኦልን ወለደ፤ ሳኦልም ዮናታንን፥ ሚልኪሳን፥ አሚናዳብን፥ አስበኣልን ወለደ። 40 የዮናታንም ልጅ መሪበኣል ነበረ፤ መሪበኣልም ሚካን ወለደ። 41 የሚካም ልጆች ፒቶን፥ ሜሌክ፥ ታሬዓ፥ አካዝ ነበሩ። 42 አካዝም የዕራን ወለደ፤ የዕራም ዓሌሜትን፥ ዓዝሞትን፥ ዘምሪን ወለደ፤ ዘምሪም ሞጻን ወለደ። 43 ሞጻም ቢንዓን ወለደ፥ ልጁም ረፋያ ነበረ፥ ልጁ ኤልዓሣ፥ ልጁ ኤሴል፤ 44 ለኤሴልም ስድስት ልጆች ነበሩት፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ዓዝሪቃም፥ ቦክሩ፥ እስማኤል፥ ሸዓሪያ፥ አብድዩ፥ ሐናን፤ እነዚህ የኤሴል ልጆች ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 10

1 ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦአ ተራራ ላይ ወደቁ። 2 ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። 3 ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ ከቀስተኞችም የተነሣ ተጨነቀ። 4 ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። 5 ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 6 ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። 7 በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8 በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9 ገፈፉትም፥ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣኦቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ ሰደዱ። 10 መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት። 11 የኢያቢስ ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ 12 ጽኑአን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ። 13 እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ 14 ስለ ጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው።

1 ዜና መዋዕል 11

1 እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2 አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም። ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ 5ብሎህ ነበር አሉት። 3 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት። 4 ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። 5 በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን። ወደዚህ አትገባም አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት። 6 ዳዊትም። ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኰንን ይሆናል አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ፥ አለቃም ሆነ። 7 ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት። 8 ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አበጀ። 9 ዳዊትም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና እየበረታ ሄደ። 10 ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ያነግሡት ዘንድ ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት። 11 የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሠላሳው አለቃ የአክሞናዊው ልጅ ያሾብአም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። 12 ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃሂው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበር። 13 እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለሰልፍ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14 በእርሻውም መካከል ቆመው ጠበቁት፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ማዳን አዳናቸው። 15 ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 16 በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተ ልሔም ነበረ። 17 ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ይሰጠኛል? ብሎ ተመኘ። 18 እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ። 19 ይህን አደርግ ዘንድ አምላኬ ይከልክለኝ፤ በነፍሳቸው የደፈሩትም እነዚህ ሰዎች ደም እጠጣለሁን? በነፍሳቸው አምጥተውታል አለ። ስለዚህም ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው። 20 የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። 21 በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። 22 በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤል ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 23 ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው። 24 የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበር። 25 እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው። 26 ደግሞም በጭፍሮች ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ 27 ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥ 28 የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ 29 ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ሴቤካይ፥ 30 አሆሃዊው ዔላይ፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥ 31 ከብንያም ወገን ከግብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥ 32 ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ 33 ዓረባዊው አቢኤል፥ ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥ 34 ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ 35 የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ 36 የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ ሚኬራታዊው ኦፌር፥ 37 ፍሎናዊው አኪያ፥ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥ 38 የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሐግሪ ልጅ ሚብሐር፥ 39 አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥ 40 ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ 41 ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ 42 የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥ 43 ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥ 44 አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮኤራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥ 45 የሽምሪ ልጅ ይድኤል፥ ወንድሙም ይድኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥ 46 መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻዊያ፥ የኤልናዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥ 47 ኤልኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል።

1 ዜና መዋዕል 12

1 በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በሰልፍም ባገዙት ኃያላን መካከል ነበሩ። 2 ቀስተኞችም ነበሩ፥ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ። 3 አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፥ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች፤ ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች፤ በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥ 4 ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኃያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥ 5 ገድሮታዊው ዮዛባት፥ ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሀሩፋዊው ሰፋጥያስ፥ 6 ቆርያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ አዛርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾቢአም፤ 7 የጌዶር ሰው የይሮሃም ልጆች የኤላ፥ ዝባድያ 8 ዳዊትም ከምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአንባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን ኃያላን፥ ሰልፈኞች፥ ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፥ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። 9 አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥ 10 ሦስተኛው ኤልያብ፥ አራተኛው መስመና፥ 11 አምስተኛው ኤርምያስ፥ ስድስተኛው አታይ፥ 12 ሰባተኛው ኤሊኤል፥ ስምንተኛው ዮሐናን፥ 13 ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥ አሥረኛው ኤርምያስ፥ አሥራ አንደኛው መክበናይ። 14 እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ ከመቶ፥ ታላቁ ከሺህ ይመዛዘኑ ነበር። 15 በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ። 16 ዳዊትም ወደነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ። 17 ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ። ትረዱኝ ዘንድ በሠላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደሆነ ግን፥ በእጄ ዓመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፥ ይፍረደውም አላቸው። 18 መንፈስም በሠላሳው አለቃ በአማሳይ ላይ መጣ፥ እርሱም። ዳዊት ሆይ፥ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴል ልጅ ሆይ፥ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፥ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፥ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው። 19 ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን። በራሳችን ላይ ጕዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እነርሱ አልረዷቸውም። 20 ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ። 21 ሁሉም ጽኑዓን ኃያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ላይ ዳዊትን አገዙት። 22 እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር። 23 እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው። 24 ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 25 ለሰልፍ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። 26 የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 27 የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤ 28 ከእርሱም ጋር ጽኑዕ ኃያል ጕልማሳ ሳዶቅ ነበረ፥ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ። 29 የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ወንድሞች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ። 30 ጽኑዓን ኃያላን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሀያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 31 በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኵሌታ አሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ። 32 እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር። 33 በጭፍራውም ውስጥ የወጡ ለሰልፍም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ። 34 የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፥ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ። 35 ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 36 በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ። 37 በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኵሌታ መሣሪያን ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሀያ ሺህ ነበሩ። 38 እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ። 39 ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ። 40 ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢበ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።

1 ዜና መዋዕል 13

1 ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ። 2 ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ። መልካም መስሎ የታያችሁ እንደሆነ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔርም ወጥቶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰምሪያዎቻቸውም ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ፤ 3 በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ አላቸው። 4 ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዓይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ። እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። 5 የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። 6 ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደ ተባለች ወደ በኣላ ሄዱ። 7 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር። 8 ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። 9 ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። 10 የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። 11 እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ብሎ ጠራው። 12 በዚያም ቀን ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ። 13 ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም። 14 የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።

1 ዜና መዋዕል 14

1 የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ። 2 ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ። 3 ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ። 4 በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፥ 5 ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ 6 ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥ 7 ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት። 8 ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ። 9 ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ። 10 ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው። 11 ወደ በአልፐራሲም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት መታቸው። ዳዊትም። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በአልፐራሲም ብለው ጠሩት። 12 አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሏቸው። 13 ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በሸለቆው አደጋ ጣሉ። 14 ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም። ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ። 15 በሾላውም ዛፍ እራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው። 16 ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት። 17 የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።

1 ዜና መዋዕል 15

1 ዳዊትም በከተማው ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት። 2 በዚያን ጊዜም ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም አለ። 3 ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4 ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ። 5 ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሀያ፤ 6 ከሜራሪ ልጆች፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ሀያ፤ 7 ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤ 8 ከኤሊጻፋን ልጆች፤ አለቃው ሸማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤ 9 ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኤሊኤል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤ 10 ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ አሥራ ሁለት። 11 ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አቢያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ። 12 እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13 ቀድሞም አልተሸከማችሁምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ አላቸው። 14 የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ። 15 ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ። 16 ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ። 17 ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን፥ 18 ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅንያን፥ በረኞችንም ዖቤድኤዶምንና ይዒኤልን አቆሙ። 19 መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20 ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር። 21 መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኒያ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22 የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ በዜማ ላይ ተሹሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና ዜማ ያስተምራቸው ነበር። 23 በራክያና ሕልቃናም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ። 24 ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሳፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦይ ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ። 25 ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 26 የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በረዳቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ። 27 ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ነበረው። 28 እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ። 29 የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልቧ ናቀችው።

1 ዜና መዋዕል 16

1 የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2 ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን ባረከ። 3 ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፤ አንዳንድም ቍራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አካፈለ። 4 በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት ያገለግሉ ዘንድ፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይወድሱት ዘንድ፥ ያመሰግኑትና ያከብሩትም ዘንድ ከሌዋውያን ወገን አቆመ። 5 አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል በመሰንቆና በበገና አሳፍም በጸናጽል ይዘምሩ ነበር። 6 ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። 7 በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ትእዛዝን ሰጠ። 8 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ። 9 ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። 10 በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። 11 እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። 12 13 ባሪያዎቹ የእስራኤል ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱንም የአፉንም ፍርድ። 14 እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ 16 ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ 17 ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፤ 18 እንዲህም አለ። ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤ 19 ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው። 20 ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። 21 22 የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። 23 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ። 24 ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ። 25 እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። 26 የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። 27 ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው። 28 የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርንና ኃይልን ለእግዚአብሔር አምጡ። 29 ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ፤ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። 30 ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጥ፤ ዓለሙም እንዳይናወጥ ጸንቶአል። 31 ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሴትን ታድርግ፤ በአሕዛብም መካከል። እግዚአብሔር ነገሠ በሉ። 32 ባሕርና ሞላዋ ትናወጥ፤ በረሀ በእርሷም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ። 33 በምድር ሊፈርድ ይመጣልና፥ የዱር ዛፎች በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል። 34 ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። 35 የመዳናችን አምላክ ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ ሰብስበህ ታደገን በሉ። 36 ከዘላለም እስከ ዘላለም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይበሉ፤ እግዚአብሔርንም ያመስግኑ። 37 እንዲሁም በየቀኑ እንደሚገባቸው በታቦቱ ፊት ዘወትር ያገለግሉ ዘንድ አሳፍንና ወንድሞቹን፥ ዖቤድኤዶምንም፥ ስድሳ ስምንቱንም ወንድሞቻቸውን በዚያ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው። 38 የኤዶታምም ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ በረኞች ይሆኑ ዘንድ ተዋቸው። 39 ካህኑም ሳዶቅንና ካህናቱን ወንድሞቹን በገባዖን በኮረብታው መስገጃ ባለው በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት አቆማቸው፥ 40 ለእስራኤልም ባዘዘው በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ ሁሉ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁል ጊዜ ጥዋትና ማታ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ። 41 ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ኤማንንና ኤዶታምን፥ በስማቸውም የተጻፉትን ተመርጠው የቀሩትን ከእነርሱ ጋር አቆመ። 42 ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ከፍ አድርገው ለማሰማት መለከትና ጸናጽል ለእግዚአብሔርም መዝሙራት የዜማ ዕቃ ይዘው ነበር፤ የኤዶታምም ልጆች በረኞች ነበሩ። 43 ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊትም ቤቱን ይባርክ ዘንድ ተመለሰ።

1 ዜና መዋዕል 17

1 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ ዳዊት ነቢዩን ናታንን። እነሆ፥ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት በመጋረጃዎች ውስጥ ተቀምጦአል አለው። 2 ናታንም ዳዊትን። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ አለው። 3 በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው። 45 ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከድንኳን ወደ ድንኳን፥ ከማደሪያም ወደ ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርሁምና የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። 6 ከእስራኤል ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ። ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ፈራጆች ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 7 አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ። 8 በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደታላላቆች ስም ለአንተ ስም አደርጋለሁ። 9 10 ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ እንደቀድሞው ዘመንና በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ቤት እንዲሠራልህ እነግርሃለሁ። 11 ወደ አባቶችህም ትሄድ ዘንድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከልጆችህ የሚሆነውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 12 እርሱ ቤት ይሠራልኛል፤ ዙፋኑንም ለዘላለም አጸናለሁ። 13 እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ከአንተ አስቀድሞ ከነበረው እንዳራቅሁ፥ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 14 በቤቴና በመንግሥቴም ለዘላለም አቆመዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል። 15 እንደዚህ ነገር ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው። 16 ንጉሡም ዳዊት ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ። አቤቱ አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው? 17 አምላክ ሆይ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕርግ ሰው ተመለከትኸኝ። 18 አንተ ባሪያህን ታውቀዋለህና ለባሪያህ ስለ ተደረገ ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምንድር ነው? 19 አቤቱ፥ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ ታስታውቀው ዘንድ ስለ ባሪያህ እንደ ልብህም ይህን ታአምራት ሁሉ አድርገሃል። 20 አቤቱ፥ እንዳንተ ያለ የለም፥ በጆሮአችንም እንደሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21 አንተ እግዚአብሔር ከግብጽ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ በታላቅና በሚያስፈራ ነገር ለአንተ ስም ታደርግ ዘንድ፥ ለአንተም ሕዝብ ትቤዥ ዘንድ እንደሄድህለት እንዳንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ አለን? 22 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነኸዋል። 23 አሁንም፥ አቤቱ፥ ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የተናገርኸው ለዘላለም የጸና ይሁን፤ እንደተናገርህም አድርግ። 24 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፥ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ጽኑና ታላቅ ይሁን፤ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ ጸንቶአል። 25 አምላኬ ሆይ፥ ቤት እንድሠራለት ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ወዳንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ። 26 አሁንም፥ አቤቱ፥ አንተ አምላክ ነህ፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 27 አሁንም በፊትህ ለዘላለም ይኖር ዘንድ የባሪያህን ቤት እንድትባርክ ፈቅደሃል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ባርከኸዋል፥ ለዘላለምም ቡሩክ ይሆናል።

1 ዜና መዋዕል 18

1 ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። 2 ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። 3 ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሃማት ድረስ መታ። 4 ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊት ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቆረጠ። 5 ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። 6 ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር። 7 ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8 ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኵሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ። 9 የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10 ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁል ጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ስለመታው ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ ይመርቀውም ዘንድ ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። 11 ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ። 12 ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደለ። 13 በኤዶምያስም ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር። 14 ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅም አደረገላቸው። 15 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ። 16 የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ። 17 የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ።

1 ዜና መዋዕል 19

1 ከዚህም በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2 ዳዊትም። አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ልያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3 የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባሪያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን? አሉት። 4 ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5 ወሬኞችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ተቀባዮች ላከ፤ ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አለ። 6 የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራምመዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ። 7 ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ። 8 ዳዊትም ይህ በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 9 የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ በሩ። 10 ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው። 11 የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፥ በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ። 12 እርሱም። ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። 13 አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ። 14 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለሰልፍ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። 15 የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 16 ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ። 17 ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18 ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። 19 የአድርአዛርም ባሪያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ።

1 ዜና መዋዕል 20

1 እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፥ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር። 2 ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፥ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቍ ነበረበት፥ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 3 በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 4 ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ። 5 ደግሞም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ። 6 ደግሞ በጌት ላይ ሰልፍ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 7 እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። 8 እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ።

1 ዜና መዋዕል 21

1 ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አንቀሳቀሰው። 2 ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች። ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፥ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ አላቸው። 3 ኢዮአብም። እግዚአብሔር ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሁሉ የጌታዬ ባሪያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለ ምን ያመጣል? 4 ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5 ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን ከመቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ። 6 የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበርና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። 7 ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፥ እስራኤልንም ቀሠፈ። 8 ዳዊትም እግዚአብሔርን። ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 9 እግዚአብሔርም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ። 10 ሂድ፥ ለዳዊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው ብሎ ተናገረው። 11 ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምትወድደውን ምረጥ፤ 12 የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንድመልስ ተመልከት አለው። 13 ዳዊትም ጋድን። እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ አለው። 14 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ። 15 እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተጸጸተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ። በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16 ዳዊትም ዓይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፉ። 17 ዳዊትም እግዚአብሔርን። ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፥ ነገር ግን ይቀሠፍ ዘንድ በሕዝብህ ላይ አትሁን አለው። 18 የእግዚአብሔርም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19 ዳዊትም በእግዚአብሔር ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20 ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆቹ ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። 21 ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ተመልክቶ ዳዊትን አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፋ። 22 ዳዊትም ኦርናን። በላዩ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ በሙሉ ዋጋ ስጠኝ፤ መቅሠፍቱን ከሕዝቡ ይከለከላል አለው። 23 ኦርናም ዳዊትን። ለአንተ ውሰደው፥ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለእንጨትም የአውድማውን ዕቃ፥ ከእህልም ቍርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ አለው። 24 ንጉሡም ዳዊት ኦርናን። አይደለም፥ ነገር ግን ለአንተ ያለውን ለእግዚአብሔር አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ አለው። 25 ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። 26 ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ጠራ፤ ከሰማይም ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት። 27 እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው። 28 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ። 29 ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። 30 ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ አልቻለም።

1 ዜና መዋዕል 22

1 ዳዊትም። ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው አለ። 2 ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ። 3 ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። 4 ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር ያሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። 5 ዳዊትም። ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በአገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ። 6 ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው። 7 ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ። ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። 8 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ። እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። 9 እነሆ፥ የዕረፍት ሰው የሚሆን ልጅ ይወለድልሃል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። 10 እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። 11 አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ። 12 ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሠልጥንህ። 13 እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም። 14 አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም ከዚያ በላይ ጨምር። 15 በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችና ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉ። 16 የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን። 17 ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ያግዙ ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው። 18 አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። 19 አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።

1 ዜና መዋዕል 23

1 ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2 የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። 3 ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸው በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ። 4 ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ። 5 አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 6 ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እነደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 7 ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። 8 የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ። 9 የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10 የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። 11 አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ። 12 የቀአት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። 13 የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥንና ያገለግል ዘንድ፥ በስሙም ለዘላለም ይባርክ ዘንድ። 14 የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15 የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። 16 የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። 17 የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። 18 የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። 19 የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ። 20 የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ። 21 የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22 አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። 23 የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ። 24 የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። 25 ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም የቀመጣል። 26 ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም አለ። 27 በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። 28 ሥራቸውም የእግዚአብሔርን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ነበረ። 29 ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ነበር። 30 ሥራቸውም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥ 31 በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥ 32 ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት ለመጠበቅ ነበረ።

1 ዜና መዋዕል 24

1 የአሮንም ልጆች ሰሞን ይህ ነው። የአሮን ልጆች ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ነበሩ። 2 ናዳብና አብዩድ ግን ልጆች ሳይወልዱ ከአባታቸው በፊት ሞቱ፤ አልዓዛርና ኢታምርም ካህናት ሆኑ። 3 ዳዊትም ከአልዓዛር ልጆች ከሳዶቅ ጋር፥ ከኢታምርም ልጆች ከአቢሜሌክ ጋር ሆኖ እንደ አገልግሎታቸው ሥርዓት ከፍሎ መደባቸው። 4 የአልዓዛርም ልጆች አለቆች ከኢታምርም ልጆች አለቆች በልጠው ተገኙ፤ እንዲህም ተመደቡ፤ ከአልዓዛር ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች አሥራ ስድስት፥ ከኢታምርም ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች ስምንት አለቆች ነበሩ። 5 ከአልዓዛርና ከኢታምርም ልጆች መካከል የመቅደሱና የእግዚአብሔር አለቆች ነበሩና እነዚህና እነዚያ እንዲህ በዕጣ ተመደቡ። 6 ከሌዋውያንም ወገን የነበረው የናትናኤል ልጅ ጸሐፊው ሸማያ በንጉሡና በአለቆቹ ፊት፥ በካህኑ በሳዶቅና በአብያታርም ልጅ በአቢሜሌክ ፊት፥ በካህናቱና በሌዋውያኑ አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት ጻፋቸው፤ አንዱንም የአባት ቤት ለአልዓዛር፥ አንዱንም ለኢታምር ጻፈ። 7 መጀመሪያውም ዕጣ ለዮአሪብ ወጣ፥ ሁለተኛው ለዮዳኤ፥ 8 ሦስተኛው ለካሪም፥ 9 አራተኛው ለሥዖሪም፥ አምስተኛው ለመልክያ፥ 10 ስድስተኛው ለሚያሚን፥ ሰባተኛው ለአቆስ፥ 11 ስምንተኛው ለአብያ፥ ዘጠኝኛው ለኢያሱ፥ 12 አሥረኛው ለሴኬንያ፥ አሥራ አንደኛው ለኤልያሴብ፥ አሥራ ሁለተኛው ለያቂም፥ 13 አሥራ ሦስተኛው ለኦፓ፥ አሥራ አራተኛው ለየሼብአብ፥ 14 አሥራ አምስተኛው ለቢልጋ፥ አሥራ ስድስተኛው ለኢሜር፥ 15 አሥራ ሰባተኛው ለኤዚር፥ አሥራ ስምንተኛው ለሃፊጼጽ፥ 16 አሥራ ዘጠኝኛው ለፈታያ፥ 17 ሀያኛው ለኤዜቄል፥ ሀያ አንደኛው ለያኪን፥ ሀያ ሁለተኛው ለጋሙል፥ 18 ሀያ ሦስተኛው ለድላያ፥ ሀያ አራተኛው ለመዓዝያ። 19 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ አባታቸው አሮን እንደ ሰጣቸው ሥርዓት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገቡበት የአገልግሎታቸው ሥርዓት ይህ ነበረ። 20 ከቀሩትም የሌዊ ልጆች፤ ከእንበረም ልጆች ሱባኤል፤ ከሱባኤል ልጆች ዬሕድያ፤ 21 22 ከረዓብያ ልጆች አለቃው ይሺያ፤ ከይስዓራውያን ሰሎሚት፤ ከሰሎሚት ልጆች ያሐት፤ 23 ከኬብሮንም ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቀምዓም፤ 24 የዑዝኤል ልጅ ሚካ፤ 25 የሚካ ልጅ ሻሚር፤ የሚካ ወንድም ይሺያ፤ 26 ከይሺያ ልጆች ዘካርያስ፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ፤ ከያዝያ ልጅ በኖ፤ 27 የሜራሪ ልጆች፤ ከያዝያ በኖ፥ ሾሃም፥ ዘኩር፥ ዔብሪ፤ 28 ከሞሖሊ አልዓዛር፥ እርሱም ልጆች አልነበሩት፤ 29 ከቂስ፤ የቂስ ልጅ ይረሕምኤል፤ የሙሲም ልጆች፤ ሞሖሊ፥ ዔዳር፥ ኢያሪሙት። 30 እነዚህ እንደ አባቶቻቸው ቤቶች የሌዋውያን ልጆች ነበሩ። 31 እነዚህም ደግሞ በንጉሡ በዳዊትና በሳዶቅ በአቢሜሌክም በሌዋውያንና በካህናት አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት፥ ታላቁም እንደ ታናሹ፥ እንደ ወንድሞቻቸው እንደ አሮን ልጆች ዕጣ ተጣጣሉ።

1 ዜና መዋዕል 25

1 ዳዊትና የሠራዊቱ አለቆችም ከአሳፍና ከኤማን ከኤዶታም ልጆች በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም ትንቢት የሚናገሩትን ሰዎች ለማገልገል ለዩ፤ በአገልግሎታቸውም ሥራ የሠሩ ሰዎች ቍጥር ይህ ነበረ። 2 ከአሳፍ ልጆች፤ ዘኩር፥ ዮሴፍ፥ ነታንያ፥ አሸርኤላ፤ እነዚህ የአሳፍ ልጆች በንጉሡ ትእዛዝ ትንቢት ከተናገረው ከአሳፍ እጅ በታች ነበሩ። 3 ከኤዶታም የኤዶታም ልጆች፤ ጎዶልያስ፥ ጽሪ፥ የሻያ፥ ሰሜኢ፥ ሐሸብያ፥ መቲትያ፥ እነዚህ ስድስቱ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ክብር በመሰንቆ ትንቢት ከተናገረው ከአባታቸው ከኤዶታም እጅ በታች ነበሩ። 4 ከኤማን የኤማን ልጆች፤ ቡቅያ፥ መታንያ፥ ዓዛርዔል፥ ሱባኤ፥ ኢያሪሙት፥ ሐናንያ፥ ሐናኒ፥ ኤልያታ፥ ጊዶልቲ፥ ሮማንቲዔዘር፥ ዮሽብቃሻ፥ መሎቲ፥ ሆቲር፥ መሐዝዮት፤ 5 እነዚህ ሁሉ ቀንደ መለከቱን ከፍ ያደርጉ ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል የንጉሡ ባለ ራእይ የሆነው የኤማን ልጆች ነበሩ። እግዚአብሔርም ለኤማን አሥራ አራት ወንዶች ልጆችንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ሰጠው። 6 እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት በጸናጽልና በበገና በመሰንቆም ይዘምሩ ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ ከአባታቸው እጅ በታች ነበሩ፤ አሳፍም ኤዶታምም ኤማንም ከንጉሡ ትእዛዝ በታች ነበሩ። 7 የብልሃተኞቹም ቍጥር እግዚአብሔርን ለማመስገን ከሚያውቁ ከወንድሞቻቸው ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ነበረ። 8 ሁሉም ተካክለው፥ ታናሹ እንደ ታላቁ፥ አስተማሪውም እንደ ተማሪው፥ ለሰሞናቸው ዕጣ ተጣጣሉ። 9 የፊተኛው ዕጣ ከአሳፍ ወገን ለነበረው ለዮሴፍ ወጣ፤ ሁለተኛው ለጎዶልያስ ወጣ፤ እርሱ ወንድሞቹም ልጆቹም አሥራ ሁለት ነበሩ፤ 10 ሦስተኛው ለዘኩር ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 11 አራተኛው ለይጽሪ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 12 አምስተኛው ለነታንያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 13 ስድስተኛው ለቡቅያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 14 ሰባተኛው ለይሽርኤል ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 15 ስምንተኛው ለየሻያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 16 ዘጠኝኛው ለመታንያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 17 አሥረኛው ለሰሜኢ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 18 አሥራ አንደኛው ለዓዛርኤል ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 19 አሥራ ሁለተኛው ለሐሸብያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 20 አሥራ ሦስተኛው ለሱባኤል ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 21 አሥራ አራተኛው ለመቲትያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 22 አሥራ አምስተኛው ለኢያሪሙት ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 23 አሥራ ስድስተኛው ለሐናንያ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 24 አሥራ ሰባተኛው ለዮሽብቃሻ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 25 አሥራ ስምንተኛው ለሐናኒ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 26 አሥራ ዘጠኝኛው ለመሎቲ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 27 ሀያኛው ለኤልያታ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 28 ሀያ አንደኛው ለሆቲር ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 29 ሀያ ሁለተኛው ለጊዶልቲ ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 30 ሀያ ሦስተኛው ለመሐዚዮት ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ፤ 31 ሀያ አራተኛው ለሮማንቲዔዘር ለልጆቹም ለወንድሞቹም ለአሥራ ሁለቱ ወጣ።

1 ዜና መዋዕል 26

1 በረኞችም እንደዚህ ተመደቡ፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም። 2 ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥ 3 አራተኛው የትኒኤል፥ አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ። 4 እግዚአብሔርም ባርኮታልና ዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥ 5 ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ። 6 ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ። 7 ለሸማያ ልጆች ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ወንድሞቹም ኃያላን የነበሩ ኤልዛባድ፥ ኤልሁ፥ ሰማክያ። 8 እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድኤዶም ልጆች ስድሳ ሁለት ነበሩ። 9 ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ አሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት። 10 ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኵር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤ 11 ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበረ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ አሥራ ሦስት ነበሩ። 12 እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ያገለግሉ ዘንድ የበረኞች የአለቆች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ። 13 በበሩም ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ ተካክለው ዕጣ ተጣጣሉ። 14 በምሥራቅም በኩል ዕጣ ለሰሌምያ ወደቀ። ለልጁም ብልህ መካር ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣውም በሰሜን በኩል ወጣ። 15 ለዖቤድኤዶም በደቡብ በኩል፥ ለልጆቹም ለዕቃ ቤቱ ዕጣ ወጣ። 16 ለሰፊንና ለሖሳ በምዕራብ በኩል፥ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በኩል ጥበቃ ከጥበቃ ላይ ዕጣ ወጣ። 17 በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ። 18 በምዕራብ በኩል በፈርባር መንገድ ላይ አራት፥ በፈርባርም አጠገብ ሁለት ነበሩ። 19 ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የበረኞች ሰሞን ይህ ነበረ። 20 ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። 21 የለአዳን ልጆች፤ ለለአዳን የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊ ለለአዳን የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ፤ 22 የይሒኤሊ ልጆች፤ በእግዚአሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብት ላይ የነበሩ ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዩኤል። 23 ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤ 24 የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። 25 ወንድሞቹም፤ ከአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት መጡ። 26 ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አለቆች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር። 27 በሰልፍም ከተገኘው ምርኮ የእግዚአብሔርን ቤት ለማበጀት ቀደሱ። 28 ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ እጅ በታች ነበረ። 29 ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች ይሆኑ ዘንድ በውጭው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 30 ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 31 ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይርያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤ 32 ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኵሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው።

1 ዜና መዋዕል 27

1 የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆችና የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ነገር ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉትም ሹማምት እንደ ቍጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሀያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። 2 ለመጀመሪያው ወር በአንደኛው ክፍል ላይ የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 3 እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያው ወር በጭፍራ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር። 4 በሁለተኛውም ወር ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 5 ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የጭፍራ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 6 ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኃያል ሆኖ በሠላሳው ላይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ነበረ። 7 ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበር። 8 ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 9 ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 10 ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 11 ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 12 ለዘጠኝኛው ወር ዘጠኝኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶታዊው አቢዔዜር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 13 ለአሥረኛው ወር አሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 14 ለአሥራ አንደኛው ወር አሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 15 ለአሥራ ሁለተኛው ወር አሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 16 በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስምዖናውያን የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ፤ 17 በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸቢያ፤ 18 በአሮን ላይ ሳዶቅ፤ በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኤሊሁ፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ፤ 19 በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት፤ 20 በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ፤ በምናሴ ነገድ እኵሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል፤ 21 በገለዓድ ባለው በምናሴ ነገድ እኵሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ፤ በብንያም ላይ የአበኔር ልጅ የዕሢኤል፤ 22 በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል፤ እነዚህ የእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23 እግዚአብሔር ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበዛ ዘንድ ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሀያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። 24 የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቍጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቍጣ ሆነ፥ ቍጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም። 25 በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዝሞት ሹም ነበረ፤ በሜዳውም በከተሞችም በመንደሮችም በግንቦችም ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ 26 መሬቱን የሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ 27 በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚሆነው በወይኑ ሰብል ላይ ሸፋማዊው ዘብዲ ሹም ነበረ፤ 28 በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ 29 በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፍጥ ሹም ነበረ፤ 30 በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ይሕድያ ሹም ነበረ፤ 31 በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ። 32 አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል ከንጉሡ ልጆች ጋር ነበረ፤ 33 አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤ 34 ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ።

1 ዜና መዋዕል 28

1 ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉ፥ የነገዶቹንም አለቆች፥ ንጉሡንም በክፍል የሚያገለግሉትን የጭፍሮች አለቆች፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆችንም፥ በንጉሥና በልጆች ሀብትና ግዛት ላይ የተሾሙትን፥ ጃንደረቦችንም፥ ጽኑዓን ኃይላኑንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 2 ንጉሡም ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አለ። ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የዕረፍት ቤት ለመሥራት እኔ በልቤ አስቤአለሁ፤ ለሥራም የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤ 3 እግዚአብሔር ግን። የሰልፍ ሰው ነህና፥ ደምም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም ብሎኛል። 4 ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የዘላለም ንጉሥ እሆን ዘንድ ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳም አለቃ ይሆን ዘንድ መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሠኝ ዘንድ ሊመርጠኝ ወደደ። 5 እግዚአብሔርም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። 6 እርሱም። ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል። 7 ትእዛዜንና ፈርዴንም በማድረግ እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘላለም አጸናዋለሁ አለኝ። 8 አሁንም የእግዚአብሔር ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር ትወርሱ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ታወርሱአት ዘንድ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፥ ፈልጉም። 9 አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል። 10 አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለመቅደስ የሚሆን ቤትን ትሠራ ዘንድ መርጦሃልና ጠንክረህ ፈጽመው። 11 ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ምሳሌውን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 12 ደግሞም ለእግዚአብሔር ቤት አደባባዮችና በዙርያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት በመንፈሱ ላሰበው ሁሉ ምሳሌን ሰጠው። 13 14 የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን በእግዚአብሔርም ቤት በሚያገለግሉበት ሥራ ሁሉ አስታወቀው። በእግዚአብሔርም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤ 15 ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎችም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩን መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ሁሉ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ 16 ለገጹ ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች ሰጠው፤ 17 ለሜንጦቹና ለድስቶቹ ለመቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን፥ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤ 18 ለዕጣኑም መሠዊዋ ጥሩውን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሰረገላ ምሳሌ ሰጠው። 19 ዳዊትም። የሥራውን ሁሉ ምሳሌ አውቅ ዘንድ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ተጽፎ መጣልኝ አለ። 20 ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን። ጠንክር፥ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፥ አትደንግጥም፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፥ አይጥልህምም። 21 እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥር በብልሃትና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል አለው።

1 ዜና መዋዕል 29

1 ንጉሡም ዳዊት ለጉባኤው ሁሉ እንዲህ አለ። እግዚአብሔር ብቻውን የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ብላቴና ለጋ ነው፤ ሕንፃው ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክ ነው እንጂ ለሰው አይደለምና ሥራው ታላቅ ነው። 2 እኔም እንደ ጕልበቴ ሁሉ ለአምላኬ ቤት ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን፥ ለናሱም ዕቃ ናሱን፥ ለብረቱም ዕቃ ብረቱን፥ ለእንጨቱም ዕቃ እንጨቱን፥ ደግሞም መረግድንና በፈርጥ የሚገባ ድንጋይን፥ የሚለጠፍ ድንጋይን፥ ልዩ ልዩ መልክ ያለውንም ድንጋይ፥ የከበረውንም ድንጋይ ከየዓይነቱ፥ ብዙም እብነ በረድ አዘጋጅቻለሁ። 3 ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ፥ ለመቅደሱ ካዘጋጀሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። 4 የቤቶቹ ግንብ ይለበጡበት ዘንድ ከኦፊር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህም መክሊት ጥሩ ብር፥ 5 በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማነው? 6 የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ነገዶች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በንጉሡም ሥራ ላይ የተሾሙት በፈቃዳቸው አቀረቡ። 7 ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና አሥር ሺህ ዳሪክ፥ አሥር ሺህም መክሊት ብር፥ አሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። 8 ዕንቍም ያለው ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በይሒኤል እጅ ሰጠ። 9 ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው። 10 ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን ባረከ፤ ዳዊትም አለ። አቤቱ፥ የአባታችን የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ተባረክ። 11 አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። 12 ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው። 13 አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፥ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። 14 ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? 15 አባቶቻችንም ሁሉ እንደነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፥ አትጸናም። 16 አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፥ ሁሉም የአንተ ነው። 17 አምላኬ ሆይ፥ ልብን እንድትመረምር፥ ቅንነትንም እንድትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ። 18 አቤቱ፥ የአባቶቻችን የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ይህን አሳብ በሕዝብህ ልብ ለዘላለም ጠብቅ፥ ልባቸውንም ወደ አንተ አቅና። 19 ትእዛዝህንም ምስክርህንም ሥርዓትህንም ይጠብቅ ዘንድ፥ ይህንም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ፥ ያዘጋጀሁለትንም ቤት ይሠራ ዘንድ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው። 20 ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባርኩ አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባታቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ባረኩ፥ ራሳቸውንም አዘንብለው ለእግዚአብሔርና ለንጉሡ ሰገዱ። 21 በነጋውም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ አንድ ሺህ ወይፈን፥ አንድ ሺህም አውራ በጎች፥ አንድ ሺህም የበግ ጠቦቶች፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም፥ ስለ እስራኤልም ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረቡ። 22 በዚያም ቀን በታላቅ ደስታ በእግዚአብሔር ፊት በሉ ጠጡም። የዳዊትንም ልጅ ሰሎሞንን ሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ እርሱንም አለቃ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ቀቡት፥ ሳዶቅንም ካህን ይሆን ዘንድ ቀቡት። 23 ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፥ ተከናወነለትም፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት። 24 አለቆቹም ሁሉ፥ ኃያላኑም፥ ደግሞም የንጉሡ የዳዊት ልጆች ሁሉ ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ሰጡት። 25 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሁሉ ፊት እጅግ አገነነው፤ ከእርሱ በፊትም ለነበሩት ለእስራኤል ነገሥታት ያልሆነውን የመንግሥት ክብር ሰጠው። 26 የእሴይም ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ። 27 በእስራኤልም ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ፤ ሰባት ዓመት በኬብሮን ነገሠ፥ ሠላሳ ሦስትም ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ። 28 ዕድሜም፥ ባለጠግነትም፥ ክብርም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ልጁም ሰሎሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 29 የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል። 30 እንደዚሁም የመንግሥቱ ነገርና ኃይሉ ሁሉ በእርሱም በእስራኤልም በአገሮችም መንግሥታት ሁሉ ላይ ያለፉት ዘመናት ተጽፈዋል።

2 ዜና መዋዕል 1

1 የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው። 2 ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ። 3 ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታ መስገጃ ሄዱ። 4 ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር። 5 የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። 6 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። 7 በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ። 8 ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው። ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። 9 አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። 10 አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና። 11 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን። ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ 12 ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው። 13 ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። 14 ሰሎሞንም ሰረገሎቹንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 15 ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 16 ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። 17 አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር።

2 ዜና መዋዕል 2

1 ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ አሰበ። 2 ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። 3 ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ። ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ሰደድህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። 4 እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘላለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራና እቀድስ ዘንድ አሰብሁ። 5 አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው። 6 ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 7 አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። 8 ደግሞም ባሪያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ስደድልኝ። 9 የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር ይሆናሉ። 10 እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ። 11 የጢሮስ ንጉሥም ኪራም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ ብሎ ለሰሎሞን መልእክት ላከ። 12 ኪራምም ደግሞ አለ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን። 13 አሁንም ከብልሃተኞችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ኪራምአቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ሰድጄልሃለሁ። 14 እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩንም፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅርጽም ሌላም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ያውቃል። 15 አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባሪያዎቹ ይስደድ፤ 16 እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንሰድዳለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ። 17 ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። 18 ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ።

2 ዜና መዋዕል 3

1 ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። 2 በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መሥራት ጀመረ። 3 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው ስፍር ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ። 4 በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሀያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው። 5 ታላቁንም ቤት በጥድ እንጨት ከደነው፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳል ቀረጸበት። 6 ቤቱንም በዕንቍ አስጌጠው፤ ወርቁንም የፈርዋይም ወርቅ ነበረ። 7 ቤቱንም ሰረገሎቹንም መድረኮቹንም ግንቦቹንም ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ፤ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ። 8 ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅ ለበጠው። 9 የምስማሮቹም ሚዛን አምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ። 10 በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱ ኪሩቤልን ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 11 የኪሩቤልም ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበረ፤ ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12 የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፥ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 13 የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሀያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፥ ፊቶቻቸውም ወደ ቤቱ ይመለከቱ ነበር። 14 ከሰማያዊውም ከሐምራዊውም ከቀዩም ሐር ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፥ ኪሩቤልንም ጠለፈበት። 15 በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዓምዶች ሠራ፥ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጕልላት አምስት ክንድ ነበረ። 16 እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በአዕማዱ ራስ ላይ አደረጋቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው። 17 አዕማዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውን በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፤ በቀኝም የነበረውን ስም ያቁም በግራም የነበረውን ስም በለዝ ብሎ ጠራቸው።

2 ዜና መዋዕል 4

1 ደግሞም ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም አሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። 2 ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። 3 በበታቹም ለአንድ ክንድ አሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። 4 በአሥራ ሁለትም በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን ሦስቱም ወደ ምዕራብ ሦስቱም ወደ ደቡብ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበር፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። 5 ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር። 6 ደግሞም አሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር። 7 አሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። 8 አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ። 9 ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፥ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። 10 ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው። 11 ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 12 ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ። 13 በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መርበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። 14 መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥ 15 አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን አሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ። 16 ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ። 17 ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። 18 ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር። 19 ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥ 20 በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 21 አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 22 ጕጦቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ።

2 ዜና መዋዕል 5

1 እንዲሁም ሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን የብርና የወርቅ ዕቃ ሁሉ ሰሎሞን አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበረው ግምጃ ቤት አኖረው። 2 በዚያን ጊዜም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያወጡ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች ሁሉ የእስራኤልንም ልጆች አባቶች ቤቶች መሳፍንት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በሰባተኛው ወር በበዓሉ ጊዜ ጊዜ ወደ ንጉሡ ተከማቹ። 4 የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ፥ ሌዋውያንም ታቦቱን አነሡ። 5 ታቦቱንም የመገናኛውንም ድንኳን በድኳኑም ውስጥ የነበረውን የተቀደሰውን ዕቃ ሁሉ አመጡ፤ እነዚህንም ሁሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ አመጡ። 6 ንጉሡም ሰሎሞን ከእርሱም ጋር የተሰበሰቡ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ በታቦቱ ፊት ሆነው ከብዛት የተነሣ የማይቈጠሩትንና የማይመጠኑትን በጎችና በሬዎች ይሠዉ ነበር። 7 ካህናቱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቱ አምጥተው በቅድስት ቅዱሳን ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች በነበረው በስፍራው አኖሩት። 8 ኪሩቤልም በታቦቱ ስፍራ ላይ ክንፎቻቸውን ዘርግተው ነበር፥ ኪሩቤልም ታቦቱንና መሎጊያዎቹን በስተ ላዩ በኩል ይሸፍኑ ነበር። 9 መሎጊያዎቹም ረጃጅሞች ነበሩና በቅዱስተ ቅዱሳን ፊት ከመቅደሱ ውስጥ ጫፎቻቸው ይታዩ ነበር፤ ነገር ግን ከውጪ አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያ አሉ። 10 በታቦቱም ውስጥ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ ሙሴ በኮሬብ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ምንም አልነበረበትም። 11 በዚያም የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር፥ በሰሞናቸውም አልተከፈሉም ነበር፤ 12 መዘምራንም የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፥ አሳፍና ኤማን ኤዶታምም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም፥ ጥሩ በፍታ ለብሰው ጸናጽልና በገና መሰንቆም እየመቱ በመሠዊያው አጠገብ በመሥራቅ በኩል ቆመው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር መቶ ሀያ ካህናት መለከት ይነፉ ነበር። ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፥ 13 መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ። እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። 14 የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።

2 ዜና መዋዕል 6

1 ሰሎሞንም። እግዚአብሔር። በጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል፤ 2 እኔ ግን ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ ማደሪያ ቤትን ሠራሁልህ አለ። 3 ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 4 እርሱም አለ። ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤ 5 እርሱም። ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤት በዚያ ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥሁም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም፤ 6 ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ ብሎአልና። 7 አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አስቦ ነበር። 8 እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን። ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ መልካም አደረግህ። 9 ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም አለው። 10 እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። 11 ከእስራኤልም ልጆች ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ። 12 13 ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፥ በላዩም ቆመ፥ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹንም ዘርግቶ እንዲህ አለ። 14 አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ 15 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቀህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። 16 አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ። አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ ይሄዱ ዘንድ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። 17 አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለዳዊት የተናገረኸው ቃል ይጽና። 18 በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን? 19 ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ባሪያህም በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። 20 ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ። በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ። 21 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። 22 ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ 23 በሰማይ ስማ፥ አድርግም፥ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፥ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው። 24 ሕዝብህም እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ስማ፥ 25 የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጥሃት ምድር መልሳቸው። 26 አንተን ስለ በደሉ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፥ 27 የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ። 28 በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥ 29 ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ ማናቸውም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 30 31 ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው። 32 ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ ስለ ብርቱውም እጅህ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 33 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። 34 ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥ 35 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው። 36 የማይበድል ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር ቢማርኩአቸው፥ 37 በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም አገር ሳሉ ተመልሰው። ኃጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥ 38 በተማረኩበትም በምርኮአቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 39 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን ይቅር በል። 40 አሁንም፥ አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዓይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮችህም የሚያደምጡ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ። 41 አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ከኃይልህ ታቦት ጋር ወደ ዕረፍትህ ተነሣ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው። 42 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ ለባሪያም ለዳዊት ያደረግህለትን ምሕረት አስብ።

2 ዜና መዋዕል 7

1 ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን በላ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ። 2 የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም። 3 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር፤ በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ። እርሱ መልካም ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና ብለውም እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 4 ንጉሡም ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። 5 ንጉሡም ሰሎሞን ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሀያ ሺህ በጎች ሠዋ። እንዲሁ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ቀደሱ። 6 ካህናቱም በየሥርዓታቸው፥ ሌዋውያኑም ደግሞ። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚለውን የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ፥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ ይዘው ቆመው ነበር፤ ካህናቱም በፊታቸው መለከት ይነፉ ነበር፤ እስራኤልም ሁሉ ቆመው ነበር። 7 ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት የነበረውን የአደባባዩን ውስጥ ቀደሰ፤ ሰሎሞንም የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ስቡንም መያዝ አልቻለምና የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ስብ በዚያ አቀረበ። 8 ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆኑ፥ ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ ያሉ እስራኤል ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 9 ሰባት ቀንም መሠዊያውን ቀድሰው፥ ሰባት ቀንም በዓል አድርገው ነበርና በስምንተኛው ቀን የተቀደሰውን ጉባኤ አደረጉ። 10 በሰባተኛውም ወር በሃያ ሦስተኛውም ቀን ሕዝቡን ወደ ድንኳናቸው አሰናበተ፤ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን ለሕዝቡም ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ደስ ብሎአቸው ሐሴትን እያደረጉ ሄዱ። 11 ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ጨረሰ፤ በእግዚአብሔር ቤትና በራሱ ቤት ይሠራው ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ አከናወነ። 12 እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ እንዲህ አለው። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት መርጫለሁ። 13 ዝናብ እንዳይወርድ ሰማያቱን ብዘጋ፥ ወይም ምድሪቱን ይበላ ዘንድ አንበጣን ባዝዘው፥ ወይም በሕዝብ ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ 14 በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈግሉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ። 15 አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ። 16 አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ። 17 አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንደ ሄደ በፊቴ ብትሄድ፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንና ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ 18 ከአባትህ ከዳዊት ጋር። በእስራኤል ላይ አለቃ፥ የሚሆን ከዘርህ አይታጣም ብዬ ቃል ኪዳን እንዳደረግሁ የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ። 19 እናንተ ግን እኔን ከመከተል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ሥርዓቴንና ትእዛዜን ብትተዉ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ ብትሰግዱላቸውም፥ 20 ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር እነቅላችኋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፥ በአሕዛብም ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት አደርገዋለሁ። 21 ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውንም ይህን ቤት እያዩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለ ምን እንዲህ አደረገ? ብለው ይደነቃሉ። 22 መልሰውም። ከግብጽ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ።

2 ዜና መዋዕል 8

1 እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 2 ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ሠራቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አኖረባቸው። 3 ሰሎሞንም ወደ ሐማትሱባ ሄደ አሸነፋትም። 4 በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን የዕቃ ቤቱን ከተሞች ሁሉ ሠራ። 5 ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መወርወሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤትሖሮን ታችኛውንም ቤትሖሮን ሠራ። 6 ባዕላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። 7 ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከኤዊያውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ 8 የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድር ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 9 ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ። 10 እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሠልጥነው የነበሩ የንጉሡ የሰሎሞን ዓይነተኞች አለቆች ሁለት መቶ አምሳ ነበሩ። 11 ሰሎሞንም። የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ ወደ ሠራላት ቤት አወጣት። 12 በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። 13 ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው በየቀኑ ሁሉ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቍርባን ያቀርቡ ነበር። 14 የእግዚአብሔርም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው ያመሰግኑ ዘንድ፥ በካህናቱም ፊት ያገለግሉ ዘንድ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ በረኞቹንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 15 እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። 16 የእግዚአብሔርም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ነበረ። የእግዚአብሔርም ቤት ተፈጸመ። 17 ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮንጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ። 18 ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባሪያዎቹ እጅ ሰደደለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ።

2 ዜና መዋዕል 9

1 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቱና ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ስውር ነገር አልነበረም። 3 የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ የማዕዱንም መብል፥ 4 የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም አለባበሳቸውንም በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ መንፈስ አልቀረላትም። 5 ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 6 እኔ ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኵሌታ አልነገሩኝም፤ ከሰማሁት ዝና ትበልጣለህ። 7 በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። 8 በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘላለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድና ጽድቅ ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ። 9 ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቱ ከቶ አልነበረም። 10 ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም ባሪያዎችና የሰሎሞን ባሪያዎች የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ደግሞ አመጡ። 11 ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። 12 የሳባም ንግሥት ወደ ንጉሡ ካመጣችው የሚበልጥ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች። 13 ነጋድራሶችና ነጋዴዎች ካመጡለት ሌላ በየዓመቱ ወደ ሰሎሞን የሚመጣ የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 14 የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድሩም ሹማምት ወርቅና ብር ወደ ሰሎሞን ያመጡ ነበር። 15 ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 16 ከጥፍጥም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 17 ንጉሡም ደግሞ ከዘሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 18 ከዙፋኑም ጋር ተጋጥመው ወደ ዙፋኑም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ የወርቅ ብርኩማም ነበረ፤ በዚህና በዚያም በመቀመጫው፤ አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎችም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 19 በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 20 ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የነበረው ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። 21 ለንጉሡም ከኪራም ባሪያዎች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር የዘሆንም ጥርስ ዝንጀሮና ዝጕርጕር ወፍም ይዘው ይመጡ ነበር። 22 ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ። 23 የምድርም ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። 24 እያንዳንዱም ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቱውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። 25 ሰሎሞንም ለፈረሶችና ለሰረገሎች አራት ሺህ ጋጥ፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 26 ከኤፍራጥስም ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። 27 ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባውንም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። 28 ለሰሎሞንም ፈረሶች ከግብጽና ከየአገሩ ሁሉ ያመጡለት ነበር። 29 የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በኦሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን? 30 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31 ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 10

1 እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብጽ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብጽ ተመለሰ። 3 ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ መጥተው ሮብዓምን። 4 አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት። 5 እርሱም። ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ። 6 ንጉሡም ሮብዓም። ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7 እነርሱም። ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ በገርነትም ብትናገራቸው፥ ለዘላለም ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት። 8 እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9 እርሱም። አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው። 10 ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች። አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፥ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ። ታናሽቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ 11 አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት። 12 ንጉሡም። በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13 ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ። 14 አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። 15 እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአሒያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ቃል እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተወስኖ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም። 16 እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ። በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፤ እስራኤል ሆይ፥ ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17 በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠባቸው። 18 ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ሰደደ፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፥ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19 እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።

2 ዜና መዋዕል 11

1 ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ሰዎች ሰበሰበ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ። 3 ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፥ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ ብለህ ንገራቸው። የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፥ በኢዮርብዓምም ላይ ከመሄድ ተመለሱ። 5 ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። 6 በይሁዳና በብንያም ያሉትንም የተመሸጉትን ከተሞች፥ ቤተ ልሔም፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን፥ 78 ቤትጹርን፥ ሦኮን፥ ዓዶላምን፥ ጌትን፥ መሪሳን፥ 9 ዚፍን፥ አዶራይምን፥ ለኪሶን፥ ዓዜቃን፥ 10 ጾርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን፥ ሠራ። 11 ምሽጎቹንም አጠነከረ፥ አለቆችንም አኖረባቸው፥ ምግቡንም ዘይቱንም የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። 12 በከተሞቹ ሁሉ ጋሻና ጦርን አኖረ። ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ። 13 በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየአገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። 14 የእግዚአብሔርም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰመሪያቸውንና ቦታቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 15 እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች ለአጋንንቱም ለሠራቸውም እምቦሶች ካህናትን አቆመ። 16 ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17 ሦስት ዓመት በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄዱ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፥ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ። 18 ሮብዓምም መሐላትን አገባ፤ አባትዋ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ነበረ፤ እናትዋም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኢል ነበረች። 19 እርስዋም የዑስን፥ ሰማራያን፥ ዘሃምን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20 ከእርስዋም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርስዋም አብያን፥ ዓታይን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት። 21 ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ አሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስድሳ ቁባቶች ነበሩት፥ ሀያ ስምንት ወንዶችና ስድሳ ሴቶች ልጆች ወለደ። 22 ሮብዓምም ንጉሥ ያደርገው ዘንድ አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23 ተጠበበም፥ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም አገር ሁሉ በምሽጉ ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ምግብ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።

2 ዜና መዋዕል 12

1 እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ እርሱና እስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ተዉ። 2 እግዚአብሔርን በድለዋልና ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞች ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 3 ከእርሱም ጋር ከግብጽ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሱካውያን፥ የኢትዮጵያ ሰዎችም ነበሩ። 4 ለይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5 ነበዩም ሸማያ ወደ ሮብዓምና ከሺሻቅ ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡባት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በሺሻቅ እጅ ተውኋችሁ። 6 የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ። እግዚአብሔር ጻድቅ ነው ብለው ሰውነታቸውን አዋረዱ። 7 እግዚአብሔርም ሰውነታቸውን እንዳዋረዱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል። ሰውነታቸውን አዋርደዋል፤ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፥ ቍጣዬም በሺሻቅ እጅ በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም፤ 8 ነገር ግን ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቁ ዘንድ ይገዙለታል ሲል ወደ ሸማያ መጣ። 9 የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዛግብትና የንጉሡን ቤት መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን ጋሻዎች ወሰደ። 10 ንጉሡም ሮብዓም በእነርሱ ፋንታ የናስ ጋሻዎችን ሠራ፥ የንጉሡንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው። 11 ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፥ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። 12 ሰውነቱንም ባዋረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ፈጽሞ እንዳያጠፋው ከእርሱ ዘንድ ተመለሰ፤ በይሁዳም ደግሞ መልካም ነገር ተገኘ። 13 ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም በረታ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል አገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ናዕማ ነበረች። 14 እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላዘጋጀም ነበርና ክፉ ነገር አደረገ። 15 የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር በነቢዩ ሸማያና በባለ ራእዩ በአዶ የትውልድ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከልም በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። 16 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 13

1 ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2 ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። 3 በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ሰልፍ ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ሰልፈኞች ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። 4 አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ። ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ 5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን? 6 የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ። 7 ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት። 8 አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው። 9 የአሮንን ልጆች የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። 10 ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፥ አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው። 11 በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹህ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል። 12 እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ ይጮኻሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ። 13 ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ በስተ ኋላቸው ነበረ። 14 ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። 15 የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት መታቸው። 16 የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17 አብያና ሕዝቡ ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። 18 በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ። 19 አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። 20 ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው፥ ሞተም። 21 አብያም ጸና፥ አሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና አሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ። 22 የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።

2 ዜና መዋዕል 14

1 አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ አሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። 2 አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ 3 የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ 4 የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ ይሁዳን አዘዘ። 5 ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የፀሐይ ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች። 6 በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፥ በዚያም ዘመን ሰልፍ አልነበረም። 7 ይሁዳንም። እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርም ግንብም መዝጊያም መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ ገና በፊታችን ናት፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል አለ። እነርሱም ሠሩ አከናወኑም። 8 ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። 9 ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። 10 አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። 11 አሳም። አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 12 እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። 13 አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ። 14 ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበረና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። 15 የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።

2 ዜና መዋዕል 15

1 የእግዚአብሔርም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ ሆነ፤ 2 አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው። አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። 3 እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። 4 በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። 5 በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ። 6 እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር። 7 እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ። 8 አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ። 9 አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። 10 አሳም በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11 በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር ሠዉ። 12 በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ 13 የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ። 14 ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ። 15 በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍት ሰጣቸው። 16 ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስላደረገች ከእቴጌነትዋ አዋረዳት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። 17 በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። 18 አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባ። 19 አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ሰልፍ አልነበረም።

2 ዜና መዋዕል 16

1 አሳ በነገሠ በሠላሳ ስድስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፥ ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ አሳ ማንም መውጣትና መግባት እንዳይችል ራማን ሠራ። 2 አሳም ከእግዚአብሔር ቤትና ከንጉሡ ቤት መዝገብ ብርና ወርቅ ወስዶ። 3 በአባቴና በአባትህ መካከል እንደ ነበረው ቃል ኪዳን በእኔና በአንተ መካከል ይሆናል፤ እነሆ ብርና ወርቅ ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ ብሎ በደማስቆ ወደተቀመጠው ወደ ሶሪያ ንጉሥ ወደ ወልደ አዴር ሰደደ። 4 ወልደ አዴር ንጉሡን አሳን እሺ አለው፥ የሠራዊቱም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰደደ፤ እነርሱም ዒዮንንና ዳንን አቤልማይምንና የንፍታሌምን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ መቱ። 5 ባኦስም በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ተወ፥ ሥራውንም አቋረጠ። 6 ንጉሡም አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ባኦስ ይሠራበት የነበረውን የራማን ድንጋይና እንጨት አስወገዱ፥ እርሱም ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። 7 በዚያን ጊዜም ባለ ራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው። በሶሪያ ንጉሥ ታምነሃልና፥ በአምላክህም በእግዚአብሔር አልታመንህምና ስለዚህ የሶሪያ ንጉሥ ጭፍራ ከእጅህ አምልጦአል። 8 ኢትዮጵያውያንና የልብያ ሰዎች እጅግ ብዙ ሰረገሎችና ፈረሰኞች የነበሩአቸው እጅግ ታላቅ ጭፍራ አልነበሩምን? በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው፥ 9 እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል። ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል። 10 አሳም በባለ ራእዩ ላይ ተቈጣ፤ ስለዚህም ነገር ተቈጥቶአልና በግዞት አኖረው፤ በዚያን ጊዜም አሳ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎችን አስጨነቀ። 11 የአሳም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 12 በነገሠም በሠላሳ ዘጠኝኛው ዓመት አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኃኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም። 13 አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በነገሠም በአርባ አንደኛው ዓመት ሞተ። 14 ለእርሱም ለራሱ በሠራው መቃብር በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ በቀማሚ ብልሃት የተሰናዳ ልዩ ልዩ መልካም ሽቱ በተሞላ አልጋ ላይም አኖሩት፤ እጅግም ታላቅ የሆነ የመቃብር ወግ አደረጉለት።

2 ዜና መዋዕል 17

1 በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ። 2 በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ። 3 እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፥ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ በኣሊምንም አልፈለገምና፤ 4 ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም። 5 እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት። 6 ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ። 7 በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ሰደደ። 8 ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ሰደደ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ሰደደ። 9 እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር። 10 በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፥ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም። 11 ከፍልስጥኤማውያን ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበር፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር። 12 ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ። 13 በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ሰልፈኞች ነበሩት። 14 ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ 15 ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 16 ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። 17 ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ 18 ከእርሱም በኋላ ዮዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። 19 ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር።

2 ዜና መዋዕል 18

1 ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ለአክዓብም ጋብቻ ሆነ። 2 ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። 3 የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን? አለው። እርሱም እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን ብሎ መለሰለት። 4 ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 5 የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት። 6 ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔርን ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን? አለ። 7 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይነግርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው አለው። ኢዮሳፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለው። 8 የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው አለው። 9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማሪያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10 የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ አለ። 11 ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር። 12 ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው። 13 ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ አለ። 14 ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው። እርሱም። ውጣ፥ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ አለ። 15 ንጉሡም። በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው። 16 እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ። 17 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን? አለው። 18 ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 19 እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው? አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። 20 መንፈስም መጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አታልለዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም። በምን? አለው። 21 እርሱም። ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ አለ። 22 አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል። 23 የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና። የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ። 24 ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ አለ። 25 የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። 26 ንጉሡ እንዲህ ይላል። በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ። 27 ሚክያስም። በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ አለ። 28 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 29 የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ሰልፍም ገቡ። 30 የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። 31 የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፥ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። 32 የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 33 አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳምባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም። ተወግቻለሁና እጅህን ግታ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ አለው። 34 በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶሪያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።

2 ዜና መዋዕል 19

1 የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። 2 ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን። ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ሆኖብሃል። 3 ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው። 4 ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ደግሞም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው። 5 በምድር ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። 6 ፈራጆቹንም። ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። 7 አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ አላቸው። 8 ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በእግዚአብሔር ስም ፍርድን እንዲፈርዱ ክርክርንም እንዲቈርጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። 9 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ እግዚአብሔርን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። 10 በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ በደምና በደም መካከል በሕግና በትእዛዝ በሥርዓትና በፍርድም መካከል ያለ ማናቸውም ነገር ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቍጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11 እነሆም፥ ለእግዚአብሔር በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን።

2 ዜና መዋዕል 20

1 እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ። 2 ወሬኞችም መጥተው። ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው ብለው ለኢዮሣፍጥ ነገሩት። 3 ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ። 4 ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ተከማቸ፤ ከይሁዳ ከተሞችም ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ። 5 ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤ 6 እንዲህም አለ። አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም። 7 አምላካችን ሆይ፥ በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘላለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን? 8 እነርሱም የተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት። 9 ክፉ ነገር፥ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮኻለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ። 10 አሁንም፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ያልፉባቸው ዘንድ ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ፈቀቅ ብለው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥ 11 እነሆ፥ ለወሮታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ያወጡን ዘንድ መጥተዋል። 12 አምላካችን ሆይ፥ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው። 13 የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር። 14 የእግዚአብሔርም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካሪያስ ልጅ በየሕዚኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤ 15 እንዲህም አለ። ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል። ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። 16 ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ ዓቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። 17 እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው። 18 ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። 19 ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በእጅግ ታላቅ ድምፅ ያመሰገኑት ዘንድ ቆሙ። 20 ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና። ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ። 21 ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፥ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። 22 ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። 23 የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ። 24 የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም። 25 ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ይሸከሙ ዘንድ አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። 26 በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም እግዚአብሔርን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። 27 የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ። 28 በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ። 29 እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ። 30 የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጥ አለች፥ አምላኩም በዙሪያው ካሉ አሳረፈው። 31 ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። 32 በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን አደረገ። 33 ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላዘጋጁም ነበር። 34 የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል። 35 ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ። 36 ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠሩ ዘንድ አንድ ሆኑ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ። 37 የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር። ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም።

2 ዜና መዋዕል 21

1 ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2 ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። 3 አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን በኵር ልጁ ስለ ሆነ ለኢዮራም ሰጠ። 4 ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ተነሥቶ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። 5 ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 6 የአክአብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 7 ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ስለ ሰጠው ተስፋ፥ እግዚአብሔር የዳዊትን ቤት ያጠፋ ዘንድ አልወደደም። 8 በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐመፀ፥ ለራሱም ንጉሥ አነገሠ። 9 ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ። 10 ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፥ በዚያንም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፥ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። 11 ዳግምም በይሁዳ ተራሮች ላይ መስገጃዎችን ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፥ ይሁዳንም አሳተው። 12 ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ጽሕፈት መጣባት። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ 13 በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ 14 እነሆ፥ እግዚአብሔር ሕዝብህንና ልጆችህን ሚስቶችህንም ያለህንም ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል። 15 አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትታመማለህ። 16 እግዚአብሔርን የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ። 17 ወደ ይሁዳም ወጡ፥ አፈረሱአትም፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም ሴቶች ልጆቹንም ማረኩ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አልቀረለትም። 18 ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር በማይፈወስ ደዌ አንጀቱን ቀሰፈው። 19 ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፥ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበር ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። 20 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሄደ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም።

2 ዜና መዋዕል 22

1 በኢየሩሳሌም የነበሩትም ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ገድለዋቸው ነበርና። የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 2 አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች። 3 እናቱም ክፉ ለማድረግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። 4 አባቱም ከሞተ በኋላ የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ እስኪጠፉ ድረስ መካሪዎች ነበሩትና። 5 በምክራቸውም ሄደ፥ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለአድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራንም አቈሰሉት። 6 ከሶርያም ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ያይ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ወረደ። 7 አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር እግዚአብሔር የአክዓብን ቤት ያጠፋ ዘንድ ወደ ቀባው ወደ ናሜሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ። 8 ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድን ሲፈጽም የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው። 9 አካዝያስንም ፈለገው፥ በሰማርያ ተሸሽጎ ሳለ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉትና። በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው ብለው ቀበሩት። ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥትን ይይዝ ዘንድ የሚችል አልነበረም። 10 የአካዝያስም እናት ጎቶሊያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን ቤተ መንግሥት ዘር ሁሉ አጠፋች። 11 የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ ጎቶሊያ እንዳታስገድለው የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዛያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት እንዲሁ ሸሸገችው። 12 በእነርሱም ዘንድ ተሸሽጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።

2 ዜና መዋዕል 23

1 በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፥ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛርያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 2 ይሁዳንም ዞሩ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3 ጉባኤውም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም አላቸው። እነሆ፥ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ልጆች እንደተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4 የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስት አንድ እጅ በመግቢያ በሮች በረኞች ሁኑ፤ 5 ከሦስት አንድ እጅም በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ አንድ እጅም በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6 ወደ እግዚአብሔር ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቅ። 7 ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ። 8 ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ። 9 ካህኑም ዮዳሄ በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10 ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11 የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፥ ምስክሩንም ሰጡት፥ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ ቀቡት። 12 ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 13 እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ ከንጉሡ ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች። 14 ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አትግደሉአት አለ። 15 ገለልም ብለው አሳለፉአት፤ እርስዋም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፥ በዚያም ገደሉአት። 16 ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ። 17 ሕዝቡም ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18 ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19 በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በእግዚአብሔር ቤት በር በረኞችን አኖረ። 20 የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረደ፤ በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አኖሩት። 21 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት። ች

2 ዜና መዋዕል 24

1 ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2 በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3 ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 4 ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። 5 ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ። ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፥ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ አላቸው። ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። 6 ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አላተጋሃቸውም? አለው። 7 ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና። 8 ንጉሡም አዘዘ፥ ሣጥንም ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። 9 የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። 10 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው አቀረቡት፥ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። 11 ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የዋነኛው ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፥ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፥ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። 12 ንጉሡና ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይገዙበት ነበር። 13 ሠራተኞችም ሠሩ፥ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፥ አጽንተውም አቆሙት። 14 በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። 15 ዮዳሄም ሸመገለ፥ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሳ ዓመት ነበረ። 16 ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። 17 ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ ንጉሡም እሺ አላቸው። 18 የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። 19 ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፥ እነርሱ ግን አላደመጡም። 20 የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል አላቸው። 21 ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። 22 እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት። እግዚአብሔር ይየው፥ ይፈልገውም አለ። 23 ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፥ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። 24 የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት። 25 ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታምሞ ነበር፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ዮዳሄ ልጅ ተበቅለው ተማማሉበት፥ በአልጋውም ላይ ገደሉት፥ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26 የተማማሉበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። 27 የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 25

1 አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ ነገር ግን በፍጹም ልብ አይደለም። 3 መንግሥትም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 4 በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም። ሰው ሁሉ በገዛ ኃጢያቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች ፋንታ አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች ፋንታ አይሙቱ ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮችን ልጆች አልገደለም። 5 አሜስያስም ይሁዳን ሰበሰበ፥ በእየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች እጅ በታች አቆማቸው፤ ከሀያ ዓመት ጀመሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ ቈጠረ፥ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች አገኘ። 6 ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7 አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ። ንጉሥ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ጋር አይደለምና የእስራኤል ጭፍራ ከአንተ ጋር አይውጣ። 8 ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የመርዳትና የመጣል ኃይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል አለው። 9 አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው። ለእስራኤል ጭፍራ የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሁን? አለው። የእግዚአብሔርም ሰው። ከዚህ አብልጦ ይሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ይችላል ብሎ መለሰለት። 10 አሜስያስም ከኤፍሬም የመጡት ጭፍሮች ወደ ስፍራቸው ይመለሱ ዘንድ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቍጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፥ ወደ አገራቸውም በጽኑ ቍጣ ተመለሱ። 11 አሜስያስም በረታ፥ ሕዝቡንም አውጥቶ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፥ ከሴይርም ልጆች አሥር ሺህ ገደለ። 12 የይሁዳም ልጆች ደግሞ አሥር ሺህ ሰዎችን በሕይወታቸው ማረኩ፥ ወደ ዓለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ ከዓለቱም ራስ ላይ ጣሉአቸው፥ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13 አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ሰልፍ እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮች ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሖሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ገደሉ፥ ብዙ ምርኮም ማረኩ። 14 አሜስያስም የኤዶምያስን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፥ የእርሱም አማልክት ይሆኑ ዘንድ አቆማቸው፥ ይሰግድላቸውም ያጥንላቸውም ነበር። 15 ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በአሜስያስ ላይ ነደደና። ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ስለ ምን ፈለግሃቸው? የሚል ነቢይ ሰደደበት። 16 እርሱም ሲናገር ንጉሡ። በውኑ አንተ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሾመነሃልን? ተው፤ ቅጣትን ስለ ምን ትሻለህ? አለው። ነቢዩም። ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ ብሎ ተወ። 17 የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ምክር አደረገና። ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ ላከ። 18 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮስያስ። የሊባኖስ ኵርንችት። ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወድ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 19 አንተም። እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ ብለህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻላህ? ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ። 20 የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22 ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፥ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 23 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24 ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ከዖቤድኤዶም ጋር የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ የንጉሡን ቤት መዛግብት፥ በመያዣ የተያዙትንም ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 25 የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26 የቀረውም የፊተኛውና የኋላኛው የአሜስያስ ነገር፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27 አሜስያስም እግዚአብሔርን ከመከተል ከራቀ በኋላ በኢየሩሳሌም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፥ ወደ ለኪሶም ኰበለለ፤ በስተ ኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፥ በዚያም ገደሉት። 28 በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።

2 ዜና መዋዕል 26

1 የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 2 ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት። 3 ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስድስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 4 አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 5 እግዚአብሔርንም መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት። 6 ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ። 7 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው። 8 አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ። 9 ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው። 10 ብዙም እንስሶች ነበሩበትና በምድረ በዳና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጕድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት። 11 ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊት ውስጥ ሰልፈኞች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቍጥራቸው ይወጡ ነበር። 12 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ። 13 ንጉሡንም በጠላቱ ላይ ያግዝ ዘንድ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ሰልፍ የሚወጣ፥ ከእጃቸው በታች የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። 14 ዖዝያንም ለጭፍራው ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቍርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። 15 በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚኖሩትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አደረገ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ። 16 ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ። 17 ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ገቡ። 18 ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ። ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብር አይሆንልህም አሉት። 19 ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። 20 ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም አባርረሩት፥ እርሱም ደግሞ እግዚአብሔር ቀሥፎት ነበርና ይወጣ ዘንድ ቸኰለ። 21 ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቈርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። 22 የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል። 23 ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ለምጻም ነው ብለውም ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 27

1 ኢዮአታምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ትባል ነበር። 2 አባቱም ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር መቅደስ አልገባም፤ ሕዝቡም ገና ይበድል ነበር። 3 የእግዚአብሔርን ቤት የላይኛውን በር ሠራ፥ በዖፌልም ቅጥር ላይ እጅግ ሠራ። 4 በተራራማውም በይሁዳ አገር ላይ ከተሞችን ሠራ፥ በዱር ስፍራዎችም አምባዎችንና ግንቦችን ሠራ። 5 ከአሞንም ልጆች ንጉሥ ጋር ተዋጋ አሸነፋቸውም። በዚያም ዓመት የአሞን ልጆች መቶ መክሊት ብር፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መሥፈሪያ ገብስ ሰጡት። እንዲሁም ደግሞ የአሞን ልጆች በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ሰጡት። 6 ኢዮአታምም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መንገዱን አቅንቶአልና በረታ። 7 የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ ሰልፉም ሁሉ፥ ሥራውም፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 8 መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ። 9 ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 28

1 አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 2 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፥ ደግሞም ለበኣሊም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችን ሠራ። 3 ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ዐጠነ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። 4 በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5 ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም መቱት፥ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞች ወስደው ወደ ደማስቆ አመጡ። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ አመታት መታው። 6 የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ነበርና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሀያ ሺህ ገደለ፤ ሁሉም ጽኑዓን ነበሩ። 7 ከኤፍሬምም ወገን የነበረው ኃያል ሰው ዝክሪ የንጉሡን ልጅ መዕሤያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕርግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8 የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሁለት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፥ እጅግም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ። 9 በዚያም ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ገደላችኋቸው። 10 አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌም ልጆች ባሪያዎች ሆነው ይገዙላችሁ ዘንድ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን? 11 አሁንም ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ። 12 ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የምሺሌሞትም ልጅ በራክያ፥ የሰሎምም ልጅ ይሒዝቅያ፥ የሐድላይም ልጅ ዓሜሳይ ከሰልፍ በተመለሱት ላይ ተቃወሙአቸው። 13 ደግሞም። በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኃጢያታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የመቅሰፍቱም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነውና አሉአቸው። 14 ሰልፈኞቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤ ሁሉ ፊት ተዉ። 15 በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፥ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፥ አጎናጸፉአቸውም፥ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፥ መገቡአቸውም፥ አጠጡአቸውም፥ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፥ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማርያም ተመለሱ። 16 በዚያን ጊዜም ንጉሡ አካዝ እርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ 17 የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። 18 ደግሞም ፍልስጥኤማውያን በቈላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ግዴሮትንም፥ ሦኮንና መንደሮችዋን፥ ተምናንና መንደሮችዋን፥ ጊምዞንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። 19 የይሁዳም ንጉሥ አካዝ እግዚአብሔርን ክዷልና፥ ከእርሱም እጅግ ርቆአልና እግዚአብሔር ስለ እርሱ ይሁዳን አዋረደው። 20 የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። 21 አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት እኵሌታውን ገፈፈ፥ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፤ ነገር ግን አንዳች አልተጠቀመበትም። 22 ይህም ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜ እግዚአብሔርን መበደል አበዛ። 23 ለመቱትም ለደማስቆ አማልክት። የሶርያን ነገሥታት አማልክት ረድተዋቸዋልና እኔን ይረዱ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ ብሎ ሠዋላቸው። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ እንቅፋት ሆኑ። 24 አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጅ ቈለፈ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ መሠዊያ ሠራ። 25 በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎች አሠራ፤ የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ። 26 የቀረውም ነገርና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኛውና የኋለኛው፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 27 አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በከተማይቱም በኢየሩሳሌም ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 29

1 ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር። 2 አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 3 በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፥ አደሳቸውም። 4 ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፥ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፥ 5 እንዲህም አላቸው። ሌዋውያን ሆይ፥ ስሙኝ፤ ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6 አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፥ 7 ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። 8 ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። 9 እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ። 10 አሁንም የቍጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ። 11 ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ። 12 ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዩአክና የዩአክ ልጅ ዔድን፥ 13 14 ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ። 15 ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ በእግዚአብሔር ቃል እንደመጣው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ገቡ። 16 ካህናቱም ያነጹት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፥ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። 17 በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀደሱ ጀመር፥ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን ቀደሱ፥ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። 18 ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው። የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መስዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ 19 ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል አሉት። 20 ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ። 21 ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢያት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን። በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አሳረጉአቸው አላቸው። 22 ወይፈኖቹንም አረዱ፥ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፥ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23 የኃጢያትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፥ እጃቸውንም ጫኑባቸው፥ ካህናቱም አረዱአቸው፤ 24 ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢያት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተስረያ ያደርጉ ዘንድ የኃጢያቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ። 25 ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ። 26 ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። 27 ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ። 28 ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ሆነ። 29 ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም። 30 ንጉሡም ሕዝቅያስና አለቆቹ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፥ አጐነበሱም ሰገዱም። 31 ሕዝቅያስም። አሁን ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፥ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መስዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። 32 ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 33 የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበረ። 34 ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። 35 የሚቃጠለውም መሥዋዕት የደኅንነቱም መሥዋዕት ስብ፥ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ሁሉ ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን፥ ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። 36 ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ።

2 ዜና መዋዕል 30

1 ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፥ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤ ጻፈ። 23 ካህናቱም በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉምና ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተመካክረው ነበር። 4 ነገሩም ለንጉሡና ለጉባኤው ሁሉ ዓይን መልካም ነበረ። 5 እንደ ተጻፈም በብዙ ቍጥር አላደረጉም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ያደርጉ ዘንድ እንዲመጡ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። 6 እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የአለቆቹን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠ ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ እስራኤልም አምላክ ተመለሱ። 7 እናንተም እንደምታዩ የተፈቱ እስኪያደርጋቸው ድረስ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8 አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፥ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቍጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ። 9 አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ። 10 መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፥ አፌዙባቸውም። 11 ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። 12 ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የአለቆቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ሆነ። 13 በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ያደርግ ዘንድ እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተከማቸ። 14 ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፥ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። 15 በሁለተኛውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም አፈሩ፥ ተቀደሱም፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። 16 እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በሥርዓታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። 17 በጉባኤውም ያልተቀደሱ እጅግ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ይቀድሱአቸው ዘንድ ንጹሐን ላልሆኑት ሁሉ ፋሲካውን ያርዱላቸው ነበር። 18 እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። 19 ሕዝቅያስም። ምንም እንደ መቅደሱ ማንጻት ባይነጻ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው ብሎ ስለ እነርሱ ጸለየ። 20 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፥ ሕዝቡንም ፈወሰ። 21 በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 22 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያንን ሁሉ ያጽናና ነበር። የደኅንነትንም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 23 24 የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችና ሰባት ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥቶ ነበርና፥ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችና አሥር ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥተው ነበርና፥ ከካህናቱም እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና ጉባኤው ሁሉ እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ፤ በደስታም እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 25 የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም አገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። 26 በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር። 27 ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምፃቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ መኖሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ።

2 ዜና መዋዕል 31

1 ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉን ፈጽመው እስካጠፉአቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ። 2 ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ያገለግሉም ዘንድ፥ ያመሰግኑም ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ። 3 በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፍለውን ወሰነ። 4 በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5 ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በኵራት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት አብዝተው አቀረቡ። 6 በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አኖሩት። 7 በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8 ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ። 9 ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10 ከሳዶቅም ወገን የሆነ ዋነኛው ካህን ዓዛሪያስ። ሕዝቡ ቍርባኑን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው ብሎ ተናገረ። 11 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤት ጐተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12 ቍርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡት። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13 በንጉሡም በሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14 የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በፈቃድ ባቀረቡት ላይ ተሾመ። 15 በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ ከእጁ በታች ነበሩ። 16 ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸው ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤ 17 በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሀያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥ 18 በማኅበሩም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሕፃናቶቻቸውና ለሚስቶቻቸው ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ተቀድሰዋልና። 19 በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰምርያዎቹ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ። 20 ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ። 21 ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም። ቸ

2 ዜና መዋዕል 32

1 ከዚህም ነገርና ከዚህ እምነት በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፥ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፥ ሊወስዳቸውም አሰበ። 2 ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን አንዳቀና ባየ ጊዜ፥ 3 ከከተማይቱ በስተ ውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ይደፍኑ ዘንድ ከአለቆቹና ከኃያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት። 4 እጅግም ሰዎች ተሰብስበው። የአሦር ነገሥታት መጥተው ብዙ ውኃ ስለ ምን ያገኛሉ? ብለው ምንጩን ሁሉ፥ በምድርም መካከል ይንዶለዶል የነበረውን ወንዝ ደፈኑ። 5 ሰውነቱንም አጸናና፥ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፥ በላዩም ግንብ ሠራበት፥ ከእርሱም በስተ ውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ በዳዊትም ከተማ ያለችውን ሚሎን አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ ሠራ። 6 የጦር አለቆቹንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ፥ ሁሉንም በከተማይቱ በር ወዳለው አደባባይ ሰብስቦ። 7 ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። 8 ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና። 9 ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ፊት ሳለ ባሪያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ። 10 የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል። እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? 11 አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል እያለ በራብና በጥም እንድትሞቱ አሳልፎ ይሰጣችሁ ዘንድ የሚያባብላችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? 12 በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፥ በእርሱም ላይ ዕጠኑ እያለ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አዝዞ፥ የኮረብታው መስገጃዎቹና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? 13 እኔና አባቶቼ በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት አገራቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ በውኑ ተቻላቸውን? 14 አምላካችሁስ ከእጄ እናንተን ለማዳን ይችል ዘንድ አባቶቼ ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ የቻለ ማን ነው? 15 አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፥ እንዲህም አያባብላችሁ፥ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶቼ እጅ ያድን ዘንድ ዘንድ ማንም አልቻለም፤ ይልቁንስ አምላካችሁ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ እንዴት ይችላል? 16 ባሪያዎቹም ደግሞ በአምላክ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17 ደግሞም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመስደብ፥ በእርሱም ላይ ለመናገር። የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ አይችልም የሚል ደብዳቤ ጻፈ። 18 ከተማይቱንም እንዲወስዱ፥ በቅጥር ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌም ሕዝብ ያስፈሩና ያስደነግጡ ዘንድ፥ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኹባቸው ነበር። 19 በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ አንደሚናገሩ መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገሩ። 20 ንጉሡም ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ጸለዩ፥ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21 እግዚአብሔርም ጽኑዓን ኃያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር እንዲያጠፋ መልአኩን ሰደደ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከወገቡ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22 እንዲሁም እግዚአብሔር ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከሰናክሬም እጅ ከሁሉም እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። 23 ብዙዎቹም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፥ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በአሕዛብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ። 24 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስኪሞት ድረስ ታመመ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ተናገረው፥ ምልክትም ሰጠው። 25 ሕዝቅያስ ግን እንደ ተቀበለው ቸርነት መጠን አላደረገም፥ ልቡም ኰራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ። 26 ሕዝቅያስም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም። 27 ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ለከበረው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶች ሠራ። 28 ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንስሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። 29 እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ሠራ፥ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። 30 ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፥ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። የሕዝቅያስም ሥራ ሁሉ ተከናወነ። 31 ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በአገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው። 32 የሕዝቅያስም የቀረው ነገር፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 33 ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

2 ዜና መዋዕል 33

1 ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። 2 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3 አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታውን መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊምም መሠዊያ ሠራ፥ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፥ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፥ አመለካቸውም። 4 እግዚአብሔርም። ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘላለም ይኖራል ባለው በእግዚአብሔር ቤት መሠዊያዎችን ሠራ። 5 በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6 በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አሳለፈ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፥ አስማትም አደረገ፥ መተተኛም ነበረ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። 78 እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን። በዚህ ቤት ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ በሙሴ የተሰጠውን ሕግና ሥርዓት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላርቅም ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሠራውን የጣዖት የተቀረጸውን ምስል አቆመ። 9 ምናሴም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ። 10 እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። 11 ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፥ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12 በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፥ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ፥ 13 ወደ እርሱም ጸለየ፤ እርሱም ተለመነው፥ ጸሎቱንም ሰማው፥ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ አወቀ። 14 ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተ ውጭው ከግዮን ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሳ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። በዖፌልም አዞረበት፥ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። 15 እንግዶችንም አማልክትና ጣዖቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፥ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማይቱ በስተ ውጭ ጣላቸው። 16 የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፥ የደኅንነትና የምስጋናም መሥዋዕት ሠዋበት፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ። 17 ሕዝቡ ግን ገና በኮረብታው መስገጃዎች ይሠዋ ነበር፤ ቢሆንም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር። 18 የምናሴም የቀረው ነገር፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት የነቢያት ቃል፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። 19 ደግሞም ጸሎቱ፥ እግዚአብሔርም እንደ ተለመነው፥ ኃጢያቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ራሱንም ሳያዋርድ የኮረብታው መስገጃዎችን የሠራበት የማምለኪያ ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 20 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቤቱም ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 21 አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። 22 አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፥ አመለካቸውም። 23 አባቱም ምናሴ ሰውነቱን እንዳዋረደ በእግዚአብሔር ፊት አንዳላዋረደ በእግዚአብሔርም ሰውነቱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ። 24 ባሪያዎቹም ተማምለው በቤቱ ገደሉት። 25 የአገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ የተማማሉትን ሁሉ ገደሉ፤ የአገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ።

2 ዜና መዋዕል 34

1 ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም። 3 በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በአሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሠሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። 4 የበኣሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሱ፤ በላዩም የነበሩትን የፀሐዩን ምስሎች የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረጹትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። 5 የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አንጻ። 6 የምናሴንና የኤፍሬምንም የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። 7 መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረጹትን ምስሎች አደቀቀ፥ በእስራኤልም አገር ሁሉ የፀሐይን ምስሎች ሁሉ ቈራረጠ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። 8 በነገሠም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። 9 ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚእብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። 10 የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡ። 11 የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ። 12 ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚያሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ 13 በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ። 14 ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስም በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15 ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን። የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16 ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም። ባሪያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ ያደርጋሉ፤ 17 በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ ብሎ አወራለት። 18 ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 19 ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20 ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን። 21 በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው። 22 ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሥ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንም ነገር ነገሩአት። 23 እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። 24 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አመጣለሁ። 25 በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። 26 እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ገር ሆኖአልና፥ 27 በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አለቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 28 እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሥ አወሩለት። 29 ንጉሡም ላከ፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። 30 ንጉሡም የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 31 ንጉሡም በስፍራው ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። 32 በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዳዘዘ አደረጉ። 33 ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ፥ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል አልራቁም።

2 ዜና መዋዕል 35

1 ኢዮስያስም ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ። 2 ካህናቱንም በየሥርዓታቸውም አቆመ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። 3 እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ። ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት፤ ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ 4 የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ ጻፈው ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፈው በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ 5 እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ፤ የሌዋውያንም ነገድ በየወገናቸው እንደ ተከፈሉ እናንተ ተከፈሉ፤ ፋሲካውንም እረዱ፥ 6 እናንተም ተቀደሱ፥ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ያደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ። 7 ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። 8 መሳፍንቱም ለሕዝቡና ለካህናቱ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቂያስ፥ ዘካሪያስ፥ ይሒኤል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችና ፍየሎች፥ ሦስት መቶም በሬዎች ለካህናቱ ሰጡ። 9 የሌዋውያኑም አለቆች ኮናንያ፥ ወንድሞቹም ሸማያና ናትናኤል፥ ሐሸቢያ፥ ይዒኤል፥ ዮዛባት ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችና ፍየሎች፥ አምስት መቶም በሬዎች ለሌዋውያን ሰጡ። 10 አገልግሎቱም ተዘጋጀ፥ ካህናቱም በስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሥ ትእዛዝ ቆሙ። 11 ፋሲካውንም አረዱ፥ ሌዋውያኑም ቁርበቱን ገፈፉ፥ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ። 12 በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። 13 ፋሲካውንም እንደ ሥርዓቱ በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ በድስትም ቀቀሉ፥ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። 14 ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። 15 የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሣፍም እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶታም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር። 16 እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። 17 የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣ በዓልን አደረጉ። 18 ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። 19 ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ። 20 ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ ላይ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። 21 እርሱም። የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። 22 ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጸናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፥ በመጊዶም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። 23 ቀስተኞችም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴናዎቹን። አጥብቄ ቈስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ አላቸው። 24 ብላቴኖቹም ከሰረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት፥ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም ሞተ፥ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25 ኤርምያስም ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። 26 የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ 27 የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።

2 ዜና መዋዕል 36

1 የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት። 2 ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። 3 የግብጽም ንጉሥ በኢየሩሳሌም ከመንግሥቱ አወጣው፥ መቶም መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ዕዳ ጣለበት። 4 የግብጽም ንጉሥ ወንድሙን ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠ፤ ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው። 5 ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 6 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ መጥቶ ወደ ባቢሎን ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። 7 ናቡከደነፆርም ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አያሌውን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፥ በባቢሎንም በመቅደሱ ውስጥ አኖረው። 8 የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ ያደረገውም ርኵሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ ልጁም ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 9 ዮአኪንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወርና አሥር ቀን ነገሠ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 10 ዓመቱ ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፥ የከበረውንም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ ወንድሙንም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ። 11 ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። 12 በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም አፍ በተናገረው በነቢዩ በኤርሚያስ ፊት ራሱን አላወረደም። 13 ደግሞም በእግዚአብሔር አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ ልቡንም አጠነከረ። 14 ደግሞም የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝቡም እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም የቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ። 15 የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። 16 እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር። 17 ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው። 18 የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ። 19 የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፥ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፥ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ። 20 ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤ 21 በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች። 22 በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። 23 የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም ይውጣ ብሎ በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አደረገው።

ዕዝራ 1

1 በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ። 2 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ 3 ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤ 4 በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን። 5 የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ። 6 በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ በገንዘቦችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው። 7 ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ። 8 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው። 9 ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ አንድ ሺህም የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝም ቢላዎች፥ 10 ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥርም ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ። 11 የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ።

ዕዝራ 2

1 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው። 2 ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከሠራያ፥ ከረዕላያ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከበላሳን፥ ከመሴፋር፥ ከበጉዋይ፥ ከሬሁም፥ ከበዓና ጋር መጡ። 3 የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤ የፋሮስ ልጆች፥ ሁለት ሺህ መቶ ሰባ ሁለት። 4 የሰፋጥያስ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት። 5 የኤራ ልጆች፥ ሰባት መቶ ሰባ አምስት። 6 ከኢያሱና ከኢዮአብ ልጆች የሆኑ የፈሐት ሞዓብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ሁለት። 7 የኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። 8 የዛቱዕ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ አርባ አምስት። 9 የዘካይ ልጆች ሰባት መቶ ስድሳ። 10 የባኒ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት። 11 የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ሦስት። 12 የዓዝጋድ ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ ሀያ ሁለት። 13 የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት። 14 የበጉዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ አምሳ ስድስት። 15 የዓዲን ልጆች፥ አራት መቶ አምሳ አራት። 16 ከሕዝቅያስ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት። 17 የቤሳይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ ሦስት። 18 የዮራ ልጆች፥ መቶ አሥራ ሁለት። 19 የሐሱም ልጆች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት። 20 21 የጋቤር ልጆች፥ ዘጠና አምስት። የቤተ ልሔም ልጆች፥ መቶ ሀያ ሦስት። 22 የነጦፋ ሰዎች፥ አምሳ ስድስት። 23 የዓናቶት ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት። 24 የዓዝሞት ልጆች፥ አርባ ሁለት። 25 የቂርያትይዓሪምና የከፊራ የብኤሮትም ልጆች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት። 26 የራማና የጌባ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ። 27 የማክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት። 28 የቤቴልና የጋይ ሰዎች፥ ሁለት መቶ ሀያ ሦስት። 29 የናባው ልጆች፥ አምሳ ሁለት። 30 የመጌብስ ልጆች፥ መቶ አምሳ ስድስት። 31 የሁለተኛውም ኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። 32 የካሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ። 33 የሎድና የሐዲድ የኦኖም ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አምስት። 34 የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት። 35 የሴናዓ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ። 36 ካህናቱ፤ ከኢያሱ ወገን የዮዳኤ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት። 37 የኢሜር ልጆች፥ ሺህ አምሳ ሁለት። 38 የፋስኮር ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት። 39 የካሪም ልጆች፥ ሺህ አሥራ ሰባት። 40 ሌዋውያኑ፤ ከሆዳይዋ ወገን የኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ ሰባ አራት። 41 መዘምራኑ፤ የአሳፍ ልጆች፥ መቶ ሀያ ስምንት። 42 የበረኞች ልጆች፤ የሰሎም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሶባይ ልጆች፥ ሁሉ መቶ ሠላሳ ዘጠኝ። 43 ናታኒም፤ የሲሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥ 44 የጠብዖት ልጆች፥ የኬራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፤ 45 የፋዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥ 46 የአጋባ ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የአጋብ ልጆች፥ የሰምላይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥ 47 የጌዴል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥ የራያ ልጆች፥ 48 የረአሶን ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ 49 የጋሴም ልጆች፥ የዖዛ ልጆች፥ የፋሴሐ ልጆች፥ 50 የቤሳይ ልጆች፥ የአስና ልጆች፥ የምዑናውያን ልጆች፥ የንፉሰሲም ልጆች፥ 51 የበቅቡቅ ልጆች፥ የሐቁፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥ 52 የበስሎት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥ 53 የሐርሳ ልጆች፥ የበርቆስ ልጆች፥ 54 የሲሣራ ልጆች፥ የቴማ ልጆች፥ የንስያ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች። 55 የሰሎሞንም ባሪያዎች ልጆች፤ የሶጣይ ልጆች፥ የሶፌሬት ልጆች፥ የፍሩዳ ልጆች፥ 56 የየዕላ ልጆች፥ የደርቆን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥ 57 የሰፋጥያስ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፈክራት ልጆች፥ የሐፂቦይም ልጆች፥ የአሚ ልጆች። 58 እነዚህ ናታኒም ሁሉና የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ። 59 ከቴልሜላ፥ ከቴላሬሳ፥ ከክሩብ፥ ከአዳን፥ ከኢሜር የወጡ እነዚህ ነበሩ፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤ 60 የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ነበሩ። 61 ከካህናቱም ልጆች፤ የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ፥ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች። 62 እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፤ ነገር ግን አልተገኘም፥ ከክህነትም ተከለከሉ። 63 ሐቴርሰታም። በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ድረስ ከቅዱሰ ቅዱሳን አትበሉም አላቸው። 64 65 ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ከነበሩ ከሎሌዎቻቸውና ከገረዶቻቸው ሌላ ጉባኤው ሁሉ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ። ሁለት መቶም ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩአቸው። 66 ፈረሶቻቸውም ሰባት መቶ ሠላሳ ስድስት በቅሎቻቸውም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥ 67 ግመሎቻቸውም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸውም ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ። 68 በኢየሩሳሌምም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ ጊዜ ከአባቶች ቤቶች አለቆች አያሌዎች ለእግዚአብሔር ቤት በስፍራው ይሠራ ዘንድ በፈቃዳቸው ሰጡ። 69 ስድሳ አንድ ሺህም የወርቅ ዳሪክ፥ አምስት ሺህም ምናን ብር፥ አንድ መቶም የካህናት ልብስ እንደ ችሎታቸው ወደ ሥራው ቤተ መዛግብት አቀረቡ። 70 ካህናቱና ሌዋውያኑም፥ ከሕዝቡም አያሌዎች፥ መዘምራኑና በረኞቹም፥ ናታኒምም በከተሞቻቸው፥ እስራኤልም ሁሉ በከተሞቻቸው ተቀመጡ።

ዕዝራ 3

1 ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ልጆች በከተሞቻቸው ሳሉ፥ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 2 የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቹም ካህናቱ፥ የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል ወንድሞቹም ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ። 3 በአገሩም ካሉት አሕዛብ ፈርተው ነበርና መሠዊያውን በስፍራው ላይ አስቀመጡት፥ በጥዋትና በማታም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡበት። 4 እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለየዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ። 5 ከዚያም በኋላ ዘወትር የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የመባቻውንም መሥዋዕት፥ የተቀደሱትንም የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት፥ ሰውም ሁሉ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የሰጠውን ቍርባን አቀረቡ። 6 በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ ገና አልተመሠረተም ነበር። 7 ለጠራቢዎችና ለአናጢዎችም ገንዘብ ሰጡ፤ የፋርስም ንጉሥ ቂሮስ እንደ ፈቀደላቸው የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ በባሕር ወደ ኢዮጴ ያመጡ ዘንድ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎች መብልና መጠጥ ዘይትም ሰጡ። 8 በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዩሴዴቅም ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ወንድሞቻቸው ካህናትና ሌዋውያን፥ ወደ ኢየሩሳሌምም የተመለሱት ምርኮኞች ሁሉ ጀመሩ፤ ሌዋውያንንም ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲያሠሩት ሾሙአቸው። 9 ኢያሱም ልጆቹም ወንድሞቹም፥ የይሁዳም ልጆች ቀድምኤልና ልጆቹ፥ የኤንሐዳድም ልጆች፥ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ያሠሩ ዘንድ በአንድነት ቆሙ። 10 አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ። 11 ደግሞ። ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እያሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በእርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ። 12 የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች የሆኑ ብዙ ካህናትና ሌዋውያን የአባቶችም ቤቶች አለቆች ግን ይህ መቅደስ በፊታቸው በተመሠረተ ጊዜ በታላቅ ድምፅ ያለቅሱ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም በደስታ ይጮኹ ነበር፤ 13 ደስ ብሎአቸው የሚጮኹትን ድምፅ ከሕዝቡ ልቅሶ ድምፅ መለየት የሚችል አልነበረም፤ ሕዝቡም በታላቅ ድምፅ ይጮኽ ነበር፥ ድምፁም ከሩቅ ይሰማ ነበር።

ዕዝራ 4

1 የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መቅደስ እንደ ሠሩ ሰሙ። 2 ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች ቤቶች አለቆች ቀርበው። የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለአምላካችሁ እንሠዋለንና፥ እንደ እናንተም እንፈልገዋለንና ከእናንተ ጋር እንሥራ አሉአቸው። 3 ዘሩባቤልና ኢያሱም የቀሩትም የእስራኤል አባቶች ቤቶች አለቆች። የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ለብቻችን ግን የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን አሉአቸው። 4 የምድሩም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይሠሩም አስፈራሩአቸው፥ 5 ምክራቸውንም ያፈርሱ ዘንድ በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ዘመን ሁሉ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት ድረስ መካሪዎችን ገዙባቸው። 6 በአርጤክስስም መንግሥት፥ በመንግሥቱም በመጀመሪያ ዘመን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ የክስ ነገር ጻፉ። 7 በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትሪዳጡ፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ለፋርስ ንጉሥ ለአርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። 8 አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ። 9 አዛዡ ሬሁም ጸሐፊውም ሲምሳይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዲናውያን፥ አፈርሳትካውያን፥ ጠርፈላውያን፥ አፈርሳውያን፥ አርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱስናካውያን፥ ዴሐውያን፥ ኤላማውያን፥ 10 ታላቁና ኃይለኛው አስናፈር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ። 11 ለንጉሡ ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው። በወንዝ ማዶ ያሉት ሰዎች ባሪያዎችህ፤ 12 አሁንም ከአንተ ዘንድ የወጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጡ ንጉሡ ይወቅ፤ ዓመፀኛይቱንና እጅግም የከፋቺቱን ከተማ ይሠራሉ፥ ቅጥርዋንም ያድሳሉ፥ መሠረትዋንም ጠገኑ። 13 አሁንም ይህች ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ የንጉሡም ግቢው እንዲጐድል ንጉሡ ይወቅ። 14 የንጉሡንም ጨው እንበላለንና፥ ንጉሡንም ሲያቃልሉት ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታውቀናል፤ 15 በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ፤ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርስዋ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። 16 ይህችም ከተማ የተሠራች እንደ ሆነ፥ ቅጥርዋም የታደሰ እንደ ሆነ፥ በወንዝ ማዶ ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን። 17 ንጉሡም ለአዛዡ ለሬሁም፥ ለጸሐፊውም ለሲምሳይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶም ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ። 18 ሰላም፤ አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነበበ። 19 እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፤ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርስዋም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። 20 በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። 21 አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም እስካዝዝ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። 22 ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለ ምን ይሄዳል? 23 የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሁምና በጸሐፊው በሲምሳይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። 24 በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተጓጐለ።

ዕዝራ 5

1 ነቢያቱም ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። 2 በዚያን ጊዜ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 3 በዚያም ዘመን በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንኑም ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? አሉአቸው። 4 ደግሞም። ይህንስ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ስም ማን ነው? ብለው ጠየቁአቸው። 5 የአምላካቸው ዓይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፥ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም። 6 በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቹም በወንዙ ማዶ የነበሩት አፈርስካውያን ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነበረ። 7 እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት። ለንጉሡ ለዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤ 8 ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁም አምላክ ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፥ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፥ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፥ በእጃቸውም ይከናወናል። 9 እነዚያንም ሽማግሌዎች። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንስ ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? ብለን ጠየቅናቸው። 10 ደግሞም እናስታውቅህ ዘንድ፥ በእነርሱም ያሉትን ሹሞች ስም እንጽፍልህ ዘንድ ስማቸውን ጠየቅን። 11 እንደዚህም ብለው መለሱልን። እኛ የሰማይና የምድር አምላክ ባሪያዎች ነን፥ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረውን፥ ታላቁም የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የፈጸመውን ቤት እንሠራለን። 12 አባቶቻችንም የሰማይን አምላክ ካስቈጡ በኋላ በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፥ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። 13 ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ። 14 ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያፈለሰውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅንና የብርን ዕቃ ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ሰሳብሳር ለተባለው ለሹሙ ሰጠውና። 15 ይህን ዕቃ ይዘህ ሂድ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ አኑረው፤ የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ አለው። 16 በዚያ ጊዜም ይህ ሰሳብሳር መጣ፥ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ አልተጨረሰም። 17 አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዓይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደ ሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፤ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።

ዕዝራ 6

1 በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ። 2 በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፥ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር። 3 በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን። 4 በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ውጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። 5 ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር። 6 አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን፥ ከዚያ ራቁ፤ 7 ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው። 8 ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ። 9 ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። 10 ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው። 11 ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ። 12 ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም። 13 ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ። 14 የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። 15 ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። 16 የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። 17 በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። 18 በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑም በየክፍላቸው አቆሙ። 19 ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። 20 ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ። 21 ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤ 22 እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።

ዕዝራ 7

1 ከዚህም ነገር በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥ 2 የዓዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ የሰሎም ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥ 3 የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ 4 የዘራእያ ልጅ፥ የኦዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ 5 የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤ 6 የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ የሻውን ሁሉ ሰጠው። 7 ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም ከሌዋውያኑም ከመዘምራኑም ከበረኞቹም ከናታኒምም በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት አያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 8 በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። 9 በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጣ ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10 ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር። 11 ንጉሡም አርጤክስስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው። 12 ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሙሉ ሰላም ይሁን፤ 13 በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ የሚወድድ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ። 14 በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ትጐበኝ ዘንድ፥ 15 ንጉሡንና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥ 16 በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ በንጉሡና በሰባቱ አማካሪዎች ተልከሃልና፤ 17 ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወደፈኖችንና አውራ በጎችን ጠቦቶችንም የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። 18 ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ። 19 ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ። 20 ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት አውጣ። 21 እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤ 22 እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ። 23 በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ለሰማይ አምላክ ቤት በሙሉ ይደረግ። 24 ደግሞም በካህናቱና በሌዋውያን በመዘምራኑም በበረኞቹም በናታኒምም በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይጣል ብለን እናስታውቃችኋለን። 25 አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ባሉ ሕዝብ ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ዳኞችንና ፈራጆች አስነሣ፤ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው። 26 የአምላክህንም ሕግ፥ የንጉሡንም ሕግ በማያደርግ ሁሉ ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ገንዘብን መወረስ ወይም ግዞት በፍጥነት ይፈረድበት። 27 28 በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያሳምር ዘንድ እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ በንጉሡም በአማካሪዎቹም በንጉሡም ኃያላን አለቆች ሁሉ ፊት ምሕረቱን ወደ እኔ የላከ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። እኔም በላዬ ባለችው በአምላኬ በእግዚአብሔር እጅ በረታሁ፤ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል ዘንድ አለቆችን ሰበሰብሁ።

ዕዝራ 8

1 በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች ቤቶች አለቆች እነዚህ ናቸው ትውልዳቸውም ይህ ነው፤ 2 ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶን፥ ከኢታምር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡስ፥ ከሴኬንያ ልጆች፥ 3 ከፋሮስ ልጆቾ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር መቶ አምሳ ወንዶች በትውልድ ተቈጠሩ። 4 ከፋሐት ሞዓብ ልጆች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች። 5 ከሴኬንያ ልጆች የየሕዚኤል ልጅ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች። 6 ከዓዲን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋር አምሳ ወንዶች። 7 ከኤላም ልጆች የጎቶልያ ልጅ የሻያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። 8 የሰፋጥያስ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች። 9 ከኢዮአብ ልጆች የይሒኤል ልጅ አብድዩ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ አሥራ ስምንት ወንዶች። 10 ከሰሎሚት ልጆች የዮሲፍያ ልጅ፥ ከእርሱም ጋር መቶ ስድሳ ወንዶች። 11 ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሀያ ስምንት ወንዶች። 12 ከዓዝጋድ ልጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር መቶ አሥር ወንዶች። 13 ከኋለኞቹ ከአዶኒቃም ልጆች ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፥ ይዑኤል፥ ሸማያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች። 14 ከበጉዋይ ልጆች ዑታይና ዘቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች። 15 ወደ አኅዋም ወደሚፈስስ ወንዝ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስቈጥራቸው በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም። 16 ወደ አለቆቹም ወደ አልዓዛር፥ ወደ አርኤል፥ ወደ ሸማያ፥ ወደ ኤልናታን፥ ወደ ያሪብ፥ ወደ ኤልናታን፥ ወደ ናታን፥ ወደ ዘካርያስ፥ ወደ ሜሱላም፥ ደግሞም ወደ አዋቂዎቹ ወደ ዮያሪብና ወደ ኤልናታን ላክሁ። 17 በካሲፍያ ስፍራ ወደ ነበረው ወደ አለቃው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ ለአምላካችን ቤት አገልጋዮችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለአዶና ለወንድሞቹ ለናታኒም የሚነግሩአቸውን በአፋቸው አደረግሁ። 18 በላያችንም መልካም በሆነው በአምላካችን እጅ ከእስራኤል ልጅ ከሌዊ ልጅ ከሞሖሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሰራብያን፥ ከእርሱም ጋር አሥራ ስምንቱን ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን። 19 ደግሞም ሐሸብያን ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን የሻያንና ሀያውን ወንድሞቹንና ልጆቻቸውን። 20 ሌዋውያንንም እንዲያገለግሉ ዳዊትና አለቆቹ ከሰጡአቸው ናታኒም ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ ናታኒም አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በስም በስማቸው ተጠሩ። 21 በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ። 22 ንጉሡንም። የአምላካችን እጅ በሚሹት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፤ ኃይሉና ቍጣው ግን እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው ብለን ተናግረን ነበርና በመንገድ ካለው ጠላት ያድኑን ዘንድ ጭፍራና ፈረሰኞች ከንጉሡ እለምን ዘንድ አፍሬ ነበርና። 23 ስለዚህም ነገር ጾምን፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱም ተለመነን። 24 ከካህናቱም አለቆች አሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሰራብያንና ሐሸቢያን ከእነርሱም ጋር አሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤ 25 ንጉሡና አማካሪዎቹ አለቆቹም በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ ያቀረቡትን ለአምላካችን ቤት የቀረበውን ብሩንና ወርቁን ዕቃውንም መዝኜ ሰጠኋቸው። 26 ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶም መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶም መክሊት ወርቅ፥ 27 ሀያም ባለሺህ ዳሪክ የወርቅ ጽዋዎች፥ ሁለትም እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩ ከሚያንጸባርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠሁ። 28 እኔም። እናንተ ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፥ ዕቃዎቹም ቅዱስ ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የቀረበ ነው፤ 29 በካህናትና በሌዋውያን አለቆች በእስራኤልም አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት ጓዳዎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ አልኋቸው። 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ይወስዱት ዘንድ ብሩንና ወርቁን ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ። 31 በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም እንሄድ ዘንድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ በመንገድም ከጠላትና ከሚሸምቅ ሰው እጅ አዳነን። 32 ወደ ኢየሩሳሌም ደረስን፥ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን። 33 በአራተኛውም ቀን ብሩና ወርቁ ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኦርዮ ልጅ በሜሪሞት እጅ ተመዘኑ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያን የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። 34 ሁሉም በቍጥርና በሚዛን ተመዘነ፤ ሚዛኑም ሁሉ በዚያን ጊዜ ተጻፈ። 35 ከምርኮም የወጡት ምርኮኞች ለእስራኤል አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስትም አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባትም ጠቦቶች፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 36 የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዙ ማዶ ላሉት ለንጉሡ ሹማምቶችና ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ።

ዕዝራ 9

1 ይህም ከተፈጸመ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው። የእስራኤል ሕዝብ ካህናቱም ሌዋውያኑም እንደ ከነዓናውያን እንደ ኬጢያውያን እንደ ፌርዛውያን እንደ ኢያቡሳውያን እንደ አሞናውያን እንደ ሞዓባውያን እንደ ግብጻውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤ 2 ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፥ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹማምቶቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል አሉኝ። 3 ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፥ የራሴንና የጢሜንም ጠጉር ነጨሁ፥ ደንግጬም ተቀመጥሁ። 4 ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ። 5 በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ። 6 እንዲህም አልሁ። አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፥ እፈራማለሁ። 7 ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛና ንጉሦቻችን ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተጣልን። 8 አሁንም ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዓይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ሞገስ ተሰጥቶናል። 9 ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ምሕረቱን ሰጠን። 10 11 12 አሁንስ አምላካችን ሆይ። ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት ረክሳለች፥ ከዳር እስከ ዳርም ድረስ ከርኵሰታቸው ከጸያፍ ሥራቸውም ተሞልታለች፤ አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ለዘላለም ለልጆቻችሁ ታወርሱአት ዘንድ ሴቶች ልጆቻችሁን ለልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለልጆቻችሁ አትውሰዱ፥ ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውንም ለዘላለም አትሹ ብለህ በባሪያዎችህ በነቢያት ያዘዝኸውን ትእዛዝ ትተናልና ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? 13 ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን። 14 በውኑ ተመልሰን ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም አሕዛብ ጋር እንገባ ዘንድ ይገባናልን? አንተስ ቅሬታ የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቈጣንም? 15 አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።

ዕዝራ 10

1 ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። 2 ከኤላም ልጆች ወገን የነበረም የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው። አምላካችንን በድለናል፤ የምድርን አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3 አሁንም እንደ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩት ምክር፥ ሴቶችን ሁሉ ከእነርሱም የተወለዱትን እንሰድድ ዘንድ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፤ እንደ ሕጉም ይደረግ። 4 ይህም ነገር ለአንተ ይገባልና፥ እኛም ከአንተ ጋር ነንና ተነሣ፥ አይዞህ፥ አድርገው። 5 ዕዝራም ተነሣ፤ አለቆቹንና ካህናቱን ሌዋውያኑንም እስራኤልንም ሁሉ እንደዚህ ቃል ያደርጉ ዘንድ አማለ፤ እነርሱም ማሉ። 6 ዕዝራም ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ጓዳ ገባ፤ ስለ ምርኮኞቹም ኃጢአት ያለቅስ ነበርና ገብቶ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። 78 ምርኮኞቹም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ፥ እንደ አለቆቹና እንደ ሽማግሌዎችም ምክር በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ሁሉ ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፥ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ እንዲለይ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አዋጅ ነገሩ። 9 ሦስት ቀንም ሳያልፍ በዘጠኝኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። 10 ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ። ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። 11 አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፥ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ አላቸው። 12 ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ መልሰው እንዲህ አሉ። እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል። 13 ነገር ግን የሕዝቡ ቍጥር ብዙ ነው፥ ጊዜውም የትልቅ ዝናብ ጊዜ ነው፥ በሜዳም ልንቆም አንችልም፤ በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። 14 አለቆቻችንም በጉባኤው ሁሉ ፋንታ ይቁሙ፤ ስለዚህም ነገር የአምላካችን ጽኑ ቍጣ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት በከተሞቻችን ያሉት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፥ ከእነርሱም ጋር የከተማ ሁሉ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ። 15 ነገር ግን የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሕዝያ ይህን ነገር ተቃወሙ፤ ሜሱላምና ሌዋዊውም ሳባታይ ረዱአቸው። 16 ምርኮኞቹም እንዲህ አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራም የአባቶችም ቤቶች አለቆች በየአባቶቻቸው ቤቶች ተለዩ፥ ሁሉም በየስማቸው ተጻፉ፤ በአሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ይመረምሩ ዘንድ ተቀመጡ። 17 እስከ መጀመሪያው ወር እስከ መጀመሪያው ቀን ድረስ ሠረተው እንግዶቹን ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ። 18 ከካህናቱም ወገን ልጆች እንግዶቹን ሴቶች ያገቡ ሰዎች ተገኙ፤ ከኢዮሴዴቅ ልጅ ከኢያሱ ልጆችና ከወንድሞቹ፥ መዕሤያ፥ አልዓዛር፥ ያሪብ፥ ጎዶልያስ። 19 ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ዘንድ እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም ከመንጋው አንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ። 20 ከኢሜር ልጆችም፤ አናኒና ዝባድያ። 21 ከካሪም ልጆችም መዕሤያ፥ ኤልያስ፥ ሸማያ፥ ይሒኤል፥ ዖዝያ። 22 ከፋስኩር ልጆችም፤ ኤልዮዔናይ፥ መዕሤያ፥ ይስማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባት፥ ኤልዓሣ። 23 ከሌዋውያንም፤ ዮዛባት፥ ሰሜኢ፥ ቆሊጣስ የሚባል ቆልያ፥ ፈታያ፥ ይሁዳ፥ አልዓዛር። 24 ከመዘምራንም፤ ኤልያሴብ፤ ከበረኞችም፤ ሰሎም፥ ጤሌም፥ ኡሪ። 25 ከእስራኤልም ከፋሮስ ልጆች፤ ራምያ፥ ይዝያ፥ መልክያ፥ ሚያሚን፥ አልዓዛር፥ መልክያ፥ በናያስ። 26 ከኤላም ልጆችም፤ ሙታንያ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ አብዲ፥ ይሬሞት፥ ኤልያ። 27 ከዛቱዕ ልጆችም፤ ዔሊዮዔናይ፥ ኢልያሴብ፥ ሙታንያ፥ ይሬሞት፥ ዛባድ፥ ዓዚዛ። 28 ከቤባይ ልጆችም፤ ይሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዘባይ፥ አጥላይ። 29 ከባኒ ልጆችም፤ ሜሱላም፥ መሉክ፥ ዓዳያ፥ ያሱብ፥ ሸዓል፥ ራሞት። 30 ከፈሐት ሞዓብ ልጆችም፤ ዓድና፥ ክላል፥ በናያስ፥ መዕሤያ፥ ሙታንያ፥ ባስልኤል፥ ቢንዊ፥ ምናሴ። 31 ከካሪም ልጆችም፤ አልዓዛር፥ ይሺያ፥ መልክያ፥ 32 ሸማያ፥ ስምዖን፥ ብንያም፥ መሉክ፥ ሰማራያ። 33 ከሐሱም ልጆችም፤ መትናይ፥ መተታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፋላት፥ ይሬማይ፥ ምናሴ፥ ሰሜኢ። 34 ከባኒ ልጆችም፤ መዕዳይ፥ ዓምራም፥ 35 ኡኤል፥ በናያስ፥ ቤድያ፥ ኬልቅያ 36 37 ወንያ፥ ሜሪሞት፥ ኤልያሴብ፥ መታንያ፥ 38 መትናይ፥ የዕሡ፥ ባኒ፥ ቢንዊ፥ ሰሜኢ፥ 39 40 ሰሌምያ፥ ናታን፥ ዓዳያ፥ መክነድባይ፥ 41 ሴሴይ፥ ሸራይ፥ ኤዝርኤል፥ ሰሌምያ፥ ሰማራያ፥ ሰሎም፥ አማርያ፥ ዮሴፍ። 42 43 ከናባው ልጆችም፤ ይዔኤል፥ መቲትያ፥ ዛባድ፥ ዘቢና፥ ያዳይ፥ ኢዮኤል፥ በናያስ። 44 እነዚህ ሁሉ እንግዶቹን ሚስቶች አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም ሚስቶች አያሌዎቹ ልጆችን ወልደው ነበር።

ነህምያ 1

1 የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል። በሀያኛው ዓመት በካሴሉ ወር እንዲህ ሆነ፤ 2 እኔ በሱሳ ግንብ ሳለሁ፥ ከወንድሞቼ አንዱ አናኒ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሰዎች ከይሁዳ መጡ፤ እኔም የዳኑትን ከምርኮ የተረፉትን የአይሁድን ነገር የኢየሩሳሌምንም ነገር ጠየቅኋቸው። 3 እነርሱም። በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል አሉኝ። 4 ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥ 5 እንዲህም አልሁ። አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ 6 እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል። 7 እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም። 89 አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ። 10 እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። 11 ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።

ነህምያ 2

1 በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር። 2 ንጉሡም። ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። 3 ንጉሡንም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ፤ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን? አልሁት። 4 ንጉሡም። ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። 5 ንጉሡንም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት። 6 ንግሥቲቱም በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ። መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ? አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ዘመኑን ቀጠርሁለት። 7 ንጉሡንም። ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ 8 በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ። 9 በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ። 10 ሖሮናዊውም ሰንባላጥና ባሪያው አሞናዊ ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ። 11 ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ። 12 በሌሊትም ተነሣሁ፥ ከእኔም ጋር አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። 13 በሸለቆውም በር ወጣሁ፥ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ። 14 ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበትም የነበረው እንስሳ የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም። 15 በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ ዘወርም ብዬ በሸለቆው በር ገባሁ፥ እንዲሁም ተመለስሁ። 16 ሹማምቱ ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹማምቱም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ገና አልተናገርሁም ነበር። 17 እኔም። እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው። 18 የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም። እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ። 19 ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፥ ቀላል አድርገውንም። ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድር ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን? አሉ። 20 እኔም መልሼ። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው።

ነህምያ 3

1 ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። 2 በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ። 3 የሃስናአ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 4 በአጠገባቸውም የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም አደሰ። በአጠገባቸውም የበዓና ልጅ ሳዶቅ አደሰ። 5 በአጠገባቸውም ቴቁሐውያን አደሱ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አላዋረዱም። 6 የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 7 በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፥ የወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች አደሱ። 8 በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል አደሰ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ። 9 በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ አደሰ። 10 በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ አደሰ። 11 የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ አደሱ። 12 በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታና የመንደሮችዋ አለቃ የአሎኤስ ልጅ ሰሎም አደሰ። 13 ሐኖንና የዛኖዋ ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያው በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ። 14 የቤትሐካሪምም ግዛት አለቃ የሬካብ ልጅ መልክያ የጕድፍ መጣያውን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ። 15 የምጽጳም ግዛት አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ከደነውም፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የሼላን መዋኛ ቅጥር ሠራ። 16 ከእርሱም በኋላ የቤትጹር ግዛት እኵሌታ አለቃ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኃያላኑም ቤት ድረስ አደሰ። 17 ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም አደሱ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ ሐሸብያ ስለ ግዛቱ አደሰ። 18 ከእርሱም በኋላ የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይ ወንድሞቹም አደሱ። 19 በአጠገቡም የምጽጳ አለቃ የኢያሱ ልጅ ኤጽር በማዕዘኑ አጠገብ በጦር መሣሪያ ቤት አንጻር ሌላውን ክፍል አደሰ። 20 ከእርሱም በኋላ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ አደሰ። 21 ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ። 22 ከእርሱም በኋላ የቈላው ሰዎች ካህናቱ አደሱ። 23 ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ። 24 ከእርሱም በኋላ የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ። 25 የኡዛይ ልጅ ፋላል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ። 26 ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ። 27 ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል አደሱ። 28 ከፈረሱ በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር አደሱ። 29 ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር አደሰ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁን በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሸማያ አደሰ። 30 ከእርሱ በኋላ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በጓዳው አንጻር ያለውን አደሰ። 31 ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞቹ የነበረ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሚፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ አደሰ። 32 ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጉ በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።

ነህምያ 4

1 ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ። 2 በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት። እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ። 3 አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ። 4 አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው። 5 በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና። 6 ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ። 7 ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። 8 መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። 9 ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን። 10 ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ። 11 ጠላቶቻችንም። ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ። 12 በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው። ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን። 13 ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው። 14 አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ። አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው። 15 ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። 16 ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። 17 ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። 18 አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ። 19 ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ። ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤ 20 የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው። 21 ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኵሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር። 22 ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን። ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው። 23 እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።

ነህምያ 5

1 በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። 2 አያሌዎቹም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር። 3 አያሌዎቹም። ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር። 4 ሌሎቹም። ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ 5 አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር። 6 እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። 7 በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም። ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። 8 እኔም። ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም። 9 ደግሞም አልሁ። የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? 10 እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። 11 እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው። 12 እነርሱም። እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። 13 ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና። ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ። አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ። 14 ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርጤክስስ ከሀያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ አሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልበላንም። 15 ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሠለጥኑ ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። 16 ደግሞም አጥብቄ የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ ብላቴኖቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ። 17 ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ። 18 ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ በአሥር በአሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልሻም ነበር። 19 አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ።

ነህምያ 6

1 እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንባላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። 2 ሰንባላጥና ጌሳም። መጥተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር። 3 እኔም። ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው። 4 እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። 5 ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤ 6 በእጁም ውስጥ። አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። 7 ደግሞም። ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፤ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፤ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ። 8 እኔም። አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት። 9 እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም። እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፤ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ። 10 እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና። በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ። 11 እኔም። እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም አልሁት። 12 እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር። 13 ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር። 14 አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦብያንና ሰንባላጥን ያስፈራሩኝም ዘንድ የወደዱትን ነቢይቱን ኖዓድያን የቀሩትንም ነቢያት አስብ። 15 ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ። 16 ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፥ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ። 17 18 ጦብያም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማች ስለ ነበረ፥ ልጁም ይሆሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ ስላገባ፥ በይሁዳ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበርና በዚያ ወራት ብዙ የይሁዳ አለቆች ወደ ጦብያ ደብዳቤዎች ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ደብዳቤዎች ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር። 19 ደግሞም በፊቴ ስለ እርሱ መልካም ይናገሩ ነበር፥ ቃሌንም ያወሩለት ነበር፤ ጦብያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።

ነህምያ 7

1 እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩ ከተሠራ በኋላ፥ ሳንቃዎቹንም ካቆምሁ በኋላ፥ በረኞቹና መዘምራኑ ሌዋውያኑም ከተሾሙ በኋላ፥ 2 ወንድሜን አናኒንና የግንቡን አለቃ ሐናንያን በኢየሩሳሌም ላይ ሾምኋቸው፤ እርሱም እውነተኛ ከሌሎቹም ይልቅ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበረ። 3 እኔም። ፀሐይ እስኪሞቅ ድረስ የኢየሩሳሌም በሮች አይከፈቱ፤ እነርሱም ቆመው ሳሉ ደጆቹን ይዝጉ፥ ይቈልፉም፤ ከኢየሩሳሌምም ሰዎች አንዳንዱን በየተራው አንዳንዱንም በየቤቱ አንጻር ጠባቆችን አስቀምጡ አልኋቸው። 4 ከተማይቱም ሰፊና ታላቅ ነበረች፤ በውስጥዋ የነበሩ ሕዝብ ግን ጥቂቶች ነበሩ፥ ቤቶቹም አልተሠሩም ነበር። 5 አምላኬም ታላቆቹንና ሹማምቱን ሕዝቡንም ሰብስቤ እቈጥራቸው ዘንድ በልቤ አደረገ፤ አስቀድመው የመጡትን ሰዎች የትውልድ መጽሐፋቸውን አገኘሁ፥ በእርሱም እንደዚህ ተጽፎ አገኘሁ። 6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው። 7 ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከአዛርያስ፥ ከረዓምያ፥ ከነሐማኒ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከበላሳን፥ ከሚስጴሬት፥ ከበጉዋይ፥ ከነሑም፥ ከበዓና ጋር መጡ። 8 የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤ የፋሮስ ልጆች፥ ሁለት ሺህ መቶ ሰባ ሁለት። 9 የሰፋጥያስ ልጆች ሦስት መቶ ሰባ ሁለት። 10 የኤራ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት። 11 ከኢያሱና ከኢዮአብ ልጆች የሆኑ የፈሐት ሞዓብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ስምንት። 12 የኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። 13 የዛቱዕ ልጆች፥ ስምንት መቶ አርባ አምስት። 14 የዘካይ ልጆች፥ ሰባት መቶ ስድሳ። 15 የቢንዊ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ስምንት። 16 የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ስምንት። 17 የዓዝጋድ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሀያ ሁለት። 18 የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት። 19 የበጉዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስድሳ ሰባት። 20 የዓዲን ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ አምስት። 21 የሕዝቅያስ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት። 22 የሐሱም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ ስምንት። 23 የቤሳይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ አራት። 24 የሐሪፍ ልጆች፥ መቶ አሥራ ሁለት። 25 የገባዖን ልጆች፥ ዘጠና አምስት። 26 የቤተ ልሔምና የነጦፋ ሰዎች፥ መቶ ሰማንያ ስምንት። 27 የዓናቶች ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት። 28 የቤትዓዝሞት ሰዎች፥ አርባ ሁለት። 29 የቂርያትይዓሪምና የከፊራ የብኤሮትም ሰዎች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት። 30 የራማና የጌባ ሰዎች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ። 31 የማክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት። 32 የቤቴልና የጋይ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሦስት። 33 የሁለተኛው ናባው ሰዎች፥ አምሳ ሁለት። 34 የሁለተኛው ኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት። 35 የካሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ። 36 የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት 37 የሎድና የሐዲድ የኦኖም ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አንድ። 38 የሴናዓ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ። 39 ካህናቱ፤ ከኢያሱ ወገን የዮዳኤ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት። 40 የኢሜር ልጆች፥ ሺህ አምሳ ሁለት። 41 የፋስኮር ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት። 42 የካሪም ልጆች፥ ሺህ አሥራ ሰባት። 43 ሌዋውያኑ፤ ከሆዳይዋ ወገን የኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ ሰባ አራት። 44 መዘምራኑ፤ የአሳፍ ልጆች፥ መቶ አርባ ስምንት። 45 በረኞቹ፤ የሰሎም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሶባይ ልጆች፥ መቶ ሠላሳ ስምንት። 46 ናታኒም፥ የሲሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥ 47 የጠብዖት ልጆች፥ የኬራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፥ 48 የፋዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥ 49 የአጋባ ልጆች፥ የሰምላይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥ 50 የራያ ልጆች፥ የረአሶን ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ 51 የጋሴም ልጆች፥ የዖዛ ልጆች፥ የፋሴሐ ልጆች፥ 52 የቤሳይ ልጆች፥ የምዑናውያን ልጆች፥ 53 የንፉሰሲም ልጆች፥ የበቅቡቅ ልጆች፥ የሐቀፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥ 54 የበስሎት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥ የሐርሻ ልጆች፥ 55 የበርቆስ ልጆች፥ የሲሣራ ልጆች፥ 56 የቴማ ልጆች፥ የንስያ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች። 57 የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች፤ የሶጣይ ልጆች፥ የሶፌሬት ልጆች፥ የፍሩዳ ልጆች፥ 58 የየዕላ ልጆች፥ የደርቆን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥ 59 የሰፋጥያስ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፈከራት ልጆች፥ የሐፂቦይም ልጆች፥ የአሞን ልጆች። 60 ናታኒም ሁሉና የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ። 61 ከቴልሜላ፥ ከቴላሬሳ፥ ከክሩብ፥ ከአዳን፥ ከኢሜር የወጡ እነዚህ ናቸው፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤ 62 የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት። 63 ከካህናቱም የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች። 64 እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፥ ነገር ግን አልተገኘም፤ ከክህነትም ተከለከሉ። 65 ሐቴርሰታም። በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ደረስ ከተቀደሰው ነገር አትበሉም አላቸው። 66 67 ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ከነበሩ ከሎሌዎቻቸውና ከገረዶቻቸው ሌላ ጉባኤው ሁሉ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ፤ ሁለቱ መቶም አርባ አምስት ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩአቸው። 68 ፈረሶቻቸውም ሰባት መቶ ሠላሳ ስድስት፥ በቅሎቻቸውም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥ 69 ግመሎቻቸውም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸውም ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ። 70 ከአባቶች ቤቶች አለቆችም አያሌዎቹ ሰዎች ስለ ሥራው ስጦታ ሰጡ። ሐቴርሰታም አንድ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ አምሳም ድስቶች፥ አምስት መቶ ሠላሳም የካህናት ልብስ በቤተ መዛግብት ውስጥ ሰጠ። 71 ከአባቶች ቤቶች አለቆችም አያሌዎቹ በሥራው ቤተ መዛግብት ውስጥ ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ ሁለት ሺህ ሁለት መቶም ምናን ብር ሰጡ። 72 የቀሩትም ሕዝብ የሰጡት ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክና ሁለት ሺህ ምናን ብር፥ ስድሳ ሰባትም የካህናት ልብስ ነበረ። 73 ካህናቱና ሌዋውያኑም፥ በረኞቹና መዘምራኑም ከሕዝቡም አያሌዎቹ፥ ናታኒምም፥ እስራኤልም ሁሉ በከተሞቻቸው ተቀመጡ።

ነህምያ 8

1 ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በከተሞቻቸው ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ያመጣ ዘንድ ጸሐፊውን ዕዝራን ተናገሩት። 2 ካህኑም ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን በማኅበሩ በወንዶችና በሴቶች አስተውለውም በሚሰሙት ሁሉ ፊት አመጣው። 3 በውኃውም በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ ወንዶችና ሴቶች የሚያስተውሉም ሲሰሙ፥ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው፤ የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር። 4 ጸሐፊውም ዕዝራ ስለዚህ ነገር በተሠራ በእንጨት መረባርብ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡ መቲትያ፥ ሽማዕ፥ ዓናያ፥ ኦርዮ፥ ኬልቅያስ፥ መዕሤያ በቀኙ በኩል፥ ፈዳያ፥ ሚሳኤል፥ መልክያ፥ ሐሱም፥ ሐሽበዳና፥ ዘካርያስ፥ ሜሱላም በግራው በኩል ቆመው ነበር። 5 ዕዝራም በሕዝቡ ሁሉ ላይ ከፍ ብሎ ሕዝቡ ሁሉ እያዩ መጽሐፉን ገለጠ፤ በገለጠውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። 6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ። አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 7 ደግሞ ኢያሱና ባኒ፥ ሰራብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሳባታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቆሊጣስ፥ ዓዛርያስ፥ ዮዛባት፥ ሐናን፥ ፌልያ፥ ሌዋውያኑም ሕጉን ያስተውሉ ዘንድ ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡም በየስፍራቸው ቆመው ነበር። 8 የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር። 9 ሐቴርሰታ ነህምያም ጸሐፊውም ካህኑ ዕዝራ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ። ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፤ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። 10 እርሱም። ሂዱ፥ የሰባውንም ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ አላቸው። 11 ሌዋውያንም። ቀኑ የተቀደሰ ነውና ዝም በሉ፥ አትዘኑም ብለው ሕዝቡን ሁሉ ጸጥ ያደርጉ ነበር። 12 ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ። 13 በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች ካህናቱም ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጕምላቸው ዘንድ ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። 14 15 በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም። ወደ ተራራ ሂዱ፤ የዘይትና የበረሀ ወይራ የባርሰነትም የዘንባባም የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፥ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ ብለው ይናገሩ ያውጁም ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። 16 ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፤ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባዩ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠራ። 17 ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፥ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። 18 ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፤ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጉ የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ።

ነህምያ 9

1 በዚህም ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ። 2 የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ። 3 በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ የቀን ሩብ ያህል አነበቡ፤ ሦስት የቀን ሩብም ያህል ተናዘዙ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። 4 ሌዋውያኑም ኢያሱና ባኒ፥ ቀድምኤል፥ ሰበንያ፥ ቡኒ፥ ሰራብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ። 5 ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ። ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ። በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። 6 አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። 7 አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፤ አብራምን መረጥህ፥ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም አልኸው፤ 8 ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፤ የከነዓናዊውንና የኬጢያዊውን የአሞራዊውንም የፌርዛዊውንም የኢያቡሳዊውንም የጌርጌሳዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ። 9 በግብጽም ሳሉ የአባታችንን መከራ አየህ፥ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፤ 10 እንደ ታበዩባቸውም አውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። 11 ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩም መካከል በደረቅ አልፉ፤ ጠላቶቻቸውን ግን ድንጋይ ለጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። 12 የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ በቀን በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ መራሃቸው። 13 ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ መልካሙንም ሥርዓትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፤ 14 የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዝንና ሥርዓትን ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። 15 ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፤ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው። 16 ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ 17 ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፤ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም። 18 ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው። ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥ 19 አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም። 20 ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው። 21 አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፥ ምንም አላጡም፤ ልብሳቸውም አላረጅም፥ እግራቸውም አላበጠም። 22 መንግሥታትንና አሕዛብን ከፍለህ ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። 23 ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፤ ይገቡና ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ተናገርህላቸውም ምድር አገባሃቸው። 24 ልጆቹም ገብተው ምድሩን ወረሱ፥ የምድሩን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው አዋረድህ፤ የሚወድዱትንም ነገር ያደረጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25 ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፤ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፤ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው። 26 ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፤ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቈጡህ። 27 ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፤ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። 28 ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፤ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፥ ገዙአቸውም፤ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፤ 29 ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፤ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፤ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም። 30 ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፤ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 31 ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውሃቸውምም። 32 አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። 33 በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል። 34 ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም። 35 በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። 36 እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፤ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ 37 ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፤ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን። 38 ስለዚህም ሁሉ የታመነውን ቃል ኪዳን አድርገን እንጽፋለን፤ አለቆቻችንም ሌዋውያኖቻችንም ካህናቶቻችንም ያትሙበታል።

ነህምያ 10

1 ያተሙትም እነዚህ ናቸው፤ የሐካልያ ልጅ ሐቴርሰታ ነህምያ፥ 2 ሴዴቅያስ፥ ሠራያ፥ 3 ዓዛርያስ፥ ኤርምያስ፥ ፋስኮር፥ አማርያ፥ መልክያ፥ 45 ሐጡስ፥ ሰበንያ፥ መሉክ፥ ካሪም፥ 6 ሜሪሞት፥ አብድዩ፥ ዳንኤል፥ ጌንቶን፥ ባሮክ፥ 78 ሜሱላም፥ አብያ፥ ሚያሚን፥ መዓዝያ፥ ቤልጋል፥ ሸማያ፤ እነዚህ ካህናት ነበሩ። 9 ሌዋውያኑም፤ የአዛንያ ልጅ ኢያሱ፥ ከኤንሐዳድ ልጆች ቢንዊ፥ ቀድምኤል፤ 10 ወንድሞቻቸውም ሰባንያ፥ ሆዲያ፥ ቆሊጣስ፥ 11 ፌልያ፥ ሐናን፥ ሚካ፥ ረአብ፥ ሐሸብያ፥ 12 13 ዘኩር፥ ሰራብያ፥ ሰበንያ፥ ሆዲያ፥ ባኒ፥ ብኒኑ። 14 የሕዝቡ አለቆች፤ ፋሮስ፥ ፈሐት ሞዓብ፥ 15 ኤላም፥ ዛቱዕ፥ ባኒ፥ ቡኒ፥ ዓዝጋድ፥ ቤባይ፥ 16 17 አዶንያስ፥ በጉዋይ፥ ዓዲን፥ አጤር፥ ሕዝቅያስ፥ 18 ዓዙር፥ ሆዲያ፥ ሐሱም፥ ቤሳይ፥ 19 20 ሐሪፍ፥ ዓናቶት፥ ኖባይ፥ መግጲዓስ፥ ሜሱላም 21 22 ኤዚር፥ ሜሴዜቤል፥ ሳዶቅ፥ ያዱአ፥ ፈላጥያ፥ 23 ሐናን፥ ዓናያ፥ ሆሴዕ፥ ሐናንያ፥ አሱብ፥ 24 25 አሎኤስ፥ ፈልሃ፥ ሶቤቅ፥ ሬሁም፥ ሐሰብና፥ 26 27 መዕሤያ፥ አኪያ፥ ሐናን፥ ዓናን፥ መሉክ፥ ካሪም፥ በዓና። 28 የቀሩትም ሕዝብ፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በረኞቹም፥ መዘምራንም፥ ናታኒምም፥ ከምድርም አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ሕግ ራሳቸውን የለዩ ሁሉ፥ ሚስቶቻቸውም፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም፥ የሚያውቁትና የሚያስተውሉትም ሁሉ ወደ ወንድሞቻቸው ወደ ታላላቆቻቸው ተጠጉ፤ 29 በእግዚአብሔርም ባሪያ በሙሴ እጅ በተሰጠው በእግዚአብሔር ሕግ ይሄዱ ዘንድ፥ የጌታችንንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ፍርዱንም ሥርዓቱንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ እርግማንና መሐላውን አደረጉ። 30 ሴቶች ልጆቻችንንም ለምድር አሕዛብ አንሰጥም፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለልጆቻችን አንወስድም፤ 31 የምድርን አሕዛብ ሸቀጥና ልዩ ልዩ እህል ሊገበዩ በሰንበት ቀን ቢያመጡ፥ በሰንበት ወይም በተቀደሰው ቀን ከእነርሱ አንገዛም፤ የሰባተኛውንም ዓመት ፍሬና ዕዳን ማስከፈል እንተዋለን ብለው ማሉ። 32 33 ስለ አምላካችንም ቤት አገልግሎት፥ ስለ ገጸ ኅብስትም፥ ዘወትርም በሰንበትና በመባቻ ስለ ማቅረብ ስለ እህሉ ቍርባንና ስለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ በዓላትም፥ ስለ ተቀደሱትም ነገሮች፥ ለእስራኤልም ስለሚያስተሰርየው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት፥ ስለ አምላካችንም ቤት ሥራ ሁሉ በየዓመቱ የሰቅል ሢሶ እናመጣ ዘንድ ትእዛዝ በራሳችን ላይ አደረግን። 34 እኛም፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ ሕዝቡም፥ እንደ አባቶቻችን ቤቶች በተወሰነ ጊዜ በየዓመቱ ወደ አምላካችን ቤት አምጥተን በሕጉ እንደ ተጻፈ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይቃጠል ዘንድ ስለ እንጨት ቍርባን ዕጣ ተጣጣልን፤ 35 በየዓመቱም የመሬታችንን በኵራት የሁሉ ዓይነት ዛፍ የፍሬ ሁሉ በኵራት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት እናመጣ ዘንድ፥ 36 በሕጉም እንደ ተጻፈ የልጆቻችንና የእንስሶቻችንን በኵራት፥ የበሬዎቻችንንና የበጎቻችንን በኵራት በአምላካችን ቤት ወደሚያገለግሉት ካህናት ወደ አምላካችን ቤት እናመጣ ዘንድ፥ 37 የእህላችንንም በኵራት፥ የእጅ ማንሣታችንን ቍርባን፥ የዛፍ ሁሉ ፍሬ፥ ወይኑንና ዘይቱንም ወደ ካህናቱ ወደ አምላካችን ቤት ጓዳዎች እናመጣ ዘንድ፥ ሌዋውያኑም ከከተሞቻችን እርሻ ሁሉ አሥራት ይቀበላሉና የመሬታችንን አሥራት ወደ ሌዋውያን እናመጣ ዘንድ ማልን። 38 ሌዋውያኑም አሥራቱን በተቀበሉ ጊዜ የአሮን ልጅ ካህኑ ከሌዋውያን ጋር ይሁን፤ ሌዋውያኑም የአሥራቱን አሥራት ወደ አምላካችን ቤት ወደ ጓዳዎች ወደ ዕቃ ቤት ያምጡት። 39 የእስራኤል ልጆችና የሌዊ ልጆችም የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም የማንሣት ቍርባንን የመቅደሱ ዕቃዎችና የሚያገለግሉት ካህናት በረኞቹና መዘምራኑ ወዳሉባቸው ጓዳዎች ያግቡት፤ እንዲሁም የአምላካችንን ቤት ከቶ አንተውም።

ነህምያ 11

1 የሕዝቡም አለቆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፤ ከቀሩትም ሕዝብ ከአሥሩ ክፍል አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፥ ዘጠኙም በሌሎች ከተሞች ይቀመጡ ዘንድ ዕጣ ተጣጣሉ። 2 ሕዝቡም በፈቃዳቸው በኢየሩሳሌም ለመቀመጥ የወደዱትን ሰዎች ሁሉ ባረኩ። 3 በኢየሩሳሌምም የተቀመጡት የአገሩ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እስራኤል ግን ካህናቱም ሌዋውያኑም ናታኒምም የሰሎሞንም ባሪያዎች ልጆች እያንዳንዳቸው በየርስታቸውና በየከተማቸው በይሁዳ ከተሞች ተቀመጡ። 4 ከይሁዳና ከብንያምም ልጆች እነዚህ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። ከይሁዳ ልጆች፤ ከፋሬስ ልጆች የመላልኤል ልጅ የሰፋጥያስ ልጅ የአማርያ ልጅ የዘካርያስ ልጅ የዖዝያ ልጅ አታያ፤ 5 የሴሎናዊውም ልጅ የዘካርያስ ልጅ የዮያሪብ ልጅ የዓዳያ ልጅ የዖዛያ ልጅ የኮልሖዜ ልጅ የባሮክ ልጅ መዕሤያ። 6 በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የፋሬስ ልጆች ሁሉ አራት መቶ ስድሳ ስምንት ጽኑዓን ነበሩ። 7 የብንያምም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የየሻያ ልጅ የኢቲኤል ልጅ የመዕሤያ ልጅ የቆላያ ልጅ የፈዳያ ልጅ የዮእድ ልጅ የሜሱላም ልጅ ሰሉ። 8 ከእርሱም በኋላ ጌቤና ሳላይ ዘጠኝ መቶም ሀያ ስምንት። 9 አለቃቸውም የዝክሪ ልጅ ኢዮኤል ነበረ፤ የሐስኑአም ልጅ ይሁዳ በከተማው ላይ ሁለተኛ ነበረ። 10 ከካህናቱ፤ የዮያሪብ ልጅ ዮዳኤ፥ ያኪን፥ 11 የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ የመራዮት ልጅ የሳዶቅ ልጅ የሜሱላም ልጅ የኪልቅያስ ልጅ ሠራያ፥ 12 የቤቱንም ሥራ የሠሩ ወንድሞቻቸው ስምንት መቶ ሀያ ሁለት፤ የመልክያ ልጅ የፋስኮር ልጅ የዘካርያስ ልጅ የአማሲ ልጅ የፈላልያ ልጅ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፥ 13 ወንድሞቹም የአባቶቹ ቤቶች አለቆች ሁለት መቶ አርባ ሁለት፤ የኢሜር ልጅ የምሺሌሞት ልጅ የአሕዛይ ልጅ የኤዝርኤል ልጅ አማስያ፥ 14 ወንድሞቻቸውም መቶ ሀያ ስምንት ጽኑዓን ኃያላን፤ አለቃቸውም የሐግዶሊም ልጅ ዘብድኤል ነበረ። 15 ከሌዋውያንም፤ የቡኒ ልጅ የአሳብያ ልጅ የዓዝሪቃም ልጅ የአሱብ ልጅ ሻማያ፤ 16 ከእግዚአብሔርም ቤት በሜዳ በነበረው ሥራ ላይ የነበሩ የሌዋውያን አለቆች ሳባታይና ዮዛባት፤ 17 በጸሎትም ጊዜ ምስጋናን የሚቀነቅኑ አለቃው የአሳፍ ልጅ የዘብዲ ልጅ የሚካ ልጅ መታንያ፥ በወንድሞቹም መካከል ሁለተኛ የነበረ በቅበቃር፥ የኤዶታምም ልጅ የጋላል ልጅ የሳሙስ ልጅ አብድያ። 18 በቅድስቲቱ ከተማ የነበሩ ሌዋውያን ሁሉ ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ነበሩ። 19 በሮቹንም የሚጠብቁ በረኞቹ፥ ዓቁብና ጤልሞን ወንድሞቻቸውም፥ መቶ ሰባ ሁለት ነበሩ። 20 ከእስራኤልም የቀሩት ከካህናትና ከሌዋውያንም እያንዳንዳቸው በየርስታቸው በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ውስጥ ነበሩ። 21 ናታኒምም በዖፌል ተቀምጠው ነበር፤ ሲሐና ጊሽጳ በናታኒም ላይ ነበሩ። 22 በእግዚአብሔርም ቤት ሥራ ላይ ከነበሩ መዘምራን ከአሳፍ ልጆች ወገን የሚካ ልጅ የመታንያ ልጅ የሐሸብያ ልጅ የባኒ ልጅ ኦዚ በኢየሩሳሌም የሌዋውያን አለቃ ነበረ። 23 ስለ እነርሱም የንጉሥ ትእዛዝ ነበረ፤ የመዘምራኑም ሥርዓት ለየዕለቱ የተሠራ ነበረ። 24 ከይሁዳም ልጅ ከዛራ ወገን የሜሴዜቤል ልጅ ፈታያ ስለ ሕዝቡ ነገር ሁሉ በንጉሡ አጠገብ ነበረ። 25 ስለ መንደሮቹና ስለ እርሾቻቸው፤ ከይሁዳ ልጆች አያሌዎች በቂርያትአርባቅና በመንደሮችዋ፥ በዲቦንና በመንደሮችዋም፥ በይቀብጽኤልና በመንደሮችዋም፥ 26 27 በኢያሱ፥ በሞላዳ፥ በቤትጳሌጥ፥ በሐጸርሹዓል፥ 28 በቤርሳቤህና በመንደሮችዋ፥ በጺቅላግ፥ 29 በምኮናና በመንደሮችዋ፥ በዓይንሪሞን፥ 30 በጾርዓ፥ በየርሙት፥ በዛኖዋ በዓዶላም በመንደሮቻቸውም፥ በለኪሶና በእርሻዎችዋ፥ በዓዜቃና በመንደሮችዋ ተቀመጡ። እንዲሁ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ድረስ ሰፈሩ። 31 የብንያምም ልጆች ከጌባ ጀምሮ በማክማስ፥ በጋያ፥ 32 በቤቴልና በመንደሮችዋ፥ በዓናቶት፥ በኖብ፥ 33 34 በሐናንያ፥ በሐጾር፥ በራማ፥ በጊቴም፥ በሐዲድ፥ 35 በስቦይም፥ በንበላት፥ በሎድ፥ በኦኖ፥ በጌሐራሺም ተቀመጡ። 36 በይሁዳም ከነበሩ ሌዋውያን አያሌ ክፍሎች ወደ ብንያም ሆኑ።

ነህምያ 12

1 ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከኢያሱ ጋር የወጡት ካህናትና ሌዋውያን እነዚህ ነበሩ፤ 2 ሠራያ፥ ኤርምያስ፥ ዕዝራ፥ አማርያ፥ 3 መሉክ፥ ሐጡስ፥ ሴኬንያ፥ ሬሁም፥ ሜሪሞት፥ 45 አዶ፥ ጌንቶን፥ አብያ፥ ሚያሚን 6 መዓድያ፥ ቢልጋ፥ ሸማያ፥ ዮያሪብ፥ ዮዳኤ፥ 7 ሰሉ፥ ዓሞቅ፥ ኬልቅያስ፥ ዮዳኤ፤ እነዚህ በኢያሱ ዘመን የካህናቱና የወንድሞቻቸው አለቆች ነበሩ። 8 ሌዋውያኑም፤ ኢያሱ፥ ቢንዊ፥ ቀድምኤል፥ ሰራብያ፥ ይሁዳ፥ ከወንድሞቹም ጋር በመዘምራን ላይ የነበረ መታንያ። 9 ወንድሞቻቸውም በቅቡቅያና ዑኒ በየሰሞናቸው በአንጻራቸው ነበሩ። 10 ኢያሱም ዮአቂምን ወለደ፥ ዮአቂምም ኤልያሴብን ወለደ፥ ኤልያሴብም ዮአዳን ወለደ፥ 11 ዮአዳም ዮናታንን ወለደ፥ ዮናታንም ያዱአን ወለደ። 12 በዮአቂምም ዘመን የአባቶች ቤቶች አለቆች እነዚህ ካህናቱ ነበሩ፤ ከሠራያ ምራያ፥ 13 ከኤርምያስ ሐናንያ፥ ከዕዝራ ሜሱላም፥ 14 ከአማርያ ይሆሐናን፥ ከመሉኪ ዮናታን፥ 15 ከሰበንያ ዮሴፍ፥ ከካሪም ዓድና፥ ከመራዮት ሔልቃይ፥ 16 ከአዶ ዘካርያስ፥ ከጌንቶን ሜሱላም፥ 17 ከአብያ ዚክሪ፥ ከሚያሚን ሞዓድያ፥ 18 ፈልጣይ፥ ከቢልጋ ሳሙስ፥ ከሸማያ ዮናታን፥ 19 ከዮያሪብ መትናይ፥ ከዮዳኤ ኦዚ፥ 20 ከሳላይ ቃላይ፥ ከዓሞቅ ዔቤር፥ 21 ከኬልቅያስ ሐሸብያ፥ ከዮዳኤ ናትናኤል። 22 ከሌዋውያኑም በኤልያሴብና በዮአዳ፥ በዮሐናንና በያዱአ ዘመን የአባቶች ቤቶች አለቆች ተጻፉ፤ ካህናቱም በፋርሳዊው በዳርዮስ መንግሥት ዘመን ተጻፉ። 23 የሌዊ ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆች እስከ ኤልያሴብ ልጅ እስከ ዮሐናን ዘመን ድረስ በታሪክ መጽሐፍ ተጻፉ። 24 የሌዋውያኑም አለቆች፤ ሐሸብያ፥ ሰራብያ፥ የቀድምኤልም ልጅ ኢያሱ እንደ እግዚአብሔር ሰው እንደ ዳዊት ትእዛዝ በየሰሞናቸው በወንድሞቻቸው ፊት ለፊት ያከብሩና ያመሰግኑ ነበር። 25 መታንያ፥ በቅቡቅያ፥ አብድዮ፥ ሜሱላም፥ ጤልሞን፥ ዓቁብ በበሮች አጠገብ የሚገኙትን ዕቃ ቤቶች ለመጠበቅ በረኞች ነበሩ። 26 እነዚህ በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ልጅ በዮአቂም በአለቃውም በነህምያ በጸሐፊውም በካህኑ በዕዝራ ዘመን ነበሩ። 27 የኢየሩሳሌምንም ቅጥር በቀደሱ ጊዜ ቅዳሴውን በደስታና በምስጋና በመዝሙርም በጸናጽልም በበገናም በመሰንቆም ለማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸው ዘንድ ሌዋውያኑን በየስፍራቸው ሁሉ ፈለጉ። 28 29 መዘምራኑም በኢየሩሳሌም ዙሪያ መንደሮች ሠርተው ነበርና የመዘምራኑ ልጆች ከኢየሩሳሌም ዙሪያና ከነጦፋውያን መንደሮች፥ ከቤትጌልገላም፥ ከጌባና ከዓዝሞት እርሻዎች ተሰበሰቡ። 30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አነጹ፤ ሕዝቡንም በሮቹንም ቅጥሩንም አነጹ። 31 የይሁዳንም አለቆች ወደ ቅጥሩ ላይ አወጣኋቸው፤ አመስጋኞቹንም በሁለት ታላላቅ ተርታ አቆምኋቸው፤ አንዱም ወደ ቀኝ በቅጥሩ ላይ ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄደ። 32 ከእነርሱም በኋላ ሆሻያ፥ የይሁዳም አለቆች እኵሌታ፥ 33 ዓዛርያስ፥ ዕዝራ፥ 34 ሜሱላም፥ ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሸማያ፥ ኤርምያስ፥ 35 መለከትም ይዘው ከካህናቱ ልጆች አያሌዎች፥ የአሳፍም ልጅ የዘኩር ልጅ የሚካያ ልጅ የመታንያ ልጅ የሸማያ ልጅ የዮናታን ልጅ ዘካርያስ፥ 36 ወንድሞቹም ሸማያ፥ ኤዝርኤል፥ ሚላላይ፥ ጊላላይ፥ መዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳ፥ አናኒ የእግዚአብሔርን ሰው የዳዊትን የዜማውን ዕቃ ይዘው ሄዱ፤ ጸሐፊውም ዕዝራ በፊታቸው ነበረ። 37 በምንጭም በር አቅንተው ሄዱ፤ በዳዊትም ከተማ ደረጃ፥ በቅጥሩም መውጫ፥ ከዳዊትም ቤት በላይ እስከ ውኃው በር ድረስ በምሥራቅ በኩል ሄዱ። 38 ሁለተኛውም የአመስጋኞቹ ተርታ ወደ ግራ ሄደ፤ እኔና የሕዝቡም እኵሌታ በስተኋላቸው ነበርን፤ በቅጥሩም ላይ፥ በእቶኑ ግንብ በላይ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ፥ ከኤፍሬምም በር በላይ፥ 39 በአሮጌው በርና በዓሣ በር በሐናንኤልም ግንብ፥ በሃሜአ ግንብ እስከ በጎች በር ድረስ ሄዱ፤ በዘበኞችም በር አጠገብ ቆሙ። 40 እንዲሁ ሁለቱ የአመስጋኞች ተርታዎች በእግዚአብሔር ቤት ቆሙ፤ ከእነርሱም ጋር እኔና የአለቆች እኵሌታ፥ 41 ካህናቱም ኤልያቄም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ሚካያ፥ ኤልዮዔናይ፥ 42 ዘካርያስ፥ ሐናንያ መለከት ይዘው፥ መዕሤያ፥ ሸማያ፥ አልዓዛር፥ ኦዚ፥ ይሆሐናን፥ መልክያ፥ ኤላም፥ ኤጽር ቆምን። መዘምራኑም በታላቅ ድምፅ ዘመሩ፥ አለቃቸውም ይዝረሕያ ነበረ። 43 እግዚአብሔርም በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፥ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ የኢየሩሳሌምም ደስታ ከሩቅ ተሰማ። 44 ይሁዳም በአገልጋዮቹ ካህናትና ሌዋውያን ደስ ስላላቸው፥ የካህናቱንና የሌዋውያኑን እድል ፈንታ እንደ ሕጉ ከከተሞች እርሻዎች ያከማቹ ዘንድ ለእጅ ማንሣት ቍርባንና ለበኵራት ለአሥራትም በየዕቃ ቤቶቹ ላይ በዚያ ቀን ሰዎች ተሾሙ። 45 እነርሱም መዘምራኑና በረኞቹም የአምላካቸውን ሥርዓት የመንጻታቸውንም ሥርዓት እንደ ዳዊትና እንደ ልጁ እንደ ሰሎሞን ትእዛዝ ጠበቁ። 46 አስቀድሞም በዳዊትና በአሳፍ ዘመን እግዚአብሔርን በዜማ ለማመስገንና ለማክበር የመዘምራን አለቆች ነበሩ። 47 እስራኤልም ሁሉ በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን ለመዘምራኑና ለበረኞቹ እድል ፈንታቸውን በየዕለቱ ይሰጡ ነበር፤ የተቀደሰውንም ነገር ለሌዋውያን ሰጡ፥ ሌዋውያኑም ከተቀደሰው ነገር ለአሮን ልጆች ሰጡ።

ነህምያ 13

1 በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ፤ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። 2 የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው፤ ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። 3 ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ። 4 ከዚህም አስቀድሞ በአምላካችን ቤት ጓዳዎች ላይ ተሾሞ የነበረው ካህኑ ኤልያሴብ ከጦቢያ ጋር ተወዳጅቶ፥ 5 ለሌዋውያን፥ ለመዘምራን፥ ለበረኞቹ እንደ ሕጉ የተሰጣቸውን የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን፥ ዕቃዎቹንም፥ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት፥ ለካህናቱም የሆነውን የማንሣት ቍርባን አስቀድሞ ያስቀመጡበትን ታላቁን ጓዳ አዘጋጅቶለት ነበር። 6 እኔ ግን በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ በሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበርና በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም። ከጥቂት ዘመንም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ለመንሁ፤ 7 ወደ ኢየሩሳሌምም መጣሁ፤ ኤልያሴብም በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ ጓዳውን በማዘጋጀት ያደረገውን ክፉ ነገር አስተዋልሁ። 8 እጅግም አስከፋኝ፤ የጦብያንም የቤቱን ዕቃ ሁሉ ከጓዳ ወደ ውጪ ጣልሁ። 9 ጓዳዎቹንም እንዲያነጹ አዘዝሁ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃዎች የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም መልሼ በዚያ አገባሁ። 10 ለሌዋውያንም እድል ፈንታቸው እንዳልተሰጠ፥ የሚያገለግሉትም ሌዋውያንና መዘምራን እያንዳንዱ ወደ እርሻው እንደ ሄዱ ተመለከትሁ። 11 እኔም። የእግዚአብሔር ቤት ስለ ምን ተተወ? ብዬ ከአለቆቹ ጋር ተከራከርሁ። ሰበሰብኋቸውም፥ በየስፍራቸውም አቆምኋቸው። 12 ይሁዳም ሁሉ የእህሉንና የወይኑን የዘይቱንም አሥራት ወደ ዕቃ ቤቶች አመጡ። 13 በዕቃ ቤቶችም ላይ ካህኑን ሰሌምያን፥ ጸሐፊውንም ሳዶቅን፥ ከሌዋውያኑም ፈዳያን ሾምሁ፤ ከእነርሱም ጋር የመታንያ ልጅ የዘኩር ልጅ ሐናን ነበረ፤ እነርሱም የታመኑ ሆነው ተገኙ፥ ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው ማከፋፈል ነበረ። 14 አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ አስበኝ፤ ለአምላኬም ቤት ያደረግሁትን ወረታዬን አታጥፋ። 15 በዚያም ወራት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጥመቂያን የሚረግጡትን፥ ነዶም የሚከመሩትን፥ የወይኑን ጠጅና የወይኑን ዘለላ በለሱንም ልዩ ልዩም ዓይነት ሸክም በአህዮች ላይ የሚጭኑትን፥ በሰንበትም ቀን ወደ ኢየሩሳሌም የሚያስገቡትን አየሁ፤ ገበያ ባደረጉበትም ቀን አስመሰከርሁባቸው። 16 ደግሞም በእርስዋ የተቀመጡ የጢሮስ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ዓሣዎችን ልዩ ልዩም ዓይነት ሸቀጥ አምጥተው በሰንበት ቀን በኢየሩሳሌም ለይሁዳ ልጆች ይሸጡ ነበር። 17 ከይሁዳም ታላላቆች ጋር ተከራከርሁና። ይህ የምታደርጉት ክፉ ነገር ምንድር ነው? የሰንበትንስ ቀን ታረክሳላችሁን? 18 አባቶቻችሁ እንደዚህ አድርገው አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ በእኛና በዚህ ከተማ ላይ አምጥቶ አልነበረምን? እናንተም ሰንበትን በማርከሳችሁ በእስራኤል ላይ መዓትን ትጨምራላችሁ አልኋቸው። 19 ከዚህ በኋላ ከሰንበት በፊት በኢየሩሳሌም በሮች ድንግዝግዝታ በሆነ ጊዜ በሮችዋ እንዲዘጉ፥ ሰንበትም እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ። በሰንበትም ቀን ሸክም እንዳይገባ ከብላቴኖቼ በአያሌዎቹ በሮችዋን አስጠበቅሁ። 20 ሁሉም አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በኢየሩሳሌም ውጭ አድረው ገበያ አድርገው ነበር። 21 እኔም አስመሰከርሁባቸውና። በቅጥሩ ውጭ ለምን ታድራላችሁ? እንደ ገና ብታደርጉት እጆቼን አነሣባችኋለሁ አልኋቸው። ከዚያም ወዲያ በሰንበት ቀን እንደ ገና አልመጡም። 22 ሌዋውያኑንም ራሳቸውን እንዲያነጹ፥ መጥተውም በሮቹን እንዲጠብቁ፥ የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ ነገርኋቸው። አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ደግሞ አስበኝ፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ራራልኝ። 23 ደግሞም በዚያ ወራት የአዛጦንና የአሞንን የሞዓብንም ሴቶች ያገቡትን አይሁድ አየሁ። 24 ከልጆቻቸውም እኵሌቶቹ በአዛጦን ቋንቋ ይናገሩ ነበር፥ በአይሁድም ቋንቋ መናገር አያውቁም ነበር። 25 ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፤ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው። ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ። 26 የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በዚህ ነገር ኃጢአት አድርጎ የለምን? በብዙ አሕዛብም መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፥ በአምላኩም ዘንድ የተወደደ ነበረ፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ አንግሦት ነበር፤ እርሱንም እንኳ እንግዶች ሴቶች አሳቱት። 27 በውኑ ይህን ሁሉ ታላቅ ክፋት እንሠራ፥ እንግዶችንም ሴቶች በማግባት አምላካችን እንበድል ዘንድ እናንተን እንስማ? 28 ከዋነኛውም ካህን ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ ለሖሮናዊው ለሰንባላጥ አማች ነበረ፤ ከእኔም ዘንድ አባረርሁት። 29 አምላኬ ሆይ፥ ክህነትን የክህነትንና የሌዋውያንንም ቃል ኪዳን ስላፈረሱ አስባቸው። 30 ከእንግዳ ነገርም ሁሉ አነጻኋቸው፤ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው በየሰሞናቸው፥ 31 በየጊዜያቸውም ለእንጨት ቍርባን ለበኵራቱም ሥርዓት አደረግሁ። አምላኬ ሆይ፥ በመልካም አስበኝ።

አስቴር 1

1 በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ። 2 በዚያም ዘመን ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ በነበረው በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥ 3 በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ የፋርስና የሜዶን ታላላቆች ሁሉ፥ የየአገሩ አዛውንትና ሹማምት፥ በፊቱ ነበሩ፤ 4 የከበረውንም የመንግሥቱን ሀብት፥ የታላቁንም የግርማዊነቱን ክብር መቶ ሰማንያ ቀን ያህል አሳያቸው። 5 ይህም ቀን በተፈጸመ ጊዜ በሱሳ ግንብ ውስጥ ለተገኙት ሕዝብ ሁሉ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ንጉሡ በንጉሡ ቤት አታክልት ውስጥ ባለው አደባባይ ሰባት ቀን ግብዣ አደረገ። 6 ነጭ፥ አረንጓዴ፥ ሰማያዊም መጋረጆች ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ በተሠራ ገመድ፥ በብር ቀለበትና በዕብነ በረድ አዕማድ ላይ ተዘርግተው ነበር፤ አልጋዎቹም ከወርቅና ከብር ተሠርተው በቀይና በነጭ በብጫና በጥቁር ዕብነ በረድ ወለል ላይ ነበሩ። 7 መጠጡም በልዩ ልዩ በወርቅ ዕቃ ይታደል ነበር፤ የንጉሡም የወይን ጠጅ እንደ ንጉሡ ለጋስነት መጠን እጅግ ብዙ ነበረ። 8 ንጉሡም እንደ ሰው ሁሉ ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ ለቤቱ አዛዦች ሁሉ አዝዞ ነበርና መጠጡ እንደ ወግ አልነበረም። 9 ንግሥቲቱም አስጢን በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች። 10 11 በሰባተኛውም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ ባለው ጊዜ፥ ንግሥቲቱ አስጢን መልከ መልካም ነበረችና ውበትዋ ለአሕዛብና ለአለቆች እንዲታይ የመንግሥቱን ዘውድ ጭነው ወደ ንጉሡ ፊት ያመጡአት ዘንድ በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርን፥ ከርከስን አዘዛቸው። 12 ነገር ግን ንግሥቲቱ አስጢን በጃንደረቦቹ እጅ በላከው በንጉሡ ትእዛዝ ትመጣ ዘንድ እንቢ አለች፤ ንጉሡም እጅግ ተቈጣ፥ በቍጣውም ተናደደ። 13 ሕግንና ፍርድን በሚያውቁ ሁሉ ፊት የንጉሡ ወግ እንዲህ ነበረና ንጉሡ የዘመኑን ነገር የሚያውቁትን ጥበበኞችን፥ 14 በመንግሥቱም ቀዳሚዎች ሆነው የሚቀመጡ የንጉሡ ባለምዋሎች ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓር፥ ምሙካን በአጠገቡ ሳሉ። 15 በጃንደረቦች እጅ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትእዛዝ ስላላደረገች በንግሥቲቱ በአስጢን ላይ እንደ ሕጉ የምናደርገው ምንድር ነው? አላቸው። 16 ምሙካንም በንጉሡና በአዛውንቱ ፊት እንዲህ አለ። ንግሥቲቱ አስጢን አዛውንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ አገር ያሉትን አሕዛብ ሁሉ በድላለች እንጂ ንጉሡን ብቻ የበደለች አይደለችም። 17 ይህ የንግሥቲቱ ነገር ወደ ሴቶች ሁሉ ይደርሳልና። ንጉሡ አርጤክስስ ንግሥቲቱ አስጢን ወደ እርሱ ትገባ ዘንድ አዘዘ፥ እርስዋ ግን አልገባችም ተብሎ በተነገረ ጊዜ ባሎቻቸው በዓይናቸው ዘንድ የተናቁ ይሆናሉ። 18 ዛሬም የንግሥቲቱን ነገር የሰሙት የፋርስና የሜዶን ወይዛዝር እንዲህና እንዲህ ብለው ለንጉሡ አዛውንት ሁሉ ይናገራሉ፥ ንቀትና ቍጣም ይበዛል። 19 ንጉሡም ቢፈቅድ፥ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ፊት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትገባ የንጉሡ ትእዛዝ ከእርሱ ይውጣ፥ እንዳይፈርስም በፋርስና በሜዶን ሕግ ይጻፍ፤ ንጉሡም ንግሥትነትዋን ከእርስዋ ለተሻለችው ለሌላይቱ ይስጥ። 20 የንጉሡም ትእዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ታላቁንም ታናሹንም ያከብራሉ። 21 ይህም ምክር ንጉሡንና አዛውንቱን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም እንደ ምሙካን ቃል አደረገ። 22 ሰው ሁሉ በቤቱ አለቃ ይሁን፤ በሕዝቡም ቋንቋ ይናገር ብሎ ለአገሩ ሁሉ እንደ ጽሕፈቱ ለሕዝቡም ሁሉ እንደ ቋንቋው ደብዳቤዎችን ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ሰደደ።

አስቴር 2

1 ከዚህም ነገር በኋላ የንጉሡ የአርጤክስስ ቍጣ በበረደ ጊዜ አስጢንና ያደረገችውን የፈረደባትንም ነገር አሰበ። 2 ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች እንዲህ አሉት። መልከ መልካም የሆኑ ደናግል ለንጉሡ ይፈለጉለት፤ 3 ሴቶችን ከሚጠብቅ ከንጉሡ ጃንደረባ ከሄጌ እጅ በታች እንዲያደርጓቸው መልከ መልካሞቹን ደናግል ሁሉ ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሴቶች ቤት ይሰበስቡአቸው ዘንድ ንጉሡ በመንግሥቱ አገሮች ሁሉ ሹማምቶችን ያኑር፤ ቅባትና የሚያስፈልጋቸውም ይሰጣቸው፤ 4 ንጉሡንም ደስ የምታሰኝ ቆንጆ በአስጢን ስፍራ ትንገሥ። ይህም ነገር ንጉሡን ደስ አሰኘው፥ እንዲሁም አደረገ። 5 አንድ አይሁዳዊ የቂስ ልጅ የሰሜኢ ልጅ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል ብንያማዊ በሱሳ ግንብ ነበረ። 6 እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከተማረኩት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም የተማረከ ነበረ። 7 አባትና እናትም አልነበራትምና የአጎቱ ልጅ ሀደሳ የተባለችውን አስቴርን አሳድጎ ነበር፤ ቆንጆይቱም የተዋበችና መልከ መልካም ነበረች፤ አባትዋና እናትዋም ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ወስዶአት ነበር። 8 የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በተሰማ ጊዜ፥ ብዙም ቈነጃጅት ወደ ሱሳ ግንብ ወደ ሄጌ እጅ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ሴቶች ጠባቂው ወደ ሄጌ ተወሰደች። 9 ቆንጆይቱም ደስ አሰኘችው፥ በእርሱም ዘንድ ሞገስ አገኘች፤ ቅባትዋንም ድርሻዋንም ከንጉሡም ቤት ልታገኝ የሚገባትን ሰባት ደንገጥሮች ፈጥኖ ሰጣት፤ እርስዋንና ደንገጥሮችዋንም በሴቶች ቤት በተመረጠ ስፍራ አኖረ። 10 ይህንም እንዳትናገር መርዶክዮስ አዝዞአት ነበርና አስቴር ሕዝብዋንና ወገንዋን አልተናገረችም። 11 መርዶክዮስም የአስቴርን ደኅንነትና የሚሆንላትን ያውቅ ዘንድ ዕለት ዕለት በሴቶች ቤት ወለል ትይዩ ይመላለስ ነበር። 12 የመንጻታቸውም ወራት ስድስት ወር ያህል በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወርም በጣፋጭ ሽቱና በልዩ ልዩም በሚያነጻ ነገር ይፈጸም ነበርና እንደ ሴቶች ወግ አሥራ ሁለት ወር እንዲሁ ከተደረገላት በኋላ ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ለመግባት የአንዳንዲቱ ቆንጆ ተራ በደረሰ ጊዜ፥ 13 በዚህ ወግ ቆንጆይቱ ወደ ንጉሡ ትገባ ነበር፤ ከሴቶች ቤት ወደ ንጉሡ ቤት ለመውሰድ የምትሻውን ሁሉ ይሰጡአት ነበር። 14 ማታም ትገባ ነበር፥ ሲነጋም ተመልሳ ወደ ሁለተኛው ሴቶች ቤት ቁባቶችን ወደሚጠብቅ ወደ ንጉሡ ጃንደረባ ወደ ጋይ ትመጣ ነበር፤ ንጉሡም ያልፈለጋት እንደ ሆነ፥ በስምዋም ያልተጠራች እንደሆነ፥ ከዚያ ወዲያ ወደ ንጉሡ አትገባም ነበር። 15 ወደ ንጉሡም ትገባ ዘንድ የመርዶክዮስ አጎት የአቢካኢል ልጅ የአስቴር ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ጠባቂው የንጉሡ ጃንደረባ ሄጌ ከሚለው በቀር ምንም አልፈለገችም ነበር፤ አስቴርም በሚያዩአት ሁሉ ዓይን ሞገስ አግኝታ ነበርና። 16 አርጤክስስም በነገሠ በሰባተኛው ዓመት አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ተወሰደች። 17 ንጉሡም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፥ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፥ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት። 18 ንጉሡም ስለ አስቴር ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ሰባት ቀን ያህል ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ለአገሮቹም ሁሉ ይቅርታ አደረገ፥ እንደ ንጉሡም ለጋስነት መጠን ስጦታ ሰጠ። 19 ደናግሉም ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ይቀመጥ ነበር። 20 አስቴርም ከእርሱ ጋር እንዳደገችበት ጊዜ የመርዶክዮስን ትእዛዝ ታደርግ ነበርና መርዶክዮስ እንዳዘዛት አስቴር ወገንዋንና ሕዝብዋን አልተናገረችም። 21 በዚያም ወራት መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ ደጁን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፥ እጃቸውንም በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ ፈለጉ። 22 ነገሩም ለመርዶክዮስ ተገለጠ፥ እርሱም ለንግሥቲቱ ለአስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረች። 23 ነገሩም ተመረመረ፥ እንዲህም ሆኖ ተገኘ፥ ሁለቱም በዛፍ ላይ ተሰቀሉ፤ ያም በንጉሡ ፊት በታሪክ መጽሐፍ ተጻፈ።

አስቴር 3

1 ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሡ አርጤክስስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፥ አከበረውም፥ ወንበሩንም ከእርሱ ጋር ከነበሩት አዛውንት ሁሉ በላይ አደረገለት። 2 ንጉሡም ስለ እርሱ እንዲሁ አዝዞ ነበርና በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች ሁሉ ተደፍተው ለሐማ ይሰግዱ ነበር። መርዶክዮስ ግን አልተደፋም፥ አልሰገደለትም። 3 በንጉሡም በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች መርዶክዮስን። የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ? አሉት። 4 ይህንም ዕለት ዕለት እየተናገሩ እርሱ ባልሰማቸው ጊዜ አይሁዳዊ እንደ ሆነ ነግሮአቸው ነበርና የመርዶክዮስ ነገር እንዴት እንደ ሆነ ያዩ ዘንድ ለሐማ ነገሩት። 5 ሐማም መርዶክዮስ እንዳልተደፋለት እንዳልሰገደለትም ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 6 የመርዶክዮስን ወገን ነግረውት ነበርና በመርዶክዮስ ብቻ እጁን ይጭን ዘንድ በዓይኑ ተናቀ፤ ሐማም በአርጤክስስ መንግሥት ሁሉ የነበሩትን የመርዶክዮስን ሕዝብ አይሁድን ሁሉ ሊያጠፋ ፈለገ። 7 በንጉሡም በአርጤክስስ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከመጀመሪያው ወር ከኒሳን ጀምሮ በየዕለቱና በየወሩ እስከ አሥራ ሁለተኛው ወር እስከ አዳር ድረስ በሐማ ፊት ፉር የተባለውን ዕጣ ይጥሉ ነበር። 8 ሐማም ንጉሡን አርጤክስስን። አንድ ሕዝብ በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አገሮች ሁሉ ተበትነዋል፤ ሕጋቸውም ከሕዝቡ ሁሉ ሕግ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕግ አይጠብቁም፤ ንጉሡም ይተዋቸው ዘንድ አይገባውም። 9 ንጉሡም ቢፈቅድ እንዲጠፉ ይጻፍ፤ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ያገቡት ዘንድ አሥር ሺህ መክሊት ብር የንጉሡን ሥራ በሚሠሩት እጅ እመዝናለሁ አለው። 10 ንጉሡም ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ፥ ለአይሁድም ጠላት ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው። 11 ንጉሡም ሐማን። ደስ የሚያሰኝህን ነገር ታደርግባቸው ዘንድ ብሩም ሕዝቡም ለአንተ ተሰጥቶሃል አለው። 12 በመጀመሪያውም ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ወዳሉ መቶ ሀያ ሰባት አገሮች፥ በየአገሩ ወዳሉ ሹማምትና አለቆች ወደ አሕዛብም ሁሉ ገዢዎች እንደ ቋንቋቸው በንጉሡ በአርጤክስስ ቃል ሐማ እንዳዘዘ ተጻፈ፥ በንጉሡም ቀለበት ታተመ። 13 በአሥራ ሁለተኛው ወር በአዳር በአሥራ ሦስተኛው ቀን አይሁድን ሁሉ፥ ልጆችንና ሽማግሌዎችን፥ ሕፃናቶችንና ሴቶችን፥ በአንድ ቀን ያጠፉና ይገድሉ ዘንድ፥ ይደመስሱም ዘንድ፥ ምርኮአቸውንም ይዘርፉ ዘንድ ደብዳቤዎች በመልእክተኞች እጅ ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ተላኩ። 14 በዚያም ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየአገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ። 15 መልእክተኞቹም በንጉሡ ትእዛዝ እየቸኰሉ ሄዱ፥ አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ። ንጉሡና ሐማ ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ከተማይቱ ሱሳ ግን ተደናገጠች።

አስቴር 4

1 መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ አመድም ነሰነሰ፥ ወደ ከተማይቱም መካከል ወጣ፥ ታላቅም የመረረ ጩኸት ጮኸ። 2 ማቅም ለብሶ በንጉሥ በር መግባት አይገባም ነበርና እስከ ንጉሡ በር አቅራቢያ መጣ። 3 የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገር ሁሉ በአይሁድ ላይ ታላቅ ኀዘንና ጾም ልቅሶና ዋይታም ሆነ ብዙዎችም ማቅና አመድ አነጠፉ። 4 የአስቴርም ደንገጥሮችዋና ጃንደረቦችዋ መጥተው ነገሩአት፥ ንግሥቲቱም እጅግ አዘነች፤ ማቁንም ለውጦ ልብስ ይለብስ ዘንድ ለመርዶክዮስ ሰደደችለት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። 5 አስቴርም ያገለግላት ዘንድ ንጉሡ ያቆመውን አክራትዮስን ጠራች እርሱም ከጃንደረቦች አንዱ ነበረ፥ እርስዋም ይህ ነገር ምንና ምን እንደ ሆነ ያስታውቃት ዘንድ ወደ መርዶክዮስ እንዲሄድ አዘዘችው። 6 አክራትዮስም በንጉሥ በር ፊት ወደ ነበረችው ወደ ከተማይቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። 7 መርዶክዮስም የተደረገውን ሁሉ፥ አይሁድንም ለማጥፋት ሐማ በንጉሡ ግምጃ ቤት ይመዝን ዘንድ የተናገረውን የብሩን ቍጥር ነገረው። 8 ለአስቴርም እንዲያሳያት ለመጥፋታቸው በሱሳ የተነገረውን የአዋጁን ጽሕፈት ቅጅ ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ገብታ ስለ ሕዝብዋ ትለምነውና ትማልደው ዘንድ እንዲነግራትና እንዲያዝዛት ነገረው። 9 አክራትዮስም መጥቶ የመርዶክዮስን ቃል ለአስቴር ነገራት። 10 አስቴርም አክራትዮስን ተናገረችው፥ ለመርዶክዮስም እንዲህ የሚል መልእክት ሰጠችው። 11 የንጉሡ ባሪያዎችና በአገሮችም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ወደ ውስጠኛው ወለል የሚገባ ሁሉ፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ ንጉሡ የወርቁን ዘንግ ካልዘረጋለት በቀር፥ እርሱ ይሞት ዘንድ ሕግ እንዳለ ያውቃሉ፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ይህን ሠላሳውን ቀን አልተጠራሁም። 12 አክራትዮስም የአስቴርን ቃል ለመርዶክዮስ ነገረው። 13 መርዶክዮስም አክራትዮስን። ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው። አንቺ። በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። 14 በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 15 አስቴርም እንዲህ ብሎ ለመርዶክዮስ እንዲመልስ አዘዘችው። 16 ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ፤ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን አትብሉም፥ አትጠጡም፤ እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም እንኳ ያለ ሕግ ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ብጠፋም እጠፋለሁ። 17 መርዶክዮስም ሄዶ አስቴር እንዳዘዘችው ሁሉ አደረገ።

አስቴር 5

1 በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች፤ ንጉሡም በቤቱ መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር። 2 ንጉሡም ንግሥቲቱ አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም በእጁ የነበረውን የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀርባ የዘንጉን ጫፍ ነካች። 3 ንጉሡም። ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል አላት። 4 አስቴርም። ለንጉሡ መልካም ሆኖ ቢታይ ንጉሡ ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ከሐማ ጋር ዛሬ ይምጣ አለች። 5 ንጉሡም። አስቴር እንዳለች ይደረግ ዘንድ ሐማን አስቸኵሉት አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ። 6 ንጉሡም በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን። የምትሺው ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ ልመናሽስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት። 7 አስቴርም መልሳ። ልመናዬና የምሻው ነገር ይህ ነው፤ 8 በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ልመናዬንም ይፈጽም ዘንድና የምሻውን ያደርግ ዘንድ ንጉሡ ደስ ቢያሰኘው፥ ንጉሡና ሐማ ወደማዘጋጅላቸው ግብዣ ይምጡ፤ እንደ ንጉሡም ነገር ነገ አደርጋለሁ አለች። 9 በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ። 10 ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ልኮም ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠራ። 11 ሐማም የሀብቱን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ንጉሡም ያከበረበትን ክብር ሁሉ፥ በንጉሡም አዛውንትና ባሪያዎች ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው። 12 ሐማም። ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ። 13 ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንምን አይጠቅምም አለ። 14 ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹ ሁሉ። ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይደረግ፥ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፤ ደስም ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ አሉት። ነገራቸውም ሐማን ደስ አሰኘው፥ ግንዱንም አስደረገ።

አስቴር 6

1 በዚያም ሌሊት እንቅልፍ ከንጉሡ ሸሸ፤ የዘመኑንም ታሪክ መጽሐፍ ያመጡ ዘንድ አዘዘ፥ በንጉሡም ፊት ተነበበ። 2 ደጁንም ከሚጠብቁት ከንጉሡ ጃንደረቦች ሁለቱ ገበታና ታራ እጃቸውን በንጉሡ በአርጤክስስ ላይ ያነሡ ዘንድ እንደ ፈለጉ፥ መርዶክዮስ እንደ ነገረው ተጽፎ ተገኘ። 3 ንጉሡም። ስለዚህ ነገር ለመርዶክዮስ ምን ክብርና በጎነት ተደረገለት? አለ። ንጉሡንም የሚያገለግሉ ብላቴኖች። ምንም አልተደረገለትም አሉት። 4 ንጉሡም። በአዳራሹ ማን አለ? አለ። ሐማም ባዘጋጀው ግንድ ላይ መርዶክዮስን ለማሰቀል ለንጉሡ ይናገር ዘንድ ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ውጭው አዳራሽ ገብቶ ነበር። 5 የንጉሡም ብላቴኖች። እነሆ ሐማ በአዳራሹ ቆሞአል አሉት። ንጉሡም። ይግባ አለ። 6 ሐማም ገባ፤ ንጉሡም። ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ምን ይደረግለታል? አለው። ሐማም በልቡ። ንጉሡ ከእኔ ይልቅ ማንን ያከብር ዘንድ ይወድዳል? አለ። 7 ሐማም ንጉሡን እንዲህ አለው። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግ፤ 8 ንጉሡ የለበሰው የክብር ልብስ፥ ንጉሡም የተቀመጠበት ፈረስ ይምጣለት፥ የንጉሡም ዘውድ በራሱ ላይ ይደረግ፤ 9 ልብሱንና ፈረሱንም ከንጉሡ አዛውንት በዋነኛው እጅ ያስረክቡት፤ ንጉሡም ያከብረው ዘንድ የሚወድደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውት በከተማይቱ አደባባይ ያሳልፉት፤ በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ተብሎ አዋጅ ይነገር። 10 ንጉሡም ሐማን። ፍጠን፥ እንደ ተናገርኸውም ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡም በር ለሚቀመጠው አይሁዳዊ ለመርዶክዮስ እንዲሁ አድርግለት፤ ከተናገርኸውም ሁሉ ምንም አይቅር አለው። 11 ሐማም ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ፥ መርዶክዮስንም አለበሰው፥ በፈረሱም ላይ አስቀመጠው፥ በከተማይቱም አደባባይ በፊቱ አሳለፈው። በፊቱም። ንጉሡ ያከብረው ዘንድ ለሚወድደው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብሎ አዋጅ ነገረ። 12 መርዶክዮስም ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን አዝኖና ራሱን ተከናንቦ ቸኵሎ ወደ ቤቱ ሄደ። 13 ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ያገኘውን ሁሉ አጫወታቸው። ጥበበኞቹና ሚስቱ ዞሳራም። በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ከአይሁድ ወገን የሆነ እንደ ሆነ በፊቱ ፈጽሞ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም አሉት። 14 እነርሱም ሲናገሩት ሳሉ እነሆ የንጉሡ ጃንደረቦች መጡ፥ አስቴርም ወዳዘጋጀችው ግብዣ ይመጣ ዘንድ ሐማን አስቸኰሉት።

አስቴር 7

1 ንጉሡና ሐማም ከንግሥቲቱ ከአስቴር ጋር ለመጠጣት መጡ። 2 በሁለተኛውም ቀን ንጉሡ በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን። ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት። 3 ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ። ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው፥ ሕይወቴ በልመናዬ ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ፤ 4 እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል ለመደምሰስም ተሸጠናልና። ባርያዎች ልንሆን ተሸጠን እንደ ሆነ ዝም ባልሁ ነበር፤ የሆነ ሆኖ ጠላቱ የንጉሡን ጉዳት ለማቅናት ባልቻለም ነበር አለች። 5 ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርን። ይህን ያደርግ ዘንድ በልቡ የደፈረ ማን ነው? እርሱስ ወዴት ነው? ብሎ ተናገራት። 6 አስቴርም። ያ ጠላትና ባለጋራ ሰው ክፉው ሐማ ነው አለች። ሐማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት ደነገጠ። 7 ንጉሡም ተቈጥቶ የወይን ጠጅ ከመጠጣቱ ተነሣ፥ ወደ ንጉሡም ቤት አታክልት ውስጥ ሄደ። ሐማም ከንጉሡ ዘንድ ክፉ ነገር እንደ ታሰበበት አይቶአልና ከንግሥቲቱ ከአስቴር ሕይወቱን ይለምን ዘንድ ቆመ። 8 ንጉሡም ከቤቱ አታክልት ወደ ወይን ጠጁ ግብዣ ስፍራ ተመለሰ፤ ሐማም አስቴር ባለችበት አልጋ ላይ ወድቆ ነበር። ንጉሡም። ደግሞ በቤቴ በእኔ ፊት ንግሥቲቱን ይጋፋታልን? አለ። ይህም ቃል ከንጉሡ አፍ በወጣ ጊዜ የሐማን ፊት ሸፈኑት። 9 በንጉሡም ፊት ካሉት ጃንደረቦች አንዱ ሐርቦና። እነሆ ሐማ ለንጉሡ በጎ ለተናገረው ለመርዶክዮስ ያሠራው ርዝመቱ አምሳ ክንድ የሆነው ግንድ በሐማ ቤት ተተክሎአል አለ። ንጉሡም። በእርሱ ላይ ስቀሉት አለ። 10 ሐማንም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት፤ በዚያም ጊዜ የንጉሡ ቍጣ በረደ።

አስቴር 8

1 በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ለንግሥቲቱ ለአስቴር ሰጠ። አስቴርም ለእርስዋ ምን እንደ ሆነ ነግራው ነበርና መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ፊት ገባ። 2 ንጉሡም ከሐማ ያወለቀውን ቀለበቱን አወጣ፥ ለመርዶክዮስም ሰጠው። አስቴርም በሐማ ቤት ላይ መርዶክዮስን ሾመች። 3 አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች፤ በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው። 4 ንጉሡም የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመችና። 5 ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ በፊቱም ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ ይህም ነገር በፊቱ ቅን ቢሆን፥ እኔም በእርሱ ዘንድ ተወድጄ እንደ ሆነ፥ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አገር ሁሉ ያሉትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈው ተንኰል ይገለበጥ ዘንድ ይጻፍ። 6 እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? አለች። 7 ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን። እነሆ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፥ እርሱም እጆቹን በአይሁድ ላይ ስለ ዘረጋ በግንድ ላይ ተሰቀለ። 8 በንጉሡ ስም የተጻፈና በንጉሡ ቀለበት የታተመ አይገለበጥምና እናንተ ደግሞ ደስ የሚያሰኛችሁን በንጉሡ ስም ስለ አይሁድ ጻፉ፥ በንጉሡም ቀለበት አትሙ አላቸው። 9 በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ። 10 በንጉሡም በአርጤክስስ ስም አስጻፈው፥ በንጉሡም ቀለበት አሳተመው፤ ደብዳቤውንም በንጉሡ ፈረስ ቤት በተወለዱት፥ ለንጉሡም አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች በተቀመጡ መልእክተኞች እጅ ሰደደው። 11 በዚያም ደብዳቤ በከተሞቹ ሁሉ የሚኖሩት አይሁድ እንዲሰበሰቡ፥ ለሕይወታቸውም እንዲቆሙ፥ በጥል የሚነሡባቸውን የሕዝቡንና የአገሩን ሠራዊት ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሴቶቻቸው ጋር እንዲያጠፉና እንዲገድሉ እንዲደመስሱም፥ ምርኮአቸውንም እንዲዘርፉ ንጉሡ ፈቀደላቸው። 12 ይህም አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በአንድ ቀን እንዲሆን ነው። 13 አይሁድም ጠላቶቻቸውን እንዲበቀሉ በዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየአገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ። 14 ለንጉሡ አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች የተቀመጡት መልእክተኞች በንጉሡ ትእዛዝ ተርበትብተውና ቸኵለው ወጡ፤ አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ። 15 መርዶክዮስም በሰማያዊና በነጭ ሐር የተሠራውን የንጉሡን የክብር ልብስ ለብሶ ታላቅም የወርቅ አክሊል ደፍቶ ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ የሱሳም ከተማ ደስ አላት፥ እልልም አለች። 16 ለአይሁድም ብርሃንና ደስታ ተድላና ክብርም ሆነ። 17 የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገርና ከተማ ሁሉ ለአይሁድ ደስታና ተድላ፥ የግብዣም ቀን መልካምም ቀን ሆነ። አይሁድንም መፍራት ስለ ወደቀባቸው ከምድር አሕዛብ ብዙ ሰዎች አይሁድ ሆኑ።

አስቴር 9

1 አዳር በሚባለውም በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ የንጉሡ ትእዛዝና አዋጅ ሊፈጸምበት በነበረው ቀን፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊሠለጥኑባቸው በነበረው ቀን፥ አይሁድ በጠላቶቻቸው ላይ እንዲሠለጥኑ ነገሩ ተገለበጠ። 2 አይሁድም ክፋታቸውን በሚሹት ሰዎች ላይ እጃቸውን ይዘረጉ ዘንድ በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በነበሩ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰበሰቡ፤ እነርሱንም መፍራት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ወድቆ ነበርና እነርሱን የሚቃወም ሰው አልነበረም። 3 መርዶክዮስን መፍራት በላያቸው ስለ ወደቀ በየአገሩ የነበሩ አዛውንትና ሹማምቶች አለቆችም፥ የንጉሡንም ሥራ የሚሠሩቱ ሁሉ አይሁድን አገዙ። 4 ያ ሰው መርዶክዮስ ከፍ ከፍ እያለ ስለ ሄደ በንጉሡ ቤት ታላቅ ሆኖ ነበርና፥ የመርዶክዮስም ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰምቶ ነበርና። 5 አይሁድም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሉአቸው፥ አጠፉአቸውም፤ በሚጠሉአቸውም ላይ እንደ ወደዱ አደረጉባቸው። 6 አይሁድም በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ አጠፉም። 78 ፈርሰኔስ፥ ደልፎን፥ ፋስጋ፥ ፋረዳታ፥ 9 በርያ፥ ሰርባካ፥ መርመሲማ፥ ሩፋዮስ፥ አርሳዮስ፥ ዛቡታዮስ የሚባሉትን፥ 10 የሐመዳቱን ልጅ የአይሁድን ጠላት አሥሩን የሐማን ልጆች ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። 11 በዚያም ቀን በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ቍጥር ወደ ንጉሡ መጣ። 12 ንጉሡም ንግሥቲቱን አስቴርን። አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችንና አሥሩን የሐማ ልጆች ገደሉ አጠፉአቸውም፤ በቀሩትስ በንጉሡ አገሮች እንዴት አድርገው ይሆን! አሁንስ ልመናሽ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ ሌላስ የምትሺው ምንድር ነው? ይደረጋል አላት። 13 አስቴርም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው በሱሳ የሚኖሩ አይሁድ ዛሬ እንደ ተደረገው ትእዛዝ ነገ ደግሞ ያድርጉ፤ አሥሩም የሐማ ልጆች በግንድ ላይ ይሰቀሉ አለች። 14 ንጉሡም ይህ ይደረግ ዘንድ አዘዘ፤ አዋጅም በሱሳ ተነገረ፤ አሥሩንም የሐማን ልጆች ሰቀሉ። 15 በሱሳም የነበሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ደግሞ ተሰብስበው በሱሳ ሦስት መቶ ያህል ሰዎች ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። 16 የቀሩትም በንጉሡ አገር ያሉ አይሁድ ተሰብስበው ለሕይወታቸው ቆሙ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ፤ ከሚጠሉአቸውም ሰባ አምስት ሺህ ገደሉ፤ ነገር ግን ወደ ብዝበዛው እጃቸውን አልዘረጉም። 17 አዳር በሚባለው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ተደረገ፤ በአሥራ አራተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉ። 18 በሱሳ የነበሩት አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን ተሰበሰቡ፤ በአሥራ አምስተኛውም ቀን ዐረፉ፥ የመጠጥና የደስታም ቀን አደረጉት። 19 ስለዚህም በመንደሮችና ባልተመሸጉ ከተሞች የሚኖሩ አይሁድ አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የደስታና የመጠጥ የመልካምም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል። 20 መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈ፥ በንጉሡም በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። 21 በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቀን፥ 22 አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ፥ የግብዣና የደስታም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ያደርጉት ዘንድ አዘዛቸው። 23 አይሁድም ለመሥራት የጀመሩትን፥ መርዶክዮስም የጻፈላቸውን ያደርጉ ዘንድ ተቀበሉት፤ 24 አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ የአይሁድ ሁሉ ጠላት ሐማ አይሁድን ያጠፋ ዘንድ ተተንኵሎ ነበር፤ ሊደመስሳቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የሚባል ዕጣ ጥሎ ነበር። 25 አስቴርም ወደ ንጉሡ ፊት በገባች ጊዜ በአይሁድ ላይ የተተነኰለው ክፉ ተንኰል በራሱ ላይ እንዲመለስ፥ እርሱና ልጆቹም በግንድ ላይ እንዲሰቀሉ በደብዳቤው አዘዘ። 26 ስለዚህም እነዚህ ቀኖች እንደ ፉር ስም ፉሪም ተባሉ። በዚህም ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ቃል ሁሉ፥ ስላዩትና ስላገኙአቸውም ነገር ሁሉ፥ 27 28 አይሁድ እነዚህን ሁለት ቀኖች እንደ ጽሕፈቱና እንደ ጊዜው በየዓመቱ ይጠብቁ ዘንድ፥ እነዚህም ቀኖች በየትውልዳቸውና በየወገናቸው በየአገራቸውም በየከተማቸውም የታሰቡና የተከበሩ ይሆኑ ዘንድ፥ እነዚህም የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ እንዳይሻሩ፥ መታሰባቸውም ከዘራቸው እንዳይቈረጥ፥ በራሳቸውና በዘራቸው ወደ እነርሱም በተጠጉት ሁሉ ላይ እንዳይቀር ሥርዓት አድርገው ተቀበሉ። 29 የአቢካኢልም ልጅ ንግሥቲቱ አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ይህችን ስለ ፉሪም የምትናገረውን ሁለተኛይቱን ደብዳቤ በሥልጣናቸው ሁሉ ያጸኑአት ዘንድ ጻፉ። 30 ደብዳቤዎቹንም በአርጤክስስ መንግሥት በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ወዳሉ አይሁድ ሁሉ በሰላምና በእውነት ቃል ላኩ። 31 እነዚህንም የፉሪም ቀኖች፥ አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥቲቱ አስቴር እንዳዘዙ፥ ለራሳቸውና ለዘራቸውም የጾማቸውንና የልቅሶአቸውን ነገር ለማክበር እንደ ተቀበሉ፥ በየጊዜያቸው ያጸኑ ዘንድ ጻፉ። 32 የአስቴርም ትእዛዝ ይህን የፉሪምን ነገር አጸና፤ በመጽሐፍም ተጻፈ።

አስቴር 10

1 ንጉሡም አርጤክስስ በምድርና በባሕር ደሴቶች ላይ ግብር ጣለ። 2 የኃይሉና የብርታቱም ሥራ ሁሉ ንጉሡም እስከ ምን ድረስ እንዳከበረው የመርዶክዮስ ክብር ታላቅነት፥ በሜዶንና በፋርስ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 3 አይሁዳዊውም መርዶክዮስ ለንጉሡ ለአርጤክስስ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤ በአይሁድም ዘንድ የከበረ፥ በብዙ ወንድሞችም ዘንድ የተወደደ፥ ለሕዝቡም መልካምን የፈለገ፥ ለዘሩም ሁሉ በደኅና የተናገረ ነበረ።

ኢዮብ 1

1 ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። 2 ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር። 3 ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። 4 ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። 5 የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ። ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር። 6 ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። 7 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 8 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። 9 ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት። በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? 10 እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። 11 ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል። 12 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ። 13 አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር። 14 መልክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ። በሬዎች እርሻ ያርሱ፥ በአጠገባቸውም አህዮች ይሰማሩ ነበር፤ 15 የሳባም ሰዎች አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 16 እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፥ በጎቹንም አቃጠለች፥ ጠባቂዎችንም በላች፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 17 እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ከለዳውያን በሦስት ረድፍ ተከፍለው በግመሎች ላይ አደጋ ጣሉ፥ ወሰዱአቸውም፥ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 18 እርሱም ገና ሲናገር ሌላ መጥቶ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤ 19 እነሆም፥ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፥ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፥ ሞቱም፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው። 20 ኢዮብም ተነሣ መጐናጸፊያውንም ቀደደ፥ ራሱንም ተላጨ፥ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 21 እንዲህም አለ። ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን። 22 በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፥ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።

ኢዮብ 2

1 ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ። 2 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። 3 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፤ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል። 4 ሰይጣንም መልሶ እግዚአብሔርን። ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። 5 ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው። 6 እግዚአብሔም ሰይጣንን። ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው። 7 ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው። 8 ሥጋውንም ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። 9 ሚስቱም። እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው) ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፥ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች። 10 እርሱ ግን አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም። 11 ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፤ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው በልዳዶስ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ። 12 ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፤ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 13 ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፤ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተዋልና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።

ኢዮብ 3

1 ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ። 2 ኢዮብም መለሰ እንዲህ አለ። 3 ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥ ያም። ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት። 4 ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤ እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥ ብርሃንም አይብራበት። 5 ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፤ ዳመናም ይረፍበት፤ የቀን ጨለማ ሁሉ ያስፈራው። 6 ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፤ በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤ በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር። 7 እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፤ እልልታ አይግባበት። 8 ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት። 9 አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤ ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥ የንጋትንም ቅንድብ አይይ፤ 10 የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥ መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና። 11 በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም? ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም? 12 ጕልበቶች ስለ ምን ተቀበሉኝ? ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ? 13 አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤ አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤ 14 የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥ 15 ወይም ቤታቸውን ብር ከሞሉ ወርቅም ካላቸው መኳንንት ጋር፥ 16 ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፥ ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር። 17 ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፤ በዚያም ደካሞች ያርፋሉ። 18 በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም። 19 ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፤ ባሪያም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል። 20 በመከራ ላሉት ብርሃን፥ ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥ 21 የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥ 22 መቃብርን ባገኙ ጊዜ በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ? 23 መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥ እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ? 24 ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥ ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል። 25 የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል። 26 ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፤ ነገር ግን መከራ መጣብኝ።

ኢዮብ 4

1 ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ። 2 አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀየማለህን? ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው? 3 እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥ 4 ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥ አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር። 5 አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፤ ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ። 6 አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥ የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን? 7 እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው? 8 እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥ መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ። 9 በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥ በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ። 10 የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥ የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ። 11 አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥ የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ። 12 ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች። 13 በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥ የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥ 14 አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ። 15 መንፈስም በፊቴ አለፈ፤ የሥጋዬ ጠጕር ቆመ። 16 እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤ የዝምታ ድምፅ ሰማሁ። 17 በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን? 18 እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፤ መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤ 19 ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥ መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥ ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ? 20 በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤ ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ። 21 ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን? አለጥበብም ይሞታሉ።

ኢዮብ 5

1 አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ? 2 ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል። 3 ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ። 4 ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም። 5 የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ። 6 ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፤ 7 የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል። 8 እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር። 9 የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል። 10 በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል። 11 የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል። 12 እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል። 13 ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል። 14 በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። 15 ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ ከኃያሉም እጅ ያድነዋል። 16 ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤ ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች። 17 እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። 18 እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ። 19 በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም። 20 በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። 21 ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም። 22 በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤ 23 ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። 24 ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም። 25 ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ። 26 በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ። 27 እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።

ኢዮብ 6

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ! 3 ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል። 4 ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል። 5 በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን? 6 የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን? 7 ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ። 8 ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ! 9 እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ! 10 መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና። 11 እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው? 12 ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን? 13 በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን? 14 ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል። 15 ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ። 16 ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፤ 17 ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ። 18 በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ። 19 የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው። 20 ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው። 21 አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ። 22 በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤ ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤ 23 ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤ ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን? 24 አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ። 25 የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል? 26 ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን? 27 በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ። 28 አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም። 29 እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ። 30 በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?

ኢዮብ 7

1 በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን? 2 አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ 3 እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። 4 በተኛሁ ጊዜ። መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። 5 ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፤ ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል። 6 ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥ ያለ ተስፋም ያልቃል። 7 ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፤ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። 8 የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፤ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። 9 ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። 10 ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም። 11 ስለዚህም አፌን አልከለክልም፤ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፤ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ። 12 ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን? 13 እኔም። አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ 14 አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤ 15 ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች። 16 ሕይወቴን ናቅኋት፤ ለዘላለም ልኖር አልወድድም። የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ። 17 ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ 18 ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? 19 የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? 20 ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ? ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ? ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? 21 ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።

ኢዮብ 8

1 ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ። 2 እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል? 3 በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን? 4 ልጆችህ በድለውት እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል። 5 እግዚአብሔርን ብትገሠግሥ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትለምን፥ 6 ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት አሁን ስለ አንተ ይነቃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያከናውንልሃል። 7 ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል። 89 ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፤ ምንም አናውቅም፤ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤ 10 እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? 11 በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን? 12 ገና ሲለመልም ሳይቈረጥም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል። 13 እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፤ የዝንጉም ሰው ተስፋ ይጠፋል። 14 ተስፋው ይቈረጣል፥ እምነቱም እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል። 15 ቤቱን ይደግፈዋል፥ አይቆምለትም፤ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም። 16 ፀሐይም ሳይተኵስ ይለመልማል፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል። 17 በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፤ የድንጋዮቹን ቦታ ይመለከታል። 18 ከቦታው ቢጠፋ። አላየሁህም ብሎ ይክደዋል። 19 እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፤ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ። 20 እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የኃጢአተኞችንም እጅ አያበረታም። 21 አፍህን እንደ ገና ሳቅ ይሞላል፥ ከንፈሮችህንም እልልታ ይሞላል። 22 የሚጠሉህ እፍረት ይለብሳሉ፤ የኃጢአተኞችም ድንኳን አይገኝም።

ኢዮብ 9

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 በእውነት እንዲህ እንደ ሆነ አወቅሁ፤ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል? 3 ከእርሱ ጋር ይከራከር ዘንድ ቢወድድ፥ ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም። 4 ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ ደፍሮትስ በደኅና የሄደ ማን ነው? 5 ተራሮችን ይነቅላል፤ አያውቁትም፤ በቍጣውም ይገለብጣቸዋል። 6 ምድርን ከስፍራው ያናውጣታል፥ ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ። 7 ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፤ ከዋክብትንም ያትማል። 8 ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥ በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል። 9 ድብ የሚባለውን ኮከብና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥ በደቡብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደርያዎች ሠርቶአል። 10 የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥ የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል። 11 እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፤ ቢያልፍብኝም አላውቀውም። 12 እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው? እርሱንስ። ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? 13 እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፤ ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ። 14 ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥ ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 15 ጻድቅ ብሆን ኖሮ አልመልስለትም ነበር፤ ወደ ፈራጄም እለምን ነበር። 16 ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን እንደ ሰማ አላምንም ነበር። 17 በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። 18 እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። 19 የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፤ የፍርድ ነገር ቢሆን። ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል። 20 ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፤ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። 21 ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፤ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። 22 ይህ ሁሉ አንድ ነው፤ ስለዚህ። ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ። 23 መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል። 24 ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፤ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፤ እርሱ ካልሆነ ማን ነው? 25 ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤ ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም። 26 የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋል። 27 እኔ። የኀዘን እንጕርጕሮዬን እረሳለሁ፤ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥ 28 ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ እፈራለሁ። 29 በደለኛ እንደሚሆን ሰው እሆናለሁ፤ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ? 30 በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ 31 በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል። 32 እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። 33 እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! 34 በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፤ 35 እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፤ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።

ኢዮብ 10

1 ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፤ የኀዘን እንጕርጕሮዬን እለቀዋለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ። 2 እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ። አትፍረድብኝ፤ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ። 3 ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅ የኃጥአንንስ ምክር ልታበራ በአንተ ዘንድ መልካም ነውን? 4 በውኑ የሥጋ ዓይን አለህን? ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን? 56 ወይስ ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥ ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፥ ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን? 7 ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ። 8 እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም፤ ከዚያም በኋላ ዞረህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ። 9 እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ፤ ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን? 10 በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን? 11 ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥ በአጥንትና በጅማትም አጠንከርኸኝ። 12 ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፤ መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች። 13 እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ። ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ። 14 ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፤ ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም። 15 በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፤ ጕስቍልናን ተሞልቻለሁ፥ መከራዬንም ተመልክቻለሁ። 16 ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤ ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ 17 ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፤ ቍጣህንም ታበዛብኛለህ፤ ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ። 18 ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ። 19 እንዳልነበረ በሆንሁ፤ ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ። 20 የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን? 21 ወደማልመለስበት ስፍራ፥ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥ 22 እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።

ኢዮብ 11

1 ነዕማታዊውም ሶፋር መለስ እንዲህም አለ። 2 በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን? ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን? 3 ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን? ብትሳለቅስ የሚያሳፍርህ የለምን? 4 አንተ። ትምህርቴ የተጣራ ነው፥ በዓይንህም ፊት ንጹሕ ነኝ ትላለህ። 5 ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት! 6 የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ማስተዋሉ ብዙ ነውና። እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ። 7 የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን? 8 ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ? 9 ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል። 10 እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥ የሚከለክለው ማን ነው? 11 ምናምንቴዎችን ሰዎች ያውቃልና፥ በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም። 12 የሜዳ አህያ ግልገል ሰው ሆኖ ቢወለድ፥ ያን ጊዜ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል። 13 14 በእጅህ በደል ቢኖር አርቀው፤ በድንኳንህም ኃጢአት አይኑር፤ አንተ ልብህን ቅን ብታደርግ፥ እጅህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፥ 15 በዚያን ጊዜ በእውነት ፊትህን ያለ ነውር ታነሣለህ፤ ትበረታለህ፥ አትፈራምም። 16 መከራህንም ትረሳለህ፤ እንዳለፈ ውኃ ታስበዋለህ። 17 ከቅትር ይልቅ ሕይወትህ ይበራል፤ ጨለማም ቢሆን እንደ ጥዋት ይሆናል። 18 ተስፋም ስላለህ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤ በዙሪያህ ትመለከታለህ፥ በደኅንነትም ታርፋለህ። 19 ትተኛለህ፥ የሚያስፈራህም የለም፤ ብዙ ሰዎችም ልመና ያቀርቡልሃል። 20 የክፉዎች ዓይን ግን ትጨልማለች፤ የሚሸሹበትንም ያጣሉ፥ ተስፋቸውም ነፍሳቸውን ማውጣት ነው።

ኢዮብ 12

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናቸሁ፤ ጥበብም ከእናንተ ጋር ይሞታል። 3 ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ማስተዋል አለኝ፤ ከእናንተም የማንስ አይደለሁም፤ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው? 4 እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፤ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል። 5 ተዘልሎ በሚቀመጥ ሰው አሳብ መከራ ይናቃል፤ ነገር ግን እግሩን ሊያድጠው ተዘጋጅቶአል። 6 የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል። 7 አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል። 8 ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል። 9 የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው? 10 የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት። 11 ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን? 12 በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፥ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል። 13 በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው። 14 እነሆ፥ ይፈርሳል፥ የፈረሰውም ተመልሶ አይሠራም፤ በሰውም ቢዘጋበት የሚከፍትለት የለም። 15 እነሆ፥ ውኆቹን ይከለክላል፥ እነርሱም ይደርቃሉ፤ እንደ ገና ይሰድዳቸዋል፥ ምድሪቱንም ይገለብጣሉ። 16 ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው። 17 መካሮችንም እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ያሳብዳል። 18 የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል። 19 ካህናትን እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል። 20 ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል። 21 በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል። 22 ጥልቅ ነገር ከጨለማ ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል። 23 አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፤ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል። 24 ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ይወስዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል። 25 ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፤ እንደ ሰካራም ይቅበዘበዛሉ።

ኢዮብ 13

1 እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፤ ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው። 2 እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፤ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም። 3 ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥ ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ። 4 እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፤ ሁላችሁ የማትጠቅሙ ባለ መድኃኒቶች ናችሁ። 5 ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ! ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር። 6 አሁንም ክርክሬን ስሙ፥ የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ። 7 በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን? ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን? 8 ለፊቱስ ታደላላችሁን? ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን? 9 ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን? ወይስ በሰው እንደምትሳለቁ ትሳለቁበታላችሁን? 10 በስውር ለሰው ፊት ብታደሉ ዘለፋ ይዘልፋችኋል። 11 ክብሩስ አያስፈራችሁምን? ግርማውስ አይወድቅባችሁምን? 12 ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፤ ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው። 13 ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፤ የሆነው ነገር ይምጣብኝ። 14 ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ። 15 እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ። 16 ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምና እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል። 17 ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥ ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ። 18 እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ። እንደምጸድቅም አውቃለሁ። 19 ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው? አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ። 20 ነገር ግን ሁለት ነገር አታድርግብኝ፤ የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤ 21 እጅህን ከእኔ አርቅ፤ ግርማህም አታስደንግጠኝ። 22 ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ። ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ። 23 ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው? መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ። 24 ፊትህን ከእኔ የሰወርህ፥ እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ስለ ምን ነው? 25 የረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን? ወይስ የደረቀውን ዕብቅ ታሳድዳለህን? 26 የመረረ ነገር ጽፈህብኛልና፤ የሕፃንነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ። 27 እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥ መንገዴንም ሁሉ መርምረሃል፤ የእግሬን ፍለጋ ወስነሃል። 28 እኔ እንደሚጠፋ በስባሳ ነገር፥ ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።

ኢዮብ 14

1 ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል። 2 እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም። 3 እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዓይኖችህን ትከፍታለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን? 4 ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም። 5 የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት። 6 እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል። 7 ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው። 8 ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥ 9 ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል። 10 ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ? 11 ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፤ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል። 12 ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም። 13 በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! 14 በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። 15 በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር። 16 አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፤ ኃጢአቴንም ትጠባበቃለህ። 17 መተላልፌ በከረጢት ውስጥ ታትሞአል፥ ኃጢአቴንም ለብጠህበታል። 18 ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፤ 19 ውኆች ድንጋዮቹን ይፍቃሉ፤ ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤ እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ። 20 ለዘላለም ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ። 21 ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም። 22 ነገር ግን የገዛ ሥጋው ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል። ች

ኢዮብ 15

1 ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ። 2 በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ንፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን? በሆዱስ የምሥራቅን ነፋስ ይሞላልን? 3 ከማይረባ ነገር፥ ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን? 4 አንተም እግዚአብሔርን መፍራት ታፈርሳለህ፤ በእግዚአብሔር ፊት አምልኮን ታስቀራለህ። 5 በደልህ አፍህን ያስተምረዋል፥ የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ። 6 የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል። 7 በውኑ መጀመሪያ የተወለድህ ሰው አንተ ነህን? ወይስ ከተራሮች በፊት ተፀነስህን? 8 የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን? ወይስ ጥበብን ለብቻህ አድርገሃልን? 9 እኛ የማናውቀውን አንተ የምታወቀው ምንድር ነው? ከእኛ ዘንድስ የሌለው የምታስተውለው ምንድር ነው? 10 በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ። 11 በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥ በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን? 12 ልብህስ ለምን ይወስድሃል? ዓይኖችህስ ለምን ይገለምጣሉ? 13 በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን እስከ ማንሣት ደርሰህ፤ ይህንም ቃል ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ። 14 ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው? 15 እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። 16 ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥ ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ? 17 18 ምድሪቱ ለብቻቸው ተሰጥታ የነበረች፥ 19 በመካከላቸውም እንግዳ ያልገባባቸው ጠቢባን። ከአባቶቻቸው ተቀብለው የተናገሩትን ያልሸሸጉትንም፥ እገልጥልሃለሁ፥ ስማኝ፤ ያየሁትንም እነግርሃለሁ። 20 ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፥ ከግፈኛ በተመደቡለት በዓመታት ሁሉ በሕመም ይጣጣራል። 21 የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፤ በደኅንነቱም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል። 22 ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ አያምንም፥ ሰይፍም ይሸምቅበታል። 23 ተቅበዝብዞም። ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፤ የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል። 24 መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፤ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል፤ 25 እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ ላይ ደፍሮአልና፥ 26 በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው ጕብጕብ እየሠገገ ይመጣበታልና፥ 27 በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥ ስቡንም በወገቡ ላይ አድርጓልና፥ 28 በተፈቱም ከተሞች ውስጥ፥ ሰውም በሌለባቸው፥ ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና 29 ባለጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፤ ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፤ 30 ከጨለማ አይወጣም፤ ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥ አበባዎቹም ይረግፋሉ። 31 ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን። 32 ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥ ቅርንጫፉም አይለመልምም። 33 እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፤ እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል። 34 የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፥ የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች። 35 ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥ ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።

ኢዮብ 16

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፤ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ። 3 በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው? 4 እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፤ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር። 5 በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፤ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር። 6 እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፤ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም። 7 አሁን ግን አድክሞኛል፤ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል። 8 መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፤ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፤ በፊቴም ይመሰክርብኛል። 9 በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፤ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፤ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፤ 10 እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፤ እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ። 11 እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፉዎችም እጅ ጣለኝ። 12 ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፤ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፤ እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ። 13 ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤ ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፤ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ። 14 በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፤ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል። 15 በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ። 16 ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፤ የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፤ 17 ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው። 18 ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን። 19 አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው። 20 ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥ ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ። 21 የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ! 22 ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።

ኢዮብ 17

1 መንፈሴ ደከመ፥ ዘመኔ አለቀ፥ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል። 2 አላጋጮች በእኔ ዘንድ አሉ፥ ዓይኔም በማስቈጣታቸው አደረች። 3 አሁንም አንተ መያዣ ሆነህ ተዋሰኝ፤ ከእኔ ጋር አጋና የሚመታ ማን ነው? 4 ልባቸውም እንዳያስተውል ከልክለኸዋል፤ ስለዚህ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም። 5 ለብዝበዛ ባልንጀሮቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዓይን ይጨልማል። 6 ለሕዝብም ምሳሌ አደረገኝ፤ በፊቱ ላይ ጺቅ እንደሚሉበት ሰው ሆንሁ። 7 ዓይኔም ከኀዘን የተነሣ ፈዘዘች፥ ብልቶቼም ሁሉ እንደ ጥላ ሆኑ። 8 ቅኖች ሰዎች በዚህ ነገር ይደነቃሉ፥ ንጹሕም በዝንጉው ላይ ይበሳጫል። 9 ጻድቅ ግን መንገዱን ያጠነክራል፥ እጁም ንጹሕ የሆነ ሰው ኃይልን እየጨመረ ይሄዳል። 10 ነገር ግን እናንተ ሁሉ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ፤ በእናንተም ዘንድ ብልሃተኛ አላገኝም። 11 ዕድሜዬ አለፈች፤ አሳቤና የልቤ መሣርያ ተቈረጠ። 12 ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤ ብርሃኑም ወደ ጨለማ የቀረበ ይመስላቸዋል። 13 ተስፋ ባደርግ ሲኦል ቤቴ ናት፤ ምንጣፌንም በጨለማ ዘርግቻለሁ። 14 መበስበስን። አንተ አባቴ ነህ፤ ትልንም። አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ። 15 እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው? 16 አብረን በመሬት ውስጥ ስናርፍ፥ ወደ ሲኦል ይወርዳል።

ኢዮብ 18

1 ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ። 2 እስከ መቼ ቃልን ታጠምዳለህ? አስተውል፥ ከዚያም በኋላ እንናገራለን። 3 ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን? ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ረከስን? 4 ቍጣ ወርሶሃል፤ አንተስ የሞትህ እንደ ሆነ፥ ምድር ስለ አንተ ባድማ ትሆናለችን? ወይስ ዓለት ከስፍራው ይነቀላልን? 5 የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም። 6 ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱም በላዩ ይጠፋል። 7 የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች። 8 እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብም ላይ ይሄዳል። 9 አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ ወስፈንጠርም ይበረታበታል። 10 በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች። 11 ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥ በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች። 12 ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል። 13 የሰውነቱ ብልቶች ይጠፋሉ፤ የሞትም በኵር ልጅ ብልቶቹን ይበላል። 14 ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፤ ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኵሉታል። 15 በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፤ በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል። 16 ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ ጫፉም ከበላይ ይረግፋል። 17 መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥ በሜዳም ስም አይቀርለትም። 18 ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ ከዓለምም ያሳድዱታል። 19 ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፤ በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም። 20 የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥ እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ። 21 በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።

ኢዮብ 19

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ነፍሴን የምትነዘንዙ፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው? 3 ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም። 4 በእውነትም የሳትሁ እንደ ሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች። 5 በእውነትም ብትጓደዱብኝ፥ መዋረዴን በእኔ ላይ ብትከራከሩ፥ 6 እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ ገለበጠኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ። 7 እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ አሰምቼም ብጠራ ፍርድ የለኝም። 8 እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል። 9 ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ። 10 በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፤ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፤ 11 ቍጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ። 12 ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ። 13 ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ። 14 ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ። 15 ቤተ ሰቦቼና ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ። 16 ባሪያዬን ብጠራ፥ በአፌም ባቈላምጥ አይመልስልኝም። 17 ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ልመናዬን ጠሉ። 18 ሕፃናቶች እንኳ አጠቁኝ፤ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ። 19 አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ። 20 አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፤ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ። 21 እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ማሩኝ። 22 ስለ ምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለ ምን አትጠግቡም? 23 ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! 24 ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ! 25 እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ 26 ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። 27 እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። 28 በእውነት። እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ 29 ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቍጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።

ኢዮብ 20

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ነፍሴን የምትነዘንዙ፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው? 3 ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም። 4 በእውነትም የሳትሁ እንደ ሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች። 5 በእውነትም ብትጓደዱብኝ፥ መዋረዴን በእኔ ላይ ብትከራከሩ፥ 6 እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ ገለበጠኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ። 7 እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ አሰምቼም ብጠራ ፍርድ የለኝም። 8 እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል። 9 ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ። 10 በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፤ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፤ 11 ቍጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ። 12 ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ። 13 ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ። 14 ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ። 15 ቤተ ሰቦቼና ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ። 16 ባሪያዬን ብጠራ፥ በአፌም ባቈላምጥ አይመልስልኝም። 17 ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ልመናዬን ጠሉ። 18 ሕፃናቶች እንኳ አጠቁኝ፤ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ። 19 አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ። 20 አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፤ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ። 21 እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ማሩኝ። 22 ስለ ምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለ ምን አትጠግቡም? 23 ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! 24 ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ! 25 እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ 26 ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። 27 እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። 28 በእውነት። እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ 29 ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቍጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።

ኢዮብ 21

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፤ ይህም መጽናናታችሁ ይሁን። 3 እናገር ዘንድ ተዉኝ፤ ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ። 4 በውኑ የኀዘን እንጉርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን? አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም? 5 ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤ እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ። 6 እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥ ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል። 7 ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ? ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ? 8 ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው። 9 ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም። 10 ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፤ ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም። 11 ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥ ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ። 12 ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥ በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል። 13 ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤ ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ። 14 እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም። 15 እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው? ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ። 16 እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን? የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት። 17 የኃጥአን መብራት የጠፋው፥ መቅሠፍትም የመጣባቸው፥ እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥ 18 በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው? 19 እናንተ። እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል። እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል። 20 ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ። 21 የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥ ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል? 22 ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔር በውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን? 23 አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል። 24 በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥ የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል። 25 ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ በተመረረች ነፍስ ይሞታል። 26 በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ ትልም ይከድናቸዋል። 27 እነሆ፥ አሳባችሁን፥ የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ። 28 እናንተ። የከበርቴው ቤት የት ነው? ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል። 29 መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን? ምልክታቸውን አታውቁምን? 30 ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥ በቍጣው ቀን እንደሚድን። 31 መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው? የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው? 32 እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥ ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ። 33 የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤ በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥ በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ። 34 የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?

ኢዮብ 22

1 ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ። 2 በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን? በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል። 3 ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን? መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን? 4 እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን? 5 ክፋትህስ የበዛ አይደለምን? ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም። 6 የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥ የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል። 7 ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥ ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል። 8 በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፤ ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት። 9 መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፤ የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል። 10 ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል። 11 እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥ የውኆችም ብዛት አሰጠመህ። 12 እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን? ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት። 13 አንተም። እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን? 14 እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፤ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል። 15 በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን? 16 ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ። 17 እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት። 18 ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤ የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት። 19 ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፤ ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል። 20 በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥ የቀረውንም እሳት በላች። 21 አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። 22 ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ 23 ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ 24 የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ 25 ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። 26 የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። 27 ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ። 28 ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል። 29 ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፤ ትሑቱንም ሰው ያድነዋል። 30 ንጹሑን ሰው ያድነዋል፤ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።

ኢዮብ 23

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ዛሬም ደግሞ የኅዘን እንጕርጕሮዬ ገና መራራ ነው፤ እጁ በልቅሶ ጩኸቴ ላይ ከብዳለች። 3 እርሱን ወዴት እንዳገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ! 4 በፊቱ ሙግቴን አዘጋጅ ነበር፥ አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር። 5 የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደ ሆነ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር። 6 በኃይሉ ብዛት ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? እንኳን! ያደምጠኝ ነበር። 7 ቅን ሰው ከእርሱ ጋር በዚያ ይከራከር ነበር፤ እኔም ከፈራጄ ለዘላለም እድን ነበር። 8 እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እርሱም የለም፤ ወደ ኋላም እሄዳለሁ፥ እኔም አላስተውለውም፤ 9 ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤ በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፤ 10 የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ። 11 እግሬ ወደ እርምጃው ተጣብቆአል፤ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም። 12 ከከንፈሩ ትእዛዝ አልተመለስሁም፤ የአፉን ቃል በልቤ ሰውሬአለሁ። 13 እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል። 14 በእኔ ላይ የተወሰነውን ይፈጽማል፤ እንደዚህም ያለ ብዙ ነገር በእርሱ ዘንድ አለ። 15 ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤ ባሰብሁም ጊዜ ከእርሱ ፈራሁ። 16 እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል። 17 ከጨለማው የተነሣ፥ ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን ከመክደኑ የተነሣ አልደነገጥሁም።

ኢዮብ 24

1 ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም? 2 የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፤ መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ። 3 የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፤ የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ። 4 ድሆቹን ከመንገዱ ያወጣሉ፤ የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ። 5 እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥ መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፤ ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል። 6 እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፤ የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ። 7 ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥ በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም። 8 ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፤ መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ። 9 ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉ ከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ። 10 ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፤ ተርበውም ነዶዎችን ይሸከማሉ፤ 11 በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፤ ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ። 12 ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፤ የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፤ እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም። 13 እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፤ መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም። 14 ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፤ ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፤ በሌሊትም እንደ ሌባ ነው። 15 የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል። የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። 16 ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፤ በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንም አያውቁም። 17 የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤ የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና። 18 እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፤ እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም። 19 ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፤ እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች። 20 ማኅፀን ትረሳዋለች፤ ትልም በደስታ ይጠባዋል፤ ዳግመኛም አይታሰብም፤ ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል። 21 የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፤ ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም። 22 ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። 23 እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥ በዚያም ይታመናሉ፤ ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው። 24 ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፤ እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፤ እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ። 25 እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው?

ኢዮብ 25

1 ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ። 2 ገዢነትና መፈራት በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ በከፍታውም ሰላም አድራጊ ነው። 3 በውኑ ለሠራዊቶቹ ቍጥር አላቸውን? ብርሃኑስ የማይወጣው በማን ላይ ነው? 4 ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል? 5 እነሆ፥ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለም፥ ከዋክብትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም። 6 ይልቁንስ ብስብስ የሆነ ሰው፥ ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ!

ኢዮብ 26

1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ። 2 ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው! 3 ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት! 4 ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ? 5 ሙታን ሰዎች ከውኆች በታች፥ በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ በታች ይንቀጠቀጣሉ። 6 ሲኦል በፊቱ ራቁትዋን ናት፥ ለጥፋትም መጋረጃ የለውም። 7 ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል። 8 ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፥ ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም። 9 የዙፋኑን ፊት ይከድናል፥ ደመናውንም ይዘረጋበታል። 10 ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥ በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አደረገ። 11 የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ። 12 በኃይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥ በማስተዋሉም ረዓብን ይመታል። 13 በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች። 14 እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?

ኢዮብ 27

1 ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ። 2 ፍርዴን ያስወገደ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም መራራ ያደረገ ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን! 3 እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥ 4 ከንፈሬ ኃጢአትን አትናገርም፥ አንደበቴም ሽንገላን አያወጣም። 5 እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፤ እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም። 6 ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም፤ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም። 7 ጠላቴ እንደ በደለኛ፥ በእኔ ላይም የሚነሣ እንደ ኃጢአተኛ ይሁን። 8 እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በለየ ጊዜ፥ የዝንጉ ሰው ተስፋው ምንድር ነው? 9 በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን? 10 ሁሉንስ በሚችል አምላክ ደስ ይለዋልን? እግዚአብሔርንስ ሁልጊዜ ይጠራልን? 11 እኔ ስለ እግዚአብሔር እጅ አስተምራችኋለሁ፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውን አልሸሽግም። 12 እነሆ፥ ሁላችሁ አይታችኋል፤ ስለ ምን ከንቱ ሆናችሁ? 13 ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ እድል ፈንታ፥ ግፈኛም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበላት ርስት ናት፤ 14 ልጆቹ ቢበዙ ለሰይፍ ይሆናሉ፤ ዘሩም እንጀራን አይጠግብም። 15 ለእርሱም የቀሩት በቸነፈር ይቀበራሉ፤ መበለቶቻቸውም አያለቅሱም። 16 እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢከምር፥ ልብስንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥ 17 እርሱ ያዘጋጀው ይሆናል፥ ነገር ግን ጻድቅ ይለብሰዋል፤ ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል። 18 የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር ይሠራል፥ ጠባቂም እንደሚሠራው ጎጆ ነው። 19 ባለጠጋ ሆኖ ይተኛል፥ ዳግመኛም አይተኛም፤ ዓይኑን ይከፍታል፥ እርሱም የለም። 20 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ታገኘዋለች፤ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች። 21 የምሥራቅ ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ይሄዳል፤ ከቦታውም ይጠርገዋል። 22 እርሱ ይጥልበታል፥ አይራራለትም፤ ከእጁ ፈጥኖ መሸሽ ይወድዳል። 23 ሰው በእጁ ያጨበጭብበታል፤ ከስፍራውም በፉጨት ያስወጡታል።

ኢዮብ 28

1 በእውነት ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ። 2 ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፤ መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል። 3 ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፤ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል። 4 ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ፤ ከሰውም እግር ተረሱ፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ። 5 እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤ በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል። 6 ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥ የወርቅም ድቃቂ አለው። 7 መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዓይን አላየውም። 8 የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም። 9 ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል። 10 ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች። 11 ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል። 12 ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? 13 ሰው መንገድዋን አያውቅም፤ በሕያዋን ምድር አትገኝም። 14 ቀላይ። በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፤ ባሕርም። በእኔ ዘንድ የለችም ይላል። 15 በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥ ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም። 16 በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም። 17 ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም። 18 ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል። 19 የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም። 20 እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? 21 ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች። 22 ጥፋትና ሞት። ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል። 23 እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል። 24 እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል። 25 ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥ 26 ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥ 27 በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት። 28 ሰውንም። እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።

ኢዮብ 29

1 ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ። 2 እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ! 3 በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥ 4 በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥ 5 ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥ 6 መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ። 7 ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥ 8 ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ። 9 አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ። 10 የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤ ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ። 11 የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤ 12 የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና። 13 ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፤ የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ። 14 ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ። 15 ለዕውር ዓይን፥ ለአንካሳ እግር ነበርሁ። 16 ለድሀው አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ። 17 የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ። 18 እኔም አልሁ። በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤ 19 ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤ 20 ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል። 21 ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ። 22 ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፤ ንግግሬም በእርሱ ላይ ተንጠባጠበ። 23 ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፤ የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ። 24 እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም። 25 መንገዳቸውን መረጥሁ፤ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።

ኢዮብ 30

1 አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ። 2 ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርና የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል? 3 በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤ የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበት ወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ። 4 በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውን ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤ የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው። 5 ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል። 6 በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ። 7 በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤ ከሳማ በታች ተሰብስበዋል። 8 የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው። 9 አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው። 10 ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም። 11 የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል። 12 በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ይገለብጣሉ፤ የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ። 13 ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ። 14 በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤ በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል። 15 ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤ ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች። 16 አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤ የመከራም ዘመን ያዘችኝ። 17 በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥ ጅማቶቼም አያርፉም። 18 ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤ እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ። 19 እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ። 20 ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም። 21 ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በእጅህም ብረታት አስጨነቅኸኝ። 22 በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ። 23 ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና። 24 ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን? 25 ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን? 26 ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤ ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ። 27 አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤ የመከራም ዘመን መጣችብኝ። 28 ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ። 29 ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ። 30 ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤ አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች። 31 ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ።

ኢዮብ 31

1 ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ? 2 የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው? 3 መዓትስ ለኃጢአተኛ፥ መለየትስ ለሚበድሉ አይደለምችን? 4 መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን? 56 በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ። በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥ 7 እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥ 8 እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል። 9 ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥ 10 ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ። 11 ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤ 12 ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና። 13 ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥ 14 እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ? 15 እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን? 16 ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥ 17 እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤ 18 እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤ 19 ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥ 20 ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥ በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፤ 21 በበሩ ረዳት ስላየሁ፥ በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥ 22 ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር። 23 የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፤ በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም። 24 ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ ጥሩውንም ወርቅ። በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤ 25 ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤ 26 ፀሐይ ሲበራ ጨረቃ በክብር ስትሄድ አይቼ፥ 27 ልቤ በስውር ተታልሎ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤ 28 ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር። 29 በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፤ 30 ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻት አንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፤ 31 በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች። በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፤ 32 መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤ 33 በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፤ 34 ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፤ 35 የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ! እነሆ የእጄ ምልክት ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤ ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ! 36 በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፤ 37 የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥ እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር። 38 እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፤ 39 ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥ የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥ 40 በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥ በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ። የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።

ኢዮብ 32

1 ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። 2 ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። 3 ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። 4 ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር። 5 ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ። 6 የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ። እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። 7 እንደዚህም አልሁ። ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። 8 ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። 9 በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም። 10 ስለዚህም። ስሙኝ፤ እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ። 11 እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤ ብልሃታችሁን አዳመጥሁ። 12 እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም። 13 እናንተም። ጥበብን አግኝተናል፤ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ። 14 እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፤ እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም። 15 እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፤ የሚናገሩትንም አጡ። 16 እነርሱ አልተናገሩምና፥ ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን? 17 እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥ እውቀቴንም እገልጣለሁ፤ 18 እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥ በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና። 19 በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥ ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ። 20 ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፤ ከንፈሬን ገልጬ እመልሳለሁ። 21 ለሰው ፊት ግን አላደላም፤ ሰውንም አላቈላምጥም። 22 በማቈላመጥ እናገር ዘንድ አላውቅምና፤ ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር።

ኢዮብ 33

1 ነገር ግን፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ። 2 እነሆ፥ አፌን ከፍቻለሁ፥ አንደበቴም በትናጋዬ ተናግሮአል። 3 ቃሌ የልቤን ቅንነት ያወጣል፤ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ። 4 የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ። 5 ይቻልህ እንደ ሆነ መልስልኝ፤ ቃልህንም አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም። 6 እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ። 7 እነሆ፥ ግርማዬ አታስፈራህም እጄም አትከብድብህም። 8 በጆሮዬ ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፥ እንዲህም ብለሃል። 9 እኔ ያለ መተላለፍ ንጹሕ ነኝ፤ ያለ ነውር ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፤ 10 እነሆ፥ ምክንያት አግኝቶብኛል፥ እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤ 11 እግሬን በግንድ አጣበቀ፥ መንገዴንም ሁሉ ተመለከተ። 12 እነሆ፥ አንተ በዚህ ጻድቅ አይደለህም፤ እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል ብዬ እመልስልሃለሁ። 13 አንተ። ለቃሌ ሁሉ አይመልስልኝም ብለህ፥ ስለ ምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ? 14 እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም። 15 በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ 16 በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ 17 ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤ 18 ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል። 19 ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል። 20 ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች። 21 ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፤ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል። 22 ነፍሱ ወደ ጕድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች። 23 የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጕም መልአክ ቢገኝለት፥ 24 እየራራለት። ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው ቢለው፥ 25 ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል። 26 ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ሞገስን ይሰጠዋል ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፤ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል። 27 እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ። እኔ በድያለሁ፥ ቅኑንም አጣምሜአለሁ፤ የሚገባኝንም ብድራት አልተቀበልሁም፤ 28 ነፍሴ ወደ ጕድጓድ እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች ይላል። 29 እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፤ 30 ይህም ነፍሱን ከጕድጓድ ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው። 31 ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ። 32 ነገር ቢኖርህ መልስልኝ፤ ትጸድቅ ዘንድ እወድዳለሁና ተናገር። 33 ያለዚያም እኔን ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።

ኢዮብ 34

1 ኤሊሁም ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ። 2 እናንተ ጥበበኞች፥ ቃሌን ስሙ፤ እናንተም አዋቂዎች፥ ወደ እኔ አድምጡ። 3 ትናጋ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን ትለያለችና። 4 ቅን የሆነውን ነገር እንምረጥ፤ መልካሙንም ነገር በመካከላችን እንወቅ። 5 ኢዮብ። እኔ ጻድቅ ነኝ፥ እግዚአብሔር ግን ፍርዴን አስወገደ፤ 6 ምንም እውነተኛ ብሆን እንደ ውሸተኛ ተቈጠርሁ፤ ምንም ባልበድል ቍስሌ የማይፈወስ ነው ብሎአል። 789 ኢዮብም። በእግዚአብሔር መደሰት ለሰው ምንም አይጠቅምም ብሎአልና ከበደለኞች ጋር የሚተባበር፥ ክፉ ከሚያደርጉስ ጋር የሚሄድ፥ መሳለቅን እንደ ውኃ የሚጠጣት እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው? 10 ስለዚህ እናንተ አእምሮ ያላችሁ ሰዎች፥ ስሙኝ፤ ክፋትን ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር፥ በደልንም ይሠራ ዘንድ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ። 11 ለሰው ሥራውን ይመልስለታል፥ ሰውም እንደ መንገዱ ያገኝ ዘንድ ያደርጋል። 12 በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም። 13 ምድርን አደራ የሰጠው ማን ነው? ዓለምንስ ሁሉ በእርሱ ላይ ያኖረ ማን ነው? 14 እርሱ ልቡን ወደ ራሱ ቢመልስ፥ መንፈሱንና እስትንፋሱን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፥ 15 ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል። 16 አስተዋይ ብትሆን ይህን ስማ፤ የንግግሬንም ቃል አድመጥ። 17 በውኑ ጽድቅን የሚጠላ ይሠለጥናልን? ጻድቅና ኃያል የሆነውስ በደለኛ ታደርገዋለህን? 18 ማንም ሰው ንጉሡን። በደለኛ ነህ፥ መኳንንቱንም። ክፉዎች ናችሁ ይላልን? 19 እነርሱ ሁሉ የእጁ ሥራ ናቸውና በአለቆች ፊት አያደላም፥ ባለጠጋውንም ሰው ከድሀው ይበልጥ አይመለከትም። 20 እነርሱ በመንፈቀ ሌሊት በድንገት ይሞታሉ፤ ሕዝቡ ተንቀጥቅጦ ያልፋል፥ ኃያላንም ያለ እጅ ይነጠቃሉ። 21 ዓይኖቹ በሰው መንገድ ላይ ናቸው፥ እርምጃውንም ሁሉ ያያል። 22 ኃጢአትን የሚሠሩ ይሰወሩበት ዘንድ ጨለማ ወይም የሞት ጥላ የለም። 23 ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመፈራረድ እንዲመጣ ጊዜ አይወሰንለትም። 24 ታላላቆችን ያለ ምርመራ ይሰባብራል፥ በእነርሱም ፋንታ ሌሎችን ያቆማል። 25 ሥራቸውን ያውቃል፤ እንዲደቅቁም በሌሊት ይገለባብጣቸዋል። 26 ሰዎች እያዩ እንደ ክፉዎች ይመታቸዋል፤ 27 28 የድሀውን ልቅሶ ወደ እርሱ ያደርሱ ዘንድ፥ እርሱም የችግረኛውን ድምፅ ይሰማ ዘንድ፥ እርሱን ከመከተል ፈቀቅ ብለዋልና፥ ከመንገዱም ሁሉ አንዱን አልተመለከቱምና። 29 በሕዝብ ወይም በሰው ዘንድ ቢሆን፥ እርሱ ቢያሳርፍ የሚፈርድ ማን ነው? ፊቱንስ ቢሰውር የሚያየው ማን ነው? 30 ይህም ዝንጉ ሰው እንዳይነግሥ፥ ሕዝቡም የሚያጠምድ እንዳይኖር ነው። 31 እግዚአብሔርን። እኔ ሳልበድል ቅጣት ተቀበልሁ፤ 32 የማላየውን ነገር አንተ አስተምረኝ፤ ኃጢአትንም ሠርቼ እንደ ሆነ፥ ደግሜ አልሠራም የሚለው ማን ነው? 33 በውኑ አንተ ጥለኸዋልና ፍዳው አንተ እንደምትወድደው ይሆናልን? አንተ ትመርጣለህ እንጂ እኔ አይደለሁም፤ ስለዚህ የምታውቀውን ተናገር። 34 የሚሰሙኝ ጥበበኞች ሁሉ፥ አስተዋዮችም እንዲህ ይሉኛል። 35 ኢዮብ ያለ እውቀት ተናግሮአል፥ ቃሉም በአእምሮ አይደለችም። 36 ኢዮብ እስከ ፍጻሜ ድረስ ምነው በተፈተነ ኖሮ! እርሱ እንደ ክፉዎች መልሶአልና፤ 37 በኃጢአቱም ላይ ዓመፅን ጨምሮአልና፥ በእኛም መካከል በእጁ ያጨበጭባልና፥ ቃልንም በእግዚአብሔር ላይ ያበዛልና።

ኢዮብ 35

1 ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ። 2 ይህ ጽድቅ እንደ ሆነ ታስባለህን? ወይስ። በእግዚአብሔር ፊት እኔ ጻድቅ ነኝ ትላለህን? 3 አንተ። ምን ጥቅም አለህ? ኃጢአት ሠርቼ ከማገኘው ይልቅ ኃጢአት ባልሠራ ኖሮ ምን እጠቀማለሁ? ብለህ ጠይቀሃልና። 4 እኔ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉ ለባልንጀሮችህ እመልሳለሁ። 5 ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ እይ፤ ከአንተም ከፍ ከፍ ያሉትን ደመናት ተመልከት። 6 ኃጢአት ብትሠራ ምን ትጐዳዋለህ? መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ? 7 ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል? 8 እንደ አንተ ያለውን ሰው ክፋትህ ይጐዳዋል፤ ለሰውም ልጅ ጽድቅህ ይጠቅመዋል። 9 ከግፍ ብዛት የተነሣ ሰዎች ይጮኻሉ፤ ከኃያላንም ክንድ የተነሣ ለእርዳታ ይጠራሉ። 10 11 ነገር ግን። በሌሊት መዝሙርን የሚሰጥ፥ ከምድርም እንስሶች ይልቅ የሚያስተምረን ከሰማይም ወፎች ይልቅ ጥበበኞች የሚያደርገን፤ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም። 12 በዚያ ስለ ክፉ ሰዎች ትዕቢት ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይመልስላቸውም። 13 በእውነት እግዚአብሔር ከንቱ ነገርን አይሰማም፥ ሁሉን የሚችል አምላክም አይመለከተውም፤ 14 ይልቁንም። አላየውም፤ ነገሩ በእርሱ ፊት ነው፥ እኔም አጠብቀዋለሁ ስትል። 15 አሁን ግን በቍጣው አልጐበኘምና። በኃጢአት እጅግ አያስብም ትላለህ። 16 ስለዚህ ኢዮብ አፉን በከንቱ ይከፍታል፥ ያለ እውቀትም ቃሉን ያበዛል።

ኢዮብ 36

1 ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ። 2 ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ። 3 እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ፈጣሪዬንም። ጻድቅ ነው እላለሁ። 4 ቃሌ በእውነት ያለ ሐሰት ነው፤ በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ። 5 እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፤ እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው። 6 እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤ ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል። 7 ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፤ ለዘላለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ። 8 በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥ 9 ሥራቸውንና መተላለፋቸውን በትዕቢትም እንዳደረጉ ይናገራቸዋል። 10 ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥ ከኃጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል። 11 ቢሰሙ ቢያገለግሉትም፥ ዕድሜአቸውን በልማት፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ። 12 ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥ ያለ እውቀትም ይሞታሉ። 13 ዝንጉዎች ግን ቍጣን ያዘጋጃሉ፤ እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም። 14 በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥ ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል። 15 የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፤ በመከራም ጆሮአቸውን ይገልጣል። 16 እንዲሁም አንተን ከመከራ ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥ በማዕድህ ላይ የተዘጋጀውም ስብ በሞላበት ነበር። 17 አንተ ግን በበደለኞች ፍርድ የተሞላህ ነህ፤ ስለዚህ ፍርድና ብይን ይይዝሃል። 18 ቍጣ ለስድብ አያታልልህ፤ የማማለጃም ብዛት ፈቀቅ አያድርግህ። 19 ባለጠግነትህ የኃይልህም ብርታት ሁሉ ያለ ችግር እንድትሆን ሊረዳህ ይችላልን? 20 ወገኖች ከስፍራቸው የሚወጡበትን ሌሊት አትመኝ። 21 ከመከራ ይልቅ ይህን መርጠሃልና ኃጢአትን እንዳትመለከት ተጠንቀቅ። 22 እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው? 23 መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ። ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው? 24 ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ። 25 ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል። 26 እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። 27 የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፤ 28 ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ። 29 የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው? 30 እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፤ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል። 31 በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ብዙም ምግብ ይሰጣል። 32 እጆቹን በብርሃን ይሰውራል፥ በጠላቱም ላይ ይወጣ ዘንድ ያዝዘዋል፤ 33 የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፤ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።

ኢዮብ 37

1 ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥ ከስፍራውም ተንቀሳቀሰ። 2 የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ። 3 እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል። 4 በስተ ኋላው ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም። 5 እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። 6 በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ። በምድር ላይ ውደቁ ይላል። 7 ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። 8 አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ። 9 ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥ ከሰሜንም ብርድ ይወጣል። 10 ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ተሰጥቶአል፤ የውኆችም ስፋት ይጠብባል። 11 የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፤ የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፤ 12 13 ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረት ቢሆን፥ ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል። 14 ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ። 15 በውኑ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያዝዛቸው፥ የደመናውንም ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን? 16 ወይስ የደመናውን ሚዛን፥ ወይስ በእውቀት ፍጹም የሆነውን ተአምራት አውቀሃልን? 17 በደቡብ ነፋስ ምድር ጸጥ ባለች ጊዜ፥ ልብስህ የሞቀች አንተ ሆይ፥ 18 እንደ ቀለጠ መስተዋት ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን? 19 እኛ ከጨለማ የተነሣ በሥርዓት መናገር አንችልምና የምንለውን አስታውቀን። 20 ማንም በእርሱ ላይ ቢናገር ፈጽሞ ይዋጣልና እኔ እናገር ዘንድ ብወድድ ሰው ይነግረዋልን? 21 አሁንም ነፋስ አልፎ ካጠራቸው በኋላ፥ ሰው በሰማያት የሚበራውን ብርሃን ሊመለከት አይችልም። 22 ከሰሜን ወርቅ የሚመስል ጌጠኛ ብርሃን ይወጣል፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈራ ግርማ አለ። 23 ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፤ በኃይል ታላቅ ነው፤ በፍርድና በጽድቅም አያስጨንቅም። 24 ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤ በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም።

ኢዮብ 38

1 እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ። 2 ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? 3 እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። 4 ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር። 5 ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? 67 አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? 8 ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? 9 ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤ 10 ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ። 11 እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፤ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ። 12 13 የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን? ለወገግታም ስፍራውን አስታወቀኸዋልን? 14 ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፤ ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል። 15 ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል። 16 ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን? 17 የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን? 18 ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር። 19 20 ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ? 21 በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፤ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። 22 በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? 23 ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው። 24 ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል? 25 26 ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ 27 ሣሩንም እንዲያበቅል፥ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥ ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥ ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? 28 በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? 29 በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? 30 ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል። 31 በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? 32 ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? 33 የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን? 34 የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? 35 መብረቆች ሄደው። እነሆ፥ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ ልትልካቸው ትችላለህን? 36 በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? 37 38 የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው? 39 40 በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን? 41 ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?

ኢዮብ 39

1 የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን? ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን? 2 እርስዋ የምትፈጽመውንስ ወራት ትቈጥራለህን? የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን? 3 ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥ ከምጣቸውም ያርፋሉ። 4 ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥ በሜዳም ያድጋሉ፤ ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም። 5 የሜዳውስ አህያ አርነት ማን አወጣው? የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው? 6 በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፤ መኖሪያውም በጨው ምድር ነው። 7 በከተማ ውካታ ይዘብታል፤ የነጂውን ጩኸት አይሰማም። 8 ተራራውን እንደ መሰምርያው ይመለከተዋል፥ ለምለሙንም ሁሉ ይፈልጋል። 9 ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን? ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን? 10 ጐሽ ይተልምልህ ዘንድ ትጠምደዋለህን? ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጕላልን? 11 ጕልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ ትታመነዋለህን? ተግባርህንስ ለእርሱ ትተዋለህን? 12 ዘርህንስ ይመልስልህ ዘንድ፥ በአውድማህስ ያከማችልህ ዘንድ ትታመነዋለህን? 13 የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፤ ነገር ግን ክንፉና ላባው ጭምተኛ ነውን? 14 እንቍላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥ በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፤ 15 እግር ይሰብረው ዘንድ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይረግጠው ዘንድ ትረሳለች። 16 የእርስዋ እንዳልሆኑ በልጆችዋ ትጨክናለች። በከንቱም ብትሠራ አትፈራም፤ 17 እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥ ማስተዋልንም አልሰጣትምና። 18 ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች። 19 ለፈረስ ጕልበቱን ሰጥተኸዋልን? አንገቱንስ ጋማ አልብሰኸዋልን? 20 እንደ አንበጣስ አፈናጠርኸውን? የማንኰራፋቱ ክብር የሚያስፈራ ነው። 21 በኮቴው በሸለቆው ውስጥ ይጐደፍራል፥ በጉልበቱም ደስ ይለዋል፤ ሰይፍም የታጠቁትን ለመገናኘት ይወጣል። 22 በፍርሃት ላይ ይስቃል፥ እርሱም አይደነግጥም፤ ከሰይፍም ፊት አይመለስም። 23 በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆና ብልጭልጭ የሚል ጦር ሰላጢንም ያንኳኳሉ። 24 በጭካኔና በቍጣ መሬትን ይውጣል፤ የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም። 25 የመለከትም ድምፅ ሲሰማ። እሰይ! ይላል፤ ከሩቅ ሆኖ ሰልፍንና የአለቆቹን ጩኸት፥ የሠራዊቱንም ውካታ ያሸታል። 26 በውኑ ከጥበብህ የተነሣ ጭልፊት ያንዣብባልን? ወይስ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ይዘረጋልን? 27 በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን? 28 በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል። 29 በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጐበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች። 30 ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፤ በድን ባለባትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።

ኢዮብ 40

1 እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው። 2 በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት። 3 ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው። 4 እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ። 5 አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፤ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም። 6 እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ። 7 እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። 8 በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን? 9 እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን? 10 በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፤ በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ። 11 የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው። 12 ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፤ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው። 13 በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን። 14 በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ። 15 ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል። 16 እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው። 17 ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው። 18 አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፤ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው። 19 እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው። 20 የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል። 21 ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል። 22 ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል። 23 እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል። 24 ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን? [25]፤ በውኑ አዞውን በመቃጥን ታወጣለህን? ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን? [26]፤ ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር ጕንጩን ትበሳለህን? [27]፤ በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን? በጣፈጠስ ቃል ይናገርሃልን? [28]፤ በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘላለም ባሪያ ታደርገዋለህን? [29]፤ ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ ለሴት ባሪያዎችህ ታስረዋለህን? [30]፤ አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን? ወይስ ነጋዴዎች ያካፍሉታልን? [31]፤ በውኑ ቁርበቱን በጭሬ፥ ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን? [32]፤ እጅህን በላዩ ጫን፤ ሰልፉን አስብ፥ እንግዲህም አትድገም።

ኢዮብ 41

1 እነሆ፥ ተስፋው ከንቱ ነው፤ ያየው ሁሉ ስንኳ በፊቱ ይዋረዳል። 2 ያንቀሳቅሰውም ዘንድ የሚደፍር የለም፤ እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው? 3 እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው? ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው። 4 ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥ ስለ መልካም ሰውነቱ ዝም አልልም። 5 የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል? በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል? 6 የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ። 7 ቅርፊቶቹ ጠንካራ ስለ ሆኑ እርሱ ትዕቢተኛ ነው፤ በጠባብ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው። 8 እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም። 9 እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል። 10 እንጥሽታው ብልጭታ ያወጣል፥ ዓይኖቹም እንደ ወገግታ ናቸው። 11 ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥ የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል። 12 እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል። 13 እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥ ነበልባልም ከአፉ ይወጣል። 14 በአንገቱ ኃይል ታድራለች፤ ግርማ በፊቱ ይዘፍናል። 15 የሥጋውም ቅርፊት የተጣበቀ ነው፤ እስከማይንቀሳቀሱም ድረስ በእርሱ ላይ ጸንተዋል። 16 ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፤ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው። 17 በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፤ ከድንጋጤም የተነሣ ያብዳሉ። 18 ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም። 19 ብረትን እንደ ገለባ፥ ናስንም እንደ ነቀዘ እንጨት ይቈጥራቸዋል። 20 ፍላጻ ሊያባርረው አይችልም፤ የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል። 21 በሎታውን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፤ ሰላጢኑም ሲሰበቅ ይስቃል። 22 ታቹ እንደ ስለታም ገል ነው፤ እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል። 23 ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፤ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል። 24 በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፤ ቀላዩም ሽበት ይመስላል። 25 ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም። 26 ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፤ በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።

ኢዮብ 42

1 ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው። 2 ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። 3 ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። 4 እባክህ፥ ስማኝ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። 5 መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ 6 ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ። 7 እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን። እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። 8 አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፤ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና። 9 ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ። 10 ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔርም ምርኮውን መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው። 11 ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፤ ስለ እርሱም አዘኑለት፥ እግዚአብሔርም ካመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አጽናኑት፤ እያንዳንዳቸውም ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት። 12 እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፤ አሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት። 13 ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት። 14 የመጀመሪያይቱንም ስም ይሚማ፥ የሁለተኛይቱንም ስም ቃስያ፥ የሦስተኛይቱንም ስም አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው። 15 እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆችም ያሉ የተዋቡ ሴቶች በአገሩ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። 16 ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ተውልድ ድረስ አየ። 17 ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ።

ዳዊት 1

1 ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። 2 ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። 3 እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። 4 ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። 5 ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም። 6 እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።

ዳዊት 2

1 አሕዛብ ለምን ያጕረመርማሉ? ወገኖችስ ለምን ከንቱን ይናገራሉ? 2 የምድር ነገሥታት ተነሡ፥ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ። 3 ማሰርያቸውን እንበጥስ፥ ገመዳቸውንም ከእኛ እንጣል። 4 በሰማይ የሚኖር እርሱ ይሥቃል፥ ጌታም ይሣለቅባቸዋል። 5 በዚያን ጊዜ በቍጣው ይናገራቸዋል፥ በመዓቱም ያውካቸዋል። 6 እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። 7 ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ። 8 ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። 9 በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ። 10 አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። 11 ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። 12 ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።

ዳዊት 3

ከልጁ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸ ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ የሚያስጨንቁኝ ምንኛ በዙ! በኔ ላይ የሚቆሙት ብዙ ናቸው። 2 ብዙ ሰዎች ነፍሴን። አምላክሽ አያድንሽም አልዋት። 3 አንተ ግን አቤቱ፥ መጠጊያዬ ነህ፥ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ። 4 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር እጮሃለሁ ከተቀደሰ ተራራውም ይሰማኛል። 5 እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም፤ እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ። 6 ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም። 7 ተነሥ፥ አቤቱ፤ አምላኬ ሆይ፥ አድነኝ፤ አንተ የጠላቶቼን መንጋጋ መትተሃልና፥ የክፉዎችንም ጥርስ ሰብረሃልና። 8 ማዳን የእግዚአብሔር ነው፥ በረከትህም በሕዝብህ ላይ ነው።

ዳዊት 4

1 ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር። 1 የጽድቄ አምላክ በጠራሁት ጊዜ መለሰልኝ፥ በጭንቀቴም አሰፋህልኝ፤ ማረኝ፥ ጸሎቴንም ስማ። 2 እናንት የሰው ልጆች፥ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? 3 እግዚአብሔር በጻድቁ እንደ ተገለጠ እወቁ፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል። 4 ተቈጡ፥ ነገር ግን ኃጢአትን አታድርጉ፤ በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ። 5 የጽድቅን መሥዋዕት ሠዉ፥ በእግዚአብሔርም ታመኑ። 6 በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። 7 በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። 8 በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።

ዳዊት 5

ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ቃሌን አድምጥ፥ ጩኸቴንም አስተውል፤ 2 የልመናዬን ቃል አድምጥ፥ ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁና። 3 በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም። 4 አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም። 5 በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ። 6 ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል። 7 እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ። 8 አቤቱ፥ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፤ መንገዴን በፊትህ አቅና። 9 በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፤ ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ። 10 አቤቱ፥ ፍረድባቸው፥ በምክራቸውም ይውደቁ፤ ስለ ክፋታቸውም ብዛት አሳድዳቸው፥ እነርሱ ዐምፀውብሃልና። 11 በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ግን ደስ ይላቸዋል፤ ለዘላለሙ ደስ ይላቸዋል፥ እነርሱንም ትጠብቃለህ፤ ስምህንም የሚወድዱ ሁሉ በአንተ ይመካሉ። 12 አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፤ አቤቱ፥ እንደ ጋሻ በሞገስ ከለልኸን።

ዳዊት 6

ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ስለ ስምንተኛ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። 2 ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ። 3 ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? 4 አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ። 5 በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው? 6 በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ። 7 ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች፤ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ። 8 ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና። 9 እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ። 10 ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።

ዳዊት 7

1 አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥ 2 ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር። 3 አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህስ ካደረግሁ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥ 4 ክፉ ላደረጉብኝም ክፉን መልሼላቸው ብሆን፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ብሆን፥ 5 ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት። 6 አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቍጣ ተነሣባቸው፤ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ። 7 የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ። 8 እግዚአብሔር በአሕዛብ ይፈርዳል፤ አቤቱ፥ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ። 9 የኃጥኣን ክፋት ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፤ እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል። 10 እግዚአብሔር የጽድቅ ጋሻዬ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው። 11 እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፥ ኃይለኛም ታጋሽም ነው፥ ሁልጊዜም አይቈጣም። 12 ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤ 13 የሞት መሣርያንም አዘጋጀበት፥ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ። 14 እነሆ፥ በዓመፃ ተጨነቀ ጉዳትን ፀነሰ ኃጢአትንም ወለደ። 15 ጕድጓድን ማሰ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል። 16 ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች። 17 እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።

ዳዊት 8

ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና። 2 ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት። 3 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ 4 ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? 5 ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። 6 በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ 7 በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ 8 የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ። 9 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ።

ዳዊት 9

ለመዘምራን አለቃ፤ በሙትላቤን፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ። 2 በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ። 3 ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ። 4 ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ። 5 አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ። 6 ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ። 7 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤ 8 እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል። 9 እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው። 10 ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና። 11 በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤ 12 ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና። 13 አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤ 14 ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል። 15 አሕዛብ በሠሩት ጕድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች። 16 እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው፤ ኃጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ። 17 ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ። 18 ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም። 19 አቤቱ፥ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው። 20 አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው ጫንባቸው፤ አሕዛብ ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ።

ዳዊት 10

1 አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ? 2 በኃጢአተኛ ትዕቢት ድሀ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ። 3 ኃጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳልና፥ ዓመፀኛም ይባርካል። 4 ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም። 5 መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶችንም ሁሉ ይገዛቸዋል። 6 በልቡ ይላል። ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም። 7 አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው። 8 በመንደሮች መሸመቅያ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፤ ዓይኖቹም ወደ ድኃ ይመለከታሉ። 9 እንደ አንበሳ በችፍግ ዱር በስውር ይሸምቃል፤ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል። 10 ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል። 11 በልቡም ይላል። እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ። 12 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችን አትርሳ። 13 ኃጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ። አይመራመረኝም ይላልና። 14 አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቍጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፤ ድሀ ራሱን ለአንተ ይተዋል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ። 15 የኃጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ የኃጢአቱንም ብድራት ክፈል ሌላ እስከማይገኝ ድረስ። 16 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ። 17 እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች፥ 18 ፍርዱ ለድሀ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳይደግሙ።

ዳዊት 11

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ ነፍሴን። እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ እንዴት ትሉአታላችሁ? 2 ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ። 3 አንተ የሠራኸውን እነሆ እነርሱ አፍርሰዋልና፤ ጻድቅ ግን ምን አደረገ? 4 እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነው፤ እግዚአብሔር፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፤ ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ። 5 እግዚአብሔር ጻድቅንና ኅጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል። 6 ወጥመድ በኅጥኣን ላይ ያዘንባል እሳትና ዲን ዐውሎ ነፋስም የጽዋቸው እድል ፈንታ ነው። 7 እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፤ ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች።

ዳዊት 12

ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ስምንተኛ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና። 2 እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ። 3 የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ፤ 4 ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈራችን የእኛ ነው፥ ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን። 5 ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር። አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ። 6 በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው። 7 አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን። 8 በሰው ልጆች ዘንድ ምናምንቴ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ሁሉ ይመላለሳሉ።

ዳዊት 13

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ? 2 እስከ መቼ በነፍሴ እመካከራለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ሁልጊዜ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይጓደዳል? 3 አቤቱ አምላኬ፥ እየኝ ስማኝም፤ ጠላቴ። አሸነፍሁት እንዳይል፥ 4 የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ። 5 እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ፥ ልቤም በመድኃኒትህ ደስ ይለዋል። 6 የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ።

ዳዊት 14

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም። 2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። 3 ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም። 4 ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤ 5 ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤ 6 ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም። 7 ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም። 8 በዚያ በታላቅ ፍርሃት እጅግ ፈሩ፥ እግዚአብሔር በጻድቃን ትውልድ ዘንድ ነውና። 9 የድሆችን ምክር አሳፈራችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ተስፋቸው ነው። 10 ከጽዮን መድኃኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።

ዳዊት 15

1 አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? 2 በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር። 3 በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ ዘመዶቹንም የማይሰድብ። 4 ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም። 5 ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።

ዳዊት 16

1 የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። 2 እግዚአብሔርን። አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። 3 ፈቃድህ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳንና ክቡራን ላይ ነው። 4 ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፤ የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም። 5 እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ። 6 ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ። 7 የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኵላሊቶቼ ይገሥጹኛል። 8 ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። 9 ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤ 10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። 11 የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።

ዳዊት 17

የዳዊት ጸሎት። 1 አቤቱ፥ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ፤ በተንኰለኛም ከንፈር ያልሆነውን ጸሎቴን አድምጥ። 2 ፍርዴ ከፊትህ ይውጣ፥ ዓይኖችህም በቅንነት ይዩ። 3 ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም። 4 የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ። 5 እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። 6 አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ። 7 የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው። 8 እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ፥ 9 ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ። 10 አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ። 11 አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፤ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ። 12 እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጕጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው። 13 አቤቱ፥ ተነሥ፤ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፤ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት። 14 አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ። 15 እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።

ዳዊት 18

ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር የተናገረው የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። እንዲህም አለ። 1 አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ። 2 እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው። 3 ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ። 4 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤ 5 የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ። 6 በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። 7 ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። 8 ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። 9 ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ። 10 በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ። 11 መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ። 12 በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ። 13 እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። 14 ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም። 15 አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። 16 ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። 17 ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። 18 በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ። 19 ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ። 20 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። 21 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። 22 ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። 23 በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። 24 እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ። 25 ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ 26 ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። 27 አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ። 28 አንተ መብራቴን ታበራለህና፤ እግዚአብሔር አምላኬ ጨለማዬን ያበራል። 29 በአንተ ከጥፋት እድናለሁና በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ። 30 የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። 31 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው? 32 ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥ 33 እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። 34 እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ። 35 ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም ለዘላለም ታጠናኛለች፥ ተግሣጽህም ታስተምረኛለች። 36 አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። 37 ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። 38 አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። 39 ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። 40 የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። 41 ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ አልሰማቸውም። 42 እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ። 43 ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። 44 በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ። 45 የባዕድ ልጆች አረጁ፥ በመንገዳቸውም ተሰናከሉ። 46 እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል። 47 በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል። 48 ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። 49 አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። 50 የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይሰጣል።

ዳዊት 19

ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። 2 ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። 3 ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። 4 ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። 5 በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ እንደ አርበኛ በመንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል። 6 አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙረቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም። 7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። 8 የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል። 9 የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው። 10 ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። 11 ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል። 12 ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። 13 የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። 14 አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።

ዳዊት 20

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 በመከራ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ። 2 ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ያጥናህ። 3 ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ። 4 እንደ ልብህ ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ። 5 በማዳንህ ደስ ይለናል፤ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፤ ልመናህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ። 6 እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፤ በቀኙ ብርታት ማዳን። 7 እነዚያ በሰረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን። 8 እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን። 9 አቤቱ፥ ንጉሥን አድነው፥ በጠራንህም ቀን ስማን።

ዳዊት 21

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል። 2 የልቡን ፈቃድ ሰጠኽው፥ የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም። 3 በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፤ ከክቡር ዕንቍ የሆነ ዘውድን በራሱ ላይ አኖርህ። 4 ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም፥ ለረጅም ዘመን ለዘላለሙ። 5 በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት። 6 የዘላለም በረከትን ሰጥተኸዋልና። በፊትህም ደስታ ደስ ታሰኘዋለህ። 7 ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም። 8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው። 9 በተቈጣህም ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ እግዚአብሔር በቍጣው ያጠፋቸዋል፥ እሳትም ትበላቸዋለች። 10 ፍሬአቸውን ከምድር ዘራቸውንም ከሰው ልጆች ታጠፋለህ። 11 ክፋትን በአንተ ላይ ዘርግተዋልና፥ የማይቻላቸውንም ምክር አሰቡ። 12 ወደ ኋላቸው ትመልሳቸዋለህ፤ ፍላጻን በፊታቸው ላይ ታዘጋጃለህ። 13 አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።

ዳዊት 22

ለመዘምራን አለቃ ስለ ንጋት ኃይል፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ። 2 አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፤ በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም። 3 በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅድስና ትኖራለህ። 4 አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው። 5 ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ አንተንም ተማመኑ አላፈሩም። 6 እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ። 7 የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ። 8 በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው። 9 አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ። 10 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ። 11 ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ። 12 ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም ፍሪዳዎች ያዙኝ፤ 13 እንደ ነጣቂና እንደሚጮኽ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ። 14 እንደ ውኃ ፈሰስሁ፤ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ። 15 ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ። 16 ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። 17 አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም። 18 ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። 19 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አንተ ጕልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። 20 ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥ ብቻነቴንም ከውሾች እጅ። 21 ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ብቻነቴንም አንድ ቀንድ ካላቸው። 22 ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ። 23 እግዚአብሔርን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፤ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት። 24 የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእኔ አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኽሁ ጊዜ ሰማኝ። 25 በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው። እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ። 26 ችግረኞች ይበላሉ፥ ይጠግቡማል፤ እግዚአብሔርንም የሚሹት ያመሰግኑታል፤ ልባቸውም ለዘላለም ሕያው ይሆናል። 27 የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሱ፤ የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ። 28 መንግሥት ለእግዚአብሔር ነውና፥ እርሱም አሕዛብን ይገዛል። 29 የምድር ደንዳኖች ሁሉ ይበላሉ ይሰግዳሉም፤ ወደ መሬት የሚወርዱት ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፤ ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች። 30 ዘሬ ይገዛለታል፤ የምትመጣው ትውልድ ለእግዚአብሔር ትነግረዋለች፤ 31 ጽድቁንም ለሚወለደው ሕዝብ፥ እግዚአብሔር ያደረገውን ጽድቁን፥ ይነግራሉ።

ዳዊት 23

የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። 2 በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። 3 ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። 4 በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል። 5 በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው። 6 ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።

ዳዊት 24

በመጀመሪያ ሰንበት የዳዊት መዝሙር። 1 ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ። 2 እርሱ በባሕሮች መሥርቶአታልና፥ በፈሳሾችም አጽንቶአታልና። 3 ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? 4 እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ። 5 እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል። 6 ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ። 7 እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። 8 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል። 9 እናንተ መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። 10 ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።

ዳዊት 25

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ። 2 አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ። 3 አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ። 4 አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ። 5 አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። 6 አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። 7 የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። 8 እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። 9 ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል። 10 የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። 11 አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ። 12 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል። 13 ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል። 14 እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል። 15 እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው። 16 እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም። 17 የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። 18 ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። 19 ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። 20 ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። 21 አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ። 22 አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።

ዳዊት 26

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እኔ በየውሃቴ ሄጃለሁና ፍረድልኝ፤ በእግዚአብሔርም አምኛለሁና አልናወጥም። 2 አቤቱ፥ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን። 3 ምሕረትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ። 4 በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም። 5 የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም። 6 እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ 7 የምስጋናን ድምፅ እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። 8 አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። 9 ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ። 10 በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች። 11 እኔ ግን በየውሃቴ ሄጃለሁ፤ አድነኝ ማረኝም። 12 እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።

ዳዊት 27

ሳይቀባ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? 2 ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ። 3 ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም፤ ሰልፍም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ። 4 እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ። 5 በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። 6 እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ። 7 አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ። ማረኝና አድምጠኝ። 8 አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ። አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ። 9 ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተውኝ። 10 አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። 11 አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ። 12 የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፈቃድ አትስጠኝ። 13 የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ። 14 እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።

ዳዊት 28

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ። 2 ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ። 3 ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ። 4 እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ። 5 ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም። 6 የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን። 7 እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ። 8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው። 9 ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።

ዳዊት 29

ከድንኳን በመውጣት ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 የአምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ። 2 የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። 3 የእግዚአብሔር ድምፅ በውኆች ላይ፥ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ። 4 የእግዚአብሔር ድምፅ በኃይል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ በታላቅ ክብር ነው። 5 የእግዚአብር ድምፅ ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል። 6 እንደ ጥጃ ሊባኖስን፥ አንድ ቀን እንዳለው አውሬ ልጅ ስርዮንን ያዘልላቸዋል። 7 የእግዚአብሔር ድምፅ የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል። 8 የእግዚአብሔር ድምፅ ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ እግዚአብሔር የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል። 9 የእግዚአብሔር ድምፅ ዋላዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ጫካዎቹንም ይገልጣል፤ ሁሉም በመቅደሱ። ምስጋና ይላል። 10 እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል። 11 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካል።

ዳዊት 30

ለቤቱ መመረቅ ምስጋና፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ተቀብለኸኛልና፥ ጠላቶቼንም ደስ አላሰኘህብኝምና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። 2 አቤቱ አምላኬ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ ምሕረትም አደረግህልኝ። 3 አቤቱ፥ ነፍሴን ከሲኦል አወጣሃት፥ ወደ ጕድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ። 4 ቅዱሳን ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ። 5 ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው፥ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን፤ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል። 6 እኔም በደስታዬ። ለዘላለም አልታወክም አልሁ። 7 አቤቱ፥ በፈቃድህ ለሕይወቴ ኃይልን ሰጠሃት፤ ፊትህን መለስህ፥ እኔም ደነገጥሁ። 8 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጠራሁ፥ ወደ አምላኬም ለመንሁ። 9 ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ? አፈር ያመሰግንሃልን? እውነትህንም ይናገራልን? 10 እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ሆነኝ። 11 ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፥ ማቄን ቀድደህ ደስታንም አስታጠቅኸኝ። 12 አቤቱ አምላኬ፥ ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።

ዳዊት 31

ለመዘምራን አለቃ፤ በማድነቅ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር፤ በጽድቅህም አድነኝ። 2 ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ፈጥነህም አድነኝ፤ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ሁነኝ። 3 አምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነህና ስለ ስምህ መንገዴን አቅና ምራኝም። 4 አንተ መታመኛዬ ነህና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ። 5 በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ፥ ተቤዥተኸኛል። 6 ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላህ፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ። 7 መከራዬን አይተሃልና፥ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ። 8 በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም፥ በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምህ። 9 ተቸግሬአለሁና አቤቱ ምራኝ፤ ዓይኔም ከኃዘን የተነሣ ተፈጀች፥ ነፍሴም ሆዴም። 10 ሕይወቴ በኅዘን አልቃለችና፥ ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት፤ ኃይሌ በችግር ደከመ፥ አጥንቶቼም ተነዋወጡ። 11 በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ፥ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ፥ ለሚያውቁኝም ፍርሃት ሆንሁ፤ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ። 12 እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፥ እንደ ተበላሸ ዕቃም ሆንሁ። 13 የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና፤ በዙሪያው ፍርሃት ነበረ፤ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴን ለመንጠቅ ተማከሩ። 14 አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ። 15 ርስቴ በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። 16 ፊትህን በባሪያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ። 17 አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ። 18 በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። 19 በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች! 20 በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ። 21 በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን። 22 እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ። 23 ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። 24 በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና።

ዳዊት 32

የዳዊት ትምህርት። 1 መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። 2 እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው። 3 ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ 4 በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፥ እርጥበቴም ለበጋ ትኵሳት ተለወጠ። 5 ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፥ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ። 6 ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፤ ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም። 7 አንተ ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፥ ከጣርም ትጠብቀኛለህ፤ ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ። 8 አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ። 9 ወደ አንተ እንዳይቀርቡ በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጕሙአቸው፥ ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ። 10 በኃጢአተኛ ብዙ መቅሠፍት አለበት፤ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ግን ምሕረት ይከብበዋል። 11 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሤትም አድርጉ፤ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ፥ እልል በሉ።

ዳዊት 33

የዳዊት መዝሙር። 1 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል። 2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት። 3 አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤ 4 የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። 5 ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች። 6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤ 7 የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው። 8 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ። 9 እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም። 10 እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል። 11 የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው። 12 እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። 13 እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። 14 ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥ 15 እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። 16 ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። 17 ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። 18 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ 19 ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ። 20 ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና። 21 ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። 22 አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።

ዳዊት 34

ባሳደደው በአቤሜሌክ ፊት መልኩን በለወጠ ጊዜ በሄደም ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፥ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው። 2 ነፍሴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፥ ገሮችም ሰምተው ደስ ይላቸዋል። 3 እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። 4 እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። 5 ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም። 6 ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው። 7 የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። 8 እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው። 9 የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት። 10 ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉትን ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም። 11 ልጆቼ ኑ፥ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ። 12 ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ? 13 አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። 14 ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም። 15 የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። 16 መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። 17 ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። 18 እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። 19 የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል። 20 እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። 21 ኃጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። 22 የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል፥ በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ አይጸጸቱም።

ዳዊት 35

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። 2 ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። 3 ሰይፍህን ምዘዝ የሚያሳድዱኝንም መንገዳቸውን ዝጋ፤ ነፍሴን። መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት። 4 ነፍሴን የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቈሉም፤ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይበሉ። 5 በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የእግዚአብሔርንም መልአክ ያስጨንቃቸው። 6 መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ያሳድዳቸው። 7 በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና። 8 ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፤ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። 9 ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። 10 አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል። አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ። 11 የክፋት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። 12 ስለ በጎ ክፋትን መለሱልኝ፥ ነፍሴንም ልጆችን አሳጡአት። 13 እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። 14 ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፤ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። 15 በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፤ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላውቅሁም፤ ቀደዱኝ አልተውኝምም። 16 ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቅጩ። 17 አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ታይልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብችነቴንም ከአንበሶች አድናት። 18 አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። 19 በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጣቀሱብኝ። 20 ለእኔስ ሰላምን ይናገሩኛልና፥ በቍጣም ሽንገላን ይመክራሉ። 21 አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፤ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ። 22 አቤቱ፥ አንተ አየኸው፤ ዝም አትበል፤ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ። 23 አምላኬ ጌታዬም፥ ወደ ፍርዴ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ። 24 አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በላዬም ደስ አይበላቸው። 25 በልባቸው። እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፤ ደግሞም። ዋጥነው አይበሉ። 26 በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቍሉ፤ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጕስቍልናን ይልበሱ። 27 ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፤ የባሪያውን ሰላም የሚወድድ እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ። 28 ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።

ዳዊት 36

ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። 1 ኃጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዓይኖቹ ፊት የለም። 2 በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል። 3 የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው፤ ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ። 4 በመኝታው ጠማማነትን አሰበ፤ መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፤ ክፋትን አይንቃትም። 5 አቤቱ፥ ምሕረትህ በሰማይ ነው፥ እውነትህም ወደ ደመናት ትደርሳለች። 6 ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች፥ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት፤ አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ። 7 አቤቱ፥ ምሕረትህን እንዴት አበዛህ! የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ። 8 ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ፥ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ። 9 የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን። 10 ምሕረትህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ። 11 የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የኃጢአተኞችም እጅ አያውከኝ። 12 ዓመፃን የሚያደርጉ ሁሉ ከዚያ ወደቁ፤ ወድቀዋል፥ መቆምም አይችሉም።

ዳዊት 37

የዳዊት መዝሙር። 1 በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ 2 እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። 3 በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። 4 በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። 5 መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። 6 ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል። 7 ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና። 8 ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና። 9 ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። 10 ገና ጥቂት፥ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። 11 ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። 12 ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለካከተዋል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል። 13 እግዚአብሔር ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና። 14 ኃጢአተኞች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፤ 15 ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። 16 ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ከኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል። 17 የኃጥአን ክንድ ትሰበራለችና፤ እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። 18 የንጹሓንን መንገድ እግዚአብሔር ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘላለም ነው፤ 19 በክፉ ዘመንም አያፍሩም በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። 20 ኅጥአን ግን ይጠፋሉ፥ የእግዚአብሔር ጠላቶች በከበሩና ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ እንደ ጢስ ይጠፋሉ። 21 ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም። 22 እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፤ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ። 23 የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል። 24 ቢወድቅም ለድንጋፄ አይጣልም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። 25 ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። 26 ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል። 27 ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ለዘላለምም ትኖራለህ። 28 እግዚአብሔር ፍርዱን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኅጥኣን ዘር ግን ይጠፋል። 29 ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ። 30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል። 31 የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም። 32 ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል። 33 እግዚአብሔር ግን በእጁ አይተወውም፥ በተፋረደውም ጊዜ አያሸንፈውም። 34 እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ። 35 ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። 36 ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። 37 ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። 38 በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል። 39 የጻድቃን መድኃኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። 40 እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከኃጢአተኞችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋል፥ በእርሱ ታምነዋልና።

ዳዊት 38

ለሰንበት መታሰቢያ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። 2 ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና። 3 ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። 4 ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና። 5 ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤ 6 እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ። 7 ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና። 8 ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ። 9 አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም። 10 ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ። 11 ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ። 12 ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ። 13 እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ። 14 እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። 15 አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ። 16 ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። 17 እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና። 18 በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ። 19 ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ። 20 ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል። 21 አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ። 22 አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

ዳዊት 39

ለመዘምራን አለቃ፥ ለኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር። 1 በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ። 2 ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ። 3 ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ። 4 አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። 5 እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው። 6 በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። 7 አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው። 8 ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ። 9 አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም። 10 መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና። 11 በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ ነፍሱም እንደ ሸረሪት ድር ታልቃለች፤ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው። 12 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፤ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና። 13 ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ።

ዳዊት 40

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 ቆይቼ እግዚአብሔር ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኽቴንም ሰማኝ። 2 ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፥ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፥ አረማመዴንም አጸና። 3 አዲስ ዝማሬን ለአምላካችን ምስጋና በአፌ ጨመረ፤ ብዙዎች ያያሉ ይፈሩማል፥ በእግዚአብሔርም ይታመናሉ። 4 እግዚአብሔርን የታመነ ወደ ትዕቢተኛና ወደ ሐሰተኛ ያልተመለከተ ሰው ምስጉን ነው። 5 አቤቱ አምላኬ፥ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፥ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ። 6 መሥዋዕትንና ቍርባንን አልወደድህም፤ ሥጋን አዘጋጀህልኝ፤ የሚቃጠለውንና ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልሻህም። 7 በዚያን ጊዜ አልሁ። እነሆ፥ መጣሁ፤ ስለ እኔ በመጽሐፍ ራስ ተጽፎአል፤ 8 አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው። 9 በታላቅ ጉባኤ ጽድቅን አወራሁ፤ እነሆ፥ ከንፈሮቼን አልከለክልም፤ አቤቱ፥ አንተ ጽድቄን ታውቃለህ። 10 እውነትህንም በልቤ ውስጥ አልሰወርሁም፥ ማዳንህንም ተናገርሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን ከታላቅ ጉባኤ አልሰወርሁም። 11 አቤቱ፥ አንተ ምሕረትህን ከእኔ አታርቅ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ። 12 ቍጥር የሌላት ክፋት አግኝታኛለችና፤ ኃጢአቶቼ ያዙኝ፥ ማየትም ተስኖኛል ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዙ፥ ልቤም ተወኝ። 13 አቤቱ፥ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። 14 ነፍሴን ለማጥፋት የሚወድዱ ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቍሉ፤ በእኔ ላይ ክፋትን ሊያደርጉ የሚወድዱ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይጐስቍሉም። 15 እሰይ እሰይ የሚሉኝ እፍረታቸውን ወዲያው ይከፈሉ። 16 አቤቱ፥ የሚፈልጉህ ሁሉ በአንተ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ፤ ሁልጊዜ ማዳንህን የሚወድዱ ዘወትር። እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ይበሉ። 17 እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ ጌታ ግን ያስብልኛል፤ አንተ ረዳቴና መድኃኒቴ ነህ፤ አምላኬ ሆይ፥ አትዘግይ።

ዳዊት 41

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። 2 እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም። 3 እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል። 4 እኔስ። አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ። 5 ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ። መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ። 6 እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል፤ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም። 7 በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ። 8 ክፉ ነገር መጣበት፤ ተኝቶአል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ። 9 ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ። 10 አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ። 11 ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ። 12 እኔን ግን ስለ ቅንነቴ ተቀበልኸኝ፥ በፊትህም ለዘላለም አጸናኸኝ። 13 ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።

ዳዊት 42

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት። 1 ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። 2 ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? 3 ዘወትር። አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ። 4 ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና፤ በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ። 5 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። 6 አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስብሃለሁ። 7 በፍዋፍዋቴህ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ። 8 እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፤ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። 9 እግዚአብሔርን። አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ለምን ረሳኸኝ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? እለዋለሁ። 10 ጠላቶቼ ሁልጊዜ። አምላክህ ወዴት ነው? ባሉኝ ጊዜ አጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ። 11 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።

ዳዊት 43

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ፍረድልኝ፥ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር፤ ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ። 2 አንተ አምላኬ ኃይሌም፥ ለምን ትተውኛለህ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ? 3 ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ። 4 ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፤ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ። 5 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።

ዳዊት 44

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት። 1 አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን። 2 እጅህ አሕዛብን አጠፋች፥ እነርሱንም ተከልህ፤ አሕዛብን ሣቀይኻቸው አሳደድኻቸውም። 3 በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፤ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ ወድደሃቸዋልና። 4 አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤ ለያዕቆብ መድኃኒትንህ እዘዝ። 5 በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን። 6 በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፤ 7 አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው። 8 ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን። 9 አሁን ግን ጠላኸን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም። 10 ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን። 11 እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን። 12 ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም። 13 ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን። 14 በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ የራስ መንቀሳቀሻ አደረግኸን። 15 ጕስቍልናዬ ሁልጊዜም በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ። 16 ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው። 17 ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም። 18 ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፤ 19 በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና። 20 የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥ 21 እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና። 22 ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል። 23 አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን። 24 ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ? 25 ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና። 26 አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ስምህም ተቤዠን።

ዳዊት 45

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለኮቶች፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት፤ የፍቅር መዝሙር። 1 ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው። 2 ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፤ ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ። 3 ኃያል ሆይ፥ በቍንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። 4 ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም፤ ቀኝህም በክብር ይመራሃል። 5 ኃያል ሆይ፥ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፥ እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፥ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ። 6 አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘላለም ነው፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። 7 ጽድቅን ወደድህ ዓመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህ ከባልንጀሮችህ ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ የደስታ ዘይትን ቀባህ። 8 በልብሶችህ ሁሉ ከርቤና ሽቱ ዝባድም አሉ፤ ከዝሆን ጥርሶች አዳራሽ ደስ ያሰኙሃል። 9 የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። 10 ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ 11 ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥ እርሱ ጌታሽ ነውና። 12 የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ። 13 ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፤ ልብስዋ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው። 14 በኋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ፥ ባልንጀሮችዋንም ወደ አንተ ያቀርባሉ፤ 15 በደስታና በሐሴት ይወስዱአቸዋል፥ ወደ ንጉሥ እልፍኝም ያስገቡአቸዋል። 16 በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ። 17 ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፤ ስለዚህ ለዓለምና ለዘላለም አሕዛብ ይገዙልሃል።

ዳዊት 46

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ምሥጢር፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። 2 ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። 3 ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ። 4 የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ። 5 እግዚአሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል። 6 አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤ እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች። 7 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። 8 የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ። 9 እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል። 10 ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። 11 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

ዳዊት 47

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ። 2 እግዚአብሔር ልዑል ግሩምም ነውና፥ በምድር ሁሉ ላይም ታላቅ ንጉሥ ነውና። 3 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። 4 ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት። 5 አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። 6 ዘምሩ፥ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ። 7 እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ በማስተዋል ዘምሩ። 8 እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፤ እግዚአብሔር በቅድስናው ዙፋን ይቀመጣል። 9 የምድር ኃይለኞች ለእግዚአብሔር ናቸውና የአሕዛብ አለቆች ወደ አብርሃም አምላክ ተሰበሰቡ፤ እርሱንም ከፍ ከፍ አደረጉት።

ዳዊት 48

በሁለተኛ ሰንበት የቆሬ ልጆች፤ የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው። 2 በሰሜን ወገን በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው፤ እርሱም የትልቁ ንጉሥ ከተማ ነው። 3 እግዚአብሔር በአዳራሾችዋ መጠጊያ ሆኖ ይታወቃል። 4 እነሆ፥ ነገሥታት ተከማችተው በአንድነት መጥተዋል። 5 እነርሱስ አይተው ተደነቁ፥ ደነገጡ፥ ታወኩ። 6 መንቀጥቀጥ እንደ ወላድ ምጥ በዚያ ያዛቸው። 7 በኃይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትሰብራለህ። 8 እንደ ሰማን እንዲሁ አየን በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል። 9 አምላክ ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ምሕረትህን ተቀበልን። 10 አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው፤ ቀኝህ ጽድቅን የተሞላች ናት። 11 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራራ ደስ ይበለው፥ የአይሁድም ሴት ልጆች ሐሤት ያድርጉ። 12 ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤ 13 በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፤ አዳራሽዋን አስቡ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ። 14 ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘላለም ይመራናል።

ዳዊት 49

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ ይህን ስሙ፤ በዓለም የምትኖሩትም ሁላችሁ፥ አድምጡ፤ 2 ዝቅተኞችና ከፍተኞች፥ ባለጠጎችና ድሆች በአንድነት። 3 አፌ ጥበብን ይናገራል፥ የልቤም አሳብ ማስተዋልን። 4 ጆሮዬን ወደ ምሳሌ አዘነብላለሁ፥ በበገናም ምሥጢሬን እገልጣለሁ። 5 ኃጢአት ተረከዜን በከበበኝ ጊዜ በክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ? 6 በኃይላቸው የሚታመኑ፥ በባለጠግነታቸውም ብዛት የሚመኩ፤ 7 ወንድም ወንድሙን አያድንም፥ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥ 8-9 ለዘላለም እንዲኖር፥ ጥፋትንም እንዳያይ፤ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና፥ ለዘላለምም ቀርቶአልና። 10 ብልሃተኞች እንዲሞቱ፥ ሰነፎችችና ደንቆሮች በአንድነት እንዲጠፉ፥ ገንዘባቸውንም ለሌሎች እንዲተዉ አይቶአል። 11 በልባቸውም ቤታቸው ለዘላለም የሚኖር፥ ማደሪያቸውም ለልጆች ልጅ የሚሆን ይመስላቸዋል፤ በየአገራቸውም ስማቸው ይጠራል። 12 ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። 13 ይህች መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥ ከእነርሱም በኋላ የሚመጡ በአፋቸው እሺ ይላሉ። 14 እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው፥ እረኛቸውም ሞት ነው፤ ቅኖችንም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥ ውበታቸውም ከመኖሪያቸው ተለይታ በሲኦል ታረጃለች። 15 ነገር ግን እግዚአብሔር ይቀበለኛልና ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል። 16 የሰው ባለጠግነት የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ አትፍራ፥ 17 በሞተ ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥ ክብሩም ከእርሱ በኋላ አይወርድምና። 18 በሕይወቱ ሳለ ነፍሱን ባርኮአልና ለሰውነቱ መልካም ብታደርግለት ያመሰግንሃል። 19 ሆኖም ወደ አባቶቹ ትውልድ ይወርዳል፤ ለዘላለም ብርሃንን አያይም። 20 አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ።

ዳዊት 50

የአሳፍ መዝሙር። 1 የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት። 2 ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። 3 አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ። 4 በላይ ያለውን ሰማይን ምድርንም በሕዝቡ ለመፍረድ ይጠራል፤ 5 ከእርሱ ጋር ለመሥዋዕት ኪዳን የቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡለት። 6 ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና። 7 ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ። 8 ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። 9 ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤ 10 የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። 11 የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። 12 ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። 13 የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? 14 ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ 15 በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ። 16 ኃጢአተኛውን ግን እግዚአብሔር አለው። ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ? ኪዳኔንም በአፍህ ለምን ትወስዳለህ? 17 አንተስ ተግሣጼን ጠላህ፥ ቃሎቼንም ወደ ኋላህ ጣልህ። 18 ሌባውን ባየህ ጊዜ ከእርሱ ጋር ትሮጥ ነበር እድል ፈንታህንም ከአመንዝሮች ጋር አደረግህ። 19 አፍህ ክፋትን አበዛ፥ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ። 20 ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፥ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ። 21 ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ፤ እኔ እንደ አንተ እሆን ዘንድ ጠረጠርህ፤ እዘልፍሃለሁ በፊትህም እቆማለሁ። 22 እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ፤ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም። 23 ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ።

ዳዊት 51

ለመዘምራን አለቃ፤ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። 2 ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ 3 እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። 4 አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ። 5 እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ። 6 እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ። 7 በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ። 8 ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል። 9 ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። 10 አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። 11 ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። 12 የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ። 13 ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። 14 የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች። 15 አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥ አፌም ምስጋናህን ያወራል። 16 መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም። 17 የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም። 18 አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ። 19 የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።

ዳዊት 52

ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ መጥቶ ለሳኦል። ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቶአል ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት። 1 ኃያል ሆይ፥ በክፋት ለምን ትጓደዳለህ? ሁልጊዜስ በመተላለፍ? 2 አንደበትህ ኃጢአትን ያስባል፤ እንደ ተሳለ ምላጭ ሽንገላን አደረግህ። 3 ከመልካም ይልቅ ክፋትን፥ ጽድቅንም ከመናገር ይልቅ ዓመፃን ወደድህ። 4 የሚያጠፉ ቃልን ሁሉ፥ የሽንገላ ምላስን ወደድህ። 5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ያፈርስሃል፤ ከቤትህም ይነቅልሃል ያፈልስሃልም፥ ሥርህንም ከሕያዋን ምድር። 6 ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፤ በእርሱም ይሥቃሉ እንዲህም ይላሉ። 7 እግዚአብሔርን ረዳቱ ያላደረገ፥ በባለጠግነቱም ብዛት የታመነ፥ በከንቱ ነገርም የበረታ ያ ሰው እነሆ። 8 እኔስ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ ነኝ፤ ለዓለምና ለዘላለም በእግዚአብሔር ምሕረት ታመንሁ። 9 አድርገህልኛልና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፥ በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ።

ዳዊት 53

ለመዘምራን አለቃ በማኽላት፤ የዳዊት ትምህርት። 1 ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም። 2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ። 3 ሁሉ በደሉ፥ አብረውም ረከሱ፤ አንድ ስንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም። 4 ሕዝቤን እንጀራ እንደሚበላ የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም። 5 እግዚአብሔር የግብዞችን አጥንቶች በትኖአልና። በዚያ የሚያስፈራ ሳይኖር እጅግ ፈሩ፤ እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና አሳፈርሃቸው። 6 መድኃኒትን ከጽዮን ለእስራኤል ማን በሰጠ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።

ዳዊት 54

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል። እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት። 1 አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ። 2 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤ 3 እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም። 4 እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው። 5 ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው። 6 ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤ 7 ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።

ዳዊት 55

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት ትምህርት። 1 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል። 2 ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤ 3 ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና። 4 ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ። 5 ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ። 6 በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ! 7 እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤ 8 ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ። 9 አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ። 10 በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤ 11 ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም። 12 ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር። 13 አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤ 14 መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን። 15 ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና። 16 እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ። 17 በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል። 18 በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት። 19 ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል። 20 ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ። 21 አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው። 22 ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም። 23 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።

ዳዊት 56

ለመዘምራን አለቃ፤ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ፤ ፍልስጥኤማውያን በጌት በያዙት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፤ ሁልጊዜም በሰልፍ አስጨንቆኛል። 2 የሚዋጉኝ በዝተዋልና ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ። 3 እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ። 4 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? 5 ሁልጊዜ ቃሎቼን ያጸይፉብኛል፤ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው። 6 ይሸምቁብኛል ይሸሽጉኝማል፥ እነርሱም ተረከዜን ይመለካከታሉ፥ ሁልጊዜም ነፍሴን ይሸምቁባታል። 7 በምንም ምን አታድናቸውም፤ አሕዛብን በቍጣ ትጥላቸዋለህ። 8 አምላክ ሆይ፥ ሕይወቴን ነገርሁህ፤ እንባዬን እንደ ትእዛዝህ በፊተህ አኖርህ። 9 በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ። 10 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ። 11 በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? 12 አቤቱ፥ የምስጋና ስእለት የምሰጥህ ከእኔ ዘንድ ነው፤ 13 ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ።

ዳዊት 57

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በዋሻ በነበረበት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ። 1 ማረኝ፥ አቤቱ፥ ማረኝ፥ ነፍሴ አንተን ታምናለችና፤ ጉዳት እስክታልፍ ድረስ በክንፎችህ ጥላ እታመናለሁ። 2 ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ። 3 ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ። 4 ነፍሴን ከአንበሶች መካከል አዳናት። ደንግጬ ተኛሁ፤ የሰው ልጆች ጥርሳቸው ጦርና ፍላጻ፥ አንደበታቸው የተሳለ ሾተል ነው። 5 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን። 6 ለእግሮቼ ወጥመድን አዘጋጁ፥ ነፍሴንም አጐበጡአት፤ ጕድጓድ በፊቴ ቈፈሩ፥ በእርሱም ወደቁ። 7 ልቤ ጨካኝ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጨካኝ ነው፤ እቀኛለሁ፥ እዘምራለሁ። 8 ክብሬ ይነሣ፥ በገናና መሰንቆም ይነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ። 9 አቤቱ፥ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም ዘንድ እዘምርልሃለሁ፤ 10 ምሕረትህ እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ብላለችና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ። 11 አምላክ ሆይ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን።

ዳዊት 58

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። የዳዊት ቅኔ። 1 በእውነት ጽድቅን ብትናገሩስ፥ የሰው ልጆች ሆይ፥ በቅን ትፈርዳላችሁ፤ 2 በልባችሁ በምድር ላይ ኃጢአትን ትሠራላችሁና፥ እጆቻችሁም ግፍን ይታታሉና። 3 ኅጥኣን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፥ ሐሰትንም ተናገሩ። 4 ቍጣቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፥ እንደ ምድር አውሬም ጆሮዋ የተደፈነ ነው፥ 5 አዋቂ ሲደግምባት የአስማተኛውን ቃል እንደማትሰማ። 6 እግዚአብሔር ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የአንበሶቹን መንጋጋቸውን ያደቅቃል። 7 እንደሚፈስስ ውኃ ይቀልጣሉ፤ እስኪያደክማቸው ድረስ ፍላጾቹን ይገትራል። 8 እንደሚቀልጥ ሰም ያልቃሉ፤ እሳት ወደቀች፥ ፀሐይንም አላዩአትም። 9 እሾኻችሁ ሳይታወቅ በትር ሆነ፤ ሕያዋን ሳላችሁ በመዓቱ ይነጥቃችኋል። 10 ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል፤ በኃጢአተኛው ደምም እጁን ይታጠባል። 11 ሰውም። በእውነት ለጻድቅ ፍሬ አለው፤ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ ይላል።

ዳዊት 59

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ሳኦል ይገድሉት ዘንድ ቤቱን እንዲጠብቁ በላከ ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ። 1 አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ። 2 ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ። 3 እነሆ፥ ነፍሴን ሸምቀውባታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ። አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም። 4 ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም። 5 አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፤ ዓመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ አትማራቸው። 6 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። 7 እነሆ፥ በአፋቸው አሰምተው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ ማን ይሰማል? ይላሉ። 8 አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ። 9 እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ። 10 የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል። 11 ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም። 12 ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ። 13 በቍጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ። 14 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ። 15 እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ ያልጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐረጕራሉ። 16 እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና። 17 ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና።

ዳዊት 60

ለመዘምራን አለቃ፤ የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ አሥራ ሁለት ሺህ በገደለ ጊዜ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ። 1 አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፤ ተቈጣኸን ይቅርም አልኸን። 2 ምድርን አናወጥሃት አወክሃትም፤ ተናውጣለችና ቍስልዋን ፈውስ። 3 ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን። 4 ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። 5 ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም። 6 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፤ ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ። 7 ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤ 8 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል። 9 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል? 10 አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም። 11 በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው። 12 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና።

ዳዊት 61

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አምላክ ሆይ፥ ልመናዬን ስማ፥ ጸሎቴንም አድምጥ። 2 ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ። 3 ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ሆነኸኛልና መራኸኝ። 4 በድንኳንህ ለዘላለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ፤ 5 አቤቱ፥ አንተ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ ስምህንም ለሚፈሩ ርስትህን ሰጠሃቸው። 6 ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀን ትጨምራለህ፥ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናሉ። 7 በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይኖራል፤ ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትንና እውነትን አዘጋጅለት። 8 እንዲሁ ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ።

ዳዊት 62

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ኤዶታም፤ የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና። 2 እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ እጅግም አልታወክም። 3 እስከ መቼ በሰው ላይ ትቆማላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድላላችሁ። 4 ነገር ግን ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ፥ ሐሰትንም ይወድዳሉ፤ በአፋቸው ይባርካሉ፥ በልባቸውም ይረግማሉ። 5 ነገር ግን፥ ነፍሴ ሆይ፥ አንቺ ለእግዚአብሔር ተገዢ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና። 6 እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፤ አልታወክም። 7 መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ የረድኤቴ አምላክ ተስፋዬም እግዚአብሔር ነው። 8 የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው። 9 ነገር ግን የሰው ልጆች ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፤ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው። 10 ዓመፃን ተስፋ አታድርጉ፥ ቅሚያንም አትተማመኑት፤ ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኵራ። 11 እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥ 12 አቤቱ፥ ምሕረትም ያንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ፍዳውን ትሰጣለህና።

ዳዊት 63

በኤዶምያስ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ። 2 ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ። 3 ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል። 4 እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ። 5 ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ። 6 በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም እናገርልሃለሁ፤ 7 ረዳቴ ሆነኸኛልና፥ በክንፎችህም ጥላ ደስ ይለኛልና። 8 ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፥ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ። 9 እነርሱ ግን ነፍሴን ለከንቱ ፈለጓት፤ ወደ ምድር ጥልቅ ይገባሉ። 10 ለሰይፍ እጅ አልፈው ይሰጣሉ፥ የቀበሮም እድል ፈንታ ይሆናሉ። 11 ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ በእርሱ የሚምል ሁሉ ይከብራል፥ ሐሰትን የሚናገር አፍ ይዘጋልና።

ዳዊት 64

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ በለመንሁ ጊዜ ጸሎቴን ስማኝ፥ ከጠላትም ፍርሃት ነፍሴን አድን። 2 ከክፉዎች ሸንጎ ከዓመፀኞችም ብዛት ሰውረኝ። 3 እንደ ሰይፍ ምላሳቸውን አሰሉ፤ መራራ ነገርን ለማድረግ፥ 4 ንጹሕንም በስውር ለመንደፍ ቀስትን ገተሩ፤ ድንገት ይነድፉታል አይፈሩምም። 5 ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፤ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፤ ማንስ ያየናል? ይላሉ። 6 ዓመፃን ፈልጓት፥ ሲፈትኑም አለቁ፤ የሰው የውስጥ አሳቡና ልቡ የጠለቀ ነው፥ 7 እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። የድንገትም ፍላጻ፤ ያቈስላቸዋል፤ 8 አንደበታቸው ያሰናክላቸዋል፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ይደነግጣሉ። 9 ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ። 10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።

ዳዊት 65

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል፥ ለአንተም ጸሎት ይቀርባል። 2 ሥጋ ሁሉ ጸሎትን ወደምትሰማ ወደ አንተ ይመጣል። 3 የዓመፃ ነገር በረታብን፤ ኃጢአታችንንስ አንተ ይቅር ትላለህ። 4 አንተ የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልኸው ምስጉን ነው፤ ከቤትህ በረከት እንጠግባለን። 5 ቤተ መቅደስህ ቅዱስ ነው በጽድቅም ድንቅ ነው። በምድር ዳርቻ ሁሉና በሩቅ ባሕር ውስጥ ላሉ ተስፋቸው የሆንህ፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ ስማን። 6 በጉልበትህ ተራሮችን አጸናሃቸው፥ በኃይልም ታጥቀሃል። 7 የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ። 8 ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ፥ በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ፤ የጥዋትንና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ። 9 ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። 10 ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። 11 በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። 12 የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። 13 ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።

ዳዊት 66

ለመዘምራን አለቃ፤ የመነሣት የምስጋና መዝሙር። 1 በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ 2 ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ። 3 እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። 4 በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ። 5 ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው። 6 ባሕርን የብስ አደረጋት፥ ወንዙንም በእግር ተሻገሩ፤ በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል። 7 በኃይሉ ለዘላለም ይገዛል፤ ዓይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፤ ዓመፀኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድርጉ። 8 አሕዛብ ሆይ፥ አምላካችንን ባርኩ፥ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ። 9 ነፍሴን በሕይወት ያኖራታል፥ እግሮቼንም ለመናወጥ አልሰጠም። 10 አቤቱ፥ ፈትነኸናልና፥ ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና። 11 ወደ ወጥመድ አገባኸን፥ በጀርባችንም መከራን አኖርህ። 12 በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን። 13-14 ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርሁትን ከንፈሮቼም ያሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለሁ። 15 ከዕጣንና ከወጠጤዎች ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለሁ፤ ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልሃለሁ። 16 እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሁሉ፥ ኑ፥ ስሙኝ፤ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ። 17 በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፥ በአንደበቴም አመሰገንሁት። 18 በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። 19 ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ፤ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ። 20 ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን።

ዳዊት 67

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ይማረን ይባርከንም፥ ፊቱንም በላያችን ያብራ፤ 2 በአሕዛብ ሁሉ መካከል ማዳንህን፥ መንገድህንም በምድር እናውቅ ዘንድ። 3 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ። 4 ለአሕዛብ በቅን ትፈርድላቸዋለህና፥ አሕዛብንም በምድር ላይ ትመራለህና አሕዛብ ደስ ይበላቸው ሐሤትም ያድርጉ። 5 አቤቱ፥ አሕዛብ ያመስግኑህ፥ አሕዛብ ሁሉ ያመስግኑህ። 6 ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል። 7 እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል።

ዳዊት 68

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ። 2 ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ ኅጥኣን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ። 3 ጻድቃንም ደስ ይበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ፥ በደስታም ደስ ይበላቸው። 4 ለእግዚአብሔር ተቀኙ ለስሙም ዘምሩ፤ ወደ ምድረ በዳ ለወጣም መንገድ አድርጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው፥ በፊቱም ደስ ይበላችሁ፤ በፊቱም ይደነግጣሉ። 5 እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። 6 እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ። 7 አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥ 8 ከሲና አምላክ ፊት፥ ከእስራኤል አምላክ ፊት ሰማያትም አንጠበጠቡ። 9 አቤቱ፥ የሞገስን ዝናብ ለርስትህ አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው። 10 እንስሶችህ በውስጡ አደሩ፤ አቤቱ፥ በቸርነትህ ለድሆች አዘጋጀህ። 11 እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠ፤ የሚያወሩት ብዙ ሠራዊት ናቸው። 12 የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች። 13 በርስቶች መካከል ብታድሩ፥ ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፥ በቅጠልያ ወርቅም እንደ ተለበጡ ላባዎችዋ ትሆናላችሁ። 14 ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ፥ በሰልሞን ላይ በረዶ ዘነበ። 15 የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፤ የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው። 16 የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው፤ በእውነት እግዚአብሔር ለዘላለም ያድርበታል። 17 የእግዚአብሔር ሰረገላዎች የብዙ ብዙ ሺህ ናቸው፤ ጌታ በመቅደሱ በሲና በመካከላቸው ነው። 18 ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ። 19 እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው፤ የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል። 20 አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው። 21 ነገር ግን እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፥ በኃጢአት የሚሄድንም የጠጕሩን አናት ይቀጠቅጣል። 22 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ከባሳን አመጣቸዋለሁ፥ ከባሕርም ጥልቅ እመልሳቸዋለሁ፥ 23 እግሮችህ በደም ይረገጡ ዘንድ፥ የውሾችህ ምላስ በጠላቶች ላይ ይሆን ዘንድ። 24 የአምላኬ የንጉሥ መንገድ በመቅደሱ፥ አቤቱ፥ መንገድህ ተገለጠ። 25 አለቆች ቀደሙ፥ መዘምራንም ተከተሉ፤ ከበሮን በሚመቱ በቈነጃጅት መካከል። 26 እግዚአብሔርን በጉባኤ፥ ጌታችንንም በእስራኤል ምንጭ አመስግኑት። 27 ወጣቱ ብንያም በጕልበቱ በዚያ አለ፥ ገዦቻቸው የይሁዳ አለቆች የዛብሎን አለቆችና የንፍታሌምም አለቆች። 28 አቤቱ፥ ኃይልህን እዘዝ፤ አቤቱ፥ ይህንም ለእኛ የሠራኸውን አጽናው። 29 በኢየሩሳሌም ስላለው መቅደስህ ነገሥታት እጅ መንሻን ለአንተ ያመጣሉ። 30 በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው። 31 መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። 32 የምድር ነገሥታት፥ ለእግዚአብሔር ተቀኙ፥ ለጌታም ዘምሩ። 33 በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል። 34 ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው። 35 እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።

ዳዊት 69

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ። 2 በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ። 3 በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ። 4 በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ። 5 አቤቱ፥ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፥ ኃጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም። 6 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ። 7 ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና። 8 ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፥ 9 የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና። 10 ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። 11 ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው። 12 በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ። 13 አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ። 14 እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ። 15 የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ። 16 አቤቱ፥ ምሕረትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤ 17 ከባሪያህም ፊትህን አትሰውር፤ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ አድምጠኝ። 18 ነፍሴን ተመልክተህ ተቤዣት፤ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ። 19 አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው። 20 ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች፤ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም። የሚያጽናናኝም አጣሁ። 21 ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ። 22 ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፤ 23 ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ። 24 መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው። 25 ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፤ 26 አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ። 27 በኃጢአታቸው ላይ ኃጢአትን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ። 28 ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ። 29 እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ፤ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ። 30 የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። 31 ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእምቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። 32 ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፤ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ። 33 እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና። 34 ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል። 35 እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፤ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል። 36 የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል። ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ።

ዳዊት 70

ለመዘምራን አለቃ፤ ለመታሰቢያ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። 2 ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቍሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም። 3 እንኳ እንኳ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ። 4 የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስ ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ። 5 እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ፥ እርዳኝ፤ ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፤ አቤቱ፥ አትዘግይ።

ዳዊት 71

አስቀድመው ስለ ማረኩ ስለ አሚናዳብ ልጆች የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር። 2 በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም። 3 በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ፤ ኃይሌ መጠጊያዬ አንተ ነህና። 4 አምላኬ፥ ከኃጢአተኛ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ። 5 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና። 6 ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው። 7 ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፤ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ። 8 አፌን ምስጋና ምላ ሁልጊዜ ክብርህንና ግርማህን እዘምር ዘንድ። 9 በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ። 10 ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፤ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ። 11 እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት። 12 አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። 13 ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጕዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ። 14 እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ። 15 ሥራን አላውቅምና አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል። 16 በእግዚአብሔር ኃይል እገባለሁ፤ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ። 17 አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ። 18 እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ። 19 አቤቱ፥ እስከ አርያም ታላላቅ ነገሮችን አደረግህ፤ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? 20 ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ። 21 ጽድቅህንም አብዛው፥ ተመልሰህም ደስ አሰኘኝ፥ ከጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ። 22 እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። 23 ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ። 24 ጕዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።

ዳዊት 72

ስለ ሰሎሞን። 1 አቤቱ፥ ፍርድህን ለንጉሥ ስጥ፥ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፥ 2 ሕዝብህን በጽድቅ፥ ችግረኞችህንም በፍርድ ይዳኝ ዘንድ። 3 ተራሮችና ኰረብቶች ለሕዝብህ ሰላምን ይቀበሉ። 4 ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ትፈርዳለህ የድሆችንም ልጆች ታድናለህ፤ ክፉውንም ታዋርደዋለህ። 5 ፀሐይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፥ በጨረቃም ፊት ለፊት ለልጅ ልጅ ይኖራል። 6 እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ፥ በምድርም ላይ እንደሚንጠባጠብ ጠብታ ይወርዳል። 7 በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። 8 ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል። 9 በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። 10 የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ። 11 ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል። 12 ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፥ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። 13 ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፥ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። 14 ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው በፊቱ ክቡር ነው። 15 እርሱ ይኖራል ከዓረብም ወርቅ ይሰጡታል፤ ሁልጊዜም ወደ እርሱ ይጸልያሉ፥ ዘወትርም ይባርኩታል። 16 በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል። 17 ስሙ ለዘላለም ቡሩክ ይሆናል፥ ከፀሐይም አስቀድሞ ስሙ ይኖራል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ይባረካሉም አሕዛብ ሁሉ ያመሰግኑታል። 18 ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። 19 የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። ይሁን፤ ይሁን። 20 የእሴይ ልጅ የዳዊት መዝሙር ተፈጸመ።

ዳዊት 73

የአሳፍ መዝሙር። 1 ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው። 2 እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ። 3 የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። 4 ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና። 5 እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም። 6 ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት። 7 ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ። 8 አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ። 9 አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ። 10 ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤ 11 እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ። 12 እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ። 13 እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። 14 ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው። 15 እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። 16 አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ። 17 ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ። 18 በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው። 19 እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። 20 ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ። 21 ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤ 22 እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ። 23 እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። 24 በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ። 25 በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ? 26 የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው። 27 እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው። 28 ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።

ዳዊት 74

የአሳፍ ትምህርት። 1 አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ? 2 አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ። 3 ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ። 4 ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ። 5 እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ። 6 እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት። 7 መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ። 8 አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ። 9 ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም። 10 አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን? 11 ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ? 12 እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። 13 አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። 14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። 15 አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ። 16 ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ። 17 አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ። 18 ይህን ፍጥረትህን አስብ። ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፥ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ። 19 የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤ የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ። 20 ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኅጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና። 21 ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ። 22 አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፤ ሰነፎች ሁልጊዜም የተላገዱህን አስብ። 23 የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤ የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይወጣል።

ዳዊት 75

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን ስምህንም እንጠራለን፤ ተኣምራትህን ሁሉ እናገራለሁ። 2 ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ። 3 ምድርና በእርስዋ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ቀለጡ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ። 4 ዓመፀኞችን። አትበድሉ አልኋቸው፥ ኃጢአተኞችንም። ቀንዳችሁን አታንሡ፤ 5 ቀንዳችሁን እስከ ላይ አታንሡ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ዓመፅን አትናገሩ። 6 ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ 7 እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። 8 ጽዋ በእግዚአብሔር እጅ ነውና፤ ያልተቀላቀለ የወይን ጠጅ ሞላበት፤ ከዚህ ወደዚያ አገላበጠው፥ ነገር ግን አተላው አልፈሰሰም፤ የምድር ኃጢአተኞች ሁሉ ይጠጡታል። 9 እኔ ግን ለዘላለም ደስ ይለኛል፥ ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬን አቀርባለሁ። 10 የኅጥኣንን ቀንዶች ሁሉ እሰብራለሁ፤ የጻድቃን ቀንዶች ግን ከፍ ከፍ ይላሉ።

ዳዊት 76

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው። 2 ስፍራው በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው። 3 በዚያም የቀስትን ኃይል፥ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ፤ በዚያም ቀንዶችን ሰበረ። 4 አንተ በዘላለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ። 5 ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ እንቅልፋቸውንም አንቀላፉ፤ ባለጠጎች ሁሉ በእነርሱ እጅ ምንም አላገኙም። 6 የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ሁሉ አንቀላፉ። 7 አንተ ግን፥ አንተ ግሩም ነህ፤ ቍጣህን ማን ይቃወማል? 8 ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፤ ምድር ፈራች ዝምም አለች፥ 9 ልበ የዋሃን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ። 10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ። 11 ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስእለትን ክፈሉ፤ በዙሪያው ያሉ ሁሉ እጅ መንሻን ለሚያስፈራው ያገባሉ። 12 የመኳንንትን ነፍስ ያወጣል፤ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል።

ዳዊት 77

ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ኤዶታም፤ የአሳፍ መዝሙር። 1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ። 2 በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም። 3 እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች። 4 ዓይኖቼ እንዲተጉ ያዝሃቸው፤ ደነገጥሁ አልተናገርሁም። 5 የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም 6 በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት። 7 እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን? 8 ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን? 9 እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን? 10 ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ። 11 የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤ 12 በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ። 13 አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? 14 ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልን አስታወቅሃቸው። 15 የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው። 16 አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ። 17 ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ። 18 የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም። 19 መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም። 20 በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።

ዳዊት 78

የአሳፍ ትምህርት። 1 ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ። 2 አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ፥ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ። 3 የሰማነውንና ያውቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም። 4 የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ። 5 ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፤ 6 የሚመጣ፥ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ፤ 7 ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤ 8 እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች። 9 የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ። 10 የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤ 11 መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥ 12 በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት። 13 ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ክምር አቆመ። 14 ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን። 15 ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው። 16 ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ። 17 ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት። 18 ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት። 19 እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን? 20 ዓለቱን መታ፤ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፤ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን? 21 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፤ 22 በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በመድኃኒቱም አልተማመኑምና። 23 ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤ 24 ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው። 25 የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው። 26 ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፤ 27 ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤ 28 በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ። 29 በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው። 30 ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥ 31 የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ። 32 ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፤ 33 ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ። 34 በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤ 35 ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ሆነ አሰቡ። 36 በአፋቸው ብቻ ወደዱት፤ በአንደበታቸውም ዋሹበት፤ 37 ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም። 38 እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም። 39 ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ። 40 በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት። 41 ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። 42 እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥ 43 በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን። 44 ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ። 45 ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤ በጓጉንቸርም አጠፋቸው። 46 ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። 47 ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ። 48 እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ። 49 የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ። 50 ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤ 51 በኵሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ። 52 ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው። 53 በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው። 54 ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚህች ተራራ፤ 55 ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ። 56 ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤ 57 ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤ 58 በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት። 59 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤ 60 የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤ 61 ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ። 62 ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ ርስቱንም ቸል አላቸው። 63 ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ቈነጃጅቶቻቸውም አላዘኑም፤ 64 ካህናቶቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም። 65 እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ 66 ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘላለምን ኀሣር ሰጣቸው። 67 የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤ 68 የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ። 69 መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት። 70 ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤

ዳዊት 79

የአሳፍ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፤ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ፥ ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት። 2 የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ፥ የጻድቃንህንም ሥራ ለምድር አራዊት፤ 3 ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፥ የሚቀብራቸውም አጡ። 4 ለጎረቤቶቻችንም ስድብ ሆንን፥ በዙሪያችንም ላሉ ሣቅና ዘበት። 5 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ትቈጣለህ? ቅንዓትህም እንደ እሳት ይነድዳል? 6 ስምህን በማይጠሩ መንግሥታት ላይ በማያውቁህም አሕዛብ ላይ መዓትህን አፍስስ፤ 7 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ስፍራውንም ባድማ አድርገዋልና። 8 የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና። 9 አምላካችንና መድኃኒታችን ሆይ፥ እርዳን፤ ስለ ስምህ ክብር፥ አቤቱ፥ ታደገን፥ ስለ ስምህም ኃጢአታችንን አስተሰርይልን። 10 አሕዛብ፥ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ያወቁ፤ 11 የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን። 12 አቤቱ፥ የተዘባበቱብህን መዘባበታቸውን ለጎረቤቶቻችን ሰባት እጥፍ በብብታቸው ክፈላቸው። 13 እኛ ሕዝብህ ግን፥ የማሰማርያህም በጎች፥ ለዘላለም እናመሰግንሃለን፤ ለልጅ ልጅም ምስጋናህን እንናገራለን።

ዳዊት 80

ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስክር መዝሙር። 1 ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ። 2 በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም፤ ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና። 3 አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን። 4 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ በባሪያህ ጸሎት ላይ እስከ መቼ ትቈጣለህ? 5 የእንባ እንጀራን ትመግበናለህ፥ እንባም በስፍር ታጠጣናለህ። 6 ለጎረቤቶቻችን ክርክር አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም በላያችን ተሣለቁብን። 7 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን። 8 ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ። 9 በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች። 10 ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ። 11 ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች። 12 አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል። 13 የዱር እርያ አረከሳት፥ የአገር አውሬም ተሰማራባት። 14 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ። 15 በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኸውን ቀኝህ የተከላትን አንሣ። 16 በእሳት ተቃጥላለች ተነቅላማለች፤ ከፊትህ ተግሣጽም የተነሣ ይጠፋሉ። 17 ለአንተ ባጸናኸው በሰው ልጅ ላይ፥ በቀኝህ ሰው ላይ እጅህ ትሁን። 18 ከአንተም አንራቅ፤ አድነን ስምህንም እንጠራለን። 19 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።

ዳዊት 81

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት፤ የአሳፍ መዝሙር። 1 በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ። 2 ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፤ 3 በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ 4 ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ። 5 ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ። 6 ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ። 7 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ በተሰወረ ዐውሎም መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ። 8 ሕዝቤ ሆይ፥ስማኝ እነግርሃለሁም፤ እስራኤል ሆይ፥ እመሰክርልሃለሁ። 9 አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም። 10 ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና፤ አፍህን አስፋ እሞላዋለሁም። 11 ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም፥ እስራኤልም አላዳመጠኝም። 12 እንደ ልባቸው ሥራ ተውኋቸው፥ በልባቸውም አሳብ ሄዱ። 13 ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፥ እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን፤ 14 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር፥ በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልሁ ነበር፤ 15 የእግዚአብሔር ጠላቶችም በተገዙለት ነበር፥ ዘመናቸውም ለዘላለም በሆነ ነበር፤ 16 ከስንዴም ስብ ባበላቸው ነበር፥ ከዓለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር።

ዳዊት 82

የአሳፍ መዝሙር። 1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል። 2 እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ? 3 ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤ 4 ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው። 5 አያውቁም፥ አያስተውሉም፤ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ፤ የምድር መሠረቶች ሁሉ ተናወጡ። 6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ 7 ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ። 8 አቤቱ፥ ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍርድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና።

ዳዊት 83

የአሳፍ የምስጋና መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? አቤቱ፥ ዝም አትበል፥ ቸልም አትበል። 2 እነሆ፥ ጠላቶችህ ጮኽዋልና፥ የሚጠሉህም ራሳቸውን አንሥተዋልና። 3 ሕዝብህን በምክር ሸነገሉአቸው፥ በቅዱሳንህም ላይ ተማከሩ። 4 ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው፥ ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ። 5 አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ፤ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ 6 የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም፥ ሞዓብም አጋራውያንም፥ 7 ጌባል አሞንም አማሌቅም፥ ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋር፤ 8 አሦርም ከእነርሱ ጋር ተባበረ፥ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ሆኑአቸው። 9 እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፥ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው። 10 በዓይንዶር ጠፉ፥ እንደ ምድርም ጕድፍ ሆኑ። 11 አለቆቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ፥ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸው። 12 የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንወርሳለን የሚሉትን። 13 አምላኬ ሆይ፥ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው። 14 እሳት ዱርን እንደሚያቃጥል፥ ነበልባልም ተራሮች እንደሚያነድድ፥ 15 እንዲሁ በቍጣህ አሳድዳቸው፥ በመቅሠፍትህም አስደንግጣቸው። 16 ፊታቸውን እፍረት ሙላው፥ አቤቱ፥ ስምህንም ይፈልጋሉ። 17 ይፈሩ ለዘላለሙም ይታወኩ፤ ይጐስቍሉ ይጥፉም። 18 ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፥ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።

ዳዊት 84

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው! 2 ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፤ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ። 3 ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች፥ ዋኖስም ጫጩቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፥ እርሱ መሠዊያህ ነው። 4 በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል። 5 አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው። 6 በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። 7 ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል። 8 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ አድምጥ። 9 አቤቱ፥ መታመናችንን እይልን፥ ወደ ቀባኸውም ፊት ተመልከት። 10 ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። 11 እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም። 12 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው።

ዳዊት 85

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ለምድርህ ሞገስን አደረግህ፥ የያዕቆብንም ምርኮ መለስህ። 2 የሕዝብህን ኃጢአት አስቀረህ፥ አበሳቸውንም ሁሉ ከደንህ። 3 መዓትህንም ሁሉ አስወገድህ፤ ከቍጣህ መቅሠፍት ተመለስህ። 4 የመድኃኒታችን አምላክ ሆይ፥ መልሰን፥ ቍጣህንም ከእኛ መልስ። 5 በውኑ ለዘላለም ትቈጣናለህን? ቍጣህንስ ለልጅ ልጅ ታስረዝማለህን? 6 አቤቱ፥ ትመለሳለህ ታድነንማለህ፤ ሕዝቡም በአንተ ደስ ይላቸዋል። 7 አቤቱ፥ ምሕረትህን አሳየን፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህንም ስጠን። 8 እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለሕዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና። 9 ነገር ግን ክብር በምድራችን ያድር ዘንድ ማዳኑ ለሚፈሩት ቅርብ ነው፤ 10 ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ። 11 እውነት ከምድር በቀለች፥ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። 12 እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል፥ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። 13 ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፥ ፍለጋውንም በመንገድ ውስጥ ያኖራል።

ዳዊት 86

የዳዊት ጸሎት። 1 አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና። 2 ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው። 3 አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ። 4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና። 5 አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና። 6 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ። 7 ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ። 8 አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም። 9 ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፤ 10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና። 11 አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል። 12 አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤ 13 ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና። 14 አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፤ በፊታቸውም አላደረጉህም። 15 አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ፤ 16 ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን። 17 ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።

ዳዊት 87

የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። 1 መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤ 2 ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። 3 የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል። 4 የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ። 5 ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። 6 እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል። 7 በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።

ዳዊት 88

የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ለመዘምራን አለቃ በማኸላት ለመዘመር፤ የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት። 1 አቤቱ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ በቀንና በሌሊት በፊትህ ጮኽሁ፤ 2 ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፤ 3 ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና። 4 ወደ ጓድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ። 5 ለዘላለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፤ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ። 6 በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጕድጓድ አስቀመጥኸኝ። 7 በእኔ ላይ ቍጣህ ጸና፥ መቅሠፍትህን ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ። 8 የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅህ፤ በእነርሱ ዘንድ ርኵስ አደረግኸኝ፤ ያዙኝ፥ መውጫም የለኝም። 9 ዓይኖቼም በመከራ ፈዘዙ፤ አቤቱ፥ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ፥ 10 በውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለህን? የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? 11 በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን? 12 ተአምራትህ በጨለማ፥ ጽድቅህንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን? 13 አቤቱ፥ እኔ ግን ወደ አንተ ጮኽሁ፤ በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች። 14 አቤቱ፥ ነፍሴን ለምን ትጥላለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ? 15 እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብሁ ነኝ፤ ከፍ ከፍ ካልሁ በኋላ ግን ተዋረድሁ ተናቅሁም። 16 መቅሠፍትህ በላዬ አለፈ፥ ግርማህም አስደነገጠኝ። 17 ሁልጊዜ እንደ ውኃ ከበቡኝ፥ በአንድነትም ያዙኝ። 18 ወዳጄንና ባልንጀራዬን ዘመዶቼንም ከመከራ የተነሣ ከእኔ አራቅህ።

ዳዊት 89

የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት። 1 አቤቱ፥ ምሕረትህን ለዘላለም እዘምራለሁ፥ እውነትህንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለሁ። 2 እንዲህ ብለሃልና። ምሕረት ለዘላለም ይመሠረታል፥ እውነትህም በሰማይ ይጸናል። 3 ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ። 4 ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ። 5 አቤቱ፥ ሰማያት ተኣምራትህን እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ። 6 እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? 7 በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው። 8 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትህም ይከብብሃል። 9 የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ። 10 አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው። 11 ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትህ። 12 ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል። 13 ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች። 14 የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ። 15 እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፥ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ። 16 በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፥ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤ 17 የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፥ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና። 18 ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና። 19 በዚያ ጊዜ ለልጆችህ በራእይ ተናገርህ እንዲህም አልህ። ረድኤቴን በኃይል ላይ አኖርሁ፤ ከሕዝቤ የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ። 20 ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁት፥ ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት። 21 እጄም ትረዳዋለች፥ ክንዴም ታጸናዋለች። 22 ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም፥ የዓመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም። 23 ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ፥ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ። 24 እውነቴና ምሕረቴም ከእርሱ ጋር ነው፥ በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል። 25 እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለሁ። 26 እርሱ። አባቴ አንተ ነህ፥ አምላኬ የመድኃኒቴም መጠጊያ ይላል። 27 እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለሁ፥ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል። 28 ለዘላለምም ምሕረቴን ለእርሱ እጠብቃለሁ፥ ኪዳኔም በእርሱ ዘንድ የታመነ ነው። 29 ዘሩንም ለዓለምና ለዘላለም፥ ዙፋኑንም እንደ ሰማይ ዘመን አደርጋለሁ። 30 ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ፥ በፍርዴም ባይሄዱ፤ 31 ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፥ ትእዛዜንም ባይጠብቁ፤ 32 ኃጢአታቸውን በበትር፥ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለሁ። 33 ምሕረቴን ግን ከእርሱ አላርቅም፥ በእውነቴም አልበድልም፤ 34 ኪዳኔንም አላረክስም፥ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም። 35 ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ። 36 ዘሩ ለዘላለም፥ ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሐይ ይኖራል። 37 ለዘላለም እንደ ጨረቃ ይጸናል፤ ምስክርነቱ በሰማይ የታመን ነው። 38 አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም፥ የቀባኸውንም ጣልኸው። 39 የባሪያህንም ኪዳን አፈረስህ፥ መቅደሱንም በምድር አረከስህ። 40 ቅጥሩን ሁሉ ጣልህ፥ አምባዎቹንም አጠፋህ። 41 መንገድ አላፊም ሁሉ ተናጠቀው፥ ለጎረቤቶቹም ስድብ ሆነ። 42 የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግህ፥ ጠላቶቹንም ሁሉ ደስ አሰኘህ። 43 የሰይፉንም ረድኤት መለስህ፥ በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም። 44 ከንጽሕናውም ሻርኸው፥ ዙፋኑንም በምድር ጣልህ። 45 የዙፋኑንም ዘመን አሳነስህ፥ በእፍረትም ሸፈንኸው። 46 አቤቱ፥ እስከ መቼ ለዘላለም ፊትህን ትመልሳለህ? እስከ መቼስ ቍጣህ እንደ እሳት ይነድዳል? 47 ችሎታዬ ምን እንደ ሆነ አስብ፤ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን? 48 ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው? ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው? 49 ለዳዊት በእውነት የማልህ፥ አቤቱ፥ የቀድሞ ምሕረትህ ወዴት ነው? 50 አቤቱ፥ የባሪያዎችህን ስድብ፥ በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልሁትን፥ 51 አቤቱ፥ ጠላቶችህን የሰደቡትን የቀባኸውን ዘመን የሰደቡትን አስብ። 52 እግዚአብሔር ለዘላለም ይባረክ። ይሁን ይሁን።

ዳዊት 90

የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት። 1 አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። 2 ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። 3 ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ 4 ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። 5 ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። 6 ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። 7 እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። 8 የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ። 9 ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። 10 የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና። 11 የቍጣህን ጽናት ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ። 12 በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን። 13 አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ስለ ባሪያዎችህም ተምዋገት። 14 በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን። 15 መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ ይለናል። 16 ባሪያዎችህንና ሥራህን እይ፥ ልጆቻቸውንም ምራ። 17 የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና።

ዳዊት 91

የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። 2 እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። 3 እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። 4 በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። 5 ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ 6 በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። 7 በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። 8 በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። 9 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። 10 ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። 11 በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ 12 እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። 13 በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። 14 በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። 15 ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። 16 ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።

ዳዊት 92

በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤ 2 በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት 3 አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። 4 አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና። 5 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው። 6 ሰነፍ ሰው አያውቅም። ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም። 7 ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፥ ለዘላለም ዓለም እንዲጠፋ ነው። 8 አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ፤ 9 አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና። 10 ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፤ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል። 11 ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች። 12 ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። 13 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ። 14 ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ። 15 አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይነግራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም።

ዳዊት 93

በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤ እግዚአብሔር ኃይልን ለበሰ፥ ታጠቀም፤ ዓለምን እንዳትናወጥ አጸናት። 2 ዙፋንህ ከጥንት ጀምሮ የተዘጋጀ ነው፥ አንተም ከዘላለም ነህ። 3 አቤቱ፥ ወንዞች ከፍ ከፍ አደረጉ፥ ወንዞች ቃሎቻቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ። 4 ከብዙ ውኆች ድምፅ ከባሕርም ታላቅ ሞገድ ይልቅ እግዚአብሔር በከፍታው ድንቅ ነው። 5 ምስክርህ እጅግ የታመነ ነው፤ አቤቱ፥ እስከ ረጅም ዘመን ድረስ ለቤትህ ቅድስና ይገባል።

ዳዊት 94

በአራተኛ ሰንበት የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ። 2 የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው። 3 አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ? 4 ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ። 5 አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ። 6 ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ። 7 እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ። 8 የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ? 9 ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን? 10 አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን? 11 የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል። 12-13 ለኃጢአተኛ ጕድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከክፉዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው። 14 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና 15 ፍርድ ወደ ጽድቅ እስኪመልስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል። 16 በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚቆም ማን ነው? ዓመፃንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው? 17 እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር። 18 እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ። 19 አቤቱ፥ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት። 20 በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠራ የዓመፅ ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን? 21 የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደምም ይፈርዳሉ። 22 እግዚአብሔር መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የተስፋዬም ረዳት ነው። 23 እንደ በደላቸውም እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ያጠፋቸዋል።

ዳዊት 95

የዳዊት ምስጋና መዝሙር። 1 ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል። 2 በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤ 3 እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና። 4 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው። 5 ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት። 6 ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ 7 እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። 8 በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ። 9 የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ ሥራዬንም አዩ። 10 ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ። 11 ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።

ዳዊት 96

ከምርኮ በኋላ ቤት በተሠራ ጊዜ። 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ። 2 እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ፥ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። 3 ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤ 4 እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና። 5 የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። 6 ምስጋናና ውበት በፊቱ፥ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። 7 የአሕዛብ ወገኖች፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ 8 ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባን ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ። 9 በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድር ሁሉ በፊቱ ትነዋወጥ። 10 በአሕዛብ መካከል። እግዚአብሔር ነገሠ በሉ። እንዳይናወጥም ዓለሙን እርሱ አጸናው፥ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል። 11 ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ፤ 12 በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤ 13 ይመጣልና፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል።

ዳዊት 97

1 እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ሐሤትን ታድርግ፥ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው። 2 ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው። 3 እሳት በፊቱ ይሄዳል፥ ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል። 4 መብረቆቹ ለዓለም አበሩ፤ ምድር አየችና ተናወጠች። 5 ተራሮችም ከእግዚአብሔር ፊት፥ ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ። 6 ሰማያት የእርሱን ጽድቅ አወሩ፥ አሕዛብም ሁሉ ክብሩን አዩ። 7 ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ፤ መላእክቱ ሁሉ፥ ስገዱለት። 8 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፥ የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው፤ 9 አንተ፥ እግዚአብሔር፥ በምድር ላይ ሁሉ ልዑል ነህና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለሃልና። 10 እግዚአብሔርን የምትወዱ፥ ክፋትን ጥሉ፤ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፥ ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል። 11 ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ። 12 ጻድቃን፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፥ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ።

ዳዊት 98

የዳዊት መዝሙር። 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ። 2 እግዚአብሔር ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ። 3 ለያዕቆብ ምሕረቱን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ። 4 ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩም። 5 ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ። 6 በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ። 7 ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ። 8 ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና። 9 ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።

ዳዊት 99

የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፤ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ። 2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ። 3 ግሩምና ቅዱስ ነውና ሁሉ ታላቅ ስምህን ያመስግኑ። 4 የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ። 5 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ። 6 ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው። እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው። 7 በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ። 8 አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው። 9 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።

ዳዊት 100

የምስጋና መዝሙር። 1 ምድር ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ 2 በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ፥ በሐሤትም ወደ ፊቱ ግቡ። 3 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን። 4 ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤ 5 እግዚአብሔር ቸር፥ ምሕረቱም ለዘላለም፥ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና።

ዳዊት 101

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ። 2 እዘምራለሁ፥ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ፤ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ። 3 በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ። 4 ጠማማ ልብም አልተጠጋኝም፤ ክፉ ከእኔ በራቀ ጊዜ አላወቅሁም። 5 ባልንጀራውን በቀስታ የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤ በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም። 6 ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፤ ዓይኖቼ በምድር ምእመናን ላይ ናቸው፤ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል። 7 ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ መካከል አይኖርም፤ ዓመፅን የሚናገር በዓይኔ ፊት አይቀናም። 8 ዓመፃ የሚያደርጉትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ከተማ አጠፋቸው ዘንድ፥ የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ በማለዳ እገድላቸዋለሁ።

ዳዊት 102

ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የችግረኛ ጸሎት። 1 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ። 2 በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ። 3 ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና፥ አጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና። 4 እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ። 5 ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ። 6 እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፤ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ሆንሁ። 7 ተጋሁ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ። 8 ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥ የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ። 9 አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና፥ 10 ከቍጣህና ከመዓትህም የተነሣ፤ አንሥተኸኛልና፥ ጥለኸኝማልና። 11 ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ። 12 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው። 13 አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥ የምሕረትዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤ 14 ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና። 15 አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፤ 16 እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና። 17 ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥ ልመናቸውንም አልናቀም። 18 ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል፤ 19 እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፤ 20 የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ፤ 21 የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፤ 22 አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ። 23 በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ። 24 በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው። 25 አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። 26 እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ 27 አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። 28 የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።

ዳዊት 103

የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን። 2 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፤ 3 ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ 4 ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥ 5 ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል። 6 እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል። 7 ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን። 8 እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። 9 ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። 10 እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። 11 ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። 12 ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። 13 አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ 14 ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ። 15 ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤ 16 ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና። 17 የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፥ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፤ 18 ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፥ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው። 19 እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፥ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። 20 ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። 21 ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። 22 ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ።

ዳዊት 104

የዳዊት መዝሙር። 1 ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤ ክብርንና ግርማን ለበስህ። 2 ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስህ፤ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋህ፤ 3 እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥ 4 መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል። 5 ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት። 6 በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። 7 ከዘለፋህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነግጣሉ፤ 8 ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፤ 9 እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ። 10 ምንጮችን ወደ ቈላዎች ይልካል፤ በተራሮች መካከል ውኆች ያልፋሉ፤ 11 የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህያዎችም ጥማታቸውን ይረካሉ። 12 የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ፥ በድንጋዩ ስንጥቅ መካከልም ይጮኻሉ። 13 ተራሮችን ከላይ የሚያጠጣቸው፤ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። 14 እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፥ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል። 15 ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል። 16 የእግዚአብሔር ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። 17 በዚያም ወፎች ይዋለዳሉ፥ የሽመላ ቤትም የእነርሱ ጎረቤት ነው። 18 ረጃጅም ተራራዎች ለዋላዎች፥ ድንጋዮችም ለእሽኮኮች መሸሻ ናቸው። 19 ጨረቃን ለጊዜዎች አደረገ፤ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። 20 ጨለማ ታደርጋለህ ሌሊትም ይሆናል፤ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። 21 የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። 22 ፀሐይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ በየዋሻቸውም ይተኛሉ። 23 ሰው ወደ ተግባሩ፥ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል። 24 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፥ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች። 25 ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት፤ በዚያ ስፍራ ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ፥ ታላላቆችና ታናናሾች እንስሶች አሉ። 26 በዚያ ጊዜ መርከቦች ይሄዳሉ፥ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ይጫወትበታል። 27 ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ። 28 በሰጠሃቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፤ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ። 29 ፊትህን ስትሰውር ይደነግጣሉ፤ ነፍሳቸውን ታወጣለህ ይሞታሉም፥ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። 30 መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ። 31 የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይሁን፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል። 32 ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል፤ ተራሮችን ይዳስሳል ይጤሳሉም። 33 በሕይወቴ ሳለሁ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ሁሉ እዘምራለሁ። 34 ቃሌ ለእርሱ ይጣፍጠው፥ እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል። 35 ኅጥኣን ከምድር ይጥፉ፤ ዓመፀኞች እንግዲህ አይገኙ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 105

ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ፥ ለአሕዛብም ሥራውን አውሩ። 2 ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፥ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። 3 በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። 4 እግዚአብሔርን ፈልጉት ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። 5-6 ባሪያዎቹ የአብርሃም ዘር፥ ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፥ ተአምራቱን የአፉንም ፍርድ። 7 እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው። 8 ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ 9 ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤ 10 ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን እንዲሆን አጸና። 11 እንዲህም አለ። ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ገመድ እሰጣለሁ፤ 12 ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች ሲሆኑ ነው። 13 ከሕዝብ ወደ ሕዝብ፥ ከመንግሥታትም ወደ ሌላ ሕዝብ አለፉ። 14-15 የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፥ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ። 16 በምድር ላይ ራብን ጠራ፥ የእህልን ኃይል ሁሉ ሰበረ። 17 በፊታቸው ሰውን ላከ፤ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ። 18 እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ። 19 ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው። 20 ንጉሥ ላከ ፈታውም፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው። 21 የቤቱ ጌታ፥ የጥሪቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥ 22 አለቆቹን እንደ ፈቃዱ ይገሥጽ ዘንድ፥ ሽማግሌዎቹንም ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ። 23 እስራኤልም ወደ ግብጽ ገባ፥ ያዕቆብም በካም አገር ተቀመጠ። 24 ሕዝቡንም እጅግ አበዛ፥ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው። 25 ሕዝቡን ይጠሉ ዘንድ በባሪያዎቹም ላይ ይተነኰሉ ዘንድ ልባቸውን ለወጠ። 26 ባሪያውን ሙሴን የመረጠውንም አሮንን ላከ። 27 የተኣምራቱን ነገር በላያቸው ድንቁንም በካም አገር አደረገ። 28 ጨለማን ላከ ጨለመባቸውም፤ በቃሉም ዐመፁ። 29 ውኃቸውን ወደ ደም ለወጠ፥ ዓሦቻቸውንም ገደለ። 30 ምድራቸው የንጉሦቻቸውም ቤቶች በጓጕንቸር ሞሉ። 31 ተናገረ፥ የውሻ ዝንብ ትንኝም በዳርቻቸው መጡ። 32 ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፥ እሳትም በምድራቸው ተቃጠለች። 33 ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፥ የአገራቸውንም ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 34 ተናገረ፥ አንበጣም ስፍር ቍጥር የሌለውም ኩብኩባ መጣ፥ 35 የአገራቸውንም ለምለም ሁሉ በላ፥ የምድራቸውንም ፍሬ በላ። 36 የአገራቸውንም በኵር ሁሉ፥ የጕልበታቸውን መጀመሪያ ሁሉ መታ። 37 ከወርቅና ከብርም ጋር አወጣቸው፥ በወገናቸውም ውስጥ ደዌ አልነበረም። 38 ፈርተዋቸው ነበርና ግብጽ በመውጣታቸው ደስ አላት። 39 ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ። 40 ለመኑ፥ ድርጭትንም አመጣላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው። 41 ዓለቱን ሰነጠቀ፥ ውኃውም ፈሰሰ፤ ወንዞች በበረሃ ሄዱ፤ 42 ለባሪያው ለአብርሃም የነገረውን ቅዱስ ቃሉን አስቦአልና። 43 ሕዝቡንም በደስታ የተመረጡትንም በእልልታ አወጣ። 44 የአሕዛብንም አገሮች ሰጣቸው፥ የወገኖችንም ድካም ወረሱ፥ 45 ሕጉን ይጠብቁ ዘንድ፥ ሥርዓቱንም ይፈልጉ ዘንድ። ሃሌ ሉያ

ዳዊት 106

1 ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። 2 የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል? 3 ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው። 4 አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤ 5 የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ። 6 ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም። 7 አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ። 8 ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው። 9 የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው። 10 ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው። 11 ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም። 12 በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ። 13 ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም። 14 በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። 15 የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ። 16 ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው። 17 ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤ 18 በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው። 19 በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ። 20 ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ። 21-22 ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ። 23 እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ። 24 የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥ 25 በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 26-27 በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው። 28 በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ። 29 በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ። 30 ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤ 31 ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። 32-33 በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ። 34 እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤ 35 ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ። 36 ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው። 37 ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤ 38 የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች። 39 በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ። 40 የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ። 41 ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው። 42 ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ። 43 ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ። 44 እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤ 45 ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ። 46 በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው። 47 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን። 48 ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 107

ሃሌ ሉያ። 1 ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ 2 እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ። 3 ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው። 4 ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም። 5 ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች። 6 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤ 7 ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው። 8 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤ 9 የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና። 10 በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤ 11 የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥ 12 ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ። 13 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው። 14 ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ። 15 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤ 16 የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና። 17 ስለ ዓመፃቸው ሰነፉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ተቸገሩ። 18 ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ። 19 በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። 20 ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው። 21 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ፤ 22 የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ። 23 በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥ 24 እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ። 25 ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ። 26 ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች። 27 ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች። 28 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው። 29 ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ። 30 ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው። 31 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ። 32 በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት። 33 ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤ 34 ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት። 35 ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፥ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ። 36 በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ። 37 እርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ፥ የእህልንም ሰብል አደረጉ። 38 ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም። 39 እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ሄዱ፤ 40 በአለቶችም ላይ ኅሣርን፥ አፈሰሰ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው። 41 ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው፤ እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው። 42 ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፤ ኃጢአትም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች። 43 ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።

ዳዊት 108

የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 ልቤ ጽኑ ነው፥ አቤቱ፥ ልቤ ጽኑ ነው፤ እቀኛለሁ በክብሬም እዘምራለሁ። 2 በገና ሆይ፥ ተነሥ፥ መሰንቆም፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ። 3 አቤቱ፥ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፥ በወገኖችም መካከል እዘምርልሃለሁ፤ 4 ምሕረትህ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና፥ እውነትህም እስከ ደመናት ድረስ ነውና። 5 አቤቱ፥ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል፥ ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትሁን። 6 ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፤ በቀኝህ አድን አድምጠኝም። 7 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ። ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ። 8 ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው። 9 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል። 10 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል? 11 አቤቱ፥ የጣልኸኝ አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም። 12 በመከራችን ረድኤትን ስጠን፤ የሰውም ማዳን ከንቱ ነው። 13 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን፤ እርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል።

ዳዊት 109

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አምላክ ሆይ፥ ምሥጋናዬን ዝም አትበል፥ 2 የኃጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቅቀውብኛልና፤ በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤ 3 በጥል ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተሰለፉብኝ። 4 በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ። 5 በመልካም ፋንታ ክፉን በወደድኋቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ። 6 በላዩ ኃጢአተኛን ሹም፤ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም። 7 በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት። 8 ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ። 9 ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን። 10 ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ። 11 ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት። 12 የሚያግዘውንም አያግኝ። ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር። 13 ልጆቹ ይጥፉ፤ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ። 14 የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ። 15 በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፤ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ። 16 ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ። 17 መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች። 18 መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች። 19 እንደሚለብሰው ልብስ። ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይሁነው። 20 ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው። 21 አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤ ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ። 22 እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ። 23 እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ። 24 ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ። 25 እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ሆንሁ፤ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ። 26 አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ምሕረትህም አድነኝ። 27 አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥ አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ። 28 እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ፤ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ ባሪያህ ግን ደስ ይበለው። 29 የሚያጣሉኝ እፍረትን ይልበሱ፤ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት። 30 እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፤ 31 ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ በድሀ ቀኝ ቆሞአልና።

ዳዊት 110

የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው። 2 እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ። 3 ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ። 4 እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም። 5 እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። 6 በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ያበዛል፤ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል። 7 በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራስ ከፍ ከፍ ይላል።

ዳዊት 111

1 ሃሌ ሉያ። አቤቱ፥ በቅኖች ሸንጎ በጉባኤም በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ። 2 የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፥ ደስ በሚሰኙባት ሁሉ ዘንድ የተፈለገች ናት። 3 ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። 4 ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው። 5 ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል። 6 የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ። 7 የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ነው፤ ትእዛዙም ሁሉ የታመነ ነው፥ 8 ለዘላለምም የጸና ነው፥ በእውነትና በቅንም የተሠራ ነው። 9 መድኃኒትንም ለሕዝቡ ሰደደ፥ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው። 10 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።

ዳዊት 112

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ትእዛዙንም እጅግ የሚወድድ ሰው ምስጉን ነው። 2 ዘሩ በምድር ላይ ኃያል ይሆናል፤ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች። 3 ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፥ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። 4 ለቅኖች ብርሃን በጨለማ ወጣ፤ መሓሪና ይቅር ባይ ጻድቅም ነው። 5 ቸር ሰው ይራራል ያበድራልም፥ በፍርድም ነገሩን ይፈጽማል። 6 ለዘላለም አይናወጥም፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል። 7 ከክፉ ነገር አይፈራም፤ በእግዚአብሔር ለመታመን ልቡ የጸና ነው። 8 በጠላቶቹ ላይ እስኪያይ ድረስ ልቡ ጽኑ ነው፥ አይፈራም። 9 በተነ ለችግረኞችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘላለም ዓለም ይኖራል፤ ቀንዱ በክብር ከፍ ከፍ ይላል። 10 ኃጢአተኛም አይቶ ይቈጣል፥ ጥርሱንም ያፋጫል፥ ይቀልጣልም፤ የኃጢአተኞችም ምኞት ትጠፋለች።

ዳዊት 113

1 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርንም ስም አመስግኑ። 2 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን። 3 ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያው ድረስ የእግዚአብሔር ስም ይመስገን። 4 እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ነው፥ ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው። 5 እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በላይ የሚኖር፤ 6 በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ 7-8 ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፥ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፤ 9 መካኒቱን በቤት የሚያኖራት፥ ደስ የተሰኘችም የልጆች እናት የሚያደርጋት። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 114

ሃሌ ሉያ። 1 እስራኤል ከግብጽ፥ የያዕቆብም ቤት ከእንግዳ ሕዝብ በወጣ ጊዜ፥ 2 ይሁዳ መቅደሱ፥ እስራኤልም ግዛቱ ሆነ። 3 ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ። 4 ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ። 5 አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ፥ምን ሆናችኋል? 6 እናንተም ተራሮች፥ እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችስ፥ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? 7 ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ ከጌታ ፊት ምድር ተናወጠች፤ 8 ድንጋዩን ወደ ውኃ መቆሚያ፥ ጭንጫውንም ወደ ውኃ ምንጭ ከለወጠ።

ዳዊት 115

1 ለእኛ አይደለም፥ አቤቱ፥ ለእኛ አይደለም፥ ነገር ግን ለስምህ ስለ ምሕረትህ ስለ እውነትህም ምስጋናን ስጥ። 2 አሕዛብ። አምላካቸው ወዴት ነው? አይበሉ። 3 አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው፤ በሰማይም በምድርም የፈቀደውን ሁሉ አደረገ። 4 የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። 5 አፍ አላቸው አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው አያዩምም፤ 6 ጆሮ አላቸው አይሰሙምም፤ አፍንጫ አላቸው አያሸትቱምም፤ 7 እጅ አላቸው አይዳሰሱምም፤ እግር አላቸው አይሄዱምም፤ በጕሮሮአቸውም አይናገሩም። 8 የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። 9 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው። 10 የአሮን ቤት ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው። 11 እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ ረድኤታቸውና መታመኛቸው እርሱ ነው። 12 እግዚአብሔር አሰበን ይባርከንማል፤ የእስራኤልን ቤት ይባረካል፥ የአሮንንም ቤት ይባረካል። 13 እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ ትንንሾችንና ትልልቆችን ይባርካል። 14 እግዚአብሔር በላያችሁ፥ በላያችሁና በልጆቻችሁ ላይ ይጨምር። 15 እናንተ ሰማይንና ምድርን ለሠራ ለእግዚአብሔር የተባረካችሁ ናችሁ። 16 የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት። 17 አቤቱ፥ ሙታን የሚያመሰግኑህ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ሁሉ፤ 18 እኛ ሕያዋን ግን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔርን እንባርካለን። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 116

ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። 2 ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። 3 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ። 4 የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ። አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። 5 እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ ነው፥ አምላካችንም ይቅር ባይ ነው። 6 እግዚአብሔር ሕፃናትን ይጠብቃል፤ ተቸገርሁ እርሱም አዳነኝ። 7 ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና፤ 8 ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድኖአልና። 9 በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ። 10 አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ፤ እኔም እጅግ ተቸገርሁ። 11 እኔም ከድንጋጤዬ የተነሣ። ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው አልሁ። 12 ስላደረገልኝ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምንን እመልሳለሁ? 13 የመድኃኒትን ጽዋ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። 14 በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ። 15 የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው። 16 አቤቱ፥ እኔ ባሪያህ ነኝ፥ ባሪያህ ነኝ፥ የሴት ባሪያህም ልጅ ነኝ፤ ሰንሰለቴን ሰበርህ። 17 ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። 18 በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፥ 19 በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፥ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ በመካከልሽም። ሃሌሉያ

ዳዊት 117

ሃሌ ሉያ። 1 አሕዛብ ሁላችሁ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፥ ወገኖችም ሁሉ ያመስግኑት፤ 2 ምሕረቱ በእኛ ላይ ጸንታለችና፤ የእግዚአብሔርም እውነት ለዘላለም ትኖራለች። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 118

ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና። 2 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ። 3 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ። 4 ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ። 5 በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም። 6 እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል? 7 እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ። 8 በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። 9 በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል። 10 አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤ 11 መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤ 12 ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው። 13 ገፋኸኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ። 14 ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ። 15 የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች። 16 የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች። 17 አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ። 18 መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አልሰጠኝም። 19 የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 20 ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ። 21 ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 22 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥ 23 ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት። 24 እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን። 25 አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና። 26 በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ። 27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት። 28 አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንህማለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 29 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።

ዳዊት 119

1 በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። 2 ምስክሩን የሚፈልጉ፥ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው፤ 3 ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ። 4 ትእዛዛትህን እጅግ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝህ። 5 ሥርዓትህን ለመጠበቅ፤ መንገዶቼ ይቀኑ ዘንድ እወድድ ነበር። 6 ትእዛዝህን ሁሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርም። 7 አቤቱ፥ የጽድቅህን ፍርድ ስማር በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ። 8 ሥርዓትህን እጠብቃለሁ፤ በፍጹም አትጣለኝ። ቤት 9 ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው። 10 በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥ ከትእዛዝህ አታርቀኝ። 11 አንተ እንዳልበድል፥ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። 12 አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። 13 የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ። 14 እንደ ብልጥግና ሁሉ በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ። 15 ትእዛዝህን አሰላስላለሁ፥ መንገድህንም እፈልጋለሁ። 16 በትእዛዝህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። ጋሜል 17 ለባሪያህ መልካም አድርግ ሕያው እንድሆን፥ ቃልህንም እንድጠብቅ። 18 ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ። 19 እኔ በምድር እንግዳ ነኝ፤ ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር። 20 ነፍሴ ሁልጊዜ ፍርድህን እጅግ ናፈቀች። 21 ከትእዛዛትህ የሳቱትን ትዕቢተኞችንና ርጉማንን ዘለፍህ። 22 ምስክርህን ፈልጌአለሁና። ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ። 23 አለቆች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፤ ባሪያህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። 24 ምስክርህም ተድላዬ ነው፥ ሥርዓትህም መካሪዬ ነው። ዳሌጥ 25 ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች፤ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። 26 መንገድህን ነገርሁ ሰማኸኝም፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። 27 የሥርዓትህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ተኣምራትህንም አሰላስላለሁ። 28 ከኀዘን የተነሣ ነፍሴ አንቀላፋች፤ በቃልህ አጠንክረኝ። 29 የዓመፅን መንገድ ከእኔ አርቅ፥ በሕግህም ማረኝ፤ 30 የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥ ፍርድህንም አልረሳሁም። 31 አቤቱ፥ ምስክርህን ተጠጋሁ፤ አታሳፍረኝ። 32 ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥ በትእዛዝህ መንገድ ሮጥሁ። ሄ 33 አቤቱ፥ የሥርዓትህን መንገድ አስተምረኝ፥ ሁልጊዜም እፈልገዋለሁ። 34 እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እፈልጋለሁ፤ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ። 35 እርስዋን ወድጃለሁና የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ። 36 ልቤን ወደ ምስክርህ አዘንብል፥ ወደ ስስትም አይሁን። 37 ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ፤ በመንገድህ ሕያው አድርገኝ። 38 እንዲፈራህ ባሪያህን በቃልህ አጽና። 39 ፍርድህ መልካም ናትና የተጠራጠርሁትን ስድብ ከእኔ አርቅ። 40 እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፤ በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ ዋው 41 አቤቱ፥ እንደ ቃልህ፥ ምሕረትህና መድኃኒትህ ይምጡልኝ። 42 በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ። 43 በፍርድህም ታምኛለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። 44 ለዘላለም ዓለም ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ። 45 ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና አስፍቼ እሄዳለሁ። 46 በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፤ 47 እጅግም በወደድኋቸው በትእዛዛትህ ደስ ይለኛል። 48 እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤ ሥርዓትህንም አሰላስላሁ። ዛይ 49 ለባሪያህ ተስፋ ያስደረግኸውን ቃልህን አስብ። 50 ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ። 51 ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፤ እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም። 52 ከጥንት የነበረውን ፍርድህን አሰብሁ፥ አቤቱ፥ ተጽናናሁም። 53 ሕግህን ከተዉ ከኃጢአተኞች የተነሣ ኅዘን ያዘኝ። 54 በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ። 55 አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን አሰብሁ፥ ሕግህንም ጠበቅሁ። 56 ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና፤ ይህች ሆነችልኝ። ሔት 57 እግዚአብሔር ክፍሌ ነው፤ ሕግህን እጠብቃለሁ አልሁ። 58 በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ተማለልሁ፤ እንደ ቃልህ ማረኝ። 59 ስለ መንገዶችህ አሰብሁ፥ እግሬንም ወደ ምስክሮችህ መለስሁ። 60 ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ አልዘገየሁምም። 61 የኃጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። 62 ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። 63 እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። 64 አቤቱ፥ ምሕረትህ በምድር ሁሉ ሞላች፤ ሥርዓትህን አስተምረኝ። ጤት 65 አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ለባሪያህ መልካም አደረግህ። 66 በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካም ምክርና እውቀትን አስተምረኝ። 67 እኔ ሳልጨነቅ ሳትሁ፤ አሁን ግን ቃልህን ጠበቅሁ። 68 አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥ በቸርነትህም ሥርዓትህን አስተምረኝ። 69 የትዕቢተኞች ዓመፅ በላዬ በዛ፤ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ። 70 ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። 71 ሥርዓትህን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ። 72 ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል። ዮድ 73 እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ። 74 በቃልህ ታምኛለሁና የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል። 75 አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥ በእውነትህም እንዳስቸገርኸኝ አወቅሁ። 76 ምሕረትህ ለመጽናናቴ ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው። 77 ሕግህ ተድላዬ ናትና ቸርነትህ ትምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር። 78 ትዕቢተኞች በዓመፅ ጠምመውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን በትእዛዝህ እጫወታለሁ። 79 የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። 80 እንዳላፍር ልቤ በሥርዓትህ የቀና ይሁን። ካፍ 81 ነፍሴ መድኃኒትህን ናፈቀች፤ በቃልህም ታመንሁ። 82 መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ ዓይኖቼ ስለ ቃልህ ፈዘዙ። 83 በጢስ እንዳለ አቁማዳ ሆኛለሁና፤ ሥርዓትህን ግን አልረሳሁም። 84 የባሪያህ ዘመኖች ስንት ናቸው? በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ? 85 ኃጢአተኞች ጨዋታን ነገሩኝ፥ አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም። 86 ትእዛዛትህ ሁሉ እውነት ናቸው፤ በዓመፅ አሳድደውኛል፤ እርዳኝ። 87 ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤ እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም። 88 እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፤ የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ። ላሜድ 89 አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል። 90 እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤ ምድርን መሠረትሃት እርስዋም ትኖራለች። 91 ሁሉም ባሪያዎችህ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል። 92 ሕግህ ተድላዬ ባይሆን፥ ቀድሞ በጐስቍልናዬ በጠፋሁ ነበር። 93 በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም። 94 እኔ የአንተ ነኝ፤ ፍርድህን ፈልጌአልሁና አድነኝ። 95 ኃጢአተኞች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፤ ምስክርህን ግን መረመርሁ። 96 የሥራህን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፤ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። ሜም 97 አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው። 98 ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። 99 ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። 100 ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ። 101 ቃልህን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ። 102 አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም። 103 ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ። 104 ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ። ኖን 105 ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው። 106 የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም። 107 እጅግ ተቸገርሁ፤ አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። 108 አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥ ፍርድህንም አስተምረኝ። 109 ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፤ ሕግህን ግን አልረሳሁም። 110 ኃጢአተኞች ወጥመድን ዘረጉብኝ፤ ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም። 111 የልቤ ደስታ ነውና ምስክርህን ለዘላለም ወረስሁ። 112 ለዘላለም ለፍጻሜውም ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልሁ። ሳምኬት 113 ዓመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግህን ግን ወደድሁ። 114 አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥ በቃልህም ተማመንሁ። 115 እናንተ ኃጢአተኞች፥ ከእኔ ራቁ፥ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ። 116 እንደ ቃልህ ደግፈኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ። ከተስፋዬም አልፈር። 117 እርዳኝ እድናለሁም፥ ሁልጊዜም ሥርዓትህን እመረምራለሁ። 118 ምኞታቸው ዓመፃ ነውና ከሥርዓትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው። 119 የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ እንደ ርኵሰት አጠፋሃቸው፤ ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ። 120 ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደንገጠ፤ ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁ። ዔ 121 ፍርድንና ጽድቅን ሠራሁ፤ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። 122 ባሪያህን በመልካም ጠብቀው፤ ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ። 123 ዓይኖቼ ለማዳንህ፥ ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ። 124 ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥ ሥርዓትህንም አስተምረኝ። 125 እኔ ባሪያህ ነኝ፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ ምስክርህንም አውቃለሁ። 126 ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው፥ ሕግህንም ሻሩት። 127 ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ። 128 ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥ የዓመፅንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ፌ 129 ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው። 130 የቃልህ ፍቺ ያበራል፥ ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል። 131 አፌን ከፈትሁ፥ አለከለክሁም፤ ወደ ትእዛዝህ ናፍቄአለሁና። 132 ስምህን ለሚወድዱ እንድምታደርገው ፍርድ፥ ወደ እኔ ተመልከተ ማረኝም። 133 አካሄድን እንደ ቃልህ አቅና፤ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ። 134 ከሰው ግፍ አድነኝ፤ ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ። 135 በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፥ ሥርዓትህንም አሰተምረኝ። 136 ሕግህን አልጠበቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዓይኖቼ ፈሰሰ። ጻዴ 137 አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድህም ቅን ነው። 138 ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው። 139 ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ። 140 ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፥ ባሪያህም ወደደው። 141 እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤ ትእዛዛትህን ግን አልረሳሁም። 42 ጽድቅህ የዘላለም ጽድቅ ነው፥ ቃልህም እውነት ነው። 143 መከራና ችግር አገኙኝ፤ ትእዛዛትህ ግን ተድላዬ ናቸው። 144 ምስክርህ ለዘላለም ጽድቅ ነው፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ። ቆፍ 145 በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ፥ ስማኝ፤ ሥርዓትህን እፈልጋለሁ። 146 ወደ አንተ ጮኽሁ፤ አድነኝ፥ ምስክርህንም እጠብቃለሁ። 147 ማለዳ ጮኽሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ። 148 ቃልህን አስብ ዘንድ ዓይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ። 149 አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ ድምፄን ስማ፤ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። 150 በዓመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ፥ ከሕግህም ራቁ። 151 አቤቱ፥ አንተ ቅርብ ነህ፥ መንገዶችህም ሁሉ ቅኖች ናቸው። 152 ከዘላለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ጀምሮ ከምስክርህ የተነሣ አወቅሁ። ሬስ 153 ሕግህን አልረሳሁምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም። 154 ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፤ ስለ ቃልህ ሕያው አድርገኝ። 155 መድኃኒት ከኅጥኣን ሩቅ ነው፥ ሥርዓትህን አልፈለጉምና። 156 አቤቱ፥ ቸርነትህ እጅግ ብዙ ነው፤ እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ። 157 ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፤ ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልሁም። 158 ቃልህን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ። 159 ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ሕያው አድርገኝ። 160 የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥ የጽድቅህንም ፍርድ ሁሉ ለዘላለም ነው። ሳን 161 ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ፤ ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ። 162 ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። 163 ዓመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፤ ሕግን ግን ወደድሁ። 164 ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ። 165 ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም። 166 አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደርግሁ፥ ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ። 167 ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች እጅግም ወደደችው። 168 መንገዶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸውና ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ። ታው 169 አቤቱ፥ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፤ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ። 170 ልመናዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፤ እንደ ቃልህ አድነኝ። 171 ሥርዓትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ። 172 ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልህን ተናገረ። 173 ትእዛዛትህን መርጫለሁና እጅህ የሚያድነኝ ይሁን። 174 አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፤ ሕግህም ተድላዬ ነው። 175 ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንህማለች፥ ፍርድህም ይርዳኝ። 176 እንደ ጠፉ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባሪያህን ፈልገው።

ዳዊት 120

የመዓርግ መዝሙር። 1 በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ሰማኝም። 2 ከዓመፀኛ ከንፈር ከሸንጋይም አንደበት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት። 3 ስለ ሽንገላ አንደበት ምንም ይሰጡሃል? ምንስ ይጨምሩልሃል? 4 እንደ በረሃ እንጨት ፍም የኃያላን ፍላጾች የተሳሉ ናቸው። 5 መኖሪያዬ የራቀ እኔ ወዮልኝ፤ በቄዳር ድንኳኖች አደርሁ። 6 ሰላምን ከሚጠሉ ጋር ነፍሴ ብዙ ጊዜ ኖረች። 7 እኔ ሰላማዊ ነኝ፤ በተናገኋቸው ጊዜ ግን በከንቱ ተሰለፉብኝ።

ዳዊት 121

የመዓርግ መዝሙር። 1 ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? 2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። 4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። 5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። 6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት። 7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል። 8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።

ዳዊት 122

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር። 1 ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሄድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ። 2 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ። 3 ኢየሩሳሌምስ እርስ በርስዋ እንደ ተገጠገጠች ከተማ ተሠርታለች። 4 የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ ዘንድ፥ ለእስራኤል ምስክር ሊሆኑ የእግዚአብሔር ነገዶች ወደዚያ ይወጣሉ። 5 ዙፋኖች በዚያ ለፍርድ ተቀምጠዋልና፥ የዳዊት ቤት ዙፋኖች። 6 ለኢየሩሳሌም ሰላምን ለምኑ፤ አንተንም ለሚወድዱ ልማት ይሁን። 7 በኃይልህ ሰላም፥ በጌጠኛ ቤትህም ልማት ይሁን። 8 ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም፥ በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ። 9 ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ።

ዳዊት 123

የመዓርግ መዝሙር። 1 በሰማይ የምትኖር ሆይ፥ ዓይኖቼን ወደ አንተ አነሣሁ። 2 እነሆ፥ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደ ሆኑ፥ የባሪያይቱም ዓይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው። 3 ማረን፥ አቤቱ፥ ማረን፤ ንቀትን እጅግ ጠግበናልና፤ 4 የባለጠጎች ስድብና የትዕቢተኞችን ንቀት ነፍሳችን እጅግ ጠገበች።

ዳዊት 124

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል። 2 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥ 3 ቍጣቸውን በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፤ 4 በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤ 5 በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር። 6 ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ። 7 ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን። 8 ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።

ዳዊት 125

የመዓርግ መዝሙር። 1 በእግዚአብሔር የታመኑ እንደማይታወክ ለዘላለም እንደሚኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው። 2 ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ሆኑ፥ ከዛሬ ጀምሮ ለዘላለም፤ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው። 3 ጻድቃን እጃቸውን ወደ ክፋት እንዳይዘረጉ የኃጥኣን በትር በጻድቃን ዕጣ ላይ አይኖርም። 4 አቤቱ፥ ለቸሮች ልባቸውም ለቀና መልካምን አድርግ። 5 ወደ ጠማማነት የሚመለሱትን ግን ዓመፃን ከሚሠሩት ጋር እግዚአብሔር ይወስዳቸዋል። ሰላም በእስራኤል ላይ ይሁን።

ዳዊት 126

የመዓርግ መዝሙር። 1 እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ እጅግ ደስተኞች ሆንን። 2 በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፥ አንደበታችንም ሐሴትን ሞላ፤ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገላቸው ተባለ። 3 እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን። 4 አቤቱ፥ በደቡብ እንዳሉ ፈሳሾች ምርኮአችንን መልስ። 5 በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ። 6 በሄዱ ጊዜ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።

ዳዊት 127

የመዓርግ መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። 2 በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ። 3 እነሆ፥ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፥ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። 4 በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው። 5 ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ብፁዕ ሰው ነው፤ ጠላቶቻቸውን በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ እርሱ አያፍርም።

ዳዊት 128

የመዓርግ መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፥ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው። 2 የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይሆንልሃል። 3 ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው። 4 እነሆ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል። 5 እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ የኢየሩሳሌምን መልካምነትዋን ታያለህ። 6 የልጆችህንም ልጆች ታያለህ። በእስራኤል ላይ ሰላም ይሁን።

ዳዊት 129

የመዓርግ መዝሙር። 1 እስራኤል። ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ ይበል፤ 2 ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ፤ ነገር ግን አላሸነፉኝም። 3 ኃጢአተኞች በጀርባዬ ላይ መቱኝ፥ ኃጢአታቸውንም አስረዘሙአት። 4 እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ የኃጢአተኞችን አንገታቸውን ቈረጠ። 5 ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። 6 በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፥ ሳይነቀል እንደሚደርቅ፥ 7 ለሚያጭደው እጁን፥ ነዶዎቹን ለሚሰበስብ እቅፉን እንደማይሞላ ይሁኑ። 8 በመንገዱም የሚያልፉ። የእግዚአብሔር በረከት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በእግዚአብሔር ስም እንመርቃችኋለን አይሉም።

ዳዊት 130

የመዓርግ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ። 2 አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፤ ጆሮህ የልመናዬን ቃል የሚያደምጥ ይሁን። 3 አቤቱ፥ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? 4 ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና። 5 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች። 6 ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች። 7 ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን። 8 እርሱም እስራኤልን ከኃጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።

ዳዊት 131

የዳዊት መዓርግ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ልቤ አይታበይብኝ፥ ዓይኖቼም ከፍ ከፍ አይበሉብኝ፤ ከትልልቆች ጋር፥ ከእኔም ይበልጥ ከሚከበሩ ጋር አልሄድሁም። 2 ነፍሴን አሳረፍኋት፥ የእናቱንም ጡት እንዳስተውት ዝም አሰኘኋት፤ ነፍሴ የእናቱን ጡት እንዳስተውት በእኔ ውስጥ ናት። 3 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን።

ዳዊት 132

የመዓርግ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤ 2 ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ። 3 በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥ 4 ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥ 5 ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ። 6 እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። 7 ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን። 8 አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት። 9 ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው። 10 ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ። 11 እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ። ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ። 12 ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘላለም ይቀመጣሉ። 13 እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ። 14 ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። 15 አሮጊቶችዋን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ። 16 ካህናቶችዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ቅዱሳኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል። 17 በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ። 18 ጠላቶችንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፤ በእርሱ ግን ቅድስናዬ ያብባል።

ዳዊት 133

የዳዊት የመዓርግ መዝሙር። 1 ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። 2 ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። 3 በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና።

ዳዊት 134

የመዓረግ መዝሙር። 1 እነሆ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ፥ በአምላካችን ቤት አደባባዬች የምትቆሙ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሁላችሁ። 2 በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ። 3 ሰማይንና ምድርን የሠራ እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ።

ዳዊት 135

1 ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ 2 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ። 3 እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤ 4 እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥ እስራኤልንም ለመዝገቡ መርጦታልና፤ 5 እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፥ ጌታችንም ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አውቄአለሁና። 6 በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ። 7 ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል። 8 የግብጽን በኵር ልጆች ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ። 9 ግብጽ ሆይ፥ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ ተኣምራትንና ድንቅን ሰደደ። 10 ብዙ አሕዛብን መታ፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ። 11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥ የከነዓንን መንግሥታት ሁሉ ገደለ፤ 12 ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ። 13 አቤቱ፥ ስምህ ለዘላለም ነው፥ ዝክርህም ለልጅ ልጅ ነው፤ 14 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና። 15 የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። 16 አፍ አላቸው፥ አይናገሩምም፤ ዓይን አላቸው፥ አያዩምም፤ 17 ጆሮ አላቸው፥ አይሰሙምም፤ እስትንፋስም በአፋቸው የለም። 18 የሚሠሩአቸው ሁሉ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁን። 19 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት። የአሮን ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት፤ 20 የሌዊ ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኩት። 21 በኢየሩሳሌም የሚያድር እግዚአብሔር ከጽዮን የተባረከ ነው። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 136

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። 2 የአማልክትን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። 3 የጌቶችን ጌታ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 4 እርሱ ብቻውን ታላቅ ተኣምራትን ያደረገ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 5 ሰማያትን በብልሃት የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 6 ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 7 ብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 8 ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 9 ለጨረቃና ለከዋክብትም ሌሊትን ያስገዛቸው፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 10 ከበኵራቸው ጋር ግብጽን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 11 እስራኤልንም ከመካከላቸው ያወጣ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 12 በጸናች እጅ በተዘረጋችም ክንድ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 13 የኤርትራን ባሕር በየክፍሉ የከፈለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 14 እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 15 ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 16 ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 17 ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 18 ብርቱዎችንም ነገሥታት የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 19 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 20 የባሳንን ንጉሥ ዐግን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 21 ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 22 ለባሪያው ለእስራኤል ርስት፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። 23 እኛን በመዋረዳችን አስቦናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 24 ከጠላቶቻችንም እጅ አድኖናልና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ 25 ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። 26 የሰማይን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።

ዳዊት 137

1 በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። 2 በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። 3 የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም። የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። 4 የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን? 5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ። 6 ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ። 7 አቤቱ፥ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ። እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን። 8 አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው። 9 ሕፃናቶችሽን ይዞ በዓለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው።

ዳዊት 138

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ። 2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህ ስምህንም አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና። 3 በጠራሁህ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ፤ ነፍሴን በኃይልህ በብዙ አጸናሃት። 4 አቤቱ፥ የምድር ነገሥታት ሁሉ ያመሰግኑሃል፤ የአፍህን ቃል ሁሉ ሰምተዋልና። 5 በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ፤ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና። 6 እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል። 7 በመከራ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ሕያው ታደርገኛለህ፤ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለህ፥ ቀኝህም ታድነኛለች። 8 እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ ለዘላለም ነው፤ አቤቱ፥ የእጅህን ሥራ ቸል አትበል።

ዳዊት 139

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። 2 አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። 3 ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥ 4 የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ። 5 አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ፤ አንተ ፈጠርኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። 6 እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም። 7 ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? 8 ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። 9 እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ 10 በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። 11 በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ 12 ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። 13 አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። 14 ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። 15 እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። 16 ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። 17 አቤቱ፥ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቍጥራቸውም እንደ ምን በዛ! 18 ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፤ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። 19 አቤቱ፥ አንተ ኃጢአተኞችን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ ከእኔ ፈቀቅ በሉ። 20 በክፋት ይናገሩብሃልና፤ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል። 21 አቤቱ፥ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን? 22 ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፥ ጠላቶችም ሆኑኝ። 23 አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤ 24 በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።

ዳዊት 140

ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1-2 አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ፤ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ። 3 ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው። 4 አቤቱ፥ ከኃጢአተኞች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ። 5 ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ። 6 እግዚአብሔርንም። አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት። 7 አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጕልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ። 8 አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፤ እንዳይጓደዱ አትተወኝ። 9 የሚከብቡኝን ራስ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው። 10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ ማዕበል ይጣሉ። 11 ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፤ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል። 12 እግዚአብሔር ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንዲያደርግ አወቅሁ። 13 ጻድቃንም በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ ቀኖችም በፊትህ ይኖራሉ።

ዳዊት 141

የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ስማኝ፤ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ቃል አድምጥ። 2 ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን። 3 አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ። 4 ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፃን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር። 5 ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና። 6 ኃያላኖቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፤ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ። 7 በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ። 8 አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፤ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት። 9 ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ። 10 እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ኃጢአተኞች በወጥመዳቸው ይውደቁ።

ዳዊት 142

ጸሎት፤ በዋሻ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት። 1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ። 2 ልመናዬን በፊቱ አፈስሳለሁ፤ መከራዬንም በፊቴ እናገራለሁ። 3 ነፍሴ በውስጤ ባለቀች ጊዜ መንገዴን አወቅሁ፤ በምሄድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ። 4 ወደ ቀኝ ተመለከትሁ አየሁም፥ የሚያውቀኝም አጣሁ፤ መሸሸጊያም የለኝም፥ ስለ ነፍሴም የሚመራመር የለም። 5 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ። አንተ ተስፋዬ ነህ፥ በሕያዋንም ምድር አንተ እድል ፈንታዬ ነህ አልሁ። 6 እጅግ ተቸግሬአለሁና ወደ ልመናዬ አድምጥ፤ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። 7 አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤ ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ።

ዳዊት 143

ልጁ ባሳደደው ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ። 2 ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባሪያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ። 3 ጠላትህ ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጐስቍሎአታል፤ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል። 4 ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ። 5 የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ። 6 እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። 7 አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን። 8 አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ። 9 አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ። 10 አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ። 11 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት። 12 በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።

ዳዊት 144

ስለ ጎልያድ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ፥ ለእጆቼ ሰልፍን፥ ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር፤ 2 መሓሪዬና መሸሸጊያዬ፥ መጠጊያዬና መድኃኒቴ፤ ረዳቴና መታመኛዬም፤ ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ። 3 አቤቱ፥ እርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? 4 ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል፤ ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። 5 አቤቱ፥ ሰማዮችህን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም፤ ተራሮችን ዳስሳቸው ይጢሱም። 6 መብረቆችህን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም፤ ፍላጾችህን ላካቸው አስደንግጣቸውም። 7-8 እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውኆች፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። 9 አቤቱ፥ አዲስ ቅኔ እቀኛልሃለሁ፤ አሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልሃለሁ። 10 ለነገሥታት መድኃኒትን የሚሰጥ፥ ባሪያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው እርሱ ነው። 11 አድነኝ፥ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር፥ ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከሆነ፥ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ። 12 ልጆቻቸው በጕልማስነታቸው እንደ አዲስ አትክልት የሆኑ፥ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ እልፍኝ ያማሩና ያጌጡ፤ 13 ዕቃ ቤቶቻቸውም የተሞሉ በየዓይነቱ ዕቃ የሚሰጡ፥ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ፥ በማሰማርያቸውም የሚበዙ፥ 14 ላሞቻቸውም የሚሰቡ፤ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ የሌለው፥ በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለ፤ 15 እንደዚህ የሚሆን ሕዝብ የተመሰገነ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው።

ዳዊት 145

የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ። 2 በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ። 3 እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም። 4 ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ። 5 የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ። 6 የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ። 7 የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ። 8 እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው፤ 9 እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው። 10 አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። 11 የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥ 12 ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ 13 መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው። 14 እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል። 15 የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። 16 አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ። 17 እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። 18 እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። 19 ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም። 20 እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል። 21 አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።

ዳዊት 146

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር። 1 ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ። 2 በሕይወቴ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ። 3 ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። 4 ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል። 5 የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው፤ 6 እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፥ በእነርሱ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፤ እውነትን ለዘላለም የሚጠብቅ፤ 7 ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል፤ 8 እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ 9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል። 10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፥ አምላክሽ ለልጅ ልጅ ነው። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 147

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር። 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው። 2 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል። 3 ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል። 4 የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል። 5 ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም። 6 እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል። 7 ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፤ 8 ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም። 9 ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል። 10 የፈረስን ኃይል አይወድድም፥ በሰውም ጭን አይደሰትም። 11 እግዚአብሔር በሚፈሩት፥ በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል። 12 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ፥ 13 ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና። 14 በወሰንሽም ሰላምን አደረገ፥ የስንዴንም ስብ አጠገበሽ። 15 ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፥ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል። 16 አመዳዩን እንደ ባዘቶ ይሰጣል፤ ጉሙን እንደ አመድ ይበትነዋል፤ 17 በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፤ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል? 18 ቃሉን ልኮ ያቀልጠዋል፤ ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችንም ያፈስሳል። 19 ቃሉን ለያዕቆብ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል። 20 ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፥ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 148

የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር። 1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት። 2 መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት። 3 ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት። 4 ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት የሰማያት በላይም ውኃ። 5 እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት። 6 ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም። 7 እባቦች ጥልቆችም ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤ 8 እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤ 9 ተራሮች ኰረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ፤ 10 አራዊትም እንስሳትም ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾችም የሚበርሩ ወፎችም፤ 11 የምድር ነገሥታት አሕዛብም ሁሉ፥ አለቆች የምድርም ፈራጆች ሁሉ፥ 12 ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፥ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ 13 የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው። 14 የሕዝቡንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የቅዱሳኑንም ሁሉ ምስጋና ወደ እርሱ ለቀረበ ለእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 149

1 ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው። 2 እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፥ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያድርጉ። 3 ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት። 4 እግዚአብሔር በሕዝቡ ተደስቶአልና፥ የዋሃንንም በማዳኑ ከፍ ከፍ ያደርጋልና። 5 ቅዱሳን በክብር ይመካሉ፤ በምንጣፋቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ። 6 የእግዚአብሔር ምስጋና በጕሮሮአቸው ነው፤ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጃቸው ነው፥ 7 በአሕዛብ ላይ በቀልን በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፤ 8 ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት፥ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩ ዘንድ፤ 9 የተጻፈውን ፍርድ ያደርጉባቸው ዘንድ። ለቅዱሳን ሁሉ ይህች ክብር ናት። ሃሌ ሉያ።

ዳዊት 150

1 ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን በመቅደሱ አመስግኑት፤ በኃይሉ ጠፈር አመስግኑት። 2 በችሎቱ አመስግኑት፤ በታላቅነቱ ብዛት አመስግኑት። 3 በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት። 4 በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት። 5 ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት። 6 እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።

ምሳሌ 1

1 የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ 2 ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፥ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፥ 3 የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፥ 4 ብልሃትን ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ ለጐበዛዝትም እውቀትንና ጥንቃቄን፥ 5 ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፥ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። 6 ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባንና ቃልና የተሸሸገውን ነገር ለማስተዋል። 7 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። 8 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናንትህንም ሕግ አትተው፤ 9 ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና። 10 ልጄ ሆይ፥ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል። 11 ደምን ለማፍሰስ ለእኛ ጋር ና እናድባ፥ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት ቢሉ፤ 12 በሕይወታቸው ሳሉ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፥ በሙሉም ወደ ጕድጓድ እንደሚወድቁ ይሁኑ፤ 13 መልካሙን ሀብት ሁሉ እናገኛለን፥ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፤ 14 ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን ቢሉ፤ 15 ልጄ ሆይ፥ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፥ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤ 16 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፥ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። 17 መርበብ በወፎች ዓይን ፊት በከንቱ ትተከላለችና። 18 እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፥ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ። 19 እንዲሁ ይህ መንገድ ትርፍን ለማግኘት የሚሳሳ ሁሉ ነው። የባለቤቱን ነፍስ ይነጥቃል። 20 ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፤ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤ 21 በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች። 22 እናንተ አላዋቂዎች፥ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? ሰነፎችም እውቀትን ይጠላሉ? 23 ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፥ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፤ ቃሌን አስተምራችኋለሁ። 24 በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፥ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፥ 25 ምክሬን ሁሉ ግን ቸል ስላላችሁ፥ ዘለፋዬንም ስላልፈቀዳችሁ፤ 26 እኔም ስለዚህ በጥፋታችሁ እስቃለሁ፤ ጥፋታችሁም በመጣ ጊዜ አላግጥባችvሁ። 27 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ጥፋታችሁም እንደ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ፥ ጭንቅና መከራ በወረደባችሁ ጊዜ። 28 የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፥ እኔ ግን አልመልስም፤ ተግተው ይሹኛል፥ ነገር ግን አያገኙኝም። 29 እውቀትን ጠልተዋልና፥ እግዚአብሔርንም መፍራት አልመረጡምና፤ 30 ምክሬን አልፈቀዱምና፥ ዘለፋዬንም ሁሉ ንቀዋልና፤ 31 ስለዚህ የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፥ ከራሳቸው ምክር ይጠግባሉ። 32 አላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና። 33 የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።

ምሳሌ 2

1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ 2 ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። 3 ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ 4 እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ 5 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። 6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ 7 እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤ 8 የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። 9 የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ። 10 ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ 11 ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥ 12 ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፤ 13 እነርሱም በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና የሚተው፥ 14 ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ደስታን የሚያደርጉ፥ 15 መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፤ 16 ከጋለሞታ ሴት አንተን ለመታደግ፥ ቃልዋን ከምታለዝብ ከሌላዪቱም ሴት፤ 17 የሕፃንነት ወዳጅዋን የምትተው የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳ፤ 18 ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፥ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ። 19 ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ የሕይወትንም ጎዳና አያገኙም፤ 20 አንተም በደጋግ ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ። 21 ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፥ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ 22 ኃጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።

ምሳሌ 3

1 ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። 2 ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና። 3 ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። 4 በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። 5 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ 6 በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። 7 በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤ 8 ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም ጠገን። 9 እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት፤ 10 ጐተራህም እህልን ይሞላል፥ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች። 11 ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። 12 እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ። 13 ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ 14 በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። 15 ከቀይ ዕንቍም ትከብራለች፥ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። 16 በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። 17 መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። 18 እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው። 19 እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። 20 በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። 21 ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። 22 ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። 23 የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። 24 በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ፥ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆንልሃል። 25 ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኃጥኣን ጥፋት አትፈራም፤ 26 እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና። 27 ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፥ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን። 28 ወዳጅህን። ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ አትበለው። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ። 29 በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ፥ እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ። 30 ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ፥ እርሱ ክፉ ካልሠራብህ። 31 በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። 32 ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። 33 የእግዚአብሔር መርገም በኃጥእ ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። 34 በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። 35 ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ የሰነፎች ከፍታቸው ግን መዋረድ ነው።

ምሳሌ 4

1 እናንተ ልጆች፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፤ 2 መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፤ ሕጌን አትተዉ። 3 እኔም አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር። 4 ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር። ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ። 5 ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልን አግኝ፤ አትርሳም፥ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል። 6 አትተዋት፥ ትደግፍህማለች፤ ውደዳት፥ ትጠብቅህማለች። 7 ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። 8 ከፍ ከፍ አድርጋት፥ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ብታቅፋትም ታከብርሃለች። 9 ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፥ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትሃለች። 10 ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ንግግሬንም ተቀበል፤ የሕይወትህም ዘመን ትበዛልሃለች። 11 የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፤ በቀናች ጎዳና መራሁህ። 12 በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይጠብብም፤ በሮጥህም ጊዜ አትሰናከልም። 13 ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፤ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና። 14 በኃጥኣን መንገድ አትግባ፥ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። 15 ከእርስዋ ራቅ፥ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም። 16 ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፥ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና። 17 የኃጢአትን እንጀራ ይበላሉና፥ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና። 18 የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። 19 የኃጥኣን መንገድ እንደ ጨለማ ነው፥ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም። 20 ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል። 21 ከዓይንህ አታርቃት፥ በልብህም ውስጥ ጠብቃት። 22 ለሚያገኙአት ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና። 23 አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። 24 የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ፥ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ። 25 ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ። 26 የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና። 27 ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ።

ምሳሌ 5

1 ልጄ ሆይ፥ ወደ ጥበቤ አድምጥ፤ ጆሮህን ወደ ትምህርቴ መልስ፥ 2 ጥንቃቄን ትጠብቅ ዘንድ ከንፈሮችህም እውቀትን እንዲጠብቁ። 3 ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና፤ 4 ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው። 5 እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፤ 6 የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፤ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፥ የሚታወቅም አይደለም። 7 አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፥ ከአፌም ቃል አትራቁ። 8 መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ፥ 9 ክብርህ ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ዕድሜህም ለጨካኝ፤ 10 ሌሎች ከሀብትህ እንዳይጠግቡ፥ ድካምህም በባዕድ ሰው ቤት እንዳይሆን። 11 በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥ 12 ትላለህም። እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ! 13 የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። 14 በማኅበርና በጉባኤ መካከል ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ። 15 ከጕድጓድህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ። 16 ምንጮችህ ወደ ሜዳ፥ ወንዞችህ ወደ አደባባይ፥ ይፈስሳሉን? 17 ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ። 18 ምንጭህ ቡሩክ ይሁን፤ ከጕብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። 19 እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፥ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፥ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ። 20 ልጄ ሆይ፥ ስለ ምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ? የሌላይቱንስ ብብት ለምን ታቅፋለህ? 21 የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና። 22 ኃጥኣንን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፥ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። 23 አልተቀጣምና እርሱ ይሞታል፤ በስንፍናውም ብዛት ይስታል።

ምሳሌ 6

1 ልጄ ሆይ፥ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፥ ስለ ሌላ ሰው እጅህን አጋና ብትመታ፥ 2 በአፍህ ቃል ተጠመድህ፤ በአፍህ ቃል ተያዝህ። 3 ልጄ ሆይ፥ ይህን አድርግ ራስህንም አድን፥ በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፤ ፈጥነህ ሂድ፥ ጎረቤትህንም ነዝንዘው። 4 ለዓይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጕልቻን አትስጥ፥ 5 እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፥ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ። 6 አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። 7 አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት 8 መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፥ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች። 9 አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? 10 ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂት ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ 11 እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። 12 ምናምንቴ ሰው የበደለኛም ልጅ በጠማማ አፍ ይሄዳል፤ 13 በዓይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ያስተምራል፤ 14 ጠማማነት በልቡ አለ፥ ሁልጊዜም ክፋትን ያስባል፤ ጠብንም ይዘራል። 15 ስለዚህ ጥፋቱ ድንገት ይደርስበታል፤ ድንገት ይደቅቃል፥ ፈውስም ከቶ የለውም። 16 እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ 17 ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ 18 ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥ 19 በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። 20 ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፥ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ 21 ሁልጊዜም በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው። 22 ስትሄድም ይመራሃል፤ ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል። 23 ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፥ 24 ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ፥ ከሌላይቱም ሴት ምላስ ጥፍጥነት። 25 ውበትዋን በልብህ አትመኘው፤ ሽፋሽፍትዋም አያጥምድህ። 26 የጋለሞታ ዋጋ እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራም ሴት የሰውን ሕይወት ታጠምዳለች። 27 በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? 28 በፍም ላይ የሚሄድ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? 29 ወደ ሰው ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም። 30 ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፤ 31 ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል። 32 ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጐደለ ነው፤ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል። 33 ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም። 34 ቅንዓት ለሰው የቍጣ ትኵሳት ነውና፥ በበቀል ቀን አይራራለትምና። 35 እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፥ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም።

ምሳሌ 7

1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ። 2 ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፤ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፤ 3 በጣቶችህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። 4 ጥበብን። አንቺ እኅቴ ነሽ በላት፥ ማስተማውልንም። ወዳጄ ብለህ ጥራት፥ 5 ከጋለሞታ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ቃልዋን ካለዘበች ከሌላይቱ ሴት። 6 በቤቴ መስኮት ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፤ 7 ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፤ ከጐበዛዝትም መካከል ብላቴናውን አእምሮ ጐድሎት አየሁ፥ 8 በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፥ 9 ማታ ሲመሽ፥ ውድቅትም ሲሆን፥ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ። 10 እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች። 11 ሁከተኛና አባያ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤ 12 አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች። 13 ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው። 14 መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ። 15 ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም። 16 በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ። 17 በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ። 18 ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን። 19 ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤ 20 በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል። 21 በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች። 22 እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥ 23 ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ። 24 ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ። 25 ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል በጎዳናዋ አትሳት። 26 ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው። 27 ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።

ምሳሌ 8

1 በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን? 2 በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች። 3 በበሩ አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፥ በደጁ መግቢያ ትጮኻለች። 4 እናንተ ሰዎች፥ እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው። 5 እናንተ አላዋቂዎች፥ ብልሃትን አስተውሉ፤ እናንተም ሰነፎች ጥበብን በልባችሁ ያዙ። 6 የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ። 7 አፌ እውነትን ይናገራልና፥ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ። 8 የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም። 9 እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፥ እውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው። 10 ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ። 11 ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ትበልጣለችና የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም። 12 እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ። 13 እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ። 14 ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ። 15 ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ። 16 አለቆች በእኔ ያዝዛሉ፥ ክቡራንና የምድር ፈራጆችም ሁሉ። 17 እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል። 18 ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። 19 ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። 20 እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥ 21 ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ። 22 እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። 23 ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ፤ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። 24 ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። 25 ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥ 26 ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፤ የመጀመሪያውን የዓለም አፈር። 27 ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥ 28 ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥ 29 ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ 30 የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ 31 ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ። 32 አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። 33 ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም። 34 የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። 35 እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና። 36 እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፤ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።

ምሳሌ 9

1 ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። 2 ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች። 3 ባሪያዎችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች። 4 አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች። 5 ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። 6 አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ። 7 ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ኅጥአንም የሚዘልፍ ነውርን ያገኛል። 8 ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፤ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። 9 ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ጥበብንም ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው፥ እውቀትንም ያበዛል። 10 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። 11 ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና። 12 ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ። ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፤ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትህን ትማራለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚያዘጋጅ ሰው ነው፤ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ተወ፤ የሚሠማራባትን መንገድ ዘነጋ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፤ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል። 13 ሰነፍ ሴት ሁከተኛ ናት፤ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም። 14 በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥ 15 በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት። 16 አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች። 17 የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል። 18 ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ እድምተኞችዋም በሲኦል ጥልቀት እንዳሉ አያውቅም።

ምሳሌ 10

1 የሰሎሞን ምሳሌዎች። ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን ለእናቱ ኀዘን ነው። 2 በኃጢአት የተገኘ መዝገብ ጥቅም የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ያድናል። 3 እግዚአብሔር የጻድቁን ነፍስ አያስርብም፤ የኅጥኣንን ምኞት ግን ይገለብጣል። 4 የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። 5 በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል። 6 በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኅጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። 7 የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኅጥኣን ስም ግን ይጠፋል። 8 በልቡ ጠቢብ የሆነ ትእዛዝን ይቀበላል፤ በከንፈሩ የሚሰንፍ ግን ይወድቃል። 9 ያለ ነውር የሚሄድ ተማምኖ ይሄዳል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይታወቃል። 10 በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል፤ ደፍሮ የሚገሥጽ ግን ሰላምን ያደርጋል። 11 የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ናት፤ የኃጥኣንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል። 12 ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች። 13 በብልሃተኛ ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤ በትር ግን አእምሮ ለጐደለው ሰው ጀርባ ነው። 14 ጠቢባን እውቀትን ይሸሽጋሉ፤ የሰነፍ አፍ ግን ለጥፋት ይቀርባል። 15 የባለጠጋ ሀብት ለእርሱ የጸናች ከተማ ናት፤ የድሆች ጥፋት ድህነታቸው ነው። 16 የጻድቅ ደመወዝ ለሕይወት ነው፤ የኃጥእ ፍሬ ግን ለኃጢአት ነው። 17 ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ዘለፋን የሚተው ግን ይስታል። 18 ጥልን የሚከድን ሐሰተኛ ከንፈር አለው፤ ሐሜትንም የሚገልጥ ሰነፍ ነው። 19 በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው። 20 የጻድቅ ምላስ የተፈተነ ብር ነው፤ የኅጥኣን ልብ ግን ምናምን ነው። 21 የጻድቅ ከንፈሮች ብዙ ሰዎችን ይመግባሉ፤ ሰነፎች ግን ከልባቸው ጕድለት የተነሣ ይሞታሉ። 22 የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም። 23 ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው። 24 የኀጥእ ሰው ፍርሃት በላዩ ይመጣበታል፥ ለጻድቃንም ምኞታቸው ትሰጣቸዋለች። 25 ዐውሎ ነፋስ ሲያልፍ ኃጥእ አይገኝም፤ ጻድቅ ግን የዘላለም መሠረት ነው። 26 ሆምጣጤ ጥርስን፥ ጢስም ዓይንን እንደሚጐዳ፥ እንዲሁም ታካች ለላኩት። 27 እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ታረዝማለች፤ የኀጥኣን ዕድሜ ግን ታጥራለች። 28 የጻድቃን አለኝታ ደስታ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል። 29 የእግዚአብሔር መንገድ ያለ ነውር ለሚሄድ አምባ ነው፥ ጥፋት ግን ክፋትን ለሚያደርጉ። 30 ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኅጥኣን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም። 31 የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ ጠማማ ምላስ ግን ትቈረጣለች። 32 የጻድቅ ከንፈሮች ደስ የሚያሰኝ ነገርን ያውቃሉ፤ የኀጥኣን አፍ ግን ጠማማ ነው።

ምሳሌ 11

1 አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። 2 ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። 3 ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች። 4 በቍጣ ቀን ሀብት አትረባም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። 5 የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኃጥእ ግን በኃጢአቱ ይወድቃል። 6 ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። 7 ኀጥእ በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። 8 ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ኀጥእም በእርሱ ፋንታ ይመጣል። 9 ዝንጉ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ። 10 በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በኀጥኣንም ጥፋት እልል ትላለች። 11 በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኀጥኣን አፍ ግን ትገለበጣለች። 12 ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል። 13 ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፤ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል። 14 መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል። 15 ለማያውቅ የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፤ ዋስነትን የሚጠላ ግን ይድናል። 16 ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ሀኬተኖችም ሀብትን ያገኛሉ። 17 ቸር ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል። 18 የኀጥእ ሰው ሞያ ሐሰተኛ ነው፤ ጽድቅን የሚዘራ ግን የታመነ ዋጋ አለው። 19 በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው። 20 ልበ ጠማሞች በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው፤ በመንገዳቸው ፍጹማን የሆኑ ግን የተወደዱ ናቸው። 21 ክፉ ሰው እጅ በእጅ ሳይቀጣ አይቀርም፤ የጻድቃን ዘር ግን ይድናል። 22 የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት። 23 የጻድቃን ምኞት በጎ ብቻ ነው፤ የኀጥኣን ተስፋ ግን መቅሠፍት ነው። 24 ያለውን የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም። 25 የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። 26 እህልን የሚያስቀር ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፤ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው። 27 መልካምን ተግቶ የሚሻ ደስታን ይፈልጋል፤ ክፉን በሚፈልግ ግን ክፉ ይመጣበታል። 28 በባለጠግነቱ የሚተማመን ሰው ይወድቃል ጻድቃን ግን እንደ ቅጠል ይለመልማሉ። 29 ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፥ ሰነፍም ለጠቢብ ተገዥ ይሆናል። 30 የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፥ ነፍሶችንም የሚሰበስብ እርሱ ጠቢብ ነው። 31 እነሆ፥ ጻድቅ በምድር ላይ ፍዳውን የሚቀበል ከሆነ፥ ይልቁንስ ኀጥእና ዓመፀኛ እንዴት ይሆናሉ!

ምሳሌ 12

1 ተግሣጽን የሚወድድ እውቀትን ይወድዳል፤ ዘለፋን የሚጠላ ግን ደንቆሮ ነው። 2 ደኅና ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን ያገኛል፤ ተንኰለኛውን ሰው ግን ይቀሥፈዋል። 3 ሰውን ዓመፃ አያጸናውም፤ የጻድቃን ሥር ግን አይንቀሳቀስም። 4 ልባም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት፤ አሳፋሪ ሴት ግን በአጥንቱ ውስጥ እንደ ቅንቅን ናት። 5 የጻድቃን አሳብ ቅን ነው፤ የኃጥኣን ምክር ግን ተንኰል ነው። 6 የኃጥኣን ቃል ደምን ለማፍሰስ ትሸምቃለች፤ የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል። 7 ኀጥኣን ይገለበጣሉ፥ ደግሞም አይገኙም፤ የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። 8 ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤ ልቡ ጠማማ የሆነ ሰው ግን ይናቃል። 9 ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። 10 ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል፤ የኀጥኣን ምሕረት ግን ጨካኝ ነው። 11 ምድሩን የሚሠራ ሰው እንጀራ ይጠግባል፤ ለከንቱ ነገር የሚሮጥ ግን አእምሮ የጐደለው ነው። 12 የኅጥኣን ፈቃድ የክፉዎች ወጥመድ ናት፤ የጻድቃን ሥር ግን ፍሬን ያፈራል። 13 ክፉ ሰው በከንፈሩ ኃጢአት ይጠመዳል፤ ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። 14 የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች፥ ሰውም እንደ እጁ ሥራ ዋጋውን ይቀበላል። 15 የሰነፍ መንገድ በዓይኑ የቀናች ናት፤ ጠቢብ ግን ምክርን ይሰማል። 16 የሰነፍ ቍጣ ቶሎ ይታወቃል፤ ብልህ ሰው ግን ነውርን ይሰውራል። 17 እውነተኛን ነገር የሚናገር ቅን ነገርን ያወራል፤ የሐሰት ምስክር ግን ተንኰልን ያወራል። 18 እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው። 19 የእውነት ከንፈር ለዘላለም ትቆማለች፤ ውሸተኛ ምላስ ግን ለቅጽበት ነው። 20 ክፉን በሚያስቡ ልብ ውስጥ ተንኰል አለ፤ በሰላም ለሚመክሩ ግን ደስታ አላቸው። 21 ጻድቅን መከራ አያገኘውም፤ ኀጥኣን ግን ክፋትን የተሞሉ ናቸው። 22 ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። 23 ብልህ ሰው እውቀትን ይሸሽጋል፤ የሰነፎች ልብ ግን ስንፍናን ያወራል። 24 የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች። 25 ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል። 26 ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። 27 ታካች ሰው አደን ምንም አያድንም፤ ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው። 28 በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ በጎዳናዋም ሞት የለም።

ምሳሌ 13

1 ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል። ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም። 2 ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች። 3 አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋትን ያገኘዋል። 4 የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች። 5 ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም። 6 በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፤ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል። 7 ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፤ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው። 8 ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም። 9 ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል። 10 በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት። 11 በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። 12 የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት። 13 ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፤ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል። 14 ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው። 15 መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፤ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት። 16 ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል። 17 መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው። 18 ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል። 19 የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፤ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ። 20 ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። 21 ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፤ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ። 22 ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች። 23 በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፤ ከፍርድ መጕደል የተነሣ ግን ይጠፋል። 24 በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጻዋል። 25 ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፤ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል።

ምሳሌ 14

1 ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፤ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች። 2 በቅን የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱን የሚያጣምም ግን ይንቀዋል። 3 በሰነፍ አፍ የትዕቢት በትር አለ፤ የጠቢባን ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች። 4 በሬ በሌለበት ስፍራ እህል አይገኝም፤ ብዙ ሲሳይ ግን በበሬዎች ኃይል ነው። 5 የታመነ ምስክር አይዋሽም፤ የሐሰት ምስክር ግን በሐሰት ይናገራል። 6 ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል አያገኛትም፤ ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም። 7 ከሰነፍ ሰው ፊት ራቅ፥ በእርሱ ዘንድ የእውቀትን ከንፈር አታገኝምና። 8 የብልህ ሰው ጥበብ መንገዱን ያስተውል ዘንድ ነው፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ሽንገላ ነው። 9 ሰነፉ በኃጢአት ያፌዛል፤ በቅኖች መካከል ግን ቸርነት አለች። 10 የራሱን ኀዘን ልብ ያውቃል፤ ከደስታውም ጋር ሌላ ሰው አይገናኝም። 11 የኅጥኣን ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ማደሪያ ግን ያብባል። 12 ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። 13 በሳቅ ደግሞ ልብ ያዝናል፥ የደስታም ፍጻሜ ልቅሶ ነው። 14 ልቡን ከጽድቅ የሚመልስ ሰው ከመንገዱ ፍሬ ይጠግባል፥ ጻድቅም ሰው ደግሞ በራሱ። 15 የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል። 16 ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፤ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል። 17 ቍጡ ሰው በስንፍና ይሠራል፤ አስተዋይ ግን ይታገሣል። 18 አላዋቂዎች ሰዎች ስንፍናን ይወርሳሉ፤ ብልሆች ግን እውቀትን እንደ ዘውድ ይጭናሉ። 19 ኃጢአተኞች በደጎች ፊት ይጐነበሳሉ፥ ኀጥኣንም በጻድቃን በር። 20 ድሀ በባልንጀራው ዘንድ የተጠላ ነው የባለጠጋ ወዳጆች ግን ብዙዎች ናቸው። 21 ባልንጀራውን የሚንቅ ይበድላል ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉ ነው። 22 ክፉ የሚያደርጉ ይስታሉ፤ ምሕረትና እውነት ግን መልካምን ለሚያደርጉ ናቸው። 23 በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፤ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ። 24 የጠቢባን ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፤ የሰነፎች ስንፍና ግን ስንፍና ነው። 25 እውነተኛ ምስክር ነፍሶችን ያድናል፤ በሐሰት የሚናገር ግን ሸንጋይ ነው። 26 እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን አለው፥ ለልጆቹም መጠጊያ ይኖራል። 27 ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘድን እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው። 28 የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። 29 ለትግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቍጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል። 30 ትሑት ልብ የሥጋ ሕይወት ነው፤ ቅንዓት ግን አጥንትን ያነቅዛል። 31 ድሀን የሚያስጨንቅ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ ለድሀ ምሕረትን የሚያደርግ ግን ያከብረዋል። 32 ኀጥእ በክፋቱ ይደፋል፤ ጻድቅ ግን በእውነቱ ይታመናል። 33 በአዋቂ ልብ ጥበብ ትቀመጣለች፤ በሰነፎች ውስጥ ግን አትታወቅም። 34 ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤ ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች። 35 አስተዋይ አገልጋይ በንጉሥ ዘንድ ይወደዳል፤ በሚያሳፍር ላይ ግን ቍጣው ይሆናል።

ምሳሌ 15

1 የለዘበች መልስ ቍጣን ትመልሳለች ሸካራ ቃል ግን ቍጣን ታስነሣለች። 2 የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፤ የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል። 3 የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ። 4 ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፤ የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል። 5 ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው። 6 በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው። 7 የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፤ የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም። 8 የኅጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። 9 የኅጥኣን መንገድ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል። 10 ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥ ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል። 11 ሲኦልና ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት የታወቁ ናቸው፤ ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው። 12 ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥ ወደ ጠቢባንም አይሄድም። 13 ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፤ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች። 14 የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፤ የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል። 15 ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፤ የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው። 16 እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል። 17 የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል። 18 ቍጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል። 19 የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፤ የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት። 20 ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል። 21 ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል። 22 ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል። 23 ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፤ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው! 24 በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል። 25 እግዚአብሔር የትዕቢተኞች ቤት ይነቅላል፤ የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል። 26 የበደለኛ አሳብ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናት፤ ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው። 27 ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፤ መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል። 28 የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል የኅጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል። 29 እግዚአብሔር ከኅጥኣን ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል። 30 የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥ መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል። 31 የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ በጠቢባን መካከል ይኖራል። 32 ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል። 33 እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፤ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።

ምሳሌ 16

1 የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 2 የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል። 3 ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች። 4 እግዚአብሔር ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን። 5 በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም። 6 በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል። 7 የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል። 8 በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል። 9 የሰው ልብ መንገዱ ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቀናለታል። 10 የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥ አፉም በፍርድ አይስትም። 11 እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የእግዚአብሔር ናቸው፤ የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው። 12 ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና። 13 የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥ በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል። 14 የንጉሥ ቍጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል። 15 በንጉሥ ፊት ብርሃን ዘንድ ሕይወት አለ፥ መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው። 16 ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው። 17 የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል። 18 ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል። 19 ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል። 20 ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ምስጉን ነው። 21 ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥ በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል። 22 ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው። 23 የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥ ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል። 24 ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው። 25 ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው። 26 የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፥ አፉ ይጐተጕተዋልና። 27 ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ። 28 ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል። 29 ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል። 30 ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፤ ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል። 31 የሸበተ ጠጕር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል። 32 ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ ይበልጣል። 33 ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ምሳሌ 17

1 ጥል ባለበት ዘንድ እርድ ከሞላበት ቤት በጸጥታ ደረቅ ቍራሽ ይሻላል። 2 አስተዋይ ባሪያ ነውረኛውን ልጅ ይገዛል፥ በወንድማማች መካከልም ርስትን ይካፈላል። 3 ማቅለጫ ለብር፥ ከውር ለወርቅ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይፈትናል። 4 ክፉ ሰው የበደለኛን ከንፈር ይሰማል፤ ሐሰተኛም ወደ ተንኰለኛ ምላስ ያደምጣል። 5 በድሀ የሚያላግጥ ፈጣሪውን ይሰድባል፤ በጥፋትም ደስ የሚለው ሳይቀጣ አይቀርም። 6 የሽማግሌዎች አክሊል የልጅ ልጆች ናቸው፤ የልጆችም ክብር አባቶቻቸው ናቸው። 7 ለሰነፍ የኵራት አነጋገር አይገባውም፤ ይልቁንም ሐሰተኛ ከንፈር ለመኰንን አይገባውም። 8 ገንዘብ ባደረገው ፊት መማለጃ እንደ ተዋበ ዕንቍ ነው፥ ወደ ዞረበትም ስፍራ ሁሉ ሥራውን ያቀናል። 9 ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል። 10 መቶ ግርፋት በሰነፍ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሣጽ በአስተዋይ ሰው ጠልቆ ወደ ልቡ ይገባል። 11 ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል፤ ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል። 12 ሰነፍን በስንፍናው ከመገናኘት ልጆችዋ የተነጠቁባትን ድብ መገናኘት ይሻላል። 13 በመልካም ፋንታ ክፉን የሚመልስ፥ ክፉ ነገር ከቤቱ አትርቅም። 14 የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው፤ ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው። 15 ኀጥኡን የሚያጸድቅና በጻድቁ ላይ የሚፈርድ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው። 16 በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። 17 ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። 18 አእምሮ የጐደለው ሰው አጋና ይመታል፥ በባልንጀራውም ፊት ይዋሳል። 19 ዓመፃን የሚወድድ ክርክርን ይወድዳል፤ ደጁንም ዘለግ የሚያደርግ ውድቀትን ይሻል። 20 ጠማማ ልብ ያለው መልካምን አያገኝም፥ ምላሱንም የሚገለብጥ በክፉ ላይ ይወድቃል። 21 ሰነፍን የሚወልድ ኀዘን ይሆንበታል፥ የደንቆሮ ልጅም አባት ደስ አይለውም። 22 ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። 23 ኀጥእ የፍርድን መንገድ ለማጥመም ከብብት መማለጃን ይወስዳል። 24 በአስተዋይ ፊት ጥበብ ትኖራለች፤ የሰነፍ ዓይን ግን በምድር ዳርቻ ነው። 25 ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ምሬት ነው። 26 ጻድቅን መቅጣት፥ ጨዋ ሰውንም በጻድቅነቱ መምታት መልካም አይደለም። 27 ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፥ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው። 28 ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ። ባለ አእምሮ ነው ይባላል።

ምሳሌ 18

1 መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። 2 ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፤ በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ። 3 ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር። 4 የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፥ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው። 5 የጻድቅ ፍርድ ይጠምም ዘንድ፥ ለኀጥእም ማድላት መልካም አይደለም። 6 የሰነፍ ከንፈር በጥል ውስጥ ትገባለች፥ አፉም በትርን ትጠራለች። 7 የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው። 8 የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል። 9 በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው። 10 የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል። 11 ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፥ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር። 12 ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች። 13 ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል። 14 የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፤ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል? 15 የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች። 16 የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች። 17 ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፤ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል። 18 ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥ በኃያላንም መካከል ትበይናለች። 19 የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፤ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው። 20 የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል። 21 ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ። 22 ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል። 23 ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፤ ባለጠጋ ግን በድፍረት ይመልሳል። 24 ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።

ምሳሌ 19

1 በከንፈሩ ከሚወሳልት ሰነፍ ይልቅ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል። 2 ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ እግሩንም የሚያፈጥን ከመንገድ ይስታል። 3 የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፤ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል። 4 ባለጠግነት ብዙ ወዳጆች ይጨምራል፤ የድሀ ወዳጅ ግን ከእርሱ ይርቃል። 5 ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፥ በሐሰትም የሚናገር አያመልጥም። 6 ብዙ ሰዎች ለጋሱን ያቈላምጣሉ፥ ስጦታ ለሚሰጥም ሁሉ ወዳጅ ነው። 7 ድሀን ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፤ ይልቁንም ወዳጆቹ ከእርሱ ይርቃሉ። እነርሱንም በቃል ቢከተላቸው አንዳች አይረቡትም። 8 ጥበብን የሚያገኝ ነፍሱን ይወድዳል፥ ማስተዋልንም የሚጠብቅ መልካም ነገርን ያገኛል። 9 ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፤ በሐሰትም የሚናገር ይጠፋል። 10 ለሰነፍ ቅምጥልነት አይገባውም፥ ይልቁንም ባሪያ በአለቆች ላይ ይገዛ ዘንድ። 11 ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል፥ ለበደለኛውም ይቅር ይል ዘንድ ክብር ይሆንለታል። 12 እንደ አንበሳ ግሣት የንጉሥ ቍጣ ነው፥ ሞገሱም በመስክ ላይ እንዳለ ጠል ነው። 13 ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ኀዘን ነው፥ ጠበኛም ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት። 14 ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት። 15 ተግባር መፍታት እንቅልፍን ታመጣለች፥ የታካችም ነፍስ ትራባለች። 16 ትእዛዝን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ መንገዱን ቸል የሚል ግን ይጠፋል። 17 ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል። 18 ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፥ መሞቱንም አትሻ። 19 ንዴተኛ ሰው መቀጮ ይከፍላል፤ ብታድነውም ደግሞ ትጨምራለህ። 20 ምክርን ስማ፥ ተግሣጽንም ተቀበል በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ። 21 በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። 22 የሰው ቸርነት የእርሱ ፍሬ ነው፤ ከሐሰተኛ ባለጠጋም እውነተኛ ድሀ ይሻላል። 23 እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ የሚፈራውም ጠግቦ ይኖራል፥ ክፉ ነገርም አያገኘውም። 24 ታካች ሰው እጁን በወጭቱ ያጠልቃታል፥ ወደ አፉ ስንኳ አይመልሳትም። 25 ፌዘኛ ብትገርፈው አላዋቂ ብልሃተኛ ይሆናል፤ አስተዋይን ሰው ብትገሥጸው እውቀትን ያገኛል። 26 አባቱን የሚያስከፋ እናቱንም የሚያሳድድ የሚያሳፍርና ጐስቋላ ልጅ ነው። 27 ልጅ ሆይ፥ ተግሣጽን ከሰማህ በኋላ ከእውቀት ቃል መሳሳትን ተው። 28 ወስላታ ምስክር በፍርድ ያፌዛል፥ የኀጥኣንም አፍ ክፋትን ይውጣል። 29 ለሚያፌዙ ሰዎች ፍርድ ተዘጋጅታለች፥ ለሰነፎችም ጀርባ በትር።

ምሳሌ 20

1 የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል፥ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በዚህም የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም። 2 የንጉሥ ቍጣ እንደ አንበሳ ግሣት ነው፤ የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል። 3 ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው፤ ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል። 4 ታካች ሰው በብርድ ምክንያት አያርስም፤ ስለዚህ በመከር ይለምናል፥ ምንም አያገኝም። 5 ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል። 6 ብዙ ሰዎች ቸርነታቸውን ያወራሉ፤ የታመነውን ሰው ግን ማን ያገኘዋል? 7 ጻድቅ ያለ ነውር ይሄዳል፥ ልጆቹም ከእርሱ በኋላ ምስጉኖች ናቸው። 8 በፍርድ ወንበር የተቀመጠ ንጉሥ ክፉውን ሁሉ በዓይኖቹ ይበትናል። 9 ልቤን አነጻሁ፥ ከኃጢአትም ጠራሁ የሚል ማን ነው? 10 ሁለት ዓይነት ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሳን ናቸው። 11 ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል። 12 የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥ ሁለቱን እግዚአብሔር ፈጠራቸው። 13 ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ፤ ዓይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ። 14 የሚገዛ ሰው። ክፉ ነው ክፉ ነው ይላል፤ በሄደ ጊዜ ግን ይመካል። 15 ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቍ ይገኛል፤ የእውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት። 16 ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው። 17 የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል። 18 አሳብ በምክር ትጸናለች፥ በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ። 19 ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ሰውን አትገናኘው። 20 አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ፥ በጽቅድቅ ጨለማ መብራቱ ይጠፋል። 21 በመጀመሪያ ፈጥኖ የተከማቸ ርስት ፍጻሜው አይባረክም። 22 ክፉ እመልሳለሁ አትበል፤ እግዚአብሔርን ተማመን፥ እርሱም ያድንሃል። 23 ሁለት ዓይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም። 24 የሰው አካሄዱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ እንግዲያስ ሰው መንገዱን እንዴት ያስተውላል? 25 ሰው በችኰላ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥ ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ነው። 26 ጠቢብ ንጉሥ ኀጥኣንን በመንሽ ይበትናቸዋል፥ መንኰራኵሩንም በእነርሱ ላይ ያንኰራኵርባቸዋል። 27 የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው የሆዱን ጕርጆች ሁሉ የሚመረምር። 28 ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ ዙፋኑም በቸርነት ይበረታል። 29 የጎበዛዝት ክብር ጕልበታቸው ናት፥ የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው። 30 የሰንበር ቍስል ክፉዎችን ያነጻል፤ ግርፋትም ወደ ሆድ ጕርጆች ይገባል።

ምሳሌ 21

1 የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። 2 የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል። 3 እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ቅን ነገርን ማድረግ ይወድዳል። 4 ትዕቢተኛ ዓይንና ደፋር ልብ የኀጥኣንም እርሻ ኃጢአት ነው። 5 የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፤ ችኵል ሰው ሁሉ ግን ለመጕደል ይቸኩላል። 6 በሐሰተኛ ምላስ መዝገብ ማከማቸት የሚበንን ጉም ነው፤ ይህን የሚፈልጉ ሞትን ይፈልጋሉ። 7 ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አይወድዱምና የኀጥኣን ንጥቂያ ራሳቸውን ያጠፋቸዋል። 8 የበደለኛ መንገድ የጠመመች ናት፤ የንጹሕ ሥራ ግን የቀና ነው። 9 ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በውጪ በቤት ማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል። 10 የኀጥእ ነፍስ ክፉን ትመኛለች፥ በፊቱም ባልንጀራው ሞገስን አያገኝም። 11 ፌዘኛ ቅጣትን በተቀበለ ጊዜ አላዋቂ ሰው ጥበብን ያገኛል፤ ጠቢብም ቢማር እውቀትን ይቀበላል። 12 ጻድቅ ስለ ኀጥእ ቤት ያስባል፥ ኀጥኣንም ለጥፋት እንደ ተገለበጡ። 13 የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም። 14 ስጦታ በስውር ቍጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ ጽኑ ቍጣን ታበርዳለች። 15 ፍርድን ማድረግ ለጻድቅ ደስታ ነው፤ ኃጢአትን ለሚያደርጉ ግን ጥፋት ነው። 16 ከማስተዋል መንገድ የሚሳሳት ሰው በሙታን ጉባኤ ያርፋል። 17 ተድላ የሚወድድ ድሀ ይሆናል፥ የወይን ጠጅንና ዘይትንም የሚወድድ ባለጠጋ አይሆንም። 18 ኀጥእ የጻድቅ ቤዛ ነው፤ በደለኛም የቅን ሰው ቤዛ ነው። 19 ከጠበኛና ከቍጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል። 20 የከበረ መዝገብና ዘይት በጠቢብ ሰው ቤት ይኖራል። አእምሮ የሌለው ሰው ግን ይውጠዋል። 21 ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል ሕይወትንና ጽድቅን ክብርንም ያገኛል። 22 ጠቢብ የኃያላንን ከተማ ይገባባታል፥ የሚታመኑበትንም ኃይል ያፈርሳል። 23 አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ ነፍሱን ከመከራ ይጠብቃል። 24 ኵሩና ተጓዳጅ ሰው ፌዘኛ ይባላል፤ እርሱም በትዕቢት ቍጣ ያደርጋል። 25 ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና። 26 ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። 27 የኀጥኣን መሥዋዕት አስጸያፊ ነው፤ ይልቁንም በክፉ አሳብ ሲያቀርቡት አስጸያፊ ነው። 28 ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፤ የሚሰማ ሰው ግን ተጠንቅቆ ይናገራል። 29 ኀጥእ ፊቱን ያጠነክራል፤ ቅን ሰው ግን መንገዱን ያጸናል። 30 ጥበብ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር በእግዚአብሔር ላይ የለም። 31 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ምሳሌ 22

1 መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፥ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል። 2 ባለጠና ድሀ ተገናኙ፤ እግዚአብሔር የሁላቸው ፈጣሪ ነው። 3 ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። 4 ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው። 5 እሾህና ወጥመድ በጠማማ ሰው መንገድ ናቸው፤ ነፍሱን ግን የሚጠብቅ ከእነርሱ ይርቃል። 6 ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም። 7 ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው። 8 ኃጢአትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፥ የቍጣውም በትር ይጠፋል። 9 ርኅሩህ የተባረከ ይሆናል፥ ከእንጀራው ለድሀ ሰጥቶአልና። 10 ፌዘኛን ብታወጣ ክርክር ይወጣል፥ ጠብና ስድብም ያልቃል። 11 የልብን ንጽሕና የሚወድድና ሞገስ በከንፈሩ ያለች፥ ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል። 12 የእግዚአብሔር ዓይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፤ እርሱ ግን የወስላታውን ቃል ይገለብጣል። 13 ታካች ሰው። አንበሳ በሜዳ ነው፤ በመንገዱ ላይ እሞታለሁ ይላል። 14 የጋለሞታ ሴት አፍ የጠለቀ ጕድጓድ ነው፤ እግዚአብሔር የተቈጣው በእርስዋ ይወድቃል። 15 ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል። 16 ለራሱ ጥቅም ለመጨመር ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለባለጠጋም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። 17 ጆሮህን አዘንብለህ የጠቢባንን ቃላት ስማ፥ ልብህንም ወደ እውቀቴ አድርግ፤ 18 እነርሱን በውስጥህ ብትጠብቅ፥ በከንፈሮችህም ላይ የተዘጋጁ ቢሆኑ፥ የተወደደ ነገር ይሆንልሃልና። 19 እምነትህ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ለአንተ ዛሬ እነሆ አስታወቅሁህ። 20-21 የእውነትን ቃል እርግጥነት አስታውቅህ ዘንድ፥ ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ፥ በምክርና በእውቀት የከበረን ነገር አልጻፍሁልህምን? 22 ድሀን በግድ አትበለው ድሀ ነውና፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው፤ 23 እግዚአብሔር የእነርሱን ፍርድ ይፋረድላቸዋልና፥ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና። 24 ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋት አትሂድ፥ 25 መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። 26 እጃቸውን አጋና እንደሚማቱ፥ ለባለ ዕዳዎች እንደሚዋሱ አትሁን፤ 27 የምትከፍለው ባይኖርህ፥ ምንጣፍህን ከበታችህ ስለ ምን ይወስዳል? 28 አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ። 29 በሥራው የቀጠፈ ሰውን አይተሃልን? በነገሥታት ፊት ይቆማል፤ በተዋረዱም ሰዎች ፊት አይቆምም።

ምሳሌ 23

1 ከመኰንን ጋር ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥ በፊትህ ያለውን በደኅና አስተውል፤ 2 ሰውነትህም ቢሳሳ፥ በጕሮሮህ ላይ ካራ አድርግ። 3 ጣፋጩ መብል አይመርህ የሐሰት እንጀራ ነውና። 4 ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። 5 በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና። 6 የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ 7 በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። 8 የበላኸውን መብል ትተፋዋለህ፥ ያማረውንም ቃልህን ታጠፋዋለህ። 9 በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥ የቃልህን ጥበብ ያፌዝብሃልና። 10 የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤ ወደ ድሀ አደጎች እርሻ አትግባ፤ 11 ታዳጊአቸው ጽኑ ነውና፥ እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና። 12 ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥ ጆሮህንም ወደ እውቀት ቃል። 13 ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል፥ በበትር ብትመታው አይሞትምና። 14 በበትር ትመታዋለህ፥ ነፍሱንም ትታደጋለህ። 15 ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ቢሆን ልቤ ደግሞ ደስ ይለዋል፤ 16 ከንፈሮችህም በቅን ቢናገሩ ኵላሊቶቼ ደስ ይላቸዋል። 17 ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤ 18 በእውነት ፍጻሜ አለህና፥ ተስፋህም አይጠፋምና። 19 ልጄ ሆይ፥ ስማ ጠቢብም ሁን ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ። 20 የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤ 21 ሰካርና ሆዳም ይደኸያሉና፥ የእንቅልፍም ብዛት የተቦጫጨቀ ጨርቅ ያስለብሳልና። 22 የወለደህን አባትህን ስማ፥ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት። 23 እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም። 24 የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፥ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። 25 አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፥ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት። 26 ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ፤ 27 ጋለሞታ ሴት የጠለቀች ዐዘቅት ናትና፥ ሌላይቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናትና። 28 እንደ ሌባ ታደባለች ወስላቶችንም በሰው ልጆች መካከል ታበዛለች። 29 ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? 30 የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? 31 ወደ ወይን ጠጅ አትመልከት በቀላ ጊዜ፥ መልኩም በብርሌ ባንጸባረቀ ጊዜ፥ እየጣፈጠም በገባ ጊዜ። 32 በኋላ እንደ እባብ ይነድፋል፥ እንደ እፉኝትም መርዙን ያፈስሳል። 33 ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። 34 በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ፥ በደቀልም ላይ እንደ ተኛ። 35 መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤ ጐሰሙኝ፥ አላወቅሁምም። መቼ እነሣለሁ? ደግሞ ጨምሬ እሻታለሁ ትላለህ።

ምሳሌ 24

1 ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትውደድ፤ 2 ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ሽንገላን ትናገራለችና። 3 ቤት በጥበብ ይሠራል፥ በማስተዋልም ይጸናል። 4 በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ። 5 ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥ አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል። 6 በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው። 7 ጥበብ ለሰነፍ ከፍ ብላ የራቀች ናት፤ በበርም አፉን አይከፍትም። 8 ክፉ ለማድረግ የሚያስብ ተንኰለኛ ይባላል። 9 የስንፍና ሐሳብ ኃጢአት ነው፤ ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል። 10 በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። 11 ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። 12 እነሆ፥ ይህን አላወቀውም ብትል፥ ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን? ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን? 13 ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፤ ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው። 14 ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፤ ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥ ተስፋህም አይጠፋም። 15 እንደ ኀጥእ በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፤ ማደሪያውንም አታውክ። 16 ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል፤ ኀጥኣን ግን በክፉ ላይ ይወድቃሉ። 17 ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥ 18 እግዚአብሔር ያንን አይቶ በዓይኑ ክፉ እንዳይሆን፥ ቍጣውንም ከእርሱ እንዳይመልስ። 19 ስለ ኃጢአተኞች አትቈጣ፥ በክፉዎችም አትቅና። 20 ለኃጢአተኛ የፍጻሜ ተስፋ የለውምና፥ የኅጥኣንም መብራት ይጠፋልና። 21 ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔርንና ንጉሥን ፍራ፥ ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ። 22 መከራቸው ድንገት ይነሣልና፤ ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል? ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፤ የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፤ ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም። የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፤ ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም። ሰይፍ መዓቱ ብትሳል ግን ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፤ ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች። 23 እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው። በፍርድ ታደላ ዘንድ መልካም አይደለም። 24 ኀጥኡን። ጻድቅ ነህ የሚለውን ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፤ 25 የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥ በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች። 26 በቀና ነገር የሚመልስ ከንፈርን ይስማል። 27 በስተ ሜዳ ሥራህን አሰናዳ፥ ስለ አንተ በእርሻ አዘጋጃት፤ ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ። 28 በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥ በከንፈርህም አታባብለው። 29 እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥ እንደ ሥራውም እመልስበታለሁ አትበል። 30 በታካች ሰው እርሻ፥ አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ። 31 እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥ ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥ የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል። 32 ተመለከትሁና አሰብሁ፤ አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ። 33 ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ 34 እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል። [በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል]

ምሳሌ 25

1 እነዚህም ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዱአቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው። 2 የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው። 3 እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም። 4 ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል። 5 ከንጉሥ ፊት ኀጥኣንን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች። 6 በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላልቆችም ስፍራ አትቁም፤ 7 ዓይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ። ወደዚህ ከፍ በል ብትባል ይሻልሃልና። 8 ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለክርክር ፈጥነህ አትውጣ፤ 9 ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥ 10 የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ አንተንም ከማነወር ዝም እንዳይል። 11 የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው። 12 የምትሰማን ጆሮ የሚዘልፍ ጠቢብ ሰው እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቍ እንዲሁ ነው። 13 በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤ የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና። 14 ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደማይከተለው ደመና ነፋስም ነው። 15 በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል። 16 አጥብቀህ እንዳትጠግብ እንዳትተፋውም ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ። 17 እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር። 18 በባልንጀራው በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው። 19 ወስላታውን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው። 20 ለሚያዝን ልብ ዝማሬ የሚዘምር፥ ለብርድ ቀን መጐናጸፊያውን እንደሚያስወግድ በቍስልም ላይ እንደ መጻጻ እንዲሁ ነው። 21 ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፤ 22 ፍም በራሱ ላይ ትሰበስባለህና፥ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይመልስልሃልና። 23 የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል። 24 ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል። 25 የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ነፍስ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምስራች እንዲሁ ነው። 26 በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ፈሳሽና እንደ ረከሰ ምንጭ ነው። 27 ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈላለግ አያስከብርም። 28 ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።

ምሳሌ 26

1 በረዶ በበጋ ዝናብም በመከር እንዳይገባ፥ እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም። 2 እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም። 3 አለንጋ ለፈረስ፥ ልጓም ለአህያ፥ በትርም ለሰነፍ ጀርባ ነው። 4 አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት። 5 ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት። 6 በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ እግሮቹን ይቈርጣል ግፍንም ይጠጣል። 7 እንደሚንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች፥ እንዲሁም ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው። 8 ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው። 9 እሾህ በስካር እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁ ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው። 10 ዋና ሠራተኛ ሁሉን ነገር ይሠራል፤ ሰነፍን የሚቀጥር ግን መንገድ አላፊውን እንደሚቀጥር ነው። 11 ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ስንፍናውን የሚደግም ሰው እንዲሁ ነው። 12 ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኽውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። 13 ታካች ሰው። አንበሳ በመንገድ አለ፤ አንበሳ በጎዳና አለ ይላል። 14 ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል። 15 ታካች ሰው እጁን ወደ ወጭት ያጠልቃል፤ ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው። 16 ታካች ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል። 17 አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ ውሻን በጅራቱ እንደሚይዝ ነው። 18 ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥ 19 ባልንጀራውን የሚያታልል። በጨዋታ አደረግሁት የሚል ሰውም እንዲሁ ነው። 20 እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፤ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል። 21 ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቍጡ ሰው ጠብን ያበዛል። 22 የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል። 23 ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቅ ነው። 24 ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል። 25 በልቡ ሰባት ርኵሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው። 26 ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል። 27 ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል። 28 ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፤ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል።

ምሳሌ 27

1 ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። 2 ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም። 3 ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቍጣ ይከብዳል። 4 ቍጣ ምሕረት የሌለው ነው፥ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል? 5 የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። 6 የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው። 7 የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል። 8 ስፍራውን የሚተው ሰው፤ ቤቱን ትቶ እንደሚበርር ወፍ ነው። 9 ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል። 10 ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። 11 ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ። 12 ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ። 13 ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው። 14 ባልንጀራውን በታላቅ ቃል ማለዳ የሚባርክ ሰው እንደሚራገም ያህል ነው። 15 በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፤ 16 እርስዋንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው። 17 ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። 18 በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል። 19 ፊት በውኃ ላይ ለፊት እንደሚታይ፥ እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል። 20 ሲኦልና ጥፋት እንዳይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዓይን አይጠግብም። 21 ብር በከውር ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፤ ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል። 22 ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም። 23 የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፤ 24 ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፥ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና። 25 ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥ ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ፥ 26 በጎች ለልብስህ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ። 27 ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።

ምሳሌ 28

1 ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል። 2 ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ፤ በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል። 3 ድሆችን የሚያስጨንቅ ምስኪን ሰው እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው። 4 ሕግን የሚተዉ ሰዎች ኀጥኣንን ያመሰግናሉ፤ ሕግ ጠባቂዎች ግን ይጠሉአቸዋል። 5 ክፉዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ። 6 በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል። 7 ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል። 8 በአራጣ ብዛትና በቅሚያ ሀብቱን የሚያበዛ ለድሀ ለሚራራ ያከማችለታል። 9 ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት። 10 ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥ እርሱ ወደ ጕድጓዱ ይወድቃል፤ ፍጹማን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ። 11 ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ ድሀ ግን ይመረምረዋል። 12 ጻድቃን ድል ባደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ፤ ኀጥኣን ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ ግን ሰው ይሸሸጋል። 13 ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። 14 ሁልጊዜ የሚፈራ ሰው ምስጉን ነው፤ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል። 15 በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መኰንን እንደሚያገሣ አንበሳን እንደ ተራበ ድብ ነው። 16 አእምሮ የጐደለው መኰንን ትልቅ ግፈኛ ነው፤ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል። 17 የሰው ደም ያለበት ሰው እንደ ጕድጓድ ይሸሻል፥ ማንም አያስጠጋውም። 18 በቅንነት የሚሄድ ይድናል፤ በጠማምነት የሚሄድ ግን ወዲያው ይወድቃል። 19 ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል። 20 የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። 21 ማድላት፥ በቍራሽ እንጀራም መበደል መልካም አይደለም። 22 ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኵላል ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም። 23 ምላሱን ከሚያጣፍጥ ይልቅ ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል። 24 ከአባቱና ከእናቱ የሚሰርቅ። ኃጢአትን አልሠራሁም የሚልም የአጥፊ ባልንጀራ ነው። 25 የሚጐመጅ ሰው ክርክርን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይጠግባል። 26 በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል። 27 ለድሀ የሚሰጥ አያጣም፤ ዓይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል። 28 ኀጥአን በተነሡ ጊዜ ሰዎች ይሸሸጋሉ፤ እነርሱ በጠፉ ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።

ምሳሌ 29

1 ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም። 2 ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል፤ ኀጥኣን በሠለጠኑ ጊዜ ግን ሕዝብ ያለቅሳል። 3 ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤ ጋለሞቶችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያጠፋል። 4 ንጉሥ በፍርድ አገሩን ያጸናል፤ መማለጃ የሚወድድ ግን ያፈርሰዋል። 5 ወዳጁን በለዘበ ቃል የሚናገር ሰው ለእግሩ መርበብን ይዘረጋል። 6 በክፉ ሰው ዓመፃ ወጥመድ ይገኛል፤ ጻድቅ ግን ደስ ይለዋል፥ እልልም ይላል። 7 ጻድቅ የድሆችን ፍርድ ይመለከታል፤ ኀጥእ ግን እውቀትን አያስተውልም። 8 ፌዘኞች ከተማቸውን ያቃጥላሉ፤ ጠቢባን ግን ቍጣን ይመልሳሉ። 9 ጠቢብ ከሰነፍ ጋር ቢጣላ፥ ሰነፍ ወይም ይቈጣል ወይም ይስቃል፥ ዕረፍትም የለም። 10 ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ ደግሞም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ። 11 ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል። 12 መኰንን ሐሰተኛ ነገርን ቢያደምጥ፥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፅኞች ይሆናሉ። 13 ድሀና ግፈኛ ተገናኙ፤ እግዚአብሔር የሁለቱንም ዓይን ያበራል። 14 ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥ ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል። 15 በትርና ተግሣጽ ጥበብን ይሰጣሉ፤ ያልተቀጣ ብላቴና ግን እናቱን ያሳፍራል። 16 ኀጥኣን ሲበዙ ኃጢአት ትበዛለች፤ ጻድቃን ግን ውደቀታቸውን ያያሉ። 17 ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል። 18 ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው። 19 ባሪያ በቃል አይገሠጽም፤ ቢያስተውል እንኳ አይመልስምና። 20 በቃሉ የሚቸኵለውን ሰው ብታይ፥ ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው። 21 ባሪያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል። 22 ቍጡ ሰው ክርክርን ያነሣሣል። ወፈፍተኛ ሰውም ኃጢአትን ያበዛል። 23 ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ መንፈሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል። 24 ከሌባ ጋር የሚካፈል ነፍሱን ይጠላል፤ መርገምን ይሰማል፥ ነገር ግን ምንም አይገልጥም። 25 ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። 26 ብዙ ሰዎች የሹምን ፊት ይሻሉ፤ የሰው ፍርድ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 27 ኃጢአተኛ በጻድቃን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ በቀና መንገድ የሚሄደውም በኀጥኣን ዘንድ አስጸያፊ ነው።

ምሳሌ 30

1 የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል። 2 እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኛም። 3 ጥበብንም አልተማርሁም፥ ቅዱሱንም አላወቅሁትም። 4 ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው? 5 የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው። 6 እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር። 7 ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፤ 8 ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ 9 እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል። 10 እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን ባሪያን በጌታው ፊት አትማ። 11 አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። 12 ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ። 13 ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ። 14 ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ። 15 አልቅት። ስጠን ስጠን የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት። ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም። በቃን የማይሉ ናቸው፤ 16 እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን ውኃ የማትጠግብ ምድርና። በቃኝ የማትል እሳት ናቸው። 17 በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል። 18 ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም። 19 እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው። 20 እንዲሁ በልታ አፍዋን የምታብስ። አንዳች ክፉ ነገር አላደረግሁም የምትልም የአመንዝራ ሴት መንገድ ናት። 21 በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም። 22 ባሪያ በነገሠ ጊዜ ሰነፍም እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥ 23 የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት ባሪያም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ። 24 በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤ 25 ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸዋን ይሰበስባሉ። 26 ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ። 27 አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸው ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ። 28 እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል። 29 መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፤ 30 የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ የማይመለስ፥ እንስሳንም የማይፈራ፤ 31 በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፤ መንጋን የምመራ አውራ ፍየል፤ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ። 32 ከፍ ከፍ ስትል ስንፍናን ያደረግህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደ ሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን። 33 ወተት መግፋት ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣ፤ እንዲሁም ቍጣን መጐተት ጠብን ያወጣል።

ምሳሌ 31

1 እናቱ እርሱን ያስተማረችበት የማሣ ንጉሥ የልሙኤል ቃል። 2 ልጄ ሆይ፥ ምንድር ነው? የሆዴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው? የስእለቴ ልጅ ሆይ፥ ምንድር ነው? 3 ጕልበትህን ለሴቶች አትስጥ፥ መንገድህንም ነገሥታትን ለሚያጠፉ። 4 ለነገሥታት አይገባም፥ ልሙኤል ሆይ፥ ነገሥታት የወይን ጠጅ ይጠጡ ዘንድ አይገባም። መሳፍንትም። ብርቱ መጠጥ ወዴት ነው? ይሉ ዘንድ፤ 5 እንዳይጠጡና ሕግን እንዳይረሱ፥ የድሀ ልጆችንም ፍርድ እንዳያጐድሉ። 6 ለጥፋት ለቀረበው ሰው ብርቱ መጠጥ ስጡት፥ ነፍሱ ለመረረውም የወይን ጠጅ ስጡት፤ 7 ይጠጣ ድህነቱንም ይርሳ፥ ጕስቍልናውንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብ። 8 አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ። 9 አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ። 10 ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል። 11 የባልዋ ልብ ይታመንባታል። ምርኮም አይጐድልበትም። 12 ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም። 13 የበግ ጠጕርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። 14 እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። 15 ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች። 16 እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፤ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። 17 ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች። 18 ንግድዋ መልካም እንደ ሆነ ትመለከታለች፤ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። 19 እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። 20 እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። 21 ለቤትዋ ሰዎች ከበረዶ ብርድ የተነሣ አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና። 22 ለራስዋም ግብረ መርፌ ስጋጃ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች። 23 ባልዋ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። 24 የበፍታ ቀሚስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። 25 ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች። 26 አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። 27 የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። 28 ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል። 29 መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። 30 ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። 31 ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፥ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።

መክብብ 1

1 በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። 2 ሰባኪው። ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። 3 ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድር ነው? 4 ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ነው። 5 ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኵላለች። 6 ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፤ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል። 7 ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ። 8 ነገር ሁሉ ያደክማል ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፤ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። 9 የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። 10 ማንም። እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል። 11 ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ከኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። 12 እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ። 13 ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፤ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት። 14 ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 15 ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፤ ጐደሎም ይቈጠር ዘንድ አይችልም። 16 እኔ በልቤ። እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፤ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ። 17 ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፤ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደ መከተል እንደ ሆነ አስተዋልሁ። 18 በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፤ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።

መክብብ 2

1 እኔ በልቤ። ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ አልሁ፤ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። 2 ሳቅን። ዕብድ ነህ፤ ደስታንም። ምን ታደርጋለህ? አልሁት። 3 የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። 4 ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፤ 5 አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፤ 6 በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ። 7 ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባሪያዎችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። 8 ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፤ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። 9 ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፤ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች። 10 ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። 11 እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። 12 እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? 13 እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ። 14 የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። 15 እኔም በልቤ። ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ። ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። 16 በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል! 17 ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 18 ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። 19 ጠቢብ ወይም ሰነፍ እንዲሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ጌታ ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 20 እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። 21 ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። 22 ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? 23 ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፥ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 24 ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። 25 ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው? 26 እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

መክብብ 3

1 ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። 2 ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ 3 ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ 4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ 5 ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ 6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ 7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ 8 ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9 ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው? 10 እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። 11 ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። 12 ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። 13 ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14 እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። 15 አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል። 16 ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ኃጢአት፥ በጽድቅም ስፍራ ኃጢአት እንዳለ አየሁ። 17 እኔም በልቤ። በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ። 18 እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች። እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ። 19 የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። 20 ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። 21 የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22 ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው?

መክብብ 4

1 እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። 2 እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፤ 3 ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል። 4 ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 5 ሰነፍ እጆቹን ኮርትሞ ይቀመጣል፤ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። 6 በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል። 7 እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱን ነገር አየሁ። 8 አንድ ሰው ብቻውን አለ፥ ሁለተኛም የለውም ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም፥ ዓይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም። ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው። 9 ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። 10 ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፤ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። 11 ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? 12 አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም። 13 ድሀና ጠቢብ ብላቴና ተግሣጽን መቀበል ከእንግዲህ ወዲህ ከማያውቅ ከሰነፍ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። 14 ምንም በመንግሥቱ አገር ደግሞ ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከግዞቱ ቤት ወደ መንግሥት ወጥቶአልና። 15 ከፀሐይ በታች የሚሄዱትን ሕያዋን ሁሉ በእርሱ ፋንታ ከሚነሣው ከሌላው ጎበዝ ጋር ሆነው አየሁ። 16 ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ አይቈጠሩም፤ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

መክብብ 5

1 ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። 2 እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። 3 ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፤ እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። 4 ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ የተሳልኸውን ፈጽመው። 5 ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። 6 ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፥ በመልአክም ፊት። ስሕተት ነበረ አትበል፤ እግዚአብሔር በቃልህ ይቈጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ያጠፋ ዘንድ ስለምን ትሻለህ? 7 ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ፥ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ። 8 ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ። 9 በጠቅላላው ግን የአገሩ ጥቅም እርሻን የሚወድድ ንጉሥ ቢኖር ነው። 10 ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 11 ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 12 እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል። 13 ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። 14 ያችም ባለጠግነት በክፉ ነገር ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። 15 ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም። 16 ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፤ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድር ነው? 17 ዘመኑን ሁሉ በጨለማ በኀዘን በብስጭት በደዌና በቍጣ ነው። 18 እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና። 19 እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20 እግዚአብሔር በልቡ ደስታን ስለ ሰጠው እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግ አያስብም።

መክብብ 6

1 ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው። 2 እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። 3 ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነፍሱም መልካምን ባትጠግብ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ። ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። 4 በከንቱ መጥቶአል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፤ 5 ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፤ ለዚህም ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። 6 ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? 7 የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። 8 ከሰነፍ ይልቅ ለጥበበኛ ጥቅም ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድ ለሚያውቅ ለድሀ ጥቅሙ ምንድር ነው? 9 በዓይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 10 የሆነው ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፤ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም። 11 ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? 12 ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?

መክብብ 7

1 ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። 2 ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። 3 ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። 4 የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። 5 ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። 6 ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 7 ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፤ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። 8 የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፤ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። 9 በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና። 10 ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። 11 ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፤ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። 12 የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው። 13 የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? 14 በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል። 15 ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። 16 እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ። 17 እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት። 18 እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው። 19 በከተማ ከሚኖሩ ከአሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። 20 በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። 21 ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፤ 22 አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና። 23 ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፤ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች። 24 የሆነው ራቀ እጅግም ጠለቀ፤ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? 25 አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ ኃጢአትም ስንፍና፥ ስንፍናም እብደት እንደ ሆነች አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። 26 እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መርበብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፤ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርስዋ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። 27 አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፤ 28 ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፤ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። 29 እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፤ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።

መክብብ 8

1 እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድፍረት ትለውጣለች። 2 እኔ። በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። 3 የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ትወገድ ዘንድ አትቸኵል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። 4 የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፤ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል? 5 ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፤ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። 6 የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። 7 የሚሆነውንም አያውቅም፤ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? 8 መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፤ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም። 9 ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፤ ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። 10 እንዲሁም ኀጥኣን ተቀብረው አየሁ፥ ወደ ዕረፍትም ገቡ፤ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 11 በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ። 12 ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤ 13 ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም። 14 በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፤ በኀጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኀጥኣን አሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። 15 ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። 16 ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፤ 17 ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፤ ደግሞ ጠቢብ ሰው። ይህን አወቅሁ ቢል እርሱ ያኘው ዘንድ አይችልም።

መክብብ 9

1 ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፤ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። 2 የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ እንደ መልካሙ ሰው እንዲሁ ኃጢአተኛው፥ እንደ መሐለኛው ሰው እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ነው። 3 አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፤ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። 4 ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። 5 ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። 6 ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። 7 እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። 8 ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። 9 በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። 10 አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። 11 እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። 12 ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ። 13 ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርስዋም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። 14 ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፤ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። 15 ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፤ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። 16 እኔም። ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፤ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ። 17 በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። 18 ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል።

መክብብ 10

1 የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል። 2 የጠቢብ ልብ በስተ ቀኙ ነው፥ የሰነፍ ልብ ግን በስተ ግራው ነው። 3 ደግሞም ሰነፍ በመንገድ ሲመላለስ እርሱ ልብ ይጐድለዋል፥ የሚያስበውም ሁሉ ስንፍና ነው። 4 ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። 5 ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስሕተት ነው፤ 6 ሰነፍ በታላቅ ማዕርግ ተሾመ፥ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ። 7 ባሪያዎች በፈረስ ላይ ሲቀመጡ መሳፍንትም እንደ ባሪያዎች በምድር ላይ ሲሄዱ አየሁ። 8 ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፥ ቅጥርንም የሚያፈርስን እባብ ትነድፈዋለች። 9 ድንጋይን የሚፈነቅል ይታመምበታል፥ እንጨትንም የሚፈልጥ ይጐዳበታል። 10 ብረት ቢደነዝዝ ሰውም ባይስለው ኃይልን ሊያበዛ ይገባዋል፤ ጥበብ ግን ሥራውን ለማከናወን ትጠቅመዋለች። 11 ደጋሚ ሳይደግምባት እባብ ብትነድፍ ለደጋሚው ትርፍ የለውም። 12 የጠቢብ ሰው የአፉ ቃል ሞገስ ናት፤ የሰነፍ ከንፈሮች ግን ራሱን ይውጡታል። 13 የአፉ ቃል መጀመሪያ ስንፍና ነው፥ የንግግሩ ፍጻሜም ክፉ እብደት ነው። 14 ሰነፍ ቃሉን ያበዛል፤ ሰው ግን የሚሆነውን አያውቅም፤ ከእርሱስ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል? 15 የሰነፍ ሥራ ያደክመዋል ወደ ከተማ መሄድ አያውቅምና። 16 ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ! 17 ንጉሥሽ የከበረ ልጅ የሆነ፥ ለብርታት እንጂ ለስካር ያይደለ በጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ የተመሰገንሽ ነሽ። 18 ተግባር በመፍታት ጣራው ይዘብጣል፥ በእጅም መታከት ቤት ያፈስሳል። 19 እንጀራን ለሳቅ የወይን ጠጅንም ለሕይወት ደስታ ያደርጉታል፥ ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል። 20 የሰማይ ወፍ ቃሉን ይወስደዋልና፥ ባለ ክንፎችም ነገሩን ይናገራሉና በልብህ አሳብ እንኳ ቢሆን ንጉሥን አትስደብ፥ በመኝታ ቤትህም ባለጠጋን አትስደብ።

መክብብ 11

1 እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፥ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኛዋለህና። 2 ለሰባት ደግሞም ለስምንት እድል ፈንታን ክፈል፥ በምድር ላይ የሚሆነውን ክፉ ነገር ምን እንደሆነ አታውቅምና። 3 ደመናት ዝናብ በሞሉ ጊዜ በምድር ላይ ያፈስሱታል፤ ዛፍም ወደ ደቡብ ወይም ወደ ሰሜን ቢወድቅ፥ ዛፉ በወደቀበት ስፍራ በዚያ ይኖራል። 4 ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም። 5 የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፥ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም። 6 ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፥ በማታም እጅህን አትተው። 7 ብርሃን ጣፋጭ ነው ፀሐይንም ማየት ለዓይን መልካም ነው። 8 ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ይበለው፤ ሆኖም የጨለማውን ዘመን ያስብ፥ ብዙ ቀን ይሆናልና። የሚመጣው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው። 9 አንተ ጐበዝ፥ በጕብዝናህ ደስ ይበልህ፥ በጕብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፥ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፤ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ። 10 ሕፃንነትና ጕብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፥ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ።

መክብብ 12

1 የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ፤ 2 ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፤ 3 ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፤ 4 የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፤ 5 ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፤ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፈቃድም ሲጠፋ፤ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፤ 6 የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ 7 አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። 8 ሰባኪው። ከንቱ፥ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። 9 ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፤ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። 10 ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ። 11 የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፥ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። 12 ከዚህም ሁሉ በላይ፥ ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ስማ፤ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፥ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል። 13 የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። 14 እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።

መኃልየ መኃልይ 1

1 ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። 2 በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና። 3 ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። 4 ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ ቤቱ አገባኝ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፤ በቅንነት ይወድዱሃል። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። 6 ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና፤ ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም። 7 ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቅትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ? 8 አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። 9 ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ። 10 የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው። 11 ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን። 12 ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። 13 ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። 14 ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው። 15 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው። 16 ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው። 17 የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።

መኃልየ መኃልይ 2

1 እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ። 2 በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት። 3 በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በልጆች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም በጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው። 4 ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። 5 በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና። 6 ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች። 7 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ። 8 እነሆ፥ የውዴ ቃል! በተራሮች ላይ ሲዘልል፥ በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። 9 ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፤ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። 10 ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ። 11 እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። 12 አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ። 13 በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ። 14 በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ፥ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና መልክሽን አሳዪኝ፥ ድምፅሽንም አሰሚኝ። 15 ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን። 16 ውዴ የእኔ ነው፥ እኔም የእርሱ ነኝ፤ በሱፍ አበባዎች መካከልም መንጋውን ያሰማራል። 17 ውዴ ሆይ፥ ቀኑ እስኪነፍስ፥ ጥላውም እስኪሸሽ ድረስ ተመለስ፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋውን ወይም የዋላውን እምቦሳ ምሰል።

መኃልየ መኃልይ 3

1 ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም። 2 እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም። 3 ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም። 4 ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም ወደ እናቴም ቤት ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሡትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ። 6 መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት? 7 እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፤ ከእስራኤል ኃያላን ስድሳ ኃያላን በዙሪያው ናቸው። 8 ሁሉም ሰይፍ የያዙ ሰልፈኞች ናቸው፤ በሌሊት ከሚወድቀው ፍርሃት የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ። 9 ንጉሡ ሰሎሞን መሸከሚያን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ። 10 ምሰሶቹን የብር፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው። 11 እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት፥ ውጡ፤ እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ።

መኃልየ መኃልይ 4

1 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው። 2 ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው። 3 ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ አፍሽም ያማረ ነው፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። 4 አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል። 5 ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው። 6 ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ። 7 ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም። 8 ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች። 9 እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ልቤን በደስታ አሳበድሽው፤ አንድ ጊዜ በዓይኖችሽ፥ ከአንገትሽ ድሪ በአንዱ ልቤን በደስታ አሳበድሽው። 10 እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ! 11 ሙሽራዬ ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠበጠባል፤ ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው። 12 እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት። 13 ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥ 14 ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋ፥ ከልዩ ልዩ ዕጣን ጋር፥ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ሁሉ ጋር። 15 አንቺ የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጕድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ። 16 የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፤ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱውም ይፍሰስ፤ ውዴ ወደ ገነቱ ይግባ፥ መልካሙንም ፍሬ ይብላ።

መኃልየ መኃልይ 5

1 እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥ ከርቤዬን ከሽቱዬ ጋር ለቀምሁ፥ እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥ የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ። ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ጠጪ፤ እስክትረኪ ድረስ ጠጪ። 2 እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ። 3 ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ? 4 ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ። 5 ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፤ እጆቼ በደጅ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠበጠቡ። 6 ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፤ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም። 7 ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት። 8 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አምላችኋለሁ፤ ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት። 9 አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? ይህን የሚያህል አምለሽናልና ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? 10 ውዴ ነጭና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው። 11 ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፤ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራ ጥቁረትም ጥቁር ነው። 12 ዓይኖቹ በሙሉ ፈሳሽ አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው። 13 ጕንጩና ጕንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፤ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ። 14 እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ እንዳለበት እንደ ወርቅ ቀለበት ናቸው፤ አካሉ ብልሃተኛ እንደ ሠራው በሰንፔር እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው። 15 እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ መልካም ነው። 16 አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።

መኃልየ መኃልይ 6

1 አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከአንቺ ጋር እንፈልገው ዘንድ ውድሽ ወዴት ሄደ? ውድሽስ ወዴት ፈቀቅ አለ? 2 ውዴ በገነቱ መንጋውን ያሰማራ ዘንድ አበባውንም ይሰበስብ ዘንድ ወደ ሽቱ መደብ ወደ ገነቱ ወረደ። 3 እኔ የወዴ ነኝ ውዴም የእኔ ነው፤ በሱፉ አበባ መካከል መንጋውን ያሰማራል። 4 ወዳጄ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ውብ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌምም ያማርሽ ነሽ፤ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ። 5 አውከውኛልና ዓይኖችሽን ከፊቴ መልሺ፤ ጠጕርሽ ከገለዓድ እንደ ወረደ እንደ ፍየል መንጋ ነው። 6 ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ወጡ ሁሉ መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው። 7 በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው። 8 ስድሳ ንግሥታት ሰማንያም ቍባቶች ቍጥር የሌላቸውም ቈነጃጅት አሉ። 9 ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት። 10 ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት? 11 የወንዙን ዳር ልምላሜ አይ ዘንድ፥ ወይኑ አብቦ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እመለከት ዘንድ ወደ ገውዝ ገነት ወረድሁ። 12 ሳላውቅ ነፍሴ በከበረው ሰረገላ ላይ አስቀመጠችኝ።

መኃልየ መኃልይ 7

1 አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት። 2 አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥ እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ። 3 እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። 4 ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው። 5 አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። 6 ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፤ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፤ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል። 7 ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! 8 ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ። 9 ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። 10 ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። 11 እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። 12 ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። 13 ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ። [14]፤ ትርንጎዎች መዓዛን ሰጡ፤ መልካሞች ፍሬዎች ሁሉ፥ አሮጌው ከአዲሱ ጋር፥ በደጃችን አሉ፤ ውዴ ሆይ፥ ሁሉን ለአንተ ጠበቅሁልህ።

መኃልየ መኃልይ 8

1 አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ እንደ ወንድሜ ምነው በሆንህ! በሜዳ ባገኘሁህ ጊዜ በሳምሁህ፥ ማንም ባልናቀኝም ነበር። 2 መርቼ ወደ እናቴ ቤት ባገባሁህ፥ በዚያም አንተ ባስተማርከኝ፤ እኔም ከመልካሙ ወይን ጠጅ ከሮማኔም ውኃ ባጠጣሁህ ነበር። 3 ግራው ከራሴ በታች በሆነች ቀኙም ባቀፈችኝ ነበር። 4 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት እንዳታነሣሡትም አምላችኋለሁ። 5 በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ በታች አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ወለደችህ፥ በዚያም ወላጅ እናትህ አማጠችህ። 6 እንደ ማኅተም በልብህ፥ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና፥ ቅንዓትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና። ፍንጣሪዋ እንደ እሳት ፍንጣሪ፥ እንደ እግዚአብሔር ነበልባል ነው። 7 ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም፥ ፈሳሾችም አያሰጥሙአትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይንቁታል። 8 እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እኅት አለችን፤ ስለ እርስዋ በሚናገሩባት ቀን ለእኅታችን ምን እናድርግላት? 9 እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፤ ደጅም ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከብባታለን። 10 እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ። 11 ለሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ቦታ ለጠባቂዎች አከራየው፤ ሰው ሁሉ ለፍሬው ሺህ ብር ያመጣለት ነበር። 12 ለእኔ ያለኝ የወይን ቦታ በፊቴ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፥ ሺሁ ለአንተ፥ ሁለት መቶውም ፍሬውን ለሚጠብቁ ይሆናል። 13 በገነቱ የምትቀመጪ ሆይ፥ ባልንጀሮች የአንቺን ቃል ያደምጣሉ፤ ቃልሽን አሰሚኝ። 14 ውዴ ሆይ፥ ፍጠን፤ በቅመም ተራራ ላይ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ምሰል።

ኢሳይያስ 1

1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ። 2 እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ። 3 በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም። 4 ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል። 5 ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል። 6 ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም። 7 ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች። 8 የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች። 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር። 10 እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ። 11 የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። 12 በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? 13 ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። 14 መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። 15 እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። 16 ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥ 17 መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። 18 ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። 19 እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ 20 እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 21 ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት። 22 ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ። 23 አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም። 24 ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ። 25 እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤ 26 ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። 27 ጽዮን በፍርድ ከእርሷም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ። 28 በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፥ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ። 29 በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፥ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና፤ 30 ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፥ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና። 31 ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፥ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።

ኢሳይያስ 2

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል። 2 በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። 3 ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ። 4 በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም። 5 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ። 6 ሕዝብህን የያዕቆብን ቤት ትተሃልና፤ ይኸውም የምሥራቅን ሰዎች አመል ስለ ተሞሉ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያንም ምዋርተኞች ስለ ሆኑ፥ ከባዕድ ልጆችም ጋር ስለ ተባበሩ ነው። 7 ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፥ ለመዛግብቶቻቸውም ፍጻሜ የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፥ ለሠረገሎቻቸውም ፍጻሜ የለውም። 8 ምድራቸው ደግሞ በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸውም ላደረጉት ለእጃቸው ሥራ ይሰግዳሉ። 9 ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፥ ጨዋውም ተዋርዶአል፤ ኃጢአታቸውንም ይቅር አትበላቸው። 10 ከእግዚአብሔር ማስደንገጥና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግባ፥ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ። 11 ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፥ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። 12 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል፤ 13 ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለው በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥ 14 በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ 15 በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥ 16 በተርሴስም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በሚያማምሩ ጣዖታትም ሁሉ ላይ ይሆናል። 17 ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፥ የሰውም ኵራት ይወድቃል፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል። 18 ጣዖቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው ይጠፋሉ። 19 እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ሰዎች ከማስደንገጡና ከግርማው ክብሩ የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ይገባሉ። 20 በዚያን ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል። 21 እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ። 22 እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?

ኢሳይያስ 3

1 እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ፥ 2 ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥ 3 ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውንም፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል። 4 አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል። 5 ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል። 6 ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ። አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥ 7 በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ። እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፤ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል። 8 የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ። 9 የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ! 10 የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን። መልካም ይሆንልሃል በሉት። 11 እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል። 12 ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ። 13 እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል። 14 እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፤ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤ 15 ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 16 ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ። የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና 17 ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋቸውን ይገልጣል። 18 በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ የጆሮ እንጥልጥሉንም፥ 19 አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥ 20 ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥ 21 አሸንክታቡንም፥ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥ 22 የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥ 23 መስተዋቱንም፥ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል። 24 እንዲህም ይሆናል፤ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል። 25 ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ። 26 በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።

ኢሳይያስ 4

1 በዚያም ቀን ሰባት ሴቶች። የገዛ እንጀራችንን እንበላለን የገዛ ልብሳችንንም እንለብሳለን፤ ስምህ ብቻ በእኛ ላይ ይጠራ፥ መሰደባችንንም አርቅ ብለው አንዱን ወንድ ይይዙታል። 2 በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጥቋጥ ለጌጥና ለክብር ይሆናል፥ ከእስራኤልም ወገን ላመለጡ ሰዎች የምድሪቱን ፍሬ ለትምክሕትና ለውበት ይሆናል። 3-4 ጌታም የጽዮንን ቈነጃጅት እድፍ ባጠበ ጊዜ፥ የኢየሩሳሌምንም ደም በፍርድ መንፈስና በሚያቃጥል መንፈስ ከመካከልዋ ባነጻ ጊዜ፥ በጽዮን የቀረ በኢየሩሳሌምም የተረፈ፥ በኢየሩሳሌም ለሕይወት የተጻፈ ሁሉ፥ ቅዱስ ይባላል። 5 እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራ ላይ ባለ ማደሪያ ሁሉ በጉባኤአቸውም ላይ በቀን ዳመናንና ጢስን በሌሊትም የሚቃጠለውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በክብርም ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል። 6 በቀን ከሙቀት ለጥላ፥ ከዐውሎ ነፋስና ከዝናብም ለመጠጊያና ለመሸሸጊያ ጎጆ ይሆናል።

ኢሳይያስ 5

1 አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው። 2 በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፥ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ። 3 አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ። 4 ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ? 5 አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል። 6 ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም፥ አይኰተኰትም፤ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁ። 7 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፥ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ። 8 ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ፥ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው! 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጆሮዬ እንዲህ አለ። በእውነት ብዙ ታላቅና መልካም ቤት ባድማ ይሆናል፥ የሚቀመጥበትም አይገኝም። 10 ከወይኑ ቦታ አሥር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ብቻ ይሰጣል። 11 ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው! 12 መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፥ እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም። 13 ስለዚህ ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ፥ ጌታን አላወቁትምና፤ ከበርቴዎቻቸውም ተራቡ፥ ሕዝባቸውም ተጠሙ። 14 ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ። 15 ሰውም ይጐሰቍላል፥ ሰውም ይዋረዳል፥ የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች፤ 16 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ብሎአል፥ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ተቀድሶአል። 17 የበግ ጠቦቶች በማሰማርያቸው ውስጥ ይሰማራሉ፥ እንግዶችም የሰቡትን ባድማ ይበላሉ። 18 በደልን በምናምንቴ ገመድ፥ ኃጢአትንም በሰረገላ ማሰሪያ ወደ ራሳቸው ለሚስቡ። እናይ ዘንድ ይቸኵል፥ 19 ሥራውንም ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ትቅረብ፥ ትምጣ ለሚሉ ወዮላቸው! 20 ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! 21 በዓይናቸው ጥበበኞች በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው! 22 የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላን የሚያሰክረውንም ለማደባለቅ ጨካኞች ለሆኑ፤ 23 በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው! 24 ስለዚህ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፥ እብቅም በነበልባል ውስጥ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል ቡቃያቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና። 25 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፥ ሬሳቸውም በአደባባይ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 26 ለአሕዛብም በሩቅ ምልክትን ያቆማል፥ ከምድርም ዳርቻ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነሆም፥ እየተጣደፉ ፈጥነው ይመጣሉ። 27 ደካማና ስንኵል የለባቸውም፥ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፥ የጫማቸውም ማዘቢያ አይበጠስም። 28 ፍላጾቻቸው ተስለዋል፥ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተለጥጠዋል፤ የፈረሶቻቸውም ኮቴ እንደ ቡላድ የሰረገሎቻቸውም መንኰራኵር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይቈጠራል። 29 ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፥ እንደ አንበሳ ደቦሎችም ያገሣሉ፤ ንጥቂያንም ይዘው ያገሣሉ፥ ይወስዱትማል፥ የሚያድንም የለም። 30 በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ቢመለከቱ፥ እነሆ፥ ጨለማና መከራ አለ፤ ብርሃንም በደመናዎችዋ ውስጥ ጨልሞአል።

ኢሳይያስ 6

1 ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። 2 ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። 3 አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር። 4 የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። 5 እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ። 6 ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። 7 አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ። 8 የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። 9 እርሱም። ሂድ፥ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። 10 በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ። 11 እኔም። ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ። ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥ 12 እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው። 13 በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፥ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል።

ኢሳይያስ 7

1 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም። 2 ለዳዊትም ቤት። ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። 3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው። አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ 4 እንዲህም በለው። ተጠበቅ፥ ዝምም በል፤ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም። 5-6 ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ። ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፤ 7 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። 8 የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፤ 9 የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም። 10 እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 11 ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን። 12 አካዝም። አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ። 13 እርሱም አለ። እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤ 14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። 15 ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። 16 ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። 17 እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው። 18 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብጽ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። 19 ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሃ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። 20 በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል። 21 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፤ 22 ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፤ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። 23 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ስፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል። 24 ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ። 25 በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተነሣ ወደዚያ አትሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።

ኢሳይያስ 8

1 እግዚአብሔርም። ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ በሰው ፊደል ጻፍበት። 2 የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝ። 3 ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች። 4 እግዚአብሔርም። ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው አለኝ። 5 እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ። 6 ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፥ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ፥ 7 እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፥ ያመጣባቸዋል፤ መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፥ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤ 8 እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፥ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፥ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች። 9 አሕዛብ ሆይ፥ እወቁና ደንግጡ፤ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ፥ አድምጡ፤ ታጠቁም፥ ደንግጡ፤ ታጠቁ፤ ደንግጡ። 10 ተመካከሩ፥ ምክራችሁም ይፈታል፤ ቃሉን ተናገሩ፥ ቃሉም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። 11 እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፥ በዚህም ሕዝብ መንገድ አንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፥ እንዲህም አለኝ። 12 ይህ ሕዝብ። ዱለት ነው በሚሉት ሁሉ። ዱለት ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፥ አትደንግጡ። 13 ነገር ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን። 14 እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል። 15 ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፥ ይወድቁማል፥ ይሰበሩማል፥ ይጠመዱማል፥ ይያዙማል። 16 ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም። 17 ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበትማለሁ። 18 እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። 19 እነርሱም። የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? 20 ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም። 21 እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፤ በተራቡም ጊዜ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፥ ወደ ላይም ይመለከታሉ፤ 22 ወደ ምድርም ይመለከታሉ፥ እነሆም፥ መከራና ጨለማ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ፤ ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።

ኢሳይያስ 9

1 ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። 2 በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው። 3 ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል። 4 በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል። 5 የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል። 6 ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። 7 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 8 ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፥ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። 9-10 በትዕቢትና በልብ ኵራት። ጡቡ ወድቆአል፥ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሠራለን፤ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፥ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን የሚሉ በኤፍሬምና በሰማርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ያውቃሉ። 11 ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ ተቋቋሚ ያስነሣበታል፥ 12 ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 13 ሕዝቡ ግን ወደ ቀሠፋቸው አልተመለሱም፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም። 14 ስለዚህ እግዚአብሔር ራስና ጅራትን፥ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል። 15 ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፤ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። 16 ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፤ ተመሪዎቹም ይጠፋሉ። 17 ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፥ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጕልማሶቻቸው ደስ አይለውም፥ ለድሀ አደጎቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 18 ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፥ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል። 19 በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። 20 ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል አይጠግብምም፤ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ 21 ምናሴ ኤፍሬምን ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።

ኢሳይያስ 10

1 2 መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ ድሀ አደጎችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፥ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው! 3 በተጎበኛችሁበት ቀን፥ መከራም ከሩቅ በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ? ክብራችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ? 4 ከእስረኞች በታች ይጐነበሳሉ፥ ከተገደሉትም በታች ይወድቃሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች። 5 ለቍጣዬ በትር ለሆነ፥ የመዓቴም ጨንገር በእጁ ላለ ለአሦር ወዮለት! 6 እርሱንም በዝንጉ ሕዝብ ላይ እልካለሁ፥ ምርኮውንና ብዝበዛውንም ይወስድ ዘንድ እንደ አደባባይም ጭቃ የተረገጡ ያደርጋቸው ዘንድ በምቈጣቸው ሰዎች ላይ አዝዘዋለሁ። 7 እርሱ እንዲሁ አያስብም፥ በልቡም እንዲህ አይመስለውም፤ ነገር ግን ማጥፋት፥ ጥቂት ያይደሉትንም አሕዛብን መቍረጥ በልቡ አለ። 8 እንዲህ ይላል። መሳፍንቴ ሁሉ ነገሥታት አይደሉምን? ካልኖ እንደ ከርከሚሽ አይደለችምን? 9 ሐማትስ እንደ አርፋድ አይደለችምን? ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደለችምን? 10 የተቀረጹ ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ ምስሎች የበለጡትን የጣዖቶችን መንግሥታት እጄ እንዳገኘች፥ 11 በሰማርያና በጣዖቶችዋም እንዳደረግሁ፥ እንዲሁስ በኢየሩሳሌምና በጣዖቶችዋ አላደርግምን? 12 ስለዚህ እንዲህ ይሆናል፤ ጌታ ሥራውን ሁሉ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ በፈጸመ ጊዜ የአሦርን ንጉሥ የኩሩ ልብ ፍሬን የዓይኑንም ከፍታ ትምክሕት ይጐበኛል። 13 እርሱ እንዲህ ብሎአልና። አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፥ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፥ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤ 14 እጄም የአሕዛብን ኃይል እንደ ወፍ ቤት አገኘች፤ የተተወም እንቍላል እንደሚሰበሰብ እንዲሁ እኔ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ ክንፉን የሚያራግብ አፉንም የሚከፍት የሚጮኽም የለም። 15 በውኑ መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይመካልን? ወይስ መጋዝ በሚስበው ላይ ይጓደዳልን? ይህስ፥ በትር የሚያነሣውን እንደ መነቅነቅ ዘንግም እንጨት ያይደለውን እንደ ማንሣት ያህል ነው። 16 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል። 17 የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ቅዱስም እንደ ነበልባል ይሆናል፤ እሾሁንና ኵርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል ይበላውማል። 18 ከነፍስም እስከ ሥጋ ድረስ የዱሩንና የሚያፈራውን እርሻ ክብር ይበላል፤ ይህም የታመመ ሰው እንደሚሰለስል ይሆናል። 19 የቀሩትም የዱር ዛፎች በቍጥር ጥቂት ይሆናሉ፥ ታናሽ ብላቴናም ይጽፋቸው ዘንድ ይችላል። 20 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የእስራኤል ቅሬታ ከያዕቆብም ቤት የዳኑት ከእንግዲህ ወዲህ በመቱአቸው ላይ አይደገፉም፤ ነገር ግን በእስራኤል ቅዱስ በእግዚአብሔር ላይ በእውነት ይደገፋሉ። 21 የያዕቆብም ቅሬታ ወደ ኃያል አምላክ ይምለሳሉ። 22 እስራኤል ሆይ፥ የሕዝብህ ቍጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን ቅሬታው ይመለሳል። ጽድቅ የተትረፈረፈበትም ጥፋት ተወስኖአል። 23 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል። 24 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በጽዮን የምትኖር ሕዝቤ ሆይ፥ አሦር በበትር ቢመታህ፥ ግብጽም እንዳደረገ ዘንጉን ቢያነሣብህ አትፍራው። 25 ቍጣዬ እስኪፈጸም መዓቴም እስኪያጠፋቸው ድረስ ጥቂት ጊዜ ቀርቶአልና። 26 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ምድያምን በሔሬብ ዓለት በኩል እንደ መታው ጅራፍ ያነሣበታል፤ በትሩም በባሕር ላይ ይሆናል፥ በግብጽም እንዳደረገ ያነሣዋል። 27 በዚያም ቀን ሸክሙ ከጫንቃህ ቀንበሩም ከአንገትህ ላይ ይወርዳል፤ ቀንበሩም ከውፍረት የተነሣ ይሰበራል። 28 ወደ አንጋይ መጥቶአል፤ በመጌዶን በኩል አልፎአል፤ በማክማስ ውስጥ ዕቃውን አኑሮአል፤ 29 በመተላለፊያ አልፎአል፤ በጌባ ማደሪያው ነው፤ ራማ ደንግጣለች፤ የሳኦል ጊብዓ ኰብልላለች። 30 አንቺ የጋሊም ልጅ ሆይ፥ በታላቅ ድምፅሽ ጩኺ፤ ላይሳ ሆይ፥ አድምጪ፤ ዓናቶት ሆይ፥ መልሽላት። 31 መደቤና ሸሽታለች፤ በግቤርም የሚኖሩ ቤተ ሰቦቻቸውን አሽሽተዋል። 32 ዛሬ በኖብ ይቆማል፤ በጽዮን ሴት ልጅ ተራራ በኢየሩሳሌም ኮረብታ ላይ እጁን ያንቀሳቅሳል። 33 እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅርንጫፎቹን በሚያስፈራ ኃይል ይቈርጣል፤ በቁመት የረዘሙትም ይቈረጣሉ፥ ከፍ ያሉትም ይዋረዳሉ። 34 ጭፍቅ የሆነውንም ዱር በብረት ይቈርጣል፥ ሊባኖስም በኃያሉ እጅ ይወድቃል።

ኢሳይያስ 11

1 ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል። 2 የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። 3 እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤ 4 ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፥ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም በትር ምድርን ይመታል፥ በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል። 5 የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል። 6 ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፥ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። 7 ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። 8 የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፥ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። 9 በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። 10 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። 11 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብጽ፥ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፥ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፥ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደ ገና እጁን ይገልጣል። 12 ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፥ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፥ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። 13 የኤፍሬምም ምቀኝነት ይርቃል፥ ይሁዳንም የሚያስጨንቁ ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፥ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። 14 በምዕራብም በኩል በፍልስጥኤማውያን ጫንቃ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፥ የምሥራቅንም ልጆች በአንድነት ይበዘብዛሉ፤ በኤዶምያስና በሞዓብም ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፥ የአሞንም ልጆች ለእነርሱ ይታዘዛሉ። 15 እግዚአብሔርም የግብጽን ባሕር ያጠፋል፤ በትኩሱም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፥ ሰባት ፈሳሾችንም አድርጎ ይመታዋል፥ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። 16 ከግብጽም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረ፥ ለቀረው ለሕዝቡ ቅሬታ ከአሦር ጐዳና ይሆናል።

ኢሳይያስ 12

1 በዚያም ቀን። አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ አጽናንተኸኛልምና አመሰግንሃለሁ። 2 እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ። 3 ውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። 4 በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ። 5 ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። 6 አንቺ በጽዮን የምትኖሪ ሆይ፥ የእስራኤል ቅዱስ በመካከልሽ ከፍ ከፍ ብሎአልና ደስ ይበልሽ እልልም በዪ።

ኢሳይያስ 13

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ያየው ስለ ባቢሎን የተንገረ ሸክም። 2 ምድረ በዳ በሆነ ተራራ ላይ ምልክትን አቁሙ፥ ድምፅንም ከፍ አድርጉባቸው፤ በአለቆችም ደጆች እንዲገቡ በእጅ ጥቀሱ። 3 ቍጣዬን ይፈጽሙ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዣለሁ፥ እኔ ኃያላኔንና በታላቅነቴ ደስ የሚላቸውን ጠርቻለሁ። 4 በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ የሆነ የብዙ ሰው ድምፅ አለ። የከተማቹት የአህዛብ መንግሥታት የውካታ ጫጫታ አለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሠራዊትን ለሰልፍ አሰልፎአል። 5 እግዚአብሔርና የቍጣው የጦር ዕቃ ምድርን ሁሉ ያጠፉአት ዘንድ ከሩቅ አገር ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ። 6 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል። 7 ስለዚህ እጅ ሁሉ ትዝላለች፥ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል። 8 ይደነግጣሉ፤ ምጥና ሕማም ይይዛቸዋል፥ እንደምትወልድ ሴትም ያምጣሉ፤ አንዱም በሌላው ይደነቃል፥ ፊታቸውም የነበልባል ፊት ነው። 9 እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል። 10 የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም። 11 ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት አዋርዳለሁ። 12 የቀሩትም ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፥ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል። 13 ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች። 14 እንደ ተባረረም ሚዳቋ፥ ማንም እንደማይሰበስበው እንደ በግ መንጋ፥ ሰው ሁሉ ወደ ወገኑ ይመለሳል፥ ሁሉም ወደ አገሩ ይሸሻል። 15 የተገኘ ሁሉ የተወጋ ይሆናል፥ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል። 16 ሕፃናቶቻቸውም በፊታቸው ይጨፈጨፋሉ፥ ቤቶቻቸውም ይበዘበዛሉ፥ ሚስቶቻቸውም ይነወራሉ። 17 እነሆ፥ ብር የማይሹትን፥ ወርቅም የማያምራቸውን ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ። 18 ፍላጾቻቸውም ጎበዞችን ይጨፈጭፋሉ፥ የማኅፀንንም ፍሬ አይምሩም፥ ዓይኖቻቸውም ለሕፃናት አይራሩም። 19 እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። 20 ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፥ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፥ እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም። 21 በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፥ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፥ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ። 22 ተኵላዎችም በግንቦቻቸው፥ ቀበሮችም በሚያማምሩ አዳራሾቻቸው ይጮኻሉ፤ ጊዜዋም ለመምጣት ቀርቦአል ቀንዋም አይዘገይም።

ኢሳይያስ 14

1 እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል። 2 አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፤ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ። 3 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4 ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ። አስጨናቂ እንዴት ዐረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ! 5-6 አሕዛብንም በመዓትና በማያቋርጥ መምታት የመታውን፥ አሕዛብንም ባልተከለከለ መከራ በቍጣው የገዛውን የኀጥኣንን በትር የአለቆችንም ዘንግ እግዚአብሔር ሰብሮአል። 7 ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። 8 ጥድና የሊባኖስ ዝግባ። አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። 9 ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፤ የሞቱትንም፥ የምድርን ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። 10 እነዚህ ሁሉ። አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፤ 11 በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። 12 አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! 13 አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ 14 ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15 ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። 16 የሚያዩህ ይመለከቱሃልና። በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17 ዓለሙን ሁሉ ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ ምርከኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። 18 የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19 አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፤ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጕድጓዱ ድንጋዮች የወረዱት ከድነውሃል፤ እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። 20 ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘላለም የተጠራ አይሆንም። 21 እንዳይነሡም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። 22 በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል እግዚአብሔር። 23 የጃርት መኖርያ የውኃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፤ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 24 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል። እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። 25 አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። 26 በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። 27 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፤ የሚያስጥለውስ ማን ነው? እጁም ተዘርግታለች፤ የሚመልሳትስ ማን ነው? 28 ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዓመት ይህ ሸክም ሆነ። 29 ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30 የድሆችም የበኵር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፤ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። 31 አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፤ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፤ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። 32 ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መመለስ ይገባል? እግዚአብሔር ጽዮንን እንደ መሠረተ፥ የሕዝቡም ችግረኞች በእርስዋ ውስጥ እንደሚጠጉ ነው።

ኢሳይያስ 15

1 ስለ ሞዓብ የተነገረ ሸክም። የሞዓብ ዔር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ። 2 ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባው በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቶአል። 3 በየመገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል። 4 ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ይሰማል፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍስዋ በውስጥዋ ተንቀጠቀጠች። 5 ልቤ ስለ ሞዓብ ጮኸ፤ ከእርስዋም የሚሸሹ ወደ ዞዓር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኰበለሉ፤ በሉሒት ዓቀበት ላይ እያለቀሱ ይወጣሉ፥ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኸት ያነሣሉ። 6 የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፥ ለጋውም ጠውልጓል፥ ልምላሜውም ሁሉ የለም። 7 ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል። 8 ጩኸት የሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ዞረ፤ ልቅሶዋም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ። 9 የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ በዲሞንም ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን አመጣለሁ።

ኢሳይያስ 16

1 በምድርም ላይ ለሠለጠነው አለቃ የበግ ጠቦቶችን በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ስደዱ። 2 እንደሚበርር ወፍ እንደ ተበተኑም ጫጩቶች እንዲሁ የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን መሻገሪያዎች ይሆናሉ። 3 ምክርን ምከሪ፥ ፍርድን አድርጊ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አድርጊ፤ የተሰደዱትን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አትግለጪ። 4 ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ጋር ይቀመጡ፤ ከሚያጠፋቸው ፊት መጋረጃ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቶአል፤ ይጨቍኑ የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። 5 ዙፋንም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ድንኳን ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል 6 ስለ ሞዓብ ትዕቢት እጅግ ስለ መታበዩ፥ ስለ ኵራቱና ስለ ትዕቢቱ ስለ ቍጣውም ሰምተናል፤ ትምሕክቱ ከንቱ ነው። 7 ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይ ይላል፤ ሁሉም ዋይ ይላል፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። 8 የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። 9 ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አረካሻለሁ። 10 ደስታና ሐሤትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፥ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። 11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች። 12 ሞዓብም መጥቶ በኮረብታ መስገጃ ላይ በደከመና ለጸሎት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ አያሸንፍም 13 እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። 14 አሁን ግን እግዚአብሔር። በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፥ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል።

ኢሳይያስ 17

1 ስለ ደማስቆ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማ ከመሆን ተቋርጣለች፤ ባድማና የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች። 2 ከተሞችዋ ለዘላለም የተፈቱ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማሪያ ሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም። 3 ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ተወገደች፤ የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 4 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የያዕቆብ ክብር ይደክማል የሥጋውም ውፍረት ይከሳል። 5 አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል፤ በራፋይም ሸለቆ ቃርሚያ እንደሚለቅም እንዲሁ ይሆናል። 6 ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፥ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። 7 በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፥ ዓይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። 8 እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፤ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፥ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፥ አያይም። 9 በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤውያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ፥ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ፥ ባድማም ይሆናሉ። 10 የደኅንነትህን አምላክ ረስተሃል፥ የረድኤትህንም ጌታ አላሰብህም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ተክለሃል፥ እንግዳንም ዘር ዘርተሃል። 11 በተከልህበት ቀን ታበቅለዋለህ፥ በነጋውም ዘርህን እንዲያብብ ታደርገዋለህ፤ ነገር ግን በኀዘንና በትካዜ ቀን መከሩ ይሸሻል። 12 እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ለሚተምሙ ለወገኖች ብዛት፥ እንደ ኃይለኛም ውኃ ጩኸት ለሚጮኹ አሕዛብ ወዮላቸው! 13 አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፥ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፥ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው ትቢያ ይበተናሉ። 14 በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ድንጋጤ አለ፤ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ነው።

ኢሳይያስ 18

1 በኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያላቸው መርከቦች ላሉባት፥ 2 መልእክተኞችን በባሕር ላይ የደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድር ወዮላት! እናንተ ፈጣኖች መልእክተኞች ሆይ፥ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደ ሆነ ወገን፥ ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሂዱ። 3 በዓለም የምትኖሩ ሁሉና በምድር የምትቀመጡ ሆይ፥ ምልክት በተራሮች ላይ በተነሣ ጊዜ እዩ፤ መለከትም በተነፋ ጊዜ ስሙ። 4 እግዚአብሔር። በፀሐይ ጮራ እንደ ደረቅ ትኩሳት፥ በአጨዳም ወራት እንደ ጠል ደመና ሆኜ በማደሪያዬ በጸጥታ ተቀምጬ እመለከታለሁ ብሎኛልና። 5 እርሱ ከመከር በፊት አበባ በረገፈ ጊዜ የወይንም ፍሬ ጨርቋ ሲይዝ የወይኑን ዘንግ በማጭድ ይቆርጣል፥ ጫፎቹንም ይመለምላል ያስወግድማል። 6 በተራራ ላይ ላሉ ነጣቂዎች ወፎች፥ ለምድርም አውሬዎች በአንድነት ይቀራሉ፤ ነጣቂዎችም ወፎች ይባጁባቸዋል፥ የምድርም አውሬዎች ሁሉ ይከርሙባቸዋል። 7 በዚያን ዘመን ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር፥ ከረጅምና ከለስላሳ ሕዝብ፥ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ከሆነ ወገን፥ ከሚሰፍርና ከሚረግጥ፥ ወንዞችም ምድራቸውን ከሚከፍሉት ሕዝብ ዘንድ እጅ መንሻ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም ወደሚገኝበት ስፍራ ወደ ጽዮን ተራራ ይቀርባል።

ኢሳይያስ 19

1 ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል። 2 ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል። 3 የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቍሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ። 4 ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5 ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል። 6 ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። 7 በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም። 8 ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ። 9 የተበጠረውንም የተልባ እግር የሚሠሩ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ። 10 ደገፋዎችዋም ሁሉ ይሰባበራሉ፥ የደመወዘኞችም ነፍስ ትተክዛለች። 11 የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቍርና ሆነች። ፈርዖንን። እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ? 12 አሁንሳ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ። 13 የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ሆነዋል፥ የሜምፎስም አለቆች ተሸንግለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብጽን አሳቱ። 14 እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤ ሰካር በትፋቱ እንዲስት እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ አሳቱ። 15 ራስ ወይም ጅራት የሰሌን ቅርንጫፍ ወይም እንግጫ ቢሆን ሊሠራ የሚችል ሥራ ለግብጽ አይሆንላትም። 16 በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ መንቀሳቀስ የተነሣ ይሸበራሉ ይፈሩማል። 17 የይሁዳም ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል። 18 በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከነዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች። 19 በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል። 20 ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም መድኃኒትንና ኃያልን ሰድዶ ያድናቸዋልና። 21 በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፥ ግብጽAውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቍርባን ያመልካሉ፥ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል። 22 እግዚአብሔርም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ እርሱም ይለመናቸዋል ይፈውሳቸውማል። 23 በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፥ አሦራዊውም ወደ ግብጽ፥ ግብጻዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብጻውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ። 2425 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን ብሎ ይባርካቸዋልና በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፥ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል።

ኢሳይያስ 20

1 የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥ 2 በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን። ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ። 3 እግዚአብሔርም አለ። ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥ 4 እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጕስቍልና ይነዳቸዋል። 5 እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል፤ 6 በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ። እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።

ኢሳይያስ 21

1 በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል። 2 ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው ይወነጅላል አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ። 3 ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። 4 ልቤ ተንበደበደ፥ ድንጋጤ አስፈራኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ። 5 ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበሉማል፥ ይጠጡማል፤ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ። 6 ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። ሂድ ጉበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር። 7 በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ። 8 ያየውም። ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፥ 9 እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ። ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ። 10 እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ። 11 ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር። ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ። 12 ጕበኛውም። ይነጋል ድግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ አለ። 13 ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ። 14 በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። 15 ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና። 16 ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ 17 ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።

ኢሳይያስ 22

1 ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ሸክም። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታቸሁ ምን ሆናችኋል? 2 ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፥ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፥ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም። 3 አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ። 4 ስለዚህ። ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፤ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ አልሁ። 5 ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፥ የቅጥርም መፍረስ ወደ ተራራም መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል። 6 ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን ገለጠ። 7 መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሰረገሎች ሞሉባቸው፥ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ። 8 የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፤ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፥ 9 የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደ በዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል፥ 10 የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ። 11 በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም። 12 በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ። 13 እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፤ እናንተ። ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል። 14 ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ። እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 15 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው። 16 መቃብር በዚህ ያስወቀርህ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሰራህ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ? 17 እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጠንክሮም ይጨብጥሃል። 18 ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ። 19 ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፥ ከሹመትህም ትሻራለህ። 20 በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥ 21 መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፥ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፥ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል። 22 የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም። 23 በታመነም ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፥ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል። 24 የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፥ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፥ ታናናሹን ዕቃ ሁሉ ይሰቅሉበታል። 25 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በታመነው ስፍራ የተከለው ችንካር ይወልቃል ተሰብሮም ይወድቃል፥ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።

ኢሳይያስ 23

1 ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም። የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፥ መግባትም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል። 2 እናንተ በደሴት የምትኖሩ በባሕርም የምትሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች ንግድ የሞሉባችሁ ሆይ፥ ጸጥ በሉ። 3 የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች። 4 ሲዶና ሆይ፥ ባሕር፥ የባሕር ምሽግ። አላማጥሁም፥ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፥ ደናግልንም አላሳደግሁም ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ። 5 ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ በጢሮስ ወሬ ምጥ ይይዛቸዋል። 6 ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ። 7 በቀድሞ ዘመን ተመሥርታ የነበረችው፥ በዚያም እንደ እንግዳ ሆና ትኖር ዘንድ እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈለሱአት የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን? 8 አክሊል ባስጫነች ከተማ በጢሮስ ላይ ይህን የወሰነ ማን ነው? ነጋዴዎችዋ አለቆች ናቸው፥ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን ናቸው። 9 የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል። 10 የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ ጐርፈሽ እለፊ። 11 በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን አገር አዘዘ። 12 እርሱም። አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ። 13 እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት። 14 እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። 15 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። 16 አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። 17 ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትምለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች። 18 ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።

ኢሳይያስ 24

1 እነሆ፥ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል። 2 እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፥ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፥ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፥ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፥ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፥ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል። 3 ምድር መፈታትን ትፈታለች፥ ፈጽማም ትበላሻላች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና። 4 ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ። 5 ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። 6 ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። 7 የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ንግድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። 8 የከበሮው ሐሤት ቀርቶአል፥ የደስተኞች ድምፅ ዝም ብሎአል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። 9 እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክርም መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል። 10 ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ቤት ሁሉ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ። 11 ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። 12 ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል። 13 የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል። 14 እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። 15 ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። 16 ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን። ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፤ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ። 17 በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። 18 የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 19 ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። 20 ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም። 21 በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። 22 ግዞተኞች በጕድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፥ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጐበኛሉ። 23 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።

ኢሳይያስ 25

1 አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህ፤ ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ። 2 ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥአንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ከቶ አትሠራም። 3 ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች። 4 የጨካኞችም ቍጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፥ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። 5 እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል። 6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። 7 በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። 8 ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። 9 በዚያም ቀን። እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል። 10 የእግዚአብሔርም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፥ ጭድም በጭቃ ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በስፍራው ይረገጣል። 11 ዋናተኛም ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፥ እንዲሁ በመካከሉ እጁን ይዘረጋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ትዕቢቱን ከእጁ ተንኰል ጋር ያዋርዳል። 12 የተመሸገውንም ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፥ ያዋርደውማል፥ ወደ መሬትም እስከ አፈር ድረስ ይጥለዋል።

ኢሳይያስ 26

1 በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘመራል። የጸናች ከተማ አለችን፤ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል። 2 እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ። 3 በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። 4 ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ። 5 በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያዋርዳታል፥ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል። 6 እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፥ ትረግጣታለች። 7 የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ። 8 አቤቱ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው። 9 ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩት ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች። 10 ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፥ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም። 11 አቤቱ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩምም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች። 12 አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ። 13 አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን በአንተ ብቻ ስምህን እናስባለን። 14 እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጐብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፥ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምንምን አድርገሃል። 15 ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ፥ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ። 16 አቤቱ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሰጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ። 17 የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮኽ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል። 18 እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላደረግነም፤ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ። 19 ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም። 20 ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። 21 በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፥ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።

ኢሳይያስ 27

1 በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፥ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል። 2 በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። 3 እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ። 4 አልቈጣም፤ እሾህና ኵርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር። 5 ወይም ጕልበቴን ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። 6 በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። 7 በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን? 8 ነዳቸው ሰደዳቸው ቀሠፋቸው፤ የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው። 9 ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኀጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው። 10 የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፤ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተፈታችና የተተወች መኖሪያ ናት፤ በዚያም ጥጃ ይሰማራል በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል። 11 ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። 12 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፥ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።

ኢሳይያስ 28

1 ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ! 2 እነሆ፥ በጌታ ዘንድ ኃያል ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ታላቅ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል። 3 የኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤ 4 በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል። 5 በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤ 6 በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል። 7 እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ። 8 ማዕዱ ሁሉ ትፋትንና ርኵሰትን ተሞልቶአታል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም። 9 እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? 10 ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። 11 በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም። ዕረፍት ይህች ናት፥ 12 የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። 13 ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል። 14 ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 15 እናንተም። ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ስላላችሁ፥ 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ የሚያምን አያፍርም። 17 ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። 18 ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ። 19 ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ ወሬውንም ማስተዋል ድንጋጤ ይሆናል። 20 ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጐናጸፊያ ጠባብ ነው። 21 እግዚአብሔርም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፥ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፥ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል። 22 አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸንባችሁ አታፊዙ። 23 አድምጡ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ። 24 በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይገለግላልን? 25 ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን? 26 ይህንም ብልሃት አምላኩ ያስታውቀዋል ያስተምረውማል። 27 ጥቁሩ አዝሙድ በተሳለች መሄጃ አያኬድም፥ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል። 28 የእንጀራ እህል ይደቅቃልን? ለዘላለም አያኬደውም፤ የሰረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም። 29 ይህም ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።

ኢሳይያስ 29

1 ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመለሱ። 2 አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እንደ አርኤልም ትሆንልኛለች። 3 በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። 4 ትዋረጂማለሽ፥ በመሬትም ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም ዝቅ ብሎ ከአፈር ይወጣል፤ ድምፅሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ጠሪ ድምፅ ይሆናል፥ ቃልሽም ከአፈር ወጥቶ ይጮኻል። 5 ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። 6 ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። 7 በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርስዋንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። 8 ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም አምሮት አለው፤ እንዲሁ የጽዮንን ተራራ የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት ይሆናል። 9 ተደነቁ ደንግጡም፤ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገደገዱ። 10 እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል። 11 ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፤ 12 ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል። 13 ጌታም። ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈርቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና 14 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፥ እንደ ገና አደርጋለሁ፤ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች። 15 ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው። ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው! 16 ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን። አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን። አታስተውልም ይለዋልን? 17 ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቈጠር ጥቂት ዘመን የቀረ አይደለምን? 18 በዚያም ቀን ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፥ የዕውሮችም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተለይተው ያያሉ። 19 የዋሃን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፥ በሰዎች መካከል ያሉ ችግረኞችም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ ያደርጋሉ። 20 ጨካኙ ሰው አልቆአልና፥ ፌዘኛውም ጠፍቶአልና፥ ለኃጢአትም የደፈጡ ሁሉ ይቈረጣሉና፤ 21 እነዚህም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው። 22 ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠ እግዚአብሔር ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል። ያዕቆብ አሁን አያፍርም፥ ፊቱም አሁን አይለወጥም። 23 ነገር ግን የእጄን ሥራ ልጆቹን በመካከሉ ባያቸው ጊዜ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። 24 በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፥ የሚያጕረመርሙም ትምህርትን ይቀበላሉ።

ኢሳይያስ 30

1 ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ምክር ይመክራሉ፥ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ይጨምሩ ዘንድ ከመንፈሴ ዘንድ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ። 2 ከአፌም ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ይጸኑ ዘንድ በግብጽም ጥላ ይታመኑ ዘንድ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ ይሄዳሉ። 3 ስለዚህ የፈርዖን ኃይል እፍረት በግብጽም ጥላ መታመን ስድብ ይሆንባችኋል። 4 አለቆች ምንም በጣኔዎስ ቢሆኑ፥ መልክተኞችም ምንም ወደ ሓኔስ ቢደርሱ፥ 5 ሁላቸው ይጠቅሙአቸው ዘንድ ስለማይችሉ፥ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኑ ሕዝብ ያፍራሉ። 6 በደቡብ ስላሉ እንስሶች የተነገረ ሸክም። ተባትና እንስት አንበሳ እፉኝትም ነዘር እባብም በሚወጡባት በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሙአቸው ሕዝብ ይሄዳሉ። 7 የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምናምን ነው፤ ስለዚህ ስሙን። በቤት የሚቀመጥ ረዓብ ብዬ ጠርቼዋለሁ። 8 አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው። 9 ዓመፀኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤ 10 ባለ ራእዮችን። አትመልከቱ ይላሉ፥ ነቢያትንም። ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥ 11 ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ ይሉአቸዋል። 12 ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል። ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና 13 ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል። 14 የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቅቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። 15 የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ፥ 16 ነገር ግን። በፈረስ ላይ ትቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም። በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። 17 ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። 18 እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፥ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። 19 በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። 20 ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ 21 ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ። መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ። 22 በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ። ወግዱ ትላቸውማለህ። 23 በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፤ 24 መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ። 25 በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ በረጅሙ ተራራ ሁሉ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይሆናሉ። 26 እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ መቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል። 27 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ስም ከሚነድድ ቍጣ ከሚትጐለጐልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም ቍጣን የሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፤ 28 እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፥ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል። 29 ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ ዓመት ሌሊት እንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላችኋል፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እስራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ እንቢልታ ይዞ እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል። 30 እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቍጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል በዐውሎ ነፋስም በወጨፎም በበረዶ ጠጠርም ይገልጣል። 31 አሦርም በበትር ከመታው ከእግዚአብሔር ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል። 32 እግዚአብሔር በላዩ በሚያወርድበት የታዘዘበቱ የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ ይሆናል፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል። 33 ከቀድሞም ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች፥ ለንጉሥም ተበጅታለች፤ ጥልቅና ሰፊም አድርጎአታል፤ እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፤ የእግዚአብሔርም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል።

ኢሳይያስ 31

1 ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! 2 እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል። 3 ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። 4 እግዚአብሔርም እንዲህ ይለኛልና። አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሳ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል። 5 እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፥ ይታደጋታል፥ አልፎም ያድናታል። 6 እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ። 7 በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ። 8 አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻሉ ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ። 9 አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 32

1 እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። 2 ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል። 3 የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፥ የሚሰሙትም ጆሮች ያደምጣሉ። 4 ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፥ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች። 5 ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም። 6 ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፥ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል። 7 የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት፤ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳ እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል። 8 ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፥ በመከበርም ጸንቶ ይኖራል። 9 እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ። 10 እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቍረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ። 11 እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ። 12 ስለ ተወደደችውም እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ። 13 በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኵርንችት ይወጣባቸዋል፤ 14 አዳራሹ ወና ትሆናለችና፥ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቀቃለችና፥ አምባውና ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናልና። 15 ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል። 16 ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል። 17 የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል። 18 ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል። 19 በረዶ ግን በዱር ላይ ይወርዳል፥ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች። 20 እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውኃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ብፁዓን ናችሁ።

ኢሳይያስ 33

1 አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፥ በአንተም ላይ ወንጀል ሳይደረግ ወንጀል የምታደርግ ወዮልህ! ማጥፋትን በተውህ ጊዜ ትጠፋለህ፤ መወንጀልንም በተውህ ጊዜ ይወነጅሉሃል። 2 አቤቱ፥ ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን። 3 ከፍጅት ድምፅ ወገኖች ሸሹ፥ በመነሣትህም አሕዛብ ተበተኑ። 4 አንበጣ እንደሚሰበስብ ምርኮአችሁ ትሰበሰባለች፥ ኩብኩባም እንደሚዘልል ሰዎች ይዘልሉበታል። 5 እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ ከፍ አለ፤ ጽዮንን በፍርድና በጽድቅ ሞላት። 6 የዘመንህም ጸጥታ፥ የመድኃኒት ብዛት፥ ጥበብና እውቀት ይሆናል፤ እግዚአብሔርን መፍራት መዝገቡ ነው። 7 እነሆ፥ ኃይለኞቻቸው በሜዳ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። 8 መንገዶች ባድማ ሆኑ፥ ተላላፊም ቀረ፤ እርሱም ቃል ኪዳንን አፈረሰ ከተሞችንም ናቀ ሰውንም አልተመለከተም። 9 ምድሪቱ አለቀሰች ከሳችም፤ ሊባኖስ አፈረ ጠወለገም፤ ሳሮን እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ። 10 አሁን እነሣለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ። 11 ገለባን ትፀንሳላችሁ፥ እብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት። 12 አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፥ ተቈርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ። 13 እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፥ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እወቁ። 14 በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎቹን ያዘ፤ ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? 15 በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደነቍር፥ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው። 16 እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች። 17 ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል። 18 ልብህም። ጸሐፊ ወዴት አለ? መዛኝስ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ? ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል። 19 ጨካኝን ሕዝብ፥ ቋንቋው ለማስተዋል ጥልቅ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ፥ አታይም። 20 የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዓይኖችህ የሰላም ማደሪያ፥ ካስማውም ለዘላለም የማይነቀል አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ፥ የማይወገድ ድንኳን የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ። 21 እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል፤ የሚቀዘፉ መርከቦች አይገቡባትም፥ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም። 22 እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል። 23 ገመዶችህ ላልተዋል፥ ደቀላቸውንም አላጸኑም፥ ሸራውንም መዘርጋት አልቻሉም። በዚያም ጊዜ የብዙ ምርኮ ብዝበዛ ተከፈለ፤ አንካሶች እንኳ ብዝበዛውን በዘበዙ። 24 በዚያም የሚቀመጥ። ታምሜአለሁ አይልም፥ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።

ኢሳይያስ 34

1 እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሙላዋ፥ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ። 2 የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። 3 ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፥ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፥ ተራሮችም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ። 4 የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል። 5 ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። 6 እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፥ በስብም፥ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኵላሊት ስብ ወፍራለች። 7 ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች። 8 የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፥ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው። 9 የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቀጠል ዝፍት ትሆናለች። 10 በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፥ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። 11 ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጕጕትና ቍራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል። 12 መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ። 13 በአዳራሾችዋም እሾህ በቅጥሮችዋም ሳማን አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች። 14 የምድረ በዳም አራዊት ከተኵሎች ጋር ይገናኛሉ፥ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች። 15 በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ። 16 በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፥ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም። 17 እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል።

ኢሳይያስ 35

1 ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። 2 እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ። 3 የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ። 4 ፈሪ ልብ ላላቸው። እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው። 5 በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። 6 በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። 7 ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል። 8 በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። 9 አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤ 10 እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።

ኢሳይያስ 36

1 እንዲህም ሆነ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው። 2 የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፥ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ። 3 የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ። 4 ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? 5 እኔ። ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃያልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? 6 እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ አንዲሁ ነው። 7 አንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ይስፈረሰ ይህ አይደለምን? 8 አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። 9 ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? 10 አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ። 11 ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት። 12 ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው። 13 ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ። የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። 14 ንጉሡ እንዲህ ይላል። ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ 15 ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። 16 ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ 17 ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለበት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። 18 ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? 19 የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? 20 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው? 21 እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ አንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። 22 የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።

ኢሳይያስ 37

1 እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። 2 የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። 3 እነርሱም። ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል። ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ኃይል የለም። 4 ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት። 5 እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ። 6 ኢሳይያስም። ለጌታችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። 7 እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት አላቸው። 8 የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። 9 እርሱም። የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ ሰማ። በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ 10 እንዲህ ሲል። ለይሁዳ ንጉሠ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። 11 እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? 12 አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? 13 የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ? 14 ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15 ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ። 16 አቤቱ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። 17 አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬም ቃል ስማ። 18 አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፥ 19 አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። 20 እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን። 21 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሃልና 22 እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው። ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። 23 የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግህበት ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። 24 አንተም። በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። 25 ቈፈርሁም ውኃም ጠጣሁ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ ብለህ በባሪያዎችህ እጅ በጌታ ላይ ተገዳደርህ። 26 እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። 27 ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታው እህል ሆነዋል። 28 እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቍጣ አውቄአለሁ። 29 ቍጣህና ትዕቢትህ ወደጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፥ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። 30 ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዱማላችሁ፥ ወይንም ትተክላላችሁ ፍሬውንም ትበላላችሁ። 31 ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። 32 ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። 33 ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። 34 በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፥ ወደዚችም ከተማ አይመጣም ይላል እግዚአብሔር። 35 ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ። 36 የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። 37 የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። 38 በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

ኢሳይያስ 38

1 በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው። 2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 3 አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ። 5 ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ። 6 አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ። 7 እግዚአብሔርም የተገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል። 8 እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። 9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሕፈት ይህ ነው። 10 እኔ። በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ። 11 ደግሞም። በሕያዋን ምድር እግዚአብሔርን አላይም፤ በዓለምም ከሚኖሩ ጋር ሰውን እንግዲህ አልመለከትም አልሁ። 12 ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፥ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። 13 እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። 14 እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። 15 ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። 16 ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ። 17 እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ። 18 ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። 19 እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል። 20 እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን። 21 ኢሳይያስም። የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል ብሎ ነበር። 22 ሕዝቅያስም። ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድር ነው? ብሎ ነበር።

ኢሳይያስ 39

1 በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ ታምሞ እንደ ተፈወሰ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻ ላከለት። 2 ሕዝቅያስም ደስ አለው፥ ግምጃ ቤቱንም፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣርያም ያለበትን ቤት ሁሉ፥ በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም። 3 ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ። እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡልህ? አለው። ሕዝቅያስም። ከሩቅ አገር ከባቢሎን መጡልኝ አለው። 4 እርሱም። በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም። በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው። 5 ኢሳይያስም ሕዝቅያስን። የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 6 እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አይቀርም፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 ከአንተም ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦች ይሆናሉ አለው። 8 ሕዝቅያስም ኢሳይያስን። የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም። በዘመኔ ሰላምና እውነት ይሁን አለ።

ኢሳይያስ 40

1 አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። 2 ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ። 3 የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። 4 ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ 5 የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። 6 ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። 7 የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። 8 ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። 9 የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች። እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። 10 እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። 11 መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። 12 ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? 13 የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? 14 ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው? 15 እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል። 16 ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም። 17 አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምናምን እንደሚያንሱ፥ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል። 18 እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ? 19 የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል። 20 ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል። 21 አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን? 22 እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥ 23 አለቆችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው። 24 ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው። 25 እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። 26 ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። 27 ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ። መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? 28 አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። 29 ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። 30 ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ 31 እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።

ኢሳይያስ 41

1 ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ ለአንድነት እንቅረብ። 2 ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የተጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። 3 አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅነት አለፈ። 4 ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋላኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ። 5 ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም። 6 ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም። አይዞህ ይለው ነበር። 7 አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፥ ስለ ማጣበቅ ሥራውም። መልካም ነው አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው። 8 ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ 9 አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና። አንተ ባሪያዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥ 10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። 11 እነሆ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል። 12 የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። 13 እኔ አምላክህ እግዚአብሔር። አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። 14 አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። 15 እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። 16 ታበጥራቸዋለህ፥ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። 17 ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። 18 በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። 1920 የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሀውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ። 21 ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። 22 ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን። 23 አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ። 24 እነሆ፥ እንዳልነበረ ናችሁ፥ ሥራችሁም ከንቱ ነው፤ የሚመርጣችሁም አስጻያፊ ነው። 25 አንዱን ከሰሜን አነሣሁ መጥቶአልም፤ አንዱም ከፀሐይ መውጫ ስሜን የሚጠራ ይመጣል፤ በጭቃ ላይ እንደሚመጣ ሰው አፈርም እንደሚረግጥ ሸክለኛ በአለቆች ላይ ይመጣል። 26 እናውቅ ዘንድ ከጥንት የተናገረው። እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፥ የሚገልጥም የለም፥ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም። 27 በመጀመሪያ ለጽዮን። እነኋቸው እላለሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምስራች ነጋሪን እሰጣለሁ። 28 ብመለከት ማንም አልነበረም፤ ብጠይቃቸውም የሚመልስልኝ አማካሪ በመካከላቸው የለም። 29 እነሆ፥ እነርሱ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ ሥራቸውም ምንምን ናት፤ ቀልጠው የተሠሩት ምስሎቻቸውም ነፋስና ኢምንት ናቸው።

ኢሳይያስ 42

1 እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። 2 አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። 3 የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። 4 በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ይበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። 5 ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 67 እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። 8 እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። 9 እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። 10 ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። 11 ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። 12 ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። 13 እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። 14 ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። 15 ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኵሬዎችንም አደርቃለሁ። 16 ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም። 17 በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች። አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ። 18 እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ። 19 ከባሪያዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹሙ ወይስ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ ዕውር የሆነ ማን ነው? 20 ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፥ ነገር ግን አትሰሙም። 21 እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ። 22 ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁላቸው በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ብዝበዛ ሆነዋል የሚያድንም የለም፥ ምርኮም ሆነዋል፥ ማንም። መልሱ አይልም። 23 ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው? 24 ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፥ እነርሱም በመንገዱ ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት ለሕጉም ያልታዘዙለት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን? 25 ስለዚህ የቍጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰበት፤ በዙሪያም አነደደው እርሱ ግን አላወቀም፥ አቃጠለውም እርሱ ግን ልብ አላደረገም።

ኢሳይያስ 43

1 አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። 2 በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። 3 እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። 4 በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። 5 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። 67 ሰሜንን። መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም። አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። 8 ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ። 9 አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው፤ ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም እውነት ነው ይበሉ። 10 ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። 11 እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። 12 ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። 13 ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? 14 የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። 15 ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 16 እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤ 17 እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 18 የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። 19 እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለህ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ። 2021 ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል። 22 ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል። 23 ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም አላደከምሁህም። 24 ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ፥ በበደልህም አደከምኸኝ። 25 መተላለፍህን። ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም። 26 አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር። 27 ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል። 28 ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስሁ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።

ኢሳይያስ 44

1 አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። 2 የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ። 3 በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥ 4 በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ። 5 ይህ። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል። 6 የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። 7 እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ። 8 አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም። 9 የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ ያፍራሉ። 10 አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? 11 እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፤ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። 12 ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። 13 ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለካዋል፤ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል። 14 የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል። 15 ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። 16 ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና። እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል። 17 የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ። አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። 18 አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉ ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። 19 በልቡም ማንም አያስብም። ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም። 20 አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም። በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም። 21 ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳ ትሆናለህ። 22 መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። 23 ሰማያት ሆይ፥ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ። 24 ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? 25 የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤ 26 የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፥ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን። የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች። ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ፤ 27 ቀላዩንም። ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤ 28 ቂሮስንም። እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን ። ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።

ኢሳይያስ 45

1 እግዚአብሔር ለቀባሁት፥ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ የነገሥታትንም ወገብ እፈታ ዘንድ፥ በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፥ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል። 2 በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፥ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቈርጣለሁ፤ 3 በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ። 4 ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፥ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቍልምጫ ስምህ ጠራሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም። 5 እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። 7 ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ፤ እነነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 8 እናንተ ሰማያት ከላይ አንጠባጥቡ ደመናትም ጽድቅን ያዝንቡ፤ ምድርም ትከፈት መድኃኒትንም ታብቅል፥ ጽድቅም በአንድነት ይብቀል፤ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ። 9 ከሠሪው ጋር ለሚታገል ወዮለት! በምድር ሸክላዎች መካከል ያለ ሸክላ ነው። ጭቃ ሠሪውን። ምን ትሠራለህ? ወይስ ሥራህ። እጅ የለውም ይላልን? 10 አባትን። ምን ወልደሃል? ወይም ሴትን። ምን አማጥሽ? ለሚል ወዮ! 11 የእስራኤል ቅዱስ ሠሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፥ ስለ ልጆቼና ስለ እጄ ሥራም እዘዙኝ። 12 እኔ ምድርን ሠርቻለሁ ሰውንም በእርስዋ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቼአለሁ፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ አዝዣለሁ። 13 እኔ በጽድቅ አስነሥቼዋለሁ መንገዱንም ሁሉ አቀናለሁ፤ እርሱ ከተማዬን ይሠራል፥ በዋጋም ወይም በደመወዝ ሳይሆን ምርኮኞቼን ያወጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 14 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ። በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። 15 የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ፥ በእውነት አንተ ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ። 16 ሁሉም ያፍራሉ ይዋረዱማል፥ ጣዖታትንም የሚሠሩ በአንድነት ወደ ውርደት ይሄዳሉ። 17 እግዚአብሔር ግን እስራኤልን በዘላለማዊ መድኃኒት ያድነዋል፥ እናንተም ለዘላለም አታፍሩምና አትዋረዱም። 18 ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፥ እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም። 19 በስውር ወይም በጨለማ ምድር ስፍራ አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብ ዘር። በከንቱ ፈልጉኝ አላልሁም፤ እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ ቅንንም አወራለሁ። 20 እናንተ ከአሕዛብ ወገን ሆናችሁ ያመለጣችሁ፥ ተሰብስባችሁ ኑ በአንድነትም ቅረቡ፤ የተቀረጸውን የምስላቸውን እንጨት የሚሸከሙና ያድን ዘንድ ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ እውቀት የላቸውም። 21 ይናገሩ ይቅረቡም በአንድነትም ይማከሩ፤ ከጥንቱ ይህን ያሳየ ከቀድሞስ የተናገረ ማን ነው? ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ፥ ከእኔም በቀር ማንም የለም። 22 እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ። 23 ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፥ አትመለስም። ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፥ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ። 24 ስለ እኔም። በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፥ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፥ በእርሱም ላይ የተቈጡ ሁሉ ያፍራሉ። 25 የእስራኤልም ዘር ሁሉ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፥ ይመካሉም ይባላል።

ኢሳይያስ 46

1 ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል። 2 ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ፤ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፥ ራሳቸው ግን ተማረኩ። 3 እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ፥ ስሙኝ። 4 እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ። 5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ? 6 ወርቁን ከኮረጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፥ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራ ዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል። 7 በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፥ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም። 8 ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ። 9 እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። 10 በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። 11 ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራዋለሁ። ተናግሬአለሁ፤ እፈጽማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ። 12 እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፤ 13 ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።

ኢሳይያስ 47

1 አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ ቅልጣናምና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ። 2 ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፤ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣዪው፤ ባትሽን ግለጪ፥ ወንዙን ተሻገሪ። 3 ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፤ እኔ እበቀላለሁ፥ ለማንም አልራራም። 4 ታዳጊያችን፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ ነው። 5 የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ። የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ። 6 በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር ርስቴንም አረከስሁ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፥ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል። 7 አንቺም። እኔ ለዘላለም እመቤት እሆናለሁ ብለሻል፤ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም። 8 አሁንም አንቺ ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጪ፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ መበለትም ሆኜ አልኖርም የወላድ መካንነትንም አላውቅም የምትዪ ይህን ስሚ፤ 9 አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች፥ የወላድ መካንነትና መበለትነት፥ በድንገት ይመጡብሻል፤ ስለ መተቶችሽ ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል። 10 በክፋትሽ ታምነሻል፤ የሚያየኝ የለም ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል። 11 ስለዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፥ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤ ጉዳት ይውድቅብሻል ታስወግጅውም ዘንድ አይቻልሽም፤ የማትውቂያትም ጕስቍልና ድንገት ትመጣብሻለች። 12 ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደ ሆነ፥ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ። 13 በምክርሽ ብዛት ደክመሻል፤ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፥ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፥ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ። 14 እነሆ፥ እንደ እብቅ ይሆናሉ፥ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፤ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፍም፥ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ያለ አይደለም። 15 የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፥ የሚያድንሽም የለም።

ኢሳይያስ 48

1 እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ 2 በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ። 3 የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል አሳይቼውማለሁ፤ ድንገት አድርጌዋለሁ ተፈጽሞማል። 4 አንተ እልከኛ፥ አንገትህም የብረት ጅማት፥ ግምባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፤ 5 ስለዚህ፥ አንተ። ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር ሳይሆንም አሳይቼህ ነበር። 6 ሰምተሃል፤ ይህን ሁሉ ተመልከት፤ እናንተም የምትናገሩት አይደላችሁምን? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲሶች ነገሮችን ከዚህ ጀምሬ አሳይቼሃለሁ። 7 እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም ። እነሆ፥ አውቄአቸዋለሁ እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። 8 አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደ ሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደተጠራህ አውቄአለሁና። 9 ስለ ስሜ ቍጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳላጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ። 10 እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። 11 ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና፤ ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም። 12 ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። 13 እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። 14 እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። 15 እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። 16 ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። 17 ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። 18 ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ 19 ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። 20 ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ ይህንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና። እግዚአብሔር ባሪያውን ያዕቆብን ታድጎታል በሉ። 21 በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። 22 ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 49

1 ደሴቶች ሆይ፥ ስሙኝ፥ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ከማኅፀን ጠርቶኛል፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንሥቶአል፤ 2 አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፥ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፤ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፥ በሰገባውም ውስጥ ሽጎኛል። 3 እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ አለኝ። 4 እኔ ግን። በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጕልበቴን ፈጀሁ፤ ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው አልሁ። 5 አሁንም በእግዚአብሔር ዓይን ከብሬአለሁና፥ አምላኬም ጕልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ የሠራኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 6 እርሱም። የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመስል ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል። 7 የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች ለሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዥዎች ባሪያ እንዲህ ይላል። ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ። 8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፥ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፥ 9 የተጋዙትንም። ውጡ በጨለማም የተቀመጡትን። ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በወና ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል። 10 የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም። 11 ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ። 12 እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ። 13 እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ። 14 ጽዮን ግን። እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። 15 በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። 16 እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ። 17 ልጆችሽ ይፈጥናሉ፤ ያፈረሱሽና ያወደሙሽ ከአንቺ ዘንድ ይወጣሉ። 18 ዓይንሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። 19 ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉና። 20 የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ። ስፍራ ጠብቦኛልና እቀመጥ ዘንድ ቦታ አስፊልኝ ይላሉ። 21 አንቺም በልብሽ፥ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝበዤ አለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ። 22 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓለማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። 23 ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። 24 በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን? 25 እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል። በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፥ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፤ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁ። 26 አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።

ኢሳይያስ 50

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናታችሁን የፈታሁበት የፍችዋ ጽሕፈት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥሁ ከአበዳሪዎች ለየትኛው ነው? እነሆ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ተሽጣችኋል፥ ስለ በደላችሁም እናታችሁ ተፈትታለች። 2 በመጣሁስ ጊዜ ሰው ስለ ምን አልነበረም? በጠራሁስ ጊዜ የሚመልስ ስለ ምን አልነበረም? መታደግ እንዳትችል እጄ አጭር ሆናለችን? ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝምን? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ውኃም በማጣት ዓሦቻቸው ይገማሉ በጥማትም ይሞታሉ። 3 ሰማያትን ጥቍረት አለብሳቸዋለሁ፥ መጋረጃቸውንም ማቅ አደርጋለሁ። 4 የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል። 5 ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም። 6 ጀርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፥ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። 7 ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና ስለዚህ አልታወክሁም፤ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፥ እንዳላፍርም አውቃለሁ። 8 የሚያጸድቀኝ ቅርብ ነው፤ ከእኔስ ጋር የሚከራከር ማን ነው? በአንድነት እንቁም፤ የሚከራከረኝ ማን ነው? ወደ እኔ ይቅረብ። 9 እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፤ ማን ይፈርድብኛል? እነሆ፥ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ ብልም ይበላቸዋል። 10 ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ፥ በጨለማም የሚሄድ፥ ብርሃንም የሌለው፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም የሚታመን፥ በአምላኩም የሚደገፍ ማን ነው? 11 እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ የእሳትንም ወላፈን የምትታጠቁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ነበልባል ባነደዳችሁትም ወላፈን ሂዱ፤ ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል፤ በኀዘን ትተኛላችሁ።

ኢሳይያስ 51

1 እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጕድጓድ ተመልከቱ። 2 ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም። 3 እግዚአብሔርም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርስዋም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፥ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔደን በረሀዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል። 4 ወገኔ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። 5 ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፥ ማዳኔም ወጥቶአል፥ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፥ በክንዴም ይታመናሉ። 6 ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም። 7 ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ። 8 እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፥ እንደ በግ ጠጕርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል። 9 የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፥ ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን? 10 ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅኸው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጠሊቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን? 11 እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። 12 የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? 13 ሰማያትንም የዘረጋው ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቍጣ የት አለ? 14 ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጕድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም። 15 ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 16 ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፥ ጽዮንንም። አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ። 17 ከእግዚአብሔር እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል። 18 ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። 19 እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? 20 ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደተያዘ ሚዳቋ በአደባባይ ሁሉ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በእግዚአብሔር ቍጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል። 21 ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ 22 ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። 23 ነፍስሽንም። እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው።

ኢሳይያስ 52

1 ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ። 2 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፥ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፥ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ። 4 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፥ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው። 5 ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ስሜም ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ይሰደባል። 6 ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፥ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፤ እነሆ፥ እኔ ነኝ። 7 የምስራች የሚናገር፥ ሰላምንም የሚያወራ፥ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፥ መድኃኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም። አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው። 8 እነሆ፥ ጕበኞችሽ ጮኸዋል፤ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። 9 እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፥ በአንድነትም ዘምሩ። 10 እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ። 11 እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንጽሐን ሁኑ። 12 እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም። 13 እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል። 14 ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤ 15 ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።

ኢሳይያስ 53

1 የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? 2 በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። 3 የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። 4 በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። 5 እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። 6 እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። 7 ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። 8 በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? 9 ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር። 10 እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። 11 ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። 12 ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።

ኢሳይያስ 54

1 አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር። 2 የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። 3 በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። 4 አታፍሪምና አትፍሪ፤ አተዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም። 5 ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል። 6 እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ። 7 ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ። 8 በጥቂት ቍጣ ለቅጽበት ዓይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፥ በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር። 9 ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፥ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ። 10 ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር። 11 አንቺ የተቸገርሽ በዐውል ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። 12 የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። 13 ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። 14 በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም። 15 እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ። 16 እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ። 17 በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 55

1 እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። 2 ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። 3 ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፤ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። 4 እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ። 5 እነሆ፥ የማታውቀውን ሕዝብ ትጠራለህ፥ የእስራኤልም ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ ወደ አንተ ይሮጣሉ። 6 እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ 7 ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ። 8 አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር። 9 ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው። 10 ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ 11 ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። 12 እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፥ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። 13 በእሾህም ፋንታ ጥድ በኩርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ ለእግዚአብሔርም መታሰቢያን ለዘላለምም የማይጠፋ፥ ምልክት ይሆናል።

ኢሳይያስ 56

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ ጽድቅንም አድርጉ። 2 ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ፥ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። 3 ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ። በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል አይበል፤ ጃንደረባም። እነሆ፥ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ አይበል። 4 እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። 5 በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ። 6 ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፥ 7 ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ። 8 ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር። ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስብለታለሁ ይላል። 9 እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ፥ እናንተም የዱር አራዊት ሁሉ፥ ትበሉ ዘንድ ቅረቡ። 10 ጕበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉ ያለ እውቀት ናቸው፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፤ ሕልምን ያልማሉ፤ ይተኛሉ፤ ማንቀላፋትንም ይወድዳሉ። 11 መብል ወዳጆች ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፥ እነርሱም ያስተውሉ ዘንድ የማይችሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉ ወደ መንገዳቸው፥ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ፥ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል። 12 ኑ የወይን ጠጅ እንውሰድ፥ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፤ ዛሬም እንደ ሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፥ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል ይላሉ።

ኢሳይያስ 57

1 ጻድቅ ይሞታል፥ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም። 2 ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። 3 እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአመንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። 4 በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? 5 እናንተ በአድባር ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? 6 በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን? 7 ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። 8 ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። 9 ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። 10 በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን። ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጕልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። 11 ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሺው በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። 12 እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረባሽም። 13 ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። 14 እርሱም። ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አውጡ ይላል። 15 ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል። የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። 16 መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። 17 ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቈጥቼ ቀሠፍሁት፥ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፤ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ። 18 መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፥ እመራውማለሁ፥ ለእርሱና ስለ እርሱም ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ። 19 የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 20 ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና። 21 ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።

ኢሳይያስ 58

1 በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር። 2 ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። 3 ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። 4 እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። 5 እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? 6 እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? 7 እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? 8 የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። 9 የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም። እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ 10 ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። 11 እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። 12 ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም። ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። 13 ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ 14 በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።

ኢሳይያስ 59

1 እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም፤ 2 ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። 3 እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። 4 በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል፤ 5 የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። 6 ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። 7 እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። 8 የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፤ መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም። 9 ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፤ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፤ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን። 10 እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዓይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን። 11 ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን፤ ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱም የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል። 12 ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። 13 ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። 14 ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና። 15 እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ። 16 ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። 17 ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። 18 እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል። 19 እርሱ የእግዚአብሔር ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። 20 ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 21 ከእርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፥ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 60

1 ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። 2 እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ 3 አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። 4 ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። 5 በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። 6 የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ። 7 የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። 8 ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? 9 እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል። 10 በቍጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል። 11 በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም። 12 ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ። 13 የመቅደሴንም ስፍራ ያስጌጡ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው ባርሰነቱም፥ ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ። 14 የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል። 15 ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ። 16 የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የያዕቆብ ኃይል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 17 በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤ 18 ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ 19 ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም፥ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አይበራልሽም። 20 እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም ጨረቃሽም አይቋረጥም። 21 ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ። 22 ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።

ኢሳይያስ 61

1 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። 2 የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፤ 3 እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። 4 ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ። 5 መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይም ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። 6 እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፥ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በክብራቸውም ትመካላችሁ። 7 በእፍረታችሁ ፋንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፥ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፈንታችሁ ደስ ይላቸዋል፤ ስለዚህ በምድራቸው ሁሉ እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘላለምም ደስታ ይሆንላቸዋል። 8 እኔ እግዚአብሔር ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ፤ ፍዳቸውንም በእውነት እሰጣቸዋለሁ፥ ከእነርሱም ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ። 9 ዘራቸውም በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ እግዚአብሔር የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ይገነዘባል። 10 አክሊልን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማትዋም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች። 11 ምድርም ቡቃያዋን እንደምታወጣ፥ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፥ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል።

ኢሳይያስ 62

1 ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም፥ ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ። 2 አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። 3 በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። 4 ከእንግዲህ ወዲህ። የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ። ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ። ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም። ባል ያገባች ትባላለች። 5 ጕልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል። 6-7 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጕበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፥ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ። 8 እግዚአብሔር። ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤ 9 ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሎአል። 10 እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጐዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓለማ አንሡ። 11 እነሆ፥ እግዚአብሔር ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል። ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት። 12 እግዚአብሔር። የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም። የተፈለገች ያልተተወችም ከተማ ትባያለሽ።

ኢሳይያስ 63

1 ይህ ከኤዶምያስ፥ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፥ አለባበሱ ያማረ፥ በጕልበቱ ጽናት የሚራመድ ማን ነው? በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ። 2 ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ? 3 መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፥ ልብሴንም ሁሉ አስድፌአለሁ። 4 የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና። 5 ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ። 6 በቍጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት። 7 እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ። 8 እርሱም። በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። 9 በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። 10 እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው። 11 እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ። የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ? 12 የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ 13 በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ ዕንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? 14 ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። 15 ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ። 16 አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው። 17 አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ። 18 የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል። 19 ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል።

ኢሳይያስ 64

1 ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! 2 እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ። 3 ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። 4 ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም። 5 ጽድቅን የሚያደርገውን በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ። እነሆ፥ እነተ ተቈጣህ እኛም ኃጢአት ሠራን፤ ስለዚህም ተሳሳትን። 6 ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። 7 ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል። 8 አሁን ግን፥ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። 9 አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘላለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፥ እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። 10 የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። 11 አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፥ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል። 12 አቤቱ፥ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን?

ኢሳይያስ 65

1 ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት። 2 መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ። 3 ይህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥ 4 በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ በስውርም ስፍራ የሚያድሩ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የረከሰው መረቅ በዕቃቸው ውስጥ አለ። 5 እነርሱም። ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው። 6 እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል። ኃጢአታችሁና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ አመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 7 በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ። 8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ። በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፉ ስለባሪያዎቼ እንዲሁ አደርጋለሁ። 9 ከያዕቆብ ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኋቸው ይወርሱአታል፥ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ። 10 ሳሮንም የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮርም ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ለፈልጉኝ ሕዝቤ ይሆናል። 11 እናንተን ግን እግዚአብሔርን የተዋችሁትን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ጉድ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን የቀዳችሁትን፥ 12 እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና። 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ 14 እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ። 15 ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። 16 እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፥ ከዓይኔም ተሰውሮአልና። 17 እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም። 18 ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። 19 እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። 20 ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጕልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። 21 ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። 22 ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። 23 እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም። 24 እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ አመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ። 25 ተኵላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፥ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኢሳይያስ 66

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? 2 እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። 3 በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤ 4 እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና። 5 በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። የጠሉአችሁ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ ወንድሞቻችሁ። ደስታችሁን እናይ ዘንድ እግዚአብሔር ይክበር ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ። 6 የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል። 7 ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። 8 ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። 9 በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ አላስወልድምን? ይላል እግዚአብሔር፤ የማስወልድስ ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ። 10 እናንተ የምትወድዱአት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፥ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፥ 11 ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናትዋም ጡት ትጠግቡ ዘንድ፤ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጕልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሉአችኋል። 13 እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። 14 ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል። 15 እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። 16 እግዚአብሔርም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በእግዚአብሔርም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ። 17 በመካከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ ገነቱ ይገቡ ዘንድ ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቄአለሁና፤ አሕዛብንና ልሳናትን ሁሉ የምሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፥ እነርሱም ይመጣሉ ክብሬንም ያያሉ። 19 በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ ወደ ፉጥ ወደ ሉድ ወደ ሞሳሕ ወደ ቶቤል ወደ ያዋን በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፥ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። 20 የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 21 ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 22 እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 23 እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 24 ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።

ኤርምያስ 1

1 በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃል። 2 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን በመንግሥቱ በአሥራ ሦስተኛው ዓመት የእግዚአብሔር ቃል መጣለት። 3 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 5 በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። 6 እኔም። ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ። 7 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ። ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና። ብላቴና ነኝ አትበል። 8 እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም። እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ 10 እነሆ። ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ። 11 ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል። ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ። 12 እግዚአብሔርም። እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ። 13 ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል። ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም። የሚፈላ አፍላል አያለሁ፥ ፊቱም ከሰሜን ወገን ነው አልሁ። 14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይገለጣል። 15 እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋ በቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። 16 ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተው ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 17 አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህም ሁሉ ንገራቸው፤ በፊታቸው እንዳላስፈራህ አትፍራቸው። 18 እነሆ፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ። 19 ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 2

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮ ጩኽ፥ እንዲህም በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የብላቴንነትሽን ምሕረት የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ። 3 እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረ፥ የቡቃያውም በkWraት ነበረ፤ የበሉት እንደ በደለኞች ይቈጠራሉ፥ ክፉም ነገር ያገኛቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 የያዕቆብ ቤት የእስራኤልም ቤት ወገኖች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁ ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ ከንቱነትንም የተከተሉ፥ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው? 6 እነርሱም። ከግብጽ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳም በባድማ gWdጓድም ባለበት ምድር፥ በውኃ ጥምና በሞት ጥላ ምድር፥ ማንም በማያልፍበትና ማንም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም። 7 ፍሬዋንና በረከትዋንም ትበሉ ዘንድ ወደ ፍሬያማ ምድር አገባኋችሁ፤ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ፥ ርስቴንም አጐሳቈላችሁ። 8 ካህናቱም። እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም፥ ባለ ኦሪቶችም አላወቁኝም፤ ገዢዎችም ዐመፁብኝ፥ ነቢያትም በበኣል ትንቢት ተናገሩ፥ የማይረባንም ነገር ተከተሉ። 9 ስለዚህ ከእናንተ ጋር እከራከራለሁ፥ ከልጆቻችሁም ልጆች ጋር እከራከራለሁ። 10 ወደ ኪቲም ደሴቶች እለፉና ተመልከቱ፥ ወደ ቄዳርም ላኩና እጅግ መርምሩ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ህኖ እንደ ሆነ እዩ። 11 በውኑ አማልክት ያልሆኑትን አማልክቱን የለወጣቸው አንድ ሕዝብ አለን? ነገር ግን ሕዝቤ ክብሩን ለማይረባ ነገር ለወጠ። 12 ሰማያት ሆይ፥ በዚህ ተደነቁ፥ እጅግም ደንግጡና ተንጥቀጡ ይላል እግዚአብሔር። 13 ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም gWdጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን gWdጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል። 14 በውኑ እስራኤል ባሪያ ነውን? ወይስ የቤት ውላጅ ነውን? ስለምን ብዝበዛ ሆነ? 15 የአንበሳ ደቦሎች በእርሱ ላይ አገሡ፥ ድምፃቸውንም ሰጡ፤ ምድሩንም ባድማ አደረጉ፥ ከተሞቹም ተቃጠሉ የሚቀመጥባቸውም የለም። 16 የሜምፎስና የጣፍናስ ልጆች አስነወሩሽ አላገጡብሽም። 17 ይህ ሁሉ የሆነብሽ እኔን ስለ ተውሽ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር አምላክሽ። 18 አሁንስ የሺሖርን ውኃ ትጠጪ ዘንድ በግብጽ መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? የኤፍራጥስንም ውኃ ትጠጪ ዘንድ በአሦር መንገድ ምን ጉዳይ አለሽ? 19 ክፋትሽ ይገሥጽሻል ክዳትሽም ይዘልፍሻል፤ አምላክሽንም እግዚአብሔርን የተውሽ እኔንም መፍራት የሌለብሽ ክፉና መራራ ነገር እንደ ሆነ እወቂ፥ ተመልከቺ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 20 ከጥንት ጀምሮ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም። አላገለግልም አልሽ፥ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ። 21 እኔ የተመረጠች ወይን ፍጹምም እውነተኛ ዘር አድርጌ ተክዬሽ ነበር፤ አንቺ ግን ክፉ የእንግዳ ወይን ግንድ ሆነሽ እንዴት ተለወጥሽብኝ? 22 በእንዶድ ብትታጠቢም፥ ለራስሽም ሳሙና ብታበዢ፥ በእኔ ፊት በኃጢአትሽ ረክሰሻል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 23 አንቺስ። አልረከስሁም በአሊምንም አልተከተልሁም እንዴት ትያለሽ? በቈላ ያለውን መንገድሽን ተመልከቺ፥ ያደረግሽውንም እወቂ፤ በመንገድም ላይ እንደ ተለቀቀች እንደ ፈጣን ግመል ሆነሻል፤ 24 በምኞትዋ ነፋስን እንደምታሸትት፥ በምድረ በዳ እንደ ለመደች እንደ ሜዳ አህያ ነሽ፤ ከምኞትዋ የሚመልሳት ማን ነው? የሚሹአት ሁሉ አይደክሙም፥ በወራትዋ ያገኙአታል። 25 እግርሽን ከሸካራ መንገድ gWroሮሽንም ከውኃ ጥም ከልክዪ፤ አንቺ ግን። እጨክናለሁ፥ እንግዶችን ወድጄአለሁና፥ እከተላቸዋለሁም አልሽ። 26 ሌባ በተያዘ ጊዜ እንደሚያፍር እንዲሁ የእስራኤል ቤት፥ እነርሱና ንጉሦቻቸውም አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም ያፍራሉ። 27 ግንዱን።አንተ አባቴ ነህ፤ ድንጋዮንም። አንተ ወለድኸኝ ይላሉ፤ ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ሰጡኝ፥ በመከራቸው ጊዜ ግን። ተነሥተህ አድነን ይላሉ። 28 ለአንተ የሠራሃቸው አማልክትህ ወዴት ናቸው? ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ KWTር እንዲሁ ናቸውና ይነሡ በመከራህም ጊዜ ያድኑህ። 29 ከእኔ ጋር የምትከራከሩ ለምንድር ነው? ሁላችሁ ዐምፃችሁብኛል ይላል እግዚአብሔር። 30 ልጆቻችሁን በከንቱ ቀሥፌአቸዋለሁ፤ ተግሣጽን አልተቀበሉም፤ ሰይፋችሁ እንደሚሰብር አንበሳ ነቢያቶቻችሁን በልቶአል። 31 ትውልድ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ተመልከቱ። በውኑ ለእስራኤል ምድረ በዳ ወይስ የጨለመች ምድር ሆንሁባትን? ሕዝቤስ ስለ ምን። እኛ ፈርጥጠናል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ አንመለስም ይላል? 32 በውኑ ቆንጆ ጌጥዋን ወይስ ሙሽራ ዝርግፍ ጌጥዋን ትረሳለችን? ሕዝቤ ግን የማይቈጠር ወራት ረስቶኛል። 33 ፍቅርን ለመሻት መንገድሽን እንዴት ታቀኛለሽ! ስለዚህ ለክፉዎች ሴቶች እንኳ መንገድሽን አስተምረሻል። 34 በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል፤ በእነዚህ ሁሉ ላይ በግልጥ አገኘሁት እንጂ በስውር ፈልጌ አላገኘሁትም። 35 አንቺ ግን። ንጹሕ ነኝ፤ በእውነት KWTaው ከእኔ ተመልሶአል አልሽ። እነሆ። ኃጢአት አልሠራሁም ብለሻልና በፍርድ እከስስሻለሁ። 36 መንገድሽን ትለውጪ ዘንድ ለምን እጅግ ትሮጫለሽ? አሦር እንዳሳፈረሽ ግብጽ ያሳፍርሻል። 37 እግዚአብሄር የታመንሽባቸውን ጥሎአልና፥ በእነርሱም አይከናወንልሽምና እጅሽን በራስሽ ላይ አድርገሽ ከዚያ ደግሞ ትወጫለሽ። a

ኤርምያስ 3

1 በሰው ዘንድ። ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። 2 ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። 3 ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የኋለኛውም ዝናብ ጠፋ፤ የጋለሞታም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ ታፍሪም ዘንድ እንቢ ብለሻል። 4 አሁንም። አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ ብለሽ አልጮኽሽልኝምን? ለዘላለም ይቈጣልን? 5 እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ። 6 እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ። ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም ጋለሞተች። 7 ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ። ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ነገር ግን አልተመለሰችም፤ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። 8 ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፤ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርስዋም ደግሞ ሄዳ እንደ ጋለሞተች አየሁ። 9 በግልሙትናዋም በመቅለልዋም ምድሪቱ ረከሰች፤ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። 10 በዚህም ሁሉ አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም። 11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። 12 ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል። ከዳተናይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥ ይላል እግዚአብሔር። 13 በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል እግዚአብሔር። 14 ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ እኔ ባላችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል እግዚአብሔር፤ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤ 15 እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። 16 በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። 17 በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። 18 በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፤ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ። 19 እኔ ግን። ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አደርግሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር የከበረችውን የአሕዛብን ሠራዊት ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ። አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር። 20 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሚስት ባልዋን እንደምታታታልል እንዲሁ አታለላችሁኝ ይላል እግዚአብሔር። 21 የእስራኤል ልጆች መንገዳቸውን አጣምመዋልና፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተዋልና በወናዎች ኮረብቶች ላይ የልመናቸውና ልቅሶአቸው ድምፅ ተሰማ። 22 ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከዳተኛነታችሁንም እፈውሳለሁ። እነሆ፥ አንተ አምላካችን እግዚአብሔር ነህና ወደ አንተ እንመጣለን። 23 በእውነት የኮረብቶችና የተራሮች ፍጅት ከንቱ ናት፤ በእውነት የእስራኤል መዳን በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 24 ነገር ግን ከትንሽነታችን ጀምሮ የአባቶቻችን ድካም፥ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም፥ እፍረት በልቶባቸዋል። 25 ከትንሽነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኛና አባቶቻችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተናልና፥ የአምላካችንንም የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና በእፍረታችን እንጋደም፥ ውርደታችንም ይክደነን።

ኤርምያስ 4

1 እስራኤል ሆይ፥ ብትመለስ፥ ወደ እኔ ተመለስ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ርkWsvትህንም ከፊቴ ብታስወግድ፥ ባትናወጥም፥ 2 ሕያው እግዚአብሔርን! ብለህም በእውነትና በቅንነት በጽድቅም ብትምል፥ አሕዛብ በእርሱ ይባረካሉ በእርሱም ይመካሉ። 3 እግዚአብሔር ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሰዎች እንዲህ ይላልና። ጥጋቱን እርሻ እረሱ በእሾህም ላይ አትዝሩ። 4 እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት KWTaዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ። 5 በይሁዳ ዘንድ ተናገሩ በኢየሩሳሌምም ላይ አውሩና። በአገሪቱ ላይ መለከት ንፉ በሉ፤ ጮኻችሁም። ሁላችሁ ተሰብሰቡ ወደ ተመሸጉትም ከተሞች እንግባ በሉ። 6 ከሰሜን ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁና ወደ ጽዮን ዓላማን አንሡ፤ ሽሹ፥ አትዘግዩ። 7 አንበሳ ከጭፍቅ ዱር ወጥቶአል፥ አሕዛብንም የሚዘርፍ ተነሥቶአል፤ ምድርሽን ባድማ ያደርግ ዘንድ ከስፍራው ወጥቶአል፥ ከተሞችሽም ሰው የሌለባቸው ፍርስራሾች ይሆናሉ። 8 የእግዚአብሔር ጽኑ KWTa ከእኛ ዘንድ አልተመለሰምና ማቅ ልበሱ፥ አልቅሱም ዋይም በሉ። 9 በዚያም ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የንጉሡና የመኳንንቱ ልብ ይጠፋል፥ ካህናቱም ይደነቃሉ ነቢያቱም ይደነግጣሉ። 10 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ፥ አንተ ሰይፍ እስከ ነፍስ ድረስ በደረሰ ጊዜ። ሰላም ይሆንላችኋል ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን እጅግ አታለልህ አልሁ። 11 በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም። ለማበጠር ወይም ለማጥራት ሳይሆን የሚያቃጥል ነፋስ በምድረ በዳ ካሉ ከወናዎች ኮረብቶች ወደ ወገኔ ሴት ልጅ ይመጣል፤ 12 ስለ እኔ ጽኑ የሆነ ነፋስ ከእነዚህ ይመጣል ይባላል። አሁንም እኔ ደግሞ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 13 እነሆ፥ እንደ ደመና ይወጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ፤ ፈረሶቹም ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው። ጠፍተናልና ወዮልን። 14 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትድኚ ዘንድ ልብሽን ከክፉ ነገር እጠቢ። ክፉ አሳብ የሚኖርብሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? 15 የተናጋሪ ድምፅ ከዳን ዘንድ ይናገራልና፥ ከኤፍሬምም ኮረብቶች መከራን ያወራልና። 16 ለአሕዛብ አሰሙና። እነሆ፥ ጠባቂዎች ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤ በይሁዳም ከተሞች ላይ ይጮኻሉ ብላችሁ በኢየሩሳሌም ላይ አውሩ። 17 በእኔ ላይ ዓመፀኛ ሆናለችና በዙሪያዋ ከብበው እንደ እርሻ ጠባቂዎች ሆነውባታል፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 መንገድሽና ሥራሽ ይህን አድርጎብሻል፤ ይህ ክፋትሽ መራር ነው፥ ወደ ልብሽም ደርሶአል። 19 አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም። 20 መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል፤ ምድርም ሁሉ ተበዝብዛለችና፤ በድንገትም ድንኳኔ በቅጽበት ዓይንም መጋረጃዎቼ ጠፉ። 21 ዓላማውን የምመለከት፥ የመለከቱንስ ድምፅ የምሰማ እስከ መቼ ነው? 22 ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም፤ ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም። 23 ምድሪቱን አየሁ፥ እነሆም፥ ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም፤ ሰማያትንም አየሁ፥ ብርሃንም አልነበረባቸውም። 24 ተራሮችን አየሁ፥ እነሆም፥ ተንቀጠቀጡ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ተናወጡ። 25 አየሁ፥ እነሆም፥ ሰው አልነበረም፥ የሰማይም ወፎች ሁሉ ሸሽተው ነበር። 26 አየሁ፥ እነሆም፥ ፍሬያማ እርሻ ምድረ በዳ ሆነች፥ ከተሞችም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ከጽኑ KWTaው የተነሣ ፈርሰው ነበር። 27 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ባድማ ትሆናለች፥ ነገር ግን ፈጽሜ አላጠፋትም። 28 ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች፥ በላይም ሰማይ ይጠKWraል፤ ተናግሬአለሁና፥ አስቤአለሁም፤ አልጸጸትም ከእርሱም አልመለስም። 29 ከፈረሰኞችና ከቀስተኞች ድምፅ የተነሣ ከተማ ሁሉ ሸሽታለች፤ ወደ ችፍግ ዱርም ይገባሉ በቋጥኝ ላይም ይወጣሉ፤ ከተማ ሁሉ ተለቅቃለች የሚቀመጥባትም ሰው የለም። 30 አንቺም የተበዘበዝሽ ሆይ፥ ምን ታደርጊአለሽ? ቀይ በለበስሽ ጊዜ፥ በወርቅ አንባርም ባጌጥሽ ጊዜ፥ ዓይንሽንም በkWl በተኳልሽ ጊዜ፥ በከንቱ ታጌጫለሽ፤ ውሽሞችሽ አቃለሉሽ፥ ነፍስሽን ይሹአታል። 31 እንደምታምጥ የበkWrዋንም እንደምትወልድ ሴት ድምፅ ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ይሰልላል፥ እጆችዋንም ትዘረጋለችና። ተገድለው ከሞቱት የተነሣ ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ! አለች።

ኤርምያስ 5

1 በኢየሩሳሌም መንገድ እየተመላለሳችሁ ሩጡ፥ ተመልከቱም፥ እወቁም፥ በአደባባይዋም ፈልጉ፤ ፍርድን የሚያደርገውን እውነትንም የሚሻውን ሰው ታገኙ እንደሆነ ይቅር እላታለሁ። 2 እነርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ቢሉ የሚምሉት በሐሰት ነው። 3 አቤቱ፥ ዓይንህ እውነትን የምትመለከት አይደለችምን? አንተ ቀሥፈሃቸዋል ነገር ግን አላዘኑም፥ ቀጥቅጠሃቸውማል ነገር ግን ተግሣጽን እንቢ አሉ፤ ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠንክረዋል፤ ይመለሱ ዘንድ እንቢ አሉ። 4 እኔም። የእግዚአብሔርን መንገድና የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና እነዚህ በእውነት ድሆችና ሰነፎች ናቸው፤ 5 ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ እናገራቸውማለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንገንድና የአምላካቸውን ሕግ ያውቃሉና አልሁ። እነዚህ ግን ቀንበሩን በአንድነት ሰብረዋል፥ እስራቱንም ቈርጠዋል። 6 ስለዚህ ኃጢአታቸው በዝቶአልና፥ የክዳታቸውም ብዛት ጸንቶአልና ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰብራቸዋል፥ የበረሀም ተkWla ያጠፋቸዋል፥ ነብርም በከተሞቻቸው ላይ ይተጋል፥ ከዚያም የሚወጣ ሁሉ ይነጠቃል። 7 በእነዚህ ነገሮች ይቅር የምልሽ እንዴት አድርጌ ነው? ልጆችሽ ትተውኛል አማልክትም ባልሆኑ ምለዋል፤ ካጠገብኋቸውም በኋላ አመነዘሩ በጋለሞቶቹም ቤት ተሰበሰቡ። 8 እንደ ተቀለቡ ፈረሶች ሆኑ፤ እያንዳንዳቸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ኋላ አሽካኩ። 9 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 10 ወደ ቅጥርዋ ወጥታችሁ አፍርሱ፥ ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉ፤ ለእግዚአብሔር አይደሉምና ቅርንጫፍዋን ውሰዱ። 11የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት በእኔ ላይ እጅግ ወንጅለዋል ይላል እግዚአብሔር። 12 እነርሱም። እርሱ አይደለም፥ ክፉ ነገርም አይመጣብንም ሰይፍንና ራብንም አናይም፤ ነቢያትም ነፋስ ይሆናሉ፥ 13 የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ የለም፥ እንዲህም ይደረግባቸዋል ብለው እግዚአብሔርን ክደዋል። 14 ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ቃል ተናግራችኋልና እነሆ፥ በአፍህ ውስጥ ቃሌን እሳት ይህንም ሕዝብ እንጨት አደርጋለሁ፥ ትበላቸውማለች። 15 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ ሕዝብን ከሩቅ አመጣባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃያል ጥንታዊ ሕዝብ ነው፥ ቋንቋቸውንም የማታውቀው የሚናገሩትንም የማታስተውለው ሕዝብ ነው። 16 የፍላጻቸውም ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ ሁሉም ኃያላን ናቸው። 17 መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም ይበላሉ፤ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችን በሰይፍ ይደበድባሉ። 18 ነገር ግን በዚያ ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈጽሜ አላጠፋችሁም። 19 እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ። አምላካችን እግዚአብሔር ይህን ነገር ሁሉ ስለምን አደረገብን? ብትሉ፥ አንተ። እንደ ተዋችሁኝ በአገራችሁም ሌሎችን አማልክት እንዳመለካችሁ፥ እንዲሁ ለእናንተ ባልሆነ አገር ለሌሎች ሰዎች ትገዛላችሁ ትላቸዋለህ። 20 ይህን በያዕቆብ ቤት አውሩ፥ በይሁዳም አሰሙ። 21 እናንተ ሰነፎች ልበ ቢሶች፥ ዓይን እያላችሁ የማታዩ፥ ጆሮም እያላችሁ የማትሰሙ ሕዝብ ሆይ፥ ይህን ስሙ። 22 በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም። 23 ለዚህ ሕዝብ ግን የሸፈተና ያመፀ ልብ አላቸው፤ ዐምፀዋል ሄደውማል። 24 በልባቸውም። የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም። 25 በደላችሁ እነዚህን አስቀርታለች፥ ኃጢአታችሁም መልካምን ነገር ከለከለቻችሁ። 26 በሕዝቤ መካከል ክፉዎች ሰዎች ተገኝተዋል፤ እንደ አጥማጆችም ያደባሉ፥ ወጥመድንም ይዘረጋሉ ሰዎችንም ያጠምዳሉ። 27 ቀፎ ወፎችን እንደሚሞላ፥ እንዲሁ ቤታቸው ሽንገላን ሞልታለች፤እንዲሁም ከብረዋል ባለ ጠጎችም ሆነዋል። 28 ወፍረዋል ሰብተውማል፥ ክፋታቸውንም ያለ ልክ አብዝተዋል፤ የድሀ አደጎች ነገር መልካም እንዲሆን አልተምዋገቱላቸውም፥ የችግረኞችንም ፍርድ አልፈረዱላቸውም። 29 በውኑ ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 30 የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤ 31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?

ኤርምያስ 6

1 እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ። 2 የተዋበችውንና የተሰባቀለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሰቍላለሁ። 3 እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል። 4 በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን። 5 ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፥ አዳራሾችዋንም እናፍርስ። 6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ዛፎችዋን ቍረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው። 7 በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፥ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ። 8 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ። 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሙአቸዋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ። 10 ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም። 11 ስለዚህ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጕልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና። 12 እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 13 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና። 14 የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ሰላም ሰላም ይላሉ። 15 ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ። 17 እኔም። የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን። አናደምጥም አሉ። 18 አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ። 19 ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ። 20 ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም። 21 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ። 22 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 23 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። 24 ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል። 25 የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በምንገድም ላይ አትሂዱ። 26 የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ። 27 መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ። 28 እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኵሰትን ያደርጋሉ። 29 ወናፍ አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፤ ኃጢአተኞች አልተወገዱም። 30 እግዚአብሔር ጥሎአቸዋልና የተጣለ ብር ብለው ይጠሩአቸዋል።

ኤርምያስ 7

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር። እግዚአብሔርን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ አሳድራችኋለሁ። 4 የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ። 5 መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥ 6 መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥ 7 ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ። 8 እነሆ፥ በማትረቡበት በሐሰት ቃል ታምናችኋል። 9 ትሰርቃላችሁ፥ ትገድላላችሁ፥ ታመነዝራላችሁ፥ በሐሰትም ትምላላችሁ፥ ለበኣልም ታጥናላችሁ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁ፤ 10 መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ። ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም አላችሁ። 11 ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ። 13 አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ በማለዳም ተነሥቼ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ 14 ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ። 15 የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ። 16 እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው። 17 እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? 18 ያስቈጡኝ ዘንድ፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ። 19 እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን? 20 እንግዲህም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም። 21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለሌላ መሥዋዕታችሁ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ። 22 ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። 23 ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። 24 ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 25 አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። 26 ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ። 27 በዚህም ቃል ሁሉ ትነግራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም። 28 አንተም። የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ተቈርጦአል ትላቸዋለህ። 29 እግዚአብሔር የቍጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጕርሽን ቍረጪ፥ ጣዪውም፥ በወናዎች ኮረብቶችም ላይ አሙሺ። 30 የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል። 31 እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠረተዋል። 32 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከማጣት የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 33 የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም። 34 ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።

ኤርምያስ 8

1 በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቹን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ። 2 በወደዱአቸውና ባመለኩአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፤ አያከማቹአቸውም አይቀብሩአቸውምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ። 3 እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህች ክፉ ወገን የተረፉ ቅሬታዎች ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ። 4 እንዲህም ትላቸዋለሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን? 5 እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም እንቢ ብሎአል። 6 አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸውንም። ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። 7 ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም። 8 እናንተስ። ጥበበኞች ነን የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ የጸሐፊ ብርዕ ሐሰተኛ ነው በሐሰትም አድርጎአል። 9 ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው? 10 ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ። 11 የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ስለም ሰላም ይላሉ። 12 አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር 13 ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፤ የሚያልፉባቸውንም ሰጠኋቸው። 14 ዝም ብለን ለም እንቀመጣለን? እግዚአብሔርን ስለ በደልን አምላካችን እግዚአብሔር አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብስባችሁ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ። 15 ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ መጠገንን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። 16 የፈረሰኞቹ ድምጽ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። 17 እነሆ፥ አስማት የማይከለክላቸውን እባቦችንና እፉኝቶችን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል። 18 ኅዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል። 19 እነሆ። እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድር ነው? 20 መከሩ አልፎአል፥ በጋው ሄዶአል፥ እኛም አልዳንነም። 21 በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠKWreማለሁ፤ አድናቆትም ይዞኛል። 22 በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?

ኤርምያስ 9

1 ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! 2 ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? 3 ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ። 5 ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ። 6 ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ያውቁኝ ዘንድ እንቢ ብለዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸውማለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድር ነው? 8 ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል። 9 በውኑ ስለዚህ ነገር አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን? 10 ለተራሮች ልቅሶን ለምድረ በዳ ማሰማርያዎችም ዋይታን አነሣለሁ፥ ሰው እንዳያልፍባቸው በእሳት ተቃጥለዋልና። ሰዎችም የከብቱን ድምፅ አይሰሙም፤ ከሰማይ ወፎች ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። 11 ኢየሩሳሌምንም የፍርስራሽ ክምር የቀበሮም ማደሪያ አደርጋታለሁ፥ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይቀመጥባት ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 12 ይህን የሚያስተውል ጠቢብ ሰው ማን ነው? ያወራስ ዘንድ የእግዚአብሔር አፍ ለማን ተናገረ? ሰው እንዳያልፍባት ምድርስ ስለምን ጠፋች፥ እንደ ምድረ በዳስ ስለ ምን ተቃጠለች? 13 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ። የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተዋልና፥ ቃሌንም አልሰሙምና፥ 14 ነገር ግን የልባቸውን ምኞትና አባቶቻቸው ያስተማሩአቸውን በኣሊምን ተከትለዋልና 15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህን ሕዝብ እሬትን አበላዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ። 16 እነርሱና አባቶቻቸውም ባላወቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ በስተ ኋላቸው ሰይፍን እሰድድባቸዋለሁ። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲመጡ አልቃሾች ሴቶችን ጥሩ፤ እንዲመጡም ወደ ብልሃተኞች ሴቶች ላኩ፤ 18 ዓይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ የዓይናችንም ሽፋሽፍቶች ውኃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ይያዙ። 19 በጽዮን። እንዴት ተበዘበዝን! ምድርንም ትተናልና፥ ቤቶቻችንንም አፍርሰዋልና እንዴት አፈርን! የሚል የልቅሶ ድምፅ ተሰምቶአል። 20 እናንተ ሴቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጆሮአችሁም የአፉን ቃል ትቀበል፥ ለሴቶች ልጆቻችሁም ልቅሶውን፥ እያንዳንዳችሁም ለባልንጀሮቻችሁ ዋይታውን አስተምሩ። 21 ሕፃናቱን ከመንገድ ጕልማሶቹንም ከአደባባይ ያጠፉ ዘንድ ሞት ወደ መስኮታችን ደርሶአል ወደ አዳራሻችንም ውስጥ ገብቶአል። 22 የሰውም ሬሳ እንደ ጕድፍ በእርሻ ላይ፥ ማንምም እንደማይሰበስበው ከአጫጆች በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ ይወድቃል። 23 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ 24 ነገር ግን የሚመካው። ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር። 25-26 አሕዛብ ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና የተገረዙትን ሁሉ፥ ግብጽንና ይሁዳን ኤዶምያስንም የአሞንንም ልጆች ሞዓብንም በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጕራቸውን በዙሪያ የተላጩትን ሁሉ፥ ባለመገረዛቸው እነርሱን የምቀጣበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 10

1 እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና። 3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እንጅ በመጥረቢያ ይሠራል። 4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። 5 እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውማን ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው። 6 አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። 7 የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? 8 በአንድ ጊዜ ሰንፈዋል፥ ደንቍረውማል፤ ጣዖታት የሚያስተምሩት የእንጨት ነገር ብቻ ነው። 9 የሠራተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፤ ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። 10 እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። 11 እናንተም። ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ። 12 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 13 ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 14 ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 15 እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 16 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 17 በምሽግ ውስጥ የተቀመጥሽ ሆይ፥ ዕቃሽን ከመሬት ሰብስቢ፤ 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በምድሪቱ የሚኖሩትን እስኪሰማቸው ድረስ በዚህ ጊዜ እወነጭፋቸዋለሁ፥ አስጨንቃቸውማለሁ። 19 ስለ ስብራቴ ወዮልኝ! ቍስሌም ክፉ ነው፥ እኔ ግን። በእውነት የመከራ ቍስሌ ነው እርሱንም መሸከም ይገባኛል አልሁ። 20 ድንኳኔ ተበዘበዘ አውታሬም ሁሉ ተቈረጠ፤ ልጆቼም ከእኔ ወጥተው አይገኙም፤ ድንኳኔንም ከእንግዲህ ወዲህ የሚዘረጋ መጋረጃዎችንም የሚያነሣ የለም። 21 እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል። 22 የወሬን ድምፅ ስሙ፤ እነሆም፥ የይሁዳን ከተሞች ባድማና የቀበሮ ማደሪያ ያደርጋቸው ዘንድ ከሰሜን ምድር ጽኑ ሽብር መጥቶአል። 23 አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። 24 አቤቱ፥ ቅጣኝ፤ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቍጣ አይሁን። 25 ያዕቆብን በልተውታልና፥ ውጠውትማልና፥ አጥፍተውትማልና፥ ማደሪያውንም አፍርሰዋልና በማያውቁህ አሕዛብ ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ መዓትህን አፍስስ።

ኤርምያስ 11

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስማ፥ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገር፥ 3-4 እንደዚህም በላቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከግብጽ አገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፤ አልሁም። ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 5 ይህም ዛሬ እንደ ሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ የማልሁትን መሐላ አጸና ዘንድ ነው። እኔም። አቤቱ፥ አሜን ብዬ መለስሁለት። 6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፥ እንዲህም በል። የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ አድርጉትም። 7 አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ ተነሥቼ እያስጠነቀቅሁ። ቃሌን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር። 8 እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ አመጣሁባቸው። 9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዘንድ አድማ ተገኝቶአል። 10 ቃሌንም ይሰሙ ዘንድ እንቢ ወዳሉ ወደ አባቶቻቸው ኃጢአት ተመለሱ፥ ያመልኩአቸውም ዘንድ እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ። 11 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ፥ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔም አልሰማቸውም። 12 በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ይጮኻሉ፤ ነገር ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ አያድኑአቸውም። 13 ይሁዳ ሆይ፥ አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለነውረኛ ነገር መሠዊያ፥ እርሱም ለበኣል ታጥኑበት ዘንድ መሠዊያ፥ አድርጋችኋል። 14 አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ከመከራቸው የተነሣ ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱም ጩኸትና ልመና አታድርግ። 15 ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ምን አላት? ስእለት ወይም የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ወይስ በእነዚህ ታመልጫለሽን? 16 እግዚአብሔር ስምሽን።በመልካም ፍሬ የተዋበች የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎ ጠራው፤ በጽኑ ዐውሎ ነፋስ ጩኸት እሳትን አነደደባት፥ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል። 17 ለበኣልም በማጠናቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉን ነገር ተናግሮብሻል። 18 እግዚአብሔርም አስታወቀኝ እኔም አወቅሁ፤ ሥራቸውንም ገለጥህልኝ። 19 እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ፤ እነርሱም። ዛፉን ከፍሬው ጋር እንቍረጥ፥ ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው ብለው ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር። 20 ኵላሊትንና ልብን የምትፈትን በቅንም የምትፈርድ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በእነርሱ ላይ የሚሆን በቀልህን ለይ። 21 ስለዚህም። በእጃችን እንዳትሞት በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር ብለው ነፍስህን ስለሚሹ ስለ ዓናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።እነሆ፥ እቀጣቸዋለሁ፤ 22 ጎበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚቀር የለም።

ኤርምያስ 12

1 አቤቱ፥ ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል? 2 ተክለሃቸዋል፤ ሥር ሰድደዋል፤ አድገዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። 3 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ አውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፥ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፤ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። 4 ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቸ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች። ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ጠፍተዋል። 5 ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ታምነህ ብትቀመጥ፥ በዮርዳኖስ ትዕቢት እንዴት ታደርጋለህ? 6 ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፤ በመልካምም ቢናገሩህም አትታመናቸው። 7 ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። 8 ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋን አንሥታብኛለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። 9 ርስቴ እንደ ዝንጕርጕር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ ይበሉም ዘንድ አምጡአቸው። 10 ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል። 11 ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፤ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት የለም። 12 በወናዎች ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። 13 ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፤ ደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፤ ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከፍሬያችሁ ታፍራላችሁ። 14 እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጐረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። 15 ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ። 16 በበኣል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ። ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። 17 ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 13

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራችን መታጠቂያ ለአንተ ግዛ፥ ወገብህንም ታጠቅባት፤ በውኃውም ውስጥ አትንከራት። 2 እንደ እግዚአብሔርም ቃል መታጠቂያን ገዛሁ ወገቤንም ታጠቅሁባት። 3-4 ሁለተኛም ጊዜ። የገዛሃትን በወገብህ ያለችውን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥ፥ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፥ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት የሚል የእግዚአብሔር ቃል መጣልኝ። 5 እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁ በኤፍራጥስም አጠገብ ሸሸግኋት። 6 ከብዙ ቀንም በኋላ እግዚአብሔር። ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም ትሸሽጋት ዘንድ ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ አለኝ። 7 እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄድሁ ቆፈርሁም፥ ከሸሸግሁበትም ስፍራ መታጠቂያይቱን ወሰድሁ። እነሆም፥ መታጠቂያይቱ ተበላሽታ ነበር፥ ለምንም አልረባችም። 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አበላሻለሁ። 10 ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ያመልኩአቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንዳማትረባ እንደዚች መታጠቂያ ይሆናሉ። 11 መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ሕዝብና ስም ምስጋናና ክብር ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን አልሰሙም። 12 ስለዚህ።የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል ብለህ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም። ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን? ይሉሃል። 13 አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት ካህናቱንም ነቢያቱንም በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። 14 ሰውንም በሰው ላይ፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ፥ እቀጠቅጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራም፥ አላዝንም፥ አልምርም። 15 ስሙ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ። 16 ሳትጨልም እግራችሁም በጨለመችው ተራራ ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨለማ ሳይለውጠው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። 17 ይህን ባትሰሙ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔርም መንጋ ተማርኮአልና ዓይኔ ታነባለች፥ እንባንም ታፈስሳለች። 18 ለንጉሡና ለንጉሥ እናት ለእቴጌይቱ። የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ተዋርዳችሁ ተቀመጡ በል። 19 የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፥ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮአል፥ ፈጽሞ ተማርኮአል። 20 ዓይናችሁን አንሥታችሁ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቱ፤ ለአንቺ የተሰጠ መንጋ፥ የተዋበ መንጋሽ፥ ወዴት አለ? 21 ወዳጆችሽ እንዲሆኑ ያስተማርሻቸውን በራስሽ ላይ አለቆች ባደረጋቸው ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? 22 በልብሽም። እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሣ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፎአል። 23 በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። 24 ስለዚህ እንደሚያልፍ እብቅ በምድረ በዳ ነፋስ እበትናቸዋለሁ። 25 ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽ የለካሁልሽም እድል ፈንታ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። 26 ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። 27 አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የግልሙትናሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ በሜዳም አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?

ኤርምያስ 14

1 ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል። 3 ታላላቆችም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ። 4 በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ። 5 ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች። 6 የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዓይኖቻቸው ጠወለጉ። 7 አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ። 8 አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ? 9 እንዳንቀላፋ ሰው ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኃያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ፥ በመካከላችን ነህ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን። 10 እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል። መቅበዝበዝን ወድደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፥ በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል። 11 እግዚአብሔርም። ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው። 12 በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ። 13 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት። በእውነት ሰላምን በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል አልሁ። 14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። 15 ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት። በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል። እነዚያ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። 16 ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁ እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም። 17 እንደዚህም ብለህ ትነግራቸዋለህ። የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ዓይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፈሳሉ። 18 ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቋት አገር ሄደዋልና። 19 በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። 20 አቤቱ፥ በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን። 21 ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታስነውር፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ። 22 በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ዝናብ ማፍሰስ ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ አንተ አይደለህምን? አንተ ይህን ነገር ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።

ኤርምያስ 15

1 እግዚአብሔርም እንደዚህ አለኝ። ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፥ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይዘነብልም፤ ከፊቴ ጣላቸው፤ ይውጡ። 2 እነርሱም። ወዴት እንውጣ ቢሉህ፥ አንተ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ ትላቸዋለህ። 3 ሰይፍን ለመግደል ውሾችንም ለመጐተት የሰማያትንም ወፎች የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ አራቱን ዓይነት ጥፋት አዝዝባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 የይሁዳም ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስላደረገው ሁሉ በምድር መንግሥታት ሁሉ መካከል ለመከራ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ይጠይቅ ዘንድ ፈቀቅ የሚል ማነ ነው? 6 አንቺ እኔን ጥለሻል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጥፍቼሻለሁ፤ ከይቅርታ ደክሜአለሁ። 7 በአገርም ደጆች ውስጥ በመንሽ አበጥሬአቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፥ ሕዝቤንም አጥፍቼአለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም። 8 መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተውብኛል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጣርንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ። 9 ሰባት የወለደች ደክማለች፥ ነፍስዋንም አውጥታለች፤ ቀን ገና ሳለ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች ተዋርዳማለች፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ። 10 እናቴ ሆይ፥ ወዮልኝ! ለምድር ሁሉ የክርክርና የጥል ሰው የሆንሁትን ወለድሽኝ ለማንም አላበደርሁም፥ ማንም ለእኔ አላበደረም፥ ነገር ግን ሁሉ ይረግመኛል። 11 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። በእውነት ለደኅንነትህ አጸናሃለሁ፤ በእውነት በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላትህ እንዲለምንህ አደርገዋለሁ። 12 በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን? 13 በዳርቻህ ሁሉ ስላለ ኃጢአትህ ሁሉ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በከንቱ እሰጣለሁ። 14 የምታቃጥላችሁ እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና ከጠላቶችህ ጋር ወደማታውቀው ምድር አሳልፍሃለሁ። 15 አቤቱ፥ አንተ ታውቃለህ፤ አስበኝ ጐብኘኝም የሚያሳድዱኝንም ተበቀላቸው እንጂ አትታገሣቸው፤ ስለ አንተ ስድብን እንደ ታገሥሁ እወቅ። 16 ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ፤ አቤቱ፥ የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። 17 በዋዘኞችና በደስተኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም፤ ቍጣን ሞልተህብኛልና በእጅህ ፊት ለብቻዬ ተቀመጥሁ። 18 ስለ ምን ሕመሜ አዘወተረኝ? ቍስሌስ ስለ ምን የማይፈወስ ሆነ? ስለ ምንስ። አልሽርም አለ? በውኑ እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃ ትሆነኛለህን? 19 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ብትመለስ እመልስሃለሁ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፥ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። 20 ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም። 21 ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፥ ከጨካኞችም ጡጫ እቤዥሃለሁ። 21 21"21  И спасу тебя от руки злых и избавлю тебя от руки притеснителей.

ኤርምያስ 16

1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አይሁኑልህ። 3 እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና። 4 በክፉ ሞት ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም አይቀበሩምም፥ በመሬትም ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፥ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ። 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰላሜን፥ ቸርነትና ምሕረትን፥ ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፥ ታለቅስም ታዝንም ዘንድ አትሂድ። 6 ታላላቆችና ታናናሾች በዚህች ምድር ይሞታሉ፤ አይቀበሩም ሰዎችም አያለቅሱላቸውም ስለ እነርሱም ገላን አይነጩላቸውም ራስንም አይላጩላቸውም፤ 7 ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፥ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። 8 ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ። 9 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በዓይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ። 10 ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ። ይህን ሁሉ ታላቅ የሆነ ክፉ ነገርን ስለ ምን እግዚአብሔር ተናገረብን? በደላችንስ ምንድር ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ላይ የሠራነው ኃጢአታችን ምንድር ነው? ቢሉህ፥ 11 አንተ እንዲህ ትላቸዋለህ። አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተው ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ አመለኩአቸውም ሰገዱላቸውም፥ እነርሱም ትተውኛል፥ ሕጌንም አልጠበቁም፤ እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም፥ ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ እልከኝነት ሄዳችኋል እኔንም አልሰማችሁም። 13 ስለዚህ ከዚህች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወዳላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ። 14 ስለዚህ፥ እነሆ። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 15 ነገር ግን።የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ። 16 እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰድዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰድዳለሁ፥ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድኑአቸዋል። 17 ዓይኔ በመንገዳቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፥ ኃጢአታቸውም ከዓይኔ አልተሸሸገም። 18 ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኃጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ። 19 አቤቱ፥ ኃይሌ፥ አምባዬ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ሆይ፥ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው። በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር የማይረባቸውንም ወርሰዋል ይላሉ። 20 በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክትን አድርጎ ይሠራልን? 21 ስለዚህ፥ እነሆ፥ አስታውቃቸዋለሁ፥ በዚህች ጊዜ እጄንና ኃይሌን አስታውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።

ኤርምያስ 17

1 የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፤ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ተቀርጾአል። 2 ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና የማምለኪያ ዐፀዳቸውን ያስባሉ። 3 በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ። 4 አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ ለዘላለምም በማታውቃትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና። 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። 6 በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል። 7 በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። 8 በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል። 9 የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል? 10 እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ። 11 ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ እንዲሁ በቅን ሳይሆን ባለጠግነትን የሚሰበስብ ሰው ነው፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል። 12 የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው። 13 አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ። 14 አቤቱ፥ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና። 15 እነሆ። የእግዚአብሔር ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ ይሉኛል። 16 እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ። 17 ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ። 18 አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው። 19 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤ 20 እንዲህም በላቸው። በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፥ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥ 22 ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ። 23 እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ። 24 እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፤ ይላል እግዚአብሔር፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥ 25 በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። 26 የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ። 27 ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም።

ኤርምያስ 18

1-2 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል፥ እንዲህም አለው። ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፥ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁ። 3 ወደ ሸክላ ሠሪው ቤትም ወረድሁ፥ እነሆም፥ ሥራውን በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። 4 ከጭቃም ይሠራው የነበረ ዕቃ በሸክላ ሠሪው እጅ ተበላሸ፥ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ መልሶ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው። 5 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 6 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ፥ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ እንዲሁ እናንተ በእኔ እንጅ አላችሁ። 7 ስለ ሕዝብ ስለ መንግሥትም እነቅል አፈርስም አጠፋም ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ 8 ይህ ስለ እርሱ የተናገርሁበት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፥ እኔ አደርግበት ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። 9 ስለ ሕዝቡም ስለ መንግሥትም እሠራውና እተክለው ዘንድ በተናገርሁ ጊዜ፥ 10 በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርግ ቃሌንም ባይሰማ፥ እኔ አደርግለት ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ። 11 አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፥ አሳብንም አስብባችኋለሁ፤ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አቅኑ ብለህ ተናገራቸው። 12 እነርሱ ግን። እንጨክናለን፤ አሳባችንን ተከትለን እንሄዳለን ሁላችንም እንደ ክፉው ልባችን እልከኝነት እናደርጋለን አሉ። 13 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአሕዛብ መካከል። እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? ብላችሁ ጠይቁ። የእስራኤል ድንግል በጣም የሚያስደነግጠውን ነገር አድርጋለች። 14 በውኑ የሊባኖስ በረዶ የምድረ በዳውን ድንጋይ ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን? 15 ሕዝቤ ግን ረስተውኛል ለከንቱ ነገርም ዐጥነዋል፤ ከመንገዱም ተሰናክለዋል ከቀድሞውም ጐዳና ርቀው ወዳልተሠራው ወደ ጠማማው መንገድ ፈቀቅ ብለዋል። 16 ምድራቸውን ለመደነቂያና ለዘላለም ማፍዋጫ አድርገዋል፤ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፥ ራሱንም ያነቃንቃል። 17 በጠላት ፊት እንደ ምሥራቅ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም። 18 እነርሱም። ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፥ በኤርምያስ ላይ አሳብን እናስብ። ኑ፥ በምላስ እንምታው፥ ቃሉንም ሁሉ አናድምጥ አሉ። 19 አቤቱ፥ አድምጠኝ፥ የክርክሬንም ቃል ስማ። 20 ለነፍሴ ጕድጓድ ቈፍረዋልና በውኑ በመልካም ፋንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም እናገር ዘንድ ቍጣህንም ከእነርሱ እመልስ ዘንድ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስብ። 21 ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፥ ለሰይፍም እጅ አሳልፈህ ስጣቸው፥ ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፥ ወንዶቻቸውም በሞት ይጥፉ፥ ጕልማሶቻቸውም በሰልፍ ጊዜ በሰይፍ ይመቱ። 22 ሊይዙኝ ጕድጓድ ቆፍረዋልና፥ ለእግሮቼም ወጥመድ ሸሽገዋልና ድንገት በላያቸው ጭፍራ ባመጣህ ጊዜ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ። 23 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ይገድሉኝ ዘንድ በላዬ የመከሩትን ምክር ሁሉ ታውቃለህ፤ በደላቸውን ይቅር አትበል፥ ኃጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፤ በፊትህም ይውደቁ፥ በቍጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው። 20 20"20  Должно ли воздавать злом за добро? а они роют яму душе моей. Вспомни, что я стою пред лицем Твоим, чтобы говорить за них доброе, чтобы отвратить от них гнев Твой. 21 21"21  Итак предай сыновей их голоду и подвергни их мечу; да будут жены их бездетными и вдовами, и мужья их да будут поражены смертью, и юноши их умерщвлены мечом на войне. 22 22"22  Да будет слышен вопль из домов их, когда приведешь на них полки внезапно; ибо они роют яму, чтобы поймать меня, и тайно расставили сети для ног моих. 23 23"23  Но Ты, Господи, знаешь все замыслы их против меня, чтобы умертвить меня; не прости неправды их и греха их не изгладь пред лицем Твоим; да будут они низвержены пред Тобою; поступи с ними во время гнева Твоего.

ኤርምያስ 19

1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ሂድ፥ ከሸክላ ሠሪ ገምቦ ግዛ፥ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ 2 በካርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፥ 3 እንዲህም በል። የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሰማውን ሰው ጆሮ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ። 4 ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹህ ደም ሞልተዋልና፥ 5 እኔም ያላዘዝሁትን ያልተናገርሁትንም ወደ ልቤም ያልገባውን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አድርገው ለበኣል ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና ስለዚህ፥ 6 እነሆ፥ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፥ በጠላቶቻቸውም ፊት በሰይፍና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፥ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ። 8 ይህችንም ከተማ ለመደነቂያና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፤ የሚያልፍባትም ሁሉ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ ይደነቃል ከንፈሩንም ይመጥጣል። 9 የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፥ ሁሉም ጠላቶቻቸውንና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ። 10 ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፥ 11 እንዲህም ትላቸዋለህ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሸክላ ሠሪው ዕቃ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀብሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ። 12 እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ። 13 የረከሱትም የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች፥ እነዚያ በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ፥ እንደ ቶፌት ስፍራ ይሆናሉ። 14 ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት ሊናገር ወደዚያ ልኮት ከነበረው ስፍራ ከቶፌት መጣ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝብ ሁሉ። 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ፥ በዚህች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።

ኤርምያስ 20

1 በእግዚአብሔርም ቤት የተሾመው አለቃ የካህኑ የኢሜር ልጅ ጳስኮር ኤርምያስ በዚህ ነገር ትንቢት ሲናገር ሰማ። 2 ጳስኮርም ነቢዩን ኤርምያስን መታው፥ በእግዚአብሔርም ቤት በነበረው በላይኛው በብንያም በር ባለው በእግር ግንድ ውስጥ አኖረው። 3 በነጋውም ጳስኮር ኤርምያስን ከግንድ ውስጥ አወጣው። ኤርምያስም እንዲህ አለው። እግዚአብሔር ስምህን። ማጎርሚሳቢብ እንጂ ጳስኮር ብሎ አይጠራህም። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ለራስህና ለወዳጆችህ ሁሉ ፍርሃት አደርግሃለሁ፤ እነርሱም በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ ዓይኖችህም ያያሉ፤ ይሁዳንም ሁሉ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ወደ ባቢሎን ያፈልሳቸዋል በሰይፍም ይገድላቸዋል። 5 የዚህችንም ከተማ ባለጠግነት ሁሉ ጥሪትዋንም ሁሉ ክብርዋንም ሁሉ የይሁዳንም ነገሥታት መዝገብ ሁሉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እነርሱም ይበዘብዙአቸዋል ይዘውም ወደ ባቢሎን ያፈልሱአቸዋል። 6 አንተም፥ ጳስኮር ሆይ፥ በቤትህም የሚኖሩት ሁሉ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ፤ አንተም በሐሰትም ትንቢት የተናገርህላቸው ወዳጆችህ ሁሉ ወደ ባቢሎን ትገባላችሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ፥ በዚያም ትቀበራላችሁ። 7 አቤቱ፥ አታለልኸኝ እኔም ተታለልሁ፥ ከእኔም በረታህ አሸነፍህም፤ ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፥ ሁሉም ያላግጡብኛል። 8 በተናገርሁ ቍጥር እጮኻለሁ፤ ግፍና ጥፋት ብዬ እጮኻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና ዋዛ ሆኖብኛልና። 9 እኔም። የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም ብል፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፥ መሸከምም አልቻልሁም። 10 የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁ፥ ማስፈራራትም ከብቦኛል። መውደቄን የሚጠብቁ የሰላሜ ሰዎች ሁሉ። ምናልባት ይታለል እንደ ሆነ፥ እናሸንፈውም እንደ ሆነ፥ እርሱንም እንበቀል እንደ ሆነ፥ ክሰሱት እኛም እንከስሰዋለን ይላሉ። 11 እግዚአብሔር ግን እንደ ኃያልና እንደ ጨካኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ስለዚህ አሳዳጆቼ ይሰናከላሉ አያሸንፉም፤ አይከናወንላቸውምና በጽኑ እፍረት ያፍራሉ፥ ለዘላለምም በማይረሳ ጕስቍልና ይጐሰቍላሉ። 12 አቤቱ፥ ጻድቅን የምትመረምር ኵላሊትንና ልብን የምትመለከት የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ክርክሬን ገልጬልሃለሁና በቀልህን በላያቸው ለይ። 13 ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔርንም አመስግኑ፤ የችግረኛውን ነፍስ ከክፉ አድራጊዎች እጅ አድኖአልና። 14 የተወለድሁባት ቀን የተረገመች ትሁን፤ እናቴ እኔን የወለደችባት ቀን የተባረከች አትሁን። 15 ወንድ ልጅ ተወልዶልሃል ብሎ ለአባቴ የምሥራች ነግሮ ደስ ያሰኘው ሰው የተረገመ ይሁን። 16 ያም ሰው እግዚአብሔር ሳይጸጸት እንደ ገለበጣቸው ከተሞች ይሁን፥ በማለዳም ልቅሶን በቀትርም ጩኸትን ይስማ፤ 17 እናቴ መቃብር ትሆነኝ ዘንድ ማኅፀንዋም ዘወትር ይዞኝ ያቆይ ዘንድ በማኅፀን ውስጥ አልገደለኝምና። 18 ድካምንና ጣርን አይ ዘንድ ዘመኔም በእፍረት ታልቅ ዘንድ ስለ ምን ከማኅፀን ወጣሁ?

ኤርምያስ 21

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 ይህም የሆነው ንጉሡ ሴዴቅያስ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅ፤ ከእኛም ይመለስ ዘንድ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ ይሆናል ብሎ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ነው። 3 ኤርምያስም እንዲህ አላቸው። ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት። 4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን ዕቃ ጦራችሁን እመልሰዋለሁ፥ እነዚያንም ወደዚህች ከተማ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ። 5 እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቍጣና በመዓት በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ። 6 በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፥ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ። 7 ከዚህ በኋላ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትንም ባሪዎቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም። 8 ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ። 9 በዚህች ከተማ ውስጥ የሚዘገይ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም ምርኮ ትሆንለታለች። 10 ለመልካም ሳይሆን ለክፋ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፥ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል። 11 የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 12 የዳዊት ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣና ማንም ሳያጠፋው እንዳይነድድ፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ። 13 እነሆ፥ በሸለቆው ውስጥ በሜዳ ላይም ባለው አምባ የምትቀመጪ ሆይ፥ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፤ እናንተም። በእኛ ላይ የሚወርድ ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው? የምትሉ ሆይ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤ 14 እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፤ በዱርዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፥ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።

ኤርምያስ 22

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለ። ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥ 2 እንዲህም በል። በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ አንተና ባሪያዎችህ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ። 4 ይህንንም ነገር ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባሪያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ። 5 ነገር ግን ይህን ቃል ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ወና እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 6 እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና። አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ። 7 መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል። 8 ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን። እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደርገ? ይላሉ። 9 እነርሱም። የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላመለኩአቸውም ነዋ ብለው ይመልሳሉ። 10 ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና፥ የተወለደባትንም አገር አያይምና ለሚወጣ እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተ አታልቅሱ አትዘኑለትም። 11 በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። 12 እንግዲህም ወደዚህ አይመለስም፥ በተማረከባት አገር ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። 13 ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤ 14 ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ ለሚል፥ መስኮትንም ለሚያወጣ፥ በዝግባም ሥራ ለሚያሳጌጥ፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት! 15 በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ አይበላምና አይጠጣም ነበርን? ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። 16 የድሀውንና የችግረኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር። 17 ዓይንህና ልብህ ግን ለስስት ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው። 18 ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል። ወንድሜ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም። ጌታ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም። 19 አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል። 20 ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን አንሺ፤ በዓባሪምም ውስጥ ሆነሽ ጩኺ። 21 በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም። አልሰማም አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ቃሌን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው። 22 በግ ጠባቂዎችሽን ሁሉ ነፋስ ይጠብቃቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ክፋትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትጐሳቈይማለሽ። 23 አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ፥ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕማም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታጓሪያለሽ! 24 እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ ማኅተም ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ እነቅልህ ነበር፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 25 ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ። 26 አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ። 27 ይመለሱባትም ዘንድ ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም። 28 በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ለአንዳች የማይረባ የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለ ምን ተጥለው ወደቁ? 29 ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። 30 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወን በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመት በይሁዳም የሚነግሥ እንግዲህ አይገኝምና። መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው ብላችሁ ጻፉ።

ኤርምያስ 23

1 የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር። 2 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል። በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸውማል አልጐበኛችኋቸውምም፤ እነሆ፥ የሥራችሁን ክፋት እጐበኝባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 3 የመንጋዬም ቅሬታ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ ወደ በረታቸው ሰብሰቤ እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ያፈራሉ ይበዙማል። 4 የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፥ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፥ ከእነሱም አንድ አይጐድልም፥ ይላል እግዚአብሔር። 5 እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቍጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እርሱም እንደ ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል። 6 በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ የሚጠራበትም ስም። እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። 7 ስለዚህ፥ እነሆ። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 8 ነገር ግን። የእስራኤልን ቤት ዘር ከሰሜን አገርና ካሰደድኋቸውም አገር ሁሉ ያወጣና የመራ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ በምድራቸውም ይቀመጣሉ። 9 ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። 10 ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ ማሰማርያ ደርቆአል፤ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም። 11 ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ድጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ፍግምግም ብለው ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 13 በሰማርያ ነቢያት ላይ ስንፍናን አይቻለሁ፤ በበኣል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤል ያስቱ ነበር። 14 በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። 15 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ። 16 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። 17 ለሚንቁኝ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር። ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ። ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። 18 ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው? 19 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፍስ ወጥቶአል፤ የዓመፀኞችን ራስ ይገለባብጣል። 20 የእግዚአብሔር ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ። 21 እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። 22 በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር። 23 እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። 24 ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር። 25 አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። 26 ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? 27 አባቶቻቸው ስለ በኣል ስሜን እንደ ረሱ፥ እያንዳንዱ ለባልንጀራው በሚናገራት ሕልማቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። 28 የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? 29 በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር። 30 ስለዚህ፥ እነሆ፥ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 31 እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው። እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 32 እነሆ፥ ሐሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም፥ ይላል እግዚአብሔር። 33 ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን። የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ። ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችሁማለህ፥ ይላል እግዚአብሔር ትላቸዋለህ። 34 የእግዚአብሔር ሸክም የሚለውን ነቢይንና ካህንን ሕዝቡንም ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። 35 አንዱም አንዱ ለባልንጀራው፥ አንዱም አንዱ ለወንድሙ እንዲህ ይበል። እግዚአብሔር የመለሰው ምንድር ነው? እግዚአብሔርስ ምን ነገር ተናገረ? 36 ለሰው ሁሉ ቃል ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን የሕያውን አምላክ ቃል ለውጣችኋልና። 37 ለነቢዩ። እግዚአብሔር ምን መለሰልህ? እግዚአብሔርስ የተናገረው ምንድር ነው? ትላለህ። 38 ነገር ግን። የእግዚአብሔር ሸክም ብትሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ። የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል። 39 የእግዚአብሔር ሸክም ብላችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። 40 የዘላለምንም ስድብ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘላለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።

ኤርምያስ 24

1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ እግዚአብሔር አሳየኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። 2 በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፤ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት። 3 እግዚአብሔርም። ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጐነት እመለከተዋለሁ። 6 ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 8 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌም ቅሬታ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን እጥላቸዋለሁ። 9 በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።

ኤርምያስ 25

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረው። 3 ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከአሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሀያ ሦስቱ ዓመታት፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፤ ነገር ግን አልሰማችሁም። 4 እግዚአብሔርም ማልዶ ተነሥቶ ባሪያዎቹን ነቢያትን ወደ እናንተ ላከ፤ እናንተም አላደመጣችሁም ጆሮአችሁንም አላዘነበላችሁም። 5 እርሱም። ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ እግዚአብሔርም ከዘላለም ወደ ዘላለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ። 6 ታመልኩአቸውም ትሰግዱላቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ አለ። 7 ለእናንተ ጕዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ ታስቈጡኝ ዘንድ አልሰማችሁኝም፥ ይላል እግዚአብሔር። 8 ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቃሌን አልሰማችሁምና እነሆ፥ 9 ልኬ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ ባሪያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናብከደነዖርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመደነቂያና ለማፍዋጫም ለዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 10 ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። 11 ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። 12 ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘላለም ባድማ አደርጋታለሁ። 13 በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። 14 ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ያስገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ። 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። የዚህን ቍጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምሰድድባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። 16 ከምሰድድባቸውም ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዱማል ያብዳሉም። 17 ከእግዚአብሔርም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፥ እግዚአብሔርም እኔን የሰደደባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። 18 ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መደነቂያ ማፍዋጫም እርግማንም አደርጋቸው ዘንድ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። 19 የግብጽንም ንጉሥ ፈርዖንን ባሪያዎቹንም አለቆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ፥ 20 የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዖፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ አስቀሎናንም ጋዛንም አቃሮንንም የአዞጦንንም ቅሬታ፥ 21 ኤዶምያስንም፥ ሞዓብንም፥ የአሞንም ልጆች፥ 22 የጤሮስን ነገሥታትም ሁሉ፥ የሲዶናን ነገሥታት ሁሉ፥ በባህር ማዶ ያለች የደሴት ነገሥታትንም፥ 23 ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ቡዝንም፥ ጠጕራቸውንም የሚቈርጡትን ሁሉ፥ 24 የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ 25 የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ 26 የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፥ የቀረቡና የራቁ፥ አንዱ ከሌላው ጋር ያሉ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፤ የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል። 27 አንተም። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከላችሁ ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፥ ስከሩም፥ አስታውኩም ውደቁም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። 28 ይጠጡም ዘንድ ጽዋውን ከእጅህ ለመቀበል እንቢ ቢሉ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ በላቸው። 29 እነሆ፥ ስሜ የተጠራባትን ከተማ አስጨንቃት ዘንድ እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 30 ስለዚህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ትናገርባቸዋለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ። እግዚአብሔር በላይ ሆኖ ይጮኻል፥ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፥ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። 31 እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ክርክር አለውና ድምፅ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፥ ኃቲአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 32 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፥ ጽኑም ዐውሎ ነፍስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። 33 በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዩች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ gWdፍ ይሆናሉ እንጂ አይከማቹም አይቀበሩምም። 34 ትታረዱና ትበተኑ ዘንድ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች፥ አልቅሱ ጩኹም፤ እናንተ የመንጋ አውራዎች፥ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። 35 ሽሽትም ከእረኞች ማምለጥም ከመንጋ አውራዎች ይጠፋል። 36 እግዚአብሔር ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። 37 ከእግዚአብሔር ጽኑ KWTa የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። 38 እንደ አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቍጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።

ኤርምያስ 26

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ቁም፥ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ ይሰግዱ ዘንድ ለሚመጡት ለይሁዳ ከተሞች ሁሉ ትነግራቸው ዘንድ ያዘዝሁህን ቃል ሁሉ ተናገራቸው፤ አንዲትም ቃል አትgWdል። 3 ምናልባት ይሰሙ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስለ ሥራቸው ክፋት ያሰብሁባቸውን ክፉ ነገር እተዋለሁ። 4 እንዲህም በላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በፊታችሁ በሰጠኋት ሕጌ ትሄዱ ዘንድ ባትሰሙኝ፥ 5 ያልሰማችሁትን በማለዳ ተነሥቼ ወደ እናንተ የላክኋቸውን የባሪያዎቼን የነቢያትን ቃል ባትሰሙ፥ 6 ይህን ቤት እንደ ሴሎ አደርገዋለሁ፥ ይህችንም ከተማ ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን አደርጋታለሁ። 7 ካህናቱም ነቢያቱም ሕዝቡም ሁሉ ኤርምያስ በእግዚአብሔር ቤት ይህን ቃል ሲናገር ሰሙ። 8 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘውን ነገር ሁሉ በፈጸመ ጊዜ ካህናትና ነቢያት ሕዝቡም ሁሉ። ሞትን ትሞታለህ። 9 በእግዚአብሔር ስም። ይህ ቤት እንደ ሴሎ ይሆናል፥ ይህችም ከተማ ባድማና ወና ትሆናለች ብለህ ስለ ምን ትንቢት ተናገርህ? ብለው ያዙት። ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በኤርምያስ ላይ ተሰብስበው ነበር። 10 የይሁዳም አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ቤት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፥ በአዲሱም በእግዚአብሔር ቤት ደጅ መግቢያ ተቀመጡ። 11 ካህናቱና ነቢያቱም ለአለቆቹና ለሕዝቡ ሁሉ። በጆሮአችሁ እንደ ሰማችሁ በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት ተናግአልና ይህ ሰው ሞት የሚገባው ነው ብለው ተናገሩ። 12 ኤርምያስም ለአለቆችና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ። በሰማችሁት ቃል ሁሉ በዚህች ቤትና በዚህች ከተማ ላይ ትንቢት እናገር ዘንድ እግዚአብሔር ልኮኛል። 13 አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል። 14 እኔ ግን፥ እነሆ፥ በእጃችሁ ነኝ፤ በዓይናችሁ መልካምና ቅን የመሰለውን አድርጉብኝ። 15 ነገር ግን ይህን ቃል ሁሉ በጆሮአችሁ እናገር ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛልና ብትገድሉኝ ንጹሕ ደምን በራሳችሁና በዚህች ከተማ በሚኖሩባትም ላይ እንድታመጡ በእርግጥ እወቁ። 16 አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ለካህናትና ለነቢያት። ይህ ሰው በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ተናግሮናልና ሞት አይገባውም አሉ። 17 ከአገሩ ሽማግሌዎችም ሰዎች ተነሥተው ለሕዝቡ ጉባኤ ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ። 18 ሞሬታዊው ሚክያስ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ነቢይ ነበረ፤ ለይሁዳም ሕዝብ ሁሉ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል ብሎ ተናገረ። 19 በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ እግዚአብሔርን አልፈሩምን? ወደ እግዚአብሔርስ አልተማለሉምን? እግዚአብሔርስ የተናገረባቸውን ክፉ ነገር አይተውምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን። 20 ደግሞም በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገረ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የቂርያትይዓሪም ሰው የሸማያ ልጅ ኦርዮ ይባል ነበር፤ በዚህችም ከተማ በዚህችም ምድር ላይ እንደ ኤርምያስ ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገረ። 21 ንጉሡም ኢዮአቄም ኃያላኑም ሁሉ አለቆቹም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ንጉሡ ሊገድለው ፈለገ፤ ኦርዮም ይህን በሰማ ጊዜ ፈርቶ ሸሸ ወደ ግብጽም ገባ። 22 ንጉሡም ኢዮአቄም የዓክቦርን ልጅ ኤልናታንን ከእርሱም ጋር ሌሎችን ሰዎች ወደ ግብጽ ላካቸው፤ 23 ከግብጽም ኦርዮን አውጥተው ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮአቄም ይዘውት መጡ፤ እርሱም በሰይፍ ገደለው ሬሳውንም ክቡራን ባልሆኑ ሰዎች መቃብር ጣለው። 24 ነገር ግን በሕዝቡ እጅ እንዳይሰጥና እንዳይገድሉት የሳፋን ልጅ የአኪቃም እጅ ከኤርምያስ ጋር ነበረች።

ኤርምያስ 27

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። እስራትና ቀንበር ሥራ በአንገትህም ላይ አድርግ፤ 3 ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ ወደ አሞንም ልጆች ንጉሥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላካቸው። 4 ለጌቶቻቸውም እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ። 5 ምድሪቱን በምድርም ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኃይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ፤ ለዓይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6 አሁንም እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ይገዙለትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7 የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጅ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እርሱን ያስገዙታል። 8 ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከደነፆር የማይገዛውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 እናንተ ግን። ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም አላሚዎቻችሁንና ቃላተኞቻችሁን መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ 10 ከምድራቸሁ እንዲያርቁአችሁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና። 11 ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚገዛለትን ሕዝብ በአገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እነርሱም ያርሱአታል ይቀመጡባትማል። 12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም በዚህ ቃል ተናገርሁ። ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ ለእርሱና ለሕዝቡም ተገዙላቸው በሕይወትም ኑሩ። 13 ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? 14 ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና። ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ። 15 እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 16 ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሐሰተኛውን ትንቢት ይናገሩላችኋልና። የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳል የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ። 17 እነርሱም አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ በሕይወትም ኑሩ። ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች? 18 እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም የቀረችው ዕቃ ወደ ባቢሎን እንዳትሄድ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይማለሉ። 19-20 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ከበርቴዎች ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ ስላልወሰዳቸው ዓምዶች ስለ kWreውም ስለ መቀመጫዎቹም በዚህችም ከተማ ስለ ቀረች ዕቃ ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ 21 በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀረችው ዕቃ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 22 ወደ ባቢሎን ትወሰዳለች እስከምጐበኛትም ቀን ድረስ በዚያ ትኖራለች፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያን ጊዜም አወጣታለሁ ወደዚህም ስፍራ እመልሳታለሁ።

ኤርምያስ 28

1 በዚያም ዓመት በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። 2 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይናገራል። የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። 3 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳትን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳታለሁ፤ 4 ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና። 5 ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ። 6 ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ። አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም። 7 ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፤ 8 ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። 9 ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል። 10 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። 11 ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲሁ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ አለ። ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ። 12 ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 13 ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ። 14 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፥ የምድረ በዳ አራዊት ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 15 ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን። ሐናንያ ሆይ፥ ስማ፤ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ እግዚአብሔር አልላከህም። 16 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከምድር ላይ እሰድድሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ አለው። 17 ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።

ኤርምያስ 29

1 ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ተረፉት የምርኮ ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው። 2 ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እናቱም እቴጌይቱ ጃንደረቦቹም የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች ጠራቢዎችና ብረት ሠራተኞችም ከኢየሩሳሌም ከወው በኋላ ነው። 3 ኤርምያስ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን እንዲህ ሲል ላከው። 4 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል። 5 ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ፤ 6 ተጋቡ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁንም አጋቡ፥ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ይውለዱ፤ ከዚያም ተባዙ ጥቂቶችም አትሁኑ። 7 በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማርክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ። 8 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ። 9 በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም። 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። 11 ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። 12 እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። 13 እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። 14 ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ። 15 እናንተም። እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል ብላችኋልና፤ 16 እግዚአብሔር በዳዊት ዙፋን ስለ ተቀመጠ ንጉሥ ከእናንተም ጋር ስላልተማረኩት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ እንዲህ ይላልና። 17 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድድባቸዋለሁ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ። 18 በሰይፍም በራብም በቸነፈርም አሳዳድዳቸዋለሁ፥ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለጥላቻና ለመደነቂያ ለማፍዋጫም ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 19 ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 20 ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ በዓይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። 22 ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ። የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል እርግማንን ያነሣሉ፤ እኔም አውቃለሁ ምስክርም ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 23 በእስራኤል ዘንድ ስንፍና አድርገዋልና፥ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፥ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና። 24 ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ በል። 25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በኢየሩሳሌም ወዳለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ መዕሤያ ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስምህ እንዲህ ስትል ልከሃል። 26 እያበደ ትንቢት የሚናገርን ሰው ሁሉ በእግር ግንድና በዛንጅር ታኖረው ዘንድ በእግዚአብሔር ቤት አለቃ እንድትሆን እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል። 27 አሁንስ ትንቢት ተናጋሪውን የዓናቶቱን ሰው ኤርምያስን ስለ ምን አትዘልፈውም? 28 እርሱ። ምርኮው የረዘመው ነውና ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፥ አታክልትንም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና። 29 ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው። 30 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 31 እግዚአብሔር ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እንዲህ ይላል ብለህ ወደ ምርኮኞች ሁሉ ላክ። እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጎአችኋልና፤ 32 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ እኔም የማደርግላችሁን መልካሙን ነገር የሚያይ ሰው በመካከላችሁ አይኖርላችሁም

ኤርምያስ 30

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። 3 እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስባት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይገዙአታል። 4 እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የሚያስፈራ ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም። 6 ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ ስለ ምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ወደ ጥቁረት ተለውጦ አየሁ? 7 ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል። 8 በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም፤ 9 ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሎች አሕዛብ እንደ ገና አይገዙአቸውም። 10 እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከምርኮ አገር አድናለሁና ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፤ ያዕቆብም ይመለሳል ያርፍማል ተዘልሎም ይቀመጣል፤ ማንም አያስፈራውም። 11 አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም ከቶ አልተውህም። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስብራትህ የማይፈወስ ቍስልህም ክፉ ነው። 13 ትጠገን ዘንድ ክርክርህን የሚፈርድልህ የለም፥ ቍስልህንም የሚፈውስ መድኃኒት የለህም። 14 ውሽሞችህ ሁሉ ረስተውሃል አይፈልጉህምም፤ በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ በጠላት ማቍሰልና በጨካኝ ቅጣት አቍስዬሃለሁና። 15 ሕመምህ የማይፈወስ ሆኖአልና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ ይህን አድርጌብሃለሁ። 16 ስለዚህ የሚውጡህ ሁሉ ይዋጣሉ፥ ጠላቶችህም ሁላቸው ይማረካሉ፤ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፥ የበዘበዙህንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ። 17 እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማንም የማይሻት፥ የተጣለች ጽዮን ብለው ጠርተውሻልና። 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ትሠራለች፥ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ ይሆናል። 19 ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም። 20 ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፥ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ። 21 አለቃቸው ከእነርሱ ውስጥ ይሆናል፥ ገዥአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፤ እኔ አቀርበዋለሁ እርሱም ይቀርባል፤ ይህስ ባይሆን ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር። 22 እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 23 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፋስ ወጥቶአል፤ የዓመፀኞችንም ራስ ይገለባብጣል። 24 የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ።

ኤርምያስ 31

1 በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። 3 እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ። በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። 4 የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ። 5 እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል። 6 በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች። ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና። 7 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ስለ ያዕቆብ ደስ ይበላችሁ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፤ አውሩ፥ አመስግኑ። እግዚአብሔር ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ። 8 እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፥ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፥ በመካከላቸውም ዕውሩና አንካሳው ያረገዘችና የወለደችም በአንድነት፤ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። 9 በልቅሶ ወጡ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፥ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና። 10 አሕዛብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና። እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። 11 እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረቱበትም እጅ አድኖታል። 12 ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ እልል ይላሉ፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። 13 በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በዘፈን ደስ ይላታል፥ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እመልሳለሁ፥ አጽናናቸውማለሁ፥ ከኅዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። 14 የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል። 15 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። 17 ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ዳርቻቸው ይመለሳሉ። 18 ኤፍሬም። ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። 19 ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም ብሎ ሲያለቅስ ሰማሁ። 20 በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 21 ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። 22 አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች። 23 የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ። የጽድቅ ማደሪያ ሆይ፥ የቅድስና ተራራ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ የሚልን ነገር እንደ ገና ይናገራሉ። 24 በይሁዳ ከተሞችና በአገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። 25 የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ ያዘነችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። 26 ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ። 27 የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 28 እንዲህም ይሆናል፤ አፈርሳቸውና ክፉ አድርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 29 በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም። አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤ 30 ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ። 31 እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 32 ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። 33 ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 34 እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን። እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና። 35 ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 36 ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘላለም ይቀራል። 37 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰማይ በላይ ቢከነዳ፥ የምድርም መሠረት በታች ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እጥላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 38 ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 39 የተለካበትም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ወደ ጎዓም ይዞራል። 40 የሬሳም ሸለቆ ሁሉ የአመድም እርሻ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሄር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘላለም አይነቀልም አይፈርስምም።

ኤርምያስ 32

1 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በአሥረኛው ዓመት፥ በናቡክደነፆር በአሥራ ስምንተኛው ዓመት፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 በዚያን ጊዜም የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ ነበር፤ ነቢዩም ኤርምያስ በይሁዳ ንጉሥ ቤት በነበረው በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ነበር። 3 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንዲህ ብሎ አስጠብቆት ነበርና። ስለ ምን እንዲህ ብለህ ትንቢት ትናገራለህ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ እርሱም ይይዛታል፤ 4 የይሁዳም ንጉሥ ሴዴቅያስ በእውነት በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፎ ይሰጣል፥ አፍ ለአፍም ይናገረዋል፥ ዓይኑም ዓይኑን ያያል እንጂ ከከለዳውያን እጅ አያመልጥም፤ 5 እርሱም ሴዴቅያስን ወደ ባቢሎን ያፈልሰዋል፥ እኔም እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከከላዳውያን ጋር ብትዋጉ ምንም አትረቡም። 6 ኤርምያስም እንዲህ አለ። የእግዚአብሄር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 7 እነሆ፥ የአጐትህ የሰሎም ልጅ አናምኤል ወደ አንተ መጥቶ። ትገዛው ዘንድ መቤዠቱ የአንተ ነውና በዓናቶት ያለውን እርሻዬን ግዛ ይልሃል። 8 እንደ እግዚአብሔርም ቃል የአጐቴ ልጅ አናምኤል እኔ ወዳለሁበት ወደ ግዞቱ ቤት አደባባይ መጥቶ። በብንያም አገር በዓናቶት ያለውን እርሻዬን፥ እባክህ፥ ግዛ፤ ርስቱ የአንተ ነውና፥ መቤዠቱም የአንተ ነውና፤ ለአንተ ግዛው አለኝ። ይህም የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሆነ አወቅሁ። 9 በዓናቶትም ያለውን እርሻ ከአጐቴ ልጅ ከአናምኤል ገዛሁ፥ አሥራ ሰባት ሰቅል ብርም መዘንሁለት። 10 በውሉም ወረቀት ላይ ፈረምሁ አተምሁትም፥ ምስክሮችንም ጠርቼ ብሩን በሚዛን መዘንሁለት። 11 የታተመውንና የተከፈተውን የውል ወረቀት ወሰድሁ፤ 12 የአጐቴም ልጅ አናምኤል፥ የውሉንም ወረቀት የፈረሙ ምስክሮች፥ በግዞትም ቤት አደባባይ የተቀመጡ አይሁድ ሁሉ እያዩ የውሉን ወረቀት ለመሕሤያ ልጅ ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት። 13 በፊታቸውም እንዲህ ብዬ ባሮክን አዘዝሁት። 14 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ብዙ ቀን ይጠበቁ ዘንድ የታተመውንና የተከፈተውን ይህን የውል ወረከት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኑራቸው። 15 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰዎች በዚህች ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ። 16 ለኔርያ ልጅ ለባሮክም የውሉን ወረቀት ከሰጠሁት በኋላ፥ እንዲህ ብዬ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ። 17 አቤቱ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ሰማይንና ምድርን በታላቅ ኃይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፥ ከአንተም የሚያቅት ነገር የለም። 18 ለብዙ ሺህ ምሕረት ታደርጋለህ፥ የአባቶችንም በደል ከእነርሱ በኋላ በልጆቻቸው ብብት ትመልሳለህ፤ ስምህ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 19 በምክር ታላቅ በሥራም ብርቱ ነህ፤ ለሁሉም እንደ መንገዱና እንደ ሥራው ፍሬ ትሰጥ ዘንድ ዓይኖችህ በአዳም ልጆች መንገድ ሁሉ ተገልጠዋል። 20 እስከ ዛሬም ድረስ ምልክትንና ድንቅን ነገር በግብጽ ምድር ደግሞም በእስራኤልና በሌሎች ሰዎች መካከል አድርገሃል፥ እንደ ዛሬም ለአንተ ስም አድርገሃል። 21 በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ። 22 ትሰጣቸውም ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልህላቸውን ምድር፥ ወተትና ማርንም የምታፈስሰውን ምድር፥ ሰጠሃቸው፤ 23 እነርሱም ገብተው ወረሱአት፤ ነገር ግን ቃልህን አልሰሙም በሕግህም አልሄዱም፥ ያደረርም ዘንድ ካዘዝሃቸው ሁሉ ምንም አላደረጉም፤ ስለዚህ ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣህባቸው። 24 እነሆ የአፈር ድልድል፥ ሊይዙአትም እስከ ከተማይቱ ድረስ ቀርበዋል፤ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም የተነሣ ከተማይቱ ለሚዋጉአት ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች፥ የተናገርኸውም ሆኖአል፤ እነሆም፥ አንተ ታየዋለህ። 25 አንተም፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ። እርሻውን በብር ግዛ ምስክሮችንም ጥራ አልኸኝ፤ ከተማይቱ ግን ለከለዳውያን እጅ ተሰጥታለች። 26 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 27 እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ 28 በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን? ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ ለከለዳውያን እጅና ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ እርሱም ይይዛታል። 29 ይህችን ከተማ የሚወጉ ከለዳውያን መጥተው በእሳት ያነድዱአታል፥ ያስቈጡኝም ዘንድ በሰገነታቸው ላይ ለበኣል ካጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥን KWrባን ካፈሰሱባቸው ቤቶች ጋር ያቃጥሉአታል። 30 የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች ከታናሽነታቸው ጀምሮ በፊቴ ክፉ ነገርን ብቻ አድርገዋልና፤ የእስራኤልም ልጆች እኔን በእጃቸው ሥራ ከማስቈጣት በቀር ሌላ ሥራ አላደረጉምና። 31 ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቍጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና፤ 32 ይህም እኔን ያስቈጡኝ ዘንድ፥ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚንኖሩ፥ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው። 33 ፊታቸውንም ሳይሆን ጀርባቸውን ወደ እኔ መለሱ፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ሳሰተምራቸው ተግሣጽን ይቀበሉ ዘንድ አልሰሙም። 34 ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ውስጥ ርkWsvታቸውን አኖሩ። 35 ይሁዳን ወደ ኃጢአት እንዲያገቡት፥ ይህንን ርkWsvት ያደርጉ ዘንድ፥ እኔ ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን ነገር፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለሞሎክ በእሳት ያሳልፉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ያሉትን የበኣልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠሩ። 36 አሁን እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አንተ ስለ እርስዋ። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ተሰጥታለች ስለምትላት ከተማ እንዲህ ይላል። 37 እነሆ፥ በቍጣዬና በመዓቴ በታላቅም መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁባት አገር ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፥ ተዘልለውም እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ 38 እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 39 ለእነርሱም ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘላለም እንዲፈሩኝ አንድ ልብና አንድ መንገድ እሰጣቸዋለሁ። 40 ለእነርሱም ከማደርገው በጎነት አልመለስም ስል፥ ከእነርሱ ጋር የዘላለምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከእኔም ዘንድ ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ። 41 ለእነርሱም መልካምን በማድረግ ደስ ይለኛል በእውነትም በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ። 42 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ይህን እጅግ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ሕዝብ ላይ እንዳመጣሁ፥ እንዲሁ የተናገርሁላቸውን በጎነት ሁሉ አመጣላቸዋለሁ። 43 እናንተም። ያለ ሰውና ያለ እንሰሳ ያለች ባድማ ናት፥ ለከለዳውያንም እጅ ተሰጥታለች በምትሉአት ምድር እርሻን ይገዛሉ። 44 ምርኮኞቻቸውንም እመልሳለሁና በብንያም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በደጋውም ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ ሰዎች እርሻውን በብር ይገዛሉ በውሉም ወረቀት ፈርመው ያትማሉ ምስክሮችንም ይጠራሉ።

ኤርምያስ 33

1 ኤርምያስ ገና በግዞት ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል መጣለት። 2 ስሙ እግዚአብሔር የሆነ፥ ያደረገው እግዚአብሔር፥ ያጸናውም ዘንድ የሠራው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 3 ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ። 4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሄር ለአፈር ድልድልና ለምሽግ ስለ ፈረሱ ስለዚህች ከተማ ቤቶች፥ ስለ ይሁዳም ነገሥታት ቤቶች እንዲህ ይላልና። 5 ከለዳውያን ለመዋጋት መጥተዋል፤ ነገር ግን በKWTaዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች ሊሞሉአቸው ነው፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ ሰውሬአለሁና። 6 እነሆ፥ ፈውስንና መድኃኒትን አመጣላታለሁ፥ እፈውሳቸውማለሁ፤ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ። 7 የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ። 8 እኔንም ከበደሉበት ኃጢአት ሁሉ አነጻቸዋለሁ እኔንም የበደሉኝን ያመፀብኝንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ይቅር እላለሁ። 9 ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ እኔም ስላመጣሁላቸው በጎነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ ስም ለምስጋናም ለክብርም ትሆናለች። 10 እግዚአብሔር እንዲ ይላል። እናንተ። ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ያለች ባድማ ናት በምትሉአት በዚህች ስፍራ፥ የሚቀመጥባቸው በሌላ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባድማ በሆኑ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ፥ 11 የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ። እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡት ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የምድርን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ባድማ ሆኖ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባለው በዚህ ስፍራ በከተሞችም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉት የእረኞች መኖሪያ ይሆናል። 13 በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች በቈላውም ባሉ ከተሞች በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም አገር በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች መንጎቹ በተቈጣጣሪው እጅ እንደ ገና ያልፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 14 እነሆ፥ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የተናገርሁትን መልካም ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 15 በዚያም ዘመን በዚያም ጊዜ ለዳዊት የጽድቅን ቍጥቋጥ አበቅልለታለሁ፤ እርሱም ፍርድንና ጽድቅን በምድር ያደርጋል። 16 በዚያም ዘመን ይሁዳ ይድናል ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትቀመጣለች፤ የምትጠራበትም ስም። እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው። 17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከዳዊት ዘንድ አይታጣም፤ 18 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም። 19 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 20 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቀንና ሌሊት በወራቱ እንዳይሆን የቀን ቃል ኪዳኔንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፥ 21 በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ልጅ እንዳይሆንለት ከባሪዬ ከዳዊት ጋር፥ ከአገልጋዮቼም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ደግሞ ይፈርሳል። 22 የሰማይን ሠራዊት መቍጠር የባሕርንም አሸዋ መስፈር እንደማይቻል፥ እንዲሁ የባሪያዬን የዳዊትን ዘርና የሚያገለግሉኝን ሌዋውያንን አበዛለሁ። 23 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 24 ይህ ሕዝብ። እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን ወገን ጥሎአቸዋል ያለውን ነገር አትመለከትምን? እንዲሁ በፊታቸው ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝብ እንዳይሆን ሕዝቤን አቃልለዋል። 25 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የቀንና የሌሊት ቃል ኪዳኔን የሰማይንና የምድርንም ሥርዓት ያላጸናሁ እንደሆነ፥ 26 እኔም ደግሞ በአብርሃምና በይስሐቅ በያዕቆብም ዘር ላይ ገዦች ይሆኑ ዘንድ ከዘሩ እንዳልወስድ፥ የያዕቆብንና የባሪያዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ምርኮአቸውን እመልሳለሁና፥ እምራቸውማለሁና።

ኤርምያስ 34

1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና ከተሞችዋን ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሂድ ለይሁዳም ንጉሥ ለሴዴቅያስ ተናገር እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ በእሳትም ያቃጥላታል፤ 3 አንተም በእርግጥ ትያዛለህ በእጅም አልፈህ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም፤ ዓይንህም የባቢሎንን ንጉሥ ዓይን ታያለች፥ እርሱም ከአንተ ጋር አፍ ለአፍ ይናገራል፥ ወደ ባቢሎንም ትገባለህ። 4 ነገር ግን፥ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል። በሰይፍ አትሞትም፥ በሰላም ትሞታለህ እንጂ፤ 5 ከአንተ በፊት እንደ ነበሩ እንደ ዱሮ ነገሥታት እንደ አባቶችህ መቃጠል፥ እንዲሁ ያቃጥሉሃልና። ወየው! ጌታ ሆይ እያሉ ያለቅሱልሃል፤ እኔ ቃልን ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 6-7 የባቢሎንም ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳን ከተሞች ሁሉ፥ ከተመሸጉት ከይሁዳ ከተሞች የተረፉትን ለኪሶንና ዓዜቃን በወጋ ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ቃል ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው። 8-9 ሰው ሁሉ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነች ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ፥ አይሁዳዊ ወንድሙንም ማንም እንዳይገዛ፥ ስለ አርነታቸው አዋጅ እንዲነገር ንጉሡ ሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 10 ሰው ሁሉ ወንድ ባሪያውንና ሴት ባሪያውን አርነት እንዲያወጣ ከእንግዲህ ወዲህም ማንም እንዳይገዛቸው ወደ ቃል ኪዳኑ የገቡ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሰሙ አርነትም አወጡአቸው። 11 ነገር ግን ከዚያ በኋላ ተመልሰው አርነት ያወጡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻቸውን አስመለሱ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም አድርገው ገዙአቸው። 12 ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 13 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁን ከባርነት ቤት ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ። 14 ሰባት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ የተሸጠላችሁን ስድስትም ዓመት የተገዛላችሁን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ አርነት ታወጡታላችሁ፥ እያንዳንዱም ያወጣዋል፤ አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 15 እናንተም ዛሬ ተመልሳችሁ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን አርነት ለማውጣት አዋጅ በመንገር ለዓይኔ ደስ የሚያሰኝን ነገር አድርጋችሁ ነበር፥ በስሜም በሚጠራበት ቤት ውስጥ በፊቴ ቃል ኪዳን አድርጋችሁ ነበር። 16 ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አስነቀፋችሁ፥ እያንዳንዳችሁም በፈቃዳቸው እንዲሄዱ አርነት ያወጣችኋቸውን ወንድና ሴት ባሪያዎቻችሁን አስመለሳችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችም እንዲሆኑላችሁ ገዛችኋቸው። 17 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፤ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ መካከል እንድትበተኑ አደርጋችኋለሁ። 18 ቃል ኪዳኔንም የተላለፉትን ሰዎች፥ እንቦሳውንም ቈርጠው በቍራጩ መካከል ባለፉ ጊዜ በፊቴ ያደረጉትን የቃል ኪዳንን ቃል ያልፈጸሙትን፥ 19 የይሁዳን አለቆችና የኢየሩሳሌምን አለቆች ጃንደረቦችን ካህናትንም በእንቦሳም ቍራጭ መካከል ያለፉትን የአገሩን ሕዝብ ሁሉ፥ 20 ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። 21 የይሁዳንም ንጉሥ ሴዴቅያስንና አለቆቹን ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ ከእናንተም ለተመለሱት ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። 22 እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ወደዚህችም ከተማ እመልሳቸዋለሁ፤ እርስዋንም ይወጋሉ ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የሌለበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።

ኤርምያስ 35

1 በይሁዳ ንጉስ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 ወደ ሬካባውያን ቤት ሄደህ ተናገራቸው፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ከጓዳዎቹ ወደ አንዲቱ አግባቸው የወይን ጠጅም አጠጣቸው። 3 የከባስንን ልጅ የኤርምያስን ልጅ ያእዛንያን ወንድሞቹንም ልጆቹንም ሁሉ የሬካባውያንን ወገን ሁሉ ወሰድኋቸው፤ 4 ወደ እግዚአብሔርም ቤት በበረኛው በሰሎም ልጅ በመዕሤያ ጓዳ በላይ ባለው በአለቆች ጓዳ አጠገብ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ጌዴልያ ልጅ ወደ ሐናን ልጆች ጓዳ አገባኋቸው። 5 በሬካባውያንም ልጆች ፊት የወይን ጠጅ የሞላባቸውን ማድጋዎችንና ጽዋዎችን አኑሬ። የወይኑን ጠጅ ጠጡ አልኋቸው። 6 እነርሱ ግን እንዲህ አሉ። የወይኑን ጠጅ አንጠጣም፥ አባታችን የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ እንዲህ ብሎ አዝዞናልና። እናንተና ልጆቻችሁ ለዘላለም የወይን ጠጅ አትጠጡ። 7 በምትኖሩባት ምድር ላይ ብዙ ዘመን እንድትኖሩ፥ በዕድሜአችሁ ሙሉ በድንኳን ውስጥ ተቀመጡ እንጂ ቤትን አትሥሩ፥ ዘርንም አትዝሩ፥ ወይንም አትትከሉ፥ አንዳችም አይሁንላችሁ። 8 እኛም የአባታችንን የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብን ቃል ባዘዘን ነገር ሁሉ ታዝዘናል፤ እኛም ሚስቶቻችንም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ዕድሜአችንን ሙሉ የወይን ጠጅ አልጠጣንም፤ 9 የምንቀመጥበትንም ቤት አልሠራንም፤ የወይን ቦታና እርሻ ዘርም የለንም፤ 10 በድንኳንም ውስጥ ተቀምጠናል፥ ታዝዘናል፥ አባታችንም ኢዮናዳብ ያዘዘንን ሁሉ አድርገናል። 11 ነገር ግን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደዚህች ምድር በመጣ ጊዜ። ኑ ከከለዳውያን ሠራዊትና ከሶርያ ሠራዊት ፊት የተነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንሂድ አልን፤ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ተቀመጥን። 12 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 13 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው። ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር። 14 የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ያዘዛቸው ቃል ተፈጸመ፤ ለአባታቸውም ትእዛዝ ታዝዘዋልና እስከ ዛሬ ድረስ አይጠጡም፤ እኔም በማለዳ ተነሥቼ ተናግሬአችኋለሁ፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም አልሰማችሁኝም። 15 ደግሞም። እያንዳንዳችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፥ ሥራችሁንም አሳምሩ፥ ታመልኩአቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠሁት ምድር ትቀመጣላችሁ እያልሁ በማለዳ ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ጆሬአችሁን አላዘነበላችሁም እኔንም አልሰማችሁኝም። 16 የሬካብ ልጅ የኢዮናዳብ ልጆች አባታቸው ያዘዛቸውን ትእዛዝ ፈጽመዋልና፥ ይህ ሕዝብ ግን አልሰማኝምና፤ 17 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በተናገርኋቸው ጊዜ አልሰሙምና፥ በጠራኋቸውም ጊዜ አልመለሱልኝምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚቀመጡ ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ። 18 ኤርምያስም ሬካባውያንን እንዲህ አላቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለአባታችሁ ለኢዮናዳብ ትእዛዝ ታዝዛችኋልና፥ ትእዛዙንም ሁሉ ጠብቃችኋልና፥ ያዘዛችሁንም ፈጽማችኋልና፤ 19 ስለዚህ በፊቴ የሚቆም ሰው ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ወገን ለዘላለም አይታጣም።

ኤርምያስ 36

1 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2 አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 3 ምናልባት የይሁዳ ቤት። እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ። 4 ኤርምያስም የኔርያን ልጀ ባሮክን ጠራ፥ ባሮክም እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። 5 ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው። እኔ ተግዤአለሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት እገባ ዘንድ አልችልም። 6 አንተ ግን ሂድ፥ ከአፌም የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆር በክርታሱ አንብብ፤ ደግሞም ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። 7 እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ጸሎታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትወድቅ ይሆናል፥ ሁሉም ከክፉ መንገዱ ይመለስ ይሆናል። 8 የኔርያም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ። 9 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም አዋጅ ነገሩ። 10 ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሄር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሐፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ጓዳ በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ በመጽሐፉ አነበበ። 11 የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ በሰማ ጊዜ፥ 12 ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ጸሐፊው ጓዳ ወረደ፤ እነሆም፥ አለቆች ሁሉ፥ ጸሐፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 13 ሚክያስም ባሮክ በሕዝቡ ጆሮ በመጽሐፉ ባነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 14 አለቆቹም ሁሉ። በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና የሚል መልእክት በኵሲ ልጅ በሰሌምያ ልጅ በናታንያ ልጅ በይሁዲ እጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርያም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ መጣ። 15 እነርሱም። እስኪ ተቀመጥ፥ በጆሮአችንም አንብብ አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው። 16 ቃሉንም ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተመካከሩ፥ ባሮክንም። ይህን ቃል ሁሉ በእርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን አሉት። 17 ባሮክንም። ይህን ቃል ሁሉ ከአፉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን ብለው ጠየቁት። 18 ባሮክም። ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፥ እኔም በመጽሐፉ ላይ በቀለም እጽፍ ነበር ብሎ መለሰላቸው። 19 አለቆቹም ባሮክን። አንተና ኤርምያስ ሂዱ፥ ተሸሸጉ፥ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ አሉት። 20 ወደ ንጉሡም ወደ አደባባይ ገቡ፥ ክርታሱንም በጸሐፊው በኤሊሳማ ጓዳ አኑረውት ነበር፤ ቃሉንም ሁሉ በንጉሡ ጆሮ ተናገሩ። 21 ንጉሡም ክርታሱን ያመጣ ዘንድ ይሁዲን ላከ፥ እርሱም ከጸሐፊው ከኤሊሳማ ጓዳ ወሰደው፤ ይሁዲም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። 22 ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር። 23 ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያህል ባነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ በካራ ቀደደው፤ ክርታሱም በምድጃ ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ጣለው። 24 ንጉሡም ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም። 25 ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም። 26 ንጉሡም ጸሐፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፥ እግዚአብሔር ግን ሰወራቸው። 27 ንጉሡም ክርስታሱንና ባሮክ ከኤርምያስ አፍ የጻፈውን ቃል ካቃጠለ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 28 ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፥ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም ባቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 29 የይሁዳንም ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ። የባቢሎን ንጉሥ በእርግጥ ይመጣል ይህችንም አገር ያፈርሳታል ከሰውና ከእንስሳም ባዶ ያደርጋታል ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። 30 ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀማጭ አይኖርለትም፥ ሬሳውም በቀን ለትኩሳት በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። 31 ስለ ኃጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን ባሪያዎቹንም እቀጣለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ። ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ጻፈበት፥ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት።

ኤርምያስ 37

1 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ። 2 እርሱም ሆነ ባሪያዎቹ የአገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 3 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። 4 እርሱንም በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር። 5 የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ። 6 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 7 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት። እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል። 8 ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል። 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አይሄዱምና። ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። 10 እናንተም የሚዋጉትን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ብትመቱት ኖሮ፥ ከእነርሱም የተወጉት ብቻ ቢቀሩ ኖሮ፥ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ተነሥቶ ይህችን ከተማ በእሳት ባቃጠሉአት ነበር። 11 የከለዳውያንም ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ፥ 12 ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን እድል ፈንታ ከዚያ ይቀበል ዘንድ ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። 13 በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፤ እርሱም። ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው። 14 ኤርምያስም። ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም አለ፤ እርሱ ግን አልሰማውም፥ የሪያም ኤርምያስን ይዞ ወደ አለቆች አመጣው። 15 አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የግዞት ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ አኖሩት። 16 ኤርምያስም ወደ ጕድጓድ ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ ኤርምያስም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥ 17 ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ። በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን? ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም። አዎን አለ። ደግሞም። በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ አለ። 18 ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው። በግዞት ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባሪያዎችህን ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው? 19 የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ? 20 ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፥ እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፤ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ። 21 ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በግዞት ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።

ኤርምያስ 38

1 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ። 2 ኤርምያስ እንዲህ ብሎአልና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፥ በሕይወትም ይኖራል። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል። 4 አለቆቹም ንጉሡን። ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና አሉት። 5 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው አለ። 6 ኤርምያስንም ወሰዱት በግዞት ቤቱም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ። 7 በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር። 8 አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው። 9 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ነቢዮን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ሁሉ ክፉ አድርገዋል፤ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል። 10 ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክም። ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው። 11 አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው። 12 ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን። ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ። 13 ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት ከጕድጓድም አወጡት፥ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ። 14 ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን። አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ አለው። 15 ኤርምያስም ሴዴቅያስን። ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም አለው። 16 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ። 17 ኤርምያስም ሴዴቅያስን። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18 ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም አለው። 19 ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን። ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ አለው። 20 ኤርምያስም እንዲህ አለው። አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል እባክህ፥ ስማ፤ ይቀናሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች። 21 ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው። 22 እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች። ባለምዋሎችህ አታልለውሃል አሸንፈውህማል፤ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ። 23 ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች። 24 ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው። ይህም ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም። 25 አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው። ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፤ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ አንተ። 26 በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ በላቸው። 27 አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁ፥ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተው። 28 ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።

ኤርምያስ 39

1 ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ 2 በሴዴቅያስም በአሥራ አንደኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በዘጠነኛው ቀን ከተማይቱ ተሰበረች። 3 የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ሳምጋርናቦ፥ ሠርሰኪም፥ ራፌስ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ራብማግ፥ ከቀሩት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ። 4 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሰልፈኞቹም ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ ኰበለሉ፥ በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥር መካከል ከነበረው ደጅ ከከተማይቱ ወጡ፤ በዓረባም መንገድ ወጡ። 5 የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፥ ሴዴቅያስንም በኢያሪኮ ሜዳ አገኙት፤ ይዘውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 6 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በዓይኑ ፊት በሪብላ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን ከበርቴዎች ሁሉ ገደለ። 7 የሴዴቅያስንም ዓይን አወጣ፥ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። 8 ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። 9 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ ወደ እርሱም የኰበለሉትን ሰዎች የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው። 10 አንዳች ከሌላቸው ከሕዝቡ ድሆች ግን የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን በይሁዳ አገር ተዋቸው፥ የወይኑን ቦታና እርሻውን በዚያን ጊዜ ሰጣቸው። 11-12 የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ። ውሰደውና በመልካም ተመልከተው፥ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ክፉን ነገር አታድርግበት ብሎ የዘበኞቹን አለቃ ናቡዘረዳንን አዘዘ። 13 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ላከ፥ ናቡሽዝባንም ራፋስቂስም ኤርጌል ሳራስርም ራብማግም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ ላኩ፤ 14 ኤርምያስንም ከግዞት ቤት አደባባይ አወጡት፥ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እንዲህም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ። 15 በግዞትም ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ። 16 ሂድ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። 17 በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። 18 ፈጽሜ አድንሃለሁ ነፍስህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 40

1 ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች መካከል የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን በሰንሰለት አስሮ በወሰደው ጊዜ ከራማ ከለቀቀው በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 የዘበኞቹም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው እንዲህም አለው። አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ፤ 3 እግዚአብሔርም አመጣው እንደ ተናገረውም አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርታችኋልና፥ ቃሉንም አልሰማችሁምና ይህ ነገር ሆነባችሁ። 4 አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ካለችው ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ቢታይህ፥ ና፥ እኔም በመልካም አይሃለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፥ ተቀመጥ፤ እነሆ፥ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ትሄድ ዘንድ መልካም መስሎ ወደሚታይህ ደስ ወደሚያሰኝህም ስፍራ ሂድ። 5 እርሱም ገና ሳይመለስ። የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፥ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ትሄድ ዘንድ ደስ ወደሚያሰኝህ ስፍራ ሂድ አለው። የዘበኞቹም አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው። 6 ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፥ ከእርሱም ጋር በአገሩ ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ተቀመጠ። 7 በየሜዳውም የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድር ላይ እንደ ሾመ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም፥ ወደ ባቢሎን ያልተማረኩትን የምድርን ድሆች፥ እንዳስጠበቀ በሰሙ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ 8 የቃሬያም ልጅ ዮሐናንና ዮናታን፥ የተንሑሜትም ልጅ ሠራያ፥ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ ከሰዎቻቸው ጋር ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። 9 የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ብሎ ማለ። ለከለዳውያን ትገዙ ዘንድ አትፍሩ፤ በምድር ተቀመጡ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል። 10 እኔም፥ እነሆ፥ ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት እቆም ዘንድ በምጽጳ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይንንና የበጋ ፍሬ ዘይትንም አከማቹ፥ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፥ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ። 11 በሞዓብም በአሞንም ልጆች መካከል በኤዶምያስም በምድርም ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የይሁዳን ቅሬታ እንዳስቀረ፥ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው በሰሙ ጊዜ፥ 12 አይሁድ ሁሉ ከተሰደዱበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ፥ ወደ ይሁዳም አገር ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፥ ወይንና የበጋንም ፍሬ እጅግ ብዙ አከማቹ። 13 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን በየሜዳውም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው። 14 የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ ይገድልህ ዘንድ የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ሰደደ ታውቃለህን? አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም። 15 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን። እባክህ፥ ልሂድ፤ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ የይሁዳም ቅሬታ እንዲጠፋ ነፍስህን ስለ ምን ይገድላል? ብሎ በምጽጳ በቆይታ ለጎዶልያስ ተናገረ። 16 የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን። በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ አለው።

ኤርምያስ 41

1 በሰባተኛውም ወር ከመንግሥት ወገንና ከንጉሡ ዋና ዋና አለቆች አንዱ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከአሥር ሰዎች ጋር ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በምጽጳ በአንድ ላይ እንጀራ በሉ። 2 የናታንያም ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩት አሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ፥ የባቢሎንም ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን ገደሉ። 3 እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፥ በዚያም የተገኙትን የከለዳውያንን ሰልፈኞች ሁሉ ገደላቸው። 4 ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ ማንም ሳያውቅ በሁለተኛው ቀን፥ 5 ጢማቸውን ላጭተው ልብሳቸውንም ቀድደው ገላቸውንም ነጭተው፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ያቀርቡ ዘንድ የእህል ቍርባንና ዕጣን በእጃቸው እየያዙ፥ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬምና ከሴሎ ከሰማርያም መጡ። 6 የናታንያም ልጅ እስማኤል ከምጽጳ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ፤ በተገናኛቸውም ጊዜ። ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ አላቸው። 7 ወደ ከተማም መካከል በመጡ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ገደሉአቸው፥ በgWdጓድም መካከል ጣሉአቸው። 8 በመካከላቸውም እስማኤልን። በሜዳ የተሸሸገ ስንዴና ገብስ ዘይትና ማርም አለንና አትግደለን የሚሉት አሥር ሰዎች ተገኙ። እርሱም ተዋቸው፥ ከወንድሞቻቸውም ጋር አልገደላቸውም። 9 እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን የሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጕድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ የሠራው gWdጓድ ነበረ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት። 10 እስማኤልም በምጽጳ የነበረውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ የንጉሡን ሴቶች ልጆች የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በምጽጳ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ ማረካቸው፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል ማርኮ ወደ አሞን ልጆች ይሄድ ዘንድ ተነሣ። 11 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ከእርሱም ጋር የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ 12 ሰዎቹን ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ሊዋጉ ሄዱ፥ በገባዖንም ባለው በታላቁ ውኃ አጠገብ አገኙት። 13 ከእስማኤልም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14 እስማኤልም ከምጽጳ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ዘወር ብለው ተመለሱ፥ ወደ ቃሬያም ልጅ ወደ ዮሐናን ሄዱ። 15 የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ ወደ አሞንም ልጆች ሄደ። 16 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምጽጳ ከገደለው በኋላ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ሰልፈኞች፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ ጃንደረቦችንም፥ ወሰዱ፤ 17 ተነሥተውም ወደ ግብጽ ይሄዱ ዘንድ በቤተልሔም አጠገብ ባለው በጌሮት ከመዓም ተቀመጡ፤ 18 እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለ ገደለው ከለዳውያንን ፈርተዋልና።

ኤርምያስ 42

1 የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝብም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥ 2-3 ነብዩንም ኤርምያስን። ዓይኖችህ እንዳዩን ከብዙ ጥቂት ቀርተናልና ልመናችን፥ እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለ እኛ፥ ስለዚህ ቅሬታ ሁሉ፥ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት። 4 ነቢዩም ኤርምያስ። ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም አላቸው። 5 ኤርምያስንም። አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ እጅ ወደ እኛ የላከውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን። 6 የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን አሉት። 7 ከአሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 8 የቃሬያንም ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥ እንዲህም አላቸው። 9 ጸሎታችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 10 ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። 11 ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ። 13 እናንተ ግን። በዚህች ምድር አንቀመጥም ብትሉ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ 14 እናንተም። አይደለም፤ ሰልፍ ወደማናይባት የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት ወደማንራብባትም ወደ ግብጽ ምድር እንሄዳለን በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥ 15 እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ግብጽ ትገቡ ዘንድ በዚያም ትቀመጡ ዘንድ ፊታችሁን ብታቀኑ፥ 16 የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብጽ ምድር ያገኛችኋል፥ ስለ እርሱም የምትደነግጡበት ራብ በዚያ በግብጽ ይደርስባቸኋል፥ በዚያም ትሞታላችሁ። 17 ወደ ግብጽም ይገቡ ዘንድ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን በሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሆንባቸዋል፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይቀርም፥ ማንም አያመልጥም። 18 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። KWTaዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብጽ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመደነቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም። 19 እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ እግዚአብሔር። ወደ ግብጽ አትግቡ ብሎ ተናግሮባችኋልና ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ። 20 እናንተ። ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፥ አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል። 21 እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፥ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም። 22 አሁንም ሄዳችሁ እንድትቀመጡ በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንድትሞቱ በእርግጥ እወቁ።

ኤርምያስ 43

1 የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፥ ለእነርሱ አምላካቸው እግዚአብሔር የላከውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ ለሕዝቡ ሁሉ መናገርን በፈጸመ ጊዜ፥ 2 የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ትዕቢተኞችም ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን። ሐሰት ተናግረሃል፤ አምላካችን እግዚአብሔር። በዚያ ትቀመጡ ዘንድ ወደ ግብጽ አትግቡ ብሎ አልላከህም፤ 3 ነገር ግን ከለዳውያን እንዲገድሉን ወደ ባቢሎንም እንዲማርኩን በእጃቸው አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ የኔርያ ልጅ ባሮክ በላያችን ላይ አነሣሥቶሃል አሉት። 4 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ በይሁዳ ምድር ይቀመጡ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 5 የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የጭፍራ አለቆችም ሁሉ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተሰደዱባቸው ከአሕዛብ ሁሉ የተመለሱትን የይሁዳን ቅሬታ ሁሉ፥ 6 ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም የንጉሡንም ሴቶች ልጆች፥ የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከሳፋን ልጅ ከአኪቃም ልጅ ከጎዶልያስ ጋር የተዋቸውን ሰዎች ሁሉ፥ ነቢዩንም ኤርምያስን የኔርያንም ልጅ ባሮክን ወሰዱ፤ 7 የእግዚአብሔርንም ቃል አልሰሙምና ወደ ግብጽ ምድር ገቡ፥ እስከ ጣፍናስ ድረስ መጡ። 8 በጣፍናስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 9 ታላላቆችን ድንጋዮች በእጅህ ውሰድ፥ የይሁዳም ሰዎች እያዩ በጣፍናስ ባለው በፈርዖን ቤት ደጅ መግቢያ ሸሽጋቸው፤ 10 እንዲህም በላቸው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ልኬ ባሪያዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆር አመጣለሁ፥ ዙፋኑንም እኔ በሸሸግኋቸው በእነዚህ ድንጋዮች ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ማለፊያውን ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል። 11 መጥቶም የግብጽን ምድር ይመታል፥ ለሞትም የሚሆነውን ለሞት፥ ለምርኮም የሚሆነውን ለምርኮ፥ ለሰይፍም የሚሆነውን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። 12 በግብጽም አማልክት ቤቶች እሳትን ያነድዳል ያቃጥላቸውማል ይማርካቸውማል፤ እረኛም ደበሎውን እንደሚደርብ እንዲሁ የግብጽን አገር ይደርባል፤ ከዚያም በሰላም ይወጣል። 13 በግብጽም ምድር ያለውን የሄልዮቱን ከተማ ሐውልቶች ይሰብራል፥ የግብጽንም አማልክት ቤቶች በእሳት ያቃጥላል።

ኤርምያስ 44

1 በግብጽ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም። 3 ይህም የሆነው ያስቈጡኝ ዘንድ ስላደረጉት ክፋት፥ ለማያውቁአቸውም ለሌሎች አማልክት ያጥኑ ዘንድ ያመልኩአቸውም ዘንድ ስለሄዱ ነው። 4 በማለዳም ተነሥቼ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ሰደድሁባችሁና። እንደዚህ እንደ ጠላሁት ያለ ርኩስ ነገር አታድርጉ አልኋችሁ። 5 ነገር ግን አልሰሙም ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት እንዳያጥኑ ጆሮአቸውን አላዘነበሉም። 6 ስለዚህ መዓቴና ቍጣዬ ፈሰሱ፥ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደዱ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ ባድማም ሆኑ። 7 አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል። ከይሁዳ ወገን ቅሬታ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ብላቴናንና ሕፃንን ከመካከላችሁ ታጠፉ ዘንድ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? 8 ሰውነታችሁንም ታጠፉ ዘንድ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ ትሆኑ ዘንድ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት በማጠናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ? 9 በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት፥ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን? 10 እስከ ዛሬ ድረስ አልተዋረዱም አልፈሩምም፥ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዓቴ አልሄዱም። 11 ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲ ይላል። እነሆ፥ ይሁዳን ሁሉ አጠፋ ዘንድ ፊቴን ለክፋት በላያችሁ አደርጋለሁ። 12 ወደ ግብጽም ይገቡ ዘንድ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ቅሬታ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብጽም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመደነቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ። 13 ኢየሩሳሌምንም እንደ ቀጣሁ፥ እንዲሁ በግብጽ ምድር የሚኖሩትን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እቀጣለሁ። 14 በዚያ ለመቀመጥ ወደ ግብጽ ምድር ከሄዱ፥ ወደ ይሁዳ አገር ተመልሰው በዚያ ይቀመጡ ዘንድ ከሚወድዱ ከይሁዳ ቅሬታ ወገን የሚያመልጥና የሚቀር ወደዚያም የሚመለስ የለም፤ ከሚያመልጥም በቀር ማንም አይመለስም። 15 ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ በዚያም የቆሙ ሴቶች ሁሉ፥ በግብጽ ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት እንዲህም አሉ። 16 አንተ በእግዚአብሔር ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም። 17 ነገር ግን እኛና አባቶቻችን ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞች በኢየሩሳሌም አደባባይ እናደርገው እንደ ነበረ፥ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ የመጠጥንም KWrባን እናፈስስላት ዘንድ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያን ጊዜም እንጀራ እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ክፉም አናይም ነበር። 18 ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርስዋም የመጠጥን ቍርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ በሁሉ ነገር ተቸግረናል፥ በሰይፍና በራብ አልቀናል። 19 እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት የመጠጥንም ቍርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ምስልዋን ለማበጀት እንጐቻ አድርገንላት ኖሮአልን? የመጠጥንም ቍርባን አፍስሰንላት ኖሮአልን? 20 ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፥ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ለሕዝቡም ሁሉ፥ መለሰላቸው እንዲህም አለ። 21 እናንተና አባቶቻችሁ ነገሥታቶቻችሁም አለቆቻችሁም የምድርም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን እግዚአብሔር ያሰበው በልቡም ያኖረው አይደለምን? 22 እግዚአብሔርም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኵሰት ይታገሥ ዘንድ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መደነቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደ ሆነ የሚኖርባት የለም። 23 ስላጠናችሁ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ስለ በደላችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዓቱም በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደ ሆነ ይህች ክፉ ነገር አግኝታችኋለች። 24 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ። በግብጽ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ። ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን አላችሁ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። 26 እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ ይሁዳ ሁሉ፥ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ። ሕያው እግዚአብሔርን! ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 27 እነሆ፥ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት እተጋባቸዋለሁ፤ በግብጽም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ። 28 ከሰይፍም የሚያመልጡ ጥቂት ሰዎች ሆነው ከግብጽ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ ሊቀመጡም ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የይሁዳ ቅሬታ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንዲጸና ያውቃሉ። 29 ቃሌም በላያችሁ ለክፋት እንዲጸና ታውቁ ዘንድ በዚህች ስፍራ እንድቀጣችሁ ምልክታችሁ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። 30 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው ነፍሱንም ለፈለገው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚፈልጉ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።

ኤርምያስ 45

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የኔርያ ልጅ ባሮክ እነዚህን ቃሎች ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 ባሮክ ሆይ፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል። 3 አንተ። እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፥ ዕረፍትንም አላገኘሁም ብለሃል። 4 እንዲህ በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ ነው። 5 ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፥ እነሆ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።

ኤርምያስ 46

1 ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 ስለ ግብጽ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት። 3 ጋሻ ጦር አዘጋጁ ወደ ሰልፍም ቅረቡ። 4 ፈረሰኞች ሆይ፥ ፈረሶችን ለgWmuና ውጡ፥ ራስ ቍርንም ደፍታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ። 5 ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 6 ፈጣኑ አያመልጥም ኃያሉም አይድንም፤ በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል ተሰናክለው ወደቁ። 7 ይህ እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዝ የሚናወጥ ማን ነው? 8 ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዙ ይናወጣል፤ እርሱም።እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እከድናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሎአል። 9 ፈረሶች ሆይ፥ ውጡ፤ ሰረገሎችም ሆይ፥ ንጐዱ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፋጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ። 10 ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና። 11 ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ፥ ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፤ መድኃኒትን ያበዛሽው በከንቱ ነው፤ መዳን የለሽም። 12 ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ gWsKWlናሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል። 13 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንዲመጣና የግብጽን ምድር እንዲመታ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 14 በግብጽ ተናገሩ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና። ተነሥ ተዘጋጅም በሉ። 15 ኃይለኞችህ ስለ ምን ተወገዱ? እግዚአብሔር ስላደከማቸው አልቆሙም። 16 ብዛታቸውም ተሰናከለ፥ ሰውም አንዱ በአንዱ ላይ ወደቀ፤ እነርሱም። ተነሡ፥ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባት ምድር እንመለስ አሉ። 17 በዚያም የግብሥ ንጉሥ ፈርዖንን። ሰዓቱን የሚያሳልፍ gWrvኛ ብለው ጠሩት። 18 እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 19 አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ልጅ ሆይ፥ ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠልማለችና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና ለምርኮ የሚሆን ዕቃ አዘጋጂ። 20 ግብጽ የተዋበች ጊደር ናት፤ ጥፋት ግን ይመጣል፥ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል። 21 በእርስዋም ያሉ የተቀጠሩ ሠራተኞች እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም። 22 ከሠራዊትም ጋር ይሄዳሉና ድምፅ እንደ እባብ ይተምማል፤ እንደ እንጨት ቈራጮችም በምሳር ይመጡባታል። 23 ይቈጠሩ ዘንድ የማይቻሉትን የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከአንበጣ ይልቅ በዝተዋልና ቍጥርም የላቸውምና። 24 የግብጽ ልጅ ታፍራለች፤ በሰሜን ሕዝብ እጅ አልፋ ትሰጣለች። 25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፤ 26 ነፍሳቸውንም በሚፈልጉ ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡክደነፆር እጅ፥ በባሪያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል እግዚአብሔር። 27 ነገር ግን አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁ፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል ተዘልሎም ይቀመጣል፥ ማንም አያስፈራውምም። 28 አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም ያሰደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።

ኤርምያስ 47

1 ፈርዖንም ጋዛን ሳይመታ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ውኃ ከሰሜን ይነሣል የሚያጥለቀልቅም ፈሳሽ ይሆናል፤ በአገሪቱና በመላዋ ሁሉ፥ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ይጐርፋል፤ ሰዎቹም ይጮኻሉ፥ በምድርም የሚሮሩ ሁሉ ያለቅሳሉ። 3 ከኃይለኞች ፈረሶች ከኮቴያቸው መጠብጠብ ድምፅ፥ ከሰረገሎቹም መሸከርከር፥ ከመንኰራኵሮቹም መትመም የተነሣ አባቶች በእጃቸው ድካም ምክንያት ፊታቸውን መልሰው ወደ ልጆቻቸው አይመለከቱም። 4 ይህም የሚሆነው ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ የቀሩትንም ረዳቶች ሁሉ ከጢሮስና ከሲዶና ይቈርጥ ዘንድ ስለሚመጣው ቀን ነው፤ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንና የከፍቶርን ደሴት ቅሬታ ያጠፋልና። 5 ቡሀነት በጋዛ ላይ መጥቶአል፤ አስቀሎና ጠፋች፤ የዔናቅ ቅሬታዎች ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ገላችሁን ትነጫላችሁ? 6 አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፥ ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ። 7 እግዚአብሔር በአስቀሎናና በባሕር ዳር ላይ ትእዛዝ ሰጥቶአልና፥ በዚያም አዘጋጅቶታልና እንዴት ዝም ትላለህ?

ኤርምያስ 48

1 ስለ ሞዓብ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ናባው ጠፍታለችና ወዮላት! ቂርያታይም አፍራለች ተይዛማለች፤ ሚሥጋብ አፍራለች ደንግጣማለች። 2 ከእንግዲህ ወዲህ የሞዓብ ትምክሕት የለም፤ በሐሴቦን ላይ። ኑ ሕዝብ እንዳትሆን እናጥፋት ብለው ክፉ ነገር አስበውባታል። መድሜን ሆይ፥ አንቺ ደግሞ ትጠፊአለሽ ሰይፍም ያሳድድሻል። 3 መፍረስና ታላቅ ጥፋት የሚል የጩኸት ቃል ከሖሮናይም ተሰማ። 4 ሞዓብ ጠፍታለች፥ ልጆችዋም ጩኸትን አሰምተዋል። 5 በሉሒት ዓቀበት ልቅሶ እያለቀሱ ይወጣሉና፥ በሖሮናይምም ቍልቍለት የጥፋትንና የመባባትን ጩኸት ሰምተዋል። 6 ሸሽታችሁ ራሳችሁን አድኑ፤ በምድረ በዳ እንዳለ KWTቋጦ ሁኑ። 7 በሥራሽና በመዝገብሽ ታምነሻልና አንቺ ደግሞ ትያዢያለሽ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል። 8 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ አጥፊ ወደ ከተማ ሁሉ ይመጣል አንዲትም ከተማ አትድንም፤ ሸለቆውም ይጠፋል ሜዳውም ይበላሻል። 9 በርራ እንድትወጣ ለሞዓብ ክንፍ ስጡአት፤ ከተሞችዋም ባድማና ወና ይሆናሉ። 10 የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደግ ርጉም ይሁን፥ ሰይፉንም ከደም የሚከለክል ርጉም ይሁን። 11 ሞዓብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ቅምጥል ነበረ፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃውም ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፤ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። 12 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሚያገላብጡትን የምልክበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ያገላብጡታል፤ ጋኖቹንም ባዶ ያደርጋሉ፥ መስቴዎቹንም ይሰብራሉ። 13 የእስራኤልም ቤት ይታመንባት ከነበረው ከቤቴል እንዳፈረ፥ እንዲሁ ሞዓብ ከካሞሽ ያፍራል። 14 እናንተ። እኛ ኃያላን በሰልፍም ጽኑዓን ነን እንዴት ትላላችሁ? 15 ሞዓብ ፈርሶአል፥ ከተሞቹም ጠፍተዋል፥ የተመረጡትም ጕልማሶች ወደ መታረድ ወርደዋል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ ንጉሥ። 16 የሞዓብ ጥፋት ሊመጣ ቀርቦአል መከራውም እጅግ ይፈጥናል። 17 በዙሪያው ያላችሁ ሁሉ ስሙንም የምታውቁ ሁሉ። ብርቱው በትር፥ የከበረው ሽመል፥ እንዴት ተሰበረ! ብላችሁ አልቅሱለት። 18 በዲቦን የምትኖሪ ሆይ፥ ሞዓብን የሚያጠፋ ወጥቶብሻልና፥ አምባሽንም ሰብሮአልና ከክብርሽ ውረጂ በጥማትም ተቀመጪ። 19 በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፥ በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤ የሸሸውንና ያመለጠችውን። ምን ሆኖአል? ብለሽ ጠይቂ። 20 ሞዓብም ፈርሶአልና አፈረ፤ አልቅሱ ጩኹም፤ ሞዓብ እንደ ተዘረፈ በአርኖን አጠገብ አውሩ። 21 በሜዳ ላይ፥ በሖሎን፥ በያሳ፥ በሜፍዓት ላይ፥ 22 በዲቦን፥ በናባው፥ በቤት ዲብላታይም ላይ፥ 23 በቂርያታይም፥ በቤትጋሙል፥ 24 በቤትምዖን ላይ፥ በቂርዮት፥ በባሶራ፥ በሞዓብም ምድር ከተሞች ሁሉ ቅርብና ሩቅ በሆኑ ላይ ፍርድ መጥቶአል። 25 የሞዓብ ቀንድ ተቈረጠ ክንዱም ተሰበረ፥ ይላል እግዚአብሔር። 26 በእግዚአብሔር ላይ ኰርቶአልና አስክሩት፤ ሞዓብም በጥፋቱ ላይ ይንከባለላል፥ ደግሞም መሳቂያ ይሆናል። 27 እስራኤል ለአንተ መሳቂያ አልሆነምን? ወይስ በሌቦች መካከል ተገኝቶአልን? ስለ እርሱ በተናገርህ ጊዜ ራስህን ትነቀንቃለህ። 28 እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፥ ከተሞችን ትታችሁ በዓለት ውስጥ ተቀመጡ፥ በገደል አፋፍም ቤትዋን እንደምትሠራ እንደ ርግብ ሁኑ። 29 እጅግ እንደ ታበየ ስለ ሞዓብ ትዕቢት ስለ ትምክህቱም ስለ kWraቱም ስለ መጓደዱም ስለ ልቡም ትዕቢት ሰምተናል። 30 ቍጣው ምንም እንደ ሆነ አውቃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ፉከራው ምንም አልሠራም። 31 ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ ለሞዓብም ሁሉ እጮኻለሁ፤ ለቂርሔሬስ ሰዎች አለቅሳለሁ። 32 አንቺ የሴባማ ወይን ሆይ፥ ከኢያዜር ልቅሶ ይልቅ ለአንቺ አለቅሳለሁ፤ ቅርንጫፎችሽ ባሕርን ተሻግረዋል፥ ወደ ኢያዜርም ባሕር ደርሰዋል፤ አጥፊው በሰብልሽና በወይንሽ ላይ መጥቶአል። 33 ሐሤትና ደስታ ከፍሬያማው እርሻና ከሞዓብ ምድር ጠፍተዋል፤ ጠጁን ከመጥመቂያው አጥፍቻለሁ፤ ጠማቂውም በእልልታ አይጠምቅም፥ እልልታቸውም እልልታ አይሆንም። 34 ከሐሴቦን ጩኸት እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ ድረስ ድምፃቸውን ሰጥተዋል፤ ከዞዓር እስከ ሖሮናይምና እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ ይደርሳል፤ የኔምሬም ውኃ ደግሞ ይደርቃል። 35 በኮረብታው መስገጃ ላይ የሚሠዋውን ለአማልክቱም የሚያጥነውን ከሞዓብ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 36 ያተረፈው ትርፉ ጠፍቶበታልና፤ ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ እንቢልታ ይጮኻል፥ ልቤም ለቂርሔሬስ ሰዎች እንደ እንቢልታ ይጮኻል። 37 ራስ ሁሉ መላጣ ጢምም ሁሉ የተላጨ ነውና፤ በእጅም ሁሉ ላይ ክትፋት በወገብም ላይ ማቅ አለና። 38 ሞዓብን እንደማይወደድ ዕቃ ሰብሬአለሁና በሞዓብ ሰገነት ሁሉ ላይ በአደባባዩም ላይ በሁሉም ቦታ ልቅሶ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 39 እንዴት ተገለበጠ! በእፍረትም የተነሣ ሞዓብ ጀርባውን እንዴት መለሰ! ብላችሁ አልቅሱ። ሞዓብም በዙሪያው ላሉት ሁሉ መሳቂያና ድንጋጤ ይሆናል። 40 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እንደ ንስር ይበርራል ክንፉንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል። 41 ከተሞቹ ተይዘዋል፥ አምባዎቹም ተወስደዋል፥ በዚያም ቀን የሞዓብ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል። 42 ሞዓብም በእግዚአብሔር ላይ ኰርቶአልና ሕዝብ ከመሆን ይጠፋል። 43 በሞዓብ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና gWdጓድ ወጥመድም በአንተ ላይ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 44 በሞዓብ ላይ የመጐብኘትን ዓመት አመጣበታለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በፍርሃት የሸሸ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቃል፥ ከgWdጓድም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 45 የሸሹ ደክመው ከሐሴቦን ጥላ በታች ቆመዋል፤ እሳት ከሐሴቦን ነበልባልም ከሴዎን ወጥቶአል የሞዓብንም ማዕዘን የሤትንም ልጆች አናት በልቶአል። 46 ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የካሞሽ ወገን ጠፍቶአል፤ ወንዶች ልጆችህ ተማርከዋልና፥ ሴቶች ልጆችህም ወደ ምርኮ ሄደዋልና። 47 ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። የሞዓብ ፍርድ እስከዚህ ድረስ ነው።

ኤርምያስ 49

1 ስለ አሞን ልጆች፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለእስራኤል ልጆች የሉትምን? ወይስ ወራሽ የለውምን? ስለ ምን ሚልኮም ጋድን ወረሰ? ሕዝቡስ በከተሞቹ ላይ ስለ ምን ተቀመጠ? 2 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአሞን ልጆች ከተማ በረባት ላይ የሰልፍ ውካታን የማሰማበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የፍርስራሽ ክምርም ትሆናለች፥ ሴቶች ልጆችዋም በእሳት ይቃጠላሉ፥ እስራኤልም የወረሱትን ይወርሳል፥ ይላል እግዚአብሔር። 3 ሐሴቦን ሆይ፥ ጋይ ፈርሳለችና አልቅሺላት እናንተም የረባት ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ሚልኮም ካህናቱና አለቆቹም በአንድነት ይማረካሉና ጩኹ፥ ማቅም ታጠቁ፥ አልቅሱም፥ በቅጥሮችም መካከል ተርዋርዋጡ። 4 ማን ይመጣብኛል ብለሽ በመዝገብሽ የታመንሽ አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ በሸለቆችሽ፥ ውኃ በሚያረካቸው ሸለቆችሽ፥ ስለ ምን ትመኪያለሽ? 5 እነሆ፥ በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ ፍርሃትን አመጣብሻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እያንዳንዳችሁም በፊታችሁ ወዳለው ስፍራ ትሰደዳላችሁ፥ የሚሸሹትንም የሚሰበስብ የለም። 6 ነገር ግን ከዚያ በኋላ የአሞንን ልጆች ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 ስለ ኤዶምያስ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? 8 ጥበባቸውስ አልቆአልን? እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፥ የዔሳውን ጥፋት፥ የምጐበኝበትን ጊዜ፥ አመጣበታለሁና ሽሹ፥ ወደ ኋላ ተመለሱ፥ በጥልቅም ውስጥ ተቀመጡ። 9 ወይን ለቃሚዎች ቢመጡብህ፥ ቃርሚያውን አይተውልህምን? ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፥ የሚያጠፉት እስኪበቃቸው ድረስ አይደለምን? 10 እኔ ግን ዔሳውን ዐራቈትሁት፥ የተሸሸጉትንም ስፍራዎች ገለጥሁ፥ ይሸሸግም ዘንድ አይችልም፤ ዘሩም ወንድሞቹም ጎረቤቶቹም ጠፍተዋል እርሱም የለም። 11 ድሀ አደጎችህን ተው፥ እኔም በሕይወት አኖራቸዋለሁ፤ መበለቶችህም በእኔ ይታመኑ። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ጽዋውን ያልተገባቸው ሰዎች ጠጥተውታል፤ አንተም ሳትቀጣ ትቀራለህን? በእርግጥ ትጠጣለህ እንጂ ያለ ቅጣት አትቀርም። 13 ባሶራ መደነቂያና መሰደቢያ መረገሚያም እንድትሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከተሞችዋም ሁሉ ለዘላለም ባድማ ይሆናሉ። 14 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምቻለሁ በአሕዛብም መካከል። ተሰብሰቡ፥ በእርስዋም ላይ ኑ ለሰልፍም ተነሡ የሚል መልእክተኛ ተልኮአል። 15 እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ የተጠቃህ፥ በሰዎችም ዘንድ የተናቅህ አድርጌሃለሁ። 16 በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ፥ ድፍረትህና የልብህ ኵራት አታልለውሃል። ቤትህን ምንም እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 17 ኤዶምያስም መደነቂያ ትሆናለች፥ የሚያልፍባትም ሁሉ ይደነቃል፥ ስለ መጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጭባታል። 18 ሰዶምና ገሞራ በእነርሱም አጠገብ የነበሩት ከተሞች እንደ ተገለበጡ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዲሁ በዚያ ሰው አይቀመጥም የሰው ልጅም አይኖርባትም። 19 እነሆ፥ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት ውስጥ እንደ አንበሳ ይወጣል፤ የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው? 20 ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋ ትንንሾች ይጐተታሉ፤ በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል። 21 ከመውደቃቸው ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ የጩኸታቸውም ድምፅ በኤርትራ ባሕር ተሰማ። 22 እነሆ፥ እንደ ንስር ወጥቶ ይበራል ክንፉንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፥ በዚያም ቀን የኤዶምያስ ኃያላን ልብ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ልብ ይሆናል። 23 ስለ ደማስቆ፤ ክፉ ወሬ ሰምተዋልና ሐማትና አርፋድ አፈሩ ቀለጡም፤ በባሕርም ላይ ኅዘን አለ፥ ታርፍም ዘንድ አትችልም። 24 ደማስቆ ደከመች ትሸሽም ዘንድ ዘወር አለች እንቅጥቅጥም ያዛት፥ እንደ ወላድም ሴት ጣርና ምጥ ያዛት። 25 የተመሰገነችው ከተማ፥ የደስታዬ ከተማ፥ ሳትለቀቅ እንዴት ቀረች? 26 ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ሰልፈኞች ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 27 በደማስቆም ቅጥር ላይ እሳት አነድዳለሁ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። 28 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታ ስለ ቄዳርና ስለ አሶር መንግሥታት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ተነሡ ወደ ቄዳርም ውጡ፥ የምሥራቅንም ልጆች አጥፉ። 29 ድንኳናቸውንና መንጋቸውን ይወስዳሉ፤ መጋረጆቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ ግመሎቻቸውንም ለራሳቸው ይወስዳሉ፥ በዙሪያቸውም ሁሉ ጥፋትን ጥሩባቸው። 30 እናንተ በአሶር የምትኖሩ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ተማክሮባችኋልና፥ አሳብም አስቦባችኋልና ሽሹ ወደ ሩቅም ሂዱ በጥልቅም ውስጥ ተቀመጡ፥ ይላል እግዚአብሔር። 31 ተነሡ፥ ዕርፊት ወዳለበት ተዘልሎም ወደ ተቀመጠው፥ ደጅና መወርወሪያ ወደሌለው ብቻውንም ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ውጡ። 32 ግመሎቻቸው ይበዘበዛሉ የእንስሶቻቸውም ብዛት ይማረካል፤ ጠgWraቸውንም በዙሪያ የሚላጩትን ሰዎች ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከዳርቻቸውም ሁሉ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 33 አሶርም የቀበሮ መኖሪያና የዘላለም ባድማ ትሆናለች፤ በዚያም ሰው አይኖርም፥ የሰው ልጅም አይቀመጥባትም። 34 በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 35 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ዋና የኃይላቸው መሣሪያ የሆነውን የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ። 36 ከአራቱም ከሰማይ ማዕዘናት አራቱን ነፋሳት በኤላም ላይ አመጣለሁ፥ ወደ እነዚያም ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ ከኤላም የተሰደዱ ሰዎች የማይደርሱበት ሕዝብ አይገኝም። 37 በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን በሚሹአት ፊት ኤላምን አስደነግጣለሁ፤ ክፉ ነገርን እርሱም ጽኑ ቍጣዬን አመጣባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በኋላቸው ሰይፍ እሰድድባቸዋለሁ፤ 38 ዙፋኔንም በኤላም አኖራለሁ ከዚያም ንጉሡንና አለቆቹን አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 39 ነገር ግን በኋለኛው ዘመን የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ኤርምያስ 50

1 እግዚአብሔር ስለ ከለዳውያን ምድር ስለ ባቢሎን በነቢዩ በኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2 በአሕዛብ መካከል ተናገሩ አውሩም፥ ዓላማውንም አንሡ፤ አውሩ፥ አትደብቁ። ባቢሎን ተወሰደች፥ ቤል አፈረ፥ ሜሮዳክ ደነገጠ፤ ምስሎችዋ አፈሩ፥ ጣዖታትዋ ደነገጡ በሉ። 3 ሕዝብ ከሰሜን ወጥቶባታል ምድርዋንም ባድማ ያደርጋል፥ የሚቀመጥባትም አይገኝም፤ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል። 4 በዚያም ወራት በዚያም ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ሆነው ይመጣሉ፥ እያለቀሱም መንገዳቸውን ይሄዳሉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ። 5 ፊታቸውንም ወደዚያ አቅንተው። ኑ፥ ከቶ በማይረሳ በዘላለም ቃል ኪዳን ወደ እግዚአብሔር ተጠጉ ብለው ስለ ጽዮን መንገድ ይጠይቃሉ። 6 ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፤ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፥ በተራሮችም ላይ የተቅበዘበዙ አደረጉአቸው፤ ከተራራ ወደ ኮረብታ አለፉ፥ በረታቸውንም ረሱ። 7 ያገኙአቸው ሁሉ በሉአቸው፥ ጠላቶቻቸውም። በጽድቅ ማደሪያ በእግዚአብሔር ላይ፥ በአባቶቻቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ እኛ አልበደልንም አሉ። 8 ከባቢሎን መካከል ሽሹ፥ ከከለዳውያንም ድር ውጡ፥ በመንጎችም ፊት እንደ አውራ ፍየሎች ሁኑ። 9 እነሆ፥ ከሰሜን ምድር የታላላቅ አሕዛብን ጉባኤ አስነሣለሁ በባቢሎንም ላይ አመጣቸዋለሁ፤ በእርስዋም ላይ ይሰለፋሉ፥ ከዚያም ትወሰዳለች፤ ፍላጾቻቸውም ባዶውን እንደማይመለስ እንደ ብልህ ጀግና ፍላጻ ናቸው። 10 የከላውዴዎንም ምድር ትበዘበዛለች፥ የሚበዘብዙአትም ሁሉ ይጠግባሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 11 ርስቴን የምትበዘብዙ እናንተ ሆይ፥ ደስ ብሎአችኋልና፥ ሐሤትንም አድርጋችኋልና፥ በመስክ ላይም እንዳለች ጊደር ሆናችሁ ተቀናጥታችኋልና፥ እንደ ብርቱዎችም ፈረሶች አሽካክታችኋልና፥ 12 እናታችሁ እጅግ ታፍራለች፥ የወለደቻችሁም ትጐሰቍላለች፤ እነሆ፥ በአሕዛብ መካከል ኋለኛይቱ ትሆናለች፤ ምድረ በዳና ደረቅ ምድር በረሀም ትሆናለች። 13 ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ባድማ ትሆናለች እንጂ ሰው አይቀመጥባትም፤ በባቢሎንም በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል በመጣባትም መቅሠፍት ሁሉ ያፍዋጫል። 14 እናንተ ቀስትን የምትገትሩ ሰዎች ሁሉ፥ በባቢሎን ላይ በዙሪያዋ ተሰለፉ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርታለችና ወርውሩባት ፍላጾችንም አትንፈጉ። 15 የእግዚአብሔር በቀል ነውና በዙሪያዋ ጩኹባት፤ እጅዋን ሰጠች፤ ግንቦችዋ ወደቁ ቅጥሮችዋም ፈረሱ፤ እርስዋን ተበቀሉ እንደ ሠራችውም ሥሩባት። 16 ዘሪውንና በመከር ጊዜ ማጭድ የሚይዘውን ከባቢሎን አጥፉ፤ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል። 17 እስራኤል የባዘነ በግ ነው፤ አንበሶች አሳደዱት፤ መጀመሪያ የአሦር ንጉሥ በላው፥ በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አጥንቱን ቈረጠመው። 18 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦርን ንጉሥ እንደ ቀጣሁ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ምድሩን እቀጣለሁ። 19 እስራኤልንም ወደ ማሰማርያው እመልሳለሁ፥ በቀርሜሎስና በባሳንም ላይ ይሰማራል፥ ሰውነቱም በኤፍሬም ተራራና በገለዓድ ላይ ትጠግባለች። 20 እነዚህን ያስቀረኋቸውን ይቅር እላቸዋለሁና በዚያን ወራት በዚያም ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የእስራኤል በደል የይሁዳም ኃጢአት ይፈለጋል ምንም አይገኝም። 21 በምራታይም ምድር ላይ በፋቁድም በሚኖሩት ላይ ውጣ፤ ግደላቸው ፈጽመህም አጥፋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዳዘዝሁህም ሁሉ አድርግ። 22 የሰልፍና የታላቅ ጥፋት ውካታ በምድር ላይ አለ። 23 የምድር ሁሉ መዶሻ እንዴት ደቀቀ እንዴትስ ተሰበረ! ባቢሎንስ በአሕዛብ መካከል እንዴት ባድማ ሆነች! 24 ባቢሎን ሆይ፥ አጥምጄብሻለሁ አንቺም ሳታውቂ ተይዘሻል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ተዋጋሽ ተገኝተሻል ተይዘሽማል። 25 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በከለዳውያን ምድር ይሠራ ዘንድ ሥራ አለውና እግዚአብሔር ዕቃ ቤቱን ከፍቶ የቍጣውን ዕቃ ጦር አውጥቶአል። 26 ከየበኩሉ በእርስዋ ላይ ውጡ፥ ጎተራዎችዋንም ክፈቱ፤ እንደ ክምርም አድርጓት ፈጽማችሁም አጥፉአት፥ አንዳችም አታስቀሩላት። 27 ወይፈኖችዋን ሁሉ እረዱ፥ ወደ መታረድም ይውረዱ፤ ቀናቸው፥ የመጐብኘታቸው ጊዜ፥ ደርሶአልና ወዮላቸው! 28 የአምላካችንን የእግዚአብሔርን በቀል የመቅደሱንም በቀል በጽዮን ይነግሩ ዘንድ ሸሽተው ከባቢሎን አገር ያመለጡት ሰዎች ድምፅ ተሰምቶአል። 29 ቀስትን የሚገትሩትን ቀስተኞችን ሁሉ በባቢሎን ላይ ጥሩአቸው፤ በዙሪያዋ ስፈሩባት አንድም አያምልጥ፤ በእስራኤል ቅዱስ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ኰርታለችና እንደ ሥራዋ መጠን መልሱላት፥ እንዳደረገችም ሁሉ አድርጉባት። 30 ስለዚህ ጐበዛዝትዋ በአደባባይዋ ላይ ይወድቃሉ፥ በዚያም ቀን ሰልፈኞችዋ ሁሉ ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 31 ትዕቢተኛው ሆይ፥ የመጐብኘትህ ጊዜ፥ ቀንህ ደርሶአልና እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 32 ትዕቢተኛው ተሰናክሎ ይወድቃል የሚያነሣውም የለም፤ በከተሞቹም ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፥ በዙሪያውም ያለውን ሁሉ ትበላለች። 33 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተገፍተዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይይዙአቸዋል፥ ይለቅቁአቸውም ዘንድ እንቢ ብለዋል። 34 ተቤዢአቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርንም ያሳርፍ ዘንድ በባቢሎንም የሚኖሩትን ያውክ ዘንድ ሙግታቸውን ፈጽም ይምዋገታል። 35 ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ፥ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 36 ሰይፍ በሚጓደዱት ላይ አለ ሰነፎችም ይሆናሉ፥ ሰይፍም በኃያላኖችዋ ላይ አለ እነርሱም ይደነግጣሉ። 37 ሰይፍ በፈረሶቻቸውና በሰረገሎቻቸው ላይ በመካከልዋም ባሉት በልዩ በልዩ ሕዝብ ሁሉ ላይ አለ፥ እነርሱም እንደ ሴቶች ይሆናሉ፤ ሰይፍም በመዝገብዋ ላይ አለ ለብዝበዛም ይሆናል። 38 እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፥ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። 39 ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኵላዎች ጋር ይቀመጡባታል፥ ሰጐኖችም ይቀመጡባታል፤ ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይቀመጥባትም፥ እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም። 40 ሰዶምንና ገሞራን በአጠገባቸውም የነበሩትን ከተምች እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ሰው በዚያ አይቀመጥም የሰውም ልጅ አይኖርባትም። 41 እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን ይመጣል ታላቅ ሕዝብና ብዙ ነገሥታትም ከምድር ዳርቻ ይነሣሉ። 42 ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው ምሕረትም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ። 43 የባቢሎን ንጉሥ ወሬአቸውን ሰምቶአል፥ እጁም ደክማለች፥ ጭንቀትም ይዞታል፥ ምጥ ወላድ ሴትን እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞታል። 44 እነሆ፥ ከእርስዋ ዘንድ በቶሎ አባርራቸዋለሁና በጠነከረው አምባ ላይ ከዮርዳኖስ ትዕቢት ውስጥ እንደ አንበሳ ይወጣል፤ የተመረጠውንም በእርስዋ ላይ እሾመዋለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ወይስ ለእኔ ጊዜ የሚወስን ማን ነው? ወይስ ፊቴን የሚቃወም እረኛ ማን ነው? 45 ስለዚህ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ የመከረባትን ምክር፥ በከለዳውያንም ምድር ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋ ትናንሾች ይጎተታሉ፤ በእውነት ማደሪያቸውን ባድማ ያደርግባቸዋል። 46 ከባቢሎን መያዝ ድምፅ የተነሣ ምድር ተናወጠች፥ ጩኸትም በአሕዛብ መካከል ዘንድ ተሰማ።

ኤርምያስ 51

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በባቢሎን ላይና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ አጥፊውን ነፋስ አስነሣለሁ። 2 በባቢሎንም ላይ የሚያዘሩትን ሰዎች እሰድዳለሁ እነርሱም ያዘሩአታል፥ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል። 3 በወርዋሪው ላይ በጥሩርም በሚነሣው ላይ ቀስተኛው ቀስቱን ይገትር፤ ለጐበዛዝትዋ አትዘኑ ሠራዊትዋንም ሁሉ አጥፉ። 4 በከለዳውያንም ምድር ተገድለው፥ በሜዳዋም ላይ ተወግተው ይወድቃሉ። 5 ምድራቸው በእስራኤል ቅዱስ ላይ በተሠራው በደል ምንም እንኳ የተሞላች ብትሆን፥ እስራኤልም ሆነ ይሁዳ በአምላኩ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጣለም። 6 ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፥ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ በበደልዋ አትጥፉ፥ የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና፥ እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። 7 ባቢሎን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ምድርን ሁሉ ያሰከረች የወርቅ ጽዋ ነበረች፥ አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ አብደዋል። 8 ባቢሎን በድንገት ወድቃ ጠፍታለች፤ አልቅሱላት፥ ትፈወስም እንደ ሆነ ለKWsልዋ መድኃኒት ውሰዱላት። 9 ባቢሎንን ፈወስናት፥ እርስዋ ግን አልተፈወሰችም፤ ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና፥ እስከ ደመናም ድረስ ከፍ ከፍ ብሎአልና ትታችኋት እያንዳንዳችን ወደ አገራችን እንሂድ። 10 እግዚአብሔር ጽድቃችንን አውጥቶአል፤ ኑ፥ በጽዮን የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ሥራ እንናገር። 11 ፍላጾችን ሳሉ ጋሻዎችንም አዘጋጁ፤ እግዚአብሔር ያጠፋት ዘንድ አሳቡ በባቢሎን ላይ ነውና የሜዶንን ነገሥታት መንፈስ አስነሥቶአል፤ የእግዚብሔር በቀል የመቅደሱ በቀል ነውና። 12 በባቢሎን ቅጥር ዓላማውን አንሡበት፥ ጥበቃን አጽኑ፥ ተመልካቾችን አቁሙ፥ ድብቅ ጦር አዘጋጁ። እግዚአብሔር በባቢሎን በሚኖሩት ላይ የተናገረውን አስቦአልና፥ አድርጎአልምና። 13 አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ፥ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ፥ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል። 14 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራሱ ምሎአል። በእውነት ሰዎችን እንደ አንበጣ እሞላብሻለሁ፥ እነርሱም ጩኸት ያነሡብሻል። 15 ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። 16 ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፍስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። 17 ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። 18 እነርሱም ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። 19 የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፥ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 20 አንቺ መዶሻዬና የጦር መሣሪያዬ ነሽ፤ በአንቺ አሕዛብን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም መንግሥታትን አጠፋለሁ፤ 21 በአንቺ ፈረሱንና ፈረሰኛውን እሰባብራለሁ፤ 22 በአንቺም ሰረገላውንና በላዩ የሚቀመጠውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ወንድንና ሴትን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ሽማግሌውንና ብላቴናውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም ጐልማሳውንና ቆንጆይቱን እሰባብራለሁ፤ 23 በአንቺም እረኛውንና መንጋውን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አራሹንና ጥማጁን እሰባብራለሁ፤ በአንቺም አለቆችንና ሹማምቶችን አሰባብራለሁ። 24 በጽዮን በዓይናችሁ ፊት ስለሠሩት ክፋታቸው ሁሉ በባቢሎንና በከለዳውያን ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ፍዳቸውን እከፍላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 25 አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እጄንም እዘረጋብሃለሁ፥ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ፥ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ። 26 ከአንተም ለማዕዘንና ለመሠረት የሚሆን ድንጋይ አይወስዱም፥ ለዘላለምም ባድማ ትሆናለህ፥ ይላል እግዚአብሔር። 27 በምድር ላይ ዓላማን አንሡ በአሕዛብም መካከል መለከት ንፉ፥ አሕዛብንም አዘጋጁባት፤ የአራራትንና የሚኒን የአስከናዝንም መንግሥታት ሰብስቡባት አለቃንም በላይዋ አቁሙ፤ እንደ ጠgWraም ኩብኩባ ፈረሶችን በላይዋ አውጡ። 28 አሕዛብን የሚዶንንም ነገሥታት አለቆችንም ሹማምቶችንም ሁሉ የግዛታቸውንም ምድር ሁሉ አዘጋጁባት። 29 ማንም እንዳይቀመጥባት የባቢሎንን ምድር ባድማ ያደርጋት ዘንድ የእግዚአብሔር አሳብ በባቢሎን ላይ ጸንቶአልና ምድር ተናወጣለች ታመመችም። 30 የባቢሎን ኃያላን መዋጋትን ትተዋል በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ጠፍቶአል እንደ ሴቶችም ሆነዋል፤ ማደሪያዎችዋም ነድደዋል መወርወሪያዎችዋም ተሰብረዋል። 31-32 ከዳር እስከ ዳር ድረስ ከተማው እንደ ተያዘች መልካምዎችዋም እንደ ተያዙ፥ ቅጥርዋም በእሳት እንደ ተቃጠለ፥ ሰልፈኞችም እንደ ደነገጡ ለባቢሎን ንጉሥ ይነግር ዘንድ ወሬኛው ወሬኛውን መልእክተኛውም መልእክተኛውን ሊገናኝ ይሮጣል። 33 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። አውድማ እንደ ተረገጠ ጊዜ፥ እንዲሁ የባቢሎን ልጅ ናት፤ ጥቂት ቈይታ የመከር ጊዜ ይደርስባታል። 34 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላኝ፥ ከፋፈለኝም፥ እንደ ባዶ ዕቃም አደረገኝ፥ እንደ ዘንዶም ዋጠኝ፥ ከሚጣፍጠውም ምግቤ ሆዱን ሞላ፥ እኔንም ጣለኝ። 35 በጽዮን የምትቀመጥ። በእኔና በሥጋዬ የተደረገ ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን ትላለች፤ ኢየሩሳሌምም። ደሜ በከለዳውያን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን ትላለች። 36 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እምዋገትልሻለሁ በቀልሽንም እበቀልልሻለሁ፤ ባሕርዋንም ድርቅ አደርገዋለሁ ምንጭዋንም አደርቀዋለሁ። 37 ባቢሎንም የድንጋይ KWlልና የቀበሮ ማደሪያ መደነቂያም ማፍዋጫም ትሆናለች፥ የሚቀመጥባትም ሰው አይገኝም። 38 በአንድነትም እንደ አንበሶች ያገሣሉ፥ እንደ አንበሳም ደቦሎች ያጕረመርማሉ። 39 በሞቃቸው ጊዜ ደስ እንዲላቸው ለዘላለምም አንቀላፍተው እንዳይነቁ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ አሰክራቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 40 እንደ ጠቦቶችና እንደ አውራ በጎች እንደ አውራ ፍየሎችም ወደ መታረድ አወርዳቸዋለሁ። 41 ሼሻክ እንዴት ተያዘች! የምድርም ሁሉ ምስጋና እንዴት ተወሰደች! ባቢሎንም በአሕዛብ መካከል መደነቂያ እንዴት ሆነች! 42 ባሕር በባቢሎን ላይ ወጣ በሞገዱም ብዛት ተከደነች። 43 ከተሞችዋ ባድማና ደረቅ ምድር ምድረ በዳም፥ ሰውም የማይቀመጥበት የሰውም ልጅ የማያልፍበት ምድር ሆኑ። 44 በባቢሎንም ውስጥ ቤልን እቀጣለሁ የዋጠውንም ከአፉ አስተፋዋለሁ፤ አሕዛብም ከዚያ ወዲያ ወደ እርሱ አይሰበሰቡም፥ የባቢሎንም ቅጥር ይወድቃል። 45 ሕዝቤ ሆይ፥ ከመካከልዋ ውጡ እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ራሳችሁን አድኑ። 46 በምድርም ከሚሰማ ወሬ የተነሣ አትፍሩ ልባችሁም የዛለ አይሁን፤ በአንድ ዓመት ወሬ ይመጣል፥ ከዚያም በኋላ በሌላው ዓመት ወሬ፥ በምድርም ላይ ግፍ ይመጣል፥ አለቃም በአለቃ ላይ ይነሣል። 47 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን የባቢሎን ምስሎች የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ምድርዋም ሁሉ ታፍራለች፤ ተወግተውም የሞቱት ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48 አጥፊዎች ከሰሜን ይመጡባታልና ሰማይና ምድር በእነርሱም ያለው ሁሉ ስለ ባቢሎን እልል ይላሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 49 ባቢሎንም ከእስራኤል ተወግተው የሞቱት እንዲወድቁ እንዳደረገች፥ እንዲሁ በባቢሎን ከምድሩ ሁሉ ተወግተው የሞቱት ይወድቃሉ። 50 ከሰይፍ ያመለጣችሁ ሆይ፥ ሂዱ፥ አትቁሙ፤ እግዚአብሔርን ከሩቅ አስቡ፥ ኢየሩሳሌምንም በልባችሁ አስቡ። 51 ስድብን ስለ ሰማን አፍረናል፤ ባዕዳን ሰዎችም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብተዋልና ነውር ፊታችንን ከድኖታል። 52 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የተቀረጹትን ምስሎችዋ የምቀጣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር በምድርዋም ላይ ሁሉ የተወጉት ያንቋርራሉ። 53 ባቢሎን ምንም ወደ ሰማይ ብትወጣ፥ የኃይልዋንም ከፍታ ብታጸና፥ ከእኔ ዘንድ አጥፊዎች ይመጡባታል፥ ይላል እግዚአብሔር። 54 ከባቢሎን ጩኸት፥ ከከለዳውያንም ምድር የታላቅ ጥፋት ድምፅ ተሰምቶአል። 55 እግዚአብሔር ባቢሎንን አጥፍቶአታልና፥ ከእርስዋም ታላቁን ድምፅ ዝም አሰኝቶአልና፤ ሞገዳቸውም እንደ ብዙ ውኆች ይተምማል፥ የድምፃቸውም ጩኸት ተሰምቶአል። 56 አጥፊው በባቢሎን ላይ መጥቶባታልና፥ ኃያላኖችዋ ተያዙ፥ ቀስታቸውም ተሰባበረ፤ እግዚአብሔር ፍዳን የሚከፍል አምላክ ነውና፥ ፍዳንም በእርግጥ ይከፍላል። 57 መሳፍንቶችዋንና ጥበበኞችዋንም፥ አለቆችዋንና ሹማምቶችዋን ኃያላኖችዋንም አሰክራለሁ፥ ለዘላለምም አንቀላፍተው አይነቁም፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 58 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰፊው የባቢሎን ቅጥር ፈጽሞ ይፈርሳል ረጃጅሞችም በሮችዋ በእሳት ይቃጠላሉ፤ የወገኖችም ድካም ከንቱ ትሆናለች፥ የአሕዛብም ሥራ ለእሳት ትሆናለች፤ እነርሱም ይደክማሉ። 59 የመሕሤያ ልጅ የኔርያ ልጅ ሠራያ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን በሄደ ጊዜ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘው ቃል ይህ ነው። ሠራያም የቤት አዛዥ ነበረ። 60 በባቢሎንም ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስለ ባቢሎን የተጻፈውን ይህን ቃል ሁሉ፥ ኤርምያስ በመጽሐፍ ላይ ጻፈው። 61 ኤርምያስም ሠራያን እንዲህ አለው። ወደ ባቢሎን በገባህ ጊዜ እይ ይህንም ቃል ሁሉ አንብብና። 62 አቤቱ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ማንም እንዳይቀመጥባት፥ ለዘላለምም ባድማ እንድትሆን ታጠፋት ዘንድ በዚህች ስፍራ ላይ ተናግረሃል በል። 63 ይህንም መጽሐፍ ማንበብ ከፈጸምህ በኋላ፥ ድንጋይን እሰርበት በኤፍራጥስም ውስጥ ጣለው፤ 64 አንተም። እኔ ከማመጣባት ክፉ ነገር የተነሣ እንዲሁ ባቢሎን ትሰጥማለች አትነሣምም በል። የኤርምያስ ቃል እስከዚህ ድረስ ነው።

ኤርምያስ 52

1 ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የሊብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2 ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 3 ከፊቱም አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ። 4 ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ዕርድ አደረገ። 5 ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። 6 በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበር፥ ለአገሩም ሰዎች እንጀራ ታጣ። 7 ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ ሸሹ፥ በሁለቱም ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማይቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ። 8 የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉት፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ያዙ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ተበትነው ነበር። 9 ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለባት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ አመጡት፤ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 10 የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በፊቱ ገደላቸው፥ የይሁዳንም አለቆች ሁሉ ደግሞ በሪብላ ገደላቸው። 11 የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሰንሰለት አሰረው ወደ ባቢሎንም ወሰደው፥ እስኪሞትም ድረስ በግዞት ቤት አኖረው። 12 በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረናው ከን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የቆመው የዘበኞቹ አለካ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 13 የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆችን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። 14 ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ሁሉ ዙሪያዋን አፈረሱ። 15 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን የሕዝቡን ድኆች፥ በከተማም ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የሕዝቡንም ቅሬታ አፈለሰ። 16 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከአገሩ ድኆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። 17 ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የናስ ዓምዶች በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናሱን ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 18 ምንቸቶቹንና መጫሪያዎችንም መኰስተሪያዎችንና ድስቶችን ጭልፋዎችንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። 19 የዘበኞቹም አለቃ ጽዋዎቹንና ማንደጃዎቹን ድስቶቹንና ምንቸቶችን መቅረዞችንና ጭልፋዎቹን መንቀሎችንም፥ የወርቁን ዕቃ በወርቅ፥ የብሩንም ዕቃ በብር አድርጎ፥ ወሰደ። 20 ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት ያሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኵሬ፥ ከመቀመጫዎቹም በታች የነበሩትን አሥራ ሁለቱን የናስ በሬዎች ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረም። 21 ዓምዶቹም፥ የአንዱ ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውፍረቱም አራት ጣት ያህል ነበረ፥ ባዶም ነበረ። 22 የናሱም ጕልላት በላዩ ነበረ፤ የአንዱም ጉልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው ሁሉ ከናስ የተሠሩ መረበብና ሮማኖች ነበሩበት፤ በሁለተኛውም ዓምድ ደግሞ እንደዚህ ያለ ነገርና ሮማኖች ነበሩበት። 23 በስተ ውጭም ዘጠና ስድስት ሮማኖች ነበሩ። በመረበቡም ዙሪያ የነበሩ ሮማኖች ሁሉ አንድ መቶ ነበሩ። 24 የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ፤ 25 ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጀንደረባ፥ በከተማይቱም ከሚገኙት በንጉሡ ፊት ከሚቆሙት ሰባቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ። 26 የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 27 የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ። 28 ናቡከደነፆር የማረከው ሕዝብ ይህ ነው፤ በሰባተኛው ዓመት ሦስት ሺህ ሀያ ሦስት አይሁድ፤ 29 ናቡከደነፆርም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ነፍስ ከኢየሩሳሌም ማርኮአል፤ 30 በናቡከደነፆር በሀያ ሦስተኛው ዓመት የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ከአይሁድ ሰባት መቶ አርባ አምስት ነፍስ ማርኮአል፤ ሰዎች ሁሉ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 31 እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ አምስተኛው ቀን፥ የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴክ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳን ንጉሥ የዮአኪንን ራስ ከፍ ከፍ አደረገ ከወህኒም አወጣው፤ 32 በመልካምም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 33 በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፥ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቴ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 34 የባቢሎንም ንጉሥ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እስኪሞት ድረስ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።

ሰቆቃው 1

1 አሌፍ። ሕዝብ ሞልቶባት የነበረች ከተማ ብቻዋን እንዴት ተቀመጠች! በአሕዛብ መካከል ታላቅ የነበረች እንደ መበለት ሆናለች፤ በአውራጆች መካከል ልዕልት የነበረች ተገዢ ሆናለች። 2 ቤት። በሌሊት እጅግ ታላቅሳለች፥ እንባዋም በጕንጭዋ ላይ አለ፤ ከውሽሞችዋ ሁሉ የሚያጽናናት የለም፤ ወዳጆችዋ ሁሉ ወነጀሉአት ጠላቶችም ሆኑአት። 3 ጋሜል። ይሁዳ ስለ መጨነቅና ስለ ባርነት ብዛት ተማረከች፤ በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች ዕረፍትም አላገኘችም፤ የሚያስጨንቁአት ሁሉ ተጨንቃ አገኙአት። 4 ዳሌጥ። ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ እርስዋም በምሬት አለች። 5 ሄ። ስለ ኃጢአትዋ ብዛት እግዚአብሔር አስጨንቆአታልና አስጨናቂዎችዋ ራስ ሆኑ ጠላቶችዋም ተከናወነላቸው፤ ሕፃናቶችዋ በአስጨናቂዎች ፊት ተማርከዋል። 6 ዋው። ከጽዮን ሴት ልጅ ውበትዋ ሁሉ ወጥቶአል፤ አለቆችዋ ማሰማርያ እንደማያገኙ ዋላዎች ሆኑ፤ ከሚያባርሩአቸው ፊት ተዳክመው ሄዱ። 7 ዛይ። ኢየሩሳሌም በጭንቀትዋና በመከራዋ ወራት ከጥንት ጀምሮ የነበረላትን የከበረን ነገር ሁሉ አሰበች፤ ሕዝብዋ በአስጨናቂዎች እጅ በወደቀ ጊዜ የሚረዳትም በሌላት ጊዜ፥ አስጨናቂዎች አዩአት በመፍረስዋም ሳቁ። 8 ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኃጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ ረክሳለች፤ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ኀፍረተ ሥጋዋን አይተዋታልና አቃለሉአት፤ እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች ወደ ኋላም ዘወር አለች። 9 ጤት። አደፍዋ በልብስዋ ዘርፍ ነበረ፤ ፍጻሜዋን አላሰበችም፤ ስለዚህ በድንቅ ተዋርዳለች፥ የሚያጽናናትም የለም፤ አቤቱ፥ ጠላት ከፍ ከፍ ብሎአልና መከራዬን ተመልከት። 10 ዮድ። አስጨናቂው በከበረ ነገርዋ ሁሉ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ ያዘዝሃቸው አሕዛብ ወደ መቅደስዋ ሲገቡ አይታለችና። 11 ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እየጮኹ ያለቅሳሉ እንጀራም ይፈልጋሉ፤ ሰውነታቸውን ለማበርታት የከበረ ሀብታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፤ አቤቱ፥ ተጐሳቍያለሁና እይ፥ ተመልከትም። 12 ላሜድ። እናንተ መንገድ አላፊዎች ሁሉ፥ በእናንተ ዘንድ ምንም የለምን? እግዚአብሔር በጽኑ ቍጣው ቀን እኔን እንዳስጨነቀበት በእኔ ላይ እንደ ተደረገው እንደ እኔ መከራ የሚመስል መከራ እንዳለ ተመልከቱ፥ እዩ። 13 ሜም። ከላይ እሳትን ወደ አጥንቴ ሰደደ በረታችበትም፤ ለእግሬ ወጥመድ ዘረጋ ወደ ኋላም መለሰኝ፥ አጠፋኝም ቀኑንም ሁሉ አደከመኝ። 14 ኖን። የኃጢአቶቼ ቀንበር በእጁ ተይዛለች፤ ታስረው በአንገቴ ላይ ወጥተዋል፤ ጕልበቴን አደከመ። ጌታ በፊታቸው እቆም ዘንድ በማልችላቸው እጅ አሳልፎ ሰጠኝ። 15 ሳምኬት። ጌታ ኃያላኖቼን ሁሉ ከውስጤ አስወገዳቸው፤ ጕልማሶቼን ያደቅቅ ዘንድ ጉባኤን ጠራብኝ፤ ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጥመቂያ እንደሚረገጥ አድርጎ ረገጣት። 16 ዔ። የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቆአልና ስለዚህ አለቅሳለሁ፤ ዓይኔ፥ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል። ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል። 17 ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች፤ የሚያጽናናት የለም፤ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፤ ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ርኩስ ነገር ሆናለች። 18 ጻዴ። በአፉ ነገር ላይ ዓመፅ አድርጌአለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ እባካችሁ፥ ስሙ መከራዬንም ተመልከቱ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ ተማርከው ሄዱ። 19 ቆፍ። ውሽሞቼን ጠራሁ እነርሱም አታለሉኝ፤ ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ ሰውነታቸውን ያበረቱ ዘንድ መብል ሲፈልጉ በከተማ ውስጥ ሞቱ። 20 ሬስ። አቤቱ፥ ተጨንቄአለሁና፥ አንጀቴም ታውኮብኛልና ተመልከት፤ ዓመፃን ፈጽሞ አድርጌአለሁና ልቤ በውስጤ ተገላበጠብኝ፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቼን አጠፋ በቤትም ሞት አለ። 21 ሳን። እኔ እየጮኽሁ እንደማለቅስ ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝ የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ስለ መከራዬ ሰምተዋል፤ አንተ አድርገኸዋልና ደስ አላቸው፤ ስለ እርሱ የተናገርኸውን ቀን ታመጣለህ እነርሱም እንደ እኔ ይሆናሉ። 22 ታው። ልቅሶዬ እጅግ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና ክፋታቸው ሁሉ ወደ ፊትህ ይድረስ፥ ስለ ኃጢአቴ ሁሉ እንዳደረግህብኝ አድርግባቸው።

ሰቆቃው 2

1 አሌፍ። ጌታ በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንደ ምን አደመናት! የእስራኤልን ውበት ከሰማይ ወደ ምድር ጣለ፥ በቍጣውም ቀን የእግሩን መረገጫ አላሰበም። 2 ቤት። ጌታ የያዕቆብን ማደሪያዎች ሁሉ ዋጠ፥ አልራራምም፤ በመዓቱ የይሁዳን ሴት ልጅ አምቦች አፈረሰ፥ ወደ ምድርም አወረዳቸው፤ መንግሥቱንና አለቆችዋን አረከሰ። 3 ጋሜል። በጽኑ ቍጣው የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ቀጠቀጠ፤ ቀኝ እጁን ከጠላት ፊት ወደ ኋላ መለሰ፥ በዙሪያውም እንደሚባላ እንደ እሳት ነበልባል ያዕቆብን አቃጠለ። 4 ዳሌጥ። ቀስቱን እንደ ጠላት ገተረ፥ እንደ አስጨናቂ ቀኝ እጁን አጸና፥ ለዓይንም የሚያምረውን ሁሉ ገደለ፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን መዓቱን እንደ እሳት አፈሰሰ። 5 ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፤ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፤ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ። 6 ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፤ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፤ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቍጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ። 7 ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ። 8 ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፤ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፤ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነት ደከሙ። 9 ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፤ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፤ ነቢያቶቻዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። 10 ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ። 11 ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ። 12 ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን። እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል። 13 ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው? 14 ኖን። ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል። 15 ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና። በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ። 16 ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፤ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ። ውጠናታል፤ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፤ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ። 17 ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፤ አፈረሰ አልራራምም፤ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ። 18 ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፤ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፤ የዓይንሽ ብሌን አታቋርጥ። 19 ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፤ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ። 20 ሬስ። አቤቱ፥ እይ፤ በማን ላይ እንደዚህ እንዳደረግህ ተመልከት። በውኑ ሴቶች ፍሬያቸውን፥ ያቀማጠሉአቸውን ሕፃናት፥ ይበላሉን? በውኑ ካህኑና ነቢዩ በጌታ መቅደስ ውስጥ ይገደላሉን? 21 ሳን። ብላቴናውና ሽማግሌው በመንገዶች ላይ ተጋደሙ፤ ደናግሎቼና ጐበዛዝቴ በሰይፍ ወድቀዋል፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ሳትራራ አረድሃቸው። 22 ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቍጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፤ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው።

ሰቆቃው 3

1 አሌፍ። በቍጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። 2 ብርሃን ወደ ሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ። 3 ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ። 4 ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ። 5 ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ። 6 ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ። 7 ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴን አከበደ። 8 በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴን ከለከለ። 9 መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ። 10 ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ። 11 መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፤ ባድማ አደረገኝ። 12 ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ። 13 ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ። 14 ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ። 15 ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ። 16 ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ። 17 ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ። 18 እኔም። ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ። 19 ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ። 20 ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች። 21 ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ። 22 ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። 23 ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው። 24 ነፍሴ። እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች። 25 ጤት። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው። 26 ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። 27 ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። 28 ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ። 29 ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር። 30 ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ። 31 ካፍ። ጌታ ለዘላለም አይጥልምና፤ 32 ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፤ 33 የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም። 34 ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥ 35 የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥ 36 የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም። 37 ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው? 38 ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን? 39 ሕያው ሰው የሚያጕረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጕረመርም ስለ ምንድር ነው? 40 ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ። 41 ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ። 42 በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም። 43 ሳምኬት። በቍጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፥ አልራራህም። 44 ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ። 45 በአሕዛብ መካከል ጕድፍና ውዳቂ አደረግኸን። 46 ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን። 47 ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። 48 ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። 4950 ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች። 51 ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች። 52 ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ። 53 ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። 54 በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፤ እኔም። ጠፋሁ ብዬ ነበር። 55 ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። 56 ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። 57 በጠራሁህ ቀን ቀርበህ። አትፍራ አልህ። 58 ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ። 59 አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ። 60 በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ። 61 ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥ 62 የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ። 63 መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ። 64 ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ። 65 የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ። 66 አቤቱ፥ በቍጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።

ሰቆቃው 4

1 አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ። 2 ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ! 3 ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች። 4 ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም። 5 ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ። 6 ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች። 7 ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ገላቸው ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ። 8 ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፤ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨት ሆኖአል። 9 ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል። 10 ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው። 11 ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቍጣውን አፍስሶአል፤ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች። 12 ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም። 13 ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ ስለ ነቢያቶችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው። 14 ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል። 15 ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል። በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም ተባለ። 16 ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም። 17 ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፤ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል። 18 ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፤ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል። 19 ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን። 20 ሬስ። ስለ እርሱ። በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ። 21 ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፤ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም። 22 ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፤ ኃጢአትሽን ይገልጣል።

ሰቆቃው 5

1 አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። 2 ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። 3 ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። 4 ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን። 5 አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም። 6 ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን። 7 አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን። 8 ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም። 9 ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን። 10 ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ። 11 በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ። 12 አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም። 13 ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። 14 ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ። 15 የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። 16 አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን! 17 ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤ 18 ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና። 19 አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። 20 ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ? 21 አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። 22 ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።

ሕዝቅኤል 1

1 በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ። 2 ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት 3 ከወሩም በአምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን አገር በኮቦር ወንዝ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፥ 4 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ። 5 ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። 6 ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። 7 እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፤ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። 8 በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። 9 ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር። 10 የፊታቸው አምሳያ እንደ ሰው ፊት ነበረ፥ ለአራቱም በስተ ቀኛቸው እንደ አንበሳ ፊት፥ በስተ ግራቸውም እንደ ላም ፊት ነበራቸው፥ ለአራቱም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው። 11 ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፥ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፥ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር። 12 እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። 13 በእንስሶቹ መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ ምስያ ነበረ፤ በእንስሶች መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ ምስያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፥ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር። 14 እንስሶቹም እንደ መብረቅ ምስያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር። 15 እንስሶችንም ስመለከት፥ እነሆ፥ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ አንድ መንኰራኵር አየሁ። 16 የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ። 17 በእያራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። 18 ቁመታቸውም የረዘመና የሚያስፈራ ነበረ፤ የአራቱም ክበብ ዙሪያው በዓይን ተሞልቶ ነበር። 19 እንስሶቹም በሄዱ ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ሄዱ። እንስሶቹም ከምድር ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከፍ ከፍ አሉ። 20 መንፈሱ ወደሚሄድበት ሁሉ እነርሱ ሄዱ፤ የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና መንኰራኵሮቹ በእነርሱ አጠገብ ከፍ ከፍ አሉ። 21 የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮቹ ውስጥ ነበረና እነዚያ ሲሄዱ እነዚህ ይሄዱ ነበር፤ እነዚያም ሲቆሙ እነዚህ ይቆሙ ነበር፤ እነዚያም ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር። 22 ከእንስሶች ራስ በላይ የሚያስፈራ በረዶ የሚመስል የጠፈር አምሳያ በራሳቸው ላይ ተዘርግቶ ነበር። 23 ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። 24 ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ እንደ ሁሉን የሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅም ሠራዊት ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። 25 በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር። 26 በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። 27 ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። 28 በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።

ሕዝቅኤል 2

1 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ። 2 በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ። 3 እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ። 4 እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው። 5 እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ። 6 አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። 7 እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ። 8 አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ፤ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ። 9 ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት። 10 በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።

ሕዝቅኤል 3

1 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ። 2 አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። 3 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። 4 እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው። 5 ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤ 6 ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር። 7 ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም። 8 እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። 9 ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። 10 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ። 11 ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ። 12 መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም። የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። 13 የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። 14 መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር። 15 በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ። 16 ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 17 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 18 እኔ ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 19 ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። 20 ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21 ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል። 22 በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ እርሱም። ተነሥተህ ወደ ቈላው ሂድ በዚያም እናገርሃለሁ አለኝ። 23 እኔም ተነሥቼ ወደ ቈላው ሄድሁ፤ እነሆም፥ በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፥ በግምባሬም ተደፋሁ። 24 መንፈስም ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ። ሂድ፥ ገብተህ ቤትህን ዝጋ። 25 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ ገመድ ያደርጉብሃል ያስሩህማል፥ አንተም በመካከላቸው አትወጣም፤ 26 እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም። 27 ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።

ሕዝቅኤል 4

1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት፥ 2 ምሽግም ሥራባት፥ አፈርም ደልድልባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት። 3 የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል። 4 አንተም በግራ ጐድንህ ተኛ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ። 5 እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ። 6 እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጐድንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ። 7 ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ክቡ ታቀናለህ፥ ትንቢትም ትናገርባታለህ። 8 እነሆም፥ ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጐድን ጐድንህ አትገላበጥም። 9 አንተም ስንዴንና ገብስን ባቄላንና ምስርን ጤፍንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፥ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጐድንህ እንደ ተኛህበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። 10 የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሀያ ሀያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜው ትበላዋለህ። 11 ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ። 12 እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ። 13 እግዚአብሔርም። እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለ። 14 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ። 15 እርሱም። እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ። 16 ደግሞም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤ 17 ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲሰለስሉ ነው።

ሕዝቅኤል 5

1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለን ጐራዴ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ወደ አንተ ትወስደዋለህ፥ ራስህንና ጢምህንም ትላጭበታለህ፤ ሚዛንንም ውሰድ ጠጕሩንም ትከፋፍላለህ። 2 የመከበብም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማይቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጐራዴ ትመታለህ፥ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ እኔም በኋላቸው ጐራዴ እመዝዛለሁ። 3 ከዚያም በጥቂቱ ውሰድ በመጐናጸፊያህም ጫፍ ቋጥራቸው። 4 ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከዚያም በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ እሳት ትወጣለች። 5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ በአሕዛብም መካከል አድርጌአታለሁ፥ አገሮችም በዙሪያዋ አሉ። 6 እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኃጢአት ለወጠች በዙሪያዋም ካሉ አገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና። 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና 8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አሕዛብም እያዩ ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ። 9 ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ። 10 ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ። 11 ስለዚህ፥ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም። 12 ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። 13 ቍጣዬም ይፈጸማል መዓቴንም እጨርሳለሁ እጽናናማለሁ፥ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ። 14 በዙሪያሽም ባሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ። 15 በቍጣና በመዓት፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ በዙሪያሽ ላሉ አሕዛብ መሰደቢያና መተረቻ፥ ተግሣጽና መደነቂያ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 16 ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፥ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ። 17 ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆቻችሁንም ያጠፋሉ፤ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ዘንድ ያልፋሉ፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

ሕዝቅኤል 6

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና ትንቢትም ተናገርባቸው። 3 እንዲህም በል። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል። እኔ፥ እነሆ፥ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታው መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ። 4 መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይሰበራሉ፤ ተወግተውም የሞቱትን ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5 የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6 በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቈረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል። 7 ተወግተውም የሞቱት በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ነገር ግን በአገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከሰይፍ ያመለጡትን ቅሬታ በአሕዛብ መካከል አስቀርላችኋለሁ። 9 ከእናንተም የዳኑት ከእኔ በራቀው በአመንዝራ ልባቸውና ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዓይኖቻቸው የተሰበርሁትን እኔን ወደ እነርሱ በተማረኩት አሕዛብ መካከል ሆነው ያስቡኛል፤ በርኵሰታቸውም ሁሉ ስላደረጉት ክፋት ራሳቸውን ይጸየፋሉ። 10 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ በከንቱ አይደለም። 11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእጅህ አጨብጭብ በእግርህም አሸብሽብ እንዲህም በል። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይወድቃሉና ስለ እስራኤል ቤት ስለ አስጸያፊ ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ! 12 በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፥ የቀረውና የዳነውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ። 13 ተወግተውም የሞቱ ሰዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ፥ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ በተራሮችም ራስ ሁሉ ላይ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ቅጠሉም ከበዛ ከአድባር ዛፍ ሁሉ በታች በሆኑ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14 እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 7

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል። ፍጻሜ፥ በምድሪቱ በአራቱ ማዕዘን ላይ ፍጻሜ ደርሶአል። 3 አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 4 ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ክፉ ነገር፥ አንድ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ ይመጣል። 6 ፍጻሜ መጥቶአል፥ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ነቅቶብሻል፤ እነሆ፥ ደርሶአል። 7 በምድር የምትቀመጥ ሆይ፥ ተራህ ደርሶአል፥ ጊዜ መጥቶአል፥ ቀን ቀርቦአል፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም። 8 አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፥ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 9 ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም፤ እንደ መንገድሽም መጠን አመጣብሻለሁ፥ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 10 እነሆ ቀኑ፥ እነሆ፥ መጥቶአል፤ ተራህ ወጥቶአል፤ ብትር አብቦአል፥ ትዕቢትም አጅብጅፎአል። 11 ግፍ ወደ ክፋት ብትር ተነስቶአል፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም፥ የሚያለቅስላቸውም የለም። 12 ጊዜው መጥቶአል፥ ቀኑ ቀርቦአል፤ መዓት በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ። 13 የሚሸጥ ወደሸጠው ነገር አይመለስም፥ ሰውም በነፍሱ ኃጢአት አይጸናም። 14 መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም አዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም። 15 ሰይፍ በውጭ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል። 16 ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ በተራራም ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኃጢአታቸው ሁሉን እገድላለሁ። 17 እጅ ሁሉ ትደክማለች ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ትቀልጣለች። 18 ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፈረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል። 19 ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጕድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። እርሱ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም ሆዳቸውንም አይሞሉም። 20 የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ። 21 በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኃጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአታል። 22 ፊቴን ከእነርሱ ዘንድ እመልሳለሁ፥ ምሥጢሬንም ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአትማል። 23 ምድር ደም ባመጣው በደል፥ ከተማም በግፍ ተሞልታለችና ሰንሰለት ሥራ። 24 ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፤ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። 25 ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ እርሱም አይገኝም። 26 ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፥ ወሬም ወሬውን ይከተላል፥ ከነቢዩም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል። 27 ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድርም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 8

1 በስድስተኛውም ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያ የጌታ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ወደቀች። 2 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ እንደ እሳት የሚመስል አምሳያ ነበረ፤ ከወገቡም ምሳሌ ወደ ታች እሳት ነበረ፥ ከወገቡም ወደ ላይ እንደ ፀዳል ምሳሌ፥ እንደሚብለጨለጭም የወርቅ ምሳሌ ነበረ። 3 እጅ መሳይንም ዘረጋ በራስ ጠጕሬም ያዘኝ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም ራእይ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ቅንዓት የሚያነሣሣ የቅንዓት ጣዖት ተተክሎ ነበር። 4 እነሆም፥ በቈላው እንዳየሁት ራእይ የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ። 5 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓይንህን ወደ ሰሜን መንገድ አንሣ አለኝ። ዓይኔንም ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ፤ እነሆም፥ በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል በመግቢያው ይህ የቅንዓት ጣዖት ነበረ። 6 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የሚያደርጉትን፥ ከመቅደሴ ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉትን ታላቁን ርኵሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ። 7 ወደ አደባባዩም መግቢያ አመጣኝ፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በግንቡ ውስጥ ፉካ ነበረ። 8 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ግንቡን ንደለው አለኝ፤ ግንቡንም በነደልሁት ጊዜ መዝጊያ አገኘሁ። 9 እርሱም። ግባ፥ በዚህም የሚያደርጉትን ክፉውን ርኵሰት እይ አለኝ። 10 እኔም ገባሁና እነሆ፥ በግንቡ ዙሪያ ላይ የተንቀሳቃሾችና የርኩሳን አራዊት ምሳሌ የእስራኤልንም ቤት ጣዖታት ሁሉ ተስለው አየሁ። 11 በፊታቸውም ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎች ቆመው ነበር፥ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፥ ሰውም ሁሉ እያንዳንዱ በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ የዕጣኑም ጢስ ሽቱ ይወጣ ነበር። 12 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በጨለማ እያንዳንዱ በስዕሉ ቤት የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ። እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል ይላሉና አለኝ። 13 እርሱም። ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠውን የሚያደርጉትን ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ። 14 ወደ ሰሜንም ወደሚመለከተው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ እነሆም፥ ሴቶች ለተሙዝ እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 15 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ርኵሰት ታያለህ አለኝ። 16 ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ መግቢያ ፊት በወለሉና በመሠዊያው መካከል ሀያ አምስት የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ ጀርባቸውም ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፤ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። 17 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? በዚህ የሚያደርጉትን ይህን ርኵሰት ያደርጉ ዘንድ ለይሁዳ ቤት ጥቂት ነገር ነውን? ምድሪቱን በግፍ ሞልተዋታል ያስቈጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፤ እነሆም፥ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫው አቅርበዋል። 18 ስለዚህ እኔ ደግሞ በመዓት እሠራለሁ፤ ዓይኔ አይራራም እኔም አላዝንም፤ ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹ አልሰማቸውም አለኝ።

ሕዝቅኤል 9

1 እርሱም። እያንዳንዳቸው የሚያጠፋ መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማይቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ። 2 እነሆም፥ እያንዳንዳቸው አጥፊውን መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፤ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ የጸሐፊም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። 3 የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፤ በፍታም የለበሰውን የጸሐፊውንም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘውን ሰው ጠራ። 4 እግዚአብሔርም። በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። 5 እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ። እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤ 6 ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ። 7 እርሱም። ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ፤ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ። 8 ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን? ብዬ ጮኽሁ። 9 እርሱም። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኃጢአት እጅግ በዝቶአል ምድሪቱም ደም፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል። 10 እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ አለኝ። 11 እነሆም፥ በፍታ የለበሰው የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው። ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ።

ሕዝቅኤል 10

1 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ እንደ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ። 2 በፍታም የለበሰውን ሰው። በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ። 3 ሰውዬውም ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ ቀኝ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ። 4 የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ። 5 ሁሉንም የሚችል አምላክ እንደሚናገረው ያለ ጽምፅ እንዲሁ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ ተሰማ። 6 በፍታም የለበሰውን ሰው። ከመንኰራኵሮች ከኪሩቤል መካከል እሳት ውሰድ ብሎ ባዘዘው ጊዜ እርሱ ገብቶ በአንድ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ። 7 ኪሩብም ከኪሩቤል መካከል እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታም በለበሰው ሰው እጅ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ። 8 በኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅን መሳይ ታየ። 9 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ፥ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ድንጋይ ነበረ። 10 የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ መልካቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ። 11 ሲሄዱም በአራቱ ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፥ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር፥ ራሱ ወደምታመለክትበት ስፍራ ወደዚያ ይከተሉ ነበር፤ ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር። 12 ገላቸውም ሁሉ ጀርባቸውም እጃቸውም ክንፋቸውም መንኰራኵሮቹም፥ ለአራቱ የነበሩ መንኰራኵሮች፥ በዙሪያቸው ዓይኖች ተሞልተው ነበር። 13 መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ ጌልጌል ተብለው ተጠሩ። 14 ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፤ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛውም የሰው ፊት፥ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም የንስር ፊት ነበረ። 15 ኪሩቤልም ከፍ ከፍ አሉ፤ ይህ በኮቦር ወንዝ ያየሁት እንስሳ ነው። 16 ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፤ ኪሩቤልም ከምድር ከፍ ከፍ ይሉ ዘንድ ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮች ደግሞ ከአጠገባቸው ፈቀቅ አይሉም ነበር። 17 ሕይወት ያላቸው የእንስሶች መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ነበረና እነዚህ ሲቆሙ እነዚያ ይቆሙ ነበር፥ እነዚህም ከፍ ከፍ ሲሉ እነዚያ ከእነርሱ ጋር ከፍ ከፍ ይሉ ነበር። 18 የእግዚአብሔርም ክብር ከቤቱ መድረክ ላይ ወጥቶ በኪሩቤል ላይ ቆመ። 19 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ እኔም እያየሁ ከምድር ከፍ ከፍ አሉ፤ በወጡም ጊዜ መንኰራኵሮች በአጠገባቸው ነበሩ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። 20 ይህ በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየሁት እንስሳ ነው፥ ኪሩቤልም እንደ ነበሩ አስተዋልሁ። 21 ለእያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ የሰውም እጅ አምሳያ ከክንፎቻቸው በታች ነበረ። 22 ፊቶቻቸውም በኮቦር ወንዝ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፤ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፤ እያንዳንዱም አቅንቶ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።

ሕዝቅኤል 11

1 መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚመለከት ወደ እግዚአብሔር ቤትም ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም፥ በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ። 2 እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። 3 እነርሱም። በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። 4 ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር። 5 የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔም የልባችሁን አሳብ አውቃለሁ። 6 በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል በጎዳናዎችዋም ግዳዮችን ሞልታችኋል። 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ይህችም ከተማ ድስቱ ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። 8 ሰይፍን ፈርታችኋል እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፥ በእንግዶችም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ፍርድ አደርጋለሁ። 10 በሰይፍ ትወድቃላችሁ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 11 ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12 በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፤ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል። 13 ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን? ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ። 14 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 15 የሰው ልጅ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ የወገኖችህም ሰዎች ሁሉ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ናቸው። 16 ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፥ ወደ አገሮችም በትኛቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ፥ በመጡባቸው አገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል። 17 ስለዚህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ። 18 ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ። 1920 በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 21 ልባቸውም ጸያፍንና ርኩስን ነገር በሚከተል በእነርሱ ራስ ላይ መንገዳቸውን እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። 23 የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ። 24 መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጥቶ ተለየ። 25 እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ።

ሕዝቅኤል 12

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። 3 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። 4 ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፥ በማታም ጊዜ በፊታቸው ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። 5 በፊታቸውም ግንቡን ንደል በእርሱም አውጣ። 6 ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው በጫንቃህ ላይ አንግተው፥ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን። 7 እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቱን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፥ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፥ በጨለማም አወጣሁት በፊታቸውም በጫንቃዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት። 8 በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 9 የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት። የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን? 10 አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው። 11 ደግሞም። እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም በስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ በል። 12 በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በጫንቃው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፥ በዓይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። 13 መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል። 14 ሊረዱትም በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። 15 በአሕዛብም መካከል በበተንኋቸው ጊዜ፥ በአገሮችም በዘራኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 16 በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 17 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ እንጀራህን በድንጋጤ ብላ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በኀዘን ጠጣ፤ 19 ለምድሪቱም ሕዝብ። ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤልም ምድር እንዲህ ይላል። ስለሚኖሩባት ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። 20 ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ባድማ ይሆናሉ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። 21 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 22 የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር። ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው? 23 ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን። ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው። 24 ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። 25 እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 26 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 27 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት። ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። 28 ስለዚህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 13

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን። የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤ 3 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው! 4 እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው። 5 ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም። 6 እግዚአብሔር ሳይልካቸው። እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፤ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል። 7 እኔም ሳልናገር። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን? 8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 እጄም ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፤ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 10 ሰላም ሳይኖር። ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና 11 ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉት ሰዎች። ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል። 12 እነሆ፥ ግንቡ በወደቀ ጊዜ። የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን? 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል። 14 ገለባም በሌለበት ጭቃ የመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳል በመካከሉም ትጠፋላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 15 መዓቴንም በግንቡ ላይ ገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፤ እኔም። ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ። 16 እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ የሰላምን ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ሰላምም የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፥ 18 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፉ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን? 19 ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል። 20 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ። 21 ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 22 እኔም ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና 23 ስለዚህ ከንቱን ራእይ እንግዲህ አታዩም ምዋርትንም አታምዋርቱም፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

ሕዝቅኤል 14

1 ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 3 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን? 45 ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው። 6 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ። 7 ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፤ 8 ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 9 ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ። 10 ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ እንደሚጠይቀውም ሰው ኃጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኃጢአት ይሆናል። 11 ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው። እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 12 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 13 የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር በማመፅ በእኔ ላይ ኃጢአት ስትሠራ፥ እኔም እጄን ስዘረጋባት የእንጀራዋንም በትር ስሰብር ራብን ስሰድድባት ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ሳጠፋ፥ 14 እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም፥ ቢኖሩባት በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 ክፉዎቹን አራዊት በምድር ባሳልፍ እነርሱም ልጆችዋን ቢያጠፉ ስለ አራዊትም ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥ 16 እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17 ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ። ሰይፍ ሆይ፥ በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥ 18 እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19 ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥ 20 ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን፥ ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም፥ ስሰድድባት! 22 ነገር ግን፥ እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን የሚያመጡ ይቀሩላታል፤ እነሆ፥ ወደ እናንተ ይወጣሉ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። 23 መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፤ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 15

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የወይን ግንድ፥ በዱር ዛፎች መካከል ያለ የወይን አረግ፥ ከዛፍ ሁሉ ይልቅ ብልጫው ምንድር ነው? 3 በውኑ ሥራ የሚሠራበትን እንጨት ከእርሱ ይወስዳሉን? ወይስ ሰዎች ዕቃ የሚንጠለጠልበትን ኵላብ ከእርሱ ይወስዳሉን? 4 እነሆ፥ ለመቃጠል በእሳት ላይ ተጥሎአል፥ እሳቱም ሁለቱን ጫፎቹን በልቶአል፥ መካከሉም ተቃጥሎአል፤ በውኑ ለሥራ ይጠቅማልን? 5 እነሆ፥ ደህና ሳለ ለሥራ ካልጠቀመ፥ ይልቁንስ እሳት ከበላው እርሱም ከተቃጠለ በኋላ እንዴት ሥራ ይሠራበታል? 6 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን ግንድ እሳት ይበላው ዘንድ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ እሰጣለሁ። 7 ፊቴንም በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ከእሳትም ይወጣሉ፥ እሳት ግን ይበላቸዋል፤ ፊቴንም በእነርሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ዓመፅን አድርገዋልና ምድሪቱን ባድማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 16

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥ 3 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል። ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። 4 በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። 5 በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም። 6 በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፤ አዎን። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። 7 በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ። 8 በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። 9 በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ። 10 ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ። 11 በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ። 12 በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ። 13 በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፤ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ። 14 ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። 16 ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፤ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም። 17 ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል። 18 ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ። 19 የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ እንዲሁም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20 ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው። 21 ልጆቼን አረድሽ፤ ለእነርሱም በእሳት በኩል አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን? 22 በርኵስነትሽና በግልሙትናሽ ሁሉ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቍተሽም ሳለሽ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም። 23 ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 24 ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የምንዝርናን ስፍራ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ ሠራሽ። 25 በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ ግልሙትናሽንም አበዛሽ። 26 ሥጋቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ። 27 ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ ድርጐሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። 28 አልጠገብሽምና ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም። 29 እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም። 30 የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31 በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም። 32 በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ። 33 ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃ ትሰጫቸዋለሽ። 34 ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ግልብጥ ነው፤ ማንም ለግልሙትና የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል። 35 ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። 36 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከውሽሞችሽ ጋር ባደረግሽው በግልሙትናሽ ርኵሰትሽ ስለ ፈሰሰ ኀፍረተ ሥጋሽም ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኵሰትሽም ጣዖታት ሁሉ ስለ ሰጠሻቸውም ስለ ልጆች ደም፥ 37 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽ ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ በአንቺ ላይ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፥ ኀፍረተ ሥጋሽንም ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ። 38 በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደምም አመጣብሻለሁ። 39 በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል። 40 ጉባኤን ያመጡብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይወጉሻል። 41 ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ እንግዲህስ ዋጋ አትሰጭም። 42 መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ ደግሞም አልቈጣም። 43 የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ሌላንም ነውር በርኵሰትሽ ሁሉ ላይ አትጨምሪም። 44 እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ። እንደ እናቲቱ እንዲሁ ሴት ልጂቱ ናት እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። 45 አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላሽ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። 46 ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። 47 አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ርኵሰት አደረግሽ። 48 እኔ ሕያው ነኝና አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 49 እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። 50 ኰርተው ነበር በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ ባየሁ ጊዜ አጠፋኋቸው። 51 ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኵሰት ሁሉ አጸደቅሻቸው። 52 አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፤ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፤ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ። 53 ምርኮአቸውን፥ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ፥ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ፤ 54 ስለ አጽናናሻቸው፥ እፍረትን ትሸከሚ ዘንድ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪ ዘንድ። 55 እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። 56 ክፋትሽ ሳይገለጥ በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን? 57 አሁን ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርስዋ መሰደቢያ ሆነሻል። 58 ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ተሸክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር። 59 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። 60 ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ። 61 እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም። 62-63 ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ታስቢ ዘንድ ታፍሪም ዘንድ ስለ እፍረትሽም ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ፥ ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 17

1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት ለእስራኤልም ቤት ምሳሌ ንገር፥ እንዲህም በል። 3 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዝግባንም ጫፍ ወሰደ። 4 ቀንበጡንም ቀነጠበ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ አኖረው። 5 ከምድርም ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻ ተከለው በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው። 6 በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ፥ እንዲሁ ወይን ሆነ አረግም ሰደደ ቀንበጥም አወጣ። 7 ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ፤ እነሆም፥ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ። 8 አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን ይሆን ዘንድ በመልካም መሬት ውስጥ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር። 9 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? ሥሩም የተነቀለው በብርቱ ክንድና በብዙ ሕዝብ አይደለም። 10 ተተክሎስ፥ እነሆ፥ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል። 11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 12 ለዓመፀኛ ቤት። ይህ ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? በላቸው። እንዲህም ብለህ ንገራቸው። እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። 13 ከመንግሥትም ዘር ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፤ አማለውም፥ የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ፤ 14 ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው። 15 እርሱ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን? 16 እኔ ሕያው ነኝና ያነገሠውና መሐላውን የናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ያፈረሰበቱ ንጉሥ በሚኖርበት ስፍራ ከእርሱ ጋር በባቢሎን መካከል በእርግጥ ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17 ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር በሰልፍ አይረዳውም። 18 ቃል ኪዳኑንም በማፍረስ መሐላውን ንቆአል፤ እነሆም፥ እጁን ሰጠ፥ ይህንም ሁሉ አድርጎአል፤ ስለዚህ አያመልጥም። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና የናቀውን መሐላዬን ያፈረሰውንም ቃል ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ። 20 መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመድም ይያዛል፥ ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ ከእርሱ ጋር እፋረዳለሁ። 21 ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ ወደ እየነፋሳቱ ይበተናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ። 22 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹ አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረጅምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ። 23 ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል። 24 የዱር ዛፎች ሁሉ ረጅሙን ዛፍ ዝቅ ያደረግሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ ያደረግሁ፥ የለመለመውንም ዛፍ ያደረቅሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌአለሁ።

ሕዝቅኤል 18

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 ስለ እስራኤል ምድር። አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ ብላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድር ነው? 3 እኔ ሕያው ነኝና እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዘንድ አትመስሉትም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4 እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች። 5 ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 6 በተራራም ላይ ባይበላ ዓይኞቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፤ 7 ሰውንም ባያስጨንቅ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ ፈጽሞም ባይቀማ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ የተራቈተውንም በልብስ ቢያለብስ፤ 8 በአራጣ ባያበድር፥ ትርፎቻም ባይወስድ፥ እጁንም ከኃጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፤ 9 በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፥ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥ 11 እርሱም ጻድቅ አባቱ የሠራውን ሁሉ ባይሠራ በተራራም ላይ ቢበላ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥ 12 ድሀውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥ 13 በአራጣ ቢያበድር፥ ትርፎቻም ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም፤ ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፤ ደሙ በላዩ ላይ ይሆናል። 14 እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲህም ባይሠራ፥ 15 በተራራ ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ 16 ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥ 17 እጁንም ድሀን ከመበደል ቢመልስ አራጣን ትርፎቻንም ባይወስድ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም። 18 አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል። 19 እናንተ ግን። ልጅ የአባቱን ኃጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን ባደረገ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና ባደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል። 20 ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም፤ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል። 21 ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22 የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። 23 በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን? 24 ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ሁሉ አትታሰብለትም፤ ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል። 25 እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 26 ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል። 27 ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል። 28 አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29 ነገር ግን የእስራኤል ቤት። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 30 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31 የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? 32 የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።

ሕዝቅኤል 19

1 አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል። 2 እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች። 3 ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። 4 አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት። 5 እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6 እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ። 7 ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች። 8 አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ። 9 በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት። 10 እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች። 11 ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ። 12 ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው። 13 አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። 14 ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።

ሕዝቅኤል 20

1 እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 3 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝና በእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4 ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ በውኑ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኵሰት አስታውቃቸው። 5 እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤልን በመረጥሁበት ለያዕቆብም ቤት ዘር በማልሁበት ቀን በግብጽም ምድር በተገለጥሁላቸውና። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ብዬ በማልሁላቸው ጊዜ፥ 6 በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው፤ 7 እኔም። ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። 8 እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ። በግብጽ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 9 ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 10 ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። 11 ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። 12 የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። 13 ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ። አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 14 ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 15 ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። 16 ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፤ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። 17 ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም። 18 ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው። በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። 19 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። 20 ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። 21 ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ። መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። 22 ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 23 ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤ 24 ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። 25 ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። 26 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። 27 ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመፅ አስቈጡኝ። 28 እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቈጣኝን ቍርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ። 29 እኔም። እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። 30 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኵሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? 31 ቍርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 32 ለእናንተም። እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም። 33 እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 34 ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። 35 ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። 36 በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 37 ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤ 38 ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ፤ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 39 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ ትሰሙኝ ዘንድ ባትወድዱ ሁላችሁ ጣዖቶቻችሁን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም። 40 በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድሩ ላይ ያመልኩኛል፤ በዚያም እቀበላቸዋለሁ፥ በዚያም ቍርባናችሁን በኵራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እፈልጋለሁ። 41 ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ። 42 ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 43 በዚያም የረከሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋታችሁ ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 44 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 45 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 46 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና ወደ ደቡብም ተናገር በደቡብም ባለው ዱር ላይ ትንቢት ተናገር፤ 47 ለደቡብም ዱር። የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠል ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል። 48 እኔም እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም በለው። 49 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ። ይህ ምሳሌን የሚመስል አይደለምን? ብለዋል አልሁ።

ሕዝቅኤል 21

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አቅና ወደ መቅደሶችም ተናገር በእስራኤልም ምድር ላይ ትንቢት ተናገር። 3 ለእስራኤልም ምድር እንዲህ በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ ሰይፌንም ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፥ ጻድቁንና ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ። 4 እኔም ጻድቁንና ክፉውን ከአንተ ዘንድ ስለማጠፋ፥ ስለዚህ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ባለ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። 5 ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር ሰይፌን ከሰገባው እንደ መዘዝሁ ያውቃል፥ እርሱም ደግሞ አይመለስም። 6 ስለዚህም፥ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ አልቅስ፤ ወገብህን በማጕበጥ በፊታቸው ምርር ብለህ አልቅስ። 7 እነርሱም። ስለ ምን ታለቅሳለህ? ቢሉህ፥ አንተ እንዲህ በላቸው። ወሬ ስለሚመጣ ነው፤ ልብም ሁሉ ይቀልጣል፥ እጆችም ሁሉ ይዝላሉ፥ ነፍስም ሁሉ ትደክማለች፥ ጉልበትም እንደ ውኃ ይፈስሳል፤ እነሆ፥ ይመጣል ይፈጸምማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 9 የሰው ልጅ ሆይ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ሰይፍ ሰይፍ የተሳለ የተሰነገለም ነው በል። 10 ይገድል ዘንድ ተስሎአል ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል፤ እኛስ ደስ ይለናልን? የልጄን በትር እንደ ዛፍ ሁሉ ንቆታል። 11 በእጁም እንዲያዝ ለመሰንገል ተሰጠ፤ ሰይፍ በገዳይ እጅ እንዲሰጥ ተሳለና ተሰነገለ። 12 የሰው ልጅ ሆይ፥ በሕዝቤ ላይ ነውና፥ በእስራኤል አለቆች ሁሉ ላይ ነውና ጩኽ ዋይም በል፤ እነርሱ ከሕዝቤ ጋር ለሰይፍ ተሰጥተዋል፤ ስለዚህ ጭንህን ጽፋ። 13 ፈተና ደርሶአል፤ የተናቀ በትርስ ደግሞ ባይኖር ምንድር ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 ስለዚህ፥ አንተ የሰው ልጅ፥ ትንቢት ተናገር፥ እጅህን አጨብጭብ፤ የተገደሉ ሰዎች ሰይፍ ሦስት ጊዜ ይደጋግም የሚከብባቸው የተገደለ የታላቅ ሰው ሰይፍ ነው። 15 ልባቸው እንዲቀልጥ መሰናክላቸውም እንዲበዛ የሚገድለውን ሰይፍ በበሮቻቸው ሁሉ ላይ አድርጌአለሁ፤ ወዮ! ያብረቀርቅ ዘንድ ተሰንግሎአል ይገድልም ዘንድ ተስሎአል። 16 ተዘጋጅተህ ፊትህ ወደ ወደደው ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሂድ። 17 እኔ ደግሞ በእጄ አጨበጭባለሁ መዓቴንም እጨርሳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 18 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 19 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣ ዘንድ ሁለት መንገዶችን አድርግ፤ ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፤ ምልክትም አድርግ፥ በከተማይቱ መንገድ ራስ ላይ አድርገው። 20 ሰይፍ ወደ አሞን ልጆች አገር ወደ ረባት ወደ ይሁዳም ወደ ተመሸገች ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣ ዘንድ መንገድን አድርግ። 21 የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ መንገዶች ራስ ላይ ቆሞ ነበር፤ ፍላጾችን ወዘወዘ፥ ከተራፊምም ጠየቀ፥ ጉበትም ተመለከተ። 22 የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ። 23 መሐላውንም በማሉ በዓይናቸው ዘንድ የሐሰት ምዋርት ይመስላል፥ ነገር ግን እነርሱ ይያዙ ዘንድ እርሱ ኃጢአትን ያሳስባል። 24 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኃጢአታችሁን ስለ አሰባችሁ መተላለፋችሁም ስለ ተገለጠ ኃጢአታችሁም በሥራችሁ ሁሉ ስለ ታየ እናንተም ስለ ታሰባችሁ፥ በእጅ ትያዛላችሁ። 25 አንተም ቀንህ የደረሰብህ፥ የኃጢአትህ ቀጠሮ ጊዜ የደረሰብህ፥ ርኩስ ኃጢአተኛ የእስራኤል አለቃ ሆይ፥ 26 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መጠምጠሚያውን አውልቅ፥ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ የተዋረደውን ከፍ አድርግ፥ ከፍ ያለውንም አዋርድ። 27 ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ፍርድ ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፥ ለእርሱም እሰጣታለሁ። 28-29 አንተም የሰው ልጅ ሆይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ቀናቸው በደረሰ፥ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ በደረሰ፥ በተገደሉት ኃጢአተኞች አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱን ራእይ ነገር ሲያዩልህ በሐሰትም ምዋርት ሲናገሩልህ። ሰይፍ፥ ሰይፍ ተመዝዞአል፥ ይገድልም ዘንድ ያብረቀርቅም ዘንድ ተሰንግሎአል በል። 30 ወደ ሰገባውም መልሰው። በተፈጠርህበት ስፍራ በተወለድህባትም ምድር እፈርድብሃለሁ። 31 ቍጣዬንም አፈስስብሃለሁ፥ በመዓቴም እሳት አናፋብሃለሁ፥ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 32 ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፥ ደምህም በምድር መካከል ይሆናል፥ ደግሞም አትታሰብም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።

ሕዝቅኤል 22

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት። 3 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! 4 ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። 5 አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል። 6 እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። 7 በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ። 8 ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ። 9 ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ። 10 በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። 11 ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ። 12 በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፤ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ። 14 በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ። 15 ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። 16 በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ። 17 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፤ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር አተላ ናቸው። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ። 20 እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። 21 አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። 22 ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ። 23 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 24 የሰው ልጅ ሆይ። አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት። 25 በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል። 26 ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፤ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። 27 በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። 28 እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል። 29 የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ። 30 ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። 31 ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 23

1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። 3 በግብጽም አመነዘሩ፥ በኰረዳነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ምዋሸሹ በዚያም የድንግልናቸውን ጡቶች ዳበሱ። 4 ስማቸውም የታላቂቱ ኦሖላ የእኅትዋም ኦሖሊባ ነበረ፥ ለእኔም ሆኑ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ኦሖላ ሰማርያ ናት፤ ኦሖሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት። 5 ኦሖላም ገለሞተችብኝ፥ ውሽሞችዋንም ጎረቤቶችዋን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። 6 እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ አለቆችና ሹማምቶች፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ ፈረሰኞች ነበሩ። 7 ግልሙትናዋንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች። 8 በግብጽም የነበረውን ግልሙትናዋን አልተወችም፤ በዚያ በኰረዳነትዋ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፥ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፥ ግልሙትናቸውንም አፍስሰውባት ነበር። 9 ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ በአሦራውያን እጅ አሳልፌ ሰጠኋት። 10 እነርሱም ኅፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፥ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ ፍርድንም ስላደረጉባት በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች። 11 እኅትዋም ኦሖሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፥ ግልሙትናዋም ከእኅትዋ ግልሙትና ይልቅ በዛ። 12 አለቆችንና ሹማምቶችን ጎረቤቶችዋን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። 13 የረከሰችም እንደ ሆነች አየሁ፥ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል። 14 ግልሙትናዋንም አበዛች፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ስዕል፥ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች። 15 በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ራሳቸውንም በቀለማዊ መጠምጠሚያ የጠመጠሙ ነበሩ፤ ሁሉም ከተወለዱባት አገር የሆኑትን የከለዳውያንን ልጆች መስለው መሳፍንትን ይመስሉ ነበር። 16 ባየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። 17 የባቢሎንም ሰዎች ወደ እርስዋ ፍቅር ወዳለበት መኝታ መጡ በግልሙትናቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። 18 ግልሙትናዋንም ገለጠች ኅፍረተ ሥጋዋንም አሳየች፤ ነፍሴም ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች። 19 ነገር ግን በግብጽ ምድር የገለሞተችበትን የኰረዳነትዋን ዘመን አስባ ግልሙትናዋን አበዛች። 20 ሥጋቸውም እንደ አህዮች ሥጋ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍቅር ተከተለቻቸው። 21 ስለ ኰረዳነትሽ ምክንያት ግብጻውያን ጡቶችሽን በዳበሱ ጊዜ የኰረዳነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ። 22 ስለዚህ፥ ኦሖሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ውሽሞችሽን አስነሣብሻለሁ፥ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። 23 እነርሱም የባቢሎን ሰዎች ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ አለቆችና ሹማምቶች ሁሉ፥ መሳፍንቶችና አማካሪዎች ሁሉ፥ በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው። 24 በመሣሪያና በሰረገላ በመንኰራኵርም በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። 25 ቅንዓቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፥ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረውን እሳት ትበላቸዋለች። 26 ልብስሽንም ይገፍፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ። 27 ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብጽ ምድር ያወጣሽውን ግልሙትናሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዓይንሽንም ወደ እነርሱ አታነሺም ግብጽንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም። 28 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽ በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ 29 እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፥ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽም ነውር፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽም ሁሉ ይገለጣል። 30 ከአሕዛብ ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን ያደረጉብሻል። 31 በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ። 32 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የጠለቀውንና የሰፋውን ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ። 33 በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞልያለሽ። 34 ትጠጪዋለሽ ትጨልጪውማለሽ ገሉንም ታኝኪዋለሽ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 35 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ። 36 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሖላና በኦሖሊባ ትፈርዳለህን? ኃጢአታቸውንም ታስታውቃቸዋለህ? 37 አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ከጣዖቶቻቸውም ጋር አመንዝረዋልና፥ ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና። 38 ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል ሰንበታቴንም ሽረዋል። 39 ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም፥ በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ። 40 ደግሞ መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልካችኋል፤ እነሆም መጡ፥ አንቺም ታጠብሽላቸው ዓይኖችሽንም ተኳልሽ ጌጥም አጌጥሽ፤ 41 በክብር አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊትዋም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም አኖርሽባት። 42 የደስተኞችም ድምፅ በእርስዋ ዘንድ ነበረ፤ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ። 43 እኔም በምንዝር ላረጀችው። አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች አልሁ። 44 ወደ ጋለሞታም እንደሚገቡ ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ኦሖላና ወደ ኦሖሊባ ገቡ። 45 ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል። 46 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ አሰጣቸዋለሁ። 47 ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 48 ሴቶችም ሁሉ እንደ ሴሰኝነታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። 49 ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

ሕዝቅኤል 24

1 በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ። 3 ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣድ፥ ምንቸቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት። 4 ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት። 5 ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ። 6 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርስዋ ላልወጣ ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም። 7 ደምዋ በውስጥዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም፤ 8 መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ። 9 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ። 10 እንጨቱን አብዛ፤ እሳቱን አንድድ፤ ሥጋውን ቀቅል፤ መረቁን አጣፍጠው፤ አጥንቶቹ ይቃጠሉ። 11 ትሞቅም ዘንድ ናስዋም ትግል ዘንድ ርኵሰትዋም በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን በፍም ላይ አድርጋት። 12 በከንቱ ደከመች፤ ሆኖም ዝገትዋ በእሳት ስንኳ አልለቀቀም። 13 በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም። 14 እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ ይመጣል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልመለስም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 16 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የዓይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም እንባህንም አታፍስስ። 17 በቀስታ ተክዝ፤ ለምዋቾችም አታልቅስ፥ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፥ ከንፈሮችህንም አትሸፍን የሰዎችንም እንጀራ አትብላ። 18 እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ወደ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ። 19 ሕዝቡም። ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን? አሉኝ። 20 እኔም እንዲህ አልኋቸው። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 21 ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኃይላችሁን ትምክሕት፥ የዓይናችሁን አምሮት፥ የነፍሳችሁን ምኞት መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 22 እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም የሰዎችንም እንጀራ አትበሉም። 23 መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም አታለቅሱምም፤ በኃጢአታችሁም ትሰለስላላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ታንጐራጕራላችሁ። 24 ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ይህም በመጣ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 25 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኃይላቸውን፥ የተመኩበትንም ደስታ፥ የዓይናቸውን አምሮት፥ የነፍሳቸውንም ምኞት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥ 26 በዚያ ቀን ያመለጠው ይህን ነገር በጆሮህ ያሰማ ዘንድ ወደ አንተ ይመጣል። 27 በዚያ ቀን አፍህ ላመለጠው ይከፈታል፥ አንተም ትናገራለህ ከዚያ ወዲያም ዲዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 25

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አቅንተህ ትንቢት ተናገርባቸው። 3 ለአሞንም ልጆች እንዲህ በል። የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሴ በረከሰ ጊዜ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ የይሁዳም ቤት በተማረኩ ጊዜ ስለ እነርሱ እሰይ ብለሃልና 4 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ አሰጥሃለሁ፥ እነርሱም በአንተ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንተ ዘንድ ይሠራሉ፤ ፍሬህን ይበላሉ ወተትህንም ይጠጣሉ፤ 5 የአሞንን ከተማ ለግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 6 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በእጅህ አጨብጭበሃልና፥ በእግርህም አሸብሽበሃልና፥ በእስራኤልም ምድር ላይ በነፍስህ ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሃልና 7 ስለዚህ፥ እነሆ፥ እጄን ዘርግቼብሃለህ፥ ለአሕዛብም አስበዘብዝሃለሁ፥ ከአሕዛብም ለይቼ እቈርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም አጠፋሃለሁ እፈጅህማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። 8 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሞዓብና ሴይር። እነሆ፥ የይሁዳ ቤት እንደ አሕዛብ ሁሉ ነው ብለዋልና 9 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥ 10 ከቂርያታይም፥ ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። የአሞን ልጆች በአሕዛብ መካከል ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ። 11 በሞዓብም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 12 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኤዶምያስ በይሁዳ ቤት ላይ በቀል አድርጎአልና፥ ቂም ይዞአልና፥ ብድራትንም አስከፍሎአልና 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። 14 በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር ቅሬታ አጠፋለሁ። 17 በመዓት መቅሠፍትም ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፤ በቀሌንም በላያቸው ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 26

1 እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ። እሰይ፥ የአሕዛብ በር የነበረች ተሰብራለች ወደ እኔም ተመልሳለች፤ እርስዋ ፈርሳለችና እኔ እሞላለሁ ብላለችና 3 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ። 4 የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፥ የተራቈተ ድንጋይም አደርጋታለሁ። 5 በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች። 6 በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች ከፈረሰኞችም ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። 8 በሜዳ ያሉትን ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፥ አምባም ይሠራብሻል አፈርንም ይደለድልብሻል ጋሻም ያነሣብሻል። 9 ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያደርጋል፥ ግንቦችሽንም በምሳር ያፈርሳል። 10 ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ ትቢያቸው ይከድንሻል፤ ሰዎችም በተናደች ቅጥር ወደ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ ሲገባ፥ ከፈረሰኞችና ከመንኰራኵሮች ከሰረገሎችም ድምፅ የተነሣ ቅጥርሽ ትናወጣለች። 11 በፈረሶቹ ኮቴ ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረመርማል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽም ሐውልት ወደ ምድር ይወድቃል። 12 ብልጥግናሽንም ይማርካሉ፥ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽንም ያፈርሳሉ፥ ተድላ የምታደርጊባቸውን ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ። 13 የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፤ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም። 14 የተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 15 ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል። የተወጉት ባንቋረሩ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች ይነዋወጡ የለምን? 16 የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያወጣሉ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ለብሰው በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ በአንቺም ይደነቃሉ። 17 በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፥ እንዲህም ይሉሻል። በባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ! 18 አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያለ ደሴቶች ከመጥፋትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ። 19 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥ 20 የቀድሞ ሕዝብ ወዳሉበት ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፤ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። 21 ለድንጋጤ አደርግሻለሁ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘላለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 27

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ፥ 3 በባሕር መግቢያ የምትኖር በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስንም እንዲህ በላት። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ። በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል። 4 ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፈጽመዋል። 5 ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፥ ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባ ወስደዋል። 6 ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፥ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ መቀመጫዎችሽን ሠርተዋል። 7 ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቅ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል። 8 የሲዶናና የአራድ ሰዎች ቀዛፎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ። 9 በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ። 10 ፋርስና ሉድ ፉጥም በሠራዊትሽ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ውበትሽን ሰጡ። 11 የአራድ ሰዎችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፥ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፥ ውበትሽንም ፈጽመዋል። 12 ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፤ በብርና በብረት በቈርቈሮና በእርሳስ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 13 ያዋንና ቶቤል ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሰዎችን ነፍሳትና የናሱን ዕቃ ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 14 ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች በፈረሶችና በፈረሰኞች በበቅሎዎችም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 15 የድዳን ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ። ብዙ ደሴቶች የእጅሽ ገበያዎች ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ። 16 ከሥራሽ ብዛት የተነሣ ሶርያ ነጋዴሽ ነበረች በበሉርና በቀይ ሐር በወርቀ ዘቦም በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቍም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 17 ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ፥ ማር ዘይትም በለሳንም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 18 ከሥራሽ ብዛትና ከብልጥግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ ደማስቆ ነጋዴሽ ነበረች፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ በነጭም በግ ጠጕር ይነግዱ ነበር። 19 ዌንዳንና ያዋን ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትና ብርጕድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ። 20 ድዳን በከብት ላይ ለመቀመጥ በመረሻት ነጋዴሽ ነበረች። 21 ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶችና በአውራ በጎች በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 22 የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በጥሩ ሽቶና በክብር ድንጋይ ሁሉ በወርቅም ስለ አንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር። 23 ካራንና ካኔ ዔድንም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ። 24 እነዚህ ባማረ ልብስ በሰማያዊ ካባ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር። 25 የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ። 26 ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ወኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ። 27 ብልጥግናሽና ሸቀጥሽ ንግድሽም መርከበኞችሽም መርከብ መሪዎችሽም ሰባራሽንም የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይወድቃሉ። 28 ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። 29 ቀዛፊዎችም ሁሉ መርከበኞችም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፤ 30 ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፥ በአመድም ውስጥ ይንከባለላሉ፤ 31 ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ ማቅም ያሸርጣሉ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። 32 በትካዜያቸውም ልቅሶ ያነሡልሻል፥ ስለ አንቺም ሙሾ ያሞሻሉ እንዲህም ይላሉ። በባሕር መካከል ጠፍቶ እንደ ቀረ እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው? 33 ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ አሕዛብን አጥግበሻል፤ በብልጥግናሽና በንግድሽ ብዛት የምድርን ነገሥታት ባለ ጠጎች አድርገሻል። 34 አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባህር ተሰብረሻል ንግድሽና ጉባኤሽ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል። 35 በደሴቶሽ የሚኖሩ ሁሉ ተደንቀውብሻል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውም ተለውጦአል። 36 የአሕዛብ ነጋዴዎች አፍዋጩብሽ፤ አንቺ ለድንጋጤ ሆነሻል፥ እስከ ዘላለምም አትገኚም።

ሕዝቅኤል 28

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህ ኰርቶአል አንተም። እኔ አምላክ ነኝ፥ በእግዚአብሔር ወንበር በባሕር መካከል ተቀምጫለሁ ብለሃል፤ ነገር ግን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። 3 እነሆ፥ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ ነህ፥ ምሥጢርም ሁሉ ከአንተ የተሸሸገ አይደለም። 4 በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጥግናን ለራስህ አግኝተሃል ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል። 5 በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጥግናህን አብዝተሃል በብልጥግናህም ልብህ ኰርቶአል። 6 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና 7 ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሌላ አገር ሰዎችን፥ የአሕዛብን ጨካኞች፥ አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ ክብርህንም ያረክሳሉ። 8 ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ ተገድለው እንደ ሞቱ በባሕር ውስጥ ትሞታለህ። 9 በውኑ በገዳይህ ፊት። እኔ አምላክ ነኝ ትላለህን? ነገር ግን በገዳይህ እጅ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። 10 በእንግዶች እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 12 የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። 13 በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር። 14 አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። 15 ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ። 16 በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ። 17 በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ። 18 በበደልህ ብዛት በንግድህም ኃጢአት መቅደስህን አረከስህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርስዋም በልታሃለች፥ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ። 19 በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል፥ እስከ ዘላለምም አትገኝም። 20 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 21 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፥ እንዲህም በል። 22 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም ባደረግሁባት ጊዜ በተቀደስሁባትም ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 23 ቸነፈርንም በእርስዋ ላይ፥ ደምንም በጎዳናዋ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያዋ በላይዋ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልዋ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 24 ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ካናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኵርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 25 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። 26 ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 29

1 በአሥረኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፥ 3 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በወንዞች መካከል የምትተኛና። ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ። 4 በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ፥ የወንዞችህንም ዓሦች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፥ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ። 5 አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፥ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም አትሰበሰብም መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ። 6 በግብጽም የሚኖሩ ሁሉ ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ። 8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ። 9 የግብጽም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ። ወንዙ የእኔ ነው የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና። 10 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ። 11 የሰው እግር አያልፍባትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም። 12 ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብጽን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፥ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመደ ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤ 14 የግብጽንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ። 15 ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በአሕዛብ ላይ ከፍ አትልም፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ። 16 የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፥ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 17 እንዲህም ሆነ፤ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ አገልግሎት አስገለገለ፤ ራስ ሁሉ የተላጨ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስላገለገለው አገልግሎት እርሱና ሠራዊቱ ደመወዝ ከጢሮስ አልተቀበሉም። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፥ ብዛትዋንም ይወስዳል ምርኮዋንም ይማርካል ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል። 20 ስለ እኔ ሠርተዋልና ስለ አገልግሎቱ ደመወዝ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጣለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 30

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥ 3 የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል። 4 ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብጽ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል። 5 ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ። 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 7 ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ። 8 እሳትንም በግብጽ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 9 በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ፥ ይመጣልና። 10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እሽራለሁ። 11 እርሱና የአሕዛብ ጨካኞች ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በተገደሉት ይሞላሉ። 12 ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣዖቶቹን አጠፋለሁ ምስሎችንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ በግብጽ ምድር አለቃ አይሆንም፥ በግብጽም ምድር ላይ ፍርሃትን አደርጋለሁ። 14 ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ። 15 በግብጽም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ብዛት አጠፋለሁ። 16 በግብጽም እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ በሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይሆኑባታል። 17 የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም gWlማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ ሴቶችም ይማረካሉ። 18 የግብጽን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ። 19 እንዲሁ በግብጽ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 20 እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 21 የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ፤ እነሆም፥ በጨርቅ በመጠቅለል ይፈወስ ዘንድ ሰይፉንም ለመያዝ እንዲበረታ አልታሰረም። 22 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስረግፈዋለሁ። 23 ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ። 24 የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፥ ተወግቶም በሚሞተው እንጕርጕሮ በፊቱ ያንጐራጕራል። 25 የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፤ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 26 ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 31

1 እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንንና የሕዝቡን ብዛት እንዲህ በላቸው። በታላቅነትህ ማንን መስለሃል? 3 እነሆ፥ አሦር ጫፉ እንደ ተዋበ፥ ችፍግነቱ ጥላ እንደ ሰጠ፥ ቁመቱም እንደ ረዘመ፥ ራሱም በደመናዎች መካከል እንደ ነበረ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ነበረ። 4 ውኆችም አበቀሉት፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ። 5 ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ ጫፎቹንም ባበቀለ ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ። 6 የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆቻቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ አደረጉ፥ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፥ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር። 7 ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። 8 በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አላጨለሙትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመሳሰለውም ነበር። 9 በጫፎቹም ብዛት ውብ አደረግሁት በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት። 10 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ቁመትህ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ራሱንም በደመናዎች መካከል አድርጎአልና፥ 11 ልቡም በቁመቱ ኰርቶአልና ከአሕዛብ በጨካኙ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እርሱም እንደ ክፋቱ መጠን ያደርግበታል እኔም አሳድደዋለሁ። 12 የሌላ አገር ሰዎች፥ የአሕዛብ ጨካኞች የሆኑ፥ ቈርጠው ጣሉት፤ በተራሮችና በሸለቆች ሁሉ ውስጥ ጫፎቹ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፥ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ከጥላው ተመልሰው ተዉት። 1314 ወደ ጕድጓድ በሚወርዱ በሰው ልጆች መካከል ሁላቸው ለታችኛው ምድር ለሞት አልፈው ተሰጥተዋልና በውኃ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሁሉ በቁመታቸው እንዳይረዝሙ፥ ራሳቸውንም በደመናዎች መካከል እንዳያደርጉ፥ ውኃንም የሚጠጡ ኃያላኖቻቸው ሁሉ በቁመታቸው እንዳይቆሙ፥ በወደቀው ግንድ ላይ የሰማይ ወፎች ሁሉ ይቀመጣሉ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይሆናሉ። 15 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶ አስለቀስሁ፤ ቀላዩንም ስለ እርሱ ሸፈንሁት ፈሳሾቹንም ከለከልሁ ታላላቆችም ውኆች ተከለከሉ፤ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት፥ የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ ዛሉ። 16 ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ከመውደቁ ድምፅ የተነሣ አሕዛብን እንቀጠቀጥሁ፤ ውኃም የሚጠጡ ሁሉ፥ ምርጦችና መልካካሞች የሊባኖስ ዛፎች፥ የዔድን ዛፎች ሁሉ በታችኛው ምድር ውስጥ ተጽናንተዋል። 17 ክንዱም ወደ ነበሩት በአሕዛብም መካከል በጥላው ወደ ተቀመጡት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ሰዎች ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወረዱ። 18 በክብርና በታላቅነት በዔድን ዛፎች መካከል ማንን መስለሃል? ነገር ግን ከዔድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል፥ በሰይፍም በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ትተኛለህ። ይህም ፈርዖንና የሕዝቡ ብዛት ሁሉ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 32

1 እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በለው። የአሕዛብን አንበሳ መስለህ ነበር፥ ነገር ግን እንደ ባሕር ዘንዶ ሆነሃል፤ በወንዞችህም ወጥተሃል፥ ወኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። 3 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ አሕዛብ ጉባኤ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። 4 በምድርም ላይ እተውሃለሁ፥ በምድረ በዳም ፊት እጥልሃለሁ፥ የሰማይንም ወፎች ሁሉ አሳርፍብሃለሁ፥ የምድርንም አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። 5 ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። 6 የምትዋኝባትንም ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖችም ከአንተ ይሞላሉ። 7 ባጠፋሁህም ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶችንም አጨልማለሁ፤ ፀሐዩንም በደመና እሸፍናለሁ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም። 8 የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በላይህ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ጥፋትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። 10 ብዙም አሕዛብን አስደንቅብሃለሁ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ስለ አንተ እጅግ አድርገው ይፈራሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣል። 11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። 12 በኃያላን ሰይፍ የሕዝብህን ብዛት እጥላለሁ፤ ሁሉ የአሕዛብ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያጠፋሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። 13 በብዙም ውኃ አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም የእንስሳም ኮቴ አይረግጠውም። 14 በዚያን ጊዜ ውኃቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 የግብጽንም ምድር ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በቀሠፍሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 16 የሚያለቅሱበት ልቅሶ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቈነጃጅት ያለቅሱበታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዛትዋ ሁሉ ያለቅሱበታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17 እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርስዋንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። 19 በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። 20 በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርስዋንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። 21 የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ሆነው ከረዳቶቹ ጋር ይናገሩታል፤ በሰይፍም የተገደሉት ያልተገረዙ ወርደው ተኝተዋል። 22 አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ መቃብራቸው በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም በሰይፍ ወድቀው ተገደሉ። 23 መቃብራቸው በጕድጓዱ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል። 24 ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብርዋ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። 25 በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ መቃብርዋ በዙሪያዋ ነው ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያስፈሩ ነበር ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል። 26 ሞሳሕና ቶቤል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ ሁሉም ሳይገረዙ በሰይፍ ተገድለዋል፤ በሕያዋን ምድር ያስፈሩ ነበርና። 27 በሕያዋንም ምድር ኃያላኑን ያስፈሩ ነበርና መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሲኦል ከወረዱ፥ ሰይፋቸውንም ከራሳቸው በታች ካደረጉ፥ ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ከሆነ ጋር ከወደቁ ካልተገረዙ ኃያላን ጋር ይተኛሉ። 28 አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ። 29 ኤዶምያስና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር በኃይላቸው ተኝተዋል፤ ካልተገረዙትና ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ይተኛሉ። 30 የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጕድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። 31 በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 32 መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 33

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው። ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥ 3 እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ 4 የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። 5 የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። 6 ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ። 7 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 8 ኃጢአተኛውን። ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 9 ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። 10 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት። እናንተ። በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። 11 እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። 12 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው። በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። 13 እኔ ጻድቁን። በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። 14 እኔም ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 15 ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 16 የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 17 ነገር ግን የሕዝብህ ልጆች። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። 18 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ ይሞትባታል። 19 ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል። 20 እናንተ ግን። የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ። 21 እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ። ከተማይቱ ተመታች አለኝ። 22 ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተች ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም። 23 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 24 የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ። አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። 25 ስለዚህ እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 26 ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 27 እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ። 28 ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፥ ማንም አያልፍባቸውም። 29 ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 30 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር። እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ ብለው ይናገራሉ። 31 ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ስስታቸውን ትከተላለች። 32 እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 33 እነሆ፥ ይህ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 34

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? 3 ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። 4 የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። 5 እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። 6 በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። 7 ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 8 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና 9 ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። 11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ። 12 እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። 13 ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። 14 በመልካም ማሰማርያ እሰማራቸዋለሁ ጕረኖአቸውም በረጅሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። 15 እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ። 17 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ። 18 የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? 19 በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። 20 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል። እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። 21 እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ 22 ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። 23 በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። 24 እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 25 የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። 26 እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናብ ይሆናል። 27 የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 28 እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም። 29 የዝናን ተክል አቆምላቸዋለሁ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም። 30 እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31 እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 35

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ 3 እንዲህም በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ። 4 ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ። 5 የዘላለም ጥል ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በኋለኛይቱ የኃጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና 6 ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል። 7 የሴይርንም ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ። 8 ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ። 9 ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 10 እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ። እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን ብለሃልና 11 ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ እሠራለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ። 12 አንተም። ፈርሰዋል መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል ብለህ በእስራኤል ተራሮች ላይ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁት ታውቃለህ። 13 በአፋችሁም ተመካችሁብኝ፥ ቃላችሁንም አበዛችሁብኝ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ። 14 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 15 የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ በላዩ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 36

1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናግረህ። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በል። 2 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠላት በእናንተ ላይ። እሰይ፥ የጥንት ከፍታዎች ለእኛ ርስት ሆነዋል ብሎአልና 3 ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለቀሩት አሕዛብ ርስት ትሆኑ ዘንድ በዙሪያችሁ ያሉ ባድማ አድርገዋችኋልና፥ ውጠዋችሁማልና፥ እናንተም የተናጋሪዎች ከንፈር መተረቻና የአሕዛብ ማላገጫ ሆናችኋልና 4 ስለዚህ፥ እናንተ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለፈሳሾችና ለሸለቆች ለምድረ በዳዎች ባዶ ለሆኑትም በዙሪያ ላሉት ለቀሩት አሕዛብ ምርኮና መሳቂያ ለሆኑት ከተሞች እንዲህ ይላል፤ 5 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያሳድዱአትና ይበዘብዙአት ዘንድ በልባቸው ሁሉ ደስታና በነፍሳቸው ንቀት ምድሬን ርስት አድርገው ለራሳቸው በሰጡ በቀሩት አሕዛብና በኤዶምያስ ሁሉ ላይ በቅንዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፤ 6 ስለዚህ ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለተራሮችና ለኮረብቶችም ለፈሳሾችና ለሸለቆችም እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የአሕዛብን ስድብ ስለ ተሸከማችሁ በቅንዓቴና በመዓቴ ተናግሬአለሁ፤ 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ስድባቸውን በእርግጥ ይሸከማሉ ብዬ ምያለሁ። 8 የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ እናንተ ግን ቅርንጫፎቻችሁን ታቈጠቍጣላችሁ፥ ይመጡም ዘንድ ቀርበዋልና ለሕዝቤ ለእስራኤል ፍሬአቸሁን ትሰጣላችሁ። 9 እነሆ፥ እኔ ለእናንተ ነኝና፤ ወደ እናንተም እመለከታለሁ፥ እናንተም ትታረሳላችሁ ይዘራባችሁማል፤ 10 እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፥ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ፤ 11 ሰውንና እንስሳውንም አበዛባችኋለሁ፥ እነርሱም ይበዛሉ ያፈሩማል፤ እንደ ጥንታችሁም ሰዎችን አኖርባችኋለሁ፥ ቀድሞም ካደረግሁላችሁ ይልቅ መልካም አደርግላችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12 ሰዎችንም፥ ሕዝቤን እስራኤልን፥ በእናንተ ላይ አስሄዳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይወርሱሻል ርስትም ትሆኛቸዋለሽ፥ ከእንግዲህም ወዲያ ልጅ አልባ አታደርጊአቸውም። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ። ሰው በሊታ ምድር ነሽ ሕዝብሽንም ልጅ አልባ የምታደርጊ ነሽ ብለዋችኋልና 14 ስለዚህ ዳግመኛ ሰው በሊታ አትሆኝም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን ልጅ አልባ አታደርጊም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 15 ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አላሰማብሽም፥ ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አትሸከሚም፥ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 17 የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት በምድራቸው በተቀመጡ ጊዜ በመንገዳቸውና በሥራቸው አረከሱአት፥ መንገዳቸውም በፊቴ እንደ መርገም አደፍ ነበረ። 18 በምድር ላይ ስላፈሰሱት ደም በጣዖቶቻቸውም ስላረከሱአት መዓቴን አፈሰስሁባቸው፤ 19 ወደ አሕዛብም በተንኋቸው ወደ አገሮችም ተዘሩ፤ እንደ መንገዳቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። 20 ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን። ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። 21 እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው። 22 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም። 23 በአሕዛብም ዘንድ የረከሰውን፥ በመካከላቸው ያረከሳችሁትን ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ በዓይናቸውም ዘንድ በተቀደስሁባችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 24 ከአሕዛብም መካከል አወጣችኋለሁ ከየአገሩም ሁሉ እሰበስባችኋለሁ ወደ ገዛ ምድራችሁም አመጣችኋለሁ። 25 ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። 26 አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። 27 መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። 28 ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። 29 ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህልንም እጠራዋለሁ አበዛውማለሁ ራብንም አላመጣባችሁም። 30 ደግሞም የራብን ስድብ ከአሕዛብ ዘንድ እንዳትሸከሙ የዛፍን ፍሬና የእርሻውን ቡቃያ አበዛለሁ። 31 ክፉውን መንገዳችሁንና መልካም ያይደለውን ሥራችሁንም ታስባላችሁ፥ ስለ በደላችሁና ስለ ርኵሰታችሁም ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 32 ይህን የሠራሁ ስለ እናንተ እንዳይደለ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ መንገዳችሁ እፈሩና ተዋረዱ። 33 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከኃጢአታችሁ ሁሉ ባነጻኋችሁበት ቀን በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ። 34 ባድማ የነበረች በመንገደኛም ሁሉ ዓይን ዘንድ ባድማ የነበረች ምድር ትታረሳለች። 35 ሰዎችም። ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች፤ የፈረሱት ባድማ የሆኑት የጠፉትም ከተሞች ተመሽገዋል ሰውም የሚኖርባቸው ሆነዋል ይላሉ። 36 በዙሪያችሁም የቀሩት አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር የፈረሱትን ስፍራዎች እንደ ሠራሁ ውድማ የሆነውንም እንደ ተከልሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፥ እኔም አደርገዋለሁ። 37 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለዚህ ደግሞ አደርግላቸው ዘንድ የእስራኤል ቤት ይሹኛል ሰውንም እንደ መንጋ አበዛላቸዋለሁ። 38 እንደ ተቀደሱ በጎች፥ በበዓላቶችዋ ቀን እንደሚሆኑ እንደ ኢየሩሳሌም በጎች፥ እንዲሁ የፈለሱት ከተሞች በሰዎች መንጋ ይሞላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 37

1 የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። 2 በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆም፥ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር። 3 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን? አለኝ። እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁ። 4 እርሱም እንዲህ አለኝ። በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ። 5 ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። 6 ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 7 እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። 8 እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። 9 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። 10 እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። 11 እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ። አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል። 12 ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ። 13 ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14 መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 15 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 16 አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና። ለይሁዳና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች ብለህ በላዩ ጻፍ፤ ሌላም በትር ውሰድና። የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ። 17 አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፥ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ። 18 የሕዝብህም ልጆች። ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥ 19 አንተ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው። 20 የምትጽፍባቸውም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ። 21 አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ 22 በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፤ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም። 23 ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 24 ባሪያዬም ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል። 25 አባቶቻችሁም በኖሩበት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል፤ ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል። 26 የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ አበዛቸውማለሁ መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ። 27 ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 28 መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 38

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሞሳሕና በቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናበት፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ 3 እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቢል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4 እመልስህማለሁ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህንም ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን ሰይፍንም ያያዙትን ሁሉ፥ ታላቁን ወገን አወጣለሁ፥ 5 ፋርስንና ኢትዮጵያን ፉጥንም ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥ 6 ጋሜርንና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ። 7 አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ አለቃ ሁናቸው። 8 ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘላለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል። 9 አንተም ትወጣለህ፥ እንደ ዐወሎ ነፋስም ትመጣለህ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ። 10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ 11 ክፉ አሳብንም ታስባለህ፥ እንዲህም ትላለህ። ቅጥርን ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለው ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤ 12 ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ። 13 ሳባና ድዳን የተርሴስም ነጋዴዎች መንደሮችዋም ሁሉ። ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል። 14 አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለዚህ ትንቢት ተናገር ጎግንም እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል ሳይፈራ በተቀመጠ ጊዜ አንተ አታውቀውምን? 15 አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ። 16 ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፥ ጎግ ሆይ፥ በዓይናቸው ፊት በተቀደስሁብህ ጊዜ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ። 17 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያቶች በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? 18 በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19 በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ። በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ 20 ከፊቴም የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች የምድረ በዳም አራዊት በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮችም ይገለባበጣሉ ገደላገደሎችም ይወድቃሉ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። 21 በተራሮቼም ሁሉ በእርሱ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22 በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። 23 ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

ሕዝቅኤል 39

1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ 2 እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ። 3 ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ። 4 አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። 5 አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6 በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 8 እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው። 9 በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፥ የጦር መሣሪያዎችንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ ጎመድንና ጦርንም ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 10 በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከምድረ በዳ አይወስዱም ከዱርም አይቈርጡም፤ የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 11 በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ የሚያልፉትንም ይከለክላል፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ይቀብራሉ፤ የሸለቆውንም ስም ሐሞንጎግ ብለው ይጠሩታል። 12 ምድሩንም ያጸዱ ዘንድ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ይቀብሩአቸዋል፥ 13 የምድርም ሕዝብ ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፥ በተመሰገንሁበትም ቀን ለክብር ይሆንላችኋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ከሰባት ወርም በኋላ ይመረምራሉ። 15 በምድርም የሚዞሩት ያልፋሉ፤ የሰውንም አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት ያኖሩበታል። 16 ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። እንዲሁ ምድሪቱን ያጸዳሉ። 17 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው። ኑ፥ ተከማቹ፥ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕት፥ እርሱም ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየስፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ። 18 የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሳንን ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ። 19 እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። 20 በሰደቃዬም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ አሕዛብም ሁሉ ያደርግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። 22 ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 23 አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ በደሉኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ ሸሸግሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ። 24 እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው ፊቴንም ከእነርሱ ሸሸግሁ። 25 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። 2627 ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ። 28 እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም፥ 29 ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 40

1 በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። 2 በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ። 3 ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆም፥ መልኩ እንደ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። 4 ሰውዬውም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አሳይህ ዘንድ አንተ ወደዚህ ተመርተሃልና በዓይንህ እይ በጆሮህም ስማ በማሳይህም ሁሉ ላይ ልብህን አድርግ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር አለኝ። 5 እነሆም፥ በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ የክንዱ ልክ አንድ ክንድ ከጋት የሆነ ስድስት ክንድ ያለበት የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ የቅጥሩንም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 6 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር መጣ በደረጃዎቹም ላይ ወጣ፥ በበሩ በኩል ያለውንም የመድረኩን ወለል ወርዱን አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 7 የዘበኛውም ጓዳ ሁሉ ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በዘበኛውም ጓዳዎች መካከል አምስት ክንድ ነበረ፤ በበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ። 8 በስተ ውስጥም ያለውን የበሩን ደጀ ሰላም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 9 የበሩንም ደጀ ሰላም ስምንት ክንድ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ ነበረ። 10 የምሥራቁም በር የዘበኛ ጓዳዎች በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፥ ለሦስቱም አንድ ልክ ነበረ፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል አንድ ልክ ነበረ። 11 የበሩንም መግቢያ ወርድ አሥር ክንድ የበሩንም ርዝመት አሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ። 12 በዘበኛ ጓዳዎችም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበሩ። 13 ከአንዱም የዘበኛ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሀያ አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ መዝጊያውና መዝጊያውም ትይዩ ነበረ። 14 ደጀ ሰላሙንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም ደጀ ሰላም ዙሪያ አደባባይ ነበረ። 15 ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ ደጀ ሰላም መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ። 16 በዘበኛ ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩባቸው፤ ደግሞም በደጀ ሰላሙ ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 17 ወደ ውጭውም አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 18 ወለሉም በበሮች አጠገብ ነበረ ይህም ታችኛው ወለል እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ። 19 ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 20 ወደ ሰሜንም መራኝ፥ እነሆም፥ በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከት በር ነበረ፤ ርዝመቱንና ወርዱንም ለካ፥ 21 የዘበኛ ጓዳዎቹም በዚህ በኩል ሦስት በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መዛነቢያዎቹም እንደ ፊተኛው በር ልክ ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 22 መስኮቶቹም መዛነቢያዎቹም የዘንባባ ዛፎቹም ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ልክ ነበሩ። ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ። 23 በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ከበርም ወደ በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 24 ወደ ደቡብም መራኝ፥ እነሆም፥ ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መዛነቢያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። 25 በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ እንደ እነዚያ መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 26 ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፥ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ወገን ሆኖ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 27 በውስጠኛውም አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ ከበር እስከ በር ድረስ በደቡብ በኩል መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 28 በደቡብም በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የደቡብን በር ለካ፤ 29 እንደዚያውም መጠን አድርጎ የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 30 በዙሪያውም ደጀ ሰላሞች ነበሩ፤ ርዝመታቸውም ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ። 31 መዛነቢያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ። 32 በውስጠኛውም አደባባይ በምሥራቅ በኩል አገባኝ፥ እንደዚያውም መጠን በሩን ለካ፤ 33 እንደዚያውም መጠን የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 34 መዛነቢያዎቹም በስተ ውጭ ወዳለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። 35 በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ እንደዚያውም መጠን ለካው፤ 36 የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩበት፥ ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ። 37 የግንቡም አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። 38 በበሮቹም በግንብ አዕማድ አጠገብ ዕቃ ቤቱና መዝጊያው ነበሩ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር። 39 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የኃጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ ደጀ ሰላም በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 40 በሰሜን በኩል ባለው በር በስተ ውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንድ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በሌላውም ወገን በበሩ ደጀ ሰላም በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 41 በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ። 42 ስለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው ክንድ ተኩል ወርዳቸውም ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን የሚያርዱበትን ዕቃ ያኖሩባቸው ዘንድ፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። 43 በዙሪያውም አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ ወደ ውስጥ ተቀልብሶ ነበር፤ በገበታዎቹም ላይ የቍርባኑ ሥጋ ነበረባቸው። 44 ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፥ እነሆም፥ ሁለት ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከት በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ደቡብ ይመለከት ነበር፤ ሌላውም ወደ ደቡብ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፥ መግቢያውም ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር። 45 ሰውዬውም። ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው። 46 ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት መሠዊያውን ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው አለኝ። 47 አደባባዩንም በአራት ማዕዘኑ ርዝመቱን መቶ ክንድ ወርዱንም መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ። 48 ወደ ቤቱም ደጀ ሰላም አመጣኝ፥ የደጀ ሰላሙንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ አሥራ አራት ክንድ ነበረ፥ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። 49 የደጀ ሰላሙም ርዝመት ሀያ ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ወደ እርሱም የሚያደርሱ አሥር ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን አንድም በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።

ሕዝቅኤል 41

1 ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። 2 የመግቢያውም ወርድ አሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱንም አርባ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ። 3 ወደ ውስጥም ገባ፥ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ። 4 በመቅደሱም ፊት ርዘመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና። ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው አለኝ። 5 የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ አድርጎ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። 6 ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፥ በመቅደሱም ግንብ ውስጥ ደገፋዎች አልነበሩም። 7 በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። 8 ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። 9 የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ። 1011 በዚህም በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል የጓዳዎች መግቢያ ነበረ የባዶውም ስፍራ ወርድ በዙሪያ አምስት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ ልዩ ስፍራ ነበረ። 12 በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ። 13 የመቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 14 ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የመቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድ አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 15 ወደ ኋላውም ባለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት በዚህና በዚያም ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 16 መድረኮቹ፥ መቅደሱና በስተ ውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፥ በሦስቱም ዙሪያ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የዓይነ ርግብ ነበሩ፤ 17 በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም ውጭውም ተለብጦ ነበር። 18 ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፤ ለእያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው። 19 በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፥ በሌላውም ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተደርጎ ነበር። 20 ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ። 21 የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደ ሌላው መልክ ነበረ። 22 መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፤ ማዕዘኖቹም እግሩም አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፤ እርሱም። በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት አለኝ። 23 ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው። 24 ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። 25 በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በስተ ውጭም ባለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ። 26 በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዓይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።

ሕዝቅኤል 42

1 በውጭም አደባባይ በሰሜኑ መንገድ አወጣኝ፥ በልዩውም ስፍራ አንጻርና በሰሜን በኩል ባለው ግቢ ፊት ለፊት ወዳለው ዕቃ ቤት አገባኝ። 2 መቶ ክንድ በሆነው ርዝመት ፊት በሰሜን በኩል መዝጊያ ነበረ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ። 3 በውስጠኛውም አደባባይ በሀያው ክንድ አንጻር በውጭውም አደባባይ በወለሉ አንጻር በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ። 4 በዕቃ ቤቶቹም ፊት በስተ ውስጥ ወርዱ አሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መዝጊያዎቻቸውም ወደ ሰሜን ይመለከቱ ነበር። 5 መተላለፊያውም አሳጥሮአቸዋልና ላይኞቹ ዕቃ ቤቶች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ። 6 በሦስትም ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩላቸውምና ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ። 7 በውጭ በዕቃ ቤቶቹ አጠገብ ያለው፥ ወደ ውጭው አደባባይ የሚመለከተው ቅጥር፥ በዕቃ ቤቶች ትይዩ የሆነ፥ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ነበረ። 8 በመቅደሱ ፊት የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው መቶ ክንድ ሲሆን በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ነበረና። 9 ከእነዚህም ዕቃ ቤቶች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባበት መግቢያ ነበረ። ይህም በቅጥሩ ራስ አጠገብ ነበረ። 10 በደቡብም በኩል በልዩው ስፍራና በግቢው አንጻር ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 11 በስተ ፊታቸውም የነበረ መንገድ በሰሜን በኩል እንደ ነበረው እንደ ዕቃ ቤቶቹ መንገድ ምስያ ነበረ። ርዝመታቸውም ወርዳቸውም መውጫቸውም ሥርዓታቸውም መዝጊያዎቻቸውም በዚያው ልክ ነበረ። 12 በደቡብም በኩል ካሉት ዕቃ ቤቶች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ። 13 እንዲህም አለኝ። በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቍርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ። 14 ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፤ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፥ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ። 15 ውስጠኛውንም ቤት ለክቶ በፈጸመ ጊዜ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ እርሱንም በዙሪያው ለካው። 16 የምሥራቁን ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 17 ዞረም፥ የሰሜኑንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 18 ዞረም፥ የደቡቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 19 ዞረም፥ የምዕራቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 20 በአራቱ ወገን ለካው። የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ይለይ ዘንድ ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።

ሕዝቅኤል 43

1 ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ። 2 እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። 3 ያየሁትም ራእይ ከተማይቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮበር ወንዝ እንዳየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 4 የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ። 5 መንፈሱም አነሣኝ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን ሞልቶት ነበር። 6 በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፥ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር። 7 እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘላለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በግልሙትናቸውና በከፍታዎቻቸው ባለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም፤ 8 መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱም መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው። 9 አሁንም ግልሙትናቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፥ እኔም ለዘላለም በመካከላቸው አድራለሁ። 10 አንተም የሰው ልጅ፥ ከኃጢአታቸው የተነሣ ያፍሩ ዘንድ ለእስራኤል ወገን ይህን ቤት አሳያቸው አምሳያውንም ይለኩ። 11 ከሠሩትም ሥራ ሁሉ የተነሣ ቢያፍሩ፥ የቤቱን መልክና ምሳሌውን መውጫውንም መግቢያውንም ሥርዓቱንም ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዓቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው። 12 የቤቱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ራስ ላይ ዳርቻው ሁሉ በዙሪያው ከሁሉ ይልቅ የተቀደስ ይሆናል። እነሆ፥ የቤቱ ሕግ ይህ ነው። 13 የመሠዊያውም ልክ በክንድ ይህ ነው፥ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፥ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው መሠረት እንዲሁ ነው። 14 በመሬቱም ላይ ካለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ነው። 15 ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት። 16 የምድጃውም ርዝመት አሥራ ሁለት ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው። 17 የእርከኑም ርዝመት አሥራ አራት ክንድ ወርዱም አሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ እኩል ክንድ ነው፥ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ። 18 እንዲህም አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው። 19 ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20 ከደሙም ትወስዳለህ፥ በአራቱ ቀንዶቹም በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ በዙሪያውም ባለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ ታስተሰርይለትማለህ። 21 ለኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፥ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በታዘዘው ስፍራ ይቃጠላል። 22 በሁለተኛውም ቀን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል። 23 ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን ነውር የሌለበትን አውራ በግ ታቀርባለህ። 24 በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፥ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል። 25 ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየልን ታቀርባለህ፥ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈን ከመንጋውም የወጣውን አንድ አውራ በግ ያቀርባሉ። 26 ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርያሉ ያነጹትማል፥ እንዲሁም ይቀድሱታል። 27 ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን የደኅንነትንም መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 44

1 ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። 2 እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል። 3 አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥበታል፤ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል። 4 በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አመጣኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 5 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ልብ አድርግ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዓትና ሕግ ሁሉ የምናገርህን ሁሉ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱንም መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ። 6 ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ 7 እንጀራዬን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ በመቅደሴ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ ቤቴንም ያረክሱ ዘንድ በልባቸውና በሥጋቸው ያልተገረዙትን እንግዶችን ሰዎች አግብታችኋልና፥ እነርሱም በርኵሰታችሁ ሁሉ ላይ ይጨመሩ ዘንድ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና ርኵሰታችሁ ሁሉ ይብቃችሁ። 8 በመቅደሴ ውስጥ ለራሳችሁ ሥርዓቴን ጠባቂዎች አደረጋችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም። 9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ልጆች መካከል ካሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ። 10 ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ እስራኤልም በሳቱ ጊዜ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ ዘንድ የሳቱ ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 11 ነገር ግን በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች ይሆናሉ፥ በቤቱም በሮች በረኞች ይሆናሉ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን ያርዳሉ፥ ያገለግሉአቸውም ዘንድ በፊታቸው ይቆማሉ። 12 በጣዖቶቻቸውም ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 ካህናትም ይሆኑኝ ዘንድ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደ ተቀደሰውም ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ነገር አይቀርቡም፤ እፍረታቸውንና የሠሩትንም ርኵሰታቸውን ይሸከማሉ። 14 ነገር ግን ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ። 15 ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙንም ወደ እኔ ያቀርቡ ዘንድ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 ወደ መቅደሴም ይገባሉ ያገለግሉኝም ዘንድ ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴንም ይጠብቃሉ። 17 ወደ ውስጠኛውም አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ ከበግ ጠጕር አንዳች ነገር በላያቸው አይሁን። 18 በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያወዛም ነገር አይታጠቁ። 19 ወደ ውጭውም አደባባይ ወደ ሕዝብ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላውን ልብስ ይልበሱ። 20 ራሳቸውንም አይላጩ የራሳቸውንም ጠጕር ይከርከሙ እንጂ ጠጕራቸውን አያሳድጉ። 21 ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ። 22 መበለቲቱንና የተፈታችይቱን አያግቡ፤ ከእስራኤል ቤት ዘር ግን ድንግሊቱን ወይም የካህን ሚስት የነበረችይቱን መበለት ያግቡ። 23 በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፥ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው። 24 ክርክርም በሆነ ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ እንደ ፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ። 25 እንዳይረክሱም ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላልተዳረች እኅት ይርከሱ። 26 ከነጻም በኋላ ሰባት ቀን ይቈጠርለት። 27 በመቅደስም ውስጥ ያገለግል ዘንድ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአትን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 28 ርስት ይሆንላቸዋል፤ እኔ ርስታቸው ነኝ፤ በእስራኤልም ዘንድ ግዛት አትሰጡአቸው፤ እኔ ግዛታቸው ነኝ። 29 የእህሉን ቍርባንና የኃጢአትን መሥዋዕት የበደልንም መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም ዘንድ እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል። 30 የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኵራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ። 31 የበከተውንና የተሰበረውን፥ ወፍ ወይም እንስሳ ቢሆን፥ ካህናት አይብሉት።

ሕዝቅኤል 45

1 ርስትም አድርጋችሁ ምድርን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድር የተቀደሰውን የዕጣ ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ በዳርቻው ሁሉ ዙሪያውን የተቀደሰ ይሆናል። 2 ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፤ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል። 3 ከዚያው ልክ ደግሞ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱም አሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል። 4 ከምድርም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፥ ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል። 5 ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን ይሆናል፥ ለሚቀመጡባቸውም ከተሞች ለራሳቸውም የርስት ይዞታ ይሆናል። 6 ለከተማይቱም ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ ርዝመቱም ሀያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል። 7 ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። 8 ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፥ አለቆቼም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም። 9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእስራኤል አለቆች ሆይ፥ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፥ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 እውነተኛ ሚዛን እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ እውነተኛውም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። 11 የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። 12 ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ይሁን፤ ሀያ ሰቅል፥ ሀያ አምስት ሰቅል፥ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ። 13 የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ ክፍል ትሰጣላችሁ። 14 የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን አሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፤ አሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና። 15 ውኃም ካለበት ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለቱ መቶ አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፤ ይህ ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ። 17 በየበዓላቱም በየመባቻውም በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የመጠጡንም ቍርባን መስጠት በአለቃው ላይ ይሆናል፤ እርሱ ለእስራኤል ቤት ያስተሰርይ ዘንድ የኃጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርባል። 18 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ መቅደሱንም አንጻ። 19 ካህኑም ከኃጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው። 20 ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፥ ይኸውም ስለ ሳተውና ስላላወቀው ሁሉ ነው። እንዲሁም ስለ ቤቱ አስተስርዩ። 21 በመጀመሪያ ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። 22 በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለአገሩ ሕዝብ ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ። 23 በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ሰባቱን ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። 24 ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ። 25 በሰባተኛውም ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ።

ሕዝቅኤል 46

1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በውስጠኛው አደባባይ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ሥራ በሚሠራበት በስድስቱ ቀን ተዘግቶ ይቈይ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በመባቻ ቀን ይከፈት። 2 አለቃውም በስተ ውጭ ባለው በር በደጀ ሰላሙ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፥ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ። 3 የአገሩም ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በእግዚአብሔር ፊት በሰንበታትና በመባቻ ይስገዱ። 4 አለቃውም በሰንበት ቀን ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶች ነውርም የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤ 5 የእህሉም ቍርባን ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፥ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባን እንደሚቻል ያህል ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። 6 በመባቻም ቀን ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ 7 ለወይፈኑም አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአውራውም በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለጠቦቶቹም እንደ ተቻለው ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህሉ ቍርባን ያቅርብ። 8 አለቃውም በሚገባበት ጊዜ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይግባ በዚያውም ይውጣ። 9 የአገሩ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ እግዚአብሔር ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የሚገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፥ በደቡብም በር የሚገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ይውጣ እንጂ በገባበቱ በር አይመለስ። 10 በሚገቡበት ጊዜ አለቃው በመካከላቸው ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ። 11 በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቍርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እንደሚቻለው ያህል፥ ለኢፍ መስፈሪያም አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል። 12 አለቃውም በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን የደኅንነቱን መሥዋዕት፥ ባቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፥ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ። 13 በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ በየማለዳው ያቅርበው። 14 ከእርሱም ጋር የእህልን ቍርባን፥ በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ እጅ መልካም ዱቄትን፥ በየማለዳው ያቅርብ፤ ይህ በዘላለሙ ሥርዓት ለእግዚአብሔር የዘወትር የእህል ቍርባን ይሁን። 15 እንዲሁ ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱንና የእህሉን ቍርባን ዘይቱንም በየማለዳው ያቅርብ። 16 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አለቃው ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ የርስት ይዞታ ይሆንላቸዋል። 17 ነገር ግን ከባሪያዎቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነጻነት ዓመት ድረሰ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለአለቃው ይመለስ፤ ርስቱ ግን ለልጆቹ ይሁን። 18 አለቃውም ሕዝቡን ከይዞታቸው ያወጣቸው ዘንድ ከርስታቸው በግድ አይውሰድ፤ ሕዝቤ ሁሉ ከይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆች ርስትን ይስጥ። 19 በበሩም አጠገብ ባለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደ ተቀደሰው ዕቃ ቤት አገባኝ፤ እነሆም፥ በኋላው በምዕራብ በኩል አንድ ስፍራ ነበረ። 20 እርሱም። ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳያወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፥ የእህሉንም ቍርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው አለኝ። 21 በውጭው አደባባይ አወጣኝ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆም፥ በአደባባዩ ማዕዘን ሁሉ አደባባይ ነበረ። 22 በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በማዕዘኑ ላሉ ለእነዚህ ለአራቱ ስፍራዎች አንድ ልክ ነበረ። 23 በአራቱም ዙሪያ ሁሉ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ። 24 እርሱም። እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው አለኝ።

ሕዝቅኤል 47

1 ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። 2 በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ፤ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር አዞረኝ፤ እነሆም፥ ውኃው በቀኙ ወገን ይፈስስ ነበር። 3 ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ። 4 ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ። 5 ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ። 6 እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ። 7 በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። 8 እርሱም እንዲህ አለኝ። ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል። 9 ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ የባሕሩም ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል። 10 አጥማጆችም በዚያ ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ ጀምሮ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ። 11 እረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም። 12 በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሆናል። 14 ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት ይህችም ምድር ርስት ትሆናችኋለች። 15 የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ፤ 16 ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን። 17 ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። የሰሜኑ ድንበር ይህ ነው። 18 የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ የምሥራቁ ድንበር ይህ ነው። 19 የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው። 20 የምዕራቡም ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው። 21 እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ለእናንተ ትካፈላላችሁ። 22 ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ። 23 መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 48

1 የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 2 ከዳንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 3 ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 4 ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 5 ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 6 ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 7 ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 8 ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የሆነ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። 9 ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል። 10 ለእነዚህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይሆናል። 11 የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። 12 ከምድርም መባ የተለየ መባ ይሆንላቸዋል፥ ከሁሉም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። 13 በካህናቱም ድንበር አንጻር ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፤ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል። 14 ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡምም፥ የምድሩም በኵራት አይፋለስም። 15 በሀያ አምስቱም ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ ለማስማርያም ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። 16 ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። 17 ለከተማይቱም ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። 18 በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ አሥር ሺህ ወደ ምዕራብም አሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል። 19 ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። 20 መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። 21 በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። 22 የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል። 23 ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 24 ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 25 ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 26 ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 27 ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 28 ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። 29 ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 30 የከተማይቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። 31 የከተማይቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፤ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር አንዱም የይሁዳ በር አንዱም የሌዊ በር፥ ሦስት በሮች ይሆናሉ። 32 በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር አንዱም የብንያም በር አንዱም የዳን በር ነው። 33 በደቡቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር አንዱም የይሳኮር በር አንዱም የዛብሎን በር ነው። 34 በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የጋድ በር አንዱም የአሴር በር አንዱም የንፍታሌም በር ነው። 35 ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም። እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።

ዳንኤል 1

1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። 2 ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ወደ ሰናዖር ምድር ወደ አምላኩ ቤት ወሰደው፥ ዕቃውንም ወደ አምላኩ ግምጃ ቤት አገባው። 34 ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም የሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ለጃንደረቦች አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ። 5 ንጉሡም ሦስት ዓመት ያሳድጉአቸው ዘንድ፥ ከዚያም በኋላ በንጉሡ ፊት ይቆሙ ዘንድ ከንጉሡ መብል ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጎአቸውን አዘዘላቸው። 6 በእነዚህም መካከል ከይሁዳ ልጆች ዳንኤልና አናንያ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። 7 የጃንደረቦቹም አለቃ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፥ አናንያንም ሲድራቅ፥ ሚሳኤልንም ሚሳቅ፥ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ ጠራቸው። 8 ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ፤ እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ። 9 እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። 10 የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን። መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ አለው። 11 ዳንኤልም የጃንደርቦቹ አለቃ በዳንኤልና በአናንያ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ የሾመውን ሜልዳርን። 12 እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ 13 ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት፤ እንዳየኸውም ሁሉ ከባሪያዎችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው። 14 ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው። 15 ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። 16 ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። 17 ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። 18 እነርሱም ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፥ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር ዘንድ አገባቸው። 19 ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፤ በንጉሡም ፊት ቆሙ። 20 ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው። 21 ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመት ተቀመጠ።

ዳንኤል 2

1 ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። 2 ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ። 3 ንጉሡም። ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኮአል አላቸው። 4 ከለዳውያኑም ንጉሡን በሶርያ ቋንቋ። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ ለባሪያዎችህ ሕልምህን ንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን ብለው ተናገሩት። 5 ንጉሡም መለሰ ከለዳውያኑንም። ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፤ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትቈረጣላችሁ ቤቶቻችሁም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ። 6 ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብታሳዩ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፤ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን አሳዩኝ አላቸው። 7 ሁለተኛም ጊዜ መልሰው። ንጉሡ ለባሪያዎቹ ሕልሙን ይንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳያለን አሉት። 8 ንጉሡ መልሶ። ነገሩ ከእኔ ዘንድ እንደ ራቀ ታውቃላችሁና ጊዜውን እንድታስረዝሙ እኔ አውቃለሁ። 9 ሕልሙንም ባታስታውቁኝ አንድ ፍርድ አለባችሁ፤ ጊዜውን ለማሳለፍ የሐሰትንና የተንኰልን ቃል ልትነግሩኝ አዘጋጅታችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ፍቺውንም ማሳየት እንድትችሉ አውቃለሁ አለ። 10 ከለዳውያኑም በንጉሡ ፊት መልሰው። የንጉሡን ነገር ያሳይ ዘንድ የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም፤ ከነገሥታትም ታላቅና ኃይለኛ የሆነ እንደዚህ ያለ ነገር የሕልም ተርጓሚንና አስማተኛን ከለዳዊንም አልጠየቀም። 11 ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፤ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ። 12 ስለዚህም ንጉሡ ተበሳጨ እጅግም ተቈጣ፥ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ። 13 ትእዛዝም ወጣ፥ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፤ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉ ዘንድ ፈለጉአቸው። 14 የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘበኞቹ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረው፤ 15 ለንጉሡም አለቃ ለአርዮክ መልሶ። የንጉሡ ትእዛዝ ስለ ምን ቸኰለ? አለው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል አስታወቀው። 16 ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ። 1718 የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው። 19 የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ። 20 ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ 21 ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል። 22 የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው። 23 ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፥ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፥ አንተ የአባቶቼ አምላክ ሆይ፥ የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ። 24 ከዚህም በኋላ ዳንኤል ንጉሡ የባቢሎንን ጠቢባን ያጠፋ ዘንድ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ገባ፤ በገባም ጊዜ። የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋ፤ ወደ ንጉሡ አስገባኝ፥ እኔም ፍቺውን ለንጉሡ አሳያለሁ አለው። 25 የዚያን ጊዜም አርዮክ ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባውና። ከይሁዳ ምርኮኞች ያለውን ለንጉሡ ፍቺውን የሚያስታውቀውን ሰው አግኝቼአለሁ አለው። 26 ንጉሡም መለሰ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን። ያየሁትን ሕልምና ፍቺውን ታስታውቀኝ ዘንድ ትችላለህን? አለው። 27 ዳንኤልም በንጉሡ ፊት መልሶ እንዲህ አለ። ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፤ 28 ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፥ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል። በአልጋህ ላይ የሆነው ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው። 29 አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል። 30 ነገር ግን ይህ ምሥጢር ለእኔ መገለጡ ፍቺው ለንጉሡ ይታወቅ ዘንድ፥ አንተም የልብህን አሳብ ታውቅ ዘንድ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም። 31 አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፤ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፤ መልኩም ግሩም ነበረ። 32 የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥ 33 ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ። 34 እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ። 35 የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ 36 ሕልሙ ይህ ነው፤ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን። 37 አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ። 38 በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል፤ አንተ የወርቁ ራስ ነህ። 39 ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል። 40 አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፤ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል። 41 እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል። 42 የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁ መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል። 43 ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፤ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም። 44 በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች። 45 ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፤ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው። 46 የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ። 47 ንጉሡም ዳንኤልን። ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው። 48 ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደርገው፥ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፥ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ ላይ ሾመው፥ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው። 49 ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፥ እርሱም ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ በር ነበረ።

ዳንኤል 3

1 ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። 2 ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ። 3 በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ። 4 አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥ 5 የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል። 6 ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል። 7 ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ። 8 በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ። 9 ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። 10 አንተ፥ ንጉሥ ሆይ። የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፤ 11 ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ። 12 በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም። 13 ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። 14 ናቡከደነፆርም። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? 15 አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። 16 ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም። ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም። 17 የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! 18 ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት። 19 የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ። 20 ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ። 21 የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። 22 የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው። 23 እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ። 24 የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። 25 እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። 26 የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ። እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። 27 መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ። 28 ናቡከደነፆርም መልሶ። መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። 29 እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ። 30 የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።

ዳንኤል 4

1 ከንጉሡ ከናቡከደነፆር በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ ሰላም ይብዛላችሁ። 2 ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ። 3 ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው። 4 እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። 5 ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ። 6 ስለዚህ የሕልሙን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ። 7 የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፤ ሕልሙንም በፊታቸው ተናገርሁ፥ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም። 8 በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት። 9 የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ። 10 የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ፤ እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ። 11 ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ። 12 ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር። 13 በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። 14 በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ። ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ። 15 ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን። 16 ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት። 17 ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው። 18 እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፤ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ። 19 የዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል አሰበ፥ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ። ብልጣሶር ሆይ፥ ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ አለው። ብልጣሶርም መልሶ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን። 20 ትልቅ የነበረው የበረታውም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥ 21 ቅጠሉም አምሮ የነበረው፥ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፤ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት ያየኸው ዛፍ፤ 22 ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፥ እስከ ሰማይም ደርሶአል፥ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው። 23 ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና። ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፈንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፤ ንጉሥ ሆይ፥ ፍቺው ይህ ነው፤ 24 በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤ 25 ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። 26 የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። 27 ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር። 28 ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ። 29 ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር። 30 ንጉሡም። ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ። 31 ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና። ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ። መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ 32 ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው። 33 በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። 34 ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። 35 በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም። ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም። 36 በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። 37 አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።

ዳንኤል 5

1 ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር። 2 ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ። አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ። 3 የዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁን ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው። 4 የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ። 5 በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፤ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ። 6 የዚያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠበት፥ አሳቡም አስቸገረው፥ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፥ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ። 7 ንጉሡም አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን ቃላተኞቹንም ያገቡ ዘንድ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን። ይህን ጽሕፈት ያነበበ ፍቺውንም ያሳየኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፥ የወርቅም ማርዳ በአንገቱ ዙርያ ይሆንለታል፥ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል ብሎ ተናገረ። 8 የዚያን ጊዜም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ያነብቡ፥ ፍቺውንም ለንጉሡ ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም። 9 ንጉሡም ብልጣሶር እጅግ ደነገጠ፥ ፊቱም ተለወጠበት፥ መኳንንቶቹም ተደናገጡ። 10 ንግሥቲቱም ስለ ንጉሡና ስለ መኳንንቱ ቃል ወደ ግብዣ ቤት ገባች፤ ንግሥቲቱም ተናገረች እንዲህም አለች። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ አሳብህ አያስቸግርህ፥ ፊትህም አይለወጥ። 11 የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው በመንግሥትህ ውስጥ አለ፤ በአባትህም ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብና ማስተዋል እውቀትም ተገኘበት፤ አባትህ ንጉሡ ናቡከደነፆር የሕልም ተርጓሚዎችና የአስማተኞች የከለዳውያንና የቃላተኞች አለቃ አደረገው። 12 መልካም መንፈስ፥ እውቀትም፥ ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም፥ እንቈቅልሽንም መግለጥ፥ የተቋጠረውንም መፍታት ንጉሡ ስሙን ብልጣሶር ብሎ በሰየመው በዳንኤል ዘንድ ተገኝቶአልና። አሁንም ዳንኤል ይጠራ፥ እርሱም ፍቺውን ያሳያል። 13 የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ንጉሡ ፊት ገባ፤ ንጉሡም ተናገረው ዳንኤልም እንዲህ አለው። ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ከማረካቸው ከይሁዳ ምርኮኞች የሆንህ ዳንኤል አንተ ነህን? 14 የአማልክት መንፈስ እንዳለብህ፥ እውቀትና ማስተዋልም መልካምም ጥበብ እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ። 15 አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ያስታውቁኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች ወደ እኔ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ያሳዩ ዘንድ አልቻሉም። 16 አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የተቋጠረንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፤ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ታስታውቀኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፥ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ ይሆንልሃል፥ አንተም በመንግሥት ላይ ሦስተኛ ገዥ ትሆናለህ። 17 የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ። ስጦታህ ለአንተ ይሁን፥ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ። 18 ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው። 19 ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር። 20 ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው። 21 ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። 22 ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም። 23 የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም። 24 ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። 25 የተጻፈውም ጽሕፈት። ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል። 26 የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው። 27 ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው። 28 ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው። 29 የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ። 30 በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። 31 ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ፤ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ።

ዳንኤል 6

1 ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሀያ መሳፍንት በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ። 2 መሳፍንቱም ሒሳቡን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም እንዳይጐዳ ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፤ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ። 3 ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፤ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ አሰበ። 4 የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም። 5 እነዚያም ሰዎች። ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ። 6 የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት። ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። 7 የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ። 8 አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ። 9 ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ። 10 ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። 11 እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። 12 ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ። ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው። 13 የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው። ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት። 14 ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ። 15 የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት። 16 የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው። 17 ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው። 18 ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፤ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ። 19 በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ። 20 ወደ ጕድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው። 21 ዳንኤልም ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። 22 በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው። 23 የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፤ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም። 24 ንጉሡም አዘዘ፥ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፥ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ። 25 የዚያን ጊዜም ንጉሥ ዳርዮስ በምድር ሁሉ ላይ ወደሚኖሩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ ወደሚናገሩ ሁሉ ጻፈ፥ እንዲህም አለ። ሰላም ይብዛላችሁ። 26 በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፥ ግዛቱም እስከ መጨረሻ ድረስ ይኖራል። 27 ያድናል ይታደግማል፥ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፥ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል። 28 ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ኑሮው ተቃናለት።

ዳንኤል 7

1 በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ ዋነኛውንም ነገር ተናገረ። 2 ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። በሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር። 3 አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች። 4 መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፥ የንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፥ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፥ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፥ የሰውም ልብ ተሰጣት። 5 እነሆም፥ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፥ በአንድ ወገንም ቆመች፥ ሦስትም የጐድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም። ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት። 6 ከዚህም በኋላ፥ እነሆ፥ ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት ሌላ አውሬ አየሁ፤ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፥ ግዛትም ተሰጣት። 7 ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት። 8 ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፤ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት። 9 ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። 10 የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። 11 የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፤ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። 12 ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ። 13 በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። 14 ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው። 15 በእኔም በዳንኤል በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ ደነገጠች፥ የራሴም ራእይ አስቸገረኝ። 16 በዚያም ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ ስለዚህ ሁሉ እውነቱን ጠየቅሁት፤ እርሱም ነገረኝ፥ የነገሩንም ፍቺ አስታወቀኝ። 17 እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው። 18 ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፥ እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ። 19 ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥ 20 በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ አሥር ቀንዶች፥ በኋላም ስለ ወጣው፥ በፊቱም ሦስቱ ስለ ወደቁ፥ ዓይኖችና ትዕቢት የተናገረ አፍ ስለ ነበሩት፥ መልኩም ከሌሎች ስለ በለጠ ስለ ሌላው ቀንድ እውነቱን ለማወቅ ፈቀድሁ። 21 እነሆም፥ ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ፥ 22 በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸውም። 23 እንዲህም አለ። አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል። 24 አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፥ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፥ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል። 25 በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ። 26 ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፥ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል። 27 መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል። 28 የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፥ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ።

ዳንኤል 8

1 በመጀመሪያ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ፥ ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፥ ለእኔ ለዳንኤል ራእይ ተገለጠልኝ። 2 በራእዩም አየሁ፤ ባየሁም ጊዜ በኤላም አውራጃ ባለው በሱሳ ግንብ ነበርሁ፤ በራእዩም አየሁ በኡባል ወንዝም አጠገብ ነበርሁ። 3 ዓይኔን አንሥቼ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግ በወንዙ ፊት ቆሞ ነበር፥ ሁለቱም ቀንዶቹ ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ አንዱ ግን ከሁለተኛው ከፍ ያለ ነበረ፥ ታላቁም ወደ ኋላው ወጥቶ ነበር። 4 አውራውም በግ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ፤ አራዊትም ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ አልቻሉም፥ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፤ እንደ ፈቃዱም አደረገ፥ ራሱንም ታላቅ አደረገ። 5 እኔም ስመለከት፥ እነሆ፥ ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፥ ምድርንም አልነካም፤ ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው። 6 ሁለትም ቀንድ ወዳለው በወንዝም ፊት ቆሞ ወዳየሁት አውራ በግ መጣ፥ በኃይሉም ቍጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ። 7 ወደ አውራውም በግ ሲቀርብ አየሁት፤ እርሱም ተመረረበት፥ አውራውንም በግ መታ፥ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው ኃይል አልነበረውም፥ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራውንም በግ ከእጁ ያድነው ዘንድ የሚችል አልነበረም። 8 አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፥ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ። 9 ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፥ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ። 10 እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም። 11 እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፤ ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፥ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ። 12 ሠራዊቱም ከኃጢአት የተነሣ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠው፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፥ አደረገም ተከናወነም። 13 ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ። ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፥ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኃጢአት የሆነው ራእይ እስከ መቼ ይሆናል? አለው። 14 እርሱም። እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ። 15 እኔም ዳንኤል ራእዩን ባየሁ ጊዜ ማስተዋሉን ፈለግሁ፤ እነሆም፥ የሰው ምስያ በፊቴ ቆሞ ነበር። 16 በኡባልም ወንዝ መካከል። ገብርኤል ሆይ፥ ራእዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮኸውን የሰውን ድምፅ ሰማሁ። 17 እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፤ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል አለኝ። 18 ሲናገረኝም ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም ዳሰሰኝ ቀጥ አድርጎም አቆመኝ። 19 እንዲህም አለኝ። እነሆ፥ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና። 20 ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። 21 አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። 22 እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፥ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፥ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም። 23 በመንግሥታቸውም መጨረሻ፥ ኃጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፥ እንቈቅልሽን የሚያስተውል ፊተ ጨካኝ ንጉሥ ይነሣል። 24 ኃይሉም ይበረታል፥ ነገር ግን በራሱ ኃይል አይደለም፤ በድንቅም ያጠፋል፥ ያደርግማል፥ ይከናወንማል፤ ኃያላንንና የቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል። 25 በመታለሉ ተንኰልን በእጁ ያከናውናል፤ በልቡም ይታበያል፥ ታምነውም የሚኖሩትን ብዙዎችን ያጠፋል፤ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቋቋማል፤ ያለ እጅም ይሰበራል። 26 የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ። 27 እኔም ዳንኤል ተኛሁ፥ አያሌም ቀን ታመምሁ፤ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ የንጉሡን ሥራ እሠራ ነበር፤ ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር፥ የሚያስተውለው ግን አልነበረም።

ዳንኤል 9

1 በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥ 2 በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ። 3 ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ። 4 ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥ ተናዝዤም እንዲህ አልሁ። ጌታ ሆይ፥ ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ፥ 5 ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤ 6 በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን ለአባቶቻችንም ለአገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም። 7 ጌታ ሆይ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት አገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው። 8 ጌታ ሆይ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። 910 በእርሱ ላይ ምንም እንኳ ያመፅን ብንሆን፥ በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን ባኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንኳ ባንሰማ፥ ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው። 11 እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፥ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን። 12 እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም። 13 በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኃጢአታችንም እንመለስ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም። 14 ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገሩን ጠብቆ በእኛ ላይ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፥ እኛም ቃሉን አልሰማንምና። 15 አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ዝና ለአንተ ያገኘህ ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፋትንም አድርገናል። 16 ጌታ ሆይ፥ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቍጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ። 17 አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። 18 አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት። 19 አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፥ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ። 20 እኔም ገና ስናገር ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን፥ 21 ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። 22 አስተማረኝም፥ ተናገረኝም እንዲህም አለ። ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። 23 አንተ እጅግ የተወደድህ ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ትእዛዝ ወጥቶአል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፥ ራእዩንም አስተውል። 24 ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። 25 ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። 26 ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። 27 እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።

ዳንኤል 10

1 በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፥ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፤ ነገሩንም አስተዋለ፥ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው። 2 በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። 3 ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። 4 ከመጀመሪያውም ወር በሀያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ሳለሁ፥ ዓይኔን አነሣሁ፥ 5 እነሆም፥ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ። 6 አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። 7 እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፥ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፤ ነገር ግን ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፥ ሊሸሸጉም ሸሹ። 8 እኔም ብቻዬን ቀረሁ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፥ ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። 9 የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ። 10 እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ። 11 እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። 12 እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። 13 የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት። 14 ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። 15 ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፥ ዲዳም ሆንሁ። 16 እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን። ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። 17 ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት። 18 ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፥ አበረታኝም። 19 እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፥ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፥ ጽና አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና። አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ። 20 እርሱም እንዲህ አለኝ። ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፥ እነሆ፤ የግሪክ አለቃ ይመጣል። 21 ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።

ዳንኤል 11

1 እኔም በሜዶናዊ በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር። 2 አሁንም እውነትን አሳይሃለሁ። እነሆ፥ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፤ በባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል። 3 ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፥ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፥ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል። 4 እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና። 5 የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም አንዱ ይበረታሉ፤ እርሱም ይበረታበታል ይሠለጥንማል፤ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል። 6 ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ፤ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፤ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፥ እርሱና ክንዱም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ። 7 ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፥ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፥ በላያቸውም ያደርጋል፥ ያሸንፍማል። 8 አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፤ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል። 9 ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል። 10 ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፤ እርሱም ይመጣል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል። 11 የደቡብም ንጉሥ ይቈጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፥ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል። 12 ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፥ ነገር ግን አያሸንፍም። 13 የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ያቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል። 14 በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ። 15 የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፥ አፈርንም ይደለድላል፥ የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፤ የደቡብም ሠራዊት የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም። 16 በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፥ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል። 17 ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፥ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፤ እርስዋም አትጸናም ለእርሱም አትሆንም። 18 ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፥ ብዙዎችንም ይወስዳል፤ አንድ አለቃ ግን ስድቡን ይሽራል፥ ስድቡንም በራሱ ላይ ይመልሳል። 19 ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፥ አይገኝምም። 20 የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል፤ ነገር ግን በቍጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል። 21 በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል። 22 የሚጐርፍም ሠራዊት ከፊቱ ይወሰዳል፥ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃ ይሰበራሉ። 23 ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ በተንኰል ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል። 24 በቀስታ ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን ይፈጥራል። 25 በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፤ ነገር ግን አሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም። 26 መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጐርፋል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ። 27 እነዚህም ሁለት ነገሥታት ክፋትን ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ያስባሉ፥ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ፍጻሜው እስከ ተወሰነው ጊዜ ነውና አይከናወንላቸውም። 28 ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰ ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል። 29 በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም። 30 የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል። 31 ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ። 32 ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም። 33 በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ። 34 በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ። 35 እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ። 36 ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፥ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፥ የተወሰነው ይደረጋልና። 37 የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም። 38 በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል። 39 በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፥ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፥ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል። 40 በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል። 41 ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፥ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ። 42 እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፥ የግብጽም ምድር አታመልጥም። 43 በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል። 44 ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል። 45 ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱስ ተራራ መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፥ ማንም አይረዳውም።

ዳንኤል 12

1 በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። 2 በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና። 3 ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። 4 ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል። 5 እኔም ዳንኤል አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፥ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፥ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር። 6 አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን። የዚህ ድንቅ ፍጻሜ እስከ መቼ ነው? አለው። 7 ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ። ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኵሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ። 8 ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም፤ የዚያን ጊዜም። ጌታዬ ሆይ፥ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድር ነው? አልሁ። 9 እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤ 10 ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ። 11 የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል። 12 የሚታገሥ፥ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው። 13 አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።

ሆሴዕ 1

1 በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እግዚአብሔር መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆሴዕን። ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፤ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው። 3 እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። 4 እግዚአብሔርም። ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ 5 በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ አለው። 6 ደግሞ ፀነሰች ሴት ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም። ይቅር እላቸው ዘንድ የእስራኤልን ቤት ከእንግዲህ ወዲህ አልምርምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤ 7 ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፤ በአምላካቸውም በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በሰልፍ ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም አለው። 8 ሎሩሃማም ጡት ባስጣለች ጊዜ፥ ደግሞ ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች። 9 እግዚአብሔርም። ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላክ አልሆናችሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው አለው።

ሆሴዕ 2

1 የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። 2 የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና። 3 ወንድሞቻችሁን። ዓሚ፥ እኅቶቻችሁንም። ሩሃማ በሉአቸው። 4 እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ግልሙትናዋን ከፊትዋ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ 5 ዕራቁትዋን እንዳልገፍፋት፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን እንዳላደርጋት፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር እንዳላደርጋት፥ በጥማትም እንዳልገድላት፤ 6 የግልሙትናዋ ልጆች ናቸውና ልጆችዋን አልምርም። 7 እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም። እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ ብላ አስነወረቻቸው። 8 ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። 9 ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም። ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች። 10 እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። 11 ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ፥ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። 12 አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። 13 ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ። 14 እርስዋም። ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። 15 እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 16 ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። 17 ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች። 18 በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 19 የበኣሊምን ስም ከአፍዋ አስወግደዋለሁና፥ በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና። 20 በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድሩ እሰብራለሁ፥ ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ። 21 ለዘላለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄ አጭሻለሁ። 22 ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። 23 በዚያንም ቀን እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ 24 ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ። 25 በምድርም ላይ ለእኔ እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን። አንተ ሕዝቤ ነህ እለዋለሁ፤ እርሱም። አንተ አምላኬ ነህ ይለኛል።

ሆሴዕ 3

1 እግዚአብሔርም። የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳ፥ እግዚአብሔር እንደሚወድዳቸው አንተም ውሽማዋን የምትወድደውን አመንዝራይትን ሴት ውደድ አለኝ። 2 እኔም በአሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስ ገዛኋት። 3 ከእኔ ጋር ብዙ ወራት ተቀመጪ፥ አታመንዝሪም፥ ለሌላ ሰውም አትሁኚ፤ እኔም እንዲሁ እሆንልሻለሁ አልኋት። 4 የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዓምድ፥ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፤ 5 ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።

ሆሴዕ 4

1 እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድሩ ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለውና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2 እርግማንና ሐሰት ግዳይና ስርቆት ምንዝርናም ወጥተዋል፤ ደምም ወደ ደም ደርሶአል። 3 ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፥ በእርስዋም የሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ጋር ይደክማሉ፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። 4 ነገር ግን ሕዝብህ ከካህን ጋር እንደሚከራከሩ ናቸውና ማንም አይከራከር፥ ማንም አይዝለፍ። 5 በቀንም ትሰናከላለህ፥ ነቢዩም ከአንተ ጋር በሌሊት ይሰናከላል፤ እናትህንም አጠፋታለሁ። 6 ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። 7 እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ። 8 የሕዝቤም ኃጢአት መብል ሆኖላቸዋል፥ ልባቸውንም ወደ በደላቸው አድርገዋል። 9 እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፥ ሥራቸውንም እመልስባቸዋለሁ። 10 እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፥ ሲያመነዝሩም አይበዙም። 11 ግልሙትናና የወይን ጠጅ ስካርም አእምሮን ያጠፋል። 12 የግልሙትና መንፈስ ሕዝቤን አስቶአቸዋልና፥ እነርሱም ከአምላካቸው ርቀው አመንዝረዋልና በትራቸውን ይጠይቃሉ፥ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። 13 በተራሮችም ራስ ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን ከአሆማም ዛፍ በታች በኮረብቶች ላይ ያጥናሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይገለሙታሉ፥ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። 14 ወንዶችም ደግሞ ከጋለሞቶች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በገለሞቱ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም ባመነዘሩ ጊዜ አልቀጣቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል። 15 እስራኤል ሆይ፥ አንተ ብታመነዝር ይሁዳ አይበድል፤ እናንተም ወደ ጌልገላ አትግቡ፥ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፥ ወይም። ሕያው እግዚአብሔርን! ብላችሁ አትማሉ። 16 እስራኤል እንደ እልከኛ ጊደር እንቢ ብሎአል፤ እግዚአብሔርስ በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋልን? 17 ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ተወው። 18 ስካርን ፈጽመዋል፥ ግልሙትናንም አብዝተዋል፤ አለቆችዋም ነውርን እጅግ ወደዱ። 19 ነፋስ በክንፍዋ አስሮአታል፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።

ሆሴዕ 5

1 ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። 2 ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ። 3 ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። 4 ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፤ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላውቁምና። 5 የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነሱ ጋር ይሰናከላል። 6 እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱም ተመልሶአልና አያገኙትም። 7 ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፤ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል። 8 በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና። ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ። 9 ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል። በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ። 10 የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ። 11 ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። 12 እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። 13 ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቊስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም። 14 እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም። 15 በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።

ሆሴዕ 6

1 ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። 2 ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። 3 እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል። 4 ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? 5 ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። 6 ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። 7 እነርሱ ግን እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ላይ ወንጅለውኛል። 8 ገለዓድ ኃጢአትን የሚሠሩ ሰዎች ከተማ፥ በደምም የተቀባ ነው። 9 ለሰውም እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ የካህናት ወገኖች በሴኬም መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ። 10 በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ በኤፍሬም ውስጥ ግልሙትና ተገኘ፥ እስራኤልም ረክሶአል። 11 ይሁዳ ሆይ፥ የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል።

ሆሴዕ 7

1 በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ። 2 እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች። 3 ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል። 4 ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል። 5 በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ። 6 እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል። 7 ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም። 8 ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። 9 እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። 10 የእስራኤልም ትዕቢቱ በፊቱ መሰከረ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። 11 ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። 12 ሲሄዱ አሽክላዬን አዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ። 13 ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐመፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ። 14 በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዐመፁ። 15 እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ። 16 ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።

ሆሴዕ 8

1 መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል። 2 እነርሱም። አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። 3 እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድዱታል። 4 ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው፤ ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። 5 ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፤ ጥሎአል፤ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም? 6 ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል። 7 ነፍስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፍስንም ያጭዳሉ፤ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል። 8 እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል። 9 ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ። 10 ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ። 11 ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል። 12 የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል። 13 መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፤ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። 14 እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች።

ሆሴዕ 9

1 እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል። 2 አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል። 3 በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ። 4 ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፤ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም። 5 በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? 6 እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። 7 የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፤ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። 8 ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ። 9 በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል። 10 እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በkWraት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ 11 የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። 12 ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! 13 እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፤ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። 14 አቤቱ፥ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። 15 ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። 16 ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። 17 አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።

ሆሴዕ 10

1 እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። 2 ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። 3 አሁንም። ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ። 4 የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል። 5 የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ። 6 ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። 7 ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች። 8 የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም። ውደቁብን ይሉአቸዋል። 9 እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን? 10 በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል። 11 ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል። 12 እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። 13 ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። 14 በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፤ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ። 15 ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፤ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።

ሆሴዕ 11

1 እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። 2 አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠዉ ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። 3 እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። 4 በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው። 5 ወደ እኔ ይመለሱ ዘንድ አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። 6 ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ በከተሞቻቸው ላይ ይወድቃል፥ ከበርቴዎችንም ያጠፋል። 7 ሕዝቤም ከእኔ ይመለሱ ዘንድ ወደዱ፤ ወደ ላይም ቢጠሩአቸው ማንም ከፍ ከፍ ያደርጋቸው ዘንድ አይችልም። 8 ኤፍሬም ሆይ፥ እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ፥ እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አዳማ እጥልሃለሁ? እንዴትስ እንደ ሲባዮ አደርግሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። 9 እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም አጠፋ ዘንድ አልመለስም፤ በመዓትም አልመጣም። 10 እግዚአብሔርን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ ባገሣም ጊዜ ልጆች እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። 11 እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ሆሴዕ 12

1 ኤፍሬም በሐሰት፥ የእስራኤልም ቤት በተንኰል ከበበኝ፤ ይሁዳም ከታመነው ቅዱሱ ከእግዚአብሔር ጋር አይጸናም። 2 ኤፍሬም ነፋስን ይበላል፥ የምሥራቅንም ነፋስ ይከተላል፤ ሁልጊዜም ሐሰትንና ተንኰልን ያበዛል፤ ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፥ ወደ ግብጽም ዘይት ይወስዳሉ። 3 እግዚአብሔርም ደግሞ ከይሁዳ ጋር ክርክር አለው፥ ያዕቆብንም እንደ መንገዱ ይቀጣል፤ እንደ ሥራውም ይመልስለታል። 4 በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤ 5 ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ። 6 እርሱም የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የመታሰቢያው ስም እግዚአብሔር ነው። 7 ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን። 8 ከከነዓን ወገን ነው፤ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል። 9 ኤፍሬምም። ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም አለ። 10 እኔም ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደ ገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ። 11 ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን አውጥቻለሁ። 12 ኃጢአት በገለዓድ አለ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፤ ወይፈኖች በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ። 13 ያዕቆብ ወደ ሶርያ አገር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም ጠባቂ ነበረ። 14 እግዚአብሔርም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢይም እጅ ጠበቀው። 15 ኤፍሬም አስመርሮ አስቈጣው፤ ስለዚህ ደሙ በላዩ ላይ ነው፤ ጌታውም ስድቡን በራሱ ላይ ይመልሳል።

ሆሴዕ 13

1 ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ። 2 አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም። የሚሠዉ ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ ይላሉ። 3 ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ። 4 እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም። 5 በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር። 6 ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ። 7 ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤ 8 ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል። 9 እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው። 10 በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም። ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ? 11 በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት። 12 የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል። 13 ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው። 14 ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች። 15 በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፤ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል። 16 ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ።

ሆሴዕ 14

1 እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ። 2 ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሳችሁ። ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በወይፈንም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን። 3 አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ። አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም በሉት። 4 ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ። 5 ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል። 6 ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል። 7 ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል። 8 ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል። 9 ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።

ኢዮኤል 1

1 ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን? 3 ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ። 4 ከተሞች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው። 5 በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ። 6 ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው። 7 ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፤ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ። 8 ለቍንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ። 9 የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ። 10 እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች። 11 መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ። 12 ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፤ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል። 13 የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፥ ዋይ በሉ፤ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ። 14 ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። 15 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል። 16 ከዓይናችን ፊት ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋ አይደለምን? 17 ዘሩ በምድር ውስጥ በሰበሰ፤ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል። 18 እንስሶች እጅግ ጮኹ፤ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተጠራጠሩ፤ የበግም መንጎች ጠፍተዋል። 19 አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ። 20 ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኩ።

ኢዮኤል 2

1 የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፥ እርሱም ቀርቦአልና በጽዮን መለከትን ንፉ፥ በቅዱሱም ተራራዬ ላይ እሪ በሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና፤ 2 የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤ ታላቅና ብርቱ ሕዝብ በተራሮች ላይ እንደ ወገግታ ተዘርግቶአል፤ ከዘላለምም ጀምሮ እንደ እነርሱ ያለ አልነበረም፥ ከእነርሱም በኋላ እስከ ብዙ ትውልድ ድረስ እንደ እነርሱ ያለ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። 3 እሳት በፊታቸው ትባላለች፥ በኋላቸውም ነበልባል ታቃጥላለች፤ ምድሪቱ በፊታቸው እንደ ዔድን ገነት፥ በኋላቸውም የምድረ በዳ በረሃ ናት፤ ከእነርሱም የሚያመልጥ የለም። 4 መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፥ እንደ ፈረሶችም ይሮጣሉ። 5 በተራራ ላይ እንዳሉ ሰረገሎች ድምፅ፥ ገለባውንም እንደሚበላ እንደ እሳት ነበልባል ድምፅ፥ ለሰልፍም እንደ ተዘጋጀ እንደ ብርቱ ሕዝብ ያኰበኵባሉ። 6 ከፊታቸው አሕዛብ ይንቀጠቀጣሉ፤ የሰውም ፊት ሁሉ ይጠቍራል። 7 እንደ ኃያላን ይሮጣሉ፥ እንደ ሰልፈኞችም በቅጥሩ ላይ ይወጣሉ፤ እያንዳንዱም በመንገዱ ላይ ይራመዳል፥ ከእርምጃቸውም አያፈገፍጉም። 8 አንዱ ካንዱ ጋር አይጋፉም፥ እያንዳንዱም መንገዱን ይጠበጥባል፤ በሰልፍ መካከል ያልፋሉ፥ እነርሱም አይቈስሉም። 9 በከተማም ያኰበkWbaሉ፥ በቅጥሩም ላይ ይሮጣሉ፤ ወደ ቤቶችም ይወጣሉ፥ እንደ ሌባም በመስኮቶች ይገባሉ። 10 ምድሪቱም ከፊታቸው ትናወጣለች፥ ሰማያትም ይንቀጠቀጣሉ፤ ፀሐይና ጨረቃም ይጨልማሉ፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ይሰውራሉ። 11 እግዚአብሔርም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ይሰጣል፤ ሰፈሩ እጅግ ብዙ ነውና፥ ቃሉንም የሚያደርግ እርሱ ኃያል ነውና፤ የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል? 12 አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። 13 ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ KWTaው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። 14 የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ KWrባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 15 በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ 16 ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። 17 የእግዚአብሔርም አገልጋዬች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ። አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤ ከአሕዛብ መካከል። አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ። 18 እግዚአብሔርም ስለ ምድሩ ቀና፥ ለሕዝቡም ራራለት። 19 እግዚአብሔርም መልሶ ሕዝቡን። እነሆ፥ እህልንና ወይንን ዘይትንም እሰድድላችኋለሁ፥ እናንተም በእርሱ ትጠግባላችሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ በአሕዛብ መካከል መሰደቢያ አላደርጋችሁም። 20 የሰሜንንም ሠራዊት ከእናንተ ዘንድ አርቃለሁ፥ ወደ በረሃና ወደ ምድረበዳ፥ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር አድርጌ አሳድደዋለሁ፤ እርሱም ትዕቢትን አድርጎአልና ግማቱ ይወጣል፥ ክርፋቱም ይነሣል አለ። 21 ምድር ሆይ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአልና አትፍሪ፥ ደስም ይበልሽ፥ እልልም በዪ። 22 እናንተ የምድር እንስሶች ሆይ፥ የምድር በዳው ማሰማርያ ለምልሞአልና፥ ዛፉም ፍሬውን አፍርቶአልና፥ በለሱና ወይኑም ኃይላቸውን ሰጥተዋልና አትፍሩ። 23 እናንተ የጽዮን ልጆች፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር የፊተኛውን ዝናብ በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፥ እንደ ቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ፥ ለእርሱም እልል በሉ። 24 አውድማዎችም እህልን ይሞላሉ፥ መጥመቂያዎችም የወይን ጠጅንና ዘይትን አትረፍርፈው ያፈስሳሉ። 25 የሰደድሁባችሁ ታላቁ ሠራዊቴ አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ። 26 ብዙ መብል ትበላላችሁ፥ ትጠግቡማላችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተአምራትን የሠራውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም። 27 እኔም በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፥ እኔም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤ ሕዝቤም ለዘላለም አያፍርም። 28 ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፥ ጐበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ 29 ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ 30 በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፥ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። 31 ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። 32 እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፥ የምስራች የሚሰበከላቸው ይገኛሉ።

ኢዮኤል 3

1 እነሆም፥ በዚህ ወራትና በዚህ ዘመን፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ፥ 2 አሕዛብን ሁሉ ሰብስቤ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ በዚያም ስለ ሕዝቤና ስለ ርስቴ ስለ እስራኤል በአሕዛብ መካከል የበተኑአቸውን ምድሬንም የተካፈሉአትን እፋረድባቸዋለሁ። 3 በሕዝቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ወንድ ልጅን ለጋለሞታ ዋጋ ሰጡ፥ ሴት ልጅን ለወይን ጠጅ ሸጡ፥ ጠጡም። 4 ጢሮስና ሲዶና የፍልስጥኤምም ግዛት ሁሉ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ብድራትን ብትመልሱልኝ ፈጥኜ በችኰላ ብድራታችሁን በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። 5 ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋልና፥ የተወደደውንም መልካሙን ዕቃዬን ወደ መቅደሳችሁ አግብታችኋልና፥ 6 ከዳርቻቸውም ታርቁአቸው ዘንድ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ለግሪክ ሰዎች ሸጣችኋልና፥ 7 እነሆ፥ እነርሱን ከሸጣችሁበት ስፍራ አስነሣቸዋለሁ፥ ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ። 8 እግዚአብሔር ተናግሮአልና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን በይሁዳ ልጆች እጅ እሸጣለሁ፥ እነርሱም ለሩቆቹ ሕዝብ ለሳባ ሰዎች ይሸጡአችኋል። 9 ይህን በአሕዛብ መካከል አውጁ ለሰልፍ ተዘጋጁ ኃያላንን አስነሡ ሰልፈኞች ሁሉ ይቅረቡ ይውጡም። 10 ማረሻችሁን ሰይፍ፥ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ፤ ደካማውም። እኔ ብርቱ ነኛ ይበል። 11 እናንተ በዙሪያ ያላችሁ አሕዛብ ሁሉ፥ ቸkWlaችሁ ኑ፥ ተሰብሰቡ፤ አቤቱ፥ ኃያላኖችህን ወደዚያ አውርድ። 12 አሕዛብ ይነሡ፥ ወደ ኢዮሣፍጥ ሸለቆም ይውጡ፤ በዙሪያ ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ እፈርድ ዘንድ በዚያ እቀመጣለሁና። 13 መከሩ ደርሶአልና ማጭድ ስደዱ መጥመቂያውም ሞልቶአልና ኑ እርገጡ፤ ክፉታቸውም በዝቶአልና መጥመቂያ ሁሉ ፈርሶአል። 14 የእግዚአብሔር ቀን በፍርድ ሸለቆ ቀርቦአልና የብዙ ብዙ ሕዝብ ውካታ በፍርድ ሸለቆ አለ። 15 ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፥ ከዋክብትም ብርሃናቸውን ሰውረዋል። 16 እግዚአብሔርም በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፥ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል። 17 እኔም በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ የዚያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም። 18 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፥ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፥ የሰጢምንም ሸለቆ ታጠጣለች። 19 በአገራቸው ንጹሑን ደም አፍስሰዋልና በይሁዳ ልጆች ላይ ስላደረጉት ግፍ ግብጽ ምድረ በዳ፥ ኤዶምያስም በረሃ ይሆናል። 20 ነገር ግን ይሁዳ ለዘላለም፥ ኢየሩሳሌምም ለልጅ ልጅ መኖሪያ ይሆናል። 21 እኔም ንጹሕ ያላደረግሁትን ደማቸውን ንጹሕ አደርገዋለሁ፥ እግዚአብሔርም በጽዮን ያድራል።

አሞጽ 1

1 በቴቁሔ ከላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ቃል ይህ ነው። 2 እንዲህም አለ። እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 4 በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። 5 የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር። 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 7 በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። 8 ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 10 በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄንም ሁሉ ጥሎአልና፥ ቍጣውም ሁልጊዜ ቀድዶአልና፥ መዓቱንም ለዘላለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 12 በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የባሶራንም አዳራሾች ትበላለች። 13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን እርጕዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 14 በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በሰልፍም ቀን በጩኸት በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት አዳራሾችዋን ትበላለች፤ 15 ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር።

አሞጽ 2

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 2 በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የቂርዮትንም አዳራሾች ትበላለች፤ ሞዓብም በውካታና በጩኸት በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤ 3 ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፥ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ሐሰታቸው አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 5 በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች። 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጻድቁን ስለ ብር፥ ችጋረኛውንም ስለ አንድ ጥንድ ጫማ ሽጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 7 የድሆችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፥ የትሑታንንም መንገድ ያጣምማሉ፤ ቅዱሱንም ስሜን ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ 8 በመሠዊያውም ሁሉ አጠገብ ለመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ ይተኛሉ፤ በአምላካቸውም ቤት ውስጥ በካሣ የተወሰደውን ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። 9 እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ኮምበል ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። 10 የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፥ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። 11 ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ናዝራውያንን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህ እንደዚህ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር። 12 እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም። ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ አዘዛችኋቸው። 13 እነሆ፥ ነዶ የተሞላች ሰረገላ እንደምትደቀድቅ እንዲሁ እደቀድቃችኋለሁ። 14 ከርዋጪም ሽሽት ይጠፋል፥ ብርቱውም በብርታቱ አይበረታም፥ ኃያሉም ነፍሱን አያድንም፤ 15 ቀስተኛውም አይቆምም፥ ፈጣኑም አይድንም፥ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ 16 በኃያላኑም መካከል ልበ ሙሉው በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል፥ ይላል እግዚአብሔር።

አሞጽ 3

1 የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ 2 እንዲህም ብሎአል። እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ። 3 በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን? 4 ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ ይጮኻልን? 5 ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን? 6 ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ክፉ ነገር በከተማ ላይ የመጣ እንደ ሆነ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን? 7 በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። 8 አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው? 9 በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና። በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ። 10 ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 11 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድሪቱ ዙሪያ ጠላት ይመጣል፤ ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፥ አዳራሾችሽም ይበዘበዛሉ። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአልጋ ማዕዘን፥ በደማስቆም በምንጣፍ ላይ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ። 13 ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። 14 እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። 15 የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቆችም ቤቶች ይፈርሳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

አሞጽ 4

1 በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችጋረኞችንም የምታሰጨንቁ፥ ጌቶቻቸውንም። አምጡ እንጠጣ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ። 2 ጌታ እግዚአብሔር። እናንተን በሰልፍ ዕቃ፥ ቅሬታችሁንም በመቃጥን የሚወስዱበት ቀን፥ እነሆ፥ በላያችሁ ይመጣል ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል። 3 እያንዳንዳችሁ በየፊታችሁ በተነደለ ስፍራ ትወጣላችሁ፤ በሬማንም ትጣላላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ይህን ወድዳችኋልና ወደ ቤቴል ኑና ኃጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላ ኑና ኃጢአትን አብዙ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን አሥራታችሁን አቅርቡ፤ 5 እርሾ ካለበትም የምስጋናውን መሥዋዕት አቅርቡ፥ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6 በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥራት፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣት ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፥ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፥ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ። 8 የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ወኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፥ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 በዋግና በአረማሞ መታኋችሁ፤ የአታክልቶቻችሁንም ብዛት ወይኖቻችሁንም በለሶቻችሁንም ወይራዎቻችሁንም ተምች በልቶአል፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 10 በግብጽ እንደ ነበረው ቸነፈርን ሰደድሁባችሁ፤ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፥ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ የሰፈራችሁንም ግማት ወደ አፍንጫችሁ አወጣሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 11 ሰዶምንና ገሞራን እግዚአብሔር እንደ ገለበጣቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፥ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 12 ስለዚህ፥ እስራኤል ሆይ፥ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ፥ እንደዚህ ስለማደርግብህ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ። 13 እነሆ፥ ተራሮችን የሠራ፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም አሳብ ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።

አሞጽ 5

1 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ። 2 የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፥ የሚያስነሣትም የለም። 3 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና። ሺህ ከሚወጣባት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት አሥር ይቀርላታል። 4 እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና። እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ 5 ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ። 6 በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ። 7 ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ፥ 8 ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልመውን፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸውን፥ 9 አምባውም እንዲፈርስ በብርቱ ላይ የድንገት ጥፋት የሚያመጣውን ፈልጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው። 10 በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ። 11 ድሀውንም ደብድባችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም። 12 ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ፥ በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና። 13 ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል። 14 በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል። 15 ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል። 16 ስለዚህ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ወዮ ወዮ ይባላል፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ። 17 በመካከልህ አልፋለሁና በወይኑ ቦታ ሁሉ ልቅሶ ይሆናል፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም። 19 ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው። 20 የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን? 21 ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም። 22 የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም። 23 የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም። 24 ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ። 25 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኛልን? 26 ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋን ኮከብ አነሣችሁ። 27 ስለዚህ ከደማስቆ ወደዚያ አስማርካችኋለሁ፥ ይላል ስሙ የሠራዊት አምላክ የተባለ እግዚአብሔር።

አሞጽ 6

1 በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተዘልለው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! 2 ወደ ካልኔ አልፋችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? 3 ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፥ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፥ 4 ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ 5 በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ 6 በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ! 7 ስለዚህ በምርኮ መጀመሪያ ይማረካሉ፥ ተደላድለው ከተቀመጡትም ዘንድ ዘፈን ይርቃል። 8 ጌታ እግዚአብሔር። የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖሩባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር። 9 እንዲህም ይሆናል፤ አሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። 10 አጥንቱንም ከቤቱ ያወጡ ዘንድ የሰው ዘመድና አቃጣዩ ባነሡት ጊዜ፥ በቤቱም ውስጥ ያለውን። እስከ አሁን ድረስ ገና ሰው በአንተ ዘንድ አለን? ባለው ጊዜ፥ እርሱም። ማንም የለም ባለ ጊዜ፤ ያን ጊዜ። የእግዚአብሔርን ስም እንጠራ ዘንድ አይገባንምና ዝም በል ይለዋል። 11 እነሆም፥ እግዚአብሔር ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። 1213 ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የለወጣችሁ፥ በከንቱም ነገር ደስ የሚላችሁ። በኃይላችን ቀንድ የወሰድን አይደለምን? የምትሉ፥ እናንተ ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን? 14 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ ሕዝብን አስነሣባችኋለሁ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፤ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።

አሞጽ 7

1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ። 2 የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። 3 እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። 5 እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። 6 እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 7 እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። 8 እግዚአብሔርም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም። እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፤ 9 የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ። 1011 የቤቴልም ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም ልኮ። አሞጽ። ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም ከአገሩ ተማርኮ ይሄዳል ብሎአልና አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል ዐምፆብሃል፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም አለ። 12 አሜስያስም አሞጽን። ባለ ራእዩ ሆይ፥ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፥ በዚያም እንጀራን ብላ፥ 13 በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር አለው። 14 አሞጽም መልሶ አሜስያስን አለው። እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ 15 እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። 16 አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ። በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፤ 17 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።

አሞጽ 8

1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ እነሆም፥ የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ። 2 እርሱም። አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ። ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም። 3 የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የሰዎችም ሬሳ ይበዛል፥ በስፍራውም ሁሉ በዝምታ ይጣላል። 4 ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ። 5 እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ 6 ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ። 7 እግዚአብሔር በያዕቆብ ክብር እንዲህ ብሎ ምሎአል። ሥራቸውን ሁሉ ለዘላለም ምንም አልረሳም። 8 በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ሙላዋም እንደ ወንዙ ትነሣለች፤ እንደ ግብጽም ወንዝ ትነሣለች ደግሞም ትወርዳለች። 9 በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለሁ። 10 ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬአችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ፥ ራስ መንጨትንም በሁሉ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ አንድያ ልጅም ልቅሶ፥ ፍጻሜውንም እንደ መራራ ቀን አደርገዋለሁ። 11 እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። 12 ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም። 13 በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ። 14 በሰማርያ ኃጢአት የሚምሉና። ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን! ደግሞ። ሕያው የቤርሳቤህን መንገድ! ብለው የሚሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።

አሞጽ 9

1 ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ። መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። 2 ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ 3 በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ 4 በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም። 5 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞ እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። 6 አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። 7 የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? 8 እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንዲነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። 10 ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። 11 በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ 12 ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። 13 እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። 14 የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። 15 በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር

አብድዩ 1

1 የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምተናል፤ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ። ተነሡ፥ በላይዋም በሰልፍ እንነሣ ብሎአል። 2 እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፤ አንተ እጅግ ተንቀሃል። 3 በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም። ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል። 4 እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 5 ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን? 6 አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተመረመረ! የተሸሸገበት ነገር ምንኛ ተፈለገ! 7 የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፤ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፤ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። 8 በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል እግዚአብሔር። 9 ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በመገደል ይጠፉ ዘንድ ኃያላንህ ይደነግጣሉ። 10 በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፥ ለዘላለምም ትጠፋለህ። 11 በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ። 12 ነገር ግን በመከራው ቀን ወንድምህን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ አይገባህም ነበር። 13 በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ አይገባህም ነበር። 14 የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ትቆም ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ትሰጥ ዘንድ አይገባህም ነበር። 15 የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፤ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። 16 በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤ አዎን ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ። 17 ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይሆናሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ። 18 እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፤ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ የለውም። 19 የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቈላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፤ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል። 20 ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፤ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። 21 በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፤ መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይሆናል።

ዮናስ 1

1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ ። 2 ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ። 3 ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ። 4 እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፥ በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። 5 መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛው ክፍል ወርዶ ነበር፥ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር። 6 የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ አለው። 7 እርስ በእርሳቸውም። ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ፥ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፥ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ። 8 የዚያን ጊዜም። ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት። 9 እርሱም። እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ በሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን እመልካለሁ አላቸው። 10 እነዚያም ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊት እንደ ኰበለለ እርሱ ስለ ነገራቸው አውቀዋልና እጅግ ፈርተው። ይህ ያደረግኸው ምንድር ነው? አሉት። 11 ባሕሩንም ሞገዱ አጥብቆ ያናውጠው ነበርና። ባሕሩ ከእኛ ዘንድ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ? አሉት። 12 እርሱም። ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል አላቸው። 13 ሰዎቹ ግን ወደ ምድሩ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ፤ ዳሩ ግን ባሕሩ እጅግ አብዝቶ ይናወጥባቸው ነበርና አልቻሉም። 14 ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው። አቤቱ፥ እንደ ወደድህ አድርገሃልና እንለምንሃለን፤ አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን አሉ። 15 ዮናስንም ወስደው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጡ ጸጥ አለ። 16 ሰዎችም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፥ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን አቀረቡ፥ ስእለትንም ተሳሉ።

ዮናስ 2

1 እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ። 2 ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ። 3 በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ። 4 ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ። 5 እኔም። ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ። 6 ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር። 7 ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ። 8 ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች። 9 ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል። 10 እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። 11 እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው።

ዮናስ 3

1 የእግዚአብሔርም ቃል ሁለተኛ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ። 2 ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው። 3 ዮናስም ተነሥቶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌም የሦስት ቀን መንገድ ያህል እጅግ ታላቅ ከተማ ነበረች። 4 ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም። በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ። 5 የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። 6 ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። 7 አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ። ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ 8 ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። 9 እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 10 እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።

ዮናስ 4

1 ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፥ እርሱም ተቈጣ። 2 ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና። አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር። 3 አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው። 4 እግዚአብሔርም። በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለ። 5 ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፤ ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ። 6 እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው። 7 በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት። 8 ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ። 9 እግዚአብሔርም ዮናስን። በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም። እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል አለ። 10 እግዚአብሔርም። አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል። 11 እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው።

ሚክያስ 1

1 በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታምና በአካዝ በሕዝቅያስም ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው፥ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው፥ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 እናንተ አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፥ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፥ ይመስክርባችሁ። 3 እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፥ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል። 4 ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፥ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ፥ በበታቹ ይቀልጣሉ፥ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ። 5 ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? 6 ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ። 7 የተቀረጹትም ምስሎችዋ ይደቅቃሉ፥ በግልሙትና ያገኘችው ዋጋ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፥ ጣዖታትዋንም ሁሉ አጠፋለሁ፤ በግልሙትና ዋጋ ሰበሰበቻቸው፥ ወደ ግልሙትናም ዋጋ ይመለሳሉና። 8 ስለዚህ ነገር ዋይ ብላ ታለቅሳለች፥ ባዶ እግርዋንና ዕራቁትዋን ሆና ትሄዳለች፤ እንደ ቀበሮ ታለቅሳለች፥ እንደ ሰጐንም ዋይ ትላለች፤ 9 ቍስልዋ የማይፈወስ ነውና፤ እስከ ይሁዳም ደርሶአልና፥ ወደ ሕዝቤም በር ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦአልና። 10 በጌት ላይ አታውሩ፤ በአኮ ላይ እንባን አታድርጉ፤ በቤትዓፍራ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ። 11 በሻፊር የምትቀመጪ ሆይ፥ በዕራቁትነትሽና በእፍረት እለፊ፤ በጸዓናን የምትቀመጠው አልወጣችም፤ የቤትኤጼል ልቅሶ ከእናንተ ዘንድ መኖሪያውን ይወስዳል። 12 ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እስከ ኢየሩሳሌም በር ድረስ ወርዶአልና በማሮት የምትቀመጠው በጎነትን ትጠባበቃለች። 13 በለኪሶ የምትቀመጪ ሆይ፥ ሰረገላውን ለፈረስ እሰሪ፤ እርስዋ ለጽዮን ሴት ልጅ የኃጢአት መጀመሪያ ነበረች፤ የእስራኤል በደል በአንቺ ዘንድ ተገኝቶአልና። 14 ስለዚህ ትሎት ለሞሬሼትጌት ትሰጪአለሽ፤ የአክዚብ ቤቶች ለእስራኤል ነገሥታት አታላይ ይሆናሉ። 15 በመሪሳ የምትቀመጪ ሆይ፥ ወራሽ አመጣብሻለሁ፤ የእስራኤል ክብር ወደ ዓዶላም ይመጣል። 16 ተማርከው ከአንቺ ዘንድ ወጥተዋልና ስለ ተድላሽ ልጆች ራስሽን ንጪ፥ ጠጕርሽንም ተቈረጪ፤ ቡሃነትሽንም እንደ ንስር አስፊ።

ሚክያስ 2

1 በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል። 2 በእርሻው ላይ ይመኛሉ፥ በግዴታም ይይዙታል፤ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፥ ይወስዱአቸውማል፤ ሰውንና ቤቱን፥ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ። 3 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በዚህ ወገን ላይ በክፉ አስባለሁ፥ ከዚያም አንገታችሁን አታነሡም፤ ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም። 4 በዚያ ቀን በምሳሌ ይመስሉባችኋል፥ በጽኑ ልቅሶም ያለቅሱላችኋል፤ እነርሱም። ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን እድል ፈንታ ይሰፍራል፥ እርሱንም የሚከለክል የለም፤ እርሻችንን ለዓመፀኞች ይከፍላል ይላሉ። 5 ስለዚህ በእግዚአብሔር ጉባኤ መካከል በዕጣ ገመድ የሚጥል አይኖርህም። 6 ትንቢት አትናገሩ ብለው ይናገራሉ፤ በእነዚህ ላይ ትንቢት አይናገሩም፥ ስድብም አይርቅም። 7 የያዕቆብ ቤት የተባልህ ሆይ፥ በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ የማይታገሥ ነውን? ወይስ ሥራው እንደዚች ናትን? ቃሌስ በቅን ለሚሄድ በጎነት አያደርግምን? 8 ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቤ እንደ ጠላት ሆኖ ተነሥቶአል፤ ቀሚስንና መጐናጸፊያን ገፈፋችሁ፤ ሳይፈሩም፤ የሚያልፉትን ከሰልፍ እንደሚመለሱ አደረጋችኋቸው። 9 የሕዝቤንም ሴቶች ከተሸለሙ ቤቶቻቸው አሳደዳችኋቸው፤ ከሕፃናቶቻቸውም ክብሬን ለዘላለም ወሰዳችሁ። 10 በዚህ ዕረፍት የላችሁምና ተነሥታችሁ ሂዱ፤ በርኵሰት ምክንያት ክፉ ጥፋት ታጠፋችኋለች። 11 ነፋስንም ተከትሎ። ስለ ወይን ጠጅና ስለ ስካር ትንቢት እናገርልሃለሁ ብሎ ሐሰትን የሚናገር ሰው ቢኖር እርሱ ለዚህ ሕዝብ ነቢይ ይሆናል። 12 ያዕቆብ ሆይ፥ ሁለንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፤ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ። 13 ሰባሪው በፊታቸው ወጥቶአል፤ እነርሱም ሰብረው ወደ በሩ አልፈዋል፥ በእርሱም በኩል ወጥተዋል፤ ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፥ እግዚአብሔርም በራሳቸው ላይ ነው።

ሚክያስ 3

1 እንዲህም አልሁ። የያዕቆብ አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ስሙኝ፤ ፍርድን ታውቁ ዘንድ አይገባችሁምን? 2 መልካሙን ጠልታችኋል፥ ክፉውንም ወድዳችኋል፤ ቁርበታቸውን ገፍፋችኋቸዋል፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያይታችኋል፤ 3 የሕዝቤን ሥጋ በልታችኋል፥ ቁርበታቸውንም ገፍፋችኋቸዋል፥ አጥንታቸውንም ሰብራችኋል፤ ለአፍላል እንደሚሆን ሥጋ ለድስትም እንደሚሆን ሙዳ ቈራረጣችኋቸው። 4 የዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፥ እርሱም አይሰማቸውም፤ ሥራቸውንም ክፉ አድርገዋልና በዚያን ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል። 5 እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚያስቱ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ በጥርሳቸው ሲነክሱ በሰላም ይሰብካሉ፤ በአፋቸው ግን አንዳች በማይሰጥ ሰው ላይ ሰልፍን ያስቡበታል። 6 ስለዚህ ሌሊት ይሆንባችኋል እንጂ ራእይ አይሆንላችሁም፤ ጨለማም ይሆንባችኋል እንጂ አታምዋርቱም፤ ፀሐይም በነቢያት ላይ ትገባለች፥ ቀኑም ይጠቁርባቸዋል። 7 ከእግዚአብሔርም ዘንድ መልስ የለምና ባለ ራእዩቹ ያፍራሉ፥ ምዋርተኞችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ከንፈራቸውን ይሸፍናሉ። 8 እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ። 9 ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ። 10 ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ። 11 አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር። እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ። 12 ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል።

ሚክያስ 4

1 በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ። 2 ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ። 3 በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም። 4 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም። 5 ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን። 6 በዚያ ቀን አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የባከነችውንና ያስጨነቅኋትንም አከማቻለሁ፤ 7 አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል። 8 አንተም የመንጋ ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወደ አንተ ትመጣለች፤ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ትደርሳለች። 9 አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን? 10 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፤ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል። 11 አሁንም። ርኩስ ትሁን፥ ዓይናችንም በጽዮን ላይ ይይ የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል። 12 ነገር ግን የእግዚአብሔርን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ ወደ አውድማ አከማችቶአቸዋልና። 13 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁና ተነሺ አሂጂ፤ ብዙ አሕዛብንም ታደቅቂአለሽ፤ ትርፋቸውንም ለእግዚአብሔር፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ።

ሚክያስ 5

1 የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ፤ ከብቦ አስጨንቆናል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ። 2 አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። 3 ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ። 4 እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፤ እነርሱም ይኖራሉ፤ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና። 5 ይህም ለሰላም ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ምድራችንንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን። 6 የአሦርንም አገር በሰይፍ፥ የናምሩድንም አገር በመግቢያው ውስጥ ያፈርሳሉ፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቾቻችንንም በረገጠ ጊዜ እርሱ ይታደገናል። 7 የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወድ ካፊያ፤ ሰውንም እንደማይጠብቅ፥ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል። 8 በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋም መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ እንዲሁ የያዕቆብ ቅሬታ በአሕዛብና በብዙ ወገኖች መካከል ይሆናል። 9 እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ከፍ ትበል፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጥፉ። 10 በዚያም ቀን ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እሰብራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ 11 የምድርህንም ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈርሳለሁ፤ 12 መተትንም ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ምዋርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆኑልህም፤ 13 የተቀረጹትን ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ለእጅህም ሥራ ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግድም፤ 14 የማምለኪያ ዐፀዶችህንም ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ። 15 ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቍጣና በመዓት እበቀላለሁ።

ሚክያስ 6

1 አሁን። ተነሣ፥ በተራሮችም ፊት ተፋረድ፥ ኮረብቶችም ቃልህን ይስሙ ብሎ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ። 2 ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳልና የእግዚአብሔርን ክርክር ስሙ። 3 ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አድርጌሃለሁ? በምንስ አድክሜሃለሁ? መስክርብኝ። 4 ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፤ በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር። 5 ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፥ የቢዖርም ልጅ በለዓም የመለሰለትን አሁን አስብ፤ የእግዚአብሔርንም የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ ከሰጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ አስብ። 6 ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? 7 እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን? 8 ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? 9 የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ የመቅሠፍትን በትር፥ እርሱንም ያዘጋጀ ማን እንደ ሆነ ስሙ። 10 በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈም ውሽተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን? 11 በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን? 12 ባለ ጠጎችዋን ግፍ ሞልቶባቸዋል፤ በእርስዋም የሚኖሩ በሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው። 13 ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቍስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈርስሁህ። 14 ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ችጋርህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን አታድንም፤ የምታድነውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ። 15 ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራውንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይኑንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም። 16 አንተን ለጥፋት፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ለማፍዋጫ እሰጥ ዘንድ የዘንበሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቃችኋል፥ በምክራቸውም ሄዳችኋል፤ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።

ሚክያስ 7

1 የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም። 2 ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም፤ ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል። 3 እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፤ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ። 4 ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው፤ ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል፤ አሁን ይሸበራሉ። 5 ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ። 6 ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና። 7 እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል። 8 ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ። 9 በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን ለእኔ እስኪያደርግ ድረስ ቍጣውን እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቅንም አያለሁ። 10 ጠላቴም ታያለች፥ እኔንም። አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ያለች በእፍረት ትከደናለች። 11 ዓይኖቼ ይመለከቱአታል፤ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ በሚሠራበት በዚያ ቀን ድንበርሽ ትስፋፋለች። 12 በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕርም እስከ ባሕር፥ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንቺ ይመጣሉ። 13 ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት በሥራቸው ፍሬ ምክንያት ባድማ ትሆናለች። 14 በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ። 15 ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳያቸዋለሁ። 16 አሕዛብ አይተው በጕልበታቸው ሁሉ ያፍራሉ፤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮአቸውም ትደነቍራለች፤ 17 እንደ እባብም መሬት ይልሳሉ፥ እንደ ምድርም ተንቀሳቃሾች እየተንቀጠቀጡ ከግንባቸው ይመጣሉ፤ ፈርተውም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፥ ስለ አንተም ይፈራሉ። 18 በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም። 19 ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል። 20 ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።

ናሆም 1

1 ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው። 2 እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል። 3 እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም። ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው። 4 ባሕሩንም ይገሥጻታል፥ ያደርቃትማል፥ ወንዞችንም ሁሉ ያደርቃል፤ ባሳንና ቀርሜሎስም ላልተዋል፥ የሊባኖስም አበባ ጠውልጎአል። 5 ተራሮችም ከእርሱ የተነሣ ታወኩ፥ ኮረብቶችም ቀለጡ፤ ምድርና ዓለም የሚኖሩበትም ሁሉ ከፊቱ ተናወጡ። 6 በቍጣው ፊት የሚቆም ማን ነው? የቍጣውንም ትኵሳት ማን ይታገሣል? መዓቱ እንደ እሳት ይፈስሳል፥ ከእርሱም የተነሣ ዓለቶች ተሰነጠቁ። 7 እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። 8 ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል። 9 በእግዚአብሔር ላይ የምታስቡት ምንድር ነው? እርሱ ፈጽሞ ያጠፋል፥ መከራም ሁለተኛ አይነሣም። 10 እርስ በእርሳቸው እንደ ተመሰቃቅለ እሾህ ቢሆኑ፥ በመጠጣቸውም ቢሰክሩ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ። 11 በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑ እንዲሁ ይቈረጣሉ፥ እርሱም ያልቃል። እኔም አስጨንቄሃለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅህም። 13 አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ። 14 እግዚአብሔርም ከስምህ ማንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፤ ከአምላኮችህ ቤት የተቀረጸውንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ፤ አንተም የተጠቃህ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ። 15 እነሆ፥ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ፥ አጥፊው ፈጽሞ ጠፍቶአልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ፥ ስእለቶችህን ክፈል።

ናሆም 2

1 የሚቀጠቅጥ በአንተ ላይ ወጥቶአል፤ ምሽግን ጠብቅ፥ መንገድንም ሰልል፤ ወገብህን አጽና፥ ኃይልህንም እጅግ አበርታ። 2 ዘራፊዎች ዘርፈዋቸዋልና፥ የወይናቸውንም አረግ አጥፍተዋልና እግዚአብሔር የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል። 3 የኃያላኑ ጋሻ ቀልቶአል፥ ጽኑዓንም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱም በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፤ የጦሩም ሶመያ ይወዛወዛል። 4 ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይነጕዳሉ፥ አደባባይም ይጋጫሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይከንፋሉ። 5 መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው በቅጥርዋ ላይ ይወጣሉ፥ መጠጊያም ተዘጋጀለት። 6 የወንዞቹም መዝጊያዎች ተከፈቱ፥ የንጉሡ ቤትም ቀለጠች። 7 ንግሥት ተገለጠች፥ ተማረከችም፥ ሴቶች ባሪያዎችዋም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ ዋይ ዋይ ይላሉ። 8 ነነዌ ግን ከዱሮ ዘመን ጀምራ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ አሁን ግን ይሸሻሉ፤ እነርሱም። ቁሙ፥ ቁሙ ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። 9 መዝገብዋ መጨረሻ የለውምና፥ የከበረውም የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቈጠርምና ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ። 10 ባዶና ባድማ ምድረ በዳም ሆናለች፤ ልብ ቀልጦአል፥ ጕልበቶችም ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሰዎችም ሁሉ ፊት ጠቍሮአል። 11 የአንበሾችም መደብ፥ የአንበሾችም ደቦል የሚሰማራበት፥ አንበሳውና አንበሳይቱ ግልገሉም ሳይፈሩ የሚሄዱት ስፍራ ወዴት ነው? 12 አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል። 13 እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰረገሎችዋንም አቃጥዬ አጤሳለሁ፥ ሰይፍም የአንበሳ ደቦሎችሽን ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽንም ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልክተኞችሽን ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ አይሰማም።

ናሆም 3

1 ለደም ከተማ ወዮላት! በሁለንተናዋ ሐሰትና ቅሚያ ሞልቶባታል፤ ንጥቂያ ከእርስዋ አያልቅም። 2 የአለንጋ ድምፅ፥ የመንኰራኵርም ድምፅ፥ የፈረሶችም ኮቴ፥ የፈጣን ሰረገላም ጩኸት ተሰምቶአል፤ 3 ፈረሰኛው ይጋልባል፥ ሰይፍም ይንቦገቦጋል፥ ጦርም ይብለጨለጫል፤ የተገደሉትም ይበዛሉ፥ በድኖችም በክምር ይከመራሉ፥ ሬሳቸውም አይቈጠርም፤ በሬሳቸውም ይሰናከላሉ። 4 ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች። 5 እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ልብስሽን በፊትሽ እገልጣለሁ፤ ኅፍረተ ሥጋሽንም ለአሕዛብ፥ ነውርሽንም ለመንግሥታት አሳያለሁ። 6 ርኵሰትንም በላይሽ እጥላለሁ፥ እንቅሻማለሁ፥ ማላገጫም አደርግሻለሁ። 7 የሚያይሽም ሁሉ ከአንቺ ሸሽቶ። ነነዌ ባድማ ሆናለች፤ የሚያለቅስላትስ ማን ነው? የሚያጽናናትንስ ከወዴት እፈልጋለሁ? ይላል። 8 አንቺ በመስኖች መካከል ከተቀመጠችው፥ ውኃም በዙሪያዋ ከነበራት፥ ምሽግዋም ባሕር ከነበረ፥ ቅጥርዋም በባሕር ውስጥ ከነበረ ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን? 9 ኢትዮጵያና ግብጽ የማይቈጠር ኃይልዋ ነበሩ፤ ፉጥና ልብያ ረዳቶችዋ ነበሩ። 10 እርስዋ ግን ተማርካ ፈለሰች፤ ሕፃናቶችዋ በመንገድ ሁሉ ራስ ላይ ተፈጠፈጡ፤ በከበርቴዎችዋም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፥ ታላላቆችዋም ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ። 11 አንቺም ትሰክሪአለሽ ወራዳም ትሆኛለሽ፤ አንቺ ደግሞ ከጠላት የተነሣ መጠጊያን ትፈልጊአለሽ። 12 አምባሽ ሁሉ የመጀመሪያውን የበሰለ ፍሬ እንደ ያዙ እንደ በለስ ዛፎች ነው፤ ቢወዛወዝ በሚበላው አፍ ውስጥ ይወድቃል። 13 እነሆ፥ በመካከልሽ ያሉ ሕዝብሽ ሴቶች ናቸው፤ የአገርሽ በሮች ለጠላቶችሽ ፈጽሞ ተከፍተዋል፥ እሳትም መወርወሪያዎችህን በልቶአል። 14 ከብበው ያስጨንቁሻልና ውኃን ቅጂ፤ አምባሽን አጠንክሪ፤ ወደ ጭቃ ገብተሽ እርገጪ፤ የጡብን መሠሪያ ያዢ። 15 በዚያ እሳት ይበላሻል፥ ሰይፍ ያጠፋሻል፥ እንደ ደጎብያ ይበላሻል፤ እንደ ደጎብያ ብዢ፥ እንደ አንበጣም ተባዢ። 16 ነጋዴዎችሽን ከሰማይ ከዋክብት ይልቅ አበዛሽ፤ ደጎብያ ተዘረጋ፥ በረረም። 17 በአንቺ ዘንድ ዘውድ የጫኑት እንደ አንበጣ፥ አለቆችሽም እንደሚንቀሳቀሱ ኩብኩባዎች ናቸው፤ በብርድ ቀን በቅጥር ውስጥ ይቀመጣሉ፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ያኰበኵባሉ፤ ስፍራቸው በየት እንደ ሆነ አይታወቅም። 18 የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ እረኞችህ አንቀላፍተዋል፤ መኳንንቶችህም ዐርፈዋል፤ ሕዝብህም በተራሮች ላይ ተበትኖአል፥ የሚሰበስበውም የለም። 19 ስብራትህ አይፈወስም፥ ቍስልህም ክፉ ነው፤ ወሬህንም የሚሰሙ ሁሉ እጃቸውን በአንተ ላይ ያጨበጭባሉ፤ ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነውና?

ዕንባቆም 1

1 ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም ይህ ነው። 2 አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም። 3 በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። 4 ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም፤ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል። 5 እናንተ የምትንቁ ሆይ፥ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና እዩ፥ ተመልከቱ፥ ተደነቁ። 6 እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። 7 እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል። 8 ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ከሩቅም ይመጣሉ፥ ለመብልም እንደሚቸኵል ንስር ይበርራሉ። 9 ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ፥ ፊታቸውንም እንደ ምሥራቅ ነፋስ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። 10 በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ መሳፍንትም ዋዛ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጉ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩንም ከምረው ይወስዱታል። 11 የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ አልፎ ይሄዳል፥ ይበድልማል፤ ኃይሉንም አምላክ ያደርገዋል። 12 አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል። 13 ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፤ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለ ምን ዝም ትላለህ? 14 ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ? 15 ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል። 16 እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። 17 ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?

ዕንባቆም 2

1 በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ። 2 እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ። አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው። 3 ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም። 4 እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። 5 እርሱ አታላይና ኵሩ ሰው ነው፤ በስፍራው ዐርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል። 6 እነዚህ ሁሉ። ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን? 7 ተረትም አይተርቱበትምን? የሚነክሱህ ድንገት አይነሡብህምን? የሚያስጨንቁህም ይነቃሉ፤ ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ። 8 የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል። 9 ከክፉ እንዲድን ጐጆውን በከፍታ ላይ ያደርግ ዘንድ ለቤቱ ክፉ ትርፍን ለሚሰበስብ ወዮለት! 10 ብዙ አሕዛብን አጥፍተሃልና ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል። 11 ድንጋይም ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከውቅር ውስጥ ይመልስለታል። 12 ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በኃጢአት ለሚመሠርት ወዮለት! 13 እነሆ፥ አሕዛብ ስለ እሳት እንዲሠሩ፥ ወገኖችም ስለ ከንቱነት እንዲደክሙ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ አይደለምን? 14 ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና። 15 ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት! 16 በክብር ፋንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጥተህ ተንገድገድ፤ የእግዚአብሔር የቀኙ ጽዋ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። 17 የሰውንም ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ይከድንሃል፤ የአራዊትም አደጋ ያስፈራራሃል። 18 የተቀረጸውን ምስል ሠሪው የቀረጸው ለምን ጥቅም ነው? ዲዳንም ጣዖት ይሠራ ዘንድ ሠሪው የታመነበቱ፥ ሐሰትን የሚያስተምር ቀልጦ የተሠራ ምን ይጠቅማል? 19 እንጨቱን። ንቃ፥ ዲዳውንም ድንጋይ። ተነሣ ለሚለው ወዮለት! በውኑ ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ ምንም እስትንፋስ የለበትም። 20 እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።

ዕንባቆም 3

1 የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት በመዝሙር። 2 አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ። 3 እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። 4 ፀዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሮአል። 5 ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል። 6 ቆመ፥ ምድርንም አወካት፤ ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘላለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘላለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘላለም ነው። 7 የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ። 8 በውኑ እግዚአብሔር በወንዞች ላይ ተቈጥቶአልን? ቍጣህ በወንዞች ላይ፥ መዓትህም በባሕር ላይ ነውን? በፈረሶችህና በማዳንህ ሰረገሎች ላይ ተቀምጠሃልና። 9 በቃልህ እንደ ማልህ መቅሠፍትህን አወጣህ፤ ቀስትህንም ገተርህ፤ ምድርን ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ። 10 ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ፤ የውኃ ሞገድ አልፎአል፤ ቀላዩም ድምፁን ሰጥቶአል፥ እጁንም ወደ ላይ አንሥቶአል። 11 ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ። 12 በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፤ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው። 13 ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፤ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ። 14 የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፤ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፤ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው። 15 ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ። 16 እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፤ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ። 17 ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ 18 እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። 19 ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ሶፎንያስ 1

1 በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ ወደ አማርያ ልጅ ወደ ጎዶልያስ ልጅ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2 ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 3 ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፤ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤ 5 በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን፥ 6 እግዚአብሔርንም ከመከተል የተመለሱትን፥ እግዚአብሔርንም ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ። 7 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጅቶአልና፥ የጠራቸውንም ቀድሶአልና በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ። 8 በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ። 9 በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ። 10 በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል። 11 እናንተ በመክቴሽ የምኖሩ ሆይ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ጠፍተዋልና፥ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቈርጠዋልና አልቅሱ። 12 በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፥ በልባቸውም። እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፥ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ። 13 ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም። 14 ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል። 15 ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥ 16 በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው። 17 በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፥ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይፈስሳል። 18 በእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።

ሶፎንያስ 2

1 2 እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፥ ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ትኵሳት ሳይመጣባችሁ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም። 3 እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። 4 ጋዛ ትበረበራለች፥ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ አዞጦንንም በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዱአታል፥ አቃሮንም ትነቀላለች። 5 በባሕር ዳር ለሚኖሩ ለከሊታውያን ሕዝብ ወዮላቸው! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የእግዚአብሔር ቃል በአንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብህም ሰው እንዳይኖር አጠፋሃለሁ። 6 ቀርጤስም የእረኞች መኖሪያና የመንጎች በረት ይሆናል። 7 የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ቅሬታ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳልና በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ። 8 በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፥ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ። 9 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፥ የሳማ ስፍራና የጨው ጕድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፤ የሕዝቤም ቅሬታ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል። 10 በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ እየታበዩም ተናግረዋልና ይህ ስለ ትዕቢታቸው ያገኛቸዋል። 11 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፤ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ። 12 እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ። 13 እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማ፥ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል። 14 መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጥዋ ይመሰጋሉ፤ ይብራና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፤ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል፤ የዝግባም እንጨት ሥራ ይገለጣልና በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል። 15 ተዘልላ የተቀመጠች፥ በልብዋም። እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ያለች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፤ አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ እንዴት ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፍዋጫል።

ሶፎንያስ 3

1 ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት! 2 ድምፅን አልሰማችም፥ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም። 3 በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ፈራጆችዋም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኵላዎች ናቸው። 4 ነቢያቶችዋ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው፤ ካህናቶችዋም መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል። 5 እግዚአብሔር በውስጥዋ ጻድቅ ነው፤ ክፋትን አያደርግም፤ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፥ ሳያወጣውም አይቀርም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም። 6 አሕዛብን አጥፍቻለሁ፤ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፤ መንገዳቸውን ማንም እንዳያልፍባት ምድረ በዳ አድርጌአለሁ፥ ከተሞቻቸውም ማንም እንዳይኖርባቸው፥ አንድስ እንኳ እንዳይቀመጥባቸው ፈርሰዋል። 7 እኔም- ይፈሩኛል፥ ተግሣጽንም ይቀበላሉ፤ ካዘዝኋትም ሁሉ ከዓይንዋ ምንም አይጠፋም ብዬ ነበር፤ እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ። 8 መዓቴንና የቍጣዬን ትኵሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፥ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሐን ልሳን እመልስላቸዋለሁ። 10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል። 11 በዚያን ጊዜ እየታበዩ የሚፎክሩትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ዳግመኛ አትኰሪምና በዚያ ቀን በእኔ ላይ ተላልፈሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አትፍሪም። 12 በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ። 13 የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይመሰጉማል፥ የሚያስፈራቸውም የለም። 14 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ። 15 እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። 16 በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም። ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ። 17 አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል። 18 ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር። 19 በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ። 20 በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ሐጌ 1

1 በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ ወደ ይሁዳ አለቃ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤል፥ ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ይህ ሕዝብ። ዘመኑ አልደረሰም፥ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል ብሎ ተናገረ። 3 የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ። 4 በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? 5 አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 6 ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። 7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። 8 ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9 እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነው። 10 ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ከልክላለች። 11 እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ። 12 የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል፥ አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ላከው ሁሉ ሰሙ፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ። 13 የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን። እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ። 14-15 እግዚአብሔርም የይሁዳን አለቃ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁንም ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስ፥ የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፤ በንጉሡም በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን መጡ፥ የአምላካቸውንም የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት ሠሩ።

ሐጌ 2

1 በሰባተኛው ወር ከወሩም በሀያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ። 2 ለይሁዳ አለቃ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፥ ለታላቁም ካህን ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፥ ለቀሩትም ሕዝብ እንዲህ ስትል ተናገር። 3 በቀድሞ ክብሩ ሳለ ይህን ቤት ያየ በእናንተ መካከል የቀረ ማን ነው? ዛሬስ እንዴት ሆኖ አያችሁት? በዓይናችሁ እንደ ምናምን አይደለምን? 4 አሁን ግን፥ ዘሩባቤል ሆይ፥ በርታ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፥ በርታ፥ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፥ በርቱና ሥሩ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5 መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ። 6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፤ 7 አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፥ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 8 ብሩ የእኔ ነው፥ ወርቁም የእኔ ነው፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9 ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 10 በዳርዮስም በሁለተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ። 11 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ካህናቱን ስለ ሕጉ ጠይቅ፤ 12 አንድ ሰው የተቀደሰ ሥጋ በልብሱ ዘርፍ ቢይዝ፥ በዘርፉም እንጀራ ወይም ወጥ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ዘይት፥ ወይም ማናቸውም መብል ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይቀደሳልን? ብለህ ካህናቱን ጠይቃቸው፤ ካህናቱም። አይሆንም ብለው መለሱ። 13 ሐጌም። በሬሳ የረከሰ ሰው ከእነዚህ አንዱን ቢነካ ያ የተነካው በውኑ ይረክሳልን? አለ። ካህናቱም። አዎን ይረክሳል ብለው መለሱ። 14 ሐጌም መልሶ እንዲህ አለ። ይህ ሕዝብና ይህ ወገን በፊቴ እንዲሁ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የእጃቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፤ በዚያም ያቀረቡት ነገር ርኩስ ነው። 15 አሁንም ድንጋይ በድንጋይ ላይ በእግዚአብሔር መቅደስ ሳይነባበር፥ ከዛሬ ጀምራችሁ ወዳለፈው ዘመን ልብ አድርጉ። 16 በዚያን ዘመን ሁሉ ሰው ሀያ መስፈሪያ ወዳለበት ምርት በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው አሥር መስፈሪያ ብቻ ነው፤ አምሳ ማድጋም ይቀዳ ዘንድ ወደ መጥመቂያው በመጣ ጊዜ፥ የተገኘው ሀያ ብቻ ነው። 17 በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ላይ በዋግና በአረማሞ በበረዶም መታኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 ከዛሬው ከዘጠነኛው ወር ከሀያ አራተኛው ቀን ጀምራችሁ የሚመጣውን ዘመን ልብ አድርጉ፤ የእግዚአብሔር መቅደስ መሠረት ከተተከለበት ቀን ጀምሮ ልብ አድርጉ። 19 ዘር በጎተራ ገና ይኖራልን? ወይንና በለስ ሮማንና ወይራ አላፈሩም፤ ከዚህች ቀን ጀምሬ እባርካችኋለሁ። 20 በወሩ በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ሁለተኛ ወደ ሐጌ እንዲህ ሲል መጣ። 21 ለይሁዳ አለቃ ለዘሩባቤል ተናገር እንዲህም በል። ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ፤ 22 የመንግሥታትንም ዙፋን እገለብጣለሁ፥ የአሕዛብንም መንግሥታት ኃይል አጠፋለሁ፤ ሰረገሎችንና የሚቀመጡባቸውንም እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ፈረሰኞቻቸውም እያንዳንዳቸው በወንድማቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። 23 ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፥ በዚያ ቀን እወስድሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔ መርጬሃለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እንደ ቀለበት ማተሚያ አደርግሃለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

ዘካርያስ 1

1 በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። 2 እግዚአብሔር በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር። 3 ስለዚህ እንዲህ በላቸው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 4 የቀደሙት ነቢያት ለአባቶቻችሁ እንዲህ ብለው ሰብከዋል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፥ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፥ ይላል እግዚአብሔር። 5 አባቶቻችሁ ወዴት ናቸው? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን? 6 ለባሪያዎቼስ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? እነርሱም ተመልሰው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ያደርግብን ዘንድ እንዳሰበ እንዲሁ አድርጎብናል አሉ። 7 በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት ሳባጥ በሚባል በአሥራ አንደኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። 8 እነሆም፥ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፤ በስተ ኋላውም መጋላና ሐመር አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። 9 እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁ። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ አለኝ። 10 በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው። እነዚህ በምድር ላይ ይመላለሱ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው ብሎ መለሰ። 11 በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መልአክ። በምድር ላይ ተመላለስን፥ እነሆም፥ ምድር ሁሉ ዝም ብላ ዐርፋ ተቀምጣለች ብለው መለሱለት። 12 የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። 13 እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። 14 ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ። ስበክ እንዲህም በል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። 15 እኔ ጥቂት ብቻ ተቈጥቼ ሳለሁ እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ ባልተቸገሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። 16 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ ይሠራባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 17 ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል። 18 ዓይኖቼንም አንሥቼ እነሆ፥ አራት ቀንዶች አየሁ። 19 ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ። እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። እርሱም። እነዚህ ይሁዳንና እስራኤልን ኢየሩሳሌምንም የበተኑ ቀንዶች ናቸው ብሎ መለሰልኝ። 20 እግዚአብሔርም አራት ጠራቢዎች አሳየኝ። 21 እኔም። እነዚህ የመጡት ምን ሊሠሩ ነው? አልሁ። እርሱም። አንድ ሰው ራሱን እስከማያነሣ ድረስ እነዚህ ቀንዶች ይሁዳን የበተኑ ናቸው፤ እነዚህ ግን ሊያስፈራሩአቸው፥ የይሁዳንም አገር ይበትኑ ዘንድ ቀንዳቸውን ያነሡትን የአሕዛብን ቀንዶች ሊጥሉ መጥተዋል ብሎ ተናገረ።

ዘካርያስ 2

1 ዓይኖቼንም አነሣሁ፤ እነሆም፥ በእጁ የመለኪያ ገመድ የያዘ አንድ ሰውን አየሁ። 2 እኔም። አንተ ወዴት ትሄዳለህ? አልሁ። እርሱም። የኢየሩሳሌምን ወርድና ርዝመት ስንት መሆኑን ሰፍሬ አይ ዘንድ እሄዳለሁ አለኝ። 3 እነሆም፥ ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥ 4 እንዲህም አለው። ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው። ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች። 5 እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 6 እናንተ ሆይ፥ ከሰሜን ምድር ሽሹ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ አራቱ የሰማይ ነፍሳት በትኛችኋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 7 አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ፥ ኰብልዪ። 8 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ ልኮኛል፤ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና። 9 እነሆ፥ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። 10 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። 11 በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ። 12 እግዚአብሔርም ይሁዳን እድል ፈንታው አድርጎ በተቀደሰችው ምድር ይወርሰዋል፥ ኢየሩሳሌምንም ዳግመኛ ይመርጣል። 13 እግዚአብሔር ከተቀደሰ ማደሪያው ነቅቶአልና ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ፥ በፊቱ ዝም በል።

ዘካርያስ 3

1 እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። 2 እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ሰይጣን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን? አለው። 3 ኢያሱም እድፋም ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። እርሱም መልሶ በፊቱ የቆሙትን። እድፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ አላቸው። እርሱንም። እነሆ፥ አበሳህን ከአንተ አርቄአለሁ፥ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ አለው። 5 ደግሞ። ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉ አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም አደረጉ፥ ልብስንም አለበሱት፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር። 6 የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያሱ እንዲህ ሲል አዳኘበት። 7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመንገዴ ብትሄድ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፥ በቤቴ ላይ ትፈርዳለህ፥ አደባባዮቼንም ትጠብቃለህ፥ በዚህም ከቆሙት ከእነዚህ ጋር መግባትን እሰጣለሁ። 8 ታላቁ ካህን ኢያሱ ሆይ፥ ስማ፤ በፊትህም የሚቀመጡት ባልንጀሮችህ ለምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ፤ እነሆ፥ እኔ ባሪያዬን ቍጥቋጥ አወጣለሁ። 9 በኢያሱ ፊት ያኖርሁት ድንጋይ እነሆ አለ፤ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዓይኖች አሉ፤ እነሆ፥ ቅርጹን እቀርጻለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የዚያችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ። 10 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ሆኖ ባልንጀራውን ይጠራል።

ዘካርያስ 4

1 ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው አነቃኝ። 2 እርሱም። የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነውን መቅረዝ አየሁ፤ የዘይትም ማሰሮ በራሱ ላይ ነበረ፥ ሰባትም መብራቶች ነበሩበት፤ በራሱም ላይ ለነበሩት መብራቶች ሰባት ቧንቧዎች ነበሩአቸው። 3 ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ሆነው፥ በአጠገቡ ነበሩ አልሁ። 4 ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። 5 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁ። 6 መልሶም። ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 7 ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም። ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ። 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 9 የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። 10 የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው። 11 እኔም መልሼ። በመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። 12 ሁለተኛም መልሼ። በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ሆነው የወርቁን ዘይት የሚያፈስሱ እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። 13 እርሱም መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም ። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁት። 14 እርሱም። በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ።

ዘካርያስ 5

1 ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አንድ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ። 2 እርሱም። የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ወርዱም አሥር ክንድ ነው አልሁ። 3 እንዲህም አለኝ። ይህ በምድር ፊት ሁሉ ላይ የሚወጣው እርግማን ነው፤ የሚሰርቅ ሁሉ በእርሱ ላይ በዚህ በኩል እንደ ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል፥ በሐሰት የሚምልም ሁሉ በእርሱ ላይ በዚያ በኩል እንደ ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል። 4 እኔ አስወጣዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ወደ ሚሰርቀውም ቤት፥ በሐሰትም በስሜ ወደሚምለው ቤት ይገባል፤ በቤቱም ውስጥ ይኖራል፥ እርሱንም፥ እንጨቱንና ድንጋዩን፥ ይበላል። 5 ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጥቶ። ዓይኖችህን አንሣ፥ ይህችም የምትወጣው ምን እንደ ሆነች እይ አለኝ። 6 እኔም። ምንድር ናት? አልሁ። እርሱም። ይህች የምትወጣው የኢፍ መስፈሪያ ናት አለኝ። ደግሞም። በምድር ሁሉ ላይ ያለ በደላቸው ይህ ነው አለ። 7 እነሆም፥ የእርሳሱን መክሊት አነሡት፤ እነሆም፥ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። 8 እርሱም። ይህች ክፋት ናት አለኝ፤ በኢፍ መስፈሪያው ውስጥ ጣላት፥ የእርሳሱንም ጠገራ በመስፈሪያ አፍ ላይ ጣለ። 9 ዓይኖቼንም አንሥቼ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁለት ሴቶች ወጡ፥ ነፋስም በክንፎቻቸው ነበረ፤ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ነበሩ፤ የኢፍ መስፈሪያውንም በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት። 10 ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ። እነዚህ የኢፍ መስፈሪያውን ወዴት ይወስዱታል? አልሁት። 11 እርሱም። በሰናዖር ምድር ቤት ይሠሩለት ዘንድ ይወስዱታል፤ በተዘጋጀም ጊዜ በዚያ በስፍራው ይኖራል አለኝ።

ዘካርያስ 6

1 ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። 2 በፊተኛው ሰረገላ መጋላ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሰረገላ ዱሪ ፈረሶች ነበሩ፥ 3 በሦስተኛውም ሰረገላ አምባላይ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሰረገላ ቅጥልጣል ፈረሶች ነበሩ። 4 ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። 5 መልአኩም መልሶ። እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው። 6 ዱሪ ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ አምባላዮቹም ከእነርሱ በኋላ ይወጣሉ፥ ቅጥልጣሎችም ወደ ደቡብ ይወጣሉ አለኝ። 7 መጋላዎቹም ደግሞ ወጡ በምድርም ይመላለሱ ዘንድ ለመሄድ ይፈልጉ ነበር፤ እርሱም። ሂዱ፥ በምድር ላይ ተመላለሱ አለ። እነርሱም በምድር ላይ ተመላለሱ። 8 ጮኾም። እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል ብሎ ተናገረኝ። 9 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 10 ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ። 11 ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በታላቁም ካህን በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፥ 12 እንዲህም በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። 13 እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፥ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል። 14 አክሊሎችም ለሔሌምና ለጦብያ ለዮዳኤም ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ። 15 በሩቅም ያሉት መጥተው የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቃችሁ ብትሰሙ ይህ ይሆናል።

ዘካርያስ 7

1 በንጉሡም በዳርዮስ በአራተኛው ዓመት ካሴሉ በሚባል በዘጠነኛው ወር በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ። 2 የቤቴልም ሰዎች ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ሰዎቻቸውንም በእግዚአብሔር ፊት ይለምኑ ዘንድ፥ 3 ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለነቢያትም። ባለፉት ዓመታት እንዳደረግሁት በአምስተኛው ወር መለየትና ማልቀስ ይገባኛልን? ብለው ይናገሩ ዘንድ ልኮአቸው ነበር። 4 የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 5 ለምድሩ ሕዝብ ሁሉ ለካህናትም እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። በዚህ በሰባው ዓመት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር በጾማችሁና ባለቀሳችሁ ጊዜ፥ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝ? 6 በምትበሉበትና በምትጠጡበትስ ጊዜ፥ ለራሳችሁ የምትበሉና የምትጠጡ አይደላችሁምን? 7 ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ገና ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ በምቾትም ተቀምጠው ሳሉ፥ ደቡቡና ቈላውም ሰዎች ባሉባቸው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ የተናገረውን ቃል መስማት አይገባችሁምን? 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮአል። እውነተኛውን ፍርድ ፍረዱ፤ ቸርነትንና ምሕረትን ሁላችሁ ለወንድሞቻችሁ አድርጉ፤ 10 መበለቲቱንና ድሀ አደጉን፥ መጻተኛውንና ችግረኛውን አትበድሉ፤ ከእናንተም ማንም በወንድሙ ላይ ክፉውን ነገር በልቡ አያስብ። 11 እነርሱ ግን ደንደሳቸውን አዞሩ እንጂ መስማትን እምቢ አሉ፤ እንዳይሰሙም ጆሮአቸውን አደነቈሩ። 12 የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት እጅ በመንፈሱ የላከውን ሕጉንና ቃሉን እንዳይሰሙ ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ ስለዚህ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ቍጣ መጣ። 13 እኔ በጠራሁ ጊዜ እነርሱ እንዳልሰሙኝ፥ እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩበት ጊዜ እኔ አልሰማም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ 14 ወደማያውቁአቸውም አሕዛብ ሁሉ በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው። እንዲሁ ከእነርሱ በኋላ ምድሪቱ ባድማ ሆናለች፥ የሚተላለፍባትና የሚመላለስባትም አልነበረም፤ ያማረችውንም ምድር ባድማ አደረጉአት።

ዘካርያስ 8

1 የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 2 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቍጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ። 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል። 4 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል። 5 የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ። 6 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ወራት በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ዓይን ዘንድ ድንቅ ቢሆን፥ በውኑ በእኔ ዓይን ዘንድ ደግሞ ድንቅ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፤ 8 አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ። 9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፥ እጃችሁን አበርቱ። 10 ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም። 11 አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 12 ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፤ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ። 13 የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። 14 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ 15 እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ። 16 የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ 17 ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 19 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ። 20 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፤ 21 በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች። እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። 22 ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ። 23 የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።

ዘካርያስ 9

1 የእግዚአብሔር ቃል ሸክም በሴድራክ ምድር ላይ ነው፥ በደማስቆም ላይ ያርፋል፤ የእግዚአብሔር ዓይን ወደ ሰውና ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ዘንድ ነው፤ 2 ደግሞም በዳርቻዋ ባለችው በሐማት ላይ፥ እጅግ ጠቢበኞች በሆኑ በጢሮስና በሲዶና ላይ ነው። 3 ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፥ ብሩንም እንደ አፈር ጥሩውንም ወርቅ እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች። 4 እነሆ፥ ጌታ ይገፍፋታል፥ በባሕርም ላይ ያለውን ብርታትዋን ይመታል፤ እርስዋም በእሳት ትበላለች። 5 አስቀሎና አይታ ትፈራለች፤ ጋዛ ደግሞ አይታ እጅግ ትታመማለች፤ አቃሮንም እንዲሁ፥ ተስፋዋ ይቈረጣልና፤ ንጉሡም ከጋዛ ይጠፋል፥ በአስቀሎናም የሚቀመጥ አይገኝም። 6 የተደባለቀ ወገን በአዛጦን ይቀመጣል፥ የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ። 7 ደሙንም ከአፉ ውስጥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቅሬታ ይሆናል፤ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፥ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል። 8 እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፤ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም። 9 አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። 10 ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆናል። 11 ለአንቺም ደግሞ ስለ ቃል ኪዳንሽ ደም፥ እስሮችሽን ውኃ ከሌለበት ጕድጓድ አውጥቻለሁ። 12 እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስሮች ሆይ፥ ወደ ጽኑ አምባ ተመለሱ፤ ሁለት እጥፍ አድርጌ እንድመልስልሽ ዛሬ እነግርሻለሁ። 13 ይሁዳን ለእኔ ገትሬአለሁ፤ ቀስቱን በኤፍሬም ሞልቼአለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ አንቺንም እንደ ኃያል ሰው ሰይፍ አደርግሻለሁ። 14 እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔርም መለከትን ይነፋል፥ በደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይሄዳል። 15 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ እነርሱም ይበሉአቸዋል፥ የወንጭፉንም ድንጋዮች ይረግጣሉ፤ እንደ ወይን ጠጅም ይጠጡአቸዋል፥ እንደ ጥዋዎችም እንደ መሠዊያም ማዕዘኖች የተሞሉ ይሆናሉ። 16 በዚያም ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ መንጋ ያድናቸዋል፤ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ይብለጨለጫሉ። 17 በጎነቱ እንዴት ታላቅ ነው! ውበቱስ እንዴት ታላቅ ነው! እህል ጐበዛዝቱን፥ ጉሽ ጠጅም ቈነጃጅቱን ያለመልማል።

ዘካርያስ 10

1 በኋለኛው ዝናብ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዝናቡን ለምኑ፤ እግዚአብሔር መብረቅ ያደርጋል፤ እርሱም የበልግ ዝናብን ለእያንዳንዱም በሜዳ ውስጥ ሣርን ይሰጣል። 2 ተራፊም ከንቱነትን ተናግረዋልና፥ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፤ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል፥ በከንቱም ያጽናናሉ፤ እረኛም የላቸውምና እንደ በጎች ተቅበዝብዘዋል ተጨንቀውማል። 3 ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዶአል፥ አውራ ፍየሎችንም እቀጣለሁ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የይሁዳን ቤት መንጋውን ጐብኝቶአል፥ በሰልፍም ውስጥ እንዳለ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል። 4 ከእርሱ ዘንድ የማዕዘኑ ድንጋይ፥ ከእርሱም ዘንድ ችንካሩ፥ ከእርሱም ዘንድ የሰልፉ ቀስት፥ ከእርሱም ዘንድ አስገባሪው ሁሉ በአንድ ላይ ይመጣሉ። 5 በሰልፍም ጊዜ ጠላቶቻቸውን በመንገድ ጭቃ ውስጥ እንደሚረግጡ ኃያላን ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነውና ይዋጋሉ፥ ፈረሰኞችም ያፍራሉ። 6 ወድጃቸዋለሁና የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፥ የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ፤ አደላድላቸዋለሁም፤ እመልሳቸዋለሁ፤ እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፥ እኔም እሰማቸዋለሁና እንዳልጣልኋቸው ይሆናሉ። 7 የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል፤ ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በእግዚአብሔር ሐሤት ያደርጋል። 8 ተቤዥቼአቸዋለሁና በፉጨት ጠርቼ እሰበስባቸዋለሁ፤ ቀድሞም በዝተው እንደ ነበሩ ይበዛሉ። 9 በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳ በሩቅ አገር ሳሉ ያስቡኛል፥ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይኖራሉ፥ ይመለሱማል። 10 ከግብጽም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ ምድር አመጣቸዋለሁ፥ የሚበቃም ቦታ አይገኝላቸውም። 11 እርሱም በጭንቅ ባሕር ያልፋል፥ የባሕርንም ሞገድ ይመታል፥ የወንዙም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል፤ የአሦርም ትዕቢት ይዋረዳል፥ የግብጽም በትረ መንግሥት ይርቃል። 12 በአምላካቸው በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፥ በስሙም ይመካሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ዘካርያስ 11

1 ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ። 2 የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ ከበርቴዎችም ጠፍተዋልና ዋይ በል፤ እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና ዋይ በሉ። 3 የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸው ድምፅ ተሰምቶአል፤ የዮርዳኖስ ትዕቢት ተዋርዶአልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ተሰምቶአል። 4 አምላኬ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል። ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ። 5 የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ ራሳቸውንም እንደ በደለኞች አድርገው አይቈጥሩም፤ የሸጡአቸውም። ባለ ጠጋ ሆነናልና እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ፤ እረኞቻቸውም አይራሩላቸውም። 6 ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ በባልንጀራውና በንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላድናቸውም። 7 እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም ጠበቅሁ። 8 በአንድ ወርም ሦስቱን እረኞች አጠፋሁ፤ ነፍሴም ተሰቀቀቻቸው፥ ነፍሳቸውም ደግሞ እኔን ጠላች። 9 እኔም። እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀረውም እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሥጋ ይብላ አልሁ። 10 እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፈርስ ዘንድ ውበት የተባለችውን በትሬን ወስጄ ቈረጥሁ። 11 በዚያም ቀን ተሰበረች፤ እንዲሁም እኔን የተመለከቱ የመንጋው ችግረኞች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አወቁ። 12 እኔም። ደስ ብሎአችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፤ ያለዚያ ግን ተዉት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። 13 እግዚአብሔርም። የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት። 14 በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት እሰብር ዘንድ ማሰሪያ የተባለችውን ሁለተኛይቱን በትሬን ቈረጥሁ። 15 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ። 16 እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል። 17 መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች።

ዘካርያስ 12

1 ስለ እስራኤል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። 2 እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ለአሕዛብ ሁሉ የመንገድገድ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ ደግሞም ኢየሩሳሌም ስትከበብ በይሁዳ ላይ እንዲሁ ይሆናል። 3 በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ። 4 በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈረስን ሁሉ በድንጋጤ፥ ተቀማጭንም በእብድነት እመታለሁ፤ ዓይኖቼንም በይሁዳ ላይ እከፍታለሁ፥ የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ በዕውርነት እመታለሁ። 5 የይሁዳም አለቆች በልባቸው። በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ብርታት አለ ይላሉ። 6 በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በቀኝና በግራ በዙሪያ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፤ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ በኢየሩሳሌም ትኖራለች። 7 እግዚአብሔርም የዳዊት ቤት ክብርና የኢየሩሳሌም ሰዎች ክብር በይሁዳ ክብር ላይ እንዳይታበይ የይሁዳን ድንኳኖች አስቀድሞ ያድናል። 8 በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፤ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል። 9 በዚያም ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን አሕዛብ ሁሉ ለማጥፋት እጋደላለሁ። 10 በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፤ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል። 11 በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደ ነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል። 12 ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ 13 የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የሰሜኢ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ 14 የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።

ዘካርያስ 13

1 በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ከኃጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል። 2 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። 3 ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ። አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል፤ ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል። 4 በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፤ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም። 5 እርሱ ግን። ከታናሽነቴ ጀምሮ ባሪያ ሆኜ ነበርሁና ገበሬ ሰው ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም ይላል። 6 ሰውም። ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቍስል ምንድር ነው? ይለዋል። እርሱም። በወዳጆቼ ቤት የቈሰልሁት ቍስል ነው ይላል። 7 ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ። 8 በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል። 9 ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፤ እርሱም። እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል።

ዘካርያስ 14

1 እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፥ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ። 2 አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይነወራሉ፤ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማ አይጠፋም። 3 እግዚአብሔርም ይወጣል፥ በሰልፍም ቀን እንደ ተዋጋ ከእነዚያ አሕዛብ ጋር ይዋጋል። 4 በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፤ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል። 5 የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፤ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፤ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል። 6 በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ እንጂ ብርሃን አይሆንም። 7 አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል። 8 በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፤ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል። 9 እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል። 10 ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፤ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች። 11 ሰዎችም ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይሆንም፤ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትኖራለች። 12 እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዓይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። 13 በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ይሆናል፤ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፥ እጁም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል። 14 ይሁዳም ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ይዋጋል፤ በዙሪያም ያሉት የአሕዛብ ሁሉ ሀብት እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ልብስም ይሰበሰባል። 15 በፈረስና በበቅሎ፥ በግመልና በአህያ፥ በዚያም ሰፈር ባለ እንስሳ ሁሉ ላይ የሆነ ቸነፈር እንደዚያ ያለ ቸነፈር ይሆናል። 16 በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ በየዓመቱ ይወጣሉ። 17 ከምድርም ወገኖች ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለማይወጡ ለእነርሱ ዝናብ አይዘንብላቸውም። 18 የግብጽም ወገን ባይወጣ ወደዚያም ባይመጣ፥ እግዚአብሔር የዳስ በዓልን ያከብሩ ዘንድ የማይወጡትን አሕዛብ የሚቀሥፍበት ቸነፈር በእርሱ ላይ ይሆናል። 19 የግብጽ ቅጣት፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ የማይወጡት የአሕዛብ ሁሉ ቅጣት እንደዚህ ይሆናል። 20 በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ተብሎ ይጻፋል፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያሉ ምንቸቶች በመሠዊያው ፊት እንዳሉ ዳካዎች ይሆናሉ። 21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆናሉ፤ የሚሠዉትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ ከእነዚያም ወስደው ይቀቅሉባቸዋል፤ በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቤት ከነዓናዊው ከእንግዲህ ወዲያ አይገኝም።

ሚልክያ 1

1 በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። 2 ወድጃችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተ ግን። በምን ወደድኸን? ብላችኋል። ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ያዕቆብንም ወደድሁ፥ ዔሳውንም ጠላሁ፤ 3 ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው። 4 ኤዶምያስ። እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ። የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል። 5 ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም። እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን ትላላችሁ። 6 እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተም። ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው? ብላችኋል። 7 በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ። እናንተም። ያረከስንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው በማለታችሁ ነው። 8 ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9 አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 10 በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 11 ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 12 እናንተ ግን። የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፤ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት። 13 እናንተ። እነሆ፥ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቍርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን? ይላል እግዚአብሔር። 14 እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን።

ሚልክያ 2

1 አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፥ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው። 2 ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፤ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ። 3 እነሆ፥ ክንዳችሁን እገሥጻለሁ፥ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ ከእርሱም ጋር በአንድነት ትወሰዳላችሁ። 4 ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 5 ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፤ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፤ እርሱም ፈራኝ፥ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ። 6 የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፥ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፤ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ። 7 ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል። 8 እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፤ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 9 ስለዚህ መንገዴን እንዳልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ። 10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳንዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን? 11 እግዚአብሔር የወደደውን መቅደስ ይሁዳ አርክሶአልና፥ የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት አድርጎ አግብቶአልና ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኵሰት ተሠርቶአል። 12 ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ እግዚአብሔር የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል። 13 ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፤ እግዚአብሔር ቍርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኀዘንም ትከድናላችሁ። 14 እናንተም። ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው። 15 እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። 16 መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ። 17 እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችኋል። እናንተም። ያታከትነው በምንድር ነው? ብላችኋል። ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፤ ወይስ። የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው።

ሚልክያ 3

1 እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 2 ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? 3 እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ። 4 እግዚአብሔርም እንደ ዱሮው ዘመንና እንደ ቀደሙት ዓመታት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ቍርባን ደስ ይለዋል። 5 ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ በሐሰትም በሚምሉ፥ የምንደኛውን ደመወዝ በሚከለክሉ፥ መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 6 እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም። 7 ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምር ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፥ እርስዋንም አልጠበቃችሁም። ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ግን። የምንመለሰው በምንድር ነው? ብላችኋል። 8 ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል። በአሥራትና በበኵራት ነው። 9 እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ። 10 በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 11 ስለ እናንተ ነቀዙን እገሥጻለሁ፥ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁም ያለው ወይን ፍሬውን አያረግፍም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 12 የተድላ ምድር ትሆናላችሁና አሕዛብ ሁሉ ብፁዓን ብለው ይጠሩአችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 13 ቃላችሁ በእኔ ላይ ድፍረት ሆኖአል፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ግን። በአንተ ላይ ደፍረን የተናገርነው በምንድር ነው? ብላችኋል። 14 እናንተም። እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ ትእዛዙንስ በመጠበቅ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ፊት ኀዘንተኞች ሆነን በመሄድ ምን ይረባናል? 15 አሁንም የሚታበዩትን ሰዎች ብፁዓን ብለን እንጠራቸዋለን፤ ክፉንም የሚሠሩ ጸንተዋል እግዚአብሔርንም ይፈታተናሉ፥ ያመልጣሉም ብላችኋል። 16 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ። 17 እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ሰውም የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚምር፥ እንዲሁ እምራቸዋለሁ። 18 ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፥ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ።

ሚልክያ 4

1 እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 2 ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ። 3 በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 4 ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ አስቡ። 5 እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። 6 መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።

The New Testament of our Lord and Saviour Jesus Christ

የማቴዎስ 1

1 የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ። 2 አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤ 3 ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤ 4 ኤስሮምም አራምን ወለደ፤ አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ 5 ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤ 6 እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። 7 ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤ 8 አሣፍም ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥም ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራምም ዖዝያንን ወለደ፤ 9 ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታምም አካዝን ወለደ፤ 10 አካዝም ሕዝቅያስን ወለደ፤ ሕዝቅያስም ምናሴን ወለደ፤ ምናሴም አሞፅን ወለደ፤ 11 አሞፅም ኢዮስያስን ወለደ፤ ኢዮስያስም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ። 12 ከባቢሎንም ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤ 13 ዘሩባቤልም አብዩድን ወለደ፤ አብዩድም ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዛርን ወለደ፤ 14 አዛርም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤ 15 ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማታንን ወለደ፤ ማታንም ያዕቆብን ወለደ፤ 16 ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። 17 እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። 18 የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። 19 እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። 20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። 21 ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። 22 በነቢይ ከጌታ ዘንድ። 23 እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። 24 ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ 25 የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።

የማቴዎስ 2

1-2 ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3 ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ 4 የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። 5-6 እነርሱም። አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። 7 ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ 8 ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው። 9 እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። 10 ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። 11 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። 12 ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። 13 እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። 14-15 እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። 16 ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። 17-18 ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ። 19 ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ። 20 የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። 21 እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። 22 በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ 23 በነቢያት። ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።

የማቴዎስ 3

1-2 በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። 3 በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና። 4 ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ። 5 ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ 6 ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። 7 ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ 9 በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። 10 አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 11 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ 12 መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። 13 ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። 14 ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። 15 ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። 16 ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ 17 እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።

የማቴዎስ 4

1 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥ 2 አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። 3 ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። 4 እርሱም መልሶ። ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። 5 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ። 6 መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። 7 ኢየሱስም። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። 8 ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ። 9 ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። 10 ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። 11 ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር። 12 ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። 13 ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። 14-16 በነቢዩም በኢሳይያስ። የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው 17 የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር። 18 በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 19 እርሱም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። 20 ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 21 ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። 22 እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። 23 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። 24 ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም። 25 ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

የማቴዎስ 5

1 ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ 2 አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ። 3 በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። 4 የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። 5 የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። 6 ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። 7 የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። 8 ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። 9 የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። 10 ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። 11 ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። 12 ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። 13 እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። 14 እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። 15 መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። 16 መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። 17 እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። 18 እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። 19 እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። 20 እላችኋለሁና። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። 21 ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። 23 እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ 24 በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። 25 አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ 26 እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም። 27 አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 28 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። 29 ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። 30 ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። 31 ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። 32 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። 33 ደግሞ ለቀደሙት። በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34 እኔ ግን እላችኋለሁ። ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ 35 በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ 36 በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። 37 ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። 38 ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 39 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ 40 እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ 41 ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። 43 ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 44-45 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። 46 የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? 47 ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? 48 እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።

የማቴዎስ 6

1 ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። 2 እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 3-4 አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። 5 ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 6 አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። 7 አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ። 8 ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና። 9 እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ 10 ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ 11 የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ 12 እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ 13 ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን። 14 ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ 15 ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። 16 ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። 17-18 አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። 19 ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ 20 ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ 21 መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። 22 የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ 23 ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! 24 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። 25 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? 26 ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? 27 ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? 28 ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ 29 አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። 30 እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? 31 እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ 32 ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። 33 ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። 34 ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።

የማቴዎስ 7

1-2 እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። 3 በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? 4 ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። 5 አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። 6 በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። 7 ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። 8 የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። 9 ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? 10 ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? 11 እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? 12 እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። 13 በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ 14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። 15 የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። 16 ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? 17 እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። 18 መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። 19 መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 20 ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። 21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። 22 በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። 23 የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። 24 ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። 25 ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። 26 ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። 27 ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። 28 ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን 29 እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።

የማቴዎስ 8

1 ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 2 እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት። 3 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። 4 ኢየሱስም። ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። 5 ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ 6 ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። 7 ኢየሱስም። እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። 8 የመቶ አለቃውም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። 9 እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። 10 ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። 11 እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ 12 የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 13 ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። 14 ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ 15 እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። 16-17 በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ። 18 ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ። 19 አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። 20 ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። 21 ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው። 22 ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው። 23 ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት። 24 እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። 25 ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት። 26 እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። 27 ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ። 28 ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ። 29 እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ። 30 ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር። 31 አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው። 32 እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ። 33 እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ። 34 እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።

የማቴዎስ 9

1 በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። 2 እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። 3 እነሆም፥ ከጻፎቹ አንዳንዱ በልባቸው። ይህስ ይሳደባል አሉ። 4 ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ። ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? 5 ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 6 ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን። ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። 7 ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። 8 ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፥ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ። 9 ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። 10 በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። 11 ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን። መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው። 12 ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ 13 ነገር ግን ሄዳችሁ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው። 14 በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። 15 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ። 16 በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 17 በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። 18 ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኰንን መጥቶ። ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት። 19 ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። 20 እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ 21 በልብዋ። ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። 22 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና። ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። 23 ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ። 24 ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት። 25 ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች። 26 ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። 27 ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት። 28 ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም። ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት። 29 በዚያን ጊዜ። እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። 30 ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ። 31 ኢየሱስም። ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። 32 እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። 33 ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም። እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ። 34 ፈሪሳውያን ግን። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። 35 ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። 36 ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። 37 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ 38 እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።

የማቴዎስ 10

1 አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። 2 የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥ 3 ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥ 4 ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። 5 እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ 6 ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ። 7 ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። 8 ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። 9 ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ 10 ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና። 11 በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ። 12 ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ 13 ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። 14 ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። 15 እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል። 16 እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። 17 ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ 18 ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። 19 አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ 20 በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና። 21 ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል። 22 በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 23 በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም። 24 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም። 25 ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው! 26 እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና። 27 በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። 28 ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። 29 ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። 30 የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል። 31 እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። 32 ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ 33 በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። 34 በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። 35 ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ 36 ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። 37 ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ 38 መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። 39 ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል። 40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። 41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። 42 ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።

የማቴዎስ 11

1 ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። 2 ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና። 3 የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው። 4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ 5 ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ 6 ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው። 7 እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? 8 ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። 9 ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። 10 እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ 11 ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12 ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። 13 ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ 14 ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። 15 የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። 16 ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። 17 እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። 18 ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም። ጋኔን አለበት አሉት። 19 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። 20 በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ። 21 ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። 22 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 23 አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። 24 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። 25 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ 26 አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። 27 ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። 28 እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። 29 ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ 30 ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።

የማቴዎስ 12

1 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። 2 ፈሪሳውያንም አይተው። እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት። 3-4 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? 5 ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? 6 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 7 ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር። 8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና። 9 ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። 10 እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። 11 እርሱ ግን። ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? 12 እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። 13 ከዚያም በኋላ ሰውየውን። እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። 14 ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። 15 ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ 16-17 በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል። 18 እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። 19 አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። 20 ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። 21 አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ። 22 ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። 23 ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና። እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ። 24 ፈሪሳውያን ግን ሰምተው። ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ። 25 ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። 26 ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? 27 እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 28 እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። 29 ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። 30 ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። 31 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። 32 በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም። 33 ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። 34 እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። 35 መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። 36 እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ 37 ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ። 38 በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና። መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ። 39 እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። 40 ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። 41 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 42 ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። 43 ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም። 44 በዚያን ጊዜም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። 45 ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል። 46 ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። 47 አንዱም። እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው። 48 እርሱ ግን ለነገረው መልሶ። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው። 49 እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ። እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ 50 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።

የማቴዎስ 13

1 በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ 2 እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። 3 በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። 4 እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት። 5 ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥ 6 ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7 ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። 8 ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9 የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። 10 ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። 11 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12 ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13 ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። 14 መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። 15 በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። 16 የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። 17 እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። 18 እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። 19 የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። 20 በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ 21 ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። 22 በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። 23 በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። 24 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። 25 ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። 26 ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። 27 የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። 28 እርሱም። ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። 29 እርሱ ግን። እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። 30 ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። 31 ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32 እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች። 33 ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች። 34-35 ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም። በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። 36 በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። 37 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ 38 መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ 39 እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። 40 እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። 41 የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ 42 ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 43 በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። 44 ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። 45 ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ 46 ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። 47 ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ 48 በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። 49 በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ 50 በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 51 ኢየሱስም። ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው አዎን አሉት። 52 እርሱም። ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል አላቸው። 53 ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። 54 ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? 55 ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? 56 እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም። 57 ኢየሱስ ግን። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። 58 በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።

የማቴዎስ 14

1 በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥ 2 ለሎሌዎቹም። ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። 3 ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ 4 ዮሐንስ። እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና። 5 ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው። 6 ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ 7 ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። 8 እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። 9 ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ 10 ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። 11 ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው። 12 ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። 13 ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። 14 ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። 15 በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። 16 ኢየሱስም። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው። 17 እነርሱም። ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት። 18 እርሱም። እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው። 19 ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። 20 ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። 21 ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። 22 ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 23 ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ። 24 ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር። 25 ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ። 26 ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ። ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ። 27 ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። 28 ጴጥሮስም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው። 29 እርሱም። ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። 30 ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። 31 ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። 32 ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። 33 በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት። 34 ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። 35 የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 36 የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

የማቴዎስ 15

1 በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። 2 ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት። 3 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ? 4 እግዚአብሔር። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤ 5 እናንተ ግን። አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥ 6 አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። 7 እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ። 8 ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ 9 የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ። 10 ሕዝቡንም ጠርቶ። ስሙ አስተውሉም፤ 11 ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው። 12 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው። ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት። 13 እርሱ ግን መልሶ። የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14 ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ። 15 ጴጥሮስም መልሶ። ምሳሌውን ተርጕምልን አለው። 16 ኢየሱስም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? 17 ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? 18 ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። 19 ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። 20 ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም። 21 ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። 22 እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። 23 እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። 24 እርሱም መልሶ። ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። 25 እርስዋ ግን መጥታ። ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። 26 እርሱ ግን መልሶ። የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። 27 እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። 28 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ። አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። 29 ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። 30 ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ 31 ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። 32 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው። 33 ደቀ መዛሙርቱም። ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት። 34 ኢየሱስም። ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም። ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት። 35 ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ 36 ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። 37 ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ። 38 የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። 39 ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።

የማቴዎስ 16

1 ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። 2 እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። በመሸ ጊዜ። ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ 3 ማለዳም። ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? 4 ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ። 5 ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። 6 ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። 7 እነርሱም። እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 8 ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? 9 ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? 10 ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? 11 ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? 12 እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ። 13 ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። 14 እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። 15 እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። 16 ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። 17 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። 18 እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። 19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። 20 ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። 21 ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር። 22 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። 23 እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። 24 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 25 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። 26 ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? 27 የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። 28 እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።

የማቴዎስ 17

1 ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። 2 በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። 3 እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 4 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። 5 እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። 6 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። 7 ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው። 8 ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። 9 ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ። የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው። 10 ደቀ መዛሙርቱም። እንግዲህ ጻፎች። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። 11 ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ 12 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው። 13 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ። 14 ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ። ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤ 15 ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና። 16 ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው። 17 ኢየሱስም መልሶ። የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። 18 ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ። 19 ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት። 20 ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። 21 ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው። 22 በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥ 23 በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ። 24 ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና። መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር*ፍ1* አይገብርምን? አሉት። 25 አዎን ይገብራል አለ። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ። ስምዖን ሆይ፥ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? አለው። 26 ጴጥሮስም። ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ። እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው። 27 ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር*ፍ2* ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው። ፍ1 አንድ ዲናር አምሳ የኢት@ ብር ሳንቲም ያህል ነው። ፍ2 እስታቴር ሁለት ብር ያህል ነው።

የማቴዎስ 18

1 በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት። 2 ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ 3 እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። 4 እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። 5 እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ 6 በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። 7 ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት። 8 እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል። 9 ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 10 ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና። 11 የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና። 12 ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን? 13 ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል። 14 እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም። 15 ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ 16 ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ 17 እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። 18 እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። 19 ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። 20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። 21 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። 22 ኢየሱስ እንዲህ አለው። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። 23 ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። 24 መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። 25 የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። 26 ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና። ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። 27 የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። 28 ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና። ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። 29 ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ። ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው። 30 እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። 31 ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። 32 ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ። አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ 33 እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። 34 ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። 35 ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።

የማቴዎስ 19

1 ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ። 2 ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው። 3 ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። 4 እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ 5 አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? 6 ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። 7 እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። 8 እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። 9 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። 10 ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። 11 እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ 12 በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው። 13 በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው። 14 ነገር ግን ኢየሱስ። ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤ 15 እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። 16 እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። 17 እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው። 18 እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ 19 አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። 20 ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው። 21 ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። 22 ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። 23 ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። 24 ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። 25 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። 26 ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው። 27 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። 28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። 29 ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። 30 ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

የማቴዎስ 20

1 መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና። 2 ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው። 3 በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፥ 4 እነዚያንም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። 5 ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6 በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና። ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው። 7 የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ አላቸው። 8 በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን። ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው። 9 በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10 ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 11-12 ተቀብለውም። እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጐራጐሩ። 13 እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው። ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? 14 ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? 15 ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን? 16 እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና። 17 ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ። 18 እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ 19 ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። 20 በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች። 21 እርሱም። ምን ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም። እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው። 22 ኢየሱስ ግን መልሶ። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አለ። እንችላለን አሉት። 23 እርሱም። ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው። 24 አሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቈጡ። 25 ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። 26 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ 27 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ 28 እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። 29 ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 30 እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ። 31 ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ። 32 ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ። 33 ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት። 34 ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፥ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።

የማቴዎስ 21

1 ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥ 2 እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 3 ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። 4-5 ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። 6 ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ 7 አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም። 8 ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። 9 የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። 10 ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። 11 ሕዝቡም። ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ። 12 ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና። 13 ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። 14 በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። 15 ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው። 16 እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም። እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። 17 ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ። 18 በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። 19 በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። 20 ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። 21 ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ 22 አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው። 23 ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። 24 ኢየሱስም መልሶ። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ 25 የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 26 ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። 27 ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። 28 ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። 29 እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። 30 ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። 31 ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። 32 ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። 33 ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 34 የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። 35 ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። 36 ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። 37 በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። 38 ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። 39 ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። 40 እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? 41 እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። 42 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? 43 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። 44 በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል። 45 የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ 46 ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።

የማቴዎስ 22

1 ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። 2 መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። 3 የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም። 4 ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ። የታደሙትን። እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ። 5 እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ 6 የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም። 7 ንጉሡም ተቈጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። 8 በዚያን ጊዜ ባሮቹን። ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ 9 እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ። 10 እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። 11 ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና። ወዳጄ ሆይ፥ 12 የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ። 13 በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን። እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ። 14 የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና። 15 ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ። 16 ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ 17 እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። 18 ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? 19 የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። 20 እርሱም። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው። 21 የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። 22 ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ። 23 በዚያን ቀን። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥ 24 እንዲህም ብለው ጠየቁት። መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ። 25 ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤ 26 እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ። 27 ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች። 28 ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ። 30 በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም። 31-32 ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን። እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። 33 ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ። 34 ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። 35 ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው። 36 መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። 37 ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። 38 ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 39 ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። 40 በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። 41-42 ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ። ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። 43-44 እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? 45 ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። 46 አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

የማቴዎስ 23

1 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው። 2 ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። 3 ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። 4 ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። 5 ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ 6 በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ 7 በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። 8 እናንተ ግን። መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። 9 አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ። 10 ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። 11 ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። 12 ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል። 13 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። 14 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። 15 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ። 16 እናንተ። ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። 17 እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? 18 ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። 19 እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? 20 እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ 21 በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ 22 በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል። 23 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር። 24 እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ። 25 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። 26 አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። 27 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። 28 እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። 29 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና። 30 በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ። 31 እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። 32 እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ። 33 እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? 34 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ 35 ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። 36 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል። 37 ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። 38 እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። 39 እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።

የማቴዎስ 24

1 ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። 2 እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። 3 እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። 4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 5 ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 6 ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። 7 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ 8 እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9 በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 10 በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ 11 ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ 12 ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። 13 እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 14 ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። 15 እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ 16 በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ 17 በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ 18 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 19 በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 20 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 21 በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። 22 እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። 23 በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 24 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። 25 እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። 26 እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ 27 መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ 28 በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። 29 ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ 30 የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ 31 መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ። 32 ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ 33 እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ። 34 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። 36 ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። 37 የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። 38 በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ 39 የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። 40 በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ 41 ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች። 42 ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። 43 ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። 44 ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። 45 እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? 46 ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ 47 እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48 ያ ክፉ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ 49 ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ 50 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ 51 ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

የማቴዎስ 25

1 በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። 2 ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። 3 ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ 4 ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። 5 ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። 6 እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። 7 በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። 8 ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። 9 ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። 10 ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። 11 በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። 12 እርሱ ግን መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። 13 ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። 14 ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ 15 ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። 16 አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ 17 እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። 18 አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። 19 ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። 20 አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። 21 ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። 22 ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። 23 ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። 24 አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ 25 ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። 26 ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? 27 ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። 28 ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ 29 ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 30 የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 31 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ 32 አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ 33 በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። 34 ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። 35 ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ 36 ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። 37 ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? 38 እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? 39 ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? 40 ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። 41 በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። 42 ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ 43 ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። 44 እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። 45 ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። 46 እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።

የማቴዎስ 26

1 ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥ 2 ለደቀ መዛሙርቱ። ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ። 3 በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ 4 ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ 5 ነገር ግን። በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ። 6 ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ 7 አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 8 ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና። ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? 9 ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ። 10 ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው። መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? 11 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ 12 እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። 13 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል። 14 በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ። 15 ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። 16 ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። 17 በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። 18 እርሱም። ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ። መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። 19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። 20 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። 21 ሲበሉም። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። 22 እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። 23 እርሱም መልሶ። ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። 24 የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። 25 አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ። መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። 26 ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። 27 ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ 28 ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። 29 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። 30 መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። 31 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ 32 ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። 33 ጴጥሮስም መልሶ። ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። 34 ኢየሱስ። እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። 35 ጴጥሮስ። ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። 36 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም። ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። 37 ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። 38 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። 39 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። 40 ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን። እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? 41 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። 42 ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና። አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። 43 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። 44 ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። 45 ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 46 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። 47 ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። 48 አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 49 ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው። 50 ኢየሱስም። ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ? አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት። 51 እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። 52 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። 53 ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? 54 እንዲህ ከሆነስ። እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ? 55 በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። 56 ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። 57 ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። 58 ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። 59 የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤ 60 ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም። 61 በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ። 62 ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ። እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን? አለው። 63 ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። 64 ኢየሱስም። አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው። 65 በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። 66 እነርሱም። ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ። 67 በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው? 68 ትንቢት ተናገርልን አሉ። 69 ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። 70 እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። 71 ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት። ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች። 72 ዳግመኛም ሲምል። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ። 73 ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አሉት። 74 በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። 75 ጴጥሮስም። ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

የማቴዎስ 27

1 ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ 2 አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። 3 በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ። 4 ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። 5 ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። 6 የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ። 7 ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። 8 ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ። 9 በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ 10 ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ። 11 ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው። 12 የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። 13 በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። 14 ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። 15 በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። 16 በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። 17 እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ 18 በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። 19 እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። 20 የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። 21 ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ። 22 ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ። 23 ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ። 24 ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። 25 ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። 26 በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። 27 በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ። 28 ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥ 29 ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤ 30 ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት። 31 ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት። 32 ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። 33 ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥ 34 በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም። 35 ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥ 36 በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37 ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ። 38 በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ። 39 የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። 40 ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት። 41 እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ። 42 ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። 43 በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። 44 ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። 45 ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 46 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 47 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ። 48 ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው። 49 ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ። 50 ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። 51 እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ 52 መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤ 53 ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ። 54 የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ። 55 ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ 56 ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ። 57 በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ 58 ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 59 ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ 60 ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። 61 መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ። 62 በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። 63 ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። 64 እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። 65 ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። 66 እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።

የማቴዎስ 28

1 በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 2 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 3 መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4 ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። 5 መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ 6 እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7 ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። 8 እነሆም፥ ነገርኋችሁ። በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። 9 እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 10 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው። 11 ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ። 12 ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። 13 እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ። 14 ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው። 15 እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል። 16 አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ 17 ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ። 18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። 19-20 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።

የማርቆስ 1

1 የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ። 2-3 እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ 4 ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። 5 የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፥ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። 6 ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሀ ማርም ይበላ ነበር። 7 ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። 8 እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር። 9 በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። 10 ወዲያውም ከውኃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና። የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ 11 በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ። 12 ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው። 13 በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ ከአራዊትም ጋር ነበረ፥ መላእክቱም አገለገሉት። 14-15 ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና። ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ። 16 በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 17 ኢየሱስም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። 18 ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 19 ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። 20 ወዲያውም ጠራቸው አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ። 21 ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። 22 እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። 23 በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ 24 እርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። 25 ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። 26 ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። 27 ሁሉም። ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። 28 ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። 29 ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። 30 የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። 31 ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው። 32 ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 33 ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። 34 በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም። 35 ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። 36 ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፥ 37 ባገኙትም ጊዜ። ሁሉ ይፈልጉሃል አሉት። 38 እርሱም። በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው። 39 በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ። 40 ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና። ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። 41 ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። 42 በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። 43 በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ 44 ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። 45 እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

የማርቆስ 2

1 ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። 2 በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። 3 አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። 4 ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። 6 ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም። ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? 7 ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ። 8 ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው። በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? 9 ሽባውን። ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 10 ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ 11 ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። 12 ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና። እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ። 13 ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14 ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። 15 በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር። 16 ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ። 17 ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። 18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም። የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። 19 ኢየሱስም አላቸው። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም። 20 ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ። 21 በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 22 በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። 23 በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24 ፈሪሳውያንም። እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት። 25 እርሱም። ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ 26 ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። 27 ደግሞ። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ 28 እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።

የማርቆስ 3

1 ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ 2 ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 3 እጁ የሰለለችውንም ሰው። ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። 4 በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። 5 ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም። እጅህን ዘርጋ አለው። 6 ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት። 7 ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ 8 እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። 9 ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10 ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። 11 ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ። 12 እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። 13 ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። 14 ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ 15 ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ 16 ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ 17 የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ 18 እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ 19 አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። 20 ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21 ዘመዶቹም ሰምተው። አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። 22 ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም። ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። 23 እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? 24 መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25 ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26 ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27 ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። 28 እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29 በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። 30 ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። 31 እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32 ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና። እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። 33 መልሶም። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። 34 በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና። እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35 የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

የማርቆስ 4

1 ደግሞም በባሕር ዳር ሊያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በታንኳ ገብቶ በባሕር ላይ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕር ዳር በምድር ላይ ነበሩ። 2 በምሳሌም ብዙ ያስተምራቸው ነበር፥ በትምህርቱም አላቸው። ስሙ። 3-4 እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። 5 ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀና ጥልቅ መሬት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6 ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7 ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው፥ ፍሬም አልሰጠም። 8 ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀና ወጥቶ አድጎ ፍሬ ሰጠ፥ አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ አፈራ። 9 የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ አለ። 10 ብቻውንም በሆነ ጊዜ፥ በዙሪያው የነበሩት ከአሥራ ሁለቱ ጋር ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 11-12 እንዲህም አላቸው። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን፥ አይተው እንዲያዩ እንዳይመለከቱም፥ ሰምተውም እንዲሰሙ እንዳያስተውሉም፥ እንዳይመለሱ ኃጢአታቸውም እንዳይሰረይላቸው ነገር ሁሉ በምሳሌ ይሆንባቸዋል። 13 አላቸውም። ይህን ምሳሌ አታውቁምን? እንዴትስ ምሳሌዎቹን ሁሉ ታውቃላችሁ? 14 ዘሪው ቃሉን ይዘራል። ቃልም በተዘራበት በመንገድ ዳር የሆኑት እነዚህ ናቸው፥ 15 በሰሙት ጊዜም ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል ይወስዳል። 16 እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ 17 ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። 18 በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ 19 የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። 20 በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው። 21 እንዲህም አላቸው። መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? 22 እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም። 23 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። 24 አላቸውም። ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። 25 ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 26 እርሱም አለ። በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ 27 እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። 28 ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። 29 ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል። 30 እርሱም አለ። የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? 31 እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥ 32 የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች። 33 መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥ 34 ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር። 35 በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ። ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው። 36 ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 37 ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። 38 እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም። መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። 39 ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው ባሕሩንም። ዝም በል፥ ፀጥ በል አለው። ነፋሱም ተወ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 40 እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም? አላቸው። 41 እጅግም ፈሩና። እንግዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? ተባባሉ።

የማርቆስ 5

1 ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። 2 ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ 3 እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ 4 ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ 5 ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። 6 ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ 7 በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ 8 አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። 9 ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ 10 ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። 11 በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና። 12 ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። 13 ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። ፍ1 ሌጌዎን ማለት ጭፍራ ማለት ነው። 14 እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። 15 ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። 16 ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። 17 ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። 18 ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። 19 ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን። ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። 20 ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ። 21 ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። 22 ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና። 23 ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። 24 ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። 25 ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ 26 ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ 27 የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች። 28 ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። 29 ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። 30 ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ። ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። 31 ደቀ መዛሙርቱም። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ። ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። 32 ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። 33 ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 34 እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት። 35 እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት። ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። 36 ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ። እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። 37 ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38 ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ 39 ገብቶም። ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። 40 በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። 41 የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ። ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። 42 ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። 43 ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው። የምትበላውን ስጡአት አላቸው።

የማርቆስ 6

1 ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2 ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና። እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? 3 ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። 4 ኢየሱስም። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። 5 በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። 6 ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። 7 አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ 8 ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። 9 በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። 10 በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። 11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። 12 ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ 13 ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው። 14 ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ። መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። 15 ሌሎችም። ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም። ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። 16 ሄሮድስ ግን ሰምቶ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ። 17 ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ 18 ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። 19 ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ 20 ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ 21 በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና 22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ 23 የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። 24 ወጥታም ለእናትዋ። ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። 25 ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። 26 ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። 27 ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ 28 ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። 29 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት። 30 ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31 እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። 32 በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። 33 ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። 34 ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። 35 በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ 36 የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። 37 እርሱ ግን መልሶ። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። 38 እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ። አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። 39 ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። 40 መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። 41 አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ 42 ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43 ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ። 44 እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ። 45 ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 46 ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 47 በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። 48 ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። 49 እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ 50 ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው። 51 ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ 52 ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር። 53 ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ። 54 ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት 55 በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር። 56 በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

የማርቆስ 7

1 ፈሪሳውያንና ከጻፎች ወገን ከኢየሩሳሌም የመጡትም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 2 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንድ በርኵስ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ። 3 ፈሪሳውያንና አይሁድም ሁሉ የሽማግሎችን ወግ ሲጠብቁ እጃቸውን ደኅና አድርገው ሳይታጠቡ አይበሉምና፥ 4 ከገበያም ተመልሰው ካልታጠቡ አይበሉም፥ ጽዋንም ማድጋንም የናስ ዕቃንም አልጋንም እንደ ማጠብ ሌላ ነገር ሊጠብቁት የተቀበሉት ብዙ አለ። 5 ፈሪሳውያንም ጻፎችም። ደቀ መዛሙርትህ እንደ ሽማግሌዎች ወግ ስለ ምን አይሄዱም? ነገር ግን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ ብለው ጠየቁት። 6 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ኢሳይያስ ስለ እናንተ ስለ ግብዞች። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ 7 የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። 8 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ ጽዋን ማድጋንም እንደ ማጠብ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ፥ ይህንም የመሰለ ብዙ ሌላ ነገር ታደርጋላችሁ። 9 እንዲህም አላቸው። ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። 10 ሙሴ። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና። 11 እናንተ ግን ትላላችሁ። ሰው አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት ነገር ሁሉ ቍርባን ማለት መባ ነው ቢል፥ 12 ለአባቱና ለእናቱ ምንም እንኳ ሊያደርግ ወደ ፊት አትፈቅዱለትም፤ 13 ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። 14 ደግሞም ሕዝቡን ጠርቶ። ሁላችሁ እኔን ስሙ አስተውሉም። 15 ከሰው የሚወጡት ሰውን የሚያረክሱ ናቸው እንጂ ከሰው ውጭ የሚገባውስ ሊያረክሰው የሚችል ምንም የለም። 16 የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ አላቸው። 17 ከሕዝቡ ዘንድ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ምሳሌውን ጠየቁት። 18 እርሱም። እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን? 19 ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው። 20 እርሱም አለ። ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። 21 ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ 22 ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ 23 ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። 24 ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ 25 ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች 26 ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። 27 ኢየሱስ ግን። ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምናአላት። 28 እርስዋም መልሳ። አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። 29 እርሱም። ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። 30 ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። 31 ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32 ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥ 33 እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ 34 ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና። ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። 35 ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ። 36 ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። 37 ያለ መጠንም ተገረሙና። ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።

የማርቆስ 8

1 በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። 2 ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ 3 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው። 4 ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት። 5 እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት። 6 ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ። 7 ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። 8 በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። 9 የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። 10 አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። 11 ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። 12 በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። 13 ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። 14 እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። 15 እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። 16 እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። 17 ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? 18 ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? 19 አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት። 20 ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት። 21 ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው። 22 ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። 23 ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው። 24 አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። 25 ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። 26 ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። 27 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። 28 እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። 29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። 30 ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። 32 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። 33 እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው። 34 ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። 36 ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? 37 ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? 38 በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።

የማርቆስ 9

1 እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ አላቸው። 2 ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤ 3 አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ። 4 ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር። 5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው። 6 እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር። 7 ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። 8 ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። 9 ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው። 10 ቃሉንም ይዘው። ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። 11 እነርሱም። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። 12 እርሱም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም። 13 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው። 14 ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ። 15 ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት። 16 ጻፎችንም። ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 17 ከሕዝቡ አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ 18 በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። 19 እርሱም መልሶ። የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። 20 ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። 21 አባቱንም። ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22 ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። 23 ኢየሱስም። ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። 24 ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ። አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። 25 ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና። አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። 26 ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም። ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። 27 ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም። 28 ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት። 29 ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው። 30-31 ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤ ለእነርሱም። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል ይላቸው ነበር። 32 እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። 33 ወደ ቅፍርናሆምም መጣ። በቤትም ሆኖ። በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። 34 እነርሱ ግን በመንገድ። ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ። 35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ። ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው። 36 ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም። 37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው። 38 ዮሐንስ መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ 39 ስለማይከተለንም ከለከልነው አለው። ኢየሱስ ግን አለ። በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤ 40 የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና። 41 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ። 42 በእኔም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። 43-44 እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል። 45-46 እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። 47-48 ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል። 49 ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል። 50 ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።

የማርቆስ 10

1 ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር። 2 ፈሪሳውያንም ቀርበው። ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። 3 እርሱ ግን መልሶ። ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው። 4 እነርሱም። ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ። 5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። 6 ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ 7 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ 8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። 9 እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። 10 በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። 11 እርሱም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ 12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው። 13 እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። 14 ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና። ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። 15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። 16 አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው። 17 እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 18 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 19 ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 20 እርሱም መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። 21 ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። 22 ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። 23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። 24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ። ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። 25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። 26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው። እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። 27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ። 28 ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ 30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። 31 ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ። 32 ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር። 33 እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥ 34 ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። 35 የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው። መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት። 36 እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው። 37 እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት። 38 ኢየሱስ ግን። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው። 39 እነርሱም። እንችላለን አሉት። ኢየሱስም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40 በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው። 41 አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር። 42 ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። 43 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ 44 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45 እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። 46 ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 47 የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ። የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር። 48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 49 ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም። አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት። 50 እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ። 51 ኢየሱስም መልሶ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም። መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው። 52 ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።

የማርቆስ 11

1 ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ። 2 በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። 3 ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው። 4 ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም። 5 በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው። 6 እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም። 7 ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም። 8 ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 9 የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ 10 በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። 11 ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ። 12 በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። 13 ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14 መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። 15 ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ 16 ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። 17 አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። 18 የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። 19 ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። 20 ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። 21 ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። 22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ። 23 እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። 24 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። 25 ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። 26 እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። 27 ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው። 28 እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። 29 ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ። 30 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው። 31 እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 32 ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ። 33 ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።

የማርቆስ 12

1 በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 2 በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 3 ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 4 ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት። 5 ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ። 6 የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 7 እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ። 8 ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 9 እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። 10-11 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን? 12 ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ። 13 በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14 መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት። 15 እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው። 16 እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት። 17 ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ። 18 ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት። 19 መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 20 ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 21 ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22 ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 23 ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? 24 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 25 ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም። 26 ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 27 የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ። 28 ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ። ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። 29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ 30 አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 31 ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። 32 ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 33 በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። 34 ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። 35 ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ። ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? 36 ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። 37 ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። 38-39 ሲያስተምርም እንዲህ አለ። ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 40 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። 41 ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 42 አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 43 ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 44 ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

የማርቆስ 13

1 እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው። 2 ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው። 3 በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም። 4 ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት። 5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። 6 ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ። 7 ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው። 8 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9 እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 10 አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል። 11 ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 12 ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤ 13 በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። 14 ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ 15 በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ 16 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። 17 በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። 18 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 19 በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። 20 ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። 21 በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ 22 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። 23 እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። 24 በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ 25 ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። 26 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 27 በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። 28 ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ 29 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። 30 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። 32 ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። 33 ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። 34 ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። 35 እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና 36 ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። 37 ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።

የማርቆስ 14

1 ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር። 2 የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና። 3 እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። 4 አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው? 5 ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት። 6 ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች። 7 ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም። 8 የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። 9 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል። 10 ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11 ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። 12 ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት። 13 ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤ 14 ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት። 15 እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ 16 በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ። 17 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 18 ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 19 እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። 20 እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው። 21 የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው። 22 ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። 23 ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። 24 እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። 25 እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው። 26 መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። 27 ኢየሱስም። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። 28 ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። 29 ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። 30 ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። 31 እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። 32 ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም። ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። 33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና። 34 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። 35 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና። 36 አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። 37 መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? 38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። 39 ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። 40 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። 41 ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። 42 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። 43 ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ። 44 አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። 45 መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤ 46 እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት። 47 በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ። 48 ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን? 49 በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው። 50 ሁሉም ትተውት ሸሹ። 51 ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ 52 ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ። 53 ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። 54 ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 55 የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ 56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። 57-58 ሰዎችም ተነሥተው። እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። 59 ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። 60 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። 61 እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው። 62 ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ። 63 ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል? 64 ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት። 65 አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት። 66 ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥ 67 ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። 68 እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ። 69 ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር። 70 እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት። 71 እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ። 72 ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።

የማርቆስ 15

1 ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። 2 ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። 3 የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። 4 ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። 5 ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። 6 በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። 7 በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። 8 ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። 9 ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ 10 የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። 11 የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። 12 ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። 13 እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ። 14 ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። 15 ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። 16 ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። 17 ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ 18 የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ 19 ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። 20 ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። 21 አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። 22 ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። 23 ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። 24 ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። 25 በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። 26 የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። 27 ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። 28 መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። 29 የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ 30 ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። 31 እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ 32 አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። 33 ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። 35 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። 36 አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። 37 ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። 38 የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። 39 በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። 40-41 ሴቶችም ደግሞ በሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት ማርያም የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሌሎች ብዙዎች ሴቶች ነበሩ። 42 አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥ 43 እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 44 ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤ 45 ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው። 46 በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ። 47 መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

የማርቆስ 16

1 ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ። 2 ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን እጅግ በማለዳ ፀሐይ ከወጣ በኋላ ወደ መቃብር መጡ። 3 እርስ በርሳቸውም። ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር፤ 4 ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። 5 ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 6 እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። 7 ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው። 8 መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው። 9 ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ አስቀድሞ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። 10 እርስዋ ሄዳ ከእርሱ ጋር ሆነው ለነበሩት ሲያዝኑና ሲያለቅሱ ሳሉ አወራችላቸው፤ 11 እነርሱም ሕያው እንደ ሆነ ለእርስዋም እንደ ታያት ሲሰሙ አላመኑም። 12 ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ለሁለቱ ወደ ባላገር ሲሄዱ በመንገድ በሌላ መልክ ተገለጠ፤ 13 እነርሱም ሄደው ለሌሎቹ አወሩ፤ እነዚያንም ደግሞ አላመኑአቸውም። 14 ኋላም በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ለአሥራ አንዱ ተገለጠ፥ ተነሥቶም ያዩትን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ ነቀፈ። 15 እንዲህም አላቸው። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 16 ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 17 ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ 18 የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። 19 ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20 እነርሱም ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፥ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፥ በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።

የሉቃስ 1

1-4 የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። 5 በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። 6 ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። 7 ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር። 8 እርሱም በክፍሉ ተራ በእግዚአብሔር ፊት ሲያገለግል፥ 9 እንደ ካህናት ሥርዓት ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን ዕጣ ደረሰበት። 10 በዕጣንም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ቆመው ይጸልዩ ነበር። 11 የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። 12 ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። 13 መልአኩም እንዲህ አለው። ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። 14 ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። 15 በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ 16 ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። 17 እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። 18 ዘካርያስም መልአኩን። እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። 19 መልአኩም መልሶ። እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ 20 እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። 21 ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። 22 በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ። 23 የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ። 24-25 ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና። ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች። 26 በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ 27 ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። 28 መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። 29 እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። 30 መልአኩም እንዲህ አላት። ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። 31 እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32 እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ 33 በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። 34 ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። 35 መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። 36 እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ 37 ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። 38 ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። 39 ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥ 40 ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። 41 ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ 42 በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43 የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? 44 እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። 45 ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። 46 ማርያምም እንዲህ አለች። 47 ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ 48 የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ 49 ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። 50 ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። 51 በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ 52 ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ 53 የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። 54-55 ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል። 56 ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች። 57 የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። 58 ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። 59 በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። 60 እናቱ ግን መልሳ። አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። 61 እነርሱም። ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። 62 አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። 63 ብራናም ለምኖ። ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። 64 ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። 65 ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ 66 የሰሙትም ሁሉ። እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። 67 አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ። 68 የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ 69-70 ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ 71 ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ 72-73 እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ 74-75 በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። 76 ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ 77 እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ 78 ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ 79 ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። 80 ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።

የሉቃስ 2

1 በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። 2 ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። 3 ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። 4-5 ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። 6 በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ 7 የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። 8 በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። 9 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። 10 መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ 11 ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። 12 ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። 13 ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። 14 ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። 15 መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። 16 ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። 17 አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። 18 የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ 19 ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። 20 እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። 21 ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። 22-24 እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ። የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ። ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። 25 እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። 26 በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። 27 በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ 28 እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ። 29 ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ 30-31 ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ 32 ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። 33 ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። 34-35 ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም። እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። 36 ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ 37 እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። 38 በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። 39 ሁሉንም እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። 40 ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ። 41 ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። 42 የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ 43 ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር። 44 ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ 45 ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 46 ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ 47 የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ። 48 ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው። 49 እርሱም። ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። 50 እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም። 51 ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር። 52 ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

የሉቃስ 3

1 ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፥ 2 ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። 3-6 በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። 7 ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና። 9 አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 10 ሕዝቡም። እንግዲህ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። 11 መልሶም። ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ ይል ነበር። 12 ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው። መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። 13 ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። 14 ጭፍሮችም ደግሞ። እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም። በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው። 15 ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ። ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥ 16 ዮሐንስ መልሶ። እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ 17 መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው። 18 ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ 19 የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ 20 ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው። 21 ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ 22 መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ። 23 ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥ 24 የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ 25 የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊም ልጅ 26 የናጌ ልጅ፥ የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ 27 የዮዳ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ 28 የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳስ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥ 29 የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ 30 የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ 31 የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ 32 የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ 33 የነአሶን ልጅ፥ የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ 34 የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ 35 የናኮር ልጅ፥ የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ 36 የቃይንም ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥ 37 የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ 38 የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ።

የሉቃስ 4

1 ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ 2 አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። 3 ዲያብሎስም። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ። እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። 4 ኢየሱስም። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። 5 ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። 6 ዲያብሎስም። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ 7 ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። 8 ኢየሱስም መልሶ። ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። 9-11 ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው፤ በመቅደስም ጫፍ ላይ አቁሞ። ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፥ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ከዚህ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። 12 ኢየሱስም መልሶ። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። 13 ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። 14 ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። 15 እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። 16 ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ። 17-19 የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። 20 መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። 21 እርሱም። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። 22 ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ። ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር። 23 እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው። 24 እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይ በገዛ አገሩ ከቶ አይወደድም። 25 ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ 26 ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም። 27 በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም። 28 በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥ 29 ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤ 30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። 31 ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ 32 ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። 33 በምኵራብም የርኵስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኾ። 34 ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ። 35 ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። 36 ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፥ እርስ በርሳቸውም። ይህ ቃል ምንድር ነው? በሥልጣንና በኃይል ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛልና፥ ይወጡማል ብለው ተነጋገሩ። 37 ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። 38 በምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር ስለ እርስዋም ለመኑት። 39 በአጠገብዋም ቆሞ ንዳዱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ያንጊዜውንም ተነሥታ አገለገለቻቸው። 40 ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። 41 አጋንንትም ደግሞ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። 42 በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ። 43 እርሱ ግን። ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል አላቸው። 44 በገሊላም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።

የሉቃስ 5

1 ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤ 2 በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። 3 ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር። 4 ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን። ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው። 5 ስምዖንም መልሶ። አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው። 6 ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። 7 በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው። 8 ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። 9 ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥ 10 እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። 11 ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት። 12 ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። 13 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው። 14 እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው። 15 ወሬው ግን አብዝቶ ወጣ፥ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤ 16 ነገር ግን እርሱ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር። 17 አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት። 18 እነሆም፥ አንድ ሽባ በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አግብተውም በፊቱ ሊያኖሩት ይሹ ነበር። 19 ስለ ሕዝቡም ብዛት እንዴት አድርገው እንዲያገቡት ሲያቅታቸው፥ ወደ ሰገነቱ ወጡ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከል በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት። 20 እምነታቸውንም አይቶ። አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። 21 ጻፎችና ፈሪሳውያንም። ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር። 22 ኢየሱስም አሳባቸውን እያወቀ መልሶ። በልባችሁ ምን ታስባላችሁ? 23 ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 24 ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ፥ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ነተሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ አለው። 25 በዚያን ጊዜም በፊታቸው ተነሣ፥ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26 ሁሉንም መገረም ያዛቸው፥ እግዚአብሔርንም አመስግነው። ዛሬስ ድንቅ ነገር አየን እያሉ ፍርሃት ሞላባቸው። 27 ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ ተመለከተና። ተከተለኝ አለው። 28 ሁሉንም ተወ፤ ተነሥቶም ተከተለው። 29 ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩ ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ። 30 ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ። 31 ኢየሱስም መልሶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ 32 ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። 33 እነርሱም። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም? አሉት። 34 ኢየሱስም። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታስጦሙ ትችላላችሁን? 35 ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ አላቸው። 36 ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም። 37 ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል። 38 አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። 39 አሮጌ የወይን ጠጅ ሲጠጣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ አሮጌው ይጣፍጣል ይላልና።

የሉቃስ 6

1 በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። 2 ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ። በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። 3-4 ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ። ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ። 5 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም። 6 በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ 7 ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 8 እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው። ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። 9 ኢየሱስም። እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። 10 ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን። እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። 11 እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ። 12 በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። 13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ 14 እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ 15 ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ 16 የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። 17 ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ 18 ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ 19 ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። 20 እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው። እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። 21 እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። 22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። 23 እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። 24 ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። 25 እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። 26 ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና። 27 ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ 28 የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። 29 ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው። 30 ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው። 31 ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። 32 የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። 33 መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። 34 እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። 35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። 36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። 37 አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ። 38 ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። 39 ምሳሌም አላቸው። ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን? 40 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። 41 በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? 42 በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን። ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። 43 ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም። 44 ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። 45 በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል። 46 ስለ ምን። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም? 47 ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። 48 ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። 49 ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።

የሉቃስ 7

1 ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2 አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። 3 ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። 4 እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው። ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ 5 ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። 6 ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም። ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ 7 ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። 8 እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል። 9 ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ። እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው። 10 የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት። 11 በነገውም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። 12 ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፥ እርስዋም መበለት ነበረች፥ ብዙም የከተማ ሕዝብ ከእርስዋ ጋር አብረው ነበሩ። 13 ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና። አታልቅሽ አላት። 14 ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም። አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ። 15 የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት። 16 ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና። ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥ ደግሞ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 17 ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ። 18 ደቀ መዛሙርቱም ለዮሐንስ እነዚህን ሁሉ አወሩ። 19 ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ። 20 ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው። መጥምቁ ዮሐንስ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ላከን አሉት። 21 በዚያች ሰዓት ከደዌና ከሥቃይ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፥ ለብዙ ዕውሮችም ማየትን ሰጠ። 22 ኢየሱስም መልሶ። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ 23 በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው። 24 የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? 25 ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። 26 ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። 27 እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። 28 እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 29 የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤ 30 ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ። 31 እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? 32 በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል። 33 መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና። ጋኔን አለበት አላችሁት። 34 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት። 35 ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች። 36 ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37 እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። 38 በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። 39 የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ። ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ። 40 ኢየሱስም መልሶ። ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም። መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ። 41 ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። 42 የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? 43 ስምዖንም መልሶ። ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም። በእውነት ፈረድህ አለው። 44 ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው። ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። 45 አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። 46 አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። 47 ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። 48 እርስዋንም። ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። 49 ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው። ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር። 50 ሴቲቱንም። እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።

የሉቃስ 8

1 ከዚህም በኋላ እየሰበከና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች እየተናገረ በየከተማይቱ በየመንደሩም ያልፍ ነበር፤ 2 አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም፥ 3 የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር። 4 ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። 5 ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት። 6 ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። 7 ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። 8 ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ። 9 ደቀ መዛሙርቱም። ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። 10 እርሱም እንዲህ አለ። ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። 11 ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። 12 በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። 13 በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው። 14 በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። 15 በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። 16 መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። 17 የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም።

የሉቃስ 9

1 አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ 2 የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥ 3 እንዲህም አላቸው። በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ። 4 በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ። 5 ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ። 6 ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። 7 የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች። 8 ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም። ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ። 9 ሄሮድስም። ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። 10 ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ። 11 ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው። 12 ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ አሥራ ሁለቱም ቀርበው። በዚህ በምድረ በዳ ነንና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። 13 እርሱ ግን። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። እነርሱም። ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን፥ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም አሉት፤ 14 አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ። በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው። 15 እንዲህም አደረጉ ሁሉንም አስቀመጡአቸው። 16 አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ። 17 ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ ከእነርሱም የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ወሰዱ። 18 ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው። 19 እነርሱም መልሰው። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም። ኤልያስ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት። 20 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ። ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ። 21-22 እርሱ ግን። የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል ብሎ ለማንም ይህን እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ አዘዘ። 23 ለሁሉም እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። 24 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። 25 ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? 26 በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል። 27 እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ። 28 ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 29 ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። 30 እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ 31 በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። 32 ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። 33 ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን። አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። 34 ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። 35 ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። 36 ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም። 37 በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት። 38 እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ። መምህር ሆይ፥ ለእኔ አንድ ልጅ ነውና ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። 39 እነሆም፥ ጋኔን ይይዘዋል፥ ድንገትም ይጮኻል አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፥ እየቀጠቀጠም በጭንቅ ይለቀዋል፤ 40 ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፥ አልቻሉምም። 41 ኢየሱስም መልሶ። እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው አለ። 42 ሲቀርብም ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኵሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው ለአባቱም መለሰው። 43 ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ፥ 44 ለደቀ መዛሙርቱ። የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሰጥ ዘንድ አለውና እናንተ ይህን ቃል በጆሮአችሁ አኑሩ አለ። 45 እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፥ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ፈሩ። 46 ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው። 47 ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ። 48 ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው። 49 ዮሐንስም መልሶ። አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው። 50 ኢየሱስ ግን። የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው። 51 የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥ 52 በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤ 53 ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም። 54 ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው። ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት። 55 እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና። ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤ 56 የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። 57 እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። 58 ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። 59 ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። 60 ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። 61 ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። 62 ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።

የሉቃስ 10

1 ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው። 2 አላቸውም። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። 3 ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። 4 ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ። 5 ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ። ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። 6 በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። 7 በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ። 8 ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ 9 በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው። 10 ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ። 11 ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ። 12 እላችኋለሁ፥ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። 13 ወዮልሽ ኮራዚን፥ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው በአመድም ተቀምጠው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። 14 ነገር ግን በፍርድ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 15 አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። 16 የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። 17 ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። 18 እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። 19 እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። 20 ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። 21 በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና። የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። 22 ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ። 23 ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው። የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። 24 እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም አለ። 25 እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። 26 እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው። 27 እርሱም መልሶ። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። 28 ኢየሱስም። እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው። 29 እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን። ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። 30 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። 31 ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። 32 እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። 33 አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ 34 ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። 35 በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። 36 እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? 37 እርሱም። ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም። ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው። 38 ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። 39 ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። 40 ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም። ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። 41 ኢየሱስም መልሶ። ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ 42 የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።

የሉቃስ 11

1 እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። 2 አላቸውም። ስትጸልዩ እንዲህ በሉ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ 3 የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ 4 ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን። 5 እንዲህም አላቸው። ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ። ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ 6 አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? 7 ያም ከውስጥ መልሶ። አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? 8 እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። 9 እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። 10 የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። 11 አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? 12 ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? 13 እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው? 14 ዲዳውንም ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ ሕዝቡም ተደነቁ፤ 15 ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዱ። በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። 16 ሌሎችም ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። 17 እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። 18 እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል እንዳወጣ ትላላችሁና ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? 19 እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 20 እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። 21 ኃይለኛ ሰው ጋሻና ጦር ይዞ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ገንዘቡ በሰላም ይሆናል፤ 22 ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል። 23 ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። 24 ርኵስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባያገኝም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ 25 ሲመጣም ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል። 26 ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሌሎችን ሰባት አጋንንት ከእርሱ ጋር ይይዛል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። 27 ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ። የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። 28 እርሱ ግን። አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ። 29 ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። 30 ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። 31 ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። 32 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 33 መብራትንም አብርቶ በስውር ወይም በእንቅብ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። 34 የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። 35 እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት። 36 እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፥ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል። 37 ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ። 38 ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ። 39 ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል 40 እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? 41 ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። 42 ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር። 43 እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ። 44 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። 45 ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው አለው። 46 እርሱም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፥ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ። 47 አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ። 48 እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ። 49 ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል፥ 50 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥ 51 ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። 52 እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ። 53-54 ይህንም ሲናገራቸው፥ ጻፎችና ፈሪሳውያን በአፉ የተናገረውን ሊነጥቁ ሲያደቡ፥ እጅግ ይቃወሙና ስለ ብዙ ነገር እንዲናገር ያነሣሡ ጀመር።

የሉቃስ 12

1 በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር። አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው። 2 ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም። 3 ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፥ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል። 4 ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ። 5 እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ። 6 አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። 7 ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። 8 እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ 9 በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። 10 በሰው ልጅም ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም። 11 ወደ ምኵራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ 12 መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና። 13 ከሕዝቡም አንድ ሰው። መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው። 14 እርሱም። አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው። 15 የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። 16 ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል። አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። 17 እርሱም። ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። 18 እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ 19 ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። 20 እግዚአብሔር ግን። አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። 21 ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። 22 ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። 23 ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። 24 ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ? 25 ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? 26 እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? 27 አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። 28 እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? 29 እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ 30 ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። 31 ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። 32 አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። 33 ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ 34 መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። 35 ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ 36 እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ 37 ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል። 38 ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው። 39 ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። 40 እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። 41 ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን? አለው። 42 ጌታም አለ። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? 43 ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው። 44 እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 45 ያ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ 46 የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። 47 የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ 48 ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። 49 በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ? 50 ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ? 51 በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ። 52 ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። 53 አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጅዋ ላይ ልጅዋም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። 54 ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ። ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው። ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤ 55 በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ። ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል። 56 እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? 57 ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው? 58 ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ። 59 እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።

የሉቃስ 13

1 በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። 2 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? 3 እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ። 4 ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ 5 ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። 6 ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። 7 የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። 8 እርሱ ግን መልሶ። ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። 9 ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው። 10 በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። 11 እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። 12 ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና። አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ 13 ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። 14 የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን። ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ። 15 ጌታም መልሶ። እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? 16 ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። 17 ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው። 18 እርሱም። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ? 19 ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ። 20 ደግሞም፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን አስመስላታለሁ? 21 ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ። 22 ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። 23 አንድ ሰውም። ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው። 24 በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም። 25 ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ልታንኳኩ ትጀምራላችሁ እርሱም መልሶ። ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላችኋል። 26 በዚያን ጊዜም። በፊትህ በላን ጠጣንም በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ፤ 27 እርሱም። እላችኋለሁ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ይላችኋል። 28 አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 29 ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፥ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። 30 እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፥ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ። 31 በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት። 32 እንዲህም አላቸው። ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት። 33 ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም ልሄድ ያስፈልገኛል። 34 ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም። 35 እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።

የሉቃስ 14

1 በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። 2 እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ። 3 ኢየሱስም መልሶ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ። 4 እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። 5 ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው። 6 ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። 7 የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። 8 ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ። 9 ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ። 10 ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ። ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። 11 ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል። 12 የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው። ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። 13 ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ 14 የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና። 15 ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ። በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው። 16 እርሱ ግን እንዲህ አለው። አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤ 17 በእራትም ሰዓት የታደሙትን። አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ። 18 ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። 19 ሌላውም። አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። 20 ሌላውም። ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው። 21 ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን። ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው። 22 ባሪያውም። ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው። 23 ጌታውም ባሪያውን። ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤ 24 እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው። 25 ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው። 26 ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 27 ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 28 ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? 29 ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። 30 ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ። 31 ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? 32 ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል። 33 እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። 34 ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል? 35 ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።

የሉቃስ 15

1 ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። 2 ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ። 3 ይህንም ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። 4 መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? 5 ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ 6 ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። 7 እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል። 8 ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? 9 ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ። የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። 10 እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል። 11 እንዲህም አለ። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12 ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። 13 ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። 14 ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። 15 ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። 16 እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። 17 ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ። እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። 18 ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ 19 ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። 20 ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። 21 ልጁም። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። 22 አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ። ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ 23 የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ 24 ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር። 25 ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ 26 ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። 27 እርሱም። ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። 28 ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። 29 እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ 30 ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው። 31 እርሱ ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ 32 ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።

የሉቃስ 16

1 ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ። ይህ ሰው ያለህን ይበትናል ብለው ከሰሱት። 2 ጠርቶም። ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው። 3 መጋቢውም በልቡ። ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ። 4 ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ። 5 የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን። ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? አለው። 6 እርሱም። መቶ ማድጋ ዘይት አለ። ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ አለው። 7 በኋላም ሌላውን። አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ? አለው። እርሱም። መቶ ጫን ስንዴ አለ። ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ አለው። 8 ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና። 9 እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። 10 ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። 11 እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? 12 በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? 13 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። 14 ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። 15 እንዲህም አላቸው። ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና። 16 ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ በኃይል ይገቡባታል። 17 ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል። 18 ሚስቱንም የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፥ ከባልዋም የተፈታችውን የሚያገባ ያመነዝራል። 19 ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። 20 አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ 21 ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። 22 ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። 23 በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። 24 እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። 25 አብርሃም ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። 26 ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ። 27 እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ 28 እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ። 29 አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። 30 እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። 31 ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።

የሉቃስ 17

1 ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ 2 ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። 3 ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው። 4 በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ። ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው። 5 ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት። 6 ጌታም አለ። የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። 7 ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ። ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው? 8 የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን? 9 ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? 10 እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ። የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። 11 ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። 12 ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ 13 እነርሱም እየጮኹ። ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። 14 አይቶም። ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። 15 እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ 16 እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። 17 ኢየሱስም መልሶ። አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? 18 ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። 19 እርሱንም። ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። 20 ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ 21 ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። 22 ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። 23 እነርሱም። እነሆ በዚህ፥ ወይም። እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። 24 መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። 25 አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። 26 በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። 27 ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። 28 እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ 29 ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። 30 የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። 31 በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። 32 የሎጥን ሚስት አስቡአት። 33 ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። 34 እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። 35 ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። 36 ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። 37 መልሰውም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም። ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።

የሉቃስ 18

1 ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ 2 እንዲህ ሲል። በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ። 3 በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች። ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር። 4 አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ። ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥ 5 ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ። 6 ጌታም አለ። ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ። 7 እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? 8 እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? 9 ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ 10 እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። 11 ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ። እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ 12 በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። 13 ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። 14 እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል። 15 እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። 16 ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ። ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 17 እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ። 18 ከአለቆችም አንዱ። ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። 19 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። 20 ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። 21 እርሱም። ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለ። 22 ኢየሱስም ይህን ሰምቶ። አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። 23 እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ። 24 ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። 25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ። 26 የሰሙትም። እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። 27 እርሱ ግን። በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል አለ። 28 ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ አለ። 29 እርሱም። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ 30 በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው። 31 አሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። 32 ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤ 33 ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል። 34 እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፥ ይህም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፥ የተናገረውንም አላወቁም። 35 ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር። 36 ሕዝብም ሲያልፍ ሰምቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። 37 እነርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል ብለው አወሩለት። 38 እርሱም። የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ጮኸ። 39 በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ። 40 ኢየሱስም ቆሞ ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? ብሎ ጠየቀው። 41 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አይ ዘንድ ነው አለው። 42 ኢየሱስም። እይ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። 43 በዚያን ጊዜም አየ፥ እግዚአብሔንም እያከበረ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

የሉቃስ 19

1-2 ወደ ኢያሪኮም ገብቶ ያልፍ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው፥ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፥ ባለ ጠጋም ነበረ። 3 ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው። 4 በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። 5 ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። 6 ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። 7 ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። 8 ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። 9 ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ 10 የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው። 11 እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። 12 ስለዚህም እንዲህ አላቸው። አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። 13 አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና። እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። 14 የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና። ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ። 15 መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ። 16 የፊተኛውም ደርሶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው። 17 እርሱም። መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው። 18 ሁለተኛውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው። 19 ይህንም ደግሞ። አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው። 20 ሌላውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ 21 ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው። 22 እርሱም። አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? 23 እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው። 24 በዚያም ቆመው የነበሩትን። ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው። 25 እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት። 26 እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል። 27 ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። 28 ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። 29 ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና። 30 በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት። 31 ማንም። ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው። 32 የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ። 33 እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ። ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም 34 እነርሱም። ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ። 35 ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት። 36 ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። 37 ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው። 38 በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ። 39 ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። 40 መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው። 41 ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ 42 እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። 43 ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ 44 አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና። 45 ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤ 46 እርሱም። ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው። 47 ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥ 48 የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።

የሉቃስ 20

1 አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና። 2 እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት። 3 መልሶም። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤ 4 የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው። 5 እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ 6 ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ። 7 መልሰውም። ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። 8 ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። 9 ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ። 10 በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 11 ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። 12 ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት። 13 የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ። 14 ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ። 15 ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? 16 ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ። 17 እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ። እንግዲህ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው? 18 በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ። 19 የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። 20 ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። 21 ጠይቀውም። መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ 22 ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። 23 እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ። ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ 24 መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም። የቄሣር ነው አሉት። 25 እርሱም። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። 26 በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ። 27 ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥ 28 እንዲህ ሲሉ። መምህር ሆይ፥ ሙሴ። ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 29 እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ 30-31 ሁለተኛውም አገባት፥ ሦስተኛውም፥ እንዲሁም ሰባቱ ደግሞ ልጅ ሳይተዉ ሞቱ። 32 ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 33 እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች? 34 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥ 35 ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ 36 ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። 37 ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ 38 ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። 39 ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው። መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት። 40 ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም። 41 እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? 42-43 ዳዊትም ራሱ በመዝሙራት መጽሐፍ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ይላል። 44 እንግዲህ ዳዊት። ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? 45 ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን። 46 ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 47 የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።

የሉቃስ 21

1 ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ። 2 አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና። 3 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ 4 እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አለ። 5 አንዳንዶቹም ስለ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ። ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ 6 ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል አለ። 7 እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ይሆን ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። 8 እንዲህም አለ። እንዳትስቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች። እኔ ነኝ፥ ዘመኑም ቀርቦአል እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። 9 ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም። 10 በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ 11 ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል። 12 ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ 13 ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። 14 ሰለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤ 15 ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። 16 ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ 17 በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18 ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ 19 በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ። 20 ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። 21 የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፥ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤ 22 የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል ጊዜ ነውና። 23 በዚያን ወራት ለእርጕዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቍጣ ይሆናልና፤ 24 በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉም ይማረካሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። 25 በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ 26 ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና። 27 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28 ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ። 29 ምሳሌንም ነገራቸው እንዲህ ሲል። በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ 30 ሲያቈጠቍጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 31 እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። 32 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 33 ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። 34 ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ 35 በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። 36 እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ። 37 ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር። 38 ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

የሉቃስ 22

1 ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። 2 የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። 3 ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ 4 ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። 5 እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። 6 እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። 7 ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ 8 ጴጥሮስንና ዮሐንስንም። ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። 9 እነርሱም። ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። 10 እርሱም አላቸው። እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ 11 ለባለቤቱም። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ 12 ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። 13 ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። 14 ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። 15 እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ 16 እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። 17 ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ 18 እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። 19 እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና። ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። 20 እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ። ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። 21 ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። 22 የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። 23 ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። 24 ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። 25 እንዲህም አላቸው። የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። 26 እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። 27 በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። 28 ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ 29-30 አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ። 31 ጌታም። ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ 32 እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። 33 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። 34 እርሱ ግን። ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። 35 ደግሞም። ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም። አንዳች እንኳ አሉ። 36 እርሱም። አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። 37 እላችኋለሁና፥ ይህ። ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። 38 እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም። ይበቃል አላቸው። 39 ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። 40 ወደ ስፍራውም ደርሶ። ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። 41 ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም። አባት ሆይ፥ 42 ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። 43 ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። 44 በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። 45 ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው። 46 ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። 47 ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። 48 ኢየሱስ ግን። ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። 49 በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። 50 ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። 51 ኢየሱስ ግን መልሶ። ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። 52 ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? 53 በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው። 54 ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። 55 በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። 56 በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ። ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። 57 እርሱ ግን። አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። 58 ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት። አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። 59 አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ። እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። 60 ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። 61 ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም። ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። 62 ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። 63 ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ 64 ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና። በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65 ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። 66 በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና 67 ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ብነግራችሁ አታምኑም፤ 68 ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። 69 ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። 70 ሁላቸውም። እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም። እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። 71 እነርሱም። ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።

የሉቃስ 23

1 ሁሉም በሞላው ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱትና። 2 ይህ ሕዝባችንን ሲያጣምም ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም። እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው ብለው ይከሱት ጀመር። 3 ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም መልሶ። አንተ አልህ አለው። 4 ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ። በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም አለ። 5 እነርሱ ግን አጽንተው። ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በይሁዳ ሁሉ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል አሉ። 6 ጲላጦስ ግን። ገሊላ ሲሉ በሰማ ጊዜ። የገሊላ ሰው ነውን? ብሎ ጠየቀ፤ 7 ከሄሮድስም ግዛት እንደ ሆነ ባወቀ ጊዜ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፤ እርሱ ደግሞ በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ነበረና። 8 ሄሮድስም ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ስለ ሰማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይመኝ ነበርና፥ ምልክትም ሲያደርግ ሊያይ ተስፋ ያደርግ ነበር። 9 በብዙ ቃልም ጠየቀው፤ እርሱ ግን አንድ ስንኳ አልመለሰለትም። 10 የካህናት አለቆችና ጻፎችም አጽንተው ሲከሱት ቆመው ነበር። 11 ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር ናቀው ዘበተበትም፥ የጌጥ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። 12 ሄሮድስና ጲላጦስም በዚያን ቀን እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ፥ ቀድሞ በመካከላቸው ጥል ነበረና። 13 ጲላጦስም፥ የካህናትን አለቆችና መኳንንትን ሕዝቡንም በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው። 14 ሕዝቡን ያጣምማል ብላችሁ ይህን ሰው ወደ እኔ አመጣችሁት፤ እነሆም፥ በፊታችሁ መርምሬ ከምትከሱበት ነገር አንድ በደል ስንኳ በዚህ ሰው አላገኘሁበትም። 15 ሄሮድስም ደግሞ ምንም አላገኘም፤ ወደ እኛ መልሶታልና፤ እነሆም፥ ለሞት የሚያደርሰው ምንም አላደረገም፤ 16-17 እንግዲያስ ቀጥቼ እፈታዋለሁ። በበዓሉ አንድ ይፈታላቸው ዘንድ ግድ ነበረና። 18 ሁላቸውም በአንድነት። ይህን አስወግድ፥ በርባንንም ፍታልን እያሉ ጮኹ፤ 19 እርሱም ሁከትን በከተማ አንሥቶ ሰውን ስለ ገደለ በወኅኒ ታስሮ ነበር። 20 ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታ ወድዶ ዳግመኛ ተናገራቸው፤ 21 ነገር ግን እነርሱ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ይጮኹ ነበር። 22 ሦስተኛም። ምን ነው? ያደረገውስ ክፋት ምንድር ነው? ለሞት የሚያደርሰው በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ አላቸው። 23 እነርሱ ግን እንዲሰቀል በታላቅ ድምፅ አጽንተው ለመኑት። የእነርሱ ጩኸትና የካህናት አለቆችም ቃል በረታ። 24 ጲላጦስም ልመናቸው እንዲሆንላቸው ፈረደበት። 25 ያንን የለመኑትንም፥ ስለ ሁከት ሰውንም ስለ መግደል በወኅኒ ታስሮ የነበረውን አስፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው። 26 በወሰዱትም ጊዜ ስምዖን የተባለ የቀሬናን ሰው ከገጠር ሲመጣ ይዘው ከኢየሱስ በኋላ መስቀሉን እንዲሸከም ጫኑበት። 27 ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት። 28-29 ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ። እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን። መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ። 30 በዚያን ጊዜ ተራራዎችን። በላያችን ውደቁ፥ ኮረብቶችንም። ሰውሩን ይሉ ዘንድ ይጀምራሉ፤ 31 በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን? 32 ሌሎችንም ሁለት ክፉ አድራጊዎች ደግሞ ከእርሱ ጋር ይገድሉ ዘንድ ወሰዱ። 33 ቀራንዮም ወደሚባል ስፍራ በደረሱ ጊዜ፥ በዚያ እርሱን ክፉ አድራጊዎቹንም አንዱን በቀኝ ሁለተኛውንም በግራ ሰቀሉ። 34 ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። 35 ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ። ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። 36 ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው። 37 አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር። 38 ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው ተብሎ በግሪክና በሮማይስጥ በዕብራይስጥም ፊደል የተጻፈ ጽሕፈት ደግሞ በእርሱ ላይ ነበረ። 39 ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ። አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። 40 ሁለተኛው ግን መልሶ። አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? 41 ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። 42 ኢየሱስንም። ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። 43 ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። 44 ስድስት ሰዓትም ያህል ነበረ፥ ጨለማም እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ሆነ፥ ፀሐይም ጨለመ፥ 45 የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከመካከሉ ተቀደደ። 46 ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። 47 የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። 48 ይህንም ለማየት ተከማችተው የነበሩ ሕዝብ ሁሉ፥ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ። 49 የሚያውቁቱ ግን ሁሉ ከገሊላ የተከተሉት ሴቶችም ይህን እያዩ በሩቅ ቆመው ነበር። 50 እነሆም፥ በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ 51 ይህም በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ አርማትያስም ከምትባል ከአይሁድ ከተማ ሆኖ እርሱ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር። 52 ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤ 53 አውርዶም በተልባ እግር ልብስ ከፈነው፥ ማንም ገና ባልተቀበረበት ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው። 54 የመዘጋጀት ቀንም ነበረ፤ ሰንበትም ሊጀምር ነበረ። 55 ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። 56 ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ። በሰንበትም እንደ ትእዛዙ ዐረፉ።

የሉቃስ 24

1 ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። 2 ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ 3 ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። 4 እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ 5 ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። 6-7 የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ። 8-9 ቃሎቹንም አሰቡ፥ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። 10 ይህንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። 11 ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። 12 ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ። 13 እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ 14 ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። 15 ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ 16 ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። 17 እርሱም። እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። 18 ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ። አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። 19 እርሱም። ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ 20 እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። 21 እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። 22 ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ 23 ሥጋውንም ባጡ ጊዜ። ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። 24 ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። 25 እርሱም። እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ 26 ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። 27 ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። 28 ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው። 29 እነርሱ። ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። 30 ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ 31 ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። 32 እርስ በርሳቸውም። በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ። 33-34 በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም። ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። 35 እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው። 36 ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። 37 ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። 38 እርሱም። ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? 39 እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። 40 ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41 እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ። በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። 42 እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ 43 ተቀብሎም በፊታቸው በላ። 44 እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። 45 በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ 46 እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፥ 47 በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል። 48 እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። 49 እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ። 50 እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። 51 ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። 52 እነርሱም፤ ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ 53 ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ።

የዮሐንስ 1

2 ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። 3 ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። 4 በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። 5 ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። 6 ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ 7 ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። 8 ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። 9 ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። 10 በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። 11 የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። 12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ 13 እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። 14 ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። 15 ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። 16 እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ 17 ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። 18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። 19 አይሁድም። አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። 20 መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። 21 እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ። ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። 22 እንኪያስ። ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። 23 እርሱም። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። 24- 25 የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። 26 ዮሐንስ መልሶ። እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ 27 እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። 28 ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። 29 በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። 30 አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። 31 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። 32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። 33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። 34 እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ። 35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ 36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። 37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። 38 ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ። ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። 39 እነርሱም። ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው። 40 መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። 41 ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። 42 እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። 43 ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው። 44 በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው። 45 ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ። 46 ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ። ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው። 47 ናትናኤልም። ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ። መጥተህ እይ አለው። 48 ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ። ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ። 49 ናትናኤልም። ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ። ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው። 50 ናትናኤልም መልሶ። መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው። 51 ኢየሱስም መልሶ። ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው። 52 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።

የዮሐንስ 2

1 በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ 2 ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ። 3 የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። 4 ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። 5 እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። 6 አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። 7 ኢየሱስም። ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው። 8 አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። 9 አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። 10 ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። 11 ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። 12 ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ። 13 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 14 በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ 15 የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ 16 ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። 17 ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። 18 ስለዚህ አይሁድ መልሰው። ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት። 19 ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። 20 ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። 21 እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። 22 ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ። 23 በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤ 24-25 ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።

የዮሐንስ 3

1 ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ። 2 መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። 3 ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። 4 ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። 5 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። 6 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። 7 ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። 8 ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። 9 ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። 10 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? 11 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። 12 ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13 ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። 14-15 ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። 16 በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። 17 ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። 18 በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። 19 ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። 20 ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ 21 እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል። 22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር። 23 ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥ 24 እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና። 25 ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ። 26 ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት። 27 ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም። 28 እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። 29 ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። 30 እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። 31 ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። 32 ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፥ ምስክሩንም የሚቀበለው የለም። 33 ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ። 34 እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና። 35 አባት ልጁን ይወዳል ሁሉንም በእጁ ሰጥቶታል። 36 በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።

የዮሐንስ 4

1 እንግዲህ። ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ 2-3 ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም። 4 በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። 5 ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ 6 በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። 7 ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም። ውኃ አጠጪኝ አላት፤ 8 ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። 9 ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። 10 ኢየሱስ መልሶ። የእግዚአብሔርን ስጦታና። ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። 11 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? 12 በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። 13 ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ 14 እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። 15 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። 16 ኢየሱስም። ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት። 17 ሴቲቱ መልሳ። ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ። ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ 18 አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። 19 ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። 20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። 21 ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። 22 እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። 23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ 24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። 25 ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። 26 ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። 27 በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም። 28 ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም። 29 ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። 30 ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። 31 ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። 32 እርሱ ግን። እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው። 33 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ። የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። 34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው። 35 እናንተ። ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ። 36 የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። 37 አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። 38 እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ። 39 ሴቲቱም። ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት። 40 የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ። 41 ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ 42 ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር። 43 ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። 44 ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። 45 ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለበዓል መጥተው ነበርና በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት። 46 ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። 47 እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። 48 ስለዚህም ኢየሱስ። ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው። 49 ሹሙም። ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው። 50 ኢየሱስም። ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። 51 እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና። ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት። 52 እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም። ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት። 53 አባቱም ኢየሱስ። ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ። 54 ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

የዮሐንስ 5

1 ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። 3 በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። 4 አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። 5 በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ 6 ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው። 7 ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። 8 ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። 9 ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። 10 ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት። 11 እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። 12 እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት። 13 ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። 14 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። 15 ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። 16 ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። 17 ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። 18 እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። 19 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። 20 አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። 21 አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። 22-23 ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። 25 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። 26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። 27 የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። 28-29 በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ። 30 እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። 31 እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም፤ 32 ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፥ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክር እውነት እንደ ሆነ አውቃለሁ። 33 እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል። 34 እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ። 35 እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ። 36 እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። 37 የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤ 38 እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። 39 እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ 40 ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። 41-42 ከሰው ክብርን አልቀበልም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ። 43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ። 44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? 45 እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። 46 ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። 47 መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?

የዮሐንስ 6

1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው። 2 በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። 3 ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 4 የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። 5 ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን። እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው። 6 ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ። 7 ፊልጶስ። እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት። 8 ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ። 9 አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል? አለው። 10 ኢየሱስም። ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር። 11 ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን። 12 ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን። አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው። 13 ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ። 14 ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ። ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ። 15 በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ። 16 በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥ 17 በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤ 18 ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ። 19 ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ። 20 እርሱ ግን። እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። 21 ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች። 22 በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤ 23 ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ። 24 ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። 25 በባሕር ማዶም ሲያገኙት። መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ? አሉት። 26 ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። 27 ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። 28 እንግዲህ። የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት። 29 ኢየሱስ መልሶ። ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው። 30 እንግዲህ። እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? 31 ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት። 32 ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ 33 የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። 34 ስለዚህ። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት። 35 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። 36 ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። 37 አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤ 38 ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። 39 ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። 40 ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 41 እንግዲህ አይሁድ። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና። 42 አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። 43 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። 44 የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 45 ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። 46 አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። 47 እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። 48 የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49 አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ 50 ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። 51 ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። 52 እንግዲህ አይሁድ። ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። 53 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። 54 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። 55 ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57 ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። 58 ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል 59 በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ። 60 ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ። 61 ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን? 62 እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? 63 ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። 64 ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና። 65 ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ። 66 ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። 67 ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ። እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። 68 ስምዖን ጴጥሮስ። ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤ 69 እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም ብሎ መለሰለት። 70 ኢየሱስም። እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው ብሎ መለሰላቸው። 71 ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና።

የዮሐንስ 7

1 ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር። 2 የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር። 3 እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ 4 ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት። 5 ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና። 6 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። 7 ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል። 8 እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም። 9 ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ። 10 ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። 11 አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። 12 በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር። 13 ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። 14 አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። 15 አይሁድም። ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር። 16 ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ 17 ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። 18 ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም። 19 ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ከእናንተ ግን ሕግን የሚያደርግ አንድ ስንኳ የለም። ልትገድሉኝ ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? 20 ሕዝቡ መለሱና። ጋኔን አለብህ፤ ማን ሊገድልህ ይፈልጋል? አሉት። 21 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። አንድ ሥራ አደረግሁ ሁላችሁም ታደንቃላችሁ። 22 ስለዚህ ሙሴ መገረዝን ሰጣችሁ፤ ከአባቶችም ነው እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ በሰንበትም ሰውን ትገርዛላችሁ። 23 የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሰው በሰንበት መገረዝን የሚቀበል ከሆነስ ሰውን ሁለንተናውን በሰንበት ጤናማ ስላደረግሁ ትቈጡኛላችሁን? 24 ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ። 25 እንግዲህ ከኢየሩሳሌም ሰዎች አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ። ሊገድሉት የሚፈልጉት ይህ አይደለምን? 26 እነሆም፥ በግልጥ ይናገራል አንዳችም አይሉትም። አለቆቹ ይህ ሰው በእውነት ክርስቶስ እንደ ሆነ በእውነት አወቁን? 27 ነገር ግን ይህን ከወዴት እንደ ሆነ አውቀናል፤ ክርስቶስ ሲመጣ ግን ከወዴት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም። 28 እንግዲህ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር። እኔንም ታውቁኛላችሁ ከወዴትም እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ እኔም በራሴ አልመጣሁም ነገር ግን እናንተ የማታውቁት የላከኝ እውነተኛ ነው፤ 29 እኔ ግን ከእርሱ ዘንድ ነኝ እርሱም ልኮኛልና አውቀዋለሁ ብሎ ጮኸ። 30 ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። 31 ከሕዝቡ ግን ብዙዎች አመኑበትና። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ይህ ካደረጋቸው ምልክቶች ይልቅ ያደርጋልን? አሉ። 32 ፈሪሳውያንም ሕዝቡ ሰለ እርሱ እንደዚህ ሲያንጐራጕሩ ሰሙ፤ የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ። 33 ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ ወደ ላከኝም እሄዳለሁ። 34 ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም፤ እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አለ። 35 እንግዲህ አይሁድ። እኛ እንዳናገኘው ይህ ወዴት ይሄድ ዘንድ አለው? በግሪክ ሰዎች መካከል ተበትነው ወደሚኖሩት ሊሄድና የግሪክን ሰዎች ሊያስተምር አለውን? 36 እርሱ። ትፈልጉኛላችሁ አታገኙኝምም እኔም ወዳለሁበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም የሚለው ይህ ቃል ምንድር ነው? ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። 37 ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ። ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ። 38 በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። 39 ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና። 40 ስለዚህ ከሕዝቡ አያሌ ሰዎች ይህን ቃል ሲሰሙ። ይህ በእውነት ነቢዩ ነው አሉ፤ 41 ሌሎች። ይህ ክርስቶስ ነው አሉ፤ ሌሎች ግን። ክርስቶስ በእውኑ ከገሊላ ይመጣልን? 42 ክርስቶስ ከዳዊት ዘር ዳዊትም ከነበረባት መንደር ከቤተ ልሔም እንዲመጣ መጽሐፍ አላለምን? አሉ። 43 እንግዲህ ከእርሱ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መለያየት ሆነ፤ 44 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ሊይዙት ወደዱ ነገር ግን እጁን ማንም አልጫነበትም። 45 ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ፈሪሳውያን መጡ፤ እነዚያም። ያላመጣችሁት ስለ ምን ነው? አሉአቸው። 46 ሎሌዎቹ። እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም ብለው መለሱ። 47 እንግዲህ ፈሪሳውያን። እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? 48 ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? 49 ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው። 50 ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ። 51 ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። 52 እነርሱም መለሱና። አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። 53 እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።

የዮሐንስ 8

1 ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። 2 ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር። 3 ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው። 4 መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች። 5 ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት። 6 የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤ 7 መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው። 8 ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ። 9 እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች። 10 ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ። አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት። 11 እርስዋም። ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም። እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት። 12 ደግሞም ኢየሱስ። እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። 13 ፈሪሳውያንም። አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም አሉት። 14 ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም። 15 እናንተ ሥጋዊ ፍርድን ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በአንድ ሰው ስንኳ አልፈርድም። 16 የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁምና እኔ ብፈርድ ፍርዴ እውነት ነው። 17 የሁለት ሰዎችም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ በሕጋችሁ ተጽፎአል። 18 ስለ ራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ፥ የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል። 19 እንግዲህ። አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ። እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው። 20 ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም። 21 ኢየሱስም ደግሞ። እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው። 22 አይሁድም። እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ። 23 እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። 24 እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው። 25 እንግዲህ። አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም። ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ። 26 ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው። 27 ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም። 28 ስለዚህም ኢየሱስ። የሰውን ልጅ ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ እኔ እሆን ዘንድ አባቴም እንዳስተማረኝ እነዚህን እናገር ዘንድ እንጂ ከራሴ አንዳች እንዳላደርግ በዚያን ጊዜ ታውቃላችሁ። 29 የላከኝም ከእኔ ጋር ነው፤ እኔ ደስ የሚያሰኘውን ዘወትር አደርጋለሁና አብ ብቻዬን አይተወኝም አላቸው። 30 ይህን ሲናገር ብዙዎች በእርሱ አመኑ። 31 ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ። እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32 እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። 33 እነርሱም መልሰው። የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ። አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ? አሉት። 34 ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው። 35 ባርያም ለዘላለም በቤት አይኖርም፤ ልጁ ለዘላለም ይኖራል። 36 እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። 37 የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38 እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ደግሞ በአባታችሁ ዘንድ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ። 39 መልሰውም። አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም። የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር። 40 ነገር ግን አሁን ከእግዚእብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ፤ አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41 እናንተ የአባታችሁን ሥራ ታደርጋላችሁ አላቸው። እኛስ ከዝሙት አልተወለድንም አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሔር ነው አሉት። 42 ኢየሱስም አላቸው። እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና። 43 ንግግሬን የማታስተውሉ ስለ ምንድር ነው? ቃሌን ልትሰሙ ስለማትችሉ ነው። 44 እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። 45 እኔ ግን እውነትን የምናገር ስለ ሆንሁ አታምኑኝም። 46 ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው? እውነት የምናገር ከሆንሁ እናንተ ስለ ምን አታምኑኝም? 47 ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም። 48 አይሁድ መልሰው። ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን? አሉት። 49 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እኔስ ጋኔን የለብኝም ነገር ግን አባቴን አከብራለሁ እናንተም ታዋርዱኛላችሁ። 50 እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ። 51 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አያይም። 52 አይሁድ። ጋኔን እንዳለብህ አሁን አወቅን። አብርሃም ስንኳ ሞተ ነቢያትም፤ አንተም። ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም ትላለህ። 53 በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት። 54 ኢየሱስም መለሰ አለም። እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ 55 አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በሆንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56 አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው። 57 አይሁድም። ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። 58 ኢየሱስም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው። 59 ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።

የዮሐንስ 9

1 ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። 2 ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት። 3 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። 4 ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። 5 በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ። 6 ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና። 7 ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ። 8 ጐረቤቶቹም ቀድሞም ሲለምን አይተውት የነበሩ። ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረ አይደለምን? አሉ። 9 ሌሎች። እርሱ ነው አሉ፤ ሌሎች። አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ አሉ፤ እርሱ። እኔ ነኝ አለ። 10 ታድያ። ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ? አሉት። 11 እርሱ መልሶ። ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ አይኖቼን ቀባና። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ አለ። 12 ያ ሰው ወዴት ነው? አሉት። አላውቅም አለ። 13 በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14 ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። 15 ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም። ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው። 16 ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ። ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን። ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ። 17 በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን። አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም። ነቢይ ነው አለ። 18 አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥ 19 እነርሱንም። እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው። 20 ወላጆቹም መልሰው። ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤ 21 ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ። 22 ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። 23 ስለዚህ ወላጆቹ። ሙሉ ሰው ነው፥ ጠይቁት አሉ። 24 ስለዚህ ዕውር የነበረውን ሰው ሁለተኛ ጠርተው። እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን አሉት። 25 እርሱም መልሶ። ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ አለ። 26 ደግመውም። ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ? አሉት። 27 እርሱም መልሶ። አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን? አላቸው። 28 ተሳድበውም። አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ 29 እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። 30 ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው። ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። 31 እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። 32 ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ 33 ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር። 34 መልሰው። አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወለድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን? አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። 35 ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ሲያገኘውም። አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው። 36 እርሱም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። 37 ኢየሱስም። አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው። 38 እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም። 39 ኢየሱስም። የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ አለ። 40 ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው። እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን? አሉት። 41 ኢየሱስም አላቸው። ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።

የዮሐንስ 10

1 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤ 2 በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። 3 ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። 4 የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ 5 ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። 6 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም። 7 ኢየሱስም ደግሞ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ። 8 ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። 9 በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። 10 ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። 11 መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። 12 እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። 13 ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። 14-15 መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ። 16 ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ። 17 ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። 18 እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። 19 እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ። 20 ከእነርሱም ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ። 21 ሌሎችም። ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ። 22 በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤ 23 ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። 24 አይሁድም እርሱን ከበው። እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት። 25 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ 26 እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። 27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ 28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። 29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። 30 እኔና አብ አንድ ነን። 31 አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። 32 ኢየሱስ። ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። 33 አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። 34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? 35 መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ 36 የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን። ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? 37 እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ 38 ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ። 39 እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ። 40 ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ። 41 ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው። ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ። 42 በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

የዮሐንስ 11

1 ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢታንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። 2 ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። 3 ስለዚህ እኅቶቹ ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል ብለው ወደ እርሱ ላኩ። 4 ኢየሱስም ሰምቶ። ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም አለ። 5 ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። 6 እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ 7 ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው። 8 ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት። 9 ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ 10 በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው። 11 ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። 12 እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። 13 ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። 14 እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤ 15 እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው። 16 ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ። 17 ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። 18 ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። 19 ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። 20 ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። 21 ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ 22 አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው። 23 ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። 24 ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። 25 ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ 26 ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት። 27 እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው። 28 ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት። 29 እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ 30 ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። 31 ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። 32 ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው። 33 ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ 34 ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት። 35 ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። 36 ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ። 37 ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ። 38 ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። 39 ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው። 40 ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት። 41 ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ። አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። 42 ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ አለ። 43 ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ። አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ። 44 የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም። ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው። 45 ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ 46 ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ነገሩአቸው። 47 እንግዲህ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ሸንጎ ሰብስበው። ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። 48 እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ። 49 በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ 50 ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። 51 ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ 52 ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ። 53 እንግዲህ ከዚያ ቀን ጀምረው ሊገድሉት ተማከሩ። 54 ከዚያ ወዲያም ኢየሱስ በአይሁድ መካከል ተገልጦ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ከዚያ በምድረ በዳ አጠገብ ወዳለች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 55 የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56 ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በመቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው። ምን ይመስላችኋል? ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን? ተባባሉ። 57 የካህናት አለቆችም ፈሪሳውያንም ይይዙት ዘንድ እርሱ ያለበትን ስፍራ የሚያውቀው ሰው ቢኖር እንዲያመለክታቸው አዘው ነበር።

የዮሐንስ 12

1 ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። 2 በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ። 3 ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ። 4 ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። 5 ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። 6 ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። 7 ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ 8 ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ። 9 ከአይሁድም ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም። 10 የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥ 11 ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና። 12 በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥ 13 የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ። 14-15 አንቺ የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ። 16 ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው። 17 አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። 18 ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። 19 ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው። አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ። 20 በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ 21 እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። 22 ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። 23 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25 ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26 የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። 27 አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። 28 አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። 29 በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ። ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች። መልአክ ተናገረው አሉ። 30 ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። 31 አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ 32 እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። 33 በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። 34 እንግዲህ ሕዝቡ። እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው? ብለው መለሱለት። 35 ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። 36 የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው። 37-38 ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም። 39-40 ኢሳይያስ ደግሞ። በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። 41 ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ። 42 ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ 43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። 44 ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ። በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ 45 እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። 46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። 47 ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። 48 የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። 49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። 50 ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።

የዮሐንስ 13

1 ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። 2 እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ 3 ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ 4 ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ 5 በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። 6 ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። 7 ኢየሱስም መልሶ። እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው። 8 ጴጥሮስም። የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም አለው። ኢየሱስም። ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። 9 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። 10 ኢየሱስም። የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም አለው። 11 አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ። ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም አለው። 12 እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? 13 እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። 14 እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። 15 እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። 16 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። 17 ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ። 18 ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ። እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። 19 በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ። 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውን የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። 21 ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል አለ። 22 ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። 23 ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ 24 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ። ስለማን እንደ ተናገረ ንገረን አለው። 25 እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነው? አለው። 26 ኢየሱስም። እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። 27 ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ። የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ አለው። 28 ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤ 29 ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ። ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና። 30 እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ። 31 ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ። አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤ 32 እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል። 33 ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም። እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። 34 እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። 35 እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። 36 ስምዖን ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ? አለው። ኢየሱስም። ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፥ ነገር ግን በኋላ ትከተለኛለህ ብሎ መለሰለት። 37 ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ አሁን ልከተልህ አለመቻሌ ስለ ምንድር ነው? ነፍሴን ስንኳ ስለ አንተ እሰጣለሁ አለው። 38 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰለት። ነፍስህን ስለ እኔ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዶሮ አይጮኽም።

የዮሐንስ 14

1 ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2 በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ 3 ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። 4 ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ። 5 ቶማስም። ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። 6 ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው። 8 ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። 9 ኢየሱስም አለው። አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ? 10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። 11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። 12 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ 13 እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። 14 ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። 15-16 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። 18 ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19 ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20 እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። 21 ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። 22 የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ። ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው። 23 ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። 24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። 25 ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ 26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። 27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። 28 እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። 29 ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ። 30 ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ 31 ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።

የዮሐንስ 15

1 እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። 2 ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። 3 እናንተ ስለ ነገርኋችሁ ቃል አሁን ንጹሐን ናችሁ፤ 4 በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። 5 እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። 6 በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። 7 በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። 8 ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። 9 አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። 10 እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። 11 ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ። 12 እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። 13 ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። 14 እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። 15 ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና። 16 እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ። 17 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ። 18 ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። 19 ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። 20 ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። 21 ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ሰለ ስሜ ያደርጉባችኋል። 22 እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም። 23 እኔን የሚጠላ አባቴን ደግሞ ይጠላል። 24 ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደረግሁ፥ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን እኔንም አባቴንም አይተውማል ጠልተውማል። 25 ነገር ግን በሕጋቸው። በከንቱ ጠሉኝ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 26 ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ 27 እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ።

የዮሐንስ 16

1 እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። 2 ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3 ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። 4 ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም። 5 አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም። ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6 ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። 7 እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8 እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ 9-10 ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ 11 ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። 12 የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14 እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15 ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። 16 ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና። 17 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ። ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። 18 እንግዲህ። ጥቂት የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም አሉ። 19 ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? 20 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21 ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም። 22 እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23 በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 24 እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። 25 ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል። 26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ 27 እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። 28 ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ። 29 ደቀ መዛሙርቱ። እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። 30 ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት። 31 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። አሁን ታምናላችሁን? 32 እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። 33 በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።

የዮሐንስ 17

1-2 ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው። 3 እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። 4 እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ 5 አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። 6 ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ 7 ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤ 8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ። 9 እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ 10 የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ። 11 ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። 12 ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። 13 አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። 14 እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። 15 ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። 16 እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። 17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። 18 ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ 19 እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ። 20-21 ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። 22-23 እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። 24 አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ። 25 ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ 26 እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።

የዮሐንስ 18

1 ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። 2 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር። 3 ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ። 4 ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና። ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው። 5 የናዝሬቱን ኢየሱስን ብለው መለሱለት። ኢየሱስ። እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6 እንግዲህ። እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። 7 ደግሞም። ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት። 8 ኢየሱስ መልሶ። እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው አለ፤ 9 ይህም። ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 10 ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥ የሊቀ ካህናቱንም ባርያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባርያውም ስም ማልኮስ ነበረ። 11 ኢየሱስም ጴጥሮስን። ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን? አለው። 12 እንግዲህ የሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት፥ 13 አስቀድመውም ወደ ሐና ወሰዱት፤ በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ለቀያፋ አማቱ ነበርና። 14 ቀያፋም። አንድ ሰው ስለ ሕዝብ ይሞት ዘንድ ይሻላል ብሎ ለአይሁድ የመከራቸው ነበረ። 15 ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ 16 ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው። 17 በረኛ የነበረችይቱም ገረድ ጴጥሮስን። አንተ ደግሞ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን? አለችው። እርሱ። አይደለሁም አለ። 18 ብርድ ነበረና ባሮችና ሎሌዎች የፍም እሳት አንድደው ቆሙ ይሞቁም ነበር፤ ጴጥሮስም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ይሞቅ ነበር። 19 ሊቀ ካህናቱም ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። 20 ኢየስስም መልሶ። እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፥ በስውርም ምንም አልተናገርሁም። 21 ስለምን ትጠይቀኛለህ? ለእነርሱ የተናገርሁትን የሰሙትን ጠይቅ፤ እነሆ፥ እነዚህ እኔ የነገርሁትን ያውቃሉ አለው። 22 ይህንም ሲል በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ። ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው። 23 ኢየሱስም መልሶ። ክፉ ተናግሬ እንደ ሆንሁ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ እንደ ሆንሁ ግን ሰለ ምን ትመታኛለህ? አለው። 24 ስለዚህ ሐና እንደ ታሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሰደደው። 25 ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር። እንግዲህ። አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን? አሉት። እርሱም። አይደለሁም ብሎ ካደ። 26 ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ። በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን? አለው። 27 ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። 28 ኢየሱስንም ከቀያፋ ወደ ገዡ ግቢ ወሰዱት፤ ማለዳም ነበረ፤ እነርሱም የፋሲካ በግ ይበሉ ዘንድ እንጂ እንዳይረክሱ ወደ ገዡ ግቢ አልገቡም። 29 ስለዚህ ጲላጦስ ወደ ውጭ ወደ እነርሱ ወጥቶ። ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ አላቸው። 30 እነርሱም መልሰው። ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር አሉት። 31 ጲላጦስም። እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት አላቸው። አይሁድም። ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም አሉት፤ 32 ኢየሱስ በምን ዓይነት ሞት ሊሞት እንዳለው ሲያመለክት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 33 ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን ጠርቶ። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? አለው። 34 ኢየሱስም መልሶ። አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን? አለው። 35 ጲላጦስ መልሶ። እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው። 36 ኢየሱስም መልሶ። መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፥ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም አለው። 37 ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። 38 ጲላጦስ። እውነት ምንድር ነው? አለው። ይህንም ብሎ ዳግመኛ ወደ አይሁድ ወጥቶ። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም። 39 ነገር ግን በፋሲካ አንድ ልፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን? አላቸው። 40 ሁሉም ደግመው። በርባንን እንጂ ይህን አይደለም እያሉ ጮኹ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።

የዮሐንስ 19

1 በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። 2 ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤ 3 እየቀረቡም። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ይሉት ነበር፤ 4 በጥፊም ይመቱት ነበር። ጲላጦስም ደግሞ ወደ ውጭ ወጥቶ። እነሆ፥ አንዲት በደል ስንኳ እንዳላገኘሁበት ታውቁ ዘንድ እርሱን ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ አላቸው። 5 ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ቀይ ልብስም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ። 6 ጲላጦስም። እነሆ ሰውዬው አላቸው። የካህናት አለቆችና ሎሌዎች ባዩትም ጊዜ። ስቀለው ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትምና እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት አላቸው። 7 አይሁድም መልሰው። እኛ ሕግ አለን፥ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባዋል፥ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና አሉት። 8 ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤ 9 ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም። 10 ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው። 11 ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው። 12 ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ። 13 ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ። 14 ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው። 15 እነርሱ ግን። አስወግደው፥ አስወግደው፥ ስቀለው እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም። ንጉሣችሁን ልስቀለውን? አላቸው። የካህናት አለቆችም። ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም ብለው መለሱለት። 16 ስለዚህ በዚያን ጊዜ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። 17 ኢየሱስንም ይዘው ወሰዱት፤ መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሉት ወጣ። 18 በዚያም ሰቀሉት፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሁለት፥ አንዱን በዚህ አንዱን በዚያ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ። 19 ጲላጦስም ደግሞ ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ ጽሕፈቱም። የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚል ነበረ። 20 ኢየሱስም የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ነበረና ከአይሁድ ብዙዎች ይህን ጽሕፈት አነበቡት፤ በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ተጽፎ ነበር። 21 ስለዚህ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት። 22 ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ። 23 ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። 24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 25 ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። 26 ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። 27 ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። 28 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ። 29 በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት። 30 ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። 31 አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። 32 ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤ 33 ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤ 34 ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ። 35 ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል። 36 ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። 37 ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል። 38 ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። 39 ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። 40 የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። 41 በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። 42 ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።

የዮሐንስ 20

1 ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። 2 እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ። ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው። 3 ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4 ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ 5 ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። 6 ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ 7 ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። 8 በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ 9 ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። 10 ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ። 11 ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ 12 ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። 13 እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም። ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። 14 ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። 15 ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። 16 ኢየሱስም። ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው። 17 ኢየሱስም። ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት። 18 መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች። 19 ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። 20 ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 21 ኢየሱስም ዳግመኛ። ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። 22 ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። 23 ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው። 24 ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። 25 ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት። እርሱ ግን። የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። 26 ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። 27 ከዚያም በኋላ ቶማስን። ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው። 28 ቶማስም። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት። 29 ኢየሱስም። ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። 30 ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ 31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።

የዮሐንስ 21

1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ተገለጠላቸው፤ 2 እንዲህም ተገለጠ። ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ ከገሊላ ቃና የሆነ ናትናኤልም የዘብዴዎስም ልጆች ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። 3 ስምዖን ጴጥሮስ። ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ አላቸው። እነርሱም። እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ በዚያችም ሌሊት ምንም እላጠመዱም። 4 በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። 5 ኢየሱስም። ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። የለንም ብለው መለሱለት። 6 እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው። 7 ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን። ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ። 8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። 9 ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ። 10 ኢየሱስም። አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ አላቸው። 11 ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም። 12 ኢየሱስም። ኑ፥ ምሳ ብሉ አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ ስንኳ። አንተ ማን ነህ? ብሎ ሊመረምረው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። 13 ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን። 14 ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ። 15 ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። 16 ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። 17 ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ። 18 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። 19 በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ። ተከተለኝ አለው። 20 ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ። ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው? ያለው ነበረ። 21 ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው። 22 ኢየሱስም። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው። 23 ስለዚህ። ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አለው እንጂ አይሞትም አላለውም። 24 ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፥ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን። 25 ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።

የሐዋርያት ሥራ 1

3 ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። 4 ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ 5 ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ። 6 እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። 7 እርሱም። አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ 8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። 9 ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። 10 እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ 11 ደግሞም። የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው። 12 በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው። 13 በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም። 14 እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር። 15 በዚህም ወራት ጴጥሮስ መቶ ሀያ በሚያህል በሰዎች ማኅበር አብረው በነበሩ በወንድሞቹ መካከል ተነሥቶ አለ። 16 ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት መሪ ስለሆናቸው ስለ ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር፤ 17 ከእኛ ጋር ተቈጥሮ ነበርና፥ ለዚህም አገልግሎት ታድሎ ነበርና። 18 ይህም ሰው በዓመፅ ዋጋ መሬት ገዛ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ አንጀቱም ሁሉ ተዘረገፈ፤ 19 በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህም ያ መሬት በቋንቋቸው አኬልዳማ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም የደም መሬት ማለት ነው። 20 በመዝሙር መጽሐፍ። መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም። ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአልና። 21-22 ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል። 23 ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ። 24-25 ሲጸልዩም። የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ። 26 ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።

የሐዋርያት ሥራ 2

1 በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ 2 ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። 3 እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። 4 በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። 5 ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ 6 ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። 7 ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ። እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? 8 እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? 9 የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ 10 በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ 11 የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። 12 ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው። እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ። 13 ሌሎች ግን እያፌዙባቸው። ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ። 14 ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። 15 ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ 16 ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። 17 እግዚአብሔር ይላል። በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ 18 ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። 19 ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ 20 ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። 21 የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል። 22 የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ 23 እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። 24 እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። 25 ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። 26 ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ 27 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። 28 የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ። 29 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። 30 ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ 31 ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። 32 ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ 33 ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34-35 ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው 36 አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። 37 ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት። ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። 38 ጴጥሮስም። ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። 39 የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው። 40 በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና። ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው። 41 ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤ 42 በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። 43 ነገር ግን በሰው ሁሉ ፍርሀት ሆነ፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ድንቅና ምልክት ተደረገ። 44 ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ 45 ያላቸውንም ሁሉ አንድነት አደረጉ። መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ፥ ማንኛውም እንደሚፈልግ ለሁሉ ያካፍሉት ነበር። 46 በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ 47 እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 3

1 ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። 2 ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። 3 እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። 4 ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ። ወደ እኛ ተመልከት አለው። 5 እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። 6 ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው። 7 በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ 8 ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። 9 ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ 10 መልካምም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደ ሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። 11 እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። 12 ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? 13 የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። 14 እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥ 15 የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። 16 በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። 17 አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ 18 እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። 19-20 እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። 21 እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና። 22 ሙሴም ለአባቶች። ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። 23 ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ። 24 ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ። 25 እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም። በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ። 26 ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።

የሐዋርያት ሥራ 4

1 ለሕዝቡም ሲናገሩ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዥ ሰዱቃውያንም፥ 2 ሕዝቡን ስለ አስተማሩና በኢየሱስ የሙታንን ትንሣኤ ስለ ሰበኩ ተቸግረው፥ ወደ እነርሱ ቀረቡ፥ 3 እጃቸውንም ጭነውባቸው አሁን መሽቶ ነበርና እስከ ማግሥቱ ድረስ በወኅኒ አኖሩአቸው። 4 ነገር ግን ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑ፥ የወንዶችም ቍጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ። 5-6 በነገውም አለቆቻቸውና ሽማግሌዎች ጻፎችም ሊቀ ካህናቱ ሐናም ቀያፋም ዮሐንስም እስክንድሮስም የሊቀ ካህናቱም ዘመዶች የነበሩት ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 7 እነርሱንም በመካከል አቁመው። በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ? ብለው ጠየቁአቸው። 8 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ እንዲህ አላቸው። እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች፥ 9 እኛ ዛሬ ለድውዩ ሰው ስለ ተደረገው መልካም ሥራ ይህ በምን እንደዳነ ብንመረመር፥ 10 እናንተ በሰቀላችሁት እግዚአብሔርም ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ እንደ ቆመ፥ ለእናንተ ለሁላችሁ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን። 11 እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፥ የማዕዘን ራስ የሆነው ይህ ድንጋይ ነው። 12 መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና። 13 ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ፥ ከኢየሱስም ጋር እንደ ነበሩ አወቁአቸው፤ 14 የተፈወሰውንም ሰው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ሲያዩ የሚመልሱትን አጡ። 15 ከሸንጎም ወደ ውጭ ይወጡ ዘንድ አዝዘው። በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? 16 የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፥ እንሸሽገው ዘንድ አንችልም፤ 17 ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው ብለው እርስ በርሳቸው ተማከሩ። 18 ጠርተውም በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው። 19 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቍረጡ፤ 20 እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም አሉአቸው። 21 እነርሱም እንደ ምን እንደሚቀጡ ምክንያት ስላላገኙባቸው፥ እንደ ገና ዝተው ከሕዝቡ የተነሣ ፈቱአቸው፤ ሰዎች ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበርና። 22 ይህ የመፈወስ ምልክት የተደረገለት ሰው ከአርባ ዓመት ይበልጠው ነበርና። 23 ተፈትተውም ወደ ወገኖቻቸው መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሉአቸውን ሁሉ ነገሩአቸው። 24 እነርሱም በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ የፈጠርህ፥ 25 በመንፈስ ቅዱስም በብላቴናህ በአባታችን በዳዊት አፍ። አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ? ሕዝቡስ ከንቱን ነገር ለምን አሰቡ? 26 የምድር ነገሥታት ተነሡ አለቆችም በጌታና በተቀባው ላይ አብረው ተከማቹ ብለህ የተናገርህ አምላክ ነህ። 27-28 በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር፥ እጅህና አሳብህ እንዲሆን አስቀድመው የወሰኑትን ሁሉ ሊፈጽሙ፥ በዚች ከተማ በእውነት ተሰበሰቡ። 29-30 አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው። 31 ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ። 32 ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም። 33 ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው። 34 በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥ 35 በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር። 36 ትውልዱም የቆጵሮስ ሰው የነበረ አንድ ሌዋዊ ዮሴፍ የሚሉት ነበረ፥ እርሱም በሐዋርያት በርናባስ ተባለ ትርጓሜውም የመጽናናት ልጅ ነው፤ 37 እርሻም ነበረውና ሽጦ ገንዘቡን አምጥቶ ከሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው።

የሐዋርያት ሥራ 5

1 ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፥ 2 ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። 3 ጴጥሮስም። ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? 4 ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው። 5 ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። 6 ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት አውጥተውም ቀበሩት። 7 ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች። 8 ጴጥሮስም መልሶ። እስቲ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን? አላት። እርስዋም። አዎን፥ ይህን ለሚያህል ነው አለች። 9 ጴጥሮስም። የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል አላት። 10 ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት አውጥተውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት። 11 በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። 12 በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። 13 ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥ 14 ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። 15 ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። 16 ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። 17 ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው። 18 በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። 19 የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና። 20 ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው። 21 በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፥ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። 22-23 ሎሌዎችም መጥተው በወኅኒው አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም። ወኅኒው በጣም በጥንቃቄ ተዘግቶ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ቆመው አገኘን፥ በከፈትን ጊዜ ግን በውስጡ አንድ ስንኳ አላገኘንም አሉአቸው። 24 የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ። እንጃ ይህ ምን ይሆን? እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። 25 አንድ ሰውም መጥቶ። እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው ብሎ አወራላቸው። 26 በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና። 27 አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። 28 ሊቀ ካህናቱም። በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው። 29 ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ። ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። 30 እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ 31 ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። 32 እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው። 33 እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። 34 ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ 35 እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 36 ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። 37 ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። 38 አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ 39 ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። 40 ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። 41 እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ 42 ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 6

1 በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። 2 አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። 3 ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ 4 እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን። 5 ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። 6 በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። 7 የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ። 8 እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። 9 የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ 10 ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። 11 በዚያን ጊዜ። በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። 12 ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አናደዱ፥ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና። 13 ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ 14 ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። 15 በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።

የሐዋርያት ሥራ 7

1 ሊቀ ካህናቱም። ይህ ነገር እንዲህ ነውን? አለው፤ 2 እርሱም እንዲህ አለ። ወንድሞችና አባቶች ሆይ፥ ስሙ። የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና። 3 ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው። 4 በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከዚያም አባቱ ከሞተ በኋላ እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው። 5 በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው። 6 እግዚአብሔርም ዘሩ በሌላ አገር መጻተኞች እንዲሆኑ አራት መቶ ዓመትም ባሪያዎች እንዲያደርጉአቸው እንዲያስጨንቁአቸውም እንዲህ ተናገረ፤ 7 ደግሞም እግዚአብሔር። እንደ ባሪያዎች በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርድባቸዋለሁ፥ ከዚህም በኋላ ይወጣሉ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል አለ። 8 የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ እንዲሁም ይስሐቅን ወለደ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው ይስሐቅም ያዕቆብን ያዕቆብም አሥራ ሁለቱን የአባቶችን አለቆች። 9 የአባቶችም አለቆች በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ 10 ከመከራውም ሁሉ አወጣው፥ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስንና ጥበብን ሰጠው፥ በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይም ቢትወደድ አድርጎ ሾመው። 11 በግብፅና በከነዓንም አገር ሁሉ ራብና ብዙ ጭንቅ መጣ፥ አባቶቻችንም ምግብን አላገኙም። 12 ያዕቆብም በግብፅ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ በመጀመሪያ አባቶቻችንን ሰደዳቸው፤ 13 በሁለተኛውም ዮሴፍ ለወንድሞቹ ታወቀ፥ የዮሴፍም ትውልድ በፈርዖን ዘንድ ተገለጠ። 14 ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የነበረውን ቤተ ዘመድ ሁሉ ልኮ አስጠራ። 15 ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ እርሱም ሞተ አባቶቻችንም፤ 16 ወደ ሴኬምም አፍልሰው አብርሃም ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በብር በገዛው መቃብር ቀበሩአቸው። 17-18 እግዚአብሔርም ለአብርሃም የማለለት የተስፋው ዘመን ሲቀርብ፥ ዮሴፍን የማያውቀው ሌላ ንጉሥ በግብፅ ላይ እስኪነሣ ድረስ፥ ሕዝቡ እየተጨመሩ በግብፅ በዙ። 19 እርሱም ወገናችንን ተተንኵሎ ሕፃናትን በሕይወት እንዳይጠብቁ ወደ ውጭ ይጥሉ ዘንድ አድርጎ አባቶቻችንን አስጨነቀ። 20 በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ በእግዚአብሔርም ፊት ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ፤ 21 በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አነሣችው ልጅም ይሆናት ዘንድ አሳደገችው። 22 ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፥ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ። 23 ነገር ግን አርባ ዓመት ሲሞላው ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ይጐበኝ ዘንድ በልቡ አሰበ። 24 አንዱም ሲበደል አይቶ ረዳው፥ የግብፅን ሰውም መትቶ ለተገፋው ተበቀለ። 25 ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር፥ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። 26 በማግሥቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፥ ሊያስታርቃቸውም ወዶ። ሰዎች ሆይ፥ እናንተስ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? አላቸው። 27 ያም ባልንጀራውን የሚበድል ግን። አንተን በእኛ ላይ ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? 28 ወይስ ትናንትና የግብፁን ሰው እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትወዳለህን? ብሎ ገፋው። 29 ሙሴም ከዚህ ነገር የተነሣ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ልጆች ወለደ። 30 አርባ ዓመትም ሲሞላ የጌታ መልአክ በሲና ተራራ ምድረ በዳ በቍጥቋጦ መካከል በእሳት ነበልባል ታየው። 31-32 ሙሴም አይቶ ባየው ተደነቀ፤ ሊመለከትም ሲቀርብ የጌታ ቃል። እኔ የአባቶችህ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ ብሎ ወደ እርሱ መጣ። ሙሴም ተንቀጥቅጦ ሊመለከት አልደፈረም። 33 ጌታም። የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና የእግርህን ጫማ አውልቅ። 34 በግብፅ ያሉትን የሕዝቤን መከራ ፈጽሜ አይቼ መቃተታቸውንም ሰምቼ ላድናቸው ወረድሁ፤ አሁንም ና፥ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ አለው። 35 ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው። 36 ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው። 37 ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች። እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው። 38 ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤ 39 ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤ 40 አሮንንም። በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት። 41 በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው። 42 እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን? 43 ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል። 44 እንዳየው ምስል አድርጎ ይሠራት ዘንድ ሙሴን ተናግሮ እንዳዘዘው፥ የምስክር ድንኳን ከአባቶቻችን ዘንድ በምድረ በዳ ነበረች፤ 45 አባቶቻችንም ደግሞ በተራ ተቀብለው እግዚአብሔር በፊታቸው ያወጣቸውን የአሕዛብን አገር በያዙት ጊዜ ከኢያሱ ጋር አገቡአት፥ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ ኖረች። 46 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያን ያገኝ ዘንድ ለመነ። 47 ነገር ግን ሰሎሞን ቤት ሠራለት። 48-50 ነገር ግን ነቢዩ። ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፥ ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፥ ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም። 51 እናንተ አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ፥ እናንተ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንደ ተቃወሙት እናንተ ደግሞ። 52-53 ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም። 54 ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት። 55 መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና። 56 እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ። 57 በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፥ 58 ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። 59 እስጢፋኖስም። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። 60 ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 8

1 በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ። 2 በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት። 3 ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር። 4 የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ። 5 ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። 6 ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። 7 ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ 8 በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። 9 ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። 10 ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ። ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። 11 ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። 12 ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። 13 ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። 14 በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። 15 እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ 16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። 17 በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። 18 ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና። 19 እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። 20 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው። የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። 21 ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። 22 እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ 23 በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና። 24 ሲሞንም መልሶ። ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው። 25 እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ። 26 የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው። 27 ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ 28 ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። 29 መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። 30 ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። 31 እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። 32 ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። 33 በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? 34 ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። 35 ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። 36 በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። 37 ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። 38 ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። 39 ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና። 40 ፊልጶስ ግን በአዛጦን ተገኘ፥ ወደ ቂሣርያም እስኪመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 9

1 ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ 2 በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። 3 ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ 4 በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። 5 ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። 6 እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ። ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም። ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው። 7 ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። 8 ሳውልም ከምድር ተነሣ፥ አይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። 9 ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም። 10 በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ። ሐናንያ ሆይ፥ አለው። እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ አለ። 11 ጌታም። ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ 12 እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል አለው። 13 ሐናንያም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ 14 በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ። 15 ጌታም። ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ 16 ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው። 17 ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ። 18 ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥ 19 መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ። 20 ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። 21 የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና። ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን? አሉ። 22 ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። 23 ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ 24 ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ 25 ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት። 26 ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት። 27 በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረ ተረከላቸው። 28 በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ 29 ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ። 30 ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት ወደ ጠርሴስም ሰደዱት። 31 በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር። 32 ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። 33 በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። 34 ጴጥሮስም። ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ አለው። 35 ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። 36 በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። 37 በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። 38 ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። 39 ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። 40 ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። 41 እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። 42 ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ፥ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። 43 በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ።

የሐዋርያት ሥራ 10

1 በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። 2 እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። 3 ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል። ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። 4 እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ። ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው። ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። 5 አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ። 6 እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል። 7 የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥ 8 ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው። 9 እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፥ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ። 10 ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፤ 11 ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ 12 በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። 13 ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። 14 ጴጥሮስ ግን። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ። 15 ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። 16 ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ። 17 ጴጥሮስም ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፥ እነሆ፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለ ስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ 18 ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን? ብለው ይጠይቁ ነበር። 19 ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፥ መንፈስ። እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ 20 ተነሥተህ ውረድ፥ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው። 21 ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው? አላቸው። 22 እነርሱም። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት። 23 እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንድግድነት ተቀበላቸው። በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፥ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። 24 በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር። 25 ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት። 26 ጴጥሮስ ግን። ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው። 27 ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፥ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ። 28 አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ 29 ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ። አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ አላቸው። 30 ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው። በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። 31 ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ። 32 እንግዲህ ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤ እርሱ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ እንግድነት ተቀምጦአል አለኝ። 33 ስለዚህ ያን ጊዜ ወደ አንተ ላክሁ፥ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዝኸውን ሁሉ እንድንሰማ እኛ ሁላችን አሁን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን። 34-35 ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ። 36 የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። 37 ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። 38 እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ 39 እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40 እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ 41 ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። 42 ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። 43 በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። 44 ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። 45 ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ 46 በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና። 47 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። 48 በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።

የሐዋርያት ሥራ 11

1 ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። 2 ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው። 3 ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት። 4 ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ። 5 እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ 6 ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። 7 ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። 8 እኔም። ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ። 9 ሁለተኛም። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። 10 ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። 11 እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። 12 መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። 13 እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና። ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ 14 እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል እንዳለው ነገረን። 15 ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው። 16 ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። 17 እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ? 18 ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና። እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ። 19 በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፥ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር። 20 ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ። 21 የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። 22 ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤ 23 እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤ 24 ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ። 25 በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤ 26 ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ። 27 በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ 28 ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ። 29 ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤ 30 እንዲህም ደግሞ አደረጉ፥ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።

የሐዋርያት ሥራ 12

1 በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። 2 የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። 3 አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ። 4 በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው። 5 ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። 6 ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። 7 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። 8 መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ። 9 ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። 10 የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። 11 ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ። ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ። 12 ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። 13 ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ 14 የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። 15 እነርሱም። አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም። መልአኩ ነው አሉ። 16 ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። 17 ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና። ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። 18 በነጋም ጊዜ። ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን? ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። 19 ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ። 20 ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና። 21 በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤ 22 ሕዝቡም። የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ። 23 ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ። 24 የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር። 25 በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።

የሐዋርያት ሥራ 13

1 በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። 2 እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። 3 በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። 4 እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። 5 በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። 6 ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ 7 እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። 8 ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። 9 ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው። 10 አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? 11 አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። 12 በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። 13 ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 14 እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። 15 ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች። ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው። 16 ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ። የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ። 17 የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። 18 በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። 19 በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። 20 ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። 21 ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ 22 እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም። እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ። 23 ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። 24 ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። 25 ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ። እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር። 26 እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። 27 በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ 28 ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ 29 ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። 30 እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ 31 በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። 32 እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ 33 ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። 34 እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ። የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል። 35 ደግሞ በሌላ ስፍራ። ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና። 36 ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ 37 ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። 38-39 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 40-41 እንግዲህ። እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። 42 በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። 43 ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። 44 በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። 45 አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። 46 ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው። የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። 47 እንዲሁ ጌታ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ። 48 አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ 49 የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። 50 አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። 51 እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። 52 በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።

የሐዋርያት ሥራ 14

1 በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። 2 ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም። 3 ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። 4 የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኵሌቶቹ ከአይሁድ እኵሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። 5 አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ 6 አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ 7 በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር። 8 በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። 9 ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ 10 በታላቅ ድምፅ። ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። 11 ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ። አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል አሉ፤ 12 በርናባስንም ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ ሄርሜን አሉት። 13 በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። 14 ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ 15 እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። 16 እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። 17 ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም። 18 ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው። 19 አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። 20 ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ። 21-22 በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ። 23 በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው። 24 በጲስድያም አልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፥ 25 በጴርጌንም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ አጣልያ ወረዱ፥ 26 ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። 27 በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ። 28 ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ።

የሐዋርያት ሥራ 15

1 አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና። እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር። 2 በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ። 3 ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፥ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው። 4 ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ። 5 ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው። ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ። 6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ። 7 ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። 8 ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ 9 ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። 10 እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ? 11 ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን። 12 ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፥ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር። 13 እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ። ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ። 14 እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። 15 ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይሰማማል፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 16-17 ከዚህ በኋላ የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እመለሳለሁ፥ የወደቀችውንም የዳዊትን ድንኳን እንደ ገና እሠራታለሁ፥ ፍራሽዋንም እንደ ገና እሠራታለሁ እንደ ገናም አቆማታለሁ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። 18 ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው። 19 ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ 20 ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ። 21 ሙሴስ ከቀደሙት ትውልድ ጀምሮ በሰንበት በሰንበት በምኵራቦቹ ሲያነቡ በየከተማው እርሱን የሚሰብኩ አሉት። 22 ያን ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ ፈቀዱ፤ እነርሱም በወንድሞች መካከል ዋናዎች ሆነው በርስያን የተባለው ይሁዳና ሲላስ ነበሩ። 23 እንዲህም ጽፈው በእነርሱ እጅ ላኩ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ። 24 ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው። ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፥ 25-26 ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን። 27 ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። 28-29 ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ። 30 እነርሱም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፥ ሕዝቡንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። 31 ባነበቡትም ጊዜ ከምክሩ የተነሣ ደስ አላቸው። 32 ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው። 33 አያሌ ቀንም ከተቀመጡ በኋላ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ሐዋርያት ሄዱ። 34 ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ። 35 ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር። 36 ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን። ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው። 37 በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ 38 ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፥ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፥ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። 39 ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። 40 ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፥ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ወጣ፤ 41 አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 16

1 ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ። 2 ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት። 3 ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፥ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና። 4 በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። 5 አብያተ ክርስቲያናትም በሃያማኖት ይበረቱ ነበር፥ በቍጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር። 6 በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ 7 በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ 8 በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። 9 ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው። ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር። 10 ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና። 11 ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ 12 ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር። 13 በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። 14 ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። 15 እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ። በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን። 16 ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። 17 እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች። የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። 18 ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን። ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። 19 ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ 20 ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። 21 እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ። 22 ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ 23 በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። 24 እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። 25 በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር 26 ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ። 27 የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። 28 ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። 29 መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ 30 ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው። 31 እነርሱም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። 32 ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። 33 በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ 34 ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። 35 በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ። እነዚያን ሰዎች ፍታቸው ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ። 36 የወኅኒውም ጠባቂ። ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው። 37 ጳውሎስ ግን። እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው። 38 ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ። የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ፤ 39 መጥተውም ማለዱአቸው፥ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው። 40 ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፥ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ።

የሐዋርያት ሥራ 17

1 በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። 2 ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ 3 ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ። ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር። 4 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ። 5 አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤ 6 ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው። ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤ 7 እነዚህም ሁሉ። ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ። 8 ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥ 9 ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው። 10 ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ 11 እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። 12 ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ። 13 በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ። 14 በዚያን ጊዜም ወንድሞቹ ወዲያው ጳውሎስን እስከ ባሕር ድረስ ይሄድ ዘንድ ሰደዱት፤ ሲላስና ጢሞቴዎስም በዚያው ቀሩ። 15 ጳውሎስን የሸኙት ግን እስከ አቴና አደረሱት፥ እንደሚቻላቸውም በፍጥነት ወደ እርሱ ይመጡ ዘንድ ወደ ሲላስና ወደ ጢሞቴዎስ ትእዛዝ ተቀብለው ሄዱ። 16 ጳውሎስም በአቴና ሲጠብቃቸው ሳለ፥ በከተማው ጣዖት መሙላቱን እየተመለከተ መንፈሱ ተበሳጨበት። 17 ስለዚህም በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር። 18 ከኤፊቆሮስ ወገንና ኢስጦኢኮችም ከተባሉት ፈላስፎች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር ተገናኙ። አንዳንዶቹም። ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል? አሉ፤ ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው። አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል አሉ። 19-20 ይዘውም። ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ ይቻለናልን? በጆሮአችን እንግዳ ነገር ታሰማናለህና፤ እንግዲህ ይህ ነገር ምን እንደሆነ እናውቅ ዘንድ እንፈቅዳለን ብለው አርዮስፋጎስ ወደ ተባለው ስፍራ ወሰዱት። 21 የአቴና ሰዎች ሁሉና በዚያ የኖሩ እንግዶች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በቀር በሌላ ጉዳይ አይውሉም ነበርና። 22 ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ። የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። 23 የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ። ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። 24 ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ 25 እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም። 26-27 ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። 28 ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን። 29 እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። 30 እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ 31 ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። 32 የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን። ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። 33 እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ። 34 አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።

የሐዋርያት ሥራ 18

1 ከዚህም በኋላ ጳውሎስ ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ መጣ። 2 በወገኑም የጳንጦስ ሰው የሚሆን አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በፊት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ከኢጣልያ መጥቶ ነበር፥ አይሁድ ከሮሜ ይወጡ ዘንድ ቀላውዴዎስ አዞ ነበርና፤ ወደ እነርሱ ቀረበ፥ 3 ሥራቸውም አንድ ስለ ነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ፤ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበረና። 4 በየሰንበቱም ሁሉ በምኵራብ ይነጋገር ነበር፥ አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር። 5 ሲላስና ጢሞቴዎስም ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፥ ጳውሎስ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እየመሰከረ ለቃሉ ይተጋ ነበር። 6 ነገር ግን በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፥ ልብሱን እያራገፈ። ደማችሁ በራሳችሁ ነው፤ እኔ ንጹሕ ነኝ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ አላቸው። 7 ከዚያም ወጥቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ገባ ቤቱም በምኩራብ አጠገብ ነበረ። 8 የምኵራብ አለቃ ቀርስጶስም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፥ ከቆሮንቶስ ሰዎችም ብዙ በሰሙ ጊዜ አምነው ተጠመቁ። 9-10 ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው። 11 በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ። 12 ጋልዮስም በአካይያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ፥ አይሁድ በአንድ ልብ ሆነው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፥ ወደ ፍርድ ወንበርም አምጥተው። 13 ይህ ሕግን ተቃውሞ እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ያባብላል አሉ። 14 ጳውሎስም አፉን ሊከፍት ባሰበ ጊዜ፥ ጋልዮስ አይሁድን። አይሁድ ሆይ፥ ዓመፅ ወይም ክፉ በደል በሆነ እንድታገሣችሁ በተገባኝ፤ 15 ስለ ቃልና ስለ ስሞች ስለ ሕጋችሁም የምትከራከሩ ከሆነ ግን፥ ራሳችሁ ተጠንቀቁ እኔ በዚህ ነገር ፈራጅ እሆን ዘንድ አልፈቅድምና አላቸው። 16 ከፍርድ ወንበርም ፊት አስወጣቸው። 17 የግሪክ ሰዎችም ሁሉ የምኩራብ አለቃ ሶስቴንስን ይዘው በወንበሩ ፊት መቱት፤ በእነዚህም ነገሮች ጋልዮስ ግድ የለውም ነበር። 18 ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጅግ ቀን ተቀምጦ ወንድሞቹንም ተሰናብቶ በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ፤ ስለትም ነበረበትና ራሱን በክንክራኦስ ተላጨ፤ ጵርስቅላና አቂላም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 19 ወደ ኤፌሶንም በደረሱ ጊዜ እነዚያን ከዚያ ተዋቸው፥ ራሱ ግን ወደ ምኵራብ ገብቶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር። 20 እነርሱም ብዙ ጊዜ እንዲቀመጥላቸው ሲለምኑት እሺ አላለም፤ 21 ነገር ግን ሲሰናበታቸው። የሚመጣውን በዓል በኢየሩሳሌም አደርግ ዘንድ ይገባኛል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ግን ወደ እናንተ ደግሞ እመለሳለሁ አላቸው። ከኤፌሶንም በመርከብ ተነሣ። 22 ወደ ቂሣርያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ። 23 ጥቂት ቀንም ቆይቶ ወጣ፥ ደቀ መዛሙርትንም ሁሉ እያጸና በገላትያ አገርና በፍርግያ በተራ አለፈ። 24 በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ። 25 እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር። 26 እርሱም በምኵራብ ገልጦ ይናገር ጀመር። ጵርስቅላና አቂላም በሰሙት ጊዜ፥ ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት። 27 እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈቀደ ጊዜ፥ ወንድሞቹ አጸናኑት፥ ይቀበሉትም ዘንድ ወደ ደቀ መዛሙርት ጻፉለት፤ በደረሰም ጊዜ አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤ 28 ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና።

የሐዋርያት ሥራ 19

1 አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ 2 አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም። አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። 3 እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም። በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። 4 ጳውሎስም። ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። 5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ 6 ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። 7 ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። 8 ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። 9 አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። 10 በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። 11 እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ 12 ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። 13 አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። 14 የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። 15 ክፉው መንፈስ ግን መልሶ። ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። 16 ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም። 17 ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ 18 አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። 19 ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። 20 እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር። 21 ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ። ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። 22 ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። 23 በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። 24 ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ 25 እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። 26 ይህም ጳውሎስ። በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል። 27 ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል። 28 ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ። 29 ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። 30 ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። 31 ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። 32 ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። 33 አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። 34 አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። 35 የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ። የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? 36 ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። 37 የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። 38 ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። 39 ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። 40 ዛሬ ስለ ተደረገው። ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና። 41 ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው።

የሐዋርያት ሥራ 20

1 ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ። 2 ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ። 3 በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ። 4 የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤ 5 እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን። 6 እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። 7 ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ። 8 ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ። 9 አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። 10 ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። 11 ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። 12 ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ። 13 እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና። 14 በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤ 15 በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፥ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን። 16 ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና። 17 ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤ 18-19 ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ 20-21 ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም። 22 አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ 23 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ። እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። 24 ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። 25 አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ። 26 ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። 27 የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። 28 በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 29-30 ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። 31 ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ። 32 አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ። 33 ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ 34 እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ። 35 እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ። 36 ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ። 37 ሁሉም እጅግ አለቀሱ፥ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤ 38 ይልቁንም። ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም ስላላቸው ነገር እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።

የሐዋርያት ሥራ 21

1 ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ 2 ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። 3 ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። 4 ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት። 5 ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ 6 እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 7 እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። 8 በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። 9 ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10 አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። 11 ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ። ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። 12 ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። 13 ጳውሎስ ግን መልሶ። እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። 14 ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ። የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን። 15 ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። 16 በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። 17 ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። 18 በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። 19 ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። 20 እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም። ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። 21 ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። 22 እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። 23 እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24 እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፥ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። 25 አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል። 26 በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ። 27-28 ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ እርዱን ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። 29 በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። 30 ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። 31 ሊገድሉትም ሲፈልጉ። ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ 32 እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። 33 በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። 34 ሕዝቡም እኵሌቶቹ እንዲህ እኵሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። 35 ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ 36 ብዙ ሕዝብ። አስወግደው እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። 37 ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን። አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን? አለው። እርሱም። የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? 38 አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብፅ ሰው አይደለህምን? አለ። 39 ጳውሎስ ግን። እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ አለ። 40 በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።

የሐዋርያት ሥራ 22

1 እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ ስሙኝ። 2 በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ። 3 እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ 4 ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። 5 እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። 6 ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ 7 በምድርም ላይ ወድቄ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። 8 እኔም መልሼ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ። 9 ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም። 10 ጌታ ሆይ፥ ምን ላድርግ? አልሁት። ጌታም። ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል አለኝ። 11 ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። 12 በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። 13 እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ። 14 እርሱም አለኝ። የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል 15 ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። 16 አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ። 17 ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥ 18 እርሱም። ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት። 19 እኔም። ጌታ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤ 20 የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ። 21 እርሱም። ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና አለኝ። 22 እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና አሉ። 23 ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥ 24 የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ። እየገረፋችሁ መርምሩት አላቸው። 25 በጠፍርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ። የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን? አለው። 26 የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ። ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው። 27 የሻለቃውም ቀርቦ። አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ አለው፤ እርሱም። አዎን አለ። 28 የሻለቃውም መልሶ። እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት አለ። ጳውሎስም። እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ አለ። 29 ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና። 30 በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፥ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፥ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።

የሐዋርያት ሥራ 23

1 ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ። 2 ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። 3 በዚያን ጊዜ ጳውሎስ። አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው። 4 በአጠገቡ የቆሙትም። የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት። 5 ጳውሎስም። ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው። 6 ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። 7 ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ። 8 ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። 9 ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ። 10 ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ። 11 በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ። ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው። 12 በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ። 13 ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤ 14 እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው። ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል። 15 እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው። 16 የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። 17 ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ። ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው። 18 እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና። ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው። 19 የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ። የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው። 20 እርሱም። አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። 21 እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው። 22 የሻለቃውም። ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው። 23 ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ። ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው። 24 ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው። 25 ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል። 26 ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። 27 ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና። 28 የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤ 29 በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም። 30 በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን። 31 ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤ 32 በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ። 33 እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት። 34 ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ። 35 ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ።

የሐዋርያት ሥራ 24

1 ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት። 2-3 በተጠራም ጊዜ ጠርጠሉስ ይከሰው ዘንድ ጀመረ እንዲህ እያለ። ክቡር ፊልክስ ሆይ፥ በአንተ በኩል ብዙ ሰላም ስለምናገኝ ለዚህም ሕዝብ በአሳብህ በየነገሩ በየስፍራውም መልካም መሻሻል ስለሚሆንለት፥ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን። 4 ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። 5 ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ 6 መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። 7 ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥ 8 ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። 9 አይሁድም ደግሞ። ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ። 10 ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ 11 እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። 12 ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። 13 አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። 14 ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ 15 እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። 16 ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። 17 ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ 18 ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። 19 ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። 20-21 ወይም በመካከላቸው ቆሜ። ዛሬ ስለ ሙታን መነሣት በፊታችሁ በእኔ ይፈርዱብኛል ብዬ ከጮኽሁት ከዚህ ከአንድ ነገር በቀር፥ በሸንጎ ፊት ቆሜ ሳለሁ በእኔ አንድ ዓመፃ ያገኙ እንደ ሆን እነዚህ ራሳቸው ይናገሩ። 22 ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው። 23 የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው። 24 ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። 25 እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ። አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት። 26 ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። 27 ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።

የሐዋርያት ሥራ 25

1 ፊስጦስም ወደ አውራጃው ገብቶ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2 የካህናቱ አለቆችና የአይሁድም ታላላቆች በጳውሎስ ላይ አመለከቱ፥ 3 ጳውሎስንም ሲቃወም እንዲያደላላቸው እየለመኑ፥ በመንገድ ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ አስበው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው ማለዱት። 4 ፊስጦስ ግን ጳውሎስ በቂሳርያ እንዲጠበቅ እርሱም ራሱ ወደዚያ ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ እንዳለው መለሰላቸው፤ 5 እንግዲህ በዚህ ሰው ክፋት ቢሆን ከእናንተ ዘንድ ያሉት ባለ ስልጣኖች ከእኔ ጋር ወርደው ይክሰሱት አላቸው። 6 በእነርሱም ዘንድ ከስምንት ወይም ከአስር የማይበልጥ ቀን ተቀምጦ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በነገውም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ። 7 በቀረበም ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱት አይሁድ ከበውት ቆሙ፥ ይረቱበትም ዘንድ የማይችሉትን ብዙና ከባድ ክስ አነሱበት፤ 8 ጳውሎስም ሲምዋገት። የአይሁድን ህግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሳርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ። 9 ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን። ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን? ብሎ መለሰለት። 10 ጳውሎስ ግን። እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም። 11 እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ። 12 በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ ብሎ መለሰለት። 13 ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ። 14 በዚያውም ብዙ ቀን ስለተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ። ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤ 15 በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ። 16 እኔም። ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው። 17 ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ። 18 ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤ 19 ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ። ሕያው ነው ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር። 20 እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን? አልሁት። 21 ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቈርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ። 22 አግሪጳም ፊስጦስን። ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም። ነገ ትሰማዋለህ አለው። 23 በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት። 24 ፊስጦስም አለ። አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ። 25 እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፥ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ። 26 ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አመጣሁት፤ 27 እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።

የሐዋርያት ሥራ 26

1 አግሪጳም ጳውሎስን። ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መለሰ እንዲህ ሲል። 2-3 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 4 ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ 5 ሊመሰክሩ ይወዱ እንደ ሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። 6 አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። 7 ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። 8 እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል? 9 እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። 10 ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። 11 በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር። 12 ስለዚህም ነገ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ 13 ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ 14 ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። 15 እኔም። ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። 16 ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። 17-18 የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ። 19 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። 20 ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ። 21 ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ። 22-23 ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም። 24 እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ። ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል አለው። 25 ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ። ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። 26 በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። 27 ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ። 28 አግሪጳም ጳውሎስን። በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ አለው። 29 ጳውሎስም። በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ አለው። 30 ንጉሡም አገረ ገዡም በርኒቄም ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፥ 31 ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ ብለው ተነጋገሩ። 32 አግሪጳም ፈስጦስን። ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር አለው።

የሐዋርያት ሥራ 27

1 ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቈረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። 2 በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። 3 በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። 4 ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ 5 በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። 6 የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። 7 ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ 8 በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። 9 ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ። 10 እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም ብሎ መከራቸው። 11 የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። 12 ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። 13 ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። 14 ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ 15 መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። 16 ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤ 17 ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። 18 ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥ 19 በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። 20 ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ። 21 ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ። እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። 22 አሁንም። አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። 23 የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም። 24 ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል አለኝ። 25 ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና። 26 ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንድንወድቅ ያስፈልገናል። 27 በአሥራ አራተኛውም ሌሊት በአድርያ ባሕር ወዲህና ወዲያ ስንነዳ፥ መርከበኞች በእኩለ ሌሊት ወደ አንድ ምድር የቀረቡ መሰላቸው። 28 መለኪያ ገመድም ቢጥሉ ሀያ በሰው ቁመት አገኙ ጥቂትም ቆይተው ሁለተኛ ቢጥሉ አሥራ አምስት በሰው ቁመት አገኙ፤ 29 ድንጋያማም ወደ ሆነ ስፍራ እንዳይወድቁ ፈርተው፥ ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ አወረዱ፥ ቀንም እንዲሆን ተመኙ። 30 መርከበኞቹም ከመርከቡ ይሸሹ ዘንድ ፈልገው ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ መጣል እንዳላቸው አመካኝተው ታንኳይቱን ወደ ባሕር ባወረዱ ጊዜ፥ 31 ጳውሎስ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ። እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም አላቸው። 32 ያን ጊዜ ወታደሮቹ የታንኳይቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት። 33 ቀንም ሲነጋ ጳውሎስ ምግብ ይበሉ ዘንድ ሁሉን ይለምን ነበር፥ እንዲህም አላቸው። እየጠበቃችሁ ምንም ሳትቀበሉ ጦማችሁን ከሰነበታችሁ ዛሬ አሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው። 34 ሰለዚህ ምግብ ትበሉ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ይህ ለደኅንነታችሁ ይሆናልና፤ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና። 35 ይህንም ብሎ እንጀራን ይዞ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። 36 ሁለም ተጽናንተው ራሳቸው ደግሞ ምግብ ተቀበሉ። 37 በመርከቡም ያለን ሁላችን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበርን። 38 በልተውም በጠገቡ ጊዜ ስንዴውን ወደ ባሕር እየጣሉ መርከቡን አቃለሉት። 39 በነጋም ጊዜ ምድሩን አላወቁትም፥ ነገር ግን የአሸዋ ዳር ያለውን የባሕር ስርጥ ተመለከቱ፥ ቢቻላቸውም መርከቡን ወደዚያ ይገፉ ዘንድ ቈረጡ። 40 መልሕቆቹንም ፈትተው በባሕር ተዉአቸው፥ ያን ጊዜም የመቅዘፊያውን ማሠሪያ ፈቱት፤ ታናሹንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ዳር አቅንተው ይሄዱ ዘንድ ጀመሩ። 41 ነገር ግን ሁለት ባሕር በተገናኙበት ስፍራ ወድቀው መርከቡን በዲብ ላይ ነዱ፤ በስተ ፊቱም ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፥ በስተ ኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ ይሰበር ነበር። 42 ወታደሮቹም ከእስረኞች አንድ ስንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ይገድሉአቸው ዘንድ ተማከሩ። 43 የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ፤ ዋና የሚያውቁትም ከመርከብ ራሳቸውን እየወረወሩ አስቀድመው ወደ ምድር ይወጡ ዘንድ፥ 44 የቀሩትም እኵሌቶቹ በሳንቃዎች ላይ እኵሌቶቹም በመርከቡ ስባሪ ይወጡ ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ሁሉ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።

የሐዋርያት ሥራ 28

1 በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን። 2 አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። 3 ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። 4 አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ። 5 እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤ 6 እነርሱም። ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ። ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ። 7 በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። 8 የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። 9 ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ 10 በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን። 11 ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት። 12 ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ 13 ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። 14 በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። 15 ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና። 16 ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት። 17 ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። 18 እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ 19 አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። 20 ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና። 21 እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም። 22 ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን አሉት። 23 ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። 24 እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤ 25 እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን። 26 ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ 27 በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው 28 ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። 29 ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ። 30 ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ 31 ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።

ሮሜ 1

3-4 ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 5 በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን፤ 6 በእነርሱም መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ እናንተ ደግሞ ናችሁ። 7 በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 8 እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ስለ ተሰማች አስቀድሜ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ። 9-10 በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤ ምናልባት ብዙ ቆይቼ ወደ እናንተ አሁን እንድመጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንገዴን እንዲያቀናልኝ እየለመንሁ ሁልጊዜ ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ። 11 ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና፤ 12 ይህንም ማለቴ በመካከላችን ባለች በእናንተና በእኔ እምነት አብረን በእናንተ እንድንጽናና ነው። 13 ወንድሞች ሆይ፥ በሌሎቹ አሕዛብ ደግሞ እንደ ሆነ በእናንተም ፍሬ አገኝ ዘንድ ብዙ ጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንዳሰብሁ እስከ አሁን ግን እንደ ተከለከልሁ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 14 ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ 15 ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ። 16 በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። 17 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። 18 እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ 19 እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። 20-21 የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። 22 ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥ 23 የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። 24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ 25 ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። 26 ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ 27 እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። 28 እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ 29 ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ 30 ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ 31 የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ 32 እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።

ሮሜ 2

1 ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና። 2 እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን። 3 አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 4 ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? 5 ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። 6 እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ 7 በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ 8 ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል። 9 ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤ 10 ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው። 11 እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና። 12 ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ 13 በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና። 14 ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ 15 እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ። 16 ይህም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁ በሰው ዘንድ የተሰወረውን በሚፈርድበት ቀን ይሆናል። 17 አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥ 18 ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፤ 19-20 በሕግም የእውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ፥ የዕውሮች መሪ፥ በጨለማም ላሉ ብርሃን፥ የሰነፎችም አስተማሪ፥ የሕፃናትም መምህር እንደ ሆንህ በራስህ ብትታመን፤ 21 እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? 22 አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን? 23 በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? 24 በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ። 25 ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል። 26 እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? 27 ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል። 28 በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ 29 ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።

ሮሜ 3

1 እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው። 2 አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው። ታዲያ ምንድር ነው? 3 የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን? 4 እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን። 5 ነገር ግን ዓመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን? ቍጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር ዓመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። 6 እንዲህ አይሁን፤ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሔር በዓለም እንዴት ይፈርዳል? 7 በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል? 8 ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው። 9 እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤ 10 እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 11 ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ 12 በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። 13 ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ 14 አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ 15 እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ 16 ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ 17-18 የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም። 19 አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ 20 ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። 21 አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ 22 እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ 23 ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ 24 በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። 25 እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ 26 ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው። 27 ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። 28 ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና። 29-30 ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው። 31 እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ።

ሮሜ 4

1 እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? 2 አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። 3 መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። 4 ለሚሠራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቈጠርለትም፤ 5 ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል። 6 እንደዚህ ዳዊት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቆጥርለት ስለ ሰው ብፅዕና ይናገራል እንዲህ ሲል። 7 ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ 8 ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው። 9 እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገረዝ ተነገረ? ወይስ ደግሞ ስለ አለመገረዝ? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። 10 እንዴት ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ተገርዞስ አይደለም፥ ሳይገረዝ ነበር እንጂ። 11 ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ 12 ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው። 13 የዓለምም ወራሽ እንዲሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም። 14 ከሕግ የሆኑትስ ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኖአል የተስፋውም ቃል ተሽሮአል፤ 15 ሕጉ መቅሠፍትን ያደርጋልና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት መተላለፍ የለም። 16-17 ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም። ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው። 18 ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። 19 የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ 20-21 ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። 22 ስለዚህ ደግሞ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። 23 ነገር ግን። ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም፥ ስለ እኛም ነው እንጂ፤ 24-25 ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታንችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው።

ሮሜ 5

1 እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ 2 በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። 3-4 ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ 5 በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። 6 ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። 7 ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። 8 ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። 9 ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። 10 ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ 11 ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። 12 ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ 13 ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም፤ 14 ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። 15 ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። 16 አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። 17 በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። 18 እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። 19 በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። 20-21 በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።

ሮሜ 6

1 እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን? አይደለም። 2 ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? 3 ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? 4 እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። 5 ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤ 6 ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። 7-8 ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን፤ 9 ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና። 10 መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቶአልና፤ በሕይወት መኖርን ግን ለእግዚአብሔር ይኖራል። 11 እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቈጠሩ። 12 እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ 13 ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። 14 ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። 15 እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም። 16 ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ። 17-18 ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 19 ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። 20 የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። 21 እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። 22 አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። 23 የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።

ሮሜ 7

1 ወንድሞች ሆይ፥ ሕግን ለሚያውቁ እናገራለሁና ሰው ባለበት ዘመን ሁሉ ሕግ እንዲገዛው አታውቁምን? 2 ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በሕግ ታስራለችና፤ ባልዋ ቢሞት ግን ስለ ባል ከሆነው ሕግ ተፈትታለች። 3 ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሳለ ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፤ ባልዋ ቢሞት ግን ከሕጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም። 4 እንዲሁ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ፥ እናንተ ለሌላው፥ ከሙታን ለተነሣው፥ ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ። 5 በሥጋ ሳለን በሕግ የሚሆን የኃጢአት መሻት ለሞት ፍሬ ሊያፈራ በብልቶቻችን ይሠራ ነበርና፤ 6 አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም። 7 እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ። አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና። 8 ኃጢአት ግን ምክንያት አግኝቶ ምኞትን ሁሉ በትእዛዝ ሠራብኝ፤ ኃጢአት ያለ ሕግ ምውት ነውና። 9 እኔም ዱሮ ያለ ሕግ ሕያው ነበርሁ፤ ትእዛዝ በመጣች ጊዜ ግን ኃጢአት ሕያው ሆነ እኔም ሞትሁ፤ 10 ለሕይወትም የተሰጠችውን ትእዛዝ እርስዋን ለሞት ሆና አገኘኋት፤ 11 ኃጢአት ምክንያት አግኝቶ በትእዛዝ አታሎኛልና በእርስዋም ገድሎኛል። 12 ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት። 13 እንግዲህ በጎ የሆነው ነገር ለእኔ ሞት ሆነብኝን? አይደለም፥ ነገር ግን ኃጢአት ሆነ፤ ኃጢአትም በትእዛዝ ምክንያት ያለ ልክ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ ኃጢአትም እንዲሆን ይገለጥ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር ለእኔ ሞትን ይሠራ ነበር። 14 ሕግ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። 15 የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም። 16 የማልወደውን ግን የማደርግ ከሆንሁ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። 17 እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚያድር ኃጢአት ነው እንጂ። 18 በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። 19 የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። 20 የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ። 21 እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። 22 በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ 23 ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። 24 እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? 25 በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።

ሮሜ 8

1 እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። 2 በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። 3-4 ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። 5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። 6 ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። 7 ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ 8 በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። 9 እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። 10 ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። 11 ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል። 12 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። 13 እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። 14 በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። 15 አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። 16 የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። 17 ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። 18 ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። 19 የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። 20 ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ 21 ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። 22 ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። 23 እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። 24 በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? 25 የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። 26 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ 27 ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። 28 እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። 29 ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ 30 አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። 31 እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? 32 ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? 33 እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? 34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። 35 ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? 36 ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። 37 በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። 38 ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ 39 ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።

ሮሜ 9

1-2 ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለብኝ ስል በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። 3 በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። 4 እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ 5 አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን። 6 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም። እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም፥ 7 ነገር ግን። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ተባለ። 8 ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው። 9 ይህ። በዚህ ጊዜ እመጣለሁ ለሳራም ልጅ ይሆንላታል የሚል የተስፋ ቃል ነውና። 10 ይህ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ፥ 11 ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፥ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ፥ 12 ለእርስዋ። ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት። 13 ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። 14 እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም። 15 ለሙሴ። የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። 16 እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ። 17 መጽሐፍ ፈርዖንን። ኃይሌን በአንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አስነሣሁህ ይላልና። 18 እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል። 19 እንግዲህ ስለ ምን እስከ አሁን ድረስ ይነቅፋል? ፈቃዱንስ የሚቃወም ማን ነው? ትለኝ ይሆናል። 20 ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን። ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? 21 ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? 22-23 ነገር ግን እግዚአብሔር ቍጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፥ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፥ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ፥ እንዴት ነው? 24 የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። 25 እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ። ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም የተወደደችው ብዬ እጠራለሁ፤ 26 እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል። 27-28 ኢሳይያስም። የእስራኤል ልጆች ቁጥር ምንም እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆን ቅሬታው ይድናል፤ ጌታ ነገሩን ፈጽሞና ቆርጦ በምድር ላይ ያደርገዋልና ብሎ ስለ እስራኤል ይጮኻል። 29 ኢሳይያስም እንደዚሁ። ጌታ ፀባዖት ዘር ባላስቀረልን እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ብሎ አስቀድሞ ተናገረ። 30 እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ 31 እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም። 32-33 ይህስ ስለ ምንድር ነው? በሥራ እንጂ በእምነት ጽድቅን ስላልተከተሉ ነው፤ እነሆ፥ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዓለት አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ እንደ ተጻፈ በእንቅፋት ድንጋይ ተሰናከሉ።

ሮሜ 10

1 ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። 2 በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። 3 የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። 4 የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። 5 ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና። 6 ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል። በልብህ። ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ 7 ወይም። በልብህ። ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። 8 ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። 9 ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ 10 ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። 11 መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። 12 በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ 13 የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። 14 እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? 15 መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? 16 ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። 17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። 18 ዳሩ ግን። ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። 19 ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ። እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ 20 ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ። ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ። 21 ስለ እስራኤል ግን። ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።

ሮሜ 11

1 እንግዲህ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? እላለሁ። አይደለም እኔ ደግሞ እስራኤላዊና ከአብርሃም ዘር ከብንያምም ወገን ነኝና። 2 እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። መጽሐፍ ስለ ኤልያስ በተጻፈው የሚለውን፥ በእግዚአብሔር ፊት እስራኤልን እንዴት እንደሚከስ፥ አታውቁምን? 3 ጌታ ሆይ፥ ነቢያትህን ገደሉ መሠዊያዎችህንም አፈረሱ እኔም ብቻዬን ቀረሁ ነፍሴንም ይሹአታል። 4 ነገር ግን አምላካዊ መልስ ምን አለው? ለበአል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ። 5 እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ። 6 በጸጋ ከሆነ ግን ከሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል። 7 እንግዲህ ምንድር ነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ 8 ሌሎቹም ደነዘዙ፤ እንዲሁም። ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው ተብሎ ተጽፎአል። ዳዊትም። 9 ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤ 10 ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውንም ዘወትር አጉብጥ ብሎአል። 11 እንግዲህ። የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። 12 ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? 13-14 ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። 15 የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን? 16 በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። 17 ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ 18 ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም። 19 እንግዲህ። እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል። 20 መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። 21 እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና። 22 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። 23 እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። 24 አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም? 25 ወንድሞች ሆይ፥ ልባሞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ምሥጢር ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ ድንዛዜ በእስራኤል በአንዳንድ በኩል ሆነባቸው፤ 26 እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል። 27 ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው። 28 በወንጌልስ በኩል ስለ እናንተ ጠላቶች ናቸው፥ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ተወዳጆች ናቸው፤ 29 እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና። 30 እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን ከአለመታዘዛቸው የተነሣ ምሕረት እንዳገኛችሁ፥ 31 እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም። 32 እግዚአብሔር ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና። 33 የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። 34 የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? 35 ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? 36 ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

ሮሜ 12

1 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። 2 የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። 3 እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። 4 በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ 5 እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። 6 እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ 7 አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ 8 የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። 9 ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ 10 በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ 11 ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ 12 በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ 13 ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። 14 የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። 15 ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። 16 እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። 17 ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። 18 ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። 19 ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። 20 ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። 21 ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።

ሮሜ 13

1 ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። 2 ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። 3 ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ 4 ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። 5 ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። 6 ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። 7 ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። 8 እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። 9 አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። 10 ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። 11 ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። 12 ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። 13 በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ 14 ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።

ሮሜ 14

1 በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። 2 ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። 3 የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። 4 አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። 5 ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንዲሻል ያስባል፥ ያ ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደ ሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። 6 ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል፤ የሚበላም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለጌታ ብሎ ይበላል፤ የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። 7 ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ 8 በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። 9 ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና። 10 አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። 11 እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። 12 እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። 13 እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንፈራረድ፤ ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቍረጡ። 14 በራሱ ርኵስ የሆነ ነገር እንደ ሌለ በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ምንም ርኵስ እንዲሆን ለሚቆጥር ለእርሱ ርኵስ ነው። 15 ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ እንግዲህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው። 16 እንግዲህ ለእናንተ ያለው መልካም ነገር አይሰደብ፤ 17 የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። 18 እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፥ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። 19 እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል። 20 በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፥ በመጠራጠር የተበላ እንደ ሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። 21 ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው። 22 ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው። 23 የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው።

ሮሜ 15

1 እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። 2 እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ። 3 ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን። አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ ተብሎ እንደ ተጻፈ ሆነበት። 4 በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና። 5 5-6 በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፥ ታከብሩ ዘንድ፥ የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ። 7 ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። 8-9 ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ደግሞም። ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ ለስምህም እዘምራለሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አሕዛብ ስለ ምሕረቱ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፥ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር እውነት የመገረዝ አገልጋይ ሆነ እላለሁ። 10 ደግሞም። አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላል። 11 ደግሞም። እናንተ አሕዛብ ሁላችሁ፥ ጌታን አመስግኑ ሕዝቦቹም ሁሉ ይወድሱት ይላል። 12 ደግሞም ኢሳይያስ። የእሴይ ሥር አሕዛብንም ሊገዛ የሚነሣው ይሆናል፤ በእርሱ አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ ይላል። 13 የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ። 14 እኔም ራሴ ደግሞ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በበጎነት ራሳችሁ እንደ ተሞላችሁ፥ እውቀትም ሁሉ እንደ ሞላባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ደግሞ ልትገሠጹ እንዲቻላችሁ ስለ እናንተ ተረድቼአለሁ። 15-16 ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። 17 እንግዲህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚሆን ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ ትምክህት አለኝ። 18-19 አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በምልክትና በድንቅ ነገር ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ፤ ሰብኬአለሁ። 20 እንዲሁም በሌላው ሰው መሠረት ላይ እንዳልሠራ የክርስቶስ ስም በተጠራበት ስፍራ ሳይሆን ወንጌልን ለመስበክ ተጣጣርሁ፤ 21 ነገር ግን። ስለ እርሱ ያልተወራላቸው ያያሉ፥ ያልሰሙም ያስተውላሉ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። 22 ስለዚህ ደግሞ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ። 23 አሁን ግን በዚህ አገር ስፍራ ወደ ፊት ስለሌለኝ፥ ከብዙ ዓመትም ጀምሬ ወደ እናንተ ልመጣ ናፍቆት ስላለኝ፥ 24 ወደ እስጳንያ በሄድሁ ጊዜ ሳልፍ እናንተን እንዳይ፥ አስቀድሜም ጥቂት ብጠግባችሁ ወደዚያ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ። 25 አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። 26 መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ያሉትን ድሆች ይረዱ ዘንድ ወደዋልና። 27 ወደዋልና፥ የእነርሱም ባለ ዕዳዎች ናቸው፤ አሕዛብ በእነርሱ መንፈሳዊ ነገርን ተካፋዮች ከሆኑ በሥጋዊ ነገር ደግሞ ያገለግሉአቸው ዘንድ ይገባቸዋልና። 28 እንግዲህ ይህን ፈጽሜ ይህን ፍሬ ካተምሁላቸው በኋላ በእናንተ በኩል አልፌ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ 29 ወደ እናንተም ስመጣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንድመጣ አውቃለሁ። 30 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤ 31-32 በእግዚአብሔር ፈቃድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር እንዳርፍ፥ በይሁዳ ካሉት ከማይታዘዙ እድን ዘንድ፥ ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ ጸልዩ። 33 የሰላምም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሮሜ 16

1 በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ 2 ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት። 3 በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 4 እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ 5 በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 6 ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 7 በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 8 በጌታ ለምወደው ለጵልያጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 9 በክርስቶስ አብሮን ለሚሠራ ለኢሩባኖን ለምወደውም ለስንጣክን ሰላምታ አቅርቡልኝ። 10 በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰገነው ለኤጤሌን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከአርስጣባሉ ቤተ ሰዎች ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 11 ለዘመዴ ለሄሮድዮና ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከንርቀሱ ቤተ ሰዎች በጌታ ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 12 በጌታ ሆነው ለሚደክሙ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ እጅግ ለደከመች ለተወደደች ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 13 በጌታ ሆኖ ለታወቀ ለሩፎን ለእኔና ለእርሱም እናት ሰላምታ አቅርቡልኝ። 14 ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ ለሄሮሜንም ለጳጥሮባም ለሄርማንም ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ። 15 ለፍሌጎንና ለዩልያ ለኔርያና ለእኅቱም ለአልንጦንም ከእነርሱ ጋር ላሉ ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 16 በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 17 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ 18 እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። 19 መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ። 20 የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 21 አብሮኝ የሚሠራ ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉቂዮስና ኢያሶን ሱሲጴጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22 ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። 23 የእኔና የቤተ ክርስቲያን ሁሉ አስተናጋጅ ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው መጋቢ ኤርስጦስ ወንድማችንም ቁአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 24 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። 25-26 እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥ 27 ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።

1 ቆሮንቶስ 1

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ጳውሎስ ወንድሙም ሶስቴንስ፥ 2 በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤ 3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4 በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤ 5-6 ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። 7 እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ 8 እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። 9 ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። 10 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 11 ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና። 12 ይህንም እላለሁ። እያንዳንዳችሁ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ። 13 ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? 14-15 በስሜ እንደ ተጠመቃችሁ ማንም እንዳይል ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ አንድን እንኳ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 16 የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ እንደ ሆነ አላውቅም። 17 ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። 18 የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 19 የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። 20 ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? 21 በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። 22 መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ 23 እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ 24 ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። 25 ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 26 ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። 27 ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ 28 እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ 29 ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። 30-31 ነገር ግን። የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።

1 ቆሮንቶስ 2

1 እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። 2 በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። 3 እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ 4-5 እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 6 በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ 7 ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። 8 ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ 9 ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን። 10 መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። 11 በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። 12 እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 13 መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። 14 ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 15 መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። 16 እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።

1 ቆሮንቶስ 3

1 እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። 2 ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ 3 ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? 4 አንዱ። እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም። እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? 5 አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። 6 እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ 7 እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። 8 የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። 9 የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 10 የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። 11 ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 12 ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ 13 በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። 14 ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ 15 የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? 17 ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። 18 ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። 19-20 የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም። ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና። 21 ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና፤ 22 ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ 23 ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።

1 ቆሮንቶስ 4

1 እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን። 2 እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል። 3 ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 4 በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። 5 ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። 6 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። 7 አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 8 አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር። 9 ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና። 10 እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። 11 እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ 12 በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ 13 እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል። 14 እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። 15 በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። 16 እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። 17 ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፥ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። 18 አንዳንዱ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ 19 ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፥ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ 20 የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። 21 ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?

1 ቆሮንቶስ 5

1 በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። 2 እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። 3-4 እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ 5 መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው። 6 መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? 7 እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ 8 ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም። 9 ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። 10 በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። 11 አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። 12 በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? 13 በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።

1 ቆሮንቶስ 6

1 ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? 2 ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? 3 የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? 4 እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? 5 አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? 6 ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? 7 እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 8 ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን። 9 ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ 10 ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 11 ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል። 12 ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። 13 መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ 14 እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። 15 ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። 16 ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። 17 ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። 18 ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። 19-20 ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።

1 ቆሮንቶስ 7

1 ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። 2 ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት። 3 ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። 4 ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። 5 ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ። 6 ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። 7 ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ። 8 ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ። እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ 9 ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ። 10-11 ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ። 12 ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤ 13 ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው። 14 ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። 15 የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። 16 አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ? 17 ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። 18 ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደ ሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደ ሆነ አይገረዝ። 19 መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ከንቱ ነው፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። 20 እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር። 21 ባሪያ ሆነህ ተጠርተህ እንደ ሆነ አይገድህም፤ አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል። 22 ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው። 23 በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ። 24 ወንድሞች ሆይ፥ እያንዳንዱ በተጠራበት እንደዚሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር። 25 ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ። 26 እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። 27 በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ። 28 ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር። 29 ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 30 የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ 31 የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 32 ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ 33 ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል። 34 ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። 35 ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም። 36 ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። 37 ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።

1 ቆሮንቶስ 8

1 ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። 2 ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 3 ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው። 4 እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5 መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ 6 ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። 7 ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለ ለመዱ። ለጣዖት የተሠዋ ነው ብለው ይበላሉና ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። 8 መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም። 9 ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። 10 አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? 11 በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። 12 እንዲህም ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13 ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም።

1 ቆሮንቶስ 9

1 እኔ ነጻ አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ ሥራዬ አይደላችሁምን? 2 የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተስ ምንም ቢሆን ሐዋርያ ነኝ። 3-4 ለሚመረምሩኝ መልሴ ይህ ነው። ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? 5 እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? 6 ወይስ ሥራን ለመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ ብቻ ነን? 7 ከቶ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይስ ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የማይጠጣ ማን ነው? 8 ይህን በሰው ሥልጣን ብቻ እላለሁን? 9 ሕግስ ደግሞ ያን አይልምን? የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ተብሎ በሙሴ ሕግ ተጽፎአልና። እግዚአብሔርስ ስለ በሬዎች ይገደዋልን? 10 ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለ እኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፎአል። 11 እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? 12 ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆኑ እኛማ ይልቁን እንዴታ? ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም። 13 በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፥ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? 14 እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል። 15 እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 16 ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ። 17 ይህን በፈቃዴ ባደርገው ደመወዝ አለኝና፤ ያለ ፈቃዴ ግን ባደርገው መጋቢነት በአደራ ተሰጥቶኛል። 18 እንግዲህ ደመወዜ ምንድር ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው። 19 ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። 20 አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ 21 ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ 22 ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። 23 በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ። 24 በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። 25 የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። 26 ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ 27 ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።

1 ቆሮንቶስ 10

1 ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ 2 ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ 3 ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ 4 ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ። 5 እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ በሚበዙት ደስ አላለውም፥ በምድረ በዳ ወድቀዋልና። 6 እነዚህም ክፉ ነገር እንደ ተመኙ እኛ ደግሞ እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። 7 ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። 8 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደ ወደቁ አንሴስን። 9 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን። 10 ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 11 ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። 12 ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 13 ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 14 ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ። 15 ልባሞች እንደ መሆናችሁ እላለሁ፤ በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ። 16 የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? 17 አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፥ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። 18 በሥጋ የሆነውን እስራኤል ተመልከቱ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉ የመሠዊያው ማኅበረተኞች አይደሉምን? 19 እንግዲህ ምን እላለሁ? ለጣዖት የተሠዋ ምናምን ነው እላለሁን? ወይስ ጣዖት ምናምን እንዲሆን እላለሁን? 20 አይደለም፤ ነገር ግን አሕዛብ የሚሠዉት ለአጋንንት እንዲሆን እንጂ ለእግዚአብሔር እንዳይሠዉ እላለሁ፤ ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። 21 የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም። 22 ወይስ ጌታን እናስቀናውን? እኛስ ከእርሱ ይልቅ እንበረታለንን? 23 ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። 24 እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ። 25 በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ፤ 26 ምድርና በእርስዋ የሞላባት ሁሉ የጌታ ነውና። 27 ከማያምኑ ሰዎች አንዱም ቢጠራችሁ ልትሄዱም ብትወዱ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ የሚያቀርቡላችሁን ሁሉ ብሉ። 28 ማንም ግን። ይህ ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ፤ 29 ስለ ባልንጀራህ ሕሊና እንጂ ስለ ገዛ ሕሊናህ አልናገርም። አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈርድ Avረ ስለ ምንድር ነው? 30 እኔም በጸጋ ብበላ፥ በነገሩ ስለማመሰግንበት ስለ ምን እሰደባለሁ? 31 እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት። 32-33 እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 11

1 እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። 2 ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ። 3 ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። 4 ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። 5 ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና። 6 ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን። 7 ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት። 8 ሴት ከወንድ ናት እንጂ ወንድ ከሴት አይደለምና። 9 ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረምና። 10 ስለዚህ ሴት ከመላእክት የተነሣ በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል። 11 ነገር ግን በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። 12 ሴት ከወንድ እንደ ሆነች እንዲሁ ወንድ ደግሞ በሴት ነውና፤ ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው። 13 በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን? 14-15 ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታልና። 16 ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም። 17 ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚከፋ እንጂ ለሚሻል ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ የማመሰግናችሁ አይደለም። 18 በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁና፥ በአንድ በኩልም አምናለሁ። 19 በእናንተ ዘንድ የተፈተኑት እንዲገለጡ በመካከላችሁ ወገኖች ደግሞ ሊሆኑ ግድ ነውና። 20 እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም፤ 21 በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል። 22 የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? አላመሰግናችሁም። 23 ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ 24 ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንሥቶ አመሰገነ፥ ቆርሶም። እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። 25 እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። 26 ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። 27 ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። 28 ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ 29 ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና። 30 ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል። 31 ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ 32 ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን። 33 ስለዚህ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34 ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።

1 ቆሮንቶስ 12

1 ስለ መንፈሳዊ ነገርም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 2 አሕዛብ ሳላችሁ በማናቸውም ጊዜ እንደምትመሩ ድምፅ ወደሌላቸው ወደ ጣዖታት እንደ ተወሰዳችሁ ታውቃላችሁ። 3 ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር። ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ፥ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር። ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ። 4 የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ 5 አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ 6 አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። 8 ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ 9 ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ 10 ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ 11 ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። 12 አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 13 አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። 14 አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። 15 እግር። እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? 16 ጆሮም። እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? 17 አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? 18 አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። 19 ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? 20 ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። 21 ዓይን እጅን። አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን። አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። 22 ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ 23 ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ 24-25 ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። 26 አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። 27 እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። 28 እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል። 29 ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? 30 ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን? 31 ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ።

1 ቆሮንቶስ 13

1 በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። 2 ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3 ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 4 ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ 5 የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ 6 ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ 7 ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 8 ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። 9 ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ 10 ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። 11 ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። 12 ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። 13 እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

1 ቆሮንቶስ 14

1 ፍቅርን ተከታተሉ፥ መንፈሳዊ ስጦታንም ይልቁንም ትንቢት መናገርን በብርቱ ፈልጉ። 2 በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤ 3 ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል። 4 በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢትን የሚናገር ግን ማኅበሩን ያንጻል። 5 ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር፥ ትንቢትን ልትናገሩ ግን ከዚህ ይልቅ እወዳለሁ፤ ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል። 6 አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ? 7 ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? 8 ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 9 እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። 10 በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ 11 እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። 12 እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ። 13 ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ። 14 በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። 15 እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ። 16 እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? 17 አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም። 18 ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 19 ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ። 20 ወንድሞች ሆይ፥ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ። 21 ሌሎችን ልሳኖች በሚናገሩ ሰዎችና በሌላ አንደበት ለዚህ ሕዝብ እነግራቸዋለሁ፥ እንዲህም ቢሆን አይሰሙኝም ይላል ጌታ ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። 22 እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 23 እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ። አብደዋል አይሉምን? 24 ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ 25 በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም። እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። 26 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 27 በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤ 28 የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር። 29 ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤ 30 በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል። 31 ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ። 32 የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ፤ 33 እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው። 34 ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና። 35 ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ። 36 ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን? 37 ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤ 38 ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ። 39 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤ 40 ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።

1 ቆሮንቶስ 15

1 ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ 2 በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። 3 እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ 4 መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ 5 ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ 6 ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ 7 ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ 8 ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ። 9 እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤ 10 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 11 እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ። 12 ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ። ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? 13 ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ 14 ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ 15 ደግሞም። ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። 16 ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ 17 ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። 18 እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። 19 በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 20 አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። 21 ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። 22 ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። 23 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ 24 በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። 25 ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። 26 የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ 27 ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። 28 ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል። 29 እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? 30 እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው? 31 በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ። 32 እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 33 አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 34 በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ። 35 ነገር ግን ሰው። ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። 36 አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ 37 የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ 38 እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። 39 ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። 40 ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፥ የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። 41 የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። 42 የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ 43 በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ 44 ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። 45 እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። 46 ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። 47 የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። 48 መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። 49 የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። 50 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። 51-52 እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። 53 ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። 54 ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። 55 ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? 56 የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ 57 ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 58 ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 16

1 ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። 2 እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ። 3 ስመጣም ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ፤ 4 እኔ ደግሞ ልሄድ የሚገባኝ ብሆን ከእኔ ጋር አብረው ይሄዳሉ። 5 በመቄዶንያም ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ አድርጌ አልፋለሁና፤ 6 እናንተም ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ምናልባት በእናንተ ዘንድ እቆይ ወይም እከርም ይሆናል። 7 አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልወድምና፤ ጌታ ቢፈቅደው የሆነውን ዘመን በእናንተ ዘንድ ልሰነብት ተስፋ አደርጋለሁና። 8 በኤፌሶን ግን እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ። 9 ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው። 10 ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው። 11 ነገር ግን ከወንድሞቹ ጋር እጠብቀዋለሁና ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ በሰላም በጉዞው እርዱት። 12 ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ ሊሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፥ ሲመቸው ግን ይመጣል። 13 ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ። 14 በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን። 15 ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኩራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ፤ 16 እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ። 17 በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም መምጣት ደስ ይለኛል፥ እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን ፈጽመዋልና፤ መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋልና። 18 እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው። 19 የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር በጌታ እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 20 ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። 21 እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ። 22 ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና። 23 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24 ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው። አሜን።

2 ቆሮንቶስ 1

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3 የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4 እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። 5 የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። 6 ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው። 7 ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና። 8 በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ 9 አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር። 10-11 እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል። 12 ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የሕሊናችን ምስክርነት ነው። 13-14 ከምታነቡትና ከምታስተውሉት በቀር ሌላ አንጽፍላችሁምና፤ በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ ደግሞ ትምክህታችን እንደምትሆኑ እንዲሁ ትምክህታችሁ እንድንሆን፥ በከፊል ስለ እኛ እንዳስተዋላችሁ ፈጽማችሁ ታስተውሉት ዘንድ ተስፋ አደርጋለሁ። 15 በዚህም ታምኜ፥ ሁለተኛ ጸጋ ታገኙ ዘንድ አስቀድሜ ወደ እናንተ እንድመጣ፥ 16 በእናንተም መካከል ወደ መቄዶንያ እንዳልፍ ደግሞም ከመቄዶንያ ወደ እናንተ መጥቼ ወደ ይሁዳ በጉዞዬ እንድትረዱኝ አሰብሁ። 17 እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን? 18 እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። 19 በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል። 20 እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው። 21 በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ 22 ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። 23 እኔ ግን ልራራላችሁ ስል እንደ ገና ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣሁ በነፍሴ ላይ እግዚአብሔርን ምስክር እጠራለሁ። 24 ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፥ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና።

2 ቆሮንቶስ 2

1 ነገር ግን ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ እንዳልመጣ ስለ እኔ ቆረጥሁ። 2 እኔስ ባሳዝናችሁ፥ እንግዲያስ በእኔ ምክንያት ከሚያዝን በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? 3 ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸውም በመምጣቴ ኀዘን እንዳይሆንብኝ ይህንኑ ጻፍሁላችሁ፥ ደስታዬ የሁላችሁ ደስታ ነው ብዬ በሁላችሁ ታምኜአለሁና። 4 በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበርና፤ ይህም እናንተን አብዝቼ የምወድበትን ፍቅር እንድታውቁ እንጂ እንዳሳዝናችሁ አይደለም። 5 ነገር ግን ማንም አሳዝኖ ቢሆን፥ እንዳልከብድባችሁ፥ በክፍል ሁላችሁን እንጂ እኔን ያሳዘነ አይደለም። 6 እንደዚህ ላለ ሰው ይህ ከእናንተ የምትበዙት የቀጣችሁት ቅጣት ይበቃዋልና እንደዚህ ያለው ከልክ በሚበዛ ኀዘን እንዳይዋጥ፥ 7 ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል። 8 ስለዚህ ከእርሱ ጋር ፍቅርን እንድታጸኑ እለምናችኋለሁ፤ 9 ስለዚህ ደግሞ ጽፌ ነበርና፤ በሁሉ የምትታዘዙ እንደ ሆናችሁ የእናንተን መፈተን አውቅ ዘንድ አሳቤ ነበር። 10 እናንተ ግን ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ፤ እኔም ይቅር ካልሁ፥ ይቅር ያልሁትን ስለ እናንተ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብዬአለሁ፥ 11 በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 12 ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም፥ 13 ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ። 14 ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ 15 በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ 16 ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? 17 የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።

2 ቆሮንቶስ 3

1 እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? 2 ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። 3 እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። 4 በክርስቶስም በኩል ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ እምነት አለን። 5 ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፥ በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤ 6 እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። 7 ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ስለዚያ ስለ ተሻረው ስለ ፊቱ ክብር የሙሴን ፊት ትኩር ብለው መመልከት እስኪሳናቸው ድረስ፥ ያ በፊደላት በድንጋዮች ላይ የተቀረጸ የሞት አገልግሎት በክብር ከሆነ፥ 8 የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ይልቅ በክብር አይሆንም? 9 የኵነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ፥ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና። 10 ያ የከበረ እንኳ እጅግ በሚበልጠው ክብር ምክንያት በዚህ ነገር ክብሩን አጥቶአልና። 11 ያ ይሻር የነበረው በክብር ከሆነ፥ ጸንቶ የሚኖረውማ እጅግ ይልቅ በክብር ሆኖአልና። 12 እንግዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ ካለን እጅግ ገልጠን እንናገራለን፥ 13 የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም። 14 ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና። 15 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ 16 ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። 17 ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። 18 እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።

2 ቆሮንቶስ 4

1 ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። 2 ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን። 3 ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። 4 ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። 5 ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። 6 በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና። 7 ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 8 በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ 9 እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 10 የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። 11 የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። 12 ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል። 13 ነገር ግን። አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ 14 ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። 15 በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና። 16 ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 17-18 የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።

2 ቆሮንቶስ 5

1 ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። 2 በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ 3 ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። 4 በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። 5 ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን። 6-7 እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን፥ 8 ታምነናል ይልቁንም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር በጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል። 9 ስለዚህ ደግሞ ብናድር ወይም ተለይተን ብንሆን እርሱን ደስ የምናሰኝ ልንሆን እንቀናለን። 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና። 11 እንግዲህ የጌታን ፍርሃት አውቀን ሰዎችን እናስረዳለን ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደ ሆንን ተስፋ አደርጋለሁ። 12 በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ የምትመልሱላቸው መልስ እንዲኖራችሁ፥ በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን እንጂ ራሳችንን ደግሞ ለእናንተ የምናመሰግን አይደለንም። 13 እብዶች ብንሆን፥ ለእግዚአብሔር ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆን፥ ለእናንተ ነው። 14 ይህን ስለቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ 15 በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 16 ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 17 ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 18 ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ 19 እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። 20 እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። 21 እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።

2 ቆሮንቶስ 6

1 አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ 2 በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። 3 አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። 4 ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 5 በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ 6 በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ 7 በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ 8 በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ 9 ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ 10 ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 11 እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤ 12 በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤ 13 ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፥ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ። 14 ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? 15 ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? 16 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 17-18 ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።

2 ቆሮንቶስ 7

1 እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ። 2 በልባችሁ ስፍራ አስፉልን፤ ማንንም አልበደልንም፥ ማንንም አላጠፋንም፥ ማንንም አላታለልንም። 3 ለኵነኔ አልልም፤ በአንድነት ለመሞትና በአንድነት ለመኖር በልባችን እንዳላችሁ አስቀድሜ ብዬአለሁና። 4 ስለ እናንተ እምነቴ ታላቅ ነው፥ በእናንተ ምክንያት ትምክህቴ ታላቅ ነው፤ መጽናናት ሞልቶብኛል፤ በመከራችን ሁሉ ደስታዬ ከመጠን ይልቅ ይበዛል። 5 ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፥ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። 6 ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ 7 በመምጣቱም ብቻ አይደለም ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም ቅንዓታችሁን ሲናገረን በእናንተ ላይ በተጽናናበት መጽናናት ደግሞ ነው፤ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ደስ አለን። 8 በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ አያለሁና አሁን ለንስሐ ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ስላዘናችሁ አይደለም፤ 9 በምንም ከእኛ የተነሣ እንዳትጎዱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና። 10 እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። 11 እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል። 12 እንግዲያስ የጻፍሁላችሁ ብሆን እንኳ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በዳዩ ወይም ስለ ተበዳዩ አልጻፍሁም። ስለዚህ ተጽናንተናል። 13 በመጽናናታችንም ስለ ቲቶ ደስታ አብልጦ ደስ አለን፥ መንፈሱ በሁላችሁ ዐርፎአልና፤ 14 ለእርሱ በምንም ስለ እናንተ የተመካሁ እንደ ሆነ አላፈርሁምና፥ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ በእውነት እንደ ተናገርን፥ እንደዚህ ደግሞ ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። 15 ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ፍቅሩ በእናንተ ላይ እጅግ በዝቶአል። 16 በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።

2 ቆሮንቶስ 8

1 ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ 2 በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ 3 እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 4 ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ 5 አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። 6 ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። 7 ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። 8 ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ 9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። 10 በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤ 11 አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ። 12 በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም። 13 ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤ 14 የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 15 ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 16 ነገር ግን በቲቶ ልብ ስለ እናንተ ያንን ትጋት የሰጠ አምላክ ይመስገን፤ 17 ምክራችንን ተቀብሎአልና፥ ትጋት ግን ስለ በዛበት ወዶ ወደ እናንተ ይወጣል። 18 ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ 19 ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ ቸር ሥራ ከእኛ ጋር እንዲጓደድ በአብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ተመረጠ። 20 ስለምናገለግለው ስለዚህ ለጋስ ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ 21 በጌታ ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለንና። 22 ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን። 23 ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖርም የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። 24 እንግዲህ የፍቅራችሁንና ስለ እናንተ ያለውን የትምክህታችንን መግለጫ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ለእነርሱ ግለጡ።

2 ቆሮንቶስ 9

1 ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ 2 በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል። 3 ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ 4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን። 5 እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ። 6 ይህንም እላለሁ። በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። 7 እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 8-9 በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 10 ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 11 በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። 12 የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤ 13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ 14 ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።

2 ቆሮንቶስ 10

1 እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ 2 በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። 3 በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4 የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 5 የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 6 መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል። 7 በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። 8 ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። 9 በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። 10 መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። 11 እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። 12 ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 13 እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። 14 ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ 15-16 በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። 17-18 የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።

2 ቆሮንቶስ 11

1 በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። 2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ 3 ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ። 5 ከእነዚህ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም። 6 በአነጋገሬ ያልተማርሁ ብሆን እንኳ፥ በእውቀት ግን እንዲህ አይደለሁም። ነገር ግን በሰው ሁሉ መካከል በነገር ሁሉ ተገልጠንላችኋል። 7 ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይሆንን? 8 እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። 9 ከእናንተም ጋር ሳለሁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ። 10 የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም። 11 ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል። 12 ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ። 13 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና። 14 ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። 15 እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። 16 እንደ ገና እላለሁ። ለማንም ሰው ሞኝ የሆንሁ አይምሰለው፤ ያለዚያ ግን እኔ ደግሞ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሞኝ እንኳ ሆኜ ተቀበሉኝ። 17 እንደዚህ ታምኜ ስመካ የምናገረው፥ በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም። 18 ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19 ልባሞች ስለምትሆኑ በደስታ ሞኞችን ትታገሣላችሁና፤ 20 ማንም ባሪያዎች ቢያደርጋችሁ፥ ማንም ቢበላችሁ፥ ማንም ቢቀማችሁ፥ ማንም ቢኮራባችሁ፥ ማንም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁና። 21 ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። 22 ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? 23 እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። 24 አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። 25 ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። 26 ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ 27 በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ። 28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29 የሚደክም ማን ነው፥ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፥ እኔም አልናደድምን? 30 ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ። 31 ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል። 32 በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ 33 በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ።

2 ቆሮንቶስ 12

1 ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። 2 ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። 3 እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ 4 ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። 5 እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። 6 ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። 7 ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። 8 ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። 9 እርሱም። ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። 10 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 11 በመመካቴ ሞኝ ሆኜአለሁ፤ እናንተ ግድ አላችሁኝ፤ እናንተ እኔን ልታመሰግኑ ይገባ ነበርና። እኔ ምንም ባልሆን እንኳ፥ ከዋነኞቹ ሐዋርያት በምንም አልጎድልምና። 12 በእርግጥ የሐዋርያነት ምልክት በመካከላችሁ በምልክትና በድንቅ ነገር በተአምራትም በሁሉ ትዕግሥት ተደረገ። 13 እኔ ራሴ ካልከበድሁባችሁ ከዚህ በቀር፥ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን ያነሳችሁበት በምን እኮ ነው? ይህን በደሌን ይቅር በሉልኝ። 14 እነሆ፥ ወደ እናንተ እመጣ ዘንድ ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ አልከብድባችሁምም፥ እናንተን እንጂ ያላችሁን አልፈልግምና። ወላጆች ለልጆች እንጂ ልጆች ለወላጆች ገንዘብ ሊያከማቹ አይገባቸውምና። 15 እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ። ከመጠን ይልቅ ብወዳችሁ በዚህ ልክ ፍቅራችሁ የሚያንስ ነውን? 16 ይሁን እንጂ እኔ አልከበድሁባችሁም፤ ነገር ግን ሸንጋይ ሆኜ በተንኰል ያዝኋችሁ። 17 ወደ እናንተ ከላክኋቸው በአንዱ ስንኳ አታለልኋችሁን? 18 ቲቶን መከርሁት ከእርሱም ጋር ወንድሙን ላክሁት፤ ቲቶስ አታለላችሁን? በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? በአንድ ፍለጋስ አልተመላለስንም? 19 ለእናንተ ስለ ራሳችን እንድንመልስ ሁልጊዜ ይመስላችኋልን? በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን፤ ነገር ግን፥ ወዳጆች፥ እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። 20 ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤ 21 እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ።

2 ቆሮንቶስ 13

1 ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሁሉ ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል። 2-3 ሁለተኛ በእናንተ ዘንድ በነበርሁ ጊዜ እንደ ተናገርሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ፥ እንደ ገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ላደረጉት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ ብዬአለሁ፥ አስቀድሜም እላለሁ። ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው። 4 በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን። 5 በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 6 እኛ ግን የማንበቃ እንዳይደለን ልታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። 7 ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የምንበቃ ሆነን እንገለጥ ዘንድ አይደለም ነገር ግን እኛ ምንም እንደማንበቃ ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው። 8 ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 9 እኛ ስንደክም እናንተም ኃይለኞች ስትሆኑ ደስ ብሎናልና፤ እናንተ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ ለዚህ ደግሞ እንጸልያለን። 10 ስለዚህ ጌታ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ እንደ ሰጠኝ ሥልጣን፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በቁርጥ እንዳልሠራ በሩቅ ሆኜ ይህን እጽፋለሁ። 11 በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 12 በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። 13 ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14 የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ገላትያ 1

1-2 በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤ 3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4 ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። 5 ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። 6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ 7 እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። 8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። 9 አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 10 ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። 11 ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ 12 ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። 13 በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ 14 ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። 15-16 ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ 17 ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። 18 ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ 19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20 ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። 21 ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። 22 በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ 23 ነገር ግን። ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24 ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

ገላትያ 2

1 ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ 2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። 3 ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ 4 ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። 5 የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም። 6 አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ 7 ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ 8 ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። 9 ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ 10 ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ። 11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። 12 አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። 13 የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። 14 ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። 15 እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ 16 ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። 17 ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። 18 ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና። 19 እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። 20 ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

ገላትያ 3

1 የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? 2 ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? 3 እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? 4 በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? 5 እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? 6 እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። 7 እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። 8 መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። 9 እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። 10 ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። 11 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። 12 ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። 13 በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ 14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ። 15 ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። 16 ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። 17 ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። 18 ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። 19 እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። 20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 21 እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤ 22 ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። 23 እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር። 24 እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ 25 እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። 26 በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ 27 ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። 28 አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። 29 እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።

ገላትያ 4

1 ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ 2 ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። 3 እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ 4 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5 እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። 6 ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። 7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። 8 ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ 9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን? 10 ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። 11 ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። 12 ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም። 13 በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥ 14 በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። 15 እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ። 16 እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? 17 በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። 18 ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። 19 ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። 20 ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ። 21 እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። 22 አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። 23 ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። 24 ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። 25 ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። 26 ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። 27 አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። 28 እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። 29 ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። 30 ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። 31 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።

ገላትያ 5

1 በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። 2 እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። 3 ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። 4 በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። 5 እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። 6 በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 7 በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? 8 ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። 9-10 የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። 11 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። 12 የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። 13 ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። 14 ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። 15 ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። 16 ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። 17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። 18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም። 19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ 20 መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ 21 መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 22 የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። 23 እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም። 24 የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። 25 በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። 26 እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።

ገላትያ 6

1 ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። 2 ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። 3 አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። 4 ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ 5 እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። 6 ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። 7 አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ 8 በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። 9 ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። 10 እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ። 11 እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። 12 በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። 13 በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። 14 ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። 15 በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። 16 በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። 17 እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ። 18 ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።

ኤፌሶን 1

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3 በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4 ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። 5 በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። 6 በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። 7 በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። 8 ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። 9 በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ 10 በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። 11 እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። 12 ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። 13 እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ 14 እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል። 15 ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለ ማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ፥ 16 ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ 17 የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። 18-19 ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ 20-21 ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ 22 ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። 23 እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት።

ኤፌሶን 2

1-2 በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። 3 በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። 4 ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ 5 ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ 6-7 በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። 8 ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ 9 ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። 10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። 11 ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ 12 በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። 13 አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። 14-15 እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ 16 ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። 17 መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ 18 በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና። 19 እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። 20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ 21 በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ 22 በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።

ኤፌሶን 3

1 ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ። 2 ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ 3 አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ 4 ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ 5-6 ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። 7 እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠንየወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት። 8-9 ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤ 10 ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ 11 ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ 12 በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን። 13 ስለዚህ ስለ እናንተ ስላለ መከራዬ እንዳትታክቱ እለምናችኋለሁ፥ ክብራችሁ ነውና። 14-15 ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ 16-17 በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥ 18-19 ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። 20 እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥ 21 ለእርሱ በቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ እስከ ትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

ኤፌሶን 4

1 እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ 2 በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ 3 በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4 በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5 አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ 6 ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። 7 ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። 8 ስለዚህ። ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። 9 ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? 10 ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። 11 እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ 12-13 ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። 14 እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ 15 ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ 16 ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። 17 እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። 18 እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ 19 ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። 20 እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ 21 በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ 22 ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ 23 በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ 24 ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። 25 ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። 26 ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ 27 በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። 28 የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። 29 ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። 30 ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። 31 መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። 32 እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።

ኤፌሶን 5

1 እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ 2 ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ። 3 ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ 4 የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፥ ይልቁን ምስጋና እንጂ። 5 ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። 6 ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ። 7 እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ፤ 8 ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ 9-10 የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ 11 ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ 12 እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ 13 ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። 14 ስለዚህ። አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። 15 እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ 16 ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። 17 ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። 18 መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ 19 በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ 20 ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። 21 ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። 22 ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ 23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። 24 ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። 25-26 ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ 27 እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። 28 እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ 29-30 ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። 31 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። 32 ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። 33 ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።

ኤፌሶን 6

1 ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። 2-3 መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። 4 እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። 5 ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ 6 የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። 7 ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ 8 ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። 9 እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። 10 በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። 11 የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። 12 መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። 13 ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። 14-15 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ 16 በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ 17 የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 18 በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ 19 ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ 20 ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ። 21 ነገር ግን እናንተ ደግሞ እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ያስታውቃችኋል፤ 22 ወሬአችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው። 23 ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። 24 ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።

ፊልጵስዩስ 1

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3-5 ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። 6 በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ 7 በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። 8 በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። 9-11 ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። 12 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 13 ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ 14 በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። 15 አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ 16 እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ 17 እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። 18 ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። 19 ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ 20 ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። 21 ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። 22 ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። 23 በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24 ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። 25-26 ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። 27 ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። 28 በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29 ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ 30 በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።

ፊልጵስዩስ 2

1 በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ 2 በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ 3 ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ 4 እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። 5 በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። 6 እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ 7 ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ 8 በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። 9 በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ 10 ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ 11 መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። 12 ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ 13 ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። 14-15 በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ 16 በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል። 17 ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል፤ ከሁላችሁም ጋር አብሬ ደስ ብሎኛል፤ 18 እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ ከእኔም ጋር አብራችሁ ደስ ይበላችሁ። 19 ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20 እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ 21 ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። 22 ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ። 23 እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 24 ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ። 25 ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛ ወታደርም የሚሆነውን፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ፤ 26 ሁላችሁን ይናፍቃልና፥ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። 27 በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፥ ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ ለእኔ ደግሞ እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም። 28 እንግዲህ እንደ ገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በብዙ ፍጥነት እልከዋለሁ። 29 እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፥ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ 30 በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን እንዲፈጽም፥ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና።

ፊልጵስዩስ 3

1 በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። 2 ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። 3 እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። 4 እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። 5 በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6 ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 7 ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ። 8-9 አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ 10-11 እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። 12 አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። 13 ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ 14 በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። 15 እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ 16 ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። 17 ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። 18 ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። 19 መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። 20 እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ 21 እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።

ፊልጵስዩስ 4

1 ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ። 2 በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። 3 አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና። 4 ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። 5 ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። 6 ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። 7 አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። 8 በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ 9 ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 10 ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። 11 ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። 12 መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። 13 ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። 14 ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። 15 የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ 16 በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። 17 በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። 18 ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። 19 አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። 20 ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 21 ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22 ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ቆላስይስ 1

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ጢሞቴዎስም ወንድሙ፥ 2 በቈላስይስ ለሚኖሩ ቅዱሳንና በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይሁን። 3-5 ስለ እናንተ ስንጸልይ፥ በሰማይ ከተዘጋጀላችሁ ተስፋ የተነሣ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ እምነታችሁ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ስለዚህም ተስፋ በወንጌል እውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ። 6 ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ እግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል። 7 ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው። 8 ደግሞም በመንፈስ ስለሚሆን ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን። 9 ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም። 10-11 በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥ 12 ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። 13-14 እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። 15-16 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። 17 እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። 18 እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። 19-20 እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። 21-22 እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። 23 ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። 24 አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። 25 ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ። 26 ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። 27 ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። 28 እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው። 29 ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።

ቆላስይስ 2

1 ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም በሥጋ ስላላዩት ሁሉ እንዴት ያለ ትልቅ መጋደል እንዳለኝ ልታውቁ እወዳለሁና። 2 ልባቸው እንዲጸናና፥ በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ። 3 የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና። 4 ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ። 5 በሥጋ ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፥ ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል። 6 እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። 7 ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። 8 እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። 9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። 10 ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። 11 የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። 12 በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። 13 እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። 14 በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። 15 አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። 16 እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። 17 እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። 18 ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። 19 እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። 20-21 ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ 22 እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። 23 ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።

ቆላስይስ 3

1 እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። 2 በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። 3 ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና። 4 ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ። 5 እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው። 6 በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል። 7 እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። 8 አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ። 9 እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ 10 የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል። 11 በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። 12 እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። 13 እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። 14 በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። 15 በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ። የምታመሰግኑም ሁኑ። 16 የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ። በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ። 17 እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። 18 ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። 19 ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው። 20 ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ። 21 አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው። 22 ባሪያዎች ሆይ፥ በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፥ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፥ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ። 23 ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ 24 ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና። የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና። 25 የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፥ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።

ቆላስይስ 4

1 ጌቶች ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና ለባሪያዎቻችሁ በጽድቅና በቅንነት አድርጉላቸው። 2 ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ። 3 በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ። 4 ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። 5 ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። 6 ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። 7 የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ ቲኪቆስ ኑሮዬን ሁሉ ያስታውቃችኋል። 8-9 ወሬያችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና፥ ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ ጋር ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው። የዚህን ስፍራ ወሬ ሁሉ ያስታውቁአችኋል። 10-11 ከተገረዙት ወገን ያሉት፥ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ስለ ማርቆስ። ወደ እናንተ ቢመጣ፥ ተቀበሉት የሚል ትእዛዝ ተቀበላችሁ። በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፥ እኔንም አጽናንተውኛል። 12 ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል። 13 ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና። 14 የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 15 በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን። 16 ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ። ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። 17 ለአክሪጳም። በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ። 18 በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

1 ተሰሎንቄ 1

1 ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። 2-3 በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ 4 በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና። 5 ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ። 6 ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤ 7 ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው። 8 ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል። 9-10 እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።

1 ተሰሎንቄ 2

1 ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። 2 ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን። 3 ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤ 4 ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። 5 እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤ 6 የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። 7 ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ 8 እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና። 9 ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን። 10 በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ 11-12 ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና። 13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። 14 እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና። 15 እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥ 16 ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል። 17 እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤ 18 ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን። 19 ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን? 20 እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።

1 ተሰሎንቄ 3

1 ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ። 2 ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤ 3 በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። 4 በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ። 5 ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ። 6 አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥ 7 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤ 8 እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና። 9-10 ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን? 11 አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤ 12-13 ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።

1 ተሰሎንቄ 4

1 እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን። 2 በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። 3 ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ 4-5 ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ 6 አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። 7 ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። 8 እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ። 9 እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤ 10-12 እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 13 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። 14 ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። 15 በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ 16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ 17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። 18 ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።

1 ተሰሎንቄ 5

1 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 2 የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። 3 ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። 4 እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ 5 ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ 6 እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 7 የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 8 እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤ 9 እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ። 10 የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ። 11 ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው። 12-13 ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 14 ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። 15 ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ። 16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 17-18 ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 19 መንፈስን አታጥፉ፤ 20-21 ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ 22 ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። 23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 24 የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 25 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። 26 ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 27 ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ። 28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

2 ተሰሎንቄ 1

1 ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። 3 ወንድሞች ሆይ፥ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤ 4 ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን። 5 ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። 6-7 ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። 8 እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ 9-10 በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ። 11-12 ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።

2 ተሰሎንቄ 2

1-2 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት። የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። 3 ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። 4 እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው። 5 ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ፥ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን? 6 በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ፥ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። 7 የዓመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ። 8 በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤ 9-10 ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። 11-12 ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል። 13 እኛ ግን፥ በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤ 14 ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ። 15 እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ። 16-17 ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ።

2 ተሰሎንቄ 3

1-2 በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጌታ ቃል እንዲሮጥ በእናንተም ዘንድ ደግሞ እንደሚሆን እንዲከበር፥ እምነትም ለሁሉ ስለማይሆን ከዓመፀኞችና ከክፉዎች ሰዎች እንድንድን ስለ እኛ ጸልዩ። 3 ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው። 4 የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል። 5 ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው። 6 ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። 7 እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤ 8 ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። 9 ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም። 10 ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን። ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና። 11 ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። 12 እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን። 13 እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። 14 በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። 15 ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት። 16 የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። 17 በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ። 18 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

1 ጢሞቴዎስ 1

1 መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ 2 በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። 3-4 ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም። 5 የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 6-7 ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል። 8 ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤ 9-11 ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው። 12 ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤ 13 አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፥ 14 የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። 15 ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ 16 ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ። 17 ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። 18 ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ 19 እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ 20 ከእነዚያም፥ እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው።

1 ጢሞቴዎስ 2

1-2 እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 3-4 ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 5 አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ 6 ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤ 7 እኔም ለዚህ ነገር አዋጅ ነጋሪና ሐዋርያ በእምነትና በእውነትም የአሕዛብ አስተማሪ ለመሆን ተሾምሁ፤ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም። 8 እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ። 9-10 እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። 11 ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር፤ 12 ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም። 13 አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና፥ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች። 14 የተታለለም አዳም አይደለም፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች፤ 15 ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች።

1 ጢሞቴዎስ 3

1 ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። 2 እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ 3 የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 4 ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 5 ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? 6 በትዕቢት ተነፍቶ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። 7 በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል። 8 እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ 9 ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 10 እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 11 እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፥ የማያሙ፥ ልከኞች፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 12 ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። 13 በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ። 14 ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይህን እጽፍልሃለሁ። 15 ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።

1 ጢሞቴዎስ 4

1-2 መንፈስ ግን በግልጥ። በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥ 3 እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ። 4 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ 5 በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። 6 ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 7 ነገር ግን ለዚህ ዓለም ከሚመችና የአሮጊቶችን ሴቶች ጨዋታ ከሚመስለው ተረት ራቅ። እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ። 8 ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። 9 ይህ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ 10 ይህን ለማግኘት እንደክማለንና፥ ስለዚህም እንሰደባለን፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው። 11-12 ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው። 13 እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ። 14 በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። 15 ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር። 16 ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።

1 ጢሞቴዎስ 5

1-2 ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው። 3 በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። 4 ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። 5 ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ 6 ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። 7 ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። 8 ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው። 9 ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ 10 ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። 11 ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤ 12 የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤ 13 ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም። 14 እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤ 15 ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና። 16 ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን፥ ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት። 17 በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። 18 መጽሐፍ። የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ። ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና። 19 ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። 20 ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሰሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። 21 አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ። 22 በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። 23 ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ። 24 የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ 25 እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።

1 ጢሞቴዎስ 6

1 የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱ አንዳይሰደብ፥ ከቀንበር በታች ያሉቱ ባሪያዎች ሁሉ ለገዙአቸው ጌቶች ክብር ሁሉ እንደ ተገባቸው ይቍጠሩአቸው። 2 የሚያምኑም ጌቶች ያሉአቸው፥ ወንድሞች ስለ ሆኑ አይናቁአቸው፥ ነገር ግን በመልካም ሥራቸው የሚጠቅሙ የሚያምኑና የተወደዱ ስለ ሆኑ፥ ከፊት ይልቅ ያገልግሉ። 3 እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ 4-5 በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ። 6 ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 7 ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ 8 አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 9 ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። 10 ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 11 አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። 12 መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 13 ሁሉን በሕይወት በሚጠብቅ በእግዚአብሔር ፊት፥ በጴንጤናዊውም በጲላጦስ ዘንድ መልካሙን መታመን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት አዝሃለሁ፤ 14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ 15 ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል። 16 እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን። 17 በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። 18-19 እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 20 ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ 21 ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።

2 ጢሞቴዎስ 1

1 በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚሆን የሕይወት ተስፋ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ 2 ለተወደደው ልጄ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። 3 ሌትና ቀን በልመናዬ ሳላቋርጥ ስለማስብህ እንደ አባቶቼ አድርጌ በንጹሕ ሕሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ 4 እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። 5 በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ። 6 ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ። 7 እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 8 እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤ 9 ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥ 10-11 አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል። 12 ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ። 13 በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ 14 መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ። 15 በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ፥ ከእነርሱም ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ናቸው። 16 ጌታ ልሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤ 17 በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ፤ 18 በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።

2 ጢሞቴዎስ 2

1 እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። 2 ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። 3 እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። 4 የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያጠላልፍም። 5 ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። 6 የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል። 7 የምለውን ተመልከት፤ ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ። 8 በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ 9 ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። 10 ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ። 11 ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ 12 ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ 13 ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና። 14 ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና። 15 የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ። 16 ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤ 17 ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤ 18 እነዚህም። ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ። 19 ሆኖም። ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል። 20 በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፥ እኵሌቶቹም ለክብር፥ እኵሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ 21 እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፥ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። 22 ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። 23 ነገር ግን ጠብን እንዲያመጣ አውቀህ ከሰነፎችና ካልተማሩ ምርመራ ራቅ፤ 24 የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። 25-26 ደግሞም። ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።

2 ጢሞቴዎስ 3

1 ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2 ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ 3 ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ 4 ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ 5 የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 6-7 ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። 8 ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። 9 ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም። 10 አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ 11 በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ። 12 በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 13 ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ። 14 አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ 15 ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። 16-17 የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።

2 ጢሞቴዎስ 4

1 በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ 2 ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 3 ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። 4 እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። 5 አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። 6 በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። 7 መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ 8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። 9 በቶሎ ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ 10 ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና፥ ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል፤ ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤ 11 ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ። ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው። 12 ቲኪቆስን ግን ወደ ኤፌሶን ላክሁት። 13 ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ። 14 የናስ አንጥረኛው እስክንድሮስ እጅግ ከፋብኝ፤ ጌታ እንደ ሥራው ይመልስለታል። 15 አንተም ደግሞ ከእርሱ ተጠበቅ፥ የምንናገረውን እጅግ ተቃውሞአልና። 16 በፊተኛው ሙግቴ አንድ ስንኳ አልደረሰልኝም፥ ሁሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም አይቍጠርባቸው፤ 17 ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ፥ ከአንበሳ አፍም ዳንሁ። 18 ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። 19 ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ። 20 ኤርስጦስ በቆሮንቶስ ቀረ፥ ጥሮፊሞስን ግን ታሞ በሚሊጢን ተውሁት። 21 ከክረምት በፊት እንድትመጣ ትጋ። ኤውግሎስና ጱዴስ ሊኖስም ቅላውዲያም ወንድሞችም ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። 22 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ቲቶ 1

1-2 የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔር ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፥ 3 በዘመኑም ጊዜ፥ መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ፤ 4 በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። 5 ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤ 6 የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው። 7 ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ 8 ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ 9 ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። 10 የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤ 11 እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል። 12 የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ። የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸተኞች፥ ክፉዎች አራዊት፥ በላተኞች፥ ሥራ ፈቶች ናቸው ብሎአል። 13-14 ይህ ምስክር እውነተኛ ነው። ስለዚህ ምክንያት የአይሁድን ተረትና ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን ሰዎች ትእዛዝ ሳያዳምጡ፥ በሃይማኖት ጤናሞች እንዲሆኑ በብርቱ ውቀሳቸው። 15 ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል። 16 እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።

ቲቶ 2

1 አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር። 2 ሽማግሌዎች ልከኞች፥ ጭምቶች፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤ 3 እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፥ የማያሙ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ 4-5 ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ ልጆቻቸውን የሚወዱ፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ንጹሖች፥ በቤት የሚሠሩ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው። 6 ጎበዞችም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲገዙ ምከራቸው። 7-8 የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። 9-10 ባሪያዎች ስለ መድኃኒታችን ስለ እግዚአብሔር የሚሆነውን ትምህርት በሁሉ ነገር ያስመሰግኑ ዘንድ፥ ለገዛ ጌቶቻቸው እንዲገዙ በሁሉም ደስ እንዲያሰኙ፥ ሳይቃወሙና ሳይሰርቁም በጎ ታማኝነትን ሁሉ እንዲያሳዩ ምከራቸው። 11 ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ 12-13 ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ 14 መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። 15 ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ።

ቲቶ 3

1-2 ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፥ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፥ ማንንም የማይሰድቡ፥ የማይከራከሩ፥ ገሮች፥ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ ኣሳስባቸው። 3 እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። 4 ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ 5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ 6-7 ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። 8 ቃሉ የታመነ ነው። እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ። ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤ 9 ነገር ግን ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤ 10-11 መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ፥ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ። 12 አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ ስልክ፥ ወደ ኒቆጵልዮን ወደ እኔ እንድትመጣ ትጋ፤ በዚያ ልከርም ቈርጬአለሁና። 13 ሕግ አዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን ምንም እንዳይጎድልባቸው በጉዞአቸው ተግተህ እርዳ። 14 ከወገናችንም ያሉት ደግሞ ፍሬ ቢሶች ሆነው እንዳይቀሩ፥ የግድ ስለሚያስፈልገው ነገር በመልካም ሥራ እንዲጸኑ ይማሩ። 15 ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። በእምነት ለሚወዱን ሰላምታ አቅርብልን። ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ፊልሞና 1

1 የክርስቶስ ኢየሱስ እስር ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ ለፊልሞና፥ 2 ለእኅታችንም ለአፍብያ፥ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ፥ በቤትህም ላለች ቤተ ክርስቲያን፤ 3 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4-5 በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 6 የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ 7 የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። 8 ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ 9 ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። 10-11 አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። 12 እርሱን እልከዋለሁ፤ 13 አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ 14 ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። 15 ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ 16 ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፥ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በስጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም። 17 እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። 18 በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤ 19 እኔ ጳውሎስ። እኔ እመልሰዋለሁ ብዬ በእጄ እጽፋለሁ፤ ከዚህም በላይ ለእኔ የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም። 20 አዎን፥ ወንድሜ ሆይ፥ በጌታ እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። 21 ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ እንድትታዘዝም ታምኜ እጽፍልሃለሁ። 22 ደግሞ ከዚህም ጋር የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ፤ በጸሎታችሁ ለእናንተ እንድሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና። 23 በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ 24 አብረውኝም የሚሰሩ ማርቆስና አርስጥሮኮስ ዴማስም ሉቃስም ሰላምታ ያቀርቡልሃል። 25 የጌታችን የኢሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ዕብራውያን 1

1 ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ 2 ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ 3 እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ 4 ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። 5 ከመላእክትስ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል 6 ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። 7 ስለ መላእክትም። መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ 8 ይላል፤ ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። 9 ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ 10 ይላል። ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ 11 እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ 12 እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም 13 ይላል። ነገር ግን ከመላእክት። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ 14 ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?

ዕብራውያን 2

1 ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። 2 በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? 3 ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥ 4 እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት። 5 ስለ እርሱ የምንናገርበትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛው አይደለምና። 6 ነገር ግን አንዱ በአንድ ስፍራ። ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ወይስ ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? 7 ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ 8 ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም፤ 9 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን። 10 ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና። 11-12 የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ 13 ስለዚህም ምክንያት። ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም። እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም። እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። 14-15 እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። 16 የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። 17 ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። 18 እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።

ዕብራውያን 3

1 ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ 2 ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ። 3 ቤትን የሚያዘጋጀው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው መጠን፥ እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሮአልና። 4 እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፥ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው። 5 ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፤ 6 እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን። 7 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል። 8-9 ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። 10 ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ። ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤ 11 እንዲሁ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ። 12 ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ 13 ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ 14 የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤ 15 እየተባለ። ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። 16 ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? 17 አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? 18 ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19 ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።

ዕብራውያን 4

1 እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ። 2 ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። 3 ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም። እንዲህ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። 4 ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ። እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤ 5 በዚህ ስፍራም ደግሞ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም። 6 እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ። 7 ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር። ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። 8 ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። 9 እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። 10 ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። 11 እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። 12 የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ 13 እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። 14 እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። 15 ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። 16 እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።

ዕብራውያን 5

1 ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ 2 እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ 3 በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። 4 እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። 5 እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ 6 እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል። 7 እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ 8 ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ 9-10 ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። 11 ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። 12 ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። 13 ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ 14 ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።

ዕብራውያን 6

1-2 ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፥ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው። 3 እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። 4 አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን 5 መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን 6 በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና። 7 ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ 8 እሾህና ኵርንችትን ግን ብታወጣ፥ የተጣለች ናት ለመረገምም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። 9 ስለ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ምንም እንኳ እንዲሁ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንዲሆንላችሁ ተረድተናል። 10 እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና። 11-12 በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 13-14 እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ። በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ ብሎ፥ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፥ በራሱ ማለ፤ 15 እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ። 16 ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና፥ ለማስረዳትም የሆነው መሐላ የሙግት ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ 17-18 ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ 19 ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው፤ 20 በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።

ዕብራውያን 7

1 የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ 2 ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። 3 አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። 4 የአባቶች አለቃ አብርሃም ከዘረፋው የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ። 5 ከሌዊ ልጆችም ክህነትን የሚቀበሉት ከህዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ ከእነርሱ አሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው፤ 6 ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል። 7 ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው። 8 በዚህስ የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ያስወጣሉ፥ በዚያ ግን የሚያስወጣ በሕይወት እንዲኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። 9 ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ 10 መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና። 11 እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? 12 ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና። 13 ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤ 14 ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም። 15-16 በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው። 17 አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና። 18-19 ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። 20-21 እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን። ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ 22 እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። 23 እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ 24 እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ 25 ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። 26 ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ 27 እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። 28 ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።

ዕብራውያን 8

1 ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ 2 እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። 3 ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው። 4 እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤ 5 እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና። 6 አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል። 7 ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። 8 እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤ 9 ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ። 10 ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል። 11 እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን። ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና። 12 ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም። 13 አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።

ዕብራውያን 9

1 ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ስርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። 2 የመጀመሪያይቱ ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው የመስዋዕቱም ኅብስት ነበረባት፤ 3 ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፥ 4 በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበረ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፤ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ፥ 5 በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ስለ እነዚህም ስለ እያንዳንዳቸው ልንናገር አሁን አንችልም። 6 ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ 7 በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ 8 ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። 9-10 ይህም ለአሁኑ ጊዜ ምሳሌ ነው፥ እንደዚህም መባና መስዋዕት ይቀርባሉ፤ እነዚህም እስከ መታደስ ዘመን ድረስ የተደረጉ፥ ስለ ምግብና ስለ መጠጥም ስለ ልዩ ልዩ መታጠብም የሚሆኑ የሥጋ ሥርዓቶች ብቻ ናቸውና የሚያመልከውን በህሊና ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም። 11 ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ 12 የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። 13 የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ 14 ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? 15 ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። 16 ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፤ 17 ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናልና፥ ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን ከቶ አይጠቅምም። 18 ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልተመረቀም። 19-20 ሙሴም ትእዛዛትን ሁሉ እንደ ሕጉ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ፥ የጥጆችንና የፍየሎችን ደም ከውኃና ከቀይ የበግ ጠጕር ከሂሶጵም ጋር ይዞ። እግዚአብሔር ያዘዘላችሁ የኪዳን ደም ይህ ነው ብሎ በመጽሐፉና በሕዝቡ ሁሉ ላይ ረጨው። 21 እንዲሁም በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጨ። 22 እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። 23 እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። 24 ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። 25 ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ 26 እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። 27 ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ 28 እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።

ዕብራውያን 10

1 ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። 2 እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? 3 ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ 4 የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። 5 ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ 6 በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም። 7 በዚያን ጊዜ። እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ 8 ይላል። በዚህ ላይ። መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥ 9 ቀጥሎ። እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። 10 በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። 11 ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ 12 እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ 13 ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። 14 አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። 15-16 መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ 17 ብሎ ከተናገረ በኋላ፥ ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። 18 የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም። 19-20 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥ 21 በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ 22 ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ 23 የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ 24 ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ 25 በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። 26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ 27 የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። 28 የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ 29 የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? 30 በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም። ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። 31 በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። 32-33 ነገር ግን ግማሽ በነቀፋና በጭንቅ እንደ መጫወቻ ስለ ሆናችሁ ግማሽም እንዲህ ካሉት ጋር ስለ ተካፈላችሁ፥ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ። 34 የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። 35 እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። 36 የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። 37 ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ 38 ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። 39 እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።

ዕብራውያን 11

1 እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። 2 ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። 3 ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። 4 አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል። 5 ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤ 6 ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። 7 ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ስዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፥ በዚህም ዓለምን ኰነነ፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። 8 አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። 9 ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ 10 መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። 11 ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። 12 ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ። 13 እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። 14 እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲፈልጉ ያመለክታሉና። 15 ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፥ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ 16 አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። 17-18 አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፥ የተስፋን ቃል የተቀበለው። በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ 19 እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው። 20 ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። 21 ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸው ባረካቸው፥ በዘንጉም ጫፍ ተጠግቶ ሰገደ። 22 ዮሴፍ ወደ ሞት ቀርቦ ሳለ በእምነት ስለ እስራኤል ልጆች መውጣት አስታወሰ፥ ስለ አጥንቱም አዘዛቸው። 23 ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን መሆኑን አይተው በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት የንጉሥንም አዋጅ አልፈሩም። 24 ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ 25-26 ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። 27 የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና። 28 አጥፊው የበኵሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ። 29 በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፥ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ። 30 የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። 31 ጋለሞታይቱ ረዓብ ሰላዮችን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙ ጋር በእምነት አልጠፋችም። 32 እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። 33 እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ 34 የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። 35 ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ 36 ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ 37 በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ 38 ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። 39-40 እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።

ዕብራውያን 12

1-2 እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። 3 በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ። 4 ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤ 5-6 እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል። 7 ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? 8 ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9 ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን? 10 እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል። 11 ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል። 12 ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ 13 ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ። 14 ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና። 15 የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥ 16 ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። 17 ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና። 18 ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤ 19 ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ፤ 20 እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤ 21 ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ 22 ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ 23 በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ 24 የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል። 25 ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን? 26 በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል። 27 ዳሩ ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል። 28 ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤ 29 አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።

ዕብራውያን 13

1-2 የወንድማማች መዋደድ ይኑር። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። 3 ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ። 4 መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። 5 አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ። አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ 6 ስለዚህ በድፍረት። ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን። 7 የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። 8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው። 9 ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና። 10 መሠዊያ አለን፥ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም። 11 ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት ወደ ቅድስት የእንስሶችን ደም ያቀርባልና፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል። 12 ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። 13 እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤ 14 በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን። 15 እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት። 16 ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና። 17 ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። 18 ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና። 19 ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። 20 በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥ 21 በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 22 ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ፥ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና። 23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ እወቁ፥ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ። 24 ለዋኖቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 25 ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

የያዕቆብ 1

1 የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። 2-3 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት 4 ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። 5 ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። 6 ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። 7-8 ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። 9-10 የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። 11 ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል። 12 በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። 13 ማንም ሲፈተን። በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። 14 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። 15 ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። 16 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። 17 በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። 18 ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። 19 ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ 20 የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። 21 ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። 22 ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። 23 ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ 24 ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። 25 ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። 26 አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው። 27 ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።

የያዕቆብ 2

1 ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ። 2 የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ 3 የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ። አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም። አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? 4 ክፉ አሳብ ያላቸውም ዳኞች መሆናችሁ አይደለምን? 5 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? 6 እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን? 7 የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን? 8 ነገር ግን መጽሐፍ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤ 9 ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል። 10 ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ። አትግደል ብሎአልና፤ 11 ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል። 12 በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ። 13 ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል። 14 ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? 15 ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥ 16 ከእናንተ አንዱም። በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል? 17 እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። 18 ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። 19 እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። 20 አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? 21 አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? 22 እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? 23 መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ። 24 ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። 25 እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 26 ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።

የያዕቆብ 3

1 ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። 2 ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 3 እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። 4 እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። 5 እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። 6 አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል። 7 የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ 8 ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። 9 በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ 10 ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። 11 ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን? 12 ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም። 13 ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። 14 ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። 15 ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ 16 ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። 17 ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። 18 የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።

የያዕቆብ 4

1 በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? 2 ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ 3 ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። 4 አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5 ወይስ መጽሐፍ። በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? 6 ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። 7 እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ 8 ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። 9 ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10 በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል። 11 ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ። ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል፤ በሕግም ብትፈርድ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። 12 ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? 13 አሁንም። ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። 14 ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። 15 በዚህ ፈንታ። ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል። 16 አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17 እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።

የያዕቆብ 5

1 አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ። 2 ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል። 3 ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል። 4 እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል። 5 በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል። 6 ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም። 7 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። 8 እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። 9 ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። 10 ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። 11 እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። 12 ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። 13 ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። 14 ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። 15 የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። 16 እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። 17 ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ 18 ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። 19 ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ 20 ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።

1 የጴጥሮስ 1

1-2 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 3-5 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል። 6-7 በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል። 8-9 እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል። 10 ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤ 11 በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። 12 ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ። 13 ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። 14 እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። 15-16 ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ። 17 ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። 18-19 ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 20-21 ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። 22 ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደደ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23 ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። 24 ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ 25 የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።

1 የጴጥሮስ 2

1 እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ 2-3 ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ። 4 በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥ 5 እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 6 በመጽሐፍ። እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። 7 እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤ 8 የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው። 9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 10 እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። 11 ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ 12 ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። 13 ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤ 14 ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። 15 በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤ 16 አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። 17 ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ። 18 ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ። 19 በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። 20 ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። 21 የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። 22 እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ 23 ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ 24 ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤*ፍ1* 25 በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። ፍ1 በግዕዝ እንዲህ ተጽፎአል። ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፅ በሥጋሁ ከመ ያውፅአነ እምኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ።

1 የጴጥሮስ 3

1-2 እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። 3 ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ 4 ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 5 እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና፤ 6 እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም። ጌታ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ። 7 እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው። 8 በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ 9 ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 10 ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ 11 ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ 12 የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው። 13 በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? 14 ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ 15 ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን። 16 በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። 17 የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና። 18 ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥ 19 በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 20 ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። 21 ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ 22 እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።

1 የጴጥሮስ 4

1-2 ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና። 3 የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና። 4 በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ፤ 5 ግን እነርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6 እንደሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና። 7 ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥ 8 ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 9 ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤ 10 ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 11 ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 12 ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ 13 ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። 14 ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። 15 ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ 16 ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። 17 ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18 ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው? 19 ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።

1 የጴጥሮስ 5

1 እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2 በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 3 ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 4 የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። 5 እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 6 እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 7 እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 8 በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 9 በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 10 በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። 11 ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። 12 እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ። 13 ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14 በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።

2 የጴጥሮስ 1

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ የሆነ ስምዖን ጴጥሮስ፥ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤ 2-3 የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 4 ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። 5 ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ 6 በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ 7 እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። 8 እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ 9 እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 10 ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። 11 እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና። 12 ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ምንም ብትጸኑ፥ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም። 13 ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል። 14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና። 15 ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ። 16 የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። 17 ከገናናው ክብር። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ 18 እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን። 19 ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ። 20 ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ 21 ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።

2 የጴጥሮስ 2

1 ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ 2 ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። 3 ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም። 4 እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ 5 ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ 6 ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ 7-8 ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ 9-10 ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ 11 ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። 12 እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ 13 የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ 14 ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። 15 ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥ 16 ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። 17 ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። 18 ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። 19 ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። 20 በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። 21 አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። 22 ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

2 የጴጥሮስ 3

1-2 ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት። በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችኋትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ። 3 በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ 4 እነርሱም። የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። 5 ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ 6 በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ 7 አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። 8 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። 9 ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። 10 የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። 11-12 ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ 13 ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። 14 ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ 15 የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። 16 በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። 17 እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤ 18 ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።

1 የዮሐንስ 1

1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ 2 ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ 3 እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። 4 ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን። 5 ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት። 6 ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ 7 ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 10 ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።

1 የዮሐንስ 2

1 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2 እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ። 3 ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን። 4 አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም። 5 ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ 6 በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል። 7 ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት። 8 ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል። 9 በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። 10 ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤ 11 ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና። 12 ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። 14 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ። 15-16 ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 17 ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 18 ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን። 19 ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ። 20 እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። 21 እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። 22 ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። 23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። 24 እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ። 25 እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው። 26 ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ። 27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 28 አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ። 29 ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።

1 የዮሐንስ 3

1 የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም። 2 ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። 3 በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። 4 ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው። 5 እርሱም ኃጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። 6 በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም። 7 ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። 8 ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 9 ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። 10 የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። 11 ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት። እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤ 12 ከክፉው እንደ ነበረ ወንድሙንም እንደ ገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ ስለ ምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥ የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። 13 ወንድሞች ሆይ፥ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። 14 እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። 15 ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 16 እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። 17 ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? 18 ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። 19-20 ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል። 21 ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥ 22 ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። 23 ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። 24 ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።

1 የዮሐንስ 4

1 ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። 2 የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ 3 ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 4 ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። 5 እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። 6 እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን። 7 ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። 8 ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። 9 በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። 10 ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። 11 ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። 12 እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። 13 ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። 14 እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። 15 ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። 16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። 17 በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። 18 ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። 19 እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 20 ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 21 እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

1 የዮሐንስ 5

1 ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። 2 እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። 3 ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 4 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 5 ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? 6 በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። 7 መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። 8 የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። 9 የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና። 10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። 11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። 12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። 13 የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 14 በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። 15 የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 16 ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም። 17 ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ። 18 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን። 19 ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን። 20 የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። 21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።

2 የዮሐንስ 1

1-2 በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤ 3 ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ። 4 ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል። 5 አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም። 6 እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት። 7 ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ገብተዋልና እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው፤ ይህ አሳቹና የክርስቶስ ተቃዋሚው ነው። 8 ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 9 ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። 10 ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ 11 ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና። 12 እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 13 የተመረጠችው የእኅትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

3 የዮሐንስ 1

1 ሽማግሌው በእውነት እኔ ለምወደው ለተወደደው ለጋይዮስ። 2 ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። 3 ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና። 4 ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም። 5 ወዳጅ ሆይ፥ ምንም እንግዶች ቢሆኑ፥ ለወንድሞች በምታደርገው ሁሉ የታመነ ሥራ ትሠራለህ፥ እነርሱም በማኅበር ፊት ስለ ፍቅርህ መስክረዋል፤ 6 ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አድርገህ በጉዞአቸው ብትረዳ መልካም ታደርጋለህ፤ 7 ከአሕዛብ አንዳች ሳይቀበሉ ስለ ስሙ ወጥተዋልና። 8 እንግዲህ ከእውነት ጋር አብረን እንድንሠራ እኛ እንዲህ ያሉትን በእንግድነት ልንቀበል ይገባናል። 9 ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። 10 ስለዚህ፥ እኔ ብመጣ፥ በእኛ ላይ በክፉ ቃል እየለፈለፈ የሚያደርገውን ሥራውን አሳስባለሁ፤ ይህም ሳይበቃው እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፥ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል። 11 ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል። በጎ የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ነው፤ ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም። 12 ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፥ እውነት ራስዋም ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፥ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። 13 ልጽፍልህ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረኝ፥ ዳሩ ግን በቀለምና በብርዕ ልጽፍልህ አልወድም፤ 14 ነገር ግን ወዲያው ላይህ ተስፋ አደርጋለሁ፥ አፍ ለአፍም እንነጋገራለን። 15 ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። ወዳጆችን በየስማቸው እየጠራህ ሰላምታ አቅርብልኝ።

የይሁዳ 1

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ 2 ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ። 3 ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። 4 ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። 5 ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። 6 መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። 7 እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። 8 እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9 የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም። 10 እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። 11 ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል። 12 እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ 13 የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው። 14-15 ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ። 16 እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል። 17 እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ 18 እነርሱ። በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። 19 እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። 20 እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ 21 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። 22 አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ 23 አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ። 24 ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው 25 ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

የዮሐንስ ራእይ 1

1 ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ 2 እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው። 4-5 ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ 6 መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን። 7 እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን። 8 ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል። 9 እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10 በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ 11 እንዲሁም። የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ። 12 የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፥ 13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14 ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ 15 እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፥ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ። 16 በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። 17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ። አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ 18 ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። 19 እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፥ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

የዮሐንስ ራእይ 2

1 በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል። 2 ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ። ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ 3 ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም። 4 ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና። 5 እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ። 6 ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና። 7 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ። 8 በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል። 9 መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ። 10 ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። 11 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። 12 በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል። 13 የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም። 14 ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ። 15 እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ። 16 እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ። 17 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል። 18 በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል። 19 ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ። 20 ዳሩ ግን። ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ 21 ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። 22 እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤ 23 ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። 24 ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፥ 25 ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ። 26-27 ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤ 28 የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ። 29 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

የዮሐንስ ራእይ 3

1 በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል። ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል። 2 ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና። 3 እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም። 4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። 6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። 7 በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል። 8 ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና። 9 እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። 10 የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። 11 እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። 12 ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። 13 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። 14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል። 15 በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። 16 እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። 17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ 18 ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። 19 እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ። 20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። 21 እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። 22 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

የዮሐንስ ራእይ 4

1 ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ። 2 ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤ 3 ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። 4 በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። 5 ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጣል፤ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፥ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 6 በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ። 7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። 8 አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። 9 እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥ 10-11 ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።

የዮሐንስ ራእይ 5

1 በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። 2 ብርቱም መልአክ። መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። 3 በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። 4 መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። 5 ከሽማግሌዎቹም አንዱ። አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ። 6 በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 7 መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው። 8 መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ። 9-10 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ። 11 አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥ 12 በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። 13 በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ። 14 አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።

የዮሐንስ ራእይ 6

1 በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። 2 አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት። 3 ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። 4 ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። 5 ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። 6 በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ። አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ። 7 አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። 8 አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። 9 አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። 10 በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። 11 ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። 12 ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ 13 በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥ 14 ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። 15 የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ 16 ተራራዎችንና ዓለቶችንም። በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ 17 ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።

የዮሐንስ ራእይ 7

1 ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። 2 የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ። 3 የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው። 4 የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። 5 ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ 6 ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ 7 ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ 8 ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። 9 ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ 10 በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። 11 መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። 12 አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። 13 ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ። እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። 14 እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። 15 ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። 16 ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ 17 በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።

የዮሐንስ ራእይ 8

1 ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። 3 ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። 4 የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። 5 መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። 6 ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። 7 ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። 8 ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ 9 በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ። 10 ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል። 11 የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። 12 አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት። 13 አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ። ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።

የዮሐንስ ራእይ 9

1 አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። 2 የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ። 3 ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው። 4 የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው። 5 አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው። 6 በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል። 7 የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፥ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤ 8 የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥ 9 የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፥ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ። 10 እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው። 11 በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል። 12 ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል። 13 ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥ 14 መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ። በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው። 15 የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። 16 የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። 17 ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። 18 ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። 19 የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ። 20 በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ 21 ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።

የዮሐንስ ራእይ 10

1 ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥ 2 የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 3 በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ። 4 ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም። ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ። 5 በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፥ 6 ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ። 7 ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ። 8 ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና ሲናገረኝና። ሂድና በባሕርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ። 9 ወደ መልአኩም ሄጄ። ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት። እርሱም። ውሰድና ብላት፥ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ። 10 ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ። 11 በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።

የዮሐንስ ራእይ 11

1 በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ። ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። 2 በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። 3 ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። 4 እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። 5 ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። 6 እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። 7 ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል። 8 በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። 9 ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፥ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። 10 እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። 11 ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፥ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። 12 በሰማይም። ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። 13 በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። 14 ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። 15 ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም። የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል 16 የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው 17 ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ። ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ 18 አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ። 19 በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።

የዮሐንስ ራእይ 12

1 ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። 2 እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። 3 ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ 4 ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። 5 አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። 6 ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። 7 በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ 8 ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። 9 ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። 10 ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል። አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። 11 እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። 12 ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና። 13 ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። 14 ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት። 15 እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ። 16 ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። 17 ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ [18] በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።

የዮሐንስ ራእይ 13

1 አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። 2 ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። 3 ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ 4 ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። 5 ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። 6 እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። 7 ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። 8 ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል። 9 ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። 10 ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው። 11 ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። 12 በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል። 13 እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል። 14 በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል። 15 የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። 16 ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ 17 የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። 18 አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።

የዮሐንስ ራእይ 14

1 አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። 2 እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ። 3 በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም። 4 ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። 5 በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም። 6 በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ 7 በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ። 8 ሌላም ሁለተኛ መልአክ። አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው። 9 ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥ 10 እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል። 11 የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም። 12 የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው። 13 ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ። 14 አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። 15 ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው። የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 16 በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች። 17 ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። 18 በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን። ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ። 19 መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ። 20 የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ።

የዮሐንስ ራእይ 15

1 ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ። 2 በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር የሚመስለውን አየሁ፥ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ። 3-4 ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ። 5 ከዚህም በኋላ አየሁ፥ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፥ 6 ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ። 7 ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአሔር ቍጣ የሞላባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው። 8 ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኃይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፥ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።

የዮሐንስ ራእይ 16

1 ለሰባቱም መላእክት። ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ። 2 ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው። 3 ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ። 4 ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። 5 የውኃውም መልአክ። ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤ 6 የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 7 ከመሰዊያውም። አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 8 አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት። 9 ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፥ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም። 10 አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፥ 11 ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፥ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም። 12 ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ። 13 ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤ 14 ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ። 15 እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። 16 በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው። 17 ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ። ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ። 18 መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፥ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ። 19 ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች። 20 ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም። 21 በሚዛንም አንድ ታላንት*ፍ1* የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና። ፍ1 አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው።

የዮሐንስ ራእይ 17

1 ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤ 2 የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ። 3 በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ። 4 ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤ 5 በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም። ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ። 6 ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ። 7 መልአኩም አለኝ። የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ። 8 ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ። 9 ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥ 10 ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል። 11 የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል። 12 ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፥ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። 13 እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፥ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። 14 እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ። 15 አለኝም። ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። 16 ያየኃቸውም አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፥ ሥጋዋንም ይበላሉ፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል። 17 እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና። 18 ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።

የዮሐንስ ራእይ 18

1 ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። 2 በብርቱም ድምፅ። ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ 3 አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ። 4 ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል። ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ 5 ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ። 6 እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፥ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ 7 ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት። በልብዋ። ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንም ከቶ አላይም ስላለች፥ 8 ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፥ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና። 9 ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ 10 ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው። አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ። 11 የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤ 12 ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ 13 ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው። 14 ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም። 15-17 እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ። በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥ 18 የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ። ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ። 19 በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ። በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ። 20 ሰማይ ሆይ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፥ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፥ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና። 21 አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል። ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም። 22 በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፥ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ 23 የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፥ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፥ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና። 24 በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።

የዮሐንስ ራእይ 19

1-2 ከዚህ በኋላ በሰማይ። ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፥ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ። 3 ደግመውም። ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል። 4 ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር። አሜን፥ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት። 5 ድምፅም። ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ 6 ሲል ከዙፋኑ ወጣ። እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል። ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና። 7 የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ። 8 ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና። 9 እርሱም። ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ። 10 ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም። እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ። 11 ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም። 12 ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ 13 በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል። 14 በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። 15 አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል። 16 በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው። 17-18 አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፥ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ። መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 19 በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ። 20 አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። 21 የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።

የዮሐንስ ራእይ 20

1 የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2 የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥ 3 ሺህ ዓመትም አሰረው፥ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል። 4 ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። 5 የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው። 6 በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። 7 ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥ 8 በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። 9 ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። 10 ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ። 11 ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12 ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። 13 ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። 14 ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15 በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።

የዮሐንስ ራእይ 21

1 አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም። 2 ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ። 3 ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ 4 እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 5 በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ። 6 አለኝም። ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ። 7 ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። 8 ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው። 9 ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ። 10-11 በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤ 12 ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር። 13 በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ። 14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር። 15 የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። 16 ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው። 17 ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ። 18 ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች። 19 የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ 20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። 21 አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ። 22 ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም። 23 ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። 24 አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ 25 በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥ 26 የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ። 27 ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።

የዮሐንስ ራእይ 22

1 በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ። 2 በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ። 3 ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፥ 4 ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል። 5 ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ። 6 እርሱም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ። 7 እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ። 8 ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። 9 እርሱም። እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ። 10 ለእኔም። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። 11 ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። 12 እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። 13 አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። 14 ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። 15 ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ። 16 እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ። 17 መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ። የሚሰማም። ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ። 18 በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ 19 ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል። 20 ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና። 21 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።